በደጀኔ አሰፋ ዳ.
እንደምን ሰነበታችሁ? በአካዳሚክ ዓለሙም ሆነ በፕሮግራም ቀረፃና ትግበራ በተሰማሩ ምሁራን ዘንድ ታዳጊ ማን ነው ወጣት የሚባሉትስ ከስንት እስከ ስንት ዓመት ዕድሜ የምላቸው ናቸው? የሚሉት ጥያቄዎች አሁንም ድረስ አከራካሪ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የዕድሜ ወሰኑም በየአገሮቹና አኅጉራት በሚወጡ ቻርተሮች ከመለያየቱ ባሻገር፣ እንደየ ተቋማቱም ልዩነት አለው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአገራችን አጠቃላይ ሕዝብ ብዛት የወጣቱ ቁጥር ታዳጊዎችን ጨምሮ ከ45 በመቶ በላይ እንደሆነ በአሁኑ ወቅት እየወጡ ያሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይኼም አገራችን ኢትዮጵያ የወጣት አገር ናት የሚያስብል ሁኔታ ነው፡፡ እሰይ! እንኳንም የወጣት አገር ሆነች! ምክንያቱም ወጣት ማለት ያልተነካ ኃይል ነው፣ እምቅ ሀብት ነው፣ የአገር ተስፋ የአገር ተረካቢ ነው … ወዘተ፡፡ ‹‹ወጣት የነብር ጣት›› እንዲሉ! የወጣት ትርጉም ይኼ ሆኖ ሳለ በአገራችን በተለይም በመንግሥት ዘንድ ወጣትን በተመለከተ በደህናው ጊዜና በአስቸጋሪ ወቅቶች እየተሰጡ ያሉ ስሞችና አስተያየቶች እርስ በርስ የሚጣረሱ ከመሆናቸው በላይ ከዚህ የተለየም ሆኖ የሚስተዋልበት ሁኔታ አለ፡፡ የዚህ አጭር መጣጥፍ ዓላማም ይኼንን ጉዳይ ‹‹በወፍ በረር›› እየዳሰሰ ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ውጤትም በተዋረድ ለማሳየት ነው፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች አገሮች ሁሉ የተለያዩ ሥርዓቶችን አስተናግዳለች፡፡ ብዙ ታሪክም ያላት አገር ናት፡፡ የወጣቱም እንዲሁ፡፡ በአገሪቱ በተከሰቱ ዋና ዋና ታሪካዊ ክስተቶች የወጣቱ ሚና ጉልህ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡ ምንም እንኳን በኢኮኖሚው ዘርፍ የመሪነት ሚና እንዳይጫወት በአገሪቱ የነበረው አስከፊ ድህነትና ሌሎች ብርቱ ተግዳሮቶች ተጭነውት የነበረ ቢሆንም፣ እነዚህን ሁኔታዎች ለመለወጥ ግን አንድም ቀን አልቦዘነም፡፡ በተለይም በፖለቲካውና በማኅበራዊ ዘርፎች የሾፌሩን ቦታ በመያዝ በነፍሱ ተወራርዶ በሕይወቱ ታላቅ ተጋድሎን እየታገለ አሌ የማይባል መስዋዕትነትን ከፍሏል፡፡ ያ ትውልድ በኢትዮጵያ! ከታሪክ የምንረዳውና አንድ በጋራ የምንስማማበት ሀቅ ቢኖር በየትኛውም ዘመን የነበረው የአገሪቱ ወጣት ለከርሱ ያደረ ራስ ወዳድ እንዳልነበር ነው፡፡ ይልቅ ዘር፣ ነገድ ሳይለይ ለተጨቆነው ጭሰኛ፣ ላብ አደር፣ ለተበዘበዘው፣ ለተረገጠው፣ መብቱ ላልተከበረለት የትኛውም የአገሩ ሕዝብ የቆመ፣ የታገለና ያታገለ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ወጣት የራሱን ዳቦ ለማወፈር የታገለ አይመስለኝም፡፡ ለዚህ እውነት እንደ ማስረጃነት የሚያገለግሉን ታጋዮች በዙሪያችን እንደ ደመና ሳይሆን በተጨባጭ በሕይወት አሉ፡፡ ካስፈለገ እነሱ ይናገሩ፣ ካልሆነም የተሰውት ታሪካቸው ድምፅ አውጥቶ ይመሰክራል፡፡
እንደ አለመታደል ሆኖ ባለፈው የወታደራዊ ደርግ ሥርዓት ወጣቱ ‹‹ብሔራዊ ወታደር” ከመሆን የዘለለ ዕድል ፈንታ አልነበረውም፡፡ በዘመኑ ወጣት ማለት ወታደር፣ ወታደር ማለት ወጣት እንደሆነ ሊታሰብ በሚችል ደረጃ በዩኒቨርሲቲ ያሉ ወጣቶችን ጭምር ወታደር ለማድረግ የወቅቱ ፕሬዚዳንትና ካድሬዎቻቸው ምን ዓይነት ማራኪና አማላይ ዲስኩር ያደርጉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ወጣቱም “ክብር ከብር ይበልጣል” በሚል እሳቤ ይመስላል ዩኒቨርሲቲውን ጥሎ ወደ ብላቴ ያቀናው፡፡ በአጠቃላይ በዘመኑ ስንት ወጣት ረገፈ? ስንቱስ ህልሙ ተኮላሸ? ይኼም ቢሆን እንኳን ያመነበት በውዴታ ያላመነበት በግዴታም ቢሆን ለአገር እንጂ ለዳቦ የተከፈለ አልነበረም፡፡ ያለፈው ታሪክ አሳዛኝ ቢሆንም፡፡
እነዚህን እንደ መግቢያ ስጠቅስ ታሪክን የኋሊት ለመተረክ ሳይሆን፣ ባለፉት ሥርዓቶች የነበሩ መንግሥታት ምንም እንኳን እንደ ተመልካቹ ጥሩም ባይባሉ መጥፎውን ወደ ጎን ትተን ለወጣቱ የነበራቸውን ቦታና ክብር ለማሳየት ነው፡፡ በአፄውም ዘመን ወጣቱ በተለይም ተማሪው ምንኛ ይከበር እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ሆኖም በአንዳንዶቻችን ዘንድ ያለፉት መንግሥታት ለራሳቸው ጥቅም እንጂ ለወጣቱ አስበው አልነበረም የሚል ሐሳብ ሊኖር እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ እዚህ ላይ ግን ማሳየት የተፈለገው ዋና ጉዳይ ወጣቱን የሚያዩበትን ዕይታ ብቻ ነው፡፡ ካስፈለገም ግን ለራሳቸው ጥቅምም እንኳን ቢሆን (ለጥሩም ይሁን ለመጥፎ) ወጣቱን ማነሳሳትና መጠቀም ከቻሉ ጉብዝና እንጂ ሌላ ሊባል የሚችል አይመስለኝም፡፡
ከዚህ አንፃር ወጣቱን በተመለከተ አሁን ባለው መንግሥታችን በየወቅቱ እየተንፀባረቀ ያለው የተለያየ አመለካከት እንዴት ይመዘናል? ምን ዓይነትስ ውጤት ይኖረዋል? የሚለውን ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ በተለይም በደህና ጊዜያት ምርጫን ጨምሮ መንግሥት ስለወጣቱ የሚናገረው ለምሳሌ ወጣቱ የልማት ኃይል እንደሆነ፣ ያለ ወጣቱ ተሳትፎ አገር ማደግ እንደማትችል… ወዘተ ሲገልጽ ደስ እንደምንሰኝ ሁሉ በአንፃሩ አገሪቱ የሆነ አጣብቂኝ ጊዜ ካሳለፈች በኋላ ስለወጣቱ የሚነዙ ደስ የማይሉ ዲስኩሮችና መጠሪያ ስሞች እንደ ገደል ማሚቱ አንዱ ካንዱ እየተቀባበሉ ወጣቱን ሲወቅጡት ማየት እንዴት ያማል መሰላችሁ? መቼስ አገር ሲባል ሺሕ ተሚሊዮን መልካም አጋጣሚዎች ቢኖሩትም ሺሕ ተቢሊዮን ተግዳሮቶች አያጡትም፡፡ መንግሥትም ጥቂት የሚባሉትን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም ህልቆ መሳፍርት የሌላቸውን ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ይጥራል፡፡ በእዚህ ረገድ ወጣቱ አገሪቱ ካላት መልካም አጋጣሚዎች አንዱ እንደሆነ ሊታሰብ የሚገባ ይሆናል፡፡ ለዚህም ይመስለኛል መንግሥት በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወጣትን በሚመለከት ራሳቸውን የቻሉ ፖሊሲዎችን እየቀረፀ ለመተግበር እየሞከረ ያለው፡፡ ሌሎችም ጥቂት ማሳያዎች ይኖራሉ፡፡ አሁን የተመደበውን 10 ቢሊዮን ብር ጨምሮ ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ ጅምሮች በቂ እንዳልሆኑ ቢታወቅም እንደ መልካም ጅምር ሊያድጉና ሊበረታቱ የሚገባቸው እንደሆኑ ግን ዕሙን ነው፡፡
ይኼ ሆኖ ሳለ ወጣቱን በሚመለከት ከሚሰነዘሩ አስተያየቶችና ስሞች መካከል ለእኔ አሳዛኝ ሆነው ካገኘኋቸው መካከል ሁለቱን ብቻ ለንፅፅር በሚያመች መልኩ በከተማ ላለው ወጣት የወጣለት ስምና በገጠር ወይም በክፍለ አገር ላለው ወጣት የተመረጠለትን የዳቦ ስም እጠቅሳለሁ፡፡ የመጀመርያው ስም ምርጫ “1997 ዓ.ም.”ን ተከትሎ በተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኘው ወጣት የወጣለት ‹‹የወል ስም›› ነው፡፡ ‹‹አደገኛ ቦዘኔ››!በእርግጥ ይኼ መጠሪያ ሁለት ቃላትን ይዟል፡፡ ቅፅል የሆነው ‹‹አደገኛ›› የሚለውንና ስም (Noun) የሆነውን ‹‹ቦዘኔ›› የሚለውን፡፡ ከእዚህ መረዳት የሚቻለው መንግሥት በአዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ‹‹ቦዘኔ›› ወይም ሥራ ፈት አሊያም ሥራ አጥ እንዳለ ያውቅ ነበር ማለት ነው፡፡ ቢያውቅም ግን ቦዘኔነትን ለማስቀረት በቂ ጥረት ሲያደርግ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ቦዘኔ ተብሎ የተፈረጀው በፖለቲካ አነጋገር ለሥርዓቱ አደጋ በሚሆን ደረጃ ወደ አደገኝነት እስካልተሸጋገረ ድረስ እንደማለት ያስመስልበታል፡፡ ሊያስጨንቀው የሚገባው ግን ቦዘኔነትን እንዴት ማስወገድ (መቀነስ) እንዳለበት ነበር፡፡
ለዚያም ይመስላል ወጣቱ “ቦዘኔ” መሆኑ፣ መደረጉ ወይም መባሉ ሳያንሰው “አደገኛ ቦዘኔ” የሚል ድሪቶን የተከናነበው፡፡ በዚህም ስንት ወጣት አዘነ፣ ሞራሉ ተጎዳ፣ ስንቱስ ስለ አገሩ ያለውን አመለካከት ለወጠ … ወዘተ ቤት ይቁጠረው፡፡ እሺ… መንግሥት የወጣቱን መጎዳት ወደ ጎን ቢተወውና ከቁብም ባይቆጥረው ይኼን “አደገኛ ቦዘኔ” የሚለውን ቃል ግን ሌሎች አገር በቀል ፓርቲዎች እንዴት ተጠቀሙበት የሚለውን እንኳን እንደ ገዥ ፓርቲ ምንም ትምህርት የወሰደበት አይመስልም፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ ዓይነት አመለካከት በወጣቱ ሰብዕና ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ አለው የሚል ጥናት ቢሠራ ምንኛ ደስ ባለኝ፡፡ እንደኔ ግምት ግን “አደገኛ ቦዘኔ” ከሚለው መጠሪያ በኃላ የሥራ አጥ ቁጥር ያሻቀበ ይመስለኛል፡፡ ‹ላይክ አትራክትስ ላይክ› እንዲሉ! በመጽሐፍ ቅዱስም በጥብቅ ከተከለከሉ ስድቦች (በተለይም ሕፃናትና ወጣቶች እንዳይሰደቡ) መካከል “ደደብ” አትበል የሚለው ነው፡፡ ለምሳሌ ልጅህን ዛሬ “ደደብ” ብትለው ነገ ስማርት “ደደብ” ወይም ሰቃይ “ደደብ” ሆኖ ታገኘዋለህ እንደ ማለት ነው፡፡ እኛ ደግሞ ስማርት ፎን እንጂ ‹‹ስማርት …›› አንሻም፡፡
ሌላኛው የጅምላ ፍረጃ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት ተከትሎ በክልልና በገጠር ላሉ ወጣቶች የወጣላቸው መጠሪያ ነው፡፡ የጥፋት ኃይል፣ የኤርትራ ተላላኪ፣ የጥፋት አጀንዳ ተሸካሚ፤… ወዘተ፡፡ “አደገኛ ቦዘኔ” ከሚለው ይልቅ ይኼኛውን የከፋ የሚያደርገው የውጭ ኃይሎች ከርቀት ሆነው የሚያበሩትና የሚያጠፉት እንጂ በራሱ የሚያስብና የሚያመዛዝን አይደለም የሚል አንድምታ ስላለው ነው፡፡ ይኼ ደግሞ እንዴት ጎጂ እንደሆነ አትጠይቁኝ፡፡ ወጣቱ አመዛዛኝ አይደለም ዝም ብሎ የሚነዳ ነው ተብሎ ከታመነበት ደግሞ ይኼ አባባል ራሱ መንግሥትን በሌላ መንገድ ተጠያቂ የሚያደርገው ይሆናል፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት ወጣት በዚህ ዘመን ለመፈጠሩ ከሥርዓቱ የበለጠ ተጠያቂ የሚሆን አለ ብየ አላስብም፡፡
አንድን ሰው አንተ ተሳስተሃልና ከመንገድህ ተመለስ ብሎ መምከርም ሆነ መገሰፅ ያባት ነው፡፡ መንግሥትም የሕዝብ አባት ነውና መገሰፅ፣ መምከር፣ ማሰር፣ ማስተማር፣ ወዘተ የሚቻልበት ሕገ መንግሥታዊ መብትም ግዴታም አለበት፡፡ ታዲያ ይኼን ሁሉ ማድረግ የሚችልበት ሥልጣንና አቅም በእጁ እያለው በጅምላ ለዚያውም አሉታዊ አንድምታ ባለው ሁኔታ ልጆቹን ስለምን ይጠራቸዋል፡፡ ለምሳሌ ከግርግሩ በኃላ በዚህ ዓመት የመጀመርያ የፓርላማ ስብሰባ ወቅት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ወጣቱን በሚመለከት የተናገሩትን ንግግርም ሆነ ከዚያ ቀጥሎ የሰማኋቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክቶች፣ ብሎም ሌሎች ጎምቱ ባለሥልጣናት በየሚዲያው ሲናገሩ የነበሩት ነገር ልቤን አስከፍቶታል፡፡ ጠቅለል አድርጌ ላቅርብው የሁሉም ንግግር አብዛኛው ወጣቱ የኢኮኖሚ ችግር እንዳለበትና ሥራ አጥነት እንደጨመረ ያሳይ ነበር፡፡ ይኼንንም ክፍተት የውጭ የጥፋት ኃይሎች ወጣቱን በገንዘብ እየደለሉ የጥፋት ተልዕኮን እንዳሸከሙትና የእነሱ ተላላኪ፣… ወዘተ እንደሆነ ያትታል፡፡ ለዚህም ክቡር ፕሬዚዳንቱ፣ “ለወጣቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ የሚሆን 10 ቢሊዮን ብር መድበናል፤” ብለው ተናገሩ፡፡ እዚህ ላይ መንግሥት ሊመልሳቸው የሚገቡ ጥያቄዎችን ያስነሳል፡፡ እነኝህም፡-
1ኛ) ይኼ 10 ቢሊዮን ብር የተበጀተው የወጣቱ ችግር የኢኮኖሚ ችግር ብቻ እንደሆነ በጥናት ተረጋግጦ ለዚያ ማስፈጸሚያ የሚሆን ነው? ወይስ…
2ኛ) የውጭ ኃይሎች ወጣቱን በብር ስለገዙት (ስለደለሉት) እኔስ ከማን አንሼ ብሎ መንግሥት አቅም እንዳለው ለማሳየትና ወጣቱን በበጀት ለማባበል? ወይስ….
3ኛ) የጥፋት ኃይል፣ ተላላኪ፣ ተሸካሚ፣ … ወዘተ በሚል አመለካከት ወጣቱን እያየንና የወጣቱን ሞራልና ሰብዕና እየነካን በዚህ በጀት ተፈላጊውን ለውጥ ማምጣት እንችላለን? የሚሉትን ጥያቄዎች ያጠቃልላል፡፡
ለእነዚህ ጥያቄዎች መልሶች ምንም ይሁን ምን ከኮሙዩኒኬሽን አንፃር ግን መንግሥት በብዙ መንገድ የሚታዩ ግልጽ ክፍተቶች እንዳሉበት ከቀድሞ ጊዜያት ጀምሮ ይስተዋላል፡፡ ለአብነት የአክሱም ሐውልትን፣ ሰንደቅ ዓላማን፣ የፖለቲካ ታማኝነትን፣ የኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ ጥያቄን (ሕዝብ ስል ወይም ወጣቱ ስል ቁጥሩን አይገልጽም)፤… ወዘተ በሚመለከቱ ጉዳዮች መንግሥት የገለጽበት ሁኔታ (ትክክል ናቸው ተብሎ በፓርቲው ቢታመን እንኳን) ትክክል (አዋጭ) ነበር ማለት አያስደፍርም፡፡ ምክንያቱም ለአብዛኛው ሕዝብ በሚመጥን፣ ሊረዳው በሚችል፣ አሊያም በሚያሳምንና በተገቢው ክብር የቀረቡ ባለመሆናቸው ቅሬታን መፍጠራቸው አልቀረምና ነው፡፡ ከእዚህ አንፃር መንግሥት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበና በሕዝቡ ዘንድ መልካም ስሜትን ሊፈጥር በሚችል መልኩ ተግባቦትን መፍጠር የሚችሉ ጎበዝ (ንቁ) የተግባቦት አመቻቾች (Spin Doctors) እንደሚሏቸው ዓይነት ሰዎችም ሆኑ ተቋማት ዕጦት ያለበት ይመስላል፡፡ ቢያንስ እውነት የሆነን ነገር እንኳን የሚገልጽበትም ሆነ ሕዝቡን የሚያስረዳበት ቋንቋና መንገድ የበለጠ የሚያናድድ እንጂ የሚያረጋጋ ሲሆን አይስተዋልም፡፡
አንድ ምሳሌ ልጥቀስና ልጨርስ፡፡ ‹‹እነሆ ዘሪ ዘርን ሊዘራ ወጣ፡፡ ዘሩንም በጭንጫ፣ በእሾህ ላይና በመልካም መሬት ላይ ዘራው፡፡ በመልካም መሬት የተዘራው 100 እጥፍ፣ በእሾህ ላይ የተዘራው 60 እጥፍ፣ በጭንጫ ላይ የተዘራው 30 እጥፍ አፈራ፤›› ይላል፡፡ በእዚህ ምሳሌ ዘሪው መንግሥት ነው ብንል፣ ዘሩ በጀት ቢሆን መሬቱ (ማሳው) ደግሞ ተቀባዩ ወይም ተዳራሹ የኅብረተሰብ ክፍል ይሆናል፡፡ ከእዚህ ጋር ተያይዞ መጠየቅ ያለበት ቢኖር ዘሪው ይኼንን ዘር (በጀት) በምን ዓይነት መሬት ላይ ነው ለማፍሰስ ያሰበው የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ እንደኔ ዕይታ ከሆነ ዘሩ ከመዘራቱ በፊት ማሳውን የማረስም ሆነ የማለስለስ ግዴታ በዘሪው ላይ የወደቀ ይመስለኛል፡፡ ማረስና ማለስለስ ደግሞ ቢያንስ የመሬቱን ባህሪ ማወቅና እንደ ባህሪው ማስተናገድ ይጠይቃል፡፡ ካልሆነ ግን አሥር ቢሊዮን አይደለም መቶ ቢሊዮኖች ብንመድብ እንኳንስ ልናተርፍ የወጣውን ገንዘብ ያህል ምርት መሰብሰብ የምንችል አይመስለኝም፡፡ ብርም ከክብር፣ ፍትፍትም ከፊት አይቀድምም፡፡ ለዚያም ነው የአገሬ ሰው “ከፍትፍቱ ፊቱ” የሚለው፡፡ ስለዚህም በየትኛውም ተቋምና የሥልጣን (የአገልግሎት ሰጪነት) እርከን የምንገኝ ሁላችንም በወጣቱ ዙሪያ ጥልቅ ተሃድሶ ያስፈልገናል ብዬ አምናለሁ፡፡
‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ከእዚህ አንፃር ምን እንደሆኑ ለመጥቀስ እሞክራለሁ፡፡ ያሉትን መልካም እሴቶች ማንበር፣ አንዳንድ ክፍተቶችን በመሙላትና መሠረታዊ ታሳቢዎችን በመቀየር አዳዲስ ሥልቶችን መተለም ከብዙ በጥቂቱ የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ ሕዝቡን በተለይም ወጣቱን በሚመጥን ሁኔታ በጥሩ ኮሙዩኒኬሽን (Participatory Communication) ልቡን መሳብ፣ ቀልቡን መግዛት፣ ሞራሉንና ተስፋውን ማነሳሳትና ሰብዕናውን በመልካም ባህሪያት ማነፅ ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ አገሩን እንዲወድ፣ ዴሞክራሲያዊና ሲቪክ አስተሳሰብን እንዲላበስ፣ የመሪነት አቅሙን የማሳደግ፣ ሞዴል የወጣት መሪዎች እንዲወጡ የማመቻቸት፣ ደጋፊም ይሁን ተቃዋሚ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማስጠበቅና ማስቀጠል የሚችልበትን ሲቪክ ከባቢ የመፍጠር፣ የባይተዋርነት ስሜትን አጥፍቶ የያገባኛል ስሜትን እንዲያጎለብት፣ በሚመለከተው ጉዳዮች እንዲሳተፍና የውሳኔ ሰጪነት ሚናውን የማረጋገጥ፣… ወዘተ ከመንግሥት በትንሹ ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም አገሪቱ የወጣት አገር ናት፡፡ ያሉ መልካም ጅምሮችንም ሆነ በእዚህ ሥርዓት የመጡ ለውጦችን ይዞ ማስቀጠል የሚችለውም እሱ ነውና! ለእዚህ ደግሞ የመጀመርያው ቁልፉ ነገር ወጣቱን በሚመለከት በጎ አመለካከት፣ ቅንነትና በወጣቱ ላይ ሊኖራቸው በሚገባ ፅኑ ዕምነት ዙሪያ በተቋማቶቻችን ማረጋጋጥን (Institutional Mainstreaming) ይሻል፡፡ ይኼ ደግሞ ከውጥኑ መንግሥት ወጣቱን የሚያስብበት መንገድ (Perception) መሠረታዊ በሚባል ደረጃ መለወጥን ይጠይቃል፡፡ አስተሳሰብ የተሃድሶ መጀመርያ ነውና! ወጣቱ ቢያጠፋ (አጥፊ ነው) ቢባል እንኳን መንግሥት በልበ ሰፊነት እየታገሰ፣ የነገዋን አገር ከሩቅ እየተመለከተ፣ እንደ መልካም እረኛ ወደ ለመለመው መስክ ሊያሰማራ እንጂ በፖለቲካዊ ቃላት መሳደብና ማንኳሰስ አይገባውም፡፡ በተለይ በሚዲያ! እዚህ ላይ ከወጣቱ የሚጠበቁ ነገሮች የሉም ለማለት ሳይሆን በሌላ ጊዜ የምመለስበት ሰፊ ጉዳይ ስለሆነና የእዚህ ጽሑፍ ዓላማ ይኼኛው ስለሆነ ነው፡፡ ቸር እንሰንብት!
ከአዘጋጁ፡-ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን ኢሜይል አድራሻቸው djmamaru@gmail.com. ማግኘት ይቻላል፡፡
