በመታሰቢያ መላከ ሕይወት ገብረ ክርስቶስ
የመጽሐፉ ርዕስ ‹‹እነሆ መንገድ ለኢትዮጵያ›› የሚል ሲሆን መጽሐፉ በዋናነት የሚያጠነጥነው በአንድ ሐልዮት (Theory) ዙርያ ነው፡፡ ይኼም ሐልዮት የልቦና ውቅር ለውጥ (Paradigm Shift) የተሰኘ ነው፡፡ መጽሐፉ በ188 ገጾች ብቻ የተጻፈ ሲሆን፣ በውስጡ ግን እጅግ በበርካታ መረጃዎችና ለውጥ አምጪ አስተሳሰቦች የታጨቀ ነው፡፡ ነገር ግን የልቦና ውቅር ለውጥ የሚለውን ሐልዮት ለመተርጎም አንባቢ የግድ አንድ መቶ ገጾችን መጓዝ ግድ ይለዋል፡፡
ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ይኼንን ቲዎሪ ሲያብራሩት ገጽ 101፣ ‹‹የልቦና ውቅር ለውጥ (Paradigm Shift) የምንለው ጉዳይ ሰፊ መሠረት ያለውና ጥልቅ የሆነ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ የልቦና ውቅር ማለት አንድ ሰው ከወላጆቹ፣ ከቤተሰቡ፣ ከማኅበረሰቡ፣ ከመምህራኑና ከአካባቢው ጭምር የሚያገኘው ይዞት የሚያድገውና የሚዋሀደው ማንነቱ ነው፤›› ይሉናል፡፡
እኔም ራሴ (የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ) ይኼንን ቃል ከዚህ በፊት ሰምቼው ስለማላውቅ ለመረዳት ትንሽ ጊዜ ወስዶብኝ ነበር፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ይኼ አስተሳሰብ በፕሮፌሰሩ ዕይታ (እኔ እንደሚገባኝ) በአገራችን ኢትዮጵያ አሁን ላለብን መሠረታዊ ችግር እንደ ዋነኛ ምክንያት ያስቀመጡት ይመስለኛል፡፡
ጸሐፊው በመጽሐፋቸው ውስጥ እጅግ የተለሳለሱ አማርኛዎችን ብቻ በመጠቀም ለማቅረብ ሞከሩ እንጂ፣ መሆን የነበረበት የልቦና ውቅር ለውጥ በዋናነት ከከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች መጀመር እንዳለበት አስረግጠው መጻፍ ነበረባቸው፡፡ በዓለማችን በየትኛውም አገር የተመዘገበ ሥልጣኔ የልቦና ውቅር ለውጥ ከመንግሥት እስከ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ሳያካሂዱ ሥልጣኔ የመጣበት ሁኔታ የለም፡፡ ጸሐፊው ዘርዘር ባለ ሁኔታ የሲንጋፖርን ልምድ ያካፈሉን ሲሆን፣ የልቦና ውቅር ለውጥ በማምጣት አሁን በዓለማችን ታላቅ ሥልጣኔ እያመራች ስላለችው ቻይና ምንም ሳይሉን አልፈዋል፡፡
ያም ሆነ ይህ መጽሐፉ በአሁኑ ወቅት ለማንም ኢትዮጵያዊ ከመንግሥት ባለሥልጣን እስከ አንደኛ ደረጃ ያለ ተማሪ ሰብዕና ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል መጽሐፍ በመሆኑ፣ ማንኛውም ሰው አንብቦ በሕይወቱ ላይ አንድ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ቢጥር መልካም ነው እላለሁ፡፡
በተለይ ወላጆችና አስተማሪዎች መጀመርያ ራሳቸው በማንበብና ለልጆቻቸው ለተማሪዎቻቸው በማስረዳት ከተጠቀሙበት ጠቀሜታው እጅግ ትልቅ ነው፡፡
የመጽሐፉ የመጀመርያው ክፍል በአመዛኙ ምክር አዘል ትምህርቶችን የያዘ ሲሆን፣ ቁም ነገሮችና ሳይንሳዊ ትንታኔዎች የሚጀምሩት ወደ መሀል ገባ ሲባል ነው፡፡
በዓለማችን ከተካሄዱት አብዮቶች አንዱና ትልቁ በቻይና የተካሄደው የባህል አብዮት ሲሆን፣ ይኼ አብዮት በቻይናውያንና ከዚያም በመላው ደቡብ ምሥራቅ እስያ አብዮቱ እንዲቀጣጠል ታላቅ አስተዋፅኦ ያበረከተ ነው፡፡ ይኼ አብዮት የቻይና ሕዝብ የልቦና ውቅር ለውጥ ለማምጣትና አሁን ቻይና የደረሰችበት የዕድገት ደረጃ እንድትደርስ ታላቁን መሠረት የጣለ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በመሆኑም ይኼ ክስተት የዚህ ታላቅ መጽሐፍ አካል መደረጉ ጠቃሚ ነው የሚል ዕምነት አለኝ፡፡
ከዚህ ቀጥሎ መጽሐፉ ውስጥ ካሉ ይዘቶች ጠቀስ ጠቀስ እያደግረኩ ልለፍ፡፡ መጽሐፉ ገና ሲጀምር በህንዳዊው ማሕተማ ጋንዲ ጥቅስ ነው የጀመረው ‹‹አቅጣጫው የተሳሳተ የተጣደፈ ሥራ ፍፃሜው ከንቱ ድካም ነው፡፡›› ይኼ አባባል አገራችን አሁን ያለችበትን ሁኔታ በጥሩ መንገድ የሚገልጽ ይመስለኛል፡፡ በአገራችን በአሁኑ ጊዜ በርካታ ነገሮች እየተሠሩ ነው፡፡ ነገር ግን ሕዝባዊ እርካታንና ማኅበራዊ ለውጥ እያመጡ አይደለም፡፡ ይኼ ማለት እየሄድንበት ያለውን ወይም የመረጥነውን አቅጣጫ በሁሉም መስክ ቆም ብለን ለመመርመር የምንገደድበት ወቅት ላይ ነን፡፡ አለበለዚያ ሄደን ሄደን በጥቅሱ እንደተገለጸው ከንቱ ወደ ሆነ ውጤት ነው የምንደርሰው፡፡
‹‹ቀበቶውንና የጫማ ክሩን ከመጀመርያው በትክክል ያላሰረ ሯጭ ዕጣ ፈንታው መሀል መንገድ ላይ ቆሞ እንደገና ለማጥበቅ መሞከርና ውጤቱም ሽንፈት ይሆናል›› (ገጽ 32)፡፡
‹‹ሥራን ከጅማሬው በትክክል መሥራት ሁልጊዜም በትክክል መሥራት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ከልጅነት ጀምሮ ዳብሮና ጎልቶ ባህል መሆን የሚገባው ጉዳይ ነው›› (ገጽ 33)፡፡
‹‹ብልሆች ከሌሎች ይማራሉ ሞኞች ከራሳቸው ስሕተት ሊማሩም ላይማሩም ይችላሉ›› H.Bohn (ገጽ 74)፡፡
‹‹ዓለም የውድድር መድረክ መሆኗ ይታወቅ፡፡ እያንዳንዷ ሰከንድም በለውጥ ሕግ ውስጥ እያለፈች ነው›› (ገጽ 77)፡፡
‹‹ገፊ ምክንያቶች የተባሉት የመጀመርያው ደንበኛው የመጠየቁ ጉዳይ ነው፡፡ ደንበኛ ሁሌ የሚፈልገውን ይጠይቃል፡፡ በዚህም ምክንያት ደንበኛ ገበያውን ይመራዋል ማለት ነው፡፡
ዛሬ ውድደርን በድል መወጣት የማሸነፍ ጉዳይ ሳይሆን በገበያ ውስጥ ለመቆየትና የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ የውድድሩ ሕግ ደግሞ የሚመራው በአነስተኛ ዋጋ ከፍ ያለ ጥራትና መልካም አገልግሎት በፍጥነት በማቅረብ ላይ የተመሠረተ ነው›› (ገጽ 78)፡፡
‹‹ደካሞችንና ሰነፎችን አቅፎ በመያዝና በመደገፍ አገር አታድግም፡፡ ሰውን የሚያከብር ደግሞ ራሱም በምላሹ ይከበራል፡፡ ዋናው ጉዳይ የሰው ሀብት ልማት ነው›› (ገጽ 88)፡፡
‹‹ጥራትና ምርታማነት በአመለካከት ለውጥ ላይ የተመሠረተ እንጂ የአንድ ሰሞን ሙከራ ድርጊት አይደለም፡፡ እንደ ግለሰብም እንደ ተቋምም ሆነ እንደ አገር ቁርጠኛና ጠንካራ ውሳኔ በየረጃው መወሰኑ የግድ ነው፡፡ በሲንጋፖርም የተሳካ የዕድገት ጉዳይ ላይ ደተደረገው ጠንካራ ውሳኔዎችን በየደረጃው ያለማወላወል በመውሰድ ነው›› (ገጽ 94)፡፡
‹‹ሲንጋፖሮች በሃያ ዓመታት ውስጥ ሦስቱንም ዋና ዋና የለውጥ አንኳሮች አሳክተው ነው ለስኬት የበቁት›› (ገጽ 97)፡፡
‹‹ትልቁ ችግር ሰዎች አዲስ ሐሳብን እንዲቀበሉ ማድረግ ሳይሆን አሮጌውን እንዲጥሉ ማድረግነው›› John M.Keynes (ገጽ 100)፡፡
ይኼ አባባል አሁን ባለው የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ለዕድገት የማይመቹ በርካታ ጎታች ባህሎችን ይዘን ሥልጣኔ በብድር ገንዘብ ለመገንባት እየሞከርን ነው፡፡ ይኼ አካሄድ ያለ ጥርጥር እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚከተን፡፡
አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝቦች የልቦና ውቅር የሥልጣኔ ሕጎች ከሚያዙት የልቦና ውቅር ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ካልቻለ፣ በዜጎች ሕይወት ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ዕድገት ሊመጣ እንደማይችል መገንዘብ አለበት፡፡ ምክንያቱም ሁሉም አመርቂ ዕድገት ያስመዘገቡ አገሮች የሄዱበት ሒደት ይኼ በመሆኑ፡፡
አቶ በረከት ስሞኦን ‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ›› በሚለው መጽሐፋቸው ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓመት ከ100 ቀናት በላይ በበዓላት እያሳለፈ ዕድገት ሊመጣ እንደማይችል ጠቁመው ነበር፡፡ የሚገርመው እኚህ ሰው ይኼንን የጻፉት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን ቁጭ ብለው ቤተ መንግሥት እያሉ ነው፡፡ በአገሪቱ ወሳኝ ሥልጣን ለረጅም ዓመታት የያዘ ሰው እንዲህ ዓይነት አስተያየት መስጠት ይችላል ወይ?
‹‹የልቦና ውቅር ለውጥና ትራንስፎርሜሽን ይመሳሰላሉ፡፡ የቢራቢሮን ሕይወት ዑደት ብንመለከት መጀመርያ እንቁላል፣ ቀጥሎ ዕጭ፣ ከዚያ አባጨጓሬ ቢሆን ለውጡ ቀጥሎ በርካታ እግሮች ያሉት አባጨጓሬ በመጨረሻ ወደ አስደናቂ በአየር የሚበር ቢራቢሮነት ይለወጣል›› (ገጽ103)፡፡
‹‹አንድ ሰው ከልቦና ውቅር ውጪ አልወጣም ካለ የልቦና ውቅር ሽባነት ያግጥመዋል ማለት ነው፡፡ የልቡና ውቅር ልምሻ ደግሞ ለማንኛውም ለግልና የጋራ ሕይወት መስተጋብር ስኬት ከፍተኛ ጠንቅ ነው›› (ገጽ 105)፡፡
‹‹አዕምሮን በአንድ አቅጣጫ ላይ ቸንክሮ ከዚያ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም ብሎ መደምደም የልቡና ውቅር ልምሻነት ያስከትላል›› (ገጽ 107)፡፡
‹‹የልቡና ውቅር የፈቃድ ውሳኔ ጉዳይ ነው እንጂ የተፈጥሮ ጉዳይ አይደለም፡፡ እኛ ሁላችን አመለካከታችንን በመቀየር ሙሉ ሰዎች ሆነን አገራችንን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ልናደርሳት እንችላለን›› (ገጽ 109)፡፡
የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አስተያየት
የልቦና ውቅር ለውጥ በአንድ አገር ወይም ማኅበረሰብ እንዴት ሊከሰት ይችላል የሚለው ጉዳይ በበቂ ሁኔታ የተብራራ አይመስለኝም፡፡ በእኔ እምነት የልቦና ውቅር ለውጥ በአንድ ማኅበረሰብ አንደኛ አስገዳጅ በሆነ መልኩ (እነ ቻይና እንዳደረጉት)፣ የሕዝብን አስተሳሰብ ባህል የአኗኗር ዘይቤ አስተዳደግ በመቀየር ማምጣት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ሌላው ሁለተኛው መንገድ ትውልድን በትምህርት በማነፅና አዝጋሚ በሆነ መንገድ በረዥም ጊዜ ጉዞ የመለወጥ መንገድ ሲሆን፣ ሦስተኛው መንገድ ኅብረተሰቡ ራሱ ትክክለኛው ወቅት ሲመጣ ከዓለም አቀፍ ኅብረተሰቡ ጋር በተለያዩ መንገዶች በሚደረግ ግንኙነት ምክንያት እስኪለወጥ ዝም ብሎ የመጠበቅ ተግባር ይመስለኛል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት አማራጮች በአንድ ኅብረተሰብ ውስጥ ፈጣን ዕድገት ለማየት ምርጫው ሥልጣን የያዘው መንግሥታዊ አካል በመሆኑ፣ ከዚያ ውጪ ያለ ማንኛውም ኅብረተሰብ ሊኖረው የሚችል ተሳትፎ ወይም ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም አናሳ ይመስለኛል፡፡
‹‹የሕይወት አጋጣሚ ዝም ብሎ እንዲመራ ከፈቀድንለት በተዘዋዋሪ ሌሎች በእኛ ሕይወት ውስጥ እንዲመሩን ፈቀድንላቸው ማለት ነው፡፡ በሰው ሕይወት ላይ ይመወሰንን ሥልጣን ያገኙ ሰዎች ደግሞ ያሻቸውን የማድረግ ሥራ ለመከወን ዕድል ይሰፋላቸዋል፡፡ በዚያው መጠንም በግልም በቡድንም እንደ አገር የሚደርሰው አካላዊ ክስተት የከፋ ይሆናል›› (ገጽ 121)፡፡
ስለዚህ ዕርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው፡፡ የምንወስደው ዕርምጃ ደግሞ ቆራጥ ዕርምጃ ሲሆን ውጤቱ ያማረ ይሆናል፡፡ ዛሬ በአገራችን ቆራጥ ዳኞች፣ መምህራን፣ ወታደሮችና አስተዳዳሪዎች ያስፈልጉናል፡፡
‹‹ጉዳዩ እንደ ትራፊክ መብራቶች ነው፡፡ የትራፊክ መብራቶች አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ናቸው፡፡ አረንጓዴ የሆነው ምሳሌ እኛ የምንችለውና የተሻለ አድርገን የምንሠራው ነው፡፡ ቢጫው ደግሞ ልንሠራው እንችላለን ነገር ግን አርኪና አጥጋቢ አድርገን መሥራት ያልቻልነው ነው፡፡ ቀይ መብራት ግን እኛ የማንችለውና የማንሠራው ነው፡፡ ብንሠራውም እንኳ ውጤቱ ጥሩ አይሆንም፡፡ ስለዚህ በዚህ ጊዜ ይኼን አልችልም፣ ከእኔ የተሻሉ ሰዎች ይሥሩት ብለን ለሌሎች ማስተላለፍ ይኖርብናል›› (ገጽ 128)፡፡
‹‹ለምሳሌ በእኛ የወጣትነት ዘመን በንጉሡ ሥርዓት ላይ ድንጋይ ወርውረናል፡፡ ባህር ማዶ ተምረን በመጣንበትና እጅግ መሥራትና ለአገር መጥቀም በሚገባን የደርግ ዘመን በ‹‹በጎመን በጤና›› ዘይቤ ከሥርዓቱ ርቀን ኖርን፡፡ እንዲሁም አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የአንድ ወጣት ዕድሜ አሳልፏል፡፡ በዚህ ጊዜ ዳር ቆመን ተመልካች ከሆንን የእኛ ለአገርም ይሁን ለወገን የመሥሪያ ጊዜያችን አልቋል ማለት ነው›› (ገጽ 134)፡፡
ሠለጠኑ ወደሚባሉ አገሮች ዓይናችንን ብንወረውር ከላይ የተዘረዘሩትን የሙሉ ሰው ባህርያት የመግለጫ ሰብዕናዎች በአብዛኛው አዳብረዋቸዋል፣ የጋራ ፀባይ አድርጓቸዋል›› (ገጽ 139)፡፡
‹‹አሁን እያነሳነው ያለው ትልቅ የለውጥ ጉዳይ ከዛሬ ሰላሳና ከዚያ በፊት በነበሩት ዓመታት አንስተነው ቢሆን የበለጠ ጥሩ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን ያኔ አልተጀመረም ተብሎ ዛሬ አይታለፍም፡፡ ሁለተኛው ምርጡ ጊዜ አሁን ነው ብለን መጀመር አለብን›› (ገጽ 146)፡፡
በጣሊያን አገር በትምህርት ላይ ሳለሁ ጣሊያኖችን በጥቂቱም ቢሆን ጠጋ ብዬ ለማወቅ ዕድሉን አግኝቻለሁ፡፡ እነሱ ዛሬ የተባለ ገንዘባቸውን እንደ አምላክ ነበር የሚያዩት፡፡ ጣዖታቸው ነበር፡፡ ሊሬ ስንት ሺሕ ዘመን የሠራ የጣሊያኖች ገንዘብ ነበር፡፡ አውሮፓን የገዛ ነው ብለው የሚመፃደቁበትም ነበር፡፡ ወደ ጀርመኖች ስንመጣ ጀርመኖች ማርክ የተባለ ገንዘባቸውን እንደዚያው ነበር የሚያዩት፡፡ ነገር ግን የዓለም ሥርዓት ሲቀየርና ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ሲቀየር ተረዱት፡፡ በአንድ በኩል የምዕራቡ ዓለም በሌላ በኩል ደግሞ የእስያ አገሮች ታላላቅ የኢኮኖሚ ዋልታዎች ሚዛኑን ከግራ ቀኝ ሲወጥሩ፣ አውሮፓውያን ግፊቱን ለመቋቋም ወደ አዲሱ አስተሳሰብና ዘመን መሸጋገር ነበረባቸው፡፡ አውሮፓውያን አንድ ሆነው እስካልቆሙ ድረስ በአዲሱ የውድድር ሥርዓት መቀጠል እንደማይችሉ በመገንዛባቸው ወደ አንድ ወጥ ስምምነት ደረሱ፡፡
ይኼ ሁኔታ ምን ያህል የልቦና ውቅር ለውጥን በአንደ ጊዜ ማምጣት እንደቻሉ የሚያሳይ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አውሮፓውያን ከ4,000 ዓመት በላይ በመካከላቸው እርስ በርስ መራራ ጦርነት ያካሄዱ ሕዝቦች ናቸው፡፡
የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ
በአጠቃላይ ፕሮፌሰሩ እያስተማሩን ያሉት እጅግ በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮችን ነው፡ በዓለም ላይ ያሉ ድንበሮች እየደፈረሱ አገሮች ተጠጋግተውና ተደጋግፈው መራመድ ካልቻሉ የመጨረሻው ውጤት ውድቀት ብቻ እንደሆነ እያስተማሩን ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን እጅግ አሳሳቢ እንደ ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ የሥርዓት ዕጦት፣ የንዘብ፣ ወዘተ ችግሮት አሉብን፡፡ ከዚህ በፊት ያልነበሩ ምንም የማይጠቅሙንን ለምሳሌ በብሔሮች መካከል የሌለን ድንበር ፈጥረን በዚሁ ምክንያት እርስ በርስ እያጣላን ስንገኝ፣ ሌሎች አገሮች ድንበሮቻቸውን አፍርሰው የጋራ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ እያዳበሩ እያካሄዱ ያሉበት ወቅት ላይ ነን፡፡
ፕሮፌሰር በትንተናቸው እስካሁን የተጓዝነው ጉዞ ጠቀሜታው እንዳለው አልቆጠሩትም፡፡ እነሆ አንድ ብለን እንጀምር እያሉ ነው፡፡ ሰሚ ካገኙ እኔም ይኼ ጉዳይ ሁሌም እያሳሰበኝ ስለነበር የ2000 ዓ.ም. አዲስ ዓመት ሲከበር ‹‹ምንይልክኢዝም›› በሚል ርዕስ ከፕሮፌሰሩ አስተሳሰብ ጋር የሚቀርረብ መጽሐፍ አሳትሜ ለንባብ አብቅቼ ነበር፡፡
ለማንኛውም ውድ አንባቢያን መጽሐፉ ባጭሩ በዚህ መልኩ ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ፡፡ የተረፈውን አንብባችሁ ተረዱ፣ በጣም ጠቃሚ መጽሐፍ ነው፡፡
ማንም ሰው ምንም ያድርግ በየትኛውም መንገድ መራመድ እንዳለበት አቅጣጫውን ማወቅና ምርጡን መንገድ መምረጥ የግድ ይላል፡፡ አለበለዚያ እንደነ ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ኢራቅ ዓይነት ውዥንብር ውስጥ ገብተን አገራችንን ማፈራረስ ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ዘመን ግሎባላይዜሽን የሚባል ጎርፍ አለ፡፡ ይኼንን የጎርፍ አቅጣጫ ተከትለን ብቻ ነው መሄድ ያለብን፡፡ አለበለዚያ ጉዞው ሁሉ ውጤት አልባ ነው የሚሆነው፡፡
ከአዘጋጁ፡-ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው metasebyamelaku@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡
