Quantcast
Channel: ዓለማየሁ ጉጀ
Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

በተሻሩት አሥራ አንድ በመቶ ካደግን በተሾሙት ስንት በመቶ ልናድግ ነው?

$
0
0

በጌታቸው አስፋው

የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ይለውጣል የተባለ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ሹም ሽር መንግሥታዊ ዕርምጃ ተወስዶ በዝምታ ማለፍ አይቻልም፡፡ የተሰማንን ስሜት መግለጽና በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ አንዳንድ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ባልተለመደ ሁኔታ አስተያየታችሁን ስጡን እያሉ ሕዝብን ሲጋብዙ ሰንብተዋል፡፡ የኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች ከጭፈራ፣ ከስፖርትና ከተረት ወሬ ተላቀው ሙያዊ አስተያየት መጠየቅ መጀመራቸው ያስደስታል፡፡ ስለሆንም ይህንን አጠር ያለ ሙያዊ አስተያየት በለመድኩት መንገድ በሪፖርተር ጋዜጣ ለማቅረብ ወሰንኩ፡፡

መንግሥትም እንደተናገረው ዓለምም እንዲቀበል ባሳመነው መሠረት ላለፉት አሥር ዓመታት በጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ዓመታዊ ዕድገት፣ የአፍሪካንና የዓለምን አማካይ በእጥፍና በየእጥፍ እጥፍ በልጠን በአሥራ አንድ በመቶ አድገናል፡፡

በተለይም ደግሞ በኢኮኖሚ ልማት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በመንገድ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ወዘተ. ረገድ የተመዘገቡት ውጤቶች ወደር የላቸውም ብሏል፣ ብዙዎችም አምነውታል፡፡

በተሻሩት ባለሥልጣናት የተመዘገበው አሥራ አንድ በመቶ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገትና የኢኮኖሚ ልማት ውጤት ካልበቃ፣ አዲስ በተሾሙት ባለሥልጣናት የስንት በመቶ ዓመታዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ወይም የኢኮኖሚ ልማት ውጤት ሊጠበቅ ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ የተኩት አምና ያቋቋሙትን ካቢኔ ቢሆንም፣ ሚኒስትሮቹ ግን በአየር ንብረት ምክንያት ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ ስምንት በመቶ ዕድገት ቢወርድም፣ ከዚያ በፊት ለአሥር ዓመታት በተከታታይ አሥራ አንድ በመቶ ዕድገት ካስመዘገቡ ከፍተኛ የመንግሥት ሹማምንት አካላት ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡

በጥረታቸው በአበረከቱት አስተዋጽኦ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥፍ ሊሆን ዋዜማ ላይ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ጂቡቲ ባቡር መስመር ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የሥራ ዓለምን ለመቀላቀል ዝግጁ ሆነዋል፡፡ የመንግሥት ሜጋ ፕሮጀክቶች በመጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ናቸው፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየተሻሙ ነው፡፡

እነኚህ ሁኔታዎች የተሻሩት ሚኒስትሮች የኢኮኖሚ ዕድገቱን ከአሥራ አንድ በመቶም በላይ ሊያደርሱት ይችሉ በነበሩበት ቁመና ላይ እንደነበሩ የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ በአዲሶቹ ተሿሚዎች የኢኮኖሚው ዕድገት ከአሥራ አንድ በመቶውም በእምርታ እንደሚዘል ሊጠበቅ ይችላል ማለት ነው፡፡

ሆኖም ግን የሹም ሽሩ ዋና ዓላማ የሆኑትን በቅርቡ ለተቀሰቀሰው ሁከት ዋና ምክንያቶች ናቸው የተባሉትን የሥራ አጥነት፣ የዋጋ ግሽበትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግሮች ይፈታል ብሎ ለማለት ግን ጠለቅ ያለ ጥናት የሚጠይቅ ይሆናል፡፡

በግርድፉ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ እንኳ ለመናገር ቢያስፈልግ ኢኮኖሚው ሲያድግ የዋጋ ግሽበቱና የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ እየባሰባቸውም ሊሄድ ስለሚችል፣ ሥራ በመፍጠር ረገድም የኢኮኖሚ ልማቱ በግንባታ ወቅት ብቻ ጥቂት ጊዜያዊ ሥራዎችን ቢፈጥርም፣ የረጅም ጊዜና ቋሚ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም ግን የለውም፡፡ ለብዙዎች የረጅም ጊዜ ቋሚ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም ያለው የገበያ ኢኮኖሚው ብቻ ነው፡፡ ችግርን ለይቶ ማወቅ ለመፍትሔ ግማሽ መንገድ እንደ መጓዝ ነው ይባላል፡፡ የሰሞኑ ሁከት በችግሮቻችን ላይ ምንም ጥናትና ምርምር ሳናደርግ፣ ወረቀትና እርሳስ ሳንጠቀም፣ ሳንደምርና ሳንቀንስ በማያወላዳ መንገድ በግልጽና በገሀድ ነግሮን አልፏል፡፡ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ደረጃ የወጣቱ ሥራ ማጣት፣ የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ዋነኞቹ ችግሮቻችን እንደሆኑ ሁከቱ አሳይቶናል፡፡ እነኚህ ችግሮች ደግሞ የኢኮኖሚ ልማት ችግሮች ሳይሆኑ የገበያ ኢኮኖሚ ችግሮች ናቸው፡፡

በብሔራዊ ኢኮኖሚ ደረጃ ከተጠቀሱት ችግሮች በተጨማሪ በአገልግሎት አሰጣጥ አንዳንድ የክፍላተ ኢኮኖሚዎች ችግሮችም እንደሚኖሩ ባያጠራጥርም፣ ለብሔራዊ ኢኮኖሚ ችግሮች የክፍላተ ኢኮኖሚዎችን አስፈጻሚ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች መቀያየር ብቻውን የሚፈለገውን ለውጥ አያመጣም፡፡ ለገበያ ኢኮኖሚ ችግር መፍትሔ ችግሩ ካለበት ከገበያ ኢኮኖሚው ብዙ ሳይርቁ መፈለግ ይገባል፡፡

ብዙ አገሮች የገጠሟቸውን የገበያ ኢኮኖሚ ችግሮች እንዴት እንደፈቱ እናውቃለን ለምሳሌ ባራክ ኦባማ እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን እንደመጡ ለገበያ ኢኮኖሚ ችግሮች መፍትሔ እንዲፈልጉ ትልቅ ኃላፊነት የሰጡት፣ ለገንዘብ ሚኒስትራቸውና ለብሔራዊ ባንክ ገዥው ነበር፡፡ ግሪክም በቅርቡ የገበያ ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ስትገባ ለመፍትሔ አፈላላጊነት በውጭ አገር በዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርነት ከሚሠሩበት ተመርጠው የተሾሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ ሌሎች አገሮችም ተመሳሳይ ችግሮች ሲገጥሟቸው ተመሳሳይ ዕርምጃ ነው የሚወስዱት፡፡

በኢኮኖሚው ረገድ እነኚህ ሁለት የኃላፊነት ቦታዎች የየትኛውም አገር የመንግሥት መሪዎች፣ ፕሬዚዳንቶችና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ቀኝ እጆች ናቸው፡፡ በሁለቱ ኃላፊነት ቦታዎች ተሿሚዎችም የዲግሪ ዓይነትና መጠን የቆለለ ወይም የዓመታት የሥራ ልምድ ያካበተ ሰው ብቻ ሳይሆን፣ በልዩ መንገድ የሚመረጡ ዕውቀትን ከሥራ ልምድ ጋር ያጣመሩ ሌላው ቀርቶ የተማሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎችና የሠሩባቸው ዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች ሳይቀሩ ለምርጫ እንደ መሥፈርት የሚወሰዱባቸው ናቸው፡፡

በእነኚህ ሁለት ኃላፊነቶች የሚመደቡ ሰዎች ከዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋማትና ከሌሎች አገሮች አቻ ኃላፊዎች ጋር በገንዘብ ኢኮኖሚክስ ቋንቋ መነጋገር፣ ማሳመንና ማመን የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ አለመታደል ሆኖ እኛ ኢትዮጵያውያን በአገርኛ ቋንቋ የጥሬ ገንዘብ ዓይነቶችን በጥሬነት ደረጃ (Liquidity Level) ከፋፍለን ልንናገር እንኳ ባለመቻላችን፣ ስለጥሬ ገንዘብ ኢኮኖሚክስ የምናነበውን ቀርቶ በውጭ አገር ቋንቋ የምንናገረውንና ከአፋችን የወጣውንም በትክክል መረዳታችን ያጠያይቃል፡፡

የቁሳዊ ምርት ኢኮኖሚ የሚለካው በጥሬ ገንዘብ መሆኑ ራሱ በጥሬ ገንዘብና በቁሳዊ ኢኮኖሚ መካከል ያለውን ተዛምዶና መስተጋብር አጥንቶና መርምሮ ማወቅና ማስተካከል፣ ከምንም በላይ  በቅድሚያ ሊሠራ የሚገባው መሆኑን ያመለክታል፡፡ ሥራን የሚፈጥር ጥሬ ገንዘብ ነው፡፡ የሸቀጥ ዋጋን የሚወስን ጥሬ ገንዘብ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ መጣኝን የሚወስንም ጥሬ ገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህም በጥሬ ገንዘብና በቁሳዊ ምርት ኢኮኖሚ መካከል ያለውን ተዛምዶና መስተጋብር ጠንቅቆ ማወቅና ለምርት ዕድገት፣ ለሥራ ፈጠራ፣ ለዋጋ ንረት፣ ለውጭ ምንዛሪ መጣኝ የሚስማማ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ላይ ውሳኔ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ለገጠማት የገበያ ኢኮኖሚ ችግር የክፍላተ ኢኮኖሚዎች አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎችን ለመቀያየር ከመታሰቡም በፊት፣ በጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ (Monetary Policy) ከተለምዶ አሠራር ለመውጣት የእነዚህ ሁለት መሥሪያ ቤቶች የሥራ ኃላፊነትና አደረጃጀት የእስከ ዛሬ ጠንካራ ጎንና ድክመት እንደገና መፈተሽ፣ መተቸት በብዙ የዘርፉ ምሁራን አስተያየት መሰጠትም አለበት፡፡ ሊሾሙላት የሚገባቸው የገንዘብ ሚኒስትሮችና የብሔራዊ ባንክ ገዥዎችም በዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋማት የገንዘብ ኢኮኖሚስት ሆኖ ለረጅም ጊዜ የሠሩ ወይም በታወቀ ዩኒቨርሲቲ የገንዘብ ኢኮኖሚክስ የተማሩና ያስተማሩ መሆን አለባቸው፡፡ ይህን የሚያሟሉ ኢትዮጵያውን በአገር ውስጥ ባይኖሩም እንኳ የተከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል ማምጣት ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ለመቀላቀልና የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየተገደደችና እየተንቀሳቀሰች ያለች አገር እንደመሆኗ ወደፊት ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለሥራ አጥነት፣ ለዋጋ ግሽበት፣ ለውጭ ምንዛሪ መጣኝ  የሚስማማ ጤናማ የገንዘብና የጥሬ ገንዘብ ገበያና የገንዘብና የጥሬ ገንዘብ ዋጋ መፍጠር ይኖርባታል፡፡

የዓለም ኢኮኖሚ አካል ሲኮን የውስጥ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ኢኮኖሚ ሁኔታዎችም ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ በአውሮፓና በእስያ የሸቀጦች ዋጋ ለውጥ ወይም የአሜሪካ ዶላር ከሌሎች አገሮች ጥሬ ገንዘቦች ጋር መመነዛዘሪያ ዋጋ ለውጥ በእኛ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እያደገ መጥቷል ወደፊትም ያድጋል፡፡

የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የውጭ ባንኮች ገብተው እንዲሠሩ እየተገደድን ነው፡፡ ባንኮቹ መጥተው መሥራታቸውና የሚያስተዋውቁት የጥሬ ገንዘብ ዓይነትና ቅንብርን የሚቀይር አዳዲስ ቴክኖሎጂ በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት፣ ዓይነትና መጠን ላይ ምን ለውጥ እንደሚያመጣ አናውቅም፡፡ በቅርቡ በአገር ውስጥ ንግድ ባንኮች እየተሞከሩ ያሉት የስልክና የካርድ ክፍያ መንገዶች፣ ኤቲኤም፣ በልዩ ልዩ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ዓይነትና መጠን ላይ ምን ለውጥ እንዳመጡ እንኳ አላጠናንም፡፡  

ከቁጠባ የባንክ ተቀማጭ በሞባይል ወይም በካርድ የግዥ ክፍያ መፈጸም ከተቻለ፣ በተንቀሳቃሽ የባንክ ተቀማጭ (Demand Deposit ወይም Current Acccount) እና በቁጠባ የባንክ ተቀማጭ (Saving Deposit) ወይም (Saving Account) መካከል ያለው የጥሬነት ደረጃ (Liquidity Level) ልዩነት ትርጉም ስለሚያጣ፣ ልዩ ልዩ የጥሬ ገንዘብ ዓይነቶችን በጥሬነት ደረጃ  መከፋፈል የማይቻል ይሆናል፡፡

ከዚህ በላይ አጠር አድርጌ በሹም ሽሩ ላይ ያቀረብኩት አስተያየት ሹም ሽሩን የሚቃወም ሳይሆን፣ ከሹም ሽሩ በተጨማሪነት ሊሠሩ ይገቡ የነበሩ ለሰሞኑ ሁከት ዋና ምክንያቶች ናቸው ያልኳቸውንና ለወደፊት የኢኮኖሚ ቀውስ እንዳይከሰት መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ የምላቸውን የፖሊሲ ለውጦች ለመጠቆም ነው፡፡

የተከሰተው ችግር የፖሊሲ ሳይሆን የአፈጻጸም ብቻ ነበር ብሎ ለማለትና በአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎችን በመተካት ብቻ ችግሩን ሙሉ በሙሉ አስወግዳለሁ ብሎ ለመተማመን፣ ወይ አሥራ አንድ በመቶ አላደግንም ነበር ወይ ደግሞ አሥራ አንድ በመቶ ማደግ በቂ አልነበረም ብሎ ማመን ያስፈልጋል፡፡ ከመንግሥት ወገን ሁለቱንም ለማለት ድፍረቱ ያለው ሰው ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡

አዲሶቹ ተሿሚዎች በምርታማነታቸው ከተሻሩት ልቀው ከአሥራ አንድ በመቶ በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊፈጥሩ ይችሉ ይሆናል፡፡ ያለ ፖሊሲ ለውጥ የገበያ ኢኮኖሚውን ችግሮች በማስተካከል ሥራ አጥነት፣ የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የብሔራዊ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት ችግሮች ይቀረፋሉ ማለት ግን አይቻልም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው Getachewasfaw240@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡   

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

Trending Articles