በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ
የኢፌዴሪ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ በአዋጅ 621/2001 ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት እንዲስፋፉና ተልዕኳቸውን በሕግ መሠረት እንዲወጡ ብሎም አሠራራቸው ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን እየሠራ ይገኛል፡፡ ኤጀንሲው በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 31 የተደነገገውን የዜጎች የመደራጀት መብት ዕውን ለማድረግ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራትን መዝግቦ ፈቃድ በመስጠት፣ ዘርፈ ብዙ የክትትልና የድጋፍ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ማኅበራት በአገራቸው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና የልማት ሥራዎች ላይ የመሳተፍ ዕድል አግኝተዋል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሙያና የብዙኃን ማኅበራት ተደራጅተው ፈቃድ በመውሰድ በአገሪቱ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡
ምንም እንኳ አብዛኞቹ ማኅበራት ተመዝግበው መንቀሳቀስ የጀመሩት በቅርብ ዓመታት ውስጥ ቢሆንም፣ ከተመሠረቱ ግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ማኅበራትም አሉ፡፡ ሆኖም እንደ ቁጥራቸው ብዛትና እንደ ዕድሜያቸው ልክ የሙያ ማኅበራት በአገሪቷ የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ አኑረዋል ማለት ግን አይቻልም፡፡ የሙያም ሆኑ የብዙኃን ማኅበራት የሕዝብን ጥያቄ በተደራጀ መልኩ እያቀረቡ እንዲፈቱ ለማስቻል በመንግሥትና በኅብረተሰቡ መካከል እንደ ድልድይ ሆነው እያገለገሉ አይደለም፡፡ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ተመዝግበው ፈቃድ የወሰዱ በጥቅሉ 333 ገደማ የሚሆኑ የሙያና የብዙኃን ማኅበራት ቢኖሩም፣ የረባ ሥራ ሠርተዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ሆኖም በጥቅሉ ሁሉም ማኅበራት ለተቋቋሙለት ዓላማ በተገቢው ሁኔታ አስተዋፅኦ አላበረከቱም ማለታችን አይደለም፡፡ ለአብነት የሚጠቀሱ ስኬታማ ሥራ መሥራት የቻሉ ማኅበራት መኖራቸው አይካድም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ያሉ ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው በጣት የሚቆጠሩ ማኅበራት መኖራቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡
አብዛኞቹ የሙያና የብዙኃን ማኅበራት የሚፈለገውን ውጤት እንዳያመጡ እንቅፋት የሆነባቸው አገሪቱ በዘርፉ የምትከተለው ሕግ መሆኑን በአፅንኦት ይገልጻሉ፡፡ ለምሳሌ የ10/90 ሕግ ማኅበራት የገንዘብ ድጋፍ ከውጭ አገር እንዳያገኙ በማድረጉ ለመዳከማቸው ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ሕገ መንግሥቱ በደነገገው መሠረት በማኅበር የመደራጀት መብት የተሰጠው ለዜጎች ብቻ ነው፡፡ በአዋጅ 621/2001 መሠረት የኢትዮጵያ ማኅበራት ፈቃድ ወስደው ለመሥራት ሁሉም አባላት ኢትዮጵያዊ መሆን ይኖርባቸዋል እንዲሁም የገቢ ምንጫቸው ከአገር ውስጥ መሆን እንዳለበት ተደንግጓል፡፡
በመሆኑም በሕግ ከተፈቀደው ውጪ ከውጭ የገንዘብ ምንጭ መጠቀም አይቻልም፡፡ የሙያና የብዙኃን ማኅበራት የአባላትን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሠሩ በመሆናቸው፣ እንደ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ሰፊ የሀብት መጠን ላያስፈልጋቸው ይችላል፡፡ 90 በመቶ የሚሆነውን ሀብት ከአገር ውስጥ በማመንጨት፣ እንዲሁም ከአሥር በመቶ የማይበልጠውን ከውጭ አገር በማምጣት ከሠሩ የተቋቋሙለትን ዓላማ ከዳር ማድረስ ይችላሉ፡፡ ማኅበራት የአባላትን መብትና ጥቅም ለማስከበር የውጭ ዕርዳታ ሳያስፈልግ በአገር ውስጥ ሀብት መሥራት ይችላሉ፡፡
በመሆኑም በአገራችን እየተንቀሳቀሱ ያሉ ማኅበራት የ10/90 ሕግ ውጤታማ ላለመሆናቸው ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ሕግ ሲወጣ ማኅበራት ሀብት የማግኘት አቅማቸው እንዳይዳከም ብዙ ታሳቢ የተደረጉ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለአብነት ያህል ማኅበራት ከተቋቋሙለት ዓላማ ጋር ግንኙነት ባላቸው ብሎም ዓላማቸውን ለማስፈጸም ብቻ የሚውሉ የተለያዩ ገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ አማራጮች ተቀምጠዋል፡፡ የንግድ ሕግ ጠብቀው ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ መሰማራት ይችላሉ፡፡ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመው ሕዝባዊ መዋጮ በማካሄድ ከአገር ውስጥ ሀብት ማመንጨት ይችላሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ አማራጮች ተጠቅመው ከጥገኝነትና ከተመፅዋችነት አመለካከት ተላቀው ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ ስለሚችሉ፣ የ10/90 ሕግ አላሠራንም ማለት ምክንያታዊና ከሕግ አንፃርም ተገቢነት የሌለው በመሆኑ ማኅበራት ቆም ብለው ማጤን ይኖርባቸዋል፡፡ ህልውናቸው የሚወሰነው ራሳቸውን ለማጠናከር በሚሠሩት ሥራ ነው፡፡
ይህ ሲባል የብዙኃንና የሙያ ማኅበራት ምንም ተግዳሮቶች የሉባቸውም ማለት አይደለም፡፡ አብዛኞቹ ሥራ መሥሪያ ቢሮ የላቸውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለሥራቸው ግብዓት የሚሆኑ ቁሳቁሶችን የማግኘት ችግር አለባቸው፡፡ በየዘርፉ ያሉ የመንግሥት ተቋማት ለሙያና ብዙኃን ማኅበራት ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል፡፡ የሙያ ማኅበራትም ለአባላት ሥልጠናና የትምህርት ዕድልን ከማመቻቸት ባለፈ ያላቸውን ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ፣ ለፖሊሲና ለስትራቴጂዎች ግብዓት የሚሆኑ የመፍትሔ ሐሳቦችን በማቅረብ እንዲሁም መንግሥትን በማማከር ለአገሪቷ አቅም መፍጠር አለባቸው፡፡ ይህንን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ማኅበራት የጎላ አስተዋፅኦ አድርገዋል ማለት አይቻልም፡፡
በቀጣይ በመስኩ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ የሙያ ማኅበራት በየዘርፋቸው ከሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ጋር የጠበቀ ቁርኝት ፈጥረው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እጅና ጓንት ሆነው መፍታት አለባቸው፡፡ የሙያ ማኅበራት ውጤታማ የሚሆኑት ያላቸውን እምቅ ዕውቀትና ክህሎት ሳይሰስቱ ለአገራቸው ማበርከት ሲችሉ ነው፡፡ በሌላ በኩል 10/90 ለሚተገብሩ የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት እንዲጠናከሩ መንግሥት የማኅበራዊ ተጠያቂነት ፈንድ (Social Accountability Fund) ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ አለበት፡፡
የሙያና የብዙኃን ማኅበራት በራሳቸው የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ተምሳሌት መሆን መቻል አለባቸው፡፡ የአባላትን መብትና ጥቅም በማስከበር፣ በጠቅላላ ጉባዔ መሪዎችን መምረጥ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት እንዲፈቱ ማድረግ፣ ያልተመለሱ መብቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲመለሱ አባላትን በማለማመድ እንደ አገር በሚደረገው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መነሻና ትምህርት ቤት መሆን አለባቸው፡፡ የአንዳንድ ማኅበራት የሥራ ኃላፊዎች የጊዜ ሰሌዳቸውን ጠብቀው ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት የሥራ አፈጻጸማቸውን አያቀርቡም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለበርካታ ዓመታት ሥልጣናቸውን ለሌሎች አባላት ሳይለቁ የሚቆዩበት ሁኔታ አግባብነት የለውም፡፡
የመተዳደሪያ ደንባቸው ላይ በተቀመጠው መሠረት በየሁለት ዓመቱ ጠቅላላ ጉባዔ በማካሄድ ሥልጣናቸውን አዲስ ለሚመረጡ ለሌሎች አባላት አሳልፈው መስጠት አለባቸው፡፡ የማኅበራት አመራር አባላቱን በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እያወያዩ ዜጎች የጠራ አመለካከት ይዘው ለልማት እንዲነሳሱ የበኩላቸውን ሚና መጫወት አለባቸው፡፡ የሙያና የብዙኃን ማኅበራት የአገሪቷ ዓይን፣ ጆሮና አፍ መሆን አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል ማኅበራት በውስጣቸው ሰፊ ቁጥር ያላቸው አባላትን በመያዛቸው ወሳኝ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸው የጠራ ግንዛቤ፣ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላል፡፡
የሙያና የብዙኃን ማኅበራት ውስጣዊ አሠራርም ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት መሆን አለበት፡፡ ይህ መሆን ሲችል ነው መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲያዊ አሠራር ሊጎለብት የሚችለው፡፡ ማኅበራት በአገሪቷ የፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ሲችሉ፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማስከበር ላይ ጉልህ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ አቅም ሲፈጥሩ በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላሉ፡፡ በዚህ ረገድ የሙያም ሆኑ የብዙኃን ማኅበራት በጉልህ የሚታይ ነገር አልሠሩም፡፡
አሁን በአገራችን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የብዙኃን ማኅበራት ገዢው ፓርቲ ያቋቋማቸውና ለእሱ በመወገን የፖለቲካ ሥራ እንደሚሠሩ አድርጎ የሚቆጥሩ አካላት አሉ፡፡ ነገር ግን የሙያና የብዙኃን ማኅበራት ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ነፃ ሆነው በገለልተኝነት ለዜጎች እኩል የሚሠሩ ናቸው፡፡ ሕጉም ይህንኑ ነው የሚደነግገው፡፡ በሌላ በኩል የሙያና የብዙኃን ማኅበራት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን ነቅሰው በማውጣት እንዲፈቱ ጫና እየፈጠሩ አይደለም፡፡ በእርግጥ ማኅበራት ይህንን እንዲያደርጉ መንግሥት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል ወይ የሚለው ጥያቄ በአግባቡ መፈተሽ አለበት፡፡ ሌላው ቀርቶ የአባላትን መብትና ጥቅም ማስጠበቅ የሚችሉበት ደረጃ ላይ አልደረሱም፡፡ ምንም እንኳን ሁሉንም ማኅበራት የሚገልጽ ባይሆንም ማኅበራት የሙያ ብቃት ባላቸው ግለሰቦች እየተመሩ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ ማኅበራት ሥልጣን ለመያዝ በሚያደርጉት ሽኩቻ በመጠመዳቸው ትርጉም ባለው ሁኔታ አገራዊ ራዕይ አንግበው ሙያውን ለማሳደግ እየሠሩ አይደለም፡፡ ይህም በዘርፉ የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ አሉታዊ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
የሙያም ሆኑ የብዙኃን ማኅበራት በሥነ ምግባር የታነፁና በዕውቀት የበለፀጉ አገር ተረካቢ ዜጎችን በማፍራት ረገድ ትኩረት ሰጥተው መሥራት አለባቸው፡፡ የአባላትን አቅም በመገንባት ዙሪያ ብዙም የተሠራ ሥራ የለም፡፡ ማኅበራት በተጨባጭ አባላትን ማፍራትና አቅም መገንባት መቻል አለባቸው፡፡ ማኅበራት ሲጠናከሩ የአባላትን መብትና ጥቅም ማስከበር ይችላሉ፡፡ የፋይናንስ አቅማቸው እንዲጠናከር የአገር ውስጥ ባለሀብቶችና ለጋሾች ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ማኅበራት እንቅስቃሴያቸው በበጎ ፈቃደኞች እንዲደገፍ ለማስቻል የበጎ ፈቃደኝነት ባህል እንዲዳብር ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ የኅትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ትኩርት ሰጥተው የሙያና የብዙኃን ማኅበራትን የሥራ እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም ያሉባቸው ተግዳሮቶች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በሰፊው መሥራት አለባቸው፡፡ ሚዲያዎች በዘርፉ ያሉ ድክመቶችን ለመፍታት የሚያስችል ጥልቅ ዕይታ መሠረት አቅጣጫ አመላካች የመፍትሔ ሐሳቦችን መስጠት መቻል አለባቸው፡፡
የሙያ ሥነ ምግባርና ብቃትን ከማሳደግ አንፃር የሙያ ማኅበራት ብዙ መሥራት ያለባቸው ሥራዎች ቢኖሩም፣ አሁንም የሚጠበቅባቸውን ያህል ርቀው መጓዝ አልቻሉም፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት የሚቆጠረው የሙያ ማኅበራት ተዝቆ የማያልቅ ትልቅ አቅም እያላቸው፣ ከስብሰባ የዘለለ ትርጉም ያለው ሥራ ለመሥራት ያላቸው ቁርጠኝነት ማነስ እንደ ድክመት የሚጠቀስ ነው፡፡ ሆኖም ለማኅበራት ተገቢው እገዛ ሳይደረግ በድፍኑ መውቀሱ አግባብ ባይሆንም፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ለሙያና ለብዙኃን ማኅበራት ትኩረት ሰጥተው አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለባቸው፡፡ የብዙኃንና የሙያ ማኅበራት ያላቸውን ምርጥ ተሞክሮ ቀምሮ ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ የአገር ውስጥም ሆነ ያደጉ አገራት ተሞክሮዎችን ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ማስፋፋት ቅድሚያ የሚሰጠው ለነገ የማይባል ተግባር ሊሆን ይገባል:: እንደ አገር የሙያም ሆኑ የብዙኃን ማኅበራት በዜጎች መብት ነክ ጉዳዮችና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደት ውስጥ በንቃት መሳተፍ የሚያስችላቸው አሠራር መዘርጋት አለበት እንላለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው chsainfo@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡
