Quantcast
Channel: ዓለማየሁ ጉጀ
Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

ትናንት ዛሬ አይደለም

$
0
0

በመርሃጽድቅ መኮንን ዓባይነህ

የኋላ ታሪካችንን ብቻ ደጋግመን በመጥቀስ ስለቀድሞው ታላቅነታችን ያለመታከት ስናወራና ይህንኑ አስመልክቶ የተለያዩ ዲስኩሮችን በየጊዜው ስናሰማ እንደመጣለን፡፡ ይህ ነው የሚባል ጥያቂ በሌለበት ወይም አስተማማኝ ማረጋገጫ ልናቀርብ በማንችልባቸው አጋጣሚዎች ሳይቀር እኛ ሐበሾች ‘ከሁሉም አንደኞች ነን’ ማለቱ አብዝቶ ይቀናናል፡፡ እስከተቻለ ድረስ በየትኛውም ዘርፍ አንደኝነት የሚጠላ ነገር አይደለም፡፡ ሆኖም በምኞት ፈረስ ስለጋለብን ብቻ በቀላሉ የምናገኘው አይሆንም፡፡

በእርግጥ የኋሊት ስንመለከት አኩሪና ፋና ወጊ የሆነ የነፃነትና የተጋድሎ ታሪክ እንዳለን እኛ ብቻ ሳንሆን መላው ዓለም ያለጥርጥር ያውቀዋል፡፡ ሆኖም ይህ የቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ውርሰ ታሪክ ብቻውን እስካሁን ከምንገኝበት ጎስቋላ የኑሮ ደረጃ አንድ ዕርምጃ እንኳ ፈቀቅ አላደረገንም፡፡

ስለሆነም በራሳችን ላይ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት የምንፈልግ ከሆነ በዚህ ረገድ እርማት የሚያስፈልጋቸው አያሌ ጉዳዮች አሉብን፡፡ ለምሳሌ (ለምለሚቱ ኢትዮጵያ) የሚለው ዝነኛው፣ ግና ደግሞ አደናጋሪው የዘወትር እንጉርጉሮአችን ከደን መራቆት፣ ከለም አፈር መከላትና ከበረሃማነት መስፋፋት የተነሳ የአገራችንን ለተደጋጋሚ ጊዜ በከፍተኛ ድርቅ መመታትና የሕዝባችንን ለችጋር መጋለጥ በቅርብ ለተከታተለ ማንኛውም ሰው ፍፁም እንቆቅልሽ ሳይሆንበት አይቀርም፡፡

ታዲያ እስከ መቼ በዚህ ዓይነቱ ራስም አዘውትሮ የመሸንገልና የማታለል አባዜ ክፉኛ እንደቆዘምን እንኖራለን? ስለራሳችን ያለን የተዛባ ሥዕል ሳይውል ሳያድር በአፋጣኝ መስተካከል ይኖርበታል፡፡ ለረዥም ጊዜ ሳያቋርጥ የቀጠለው ይኸው ቅዠታችን ከቶ እንዳላዋጣን መተማመን ይኖርብናል፡፡

እዚህ ላይ ላንዳፍታ ቆም ብሎ ማሰብ ይበጀናል ጎበዝ፡፡ የተሻለ አማራጭ ካልጠፋ በስተቀር አምና ሲማስን በከረመ በሬ ዘንድሮ ጠምዶ ለማረስ መሞከሩ እምብዛም አያተርፈንም፡፡ ስለሆነም ለኋለኛው ታሪካችን ያለን ወደር የሌለው ቀናዒነት እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን የምንገኝበትን እጅግ የተወሳሰበ ፖለቲካዊና ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በጥልቀት መመርመርና ያላንዳች ማወላወል መሠረታዊ የአቋም ሽግሽግ ማካሄድ አለብን፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ አገራችን ኢትዮጵያ ባላት ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት ፀጋ ያን ያህል የምትታማ አይደለችም፡፡ ይሁን እንጂ አብዝቶ የሚነገርለት ይኸው ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብቷ ክምችት በሚገባ ለምቶና በልፅጎ የኛን የዜጎቿን ኑሮ ለማሻሻል ከቶ አልተቻለውም፡፡ ከዚህ አንፃር ቀዳሚውን ሥፍራ መስጠትና እጅ ለእጅ ተያይዘን መረባረብ ያለብን ለዘመናት ስንማቅቅ ከቆየንበት አስከፊ የድህነት አዘቅት ቀስ በቀስ ለመውጣትና በዓለም አደባባይ አንገታችንን ቀና አድርገን ለመታየት መሆን ይኖርበታል፡፡ ያኔ ብቻ ነው ስለጠቅላላው ማንነታችን በተለይ ደግሞ ስለትናንቱ አስመኪ ሥልጣኔያችን እንደ ልባችን በኩራት ለመናገርና በአኅጉራዊም ሆነ በዓለም አቀፋዊ መድረኮች ሳይቀር ሊኖረን ስለሚገባው ሥፍራ ሽንጣችንን ገትረን በከፍተኛ መተማመን ብንከራከር ወይም አጥብቀን ብንሟገት የሚያምርብን፡፡

እኛ ኢትዮጵያዊያን ዘመናትን የተሻገረና ቀድሞውኑ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ ፖለቲካዊ ውቅርና ማኅበራዊ እሴት አለን፡፡ ካሸለብንበት ለመንቃትና ከወደቅንበት ለመነሳት ትንሽ መንፈራገጥ ብቻ ይበቃናል፡፡ በዚህ ረገድ የራሳችን የሆነውን ድርሻ በአግባቡ የተወጣን እንደሆነ የሌሎች ተባባሪ ወገኖችን የማያቋርጥ ድጋፍና ዕርዳታ ለማግኘት ከቶ አያዳግተንም፡፡

ያን ያህል አዲስና እስካሁን ያልተለመደ ነገር ነው ባይባልም በቅርቡ እንደተከታተልነው አገራችን ኢትዮጵያ እነሆ እ.ኤ.አ ጁን 28 ቀን 2016 ኒውዮርክ ከተማ ተካሂዶ በነበረው 70ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ አማካይነት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና ለሁለት ዓመታት ያህል ዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ እንድታገለግል ለሦስተኛ ጊዜ መመረጧን እናስታውሳለን፡፡ ሥራዋን በይፋ ከሌላዋ አፍሪካዊት አገር ከአንጎላ የምትረከበውም ከመጪው ጃንዋሪ 1 ቀን 2017 ጀምሮ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለመላው የመንግሥታቱ ድርጅት አባል አገሮች በዙር የሚዳረሰውን ይህንኑ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ መንበረ ሥልጣን ለማግኘት ሰፊና ተከታታይነት ያለው የዲፕሎማሲ ዘመቻ ሲካሄድ እንደቆየ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን አማካይነት ተደጋጋሚ መረጃ እንዲደርሰን ተደርጓል፡፡ አሁንም አብቅቷል ማለት አይቻልም፡፡ ለነገሩ ባሳለፍናቸው በደርግና በአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥታትም ቢሆን ተመሳሳይ ዕድሎችን አግኝተን አገልግለናል፡፡ የመጀመሪያው እ.ኤ.አ ከ1967 እስከ 1968 ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከ1989 እስከ 1990 እንደነበር ይታወሳል፡፡

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ አገራችን ኢትዮጵያ ከመንግሥታቱ ድርጅት መሥራች አገሮች አንዷ እንደመሆኗ መጠን አሁን ለሦስተኛ ጊዜ ለመመረጥ የበቃችበት አጋጣሚ ቢያንስ እንጂ የሚበዛባት ይሆናል ተብሎ የሚገመት አይደለም፡፡ በእርግጥ ዘግይቶ የተገኘው ይህ የመመረጥ ዕድል ሌላው ወርቃማ አጋጣሚ ነውና ቀደም ሲል ይበልጥ በምትታወቅባቸው በሰላም ማስከበርና በዲፕሎማሲ መስኮች እስካሁን ስታደርገው እንደቆየችው ሁሉ፣ ለመንግሥታቱ ማኅበር ተጨማሪ አገልግሎት በማበርከት ተገቢውን ክብርና ሞገስ ልታገኝበት እንደምትችል አያጠራጥር ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ዘወትር የተለጠጠ ታላቅነት አጥብቆ ለሚሰማን ለእኛ ለዜጎቿ አገራችን የተሻለ መኩሪያና መታበያ ልትሆን የምትችለው፣ ቅድሚያውን ለራሷ ውስጣዊ ሰላምና መረጋጋት በመስጠት አበክራ የሠራች እንደሆነ ብቻ ነው፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ የምንገኝበት ጂኦ ፖለቲካዊ አካባቢ ለማያባሩ የእርስ በርስ ግጭቶችና ደም አፋሳሽ ጦርነቶች ክፉኛ የተጋለጠ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያም ከሁሉ በላይ ለራሷ ዘላቂ ደኅንነት ስትል በዙሪያዋ ያሉት እነዚህ ግጭቶች ጨርሶ እንዳይባባሱና እሷንም እንዳይጠቀልሏት በንቃት መቆምና ራሷን በብቃት መከላከል ይኖርባታል፡፡

በእርግጥ እስካሁን በዚህ ረገድ ሰፊ ችግር ነበረባት የሚያሰኝ ጉልህና ተጨባጭ ህፀፅ ታይቶባታል ለማለት አይቻል ይሆናል፡፡ በአንፃሩ ወደ ግጭት የገቡ አጎራባች አገሮችንና ማኅበረሰቦችን ቀርቦ ለመሸምገልና እርስ በርስ ለማስታረቅ የምታሳየው ትጋት፣ በአንድም ሆነ በሌላ ቀላል ያልሆነ ተቀባይነትን እንዳስገኘላት መካድ አይቻልም፡፡

ያም ሆኖ ታዲያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መልሶ ታላቅ ለመሆን ያለንን ፅኑ ምኞት ከወዲሁ የሚያመክኑና ምናልባትም አገራዊ ህልውናችንን ሳይቀር ክፉኛ የሚገዳደሩ፣ ብሎም ከተፈጥሯዊ ልዩነቶቻችን ባሻገር በዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች ሥርዓት ውስጥ እንደ አንድ ሉዓላዊ ምልዓተ ሕዝብ ለዘመናት እርስ በርስ ተደጋግፈን፣ ተሳስረንና ተጋምደን የቆየንባቸውን መሠረታዊ እሴቶች ቀስ በቀስ የሚሸረሽሩና ወደለየለት ውድቀት የሚገፉ ከባድ ፈተናዎች ይደራረቡብን ጀምረዋል፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በፍፁም ድህነትና ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ዝቅተኛ ያኗኗር ሁኔታ ዘወትር መማቀቃችን አንሶ ከዚህ በፊት አይተነውና ሰምተነው በማናውቀው ሁኔታ ዘር፣ ጎሳና ብሔር ለይተን አንዱ በሌላው ላይ የማጎምጎሙና እርስ በርስ የመቆራቆሱ አሉታዊ ዝንባሌና ከዚሁ የሚመነጨው አፍራሽ እንቅስቃሴያችን፣ እንደኔ ወደፊት የመራመድ ምልክት ሳይሆን የኋላቀርነት ማሳያ ነው፡፡

እንግዲህ ለሌሎች ሕዝቦች ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት አበክራ በምትሠራው ውዲቷ አገራችን ውስጥ ለምን ይህ ይሆናል ብሎ ያለይሉኝታ መጠየቅ የአባት ይመስለኛል፡፡ አሁን አሁን መሬት ላይ እንደሚታየው በእጃችን ላይ ያለው የራሳችን ውስጣዊ ሰላም በተለያዩ ምክንያቶች አልፎ አልፎ ሲናጋ፣ የንፁኃን ዜጎች ሕይወት ያላግባብ ሲቀጠፍም ሆነ ንብረት ሲወድም በዓይናችን በብረቱ እየተመለከትን ዝም ማለት አይገባንም፡፡ ይህንኑ ውስጣዊ ችግር ወደ ጎን በመተው እንደ ድሮው ድንበር ተሻግረንና ውቅያኖስ አቋርጠን የሌሎች አገሮችን ሰላምና መረጋጋት ዕውን ለማድረግ እንተጋለን ብንል ፍፁም ግብዝነት ይሆንብናል፡፡ እንግሊዞች ‘‘ችሮታ የሚጀምረው ከቤት ነው’’ ይላሉ፡፡ ስለሆነም ውስጣዊ ሰላማችንን የሚያደፈርሱ ዓይነተኛ ችግሮች በአገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ የተፈቀደውን የመጨረሻ እልባት ልንሰጣቸው ይገባል፡፡ ወትሮውንም ቢሆን በሽታውን የደበቀ መድኃኒት እንደማይገኝለት የታወቀ ነውና፡፡

እስካሁን የችግሮቻችን ሁሉ ዋና ማጠንጠኛ የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕጦት እንደሆነ በመርህ ደረጃ ተግባብተን ይሆናል፡፡ ይህ ግን አጠቃላይ አነጋገር በመሆኑ ለተጨባጭ ችግሮቻችን ተጨባጭ መፍትሔዎችን አላመጣም፡፡ ይልቁንም አጠቃላይ አነጋገር በፀባዩ ዝርዝሮችን በጉልህ አውጥቶ የማሳየት አቅም የለውም፡፡ ዲያብሎስ ደግሞ ከነገረ ቀደም ራሱን የሚወሽቀው በዝርዝሮች ውስጥ እንደሆነ ከወዲሁ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው merha1@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡ 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

Trending Articles