በፀዳሉ ንጉሤ
በዚህ ርዕስ ዙሪያ ላነሳው ላሰብኩት አንጓ ጉዳይ መነሻ እንዲሆነኝ አንድ ሐሳብ ላስቀድም፣ የአመራር ኃላፊነት ከምንም ነገር በፊትና በላይ ችግር መለየት (Problem Identification) እና መፍታት ነው፡፡ በዚህ መሠረት አመራር ከትናንት ለዛሬ የተላለፈን ችግር ለይቶ መፍታት አለበት፡፡ በተጨማሪም ዛሬ በራሱ ምክንያት የፈጠራቸውን ችግሮችም እንደዚሁ ለይቶ መፍታት ይገባዋል፡፡ እንደገና ደግሞ ነገ ሊፈጠሩ የሚችሉና ኅብረተሰብን ሊያቃውሱ የሚችሉ ችግሮችን ከወዲሁ ለይቶ በበቂ ዝግጅት ሊያስወግዳቸው መሥራት ይገባዋል፡፡ (አዲስ ራዕይ መጽሔት፣ 11ኛ ዓመት፣ ቅፅ 5፣ ቁጥር 4፣ መጋቢት - ሚያዝያ 2008፣ ገጽ 30፡፡)
እውነት ነው ተልኮውን ጠንቅቆ የተረዳ፣ በጥቅም ያልታወረና ልቡ ያልደነደነ አመራር ማድረግ ያለበትና መሆንም ያለበት ከላይ የተጠቀሰውን ነው፡፡ ‹‹የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ›› እንዲሉ፣ አንዳንድ የወረደ ሥነ ምግባር ያላቸው ኪራይ ሰብሳቢዎች አሁን አሁን የሚያሳዩት ትዕቢትና እብሪት ገደቡን እያለፈ ድርጊታቸውም ቅኖችን እየተፈታተነ ነው፡፡ በኪራይ ሰብሳቢ አስተሳሰብና ተግባር በተዘፈቁ ሰዎች ላይ መወሰድ ያለበት ዕርምጃ በዘገየ ወይም በግማሽ ልብ ብቻ የሚፈጸም ሲሆን . . . ኪራይ ሰብሳቢዎች የልብ ልብ እየተሰማቸው የአይነኬነት መንፈስ እያዳበሩ ይሄዳሉ፡፡
(ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 34) የሚለው አገላለጽ አሁን አሁን በገሀድ እየተፈጸመ ነው፡፡ መንግሥትን ምን ነካው እያስባለም ነው፡፡ ለትዝብት ያህል ይኼን ካልሁኝ ይበቃል፡፡ ወደ ርዕሰ ጉዳዬ ልመለስ፡፡
‹‹በ2015 ዓ.ም. ሙስና ለልማትና መልካም አስተዳደር እንቅፋት ከማይሆንበት ደረጃ በማድረስ በዓለም ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ከሆኑ የፀረ ሙስና ተቋማት አንዱ ሆኖ #Uንም$ እንዲሉ የተቋሙን ችግር በመንግሥት ለማላከክ የወሬ ዘመቻ ከከፈቱ ሰንበትበት ብለዋል፡፡ ወሬው አልፎ ተርፎም የኪራይ ሰብሳቢዎች እጅ አለበት እስከማለት ተደርሷል፡፡ የጎራ መደበላለቅ ይላል ይኼ ነው፡፡ ይኼ ራሱ ብዙ የሚያነጋግር ጉዳይ ቢሆንም በይደር ልለፈውና ወደ ዋናው ጉዳይ ልመለስ፡፡
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የዓቃቤ ሕግ ሙያተኞችን ወደ ራሱ ሲያዛውር የሄደበት አግባብ አብዛኛውን የኮሚሽኑን ሠራተኞች ያስደመመና ያስገረመ ሆኖ አልፏል፡፡ ይህ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ድርጊት ውስጠ ወይራ ነው፡፡ እያንጓለለ! እያንጓለለ! እያንጓለለ! ‘አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ'ብዙኃኑን ሠራተኞች ጉድ አስብሏል፡፡ ይህ ጉዳይ በሠራተኞች ዘንድ ብዙ ጥያቄዎችንም አስነስቷል፡፡ ለምሳሌ፡-
- ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በቅርብ ሙያውን የተቀላቀሉትንና ምንም ተሞክሮ የሌላቸውን ተቀብሎ ሰፊ ልምድና ተሞክሮ ያላቸውን፣ በሙያው ተክነናል የሚሉትን፣ በአመራር ላይ የነበሩትንም ሳይቀር ለምን ተዋቸው? ብለው የሚጠይቁ በርካቶች ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ፣
- ለካ መንግሥት ውስጥ አወቅ ነው፣ ብዙ ነገር ይታወቃል ማለት ነው? ግን ይኼ ነገር በእንደዚህ መታለፉ አስተማሪ ነው? የሚሉም አልታጡም፡፡
ይሁንና ይህ በእንዲህ እንዳለ #[ጅም ጦር ባይወጉበትም ያስፈራሩበት$ ሆነ እንጂ፡፡
እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጉዳይ የአንድ ተቋም አመራር የተቋሙን ዓላማ አስፈጻሚ የሥራ ሒደቶች ዓላማ የማስፈጸም ድርሻ በእኩል ዓይን በማየት፣ ሁሉም ዓላማ አስፈጻሚ የሥራ ሒደቶች የሥራ ድርሻቸውን በትክክል እንዲወጡ ተገቢውን ድጋፍና እገዛ ሊያደርግ ይገባል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ አመራሩ አንዱን ዓላማ አስፈጻሚ የሥራ ሒደት አግዝፎ ሌላውን አኮስሶ/አሳንሶ በማየት የሚደረግ አመራር፣ በተቋሙ ውጤታማነት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡
በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ላለፉት ዓመታት የሥራ እንቅስቃሴ ስኬት መታጣት አንዱ የአመራሩ በዓላማ አስፈጻሚ የሥራ ሒደቶች ላይ የነበረው የተንሸዋረረ አመለካከት ነው ማለት ይቻላል፡፡
የኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች የሕግ ሰዎች መሆናቸው ይመስላል የሙስናና የብልሹ አሠራር ችግሮች ሕግን በማስፈጸም ብቻ የሚፈቱ እስከሚመስል ድረስ ትልቅ ትኩረት ይሰጥ የነበረው፣ ለምርመራና ዓቃቤ ሕግ የሥራ ሒደት ነበር፡፡ (ሕግ የማስፈጸሙ ሥራስ በትክክል ይፈጸም ነበር ወይ? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ) የምርመራና ዓቃቤ ሕግ የሥራ ሒደት ሥራ ደግሞ ራሱ በባህሪው ለሙስናና ለብልሹ አሠራር ተጋላጭ በመሆኑ፣ የሥነ ምግባር ችግር/ስብራት ያለባቸው አመራሮችም ሆኑ ፈጻሚዎች በችግሩ ውስጥ አልወደቁም ማለት አይቻልም፡፡ ለዚህም ነው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እያንጓለለ! እያንጓለለ! እያንጓለለ! በድርጊቱ የከፋውንና የተበላሸውን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ ዝውውሩን የቋጨው፡፡
የሙስና ወንጀል ድርጊት ይጋባል/ይሸጋገራል የሚለው የምሁራን አገላለጽ እውነትነት አለው፡፡ በኮሚሽኑ በምርመራና የዓቃቤ ሕግ የሥራ ሒደት የሥነ ምግባር ችግር ባለባቸው ሠራተኞች የተጀመረው የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር አነሰም በዛ፣ ቀስ በቀስ ወደ ሌሎች ዓላማ አስፈጻሚና ድጋፍ ሰጭ የሥራ ሒደቶችም በመዛመቱ ሙስናና ብልሹ አሠራር እንደ ችግር ማይታይበት ደረጃ ዝቅ እንዲል ‹‹ታግሎ ያታግላል››የተባለለት የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ በኅብረተሰቡ ዕይታ ጥያቄ ውስጥ የገባበት ሁኔታ ተስተውሎ አልፏል፡፡
ለምሳሌ፡- ላለፉት ጥቂት ዓመታት የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ራሱ በሚያመቻቻቸው የትምህርት/ሥልጠና መድረኮች፣ በታዳሚ የኅብረተሰቡ አካላት ዘወትር ከሚነሱ ጥያቄዎች ጥቂቱን ልጥቀስ፡-
- ራሱ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከሙስናና ከብልሹ አሠራር ነፃ ነው ወይ?
- የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከተቋቋመ ወዲህ ሙስና ጨምሯል ወይስ ቀንሷል?
- ለፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሌላ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሊቋቋምለት ይገባል የሚሉ ሰዎች አሉ፣ መነሻቸው ምን ሊሆን ይችላል?
- የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከወገብ በታች ነው የሚሠራው ይባላል፣ እንዲህ የሚባለው ከምን መነሻ ነው?
- በሚዲያ የምትለቋቸው ቅጣቶች ከተፈጸመው ወንጀል ጋር ተመጣጣኝ አይደሉም፣ ቅጣቱ በጣም ዝቅተኛ ነው፣ ይኼ ሌሎችም ወንጀሉን እንዲፈጽሙ የሚያበረታታ አይሆንም ወይ? ወዘተ…
እነዚህና መሰል ከኅብረተሰቡ የሚነሱ አሽሙር አዘል ጥያቄዎች የኮሚሽኑ አመራር መለስ ብሎ ራሱን እንዲያይና ጉድለቶቹን እንዲያርም ጉልህ ግባቶች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ‹‹አስተሳሰቡ ያልተለወጠ ለውጥ አያመጣም›› እንዲሉ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ፣ ኅብረተሰቡም በኮሚሽኑ ላይ የነበረው አመኔታ ጥያቄ ውስጥ እየገባ እንደሄደ ከላይ የተጠቀሱ ጥያቄዎች እውነተኛ ማሳያ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
መንግሥት ለተቋሙ በአዋጅ የሰጠው ተግባርና ኃላፊነት በጣም ሰፊ፣ ለአገር ሰላማና ህልውና ወሳኝ ሆኖ ሳለ ተቋሙ መሆን የሚገባውን ሆኖ ባለመገኘቱ በአገርና በሕዝብ ላይ ተጋርጦ የነበረው ጥፋትና አደጋ ቀላል እንዳልነበረ ግልጽ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ‹. . . የት ላይ እንደወደቅክ ሳይሆን የት ላይ እንዳዳለጠህ ተመልከት› እንዲሉ፣ ድጥን ለይቶ ውድቀትን ተቀብሎ ለዘላቂ መፍትሔ እየተሠራ አይደለም፡፡
ሠራተኞች በፌዴራል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ እየለቀቁ ይገኛሉ፡፡ አመራሩም በኮሚሽኑ የሸፈነውን የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ብልሹ አሠራር በጥልቀት አጥንቶ ከመፍታት ይልቅ፣ <span style="font-size:12.0pt;line-height:200%;font-family: "Ge" ez-1","sans-serif";mso-fareast-font-family:mingliu;mso-bidi-font-family:="" mingliu;color:black'="">#Wራተኞች የሚለቁት ለተሻለ ገቢ ፍለጋ ነው<span style="font-size:12.0pt; line-height:200%;font-family:"Ge" ez-1","sans-serif";mso-fareast-font-family:="" mingliu;mso-bidi-font-family:mingliu;color:black'="">$ በሚል ሽፋን በማደናገር የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አሁንም ከሰፊ ችግሩ ጋር ይገኛል፡፡
በስተመጨረሻም የምርመራና የዓቃቤ ሕግ የሥራ ሒደት ከፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መነሳት በኮሚሽኑ አፈጻጸም ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ ምን ሊሆን ይችላል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ተገቢ ስለሚሆን በማስከተል በጥቂቱ በማሳየት ሐሳቤን ላጠቃል፡፡
የምርመራና የዓቃቤ ሕግ የሥራ ሒደት ከኮሚሽኑ ቢነሳም የኮሚሽኑን ራዕይ ለማሳካት አሁንም የሥራው 83.3 በመቶ ያለው በኮሚሽኑ ነው፡፡ ምናልባትም የተነሳው የሥራ ሒደት የሥራ ድርሻ የሥራው 16.6 በመቶ እንደሆነ በቀላል የሒሳብ ሥሌት ማወቅ ይቻላል፡፡ በኮሚሽኑ ስድስት ዓላማ አስፈጻሚ የሥራ ሒደቶች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የተነሳው አንዱ ነው፡፡ አምስቱ አሁንም አሉ፡፡ ስድስቱ ዓላማ አስፈጻሚ የሥራ ሒደቶች መቶ በመቶ የሚያስፈጽሙ ከሆነ፣ አምስቱ ስንት በመቶ? አንዱስ ስንት በመቶ? በሚል ሒሳባዊ ሥሌት በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡
ይሁን እንጂ አመራሩ 83.3 በመቶ ሥራው በኮሚሽኑ ያለ መሆኑን ተረድቶ፣ የሥራውን 16.6 በመቶን ደግሞ ከፌዴራል ፖሊስና ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጋር በሚኖር ቅንጅታዊ አሠራር ተግቶ በመሥራት ራዕይን፣ ተልዕኮንና ዓላማን ለማሳካት ቁርጠኝነቱ፣ ቀናነቱና በጎ አመለካከቱ አለ ወይ? ብሎ ለሚጠይቅ አሁንም እዚያ ላይ ሰፊ ክፍተት አለ፡፡
ሙስናና ብልሹ አሠራርን ታግሎ የማታገል ሥራ ችላ ሊባል የሚገባው ጉዳይ እንዳይደለ ግልጽ ይመስለኛል፡፡ በአንድ ሥርዓተ ማኅበር ውስጥ ሙስናና ብልሹ አሠራር ከተስፋፋና ከተንሰራፋ አገርን እስከማፈራረስ ድረስ ይደርሳል፡፡ በመንግሥት ተቋሙ ትኩረት ሊቸረው ይገባል በማለት ሐሳቤን በአጭሩ እቋጫለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
