በልዑልሰገድ ግርማ
ኅዳር ወር በኢትዮጵያ ታሪክ የተለያዩ በሽታዎችን በማስተናገድ ትታወቃለች፡፡ እ.ኤ.አ. በኅዳር 1535 በቱርክና በየመን ወታደሮች የተደገፉት የኢማም አህመድ ኢብን ኢብራሂም ወታደሮች በወረርሽኝ በሽታ እንደተጠቁ ታሪክ ይዘክራል፡፡ በተመሳሳይ ወር አፄ ቴዎድሮስን ለመዋጋት የመጣው እንግሊዛዊው ጄኔራል ናፒየር ወታደሮቹ በወረርሽኝ በሽታ ተጠቅተዋል፡፡ በኅዳር 1888 ዓ.ም. ጣሊያኖች በከብቶች አማካይነት ተላላፊ በሽታን ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት አገራችን አብዛኛውን የከብት ሀብቷን እንድታጣ አድርገዋል፡፡ ከ1918 ዓ.ም. እስከ 1919 ዓ.ም. ዓለምን ባጠቃው የስፔን ኢንፍሉዌንዛ አገራችን በኅዳር ወር በመጠቃቷ ‹‹የኅዳር በሽታ›› በመባል ይታወቃል፡፡ የንፋስ በሽታ በመባልም ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ሁሌም በየዓመቱ ኅዳር 12 ቀን ቆሻሻን ሰብስቦ በማቃጠል የኅዳር በሽታን እያስታወስነው እንገኛለን፡፡ ይኼ ልማድ ከፍተኛ አገር በቀል ማኅበራዊ እሴት መሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል፡፡
በየዓመቱ ኅዳር 12 ቀን ሁሉም ሰው ቤቱንና አካባቢውን በቋሚነት በማፅዳትና ቆሻሻን በማቃጠል ይታወቃል፡፡ በተለይም አዲስ አበባ በዕለቱ በጭስ ጉም በመታፈን ለዓለም የአየር ብክለት አስተዋፅኦ የምታደርግ ይመስላል፡፡ ይኼ ልምድ እጅግ ጠቃሚ መሆኑ ቢታመንም፣ በዓመት አንድ ቀን ብቻ መሆኑ ግን ጥቅሙን አናሳ ያደርገዋል፡፡ በተለይም አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት በቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ችግር ተተብትባ ባለችበት ወቅት፣ እያንዳንዱ ቀን ኅዳር 12 የሚል ስያሜ ቢሰጠው አይበዛበትም፡፡ የቆሻሻን አላስፈላጊነት በመረዳት የፅዳት ዘመቻው መካሄዱ ቁልፍ ማኅበረሰባዊ ተግባር መሆኑ አያጠራጥርም፡፡
አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አገርን ለአደጋ የሚያጋልጡ የውስጥ ችግሮቹን ለመፍታት የአሥራ አምስት ዓመታት ውዝፍ ሒሳቡን ለማወራረድ ከአንድ ዓመት በላይ ሊወስድ የሚችል እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ መንግሥት የሚታጠነው ወይም የሚታደሰው ትምክህተኝነት፣ ጠባብነትና ኪራይ ሰብሳቢነት የተባሉ ቆሻሻዎቹን ለማፅዳትና ለማቃጠል ነው፡፡ መንግሥት የሕዝብ ተወካይ እንደመሆኑ መጠን በመታጠኑ (በመታደሱ) ሒደት ሕዝብን እንደሚያሳትፍም ቃል ገብቷል፡፡ የመታጠኑ (የመታደሱ) ሒደት አሥራ አምስት ዓመታትን ጠብቆ መሆኑ ግን ተገቢ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ማግሥት ጀምሮ ያስመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ እንዲሁም በ2008 ዓ.ም. በተለያዩ አካባቢዎች በተነሱ የከተማና ከተማ ቀመስ አካባቢዎች ረብሻዎች በመነሳት እያደረጋቸው ያለው ተሃድሶዎች (መታጠኖች) ኢሕአዴግን ‹‹በመከራ ብቻ የሚመከር ፓርቲ›› ያደርገዋል፡፡ ተሃድሶአዊ እንቅስቃሴዎች ዘላቂና ተቋማዊ ባለመሆናቸው ዋጋ እንደሚያስከፍሉ አይተናቸዋል፡፡ የደረሱብን ችግሮች ምንም ዕድገት ካለመመዝገብ ጋር የተያያዙ ሳይሆኑ፣ ዓለም የመሰከረላቸው ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገቶች ከሕዝብ ቁጥር ዕድገትና በየዓመቱ እንደ አሸን ከሚፈላው የተማረ የሰው ኃይል ቁጥር ጋር ባለመመጣጠናቸው ብቻ ነው፡፡ ጠባብነት፣ ትምክህተኝነትና ሙስና ደግሞ ዋነኞቹ የችግሮቹ ማባባሻዎች ናቸው፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ከነበረችበት ዘርፈ ብዙ እርስ በርስ የመቆራቆስ አባዜ ወጥታ የራሷ በሆነ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሞዴል ሆና መንቀሳቀስ ከጀመረች ሁለት ተኩል አሥርት ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ በእነዚህ ጊዜያት አገራችን አካታች የሆነ የሽግግር መንግሥት በመመሥረት፣ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚያውጅ ሕገ መንግሥት በማፅደቅና ተግባራዊ በማድረግ፣ ሥር ሰዶ የነበረውን የድኅነት መጠን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ የተለያዩ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ፣ የውጭ ግንኙነታችንን ከብሔራዊ ደኅንነታችን ጋር በማስተሳሰር፣ የአፍሪካ ቀንድን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ሌት ተቀን በመትጋት፣ የአፍሪካን ጥቅሞች ለማስከበርም በዓለም አቀፍ ደረጃ ድምጿን በማሰማት፣ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ለፍትሐዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም በማስተባበርና በማስተሳሰር፣ እንዲሁም ግድቡን በራሷ አቅም መገንባት በመጀመርና ሌሎችንም ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸውን ሥራዎች በማከናወን በዓለም ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ጥቂት አገሮች ተርታ ለመሠለፍ በቅታለች፡፡
ሆኖም እነኚህ ዓመታት አልጋ ባልጋ ሆነው አላለፉም፡፡ የኦነግ ከሰላማዊ ትግሉ በይፋ መውጣትና ያስከተለው አሰቃቂ ጭፍጨፋ፣ የኤርትራ መንግሥት እብሪተኛ ወረራ፣ የሕወሓት ለሁለት መሰንጠቅ፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተፅዕኖ፣ የድኅረ 1997 ዓ.ም. ምርጫ ምስቅልቅልና የቅርቡ የኦሮሚያና የአማራ ብጥብጦች ካጋጠሙን ችግሮች በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህና ሌሎች ችግሮች መነሻዎቻቸውን ያበረከቱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ትምክህተኝነት፣ ጠባብነት፣ እብሪተኝነት፣ ኢሕገመንግሥታዊ በሆነ መንገድ ሥልጣን መሻት፣ ሙስናና የመልካም አስተዳዳር ዕጦት ጥቂቶቹ አንገራጋጭ ምክንያቶች ሲሆኑ፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ መዋቅራዊ ሽግግር ውስጥ ላሉ አገሮች በብዛት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ናቸው፡፡ በርካታ ከፍተኛ የዕድገት እርከን ላይ የደረሱ አገሮችም ተመሳሳይ ችግሮችን በማሳለፍ ዜጎቻቸው የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ አድርገዋል፡፡
የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ትርምስም በሽግግር ላይ ለምትገኝ አገር አስገራሚ ባይሆንም፣ ይኼንንና ተመሳሳይ ችግሮችን ለመቅረፍ መንግሥትና ሕዝብ እጅና ጓንት ሆነው መጓዝ ይገባቸዋል፡፡ ለእዚህም የችግሮቹን መንስዔ ከሥር መሠረቱ ለይቶ ማወቅና መግባባት የመጀመርያው ተግባር ነው፡፡ በተለያዩ ሚዲያዎች መከታተል እንደተቻለው የሁከቱ መነሻዎች ሁለት ናቸው፡፡ የመልካም አስተዳደር ሙሉ አለመሆኑና ይኼንኑ የሕዝብ ጥያቄ በመጥለፍና የቀለም አብዮትን በማስነሳት የሥልጣን ጥምን፣ እንዲሁም የጠባብነትን አጀንዳን ለማራመድ የሚፈልጉ ኃይሎች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ እዚህ ላይ ደርግ የሕዝብን ጥያቄ በመጥለፉ አገራችን የኋልዮሽ እንድትጓዝ መደረጓን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡
ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ላይ መንግሥት መመሥረት ያስፈለገው በኢትዮጵያ ለዘመናት የተጠራቀሙትን ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመቅረፍና የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት ለማረጋገጥ ሲሆን፣ ለሃያ አምስት ዓመታት በተጓዘበት ጉዞ ላይ ውስጣዊና ውጫዊ ጋሬጣዎችን እየተቋቋመ እዚህ ደርሷል፡፡ እንደ እሳት በሚንቦገቦግ የአፍሪካ ቀንድ አንፃራዊ የሆነ ሰላምን በማስፈንና የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ኢሕአዴግ የሚመሰገን ሲሆን፣ ውስጡን ተብትበው በያዙት ችግሮች ምክንያት ግን በየቀኑ መታጠን ያለበት ፓርቲ መሆኑን አያከራክርም፡፡ በከባድ ውጣ ውረድ ያለፈባቸውን መንገዶች በመጠነኛ ተሃድሶ (መታጠን) ብቻ በማሳለፍ ዘርፈ ብዙ የሆኑ የዕድገት ምንጮችን ጉዞ ወደኋላ አስቀርቷል፡፡ ነገር ግን የሁሉም አስተዋፅኦ እንዳለበት ደግሞ አያጠራጥርም፡፡ የመጣንበት ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሁኔታ እንዳንተማመንና በጎሪጥ እንድንተያይ ማድረጉ፣ የብሔራዊነት ስሜትን የሚፈጥሩ ሥልቶች አለመነደፋቸውና ራስን በራስ ማስተዳደር የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ መርህ በቅጡ አለመረዳት ወይም አጣሞ ማቅረብ ዋና ዋናዎቹ ችግሮች ናቸው፡፡
የኅዳር 12 ቀን የመታጠን ልምድ መነሻ ያደረገው በኅዳር ወር 1918 ዓ.ም የገባው የኅዳር በሽታ ነው፡፡ በመሆኑም የአካባቢ ንፅህና እጅግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ ሁሉም ከየቤቱ ያወጣውን ቆሻሻ በማቃጠል በሽታውን ለማስወገድ ጥረት አድርጓል፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥትም ቤቱን በመጥረግ እያወጣ ያለውን ቆሻሻ እያቃጠለ መሆኑ ጭሱ ምስክር ነው፡፡ ከላይ የተጀመረው የካቢኔ ለውጥም ትምህርትን፣ የሥራ ልምድንና ስኬትን በማጣመር የተደረገ በመሆኑ አዲስ ጅማሮ ሊባል የሚችል ሲሆን፣ ሁሉም በየመስኩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ አንድ ነባር የሕወሓት ታጋይ እንደተናገሩት ምሁራን ሚኒስትሮቹ ስኬታማ ሊሆኑ የሚችሉት ዕውቀት ካላቸው ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰው ስለተማረ ብቻ ስኬታማ ሊሆን እንደማይችል የሚያወሱት እነኚሁ ነባር ታጋይ፣ ለውጥ ለማምጣት ከትምህርትና ከልምድ የተገኘ ዕውቀት ወሳኝ ነው ይሉናል፡፡ ይኼው የካቢኔ አሰያየም እየወረደ እስከ ቀበሌ እንደሚደርስም ተገልጾልናል፡፡ ‹‹መንግሥት ሲታጠን እንዲህ ነው›› ማለት ነው፡፡
መንግሥት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ አይታጠንም፡፡ በአብዛኛው ከአመለካከት ለውጥ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ጊዜ መፍጀቱ አይቀሬ ነው፡፡ ለሃያ አምስት ዓመታት የተከማቸ ቆሻሻ በአንድ ቀን አይቃጠልም፡፡ ቆሻሻውን ከደህናው የመለየት ሥራም እንዲሁ ጊዜ የሚፈጅ ነገር ነው፡፡ ዋናው ነገር በዕቅድ መጓዙ ነው፡፡ መታጠኑ እንዳለ ሆኖ የተጀመሩ የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ መንገዶችን ማስፋት ዋናው ሥራ ነው፡፡ ይኼንን ከሚያኮላሹ የውጭ ኃይሎችና አገርን መበታተን የስኬታቸው መንገድ አድርገው የሚወስዱትን የውስጥ ሴረኞችንም ቢሆን መካላከል ወሳኝ ሥራ ነው የሚሆነው፡፡
መንግሥት መታጠን የሚያስፈልገው ብቸኛው አካል አይደለም፡፡ በቢሊዮኖች በሚቆጠር ገንዘብ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በማባበል የሕዝብ ፕሮጀክቶች ከሚገባው የጥራት ደረጃ በታች እንዲከናወኑና ረዥም ጊዜ በመፍጀት ጥቅም እንዳይገኝባቸው በማድረግ የግሉ ሴክተር አባላት ዋነኛ ተዋናይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ልምድ የወሰደችባቸው ኮሪያና ታይዋን የግል ባለሀብቶች በመጀመርያዎቹ የዕድገት ዓመታት እንኳን የገንዘብ ጥማቸውን ለማርካት ሲሉ በሕዝብ ፕሮጀክቶች ጥራትና ጊዜ ላይ አይደራደሩም ነበር፡፡ በመሆኑም ብሔራዊ ዕድገትንና ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ አልነበሩም፡፡ ሆኖም እነዚህን ኪራይ ሰብሳቢዎች ባለማቋረጥ በመታገል አገሮቹ አሁን የደረሱበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ መታጠን (መታደስ) ማለትም ‹‹ያለማቋረጥ መታገል›› ማለት ነው፡፡
የመንግሥትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መታጠን ከሚገባቸው መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ትምህርትን እንደ መሣሪያ ከማስታጠቅ ይልቅ ጥርጣሬንና ጥላቻን የሚዘሩ መምህራንን በጉያቸው አቅፈው የሚገኙት በርካታ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ መምህራን የተሠለፉበትን የትምህርት መስክ በሚገባ ማወቃቸውም አጠራጣሪ ነው፡፡ የትምህርትን ውጤት በዘርና በፖለቲካ አመለካከት የሚለኩም አሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ከእነዚህ የትምህርት ተቋማት የሚወጡ ወጣት ባለሙያዎችም የተበረዘ ዕውቀት በመያዝ በአጭር ጊዜ ለመክበር በሚደረግ ጥረት ሲባዝኑ ይታያሉ፡፡ የተቋማቱ ስኬታማነት የተመሠረተው በሚያስመርቋቸው ተማሪዎች ብዛት ነው፡፡ የጥራቱ ነገር ለማን እንደተተወ አይታወቅም፡፡ የዲፓርትመንት አመዳደብ፣ የሬጅስትራር አገልግሎት፣ የመምህራን ዝግጅት፣ የተማሪዎች አቀባበልና ተያያዥ ጉዳዮች አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተማሪዎች የሚሞሉ መምህራንን መገምገሚያ ቅጾች በዘረኝነት ላይ የተመሠረቱ ሆነው ይታያሉ፡፡ ብቃት የሌለውን መምህር የወንዜ ልጅ ነው በማለት ብቻ ዓይኔን ግንባር ያድርገው በማለት የመጠቀ ምሁር አድርገው ያቀርቡታል፡፡ የዲፓርትመንት ኃላፊዎችና የፋካልቲ ዲኖችም አልፎ አልፎ በወዳጅነት ሲሾሙ ይታያል፡፡ በአንድ የግል ኮሌጅ የሲቪክ መምህር የነበረ ወዳጄ የተማሪዎችን ግሬድ ካስገባ በኋላ ተጠርቶ የወደቁ ተማሪዎችን ግሬድ እንዲያስተካክልና እንዲፈርም ይጠይቁታል፡፡ በእዚህ ክፉኛ የደነገጠው ወዳጄ ግሬዱን ራሳቸው እንደገና እንዲሠሩትና እንዲፈርሙበት በመንገር ከተቋሙ ጋር የነበረውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አቁሟል፡፡ በእዚህ መልኩ ከከፍተኛ የትምህርት ቤት ተቋማት የሚወጡ ምሩቃን ምን ዓይነት አገልጋይ እንደሚሆኑ መገመት ይቻላል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት የፅድቅም የኩነኔም ቦታዎች ናቸው፡፡ ተቋማቱ ምዕመናኖቻቸውን መንፈሳዊ ምግብ እየመገቡ ከክፉ ሥራ እንዲርቁ በማድረግ ለመንግሥተ ሰማያት እንዲበቁ በርትተው እንደሚሠሩ ሁሉ ስኳር በብዛት የሚላስባቸው ቦታዎችም ናቸው፡፡ በአገራችን የሚገኙ በርካታ የሃይማኖት ተቋማትም ሊታጠኑና በየራሳቸው ሃይማኖታዊ ፍልስፍና ያለማቋረጥ ፀሎት የሚገባቸው ናቸው፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ አማኝ እንደመሆኑ፣ የሃይማኖት ተቋማት የሚኖራቸው ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም፡፡ በእነዚሁ ተቋማት ውስጥ ዓለማዊ የሆነው የገንዘብ ፍቅር በመበርታቱና ይኼንኑ ለመሸፈን በሚደረግ ጥረት ትምክህተኛነትና ጠባብነት ሰተት ብለው ገብተው ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ የበርካቶች ሃይማኖቶች መገኛ እንደመሆኗ መጠን መቻቻል ወሳኙ አብሮ የመሆኛ ሥልት እንደመሆኑ በጥንቃቄ ሊኬድበት ይገባል፡፡ ለእዚህም የተቋማቱ የሥራ መሪዎች ዓለማዊና መንፈሳዊ ተሃድሶ (መታጠን) ያስፈልጋቸዋል፡፡
መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መንግሥት ባልተሰማራባቸው የሥራ መስኮች እንዲሁም በክፍተቶች ውስጥ በመግባት ሕዝብንና መንግሥትን ለማገዝ የተቋቋሙ አካላት ናቸው፡፡ በሁሉም ባይሆን በእነዚሁ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ አመራሮች የግል ጥቅማቸውን ሲያካብቱ ይታያል፡፡ መንግሥት የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያወጣውን የ70 - 30 ደንብ አምርረው ይቃወማሉ፡፡ ይኼ ችግር ወደ ሲቪክ ተቋማት ሲመጣ ደግሞ ጉዳቱ እጥፍ ድርብ ነው፡፡ ገንዘብን ከማጭበርበር በላይ ትምክህተኝነትንና ጠባብነትን የሚያስተናግዱ የእነዚሁ ተቋማት መሪዎች ቤት ይቁጠራቸው፡፡ የሚታገሏቸውን ኢፍትሐዊነት፣ ኢዴሞክራሲያዊነት፣ የፆታ መድሎዎች፣ ሙስና፣ ጠባብነትንና ትምክህተኝነትን በየከረባታቸው ሥር ደብቀው ‹‹ሙያ በልብ ነው›› የሚሉ እንዲሁ በርካቶች ናቸው፡፡ እነዚህ መታጠንም መጠረግም የሚገባቸው ናቸው፡፡
የግሉ የሚዲያ ዘርፍም ሌላው ሊታጠን የሚገባው የሙያ ዘርፍ ነው፡፡ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን የሚገባቸውን ባለመወጣታቸው መታጠን የሚገባቸው ቢሆንም፣ እንደግሉ የሚዲያ ዘርፍ በተለይም እንደ ግሉ ፕሬስ ጥፋታቸው የከፋ አይደለም፡፡ ለማንም ሳይወግኑ ወይም ውግንናቸውን ለሕዝብ ለማድረግ ለእውነትና ለእውነት ብቻ መቆም ሲገባቸው ሕዝብን በመከፋፈልና ጥላቻን በመዝራት የሚታወቁ የግሉ ፕሬስ ወገኖች ተፈጥረው ሲከስሙ ተመልክተናል፡፡ የግሉ ፕሬስ የተለያዩ አመለካከቶች ማስተናገጃ እንጂ ፅንፍ በመያዝ የግል ዓላማን ማሳኪያ መሣሪያ አይደለም፡፡ በሩዋንዳ የተከሰተውን የዘር ጭፍጨፋ የግሉ የሚዲያ ዘርፍ ምን ያህል እንዳከፋው የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ተመሳሳይ ጉዳዮች እንዳይከሰቱ ልጓም ማበጀቱ ምንም ዓይነት ክፋት የለውም፡፡
በአገራችን ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሥርተዋል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች (አብዛኛዎቹ) ዋና ዓላማቸው በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የምርጫ ውድድር በማድረግ ለሥልጣን መብቃት ሳይሆን፣ ኢሕአዴግን ከሥልጣን ማውረድ ነው፡፡ ገዢውን ፓርቲ ዕለት በዕለት በመከታተል የሚሠራቸውን ህፀፆች በማሳየት ለሕዝብ የሚጠቅም ሐሳብና አማራጭ ማቅረብ ሲገባቸው፣ ከአስተሳሰብና ከዓላማ ችግር በመነጨ የረባ ነገር ሳያከናውኑ እየባዘኑ ይገኛሉ፡፡ የምርጫ ወቅትን ብቻ ጠብቀው የሚያደርጓት መፍጨርጨር ለምን ሌላኛው ምርጫ እስከሚመጣ እንደማይቀጥል ግልጽ አይደለም፡፡ ምናልባትም የበጀት ዕጥረት የሚኖርባቸው ይመስላል፡፡ የበጀት፣ የአመለካከትና የስትራቴጂ ጉድለቶቻቸውን አሟልተው እስከሚገኙ ግን ኢትዮጵያ የመድበለ ፖለቲካ ፓርቲ ሥርዓት ምች እንደመታት ይቀራል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተግባር፣ ፕሮግራም፣ ፖሊሲና አካሄድ ያልገባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት በብዛት የሚገኙበት አገር ኢትዮጵያ ሳትሆን አትቀርም፡፡ የትምህርትና ሥልጠና ዕጥረት ለክህሎቱ አለመኖር አስተዋጽኦ አለው፡፡
ከእነዚህ ችግሮችም ባሻገር ኢሕአዴግን ለማስወገድ ብለው ከሻዕቢያ ጋር ወዳጅነት የፈጠሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ነን ባዮችም አሉ፡፡ ኢትዮጵያን ለማደፍረስ ሌት ተቀን ከአሸባሪዎች ጋር ከሚሠራ ቡድን ጋር አብሮ መገኘት አሸባሪነት እንጂ ሌላ ምን ይባላል? ፍትሐዊ ሐሳብና ምክንያታዊነት ናፍቆናል፡፡ ሕዝቡን በዘር መከፋፈል፣ ከፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር መተባበር፣ ኢትዮጵያ ብድርም ሆነ ዕርዳታ እንዳታገኝ ለጋሾችን መወትወት፣ ታጣቂ ከሆኑ ጽንፈኞች ጋር አብሮ መሠለፍ፣ ብሔራዊ ፕሮጀክቶችን ማጥላላትና በመሳሰሉት ሁኔታዎች መጠለፋቸው ከርመውም እንጭጭ መሆናቸውን ያሳብቅባቸዋል፡፡ ሁሉም እንዲህ ናቸው ማለት ግን አይደለም፡፡ በፕሮግራምና በመልካም አስተዳደር ዕጦት የሚሰቃዩት እነኚሁ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ኢሕኢዴግን ለማብጠልጠል ግን ቁጥር አንድ ናቸው፡፡ ኢሕአዴግን ከሥልጣን ማስወገድ ብቸኛው ፕሮግራማቸውና አጀንዳቸው የሆኑ በርካቶች ናቸው፡፡ ከተመረጥኩኝ በኃላ መራጮቼን አማክሬ ፕሮግራም እቀርፃለሁ ሲሉ የተደመጡም አሉ፡፡ የሚቀለድበት ክፍለ ዘመን ላይ አለመሆናቸውን አያውቁትም? በየደቂቃው መታጠን አለባቸው፡፡
መታጠን ያለባቸው ከላይ የተጠቀሱት ብቻ አይደሉም፡፡ ብንዘረዝራቸው በርካቶች ናቸው፡፡ ዋናው ጥያቄ ካልታጠንን ምን እንሆናለን? የሚለው ነው፡፡ ካልታጠንን የዓለም ራስ ሆነን እንደነበርን ሁሉ የዓለም ጭራ እንሆናለን፡፡ አሁን የጀመርነው የዕድገት ጉዞ በአጭሩ ይቀጫል፡፡ በአካባቢያችንም ሆነ በዓለም ዙሪያ የምናደርገው ሰላምን የማስፈን፣ የአየር ብክለትን የመዋጋትና ዘላቂ ልማትን የማምጣት ውጥናችን ወረቀት ላይ ብቻ ይቀራል፡፡ በዘመናችን የራሳችንን አሻራ የማንተው እንሆናለን፡፡ የውጭና የውስጥ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች መፈንጫ እንሆናለን፡፡ በመሆኑም የተጀመረው ተሃድሶ ለመንግሥት (ለኢሕአዴግ) ብቻ ሳይሆን ሁሉም እንደሚመለከተው አውቆ በፍጥነት መንገድ ላይ ጉዞውን መጀመር አለበት፡፡ ከሁሉም በላይ የአመለካከት ለውጥ ላይ መሥራት ዋናው የመታጠን ዘንግ መሆን ይገባዋል፡፡ የመንግሥትም ሆነ የግሉ ሚድያ የመታጠን አስተሳሰቦችን ማቀንቀን አለባቸው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ለውጡን (መታጠኑን) መታደሱን የማያቋርጥ ማድረግ ነው፡፡
ያለንበት ዘመን ዓለም እየደረሰችበት ያለውን የቴክኖሎጂ የዕድገት ደረጃ እግር በእግር በመከተል የአገልግሎታችን፣ የግብርናችንንና እንዲሁም የኢንዱስትሪ ዕድገታችንን የምናዘምንበት፣ ዜጎቻችንን በወቅቱ ዕውቀትና ክህሎት የምናስታጥቅበት፣ ከዓለም አቀፍ የምርት ሥርዓት ጋር ለመጣጣም የትብብር ደረጃችንን እጅግ ከፍ የምናደርግበት፣ እንደ የአየር ንብረት ለውጥ ካሉ ድንበር የለሽ ዓለም አቀፋዊ ችግሮችን ለመቋቋም ልዩ ጥረት የምናደርግበት፣ ከሕዝብ ብዛት መጨመር ጋር ተያይዞ የሚመጡ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት የማያቋርጥ ጥረት የምናደርግበት ጊዜ ነው፡፡ ይኼ ሲሆን ብቻ ነው ዘላቂ ልማት ማምጣት የሚቻለው፡፡
ዘላቂ ዕድገትን ለማምጣት ዛሬ ላይ ያለና ለስኬት የሚያበቃን የለውጥ ስትራቴጂን የራስ በማድረግ የዕድገት መሰላሉን መውጣት ይቻላል፡፡ ለዚህም ዜጎች ለተለዋዋጩ ዓለም ራሳቸውን በማዘጋጀት ተራራውን መውጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም ታዳጊ አገሮች ፍትሐዊ ዕድገትን ለሕዝቦቻቸው ለማጎናፀፍ ዘርፈ ብዙ መዋቅራዊ ለውጦችን ማስፋፋት አለባቸው፡፡
ለእዚህም ዓለም እየተጓዘበት ባለበት መንገድ ራስን ማስገባት የግዴታ ነው፡፡ ከድኅነት ለመውጣትም ራስን ከጊዜው የዓለም ሁኔታ ጋር ማስማማት የማያቋርጥ እንቅስቃሴ በሆነበት በእዚህ ዘመን፣ ባለፈውና በተከናወነው ታሪክ በትዝታና በቁዘማ ቂም በቀልን እያኘኩ መኖር የትም አያደርስም፡፡
አገራዊ ፖሊሲዎቻችን ከዓለም አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታዎችና እንደ አየር ንብረት ለውጥ ካሉ ድንበር የለሽ ተፅዕኖ አድራጊዎች ጋር የተጣጣመ መሆን አለበት፡፡ ከላይ የተጠቀሱት አንገራጋጮች መስመር እየያዙና እየሰከኑ ሲሄዱ ዜጎች በሰላምና በደስታ መግባትና መውጣት ይጀምራሉ፡፡ ለአገራቸውና ለወደፊቱ ትውልድም የተሻለ ነገር ጥለው ያልፋሉ፡፡ በመሆኑም አንገራጋጮቹን በማንገራገጭ ሽግግራዊ መንገራገጩን ጤናማ ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው መፍትሔ ውይይት፣ ውይይትና ውይይት ብቻ ናቸው፡፡ መታደስ (መታጠን) የማያቋርጥ እንቅስቃሴ መሆን አለበት፡፡
ከአዘጋጁ፡-ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው leulsegedg@yahoo.com. ማግኘት ይቻላል፡፡
