Quantcast
Channel: ዓለማየሁ ጉጀ
Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

ኩነባ ለዓለም የተደበቀች የታሪክና የቱሪስት ሀብት

$
0
0

 

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

ቱሪዝም ማለት ሰዎች ከሚኖሩበት አካባቢ ወጣ ብለው ለመዝናናት፣ አካባቢን ለማወቅ፣ ለማጥናትና ለሥራ ጉዳይ ከአንድ ዓመት በላይ የማይቆዩበት ጉብኝት ሊሆን ይችላል፡፡ ቱሪስት የሚለው ቃል በአገልግሎት ላይ እ.ኤ.አ. ከ1172 ጀምሮ ሲሆን፣ ቱሪዝም የሚለው ደግሞ እ.ኤ.አ. ከ1811 ጀምሮ እንደሆነ የዋለውና መሽከርከር ወይም መዞር ማለት እንደሆነ ዊልያም ኤፍ ቲዮባልድ እ.ኤ.አ. በ1994 ባሳተመው መጽሐፉ ይገልጻል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንድን ሥፍራ ከመንፈሳዊ ፋይዳው አኳያ መጎብኘት ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የነበረ ስለሆነ ‹‹ጉብኝት››፣ ‹‹ጉዞ››፣ እንጂ ዙረት ተብሎ ሊወሰድ እንደማይገባ የሚያሳስቡ አሉ፡፡

በአገራችን ቱሪዝም መቼ እንደተጀመረ ማወቅ የሚያስቸግር ቢሆንም ንግሥት ሳባ ወደ እየሩሳሌም ያደረገችውን ጉዞ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሌሎችም ከአካባቢያቸው ርቀው ባህር ተሻግረው ለጉብኝት የሄዱበትን ጊዜ መጥቀስ በእጅጉ አስቸጋሪ ነው፡፡ ወደ አገራችን ከጥንታዊት ግሪክ፣ ሮም፣ ቻይናና ከአጎራባች የዓረብ አገሮች የመጡት ጎብኝዎችን መተንተንም ቀላል አይሆንም፡፡ በዚህ ረገድ አፋሮች ቱሪስቶችን ተቀብሎ በማስተናገድ ረገድ የረጅም ጊዜ ታሪክ እንዳላቸው አያጠያይቅም፡፡

በእርግጥም በአፋር ውስጥ ከፍተኛ የቱሪስት መስህቦችና ከፍተኛ የቱሪስት ገቢ የሚያስገኙ ሥፍራዎች ሲኖሩ፣ እነዚህም የተፈጥሮ መስህቦች፣ የቅሪተ አካል ቁፋሮ የተገኙባቸው ሥፍራዎች፣ ጥንታዊ ከተሞች፣ ቤተ መንግሥቶች፣ መስጊዶች፣ የመቃብር ሥፍራዎች፣ ሙስሊሞች እምነታቸውን መሠረት በማድረግ የሚጎበኟቸው ቦታዎች፣ ለባህላዊ ወይም እምነታዊ ሕክምና የሚገኙባቸው ሥፍራዎች፣ የደንና ዱር እንስሳ ክልሎች፣ የገበያ ሥፍራዎች፣. . . ተብለው ሊተነተኑ ይችላሉ፡፡

በአፋር ክልል ውስጥ አምስት ዞኖች ሲኖሩ አንደኛው ዞን ሁለት (በአሁኑ አጠራር ኪልባቲ ረሱ)  የሚባለው አንዱ ነው፡፡ በዚህ ዞን ሥር የሚገኙ ወረዳዎች አብኣላ፣ በራህሌ፣ ዳሎል፣ ኮነባ፣ ኢረብቲ፣ መጋሌ፣ አፍዴራ፣ ቢኡ ወረዳ ናቸው፡፡ ስፋቱም 18,068.34 ካሬ ኪሎ ሜትር ነው፡፡ የሕዝቡ አሠፋፈርም 22 ካሬ ኪሎ ሜትር ነው፡፡ ዞን ሁለት በደቡብ ከዞን አንድ፣ በደቡብ ምዕራብ ከዞን አራት፣ በምዕራብ ከትግራይ፣ በስተሰሜን ከኤርትራ ጋር ይዋሰናል፡፡  የዞን ሁለት ዋና ከተማ አብዓላ ነው፡፡ ዞን ሁለት በዚች ምድር በጣም ሞቃታማ ተብለው ከተመዘገቡት ሥፍራዎች አንዱ ሲሆን፣ መካከለኛው የሙቀት መጠኑም 34 ዲግሪ ሴሊሺየስ ነው፡፡ ስለዚህ የሚያቃጥለው ሙቀት ራሱ የቱሪስት መስህብ ለመሆን የታደለ አካባቢ ነው፡፡

ትኩረት 1 ኩነባዶብዓዎችየሚገኙባትመሆኗ

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ነሐሴ 4 እና መስከረም 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በዚሁ ጋዜጣ እንዳሠፈረው፣ አንዳንድ የታሪክ ጸሐፊዎች የዶብዓዎችና የበለው ሕዝቦች ጠፍተዋል በማለት ሲጠቅሱ ይስተዋላል፡፡ በዚህም መሠረት  ስፔንሰር ትሪሚንግሃም የተለያዩ መረጃዎችን መሠረት አድርጎ እንዳቀረበው (ኢስላም ኢን ኢትዮጵያ 1965፣ 81) ዶብዓዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሰው የሚገኙት በ15ኛው ክፍለ ዘመን በነበሩት በቅዱስ መርቆሪዎስ ሥራ ውስጥ ሲሆን፣ በዚህም ሥራ ያህያ የሚባል የዶብዓ ሙስሊም ባለሥልጣን (መሪ) በ13ኛው ክፍለ ዘመን እንደነበረ ተገልጧል፡፡ አልቫሬዝም እ.ኤ.አ. በ1520 ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ከድባርዋ (ዛሬ ኤርትራ) ጀምሮ እስከ ሐይቅ ድረስ ያለው ሥፍራ ዶብዓ ተብለው በሚጠሩ ገዥዎች እንደሚተዳደር ጠቅሶ፣ እነሱም ሙስሊሞች እንደሆኑ አሥፍሯል፡፡ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ እንደሚለው መሪዎቹ ‹‹ዘላኖች›› ሲሆኑ መሪያቸውም ሹም ጃናሞራ ተብሎ እንደሚጠራ ገልጧል፡፡ የሹም ጃናሞራ ኃላፊነትም ሥነ ሥርዓት ማስከበር እንደሆነ ይጠቁማል፡፡

ስለዶብዓ ሌላው መረጃ የምናገኘው በአፄ በዕደ ማርያም ዜና መዋዕል ውስጥ ሲሆን፣ በዚህም ዜና መዋዕል እኝህ አብያተ ክርስቲያናትን በማሳነፅ የሚታወቁ ንጉሠ ነገሥት (1454 እስከ 1486) ዶብዓዎችን ለማስገበር ራሳቸው እስከ አምባላጌ እንደ ዘመቱ ሠፍሯል፡፡

ከዶብዓዎች ጋር በተያያዘ ሌላው የመረጃ ምንጫችን ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ሆነው ይገኛሉ፡፡ እኚህ የቀዳማዊ ኢማኑኤል አገልጋይ የነበሩ ቄስ እ.ኤ.አ በ1515 ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በአፄ ልብነ ድንግል መንግሥት ዘመን ነበር፡፡

ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ‹‹ቸርች ኤንድ ስቴት ኢን ኢትዮጵያ›› በተሰኘው ታዋቂ መጽሐፋቸው (1972፣81-82) እንዳሠፈሩት ዶብዓዎች ከሰሜን አክሱም፣ አዳፋ፣ ጥራሬ ወንዝን በመሻገር በዋግ (ሰቆጣ)፣ ኮረም፣ ራያ፣ ኢፋት፣ ደዋሮ በሚወስደው ጉዞ መስመር  በተለይም በሰቆጣ፣ ኮረምና ራያ አካባቢ ባለው ሥፍራ ሊኖሩ እንደሚችሉ በገጽ 81 በሠፈረው ካርታ መረዳት እንችላለን፡፡ በተጠቀሰው የጉዞ መስመር (መንገድ) ምዕራባውያን ሚሲዮናውንና አሳሾች የተጓዙ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ አባ ፊሊጶስ ዘ ደብረ አሰቦ አንዱ ናቸው፡፡ በገድለ ፊሊጶስ (ገጽ 219 እስከ 220) ሠፍሮ እንደሚገኘውም፣ እኝህ የሃይማኖት አባት እ.ኤ.አ. በ1334 በተጠቀሰው የጉዞ መስመር በተጓዙበት ጊዜ ያገኙትን ሁሉ የሚገድሉና እምነት የሌላቸው ዶባዓዎች በሚኖሩበት በኩል አድርገው ወደ ትግራይ መሄዳቸውን ይገልጻል፡፡ ስለዚህ የጉዞ መስመር በገድለ ቀዊስጦስ፣ በገድለ አሮን፣ በገድለ ኤውስጣቴዎስ ተጠቅሷል፡፡ ይልቁንም በዚህ ሥፍራ ‹‹ቆርቀዋራ›› ተብሎ የሚጠራ ሥፍራ ሲኖር፣ ይህም ሥፍራ ዛሬ ከማይጨው ወደ ሰሜን ዓዲ ሼሁ ከመድረሱ በፊት ‹‹ዓብየታ ቆርቆራ›› ከሚባለው ቦታ ጋር የሚገናኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ከሐሸንጌ 40 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ የሚገኝና የሐሸንጌ ሕዝቦች ዝርያዎችና ዋጅራቶች የሚኖሩበት አካባቢ መሆኑ ነው፡፡ በፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ሥራ እንደምናገኘው ግን ይህ መንገድ የጨው ንግድ ቅፍለት የሚጓዝበት መስመር ነው፡፡ ይህም ሆኖ ደግሞ ገረዓልታ (ሐውዜን) ቆርቆር ተብሎ የሚታወቅ ሥፍራ በመኖሩና ውቅር ዓብያተ ክርስቲያናትም ‹‹እንዳቆርቆር›› እየተባሉ ስለሚጠቀሱ፣ እንዲሁም ትክክለኛው የጨው ንግድ መስመር በመሆኑና ለአፋርም የቀረበ ስለሆነ፣ እነ አልቫሬዝም ወደ መሀል ኢትዮጵያ የመጡት በዚህ በኩል አድርገው ስለሆነ ቆርቆርን ለመፈለግ ጊዜ ማባከን የሚያስፈልግ አይመስልም፡፡

በኩነባ ወረዳ አካባቢ ይኖሩ የነበሩት የዶብዓ ጎሳ መሪዎች ሲሞቱ ለክብራቸው መታሰቢያ ረዣዥምና ጠፍጣፋ የሆኑ ድንጋዮችን በመቃብሮች ላይ መኮልኮል የተለመደ ነበር፡፡ እነዚህ የመታሰቢያ ድንጋዮች የሟቹ ቤተሰቦች እነሱን በማየት እንዲያስታውሱትና በሕይወት የነበረው ሕዝብም ሆነ መጭው ትውልድ ስለዚያ ሰው እንዲያውቅ ተብለው የቆሙ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የሟቹ ዘመድ (ናንገሉ) ለሟቹ ክብር ሲል የቁም ድንጋይ ጠርቦ በራሱ ትከሻ ተሸክሞ በመቃብሩ ላይ ይተክል ነበር፡፡ 

በኩነባ የሚኖሩ የዶብዓ ጎሳዎች በዘመኑ ገዥ መደቦች የነበሩ ሲሆን፣ በዚህ አካባቢ ዶብዓ ካሬ በተባለ ሥፍራ ዶብዓ ተብሎ የሚጠራ መንደር ነበር፡፡ ይህ መንደር ዛሬ ሙሉ በሙሉ ፈርሶና በከፊልም ተቀብሮ የሚገኝ ጥንታዊ መኖሪያ ሠፈር ነው፡፡ በአሁን ጊዜ ቦታዎቹ ሲቆፈሩ ውስጡ ድስት፣ እንስራ፣ ወዘተ ይወጣል፡፡ በዚህም አካባቢው ሠፈሩ ዶብዓዎች የጠፉበት መሬት በሚባል ይታወቃል፡፡ ዶብዓ የሚባሉ ጐሳዎች ጥንታዊ ናቸው፡፡ መናኸሪያቸው አሳገራ የሚባል ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ የመኖሪያ አካባቢያቸው ሲቆፈር ከውስጥ የተለያዩ ዕቃዎች ይወጣሉ፡፡ 

ይህም ሆኖ የአገራችን የታሪክ ዘጋቢዎች በምድረ ገጽ ያሉትን ሕዝቦች ፈረንጆች የጻፉትን ስህተት ሲደጋግሙ ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው ሁሉ ዶብዓዎች ከምድር ገጽ አልጠፉም፡፡ በአፋር ብሔራዊ ክልልና በትግራይ፣ እንዲሁም በአማራና በኦሮሚያ ክልል እንደሚገኙ ዛሬም በሕይወት የሚገኙ የዶብዓ ጎሳ አባላት ያስረዳሉ፡፡ የቦታ መረጃዎችን አስቀድመን እንመልከት፡፡

ዶብዓዎች የበለው ዝርያ እንደሆኑ የሚጠቅሱ አንዳንድ መረጃዎች ሲኖሩ፣ ይህም ‹‹ኢማም አህመድ ኢብራሂም›› በተሰኘው በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በተጠናቀረውና በታተመው መጽሐፍም አግባብ ባለው ሥፍራ ተጠቅሷል፡፡ በመሠረቱ በለዎች በተለያዩ የአፋር ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ በተለይም በጎሌና ወረዳ፣ በኩሎዋንና በዓይነ ማሊ ይገኛሉ፡፡ በለዎች በለውኬ ዓይነ መሊ፣ በለውኬ ዋኒሳና በለውኬ ዓበሬ ተብለው ይጠራሉ፡፡ የበለውታ ተወላጅ የሆኑ በአርቤቶ፣ በቡሬ ሙዳይቱ፣ በገዋኔ የሚገኙ ሲሆን ጀግኖች እንደሆኑ የተመሰከረላቸው ናቸው፡፡ 

