Quantcast
Channel: ዓለማየሁ ጉጀ
Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

የኢትዮጵያ መሠረተ ካፒታል ምንድነው?

$
0
0

በመታሰቢያ መላከሕይወት ገብረክርስቶስ

በአማርኛ ቋንቋችን መሠረት ትምህርት፣ መሠረተ ጤና፣ መሠረተ ልማት፣ መሠረተ ፍጆታ፣ ወዘተ በስፋት የምንጠቀምባቸው ቃላት ሲሆኑ፣ መሠረተ ካፒታል የሚለው ቃል በስፋት ሥራ ላይ ውሏል ማለት አይቻልም፡፡ ቃሉን በአጭሩ ለመግለጽ መሠረተ ካፒታል ማለት አንድን አገር ለማደግ ስትወስን ያላትን የተፈጥሮና የሰው ሀብት ለማልማት የምትጠቀምበት የመጀመሪያ መነሻ ካፒታል ወይም ሀብት ብለን ልንገልጸው እንችላለን፡፡ ይህ ደግሞ በአገር ደረጃም ሆነ በግለሰብ  ደረጃ የሚሠራ ነው በእንግሊዝኛ ቋንቋ (Paidup Capital) እንደ ማለት ነው፡፡

ዛሬ በልፅገው ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ አገሮችን ታሪክ ስናጠና የምንረዳው ነገር ቢኖር፣ ሁሉም ያደጉበት መንገድ የተለያየ መሆኑን ነው፡፡ ለምሳሌ እንግሊዞች ለማደግ የተጠቀሙበት መንገድ አገራቸውን ጥለው ወደ ሌሎች የዓለም ክፍል በማምራት፣ የሌሎች ሕዝቦችን የተፈጥሮ ሀብትና ጉልበት በመበዝበዝ መነሻ ካፒታል መፍጠር ችለዋል፡፡ እንግሊዞች በታሪክ የሚታወቁበትን ወርቅና አልማዝ ተገኘ በተባለበት ቦታ ሁሉ በብዛት በመጓዝ ያንን ሀብት እንደ መነሻ ተጠቅመው፣ በዓለም ላይ ሰፊ ወታደራዊ ኃይል መገንባት ችለዋል፡፡ ይህንን ወታደራዊ ኃይል ደግሞ ተጠቅመው ቅኝ አገዛዝን፣ ቋንቋቸውንና ባህላችውን አስፋፍተዋል፡፡

አሜሪካኖች ደግሞ የሚታወቁት ከአገራቸው ወጥተው ሌሎች አገሮችን በመውረር ሳይሆን፣ ከአፍሪካ የሚመጡ ባሪያዎችን ጉልበት በመጠቀም ወረው የያዙትን የሰሜን አሜሪካ ግዛት በማቅናት አስደናቂ ዕድገትና ሥልጣኔ መገንባት ችለዋል፡፡

በቅርቡ ደግሞ አስደናቂ ሥልጣኔ መገንባት የቻሉት የዓረብ አገሮች የነዳጅ  ሀብትን እንደ መነሻ ካፒታል በመጠቀም፣ ለሰው ልጆች ኑሮ ተስማሚ ባልሆነው በረሃማው አገራቸው ላይ ትልቅ የግንባታ ጥበብና ሥልጣኔ ማምጣት ችለዋል፡፡

የፖለቲካ ምሁራን ይህንን ዓይነት ሥልጣኔ (Lumpenish Civilization) ብለው ይጠሩታል፡፡ ይህ ማለት ሥልጣኔው በአንድ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ብቻ የተመረኮዘ፣ ከትውልድ ትውልድ የማይተላለፍ፣ የሥልጣኔ ሳይንስ ሥርዓትን ያልተከተለ እንደ ማለት ነው፡፡ እኔ ይህንን ቃል ወደ አማርኛ ስመልሰው ‹‹ድሪቶ ሥልጣኔ›› ብሎ መሰየም የተሻለ ይመስለኛል፡፡ የአንድ አገር ግንባታ ፍፁም በሳይንስና በሳይንቲስቶች ተመርቶ፣ ዘመኑ ያፈራውን ዕውቀት ተከትሎ የማይመራ ከሆነ ከላይ የተጠቀሰው ስም ጥሩ ይመስለኛል፡፡

በሩቅ ምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ እስያ ያሉ አገሮች ደግሞ እንግሊዞችና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ርካሽ የሰው ጉልበት ፍለጋ ዕውቀታቸውን ይዘው በእነዚህ አገሮች ባደረጉት ከፍተኛ መስፋፋት ምክንያት፣ ዘመናዊውን ዕውቀት መተዋወቅ በመቻላቸው ይህን ዕውቀት በመጠቀም በአገራቸው ባደረጉት የኢንዱስትሪ አብዮት ከፍተኛ መሠረተ ካፒታል መፍጠር ችለዋል፡፡ ከአውሮፓውያን በተማሩት ዕውቀት ላይ የራሳቸውን ፈጠራ በመጠቀም አሁን በዓለማችን እጅግ አስደናቂ ልማት ላይ መድረስ ችለዋል፡፡

ከላይ በአጭሩ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በሁሉም አገሮች ያለው መሠረተ ካፒታል አፈጣጠር የተለያየ መሆኑን ነው፡፡

ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ ኢትዮጵያ ገና ያላደጉ አገሮች ተብለው ከሚጠሩ አገሮች ተርታ የምትመደብ ሲሆን፣ አስተማማኝና ዘለቄታ ያለው ሥልጣኔ መገንባት እንድትችል መጠቀም ያለባት መሠረተ ካፒታል እንዴትና ምን እንደሆነ አግባቡ ማወቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮና የሰው ሀብት ዜጎችን ሕይወት ሊለወጥ በሚችል መንገድ እንደ መነሻ የሚሆን የካፒታል ምንጭ ወይም መሠረተ ካፒታል እንዴት ማግኘት ትችላለች የሚለው ድምዳሜ ላይ ለመድረስ፣ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው የኢሕአዴግ መንግሥት እየሄደበት ያለውን መንገድ መመልከቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን እንደያዘ መጀመሪያ ዕርዳታ መቀበልን እንደ ዋና ስትራቴጂ አድርጎት ቆይቷል፡፡ ከዚያም በመቀጠል ከውጭ አገር መንግሥታትና ባንኮች ብድር በመውሰድ ልማትን ማፋጠን ይቻላል የሚል አቅጣጫ አስቀምጦ ላለፉት 26 ዓመታት ሲጓዝ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን እነዚህ አማራጮች አስተማማኝ እንዳልሆኑና የዜጎችን ሕይወት በመለወጥ በኩል አመርቂ ውጤት ማምጣት እንደማይቻል በጊዜ በመገንዘብ፣ ሌሎች አማራጮችን ማፈላለግ ይገባው ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡

በተለይ የማዕድን ሀብትን በአፋጣኝ በማልማት በራስ አቅም ከፍተኛ መሠረተ ካፒታል መፍጠር የሚቻል ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ ግን ‹‹ለኢትዮጵያ ሕዝብ የማዕድን ልማት አያስፈልገውም›› የሚል አቋም ይዞ ከፍተኛ ጊዜ ያቃጠለ ከመሆኑም በላይ፣ አሁንም በመንግሥት ደረጃ ግልጽና አሻሚነት የሌለው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕድገት መነሻ ካፒታል ሊሆን የሚችለውን አቅጣጫ በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡

እዚህ ላይ እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ ለአገራችን ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጠውን የዓባይን ግድብ ለመገንባት የሚያስችል የገንዘብ ምንጭ ለማግኘት ምን ያህል እንደተቸገርን ለሁላችንም ግልጽ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚያ በፊት የማዕድን ልማት እንዲፋጠን ተግተን ሠርተን ቢሆን ኖሮ፣ ዓባይን ለመገደብ ብዙ ሳንቸገርና በራሳችን አቅም ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችን ሳንጎዳ ማልማት በቻልን ነበር፡፡

ካለፉት 40 ወይም 50 ዓመታት በፊት በዓለማችን ያልነበረ አሁን በስፋት ያለ ነገር ቢኖር፣ በብዙ የዓለማችን ክፍሎች  የተትረፈረፈ የገንዘብ ክምችት መፈጠሩ ነው፡፡

ለምሳሌ በአሁን ወቅት በትሪሊዮን የሚቆጠር የዶላር ክምችት ያላት ቻይና የዛሬ 40 ወይም 50 ዓመት እጅግ ደሃ ከሚባሉ አገሮች ውስጥ የምትመደብ ነበረች፡፡  ቻይና የዜጎችዋን ጉልበት እንደ መሠረተ ካፒታል በመጠቀም ዛሬ በዓለማችን አስደናቂ ሥልጣኔ መገንባት የቻለች አገር ሆናለች፡፡ ሰሞኑን ቢቢሲ እንዳስነበበን ቻይና እ.ኤ.አ ከ2012 እስከ 2015 በአገርዋ የተጠቀመችው የሲሚንቶ መጠን አሜሪካ ከ1900 እስከ 1999 ድረስ ከተጠቀመችው ሲሚንቶ ማለት 20ኛው ክፍለ ዘመን ጋር እኩል መሆኑን ነው፡፡ ይህ በእጅጉ የሚያስደንቅ ዜና ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ወይ ቱታ ለብሰን እንደ ኮሙዩኒስት አገሮች በወታደራዊ ዲሲፕሊን እየተመራን ዶማና አካፋ ጨብጠን የካፒታል መሠረት መፍጠር አልቻልንም፡፡ ወይም ደግሞ ገንዘብ ያለው ባለሀብት ያለ ገደብ ወደ አገር ውስጥ እየገባ እኛ ያንን ገንዘብ በመጠቀም የአገራችንን መሬት እያለማን ካፒታል መፍጠር አልቻልንም፡፡ ታዲያ የኢትዮጵያ ርዕዩተ ዓለማዊ የልማት አቅጣጫ ምንድነው? ይህ ጥያቄ በእጅጉ ወሳኝ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

በዓለማችን ያሉ ሁሉም ሥልጣኔዎች አንድ የሚያርጋቸው ባህርይ ተወደድም ተጠላም የግድ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ትውልድ ጉልበት ተበዝብዞ፣ ተጨቁኖ ወይም ሌላ መስዋዕትነት ሳይከፍል ዕድገትን መመኘት ከቶውንም የሚታሰብ አይደለም፡፡ ሁሉም ሥልጣኔዎች የጀርባ ታሪካቸው ቢጠና እጅግ አስቸጋሪና እልህ አስጨራሽ ሒደቶችን አልፈው ነው ዕድገት ማማ ላይ የተፈናጠጡት፡፡ ሌላው እኔን የሚያሳስበኝ ጉዳይ አሁን እኛ እየሠራናቸው ያሉ  ተግባራት በአብዛኛው ሲገመገሙ በበቂ ሳይንሳዊና ደረጃቸውን ጠብቀው በርካታ ትውልዶች ተጠቃሚ ሊያደርጉ በሚችሉበት ሁኔታ ሳይሆን እየተተገበሩ ያለው፣ ጊዜያዊ ችግርን ለመቅረፍና ለፕሮፓጋዳ ፍጆታ ወይም ቁጥር ለማሟላት በሚችል መንገድ መካሄዳቸው ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እነዚህን ፕሮጀክቶች (Feel Good Projects) ብለን ልንጠራቸው እንችላለን፡፡ ይህ ማለት ለአካባቢው ማኅበረሰብ ይህ ነገር ተሠራልህ ለማለት ያህል የተሠሩ እንጂ፣ ኅብረተሰቡ ኪስ ሊገባ የሚችል ፋይዳ የላቸውም፡፡

የተፈጥሮ ሀብትን በመጠቀም መሠረተ ካፒታል ከመፍጠር አኳያ በርካታ የአፍሪካ አገሮች በርካታ ስህተቶች የሠሩ በመሆናቸው፣ እኛ ከእነዚህ ስህተቶች በመማር የተሻለ የመሥራት ዕድሉ አለን፡፡

ለምሳሌ ናይጄሪያ ያላትን የነዳጅ ሀብት ተጠቅማ የዜጎችዋን ሕይወት መለወጥ ሲገባት፣ በአሁኑ ጊዜ ናይጄሪያ ውስጥ ያለው ድህነት የነዳጅ ሀብት ባለቤት ከመሆንዋ በፊት ከነበረው ድህነት በእጅጉ የከፋ ነው፡፡ ይህ የሆነው በተለያዩ ጊዜያት የተፈራረቁ መንግሥታት ይህንን ሀብት በአግባቡ ማስተዳደር ባለመቻላቸው ነው፡፡ ገንዘብ ተበድረው ለአልባሌና በአግባቡ ላልተጠና ፕሮጀክት እያዋሉ፣ ገሚሱ ደግሞ በሙስና እየተዘረፈ አገሪቱን ማለቂያ ለሌለው ለዕዳ ጫናና ለድህነት ሲዳርጋት ቆይቷል፡፡

እኛ ከዚህ ስህተት በመማር የተሻለ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያው የተፈጥሮ ማዕድን በሚገኝበት ጊዜ ያንን ማዕድን ባለበት ቦታ በዓለማችን የተትረፈረፈ የገንዘብ ሀብት ላላቸው አገሮች እዚያ መሬት ውስጥ እንዳለ በግልጽ ጨረታ በመሸጥ፣ በ50 ወይም በ100 ዓመታት ጊዜ ውስጥ  አልምተው እንዲወስዱት በማድረግ በአንድ ጊዜ አገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንድታገኝ ማድረግ ይቻላል፡፡ አሁን ያለውን ትውልድና መጪውን ትውልድ በአስተማማኝ ሁኔታ የሚጠቅም መሠረተ ካፒታል ወይም ዕዳ አልባ የሆነ የገንዘብ ክምችት መፍጠር ይቻላል፡፡

እስካሁን ባለው አሠራር በቁጥ ቁጥ ገንዘብ እየተበደርን አንዱ ልማት ከሌላኛው ጋር መናበብ እያቃተው፣ የተገነባው ልማት ከወጣለት ወጪ አኳያ ጥቅም ሳይሰጥ ዕዳው ብቻ እየቆለለ የሚሄድበት ሁኔታ ባለፉት ዓመታት በተጨባጭ የታየ ጉዳይ ነው፡፡

ለምሳሌ በመላው አገሪቱ ብዙ ሚሊዮን ዶላሮች ተበድረን የገነባነው የመንገድ መሠረተ ልማት ሁሉም ሊባል በሚቻል መልኩ ከአቅም በታች እያገለገለ ነው፡፡ መሻሻል አላሳየም፡፡ እዚህ አጠገባችን ያለው የአዲስ - ለአዳማ የፍጥነት መንገድ ተገንብቶ ከተመረቀ በርካታ ወራት ያሳለፈ ቢሆንም፣ አሁንም በመንገዱ ላይ ያለው የትራፊክ ፍሰት እጅግ አናሳ ነው፡፡

ሌላው ሥለ መሠረተ ካፒታል ስንነጋገር የሁሉም ኢኮኖሚዎች መሠረት የሆነውን መሬት በተመለከተ እያራመድን ያለው ፖሊሲ፣ አሁንም ከ26 ዓመታት በኋላ አጨቃጫቂ መሆኑ ነው፡፡

ሰሞኑን በቴሊቪዥን እየተመለከተ ነው ያለው የኢሕዴግና የተቃዋሚ ፓርቲዎች  ድርድር ገና ወደ ፍሬ ነገሩ ያልተገባ ቢሆንም፣ በጣም በእርግጠኝነት ልናገረው የምንችለው ነገር ወደ ዋናው ድርድር መገባት ከተጀመረ አሁንም የመጀመሪያው አጀንዳ ሆኖ የሚቀርብ ይመስለኛል፡፡

ከ1966 ዓ.ም. አብዮት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ እየጠየቀ ያለው መሬት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የዜጎች የባለቤትነት መብት እንዲረጋገጥ ሆኖ ሳለ፣ አሁንም በተለይ የገጠር መሬት ገበሬው በባለቤትነት ስሜት ሊያለማው፣ አስይዞ ሊበደርበት፣ ሊሸጠውና ሊለውጠው ባለመቻሉ አገሪቱ ማለቂያ ለሌለው የድህነት አዙሪት ውስጥ ለመኖር ተገዳለች፡፡ ገበሬው በመሬቱ ላይ የባለቤትነት ስሜት ስለሌለው ገንዘብንና ጉልበቱን ለቋሚ ሀብት እያዋለ አይደለም፡፡

እዚህ ላይ ሒሳባዊ ሥሌት እንሥራ፡፡ መንግሥት እንደነገረን በአገራችን ሊታረስ የሚችል ከ40 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በላይ እንዳለ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ የዋለው 13 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ብቻ ነው፡፡ ይህንን 13 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ብቻ ውሰደን እያንዳንዱ አባወራ አንድ ሔክታር አለው እንበልና በዚህ መሬት ላይ እያንዳንዱ ገበሬ በዓመት 10,000 ብር የሚያወጣ ቋሚ ሀብት ቢያፈራ፣ 10,000x13 ሚሊዮን= 130 ቢሊዮን ብር አገራዊ ሀብት እናፈራለን፡፡ 130 ቢሊዮንxበ26 ዓመት (ማለት ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ያስተዳደረበት ጊዜ) 3.380 ትሪሊዮን ብር የሚያወጣ ቋሚ ሀብት በገጠሪቷ ኢትዮጵያ እናፈራለን ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን ይህንን ሀብት የሚወርስ ወጣት ትውልድ እንዴት አድርጎ ነው ስደት የሚሄደው? ይህ ሥሌት በዝቅተኛው የብር መጠን ተሠራ እንጂ ከዚህ በበለጠ ሊያድግ የሚችልበት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ባለፉት 26 ዓመታት ይህን ያህል ሀብት ሳናፈራ ቀርተናል ማለት ምን ያህል ጉዳት እንደሚያስከትል ለማንም ጤነኛ አዕምሮ ላለው ሰው በቀላሉ መረዳት የሚቻል ጉዳይ ነው፡፡

መሬት  የመንግሥት ነው የሚለው አዋጅ ምን ያህል ለድህነት እንዳደረገን ከላይ የተገለጸው ማስረጃ ከበቂ በላይ ይመስለኛል፡፡ በከተሞች ደግሞ እጅግ የተጋነነ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ያላገናዘበ አልፎ አልፎም እጅግ ከበለፀጉ አገሮች የመሬት ዋጋ ጋር እንኳን ሲነፃፀር በእጅጉ የበለጠ ዋጋ እየቀረበ ነው፡፡ ይህ በእርግጠኝነት ጤነኛ ያልሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓት በአገራችን መኖሩን ለማስረዳት ከበቂ በላይ ነው፡፡

አሁን ለድርድር እያኮበኮቡ ያሉትም የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር አጀንዳዎችን ወይም (Road Map) መራሔ መንገድ ምን እንደሆነ ለሕዝብ ቢያነብቡና ለውይይት ቢቀርብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ አሁንም የዛሬ 26 ዓመት የተሠራው ስህተት እንዳይደገም፣ ማንኛውም የሕገ መንግሥት መሻሻል ወይም የፖሊሲ ለውጥ በዓለም ደረጃ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችልና የኢትዮጵያን ሕዝብ እርካታ ሊፈጥር የሚችል መሆን አለበት፡፡ ኢሕአዴግ የዛሬ 26 ዓመት ብቻውን አገር በመቆጣጠር በማናለብኝነት ሊታረም የማይችል ታላላቅ ታሪካዊ ስህተቶች ሠርቷል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ ይህንን ለመዳሰስ አልፈልግም፡፡ ነገር ግን ሁላችንም ይህንን ስለምናውቀው አሁን ስህተት ላለመሥራት  ድርድሩና ውይይቱ በመንግሥትና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ምሁራን በሁሉም መስክ ተሳታፊ መሆን አለባቸው፡፡

አሁን ባሉት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የኢትዮጵያ ምሁራን በበቂ ሁኔታ አሉ ለማለት አያስደፍርም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተው በየምርጫው በመሳተፍ ኢሕአዴግን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አስመሰሉት እንጂ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም የፈየዱት ነገር የለም፡፡ የመጫወቻ ሜዳ በሌለበት ሁኔታ የፖለቲካ ጨዋታ ሲጫወቱ ነው የከረሙት፡፡ የኢሕአዴግ የምርጫ ሠርግ በየአምስት ዓመቱ ሲደገስ እንደ ሚዜ ሲያጫፍሩ ከርመው፣ ኢሕአዴግ ሙሽራው ቤተ መንግሥት ሲገባ እነሱ ወደ ጎጆአቸው ያቀናሉ፡፡ አንድም የፖለቲካ ፓርቲ ዝርዝር ማኒፌስቶውን እንኳን በስፋት አዘጋጅቶ በየመጻሕፍት ቤቱ ለመሸጥ የሞከረ የለም፡፡ ይህ ማለት የኢትዮጵያ ሕዝብ እነዚህን ፓርቲዎች እንዴት ሊረዳቸው ይችላል፡፡

ባለፉት 100 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የምዕራባውያን ትምህርት ተስፋፍቶ የነበረ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ያላት አንዱ ትልቅ ሀብት የምሁራን ሀብት ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ምሁራን በበቂ ሁኔታ ያሳተፈ የፖለቲካ ድርድር ካልተካሄደ፣ አሁንም እንደገና እርማት የሚፈልግ ሕገ መንግሥትና የመንግሥት ፖሊሲ ነው የሚኖረን፡፡ ኢሕአዴግ ገፍተው ወደፊት የመጡትን ምሁራን ብቻ ሳይሆን ለማቅረብ መሞከር ያለበት፣ ምሁራን ከያሉበት ተፈልገው ለአገራቸው እንዲሠሩ መጋበዝ አለባቸው፡፡

ባለፉት 100 ዓመታት ከአፄ ምኒልክ በስተቀር ሌሎች መንግሥታት ኢትዮጵያ መሠረተ ካፒታል እንድታፈራ የሠሩት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ መንግሥት ደግሞ ከወጣቱ ብዛትና አቅም ጋር የሚመጣጠን መሠረተ ካፒታል ፈጥሮ የወጣቱን እርካታ መፍጠር ካልቻለ፣ የመጨረሻው ውጤት የፖለቲካ አለመረጋጋትና የአገር መፍረስ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም በዚህ አቅጣጫ ሰፊ ሥራ መሠራት አለበት፡፡

መሠረተ ካፒታል በመፍጠር ሒደት ላይ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ መውሰድ ጠቃሚ ቢሆንም፣ ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር መጣጣሙን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ኢሕአዴግ በርካታ ትምህርቶች ከደቡብ እስያ አገሮች እንደተማረ ደጋግሞ ይነግረናል፡፡ ነገር ግን የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮችና እኛ ያለን የተፈጥሮ ሀብት በእጅጉ ይለያያል፡፡ መሬትን ብንወስድ በደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች እጅግ ውስን ሀብት ሲሆን፣ በአገራችን ደግሞ በእጅጉ የተትረፈረፈ ሀብት ነው፡፡ በረሃ የሚባሉት የአፋርና የሱማሌ ክልሎች እንኳን ያላቸው የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር የውኃ ሀብት እጅግ ሰፊ ነው፡፡ በመሆኑም በምሁራኖቻችን (በካድሬዎች ሳይሆን) የሚጠቅመንን ፖሊሲ ማጥናት በእጅጉ ወሳኝ ተግባር ነው፡፡

ኢሕአዴግ የዛሬ 26 ዓመት ሥልጣን ላይ ሲወጣ ለምሁራን ፖሊሲ በማውጣት ሒደት ላይ ሰፊ ዕድል ባለመስጠቱ፣ ዛሬ የምናያቸው ውስብስብ ችግሮች ሊፈጠሩ ችለዋል፡፡ አሁንም ይህ ስህተት እንዳይደገም ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡

ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ተፈተው ምርጫ ከተወዳደሩ በኋላ አንድ የተናገሩት አስደናቂ አባባል አለ፡፡ ‹‹በምርጫ ውጤት ከ75 በመቶ በላይ ባገኝና ፓርላማውን ተቆጣጥሬ ለብቻዬ ሕግ አውጪ ብሆን ኖሮ፣ በሕግ ማውጣት ሒደት ላይ ብዙ ስህተት እሠራ ነበር፡፡ ነገር ግን ከ75 በመቶ በታች በማግኘቴ ከሌሎች ጋር የማወጣው ሕግ ለአገር የሚጠቅም ይሆናል፤›› ብለው ነበር፡፡ ይህ አባባል ለሁላችንም በቂ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ በተጨማሪም የአንድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫ ነው፡፡ አገር የጋራ እንደ መሆንዋ ሁሉ፣ ሁሉንም ዓይነት አስተሳሰቦች በነፃነት የሚስተናገዱበት መድረክ መፍጠር እጅግ ቢዘገይም አሁን ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው metasebyamelaku@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡      

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

Trending Articles