በሽብሩ ተድላ
ሁለት የታወቁ የአማርኛ የግጥም ደራስያን (ተስፋዬ ገሠሠና በዕውቀቱ ሥዩም) ለአንድ የዑመር ኻያም ግጥም በየፊናቸው የሰጡትን ትርጉም (ትርጉም ማለቱ አከራካሪ፣ አወዛጋቢ ቢሆንም) ወይም ዕይታቸውን ላካፍላችሁ፡፡
ተስፋዬ ገሠሠ ‹‹መልክአ ዑመር›› ብሎ በሰየማት በ1987 ዓ.ም. የታተመች ውብ የአማርኛ ግጥም መድበል ‹‹የቅኔው መጽሐፍ ሳይቀር ይያዝና›› በሚል ርዕስ ያቀረባት የዑመር ኻያም ግጥም ናት የዚህ ጽሑፍ መንስኤ የሆነች፡፡ ይህችኑ ግጥም በዕውቀቱ ሥዩም ‹‹የማለዳ ድባብ›› ብሎ በሰየማት በ2009 ዓ.ም. በታተመች የአማርኛ ግጥም መድበል ውስጥ ‹‹የምድረ በዳ በረከት›› በሚል ርዕስ አበርክቶልናል፡፡ የእኔ አስተያየት (ጽሑፍ) ያጠነጠነው በሁለቱ አንጋፋ ደራስያን፣ በአንድ ግጥም ዕይታ (ትርጉም) ላይ ነው፡፡
ይህንን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ያነሳሳኝ የአለኝታ ደስታ ነው፡፡ ‹‹ማለት›› ብሎ የሚጀምር አረፍተ ነገር ስሰማ የምደነግጠውን ያህል፣ በወጣት ትውልድ የሚጻፉ የአማርኛ ግጥሞችን ሳነብ እረካለሁ፣ እኩራራለሁ፣ የባህል አለኝታዬ ካንቀላፋበት ይነቃል፣ ከሰመመን ይላቀቃል፣ ምንጩ አልደረቀም እላለሁ፡፡ ወጣት የአማርኛ ደራስያን (ገጣሚዎች) በርክተዋል፣ ብዙ ናቸው፤ የባህላችንም አለኝታዎች ናቸው፣ እኛ በርቱ እንበላቸው፣ ማበረታታቱ በተለይ የዕድሜ ባለፀጋዎች ኃላፊነት ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር ታይታ፣ ይች የእኔ ጽሑፍ ለወጣት ደራስያን እንደ ማበረታቻ ትወሰድልኝ፣ ስለግጥም መወያየት ባህል ተንኳሽ ትሁንልኝ፡፡
ግጥም አጠር፣ መጠን ባለ መጠን የተለያዩ ትርጉሞችን ለመስጠት ያመቻል፤ በጣም ዝርዝር ከሆነ፣ ሌላ ፍች አያስፈልገውም ይሆናል፡፡ ምንም ‹‹ግጥም›› ‹‹የሥዕልን›› ያህል የተለያዩ ትርጉሞችን ለመስጠት ዕድልን ባያበርክትም፣ የምርጥ አጭር ግጥም፣ ፍችው (ትርጉሙ) የሚያበርክተው የጥበቷ ተቃራኒ ነው፣ ትርጉሙ መጠነ ብዙ ሊሆን ይችላል፡፡ በውስን ቃላት የተዋቀረ፣ ነጥሮ የወጣ፣ ብዙ ትርጉም ያለው ሲሆን፣ በአንፃሩ ያለ የሌለውን ማዕድ አድርጎ ያቀረበ ግጥም ግልብ ይሆናል፡፡ የዑመር ግጥሞች በአራት መስመሮች ነው የሚቋጩ፤ ስለሆነም ውብም፣ ፍልስፍና አዘልም ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ትርጉመ ብዙ ሊሆንም ይችላል፡፡
አሁን ወደ ተነሳንበት ጉዳይ ልመለስ፡፡ ሁለቱ ታዋቂ ደራስያን (ተስፋዬ ገሠሠና በዕውቀቱ ሥዩም፣ በታሪክ አጋጣሚ ሁለቱም ወዳጆቼ ናቸው) በዕድሜ ይለያያሉ፣ በመሃላቸው ቢያንስ የ40 ዓመት ክፍተት ያህል አለ ብዬ እገምታለሁ፡፡ የሁለቱ ታዋቂ የግጥም ደራስያን፣ የስንኝ አወቃቀሮችም የተለያዩ ናቸው፡፡
የተስፋዬ ገሠሠ ሞቅ ደመቅ ያለ ነው፣ ፊት ለፊት ነው፣ የፈካ ነው፣ የሳቅ፣ የፈገግታ ምንጭ ነው፣ ሥዕላዊ ነው፡፡
ምሳሌ አንድ
የበረሃ ልጆች (ጎሕ ሲቀድ በምትባል የግጥም መድበል)
‹‹ለዘንፋላ ጡቶች ላረግራጊ ሽንጥ
ለለስላሳ ገላ ከንፈረ ምጥምጥ፤
ገንዘብ፤ ጤና ብቻ አይበቃም ድርጓቸው
ሕይወት፤ ጭንቀት፣ ጥበት፡-
ነፍስ ነው ግብራቸው!!››
(ለውቤ በረሃ ኮረዳዎች የተገጠመ ይመስላል)
ምሳሌ ሁለት
ግጥሞቹ ‹‹ዛሪያዊ›› ናቸው፣ ‹‹ኑረታዊ›› (Existential) ናቸው፡፡
ሕይወት ለመንግሥቱ ለማ
‹‹ . . .
አይመልሱትን ነገር የትናንቱንና የትናንቱን በስቲያ
አይናፍቁት ነገር ነገን ተነገወዲያ
ኧረ ወዲያ! ወዲያ ወዲያ!
ሽህ ቅኔ ቢቀኙ
ሽህ ሚሾ ቢወርድ አዳሜ ቢንጫጫ
መንጌ ‹‹ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ!››
ኧረ ወዲያ! ወዲያ! ወዲያ!››
የበዕውቀቱ ሥዩም ስልት፣ አቀራረብ፣ ከሚታሰበው፣ ካነገብነው ነባር ግንዛቤ፣ የተገላቢጦሽ ነው፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን የሚያናጋ፣ የሚያዛባ ነው፣ ዙሪያ ጥምጥም ዕይታን ያበረክታል፣ በእርሰ በርስ የማይዳሰሱ ገጽታዎች ያሉ አይመስልም፡፡
ምሳሌ አንድ
ፍግ ላይ የበቀለች አበባ (ስብስብግጥሞች በምትባል የግጥም መድበል)
‹‹አበባይቱም አለች፣
ፍግ ላይ የበቀለች
ምንድን ነው ጥበቡ?
ኔክታር ማጣፈጡ
አደይን ማስዋቡ፣
እኔም መለስኩላት፣
ይብላኝ ለንብ እንጂ ዝምብማ ይተጋል
ከቆሻሻ ዓለም ውስጥ ጣ'ምን ይፈልጋል፡፡››
ምሳሌ ሁለት
ዳዊት እና ጎልያድ
‹‹እግዜርና ዳዊት፣ አብረው ተቧደኑ
ብቻውን ታጠቀ፣ ጎልያድ ምስኪኑ
አንዳንዱ ተገዶ፣ ለሽንፈት ሲፈጠር
በጥቅሻ ይወድቃል፣ ስንኳንስ በጠጠር፡፡››
እኛ ‹‹ንብን›› ስናሞካሽ እርሱ ‹‹ዝንብን››፣ እኛ ‹‹ለዳዊት›› ስናዝን፣ እርሱ ‹‹ለጎልያድ›› ያደላል፡፡ ምን ያድርግ ከላይ የተወሰነበት ነው ብሎ ስኖቹ አስተካዥ ናቸው፡፡ ሰፊ አስተያየትንና ጥልቅ ግንዛቤን የተጎናጸፉ ናቸው፡፡
በሁለቱ መኻል ያለው የዕድሜ ልዩነት፣ የዕይታ ልዩነትን ሊያስከትል ይችላል አድማሳቸው፣ አቅጣጫቸው (በአጭሩ ወደ ግጥሙ የሚመለከቱበት መስኮት) አንድ አይሆንም፣ ዕድሜና ስልት ይለያዩዋቸዋል፡፡ ከላይ የሠፈሩት ግጥሞች፣ ስለደራስያኑ መጠነኛ ግንዛቤ ያስጨብጡናል ብዬ እገምታለሁ፡፡
ወደ ዋናው ጉዳይ ልመለስ፡፡ ግጥም ከአንድ የቋንቋ ጋን ወደ ሌላ የቋንቋ ጋን ሲገለበጥ ምን መስሎ ይገልበጥ ለሚለው? እያንዳንዱ አንባቢ ሊተችበት የሚችል ሁኔታ ነው፡፡ በባህል አባዜ ይታሰራል፣ በተሞክሮ ይገረገራል፣ በቋንቋ ቃላት ምንጭነትም (ባሕር አከል/ኩሬ መሰል) ይወሰናል፡፡
ግጥም ከመጀመሪያ ከተደረሰበት ቋንቋ ወደ ሌላ ቋንቋ ሲቀለበስ፣ ሲተረጎም፣ ውበቱ ለዛው የሚገለጠው በአካባቢ ዕይታ ስለሆነ፣ አዲሱ ቋንቋ የሚያስተናግደውን ባህል፣ ማኅበራዊ አስተሳሰብ፣ መዳሰስ ማካተት ይገባዋል፡፡ ደረቅ የግጥም ትርጉም፣ ለዛውን ይገፈፋል፣ ውብ ግጥምም አይሆንም፡፡ ይህች ጽሑፍ በዚህ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተች ናት፡፡
የዑመር ኻያም (OMAR KHAYYAM) ግጥም ከፐርሽያን (ፋርስ) ቋንቋ በኤድዋርድ ፊትዝጀራልድ ወደ እንግሊዝኛ የተቀለበሰው (የእንግሊዝኛ ትርጉም - English translation of the original) እነሆ፡፡
Here with a loaf of bread beneath the Bough,
A Flak of wine, a Book of Verse-and Thou
Beside me singing in the Wilderness
And Wilderness is Paradise enow.
የዑመር ኻያም ግጥም መልእክት እንደ ሽርሽር መውጣት ሆና፣ ስንቅንና አካባቢን (ቦታን) አገናዝበን እንድንመለከታት ትጋብዘናለች፡፡ ከዚያም ሁኔታዎችን ያገናዘበ ትርጉም፣ እይታና ስሜት ታበረክትልናለች፡፡ ሽርሸር ሲወጣም ትንሽ ዳቦ፣ አንድ ፋሽኮ ቪኖ (ወይን)፣ የግጥም መጽሐፍ ይዞ ሰወር አለ ቦታ፣ በዛፍ ሥር ተጠልሎ፣ ወዳጅን እያስዘፈኑ መደሰት ነው፡፡ የተያዘውንም ስንቅ እንዲሁም አካባቢውን፣ ብሎም የደስታው ምንጭ ምን እንደሆነ ማጤን ያሻል፣ አስተዋፅኦ ያደረጉ ይመስላል፡፡ ስንኙ በአራት መስመሮች (ሩብያት) የተወሰነ ነው፡፡
እንግዲህ የሁለቱን ቁንጮ የአማርኛ ደራስያን (ገጣሚዎች) አተረጓጎም ልመልከት፣ ስመለከት ግን፣ ከሦስት አቅጣጫዎች ብቻ እንዲሆን ወስኛለሁ፡፡ ያንን ያደረግኩበት ምክንያት ግንዛቤው ሳይኮላሽ መንዛዛቱ ይቀንሳል ብዬ ስለገመትኩ ነው፡፡ ሦስቱ አቅጣጫዎች (የግጥሙ መፈተሻ) እንሆ፡- ትርጉሞቹ ከዋናው (ከዑመር ግጥም) ጋር የይዘት ተመሳሳይነት፤ ትርጉም የተዋቀረባቸው ቃላት ብዛትና አካባቢውን አጢኖ ትርጉም ለምን ወይም ለማን ትኩረት እንደተሰጠ፣ ናቸው፡፡
እንግዲህ ትርጉሞችን አንድ ባንድ ላውሳ፡፡
በተስፋዬ ገሠሠ (1987 ዓ.ም.) መልክአ ዑመርበምትባል የግጥም መድበል እንደቀረበች፤
የቅኔው መጽሐፍ ሳይቀር ይያዝና
‹‹እንግዲህ ከዛፍ ሥር ጋደም ይባልና፣
የግጥም መጽሐፍ ሳይቀር ይያዝና፣
ፍትፍቱ ባገልግል፣ ጠላው በቅምጫና፣
ጠጁ በብርሌ ቡናው በጀበና፣
እጣኑ ከገሉ ቦለለል ይልና፣ እግር ባልዞረበት ሥውር አለ ስፍራ
ካጀብ ተለይቶ ከግርግር ርቆ ሆኖ ካንች ጋራ››
. . . .
ኸዚያ ወዲያማ፣
ኸዚያ ወዲያማ፣
ዝፈኝልኝ ነዋ እንጉርጉሮ በይ፣
‹‹አራዳም እንደሰው ይናፍቃል ወይ፣
አራዳ አራዳዬ አራዳ አራዳዬ፣
ሆይ-ሆይ! ገነት ማለት፣ ይች ናት ሆድዬ!››
በዕውቀቱ ሥዩም (2009 ዓ.ም.) የማለዳ ድባብበምትባል የግጥም መድበል፣ ‹‹የምድረ በዳ በረከት›› በምትል ርዕስ እንደቀረበች፤
አንዲት ብርጭቆ ወይን፣
አንዲት ጤፍ እንጀራ፣ አንዲት አሪፍ ግጥም፣
እነዚህ ባሉበት በምድረ በዳ ላይ ቁጭ ብለሽ ከጎኔ፣
ሌላው ምን ይሠራል፣
ምድረ በዳው ሁሉ ዓደይ ለብሶ ያደርራል፡፡
ተስፋዬ ገሠሠ የአካባቢውን ድባብ በዝርዝር አስፍሯል፤ የግጥም መጽሐፍ፣ በዳቦ ፋንታ ፍትፍት በአገልግል፤ በወይን ፋንታ ጠጅ፣ ጠላ፤ እንዲሁም ዋናውን የሠፈር ባህል ቡና እና እጣንን ያካትታል፡፡ ዘወር ያለ ቦታንም ይመርጣል፣ ከግርግር ይሰወራል፣ ዛፍ ሥር ይጠለላል፡፡ እንጉሮውም ስለአራዳ ይሆናል፣ መኻል አዲስ አበባ፡፡
ዑመር ያወሳቸውን ሁሉ፣ ተስፋዬ ገሠሠ (ስንቅም ሆነ አካባቢ) አውስቷል፣ ያልነበረም ጨምሮበታል (ቡና፣ እጣን)፡፡ እይታውን አገር ቤት አስገብቶታል፡-
ዝፈኝልኝ ነዋ እንጉርጉሮ በይ፣
‹‹አራዳም እንደሰው ይናፍቃል ወይ፣
አራዳ አራዳዬ አራዳ አራዳዬ፣
ሆይ-ሆይ! ገነት ማለት፣ ይች ናት ሆድዬ!››
በተስፋዬ ገሠሠ ቅልበሳ የዑመር ግጥም ሙሉ በሙሉ አገራዊነት ተላብሳለች፡፡
በዕውቀቱ ሥዩም “ዊልደርነስ” (wilderness) ለሚለው ቃል የመጽሐፍ ቅዱስ ዓይነት ትርጉም ሰጥቶ “ምድረ በዳ” ብሎታል (ምሳሌ፤ ሙሴ በምድረ በዳ)፡፡ የቃሉ (wilderness) ተራ ትርጉሙ ዘወር ያለ፣ ጸጥ ያለ፣ ሰው የማይታይበት፣ ተፈጥሮ የገነነበት አካባቢ ነው፡፡ እንዲሁም የበዕውቀቱ እይታ የዑመርን ግጥም ይዘት ሙሉ በሙሉ አያካትትም፡፡ ለማካተት ከተሞከረበትም ገፅታ ሲታይ አቀራረቡ ከዑመር ካቀረበው ሁኔታ ጋር ይለያያል፡፡ ለምሳሌ ዑመር አንድ ፋሽኮ ቪኖ ሲያቀርብ፣ በዕውቀቱ አንድ ብርጭቆ ወይን ያቀርባል፣ ዑመር አንድ የቅኔ መጽሐፍ ሲያቀርብ፣ በዕውቀቱ አንዲት አሪፍ ግጥም ይላል፡፡ በዛፍ ጠለላ ስር ቆይታን አያመለክትም፤ እንዲያውም አካባቢውን “ምድረ በዳ” ያደርገዋል፡፡ ቆይታው በዘፈንም ሆነ በእንጉርጉሮ አልታጀለም፣ አልታጀበም፡፡
ይህም ሆን ተብሎ የተደረገ ይመስላል፣ አካባቢውን በጎላ መልኩ በአንድ ሌሊት ለመቀየር፣ አበባ አላብሶ ለማደር፡፡ የምድረ በዳው አበባ ለብሶ ማደር፣ ክስተቱን፣ ድርጊቱን፣ ሁኔታውን፣ ግሩም ድንቅ ያደርገዋል፣ ተዓምር ያስመስለዋል (ምደረ በዳን ባንዲት ሌሊት አስሽብርቆ ማደር)፡፡ ለምለም የሆነን አካባቢ፣ አበባ ቢጨምሩበት፣ አንፃራዊ መብቱ የጎላ አይሆንም፡፡ ኮረዳዋ በዑመር ጎኑ መገኘት ብቻ ደስታን ለዑመር ያጎናፅፈዋል፣ አካባቢው ራሱ መንግሥተ ሰማያት ይሆናል፣ ሌላው ምን ያደርጋል ብሎ ይደመድማል፡፡
በበዕውቀቱ የግጥም ቅልበሳው በአምስት መስመሮች ነው የተዋቀረ፣ “ሩብያትነቱን” ለጥቂት ነው የሳተ፡፡ በዚህ ዑመር ይደሰት ነበር ብዬ እገምታለሁ፣ የቃላት ቋት ለእርሱ፣ ለዑመር፣ “ሃራም” ስለነበረ፣ “የምን ጋጋታ ነው?"“እፍኝ ሙሉ ውብ ቃላት ይበቃሉ” ብሎ ያምን ነበር ብዬ ስለምገምት፡፡
በበዕውቀቱ እይታ ወይን (ቪኖም) የተያዘው በአንድ ብርጭቆ ነው፣ ዑመርና ወዳጁ ተራ በተራ ፉት ሊሉ ይሆናል፤ ያም የቅርበት፣ የፍቅር ሌላው መግለጫ ይሆናል፡፡ አንዲት አሪፍ ግጥም ነች የተሰነቀች፣ እሷው ናት በጋራ እምትነበነብ ማለት ነው፤ አንድ ብርጭቆ እንደመጋራቱ ሁሉ፡፡ የኮረዳዋ ከዑመር ጎን ሻጥ ማለት መንግሥተ ሰማያት እንደመግባት ያህል ይወሰዳል፡፡
ተስፋዬ “ሩብያቱን” በአሥራ ሁለት መስመሮች ይመነዝራል፡፡ ምነው የረፋድ መንገድ አደረግክብን? ብለን ልናማው እንችላለን፡፡ ቢሆንም ረፋድን በተዋበ አካባቢ ነው ያሳለፍነው፡፡ የተጓዝነው ብለን ልንጽናናም እንችላለን፡፡ እርሱም ጉዞውን ለማስዋብ ነው ባህላዊ ከባቢ ያሰፈርኩላችሁ ሊለን ይችላል፡፡
በዕውቀቱን ደግሞ ምነው ኮረዳዋን ብቻ የመንግሥት ሰማያት መጎናጸፊያ አደረግኻት፣ የአካባቢውን ድባብ ፋይዳ ቢስ አደረግኸው? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፣ በወቀሳ መልኩ፡፡ ዕድሜን አገናዝቦ፣ ያንን እርሱት፣ ተዉት! የምን ኮተት ማብዛት ነው? ሊለን ይችላል፡- ትኩስ ኃይል፡፡
የሁለቱም መልስ ተመሳሳይ ወይም አንድ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ዕድሜያችን! ብለው ይመልሱ ይሆን? “እረጭ” በማለት ላይ ያለ ደም እና “ትኩስ” ደም መኻል ያለ ልዩነት ብለን ልንደመድም እንችል ይሆናል፡፡
ተስፋዬ ገሠሠ የዑመርን ግጥም ወደ አገር ቤት ሲያስገባት፣ ቡና አፍልቶ፣ እጣን አጢሶ ነው፣ የገጠመኝ ፀጋ፣ ዕድሜ ባስነገበው መስኮት ላይ ሆኖ አይቶ፡፡ በዕውቀቱ ሥዩም፣ ያለአካባቢ ድባብ (የዛፍ ጠለላም ሆነ፣ የጣን ጢስ፣ ቡና ሌላ፣ ሌላ)፣ የኮረዳዋ መገኘት ብቻ፣ መንግሥተ ሰማያት የመግባት ያህል ነው አለ፡፡ እንጉርጉሮም ሆነ ዘፈን አላስፈለጉም፡፡ ይባስ ብሎ፣ ቆይታን አንድ አዳር አከለበት፣ ዑመር ያላወሳውን (ምድረ በዳው አበባ ለብሶ ያድራል አለ፣ እዚህ አድራለች ማለት ነው፣ እርሷ በሌለችበት አዳር ይህ ተዓምር አይከሰትም ብሎ መገመት ይቻላል)፡፡ የኮረዳዋ እዚያ መገኘት እርካታ አበረከተ፣ ለዑመር ብቻ ሳይሆን ለአካባቢውም ጭምር፣ አካባቢውን አስሸበረቀው፣ አበባ አላበሰው፡፡
እንግዲህ ይህ ዓይነት ዘገባ፣ የሌሎች ተመሳሳይ ዘገባዎች መተንኮሻ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፣ ተስፋ የሁላችንም ከዛሬ ወደ ነገ መሸጋገሪያ ነው፤ ስለሆነም ተመሳሳይ ትችቶች በተለይ በወጣቱ ኃይል ይቀርባሉ ብዬ በተስፋ እጠባበቃለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ሽብሩ ተድላ (ፒኤችዲ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂና የፓራሲቶሎጂ ልሂቅ (ኢመረተስ) ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎቻቸውን አሳትመዋል፡፡ በቅርቡም ጥልቅ ማኅበራዊና ሰብአዊ (ሶሺያል ኤንድ ሂዩማኒስት) ጉዳዮችን በጥልቀት ያቀረቡበት ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስ አበባ፡- የሕይወት ጉዞ እና ትዝታዬየተሰኘ መጽሐፍ ለኅትመት አብቅተዋል፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው shibrut@gmail.comማግኘት ይችላል፡፡
