በይነበብ ባህሩ
አዲስ አበባ ከተማ በአየር ካርታና በነባሩ የመሬት ይዞታ ክልሉ 54 ሺሕ ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያላት፣ በአፍሪካ በፍጥነት እያደጉ ከመጡ ከተማዎች በቀዳሚነት የምትጠቀስ ናት፡፡ መታወቂያ የሌለውና በደባልነት የሚኖረው ሕዝብ ሳይቆጠርም እስከ 3.8 ሚሊዮን ሕዝብ ይኖርባታል፡፡ ከተማዋ ከአገራዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መዲናነቷ ባሻገር የአኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶችና ማኅበራት መገኛ መሆን ጀምራለች፡፡
በዚህና መሰል በጎ ገጽታዎች መካከል አሁንም የኤሌክትሪክ ኃይልና ንፁኅ የመጠጥ ውኃ እጥረት ካለባቸው ከተሞች መካከል ትመደባለች፡፡ ምንም እንኳን የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮምና የመሠረተ ልማት ግንባታ በፍጥነት እየተቀረፉ የመጡ ቢሆንም፣ ከመኖሪያ ቤት እጥረት፣ ከትራንስፖርት አለመሟላት፣ ከኑሮ ውድነትና ከሌሎች ማኅበራዊ ፈተናዎች (ልመና፣ ሴተኛ አዳሪነት፣ ሌብነት …) ጋር በተያያዘ ገና ያልተፈቱ በርካታ ችግሮችም የታጨቁባት ናት፡፡
በዛሬው ሒሳዊ አስተያየቴ ግን ከተማዋን ክፉኛ እየፈተነ ስላለው የመሬት ይዞታ ወረራ ሕገወጥነትና ሙስናን አስመልክቶ አንዳንድ ነጥቦችን እናወጋለን፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግር እንደ ሪፖርተር ጋዜጣ የሞገተ ባለመኖሩ ደግሞ ምልከታዬ በዚሁ ጋዜጣ ላይ እንዲሰፍር አነሳስቶኛል፡፡ እርግጥ የአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤትና የመሥሪያ ቦታ ችግር ከምስቅልቅሉ አካሄድ ይወጣ ይሆን ማለትም እፈልጋለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ በከተሞች ያለው ዜጋ የመኖሪያ ቤት እንደ ልቡ የሚሠራበት ዕድል እየጠበበ ነው የመጣው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ባለርስትና ፊውዳሉ ወይም ለገዥው መደብ የቀረበው ወገን በስፋት ይይዘው የነበረው ቦታና ቤት ከደርግ ሥርዓት መምጣት ጋር ሲያከትም፣ እንደ ልብ ቤትና ይዞታ መያዝ የሚቻል አልነበረም፡፡ ያም ሆኖ ከ1996 ዓ.ም. በፊት ቤት አልሚ ግለሰቦች እንደነበሩ መካድ አይቻልም፡፡
በከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅ ቁጥር 47/1967 መሠረት ወደ መንግሥት የዞሩት ቤቶች ሲታዩ የግለሰብ ይዞታ ምን ያህል ሰፊ ድርሻ እንደነበረው መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ያም ሆኖ ደርግ የሚከተለው የሶሻሊስት ሥርዓት በአንድ በኩል በቤት ልማት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችን የማያበረታታ፣ በሌላ በኩል የግል ቤት ግንባታ በተለይ ለኪራይ የሚውል ግንባታ ለመሥራት የሚያስችል አልነበረም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ዜጎች (ምንም እንኳን የሕዝቡ ቁጥር እንዲህ እንደ አሸን ባይፈላም) አንገት ማስገቢያ ጎጆ የሚሠሩበት እራፊ መሬት የሚቸገሩ አልነበረም፡፡
ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ ሥር ነቀል ሕገ መንግሥታዊ ዕርምጃ ከተወሰደባቸው መስኮች አንዱ መሬት ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 መሠረት ‹‹መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት›› በመሆኑ ዋነኛው የአገሪቱ መሬት ባለይዞታ ሕዝብና መንግሥት ብቻ ናቸው፡፡ ግለሰብ መሬት ላይ ያረፈ ቤትና ንብረት ይኖረው እንደሆነ እንጂ የመሬት ባለቤትነቱ አብቅቷል፡፡
