Quantcast
Channel: ዓለማየሁ ጉጀ
Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

ባህላዊ የፋሲካ ማዕድ

$
0
0

በዓለም የሚገኙ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ለ55 እና ለ48 ቀናት የሚዘልቀውን የፋሲካ (ትንሣኤ) ጾም የሚፈቱት የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችን በማዘጋጀት ነው፡፡ የጾሙ ወቅት ከእንስሳት ተዋጽኦና ከመጠጥ የሚቆጠቡበት ሲሆን፣ ሲፈታ ደግሞ አንደየአገሩ ባህል የተለያዩ ማዕዶችን ያዘጋጃሉ፡፡ ዳቦ ወይም ኬክ ከማዕዱ መቅረት ከሌለባቸው ምግቦች አንዱ ነው፡፡

ሩሲያ

የፒራሚድ ቅርፅ ያለው ኬክ በትንሳኤ በዓል ዕለት ማቅረብ የተለመደ ነው፡፡ ኬኩ ሃይማኖታዊ የሆኑ ምልክቶች የሚቀረፁበት ነው፡፡ በተለይ የክርስቶስ መነሳትን የሚያመላክቱ ቅርጾች በኬኩ ላይ ይደረጋሉ፡፡

ጣሊያን

በጣሊያን ለትንሣኤ በዓል የሚጋገረው ኬክ የርግብ ቅርፅ ያለው ነው፡፡

ግሪክ

ግሪኮች በትንሣኤ ማዕዳቸው ላይ ከሚያቀርቧቸው ምግቦች አንዱ ኬክ ነው፡፡ ኬኩ በተቀቀለና ቀይ የምግብ ፓውደር በተቀባ እንቁላል ይጌጣል፡፡ ተምሳሌቱም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው፡፡

ምሥራቅ አውሮፓ

በምሥራቅ አውሮፓ በትንሣኤ በዓል ጣፋጭ ዳቦ አዘጋጅቶ የመብላት ባህል አለ፡፡ ዳቦው በመስቀል ቅርፅ የሚጋገር ነው፡፡ በተለይ በስሎቫኪያና በክሮሺያ የተለመደ ሲሆን፣ በጣሊያን በአንዳንድ ስፍራዎችም ይዘወተራል፡፡

ስፔን

ስፔናውያን ከሰሞነ ሕማማት ጀምረው የፋሲካ ኬክ በባህላዊ መንገድ ያዘጋጃሉ፡፡ ይህ ኬክ የዶናት ዓይነት ቅርፅ ያለው ሲሆን፣ መሐሉ ላይ የተቀቀለ እንቁላል ሳይላጥ ይደረግበታል፡፡

እንግሊዝ

በእንግሊዝ ፋሲካን በዓል የሚያስመስለው፣ በቅመማ ቅመም የጣፈጡና በላያቸው ላይ የመስቀል ቅርፅ የተሠራባቸው ትናንሽ ዳቦዎች ገበታው ላይ ሲቀርቡ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ በእያንዳንዱ ዳቦ ውስጥ 11 ወይም 12 ዘቢብ የሚደረግ ሲሆን፣ ምሳሌውም ሐዋርያትን ለማስታወስ ነው፡፡

ሜክሲኮ

በሜክሲኮ በቺዝ ቀረፋና በቅሩንፉድ የጣፈጠ ዳቦ ለትንሣኤ ማቅረብ የተለመደ ነው፡፡ ቀረፋው ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን የእንጨት መስቀል የሚያመላክት ሲሆን፣ ቅሩንፉዱ ደግሞ የተወጋበት ሚስማር ተምሳሌት ነው፡፡ ዳቦው ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡

አብዛኞቹ የኦርቶዶክስ ክርስትና ተከታይ አገሮች ‹‹ኩሊች›› የተባለ ኬክ ያዘጋጃሉ፡፡ ከስንዴ ዱቄትና ከተለያዩ ቅመማ ቅመሞች፣ እንቁላል፣ ዘቢብ፣ ኦቾሎኒ የሚዘጋጀው ይህ ኬክ ቀጠን ብሎ ረዘም ያለ ነው፡፡ በትንሣኤ ዋዜማ ቅዳሜ ሌሊት የፀሎት ሥነ ሥርዓት ካለቀ በኋላ፣ በቄሶች ተባርኮ የሚቆረስም ነው፡፡ ይህ ኬክ በተለይ በቡልጋሪያ፣ ጆርጂያና ሩሲያ የተለመደ ነው፡፡ ምዕመኑም ዳቦው እንዲባረክለት በሌሊቱ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ ዳቦውን ይዞ ይገኛል፡፡

ብራዚል

በብራዚል ለትንሣኤ በዓል የሚቀርበው ምግብ ከተለነቀጠ ኦቾሎኒ፣ ከስኳርና ከካሳቫ ዱቄት የሚጋገር ዳቦ ነው፡፡

ዴንማርክ

ዴንማርክ ለትንሣኤ ማዕድ ማወራረጃ በተለየ ሁኔታ በሚጠመቀው ቢራ ትታወቃለች፡፡ በዴንማርክ ለፋሲካ በዓል የሚዘጋጀው ቢራ በሌሎች ጊዜያት ከሚዘጋጀው ጠንከር ያለ ነው፡፡

(ዘ ቴሌግራፍ)

********

ሆድ እና ህሊና

በመብል የወፈረን የቀፈቱን ክብደት

በኪሎ ሊፈርጅ

መንገድ ካለ ሚዛን … በተራ በተራ

ይወጣል … ይለካል ይወርዳል አልፎ ሒያጅ፡፡

ነገር ተገልብጦ

ሰው ሚዛን ላይ ወጦ

ማሰብ እና መሥራት …የዕውቀቱን ዳርቻ የሚለካ ነገር

በቴክኖሎጂ ውስጥ አንድ ቀን ቢፈጠር

ሚዛን ሲያይ የሚሮጥ

እሳቤው የከሳ ሺ ሰው እናይ ነበር፡፡

  • አንዳርጋቸው አበጀ ‹‹የማማት ፆመኛ›› (2005)

***********

 

ከሥራፈትነት የገላገለን አዳም ነው

አዳም ባመጣው ኃጢአት ነው የሰው ልጆች የምንሰቃየው የሚሉ ወገኖች ይኖሩ ይሆናል፡፡ አዳም የተከለከለው ዕፀ በለስ  በመብላቱ ወደ ምድር ተሰደድን ይሉ ይሆናል፡፡ ለኔ ግን አዳም ዕፀ በለስ መብላቱ ለበጐ ነው፡፡ አዳም ዕፀ በለስ  ባይበላና እስከአሁን በገነት የምንኖር ብንሆን ምን ዓይነት ሕይወት ነበር የምንኖረው? በጣም አሰልቺ ሕይወት ነበር የሚሆነው፡፡ የሰው ልጅ ምንም ነገር ሳይሠራ መኖር ምን ያህል አሰልቺ እንደሆነ ከሕይወት ልምዳችን የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ከሥራ ፈትነት የገላገለን ግን አዳም ነው፡፡ ምንም ዓይነት ሥራ በሌለበት ዓለም ምንም ዓይነት ጣፋጭ ሕይወት ሊኖር አይችልም፡፡ እርስ በእርሳችን እንኳን ምንም ነገር ማውራት ሐሳብ ለሐሳብ መጋራት አንችልም፡፡ ሥራ ከሌለ ምንም ዓይነት ሐሳብ አይኖርም፡፡ የሐሳብ ልዩነት ከሌለ ደግሞ የሐሳብ መጋራት የለም ማለት ነው፡፡

  • አብርሃም ሐዱሽ ‹‹ነገር በምሳሌ …›› (2005)

******

አሳ ጐርጓሪ

ውሻው ደንዲ ከተማ (ስኮትላንድ) የሚገኝ ሥጋ ቤት ዘሎ ገብቶ ሊቆረጥ ከተደረደረው ሥጋ በቅርቡ ያገኘውን መንትፎ ይሄዳል፡፡ ውሻው የጠበቃው ጐረቤቱ መሆኑን ያወቀው ባለ ሥጋ ቤት ስልክ ደውሎ “ውሻህ ከልኳንዳዬ ለጥብስ የሚሆን ምርጥ ሥጋ ቢሰርቅ ለደረሰብኝ ኪሳራ ተጠያቂ ትሆናለህ ወይ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡

“በሚገባ እንጂ፤ ለመሆኑ የሥጋው ዋጋ ስንት ነው?”

“ሰባት ፓውንድ ነው” አለ ባለሥጋ ቤቱ ተደስቶ፡፡

ከጥቂት ቀናት በኋላ ለባለ ሥጋ ቤቱ በፖስታ ቤት በኩል የሰባት ፓውንድ ቼክ ደረሰው፡፡ ከቼኩ ጋርም “ለምክር አገልግሎት የተጠየቀ ሒሳብ 150 ፓውንድ” የሚል ኢንቮይስ ተያይዞ ነበር፡፡

*************

ፀጉራሙ ባለመንጃ ፈቃድ

      ወጣቱ የመንጃ ፈቃድ ስላወጣ መኪናቸውን መጠቀም ይችል እንደሆነ ካህን አባቱን ጠየቃቸው፡፡ “አባቱም የትምህርት ውጤትህን ካሻሻልህ፣ መጽሐፍ ቅዱስህን ካጠናህ ፀጉርህን ከተስተካከልክ በጉዳዩ ላይ ልንገጋገር እንችላለን” አሉት፡፡

      ልጅየው ከወር በኋላ ነገሮችን አስተካክሎ መኪናቸውን መጠቀም ይችል እንደሆነ በድጋሚ ጠያቃቸው፡፡

      ውጤትህ ተሻሽሏል መጽሐፍ ቅዱስህንም በትጋት አጥንተሃል፡፡ ሆኖም ፀጉርህን አልተቆረጥክም አሉት፡፡

“አባዬ፣ ሰለዚህ ጉዳይ ብዙ ሳስብ ነበረ፡፡ የሳምሶን ፀጉር ረጅም አልነበረምን? ሙሴና ኖህ እንዲሁም ኢየሱስ ረጅም ፀጉር አይደል የነበራቸው?”

“እዚህ ላይ እውነት አለህ፣ ልጄ አሉ አባቱ “ነገር ግን እነዚህ የጠቀስካቸው ሁሉ የሚጓዙት በእግራቸው ነበር፡፡”
*****

 

‹‹ሚቺቃፓ›› የካፊቾ ባህላዊ ምግብ

 

ሚቺቃፓ የከብት ሥጋን እንደ ጉራጌ ክትፎ ሳይደቅ በጎረድ ጎረድ መልክ በመክተፍ የሚዘጋጅ የካፊቾ ብሔረሰብ ባህላዊ ምግብ ነው፡፡ ሚቺቃፓን ለማዘጋጀት በትኩሱ ከታረደ የከብት ሥጋ ከታናሽ ታላቅና ሽንጥ ላይ ጮማ ያልበዛበት ሥጋ ይመረጣል፡፡ ከዚያም ሥጋው በደንብ በተሞረደ ቢለዋ ዝርግ መክተፊያ ላይ ጎረድ ጎረድ (ቃፓ) ተደርጎ ይከተፋል፡፡ የተከተፈው ሥጋ በትልቅ የሸክላ ጣቢያ (ጣቦ) ላይ ይደረጋል፡፡ ነጭ ሽንኩርትና ጨው አንድ ላይ ተደቁሶ ሥጋው ላይ ይጨመራል፡፡ ከዚያም ቅቤ ኮራኖ (ትንሽ ማሰሮ) ውስጥ ተደርጎ ምድጃ ዳር በማስቀመጥ እሳት በደንብ መቶት መቅለጥ ሲጀምር ጎርድ  ጎረዱ ሥጋ ላይ ይጨመርና ይማሰላል፡፡ ሥጋው ግን እሳት አይነካውም፡፡ ጥሬውን ከነጭ ሽንኩርት፣ ጨውና ቅቤ ጋር ተዋህዶ የሚበላው፡፡ ማባያው ከምርጥ ቆጮ የተጋገረ ሳሳ ያለ ቂጣ ነው፡፡ ይህ ምግብ በዋናነት የሚዘጋጀው ለመስቀልና ሌሎች ዓመታዊ ክብረ በዓላት ሲሆን፣ አቅም ያለው ሰው በእንግዶች ሲጎበኝ አዘጋጅቶ በማቅረብ ዘመዶቹንም ሆነ ጓደኞቹን ሊያስተናግድበት ይችላል፡፡ አዳኞች የድኩላ ሥጋ በከብት ሥጋ ምትክ በመጠቀም እላይ በተጠቀሰው መልክ ሚቺቃፓ የሚያዘጋጁበት ሁኔታ አለ፡፡ ከከብትም ሆነ ከድኩላ ሥጋ የሚዘጋጀው ሚቺቃፓ ከተበላ በኋላ በደንብ የበሰለ የጤፍ ወይም ደጋ ከሆነ የገብስ ዶጮ (ቦርዴ ጠላ) ይጠጣበታል፡፡

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

Trending Articles