ትኩረት 2 የነብዩሙሐመድተከታዮችመኖሪያናመቃብርበኩነባመኖሩ

ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ እንደ ኤርትራና ሶማሊያ ያሉ አገሮች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የታሪክ መረጃዎችን ለራሳቸው እንደሆኑ አድርገው በማቅረብ ላይ ቢሆኑም፣  በተለይም ሶማሊያን፣ ኤርትራንና ጅቡቲንና ከፊል ሱዳንን በተለይ ሶዋንኪንን በአንድ ላይ ታስተዳድር የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር ከብዙ ሺሕ ዓመታት ጀምሮ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን የጠበቀ ማኅበራዊ ግንኙነት እንደነበራት የታሪክ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እስልምና በአፋር ግዛት በሚገኙ ወደቦች በኩል አድርጎ ወደ ተቀረው የኢትዮጵያ ግዛት የገባው በመካ መስፋፋት በተጀመረበትና ገና መዲና ባልገባበት ጊዜ ነው፡፡ በአፋር ውስጥ በተለይም በዳሎል ወረዳ በኩነባ ዞን በተለይም በኢፊሶ፣ በዒሲና በሌሌገዲ ያሉ የሱሐባዎች (መጀመሪያዎቹ የነብዩ ሙሐመድ ተከታዮች) መቃብሮች መገኘታቸውም በዚህ አካባቢ መኖራቸውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ስለሆነም ከነጋሺ አሥር ኪሎ ሜትር ወደ ምሥራቅ በተለይም ዓፅቢ ደራ ተብሎ ከሚጠራው ጥንታዊ ከተማ በስተሰሜን ካለው ነጭ ተራራ በስተምሥራቅ ከሚገኘው ሥፍራ ያለው በተለየ ስሙ ‹‹ሠፈር›› ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ያሉ ጥንታዊ መቃብሮች፣ በዓፅቢ ደራ የሚገኙት ጥንታዊና ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት፣ በአካባቢው የሚገኙ የጥንታዊ ከተማ ፍርስራሾች፣ በአፋር ኩነባ ወረዳ ውስጥ ኢፊሶ ተብሎ ከሚጠራው ወንዝ ዳርቻ ያለው የነቢዩ ሙሐመድ ተከታዮች መቃብር፣ ከዚህ የተራራ ግርጌ ወንዙን ተከትሎ በመጓዝ፣ አሥር ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በሚገኘውና ሌሌገዲ ተብሎ በሚጠራው የወንዝ ዳርቻ ያለው ተመሳሳይ መቃብር መኖር፣ ከሌሌገዲ በስተምዕራብ ማለትም ከኩነባ በስተሰሜን ዒሲ ተብሎ በሚገኘው ሥፍራ ያለው የሱሐባዎች ቀብር በዚህ ጥናት በጥቅሉም ቢሆን ተካቷል፡፡

በጥናቱ ወቅት የተስተዋለው ከፍተኛ ታሪካዊ ቁም ነገርም የመቃብሮቹ ሥፍራዎች በሚገኙበት በዓፅቢ ደራ፣ የአብርሃ ወየአፅበሃ እናት የነበሩት የንግሥት ሶፊያ ቤተ መንግሥት በተለይም እስቲፊያ በሚባል ቦታ ላይ መኖሩ ነው፡፡ የአካባቢም ሰዎችም ዓፅቢ ደራና አካባቢዋ የነገሥታት መቀመጫዎች እንደነበሩም በአጽንኦት ይገልጻሉ፡፡ ምናልባትም አብርሃ ወአፅብሐ ክርስትናን የተቀበሉት እዚህ ሊሆን እንደሚችል የጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናቱ ታሪክ ይፈነጥቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዕምባ ቀንጨበት በጥድ፣ በወይራና በሌሎችም ጠንካራ ዛፎች የተሞላ ሲሆን ጥንት ይሠሩ የነበሩ መርከቦች ከዚህ ተራራ እየተቆረጠ ይወሰድ በነበረ ግንድ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ፡፡ ከዓፅቢ ደራ ከተማ በስተሰሜን ምሥራቅ ሣፍር ወይም ሠፈር ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ፣ የነቢዩ ሙሐመድ ተከታዮች መቃብር አለ ተብሎ የመታመኑም ጉዳይ፣ ከነጋሺ ይልቅ በወንዞች የተከበበችውና በአየር ጠባይዋ ደጋ የሆነችው ዓፅቢ ደራ የንጉሥ አስሐማ ዋና ከተማ ልትሆን እንደምትችል መገመት ይቻላል፡፡ ከዚህም በላይ የመቃብሮቹ በየአሥር ኪሎ ሜትር ያህል ተራርቀው የመገኘታቸውና በሁሉም ሥፍራዎች ክረምት ከበጋ የማያቋርጥ የወንዝና የምንጭ ውኃ መኖሩ፣ የግብርና ልማትም መገኘቱ ከዓረቢያ የመጡት እንግዶች ከንጉሡ ዕይታና እንክብካቤ ሳይርቁ መኖራቸውን ይጠቁማል፡፡ 

ደጋማ ከሆነው ከዓፅቢ ደራ ከተማ ማለትም ከተራራው ግርጌ በስተምሥራቅ ኩነባ የተባለችው ቆላማ የአፋር ወረዳ ትገኛለች፡፡ የወረዳዋ ዋና ከተማ የሆነችው ኩነባም በሁለት ታላላቅ ወንዞች መሀል የምትገኝ ስትሆን ከሁለቱ ወንዞች አንደኛውና በስተሰሜን የሚገኘው ኢፊሶ፣ ሁለተኛውና በስተደቡብ የሚገኘው ደግሞ ሓናቢ ድኤራ የተባለ ወንዝ አጠገብ የሚገኝ ነው፡፡ ወንዙ ዳር ደግሞ ሱሐባዎቹ ያለሙት የአትክልት ሥፍራ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ነበር፡፡

የኩነባና የአካባቢው ነዋሪዎች ‹‹አያት ቅድመ አያቶቻችን ለእኛ፣ ለእነሱ ደግሞ አያት ቅድመ አያቶቻቸው ነገሯቸው›› ብለው እንደሚያስረዱት፣ በኢፊሶ ወንዝ በተለይም ኢፊሶ ተብሎ ይታወቅ በነበረ ጥንታዊ ገበያ አካባቢ፣ በሌሌገዲና በበልበል የነቢዩ ሙሐመድ ተከታዮች ይኖሩ ነበር፡፡ በእነዚህም ሥፍራዎች የእነርሱና የሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች መቃብሮች፣ የመኖሪያ ቦታ ፍርስራሾች፣ የመቃብር ትክል ድንጋዮች፣ የተምር ተክሎችና ከእነሱ ጋር የተያያዙ ታላላቅ ዛፎች አሉ፡፡ ከሌሌገዲ ትንሽ ወጣ ብሎም ዑቡክና ዒሲ በሚባሉ ከኩነባ በስተሰሜን ምሥራቅ የነቢዩ ሙሐመድ ተከታዮች መቃብሮች ሲኖሩ፣ ትክክለኛ መቃብሮቻቸው መሆናቸውን የሚያመለክቱ የጽሑፍ መረጃዎች እንዳሉ ሼኽ ሙሐመድ ሷሊህ አህመድ የተባሉ የኩነባ የሃይማኖት አባት ያስረዳሉ፡፡

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የኢፊሶ አናት ከሆነው ከዓፅቢ ደራ ተራራ ላይ በተለይም ሠፈር ተብሎ በሚታወቀው ሥፍራ የነቢዩ ሙሐመድ ተከታዮች መቃብር እንዳለ ሲነገር፣ ይህ ሥፍራ ከኢፊሶ የሦስት ሰዓት መንገድ ይሆናል፡፡ ከሠፈር እስከ ነጋሺ ያለው የእግር መንገድ ከአራት ሰዓት የበለጠ እንዳልሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ያስረዳሉ፡፡ በተመሳሳይ ከኢፊሶ እስከ ኩነባ፣ ከኩነባ እስከ ሌሌገዲና ከሌሌገዲ እስከ ዒሶ ያለው የእርስ በርሳቸው ርቀት ከአምስት እስከ ስድስት ኪሎ ሜትር ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም አንደኛው የነቢዩ ሙሐመድ ተከታይ ሠፈር ከሌላው ከአንድ ሰዓት ያልበለጠ ጊዜ የሚወስድ መሆኑ ነው፡፡

አስረጅዎቹ እንደሚሉት የነብዩ ሙሐመድ ተከታዮች ሹዓይባ ከምትባለውና ከጅዳ በስተ ደቡብ ከምትገኝ ሥፍራ ተነስተው በሚዕዲር በኩል ወደ ኩነባ መጡ፡፡ በሐበሻ ምድርም ምንም ዓይነት በደልና የእምነት ተፅዕኖ ሳይደረግባቸው ቆዩ፡፡ በዚያን ጊዜ ወደ ሐበሻ ምድር ጉዞ ያደረጉት ሰዎች ቁጥር 11 ሲሆን 12 ሰዎች ነበሩ የሚሉም አሉ፡፡ ከእነዚህ ሰዎች መካከል የሐበሻዋን ኡማ አይመን በረካን ሳይጨምር አራቱ ወይም አምስቱ ሴቶች ነበሩ፡፡

አህመድ ቢኒ ዘይኒ በተጠቀሰው መጽሐፋቸው ምዕራፍ 1 ገጽ 245 እስከ 246 1983 እንዳሠፈሩት ከነብዩ ሙሐመድ ተከታዮች መካከከል አንዳንዶቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ራሳቸውን ለማዳን ሲባል ብቻቸውን ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አብዱልራህማን ቢኒ ኦውፍ፣ ዙቤር ቢኒ ዓዋም፣ ኡስማን ቢኒ አፋንና ባለቤታቸው የነብዩ ሙሐመድ ሴት ልጅ ሩቅያ እንደነበሩ ጸሐፊው ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ጸሐፊው ስለሁለተኛው ስደት (ሒጅራ) ሲያወሱ ጃእፈር ቢኒ አቡጣሊብ፣ አብዱላሂ ቢኒ ጃህሽና ኡሙ ሀቢባ (የአቢ ሱፍያን ልጅ) ከስደተኞቹ መካከል እንደነበሩ ይገልጹና ታላቁ የነብዩ ሙሐመድ ሰሀባ የነበሩት አቡ ሙሣ አል አሸአሪ እንደነበሩበትም አሥፍረዋል፡፡

የጀዋሂሩል ሐበሻን መጽሐፍ ጸሐፊ ስለአህመድ አልነጃሺ አገር በጻፉበት ጊዜ፣ የነጃሺ አገር ከምዕድር ከተማ የአራት ወይም የአምስት ቀናት ጉዞ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ምዕድር በአፋር ጠረፍ የምትገኝ ከተማ ስትሆን በዚህ አካባቢ የጠልጠል ዓረቦች ይገኛሉ ይባላል፡፡ ስለዚህ አቡ ሙሣ አል አሸዓሪ በዚህ በኩል አቋርጠው ወደ ነጃሺ አገር እንደሄዱ ይገመታል፡፡ ይህ የተጠቀሰውም ርቀት በምዕድርና በነጃሺ መቃብር መካከል ካለው ርቀት ጋር እኩል መሆኑን መገንዘብ ጥሩ ነው፡፡ በእነዚህም ምክንያቶች የእስልምና ሃይማኖት ከዓረብያ ተነስቶ ወደ ቀይ ባህር ምዕራባዊ ግዛት ማለትም ወደ አፍሪካ የደረሰው በሦስት አቅጣጫ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

 በጥቅሉ የነቢዩ ሙሐመድ የቅርብ ተከታዮች ወደ ሐበሻ ያደረጉት ስደት (ሒጅራ) በኢስላም ታሪክ ላቅ ያለ ቦታ የተሰጠው ክስተት መሆኑና አገራችን ኢትዮጵያም ቀደም ሲል የአይሁዶች እምነት ተከታዮችን፣ ቀጥሎም የክርስትና እምነት ተከታዮችን ተቀብላ እንዳስተናገደች ሁሉ፣ የእስልምና እምነት የሚከተሉ እንግዶችን በማስተናገድ ረገድ ግንባር ቀደም መሆኗን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ይህች ውድ አገራችን ሙሐመድ ኢብን ሐቢብ የተባለ ጸሐፊ እንደተረከው ነብዩ ሙሐመድ፣ ‹‹እኔ ራሴም ብሆን የምሰደድባት የተምር ተክል ያለባት አገር ናት›› ማለታቸውን ጠቅሷል፡፡ በነገራችን ላይ የተምሩ ዛፍ ዛሬም በኩነባ ይገኛል፡፡ በሌሎች የአፋር ግዛቶችም እየተመረተ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ አጠናቃሪ ከወረታ ወደ ደብረ ታቦር በተጓዘበት ጊዜም የተምር ተክሎችን የተመለከተ ሲሆን፣ የፉትሑል ሐበሽ ጸሐፊ በመጽሐፋቸው እንዳሠፈሩትም ‹‹ኢማም አህመድ ኢብራሂም›› በተሰኘ መጽሐፉ ጠቅሶታል፡፡

የነቢዩ ሙሐመድ ተከታዮች ወደ ሐበሻ የገቡባቸውና አቅጣጫዎች ሦስት ሲሆኑ፣ እነዚህም ሦስቱ አቅጣጫዎች፣

1ኛ. ከዳህላክ ደሴቶች እስከ ዜይላዕ ከተማ ድረስ ተዘርግቶ በሚገኘው በአፋር ሦስት ማዕዘናዊ መሬት በኩል

2ኛ. በምፅዋና በደከኑ ‹ዛሬ ሀርጊጎ› በሚባሉ፣

3ኛ. የኩነባ ምድር ተብላ በምትታወቀው ግዛት በኩል መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ስለሆነም የእስልምናን ሃይማኖት በአፋር ምድር ላይ በሰፊው ለመሠራጨት ያስቻለው አንደኛው ምክንያት፣ የነቢዩ ሙሐመድ ተከታዮች ከመጀመሪያው ሒጅራ ጀምሮ የኖሩበት ሰላማዊ ሥፍራ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ በተለያዩ ታሪካዊ ሰበቦች ከዓረቢያ ፈልሰው ወደ አፋር በመምጣታቸው ነው፡፡ የፈለሱበትም ምክንያት የእርስ በርስ ጦርነት፣ ረሃብና ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የነበረው ንግድ ሊሆን ይችላል፡፡ ከእነዚህም ሁሉ ይልቅ በመጀመሪያዎቹ የእስልምና ዘመናት በዓረቢያ መሬት ይካሄድ የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት እንደ ዋነኛ ምክንያት ሊቆጠር ይችላል፡፡ በተለይም ደግሞ የሦስተኛውን ከሊፋ ኡስማን ኢብኒ አፋን መገደል ተከትሎ የተጫረው የእርስ በርስ ጦርነት ‹‹አልፊትነቱል ኩብራ›› የተባለውን ታላቁን ሽብር ወይም ታላቁ መከራ ማስከተሉ ይታወሳል፡፡ እንዲሁም የዘይድ ቢኒ አሊይ ዘይኑል ዓብዲን የተገደሉበት የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት፣ ብዙ ዓረቦች የትውልድ ቀዬአቸውን ለቀው ወደ ሌላ አገር ለመሰደድ መገደዳቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ ጊዜ በዛሬይቱ ኤርትራም፣ ሶማሊያም፣ ጅቡቲም እንደኖሩ አሌ አይባልም፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያት በተጨማሪም ዛሬ በአፋር ምድር ለሚኖሩት ሕዝቦች ቅድመ አያቶች ከነበሩት መካከል፣ የሃይማኖትን ትምህርት ማስተማር ብቸኛውና ዋና ተልዕኳቸው በማድረግ በተናጠልም ሆነ በቡድን አገራቸውን ለቀው ወደ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ በመምጣት ትልቅ መስዋዕትነት የከፈሉ በርካታ ዓረቦች አሉ፡፡ በቀይ ባህር ግራና ቀኝ በምሥራቅና በምዕራባዊ ጠረፎች የነበሩ ነጋዴዎች ያደርጉት የነበረው የንግድ እንቅስቃሴም፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዓረቦች ወደ አፍሪካ ቀንድ እንዲመጡ እንዳደረጋቸው አይጠረጠርም፡፡

