(ክፍል አንድ)
በጀማል ሙሐመድ (ዶ/ር)
የህንዱገጠመኝ
እ.ኤ.አ. በ1998 በደልሂ ከተማ፣ በህንዳዊው የመገናኛ ብዙኃን ተቋም፣ ከ18 ታዳጊ አገሮች የተውጣጣን 19 ጋዜጠኞች ከትመናል ከደቡብ አሜሪካ፣ ከአፍሪካና ከእስያ፡፡ ለምን ተግባር? ስለ የልማት ጋዜጠኝነት ልንማር፡፡ እስካሁን የማልረሳውና በጣም የሚገርመኝ ጋዜጠኞቹ ደጋግመው ያቀርቡት የነበረ አንድ ስሞታ አለ፡፡ ‹‹የልማት ዘገባ መሥራት አስደሳች አይደለም›› የሚል ያቀርቡት የነበረው ዋና ምክንያታቸው ደግሞ ‹‹የልማት ፕሮግራሞች ወይም መጣጥፎች ታዳሚውን አያስቡም፣ የመነበብ፣ የመሰማት ወይም የመመልከት ፍላጎትን የሚዘጉ ናቸው፤›› የሚል ነው፡፡ የጋዜጠኝነትን ‹‹ሀሁ›› እየተማርኩ በነበርኩበት ወቅት ስለሆነ፣ ልማትን ከሚናፍቁ ታዳጊ አገሮች፣ ስለ የልማት ጋዜጠኝነት ሊማሩ መጥተው፣ የልማት ዘገባን ወይም የልማት ጋዜጠኝነትን የሚያስጠላ ቀለም ቀብተው ማቅረባቸው ግራ አጋባኝ፡፡ በዚህ ላይ በዲፕሎማ ደረጃ ልንማር የሄድነው፣ ራሱን የልማት ጋዜጠኝነትን ነው፡፡ ጥያቄው በአገራችን በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ውስጥ በሚሠሩ ጋዜጠኞች መካከል መኖሩን ለመረዳት ከህንድ ከተመለስኩ በኋላ ብዙም ጊዜ አልፈጀብኝም፡፡ እናም የልማት ጋዜጠኝነት ወይም ዘገባ ‹‹በደባሪነት›› የመከሰሱ ጉዳይ ለረጅም ጊዜ በአዕምሮዬ ሲብላላ መቆየቱ አልቀረም…
የመገናኛብዙኃንባለቤትነት
መገናኛ ብዙኃንን በተመለከተ፣ በዓለም ዙሪያ ሦስት ዓይነት የባለቤትነት ዘርፎች አሉ፡፡ የመንግሥት፣ የንግድና የማኅበረሰብ፡፡ የእኔ ትኩረት በመንግሥት ሥር ስለሚገኙ መገናኛ ብዙኃን ስለሆነ፣ በእሱው ላይ ብቻ አተኩራለሁ፡፡ የልማት ጋዜጠኝነትም በዋናነት የሚቀነቀነው በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ወይም መገናኛ ብዙኃኑን በሚያስተዳድረው መንግሥት ነው፡፡ እንደሚታወቀው፣ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በዋናነት አንድን አገር እየመራ ያለን መንግሥት ፍላጎትና አጀንዳ ለማራመድ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ወይም አገላለጹን ለስለስ እናድርገው ካልን፣ አንድን አገር እየመራ ያለው መንግሥት ያወጣቸው ልዩ ልዩ የልማት መርሐ ግብሮች ከግብ እንዲደርሱ እየተካሄደ ያለውን ርብርብ ከሙሉ ልብ ማገዝ ነው ዓላማቸው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በሥሩ የሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙኃን የሚከተሉትን ፍልስፍና በተመለከተ፣ የልማት ጋዜጠኝነት (Development Journalism) መሆኑን ውሎ አድሯል፡፡ በልማት ጋዜጠኝነት ጽንሰ ሐሳብ መሠረት መገናኛ ብዙኃን በሚሠሩበት አገር እየተካሄደ ያለው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ውስጥ ግንባር ቀደሙን ሚና መጫወት አለባቸው፡፡ ልማቱ እንዲፋጠን፣ እንዲስፋፋና የኅብረተሰቡን ኑሮ ትርጉም ባለው መንገድ እንዲቀይር ተገቢውን መረጃ በመስጠትና በማስተማር ተግተው መሥራት አለባቸው፡፡
የልማትጋዜጠኝነትመሠረታዊሐሳብናትግበራው
የልማት ጋዜጠኝነት መሠረታዊ ሐሳብ እንደሚያስረዳው፣ መገናኛ ብዙኃኑ የልማት ፕሮጀክቶች የመሠረት ድንጋይ ሲጣል ሳይሆን፣ ፕሮጀክቶቹን ለማቀድ የመንግሥት አካላትም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኅብረተሰቡን ሲያወያዩ መገናኛ ብዙኃኑ ከሥፍራው በመገኘት የውይይቱን ሒደት መዘገብ አለባቸው፡፡ ኅብረተሰቡ ስላሉበት የልማት ችግሮች በራሱ አነሳሽነት ውይይት ካደረገም እንዲሁ መዘገብ ይገባቸዋል፡፡ እንዲያውም የዚህ ዓይነቱን ተነሳሽነት ይበልጥ መደገፍ አለባቸው፡፡ በኅብረተሰቡ ቁርጠኝነት የሚጀመር የልማት ጥረት ከግብ የመድረስና ዘላቂ የመሆን ዕድሉ እጅግ ሰፊ ነውና፡፡
በዚህ መንገድ የልማት ችግሮችን ለመለየት በሚካሄዱ የውይይት መድረኮች የጀመሩትን የዘገባ ሥራ፣ በዕቅድ ውይይቱ፣ ከዚያም በተለያዩ ደረጃዎች የሚከወኑትን የልማት ፕሮጀክቱ ትግበራዎች በቅርብ በመከታተል ይዘግባሉ፡፡ በልማት ፕሮጀክቱ ምን ሊሠራ ነው የታሰበው? ያ የተለየ ፕሮጀክት እንዴትና ለምን ተመረጠ? በትግበራው ኅብረተሰቡን በምን መንገድ ያሳትፋል? የመንግሥትስ ሚና ምንድነው? የትግበራ ሒደቱ ምን ይመስላል? ያጋጠሙት ዋና ዋና ችግሮች ካሉ ምን ምን ናቸው? በልማት ፕሮጀክቱ ክወና ላይ የፈጠሩት ተፅዕኖስ ምንድነው? በምንስ መንገድ ተፈቱ? ለችግሮቹ መከሰት ተጠያቂው ማን ነው? በምን መንገድ ዕርምት ተወሰደ? ሲጠናቀቅ እነማንን ተጠቀሚ ያደርጋል? የትኛውን የኅብረተሰብ ችግር በዘላቂነት ይፈታል? ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች የሚቀስሙት ትምህርትና ተመክሮ ምንድነው?
በአጭሩ በልማት ጋዜጠኝነት ፍልስፍና ላይ ተመሥርቶ የሚሠራ መገናኛ ብዙኃን ሚና ‹‹እዚህ ይኼ ሆነ፣ እዚያ ያ ተከሰተ›› እያሉ መሮጥ አይደለም፡፡ ማለቂያ የሌለውን የስብሰባዎች ዘገባ ማዥጎድጎድ አይደለም፣ ለስብሰባዎቹ የተለያዩ ስሞችን በመለጠፍ ‹‹ሰሚናር፣ ወርክሾፕ፣ ሥልጠና፣ የጋራ መግባቢያ መድረክ፣ ወዘተ›› እያሉ የዜና ድሪቶ ማግተልተል አይደለም፡፡ ወይም የልማት ፕሮጀክቱ እስከሚመረቅ ጠብቀው አብረው ሽር ጉድ ማለት፣ አብረው ‹‹ሪቫን›› ማስቆረጥ አይደለም ሚናቸው፡፡
መገናኛ ብዙኃኑ የልማት ሥራዎቹ የሒደት አካል መሆን አለባቸው፡፡ ስኬቱን ለማብሰር፣ አሜኬላውን አብረው መጥረግ አለባቸው፣ በዘገባ ሥራቸው፡፡ የአንድ የልማት ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ ሲጣል ካጯጯሁ በኋላ፣ የትማቸውን ከርመው የፕሮጀክቱ ሥራ፣ በአግባቡም ይሁን አላግባብ የፈጀውን ጊዜ ፈጅቶ፣ የበላውን በጀት በልቶ ተጠናቆ ‹‹ሪቫን›› ሲቆረጥ (ሲመረቅ) በለመደ አፋቸው ማጯጯህ አይደለም፡፡ ይኼማ ለፕሮፓጋንዳ ተግባር የተሰለፈ (ያሰፈሰፈ) ብለው ይሻላል፡፡ መገናኛ ብዙኃን ተግባር ነው፡፡ ከዚህ ዓይነቱ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባ ሕዝቡ የሚያገኘው ፋይዳ በጣም ውስን ነው ለምን ቢሉ የእሱ ተሳትፎም ይሁን የባለቤትነት ድርሻ ያልታየበት ነውና፡፡
አብዛኛው ሕዝብ አርሶ አደር ብቻ ሳይሆን ድሃ በሆነባት አገር ኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን፣ በተለይም በመንግሥት (በፌዴራልም ሆነ በክልል) ቁጥጥር ሥር የሚገኙት፣ በአገሪቱ የሚካሄደውን የልማት ሥራ ከመደገፍ ውጭ አማራጭ ሊኖራቸው አይችልም፡፡ በድርቅ፣ እልፍ ሲልም በርሀብ በምትጠቃ አገር ኢትዮጵያ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በአገሪቱ የሚካሄደውን የልማት ሥራ ከመደገፍ ውጭ አማራጭ ሊታያቸው አይገባም፡፡ አንድ የመንግሥት ኃላፊ በአንድ መድረክ ላይ ሲናገር እንደ ሰማሁት፣ ልብሱን በመርፌ እየጠቀመ የሚለብስ ሰው ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ድህነታችን ያን ያህል የከፋ የከረፋ ነው፡፡
እናም መገናኛ ብዙኃኑ በየአደባባዩ ያለውን (የህዳሴውን ግድብ፣ የባቡር መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን፣ የታላላቅ መንገድ ግንባታዎችን፣ ወዘተ) ብቻ ሳይሆን በየጓዳውና በየጎድጓዳው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ጥረቶችን በጥልቀት መዘገብ አለባቸው፡፡ በሌላ አነጋገር የልማት ሥራ ተብሎ የሚናቅ ነገር መኖር የለበትም፡፡ ዜጎች ራሳቸውን ከድህነት ለማውጣት የሚያደርጉትን መፍጨርጨር፣ እያገኙ ያሉትን ድጋፍ፣ እያጋጠማቸው ያለውን እንቅፋትና እንቅፋቱ የሚወገድበትን መንገድ፣ እያስመዘገቡ ያሉትን ውጤት፣ ወዘተ ጠንክሮ መዘገብን ይጠይቃል፡፡ የመንግሥት ተቋማት፣ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የግል ባለሀብቶች፣ ወዘተ የሚያደርጉትን ጥረት ብቻ ሳይሆን፣ እልህ አስጨራሽ ትግልና የትግሉን ዳገትና ቁልቁለት መንገር ብቻ ሳይሆን አሳምረው ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንደ ተላጠ መንደሪን የሚያጓጓውን የትግሉን ፍሬ ብቻ ሳይሆን፣ ያን ፍሬ ገና ከችግኙ ሊያጨነግፉ ተጋርጠው የነበሩ መሰናክሎችን፣ የተከፈሉ እልህ አስጨረሽ ጥረቶችን፣ ወዘተ ልቅም አድርገው ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ይህንሲያደርጉአምስትዋናዋናፋይዳዎችይገኛሉ
አንድ፣ በተመሳሳይ የልማት ተግባር ላይ የሚሳተፉ የኅብረተሰብ ክፍሎችና የመንግሥት አካላት ተጨባጭ የሆነ ትምህርት ይቀስሙበታል፡፡ ሁለት፣ በልማት ትግሉ ውስጥ ያለፉት ይበልጥ ይበረታቱበታል፡፡ ለተጨማሪ ጥረትና ትግል ይነሳሱበታል፡፡ ሦስት፣ የመገናኛ ብዙኃኑ ዘገባም ማራኪና ተወዳጅ ይሆናል፡፡ ከማሰልቸትና እንጨት እንጨት ከማለት ይድናል፡፡ (እኒያ በህንድ አገር፣ በኒው ደልሂ ከተማ የልማት ጋዜጠኝነት ላይ አመድ በመንፋት፣የጋዜጠኝነት የወተት ጥርሴ ገና ሳይጠነክር ግራ ያጋቡኝ የሥልጠና ባልደረቦቼ ጥያቄም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መልስ ያገኛል፡፡) አራት፣ በልማት ሥራ ፕሮጀክቶች ላይ እንደ አልቀት ተጣብቀው የሕዝብን ሀብት የሚመጠምጡ ሙሰኞች እየተጋለጡ፣ ተገቢ ዋጋቸውን ያገኛሉ፡፡ ችግሩ ሥር ሳይሰድና ብዙ ኪሳራ ሳይከተል በቀላሉ መታረም ይችላል፡፡ ከዚህን መሰል የሙስና ተግባራቸው ይቆጠባሉ፡፡ (ነኝ ማለትና መሆን ለየቅል ናቸውና የልማት ጋዜጠኝነት ችግሩ እንዳይከሰት በማድረግ ወይም ችግሩ ብቅ ሲል በማድረቅ ተገቢውን ሚና መጫወት አልቻለም፡፡ ይኼው ከ50 በላይ ‹‹ከፍተኛ ኃላፊዎችንና ባለሀብቶችን በሙስና ወንጀል አስሬያለሁ›› በማለት መንግሥት እየተናረገ ነው፡፡ መንግሥት ‹‹እየተከተልኩት ነው›› የሚለው የልማት ጋዜጠኝነት በትክክል (በከፊል እንኳን) ሥራ ላይ ቢውል ኖሮ፣ ይህ ሁሉ ጥፋት ባልተከሰተ ነበር) አምስት፣ ከዚህ ትምህርት በመቅሰም ሌሎቹ በልማት ፕሮጀክት ላይ የሚለጠፉ አልቀቶች ከዚህን መሰል የሙስና ተግባራቸው ይቆጠባሉ፡፡
የልማትጋዜጠኝነትዘገባከሌላውየሚለይበት
የህንድ የሥልጠና ባልደረቦቼ (የአገሬም የመንግሥት ጋዜጠኞች) ጥያቄ ሙሉ በሙሉ መልስ ያገኝ ዘንድ፣ ተጨማሪ ነጥቦችን እናንሳ፡፡ የልማት ጋዜጠኝነት ዘገባ ይበልጥ ሳቢና ተወዳጅ እንዲሆን ለማድረግ፣ ከሌላው ዓይነት ጋዜጠኝነት የሚለይበትን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
አንደኛ፣ የልማት ጋዜጠኝነት፣ የአራጋቢት ሚና አይጫወትም፡፡ ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ መረጃዎችን እያነፈነፈ አያራግብም፡፡ ዓላማው ስሜት የሚያነሳሱ መረጃዎችን በማደን፣ ለመገናኛ ብዙኃኑ ተሰሚነትንና ገበያን መፍጠር አይደልም፡፡ ይህ የንግድ መገናኛ ብዙኃን ባህሪ ነው፡፡ ‹‹እከሌ የሚባለው የፊልም ተዋናይ ወይም የስፖርት ተጫዋች እከሌ ከምትባለው ተፋቶ፣ እከሌ ከምትባለው ጋር እየተቃበጠ ነው›› ወይም ‹‹እከሊትን አጨ›› ዓይነት ‹‹ዜና›› ተብዬ የአውሮፓ ልቅምቃሚ ወሬዎችን ማናፈስ አይደለም፡፡ ወይም ኳስ ሜዳ ገብተው ሊጫወቱ ይቅርና በአጋጠሚ እንኳን ኳስ በእግራቸው ነክተው የማያውቁትን ወጣቶች የአውሮፓ የኳስ ክለብ አፍቃሪ (አምላኪ?) ማድረግ አይደልም፡፡ ወይም የእንግሊዝ አገርን ካርታ በውል ሳያውቅ ‹‹ማንቼስተር››፣ ‹‹አርሴናል›› እያለ ልቡ ውልቅ የሚል ወጣት፣ ከዚያም አልፎ እነዚህን የኳስ ክለቦች ደግፎ፣ ከመደገፍል አልፎ አምልኮ አይነኩብኝ በማለት በፍለጥ የሚፋለጥ፣ በቦከስ የሚቧቀስ ትውልድ ማፍራት አይደለም፡፡
ሁለተኛ፣ የልማት ጋዜጠኝነት፣ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ አይደለም፡፡ በፕሮፓጋንዳ ሥልት የተቃኘ መረጃ (ዜና፣ ፕሮግራም፣ መጣጥፍ፣ ወዘተ) ሁለት መሠረታዊ ባህርያት አሉት፡፡ አንደኛ፣ ስለአንድ ጉዳይ የሚነግረን መረጃ በአብዛኛው ሙሉ አይደለም፣ መረጃ ሰጪው አካል የሚነግረን እንድንሰማ የሚፈልገውን ብቻ መርጦ ስለሆነ ከልማት አንፃር ካየነው፣ እንዳንሰማ የተደረገው መረጃ፣ ይበልጥ ማወቅ የሚገባን ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም የደበቀን ነገር ሳይኖር፣ ሁሉንም መረጃ ይነግረናል፡፡ ነገር ግን ቢያንስ የተወሰኑትና ሆኖም ቁልፍ የሆኑትን እውነታዎች ገለባብጦ ያቀርብልናል፡፡ እውነቱን ውሸት ወይም በተወሰነ መጠን ውሸት፣ ውሸቱን ደግሞ እውነት ወይም በተወሰነ መጠን እውነት አድርጎ ያቀርብልናል፣ ወይም ይግተናል፡፡
በዚህ ሒደት አንዳንድ ሰዎች ነገሩ ሊምታታባቸው ወይም ሊሳከርባቸው ይችላል፣ ችግር የለም፡፡ የፕሮፓጋንዳ አንዱ ዓላማ ይኼው ነው፡፡ ቢቻል፣ የፈነቀሉትን ድንጋይ ፈንቅሎ፣ ‹‹ድንጋዩን ዳቦ ነው›› ብሎ ጭምር የራስን አስተሳሰብ ሰዎች እንዲገዙት ማድረግ ነው፡፡ ያ ካልተሳካ፣ እንዲምታታባቸው ማድረግ፣ ለፕሮፓጋንዲስቱ በራሱ ውጤት ነው፡፡ ምንም ይሁን ምን የተምታታባቸው ሰዎች፣ አሁን በበፊቱ አቋማቸው ላይ አይደሉም፡፡ አሁን የበፊቱን ያህል የመደገፍ ወይም የመቃወም ጉልበት የላቸውም፡፡ ለፕሮፓጋንዳ ሰው ይህ በራሱ ውጤት ነው፡፡ ለልማት ዘገባ ጋዜጠኛ ግን ይኼ ክስረት ነው፡፡
ሁለተኛው የፕሮፓጋንዳ ባህሪ ድግግሞሹ ነው፡፡ እያቀረበ ያለው ጉዳይ ምንም ይሁን ምን፣ ድግድሞሹ ለከት የለውም፡፡ ‹‹ውኃ ቢወቅጡት እምቦጭ›› የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር፣ በነፕሮፓጋንዳ መንደር አይሠራም፣ ‹‹ውኃ ቢወቅጡት ውጤት›› የተባለ እስኪመስል፡፡ የምሳሌያዊ አነጋገር ጉዳይ ከተነሳ አይቀር፣ በፕሮፓጋንዲስቶች መንደር የሚሠራው ተረትና ምሳሌ፣ ‹‹ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል›› የሚለው እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ሦስተኛ፣ የመዝናኛ ድግስ ማቅረቢያ መድረኮች አይደለም፡፡ አዎ የማለዳው የመገናኛ ብዙኃን ዓላማ ‹‹ማሳወቅ፣ ማስተማርና ማዝናናት›› የሚል እንደ ነበር ለብዙዎቹ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይህ ማለት ግን አንደኛ ነገር፣ ሦስቱ ዓላማዎች ተለያይተው መከወን አለባቸው ማለት አይደለም፡፡ ሦስቱ የዓላማ ዘሮች አንድ ላይ በመሰናሰን እንደ ዝግጅቱ ግብ አንዱ ወይ ሁለቱ መጉላታቸው እንደ ተጠበቀ ሆኖ መቅረብ አለባቸው፡፡ ‹‹ማዝናናት›› የሚለው ዓላማ ለብቻው ተገንጥሎ ማለትም ማስተማርና ማሳወቅን ወዲያ ጥሎ ወይም የሁለቱን ዓላማ እጅግ አድክሞ መቅረብ አለበት ማለት አይደለም፡፡
በአጭሩ የሬድዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ በዘፈንና በድራማ ይጥለቅለቁ ማለት አይደለም፡፡ በተለይም በኅብረተሰቡ ውስጥ የማኅበራዊ ለውጥ ወይም የልማት አጋዥ ሆነው እንዲያገለግሉ በሚጠበቁ የመንግሥት ወይም የማኅበረሰብ መገናኛ ብዙኃን ከዚህን መሰሉ አሠራር መራቅ ግዳቸው ነው፡፡ ለምን ቢሉ፣ ከዚህ በላይ የሚጠበቅባቸው ዓላማ አላቸው፡፡ ሙዚቃ፣ ድራማ፣ ወዘተ ማሰራጨት ይህን ዓላማዬ ብለው የሚቋቋሙ የግል (የንግድ) ኤፍ ኤም ጣቢያዎች ተግባር ነው፡፡ ሲኒማና ቴያትር ቤቶችም ዋና ሥራቸው ይኼው ነው፡፡
ማዝናናት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ እጅግ በተዛባ መንገድ በመተርጎሙና ሥራ ላይ በመዋሉ፣ ይህ ሁኔታም ከጋዜጠኞች አልፎ የታዳሚውን አመለካከት በመቅረፁ፣ ለምሳሌ አንድ ‹‹ትምህርታዊ›› የሬድዮ ፕሮግራም ከመቅረቡ በፊት ወይም እየቀረበ እያለ በመሀል ወይም ልክ ቀርቦ እንዳበቃ ዘፈን ካልተላለፈ፣ ወደ ጣቢያው ስልክ በመደወል ቅሬታቸውን የሚያሰሙ ቀላል የማይባሉ አድማጮች ተፈጥረዋል፡፡ ‹‹ፕሮግራማችሁ ዘፈን የለውም፣ ይደብራል፣ አትደብሩን፣ ዘፈን ልቀቁብን››… ወዘተ በማለት ቅሬታ የሚያሰሙ ታዳሚዎችን ቃል መስማት የተለመደ ነገር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ለምን? ምክንያቱም ‹‹ማዝናናት›› የሚለው አንዱ የመገናኛ ብዙኃን ዓላማ፣ ለታዳሚዎች ዘፈን ወይም ሙዚቃ ማቅረብ ተደርጎ ስለተወሰደ፡፡
መጀመሪያ ነገር ‹‹ትምህርታዊ›› ፕሮግራሙ ሲዘጋጅ በአብዛኛው በአቀራረቡ በአድማጩ ላይ ጉጉት እንዲፈጥርና የአድማጩን ልቦና እንዲማርክ ተደርጎ አይዘጋጅም፡፡ ፕሮግራሞች ይህን ማድረግ ቢችሉ፣ የታዳሚውን ስሜት ጨምድደው መያዝ በቻሉ ነበር፡፡ ይህን ማድረግ ሲችሉ ደግሞ፣ አዝናኑ ማለት እሱ ነው፡፡ በመገናኛ ብዙኃን ሥራ ውስጥ ማዝናናት ማለት የመደመጥ/የመነበብ ፍላጎትንና ጉጉትን በታዳሚዎች ልብ ውስጥ መለኮስ መቻልና ያን የተለኮሰ ፍላጎት ማርካት ነው፡፡ አራት ነጥብ፡፡
ግን ምን ይሆናል፣ ማዝናናት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ እጅግ በተዛባ መንገድ በመተርጎሙና ሥራ ላይ በመዋሉ፣ ብዙዎቹ የአገራችን መገናኛ ብዙኃን የሥራ ክፍፍላቸውን ወይም መደባቸውን ሳይቀር በዚህ መንገድ ቃኝተውታል፡፡ አንዳንዶቹን ፕሮግራሞች ለምሳሌ የድራማ፣ የዘፈን ምርጫ፣ የሥነ ግጥም፣ ወዘተ ያሉበትን ‹‹የመዝናኛ ፕሮግራም›› በማለት ከፍለዋል፡፡ ይህ ክፍፍልም ወደ ጋዜጠኞቹ የሥራ መደብ በመግባት ‹‹የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጅ›› የሚል ፈጥሯል፡፡ ወደ ቀናት ድረስ በመዝለቅ ‹‹የዚህ ቀን›› ለምሳሌ የእሁድ መዝናኛ የሚል ፈሊጥ ወልዷል፡፡
ጉዳቱ ምንድነው? ከራሳቸው ከጋዜጠኞች አንፃር ብዙዎቹ ጋዜጠኞች ‹‹መዝናኛ›› የሚል ‹‹ታርጋ›› ከተሰጣቸው ፕሮግራሞች ውጭ ባይመደቡ ይመርጣሉ፡፡ ለምን?
አንደኛ፣ ሌሎቹ ፕሮግራሞች ለታዳሚው ‹‹አሰልቺ፣ ምንችኬና ደባሪ ናቸው›› የሚል እምነት አብዛኛዎቹ ጋዜጠኞች ስላላቸው፣ ታዳሚ የማይፈልገው ፕሮግራም መሥራት ጥቅሙ ምንድነው? ተደብሮ፣ መደበር ካልሆነ በስተቀር? ይህ የሥነ ልቦና ዝግጅት በራሱ በሌሎቹ ወይም ‹‹ትምህርታዊ›› በሚባሉት ፕሮግራሞች አዘገጃጀት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው፡፡ ‹‹እኔ ወጤ መቼ ይጣፍጥልኛል›› እያለች ወጥ የምትሠራ ሴት ወጧ የመጣፈጡ ነገር አጠያያቂ ነው፣ ‹‹ጣት ሊያስቆረጥም›› ይቅርና፡፡
ሁለተኛ፣ ‹‹የመዝናኛ ፕሮግራሞች›› ሥራቸው ቀላል ነው ተብሎም ይታመናል፡፡ ከማንም ጋር የማያነካኩ ከመሆናቸውም በላይ፣ ያለ ውጣ ውረድ በቀላሉ የሚገኙ ናቸው፡፡ አንድን የሙዚቃ ወይም የድራማ ባለሙያ ማነጋገር ወይም ከስቱዲዮ ቁጭ ብሎ ዘፈን እያከታተሉ መጋበዝ ጠና ሲል የስልክ መልዕክት መቀበልና ማስተላለፍ ቢኖር ነው፡፡ ከሌላው የዘገባ ተግባር አንፃር ሲታይ በጣም ቀላል ሥራ ነው፡፡ በአጭሩ ለስንፍና ይመቻል፡፡
ሦስተኛ፣ የታዳሚው ቁጥር በሽ (በብዙ ሺዎች) ነው፡፡ ጋዜጠኛው ከሚጠብቀው በላይ አድማጭ ወይም ተመልካች ያለው ፕሮግራም የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ለዚህም ተጠያቂዎቹ እኛ ባለሙያዎቹ ከመሆን አንዘልም፡፡ ማዝናናት የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ የመደመጥ ወይም የመነበብ ፍላጎትንና ጉጉትን በታዳሚዎች ልብ ውስጥ በመለኮስ እሱን ለማርካት መሥራት (መዘገብ) መሆኑ ቀርቶ፣ ቁንፅል ትርጓሜ ሰጥተን በመተግበራችን የተከሰተ ነው፡፡
የማስታወቂያ ድርጅቶችም መረባረባቸው የማይቀር ነው፡፡ እነሱ አንደዚያ ናቸው፡፡ እነሱ እንደ አቧራ ናቸው፡፡ ነፋሱን ተከትለው ነው የሚከንፉት፡፡ መዝናኛ የሚባሉ ፕሮግራሞች ነፋስ ሆነው ታዳሚውን ሲነዱት፣ ማስታወቂያ ድርጅቶች አቧራ ሆነው ይከተላሉ፡፡ ይኼ ሁኔታ ሁለት መልክ ያለው ነው፡፡ ጥቅምም፣ ጉዳትም፡፡ ጥቅሙ፣ ፕሮግራሙ የማስታወቂያ ድርጅቶችን መጎተት ስለቻለ የመገናኛ ብዙኃኑ ደጎስ ያለ ጥቅም ያገኛል፡፡ ጉዳቱ በመገናኛ ብዙኃን መልዕክት አማካይነት የአመለካከትና የአስተሳሰብ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አብዛኛው ሕዝብ ከመዝናኛ ፕሮግራሞች ጋር እንደ ሙጫ ይጣበቃል፡፡ የመዝናኛ ፕሮግራሞች እያዝናኑ አያሳውቁም ወይም አያስተምሩም ባይባልም፣ የሚሰጡት ትምህርት አንደኛ መጠኑ የሌሎቹን ‹‹ትምህርታዊ›› ተብለው የተያዙትን ያህል አይሆንም፡፡ ሁለተኛ፣ በአቀራረቡ ትምህርታዊ እንደሚባሉት ቀጥተኛና እሱኑ ዓላማ አድርጎ የሚቀርብ አይደለም፡፡ ካስተማረም፣ በተዘዘዋሪ ማስተማር ነው የሚቀናው፡፡ ይህ ደግሞ አብዛኛው ኀብረተሰብ በዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ላይ በሚገኝበት አገር ውጤታማነቱ ያን ያህል አይደለም፡፡
በሌላ በኩል ከመዝናኛ ውጭ ያሉ ፕሮግራሞች በደፈናው የማያስደስቱ፣ የማይስቡና ደባሪ ተደርገው ስለተወሰዱ፣ ታዳሚው ወይም በጥቅሉ ሕዝቡ ርቋቸዋል፡፡ ወይም እነሱን ለማዳመጥና ለመከታተል ከፊትና ከኋላቸው በሙዚቃና በዘፈን መታጀብ አለባቸው፡፡ ልደመጥ ካሉ፣ በዘፈን መሀል የሚገባ ሳንዱዊች መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ትምህርታዊ የሆኑ ፕሮግራሞች አዘጋጆች በዚህ በኩል የተዋጣላቸው ሳንዱዊች አዘጋጆች ናቸው፡፡
ይህ ግን በራሱ ተደማጭነትን ወይም ተፈላጊነትን የማረጋገጫ መንገድ ላይሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱ አጭር ነው፡፡ ሰው በተፈጥሮው መራጭ ነው፡፡ መርጦ እንደሚወድ፣ መርጦ እንደሚበላ፣ መርጦ እንደሚለብስ ሁሉ፣ የመገናኛ ብዙኃንን መረጃዎችንም ሆነ ይዘቶችን መርጦ ነው የሚወስደው፣ መርጦ ያዳምጣል፣ ይሰማልም፣ መርጦ ያያል፣ ያነባልም፡፡ እናም ምንም እንኳን የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ወይም ጋዜጠኞች ለፕሮግራማቸው ‹‹ጣዕም›› ለመስጠት በማሰብ ዘፈን ከታች፣ ዘፈን ከላይ በማድረግ የፕሮግራማቸውን ይዘት መሀል ላይ በማስቀመጥ ሳንዱዊች ቢጤ ቢሠሩም፣ ታዳሚዎች ተፈጥሯዊ የመምረጥ ክሂላቸውን በመጠቀም፣ የሳንዱዊቹን ላይና ታች ብቻ ‹‹በመመገብ›› መሀሉን እንዳልበሰለ እንቁላል የመጣላቸው ዕድል የሰፋ ነው፡፡
ዞሮ ዞሮ ግን የሳንዱዊች ሥልት በተለይም በሬድዮ ጋዜጠኞች ፕሮግራምን የማስወደድ እንኳን ባይሆንም የማስደመጥ ብቸኛው ‹‹አማራጭ›› ተደርጎ ከተወሰደ ዘመን ተቆጠረ፡፡ ለዚህም ነው፣ ‹‹ወደሚቀጥለው ፕሮግራም ከማለፋችን በፊት፣ ዘና እንድትሉ አንድ ሙዚቃ እንጋብዛችሁ›› የሚል ፈሊጥ የተለመደ መሆኑ፡፡ ፕሮግራሞችን በዘፈን ማጀብ የተለመደ የሥርጭት ሥልት ተደርጎ ከመወሰዱና አድማጩም በዚህ የአሠራር ልማድ ከመቃኘቱ (ከመቅረፁ) የተነሳ፣ ከፍ ሲል እንደ ተገለጸው በርካታ አድማጮች ወደ ሬድዮ ጣቢያዎች ስልክ በመደወል ‹‹ዛሬ ሙዚቃ አሳንሳችኋል… ቆየት ካሉ ሙዚቃዎች ጋብዙን… ዛሬ ዘመናዊ ሙዚቃ አንሷል…›› ሲሉ የሚደመጠውም ለዚህ ነው፡፡ እነዚህን መሰል አድማጮች ወይም ታዳሚዎች በተላለፈው ትምህርታዊ ፕሮግራም ላይ አስተያየት ለመስጠት ቢረባረቡ ምንኛ ጥሩ ነበር፡፡ ምንኛ የጣቢያውን ውጤት ማመላከቻ በሆነም ነበር፡፡ ሆኖም የእነሱ ዋና ጭንቀታቸው ከላይና ከታች ስለቀረበው ወይም መቅረብ ስላለበት ዳቦ እንጂ፣ ስለእንቁላሉ አይደለም፡፡ የጣቢያው ዓላማ ደግሞ ከመሀል የቀረበው እንቁላል እንዲበላለት፣ እንዲሰለቀጥለት ነው፡፡
በዚያም አለ በዚህ ‹‹ማዝናናት›› የሚለው ዓላማ በተንሻፈፈና ቁንፅል በሆነ መንገድ መተርጎሙና መተግበሩ፣ መገናኛ ብዙኃን በኅብረተሰቡ አመለካከትና አስተሳሰብ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ በመፍጠር፣ ሕዝቡ በተለያዩ መስኮች (ግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ወዘተ) እየተደረገ ያለው የልማት ጥረት አካል በማድረግ፣ ቀጥተኛ ተሳታፊና ከፍተኛ የድጋፍ ኃይል እንዲሆን ለማስቻል የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመጫወት ታላቅ እንቅፋት ፈጥሮባቸዋል፡፡ ‹‹በምን መንገድ?›› ከተባለ ተደማጭነትን በማሳጣት፡፡ (እዚህ ላይ፣ ‹‹ታዕማኒነት በማሳጣት›› አላልኩም፡፡ እሱም የራሱ የሆነ ድርሻ አለው፣ ሆኖም የራሱ የሆነ ወሰብሰብ ያለ ችግር ያለበት ስለሆነ፣ በሌላ ጊዜ ለብቻው ማየቱ ይመረጣል፣ ኢንሻ አሏህ!)
ሌላው ለአገራችን በተለይም ‹‹በልማት ጋዜጠኝነት ፍልስፍና እንመራለን›› ለሚሉት ማለትም ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ፕሮግራሞች ተደማጭነት ወይም በአጭሩ ተፈላጊነት መቀነስ ትልቅ ሚና ያለው ተግዳሮት የሚቀርቡት ፕሮግራሞች ሊተነበዩ የሚችሉ (Predictable) የመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡ እዚህም ላይ ዘፈን እንዱ ‹‹ባለድርሻ አካል›› ነው፡፡ ስለትምህርት የሚወያይ ፕሮግራም የሚቀርብ ከሆነ፣ የፕሮግራሙ አዘጋጅ አስቀድሞ ‹‹ተማር ልጄ›› የሚል ዘፈን ይጋብዛል፡፡
የዚህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች ፕሮግራሞቹን ተተንባይ በማድረግ፣ አጓጊ እንዳይሆኑ ያደርጓቸዋል፡፡ ምን እንደሚከተል ያወቀ ታዳሚ ልብና ጆሮውን አይሰጥም ወይም በግማሽ ልብ ነው የሚያዳምጥና የሚከታተል፡፡ ሁለተኛው ችግር አቀራረቡን አሰልቺ ያደርገዋል፡፡ አላስፈላጊ ድግግሜ በማምጣት ይህ አጠቃቀም ልክ ከማሳጣቱ የተነሳ፣ አንዳንድ ጋዜጠኞች ከሚቀርበው ይዘት ጋር የሚገጥም ዘፈን ሲያጡ፣ ከፕሮግራሙ ውስጥ ያለ አንድ ቃል ወይም ሐረግ የያዘን ዘፈን ይጠቀማሉ፡፡ ለምሳሌ እነሱ ያዘጋጁት ፕሮግራም ስለጤና አጠባበቅ የሚዳስስ ፕሮግራም ቢሆን፣ ስለጤና የሚያወሳ ዘፈን ካጡ፣ ‹‹ያላንተ ጤናም የለኝ›› እያለች አንዲት ዘፋኝ ያንጎራጎረችውን የፍቅር ዘፈን ሊያስደምጡን ይችላሉ፡፡ ለምን? ከዘፈኑ ውስጥ ‹‹ጤና›› የምትል ቃል ስላለች ብቻ! ይኼውላችሁ የሚዲያዎቻችን የዘፈን አጠቃቀም እንዲህ ቅጥ አጥቷል፡፡ እና እነዚህን ዓይነት መገናኛ ብዙኃን ‹‹ደንባራ›› ቢባሉ ‹‹በዛባቸው›› ይባል ይሆን?
ቅጥያጣውየአየርጊዜሽያጭ
ልክ ያጣው የአየር ጊዜ ሽያጭም፣ ሌላው የልማት ጋዜጠኝነት ሥጋት ወይም እንቅፋት ነው፡፡ የመንግሥት ሬድዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች (ኢቢሲም ሆነ የየክልሎቹ) የአየር ጊዜ ሽያጫቸው ገደቡ እስከምን ድረስ ነው? ለጤና ጥበቃ፣ ለግብርና፣ ለገቢዎች፣ ለፖሊስ፣ ለትራንስፖርት… ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ወይም ቢሮዎች ዛሬ የአየር ጊዜ ሸጠዋል፡፡ የመንግሥት ተቋም ናቸውና ሰጥተል ቢባልም ችግር የለም፡፡ የመንግሥት ተቋማቱ ለአየር ጊዜው ደጎስ ያለም ሆነ አነስ ያለ ገንዘብ ቢከፍሉ ስለእሱ የሚያጨቃጭቀን ነገር የለም፣ የገንዘብ ዝውውሩ ከቀኝ ኪስ ወደ ግራ ዓይነት ነውና ከመንግሥት፣ ወደ መንግሥት፡፡
ዋናውና አሳሳቢው ጥያቄ እነዚህ ተቋማት ያንን የወሰዱትን የአየር ጊዜ ‹‹ለምን ተግባር ያውሉታል?›› የሚለው ነው፡፡ ለምሳሌ የፌዴራሉ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ወይም አንድ የክልል ጤና ቢሮ፣ የሬድዮ ወይም የቴሌቪዥ የአየር ጊዜን በመጠቀም ኅብረተሰቡን ስለተለያዩ ጤናን የሚመለከቱ ጉዳዮች ትምህርት ቢሰጥ ‹‹ሥራው ባለቤቱን አገኘ›› ማለት ይኼ ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱን ሥራ ጋዜጠኛው ከሚሠራው፣ የሕክምና ባለሙያው ቢሠራው ይመረጣል፡፡ ጉዳዩን ከሥር ከመሠረቱ ያውቀዋልና፡፡ አንዳንድ ከጋዜጠኝነት ጋር የሚገናኙ የቴክኒክ ጉዳዮችን በሬድዮ/ቴለቴቪዥን ትምህርት ለሚሰጡት የሕክምና ባለሙያዎች አጫጫር ሥልጠና በመስጠት አቅማቸውን መገንባትና ክፍቱተን መሙላት ይቻላል፡፡ መንግሥታዊ ተቋማቱ (ግብርና፣ ገቢዎች፣ ፖሊስ…) የአየር ጊዜውን በዚህ መንገድ የሚጠቀሙበት ከሆነ፣ ማንኛውም ተቋም መውሰዱ መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ልማትን የማገዙን ተግባር ስለሚያቀላጥፈው እሰዬ የሚያስብል ነው፡፡
ሆኖም ነገር የሚመጣው፣ ማለትም ከልማት የጋዜጠኝንት መርሕ ጋር መላተም የሚመጣው መንግሥታዊ ተቋማቱ የወሰዱትን ወይም የገዙትን (በተባባሪነት የሚያሩትን) የአየር ጊዜ የሥራ ዕቅዳቸውና አፈጻጸማቸው ሪፖርት ማቅረቢያ መድረክ ማድረግ ሲጀምሩ ነው፡፡ ይኼን ይኼን ሠራን፣ እንዲህ እንዲህ ፈጸምን›› በማለት ስለሠሩት የልማት ተግባር ማሳወቂያ መሣሪያ አድርገው መጠቀም የለባቸውም፡፡ ለምን?
አንደኛ፣ አንድ ተቋም ስለራሱ የሥራ ክንውን ሚዛናዊ ሆኖ ይዘግባል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ‹‹ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ›› ነውና የሠሩትን አጋነው ማቅረባቸው አይቀርም፡፡ ሳያጋንኑ ቢነግሩን እንኳን፣ ያጎደሉትንና ያበላሹትን ደፍረው አይናገሩም፡፡ ‹‹እንናገራለን›› ቢሉም እንኳን፣ ሁሉንም ፍርጥርጥ አድርገው አይናገሩም፡፡ ሕዝብ ደግሞ ሁሉንም የማወቅ መብት አለው፡፡
ሁለት፣ ጣቢያውን በከፍተኛ ደረጃ ለገፅታ ግንባታ ያውሉታል፡፡ እሳት የላሱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የተቋማቸውን ስምና ዝና ለመትከል ይጠቀሙበታል፡፡ የልማት ጋዜጠኝነት ዓላማ ግን እሱ አይደለም፡፡ ሕዝቦች ከድህነትና ኋላ ቀርነት እንዲላቀቁ ያለባቸውን የመረጃና የእውቀት ድህነት ማስገድ ነው፡፡ (የገፅታ ግንባታቸውን በሌሎች የኮሙዩኒኬሽን መንገዶች፣ በማስታወቂያ፣ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት፣ ወዘተ ነው ማከናወን ያለባቸው)
ሦስት፣ ተጠያቂነት ይጠፋል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር የገነገነው ተጠያቂነት በመጥፋቱ ነው፡፡ ተጠያቂነት ሕይወት ከማንሰራራት አልፎ፣ ወደ ባህልነት ሊቀየር የሚችለው የጣቢያዎቹን ማይኮች ጋዜጠኞች ሲይዟቸው ነው፡፡ በየተቋሙ ሥር ያሉ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ሲቆጣጠሯቸው አይደለም፣ አይገባቸውምም፡፡ (ወይም ለተባባሪ መሥሪያ ቤት የተሰጠ በማለት፣ የዚያ መሥሪያ ቤት የኮሙዩኒኬሽን ክፍል በቀደደው ቦይና ባሰመረው መስመር ላይ የጋዜጠኛው ዘገባ እንዲፈስ ማድረግ አይደለም፡፡) አንዳንድ የአየር ጊዜ የገዙ የመንግሥት ተቋማት፣ የአየር ጊዜ በገዙት ሬድዮ ወይም ቴሌቪዥን ጣቢያ የዜና እወጃ ወቅት የተነገረባቸውን የሕዝብ ቅሬታ በአየር ጊዜያቸው የማስተባበያ ፕሮግራም እሰከመሥራት መድረሳቸው ይነገራል፡፡
አራት፣ ታዳሚው መገናኛ ብዙኃኑን ይርቃል፡፡ ስኬታቸውን በመሰቃቀል፣ የአንድ ወገን ዘገባ በማቅረብና ከዚያም አልፈው ደግመው ደጋግመው በማስጮህ ታዳሚውን ያሰለቹታል፣ ያደነቁሩታል፡፡ አደንቋሪ ይጮሀል እንጂ ሰሚ የለውም፡፡ እስካሁንም ይኼ አልሆነም ለማለት አይቻልም፡፡
አምስት፣ ጋዜጠኞቹ ምን ይሥሩ? ሁሉም ወይም ብዙዎቹ የመንግሥት ተቋማት የአየር ጊዜ ከወሰዱ ወይም ከገዙና ስለራሳቸው፣ ራሳቸው እየዘገቡ የሚያሰራጩ ከሆነ፣ ጋዜጠኞች ለምን ያስፈልጋሉ?
ሙያንለባለሙያአለመተው
የዜናዘገባከጋዜጠኞችእጅወጣ?
ከላይ የተጠቀሰው ዓይነት ተግባር ወደ ዜና ዘገባም አልገባም ለማለት ያስቸግራል፡፡ ኢቢሲ፣ በዜና እወጃው ወቅት ‹‹የዚህ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ›› ወይም ‹‹የዚህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የኮሙዩኒኬሽን… ዜናውን አድርሶናል›› በማለት ዜና ማሰራጨት ከጀመረ እጅግ ሰነባብቷል፡፡ ‹‹ዜናውን አድርሶናል›› ማለት ምን ማለት ነው? ለአንድ መገናኛ ብዙኃን ዜና መሥራት ያለበት ማን ነው? መልሱ አጭር ነው፡፡ አንድ ራሱ፣ ሁለት የዜና አገልግሎት ድርጅት፡፡ (ከሌላ የመገናኛ ብዙኃን ሊወስድ ቢችልም፣ ያ ዋና ምንጭ ተድርጎ አይወሰድም፡፡ ቢወስድም ዞሮ ዞሮ የዜናው ሥራ ባለቤትነት ከጋዜጠኞች እጅ አይወጣም፡፡)
ዜና፣ በተለይም በብዙኃን መገናኛ የሚተላለፍ ዜና ተፈጥሯዊ ባለቤቶች ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ ከእነሱ ውጭ ባለባለሙያ አይሠራም፣ ቢሠራም የሙያውን ሥነ ምግባር የተከተለ አይደለም፡፡ በተጨማሪም ታዕማኒነት አይኖረውም፡፡ ኢቢሲ ሰማይ እስከሚነካ፣ ለሕዝብ ሳይሆን ለመንግሥት ወግኖ ቢሠራ፣ ዜና በሚዘግበው ጋዜጠኛ ኅሊና ውስጥ ግን ሕዝብን የማገልገል ሙያዊ ግዴታውና ሥነ ምግባሩ ይጮህበታል፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ፣ የመረጃ ምንጭ ከመሆን አልፎ፣ ያለሙያው ገብቶ ዜና ሲዘግብ በኅሊናው ውስጥ የሚጮህበት የሙያ ግዴታውና ሥነ ምግባሩ መሥሪያ ቤቱን በሚገባ ስለማስተዋወቁ (ስለማንቆላጰሱ) ነው፡፡ ስለሆነም ልማታዊ ዘገባውን ቀርቶ፣ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ተብሎ የሚሠራውን ዜና እንኳን ሳይቀር ጋዜጠኛው ቢሠራው ይመረጣል፡፡ ለማኅበራዊና ልማታዊ ዘገባውማ የግድ ነው፡፡
የሕዝብ ግንኙነት (የኮሙዩኒኬሽን) ባለሙያዎች ዋና ተግባራቸው የማይነጥፍ የመረጃ ምንጭ መሆን ነው፡፡ ለብዙኃን መገናኛ ዜና መሥራት አይደለም፡፡ ጋዜጠኛው የት ሄዶ? ጋዜጠኛው መረጃ ሲጠይቃቸው መልካም አፈጻጸም ካልሆነች ውጣ ውረድ የሚያበዙ፣ ስብሰባ የሚበዛባቸው ጥቂቶች እንዳልሆኑ ይታወቃል፡፡ መልካም አፈጻጸም ስትኖር ደግሞ የዘግቡልን ኡኡታ የሚያሰሙ እንዳሉ በብዙኃን መገናኛው ሠፈር የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ መልካም አስተዳደር ቁልፍ ችግር ለመሆን በበቃበት ሒደት ውስጥ፣ የዚህ ዓይነቱ የተዛነፈ የሚዲያ አጠቃቀም አንዱ ባለድርሻ አካል እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ‹‹አልነበረም›› የሚል ካለ፣ እንዲህ ትልቅ ችግር ነው ብሎ መንግሥት ዕውቅና ሰጥቶት እያለ፣ ምነው በውል ሳይዘገብ መቅረቱ?
የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተጠሪነት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሳይሆን፣ ለተወካዮች ምክር ቤት መሆኑም አንድ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት፣ የመንግሥት ተቋማትና ኃላፊዎቻቸው በገቡት ቃል መሠረት የሕዝብን አደራ እየተወጡ ለመሆናቸው አንዱ የሚያረጋግጥበት መንገድ ነው፣ የመገናኛ ብዙኃኑ ዘገባ፡፡ እናም እዚህ ጋር መደናበሩ አለ፡፡ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ መገናኛ ብዙኃኖቻችን እየተደናበሩ ነው፣ በዚያውም የልማት ጋዜጠኝነትን እያጠለሹት፡፡ ( ሳምንት ይቀጥላል)
ከአዘጋጁ፡-ጸሐፊው የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው jemalmohammed99@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡
