Quantcast
Channel: ዓለማየሁ ጉጀ
Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

‹‹ሕዝብ ሀብት ነው›› የሚለው አነጋገር እስከምን ድረስ ነው?

$
0
0

በሮቤ ባልቻ

ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረ አንድ የመካከለኛው ምሥራቅ ንጉሥ፣ ባለሟሎቹ በመላ አገሪቱ ተዘዋውረውና ሕዝቡን ቆጥረው፣ ውጤቱን እንዲያቀርቡለት አዝዞ እንደነበር በብሉይ መጽሐፍ ተጽፏል፡፡ ባለሟሎቹ ግን ‹‹ሕዝብ መቆጠር የለበትም፣ ይህ ከንጉሡ ሐሳብ ይራቅ›› ብለው ቢከራከሩም የንጉሡ ቃል ፀና በመጨረሻም ቆጠራው ተካሄደ ባለሟሎቹ ሪፖርታቸውን አቀረቡ፡፡ ‹‹ሰይፍ መምዘዝ የሚችል ጎልማሳ›› ይህን ያህል ብለው ጀምረው ሕፃናት፣ ሴት፣ ወንድ፣ ሽማግሌውን ከፋፍለው በማስቀመጥ ለንጉሡ አቀረቡ፡፡

ዘመኑ ግጭትና ጦርነት በአካባቢው የሰፈነበት፣ መሬት ነጥቆ መያዝ የበዛበት ስለነበር የንጉሡ ፍላጎት ‹‹ሰይፍ መምዘዝ›› የሚችለውን ጎልማሳ ብዛት የማወቅ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ በዘመኑ ቋሚ የሚባል ሠራዊት ስለሌለ፣ ከወራሪ ጠላት ለመከላከልና ሲያስፈልግም ለማጥቃት አቅምን መፈተሹ ብልህነት ነበር፡፡

ዛሬ አገሮች የሕዝባቸውን ቁጥር በየዕድሜ ክልሉና ፆታ መድበው ማወቅ የሚፈልጉት እንደ ጥንቱ ዘመን የጦር ሜዳ አቅማቸውን ለማጤን አይደለም፡፡ የተፈጥሮ ሀብቶቻቸውን አጠቃቀም ሚዛናዊ ለማድረግ የማኅበራዊ አገልግሎት አሰጣጣቸውን ተደራሽነት ለመገምገምና፣ ይኼ ተዛብቶ ሲገኝ ደግሞ በዕቅድ ላይ የተመረኮዘ አፋጣኝ ማስተካከያ ለማድረግ ነው፡፡

 

በኢትዮጵያም የሕዝብ ቁጥር ማወቅ አስፈላጊነት ታምኖበት ጉዳዩን የሚከታተል መሥሪያ ቤት ከተቋቋመ ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ በዚሁ መሥሪያ ቤት ቆጠራ ላይ ተመሥርቶ ከሃምሳ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ሃያ ሚሊዮን እንደሆነ በየትምህርት ቤቱ ሲነገረን ነበር፡፡ እኛ የዚያን ጊዜ ተማሪዎች ዛሬ አዛውቶች ነንና የአሁኑ ቁጥራችን ከመቶ ሚሊዮን በላይ ማሻቀብ ሳያስገርመን አይቀርም፡፡

በዘመኑ ለነበርን ሃያ ሚሊዮን የሕዝብ ቁጥር ብዙ ነው፡፡ የአንድ ሚሊዮን ብር ቃል መስማትም እንግዳ ነበር፡፡ እንደ ሕዝቡ ቁጥር ኢኮኖሚውም ዝቅ ያለና በዝግታ የሚሄድ ነበር፡፡ የሕዝብ ብዛቱ ዝቅተኝነትና የመግዛት አቅሙም ደካማ መሆን የሚፈለገውን አገራዊ ምርት በቀላሉና በንፅፅር በዝቅተኛ ዋጋ እንድናገኝ ረድቶናል፡፡ የዚያን ዘመን ሰዎች ‹‹ . . ደጉ ዘመን . . . ››፣  ‹‹ . . ዱሮ ቀረ . . .  ›› ብለን አንዳንዴ የምናስበው ብሶት ከዚያ የመጣ ይመስላል፡፡

ምንም እንኳን የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚና የገበያ ሥርዓት በአገራችን ላይ የሚያሳርፈው ጫና ቀላል ባይሆንም ዛሬ በምድራችን ላይ ያለው ለውጥና ዕድገት ከዱሮው በብዙ እጅ የላቀ ነው፡፡ የማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፎች ብዛትና የኢኮኖሚ መስኮቹ ስፋት የጎላ ልዩነት እንዳላቸው በግልጽ የሚታይ ነው፡፡

ሆኖም ግን ለውጡና የሚካሄደው የኢኮኖሚ ዕድገት ከከፊሉ ሕዝብ በግልጽ የሚታይ አይደለም፡፡ የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መሄድና የምርትና የተፈጥሮ ሀብቶች አጠቃቀም ውስንነት ፍሬው ለሁሉም እኩል እንዳይታይ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖር፣ መልካም አስተዳደር አለመስፈን የችግሮቹን ስፋት ያገዝፉታል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት የአገራችንን ሕዝብ ቁጥር ሚዛናዊነት የሚከታተል፣ ለኅብረተሰቡም ስለቤተሰብ ምጣኔ አስፈላጊነት ትምህርት የሚሰጥና ቅስቀሳ የሚያካሄድ መሥሪያ ቤት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ መሥሪያ ቤቱ የአጭርና በረዥም ጊዜ ፖሊሲዎችን በመቅረፅና በመንግሥት በማስፀደቅ ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያካሄድ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ሥር የሚገኘውና የሥነ ሕዝብ ጉዳይ የሚመለከተው ድርጅትም ድጋፍ በማድረግ አብሮ ይሠራ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ይኼ መሥሪያ ቤት ራሱን ችሎ ባይቆምም በጤና ጥበቃ ሥር ተጠቃሎ እንደ አንድ ዘርፍ የሚንቀሳቀስ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ በአሁኑ የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ በአገር ደረጃ የሥነ ሕዝብ ፖሊሲን ውጤታማ ለማድረግ ከክልሎች ጋር በቅርበት ምን ያህል እየሠራ እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በተጨባጭ የሚታየውና እርግጠኛ መሆን የሚቻለው ግን ፈጣን የሕዝብ ቁጥር መጨመር እየተስተዋለ መሆኑ ነው፡፡ ዛሬ በአዲስ አበባ በዙሪያዋ የሚንቀሳቀሰውን ሕዝብ የሚያስተናግድ የእግረኛ መንገድ እየጠበበ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ከተሞችና ክልሎችንም ብንመለከት የሕዝቡ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

‹‹ሕዝብ ሀብት ነው!›› የሚለው አነጋገር የአገሪቷን የተፈጥሮ ሀብት የኢኮኖሚ ደረጃና የሰው ሀብት አጠቃቀም ብቃትን ከግምት ያስገባ ሲሆን ነው፡፡ 

ቁጥሩ እየጨመረና እየበዛ የመጣ ዜጋ፣ በገጠርም ይሁን በከተማ ብቁ የመሠረታዊ ፍላጎት፣ አገልግሎቶቹ እንዲሟሉለት ይፈልጋል፡፡ ከምግብና መጠለያ ሌላ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና አገልግሎት የሥራ መስክና ሌሎችም እንዲሟሉለት ይፈልጋል፡፡ ቁጥሩ በፍጥነት እየጨመረ ለሚመጣው ዜጋ ደግሞ እነዚህን ፍላጎቶች ለማሟላት አገር አቅም ስታጣ ተስፋ መቁረጥ ይመጣል፡፡ ተስፋ መቁረጥ ደግሞ ውጤቱና መዘዙ ብዙ ነው፡፡ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የኮረብታዎችና ከፍታዎች ዛፎችና ቁጥቋጦዎች ተመንጥረው፣ ለቤት መሥሪያና ለእርሻ ተግባር እየዋሉ መሆናቸውን የምንመለከተው ለዚህ ነው፡፡ ጨፌያማና ረግረግ የነበሩ፣ ቄጠማና ሳር እየታጨደ ለተለያየ አገልግሎትና ለከብት መኖ ይዘጋጅባቸው የነበሩ በርካታ የአገራችን አካባቢዎች ዛሬ ላይ ደርቀዋል፡፡ በዙሪያቸው የነበሩ ተክሎችና ዛፎች ያላግባብ እየተመነጠሩ ወደ እርሻ ማሳነት ስለተቀየሩ መሬት ርጥበት ማቆየትና ውኃ መያዝ አልቻለችም ነበር፡፡ የእርሻ ማሳና የግጦሽ ሥፍራዎች ማስተናገድ የሚችሉት የሕዝብ ቁጥር በአየካባቢው ይታወቃል፡፡ የሚወለደው አዳዲስ ትውልድ በነበረው የገጠር መሬት መስተናገድ የማይችልበት ሁኔታ ሲፈጠር፣ ጥብቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን መጠቀም ይጀምራል፡፡ ይህ ደግሞ ለአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት ጥፋት ይዞ ይመጣል፡፡

ዛሬ በአንዳንድ ክልሎችና ዞኖች አካባቢዎችን መልሶ ለማልማት ብርቱ እንቅስቃሴዎች ሲካሄዱ ይታያሉ፡፡ ይህ መልካም የበለጠ ሊተጋበት የሚገባ ተግባር ነው፡፡

በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ጋራው ሸንተረሩ እየተመነጠረ ወደ እርሻ ማሳነትና ቤት መሥሪያ ሲውል ከአዲስ አበባ ቅርብ ርቀት ላይ መመልከት ይቻላል፡፡ ከሚካሄደው የመልሶ ማልማት ጥረት በተቃራኒ የሚስተዋሉ ተግባራትም አሉ ማለት ነው፡፡

የሕዝብ ቁጥር አካባቢዎች ሊያስተናግዱ ከሚችሉት በላይ ሆኖ እያደገ ከመጣ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ያላግባብ መጠቀም ይከተላል፡፡ ይኼ በአገራችን መታየት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

ሌላው ደግሞ ከትውልድ አካባቢው እየለቀቀ ወደ ከተሞች የሚሰደድ የኅብረተሰብ ክፍል ይበዛል፡፡ በከተሞች አካባቢ ያሉ ኢንዱስትሪዎች፣ ፋብሪካዎችና ሌሎች የልማት ተቋማት የሰው ኃይል መፈለጋቸው አይቀርምና መልካም ነው ሊባል ይችላል፡፡ ወደ አዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች ከየክልሉ የሚገባው የሰው ኃይል ቁጥር ግን ሥራው ከሚፈለገው በላይ ነው፡፡ ሥራ በማጣት በየከተሞች የሚንገላታውና በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋል ያልቻለው የሰው ኃይል ባክኖ የምንመለከተው በአብዛኛው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ሌላው የታዳጊ ሕፃናት በአዲስ አበባና በሌሎችም የክልል ከተሞች በርክቶ መታየት ነው፡፡ የሕፃናቱ ዕድሜ ሲታይ የትምህርት፣ የቤተሰብ ክብካቤና መልካም አስተዳደግ ማግኘት የሚገባቸው ዕድሜ ላይ እንዳሉ እንመለከታለን፡፡ ይኼ ሳይሆን ቀርቶ፣ በወላጆች ፈቃድ ወይም በሌላ መንገድ ወደ የከተሞች እየፈለሱ የማይገባ ሕይወት እየኖሩ ነው፡፡ አንዳንዶቹም ለተለያዩ ችግሮች ሲዳረጉ ይታያሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ያገኙትን ትናንሽ ሥራዎች እየሠሩ ለመኖር ሲጣጣሩ ይታያሉ፡፡ ቤተሰብ ከስድስት እስከ አሥራ አንድ ዓመት ዕድሜ ክልል ያሉትንና በየከተሞች የሚታዩትን ሕፃናት ልጆቹን ለምን ወደ ከተሞች ይለቃል? ብለን ስንጠይቅ በአብዛኛው ምክንያቱ የአቅም ችግር ወይም ድህነት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ማሳደግ ከሚችለው በላይ እያንዳንዱ ቤተሰብ ልጅ እየወለደ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በርግጥ በየአካባቢው የተሟላ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ በግርድፉ ግን በመጓጓት የወለደውን አንድ ሁለት ልጁን ከቤት ወጥቶ እንዲለየው የሚመርጥ  ወላጅ አይኖርም፣ ቢኖርም በጣም ጥቂት ነው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡

ፌዴራል መንግሥትና ክልሎች የሥራ ኃይል የሆነው ወጣቱን ክፍል ሥራ ፈጣሪና በአገሪቱ ልማት ተሳታፊ እንዲሆን የሚያካሂዱት ጥረት ይታያል፡፡ ጥራቱ የሚደገፍና በስፋትም መቀጠል የሚኖርበት ነው ብሎ አስተያየት መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ግን ከአገሪቱ የሕዝብ ብዛት ከግማሽ በላይ ቁጥር ከያዘው ወጣት ምን ያህሉን ማገዝ ይቻላል? ነው ጥያቄው፡፡

የአገር ኢኮኖሚና ሥራ ላይ እየዋለ ያለው የተፈጥሮ ሀብት፣ ሥራ ፈላጊውንና ዕውቀቱ እና ክህሎቱ ያለውን ኃይል በስፋት ማቀፍ የሚችል አይደለም፡፡ በአገሪቱ ያለው የሥራ ዕድል ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር መጣጣም ሲሳነው፣ እያንዳንዱ ሰው አማራጭ የመሰለውን ያልተገባ ዕርምጃ ወደ መውሰድ ይመለከታል፡፡

ዛሬ መንግሥታዊ ተቋማትና ሕዝቡ ሊቋቋሙት የሚሞክሩት ሕገ ወጥ ስደትና የሰዎች ዝውውር ተግባር የማይመለከተው ይህን ነው፡፡ በእርግጥ የአገሪቱ የተፈጥሮ ሀብት መጪውን ትውልድ የማስተናገድ አቅም ገና አለው ሊባል ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ዕውቀት፣ ክህሎትና የኢኮኖሚ አቅም በበቂ ሳይኖር አገር ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በብቃት መጠቀም አይቻልም፡፡ ዛሬ ወጣቱ ባለው የሙያ መስክ በኅብረት እየተደራጀ የራሱን የሥራ መስክ እንዲመሠርት መንግሥት ያበረታታል፡፡ የመሥሪያ ቦታና መነሻ ብድር ፈንድም ተዘጋጅቶለታል፡፡ ይህ መልካም ጅምር ነው፡፡ ብዙ ቁጥር ያላቸው ወጣቶችም በዕድሉ ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል፡፡ ዕውቀቱ፣ ክህሎቱና ፍላጎቱ ላላቸው ይኼንን ዕድል በአገር ደረጃ በስፋት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በየመስኩ ሥልጠናዎችና ማበረታቻዎች መስጠትም ጎን ለጎን መሄድ ያለበት ነው፡፡ በተለይም ወደ ዋና ከተማው የሚደረገውን ፍልሰትና ወደ ውጭ የሚደረገውን ሕገ ወጥ ስደት ለመቀነስ ክልሎች የሥራ ዕድሎችን በስፋት እንዲከፍቱ ብዙ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ኢንቨስትመንት በክልሎች እንዲስፋፉ መሠረታዊ የልማት አውታሮች የመዘርጋቱ ሥራ ተጠናክሮ መካሄድ ይኖርበታል፡፡ ዛሬ ያለውን የሰው ኃይል ፀጋ በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል አድካሚና ሰፊ ሀብት የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል፡፡ በሙያዊ ጥናት ከታገዘ ግን ያለው እምቅ የሰው ኃይል ለዕድገት እንጂ ለድህነትና ለስደት እንደማይውል ተስፋ አድርጎ በጥንካሬ መሠራት ያስፈልጋል፡፡

ሐሳቤን ለማጠቃለል ለወደፊቱስ ምን መደረግ አለበት? በሚለው ነጥብ ላይ ጥቂት አስተያየቶች ልስጥ፡፡

የቤተሰብ ምጣኔ ትምህርቶችን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች የሚያስተላልፉ መንግሥታዊና የግል ድርጅቶች በአገር ውስጥ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በሬዲዮና በቲቪ የሚሰጡዋቸውን መልዕክቶች አልፎ አልፎ እንከታተላለን፡፡ እነዚህ ድርጅቶች በዚህ ብቻ ባይወሰኑና ሕዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ለጥቂት ደቂቃዎች መድረክ እየተሰጣቸው መልዕክቶች የማስተላለፍ ልምድ ቢያዳብሩ ይረዳል፡፡

በክልሎችና በገጠር መንደሮችም ጭምር የተቀናጀ ሥራ በየቋንቋው መሥራት የሚቻልበት ሁኔታ ቢታሰብበት፣ ካለም ቢጠናከር መልካም ነው፡፡ የየአካባቢውን ሕዝብ ባህልና እምነት በማይነካ መልኩ መልዕክቶች እንዲተላለፉ የሃይማኖት አባቶችና የአካባቢ ሽማግሌዎች በቂ ግንዛቤ ጨብጠው፣ የሐሳቡ ተካፋይ  እንዲሆኑ ማስቻልም ጠቀሜታ አለው፡፡ የመልዕክቱ ዋና ማጠንጠኛ ሊሆን የሚገባው የትዳር ጓደኛሞች መውለድ ያለባቸው የልጆች ቁጥር በአግባቡ ማሳደግ የሚችሉትን ያህል ብቻ እንዲሆን የምክር አገልግሎትና ትምህርት መስጠት ነው፡፡ ይህ አገልግሎት በአንዳንድ ሥፍራዎች እየተካሄደም ቢሆን፣ መዳበርና መስፋፋት ይኖርበታል፡፡

ይህንን ትምህርትና አገልግሎት ለአብዛኛው ሕዝብ ማዳረስ በጽሑፍ እንደምገልጸው ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ በቂ በጀት፣ የሠለጠነ የሰው ኃይልና ከልብ ለዓላማው ስኬት መሠለፍን ይጠይቃል፡፡ በተለይም ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ የአመራር አካላትን ይህንን ሥራ ወደ ተግባር ለመቀየር ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል፡፡

ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ቤተሰቦች ባሉባቸው አካባቢዎች የጎልማሶች ትምህርት በበጎ ፈቃደኞች ድጋፍ ተስፋፍቶ እንዲቀጥል ሁኔታዎች መመቻቸት ይኖርባቸዋል፡፡ በቤተሰብ ምጣኔ ላይ የሚዘጋጁ የበራሪ ወረቀቶችና ፓምፍሌቶች ኅትመት ትኩረት ሊያገኙ ይገባል፡፡ ለቤተሰብ በቂ ትምህርት፣ ቅስቀሳና ተፈላጊዎቹን አገልግሎቶች የሚያዳርሱ ባለሙያዎች በብቃት መሠልጠንና መሰማራት ይኖርባቸዋል፡፡

ይህንን አገልግሎት ለብዙኃኑ ሕዝብ ለማዳረስ ጠንካራ አመራር ሊሰጥ የሚችል ባለበጀት የሥነ ሕዝብ ቢሮ ከአሁኑ በተሻለ መልኩ መልሶ ማደራጀት ወይም ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

ከአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅምና የዕድገት ጉዞ በጣም በፈጠነ መልኩ የሕዝብ ቁጥር መጨመሩን ከቀጠለ ጉስቁልናና ድህነት የሚለቀን አይመስልም፡፡ ቤተሰብ ልጆች አፍርቶ ለማሳደግ አቅም ከሌለው፣ መንግሥታዊ ተቋማትም የሚሰጡት ድጋፍ ሁሉን ተደራሽ ለማድረግ አቅሙ ከሌላቸው፣ ዛሬ የምናየው ችግር እየተባባሰ ይሄዳል፡፡ የሕፃናት ወደ ከተሞች ስደት፣ የወጣቶች ለሕገ ወጥ ደላሎች ሴራ መጋለጥና መንከራተት ተንሰራፍቶ ይቀጥላል፡፡

አገር አቅሟን መጥና የሰው ሀብት ማፍራት አለባት፡፡ ልትንከባከበውና ልታሳድገው የማትችለውን የሰው ቁጥር ያለበቂ ምክርና የቁጥጥር አገልግሎት ዝም ብሎ ማፍራቱ የሚያስከትለው ጎጂ ውጤት ሊታየን ይገባል፡፡

በኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚፈጠር ሕዝብ በቂ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክብካቤ አግኝቶ፣ ሰብአዊ ክብሩ ተጠብቆ በየአካባቢው የሚኖርበት ዘመን መምጣት አለበት፡፡ እዚያ ዘመን ላይ ለመድረስ ደግሞ የጉዞው መጀመሪያ ከአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ አቅም ጋር የሚጣጣም የሕዝብ ቁጥር መኖር ነው፡፡ ይኼ አቅጣጫ ሳይዘነጋ ብርቱ ትኩረት ሊያገኝ ይገባል፡፡ ጋራውና ሸንተረሩ የውበት፣ የልምላሜ፣ የምንጮች መፍለቂያ ይሁኑ፤ መጪው ዘመን የተመጠነ የሕዝብ ቁጥር ታይቶ፣ ሁሉም ዜጋ መልካም ኑሮና ሕይወት እንዲያገኝ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በስፋት ይሠራበት፡፡

በየመስኩ የሠለጠኑ ባለሙያዎችም የተሻለ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት በምድሪቱ እንዲኖር የድርሻቸውን ያለመሰልቸት ሊወጡ ይገባል፡፡ ይህ ሁሉ ግቡን ሊመታ የሚችለው ግን መንግሥት በቂ ትኩረት ለዚህ አካባቢ ሲሰጥ ነው፡፡ ዘርፉ በበቂ በጀትና ዕቅድ እንዲመራ በተለይም የመስኩ ባለሙያዎች መንግሥትን የማሳመንና አብሮ የመሥራት ትልቁን የኃላፊነት ድርሻ መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡     

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

     

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

Trending Articles