ትኩረት 3 በአፋርውስጥየሚገኙእስላማዊቅርሶች

በዚህ ክልል ብዙ እስላማዊ ቅርጻ ቅርጾች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ፡-

አንደኛ የነቢዩ ሙሐመድ ታላቅ ሰሃባ የነበሩት የሰይድ ‹‹ኦካሻ›› መቃብር በ‹‹ገረዶ›› ይገኛል፡፡ የገረዶ ከተማ ከቤጃ ከተማ በስተሰሜን ምዕራብ ወደ ነጃሺ መቃብር በሚወስደው በ‹‹ሰሙቲ›› መንገድ ላይ ትገኛለች፡፡ የመቃብሩ ርዝመት 30 ክንድ ሲሆን፣ ከተራራ ሥር ከሚፈልቅ የምንጭ ውኃ አጠገብ ነው የሚገኘው፡፡ ይህ ግን የነብዩ ሙሐመድ ሰሃባ ከመሆን አያግዳቸውም፡፡ ከነቢዩ ሙሐመድ ሰሃባዎች መካከል ኡካሽ በመባል የሚታወቁ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ ወደ ነጃሺ ከተሰደዱት ‹‹ሰሃባዎች›› በተለያዩ መንገድ ተጉዘው እንደነበረ ብዙ የታሪክ ጸሐፊዎች ስለሚገልጹ፣ በስደት የመጡ ሰዎች ቁጥር በትክክል ተመዝግቦ ስለማይታወቅ፣ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ መቃብሩን የነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) ሰሃባ የሆኑት የሰይድ ‹‹ኦካሻ›› መቃብር ነው ብለው በቁርጠኝነት ስለማያረጋግጡ፣ ኡካሽ የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሰሃባ ነበሩ ለማለት ይቻላል፡፡

ሁለተኛ በኢፊሶ ወንዝ አምስት ታላላቅ ማስረጃዎች የሚገኙ ሲሆን፣ አንደኛው የነብዩ ሙሐመድ ተከታዮች መቃብር፣ ሁለተኛው የዚያን ጊዜ የነበሩ ሰዎች ይሰግዱበት ነበር ተብሎ የሚነገርለት ጥንታዊ መስጊድ፣ ሦስተኛው የዚያን ጊዜ የነበሩ ሰዎች የጀመሩት የመስኖ እርሻ፣ አራተኛው እንደ ምግብ የማጥገብ ባህርይ ያለው ክረምት ከበጋ የማይደርቅ ምንጭ፣ አምስተኛው ወደ ኩነባ ከመዞሩ በፊት ከጥንት ጀምሮ ይጠቀሙበት የነበረው የወንዝ ውስጥ ገበያ ናቸው፡፡

ትኩረት 4ለመርከብመሥሪያየሚያገለግለውዛፍ

አፋሮች በቀይ ባህር ወደቦቻቸው ጀልባዎችንና መርከቦችን ይሠሩ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን መርከቦቻቸውም ለዓሳ ማስገሪያ፣ ለንግድና ለጦርነት የሚያገለግሉ ነበሩ፡፡ በጀልባዎቻቸው በምዕራብ ቀይ ባህር የሚገኙ በዓይነታቸው ልዩና በሩቅ ምሥራቃውያን ዘንድ ተወዳጅነት የነበራቸውን ዓሳዎች ያጠምዱ የነበረ ሲሆን፣ ጥልቅ ባህር ጠላቂዎቻቸውም ሉል እያወጡ ለገበያ ያቀርቡ ነበር፡፡ የአፋሮች ሥልጣኔ ከጥንት ፊንቃውያን፣ ግሪካውያን፣ ሮማውያን፣ ግብፃውያንና ሩቅ ምሥራቃውያን ጋር የተያያዘ በመሆኑ ተመሳሳይ የሥልጣኔ አቅጣጫ እንደሚከተል አያጠያይቅም፡፡ የታሪክ መረጃዎቹ የሚያረጋግጡትም ይህንኑ ሀቅ ነው፡፡ ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉትን መረጃዎችን እንመልከት፡፡

ከእስልምና የታሪክ ምዕራፎች እንደምንረዳውም በጥንታዊ የአፋር የባህር ወደቦች የጦር መርከቦች እየተሠሩ ወደ የመን፣ ዓረቢያና ፐርሺያ ይዘምቱ ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል አፄ ካሌብ በተለያዩ ወደቦች ያሠሯቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር መርከቦች በሰፊው ተጠቅሰው ይገኛሉ፡፡ በቁርዓን ውስጥ 105 ምዕራፍ የተጠቀሰውም ከዚህ ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው፡፡

የአፋር ሥልጣኔን የሚያወሱ የታሪክ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የንግድ እንቅስቃሴውና የመርከብ ኢንዱስትሪው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ቀጥሎ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1874 ጀምሮ ቱርክ ሐረርን ስትይዝም የመርከብ ንግዱ አልተቋረጠም፡፡ በዚህ ክፍለ ዘመን ቱርኮች፣ እንግሊዞችና ፈረንሣዮች ያልነበሩ ሲሆን፣ ሁሉም ጉዟቸውን በቀይ ባህር አካባቢ አስፋፍተው የንግድ መርከብ ልውውጥ ለማድረግ ፍላጎት የነበራቸው፡፡ ያ ሁሉ መርከብ ይሠራ የነበረው ግን ከአፋርና ከአካባቢው ጫካዎች ይገኝ በነበረ ለመርከብ መሥሪያ የሚያገለግል ኦሎኦይቶ ከሚባል በቀላሉ የማይሠበር (ግነት ቢሆንም አንዳንዶች በመጥረቢያ የማይቀረጥ ይሉታል) ዛፍና እንደ ወይራ፣ ዝግባና ሌሎች ጠንካራ ዛፎች ነበር፡፡ የእነዚህ ዛፎች ቅሪት አሁንም በአፋር ወንዞች በተለይም በኢፊሶ ይገኛል፡፡

ትኩረት 5የተፈጥሮሀብቶች

የአፋር ሕዝብ ጥንት ዘመኑ ይህ ነው ተብሎ ከማይቆጠርበት ጊዜ ጀምሮ በግመልና በሌሎች አጋሰሶች ቅፍለት ጨው፣ የውጭ ሸቀጣ ሸቀጦችን ወደ ትግራይ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ሸዋ፣ ወሎ፣ ጅማ፣ ሲዳማ፣ ባሌ፣ አርሲ እየወሰደ ሲሸጥ በምትኩም ጥራጥሬ፣ የዝሆን ጥርስ፣ የነብርና የዝሆን ቆዳዎች፣ ዕጣን፣ ከርቤ፣ ዝባድ፣ ቅመማ ቅመሞችን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ወደ ሩቅ ምሥራቅ፣ ወደ አውሮፓና ወደ ሰሜን አፍሪካ ይልክ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ዛሬም ቢሆን በጣም ጣፋጩና ለጤና ተመራጩ ማር የሚገኘው በኩነባና በሌሎች የአፍር ክልል ዞኖች ነው፡፡ በጣም የሚያስደንቀው ደግሞ እንጨቱ የጥንት ግብፃውያን በእጅጉ ይፈልጉት የነበረውና ሽቶን የሚያስንቀው የዛፍ ሥር የሚገኘው፣ ኩነባን ጨምሮ በሌሎችም የአፋር ዞኖች ነው፡፡ ብርቅዬ እንስሳት፣ አዕዋፍና፣ ትልቁ የዱር እንስሳት ፓርክ ጭምር ነው፡፡

ማጠቃለያ

አፋር በአሁኑ ዘመን በመላው ዓለም የምትታወቀው ድንቅነሽ ወይም ሉሲ  ተብላ በምትጠራውና 3.5 ሚሊዮን ዕድሜ አላት ተብላ በምትገመተው ቅሪተ አካል፣ ከእሷ በፊትና በኋላ በነበሩ ቅሪተ አካላተ፣ ጥንታዊ ቁሳቁሶችና የጥንታዊ የሰው ዘር መረጃዎች ነው፡፡ እስካሁን የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ሌሎች ጥንታዊ የሰው ዘር መረጃዎች በአፋር ከርሰ ምድር ይገኛሉ ተብለው ይገመታሉ፡፡ ከቅሪተ አካላትና ከሌሎች ጥንታዊ የታሪክ መረጃዎች በተጨማሪ ሌሎች ተጨባጭና ረቂቅ ቅርሶች አሉ፡፡ 

ከእነዚህ በተጨማሪም የአፋር ሕዝብ ታሪክን የሚያስታውሱ ለምሳሌ የመኖሪያ ቤቶች፣ በተለያዩ የመቃብር ሥፍራዎች ላይ የሚገኙ ትክል ድንጋዮች፣ የመገልገያ ቁሳቁሶች፣ ስመ ገናና የነበሩ የሙስሊም እምነት አባቶች የመቃብር ሥፍራዎችና እነሱ ሲያስተምሩባቸው የነበሩ መድረሳዎች በሰሜን ሸዋ፣ በወሎ፣ በትግራይ፣ በድሬዳዋና በሐረር ይገኛሉ፡፡ አዱሊስ፣ ታጁራ፣ ዘይላ፣ ወዘተ የመሳሰሉ ዝነኛ የባህር ወደቦች  የአፋርን ታሪክ የሚመሰክሩ መረጃዎች ናቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

Trending Articles