Quantcast
Channel: ዓለማየሁ ጉጀ
Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

ፊደል ካስትሮ የዓለም የነፃነት ታጋዮች ትዕምርት

$
0
0

 

ፊደል ካስትሮ

የዓለም የነፃነት ታጋዮች ትዕምርት

በሞላ ዘገየ፣ የሕግ አማካሪና ጠበቃ

የታላቁ አብዮተኛና የነፃነት ታጋይ የፊደል ካስትሮ ሕልፈተ ሕይወት ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ፣ በእኚህ የሃያኛው ክፍለ ዘመን የነፃነት ተጋድሎ ትዕምርት (Icon) ሕይወት ዙሪያ ሰፊ ዘገባና ትንታኔ ሲቀርብ ሰንብቷል፡፡ ነገሩ የጀግና ሞቱ ልደቱ እንደሚባለው ነው፡፡ ፊደል በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ካነጋገሩትም በላይ ካለፉ በኋላ ስለእሳቸው ብዙ እየተባለ፣ ብዙ እየተተነተነ ይገኛል፡፡ አንዳንዶች በተለይ ምዕራባውያኑ ፊደል ካስትሮ አምባገነነን ነበሩ ብለው ሲከሷቸው፣ የተቀረው ዓለም አብዮተኛነታቸውንና የነፃነት ታጋይ መሆናቸውን ያስተጋባል፡፡ እኔ በበኩሌ ዝቅ ብዬ በምትጠቅሳቸው መሠረታዊ መነሻዎች ምክንያት ፊደል ካስትሮ ታላቅ የነፃነት ታጋይና አብዮተኛ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የነፃነት ትግሎች በተቀጣጠሉበትና በየአካባቢው አብዮቶች በሚከሰቱበት ዘመን፣ በተለይ በሃያኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ (1960ዎቹና 70ዎቹ) ካስትሮ፣ ቸጉቬራና ሆቺሚኒ ከሁሉም ታጋዮች አንደበት የማይጠፉ፣ በርካታ የነፃነት ትግሎችና አብዮቶች እንዲቀሰቀሱና እንዲቀጣጠሉ መንገድ የጠረጉ የነፃነት ተጋድሎ ትዕምርቶች ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን በተለያዩ ጎራዎች የተሠለፈው፣ በተለምዶ “ያ ትውልድ” እየተባለ የሚጠራው የአገራችን አብዮታዊ ትውልድ፣ ለእነዚህ የነፃነት ታጋዮች ከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት ነበረው፡፡ ጽሑፎቻቸውን አንብቧል፣ መንገዳቸውን ለመከተልም ሞክሯል፡፡ በዚያ ሒደት አተረፍን ወይስ ከሰርን የሚለውን ጥያቄ ለጊዜው እናቆየውና ብዙዎቻችን የእነ ካስትሮ አድናቂዎችና የእነሱ ፈለግ ተከታዮች እንደነበርን ግን በሕይወት ያለነው ምስክሮች ነን፡፡  

ለዚህች ጽሑፍ መነሻ ከሆኑኝ ምክንያቶች ውስጥ ዕድሜያቸውን ሙሉ ከሚገፉትና ከሚጠቁት ወገኖች ጎን ቆመው በመታገል ላሳለፉት ካስትሮ ያለኝ ታላቅ አክብሮት የሚጠቀስ ሲሆን፣ በጽሑፌ የሶማሊያ ተስፋፊ አገዛዝ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ካስትሮና የኩባ ሕዝብ ለአገራችን የዋሉትን ውለታ ለመዘከር፣ በተለይ ደግሞ ከጦርነቱ በኋላ በነበረው የጅጅጋ መልሶ ማቋቋም መርሐ ግብር ሒደቱን በአውራጃ አስተዳዳሪነትና በአስተባባሪነት ስመራ የኩባ ሠራዊት አባላት በመልሶ ማቋቋም ሥራው የተጫወቱትን ሚና በቅርብ ስለማውቅ፣ የተወሰኑ ትውስታዎችን ለማጋራትና በሥራ አጋጣሚ ወደ ኩባ የመሄድ ዕድል አጋጥሞኝ ስለነበር በጉዞዬ እነ ካስትሮ የመሠረቱት ሥርዓት ለኩባ ሕዝብ ያስገኘውን ትሩፋት በወፍ በረር የማየት ዕድል አግኝቼ ስለነበር፣ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ አንዳንድ ነጥቦችን ለአንባቢያን ላጋራ እፈልጋለሁ፡፡

ፊደል የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለውለታ

ፊደል ካስትሮና የኩባ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባለውለታ ናቸው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያስታውሰው በዚያድ ባሬ የሚመራው የሶማሊያ ተስፋፊ አገዛዝ ዓለም አቀፍ ሕግጋትንና የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ቻርተር ወደጎን ብሎ፣ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ጥሶ አገራችን በወረረበት በዚያ እጅግ አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ከቆሙት ጥቂት አገሮች መካከል ኩባ በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች፡፡ ኢትዮጵያ በአብዮቱና አብዮቱን እንመራዋለን በሚሉ ኃይሎች የእርስ በርስ ሽኩቻ ምክንያት ተዳክማለች በሚል ሥሌት ከሰኔ ወር 1969 ዓ.ም. ጀምሮ በአገራችን ላይ ለመስፋፋት ወረራ የጀመረው የሶማሊያ ወራሪ ሠራዊት፣ እስከ ኅዳር ወር 1970 ዓ.ም. ድረስ ለስድስት ወራት በተለያዩ አቅጣጫዎች በከፈተው ጥቃት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ አካባቢዎችን በቁጥጥር ሥር ከማድረጉም በላይ፣ በንብረትና በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ ነበር፡፡

በተስፋፊው የዚያድ ባሬ መንግሥት አሻፈረኝ ባይነት ምክንያት ሳይሳካ ቢቀርም፣ ሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ወደ አላስፈላጊ ጦርነት እንዳይገቡና የሰው ሕይወት በከንቱ እንዳይጠፋ ለማድረግ ፊደል ካስትሮ ከደቡብ የመን መሪዎች ጋር በመሆን፣ የኢትዮጵያና የሶማሊያ መሪዎች ችግራቸውን በውይይትና በድርድር እንዲፈቱት ለመሸምገል ሞክረዋል፡፡ አወንታዊ ውጤት አልተገኘም፡፡

የሶማሊያ መንግሥት የሶሻሊዝምን ፈለግ እንደሚከተል የሚምልና የሚገዘት፣ ነገር ግን እጅግ ኋላቀርና ተስፋፊ የሆነ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የሚከተል መንግሥት ነበር፡፡ በአንድ በኩል ተራማጅ በመምሰል ከሶሻሊስቱ ጎራ፣ በተለይ ከሶቪየት ኅብረት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ለመመሥረት እየሠራ፣ እዚያው በዚያው ከአሜሪካና ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጉያ ውስጥ ለመግባት የሚፈልግ አገዛዝ እንደነበረም የሚታወቅ ነው፡፡ በኋላ እንደታየውም ሶሻሊስት አገሮች በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል የሚደረገውን ጦርነት እንደማይደግፉ ጠቅሰው፣ የሚሻለው ችግሩን በሰላማዊ መንገድ መፍታት መሆኑን በገለጹለት ማግሥት አቅጣጫውን ወደ ዓረብ አገሮችና አሜሪካ አዙሯል፡፡ 

ይህን የዚያድ ባሬን መንታ አካሄድና መሰሪነት በሚገባ የተገነዘቡት ፊደል ካስትሮ፣ በዚያ ብዙዎች የሶማሊያን አሸናፊነት በፍፁም እርግጠኛነት በሚናገሩበትና አገራችን ችግር ላይ በነበረችበት እጅግ ፈታኝ ወቅት ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጋር ሆነው የተቃጣብንን ወረራ ለመመከት ቁርጠኛ አቋም በመያዝ በርካታ ኩባውያን ወታደሮችን፣ ወታደራዊ ቁሳቁሶችንና የሕክምና ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ልከዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያስታውሰው በዚያ በተስፋፊው ሠራዊት የተቃጣብንን ወረራ ለመመከት በተደረገው ከፍተኛ መስዋዕትነት የጠየቀ ጦርነት ኩባውያን በቆራጥነት ተሳትፈዋል፡፡ ከመካከላቸውም ብዙ ወታደሮች መስዋዕት ሆነዋል፡፡ የኩባ የሕክምና ባለሙያዎችም ቢሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

ጦርነቱን በድል ከተወጣን በኋላ የጅጅጋን ከተማ እንደገና መልሶ መገንባትና ማልማት ትልቅ ብሔራዊ አጀንዳ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ጅጅጋ ከተማን መልሶ ለማቋቋም ብሔራዊ ጥሪ አድርጎ ከፍተኛ ርብርብ በሚያደረግበት ወቅት በኮሎኔል ፔሪ  የሚመራው የኩባ ጦር ያደረገው አስተዋጽኦ በጣም ከፍተኛ እንደነበር የዓይን ምስክር ነኝ፡፡ ከጦርነቱ በኋላ የጅጅጋ አስተዳዳሪና የመልሶ ማቋቋሙ አስተባባሪ ስለነበርኩ፣ ኩባውያን በጦርነት የደቀቀውን አካባቢ መልሶ ለመገንባት በተደረገው ጥረት ውስጥ ያደረጉት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን በሒደቱ የተሳተፍን ሁሉ በአድናቆት የምናስታውሰው ነው፡፡ በዚያ ፍፁም የአገርና የሕዝብ ፍቅር በተሞላበት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያውያንና በኩባውያን ትብብር የተገነቡትን መሠረተ ልማቶች የኢትዮጵያ ሶማሊያ ሕዝብ ያስታውሳቸዋል፡፡ በበኩሌ በዚያ የታሪክ አጋጣሚ ከበርካታ ኩባውያን ጋር የመገናኘትና የመሥራት ዕድል አጋጥሞኝ ስለነበር ኩባውያን ምን ያህል ግልጽ፣ ቅንና ሥራ ወዳዶች እንደሆኑ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ከእነሱ ጋር ያሳለፍኩትን ጊዜም በልዩ ሁኔታ አስታውሰዋለሁ፡፡

በእርግጥ የኩባ ድጋፍና አስተዋጽኦ በዚህ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ በአብዮቱ ዘመን በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች ልዩ ልዩ መስኮች ሁኔታዎችን ለማሻሻልና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማስፋት ባደረግናቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ የኩባውያን ድጋፍ ቀላል ግምት የሚሰጠው አልበረም፡፡ በርካታ ኩባውያን የጤና ባለሙያዎች፣ የእንስሳት ሐኪሞች፣ መምህራን፣ ወዘተ. ወደ አገራችን መጥተው የልማት ሥራዎቻችንን ደግፈዋል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የፊደል ካስትሮ መንግሥት በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ምክንያት ወላጆቻቸውን ላጡ ኢትዮጵያውያን ነፃ የትምህርት ዕድል በማመቻቸት አያሌ ኢትዮጵያውያን ወደ ኩባ አቅንተው በልዩ ልዩ መስኮች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በዚህ መርሐ ግብር አማካይነት ወደ ኩባ ሄደው ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ አገራቸው የተመለሱት ኢትዮጵያውያን የእኚህን የነፃነት ታጋይ ሕልፈተ ሕይወት አስመልክተው መታሰቢያ ዝግጅት ማድረጋቸውን በመስማቴ በእጅጉ ተደስቻለሁ፡፡ ውለታን አለመዘንጋት ታላቅነት ነው፡፡ ሊከበርም ይገባዋል፡፡ የፊደል ካስትሮና የኩባ ሕዝብ ውለታ ሁልጊዜም ሲታወስ ይኖራል፡፡

ይህን ክፍል ከመዝጋቴ በፊት አንድ ሊታወስ የሚገባውና የፊደል ካስትሮንና የመንግሥታቸውን አርቆ አሳቢነት የሚያሳይ ነጥብ ላንሳ፡፡ እንደሚታወቀው የሶማሊያ ተስፋፊ ኃይል ከተደመሰሰ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት “በምሥራቅ የተገኘው ድል በሰሜንም ይደገማል” በማለት ትኩረቱን ወደ ሰሜን፣ በተለይም ወደ ኤርትራ አድርጎ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በምሥራቅ ባገኘው ድል ተበረታቶ፣ አማፂያኑንም በተመሳሳይ ሁኔታ ለማንበርከክ የሶሻሊስት አገሮች የጦር መሣሪያና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርጉለት ቢጠይቅም፣ የኩባ መንግሥት ጉዳዩ የእርስ በርስ ጦርነት መሆኑን አስታውሶ እንደዚያ ባለ ጦርነት እንደማይሳተፍ አቋሙን ግልጽ አድርጓል፡፡ ከዚህም በላይ ብዙም ዝርዝር መረጃ ባይኖረኝም፣ ካስትሮ አማፂዎችንና መንግሥትን ለመሸምገልም ሙከራ ሳያደርጉ የቀሩ አይመስለኝም፡፡ በእኔ አስተያየት በወቅቱ የኩባ መንግሥት የወሰደው አቋም፣ ማለትም በውስጥ ጉዳያችሁ አንገባም ማለቱ እጅግ የሚያስደንቅ አቋም ነው፡፡ በአንድ ሕዝብ መሀል ገብተን አናቦካም ማለታቸው ሲሆን፣ ይህም ከቆሙለት የነፃነት ትግል አንፃር ትክክለኛ አቋም ነው፡፡

ካስትሮ ለእምነታቸው ኖረው በእምነታቸው ፀንተው አለፉ

ፊደል ካስትሮ ለእምነታቸው ኖረው፣ በእምነታቸው ፀንተው ያለፉ ታላቅ የነፃነት ታጋይና አብዮተኛ ናቸው፡፡ “ለእምነታቸው ኖሩ፣ በእምነታቸው ፀንተው አለፉ” የምልበትን ምክንያት ትንሽ ዘርዘር አድርጌ ለማቅረብ ልሞክር፡፡ የሕይወት ታሪካቸው እንደሚያስረዳው እ.ኤ.አ ነሐሴ 13 ቀን 1926 ሃቫና ውስጥ የተወለዱት ፊደል፣ በስኳር አገዳ ልማት የተሰማሩና ደህና ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ልጅ ነበሩ፡፡ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ምርጥ ከሚባሉት የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ከተከታተሉ በኋላ፣ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ሃቫና ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት አጠናቀዋል፡፡ የነበራቸው ቤተሰባዊ መሠረትና የተከታተሉት የትምህርት መስክ በጊዜው የተሻለ ኑሮ መምራት የሚያስችላቸው ቢሆንም፣ ፊደል የመረጡት ይህን አልበረም፡፡ ጥቂቶች የቅንጦት ሕይወት የሚመሩባትና ብዙኃኑ ሕዝብ በከፍተኛ ችጋር ውስጥ የሚኖርባትን የዚያን ጊዜዋን ኩባን አዕምሯቸው ሊቀበላት አልፈቀደም፡፡ የጥብቅና ፈቃድ አውጥተው ለድሆች ለመቆም ቢሰማሩም  ብዙም ሳይቆይ እንዲዘጋ ሆኗል፡፡

ፊደል ገና ከወጣትነታቸው ጊዜ ጀምሮ የላቲን አሜሪካ አምባገነንና የአሜሪካ አሻንጉሊት የሆኑ መሪዎችን ለማስወገድ፣ በተለይ የዶሚኒካን ሪፐብሊክና የኮሎምቢያን አምባገነናዊ መሪዎች ለማስወገድ በተደረጉት እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ይህ ገና ከወጣትነት ዘመናቸው ጀምሮ የነበራቸው ከተጠቁትና ከተገፉት ጋር የመቆም ስሜት የባቲስታን አምባገነናዊ አገዛዝ አስወግደው ሥልጣን ከያዙ በኋላም ይበልጥ ተጠናክሮ በመቀጠሉ ፊደል በተለያዩ የላቲን አሜሪካ፣ የአፍሪካና እስያ አገሮች ውስጥ ሲካሄዱ ለነበሩ የነፃነት ትግሎች ወታደር፣ ወታደራዊ ቁሳቁስና የሕክምና ባለሙያዎችን በመላክ ዓለም ሲያስታውሰው የሚኖር አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በአፍሪካ የነበራቸውን ተሳትፎ በምሳሌነት ብንጠቅስ ለአልጄሪያ፣ ለኮንጎ ብራዛቪል፣ ለአንጎላና ለሞዛምቢክ የነፃነት ንቅናቄዎች ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካን የነፃነት ታጋዮች ሳይታክቱ ደግፈዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ የነፃነት ትግሉን የደገፉትን ኃይሎች ባመሰገኑበት አጋጣሚ፣ በግንባር ቀደምትነት የጠቀሱት የፊደል ካስትሮንና የኩባን ሕዝብ ውለታ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ምዕራባውያን በተለይ የአሜሪካ ተከታታይ መሪዎች እነ ማንዴላን በአሸባሪነት መዝገብ ውስጥ ሲያስቀምጧቸው፣ ካስትሮ የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ መሪዎችን በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በሞራል እየደገፉ ዘረኛውን የአፓርታይድ ሥርዓት በፅኑ ታግለዋል፡፡ ከሚጠቁትና ከሚገፉት ጎን መቆም ማለት ይኼ ነው፡፡ ለነፃነትና ለፍትሕ መቆም ማለት ይኼ ነው፡፡

በሥራ ምክንያት ወደ ኩባ በሄድኩበት ወቅት በግልጽ የተረዳሁት ነገር ቢኖር፣ ኩባ ውስጥ የኮሙዩኒስት ፓርቲ አባል መሆን ማለት የሕዝብ አገልጋይ መሆን ማለት ነው፡፡ የኮሙዩኒስት ፓርቲ አባል መሆን ማለት ከሕዝብ በታች እየኖሩ፣ ለሕዝብ ልዕልና መኖር ማለት ነው፡፡ ኩባ ከመሄዴ ቀደም ብሎ በትምህርትና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ወደተለያዩ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ለመሄድና በእነዚህ አገሮች ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለማየት ችዬ ነበር፡፡ የኩባ ኮሙዩኒስት ፓርቲና የፓርቲው አሠራር ከቻይና፣ ከሰሜን ኮሪያ፣ ከምሥራቅ አውሮፓ ኮሙዩኒስት ፓርቲዎች፣ ወዘተ ጋር በዓይነቱም በይዘቱም በጣም የተለየ ነው፡፡ ለምሳሌ የአንድ ዕቃ እጥረት ተፈጥሮ ዜጎች ከተሠለፉ፣ የመጨረሻው ሠልፍ ላይ የሚገኘው የኮሙዩኒስት ፓርቲ አባል ነው፡፡ የአገር ግንባታ ጥሪ የተደረገ እንደሆነ ደግሞ ግንባር ቀደም ሆነው መስዋዕትነት የሚከፍሉት የኮሙዩኒስት ፓርቲው አባላት ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ የኮሙዩኒስት ፓርቲ አባላት በኅብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ አድናቆትና ከበሬታ አላቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ የኮሙዩኒስት ሥርዓትን የሚጠሉ ሰዎች እንኳን ኮሙዩኒዝምን እጠላለሁ ካስትሮን ግን እወደዋለሁ ይሉ ነበር ፡፡

እዚህ ላይ ሊጠቀስ የሚገባው ሌላ መሠረታዊ ነገር አለ፡፡ በአብዛኞቹ ሶሻሊስት አገሮች ሀብት ማካበትና ሙስና ዋናው የሥርዓቱ መገለጫ ሲሆን፣ የኩባ ኮሙዩኒስት ፓርቲ አባላት በአንፃሩ በምንም ዓይነት ሁኔታ በሙስናና በሀብት ማካበት አይታሙም፡፡ ሌላው ቀርቶ ፊደል ካስትሮን ጨምሮ ትልልቆቹ የፓርቲ አባላት የግል መኖሪያ ቤት እንኳን የላቸውም፡፡

የሕዝቦችን እኩልነት በሚመለከት ረገድም የኩባ ሁኔታ የሚያስደንቅና ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ ጥቁርና የነጭ እኩልነት የተከበረበት አገር ነው ኩባ፡፡ ኩባ ውስጥ በምንም ዓይነት የዘር መድሎ የሚባል ነገር የለም፡፡ በሕግም ያስቀጣል፡፡ በሞራል ሕግም ያስንቃል፡፡ ነጭና ጥቁር እኩል ተከብሮ የሚኖርበት አገር ነው ኩባ፡፡ የሴቶች መብትና ነፃነት ደግሞ በጣም የተከበረ ነው፡፡ ከእነሱ 90 ማይል ርቆ የሚገኘውና በዴሞክራትነቱና በሰብዓዊ መብት ጠባቂነቱ የሚኩራራው የአሜሪካ ማኅበረሰብ እስካሁንም በዚህ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ በእጅጉ ወደኋላ የቀረ ነው፡፡ አሜሪካ አሁንም ሰዎች በተለይ ጥቁሮች የሚናቁበት፣ በገፍ የሚታሰሩበትና የሚሞቱበት አገር ስለሆነ፣ በዚህ በዜጎች እኩልነትና መከባበር ጉዳይ ላይ ከኩባውያን የሚማረው ብዙ ነገር አለ፡፡

የኩባ መንግሥት በትምህርት፣ በጤናና መሠረተ ልማት ግንባታና በወንጀል መከላከል በኩል በጣም ውጤታማ መንግሥት ነው፡፡ ኩባውያን ልጅ ሲወልዱ ልጃቸውን እንዴት እንደሚያስተምሩ አያስቡም፡፡ የአገሪቱ ልጆች ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ዩኒቨርሲቲ ለሚማሩት ትምህርት ሁሉንም ውጪ የሚሸፍነው የኩባ መንግሥት ነው፡፡ ትምህርትንና ጤናን በሚመለከት አንድም ወላጅ ልጄን እንዴት ላስተምር፣ እንዴት ላሳክም ብሎ አይጨነቅም፡፡ የኩባ መንግሥት ነው ኃላፊነቱን የሚወስደው፡፡  ትምህርትንና ጤናን በሚመለከት ረገድ በልጽገዋል የሚባሉት አገሮችም የኩባን ያህል ለሕዝባቸው አገልግሎት አይሰጡም፡፡ ፊደል በዚህ ምክንያት በኩባ ሕዝብ ለዘለዓለም ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡

ሁሉም ዜጋ ወንጀልን የሚዋጋና ወንጀለኞችን አሳልፎ የሚሰጥ በመሆኑ የወንጀለኞችና የተደራጁ ማፍያዎች በሚርመሰመሱበት አኅጉር ውስጥ በኩባ  ወንጀል የለም፡፡  ጥቁር ገበያና የሴት ልጅ መደፈር በከፍተኛ ደረጃ የሚያስቀጡ ወንጀሎች ናቸው፡፡ በጥቁር ገበያ ተሳትፈው የሚገኙትንና ሴት ልጅ የሚደፍሩትን ሕዝቡ ራሱ አሳልፎ ስለሚሰጣቸው በእነዚህ ወንጀሎች የሚሳተፍ የለም፡፡

እንደሚታወቀው የአሜሪካ መንግሥታት በተደጋጋሚ ጊዜያት ፊደል ካስትሮን ለመገልበጥ ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ አደርጎባቸው ሙከራዎች ሁሉ ከሽፈዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ፊደል ካስትሮና ጓዶቻቸው የመሠረቱት ሥርዓት ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ተባይነት ስላለውና ሕዝቡ ከመንግሥት ጋር ስለሚቆም ነው፡፡ አሜሪካውያን ያን ሁሉ የኩባ ዳያስፖራ እያደራጁና በዚያች አገር ላይ ማዕቀብ እየጣሉ ሥርዓቱን ለማሽመድመድ ቢሞክሩም እስካሁን አልተሳካላቸውም፡፡  

በነገራችን ላይ አንዳንድ ሰዎች በተለይ የምዕራብ መገናኛ ብዙኃን የፊደል ወንድም ራውል ካስትሮ ፊደልን ተክተው የአገሪቱ መሪ መሆናቸውን እየጠቀሱ፣ ካስትሮ የቤተሰብ ሥረወ መንግሥት መሥርተዋል እያሉ ይከሷቸዋል፡፡ ይህ ግን አንድም እውነታውን ካለማወቅ፣ ወይም ደግሞ በምዕራቡ ሚዲያ አካባቢ በተደጋጋሚ እንደሚስተዋለው እውነታውን ከመካድ የሚመጣ “ስህተት” ነው እንጂ ራውል ካስትሮ ራሳቸው ከወጣትነታቸው ጊዜ ጀምሮ የነፃነት ታጋይና አብዮተኛ ናቸው፡፡ የኩባ ሕዝብ ራውል ካስትሮ ልክ እንደ ወንድማቸው ለደሃዎች የሚቆሙ የነፃነት ታጋይ መሆናቸውን በሚገባ ስለሚያውቅና ስለሚቀበላቸው ነው የሽግግሩ ሒደት ኮሽታ ያልነበረው፡፡

ታላቁ አብዮተኛና የነፃነት ታጋይ ፊደል ካስትሮ በተወለዱ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ቢለዩም፣ በአገራቸውና በዓለም ዙሪያ ሁሉ የሠሯቸው አኩሪ ሥራዎች ስማቸውን ከመቃብር በላይ የሚያውሉ ናቸው፡፡ ነፍስ ይማር !!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው molla.zegeye@yahoo.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

Trending Articles