Quantcast
Channel: ዓለማየሁ ጉጀ
Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

የፖለቲከኞችና የምሁራን ሐሳቦች ማጠቃለያ ገጾችና የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ

$
0
0

ሪፖርተር ጋዜጣን በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ የመልካም አስተዳደር መስፈን ውስጥም ሆነ ሚዛናዊ ዘገባን ለማቅረብ ከሚጥሩ የአገራችን የኅትመት ሚዲያዎች በቀዳሚነት እጠቅሰዋለሁ፡፡ ለዚህ አባባል መነሻ የሚሆነው ጋዜጣው በርዕሰ አንቀጹ ሳይቀር ለተከታታይ ሳምንታት፣ ወራትና ዓመታት ምን ላይ አተኩሮ ሲወተውት ነበር የሚለውን ዘወር ብሎ በጥናት መመርመር፣ በተለይ ለፖሊሲ አውጭውና ለገዥው ፓርቲ ሰዎች መጠቆም ይኖርብኛል፡፡

ዞሮ ዞሮ የጽሑፌ መነሻ ሪፖርተርን ማወደስ ወይም ለገዥው ፓርቲ ‹‹ሲነግሩህ ለምን አትሰማም?›› የሚል ወቀሳ ማድረስ ባለመሆኑ ይህን እዚሁ ላይ ልግታና ወደ ጉዳዬ ልግባ፡፡ አሁን ኢትዮጵያችን ምቾት የሚሰጥ ሁኔታ ላይ እንዳልሆነች ጠንቋይ መሆን አያስፈልግም፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚያቀርባቸው እንግዶችም ሆኑ ጽሑፎችም ይህንኑ ተረድተው ለመፍትሔው የሚጮኹ ናቸው፡፡

በአገሪቱ በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በተለያየ ምክንያት የተነሳ ‹‹የሕዝብ ጥያቄ›› ቀስ በቀስ አቅጣጫውን እየሳተ ነው፡፡ መንግሥት በጽንፈኛ ተቃዋሚዎችና የውጭ ኃይሎች አጀንዳ ‹‹የሕዝቡ ጥያቄ እየተጠለፈ ነው›› ቢልም፣ የተደራጀና ጠንካራ የፖለቲካ ኃይል የማይመራው የሕዝብ ቅሬታ በማኅበራዊ ድረ ገጾችና ውጭ ባሉ መገናኛ ብዙኃን ይቀጣጠል ይዟል፡፡

በዚህም ምክንያት በተጠቀሱት ክልሎች በተለይም አንዳንድ ዞኖች ከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየታየ ነው፡፡ ገበያ የለም፣ የንግድና የአገልግሎት መስኩ ተዳክሟል፣ ዜጎች በግጭት ሥጋትም ይባል በተለያዩ ምክንያቶች በሰላም ወጥተው መግባት አልቻሉም፡፡ በአንዳንድ የገጠር ወረዳዎችም ቀደም ሲል በኦሮሚያ እንደታየው የመንግሥት መዋቅሩን የማፈራረስና አመራሩን የማሳደድ የለየለት ሕገወጥነት ታይቷል፡፡ ይህ ድርጊት ለጊዜው ጋብ ያለ ቢመስልም ሥጋቱ እንዳረበበ ነው፡፡

የእነዚህ ክስተቶች ድምር ውጤት በአገሪቱ ንግድና ኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝምም ሆነ በአገር ገጽታ ግንባታው ላይ ያለ ጥርጥር የጎላ ጥላ አጥልቷል፡፡ የገዥው ፓርቲና የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከመደበኛ ሥራቸው ላይ እግራቸውን ነቅለው፣ ‹‹ዳግም ተሃድሶ የ15 ዓመታት የአገሪቷ ጉዞ ስኬቶችና ፈተናዎች››ን ዋነኛ አጀንዳ አድርገው መምከር ይዘዋል፡፡ ይህ ምክክር ይበልጥ ሕዝቡንና ገለልተኛውን ወገን (ምሁሩንና ሰላማዊውን ፖለቲከኛ) ካሳተፈ የአገር ግንባታው አካል ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ በር ዘግቶ የሚደረግ ማሻሻያ ግን በቀላሉ ሕዝቡን ያረካል ለማለት ያዳግታል፡፡

በዚህ ወሳኝ የሕዝቡ የለውጥ ፍላጎት ከፍ ባለበትና መንግሥትም ‹‹ለዳግም ተሃድሶ›› በተዘጋጀበት ወቅት ላይ ነው እኔም ይህን ብዕር ለማንሳት የወደድኩት፡፡ ይኸውም ቢያንስ ባለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የሚባሉ፣ ድምፃቸውን ያሰሙና ያመኑበትን ሐሳብ ያራመዱ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና የአገር ተቆርቋሪ ሰዎችን ሐሳቦች ለመመርመር የተገደድኩት፡፡ በየመጻሕፍቱ  የማጠቃለያ ገጾች ላይ የተሰነዘሩ ጠቃሚ የሚመስሉኝን አገራዊ ምክሮች እንወያይባቸው ዘንድ ወደዚህ ለማምጣት የወደድኩት፡፡

መጻሕፍቱ ግን ታስቦባቸው የተደራጁ ሳይሆኑ በአጋጣሚ እጅ የገቡ መሆናቸውን መግለጽ ይኖርብኛል፡፡ እንደ ነፃ አስተያየት ግን በየመጻሐፍቱ ውስጥ የተጠቀሱ ሚዛናዊና አገራዊ ምክረ ሐሳቦች ለመንግሥትና ለሕዝብ ጥቅም አንድ አስተዋጽኦ ያበረክቱ እንደሆን እንጂ የሚጎዱ አይደሉም፡፡ ከ25 ዓመታት በኋላ ‹‹25ኛው ተሃድሶ›› ለሚለው ኢሕአዴግም ዓይኑን ሊገልጡለት የሚችሉ ይመስለኛል፡፡

ኢትዮጵያዊነትና የብሔር ብሔረሰብ መብቶች እንደማይጣጣሉ አድርጎ መገንዘብና መተግበር

ይህን ሐሳብ ከእነርዕሱ የተጠቀሙበት የ‹‹ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ›› ደራሲና ፖለቲከኛ አቶ ገብሩ አሥራት በገጽ 384 ላይ ነው፡፡ ዶ/ር ዘውዱ ውብ እንግዳ ‹‹የፌዴራላዊ መንግሥት አመጣጥ››፣ አቶ ኃይሉ ሻውል ‹‹ሕይወቴና የፖለቲካ ዕርምጃዬ››፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ‹‹ዳንዲ. . .›› እና መሰል ትንታኔዎች በአንድም በሌላም የተንፀባረቁ ሐሳቦች ናቸው፡፡

አቶ ገብሩ፣ ‹‹ኢሕአዴግ ከሥልጣን ቢወገድም በአገራችን ዘላቂ ዕድገትና መረጋጋት እንዳይሰፍን ምክንያት የሆነው የጠላትነት ፖለቲካ ካልጠፋ፣ ልማትና መረጋጋት ይገኛል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው፤›› ብለው ከተዛባው ታሪካዊ ፉክክር በመውጣት፣ የጋራ እሴትና የጋራ አመለካከት የገነቡ ብሔር ብሔረሰቦች ከታጠሩበት ክልልና ብሔር ወጥተው በዴሞክራሲያዊነት ላይ የተገነባ ኢትዮጵያዊነትን በጋራ መፍጠር ይኖርባቸዋል ሲሉ አትተዋል፡፡

ለዚህም ከሕዝቡ በላይ በአገራዊ ስሜት የተደራጁ ኅብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች መፈጠርና መጠናከር አለባቸው፡፡ ምሁራን ከብሔር ባርኔጣ እየወጡ በአገራዊ ጃንጥላ ውስጥ ታቅፈው መምከር ይገባቸዋል፡፡ የሲቪክ ማኅበራትን ጨምሮ እነዚህ ኃይሎች በኢትዮጵያዊነትና በብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበር መካከል ያለውን አንድነትና ልዩነት በሚገባ አጢነው መጓዝ ይኖርባቸዋል ነው የሚሉት፡፡

በዚህ ሐሳብ ላይ የጠቃቀስኳቸው ሰዎችም ሆኑ ብዙዎቹ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ የሚከታተሉ ወገኖች ከኢሕአዴግ ዓይነቱ ‹‹ዘውጌ ጠመድ›› (የብሔር ልዩነት ላይ ይበልጥ የሚያተኩር ፖለቲካ) ከደርግ ዓይነት ጽንፈኛ አሃዳዊነት (አንድ ጸሐፊ በመውደድ ብዛት ልጇን ከልክ በላይ አቅፋ እንደገደለች እናት ብለውታል) ውጪ የሆነ አስተሳሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡ በፌዴራል ሥርዓት ማንነቱን፣ ታሪኩን፣ ቋንቋውንና ባህሉን እንዲያውቅና እንዲያዳብር መደረግ አለበት፡፡ በአገሩ ደግሞ በፍትሐዊና በእኩልነት መርህ እየተጠቀመና እየተሳተፈ አንድነቱን ማጠናከር አለበት፣ ይገባልም፡፡

ይህ ወሳኝና አማራጭ መንገድ የግድ የሚፈለግበት ጊዜ መቃረቡን አሁን መሬት ላይ ያለው ሀቅ ቁልጭ አድርጎ እያሳየ ነው፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት አገሪቱ ወድቃ እየተነሳች ለውጥ አስመዝግባለች፡፡ በየትኛውም የአገሪቱ ጫፍ ቢሆን ደርግ ሲሄድ በነበሩበት ይዞታ ላይ ያሉ ዜጎችና አካባቢዎች እንደሌሉ አፍ ሞልቶ መናገር ይቻላል፡፡ ገጽታችንም መሻሻል ጀምሯል፡፡ ይኼም ሆኖ ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ የትግራይ ሕዝብ ብቸኛ ተጠቃሚ መሆኑ እየተቀነቀነ ነው፡፡

ሰፊ የሚባሉት የአማራና የኦሮሚያ ክልል ሕዝቦች ደግሞ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥቅማቸው እንደቀረ፣ አናሳ የሚባሉ ሌሎች ብሔረሰቦችም (በተለይ ደቡብ) በሌሎች የክልሉ ብዙኃን ተገፍተናል የሚል ቅሬታ ውስጥ ናቸው፡፡ እነዚህን ሁለት ጫፍ የነኩ ዝንባሌዎች እያረመ ሊሄድ የሚችለው ደግሞ ዴሞክራሲያዊና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የአገሪቱ ሕዝቦች የየራሳቸው ቋንቋ ቢኖራቸውም የጋራ መግባቢያ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የየራሳቸው ባንዲራ ቢኖራቸውም ከፍ ብሎ የሚሰቀልና ሁሉም የተግባቡበት የአንድነት መገለጫ ሰንደቅ ሊኖር ይገባል፡፡ የየራሳቸው ታሪክ ቢኖራቸውም ሁሉን ያቀፈ አገራዊ ታሪክ፣ አገራዊ ትምህርት፣ አገራዊ የጋራ የኢኮኖሚ ፕሮጀክት (እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ)፣ አገራዊ ሠራዊት፣ አገራዊ አየር መንገድ፣ አገራዊ የእግር ኳስ ቡድንና አገራዊ ፓርቲ. . . ሊኖር ግድ ነው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲን ነገር ካነሳን ኢሕአዴግ እንኳን ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ መሆን አልቻለም፡፡ የብሔራዊ ድርጅቶች የጋራ ግንባር ብቻ ነው፡፡ እንደ ቅንጅት፣ ደቡብ ኅብረት፣ መድረክና አንድነት . . . ያሉትም ተወልደው በእግራቸው ሳይቆሙ የመከኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ በዚህች አገር 80 የብሔር ፓርቲዎች ተበጣጥሰው በመንደር ልጅነት እየተሰበሰቡ ፈቃድ ከሚያወጡ፣ ተባብረውና በአንድ አገራዊ ራዕይ ሥር ተሠልፈው ሦስትና አራት ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ቢሆኑ ምንኛ በታደልን ነበር? (እዚህ ላይ የህንድን ተሞክሮ እንመልከት ከ1,500 በላይ ማንነት ያላቸው ብሔሮች ቢኖሯትም፣ ፖለቲካው የሚወሰነው ግን በሁለትና በሦስት አገራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ነው፡፡ በቃ!

እውነተኛና የማያከራክር የፌዴራል ሥርዓትን መተግበር

በመሠረቱ በኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት መከተል ላይ የሚነሱ ልዩነቶች እየጠበቡ ነው የመጡት፡፡ አሁን አሁን ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነውን ‹‹የቀድሞ ባንዲራ›› በመምዘዝ የአሃዳዊነት አቀንቃኝ የሚመስሉ ወገኖች ቢታዩም (እነሱ ዓላማቸው በግልጽ ገና አልተነገረም)፣ አብዛኞቹ የፖለቲካ ኃይሎች ከአሃዳዊነት እሳቤ መላቀቃቸውን በምርጫ ክርክሮች፣ በፓርቲዎች ማኒፌስቶዎችና በልዩ ልዩ መግለጫዎች ሲገልጹ ተደምጧል፡፡

ከዚያ ይልቅ አሁን ክርክሩ በተግባር ላይ በዋለው ፌዴራሊዝም ቋንቋ (ብሔር) ተኮር መሆን ላይ ሆኗል፡፡ እርግጥ ይህ ሙግትና ከሕገ መንግሥቱ መፅደቅ አንስቶ ‹‹አገራዊ ስሜትን ያጠፋል፣ ሕዝብን ከሕዝብ ያለያያል፣ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላ ሄዶ ለመሥራት እንቅፋት ይፈጥራል. . .›› ተብሎ ሲነቀፍ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡  (የዶ/ር ዘውዱ ውብ እንግዳን ‹‹የፌዴራላዊ መንግሥት ታሪካዊ አመጣጥና የመንግሥት ግንባታ ችግሮችና ኢትዮጵያን›› ከ15 ዓመታት በፊት የቀረበ መጽሐፍ ይመለከቷል)

ብዙዎቹ ድርሳናት እንደሚስማሙበት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የተሞከረው እ.ኤ.አ. ከ1952 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ የኤርትራ ፌዴራላዊ ግንኙነት ነበር፡፡ እሱም ከሸፈ፡፡ ደርግም ብዙ ዋጋ ከተከፈለ በኋላ በዚያው በኤርትራ መዘዝ የራስ ገዝና የልዩ ራስ ገዝ (Regional Autonomus and Special Regional Autonomus) ሥርዓት ለመተግበር ሞክሯል፡፡ ‹‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ›› ሆነ እንጂ፡፡ የኢሕአዴግ የፌዴራል አወቃቀር ላይ የጋራ አስተዳደር (Shared Rule) እና የራስ አስተዳደር (Self Rule) መርሆች በተሟላ መንገድ እየተተገበሩ አለመሆናቸው ይወሳል፡፡

ከዚህም በላይ ግን አሁን ያለው ፌዴራሊዝም ብሔርና ቋንቋ ተኮር በመሆኑ፣ የብሔር ብሔረሰቦችን ታሪካዊና መልከዓ ምድራዊ ግንኙነትን እንደዘነጋ ይተቻል፡፡ ለዚህ ሐሳብ አቶ ገብሩ (በገጽ 387) በስፋት ያተቱት ዘገባ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ‹‹በአገሪቱ ከአፋር፣ ከሶማሌና ከኦሮሚያ በስተቀር ሌሎች አካባቢዎች በርካታ ብሔረሰቦችን ይዘው ነው፤›› ይሉና በትግራይ ከትግሪኛ በተጨማሪ የኢሮብና የኩናማ ብሔረሰቦች ያውም ልዩ ዞን ወይም አደረጃጀት ሳይኖራቸው፣ የአማራ ክልልም ከአማርኛ ተናጋሪው በተጨማሪ የአገው፣ የኦሮሞና የአርጎባ ብሔረሰቦችን በልዩ ዞን ደረጃ ለይቶ ይዟል፡፡ ቤንሻጉል አምስት፣ ጋምቤላ ከአራት በላይ፣ ሐረሪ ቢያንስ ሦስት ብሔረሰቦችን፣ ደቡብ ክልል ደግሞ ከ52 በላይ ብሔሮችን ይዘዋል ይላሉ፡፡

በዚህ መነሻ ብዙዎቹን ጸሐፍት የሚያስማማው በክልሎች ብዙኃን ከሚባለው ማኅበረሰብ ውጪ ያሉ ጎሳዎችና ሕዝቦች የመደመጥ ዕድላቸው ይቀጭጫል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ታሪካዊ ትስስርና ጂኦግራፊያዊ ቅርበት በመዘንጋቱ አፍንጫው ላይ ያለውን መዋቅርት ትቶ ሌላ ጫፍ ለመሄድ ይዳረጋል፡፡ ከሁሉ በላይ የክልሎች ነፃነት ተጨፍልቆ ፌዴራላዊ ጠቅላይነት ሲጎላ፣ በዴሞክራሲያዊና በማዕከላዊነት ሥልጣንና ትዕዛዝ ሲንቆረቆር ብሎም የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ሲደፈቅ ሥርዓቱ ‹‹ሥውር አሃዳዊ›› መሆኑ አይቀርም ነው የሚሉት፡፡

የብሔር ተኮር ፌዴራላዚም ጣጣው ዜጎች ‹‹ማንነታቸውን›› ብቻ የሀብትና የሥልጣን ማግኛ አድርገው መውሰድ ሲጀምሩና አሁን እየታየ እንዳለው ዓይነት አመለካከት እየጎላ ሲመጣ ነው፡፡ ለምሳሌ በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል የውዝግብ ምንጭ ሆኖ የታየው የወልቃይትና የጠለምት አካባቢ በትግራይ ክልል ውስጥ ከገባ 25 ዓመታት ሆኖታል፡፡ ከዚያ በፊትም በተለያዩ ታሪካዊ ክስተቶች አንዴ ወዲህ ሌላ ጊዜ ወዲያ ሆኗል፡፡ ያለ ጥርጥርም በአካባቢው የተወለደና የተሳሰረ ‹‹ወልቃይትነቴን›› የገነባ ማኅበረሰብም ተፈጥሯል፡፡ ግን ዛሬ ዘሩንና አንጓውን እየቆጠረ መሳሳብ ፈለገ፡፡

‹‹ለምን?›› ሲባል በትግራይ መከለሌ ልማት አላመጣልኝም፣ ሥልጣን አላስገኘልኝም፣ ውክልና በተሟላ መንገድ አላገኘሁም. . . እያለ ፌዴራሊዝሙ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ሰበዞችን መዘዘ፡፡ በተመሳሳይ በደቡብ ክልል በኮንሶ በክልሉ የተደራጀውን ዞንና የመንግሥት አወቃቀርን እስከመበተን ደርሶ በጎሳው ሥሪት መተዳደር የጀመረው ‹‹የማንነት ጥያቄ አልተመለሰም›› በሚል ነው፡፡ አሁን አሁን አንዱ የሥርዓቱ ችግር መስሎና ሆኖ ጎልቶ በመረጃ እየተደገፈ የሚቀርበው ለዓመታት የተገፋው በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉልና በሶማሌ የኖረ የመሀል አገር ሕዝብ ጉዳይ ነው፡፡

ይህ ሕዝብ በመላው አገሪቱ ቢያንስ ከ100 ዓመታት ለበለጠ ጊዜ ሠርቶ ከመኖር ባሻገር ተዋልዶና ተጋብቶ ‹‹ባለአገር›› እንዳልነበረ በሥርዓቱ የመደራጀት፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት ዕጦት ደርሶበት ለችግር ዳርጎታል የሚሉ ነበሩ፡፡ በተለይ ሕዝቡ ከቀደሙ ገዥዎች አንፃር የሚያስደምረው ‹‹ነፍጠኛ›› የሚል ስያሜ ሲለጠፍበት ከፍተኛ መከራና እንግልትም ሊደርስበት ችሏል፡፡ ይህ ያልተገባ አዝማሚያ ዛሬ ደግሞ ተገልብጦ በመላ አገሪቱ በላባቸው ሠርተውና ለፍተው ለዘመናት የኖሩ የሌሎች ክልሎች ተወላጆች ላይ ሲነጣጠር ታይቷል፡፡

ከእነዚህ እውነታዎች አንፃር የፌዴራል ሥርዓቱ በጠባብ ብሔርተኛውም ሆነ በጠቅላይነት በሚታማው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ ሳይናወጥ የሁሉንም ሕዝቦች የግልና የቡድን መብቶች የሚያስከብር መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ከብሔርና ከቋንቋ ባሻገር መልከዓ ምድር፣ ሥነ ልቦናና ታሪካዊ ቁርኝት ብሎም የማንነት ባህል መስተጋብርን መሠረት ማድረግ ሊኖርበት ይችላል፡፡ ይህን መፈተሽ የዚህ ትውልድ ቀዳሚ ድርሻ መሆን አለበት፡፡

እውነተኛ ዴሞክራሲና ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ፍትሕን ማስፈን

ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የሚከተለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ የእውነተኛ ዴሞክራሲ መልክ የለውም፡፡ ‹‹አስመሳይና ለዘብተኛ አምባገነን ነው፤›› የሚሉ ምሁራንና ፖለቲከኞች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ የተነሳሁት የመጽሐፍ ገጾችን በመምዘዝ ነውና ከዶ/ር መረራ፣ ዶ/ር ነጋሶ፣ ፕ/ሮ መስፍን፣ (የክደት ቁልቁለት)፣ አቶ ገብሩ አሥራት፣ አቶ ስዬ አብረሃ፣ አቶ ልደቱ አያሌውና አቶ ኃይሉ ሻውል አንስቶ በፖለቲካ ምክንያት ከጋዜጠኝነታቸው ወደ ተንታኝነት የተቀየሩት ‹‹ትንንሾቹ›› ጸሐፍት ድረስ የኢሕአዴግ ዴሞክራሲ ምኅዳረ ጠባብ፣ ባለ ልጓምና በገደብ የተሰናከለ መሆኑን ደግመው ደጋግመው ሰልቀውታል፡፡ ጽፈውታል፡፡

መንግሥትም ቢሆን አልፎ አልፎ ‹‹ዴሞክራሲያችን ገና ለገና ታዳጊ ነው›› በሚል ለመፅናናት ከመሞከር ውጪ አካሄዱን እንደ ጤነኝነት ቆጥሮ ቁጭ አለ፡፡ ሕዝቡም አውቆ እንዳላወቀ፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱም ሆነ ፍትሐዊ የማኅበረ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንደተሸራረፈ እያወቀ ‹‹ዝም አለ››፡፡ ይህ አካሄድ ግን ሄዶ ሄዶ የሚጋብዘው ነውጥ፣ ግጭትና ቀውስን እንጂ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግልን አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ነፃ ሐሳብ፣ መደራጀት፣ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግን የቀመሰ ትውልድ በዝቷል፡፡ ዓለም የዘረጋው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልቅ የመረጃ ግብይት ውስጥ ከቶታል፡፡ በነፃነት የመምረጥ ሙከራን አጣጥሟል፡፡ ይህ ግን መቀጠል አልቻለም፡፡ በማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ፍትሕ ረገድ ቀስ በቀስ ከድህነት እየወጣ ያለ አገር ቢሆንም በነፍስ ወከፍ ገቢ፣ በሥራ ዕድልና በድህነት ቅነሳ ረገድ ገና የችግር ማጥ ውስጥ ያለው ሕዝብ ቁጥር ትንሽ አይደለም፡፡ አሁንም በከተሞች ድህነት፣ ልመናና ሴተኛ አዳሪነት፣ በገጠርም የተባባሰ ስደትና ፍልሰት አለ፡፡ ከሁሉ በላይ በአጭር ጊዜ እሴት ሳይፈጥር የሚበለፅግ ሀብታምና ከመሬት ያልተነሳ ደሃ እየተራራቀ የመጡበት ሁኔታ ጎልቶ እየታየ ነው፡፡ የኑሮ ውድነት የሚያናውዘው፣ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ያስመረረውም ዜጋ ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ጉዳይ ሲነሳ ተወቃሹ መንግሥት ብቻ እንዳልሆነ ግን እርግጥ ነው፡፡ በቀዳሚነት በምን ቸገረኝነትና በግዴለሽነት የተጥለቀለቀው ‹‹የተማረው ክፍል›› ኃላፊነቱን አልተወጣም ሊባል ይችላል፡፡ በአገር ሽማግሌነትና በሃይማኖት መሪነት የሚታወቁ ‹‹አንጋፋ ሰዎች›› አድርባይነትና ከሕዝቡ ስሜት የተነጠሉ መሆናቸውም ሌላው ችግር ነው፡፡ ዋነኞቹ ተወቃሾች ግን ሰላምንና ዴሞክራሲን መርህ አድርገው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች  (አባላትና መሪዎቻቸው) ናቸው፡፡

ማንኛውም ኃይል የፖለቲካውን መድረክ ሲቀላቀል ሕዝባዊ ኃላፊነትን ለመሸከም፣ አገሪቱ የጎደላትን ለመሙላትና ሌላው ዓለም የደረሰበት እንድትደርስ ለማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ትልቅ ዓላማ ደግሞ የሚከፈለው የኑሮ ውጣ ውረድን መስዋዕት አድርጎ፣ ተቻችሎና ተደማምጦ መሆን አለበት፡፡ ሰው መቼም ገንዘብ ለማግኘት፣ ድጎማና ፍርፋሪ ለመለቃቀም ፖለቲከኛ ያውም ‹‹ትልቅ›› ፖለቲከኛ መሆን አያስፈልገውም፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ እየዋኙ ያሉ ኃይሎች ከጽንፈኛና ከጥላቻ ፖለቲካ ሊወጡ አልቻሉም፡፡ ቢወጡም ግንባር ቀደም ታጋይና የመስዕዋትነት ሰው መሆን የሚችሉ አይደሉም፡፡ ከሁሉም በላይ አገራዊና ኅብረ ብሔራዊ መሆን የተሳናቸው ድንክዬዎች ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ደግሞ እውነተኛውን ዴሞክራሲም ሆነ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ተወዳዳሪነትን ማበልፀግ ፈጽሞ ሊሳካ የሚችል አይደለም፡፡

በአጠቃላይ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ስለልማትና ዕድገት ብቻ የሚታሰብበት ሳይሆን፣ ቅድሚያ ለሰላምና ለዘላቂ አገራዊ ፖለቲካ መነጋገርን የግድ የሚባልበት ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ልዕልናና እኩልነት የሚያስቡና ለአገሪቱ አብሮነትና ሰላም የሚጨነቁ ኃይሎች ሁሉ ሊያጤኑት የሚገባው ጉዳይም ይኸው ነው፡፡ በግሌ ከላይ እንደጠቃቀስኩት ባነበብኳቸው ፖለቲካ ነክ ኅትመቶች የማጠቃለያ ገጾች ላይ ያገኘኋቸውንና በጋራ አቋም የተያዘባቸውን ቢያንስ በሁለት ነጥቦች አቅርቤያለሁ፡፡ በቀጣዩ ጊዜም ቀሪ ነጥቦችን ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡ እናንተም የምታነሷቸው ምክረ ሐሳቦች ካሉ እንወያይባቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊዋን በኢሜይል አድራሻቸው   hdebebe@yahoo.comማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

Trending Articles