በታደሰ ማሞ
ጊዜ የለም፡፡ ምናልባትም አሉን የምንላቸው የዱር እንስሳት ነበር ሆነው በፎቶግራፍና በሥዕል ብቻ ለመጪው ትውልድ የምናሳይበት ጊዜ እየቀረበ ያለ ይመስላል፡፡ የዱር እንስሳት ከሰው ራቅ ብለው በራሳቸው የመኖሪያ ሥፍራ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ተደርገው ቢፈጠሩም፣ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖና የሰው ልጅ ወደ መኖሪያቸው ዘልቆ እየገባና በአደን መውጫ መግቢያ እያሳጣቸው ስላዋከባቸው፣ እነሆ በመጨረሻው የመጥፊያ ዘመናቸው ላይ ሆነውና መንታ መንገድ ላይ ቆመው የድረሱልን ጥሪ በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡
ይህ ጽሑፍ መነሻና መድረሻው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የዱር እንስሳትና የመኖሪያ አካባቢያቸው በከፍተኛ አደጋ ላይ መውደቃቸውንና ከመኖር ወደ አለመኖር እየተንደረደሩ መሆኑን መግለጽ ነው፡፡ እነዚህ የአገርና የሕዝብ ሀብት የሆኑት የተፈጥሮ ስጦታዎች አንዴ ከምድር ላይ ከጠፉ መልሶ ለማግኘት የሚቻልበት መንገድ ባለመኖሩ፣ ሳይቃጠል በቅጠል የሚለውን ብሂል በማስቀደም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ከጥፋት እንዲታደጓቸው አደራ ማለትና የእነሱ አንደበት ሆኖ ማስተጋባት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ በቱሪዝም መስህብነት በተለይ በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገቡት እንደ ላሊበላ፣ ፋሲል ግንብ፣ የሐረር ጀጎል ግንብ፣ የአክሱም ሐውልቶችና የመሳሰሉት አስታዋሽ አግኝተው እድሳት ሲደረግላቸው፣ በኢትዮጵያ ብቻ በብርቅዬነት የተመዘገቡት የዱር እንስሳት ግን አስታዋሽ አጥተው ህልውናቸው ከፍተኛ ችግር ውስጥ መውደቁን መንግሥትና ሕዝብ ተገንዝበው አስቸኳይ መፍትሔ እንዲፈልጉ ማድረግ የዚህ ጽሑፍ ቀዳሚ ዓላማ ነው፡፡
ለዚህም ነው ስለማይናገሩት የዱር እንስሳት እኛ እናውራላቸው፣ ልሳን እንሁናቸው፣ አንደበት እንሁናቸው በሚል ርዕስ ይህን ጽሑፍ ማዘጋጀት የፈለግኩት፡፡ ወዲህም የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የሥራ ባልደረባ በመሆን፣ በአገሪቱ የሚገኙ የዱር እንስሳት መኖሪያ ፓርኮችና መጠለያዎችን ከሞላ ጎደል ለመጎብኘት በመታደሉ በዱር እንስሳቱ ላይ የተፈጠሩ ጫናዎችን በቅርብ ርቀት ለማየት ችሏል፡፡ በዚህ መነሻ በምናቡ የሚመላለሰውን ዕረፍት የሚነሳ ጉዳይ ለአደባባይ ማብቃት መፈለጉም ሌላው ለዚህ ጽሑፍ መጻፍ ተጠቃሽ ምክንያት ነው፡፡
እዚህ ላይ ዶዶ የተባለችውን የወፍ ዝርያ በምሳሌነት ላንሳ፡፡ ዶዶ የተባለችው የወፍ ዝርያ በህንድ ውቅያኖስ አካባቢ በምትገኘውና የአፍሪካ አኅጉር ክፍል በሆነችው የሞሪሽየስ ደሴት ጫካዎች ውስጥ፣ እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የአካባቢው ጌጥ ሆና ትኖር የነበረች ፍጡር ናት፡፡ አውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች በተይም ፖርቹጋሎች ሥፍራውን እያሰሱ ሲደርሱ ግን የዚህች ወፍ ዕጣ ፈንታ ለጥፋት መጋለጥ ሆነ፡፡
ዶዶ መብረር የማትችል ነገር ግን ለመሮጥ የታደለች ቁመቷ እስከ አንድ ሜትርና ክብደቷም ከ10 እስከ 20 ኪሎ ግራም የሚመዝን እንዳነበረች በቅርቡ በእሷ ላይ ይፋ የሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ እነዚህ የቅኝ ግዛት አባዜ የተጠናወታቸው አሳሾች የዶዶ ዝርያዎችን እያጠመዱና እየያዙ ቀለባቸው በማድረግ ለወሬ ነጋሪ እንኳን ሳያስተርፉ ጨረሷቸው፡፡ ወደ ሌላ አካባቢ ለመሸሽ አቅሙ ያልነበራት ዶዶ የተፈጥሮ ጠላቶቹ ከሆኑት በተጨማሪ የሰው ልጆችም ዋና አሳዳጆቿ ሆነው ዝርያዋን አጠፉት፡፡ በሌላ ዓለም አንድም ተመሳሳይ ያልነበራት ዶዶ ታሪክ ሆና ነበረች ተብላ ቀረች፡፡ ሌላው ቀርቶ ዶዶ የጠፋችው ከካሜራ መፈልሰፍ በፊት በመሆኑ ትክክለኛ ገጽታዋንና መልኳን በዓይን አይተዋት የገለጿትን ሰምቶ ከመናገር በስተቀር፣ አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ስለማንነቷ ማስፈር አልተቻለም፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2007 ወዲህ በሞሪሽየስ ጫካዎችና ዋሻዎች በተደረገ አሰሳ በተገኙ ቅሪተ አካሎቿ ምን ዓይነት ቅርፅና መልክ እንደነበራት በመላምት ማስቀመጥ ተችሏል፡፡ ለዶዶ ከምድር መጥፋት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠያቂዎቹ የፖርቹጋል ቅኝ ገዢዎች ናቸው፡፡ የዶዶ መጥፋት መዘዙ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ዛሬ እንደ ዶዶ ለጥፋት የተጋለጡ ብዙ የዱር እንስሳት በአገራችን አሉ፡፡
በዚያው በሞሪሽየስ ምድር ላይ የሚገኘው ታምባላክ አኪዩ ወይም የዶዶ ዛፍ (Tambalac Ocque or Dodo Tree) የተባለው የዛፍ ዓይነት ወፏ ከጠፋች ከጥቂት ዓመታት በኋላ፣ ዝርያው ምን እንደነካው ሳይታወቅ ምድርን መሰናበት ጀመረ፡፡ ተመራማሪዎቹ ግራ ተጋብተው እሳት ሳይነካው የመጥረቢያ ዘር ሳያርፍበት እየጠፋ በሄደው በዚህ ዛፍ ላይ ምርመራቸውን ሲያደርጉ ምክንያቱን ደረሱበት፡፡ ለካስ የዚህ ዛፍ ፍሬ መብቀል የሚችለው ዶዶ የተባለችው ወፍ ከበላችው በኋላ በሆዷ ውስጥ አልፎ ከኩሷ ጋር መልሳ ስትጥለው እንደነበረ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ ሆኖም የዶዶ ወፍ በምድር ላይ ስለሌለች የዛፉን ፍሬ ተርኪ በተባለው የወፍ ወይም የዶሮ ዝርያ ከርስ እንዲያልፍ በማድረግና መልሶ የሚበቀልበትን ዘዴ በመፈለግ ዛፉን ለጊዜው ከመጥፋት ታድገውታል፡፡
የዶዶን ነገር ያለምክንያት አላነሳሁትም፡፡ በምድር ላይ የአንዱ መኖር ለአንዱ የቱን ያህል አስፈላጊ እንደሆነና የተፈጥሮ ሕግን ጠብቆ ሚዛናዊ በማድረግ ረገድ ምን ያህል የተቆላለፈና የተሳሰረ ነገር እንዳለ ለማሳየት ነው፡፡ ሆኖም ይህ የተፈጥሮ ሚዛን የሰው ልጅ ጣልቃ ሲገባበት በአጭር ጊዜ ተንዶ የቱን ያህል ለአደጋ እንደሚጋለጥም፣ ሌሎች ይህን መሰል አያሌ ምክንያቶችን በማንሳት ማስረዳት ይቻላል፡፡
የዱር እንስሳት በመንታ መንገድ ላይ
የዱር እንስሳት በተፈጥሮ በታደሉትና ከሰው ንክኪ ነፃ በሆነ ጫካ፣ ደን፣ ቁጥቋጦ፣ ሜዳማና ተራራማ ሥፍራ አሊያም በተራሮችና በውኃማ አካላት ውስጥ የሚኖሩ የተፈጥሮ ሀብትና በረከቶች ናቸው፡፡ ከደቃቃ ወይም ጥቃቅን ነፍሳት አንስቶ እስከ ትልቁ ዝሆንና ሻርክ ድረስ፣ እንዲሁም ከትንንሽ የአረም ዝርያዎች አንስቶ እስከ ትልልቁ የዋርካና የባህር ዛፍ ድረስ ተጠቃሽ የሆኑት የእንስሳትና የዕፅዋት ዝርያዎች፣ የዱር ሕይወትን ዑደትና መስተጋብር በመጠበቅ ብሎም ለአንዱ መኖር የአንዱ ማለፍ ግድ እየሆነና ተፈጥሮአዊ ሚዛኑን በመጠበቅ፣ ሚስጥራዊነታቸው እንደተጠበቀ ዛሬ ድረስ መዝለቃቸው ዋናው የተፈጥሮ ሚስጥር ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ ዛሬ የሰው ልጅ የቅርብ አጋር የሆኑት የቤት እንስሳት ቀደም ባለው ጥንታዊ ዘመን የዱርና የጫካ ነዋሪ እንደነበሩ በተለያዩ ጥናቶች ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬም ድረስ በየጫካው የሚኖሩ አምሳያዎቻቸውን በቅርብ ርቀት በመመልከት መገንዘብ ይቻላል፡፡ የሰው ልጅ በዱር ሕይወት ላይ በፈጠረው ጫናና አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት እ.ኤ.አ. እስከ 2014 ባለው ጊዜ የዱር ሕይወት ሀብት የሆኑ 52 በመቶ የዱር እንስሳትና ዕፅዋት ብቻ ቀርተው፣ 48 በመቶ የሚሆኑት መውደማቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የተፈጥሮን ዑደት በማመጣጠን በምድር ላይ የነበረው ሁሉ እንደነበረ እንዲዘልቅና የተፈጥሮ መዛባት እንዳይከሰት፣ በዱር ሕይወት ውስጥ የሚገኙ የዱር እንስሳትና ዕፅዋት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል፡፡ በየሚኖሩበት የአየር ፀባይና ሥፍራ ለመኖርና ራሳቸውን ለመተካት በሚያደርጉት ትግል ሲወድቁም ሆነ ሲጥሉ፣ የአኗኗር ዘይቤያቸውን በደመነፍስ በማስፈጸም የተፈጥሮ ግዴታቸውን ይወጣሉ፡፡ የዱር እንስሳቱ ለሰው ልጅ የምግብ ምንጭ ከመሆን አልፈው የምድርን ለምነት ለመጠበቅ፣ እንዲሁም ዕፅዋቱ ከምግብ ምንጭነታቸው ሌላ የባህላዊ መድኃኒቶች ምንጭ በመሆንና የሰው ልጆች የሚተነፍሱትን ንፁህ አየር ሰጥተው ካርቦንዳይ ኦክሳይድን በመውሰድ ረገድ፣ ተኪ የሌለው ድርሻ እንደሚያበረክቱ ተደጋግሞ የተባለ ጉዳይ ነው፡፡
በዱር እንስሳት ላይ የተጋረጠ አደጋ
የተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ እጅግ ሰፊ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት በተለይ ብርቅዬና ዋና ዋና በሆኑት የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ላይ የተጋረጠውን አደጋ የመብረቅ ብልጭታ በሚመስል ሁኔታ ማሳየት ግድ ይለኛል፡፡ በኢትዮጵያ 24 ብሔራዊ ፓርኮች፣ 21 የዱር እንስሳት ቁጥጥር አደን ቀበሌዎች፣ ሁለት የዱር እንስሳት መጠለያዎች፣ አምስት የዱር እንስሳት መኖሪያ ቀጣናዎችና አሥር የኅብረተሰብ ተኮር የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡
ከእነዚህ ውስጥ 12 ብሔራዊ ፓርኮችና ሁለት የዱር እንስሳት መጠለያዎች በኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን በቀጥታ የሚተዳደሩ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ እንደ አቀማመጣቸውና የሚገኙበት አካባቢ በክልል መንግሥታት ይተዳደራሉ፡፡ ባለሥልጣኑ ከአንድ ክልል በላይ የሚያዋስናቸውን ፓርኮችና መጠለያዎች የሚያስተዳድር ሲሆን፣ ክልሎች ደግሞ በገጸ ምድራቸው ውስጥ ከሌላ ክልል ጋር የማይዋሰኑ ፓርኮችን ያስተዳድራሉ፡፡ ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚዋሰኑትም በባለሥልጣኑ እንደሚተዳደሩ ይታወቃል፡፡
በአጠቃላይ በእነዚህ ፓርኮችና መጠለያዎች ውስጥ ብዙ ሺሕ ቁጥር ያላቸው የዱር እንስሳት ይኖራሉ፡፡ ስለእያንዳንዳቸው ለመግለጽ ቦታና ጊዜ የማይበቃ ከመሆኑም በላይ፣ አንባቢያንም ማሰልቸት ስለሚሆን በዋናነት በባቢሌ በዝሆን፣ በስንቅሌ በስዌይን ቆርኬ፣ በሰሜን ተራራዎች በዋልያ፣ በባሌ በቀይ ቀበሮና በደጋ አጋዘን፣ በአዋሽ በሳላና በመሳሰሉት ላይ የተጋረጡ አደጋዎችን በማሳየትና በወፍ በረር ቅኝት በመቃኘት፣ የሚመለከታቸው ሁሉ ከተኙበት እንዲነቁ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አምኜበታለሁ፡፡
የዋልያ የመጨረሻ ድምፅ
ዋልያን ከሌሎቹ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ብርቅዬ የዱር እንስሳት መካከል የተለየ የሚያደርገው፣ ከኢትዮጵያም በሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ብቻ የሚገኝ ለመጥፋት የተቃረበ የዱር እንስሳ መሆኑ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ለግጦሽ በነፃነት የሚሰማራባቸው በፓርኩ ውስጥ ያሉት እንደ ሳንቃበር፣ ቧሂት፣ ምጪብኝ፣ ጨነቅ፣ ሲሊቅና የሊማሊሞ ተራራ ጥጋ ጥጎችና ጫፎች ከአካባቢ አየር መለዋወጥ ጋር ተያይዞ ባለው ሁኔታ የቀድሞ ይዞታቸውን ከመልቀቃቸው በተጨማሪ፣ ነዋሪዎች ከብቶችን ይዘው ወደ አካባቢው መዝለቃቸው የዋልያን ኑሮ የበለጠ አጣብቂኝ ውስጥ ከተውታል፡፡
ዋልያ የተፈጥሮ ጥቃት አድራሾቹ የሆኑትን እንደ ነብር፣ ጅብ፣ የሎስ አሞራ፣ ቀበሮና የመሳሰሉትን ለመሸሽና ዝርያውን ለማስቀጠል የሚያደርገው ትግል በሰው ልጆች ጣልቃ ገብነትም እየተረበሸ መሆኑ ዘወትር በፓርኩ ውስጥ የሚስተዋል ጉዳይ ነው፡፡ የሰሜን ተራሮችን በዓለም አቀፍ ቅርስነት የመዘገበው ዩኔስኮ በአካባቢው የተፈጠረውን የሰዎች ጣልቃ ገብነት በአስቸኳይ ማስቆም ካልተቻለ፣ ፓርኩን ከዓለም አቀፍ መዝገብ ላይ እሰርዛለሁ ማለቱን ተከትሎ በመንግሥት ደረጃ የሚከናወኑ ሥራዎች ቢኖሩም ፈጥነው መፍትሔ የሚያመጡ ባለመሆናቸውና ከአንጀት ጠብ ለማለት ጊዜ የሚፈጅባቸው መሆኑ ለዋልያው ራስ ምታት የፈየደው ነገር የለም፡፡ ድምፅ በሌላቸው አካባቢ ሠራሽ ወጥመዶች እየታነቀ የሚያልቀው የዋልያ ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ የተፈጠረው ሁለገብ ጫና በዋናነት በዚያው አካባቢ ብቻ ለመኖር ተገዶ በሚገኘው ዋልያ አይቤክስ ላይ የፈጠረው ችግር፣ የዱር እንስሳው አድኑኝ ብሎ የሚጮህበት የመጨረሻ ወቅት ላይ የሚገኝ አስመስሎታል፡፡ የፓርኩ ጫና ከዋልያ በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኙትንና ብርቅዬ የሆኑትን ጭላዳ ዝንጀሮ፣ ቀይ ቀበሮ፣ የምኒሊክ ድኩላና የመሳሰሉት ላይ ውጥረት እንደፈጠረ ልብ ማለት ይገባል፡፡ በተለይ ቁጥሩ አንድ ሺሕ ለማይሞላውና የአካባቢው ጌጥ ለሆነው ዋልያ ፈጥነን ልንደርስለት ይገባል፡፡
የስዌይን ቆርኬ በውኃ ጥም የተቃጠለው አሳዛኝ ፍጡር
የስዌይን ቆርኬ ሌላው ኢትዮጵያዊ ብርቅዬ የዱር እንስሳ ነው፡፡ ይህን የዱር እንስሳ ከሻሸመኔ ወደ ሃላባ በሚወስደው መንገድ አጄ ላይ ሲደርሱ በስተግራ ተገንጥሎ በመግባት፣ ዙሪያዋን በሰዎች በተከበበችው የስንቅሌ የቆርኬዎች መጠለያ ሜዳ ላይ ግራ ተጋብቶ ወዲያ ወዲህ ሲል መንጋውን ማየት ይቻላል፡፡
በዚች የበሬ ግንባር በምታህል ሣራማ ምድር ላይ ቀንም ሌትም ወዲህ ወዲህ እያሉ የሚውሉት ከሰባት መቶ ያልዘለሉ ቆርኬዎች፣ በተለይ ለመኖር አስፈላጊ የሆነውን ውኃ ለመጠጣት የሚችሉበት አማራጭ ሁሉ በሰዎች ከበባ በመታፈኑ በምን ተዓምር እየኖሩ እንደሆነ ለመረዳትም ይከብዳል፡፡ ገራገሮቹ የመጠለያው ሠራተኞች የጧት ጤዛ እየላሱ ነው የውኃ ጥማቸውን ለመመለስ የሚሞክሩት የሚል ቀልድ መሰል እውነታ ቢናገሩም፣ ቀደም ባለው ዘመን ወደ ሐዋሳ ሐይቅና ከአካባቢው በቅርብ ርቀት ወደሚገኘው ብላቴ ወንዝና ገባሮቹ እየዘለቁ ይጠጡ የነበረበት መንገድ ሁሉ በአካባቢው በሰፈሩ ዜጎች ስለተዘጋ፣ መድረሻው ጠፍቷቸው እልቂታቸውን እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡
ዋናው ችግራቸው የውኃ ጥም ይሁን እንጂ የሚወልዷቸው ጥጆችና መንጋው ራሱ በተለይ በአካባቢው በብዛት በሚገኘው የጅብ መንጋ መወረራቸው፣ እንዲሁም የግጦሽ መሬታቸው በቤት እንስሳት ዘወትር መወረሩና በአካባቢው የእርስ በርስ ግጭት በተፈጠረ ቁጥር የእልህ መወጫና የጥይት ሲሳይ መሆናቸውም ሌላውም አጣብቂኝ ነው፡፡ በተለይ የከርሰ ምድር ውኃን ለማውጣት የተደረገው ጥረት ከመሬት ሥር በቅርብ ርቀት ውኃ አልተገኘም በሚል ሰበብ ፍፃሜ አለማግኘቱን፣ ሌሎችም ተደራራቢ ችግሮች በአፋጣኝ ምላሽ ካልተሰጣቸው የስዌይን ቆርኪ ጉዳይ በቅርቡ ተረት ተረት ይሆናል የሚል ሥጋት በሁሉም ዘንድ አለ፡፡
የደጋ አጋዘን አደን መውጫ መግቢያ አሳጥቶታል
በባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ፣ በአርሲና በምዕራብ ሐረርጌ ተራራማ ቦታዎች ላይ ደጋውን የአየር ክልል እየተከተለ የሚኖረው የደጋ አጋዘን ሌላው ኢትዮጵያዊ ብርቅዬ የዱር እንስሳ ነው፡፡ ይህ እንስሳ የግጦሽና የመጠጥ ውኃ ችግሩ በአንፃራዊነት ከሌሎች የተሻለ መሆኑ ቢነገርለትም፣ ሕጋዊም ሆኑ ሕገወጥ አዳኞች በብርቱ የሚፈልጉት በመሆናቸው ሁልጊዜም የጥይት ድምፅ ሲያስበረግገው ይኖራል፡፡
ሕጋዊ አዳኞች ለአንድ ለአደን ለደረሰ የደጋ አጋዘን 15 ሺሕ ዶላር እንዲከፍሉ መጠየቃቸው ተፈላጊነቱን ያበዛው ሲሆን፣ ብርቅዬ እንስሳ መሆኑ እየታወቀ በሕጋዊ አደን ስም ህልውናው ለአደጋ የተጋለጠ እንዲሆን የተፈረደበት መሆኑ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ተራራ እየተከተለ በሚኖርባቸው አካባቢዎች ያሉ ትልልቅ ዕፅዋት ለፋብሪካ ፍጆታ የሚመነጠሩ መሆናቸውና አንዳንዴም ግራ እየተጋባ ለአደጋ በሚያጋልጠው ሥፍራ እንዲኖር መገደዱም የደጋ አጋዘን ሌላው ሥጋት ነው፡፡
ሳላና አዋሽ እየተራራቁ ነው
በእርግጥ ሳላ ብርቅዬ የዱር እንስሳ አይደለም፡፡ ሆኖም ማንኛውም ወደ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ የሚዘልቅ እንግዳ ሳላን ሳይመለከት መመለስ ራስ ምታት ይሆንበታል፡፡ በረጃጅም ቀንዶቹ ጀርባውን እያከከ በአዋሽ ሳራማ ሜዳዎችና በዋናው መንገድ ዳር ይታይ የነበረው ሳላ ዛሬ ዛሬ ህልም ሆኗል፡፡
በዋናነት የሚውልበት መስክ በቤት እንስሳት መወረሩ፣ ከሁሉ በላይ ውኃ ለመጠጣት ወደ አዋሽ ወንዝ ያቀናባቸው የነበሩ መንገዶች በኢንቨስትመንት ሰበብ የሰው መተራመሻ መሆናቸው፣ እንዲሁም ሕገወጥ አዳኞች ለሥጋው ሲሉ እሱ ላይ መተኮሳቸው የአዋሽ ጌጥ የሆነውን ሳላ ዱካው ከአካባቢው እንዲጠፋ ምክንያት ሆነውታል፡፡
የባቢሌው ዝሆን ሊያከትም ጫፍ ደርሷል
የዱር እንስሳትን ጫና ተመልክተው የሚያዝኑ ሰዎች ከሁሉ በላይ ደም እንባ የሚያለቅሱበት ሥፍራ የባቢሌው ዝሆን ስቃይ መሆኑን ሁሉም ይስማሙበታል፡፡ በግዙፍነቱ ልዩ ግርማ ሞገስ የተላበሰውን የአፍሪካ ዝሆን ለመጠበቅ ተብሎ የተከለለው የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ሥፍራ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ በሕገወጥ ሰፋሪዎችና ዝሆንን ለጥርሱ ሲሉ በሚያድኑ ሰዎች በመሞላቱ የባቢሌ ዝሆኖች ጠፍተዋል ማለት ይቀላል፡፡ ቁጥራቸው 50 የማይሞላ ዝሆኖች ከሰዎች ንክኪ የተሻለ ነው በሚባለው ፈዲስ አካባቢና ሌሎች ሥፍራዎች ወዲያ ወዲህ እያሉ ራሳቸውን ለማቆየት ቢሞክሩም፣ ጫናው ከመቼውም ጊዜ በላይ በርክቶባቸው ዋና ዋናዎቹና ትልልቆቹ ዝሆኖች አልቀው፣ ትንንሾቹ ወይም ኤልሞሌ የሚባሉት ብቻ በጥቂቱ እየታዩ እንደሆነ ለማየት ዕድሉ የተፈጠረላቸው የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ፡፡ በየዓመቱ አርባና ሃምሳ ዝሆኖች እየተገደሉ ቁጥራቸው ከ300 የማይበልጡ ዝሆኖች አሁን በባቢሌ አሉ እያሉ ለመናገር የማይቻልበት ጊዜ ላይ እንደተደረሰ መረዳት ይቻላል፡፡ ባቢሌን ያለ ዝሆን ማሰብ እንዴት ይከብዳል? በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው ቀይ ቀበሮም በተለይ ከለማዳ ውሾች ጋር በሚኖረው ግንኙነት በውሻ በሽታና በአላስፈላጊ መዳቀል ዝርያው አደጋ ላይ እየወደቀ መሆኑን ተመራማሪዎች እየገለጹ ነው፡፡
ማጠቃለያ
ለማሳያ ያህል በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ላይ የተጋረጡት ችግሮች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ የዱር እንስሳት የመኖሪያ ፓርኮች ያለባቸው ጫና የበረታበት ጊዜ ነው፡፡ እነ ቻይና በአንድ ወቅት የተፈጥሮ ሀብታቸውን አውድመው ከችግር ከወጡ በኋላ፣ መልሰው ደኑን መትከልና አካባቢን አረንጓዴ ማድረግ ቢችሉም በደኑ ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን የዱር እንስሳት ግን መመለስ አልቻሉም፡፡
አሁን በኢትዮጵያችን እየተፈጠረ ያለው ሁኔታም የዚህ ተመሳሳይ በመሆኑ፣ በተለይ ለብርቅዬዎቻችንና ዳግም ልንተካቸው ለማንችላቸው የዱር እንስሳቶቻችን ፈጥነን ልንደርስላቸው ይገባል፡፡ ለመሆኑ ይህንን ከባድ አገራዊ አደራ መሸከም ያለበት ማን ይሆን? ʻቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝምʼ እንዳይሆን ብቻ!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው tademaa@yahoo.comማግኘት ይቻላል፡፡
