በጎንደር ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት
የአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ልክ እንደ ኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 341/1995 የተቋቋመ ሲሆን፣ በተመሠረተበት በ1999 ዓ.ም. ወቅት 13 የከተማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችና አንድ የክልል ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን በአባልነት ይዞ የተመሠረተ ነበር፡፡
ዓላማውም በክልሉ ውስጥ ያሉ ሕጋዊ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትን መብትና ጥቅም ማስከበር፣ ግዴታቸውን ማስረዳት፣ አቅማቸውን ማጠናከር፣ ንግድ ነክ አዋጆችን ደንቦችንና መመርያዎችን እንዲያውቁ ማገዝ፣ የተለያዩ ሥልጠናዎችን መስጠት፣ ችግሮች ሲከሰቱ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመወያየት መፍትሔ ማፈላለግ፣ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትና ባዛሮችን በማካሄድ የክልሉን የኢንቨስትመንት አማራጮች ማስተዋወቅና የገበያ ትስስር መፍጠር ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ምክር ቤቱ ከተቋቋመበት ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2004 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ያሉት የከተማ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባላት ቁጥር ከ28 የማይበልጥና አባላቱም 14 ሺሕ ብቻ የነበሩ ሲሆን፣ የክልሉ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ከወረዳና ከከተማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ጋር ባደረገው ጠንካራ የቅንጅት ሥራ የከተማና ወረዳ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባላት ወረዳዎችን ቁጥር 167፣ ነጋዴዎችን ደግሞ ከ240 ሺሕ በላይ ማድረስ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባል ከሆኑት ማኅበራት አንዱ የሆነው የአማራ ክልል የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከተቋቋመበት ጀምሮ ስድስት ጠቅላላ ጉባዔዎች ያካሄደ ሲሆን፣ በመጀመርያው ጠቅላላ ጉባዔ አቶ ይርጋለም አድማሱን በፕሬዚዳንትነት እንዲሁም አቶ ጌታቸው አየነውን በምክትል ፕሬዚዳንትነት መርጦ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በተካሄዱት ከሁለተኛው ጠቅላላ ጉባዔ እስከ ስድስተኛው ጠቅላላ ጉባዔ አምስት ጠቅላላ ጉባዔዎች አቶ ጌታቸው አየነው በፕሬዚዳንትነት የተመረጡ ሲሆን፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች በአምስቱ ጠቅላላ ጉባዔዎች ከክልሉ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የሚወከሉ የተለያዩ አምስት ግለሰቦች ተመርጠዋል፡፡
በዚህ ጽሑፍ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ አቫንቲ ሆቴል የተከናወነውን ስድስተኛውን ጠቅላላ ጉባዔና የስብሰባውንና የምርጫውን ክስተት ይተነትናል፡፡ ስብሰባው ሲጀመር ፕሬዚዳንቱ አቶ ጌታቸው አየነው የጠቅላላ ጉባዔ ወንበር ብዛት 200 መሆኑንና በአጠቃላይ 167 የከተማና የወረዳ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች፣ እንዲሁም አንድ ክልላዊ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በአባልነት መኖሩን ጠቅሰው ለእያንዳንዱ አባል ምክር ቤት አንድ አንድ ወንበር የተሰጠ ሲሆን፣ ከ3,500 አባላት በላይ ያላቸው አባል ምክር ቤቶች እንደ ቁጥራቸው ተጨማሪ ወንበር እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ጥሪ ከተደረገላቸው 200 የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ውስጥ 106 አባላት በቦታው መገኘታቸውንና ከግማሽ በላይ መሆኑን በማረጋገጥ ጠቅላላ ጉባዔው መቀጠል እንደሚችል ተናገሩ፡፡
በክብር እንግድነት የተገኙት አቶ ተዋቸው የአማራ ክልል ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ በተጋባዥነት አቶ ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር የኢትዮጵያ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና አቶ አበባው መኮንን የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ተገኝተዋል፡፡
የ2007 ዓ.ም. እና የ2008 ዓ.ም. የሥራ ክንውን ሪፖርት በፕሬዚዳንቱ ሲቀርብ አበረታች ተግባራት፣ ከአባላት ጋር ያለ የግንኙነት መረብ፣ ስለ ምክክር መድረክ፣ ስለቢዝነስ ዳይሬክተሪ፣ ንግድ ትርዒትና ባዛር፣ የጽሕፈት ቤት ግንባታ ቦታ ጉዳይ፣ በገቢና በወጪ እንዲሁም በመሳሰሉት ዝርዝር ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፣ ያጋጠሙ ችግሮችም ተዳሰውበታል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሪፖርታቸውን አጠናቀው ወደ ውይይት ከመግባት አስቀድሞ እንግዶቹ አቶ ተዋቸው፣ አቶ ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔርና አቶ አበባው መኮንን አስቸኳይ ሥራ እንዳለባቸው ተገልጾ የስብሰባ አዳራሹን ለቀው ሲሄዱ የጠቅላላ ጉባዔውም አባላት ተነስተው በክብር ሸኝተዋቸዋል፡፡ አመቻች ኮሚቴ ተሳታፊው የተለያዩ ሐሳቦችን ካቀረበ በኋላ ከተሰናባች ቦርድ አባል የሆኑ ሦስቱ ማለትም አቶ አሰፋ አላምረው ሰብሳቢ፣ አቶ ደመላሽና አቶ አማረ ሰለሞን አባላት ሆነው መድረክ ላይ ተሰየሙ፡፡ አመቻች ኮሚቴው የምርጫ ሕጎችን በማፅደቅ ሦስት አስመራጭ ኮሚቴዎችን በማስመረጥ መድረኩን ለአስመራጭ ኮሚቴዎች በማስረከብ አመቻች ኮሚቴው መድረኩን ሲለቅ አስመራጭ ኮሚቴው መድረክ ላይ በመውጣት ምርጫው ተከናወነ፡፡
ትዝብቶች
- የአመቻች ኮሚቴ ሰብሳቢ አስመራጭ ኮሚቴ ለማስመረጥ ዕድል ሲሰጡ ሁለቱን ዕድል ከተሰናባች የቦርድ አባላት የሰጡ ሲሆን፣ አንዱን ደግሞ ለባህር ዳር ዘርፍ ቦርድ ተወካይ በመስጠት ገና ከጅምሩ የምርጫው ፍትሐዊነት ጥያቄ ውስጥ መግባት ጀመረ፡፡ የጉባዔው ተሳታፊዎች ጉዳዩን ቢቃወሙም ንግግራቸው የጆሮ ቀለብ ከመሆን አልዘለለም፡፡
- የምርጫ አመቻች ኮሚቴ ሰብሳቢ የፕሬዚዳንቱን ምርጫ በተመለከተ ለውይይት አቅርቦ ሲያፀድቅ ለፕሬዚደንትነት ሦስት ዕጩዎች እንደሚቀርቡና የወደቁት ሁለቱ ዕጩዎች ያለውድድር በቀጥታ የቦርድ አባል እንዲሆኑ በማፀደቅ የምርጫውን አቅጣጫ አስቀድሞ ለታለመለት ሰው እንደተዘጋጀ ያሳብቅ ነበር፡፡
- አስመራጭ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት ለማስጠቆም በሰጠው ዕድል አመቻች ኮሚቴው የሠራውን ሥራ በመድገም የባህር ዳር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ተወካይ ፕሬዚዳንት የአመቻች ኮሚቴ ሰብሳቢውን አቶ አሰፋ አላምረውን ሲጠቁም፣ የተሰናባች የቦርድ አባል የሆኑት ደግሞ አቶ ጌታቸው አየነውን ጥቆማ ሲሰጡ፣ የደሴ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ታምራት ደግሞ ከደሴ ተጠቁመዋል፡፡ በዚህ ዕድል የመስጠት ሥርዓት በርካታ ሰዎች እጃቸውን ያወጡ ቢሆንም የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢው ከወልድያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የመጡት አስቀድሞ ለማን ዕድል መስጠት እንዳለበት ተወስኖ የተሰጣቸው መሆኑን በሚያሳብቅባቸው ሁኔታ ለእነዚህ ሦስት ሰዎች ብቻ ዕድሉን በመስጠት ተልዕኳቸውን በአግባቡ መወጣት ችለዋል፡፡
- ለፕሬዚዳንትነት የተወዳደሩት አቶ አሰፋ አላምረውና አቶ ታምራት ራሳቸውን እንዲገልጹ ዕድል ተሰጥቷቸው መድረክ ላይ ሲወጡ ሁለቱም በተመሳሳይ ቃል በፕሬዚዳንትነት መምራት እንደማይችሉ፣ ከእነሱ ይልቅ አቶ ጌታቸው አየነው በፕሬዚዳንትነት ለአሥረኛ ዓመት ቢቀጥሉ ደስተኛ እንደሚሆኑ በመግለጽ ሜዳውን ለአቶ ጌታቸው ብቻ በማመቻቸት ብቻቸውን ተወዳድረው ለእሳቸው ብቻ ቦታው እንዲሰጥ ቃላቸውን ሲሰጡ ሁለቱ ተወዳዳሪዎች ግን ሚዜ በመሆን የቦርድ አባልነታቸውን ብቻ ማረጋገጥ እንደሚፈልጉ ገለጹ፡፡ ይህም በተራ ቁጥር ሁለት ያነሳነው የዕጩዎቹ ጉዳይ ለምን እንደዚያ እንደሆነ የበለጠ ግልጽ እየሆነ መጣ፡፡
ለፕሬዚዳንትነት የተወዳደረ ዕጩ ተወዳዳሪ ከቦርድ አባልነት ዕጩነት ውጪ ይደረግ ቢባል ኖሮ ሁለቱ ለውድድር አይቀርቡም ነበር፡፡ ለፕሬዚዳንትነት ዕጩ በመሆን ለውድድር በመቅረብ ነገር ግን የቦርድ አባል ብቻ መሆን እንደሚፈልጉ ከመግለጽ ባሻገር፣ ሌላ ተወዳዳሪ ከአቶ ጌታቸው ጋር እንዳይወዳደር በማድረግ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደሚባለው ሆኖ ጉዳዩ የተበላ ዕቁብ እንደሆነ አብዛኛው የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ተገነዘቡ፡፡
- አስመራጭ ኮሚቴው የቦርድ አባላትን ለማስመረጥ ባደረገው የጥቆማ ሥነ ሥርዓት አሁንም ተደጋጋሚ ዕድሎች ለነባሩ የቦርድ አመራሮች በመስጠት አብዛኛዎቹ የቦርድ አመራሮች በድጋሚ ተመርጠው የምርጫው ድራማ ተጠናቋል፡፡ አንድ አረጋዊ የጠቅላላ ጉባዔው አባል ሁኔታውን ታዝበው ስለአካሄዱ በጠቅላላ ጉባዔው ፊት ሲናገሩ እንዲህ አሉ፡፡ ‹‹እኔ እንግዳ ነኝ፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉባዔ ስሳተፍ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ሁላችሁንም አላውቃችሁም፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ መድረክ ላይ የነበረው ከታች ያለውን ዕድል ይሰጥና ከታች ያለው ከላይ ይወጣል፡፡ ከላይ የወጣው ደግሞ መልሶ ለዚያው ሰው ዕድል ይሰጣል፡፡ በተደጋጋሚ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ዕድሉ ተሰጠ፡፡ ይህ ከሆነ ያንን ያህል ኪሎ ሜትር አቋርጠን ከወረዳችን ለምን መጣን? ተመራጩ እየታወቀ ለምን ታደክሙናላችሁ?›› በማለት በአረጋዊነት የንግግር ለዛ ሲናገሩ ሁሉም በፈገግታና በአግራሞት አዳምጧቸዋል፡፡
- የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት የሆኑት ሦስቱ መድረክ ላይ ሆነው በተደጋጋሚ ባደረጉት ተመሳሳይ ንግግር የቦርድ ሥራ ለመሥራት ራቅ ካሉ ከተሞችና ወረዳዎች ከሆኑ የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን ስለማይመች፣ ጥቆማ ሲሰጥ ከቅርብ ያሉት ሰዎች ቢጠቆሙ ይመረጣል በማለት የአስመራጭ ኮሚቴ ማልያን ለብሰው ለማን ክለብ እንደሚጫወቱ አስቀድመው ከማስታወቃቸው ባሻገር የምርጫውን ሱሪ ሊመረጡ አስቀድመው በወሰኗቸው ሰዎች ልክ መስፋት ጀመሩ፡፡
ይህንን ሐሳብ ሦስቱም አስመራጭ ኮሚቴዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ አንድ አስተያየት ሰጪ አካሄዱን በመንቀፍ፣ ‹‹እናንተ ምርጫ እንድታስፈጽሙ እንጂ መራጩን አቅጣጫ እንድታስይዙ አልተመረጣችሁም፤›› በማለት ቢነግራቸውም አስቀድመው የተዘጋጁበትን ተግባራዊ ለማድረግ ቆርጠው የተነሱ በመሆናቸው አብዛኛዎቹ ነባር አመራሮች እንዲቀጥሉ ሆነዋል፡፡ የጎንደር የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ለቦርድ አመራርነት ቢጠቆሙም በምርጫው ፍትሐዊነት ስለማናምንበት መመረጥ አልፈልግም በማለት ከሌሎች የጎንደር የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባላት ጋር በመሆን ስብሰባውን ረግጠው ወጥተዋል፡፡
- ጠቅላላ ጉባዔው ከመካሄዱ ሁለት ቀናት አስቀድሞ በዕለተ ዓርብ መስከረም 27 ቀን 2009 ዓ.ም. የክልሉ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባካሄደው የቦርድ ስብሰባ፣ የወቅቱን ሁኔታ እንደ ምክንያት በማድረግ ጋዜጠኛ በጠቅላላ ጉባዔ ተሳታፊ እንዳይሆንና ምንም ዓይነት ሪፖርት ወደ ውጪ እንዳይወጣ አስቀድሞ የመከላከል ሥራ ተሠርቷል፡፡ ይኼም የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማኅበራትና የአገር አቀፍ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ምርጫን በተመለከተ በመገናኛ ብዙኃን በስፋት መገለጹ፣ በአማራ ክልል የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ስድስተኛ ጠቅላላ ጉባዔም እንዳይደገም የተሠራ ሥራ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
- ይህ ጠቅላላ ጉባዔ በሚከናወንበት ወቅት የምርጫውን ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ በታዛቢነት መገኘት ያለባቸው የክልሉ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ እንዲሁም የእናት ማኅበሩ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተወካዮች መገኘት የነበረባቸው ቢሆንም፣ ምርጫው ሲካሄድ ምንም ዓይነት ታዛቢና ዕርምት ሰጪ በሌለበት በየጊዜው የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱን ምርጫ ወደፈለጉት አቅጣጫ በመውሰድ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ቡድኖች በአብዛኛው እንግዳና አዲስ የሆኑትን ከከተሞችና ወረዳዎች የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የመጡትን የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ባስገረመ መልኩ ያለታዛቢ ምርጫው ተከናውኗል፡፡
- ጠቅላላ ጉባዔው የተካሄደው ዕለተ እሑድ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲሆን፣ አንድም አባል ምክር ቤት ለጠቅላላ ጉባዔ የጥሪ ደብዳቤ አልደረሰውም፡፡ ለሁሉም አባል ምክር ቤቶች ጥሪ የተላለፈው በስልክ ሲሆን፣ የስልክ መልዕክቱም መተላለፍ የተጀመረው ከአምስት ቀናት በፊት ከመስከረም 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዓርብ መስከረም 27 ቀን 009 ዓ.ም. ድረስ ነው፡፡ የጠቅላላ ጉባዔ ጥሪ አንድ ቀን እስኪቀረው እየተላለፈ ቢቆይም በዚህ ወቅት ከኔትወርክ ውጪ የሆኑና ስልካቸው ዝግ የሆነ አባላት መልዕክቱ ሳይደርሳቸው ቀርቷል፡፡ እንግዲህ ከአዲአርቃይ ወረዳና ከጃናሞራ ወረዳ ጀምሮ እስከ ደጀን ከተማና የሰሜን ሸዋ ወረዳ ከተሞች ድረስ ያሉትን 167 የወረዳና የከተማ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ መልዕክት ሲተላለፍ አብዛኞቹ ስልካቸው በመዘጋቱ፣ አካባቢቸው ኔትወርክ ባለመኖሩና ከጊዜው ማጠር የተነሳ እንዲሁም አስቀድመው በሌላ ፕሮግራም ጊዜያቸው በመያዙ መገኘት ያልቻሉ አሉ፡፡
- ከጠቅላላ ጉባዔው ክንውን አንድ ቀን በፊት ላለፉት ሦስት ዓመታት ይዘጋጅ የነበረው የንግድ ማውጫ (Business Directory) የተመረቀ ሲሆን፣ በውይይት ወቅት አስተያያት ሰጪዎች ሐሳብ ሲሰጡ የቢዝነስ ዳይሬክተሪው ኅትመትና ጥራት ይዘት በጠንካራ ጎኑ በማንሳት ጠቅላላ ጉባዔው መደረግ የነበረበት በታኅሳስ 2008 ዓ.ም. ሲሆን፣ እስከ ዛሬ የዘገየው ይህንን የንግድ ማውጫ በማስመረቅ የምርጫ መቀስቀሻ ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ እንደሚመስል አንስተዋል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ በቢዝነስ ዳይሬክተሪው የፋይናንስ እንቅስቃሴ ሪፖርት 3,408,500 ብር ቃል የተገባ ሲሆን፣ 2,442,775 ብር የተሰበሰበና የሚሰበሰብ ደግሞ 965,725 ብር መሆኑን ሲገልጹ የኦዲት ሪፖርት አልቀረበም፡፡ ከተሳታፊው ለምን ኦዲት ሪፖርት እንዳልቀረበ ተጠይቆ ሲመለስ በምክንያትነት የቀረበው ገንዘቡ ተጠቃሎ ገቢ ባለመደረጉ እንደሆነ ቢገለጽም፣ በኦዲት ሕግ ተሰናባቹ ቦርድ በተሰብሳቢ አስይዞ ኦዲት ማስደረግ እየቻለ አለማስደረጉ ቀጣዩ አመራር ራሳቸው እንደሚሆኑ አመላካች ከመሆኑም ባሻገር፣ በሒሳብ እንቅስቃሴውም በጠቅላላ ጉባዔው አባላት በኩል ጥርጣሬን አጭሮ አልፏል፡፡
- ለጠቅላላ ጉባዔው ዝግጅት መጽሔት የታተመ ቢሆንም የጠቅላላ ጉባዔ መጽሔት እንደመሆኑ የሥራ ክንውን ሪፖርትና የኦዲት ሪፖርት በመጽሔቱ ተካቶ አልታተመም፡፡ ይህንን ሐሳብ በጉባዔው ያነሳው ተሳታፊ ቢኖርም፣ ከዚህ በፊትም በተካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔዎች ሐሳቡ ቀርቦ የነበረና በየጊዜው ለምን ማካተት እንደማይፈለግ ግልጽ አይደለም፡፡
- ምርጫው ተከናውኖ ካለቀ በኋላ ለነባር የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት የምስክር ወረቀት በፍሬም ተዘጋጅቶ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ሌላውን ሽልማት ግን የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ቢሮ በመሄድ እንዲወስዱ ተነግሯቸው ጠቅላላ ጉባዔው ተበትኗል፡፡ የቦርዱ አባላት ወደ ቢሮ ሄደው ያገኙት ሽልማት ‹ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ› እንደሚባለው ለእያንዳንዳቸው የላፕቶፕ ኮምፒዩተር ሽልማት ሲሆን፣ ጠቅላላ ግምቱ 120,000 ብር አካባቢ በማውጣት በመሸላለም ተወዳድሰውበታል፡፡ ከ11ዱ የቦርድ አባላት ሁለቱ በስብሰባ በአብዛኛው ስለማይገኙ በሚል ያልተሸለሙ ሲሆን፣ ለጠቅላላ ጉባዔ ዝግጅት ስፖንሰር ካደረጉ ድርጅቶች ከተገኘ ገንዘብ የተገዛ መሆኑንና ከጽሕፈት ቤቱ መደበኛ ሒሳብ ገንዘብ ወጪ አለመደረጉን ሲገልጹ ከመስማት ባሻገር፣ ላፕቶፕ ያልተሸለሙ የቦርድ አባላት ቅሬታቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡
ጠቅላላ ጉባኤው ከተበተነ በኋላ የላፕቶፕ ሽልማቱን ጉዳይ የሰሙት የጠቅላላ ጉባዔው አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል አንደኛ ሽልማቱን ከጠቅላላ ጉባዔው ፊት ከምስክር ወረቀቱ ሥጦታ ጋር አብሮ ያልተደረገው ለምንድን ነው? ሁለተኛ ቦርዱ ለራሱ ሽልማት ራሱ መወሰን ይችላል ወይ? ሦስተኛ ከ11ዱ የቦርድ አባላት መካከል ሁለት የቦርድ አባላት ሳይሸለሙ የቀሩት ለምንድነው? በማለት ተጠያቂ በሌለበት ጉዳዩን አንስተዋል፡፡
- የጠቅላላ ጉባዔ ተሳታፊ የሚሆኑ ሁሉም አባላት ማለትም የቦርድ አባላትን ጨምሮ የንግድ ሥራቸውን ከሚያከናውኑበት ከተማና ወረዳ ተወክለው የመጡ መሆን እንዳለባቸው ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ከሥር መሠረታዊ ንግድና ዘርፍ ማኅበራቸው በተሠራው ቀመር መሠረት ተወክለው መምጣት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ነባሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርቱን ካቀረበና በሪፖርቱ ላይ አስተያየት ተቀብሎ ካፀደቀ በኋላ፣ ለምርጫ ተሳታፊ መሆን የሚችሉት ከሚኖሩበት ከተማና ወረዳ ንግድና ዘርፍ ማኅበራቸው ተወክለው ከመጡ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም አሁን በፕሬዚዳንትነት የተመረጡትና ሌሎች ሁለት የቦርድ አባላት ነዋሪነታቸው ባህር ዳር ከተማ ሲሆን፣ የባህር ዳር ከተማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በጠቅላላ ጉባዔ እንዲሳተፉ ወክሎ የላካቸው አለመሆኑ እየታወቀ፣ እንኳንስ ለአመራርነት መመረጥ ቀርቶ በምርጫው ወቅት የጠቅላላ ጉባዔ አባል መሆን የማይችሉበትን የሕግ ሥርዓት በመጣስ ከዚህ በፊት በተካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔዎች በተመሳሳይ መንገድ ሕግ እየተጣሰ ዕርማት የሰጠ ባለመኖሩ ዛሬም ሕግ ተጥሷል፡፡ አዳዲስ የወረዳና የከተማ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አመራሮች ዕይታ በዚህ ጠቅላላ ጉባዔ ለመጀመርያ ጊዜ የተገኙ ከተለያዩ ከተማና ወረዳ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት የመጡ አዲስ አመራሮች በሰጡት አስተያየት፣ በክልሉ ምርጫ እንዲህ ዓይነት የቡድን ስሜት በተንፀባረቀበት መንገድ ምርጫ ይካሄዳል ብለው እንደማይጠብቁና እኛ ከመጣንበት ወረዳና ከተማ አንተ ትሻላለህ፣ አንቺ ትሻያለሽ በመባባል በፍፁም ትህትና የተመራረጥን ነው፡፡ እዚህ ስንመጣ ያየነው ግን ከዚህ በተቃራኒ ለመመረጥ ይህን ያክል ተደራጅቶ በመግባት ለረዥም ዓመታት ቦታውን በመያዝ ለሌላ ተተኪ ለመልቀቅ አለመፈለግ ያውም በነፃ ለሚከናወን አገልግሎት በጣም ተደንቀናል ብለዋል፡፡ መቼም ይህንን ያህል ዋጋ ከፍለው፣ ለመመረጥ ሰማዕትነት ከፍለው፣ ስማቸው ጠፍቶ ይህንን ሁሉ ልፋት የሚለፉት ለፅድቅ ወይም ለነፍስ ነው? ለማለት ከመቸገር ባለፈ የንግዱን ማኅበረሰቡን ለማገልገልም ካለ ፍላጎት ነው ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው ሲሉ አክለው ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በነፃ ያለዋጋ ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጥበት ተቋም ቢሆንም ከዓላማ ውጭ የግል መጠቀሚያ የማድረግ፣ ሥራውን መተዳደሪያ የማድረግ፣ የአንዳንድ ጥቅማ ጥቅም ማግኛ ማዕከል እያደረጉት ሳይሆን እንደማይቀር የታዘቡ አሉ፡፡ የክልል የንግድና ዘርፍ ማኅበራት እንዲህ ይሆናል ብለው እንደማይጠብቁም ገልጸዋል፡፡ የንግድ ሚኒስቴርና የአማራ ክልል ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ የነጋዴው ማኅበር የተጠናከረና ለአገር የኢኮኖሚ ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን በመገንዘብ ሁልጊዜ የሚደረገውን ድጋፍ፣ ክትትልና እገዛ ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው በተቋሙ ግልጽነትና ተጠያቂነት የተሞላበት
አሠራር ሲሰፍን በመሆኑ፣ እንዲህ ዓይነቱ የተበላሸና የቡድን ስሜት የተንፀባረቀበት አሠራር ባህል እየሆነ የመጣ ስለሆኑ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱንና የቢሮውን ሥራ በዜሮ የማባዛት ያህል ነው፡፡
በመሆኑም ለንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የዕውቅና ምስክር በመስጠት አደራጅ የሆነው የንግድ፣ ሚኒስቴርና የአማራ ክልል ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ፣ እንዲሁም እናት ማኅበር የሆነው የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በተከናወነው ኢዴሞክራሲያዊ ምርጫና የቡድን ስሜት የተንፀባረቀበትን መሠረታዊ የሕግ ክፍተቶች ያለበትን ጉባዔ በዕንጭጩ እንዲቋጭ በማድረግ አስተማሪ ዕርምጃ መውሰድ የሚቻልበትን አሠራር ማስፈን ካልተቻለ፣ የድራማው ተዋናዮች በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደተሰማው ይህ ጉዳይ የአንድ ሰሞን ነው፡፡ ሁልጊዜ ምርጫ ሲከናወን የተወሰኑ ሰዎች ቢያጉረመርሙም ማንም ምንም ሊያደርግ አይችልም እያሉ፣ በአጠቃላይ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የግለሰቦች መፈንጫ መሆናቸውና የተቋቋሙበትን ዓላማ የማያሳኩ ሽባ ተቋማት ሆነው እንደሚቀጥሉ ሥጋት ስላለ፣ ማን ምን የማድረግ ሥልጣን እንዳለው ማሳየት ቢቻል መልካም ነው፡፡
ስለዚህ ጠቅላላ ጉባዔው በአጠቃላይ ያሉበትን መሠረታዊ የሕግ ክፍተቶች በማስረጃ በተደገፈ ሙያዊና ከአሉባልታ በፀዳ መንገድ በሰዎች ምስክርነትና በሰነድ ማስረጃነት ሊመረምር የሚችል አካል ተቋቁሞ ምርመራ በማካሄድ፣ የሚመለከተው አካል ነፃና ገለልተኛ ውሳኔ በመስጠት ሕግን ማስከበር ይገባል፡፡ የጎንደር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፡፡ (የማይነበብ ፊርማና ማኅተም አለው)
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው gondarchamber@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡
