በመንግሥቱ መስፍን
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ‹‹የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን›› የምርመራ ሪፖርት አዳምጧል፡፡ ጉዳዩ ደግሞ በአገሪቱ በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በርከት ያሉ ወረዳዎች ላይ በተከሰተው ሰላማዊ ሠልፍ ሁከትና የመንግሥት ታጣቂዎች ግድያ ላይ ያነጣጥራል፡፡ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መሞታቸውንና ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ሀብት መውደሙን አረጋግጧል፡፡
‹‹ይህ ድርጊት የተከሰተው ደግሞ ሕገ መንግሥቱ በፈጠረው ቀውስ ሳይሆን የሕገ መንግሥት ውሳኔዎችን በጊዜው ምላሽ ባለመስጠትና በመልካም አስዳደር ዕጦት ነው፤›› የሚለው ሪፖርት ለዚህም በችግር ውስጥ ዋነኛ አጥፊና ተዋናይ የነበሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አክቲቭስቶች እንዲጠየቁም አሳስቧል፡፡ ይኼ መግለጫ ‹‹መንግሥት ያልተመጣጠነ ዕርምጃ ወስዷል፤›› የሚለውን ትችት ፉርሽ ያደረገ ሲሆን፣ ስለታሠሩና ደብዛቸው ጠፍቷል ስለሚባሉ ዜጎችም ያለው ነገር የለም፡፡ ከሁሉ በላይ በዚያም ተባለ በዚህ ንብረታቸው ወድሞ ለስደትና ለልመና የተጋለጡ ቤተሰቦችን ጉዳይ ትኩረት የሰጠው አይመስልም፡፡
የማይካደው እውነት ግን ሕዝቡ ያነሳውን ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ወደራሳቸው የፖለቲካ ዓላማ በመቀየር ለከፍተኛ ጥፋት አውለውታል ያላቸውን በውጭ የሚገኙ የትጥቅ ተቃዋሚዎችን ነው፡፡ አንዳንድ ታዛቢዎች ታዲያ መንግሥትስ እንደተቋም ራሱን ችሎ የሚጠየቅበት ጥፋት ምንድነው? ሲሉ በግርምት ጠይቀዋል፡፡
ከዚህኛው መግለጫ ተቃራኒ ሊባል የሚችል የምርመራ ውጤት በተለይ በሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) የቀረበው መጋቢት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ሲሆን፣ ‹‹140ኛ ልዩ መግለጫ›› የሚል ገዥ ርዕስም ተሰጥቶታል፡፡ መግለጫው የወጣበት ጊዜ ገና ግለቱ ባልበረደለት አፍላ ወቅት ላይ በመሆኑ ‹‹በመንግሥት፣ የፀጥታና ታጣቂ ኃይሎች በዜጎች ላይ የሚፈጸም አስቀያሚ ግድያ ሕገወጥ እስር፣ ድብደባ፣ ማስፈራራትና ማዋከብ በአስቸኳይ ይቁም!›› የሚል ማስጠንቀቂያንም ያዘለ ነበር፡፡
ይኼ የሟቾችና የከፍተኛ ቁስለኞችን ዝርዝር፣ ፎቶ ግራፍ ጭምር የያዘ የሰመጉ ሪፖርት እጅግ ዝርዝር የምርመራ አካሄድ የተከተለና ግልጽነትን የተከተለ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችም ሪፖርቱን በገለልተኝነቱ የተቀበለው ሲሆን፣ ‹‹የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ለተቃውሞ በወጡ ዜጎች ላይ በወሰዷቸው ከመጠን ያለፉ የኃይል ዕርምጃዎች የበርካታ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በርካታ ሰዎች በጥይት ተመትተው የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በርካቶች ታስረዋል፡፡ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች የደረሱበት አይታወቅም፡፡ ኪሳራ ያስከተለ ከባድ የንብረት ውድመት ደርሷል፤›› ይላል፡፡ ይኼም ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 30(1) ጋር እንደሚጋጭም ጠቁሟል፡፡
የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሰሞኑን ካቀረበው ሪፖርት የማይገኝ፣ ነገር ግን ሰመጉ ያቀረበው ሪፖርት የያዘው አወዛጋቢ ሀቅም አለ፡፡ ይኸውም ‹‹መንግሥት በችግሩ ውስጥ ተጠያቂ ነው፤›› ያለበት መከራከሪያ ነው፡፡ ሰመጉ በሪፖርቱ በገጽ 4 ላይ ‹‹መንግሥት የተቀናጀ የማስተር ፕላኑን በማቅረብ ሒደት ዜጎችን በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ገጠርና ከተማ ነዋሪዎችን ባለማሳተፉ፣ ረቂቅ ሰነዱንም እስከዛሬ ድረስ ለሕዝብ ይፋ ባለማድረጉ የበርካታ ዜጎችን ሕይወት ለቀጠፈውና የአካል የንብረት ጉዳት ለተከሰተው ቀውስ ምክንያት ሆኗል፡፡ ረቂቅ ማስተር ፕላኑ ለባለሙያዎችና ለሌሎችም ባለድርሻ አካላት ቀርቦ ግልጽ ውይይት፣ ክርክርና ትችት ሊደረግበት ሲገባ ለዓመታት በሚስጥር መያዙና ይዘቱም ለዜጎች አለመገለጹ ለጥርጣሬ፣ ለውዥንብርና ደም ላፋሰስ ግጭት መንስዔ ሆኗል፤›› ነው የሚለው፡፡
እንደማንኛውም ተቆርቋሪ ዜጋ ‹‹ከሰላማዊ ሠልፍ ወደ ሁከት፣ ብጥብጥና አመፅ የተቀየረን የሕዝብ ቁጣ መንግሥት በምን ሊያረጋጋው ይችል ነበር?›› የሚል ጥያቄ በጭንቅላታችን ይመላለሳል፡፡ በተለይ ሁከቱ ተባብሶ በነበረበት ከኅዳር አጋማሽ እስከ ጥር 2008 ዓ.ም. በተለይ በኦሮሚያ ክልል ብቻ በ18 ዞኖችና በ300 ወረዳዎች የተነሳ የሕዝብ ማዕበል ሴት ወንድ፣ ልጅ አዋቂ፣ እግረኛና ፈረሰኛ አሳትፎ እያለ ማብረጃው ምን ሊሆን ይችል ነበር ማለት ተገቢ ነው፡፡
ይኼ ማለት ግን በጠራራ ፀሐይ ሕፃናትን ጨምሮ (ከ13 ዓመት በታች ሁሉ) አልተገደሉም ማለት አይደለም፡፡ በጥይት ግንባራቸውን መምታት በምንም መንገድ ሕጋዊ ሊሆን አይችልም፡፡ በተለይ ሰመጉ ይፋ ባደረገው መረጃ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የፌዴራል ፖሊስና የኦሮሚያ ልዩ ኃይል በግድያው መሳተፋቸው ብቻ ሳይሆን አንዳንዶቹ ሟቾች ወደ መስጊድ ሲሄዱና ትምህርት ቤታቸው ላይ መገደላቸው ‹‹እንዴትና ለምን?›› ያስብላል፡፡
ሌላው በተለይ የሰመጉ ሪፖርትና የተጎጂዎች የስም ዝርዝር አስደንጋጭ አንድምታ በኦሮሚያ ቤት ንብረታቸው የተቃጠለባቸው አብዛኛዎቹ አርሶ አደሮች የሆኑበት 800 አባዎራዎች ጉዳይ ነው፡፡ የእነዚህ ዜጎች ስም ዝርዝር እንደሚያሳየው ጉዳት የደረሰባቸው በአብዛኛው የኦሮሞ ብሔረሰብ አባል ያልሆኑና ‹‹መጤ›› ኢትዮጵያዊያን መሆናቸው ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሰውን ውድመት ተከትሎ ኩም ቁሊት ቀበሌ በተባለ ሥፍራ ‹‹መጤዎቹ›› 96 የኦሮሞዎችን ንብረት ማቃጠላቸውም ተጠቅሷል፡፡ ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦሕዴድ/ አባላትና የሥራ መሪዎች ቤት ንብረትም ወድሟል፡፡ ይኼ ያልተሸፈነ እውነት ታዲያ ኢሕአዴግ ከሚለው ‹‹ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ተፈጥሯል›› ጋር እንዴት ይታረቅ ይሆን? ያስብላል፡፡
በሰመጉ ምርመራ ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡ የየአካባቢው ነዋሪዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠይቀው በሰጡት አስተያየት ‹‹ይኼ ሕዝብን በሕዝብ ላይ የማነሳሳት ድርጊት የሚፈጸመው በዋነኛነት በጥቂት የራሳቸው ያልሆነውን መሬትና ሀብት ለመንጠቅና ያለአግባብ በሚፈለጉ የአካባቢ ሀብታሞች አነሳሽነትና መሪነት እንዲሁም በመሰል ጥቅም ፈላጊ ባለሥልጣኖች አይዞህ ባይነት ነው፤›› ብለዋል ሲል ሪፖርቱ ገጽ 30 ላይ አስፍሮታል፡፡
የዘንድሮው የሰብዓዊ ጥሰት በኦሮሚያ ብቻ አልነበረም፡፡ ሰሞኑን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት በአማራ ክልል በቅማንት የማንነት ጥያቄ ስም በሰሜን ጎንደር በተለይ መተማ፣ ጭልጋና አርማጮህ የ96 ዜጎች ሕይወት እንዳለፈ ገልጿል፡፡ ከ100 በላይ ቁስለኛና በመቶዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶችና ሱቆች መቃጠል መገለጹ ሲታሰብ የምን ያህል ዜጎት ሕይወት እንደተመሰቃቀለ መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ኮሚሽኑ ክልሉ ሕዝቡን ይቅርታ እንዲጠይቅ የውሳኔ ሐሳብ ሰጥቶ ፓርላማው አፅድቆ ወስኗል፡፡
ሲያልፍ ቀላል ቢመስልም በግጭቱ ለምን የሱዳን ጎንደር የምዕራብ ዋና መንገድ ለአንድ ሳምንት ተዘግቶ ነበር፡፡ የጎንደር ማረሚያ ቤት ቃጠሎና መሰበር እንዲሁም እስካሁንም ያንዣበበ ፍርሃትና መጠራጠር የዚያው መዘዝ አካል ነው፡፡ የኮሚሽኑ ሪፖርት የሚያሳየው ግን የዚያ ግጭት መዘዝ የቅማንት ሕዝብን ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ በፍጥነትና በሕጉ መሠረት ያለመመለስና የውጭ ጽንፈኛ ኃይሎች ያነሱት ሰፊ ቅስቀሳ ነው፡፡
የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ሆነ ሰመጉ የማጣሪያ ግምገማና ሪፖርት አያቅርቡበት እንጂ በምዕራብ ትግራይ ጠገዴ አካባቢ የሚኖሩ የአማራና የትግራይ ብሔር ዜጎች ‹‹የማንነት›› በሚመስል ጥያቄ ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ተፈናቅለናል ተሰደናል ከሚባሉት በላይ የደረሱበት ያልተውቁ እየተባለ መረጃ የሚወጣባቸው ዜጎች ጉዳይ የአገሪቱን ፖለቲካ ክፉኛ የሚያጨልሙ ናቸው፡፡
አሁን ሪፖርቱ በማንም ይውጣ በማን ዜጎች በየአካባቢው ተገድለዋል፣ ቆስለዋልና ታስረዋል የሚለው ገለጻ የሚያሻማ አልሆነም፡፡ ስደትና ውጣውረድም ከዚህ ተነጥሎ ሊታይ አይችልም፡፡ ለዚህ ፀረ ሕገ መንግሥታዊ ክስተት እውን መሆን መብታቸውን ተላልፈውና ባልተገባ መንገድ ሁከት ያስነሱ ዜጎች ቢጠየቁም፣ በተለይ አላግባብ ሕይወታቸው ያለፉ ንፁኃን ደምም ፍርድ ሊያገኝ ይገባል፡፡ የሁከቱ መቀስቀስ መንስዔ የሚባሉትም (መንግሥትም ይሁን ተቃዋሚዎች)ም ይቅርታ ጠይቀው አልያም ተጠያቂ ሆነው ከሒደቱ ትምህርት ካልተወሰደ ሪፖርቱም ሆነ ማጣራቱ ፍሬ አልባ ናቸው፡፡
ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ አገሪቱ በአንፃራዊ ሰላምና ዴሞክራሲ ሒደት ገብታለች፡፡ በዚህም ውስጥ እየመጣ ያለ ፈጣን ልማትና ለውጥ አለ የሚሉ ወገኖችን ያህል፤ የፌዴራል ሥርዓቱ ከአንድነት ይልቅ መነጣጠልን፣ ግጭትና ሁከትን አምጥቷል የሚሉም አሉ፡፡ መንግሥትም በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተደራጁ ወይም ሰላማዊ ሠልፍ ያደረጉ ዜጎችን በጥይት ከማስገደል አልታቀበም የሚሉ ድምፆች ይሰማሉ፡፡
ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ በአርባ ምንጭ፣ በሐዋሳና በጎንደር ከተሞች በሃይማኖት ግጭት ስም፤ ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ ለተደጋጋሚ ጊዜ በተለይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኦሮሚያና የአሞቦ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጥያቄ በግድያ ተመልሷል፡፡ ከሁሉ በላይ ከምርጫ 97 በኋላ ይፋ በሆነ የምርጫ ውጤት በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች በተለይ በአዲስ አበባ በመንግሥት ተጠቂዎች የተገደሉ ከ196 በላይ ዜጎች ሕልፈት ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ነው፡፡
ዘንድሮ በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተከሰተው የሕዝብ ጥያቄና ሁከት ሲታይም በ25 ዓመታት የዚህ መንግሥት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት የተከሰተበት ነው፡፡ ከ280 በላይ ዜጎች ግድያና ያንኑ ያህል ቁስለኛ ያውም በግልጽ ‹‹ታጥቀዋል›› ሊባሉ በማይችሉ ዜጎች ላይ መድረሱ ‹‹የተመጣጠነ ዕርምጃ›› ወሰኑ እምን ድረስ ነው ያስብላል? በዚህ ድርጊት ውስጥስ የገደለ፣ ትዕዛዝ የሰጠ ወይም የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን ያቀነባበረ ካልተጠየቀ በምን ሊጠየቅ ይሆን?
የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ሆነ ሰመጉ ሁለቱም የተስማሙበት ‹‹የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን›› ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለመንግሥት እንዴት? የት? መቼ? ለምን? እና በምን? የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊፈጸም ቻለ የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ዕድል የሚሰጠው ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ‹‹ያካተተ›› ሕገ መንግሥትን አንቀጾች በመጥቀስ ብቻ ‹‹ዴሞክራቶች›› ነን ለማለት አይቻልም፡፡ ሕዝብ አልተከፋም ይደግፈናል እያሉ መታበይም አጉል ልበድፍንነት ነው፡፡
ሌላው ከሪፖርቶቹ ውዝግብ በመውጣት ትምህርት ሊወሰድበት የሚገባው ተግባር በቀጣይስ ለዘለቄታው ችግሮቹ እንዴት ተፈቱ፤ እየተፈቱስ ነው ማለት ሲቻል ነው፡፡ አሁንም ድረስ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ‹‹ወታደራዊ›› አስተዳደር የሚመስል ውጥረት አለ፡፡ በከፋ ሙስናና አገር አጥፊ ምዝበራ የተጠረጠሩ የመንግሥት አካላት ወይ በሥልጣን ላይ ናቸው፣ አልያም ከኃላፊነት ቢነሱም ሲጠየቁ አልታዩም፡፡ (ሰሞኑን ቱባ የሚባሉ አንዳንድ ተጠርጣሪዎች እየተያዙ ቢሆንም)
በአዲስ አበባ ዙሪያም ሆነ በከተማ ዳርቻዎች በሕገወጥ መንገድ የተያዙ መሬቶች ጉዳይ አሁንም በእንጥልጥል ላይ ነው፡፡ ግማሹ በግብረ ኃይል ሲፈርስ፤ ሌላው ከመንግሥት አካላት መረጃ አገኘሁ ‹‹አንነካም››፣ እያለ ሲሻሻጥ ይውላል፡፡ የአዲስ አበባና ፊኒፊኔ ዙሪያ የጋራ ማስተር ፕላን ጉዳይም በምን ሁኔታ እንደተቋጨ ግልጽ መረጃ ሲወጣ አልታየም፡፡
በአማራና በቅማንት ማኅበረሰብ በኩልም ተንጠልጥሎ የቀረ አጀንዳ አለ፡፡ ሌላው ቀርቶ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የምክር ቤት አካላት ሳይቀር ውሳኔ ትክክል እንዳልሆነ በሌሎች ግፊት እየተቀነቀነ እንዳለ ‹‹የማንነት ጥያቄ›› ይነገራል፡፡ እንዲሁም በኦሮሚያ፣ በደቡብም ሆነ በትግራይ ክልሎች እምብዛም ፈጣን መልስ የማያገኙ የማንነት ጥያቄዎች የአማራና የቅማንት በአጭር ጊዜ እንዴት ተጣድፎ ተወሰነ? ለሚለው ጥያቄም በቂ መልስ የሚሰጥ ወገን የለም፡፡
በውጭ የሚኖረው ‹‹ጽንፈኛ›› የተባለው ተቃዋሚ ኃይል ሁሉ ዓላማው ሥልጣን ማግኘት መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ስለሆነም የተለያዩ ማደናገሪያዎችንም ሆነ የሕዝብን ሥጋቶችን ቢያቀጣጥል እንደመደበኛው ሥራው ነው ሊቆጠር የሚችለው፡፡ ሕዝቡም ይህንን ይዞ ቢነጉድ የሚጠበቅ ነው፡፡
ከዚያ ይልቅ መፍትሔው ያለው በመንግሥት እጅ ነው የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ በአንድ በኩል የሕዝብ አመኔታን ባተረፈ መልኩ አሳታፊና ግልጽ በሆነ መንገድ መሥራት አለበት፡፡ መሬት ሲሸጥ፣ ወሰን ሲለይ፣ ማንነት ዕውቅና ሲያገኝ ወዘተ. ሕዝብ ካላወቀ ማን ሊያውቅ ነው? ሌላው ተጠያቂነት የሚባለውን የገዘፈ ጉዳይ ከመሸርሸር ሊወጣ ግድ ይለዋል፡፡ ሌባን፣ ሙሰኛን፣ ጠባብና ዘረኛን፣ ትምክህትኛና ጽንፈኛና፣ አክራሪና ሌላውንም ወንጀለኛ መንግሥት ደፍሮ ለሕግና ለሕዝብ ካልሰጠ ማን ሊቀበለው ይችላል?
በመጨረሻ መንግሥት ሆደ ሰፊ፣ ይቅር ባይና ይቅርታ ጠያቂ መሆን አለበት፡፡ አሁን በተነሳንበት ርዕስ ጉዳይ አንፃር በመንግሥት ትዕዛዝ ሥር ያሉ ተጠያቂዎች ንፁሐንን ገድለዋል፡፡ በማወቅም፤ በድፍረትም ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን እነዚህ በወገኖቻቸው ላይ የተኮሱ ተጠያቂዎች ላደረሱት በደል መንግሥት ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ፣ የተበደለን መካስና አገር ማረጋጋት አለበት፡፡ በተጨባጭ ወንጀል ያልተጠረጠረ እስረኛም ካለ ይቅር ሊባል ግድ ነው፡፡
ከሁሉ በላይ ሕዝቡን ያስቆጣውን ጉዳይ በግልጽ ለይቶ ፊት ለፊት መታገልና ውስጥን መፈተሽ ይገባል፡፡ ችግሩ ሌላ ሆነ ወደ ውጭ ብቻ ጣትን መቀሰር (ለምሳሌ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማሳደድ) እንደመፍትሔ ከተወሰደ ያለጥርጥር ነገም መፍትሔ አይመጣም፡፡ በራሳችን ዜጎች ሕጋዊ ዕውቅና ባላቸው ተቋማት እየወጡ ያሉ አወዛጋቢ የሰብዓዊ መብት መግለጫዎችም ከፕሮፓጋንዳ ያለፈ ትርጉም አይኖራቸውም፡፡ ስለዚህ ሁሉም ራሱን ለተጠያቂነት ያዘጋጅ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