ይህን በመርህና በሕገ መንግሥት የፀና ድንጋጌ እያፈረሰውና ጥርሱን እያወላለቀው የሚገኘው አደጋ ግን ሕገወጥነት፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር ሆኗል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች አንዳንድ ሕገወጥ ባለሥልጣናት፣ ደላላና ጉዳይ ገዳይ በጥምር በጀመሩት ዘመቻ ‹‹የመሬትና የቤት ባለቤት መሆን የሚሻውን ዜጋ›› ለከፍተኛ ጉዳት እያጋለጡት ይገኛሉ፡፡ መንግሥትም ጀምሬዋለሁ በሚለው ፍትሐዊ ልማት የማረጋገጥ ትግል ውስጥ ሕገወጥ ድርጊት ዋነኛ እንቅፋት ሆኖ ተደንቅሯል፡
ሰሞኑን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ከሃና ማርያም ቤተ ክርስቲያን አለፍ ብሎ በሚገኘው ‹‹ቀርሳ ኮንቶማ›› የሚባል አካባቢ በሰነድ አልባ (ጨረቃ) ቤቶች ላይ የደረሰው ክስተት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ እነዚህ 20 ሺሕ የሚደርሱ ቤቶች በአማካይ በቤት አምስት ቤተሰብ ቢኖር ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ቦታ ይዘውና ቤት ሠርተው መኖር የጀመሩ ነበሩ፡፡ ይህ ከነደብረ ብርሃን፣ ደብረ ማርቆስ፣ ኮምቦልቻና ወልድያ ዓይነት የዞን ከተሞች የሚመጣጠን ሕዝብ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡
እንግዲህ መራራውን እውነት መፈተሽ የሚያስፈልገው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ይህን ሁሉ መሬት ከሕገወጥ ደላሎችና አጭበርባሪ የወረዳ አስተዳዳሪዎች ወይም ከአካባቢ ገበሬዎች ሲገዙም መንግሥት የት ነበር? ሲባል ነው፡፡ የከተማዋ አስተዳደርስ ይህን ያህል ጊዜ በስብሰባና በግምገማ ‹‹ልቡ ሲጠፋ›› እንዴት ችግሩን አላየውም? ሌላው ይቅር እነዚህ ወገኖችን እንደ ሕጋዊ በመቁጠር ኤሌክትሪክ፣ ውኃና የውስጥ ለውስጥ መንገድ እንዲገባላቸው ማን አደረገ? የሚሉ ጥያቄዎችን መምዘዝ ሲቻል ነው፡፡
አሁን እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያስረዱት ሕገወጦች በሙስና በተዘፈቀውና በነፍስ ወከፍ ከመሬት ወራሪዎች በአሥር ሺዎች ጉቦ እያስከፈሉ ነበር ይኼ ሁሉ ቤት የተሠራው፡፡ በዚሁ መዘዝም ራሳቸው የፈቀዱትና ጉቦ ሲለቃቅሙ የኖሩት ሕገወጦች ‹‹ና ተነሳ›› ብለው ሲያወያዩት ‹‹ሆ›› ብሎ አንገት ለመቁረጥና ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ወጥቶ ለመግደል እሰከመነሳት ደርሷል፡፡ ነገ ከነገወዲያም ከቂምና በቀል ስለመውጣቱ፣ በሥርዓቱ ላይም ኩርፊያ ስላለመሰነቁ ማረጋገጫ ማስቀመጥ ያዳግታል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአሁኑ ጊዜ 54 ሺሕ ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት አላት ቢባልም፣ ከፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ከተሞች ጋር በምትጎራበትባቸውና በከተማዋ ዳርቻዎች ከ150 ሺሕ ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆን መሬት በሕገወጥነት እንደተያዘ ይገመታል፡፡ ይህ የሆነው በውስጥ ለውስጥና በኪስ ቦታዎች ላይ ከተያዙ ሥፍራዎች ውጭ ሲሆን፣ በአብዛኛው ያለ ካርታ ከአርሶ አደር በተገዙ መሬቶች ላይ የሰፈሩ ናቸው፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ የሕዝብና የአገር ሀብትስ እንዴት መፍትሔ ሊያገኝ ነው? ብሎ ሲታሰብ ሌላ ራስ ምታት ይቀሰቅሳል፡፡ ድርጊቱስ (ሕገወጥ ወረራውና የውንብድና መሬት ሽያጩ) በምን ይቆም ይሆን? ብሎ መፈተሽ ግድ ይላል፡፡
የአዲስ አበባ የቤት ረሃብ ሕገወጥነትን አስፋፍቶ ይሆን?
በአዲስ አበባ ከተማ እስከ ቅርብ ጊዜ ባለው መረጃ 150 ሺሕ ቤቶች በቀበሌ አስተዳደር ሥር ናቸው፡፡ ከነዋሪው መካከልም የግል ይዞታ አለው የሚባለው ከ38 በመቶ ያነሰ ነው፡፡ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ተቋማት የያዙት ቦታም እስከ 18 በመቶ የመሬት ይዞታ እንደሚሸፍን ይገመታል፡፡ ከዚህ ሌላ መንገዶች፣ አረንጓዴ ቦታዎችና ክፍት መሬቶችም የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡
በ1999 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው የአገሪቱ ስታስቲክስ መረጃ እንደሚያስረዳውም በአዲስ አበባ እስከ 700 ሺሕ የሚደርሱ ቤቶች በግለሰብ ይዞታ ሥር ናቸው፡፡ ይሁንና ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በከተማዋ አቅም ኖሮት በቤት አልባነት እየተፈተነ ካለው የተከራይነት እስር ቤት ለመውጣት የሚፈልገው የከተማዋ ነዋሪ ቁጥር ከ1.5 ሚሊዮን በላይ እንደሆነም በሌላ የከተማ የአስተዳደሩ የዳሰሳ ጥናት ተረጋግጧል፡፡ እንግዲህ ይህ ቁጥር ከክልል ወደ አዲስ አበባ መምጣት የሚሻው፣ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው፣ ዕድሜና ኢኮኖሚ ‹‹ጎጆ እንዲወጣ›› ከሚያነሳሳው ሕዝብ ጋር ተዳምሮ ሲታይ የት እንደሚደርስ መገመት ይቻላል፡፡
እርግጥ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በተለይ ከ1998 ዓ.ም. ወዲህ የቤት ልማት መርሐ ግብርን አማራጭና ወሳኝ መፍትሔ ማድረጉ አንድ ጠቃሚ ዕርምጃ ነው፡፡ እስካሁንም 56 በሚደርሱ የአገሪቱ ከተሞች ከ250 ሺሕ በላይ የጋራ የኮንዶሚኒየም የቁጠባ ቤቶች ተገንብተው ለዜጎች ተላልፈዋል፡፡ ከዚህ ውስጥም ከ143 ሺሕ በላይ የሚሆኑት በአዲስ አበባ ከተማ ተገንብተው መተላለፋቸው ቢያንስ አብጦ ሊፈነዳ የደረሰውን የመኖሪያ ቤቶች ችግር ማስተንፈስ ችሏል፡፡ አሁን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተጨማሪ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች በመገንባት ላይ ናቸው፡፡
በግል ሪል ስቴት ልማትና የተሻለ አቅም ባላቸው የቤት ሠሪ ማኅበራት የተሠሩ፣ እንዲሁም በሕጋዊ የመሬት ጨረታ በሊዝ ተወዳድረው ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት የገነቡ ከሩብ ሚሊዮን የማያንሱ የከተማዋ ቤቶችም አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ከፍተዋል፡፡ በጀሞ፣ ላፍቶ፣ አያት፣ ሲኤምሲና መሰል አካባቢዎች አዳዲስ መለስተኛ ከተሞች የፈጠሩ ግንባታዎች ለአባባሉ አብነቶች ናቸው፡፡
እንዲህም ሆኖ የአዲስ አበባን የመኖሪያ ቤት ረሃብ ማስታገሻውን አላገኘም፡፡ ለጋራ ኮንዶሚኒየም ባለዕድለኝነት ተመዝግበው ዕጣ የሚጠብቁ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ገና ቤቶች ልማትን እየተማፀኑ ነው፡፡ ሕገወጥ የመሬት ወረራው ላይ እየተዋከበ ውስን የሆነውን የደሃ አገር የግለሰቦች ሀብት እያስበላ ያለውም ‹‹የጨነቀው እርጉዝ ያገባል›› እንዲሉ ሆኗል፡፡
እንግዲህ ጥያቄው የከተማዋንና የአገሪቱን ነዋሪዎች የቤት ችግር ለመፍታት የታዩና ያልዩታ መፍትሔዎችን ሁሉን አሟጦ መጠቀም አያስፈልግም ወይ? ሲባል ነው፡፡ ለምሳሌ በጋራ ኮንዶሚኒየም ግንባታ ረገድ ዕጣ ከሚወጣባቸው ቤቶች በተጨማሪ፣ ‹‹ለመልሶ ማልማት ምትክ ቤት፤›› እየተባለ በሺዎች ከሚቆጠሩ የቀበሌ ቤቶች ለመሀል ከተማ ተነሽዎች በዱቤ ይሸጣል፡፡ መንግሥት ግን የመሀል ከተማ ቦታዎችን እያፀዳ በውድ ዋጋ ለቢዝነስና ለሌላ ዘርፍ እየሸጠ ነው፡፡ ግን ይህን ከኮንዶሚኒየም ባነሰ ምትክ አነስተኛ የቁጠባ ቤቶችን በተለይ አሁን በሕገወጥ መንገድ በተወረሩ አካባቢዎች መሥራት አይቻልምን?
ሌላው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅ 47/1968ን ተከትሎ በተለያየ ስምና ቅርጽ የቀጠለ ተቋም የመንግሥት ቤቶችን እያከራየ ያለ ነው፡፡ በቅርቡ ለፓርላማ ሪፖርቱን ሲያቀርብ እንደሰማነው ግን የያዛቸውን ዘመናዊ ቪላዎችና አፓርትመንቶች በቅናሽ ዋጋ በማከራየቱ የሚያስገባው ገቢ በዓመት ለኪራይ የሚወጣውን እንኳን ለመሸፈን አላስቻለውም፡፡ በዚያ ላይ የገነነ የሙስናና የአድልኦ ድርጊት የሚፈጸምበት ነው፡፡ ‹‹በመቶዎች ብር የተከራዩ አንዳንድ ሰዎች የራሳቸውን ቤት ሠርተው በአሥር ሺዎች ለሦስተኛ ወገን አከራይተው የሚኖሩበት፣ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት የራሳቸውን ቤት አከራይተው የሚኖሩበት፣ ለሥርዓቱ አገልጋዮችና የቅርብ ሰዎች ካልሆነ ዜጋው የማይጠቀምባቸው ቤቶችን የሚያስተዳድር የኢፍትሐዊነት ተምሳሌት፤›› የሚለውን ጥብቅ ትችት መቅረፍ ያልቻለ ተቋም ነው፡፡ እዚህ ላይ ለምን ‘ሪፎርም’ ማሰብ አልተለቻለም?
ተጨማሪው መፍትሔ መንግሥት ‹‹እኔ ብቻ ቤት ልሥራ›› ከማለት መውጣት አለበት የሚለው ነው፡፡ እርግጥ ለግል የቤት አልሚዎች (ሪል ስቴቶች) በመፈቀዱ በሕዝብ መሬት የተንደላቀቁ የቅንጦት ቤቶች ተገንብተው ለከፍተኛ ገቢ ያለው ዜጋ እየተሸጡ ነው፡፡ ይህ ግን ደሃውንና መካከለኛ ገቢ ላይ ያለውን አይታደግም፡፡ ስለዚህ በመንግሥት ድጎማ፣ በሕዝብ መሬት ላይ ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸውን ቤቶች የሚሠሩ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ተቋራጮች መግባትና ማልማት አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ እጥረቱን በማይሆን መፍትሔ ለመፍታት እጅግ አዳጋችና ፈታኝ መሆኑ ሊጤን ይገባዋል፡፡
ገጠሬው እያጥለቀለቃት ያለው አዲስ አበባ ምን ይበጃት?
ኢትዮጵያ ከአገር ውስጥ ወደ ውጭ የሚደረገው ስደት ብቻ አይደለም የሚያስጨንቃት፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ (በተለይ ወደ አዲስ አበባ) እየተባባሰ የመጣው ፍልሰት ነው፡፡ ስለዚህ አባባል ጥሩ ማሳያው ከሊስትሮና ከሎተሪ ሻጭ አንስቶ እስከ ትልልቁ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከከተማዋ ‹‹ልጆች›› (አራዶች) ይልቅ የገጠሩ እያጥለቀለቋት መሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም በሌሎች አካባቢዎች ያፈራውን ሀብት ይዞ፣ ቤት ንብረቱን እየሸጠ ጭምር ወደ አዲስ አበባ በየጊዜው እየተመመ ያለው ዜጋ እየበረከተ ነው፡፡
ይህን ፍልሰት አስመልክቶ ጠንከር ያለ ጥናት ስለመደረጉ መረጃ ባይኖርም፣ መነሻውን አስመልክቶ ግን ግምታዊ መላምት ማስቀመጥ ይቻል ይሆናል፡፡ አንደኛውና ዋናው የተሻለ ሥራ ለማግኘትና የተሻለ ሕይወት ለመኖር (በተለይ ትምህርት ለማግኘት) ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ ክልሎች እየታየ ያለው የሰላም ዕጦትና ‹‹የመኖር ዋስትና ማጣት›› (ኦሮሚያና ጋምቤላን በመሰሉ ክልሎች) እንዲሁም በደቡብ ክልል ጥቂት ዞኖች ከነባሩ ውጪ ያለውን ዜጋ ለመግፋት የሚደረገው ሙከራ አቅም ያለው ‹‹መንግሥት ወዳለበት ልጠጋ›› እንዲል እያደረገው ይመስላል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ከወራት በፊት ባቀረበው የገጠር-ከተማ ፍልሰት መለስተኛ ጥናት ‹‹በገጠር የመሬት መጣበብ ችግር በቁራሽ የእርሻ መሬት ላይ የሚሰፍረው ሰው ብዛትና የነፍስ ወከፍ መሬት ድርሻ በየጊዜው ማነስ በገጠር ሥራ አጥነት ያስፋፋል፣ ብዙ የሥራ ኃይልና ጉልበት ይወዝፋልና ወደ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት ያባብሳል፤›› ሲል ደምድሟል፡፡ አሁን በአገሪቱ ያለው ያለ ሥራ የተቀመጠው ጉልበት (Sulplus Labour) ከ600 በመቶ በላይ እንደሚደርስ በማስመልከት ነው፡፡ ብዙዎቹ በሕገወጥ መንገድ የተያዙ መሬቶችና ሕገወጥ ግንባታዎች እየተፈጸሙ ያሉት ከክልል በመጣው ኃይል መሆኑ ሲታይ የድምዳሜውን ትክክለኛነት ያረጋግጣል፡፡
እንግዲህ ለዚህም መፍትሔ ማበጀት ለነገ የሚባል ሥራ አይሆንም፡፡ አንደኛው በገጠር ከግብርና ወደ ሌላ መስክ ትራንስፎሜሸንን ማፋጠን ግድ ይላል፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራውም ያለማቅማማት ሊገባበት ይገባል፡፡ ከሁሉ በላይ የፌዴራሊዝምን ‹‹ለብሔር ባርኔጣና ለጠባብነት ልክፍት ማቀንቀኛ›› እያደረጉ ያሉ መንግሥት ውስጥ ያሉ ሰዎች፣ ፖለቲከኞችም የሚባሉ ጥገኞች በይፋ ቁጣና ተግሳጽ ሊደርስባቸው ይገባል፡፡ መወገዝም አለባቸው፡፡ የዜጎችን ተንቀሳቅሶ የመሥራትና በየትም የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብቶች እየገፉ አገር ለመገንባት ማሰብ ከንቱ ጨዋታ ነው፡፡
ማጠቃለያ
አዲስ አበባ የሁላችንም ከተማ ነች፡፡ ሕገወጥነትንም የምታገለው ሁላችንም መሆን አለብን፡፡ በተለይ ግን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ መታገልና ማስተካከል አለበት፡፡ በመሬት ወረራ ላይ የታየው መዘናጋትና ‹‹የመሬት ባንክ አለን›› እየተባለ ሥውር ሕገወጥነትን ማበረታታት በፍፁም መታረም አለበት፡፡ ይህ የደሃ ዜጎችን ሀብት ለጥቂት ዘራፊዎች እየማገደ ያለ ድርጊት ዛሬ የሕይወት ዋጋም ማስከፈል ጀምሯል፡፡ ነገ በጊዜ ካልታረመም ዕዳው ከዚህ የባሰ ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡን ያሳተፈና በሆደ ሰፊነት የተያዘ የትግል ሥልት በመከተል ሳያቅማሙ ውጤት ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ያለጥርጥር ትግሉም ከውስጥ መጀመር አለበት፡፡
ሕዝቡም ቢሆን ከሙሰኛውና ከኪራይ ሰብሳቢው እግረ ሙቅ መላቀቅ አለበት፡፡ መንግሥት መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው ብሎ በቁጠባ ሲሸጥ እያየ በሕገወጥ መንገድ በአቋራጭ መግባትን ምን አመጣው? እየተጠረጠረ ገብቶ በመከራ ያገኘውን ሀብትስ ስለምን ይበትናል? ከዚህ ይልቅ ሕጋዊውን መስመር ተከትሎ፣ መንግሥት ላይም ተፅዕኖ እያሳደረ የቤት ባለቤት መሆን ለምን አይመርጥም መባል ይኖርበታል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው yinebeb@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡
