በተክለብርሃን ገብረሚካኤል
ይህን መጣጥፍ እንዳቀርብ የቀሰቀሱኝ፣ እሁድ መስከረም 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በወጣው ‹‹ሪፖርተር›› (በአማርኛ ቋንቋ) ላይ የወጡት ሁለት ድንቅ ጽሑፎች ናቸው፡፡ አንደኛው ጽሑፍ ‹‹ባንኮች በተጠናቀቀውና በመጪው ዘመን›› በሚል ርዕስ በጋዜጣው ሪፖርተር የቀረበው ምርጥ ዘገባ ሲሆን፣ ሁለተኛው ጽሑፍ ደግሞ፣ ‹‹የአደጋ ጠርዝ ላይ የጣሉን የኢኮኖሚ ጉዳዮች›› በተሰኘ ርዕሰ ጉዳይ ብዙ ጊዜ በዚሁ ጋዜጣ ላይ በኢኮኖሚና ፋይናንስ ነክ ጉዳዮች ላይ የሚጽፉ ዓምደኛ ጌታቸው አስፋው ያስነበቡን ሙያዊ መጣጥፍ ነው፡፡ ሁለቱንም ጸሐፊዎች እያመሰገንኩ፣ እግረ መንገዴን በኢትዮጵያችን የጋዜጠኝነት ሙያ ታሪካዊ ሊባል የሚችል እምርታ እንዲያሳዩ ላደረገው ‹‹ሪፖርተር›› ጋዜጣ ያለኝን ከፍተኛ አድናቆት ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
በአቶ ጌታቸው አስፋው የኢኮኖሚ ትንታኔ እንጀምር፡፡ ጌታቸው የኢትዮጵያን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሁኔታ ለመቃኘት የሞከሩት ከአገሪቱ የውጭ ክፍያዎች ሚዛን/ሒሳብ (ባላንስ ኦፍ ፔይመንትስ አካውንት) አኳያ ነው፡፡ ሒሳቡ አስደንጋጭ የኢኮኖሚ ውድቀት ምልክቶችን ያሳያል፡፡ ጸሐፊው የተጠቀሙባቸው የኢኮኖሚ አኃዞች የ2006 እና የ2007 ዓ.ም. ናቸው፡፡ በ2007 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ሸቀጦች (ቁሳዊ) ወይም የምርት ኤክስፖርት ያገኘችው ጠቅላላ የውጭ ምንዛሪ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ያህል ብቻ ሲሆን፣ በዚያው ዓመት ከውጭ ለምታስመጣቸው ቁሳዊ ሸቀጦች (ኢምፖርት) የከፈለችው የውጭ ምንዛሪ 16.5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው፡፡ በዚህ መሠረት፣ የውጭ የሸቀጥ ንግድ ጉድለቱ 13.5 ቢሊዮን ዶላር መሆኑ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የኤክስፖርት ገቢ የኢምፖርት ወጪውን የሚሸፍነው በአሥራ ስምንት በመቶ ብቻ ነው (ሃያ በመቶ እንኳን አልሞላም)፡፡ በጣም አስደንጋጭ የኢኮኖሚ ውድቀት ምልክት ነው፡፡ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ፣ ኤክስፖርት በ2006 ዓ.ም. ከነበረበት 3.3 ቢሊዮን ዶላር፣ በ2007 ዓ.ም. ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር መቀነሱና ከዚህ በተቃራኒ ኢምፖርት ከ13.7 ቢሊዮን ዶላር ወደ 16.5 ቢሊዮን ዶላር መጨመሩ ነው፡፡
ሌላው አስደንጋጭ ክስተት እንደ ቱሪዝምና የአየር ትራንስፖርት (የኢትዮጵያ አየር መንገድ) ካሉት አገልግሎቶች የምናገኘው የውጭ ምንዛሪ ወጪን እንኳን መሸፈን ሳይችል ቀርቶ፣ በ2007 ዓ.ም. 341 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ማስመዝገቡ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአብዛኛው ‹‹ዳያስፖራው›› የሚልከውን ሐዋላ የሚያካትተው ከግል ምንጮች የሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ በ2006 ዓ.ም. ከነበረበት አራት ቢሊዮን ዶላር ወደ 4.8 ቢሊዮን ዶላር ቢጨምርም፣ የሚያመለክተው ኢኮኖሚያዊ ስኬትን ሳይሆን ጥገኝነትን ነው፡፡
ከላይ ከቀረበው መረጃ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አገሪቱ ከመንግሥታዊ ምንጮች የምታገኘው የውጭ ዕርዳታ የቀነሰ ሲሆን፣ የውጭ ብድር ግን ከ2.7 ቢሊዮን ዶላር ወደ 4.8 ቢሊዮን ዶላር ጨምሯል፡፡ በተመሳሳይ የውጭ ኢንቨስትመንትና የተከማቸ የውጭ ዕዳ ከፍተኛ ጭማሪዎች አስመዝግበዋል፡፡ አገሪቱ ከመንግሥታዊ ምንጮች የምታገኘው የውጭ ዕርዳታ የቀነሰው፣ ምናልባት ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ከመንግሥት ሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር በተዛመደ የሚያደርገው አሉታዊ ተፅዕኖ ሊሆን እንደሚችል የተገመተ ሲሆን፣ የውጭ ብድርና የተከማቸው የውጭ ዕዳ የጨመሩት ደግሞ መንግሥት ለልማት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከግል አበዳሪዎች ጭምር ለማግኘት በመሞከሩ እንደሆነ ይታመናል፡፡
እንዲያውም መንግሥት በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ የተከማቸው የአገሪቱ የውጭ ዕዳ ሃያ አንድ ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን፣ አንዳንድ የውጭ ምንጮች አኃዙን ወደ ሰላሳ ቢሊዮን ዶላር ያስጠጉታል፡፡ አቶ ጌታቸው ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለውጭ ዕዳ ክፍያ (ለዋናውና ለወለድ ክፍያ) 35 ቢሊዮን ብር ወይም አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ (በአንድ ዶላር 22 ብር ሒሳብ) እንደምትከፍል ነግረውናል፡፡ ይህ ክፍያ እየጨመረ ከሚሄደው የውጭ ዕዳ ጫና (የተከማቸው) አብሮ እያደገ እንደሚሄድ መገመት አያዳግትም፡፡ የውጭ ዕዳ ክፍያውና የኤክስፖርት ገቢ መቶኛ ምጣኔ ከሃምሳ ሦስት በመቶ በላይ መሆኑ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በኤክስፖርታችን ከሃምሳ በመቶ በላይ ለውጭ ዕዳ ክፍያ የምናውል ከሆነ፣ የኢምፖርት ወጪውን በምን እንሸፍነዋለን? ኢምፖርቱን እያደገ በሚሄድ የውጭ ብድር ለመሸፈን ከተገደድን፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አዙሪት ቀለበት ውስጥ እንደምንገባ ጥርጥር የለውም፡፡
የውጭ ኢንቨስትመንት የኢምፖርትን ወጪ በከፊል ሊሸፍን ይችላል፡፡ ግን ይህም ራሱ የውጭ ዕዳነት ባህሪ አለው፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች የሚያገኙትን ትርፍ በውጭ ምንዛሪ ወደየአገሮቻቸው የመላክ መብት አላቸው፡፡ ኢንቨስትመንታቸውን ዘግተው ሲሄዱ ደግሞ ቢያንስ በውጭ ምንዛሪ ያስገቡትን ካፒታል ያህል ወደየአገሮቻቸው ይዘው መመለስ ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የውጭ ክፍያዎች ሒሳብ የሚያሳየው አጠቃላይ ጉድለትን ሲሆን፣ ይኼንን ኪሳራ ለመሸፈን የአገሪቱን መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሪ መቀነስና ብሎም ማሟጠጥ ስለሚያስፈልግ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊፈታ በማይችል የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር ውስጥ የመግባት አደጋ ሊከሰት እንደሚችል፣ እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ ችግሩ መከሰት ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ ውድቀቱ ዋና መገለጫ እየሆነ መጥቷል፡፡
አቶ ጌታቸው ሌሎች አጠቃላይ የኢኮኖሚ ውድቀት ምልክቶችንም እንደሚከተለው መዝግበውልናል፡፡ ስልሳ በመቶ የሚሆነው የገበሬ መሬት ይዞታ ስፋት ከአንድ ሔክታር በታች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሱዳን ሽንኩርት ‹‹ኢምፖርት›› ታደርጋለች፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የውጭ ጥገኝነቱ በውጭ ዕርዳታና ብድር ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹ዳያስፖራው›› በሚልከው ሐዋላ ላይም ነው፡፡ ሥራ አጥነት ተንሰራፍቷል፡፡ ሥራ አጥነት ስውር ሥራ አጥነት እንዲጨምር ተደርጐ ከተሰላ፣ ለሥራ የበቃው ሕዝብ ሁሉ እንደ ሥራ አጥ የሚቆጠርበት ደረጃ ሊደርስ ይችላል፡፡ በቀን ለስምንት ሰዓት የተቀጠረ የመንግሥትና የግል ሠራተኛ፣ በቀን አራት ሰዓት ከሠራ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የስውር ሥራ አጥነት መጠን እጅግ ሰፊ ነው፡፡ የጥቃቅንና የአነስተኛ ድርጅቶች እንቅስቃሴ በእጅጉ ቀዝቅዟል፡፡ ‹‹የኮብልስቶን›› ሥራም እንደዚሁ ተቀዛቅዟል፡፡ ሳይሠራ የሚበላው ሕዝብ ቁጥር በጣሙን ጨምሯል፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ ግልጽና ስውር ሥራ አጥነት በተንሰራፋበት የኢኮኖሚ ዕድገቱ እንዴት አሥራ አንድ ነጥብ ምናምን በመቶ ሊሆን ቻለ? ብለው ይጠይቃሉ አቶ ጌታቸው፡፡ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን እንዲህ እያሉ ይቀጥላሉ፡፡ ኢትዮጵያ የገዛ ልጆቿና የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ወደ ዓረብና ሌሎች አገሮች እንዲኮበልሉ ቪዛና ፓስፖርት እየሰጠች መሸኘት ከጀመረች አያሌ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ሠርቶ ያላለፈልንን፣ መቶ ፈረንጆች ‹‹ኢንዱስትሪ ፓርኮች›› አቋቁመው እንዲያልፍልን መንግሥታችን ሌት ከቀን እየሠራ ነው፡፡ የገቢና የሀብት ልዩነት ጣሪያ ነክቷል፡፡ በመጨረሻምአቶ ጌታቸው እንደሚከተለው በማለት ማስጠንቀቂያና ምክር ይሰጡናል፡፡ ‹‹ዝምታ ሁላችንንም ገደል ውስጥ ይከተናል፡፡ ኢኮኖሚው ወደ መውደቅ ያዘነበለ መሆኑ የሚታያቸው ሁሉ ደመናውን ለመግፈፍ አስተያየታቸውን ቢለግሱ ጥቅሙ ለሁላችንም ነው፤›› ሸጋ መክረውናል፣ ተገቢም ማስጠንቀቂያ ሰጥተውናል፡፡ የጋዜጣው ሪፖርተር ዘገባ ግን ከዚህ በጣም የተለየ ነው፡፡ ለባንክ ኢንዱስትሪው መጪው ጊዜ ብሩህ መሆኑን ብቻ አይደለም የሚነግረን፣ ያለፉትም ዘመናት በትርፋማነት የተንበሸበሹ እንደነበሩ ነው የሚያበስረን፡፡ ይገርማል፣ አንድ እውነታ ሁለት መነጽሮች ያስብላል፡፡ ለማንኛውም እስኪ አሁን ደግሞ ወደ ጋዜጣው ሪፖርተር ዘገባ እንዙር፡፡
የባንክ ኢንዱስትሪው ትርፋማነት
የሁለቱ የመንግሥት ባንኮች (የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ) እና የአሥራ ስድስት የግል ባንኮች ድምር ወይም ጠቅላላ ትርፍ (ከታክስ በፊት) በ2007 በበጀት ዓመት ከነበረበት ደረጃ በመጨመር፣ በ2008 የበጀት ዓመት ወደ 21.5 ቢሊዮን ብር ገደማ አሻቅቧል፡፡ ከዚህ ውስጥ የአሥራ ስድስት የግል ባንኮች ጥቅል ትርፍ 6.3 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻውን 13.4 ቢሊዮን ብር አትርፏል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ትርፍ ደግሞ (ይህ የተጣራ መሆኑ ተገልጿል) 414 ሚሊዮን ብር ያህል ሆኗል፡፡ የአሥራ ስድስቱ የግል ባንኮች ጥቅል ትርፍ በ2007 የበጀት ዓመት 5.4 ቢሊዮን ብር ገደማ ስለነበር፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ድምር ትርፋቸው በአንድ ቢሊዮን ብር ያህል ማደጉን ያመለክታል፡፡
በሌላ በኩል የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በ2008 የበጀት ዓመት ከፍተኛ የትርፍ መቀነስ ሁኔታ ታይቶበታል፡፡ ይህ ችግር ምናልባት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያ ክልል ከተከሰተው ያለመረጋጋት ሁኔታ የተዛመደ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ብርሃን ባንክ ትርፉን በከፍተኛ መጠን ማሳደጉ ተዘግቧል፡፡
የባንክ ኢንዱስትሪው ስኬት በትርፋማነት ብቻ አልተወሰነም፡፡ የጋዜጣው ሪፖርተር ስኬቶቹን እንደሚከተለው በዝርዝር ያቀርባቸዋል፡፡ አዲስ ወጥ የሆነ የቼክ ክፍያ ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ማሽኖች (ኤቲኤሞች) በሁሉም ባንኮች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ሥርዓቱ የተዘረጋላቸው ኢትስዊች በሚባል ኩባንያ ነው፡፡ በሌላ በኩል በተለይ ከቡና ዋጋ መውረድ ጋር በተያያዘ የባንክ ዕዳቸውን በወቅቱ መክፈል የታያቸው የደቡብ ቡና ነጋዴዎች ለብድር ያስያዙት ንብረት በሐራጅ ተሸጦ ችግር ውስጥ እንዳይገቡ የእፎይታ ጊዜ መስጠቱ (በብሔራዊ ባንክ) እንግዳ ነገር ቢሆንም፣ ነጋዴዎቹን በመታገድ ረገድ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ፈላጊዎች ለአገልግሎቱ ከአንድ በላይ ባንክ መጠቀም እንደማይችሉ የተላለፈው መመርያ ደግሞ በአገሪቱ የደረሰውን አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያመለክታል፡፡ በሌላ በኩል ሁሉም ባንኮች በኮር ባንኪንግ ቴክኖሎጂ እንዲተሳሰሩ መደረጉ እንደ አንድ ትልቅ ስኬት ተቆጥሯል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁ ነው የሚባለውን የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ማስጀመሩም የሚጠቀስ ነው፡፡ ኤጀንት ባንኮች የሚባሉትም ሥራ መጀመራቸው ተዘግቧል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክን መጠቅለሉም ትልቅ የቢዝነስ ዜና ሆኖ አልፎአል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ፣ ሌሎች ባንኮችም ሊጠቃለሉ እንደሚችሉ ተወስቷል፡፡
ከባንክ ኢንዱስትሪው ስኬታማነት ጋር ሊታይ የሚችለው ሌላው ጉዳይ፣ የአንዳንድ የባንክ ሥራ አስኪያጆችና ፕሬዚዳንቶች የወር ደመወዝ ከመቶ ሺሕ ብር በላይ ማሻቀቡ ነው፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ መመደቡ፣ በባንኩ ሥርዓት አድሎአዊ አሠራር እንዳለ አመላካች ሆኖአል፡፡ ዝርዝር ዘገባቸው በመቀጠል የሁለቱ የመንግሥት ባንኮችና የአሥራ ስድስቱ የግል ባንኮች ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ 435 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተመልክቷል፡፡ ይህ አኃዝ በ2007 በጀት ዓመት ከነበረው 367.4 ቢሊዮን ብርና በ2006 በጀት ዓመት ከነበረው 292.8 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል፡፡
በተመሳሳይ አሥራ ስድስት የግል ባንኮች ተቀማጭ ገንዘባቸውን ከ100 ቢሊዮን ብር ገደማ በ2008 ዓ.ም. ወደ 147 ቢሊዮን ለማሳደግ ችለዋል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻውን የተቀማጭ ገንዘቡን መጠን ወደ 288.4 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ መቻሉ የባንኩን አንፃራዊ ግዙፍነት ያመለክታል፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2008 በጀት ዓመት የሰጠው አዲስ ብድር (ክምችት አይደለም) 92 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ 16ቱ የግል ባንኮች ደግሞ በድምሩ 93 ቢሊዮን ገደማ አዲስ ብድር ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2008 በጀት ዓመት የሰጠው ብድር መጠን ደግሞ 11.84 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተመልክቷል፡፡ የባንክ ሥራ ጤናማነትን ለመለካት ጥቅም ላይ ከሚውሉት አብይ መሥፈርቶች የተበላሸ ብድር ጥምርታ (ምጣኔ) አንዱ ነው፡፡ ይህ መስፈርት ብሔራዊ ባንክ ከደነገገው አምስት በመቶ ከበለጠ (ብድር/የተበላሸ ብድር ጥምርታ) የባንኮች ጤናማነት ጥሩ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ የጤናማነት መለኪያ መሠረት የሁሉም ባንኮች ማለት ይቻላል አማካይ ጥምርታ አምስት በመቶ አካባቢ በመሆኑ፣ ሁሉም ባንኮች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡ የአንድ ባንክ ጥምርታ 7.9 በመቶ በመድረሱ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል የመንግሥት ቦንድ ግዢ (27 በመቶ) በ2008 ዓ.ም. ይቀራል ወይም ይሻሻላል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ግን አምስት ዓመት የሞላው ግዢ እየታሰበ ተመላሽ መሆን ጀምሯል፡፡ የባንኮችን የ2009 ዓ.ም. ዕቅድ በተመለከተ፣ ሁሉም ባንኮች ከ25 እስከ 30 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ አስበዋል፡፡ የጋዜጣው ዘጋቢ ይህን በመረጃ የታጀበ ግሩም ዘገባቸውን እዚህ ላይ ይደመድማሉ፡፡
ትንታኔ፣ ድምዳሜ፣ ማጠቃለያና የመፍትሔ ሐሳብ
ከላይ የቀረቡት ሁለት ዘገባዎች የኢኮኖሚውን እንቆቅልሽ ያመለክታሉ፡፡ አጠቃላይ ኢኮኖሚው የመውደቅና የመዝቀጥ አዝማሚያ እያሳየ ነው እየተባለ፣ የባንክ ኢንዱስትሪው ግን የትርፋማነትና በአጠቃላይም የኢኮኖሚ ስኬት ደሴት መስሎ ይታያል፡፡ ለምሳሌም የአጠቃላዩ ኢኮኖሚ የውጭ ክፍያዎች ሚዛን በጊዜው ዋጋም እንኳን ከፍተኛ የውጭ ንግድ ጉድለት ያሳየ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ሒሳቡም ያስመዘገበው ኪሳራ ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ሥራ አጥነትና ስውር ሥራ አጥነት መኖር የቁሳዊ ምርት አለማደግን፣ ወይም በአነስተኛ መጠን ብቻ ማደግን፣ ወይም መቀነስን ስለሚያመለክት አቶ ጌታቸው እንደሚሉት የኢኮኖሚውን ወደ ውደቀት ማዘንበል ያሳያል፡፡ የአጠቃላይ ኢኮኖሚውን ሁኔታ በገንዘብ ሳይሆን፣ በቁሳዊ ምርትና በተጨባጭ አገልግሎት ስንለካው፣ ያሉት የምርትና የአገልግሎት እጥረቶች ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ምናልባት በሕዝብ ዕድገት መጠን እንኳን አለማደጉን ነው የሚጠቁሙት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት በዓመት በ2.7 በመቶ እንደሚያድግ ይገመታል፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የምግብ ምርት ዕድገት በዓመት በ2.7 በመቶ ካደገ፣ ከድሮው የባሰ የምግብ እህል ምርት እጥረት ሊኖር አይገባም ወይም በፊት እጥረት ካልነበረ፣ ዛሬ እጥረት ይፈጠራል ተብሎ አይገመትም፡፡ ከዚህ ምሳሌ አኳያ መንግሥት ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት በአሥራ አንድ በመቶ አደገ ሲል፣ ካለው የተጨባጭ ምርትና አገልግሎት እጥረት ጋር የሚጣጣም ነገር አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው በአሁኑ ጊዜ የንፁህ ውኃ፣ የምግብ፣ የትራንስፖርት፣ የመኖሪያ ቤት፣ ወዘተ እጥረቶች እየተባባሱ ነው እንጂ የመጡት አልተሻሻሉም፡፡
አጠቃላዩ ቁሳዊ ኢኮኖሚ በተጨባጭ ምርትና አገልግሎት ሲለካ፣ ከላይ እንደተመለከተው፣ ምናልባት በዓመት በሦስት በመቶ አድጎ ሊሆን ይችላል እንጂ፣ መንግሥት እንደሚለው በየዓመቱ በአሥራ አንድ በመቶ ማደጉን ለመቀበል በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በሌላ በኩል ኢኮኖሚው በገንዘብ ሲለካ ዕድገቱ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ሊሆን የሚችለው በአብዛኛው ኢኮኖሚው ውስጥ ለመገበያያ የሚውለው የጠቅላላ ገንዘብ መጠን ዕድገት ከምርት ዕድገት ሲበልጥ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ መንግሥት የሚያወጣቸው የኢኮኖሚ አኃዞች ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት በጊዜው ዋጋ 1.3 ትሪሊዮን ብር ገደማ መድረሱን ያመለክታሉ፡፡ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን የገንዘብ መጠን ዕድገት የሚወስኑት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እያሳተመ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚያስገባው ጥሬ ገንዘብ፣ በዚህ ላይ ተመሥርተው (በተቀማጭ ገንዘብ በኩል) ባንኮች በብድር መልክ የሚፈጥሩት ገንዘብ፣ የተጣራ የውጭ ምንዛሪ ግኝትና የገንዘብ ዝውውር ፍጥነት ናቸው፡፡ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ገንዘብ መጠን ዕድገት ከቁሳዊ ምርትና ተጨባጭ አገልግሎት ዕድገት ከበለጠ፣ የመጨረሻ ውጤቱ የዋጋ ንረት ይሆናል፡፡
ከላይ የቀረበው ምሳሌ የሚያሳየን፣ ምርት ሳያድግም፣ በገንዘብ መጠን ማደግ ምክንያት ዋጋ ከናረ፣ ምርት በገንዘብ ሲለካ (በዋጋ ሲለካ)፣ ከፍተኛ ዕድገት ሊታይ እንደሚችል ነው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ለጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት በጊዜው ዋጋ የሚሰጠው የ1.3 ትሪሊዮን ብር አኃዝ ምናልባት በዚህ መንገድ ዋጋው የናረ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ባንኮች ግን በመሠረቱ የገንዘብ ነጋዴዎች እንደመሆናቸው፣ ገቢያቸውና ወጪያቸው ከገንዘብ መጠን ዕድገትና ከዋጋ ንረት ጋር አብሮ የማደግ አዝማሚያ ስላለው፣ ትርፋቸው በጊዜው ዋጋ የመጨመር አዝማሚያ ቢያሳይ የሚጠበቅ ነው፡፡ ለምሳሌ በኢምፖርት ሌተር ኦፍ ክሬዲት አገልግሎት ላይ የሚያስከፍሉት የአገልግሎት ክፍያ ዋጋው ከጨመረው ከኢምፖርት ጋር አብሮ ይወጣል፡፡ የኢምፖርት ዋጋው ከ100,000 ብር ወደ 5,000,000 ብር ከናረ፣ ባንኮች የሚያስከፍሉት የአገልግሎት መቶኛ ክፍያ ሁለት በመቶ ከሆነ፣ ገቢያቸው ከሃያ ሺሕ ብር ወደ መቶ ሺሕ ብር ያድጋል (በጊዜው ዋጋ) ፡፡ እዚህ ላይ ገቢያቸው በዋጋ ንረቱ መጠን ስላደገ፣ በቁሳዊ ምርት ገቢያቸው ሲለካ አልጨመረም፣ አልቀነሰም፡፡ በሌላ በኩል በሚሰጡት ብድር ላይ በሚያስከፍሉት የወለድ ተመንና በተቀማጭ ገንዘብ ላይ በሚከፍሉት ወለድ መካከል ያለው ልዩነት ከዋጋ ንረት ካነሰ፣ በጊዜው ዋጋ ያተረፉ ቢመስሉም ትርፋቸው ከዋጋ ንረት በተጣራ መንገድ ከተሰላ የሚያስመዘግቡት ኪሳራ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከባንኮች ገቢዎች ኢምፖርት/ኤክስፖርት ሌተር ኦፍ ክሬዲት፣ የውጭና የአገር ውስጥ ሐዋላ አገልግሎትና ሌሎች አገልግሎቶች ከዋጋ ንረት ጋር አብረው እንዳደጉ ስለሚገመት፣ ለትርፋቸው (በጊዜው ዋጋ) መጨመር አስተዋጽኦ ሲያደርጉ፣ ቁሳዊ ምርት በመግዛት ኃይላቸው ግን ብዙም ለውጥ እንዳላደረጉ ይገመታል፡፡
በሌላ በኩል ከባንኮች ወጪዎች መካከል የቅርንጫፍና የዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ፣ የተሽከርካሪና የኮምፒዩተር ግዥ፣ የቤንዚንና የሌሎች ቁሳቁሶች ግዢ ከዋጋ ንረት ጋር አብረው ስለሚወጡ፣ በጊዜው ዋጋ ትርፋቸውን የመቀነስ ተፅዕኖ ያደርጋሉ፡፡ የደመወዝ ወጪ ላይ ግን ባንኮች ዕድገቱን ከዋጋ ንረት በታች ለማድረግ ስለቻሉ፣ ለትርፋቸው (በጊዜው ዋጋ) በዋጋ ንረት መጠን አለመቀነስ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይኼውም በአጠቃላይ የባንክ ሠራተኞች ደመወዝ ከመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ በአማካይ በከፍተኛ መጠን ይበልጣል፡፡ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የመንግሥት ሠራተኞች (ሲቪል ሰርቪስ) አማካይ ደመወዝ በአራትና በአምስት እጥፍ ገደማ ሲጨምር (በጊዜው ዋጋ) የባንክ ሠራተኞች ደመወዝ ግን ቢያንስ አሥር እጥፍ እንደጨመረ ይገመታል፡፡ ለምሳሌ አንድ የቢኤ ዲግሪ ያለው የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ በመንግሥት መሥሪያ ቤት በደርግ ዘመን ያገኘው የነበረው የጀማሪ ደመወዝ 500 ብር የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ከ2,000 እስከ 2,500 ብር ያገኛል፡፡ በሌላ በኩል በጋዜጣው እንደተገለጸው የባንክ ሥራ አስኪያጆች ደመወዝ በአሁኑ ጊዜ ከወር ከመቶ ሺሕ ብር በላይ አሻቅቧል ከተባለ፣ በፊት ከነበረበት አሥር ሺሕ ብር ገደማ ስለሆነ እዚህ የደረሰው ጭማሪው አሥር እጥፍ መሆኑ ነው፡፡ ይሁንና ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የገበያ ዋጋ በሰላሳ እጥፍ ስለጨመረ (የጤፍ ዋጋን ያስታውሷል፡፡ ከ60 ብር ወደ 1,800 ብር በኩንታል)፣ የባንክ ሥራ አስኪያጆች ደመወዝ ማደግ የነበረበት ወደ መቶ ሺሕ ብር ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ሦስት መቶ ሺሕ ብር ነበር ማለት ነው፡፡
ለባንክ ኢንዱስትሪው አትራፊነት አስተዋጽኦ ካደረጉ ነገሮች መካከል በመንግሥት ትዕዛዝ የሚደረገው የባንክ ዕዳ ስረዛ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ለ‹‹ኢንዶውመንቶች›› በመንግሥት ትዕዛዝ የተደረገው የ2.5 ቢሊዮን ብር ዕዳ ስረዛ የሚታወስ ነው፡፡ ይህ አድራጎት አሁንም እንዳልቀረ ይነገራል፡፡ የባንኮች የተበላሸ ብድር መሥፈርት ጤናማ ነው (ከአምስት በመቶ በታች) የሚባለው ዕዳ እየተሰረዘ በመሆኑ፣ የባንኮች ትርፋማነት አጠያያቂ ነው፡፡ ዕዳ ሲሰረዝ የመጠባበቂያ ገንዘብ ስለሚቀንስ (ፕሮቪዥንስ)፣ ትርፍ እንደሚጨምር የታወቀ ነው፡፡ ሌላው በጣም አሳሳቢ ጉዳይ የባንክ ኢንዱስትሪው አትራፊነትና ስኬታማነት በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ አለመታየቱ ነው፡፡ እንዲያውም የባንክ ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ላይ ያለው ተፅዕኖ አዎንታዊ መሆን ሲገባው፣ አሉታዊ ሆኖአል እየተባለ ይተቻል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚያሳትመው ገንዘብና ንግድ ባንኮች በብድር አማካይነት በሚፈጥሩት ተጨማሪ ገንዘብ ምክንያት የዋጋ ንረቱ ጣሪያ ስለነካ፣ የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ አመሰቃቅሎታል፡፡ ሌላው ትችት ባንኮች ሕዝቡን አዘርፈውታል የሚለው ነው፡፡ ለብድር ብቁ ያልሆኑ ሰዎች ከባንክ ከፍተኛ ብድር እየተሰጣቸው፣ ከሕዝቡ መሬትና ቦታ በሊዝ ሽፋን እየተሰጣቸው፣ ከሕዝቡ መሬትና ቦታ በሊዝ ሽፋን እየነጠቁሕንፃዎችን ገንብተዋል፣ ሌሎች ንብረቶችንም አፍርተዋል ነው የሚባለው፡፡ እንዲሁም የባንክ ሠራተኞችና የባንክ ባለአክሲዮኖች የደመወዝ፣ የትርፍ ክፍፍልና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን በተመለከተ ከቀረው ሕዝብ የተሻለ ሁኔታ ላይ ስለሚገኙ፣ ለሕዝቡ ሊያበረክቱት የሚችሉት አስተዋጽኦ አናሳ ነው እየተባሉም ይወቀሳሉ፡፡
ከላይ ከቀረበው ትንታኔ የምንደርስባቸው ድምዳሜዎች ምንድን ናቸው? ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
- የባንኮች ትርፍ በጊዜው ዋጋ በከፍተኛ መጠን የጨመረ ቢመስልም፣ ተጨባጭ ምርትና አገልግሎት በመግዛት ኃይሉ ግን ቀንሷል፣
- የባንክ ኢንዱስትሪው አንፃራዊ ትርፋማነትና ስኬታማነት ከአጠቃላዩ የኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር አይጣጣምም፣
- በባንኮች የሚሰጠው ብድር ከምርት ዕድገት ይልቅ ከፍተኛ የዋጋ ንረት በማስከተሉ፣ በኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ የኑሮ ችግር አስከትሏል፣
- ባንኮች የሙስናና የዝርፊያ መሣሪያ ሆነው አገልግለዋል፣
- የባንኮች ትርፋማነት በከፊል በትዕዛዝ ከሚሰረዝ የባንክ ዕዳ ጋር የተቆራኘ ነው፣
- የባንክ ኢንዱስትሪው በለሙት ኢኮኖሚዎች እንደሚደረገው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመቀጠም እያደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው ነው፣
- የባንክ ኢንዱስትሪው ለነፃ ውድድር በሚያመች ሁኔታ ገና በደንብ ሳይስፋፋ ወደ ማጠቃለል ሒደቱ ውስጥ መግባቱ (ንግድ ባንክ የኮንስትራክሽን ባንክን እንደጠቀለለው) ጤናማ የዕድገት አቅጣጫ አይደለም፣
- በመሠረቱ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትና የማስፋቱ ተግባር የአጠቃላዩ ኢኮኖሚ ድርሻ እንጂ በቀዳሚነት ከባንክ ኢንዱስትሪው የሚጠበቅ አይደለም፣
- የሥራ አጥነትና የስውር ሥራ አጥነት መንሰራፋት ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ከሕዝብ ዕድገት በላይ አለማደጉን ከማመልከቱም በተጨማሪ፣ ምናልባትም የነፍስ ወከፍ ምርት ቀንሶ፣ የሕዝቡ የኑሮ ደረጃ ማሽቆልቆሉን እንደሚያሳይም ይታመናል፣
- በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የአገሪቱ የተከማቸ የውጭ ዕዳ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ሲሆን፣ ለዚህ ዕዳ ክፍያ የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ከኤክስፖርት ከሚገኘው ከሃምሳ በመቶ በላይ ሆኖአል፣
- እስካሁን የውጭ ኢንቨስትመንት ለምርት ዕድገትና ለሥራ ስምሪት መስፋፋት ያደረገው አስተዋጽኦ አነስተኛ ነው፤
ለማጠቃለል ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በኢኮኖሚው የታየው ዕድገት የተጨባጭ ምርትና አገልግሎት ዕድገት ሳይሆን፣ የገንዘብ መጠን ዕድገትና በዚህም ምክንያት የሚከሰተው የዋጋ መናር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሥራ ስምሪትንና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን የማስፋት አቅሙ ዝቀተኛ ሲሆን፣ በአጠቃላይም ዕድገቱ መንግሥት እንደሚለው ባለሁለት አኃዝ ሳይሆን፣ ምናልባት ከሕዝብ ዕድገት ጋር ብቻ የሚመጣጠን እንደሆነ ይገመታል፡፡ በሌላ በኩል የባንክ ኢንዱስትሪው በዚህ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዓውድ ውስጥ ለብቻው እንደ አንድ የኢኮኖሚ ስኬታማነት ደሴት ሆኖ መውጣቱ የጤናማነት ምልክት እንዳልሆነ ይገመታል፡፡ ከዚህ ማጠቃለያ በመነሳት፣ ሊቀርቡ የሚችሉት አጠቃላይ የመፍትሔ ሐሳቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡
- የኢትዮጵያ ርዕዮተ ዓለማዊ አቅጣጫ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲና ከልማታዊ መንግሥት ወደ ሊበራል ዴሞክራሲና ፍትሐዊ ካፒታሊዝም እንዲቀየር ማድረግ፣
- ፍትሐዊ የመሬት ይዞታ ሥርዓት ማዋቀር፣
- የትምህርትና የሙያ ሥልጠናን የጥራት ደረጃ በከፍተኛ መጠን ማሻሻል፣
- የባንክ ብድር አስፈላጊዎቹን ቅድመ ግዴታዎችን ለሚያሟሉ፣ ለብድር ብቁ ለሆኑና የቢዝነስ ክህሎት ላላቸው ሰዎች ብቻ እንዲሰጥ ማድረግ፣
- በትዕዛዝ የባንክ ብድር የመስጠትንና የባንክ ዕዳ የመሰረዝና አድሎዓዊ አሠራር ማስቀረት፣
- የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር በኢኮኖሚክስ ሳይንስ ላይ የተመሠረተ የገንዘብና የመንግሥት በጀት ፖሊሲ መቅረፅ (ሞኒተሪ ኤንድ ፊስካል ፖሊሲ)፣
- የተወዳዳሪ ባንኮች ቁጥር ከኢኮኖሚው ስፋት ጋር የሚመጣጠን ሳይሆን፣ ብዛታቸውን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ማቆም፣
- ከጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት እያደገ የሚሄድ ድርሻ ለኤክስፖርት እንዲውል የሚያበረታቱ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን መውሰድ፡፡
እነዚህንና ሌሎች የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ፣ የባንክ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለብቻው የኢኮኖሚ ስኬታማነት ደሴት ሆኖ የሚወጣበትን ሁኔታ ማስቀረት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ የባንኮች ዕድገትና ትርፋማነት የአጠቃላይ ኢኮኖሚው ዕድገትና ስኬት የሚሆንበትን መላ ልንፈልግ ይገባል እላለሁ፡፡ በመጨረሻም፣ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ባቀረቡት ጽሑፎች ተነሳስቼ ይህን መጣጥፍ ለማቅረብ ያስቻሉኝን አቶ ጌታቸው አስፋውንና የጋዜጣውን ዘጋቢ በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡ ሰላም!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
