በሳሙኤል ረጋሳ
የነገሮች ክስተት በጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ የተገደቡ ናቸው፡፡ ስለተፈጠረው ክስተት ለመነጋገርና ለመረዳዳት፣ እንዲሁም ለማሰብና ለመወሰን የምንችለው በዚሁ ውስን ወቅት ነው፡፡ አንዳች ነገር ማድረግ እየተገባን ምንም ሳናደርግ ብንቀር ወይም ማድረግ የማይገባንን አድርገን ጥፋት ቢደርስ ኃላፊነቱ የዚያ ዘመን ትውልድ ይሆናል፡፡ ሐሳባችንን ለመግለጽ ባንፈልግም ለመደበቅ ደግሞ የሚያስቸግሩ ሁኔታዎች አሉ፡፡
የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ስናጤነው ዛሬ ያለችበት ወቅት ያለምንም ማመንታት አደገኛ ሁኔታ መሆኑን በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው አገሪቱን ለማዳን የሚችለውን ማከናወን ይኖርበታል፡፡ ሕዝብና መንግሥት፣ መንግሥትና ተቃዋሚ ድርጅቶች ሊነጋገሩም ሆነ ሊደማመጡ አልቻሉም፡፡ በየፊናቸው በተናጠል የሚናገሩትም የአንዱ ለሌላው በማይገባ የባቢሎን ቋንቋ ነው፡፡ የመነጋገሪያውና የመደማመጫው ጊዜ ግን አሁንና አሁን ብቻ ነው፡፡ ይኼ የመጠቀሚያ ጊዜያችን አልፎ ነገሮች አሁን በተያዙት አቅጣጫ ይበልጥ እየተወሳሰቡ ከሄዱ ውሉ የጠፋበት ልቃቂት ስለሚሆኑ፣ ብዙዎቻችን አሁን ላይ ሆነን ለመገመት የሚያስቸግረን የጥፋት ዘመን ሊከተለን ይችላል፡፡ በተለይ መንግሥት ነገሮችን ከቁብ ባለመቁጠሩ ይሁን በንቀት ችግሮችን ተቀብሎ የመፍትሔ ሐሳብ ሲያስቀምጥ አይታይም፡፡
አሁን በመንግሥት ዘንድ የሚታየው ትልቅ ክፍተት አዲስ ሐሳብ የሚያመነጭ፣ እንዲሁም ለችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ የሚሰጥ ጠንካራ የበላይ አመራር ያለመኖር ይመስላል፡፡ አማካሪ እየተባሉ በማዕከል የተኮለኮሉት የቀድሞ ባለሥልጣናት የአሁንም ቢባል ያስኬዳል እንዳሁኑ ዓይነት አስደንጋጭ ሁኔታ ሲከሰት በቂ ጥናት በማካሄድ መንግሥትን የማማከር ሚናቸው ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ በተጨባጭም ከሰሞኑ በቴሌቪዥን እንዳየናቸው የኢሕአዴግ ፖሊሲና አቅጣጫ የመንግሥተ ሰማያት መንገድ መሆኑን ሊያሳዩን እንዳየናቸው፣ የኢሕአዴግ ፖሊሲና አቅጣጫ ምንም ችግር የሌለበት ትክክለኛ መንገድ መሆኑን ለማስተማር ካድሬ እንጂ አማካሪ መሆን አያስፈልግም፡፡ ለነገሩማ ምክርም የሚሰጠው ለሚሰማና ጆሮ ላለው ነው፡፡ ኢሕአዴግ በተፈጥሮው የተጠናወተው ክፉ በሽታ የሦስተኛ ወገን ሐሳብን እንዳስፈላጊነቱ መቀበል ሳይሆን፣ በራሱ የድርጅት ግምገማ ተወቅጦና ተሰልቅጦ የሚቀርብለትን የራሱን ድርጅታዊ አሠራር የሚያጠናክር የቡድን ሐሳብን ነው፡፡
ይኼ በረሃ በነበሩበት ጊዜ ግለሰቦች የተለያየ አመለካከት እንዳይዙና እንዳያፈነግጡ ተብሎ ድርጅታቸውን ለማጠናከር ሲገለገሉበት የነበረ አሠራር ነው፡፡ በወቅቱ ተገቢነት ይኖረው ይሆናል፡፡ ችግሩ መንግሥት ሆነውም ይኼው ለ25 ዓመታት በዚሁ ቀጥለዋል፡፡ አሁን አስፈላጊው ነገር መንግሥት ከራሱ አባላት ብቻ ሳይሆን ወጣ ብሎ መስማት ያለበትና ሊቀበለው የሚገባውም የሕዝቡን የልብ ትርታ አዳምጦ ፍላጎቱ ምን እንደሆነ ማወቁ ነው፡፡ ማወቅ ብቻ ሳይሆን እንደ መንግሥት ሊፈጽም የሚችለውንና የሚገባውን መፈጸም፣ የማይቻለውን ግን ከነምክንያቱ ለሕዝቡ በማስረዳት ከሁሉም አካላት እምነት ማግኘት አለበት፡፡
ያለበለዚያ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ከኑሮዬ አፈናቀለኝ፣ መኖሪያዬን አሳጣኝ፣ ልጆቼ ተበተኑ ብሎ በስንት ትግል በሕዝብ ጥያቄ እንዲቆም የተደረገውን የማፈናቀል ሥራ፣ አደባባይ ወጥቶ ‹‹ሕዝቡ የማይገባው ስለሆነ ለጊዜው በእንጥልጥል አቆየነው እንጂ ነገ መልሰን እናፈናቅላችኋለን›› ብሎ በድፍረት ለኢትዮጵያ ሕዝብ መንገር፣ ያለውን ውጥረት ለማርገብ ሳይሆን በእሳት ላይ ቤንዚን መጨመር ነው፡፡
ኢሕአዴግ ሆይ! አሁን እንዲህ አድርግ፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ዜጐች የሆኑ ተቃዋሚዎች ተሰብስበው በአገሪቱ ፖለቲካዊና ወቅታዊ ችግሮች ላይ እንዲወያዩ መንገዱን አመቻችላቸው፡፡ አንተም በዚሁ መድረክ ላይ የራስህንና የምታምንበትን አቋም አራምድ፡፡ እነሱ የሚያቀርቡት በኢሳትና በኦኤምኤን የሚያስተላልፉትን ነው፡፡ አንተም የምታቀርበው በኢቢሲና በአዲስ ዘመን የምታቀርበውን ነው፡፡ ሕዝቡ ግን ጐን ለጐን ተቀምጣችሁ ሐሳባችሁን የምትገልጹበትን መንገድና ለአገር ጠቃሚ የሆነውን ሐሳብ ይገመግማል፡፡ በተለይ መድረክ አጥተው ታፍነን ሞተናል የሚሉ ተቃዋሚዎች ይህን ዕድል ሲያገኙ የሕዝባቸውን መንፈስ ይረዳሉ፡፡ ሐሳባቸውን በአደባባይ ማቅረባቸውን እንደ አንድ ውጤት ይቆጥሩታል፡፡ በመጨረሻም ሕዝቡ የሚቀበለው ሐሳብ በዲሞክራሲያዊ አሠራር እንዲተገበር ይደረጋል፡፡
ከዚህ በተረፈ አሁን ባለው ሁኔታ ሠልፍ የወጣን፣ የተቃወመን፣ ሥራ ያቆመን፣ ቤት የዋለን፣ ገበያ ያልወጣን፣ ሱቅ የዘጋን ሁሉ መሣሪያ በያዙ አካላት መቆጣጠር እንደማይቻል መንግሥት ማወቅ አለበት፡፡ ይኼ የሌባና የፖሊስ ጨዋታ እሽክርክሮሽ መሞከርም የለበትም፡፡ ሰሞኑን ኦሮሚያ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ግለሰቦች ሱቅ ዘግተዋል፡፡ ገበያዎች ሳይቆሙም ቀርተዋል፡፡ በዚህ ሒደት በዋናነት የሚጎዳው መንግሥት አይደለም፡፡ የፀጥታ ችግር ጉዳይም የለበትም፡፡ ተጐጂው አካል ምርቱን አምርቶ ለዓመት በዓል ገበያ ሊያቀርብ ያልቻለው አምራችና በገበያው መጠቀም ያልቻለው ሸማች ሕዝብ ነው፡፡ የሱቆችም መዘጋት እንዲሁ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ዕርምጃዎች ረዘም ላለ ጊዜ ሊቀጥሉ የማይችሉ ግን የተቃውሞ ምልክት ናቸው፡፡ በራሳቸው ጊዜ የሚቆሙ ናቸው፡፡ ነገር ግን መንግሥት የተዘጉትን ሱቆች ሁሉ በማሸግ ለድርጊቱ መባባስ ተባባሪ መሆን የለበትም፡፡
በየከተማው የቆሙትን ባጃጆችና ታክሲዎች ታርጋ መፍታትና የመሳሰሉት ዕርምጃዎችን መውሰድ ከመንግሥት የሚጠበቅ ተግባር አይደለም፡፡ ይኼን ያደረጉት አብዛኞቹ ሰዎች ባልታወቁ ሰዎች በንብረታችን ላይ ጉዳት ይደርሳል ከሚል ሥጋት ነው፡፡ በፈቃዳቸው ያደረጉ ቢኖሩም ባናሟሙቀው ይሻላል፡፡ ለመሆኑ መንግሥት ያሸጋቸውን ሱቆችና ታርጋቸውን የፈታባቸውን ተሽከርካሪዎች ምን ሊያደርጋቸው ነው? አንድ ግልጽ ነገር አለ፡፡ መንግሥት የከለከለውን ሁሉ ይፈቅዳል፡፡ እሽጉም ይቀደዳል፣ ሰሌዳውም ይመለሳል፡፡ የዚህ ዓይነት ድርጊቶች መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተዓማኒነትና መንግሥታዊ ግርማ ሞገሱን ያሳጡታል፡፡ መንግሥት ለሚያልፍ ነገር ሁሉ ከሕዝብ ጋር እልህ መጋባትና አታካሮ ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ እነዚህ የዕለት ተዕለት አምባጓሮዎች የሕይወትና የንብረት መስዋዕትነት እየጠየቁ ነው፡፡ ይኼን ሁሉ ወደ ጐን አድርገን ወደ ውይይት እንግባ፡፡
ለመሆኑ የኢሕአዴግ መንግሥት አንድ ቀን ሥልጣኔን እለቃለሁ ሌላም የሚተካኝ ይመጣል ብሎ ያስባል? ነገሩ ቢታሰብም ባይታሰብም ውሎ አድሮም ቢሆን አይቀሬ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ሁልጊዜ መጣር ያለበት ከዕለት ሥራው ጐን ለጐን አገሪቱን በሰላማዊ መንገድ ሌሎች የሚረከቡበትን የረጅምም ሆነ የአጭር ጊዜ ዓላማ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይኼ የአስተሳሰብ ጠቃሚነቱ ለሁሉም ነው፡፡ በተለይ የገዢው ፓርቲ መንግሥት ጥሮ ግሮ ያስመዘገባቸው የልማትም ሆነ የፖለቲካ ውጤቶች እውቅና ያገኛሉ፡፡ በክብርም ለትውልድ ይተላለፋሉ፡፡ በእልህና በጉልበት የመጠቀሙ ጉዳይ ሕይወትና ንብረት የሚያወድምና የተለፋበትን ሁሉ ውጤት አልባ የሚያደርግ ነው፡፡
ሌላው የኢሕአዴግ መንግሥት ዋና ችግር የአቅም ጉዳይ ነው፡፡ አብዛኞቹ ሹሞች የሚሾሙት በፖለቲካ ወገንተኝነታቸው እንጂ በእውነተኛ ትምህርት፣ ብቃት፣ ብስለትና ለቦታው ተገቢ በመሆን አይደለም፡፡ አብዛኞቹ ባለሥልጣናት ዲግሪው በልካቸው የተፈጠረላቸው እንጂ እነሱ በያዙት ዲግሪ እኩል ቀርቶ ግማሹም ችሎታ የላቸውም፡፡ ዛሬ የማስተርስ ዲግሪ ይዘው በአስተርጓሚ ካልሆነ በስተቀር የውጭ ዜጐችን በእንግሊዝኛ አነጋግሮ ሐሳብ መረዳትና የራስ ሐሳብን ማስረዳት የሚችሉ የሉም ማለት ይቻላል፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን እንደያዘ የተማሩ አባላትን ሲመለምል ከጐን ያሉት ነባር ታጋዮች ቦታዬን የሚቀማኝ መጣ በማለት ያለጥፋት በግምገማ ያባርሩ እንደነበር ይፋ አድርጐ ነበር፡፡ ዛሬም ይኼ አስተሳሰብ የለም ይሆን?
የአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሚኒስትር ዴኤታ የነበረ ሰው በውጭ ቴሌቪዥን በየቀኑ የሚሰጠውን አስተያየት ያዳመጠ ሁሉ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሚኒስትር ደረጃም ቢሆን ብስለታቸውንና እውቀታቸውን ለመገምገም በቂ ናሙና ነው፡፡ ይኼ ሰው የግለሰቦችን ስም እያጠፋ የሚሰጠው አስተያየት በጣም የሚቀፍ ነው፡፡ የአገር ተቆርቋሪነትና የአገርን ሚስጥር መጠበቅ ብሎ ነገር አልፈጠረበትም፡፡ መንግሥትን መቃወሙን ብቻ ነው የሚያየው፡፡ የሚናገራቸው ነገሮች ሁሉ ታስበውና ተጠንተው ለሚዲያ የሚቀርቡ አይደሉም፡፡ እንዲሁ አፉ ላይ የመጣውን ሁሉ ያለ ይሉኝታ ይዘረግፈዋል፡፡ ታዲያ ኢሕአዴግ ይኼንንና ብዙ የእሱ ቢጤዎችን ከተራ የመንደር ጐረምሶች ውስጥ ሲሾም መሥፈርቱ ምንድን ነበር? ይኼ ሰው ምንም ሳይታወቅ በክልሎች ኮታ የተሾመ ይመስላል፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት አሿሿም ሲገርመን ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ በቅርቡ በሪዮ ኦሊምፒክ ጭቅጭቅ የፈጠረው የኦሊምፒክ ውጤት ማሽቆልቆልን ተከትሎ፣ በአትሌቶችና በባለሙያዎች መካከል የተፈጠረው ያለመግባባት እስካሁን አልበረደም፡፡
የሚገርመው ነገር ኢሕአዴግ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ካቋቋመ ጀምሮ በፕሬዚዳንትነት የሚመራው በቋሚነት የአማራ ክልል ተወካይ ነው፡፡ ቦታው ለአማራ ክልል የተሰጠ በመሆኑ አባላት ከየክልሉ መጥተው ሲሰበሰቡ የአማራ ክልል አቶ እከሌን የላከልን ስለሆነ ቀጣይ ፕሬዚዳንታችን እሳቸው ናቸው ተብሎ ያለምርጫ በጭብጨባ ይደመደማል፡፡ ስለዚህ ይኼ ቦታ የአማራ ነው የሚል ስም ይሰጠዋል፡፡ ሌሎች በርካታ መሥሪያ ቤቶችም እንደዚሁ ናቸው፡፡
ቀደም ሲል በነበሩት መንግሥታት የአንድ ክፍለ ሀገር ፖሊስ አዛዥ የሚሾመው በፖሊስ ትምህርት የገፋ፣ በሙያውና በአገልግሎቱ ቢያንስ የብርጋዴር ጄኔራልነት ማዕረግ የነበረው ሰው ነበር፡፡ አሁን ግን ከአንድ በላይ ክፍለ ሀገሮች ተሰብስበው አንድ ክልል በሆኑበት ዘመን የክልል ፖሊስ አዛዥ የሚሆነው ስለፖሊስ ሥራና ትምህርት ምንም እውቀት የሌለው፣ በሥራ ልምዱም ሆነ በዕድሜው ያልገፋ ጃኬትና ቲሸርት ለባሹ ወጣት የድርጅት አባል ነው፡፡ ታዲያ ይኼ ሰው በማያውቀው ሙያና ከፍተኛ ኃላፊነት በሚጠይቀው የፖሊስ አመራር ላይ ተመድቦ ስህተቶች ቢፈጸሙ ኃላፊነቱ የማን ነው? በአሁን ጊዜ መንግሥት ስለሰዎች ብቃትና የሥራ ጥራት የሚጨነቅ አይመስልም፡፡ የሚያስጨንቀው ነገር ቢኖር መዋቅሮቹ ሁሉ በአባላት መሞላታቸው ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የኢሕአዴግ አባል በመሆናቸው የማያውቁትን ሥራ ሊያከናውኑ አይችሉም፡፡ እንዲያውም ያበላሹታል፡፡ መንግሥትን ከሕዝብ እያቆራረጠ ያለው አንዱ ጉዳይም ይኼ ነው፡፡ ሁሉም ሥራዎች በተገቢው ሠራተኛ መሞላት አለባቸው፡፡ የተለያዩ የአሠራር ድክመቶችና የመልካም አስተዳደር ዕጦት አንዱ መነሻ ይኼ ነው፡፡
ሌላው የአገራችን መፃኢ ዕድል ሊያጨልመው የሚችለው በውጭ አገር ያሉ የተቃዋሚዎች ሁኔታ ነው፡፡ መንግሥትን አምርሮ በመጥላት በጥፋት መንገድ ጭምር ከሥልጣን ለማውረድ ሰፊ ቅስቀሳ ያካሂዳሉ፡፡ ነገር ግን ሐሳባቸው እንኳ ቢሳካ አገሪቱን ለማረጋጋት አንድም ሐሳብ ሆነ ሥጋት አይታያቸውም፡፡ በተለያዩ ቋንቋዎች የ24 ሰዓት የአየር ጊዜ ስላላቸው ሙሉውን ጊዜ በመጠፋፋት መንግሥትን እናውርድ እያሉ ይሰብካሉ፡፡ ‹‹የቸገረው ደሃ ይገባል ከውኃ›› እንደሚባለው ይህንን የመጠፋፋት ቅስቀሳ የሚከታተሉና የሚደግፉ በአገር ውስጥም መኖራቸው ነው፡፡ ምክንያቱም የመንግሥት ሚዲያዎች ትልልቅ የአገር ጉዳዮችን ወደ ጐን በመተው በአሰልቺ ፕሮግራሞች በመጠመዳቸው ነው፡፡
የቂሊንጦ እስር ቤት ተቃጥሎ ቤተሰብና ሕዝብ በጭንቀት ውስጥ እያለ የእኛ ሚዲያዎች ምንም እንዳልተፈጠረ ሕዝቡ ለመንግሥት የሚሰጠውን ድጋፍ ያስተላልፋሉ፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ሳይወድ ሙሉ በሙሉ እንኳ እውነትነት ባይኖረው ስለቃጠሎው ፍንጭ ይሰጡኛል ብሎ እነዚህን የውጭ ሚዲያዎችና ማኅበራዊ ድረ ገጾችን ሲከታተል ይውላል፡፡ እነዚህ የውጭ ሚዲያዎችን ለመጠፋፊያነት የሚጠቀሙ ጽንፈኛ ዳያስፖራዎች ምን ዓይነት የፖለቲካ አጀንዳ አላቸው? እርስ በርሳቸውስ ተግባብተው አገሪቱን መምራት ቀርቶ ብቁ አመራር እንዲፈጠር ማድረግ ይችላሉ? ወይስ እንደ ዶሮዋ ‹‹ባልበላውም አፈሰዋለሁ›› ነው፡፡
አሁን ኢሕአዴግን ሰንገው የያዙት ኢሳትና ኦኤምኤን ጣቢያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ጣቢያዎች የአማራና የኦሮሞን ሕዝብ ስሜታዊነት አይተው ጥግ ድረስ ሄደው ለመቀስቀስ የሚሞክሩ ናቸው፡፡ በየፊናቸው የሚያስተላልፉት ፕሮግራም ይዘት ግን ሁለቱን ሕዝቦች የሚያቃርኑና የሚያለያዩ ናቸው፡፡ አንዱ የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ በጎሰኝነት ፈርጆ ስለአንዲት ኢትዮጵያ ያወራል፡፡ ሌላው ስለብሔር ጭቆና ብቻ የሚመለከተው ይመስላል፡፡ ለመሆኑ ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን ያስባሉ? አሀዳዊት ወይስ ፌዴራላዊት? ፌዴራላዊት ካሉ ክልሎች እንዴት ይፈጠራሉ? እንዳሁኑ በብሔር ብሔረሰብ አሠፋፈር ወይስ ሁሉንም ሕዝቦች አንድ ላይ አሰባጥረው ሌላ ክልል ነው የሚፈጥሩት፡፡ ጣቢያውን የሚመሩት ወጣት ልጆች በዚች ጉዳይ እንኳ ዝንተ ዓለም አይስማሙም፡፡ የሚያስማማቸው አንድ ነገር ቢኖር ኢሕአዴግን ማስወገድ ነው፡፡ ይኼ እነሱ የሚስማሙበትን አንድ ነገር ብዙ ሰው ይጋራዋል፡፡ ነገር ግን የዕለት ጉዳይን ብቻ የሚያስቡ ክፍሎች ነፃ የአየር ጣቢያ አገኘን ብለው ቀኑን ሙሉ የሚሰብኩንን ፍሬ አልባ ዲስኩር በጭፍን መቀበል ይቸግራል፡፡ ከኢሕአዴግ አገሪቱን ተረክቦ የሚመራንና በሰላም የሚያሸጋግረን፣ እንዲሁም የማረጋጋት ሥራ በብቃት ሊወጣ የሚችል ድርጅት ያስፈልገናል፡፡ በተለይ በአገር ውስጥ ያላችሁ ተቃዋሚዎች ይህንን ማሟላት ይጠበቅባችኋል፡፡
በመጨረሻ ወጣቶቻችን ይኼን ጉዳይ እንዴት ማየት ይገባቸዋል? የኢትዮጵያን ሕዝብ ችግር ወጣቶች ሲያስተጋቡ ኖረዋል፡፡ ችግሮችን በሚያነሱበት ጊዜ ሁሉ ሊከተል የሚችለውን መጨረሻ አይገምቱትም፡፡ በጣም የሚያስቆጨው በ1966 ዓ.ም. ወጣቱ በረጅም ትግል ሊያገኝ የተቃረበውን ድል በስሜታዊነት በመምራቱ ድሉን በቀላሉ ለወታደራዊ አገዛዝ አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ይቺ ትንሽ የምትመስል ስህተትና ወጣትነት ያስከተለው የወደፊትን በርቀት ያለማስተዋል የአገሪቱን ዕድል መቀመቅ ከትቶታል፡፡
ብዙ ነገሮች አዕምሮአችንን የሚገዙት በተደጋጋሚ በምናየውና በምንሰማው ነገር ነው፡፡ አዕምሮአችን በተደጋጋሚ ያየውንና የሰማውን በውስጣችን ጥልቅ መሠረት ያስይዛቸዋል፡፡ እንደ አቀባበላችን ሁኔታና እንደ ነገሩ ይዘት የፍቅር ወይም የጥላቻ ስሜት ይፈጥርብናል፡፡ ይኼ ቅቡልነት በአንድ ጫፍና በሌላ ጫፍ የጥላቻ ወይም የፍቅር መደብ ስለሚይዝ ሰዎች እንደተፈጠረባቸው ስሜት በአመለካከት ይለያየሉ፡፡ የነገሮች የውስጥ ስርፀት ባደገ ቁጥር አንዱ በአንዱ ላይ በምክንያት ሳይሆን በስሜት የሚፈጠር ጥላቻ ይኖረዋል፡፡
በስሜታዊነት አንመራ፡፡ ስሜታዊነት ያልፋል፡፡ የእሱ ውጤት የሆነው ጥላቻም ይኖረዋል፡፡ የሚያስከተለው ፀፀትና ቁጭት ግን ዝንተ ዓለም አያልፍም፡፡ ስለአገራችን ሁኔታ አንድ የተጨበጠ ነገር ተወያይተን ማግኘት አለብን፡፡ ሰዓት በጨመረ ቁጥር ቀኑ ሊጨልም ነው፡፡ አሁን ለዓይን ያዝ ባደረገበት አመሻሽ ላይ ነን፡፡ መንግሥት መብራት አብርቶ ሕዝቡ እንዲተያይና እንዲወያይ ያድርግ፡፡ ልንነጋገርባቸው የሚገቡን ነገሮች ሁልጊዜ አይኖሩም፡፡ ትክክለኛው የመነጋገሪያ ጊዜ ካለፈ የምንነጋገርበት ጉዳይ ስለማይኖር መፍትሔው ሌላ አማራጭ ይሆናል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
