በጌታቸው አስፋው
በወደቀ ዛፍ ላይ ምሳር ይበዛበታል እንዲሉ በርካታ ዓመታት ፈጣን ዕድገት አስመዝግባችኋል እንዳላሉን ሁሉ እነዚህ የዓለም ባንክና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ንግድና ልማት ጉባዔ አሁን ምን ዓይተው ነው በአንድ ወር ውስጥ ግራ አጋቢ ዱላ ቀረሽ የማያስደስቱ ሪፖርቶች እየደጋገሙ የሚያወጡብን?
የዓለም ባንክ ሰዎች ብራችሁ በሰባ በመቶ ያህል ያላግባብ ውድ ስለሆነ አርክሱት ባሉን ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ የተመድ የንግድና ልማት ጉባዔ በብዙ ዓመታት የሒሳብ ቀመር የተለፋበትን መካከለኛ ገቢ የመግባት ምኞት አጣጣለብን፡፡ በጦርነት የሚታመሱት የመንና አፍጋኒስታን የቻሉትን እኛን አትችሉም አሉን፡፡ ያልገባን አይምሰላቸው፡፡ ብራችንን በዶላር ምንዛሪ በሰባ በመቶ ቀንሱ ያሉን ነፍስ ወከፍ ገቢያችን በዶላር ሲለካ ከሞላ ጎደል በግማሽ ወደታች እንዲወርድና መካከለኛ ገቢ እንዳንገባ አስበው ነበር፡፡ ብራችንን አናረክስም ብንላቸው በሌላ መንገድ ዙረው አሁንም ቢሆን መካከለኛ ገቢ ውስጥ ልትገቡ አትችሉም አሉን፡፡
ሞኝ መሰልናቸው እንዴ? ሞኞቹስ እነርሱ፡፡ በቁጥር መጫወት የተካንበት ጉዳይ እንደሆነ አያውቁም እንዴ? ሙያ በልብ ነው ብለን እንጂ እንኳንስ የአምናውንና የዘንድሮውን፣ የከርሞውንም ከዓመታት በኋላ የሚሆነውን ምንዛሪ ላይ ቆመን እናውቃለን፡፡ የመጣንበትንም የምንሄድበትንም አቋራጭ መንገድ የጉዟችንን ፍጥነትም እኛ እናውቀዋለን፡፡
ሙያ በልብ ነው እንዲሉ ጊዜው እስከሚደርስ በአዕምሯችን ውስጥ እንያዘው ብለን ነው ዝም ያልነው፡፡ ንገሩን ከአሁኑ አሳውቁን ካሉንም ʻነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌʼ እንዲሉ፣ ከቀደም ተሞክሯችን ምሳሌ ጠቅሰን እናስረዳቸዋለን፡፡ ምሳሌ እንዲሆነኝ ከዚህ ቀደም በአንድ ጽሑፌ ያቀረብኩትን ማስረጃና የማስረጃ ትንታኔ በድጋሚ አቀርበዋለሁ፡፡
እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በቢሊዮን ብር | |||
ዘርፍ | የ2003 ምርት መጠን |
ንፅፅር | |
በ1992 ዋጋ | በ2003 ዋጋ | ||
ግብርና | 64.7 | 212.5 | 3.3 እጥፍ |
ኢንዱስትሪ | 21.2 | 49.8 | 2.3 እጥፍ |
አገልግሎት | 73.4 | 207.2 | 2.8 እጥፍ |
ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት | 157.5 | 469.5 | 3.0 እጥፍ |
ነፍስ ወከፍ ገቢ | 1946 | 6267 | 3.2 እጥፍ |
ምንጭ፡ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርና ብሔራዊ ባንክ
በ1992 ዓ.ም. መለኪያ ቋሚ ዋጋ የተለካው የ2003 ዓ.ም. እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (Real GDP) መለኪያው ወደ 2003 ዓ.ም. ቋሚ የምርት ዋጋ መከለስ ምክንያት፣ በ1992 ዓ.ም. ቋሚ ዋጋ የተለካው የ2003 ዓ.ም. እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርትና ነፍስ ወከፍ ገቢ ሦስት እጥፍ ሆኗል፡፡
የምርት መለኪያ ዋጋውን በየአሥር ዓመቱ እንደምንከልሰውና የ2003 ዓ.ም. መለኪያ ቋሚ ዋጋ አሥር ዓመት ሙሉ ተንከባለው በተጠራቀሙ የዋጋ ግሽበቶች ባበጠው የ2013 ዓ.ም. ቋሚ ዋጋ መለኪያ እንደምንተካም እናውቃለን፡፡ የመካከለኛ ገቢ ደረጃ መግቢያ ዓመቱ በእኛ አቆጣጠር 2017 በአውሮፓውያን 2024 ሳይደርስ፣ በእኛ 2013 ዓ.ም. ከልሰን ነፍስ ወከፍ ገቢያችንን እንኳንስ አንድ ሺሕ ዶላር ሦስት ሺሕ ዶላርም እንደምናደርሰው እኛ እናውቃለን፡፡ ታዲያ እነዚህ የተከበሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ቸኩለው የማይሆን ወሬ ምን አስነገራቸው? ጊዜው ሲደርስ እንነጋገርበት አልነበረም እንዴ?
ሌላው መካከለኛ ገቢ ውስጥ አያስገባቸውም ብለው ያቀረቡት ምክንያት የአመጋገብና የትምህርት ጉዳዮችን በተመለከተ ነው፡፡ የደሃ ደሃና ደሃ የሆኑት ባያገኙም፣ በመካከለኛ ገቢ ውስጥ የሚገኙ ከተሜ ምሁሮቻችንና ልሂቆቻችን ለቁርስ ቢሻቸው ጮርናቄ፣ ቢሻቸው ሳምቡሳ፣ ቢሻቸው ሽልጦ፣ ቢሻቸው ርሚጦ፣ አምባሻም አማርጠው ለምሳም ቢሻቸው ሽሮ ተጋሚኖ፣ ቢሻቸው ሽሮ ፈሰስ፣ ቢሻቸው ሽሮ ፍርፍር አማርጠው ይበሉ የለም እንዴ?
እንደ እናንተ ለቁርስ የዳቦ ቅቤው፣ ማርማላታው፣ ሞርቶዴላው፣ እንቁላሉ፣ ወተቱ ዋናው ቁርስ የብርቱካን ጭማቂው ቀርቦ፣ ለምሳም ፕሪሞ፣ ሰኮንዶ፣ ቴርሶ፣ ዲዘርት እያሉ በቅደም ተከተል ያላግባብ ጠረጴዛ የሚያጣብብ በሰባትና ስምንት ሳህን የሚቀርብ በየዓይነቱ ምግብ መመገብ አቅቷቸው መሰላችሁ እንዴ? ጠረጴዛ ስለሌለ ቢኖርም እንዳይጣበብ ብለው እንጂ፡፡
በእርግጥም የምርታችንን ብዛትና የገቢያችንን መጠን መሬት አውርደን በገበያ ውስጥ ማሳየት አቅቶን ይሆናል፡፡ ዛሬ አንድ ሁለተኛ ደረጃ የጨረሰና በመንግሥት መሥሪያ ቤት በተላላኪነት የተቀጠረ ወጣት የወር ደመወዙ 600 ብር ሲሆን፣ ይህም ሸቀጥን በመሸመት አቅሙ በምግብ፣ በአልባሳትና በመጠለያ መሠረታዊ የኑሮ ደረጃ መለኪያዎች ስንመዝነው ሃያ አራት ኪሎ ጤፍ፣ አንድ ጂንስ ሱሪ፣ ለአንድ ጠባብ ክፍል ቤት የአሥር ቀን ኪራይ ይችላል፡፡ ይሁንና ይህ በተሃድሶው የሚሻሻል ጉዳይ ነው፡፡
ለመንግሥት ሠራተኛው/ዋ የሚከፈለው የወር ስድስት መቶ ብርም በሰዓት ሒሳብ ሲሰላ ሦስት ብር ከሰባ አምስት ሳንቲም እንደሚሆን ሳይታወቅ ቀርቶ አይደለም፣ ከአሜሪካው በሰዓት አሥር ዶላር ወይም በእኛ ገንዘብ በሰዓት ሁለት መቶ ሃያ ብር ዝቅተኛ ደመወዝ ጋር ሲነፃፀር ልዩነቱ የተጋነነ አይደለም ተብሎ እንጂ፣ በሌላ አይደለም ካስፈለገም በተሃድሶው የሚስተካከል ነው፡፡
ጡረተኞችም ድሮ በደህናው ጊዜ ጮማ ይቆርጡባት የነበረችውንና ለጡረታ ያጠራቀሟትን ያቺው አንድ ብር ሳትጨምር ሳትቀንስ ዛሬ ከሰላሳ ዓመት በኋላ ስትከፈላቸው አንድ ሎሚ እንኳ ልትገዛላቸው እንደማትችል ሳይታወቅ ቀርቶ አይደለም፡፡ ትክክል ካልሆነም በተሃድሶው ይስተካከላል፡፡
ነገ ምን እበላለሁ ብሎ የሚያስብና የሚጨነቅ ብዙ ሕዝብ በመገኘቱ ከዓለም አንደኛ እንደምንሆን ሳይገመት ቀርቶ አይደለም፡፡ ሰማንያ አምስት በመቶ የሚሆነው ገበሬ አሥራ አምስት በመቶ የሚሆነውን ከተሜ እንዴት አጥግቦ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ አይችልም ብለን ሳይገርመንና ሳንደነቅ ቀርቶም አይደለም፡፡ የመኪና መንገድ ጠፍቶ ገበያ ባይወጣም ምርቱ የተትረፈረፈ ነው፡፡ ይህም በተሃድሶው መልስ የሚያገኝ ጉዳይ ነው፡፡
በበለፀጉት አገሮች ሁለት በመቶ የሚሆነው ገበሬ ዘጠና ስምንት በመቶ የሚሆነውን ከተሜ የተመጣጠነ ምግብ አጥግቦ እንደሚመግብም እናውቃለን፡፡ እንኳንስ ለሰው ለድመትና ለውሾችም የማስታወቂያ ጋጋታ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን እንደሚያጣብብ ሳንሰማ ቀርተን አይደለም፡፡ ቢሆንም ቢሆንም ድክመታችን ብቻ ሳይሆን ጥንካሬያችንም ቢቆጠር እንደ በለፀጉት አገሮች ቢሊየነሮችንም ያፈራን መሆኑ ቢለካ፣ እንኳን ለመካከለኛ ገቢ ደረጃ ለከፍተኛ ገቢ ደረጃ ልንታጭም እንችላለን፡፡ ይህም ትክክል ካልሆነ በተሃድሶው ይስተካከላል፡፡
ታዋቂው ኢኮኖሚስት ዴቪድ ሪካርዶ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት በገበያ ኃይሎች የሠራተኛ ፍላጎትና አቅርቦት መስተጋብር ሥራ አጥነት የሚወገደው፣ የደመወዝ መጣኝ ሠራተኛው ትውልድ ለመተካት በማይፈልግበት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ሲሆን ነው ብሎ አልነበር?
በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ተከታይነት ከአንደኞቹ እኩል ሆነን የሪካርዶን ጽንሰ ሐሳብ ተጠቅመን የሕዝብና የኢኮኖሚ ማመጣጠን ፖሊሲ መንደፍ ይሻላል ብለን እንጂ ሳናውቅ ቀርተን አይደለም፡፡ ሁልጊዜ ልማታዊ ብቻ ሆነን ልንኖር ኖሯል እንዴ? ካላስፈለገም በተሃድሶው የሚስተካከል ነው፡፡
በትምህርቱስ ቢሆን አስተምረን ለባዕድ አገሮች በግርድናና በሎሌነት እንዲያገለግሉ ላክናቸው እንጂ፣ በመንግሥት ደረጃ ብቻ ከሰላሳ በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተን በየዓመቱ በመቶ ሺዎች አስመርቀን የለም እንዴ? በእርግጥ ብዙዎቹ ወረቀቱ ብቻ እንጂ ዕውቀቱ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ይህም ቢሆን የግለሰቡ ድክመት እንጂ የአገር ድክመት አይደለም፡፡ በግለሰብ ድክመት ደግሞ አገር ልታገኝ የሚገባትን መካከለኛ ገቢ የመግባት ደረጃ ልታጣ አይገባትም፡፡ ካልሆነም በተሃድሶው ይስተካከላል፡፡
በስኬታችን ስንትና ስንት ሽልማት ያገኘንበትን በዩኔስኮ የተመሰከረልንን የልጆች ትምህርት፣ የአዋቂዎች ትምህርት እየተባለ ለመካከለኛ ገቢ ደረጃ አልበቁም እንባላለን እንዴ? ይኼስ በወደቀ ዛፍ ላይ ምሳር ይበዛበታል እንዲሉ ገና ለገና በወንድማማቾች መካከል ሁከት ተከስቶ ነበር ብለው ቤንዚን ሊያርከፈክፉበት አስበው ነው እንጂ፣ እንደ ዘፋኟ እነርሱ አልነበሩም ʻበማደግም በመረጋጋትም የእኛ አንደኛʼ እያሉ ሲዘፍኑልን የነበሩት?
የተመድ ንግድና ልማት ጉባዔ ሰዎች አትቸኩሉ፣ ቸኩላችሁም አትሳሳቱ፡፡ በእኛ 2013 በእናንተ 2020 እንገናኝ፡፡ የምርት መለኪያ ዋጋችንን ከልሰን በቅጽበት ነፍስ ወከፍ ገቢያችንን በሦስት እጥፍ አሳድገን መካከለኛ ገቢ ውስጥ መግባት አለመግባታችንን ያኔ ትወስናላችሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getachewasfaw240@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡
