Quantcast
Channel: ዓለማየሁ ጉጀ
Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

የፀረ ሙስና ትግሉን ለማስተባበር ከመንግሥት እውነተኛ የሆነ በቂ ድጋፍ ሊገኝ ይገባል

$
0
0

በይስማ እውነቱ

ሙስና በኢትዮጵያ ለዘመናት እንደ ባህል ጭምር እየተወሰደ የኖረ ነው፡፡ የሙስና ተቀባይና ሰጪም እንደ መብትና ግዴታ አድርጎ የሚጠቀሙበት ዘርፍም ነበር፡፡ ከደርግ መንግሥት በፊት ‘ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል’ እየተባለ በተለይም የመንግሥት ሹመኞችና የጎበዝ አለቃ የሆኑ ሰዎች በጠራራ ፀሐይ ጉቦ ይሰጡና ይቀበሉ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ጉዳይ ለማስመፈጸም፣ ሹመት ለማግኘት፣ የተጣሉትን ሰው ለመበቀል፣ አንድ ጉዳይ ከአንዱ ተነጥቆ ለሌላ እንዲሰጥ ጉቦ ይሰጥ ነበር፡፡ ጉቦ የሚሰጠው በጥሬ ገንዘብ ወይም በንብረት ነበር፡፡ ለምሳሌ ከጥሬ ገንዘብ በተጨማሪ ሠንጋ በሬ፣ በግ፣ መሬት፣ ቤት ወይም ፋብሪካ መስጠት፣ አንዳንዴ ሴት ልጅ በመዳርም ጭምር እንደ ጉቦ ይወሰድ ነበር፡፡ የደርግ መንግሥት ሲመጣ የዕዝ ኢኮኖሚ ሥርዓት ሲያራምድ ስለነበር በግሉ ዘርፍ እዚህ ግባ የሚባል የግል ባለሀብት አልነበረም፡፡ ሁሉም ነገር የመንግሥት ስለነበር፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ሹመኞች አንዳንድ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ጉቦ ይጠይቁና ይቀበሉ ነበር፡፡ ጉቦ ብቻም አይደለም የሚወስዱት፡፡ ከጉቦ ውጪ በዘመድ፣ በሃይማኖት፣ በብሔር የማዳለት፣ የመንግሥት ንብረት የመስረቅ፣ የማጭበርበር ከደርግ መንግሥት በፊትም ሆነ በኋላ የተለመደ ነበር፡፡ ጉቦ መስጠትና መቀበል ቢኖርም የጉቦ ገንዘብ መጠኑ ግን በጣም ትንሽ ነበር፡፡ የባለሀብት የካፒታል መጠንም ውስን ስለነበር፡፡

ስለ ደርግ ሥርዓት ዛሬ ላይ የሥራ ውጤታማነትን ብዙ ባላውቀውም የሠርቶ አደር ቁጥጥር ኮሚቴ የተዋቀረው ጉቦ የሚወስዱትን ሰዎች ለመቆጣጠር ነበር ሲባል ሰምቼለሁ፡፡ በጥቁርና በነጭ ካሜራ ቪዲዮ የተቀረፀ ጉቦ ‘ጉቦ…’ የሚባል ዘፈንም በቴሌቪዥን አይ ነበር፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የደርግን ሥርዓት ገርስሶ ወደ ሥልጣን የመጣ ሰሞን እነዚህን የሕዝብ ነቀርሳ የሆኑ ጉዳዮች ላይ አቋሙ በጣም ጠንካራ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ እንዲያውም ወደ ግንቦትና ሰኔ ወር 1983 ዓ.ም. አካባቢ ስርቆት የፈጸሙትን ሰዎች አስፋልት ላይ ይረሽን ነበር፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የዕዝ ኢኮኖሚ ሥርዓትን በማፍረስ ወደ ካፒታሊስት ሥርዓት ሲቀይር አንዳንድ የመንግሥት ተቋማት ወደ ግል ይዞታ ይዞሩ ነበር፡፡ ያኔ ነው እንግዲህ የመንግሥት ኃላፊዎች የጉቦ የገንዘብ መጠንን በማሳደግ መጠየቅና መቀበል የጀመሩት፡፡ ብዙዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ማረሚያ ቤት ገብተው እንደነበር እስታውሳለሁ፡፡ በተለይም አቅም ያላቸው የግል ባለሀብቶች ብቅ ብቅ ማለት ሲጀምሩ ዘመናዊ ሆቴሎች፣ መዝናዎች፣ የግል ሆስፒታሎች፣ ሪዞርቶች፣ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች ሲገነቡ፣ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች አገር ውስጥ መግባት ሲጀመሩ በቃ የመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞች ይህን እያዩ በመጓጓት ድርሻችንን እንውሰድ በሚል ዕሳቤ ወደ ሙስና ጭልጥ ብለው የገቡ ይመስለኛል፡፡ ዘመናዊ አልባሳትም ወደ አገሪቱ መግባት ጀመረ፡፡ የመንግሥት በጀትም ከአሥር ቢሊዮን በታች የነበረው ወደ 100 ቀጥሎም ወደ 200 ቢሊዮን አሁን ደግሞ ወደ 300 ቢሊዮኖች እያደገ ነው፡፡ ዕቃ ከአገር ውስጥ ወደ ውጭ በብዛት መላክ ወይም ከውጭ ወደ አገር ውስጥ በብዛት ማስገባት ተጧጧፈ፡፡ ተጨቁነው የኖሩት የግል ባለሀብቶች ብዙ ገንዘብ መያዝ ጀመሩ፡፡ የዶለር ዋጋ ምንዛሪ ከ2.07 ወደ 21 እና በላይ አደገ፡፡  

በዚህም ሀብት የሚፈልጉ የመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞች ልባቸውን ያማለለውንና ለሕዝብ ከመኖር ይልቅ ለራሳቸው መኖርን መርህ አድርገው ተያያዙት፡፡ ኃላፊነት መርሳት ጀመሩ፡፡ በሀብት ላይ ሀብት የሚፈልግ ባለሀብት ለመንግሥት ሹመኞች ጉቦ መስጠት የጀመረው በቂ ገንዘብ ማግኘት ሲጀምር ነው፡፡  አንዳንዱ ባለሀብት በብድር ባገኘው 5000 ብር የጀመረውን የንግድ እንቅስቃሴ አሥር ዓመት ባልሞላበት ጊዜ ውስጥ አሥር ሚሊዮን አደረሰው፡፡ ይህ ዕድገት ሜርኩሪ ወይም አልማዝ ሸጦ ሳይሆን በሰጥቶ መቀበል መርህ ከመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞች የተቸረው ስጦታ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ እዚህ ላይ በልፋታቸው ያደጉትን ባለሀብቶች ይህ ጉዳይ አይመለከትም፡፡ ብዙ ልማታዊ ባለሀብት አለና፡፡ ገንዘብ የሚፈልግና ሕዝብን በመርሳት ለራሱ መኖር የጀመረው የመንግሥት ሠራተኞም ሆነ ሹመኛ የተሰጠውን ኃላፊነት ተጠቅሞ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለአንዱ በማዳላት ሌለውን በመጉዳት ጥቅም ማግኘትን ሙያ እያደረገ መጣ፡፡ የመንግሥትን ጥቅም በማስቀረት ቢያንስ ሲሶውን ወደ ኪሱ ማስገባት ጀመረ፡፡ አመቺ መንገድ ሲያገኝ በግልም ሆነ ከሌላ ጋር በመሆን የመንግሥት ሀብትና ንብረት መስረቅ ጀመረ፡፡ በማጭበርበር ገንዘብ ማግኘት እንደ ጀብዱና እንደ መብት እየወሰደ መጣ፡፡ ሌሎች ምቹና አዋጪ ነው ያላቸውን ዘዴዎችን በሙሉ በመጠቀም ገንዘብና ሀብት አገኘ፡፡

ከፍተኛ ገንዘብ ያገኘው የመንግሥት ሹመኛ ባገኘው ገንዘብ ንብረት አፈራ፣ ዛሬ ላይ የመንግሥት ሹመኛ ሆኖ ከሚከፈለው ከ3,500 እስከ 5,000 ብር ባልሞላ ገንዘብ ዘመናዊ ቤት ገነባ፣ በዶለር ማከራየት ወይም ከ30 እስከ 50 ሺሕ ብር በላይ በማከራየት መንግሥት በሹመቱ በሰጠው ቤት ውስጥ በነፃ መኖር ሥራዬ ብሎ ተያየዘ፡፡  ልጆቹን አገር ውስጥ ወይም ውጭ አገር ጥሩ ትምህርት ቤት ያስተምራል፡፡ ዘመናዊ ሆቴልና ሪዞርት ሚስቱንና ልጆችን ይዞ እንደ ልቡ ይዝናናል፡፡ ሲያስፈልግ ውጭ አገር ሄዶ ይዝናናል፡፡ ልማታዊ ያልሆነው ባለሀብት የአየር መንገድ ትኬት እየገዛለትና ወጪውን እየቻለለት ይዝናናል፡፡ በድህነት ጊዜ ያገባትን ሚስቱን ትቶ በጣም ውብና ዘመናዊ ሴት ያገባል ወይም ቤት ተከራይቶ ያስቀምጣል (ጎተራ አካባቢ ያለውን ኮንዶሚኒየም ይመለከቷል) ወይም ይወሽማል፡፡ ያኔ ሳይማር ያስተመረውን ኅብረተሰብ ይረሳል፣ ለኅብረሰብ መኖር ይረሳና ለራሱና ለቤተሰቡ ብቻ መኖር ይጀምራል፡፡ ቅንጦት ሕይወትን ስለለመደ የመረጠውን ሕዝብን አያስታውስም፡፡ በሐዝብ ስም ይምላል፣ ነገር ግን ጭንቅላቱ በጥጋብና በትዕቢት ስለተወጠረ ሕዝብን ይረሳል፡፡ ሕዝብ የት እንዳለም አያውቅም፣ ሁሉም እንደ እሱ ደልቶት የሚኖር ይመስለዋል፡፡ የሙሰኛ ሹመኛ የመጨረሻ እውነታውም ይህ ነው፡፡

በሰጠው አገልግሎት ዝቅተኛ ጥቅም የሚያገኘው የመንግሥት ሠራተኛም ቢሆን ዘመናዊ ሞባይል ይገዛል፡፡ ሳምሰንግ፣ አፕል፣ ዘመናዊ ልብስ ገዝቶ ይለብሳል፡፡ በተለይም ወጣት ከሆነ መኪና ያስፈልጋዋል፣ ከሴት ጓደኛው ጋር ዘመናዊ ሆቴልና  የመዝናኛ ቦታ ላይ መታየትንና ጊዜ ማሰለፍ ይፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ ወጣት ስለሆነ መዝናናት ይፈልጋል፡፡ ሙሰኛ የመንግሥት ሠራተኞች የቤት ሽሮ መብላት አይፈልጉም፡፡ ምሳ ቋጥረው ቢሮ አይመጡም፡፡ ከተማ ውስጥ እንደ አንበሳ የሚበላው ጥሬ ሥጋ እንደ አሸን ተደራሽ ከሆነው ቢራ ጋር ማጣጣም ይፈልጋል፡፡ የቤት ኪራይ በአሁኑ ጊዜ ውድ ስለሆነ ቢያንስ የተሻለ ኮንዶሚኒየም ቤትም ቢሆን ተከራይቶ መኖር ይፈልጋል፡፡ ብዙዎቹበቂ ገንዘብ ካለቸው ኮንዶሚኒየም ይገዛሉ፡፡ ካልሆነም የገበሬ መሬት ይገዛሉ፣ ቤት ይሠራሉ፣ ሕገወጥ ተብሎ ካልፈረሰ ቤት አለኝ ለማለት ይፈልጋሉ፡፡ ይህ በዕውቀታቸውና በክህሎታቸው በአንስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው ሀብታም ለመሆን የሚጥሩ መልካም ዜጋ የሆኑ ወጣቶችንና ሌሎችን አይመለከትም፡፡ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው ለጥቅም ብለው ሕዝብን የሚያጉላሉ ወጣት ተቀጣሪ ሠራተኞች ብቻ ለማለት ነው፡፡ ይህንን ስል ወጣት ያልሆኑት ሙስና አይሠሩም ማለቴ አይደለም፣ ይሠራሉ፡፡ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ በዕድሜ ከፍ ያሉና ሙስና የሚሠሩት ሰዎች በብዛት ሹመኞች ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ሠራተኞችና ሹመኞች የተጣለባቸውን የሕዝብ አደራ ወደኋላ በመተውና በመርሳት ወደ ገንዘብ ፍለጋ በሚሰጡት አገልግሎት ላይ ኅብረተሰቡን የሚያጉላሉት፡፡ አንድ ጊዜ ክፍለ ከተማ የመጀመሪያ ቀን ጃኬት ለብሼ አገልግሎት ፍለጋ ሄድኩ፡፡ የሚያናግረኝን አጥቼ ተመለስኩ፡፡ በሌላ ቀን ስብሰባ ነበረኝና ሙሉ ልብስ ለብሼ አጋጣሚውን ተጠቅሜ ባለፈው ጊዜ የሚያነግረኝ ወደ አጣሁበት ቢሮ ስሄድ እንደ ንብ ነበር እየወራሩ ምን እንደምፈልግ የተጠየቅኩት፡፡ ላለው አገልግሎት አሰጣጥ ፈጣን ነው፡፡ በገንዘቡ አገልግሎቱን ያፈጥናል፡፡ የመንግሥት ሹመኞች የመንግሥትና የሕዝብ ሀብትና ንብረት ይዘርፋሉ፡፡ ለዘረፋውም ስትራቴጂና ሥልት ቀይሰው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የሚገርመው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር፣ የመልካም አስተዳደር ማስፋን በሚሉ ጉዳዮች ግንባር ቀደም ሆነው መፈክር የሚያስሙት እነሱ መሆናቸው ነው፡፡ በአጭር ቃል ኪራይ ሰብሳቢነትን ደፍቀን፣ የሁለተኛውን ዕድገትና ትራንስፎሜሽን በመሳካት፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን የኢትዮጵያን ህዳሴ ዕውን እናደርጋለን ሲሉ እነሱን የሚቀድም የለም፡፡ የጆሮ ታምቡር እስከሚበጠስ ኪራይ ሰብሳቢነት የመልካም አስተዳደር ችግር ነው እያሉ ያስተጋባሉ፣ ይዘምራሉ፡፡ ይጮሃሉ፣ ይጮሃሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ማንም አይችላቸውም፣ በጣም የተካኑ ናቸው፡፡  ሙስና የማይሠሩ ሰዎች ደግሞ አድማጭ ናቸው፡፡ የተናጋሪዎችን ሌብነት ስለሚያውቁ ከንፈር ይነክሳሉ፡፡ ይገረማሉ፡፡ ኢሕአዴግ ራሱ ሌባ ነው ይላሉ፣ ያማሉ፡፡ ዕርግማናቸው ግን አይደርስላቸውም፡፡

በአንድ መንግሥት ተቋማት ውስጥ ቢበዛ 20 ሠራተኞችና ሹመኞች ጥቅም ሊያስገኝ በሚችል ቦታ ላይ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ እነዚህ 20 ሠራተኞችና ሹመኞች ከ100 በላይ ባለሀብቶች ጋር ግንኙነት ይኖራቸዋል፡፡ ባለሀብቱ በተለይም በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚፈልግ ከሆነ ለመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞች በማንኪያ ጥቅም ሰጥቶ በአካፋ የሚገመት የራሱን ጥቅም ያጋብሳል፡፡ ሁሌም በተለይም ‘ኢንተርፕሩነር’ የሚሆኑ ሰዎች ሀብታሞች እንደሚሆኑ ዕሙን ነው፡፡ ስለሆነም ለመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞች ጉቦ ሲሰጡ ወይም ሲያጭበረብሩ ወይም ሲሠሩ የኢንተርፕሩነር ዕውቀታቸውን በሚገባ ይጠቀማሉ፡፡ ለዋና ሥራቸው ብቻ ሳይሆን ለሙስና ሥራም የኢንተርፕሩነር ክህሎት ያላቸው ስለሆኑ፣ የመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞችን በቀላሉ በማማለል ሙስና ውስጥ ያስገባቸዋል፡፡ ሙስና የሚሠሩ የመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞችም የኢንተርፕሩነር ክህሎት እንዳለባቸው አንርሳ፡፡ ሌሎች ጥቅም ሊያስገኝ የማይችል ሥራ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞችና ሹመኞች ለሙስና ባይተዋር ስለሆኑ ጠቋሚ ይሆኑ እንደሆነ እንጂ የሚያገኙት ጥቅም አይኖራቸውም፡፡ እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት ጉዳይ በአንድ ወቅት ጥቅም ሊገኝ በሚችል ቦታ ላይ ተሰማርተው ሲሠሩ የነበሩ ሠራተኞችና ሹመኞች የሌሎችን የሙስና ወንጀል ለመጠቆም በጣም የተካኑ ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በቀጥታም ሆነ በተዛዋዋሪ ጥቅም ፈልገው ወይም አንዱ ሲጎዳ ዕርካታ ማግኘት ፈልገው ጥቆማ የሚያቀርቡ ሠራተኛ ያልሆኑ ሰዎችም እንዳሉ ሳንዘነጋ ማለቴ ነው፡፡

እንግዲህ የኢሕአዴግ መንግሥት ከላይ የተገለጹት የሙስና ወንጀሎች እየተንሰራፉ ከመጡ በአገር ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ከወዲሁ በመገንዘብ ነበር፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽንን በግንቦት ወር 2003 ዓ.ም. በሕግ ያዋቀረው፡፡ ይህ ተቋም ሦስት ዋና ዋና ዓላማዎች ነበሩት፡፡ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ትምህርቶችን ማስተማር፣ በመንግሥት ተቋማት ሙስናና ብልሹ አሠራር መከላከል፣ የሙስና ወንጀል ጥቆማዎችን መቀበል፣ መመርመር፣ መክሰስ፣ ማስቀጣትና የተመዘበረ ሀብት ማስመለስ ሦስቱ ዓላማዎች ነበሩ፡፡ ይህ ተቋም ከተቋቋመ አሥራ አምስት ዓመታት አልፈውታል፡፡ በአሥራ አምስተኛው ዓመት ላይ ግን በአዋጅ ቁጥር 943/2008 የምርመራና የዓቃቤ ሕግ ሥራ ከኮሚሽኑ ተቀንሶ ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ለፌዴራል ፖሊስ ተሰጠ፡፡ በዓለም ላይ የተለያዩ የፀረ ሙስና ኮሚሽን አደረጃጀቶች ሲኖሩ፣ አንድም አገር የሙስና ወንጀል ምርመራ ሥራን በፖሊስ ሥር አላደራጀም፡፡ በዓለም ላይ በፀረ ሙስና ሥራ ተጠቃሽ የሆኑ እንደ ሆንግ ኮንግ ያሉት አገሮች የዓቃቤ ሕግ ሥራ ብቻ በፍትሕ ሚኒስቴር ወይም በጠቅላይ ዓቃቤ ሥር አደራጅተው የምርመራ ሥራ የሚከናወነው ግን በፀረ ሙስና ኮሚሽን ነው፡፡ የሙስና ምርመራ ሥራ ነፃና ገለልተኛ በሆነ ሁኔታ በማደራጀት ለአገሪቱ መሪ ያደረጉ አገሮችም አሉ፡፡ ቀደም ሲል እንደ ኮሚሽኑ ዓይነት የምርመራና ዓቃቤ ሕግ ሥራ አንድ ላይ አደራጅተው የፀረ ሙስና ትግል ላይ ውጤታማ የሆኑ አገሮችም በብዛት አሉ፡፡

በአገራችን በአንድ ወቅት የቅጽበታዊ እንቅስቃሴ የምርመራ ሥራን በፌዴራል ፖሊስ ሥር እንዲደራጅ መደረጉ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ እዚህ ላይ ሙሰኛ የሆኑ አንዳንድ አዋቂ ነን የሚሉ ሰዎች ዓላማቸው ፀረ ሙስናን ማዳከም ስለሆነ፣ የማይሆነውንና ከዕውነታ ውጪ የሆኑ ነገሮችን ሲቀባጥሩ አነባለሁ፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች በአንድ ወቅት በሙስና ወንጀል የተከሰሱና የተቀጡ እንደሆኑ እገምታለሁ፣ ወይም ዘመዶቻቸው የሙስና ተጠያቂ የሆነባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ የሆነ ሆኖ በሆንግ ኮንግ ፀረ ሙስና ኮሚሽን እ.ኤ.አ በ1974 የተቋቋመው በፖሊስ ውስጥ ሙስና በጣም እየተስፋፋ ስለመጣ ነበር፡፡ መንግሥታችን የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ሙስናን መከላከልና መዋጋት የሞት ሽረት  ጉዳይ እንደሆነ በግልጽ ባስቀመጠበት ሁኔታ፣ የምርመራ ሥራን ወደ ፌዴራል ፖሊስ መውሰዱ የአገሪቱን የሙስና ወንጀል ችግር ይቀረፋል ብሎ አስቦ ከሆነ በጣም ተሰስቷል፡፡ የፖሊስ ሥራ በአብዛኛው እስከታችኛው አደረጃጀት ድረስ በኅብረተሰብ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ፣ እንደ እኛ ባለ አገር ውስጥ ፍትሐዊ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ይሰጣል ተብሎ ታስቦ ከሆነ ራስን እንደማታለል ይቆጠራል፡፡ ምናልበት ለመንግሥት ቅርበት ባለው የፖሊስ አደረጃጀት ውስጥ ፍትሐዊ አገልግሎት ሊሰጥ ይችል ይሆናል፡፡

አሁን ደግሞ የኮሚሽኑ የሥራ እንቅስቃሴ ውጤታማ ነበር ወይ? ኮሚሽኑ ሦስቱን ዓላማዎች ለማሳካት ችሎ ነበር ወይ? የሚለውን በዝርዝር ማየት ያስፈልጋል፡፡ ኮሚሽኑ ተግባራቱን የሚያከናውነው በመንግሥት በተመደበ በጀት ነው፡፡ በኮሚሽኑ በሥነ ምግባርና በፀረ ሙስና ሙያ ላይ ስፔሻለይዝድ ያደረገ ባለሙያ የለውም፡፡ ሚዲያን በነፃ እንዲጠቀም አልተፈቀደለትም፡፡ የሙስና ወንጀል ጥቆማ ከጠቋሚዎች በመቀበል እንጂ የራሱ የሆነ ‘ኢንተለጀንስና ሰርቪላንስ’ የለውም፡፡ ቀደም ሲል በዝርዝር በተገለጸው ሁኔታ የመንግሥት ሹመኞች ተቋሙን አይደግፉም፣ እንዲኖር አይፈልጉም፡፡ በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚፈልጉ ባለሀብቶች ከመንግሥት ሹመኞች በስተጀርባ በመሆን የኮሚሽኑን የማስፈጸም አቅም ይፈታተናሉ፡፡ መንግሥት ሀብትና ንብረት ለመዝረፍ ወይም ከሚሰጡት አገልግሎቶች ጥቅም የሚፈልጉ የመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞች የስም ማጥፋት ዘመቻ ያደርጉበታል፡፡ በጣም ያስወራሉ፣ ያወራሉ፡፡ በዚያ ላይ በሙስና ወንጀል የተከሰሰ ሰው ያላቸው የኅብረተሰብ አባላት የኮሚሽኑ እውነተኛ ጠላቶች ናቸው፡፡ ቢችሉ ኖሮ ሕንፃውን ያቀጥሉ ነበር፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ላይ ጭፍን ጥላቻ ያላቸው ተቃዋሚዎችና ሌሎች ሀብታሞች ሲሆኑ ወይም በአንድ ወቅት ደሃ የነበሩ የመንግሥት ሹመኞች የኑሮ መሻሻልን ስለሚያዩ፣ ኮሚሽኑ ኢሕአዴግ ሥራ የሚለውን የሚሠራና ሰውን ያላግባብ የሚያጠቃ ተቋም ነው ስለሚሉ ልፋቱን ጥላሸት ይቀቡታል፡፡ የኮሚሽኑን ሠራተኞችም የኅብረተሰቡ አካል ስለሆኑ በሙሰኞች መደለላቸው አይቀርም፣ በደላሎች ይጠፈራሉ፡፡ በዚህና በመሳሰሉት ኮሚሽኑ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ቢኖሩም አመርቂ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ቢያንስ ሙስና የአገሪቱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር መሆኑን በኅብረተሰቡ አዕምሮ ውስጥ በጥልቀት እንዲገባ አድርጓል፡፡

ኮሚሽኑ በመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሰደረው ተፅዕኖም የሚናቅ አልነበረም፡፡ ኮሚሽኑ ተቋማትን በተደጋጋሚ በመጎበኘቱ ብቻ ሙስና በአገሪቱ ቢያንስ በይፋ ሰው በሚያየው ሁኔታ በግልጽ አይሠራም፡፡ እንደ ሌሎች አገሮች በጠራራ ፀሐይ ኅብረተሰቡ ስለሙስና አይጠይቅም፡፡ የነበረው ችግር ግን አንዳንድ ሕገወጦች ሕገወጥ ጉዳዮችን ለማስፈጸም የመንግሥት ሠራተኞችንና ሹመኞችን የሙስና አካል ስለሚያደርጉ፣ የመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞችን የግል ተጠቃሚነት መሠረት ያደረጉ አገልግሎት ስለሚሰጡ፣ እንዲሁም በሕጋዊ መንገድ ጉዳይ የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙ የኅብረተሰብ አካላት ለሙስና ባይተዋር ተመልካች በመሆናቸው ኮሚሽኑ ምንም አልሠራም ስለሚሉ ኮሚሽኑን እጀ ሰበራ አድርጎታል፡፡

ኮሚሽኑ በኅብረተሰቡ ዘንድ በብዛት የሚታወቀው በሙስና ወንጀል ምርመራና በዓቃቤ ሕግ ሥራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሙስና ምርመራ ሥራ የሚከናወነው ከኅብረተሰቡ በመጣ ጥቆማ ነው፡፡ ጥቆማ አቅራቢዎች ደግሞ ራሳቸው ብዙ ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ ያቀረቡት ጥቆማ በአንድ ሌሊት ተመርምሮ ሰዎች ማረሚያ ቤት እንዲገቡ ተደርገው እነሱ ያሰቡት እንዲሳካላቸው በጣም ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ላይ በተለይም ባለሀብት ወይም የመንግሥት ሹመኛ ወይም የሹመኛ ዘመድ ታስሮ ከሆነ፣ በየፊናው ለማስለቀቅ የሚደረገው ጥረት  የፀረ ሙስና ትግሉን የሚፈታተን ነው፡፡ በዚህ ላይ የደላሎች ጉዳይ በጣም ከባድና ለማጥፋትም የሚቻል አይደለም፡፡ ደላሎች ደግሞ የመንግሥት ሹመኞችና ባለሀብቶች መሆናቸው ጉዳዩን በጣም ያወሳስበዋል፡፡ አንድ ባለሀብት ወይም ሹመኛ ከታሰረ የኮሚሽኑ መርማሪና ዓቃቤ ሕግ ባለሙያዎችና ዳኞች  ተደጋጋሚ የደላሎች ጉብኝት አለባቸው፡፡ የሙስና ተጠርጣሪዎችን ለማስፈታት የመንግሥት ሹመኞች ተፅዕኖ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የደላሎች ሚና በጣም በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ የሄዱበት መንገድ ካልተሳካላቸው ለእነሱኮሚሽኑ ሌባ ነው፡፡ ስለሆነም ይህም የኮሚሽኑን ልፋት እጀ ሰበራ አድርጎታል፡፡ ስለሆነም መንግሥት ይህን የኅብረተሰብ ነቀርሳ የሆነ የሙስና ችግሮችን ለመቀነስ እንዲቻል የኮሚሽኑን የማስፈጸም አቅም በበቂ ሁኔታ መገንባት ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ የፀረ ሙስና ትግሉን ለማጎልበት የሚከተሉት ትኩረት ተሰጥተው ሊተገበሩ ይገባል፡፡

  1. ኮሚሽኑ ለሚያከናውነው ሥራ በቂ በጀት፣ የሰው ኃይልና ቁሳቁስ መመደብ ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ በፀረ ሙስና ትግሉ ውጤታማ የሆኑ ተቋማትን ተሞክሮ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ሠራተኞች በሥነ ምግባር ታንፀው የፀረ ሙስና ትግሉን በኃላፊነት ስሜት እንዲያከናወኑ፣ ኮሚሽኑም በሙያው ልምድ ያካበቱ ሠራተኞች ለማቆየት እንዲችል የኮሚሽኑ ሠራተኞች ከፍተኛ የደመወዝ ተከፋይ ማድረግ ይገባል፡፡
  2. የመንግሥት ሹመኞች፣ ባለሀብቶችና ደላሎች በኮሚሽኑ ሥራ ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድሩ ገለልተኛና ነፃ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ የፈረጠመ የማስፈጸም አቅም ያለው ተቋም ሊሆን በሚችል ሁኔታ መደራጀት አለበት፡፡ መንግሥትም ያለበትን ችግር በቅርበት በመከታተል ድጋፉን መስጠት ይኖርበታል፡፡
  3. ያለወቅታዊ ጥናትና መረጃ በግለሰቦች የክፋት ፍላጎትና ጥንስስ ለፌዴራል ፖሊስ የተሰጠው የሙስና ወንጀል ምርመራ ሥራ ተመልሶ በኮሚሽኑ ሥር እንዲደራጅና ኮሚሽኑ የራሱ የሆነ ኢንተለጀንስና ሰርቪላንስ በማደራጀት እንዲንቀሳቀስ ቢደረግ መልካም ነው፡፡ የዓቃቤ ሕግ ሥራ በሌሎች አገሮችም ለብቻው ተደራጅቶ ስለሚንቀሳቀስ ተቋሙ ብቃትና ክህሎት ባለው የባለቤትነት ስሜት በተላበሰ ቁርጠኛ አመራር ሊመራ ይገባል፡፡
  4. ኮሚሽኑ በተለይም ሕፃናትና ወጣቶች በሥነ ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ የሚያስችሉ ሥራዎችን እንዲሠራ ነፃ የመንግሥት ሚዲያ ይፈቅድለት፡፡ ኮሚሽኑም የተሰጠውን የመንግሥት ነፃ ሚዲያ ተጠቅሞ የኅብረተሰቡን የሥነ ምግባር ደረጃ የሚያሳድጉ ትምህርቶችን እንዲያስተምር ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር ይደረግ፡፡
  5. ኮሚሽኑ የአደረጀጀት ስፋቱን በማሳደግ በተለያዩ ቦታዎች ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን እንዲከፍትና በተለይም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ አስተዳደር ተደራሽነቱን ማሳደግ ይኖርበታል፡፡
  6. ኮሚሽኑ ከላይ የተቀመጡት ተፈጽመውለት የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ሥራዎችን በተጠናከረ እንዲያከናውን ብቃትና ክህሎት ያለው አመራር በየደረጃ ስለሚያስፈልገው፣ መንግሥት የአሁኑን ነባራዊ ሁኔታ በመፈተሽ ጠንካራ፣ ተነሳሽነቱ ያለው፣ በዕውቀት፣ በክህሎትና በቁርጠኝነት ሊመራ የሚችል አመራር ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡
  7. የኮሚሽኑ የፀረ ሙስና ትግል እንቅስቃሴም ዕውቀትና ክህሎት፣ ነፃና ገለልተኛ አዕምሮ ባለቸው አካላት በግልጽና በመረጃ እየተደገፈ የሱፐርቪዥን፣ የክትትልና ድጋፍ ሥራ እንዲያከናውን ሊደረግ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይታደጋል!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው bekeleayele2008@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

Trending Articles