ሀገር ማለት ልጄ፣ ሀገር ማለት፤
እንዳይመስልሽ የተወለድሽበት ቦታ፣
የተወለድሽበት አፈር፣
እትብትሽ የተቀበረበት ቀድመሽ የተነፈስሽው አየር፤
ብቻ እንዳይመስልሽ፡፡
ሀገር ረቂቅ ነው ቃሉ፡፡
ሀገር ውስብስብ ነው ውሉ፡፡
ሀገር ማለት ልጄ
ሀገር ማለት ምስል ነው፣ በህሊና የምታኖሪው…
…በእውቀትሽና በሕይወትሽ
በውነትሽና በስሜትሽ
የምትቀበይው ምስል ነው፣
በህሊናሽ የምታኖሪው፤
ስወጅ ሰንደቅ ታደርጊው
ቢያስጠላሽ የማትቀይሪው፡፡
ሀገር ማለት የኔ ልጅ
ሀገር ማለት ቋንቋ ባንደበት አይናገሩት
በጆሮ አያዳምጡት
አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ አፋርኛ፣ ቅማንትኛ፡፡
ጉራግኛ ወይ ትግርኛ ብለው የማይፈርጁት፡፡
- ከበድሉ ዋቅጅራ ‹‹ሀገር ማለት ልጄ›› (2004 ዓ.ም.) የተቀነጨቡ ስንኞች
*****
‹‹አገር መውደድ…››
‹‹አገርን መውደድ ራስን መውደድ ነው፡፡ ሰው የሰውነቱ ክብር የሚታወቀውና የሚታፈረው አንገቱን ቀና አድርጎ በኩራት ለመናገርና ቃሉ ክብደት ለማግኘት የሚችለው ሐዘኑንና ልቅሶውን፣ ደስታውንና ዘፈኑ የሚያምርበት፡፡ ሰው ስለ መብቱ ቢሟገት የሚሰምርለት በአገሩ ነው…››
መስፍን ወልደማርያም ‹‹ኢትዮጵያዊነት፣ ልማት በኅብረት›› (1966 ዓ.ም.)
* * *
የአፍሪካውያን መካነ መቃብር በድሬዳዋ
ድሬዳዋ ውስጥ በተለምዶ ነምበር ዋን በሚባለው አካባቢ የሚገኘው የአፍሪካውያን መካነ መቃብር 70 አፍሪካውያን ወታደሮች ያረፉበት ነው፡፡ ከእነኚህ መካከል 60ዎቹ የፋሺስት ወራሪ ሠራዊትን ከኢትዮጵያ ምድር ጠራርጎ ለማስወጣት ከቃል ኪዳኗ አጋር የእንግሊዝ ጦር ጋር በምሥራቅ አፍሪካ በኩል የገቡት የቅኝ ግዛቶች (ኬንያ፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ…) ወታደሮች መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በቀብር ሥፍራው ከተቀበሩት አፍሪካውያን መካከል የአምስቱ አፍሪካውያን ዜግነትና ማነነት ግን አይታወቅም፡፡
ከ70ዎቹ አፍሪካውያን በተጨማሪ በጦርነቱ ወቅት የተገደሉ ሦስት የብሪታንያ አየር ኃይል አባል የነበሩ እንግሊዛውያን ቀብራቸው በሀገሬው የቀብር ሥፍራ ቢቀበርም ቆይቶ አስከሬናቸውን ለይቶ ማውጣት ባለመቻሉ በአፍሪካውያን መካነ መቃብር ውስጥ መታሰቢያ ተተክሎላቸዋል፡፡
ይህንን ታሪካዊ ሥፍራ የእንግሊዟ ንግሥት ኤልዛቤትና የኬንያው መሪ ጆሞ ኬንያታ የጎበኙት ሲሆን ለሀገራችን መስዋዕት ለሆኑ ለእነኚህ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን እንደ ሀገር ተገቢውን ክብር እየሰጠን መሆን ያለመሆኑ በሚገባ ሊጣራ ይገባል፡፡
- አዲስ ቸኮል፣ ከድሬዳዋ
* * *
አመፀኛ ዋሻ
ሰሜን ሸዋ፣ መንዝ ውስጥ ቀያ ገብርኤል በተባለ ቦታ የሚገኘው አመፀኛ ዋሻ እጅግ የገዘፈ ታሪክ ያለው ነው፡፡ ከወራሪው የፋሽስት ሠራዊት ጥቃት ለመሸሽ በዋሻው ውስጥ የተጠለሉ 5,500 ያህል ሰዎችን አረመኔዎቹ የፋሺስት ሠራዊት ወራሪዎች በመርዝ ጋዝ አፍነው ፈጅተዋቸዋል፡፡ በየካቲት ወር 2008 ዓ.ም. የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች የተወሰኑ የምክር ቤት አባላትና ሌሎች እንግዶች ከአካባቢው ነዋሪ ጋር በመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በዋሻው ውስጥ በመግባት ያንን አሰቃቂ የጠላት ግፍ ተመልክተዋል፡፡
- ‹‹እኔ ለአገሬ (፲፱፻፴፫ - ፳፻፰)››
* * *
ባፈነገጠ አለባበሳቸው ከስብሰባ የተባረሩት ሚኒስትር
በቅርብ የተሾሙት የደቡብ ሱዳኑ የመስኖና ውኃ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ማቢዮር ጋራንድ ደማቢዮር ሙሉ ጥቁር ለብሰው ቦው ታይ (ቢራቢሮ ከረባት) አድርገው ወደ አንድ ስብሰባ ያመራሉ፡፡ ስብሰባውን ይመሩ የነበሩት የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ሚኒስትሩን እንዳዩዋቸው በብስጭት ከስብሰባ አባረዋቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሚኒስትሩን ያባረሯቸው ለስብሰባ ከሚለበስ አለባበስ ያፈነገጠ አለባበስ በመከተላቸው ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በሚኒስትሩ ያልተገባ አለባበስ መበሳጨታቸውን የዘገበው ዴይሊ ሞኒተር፣ ሚኒስትሩ ቤታቸው ሄደው ቢራቢሮ ከረባታቸውን በረዥም ከረባት ለውጠው ጥቁር ኮፍያ አድርገው ቢመጡም በድጋሚ ወደ ስብሰባው እንዳይገቡ መከልከላቸውን አሳውቋል፡፡ የተለያዩ ግለሰቦች በጉዳዩ ላይ አስተያየት እየሰጡ ነው፡፡ አንዳንዶች የሚኒስትሩ አለባበስ እንደ ትልቅ ነገር ተወስዶ ከስብሰባ መታገዳቸው አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ሀገሪቱ ያለችበት ቀውስ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
