በማሚ ኮ.
ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ገነት የሆነ ሥፍራ አለ፡፡ ሱባ የተፈጥሮ ደን በመባል ይታወቃል፡፡ ሱባ ስትደርሱ መግቢያው አካባቢ የተለያዩ መረጃ ጽሑፎችና የሐሳብ መስጫ የምትመስል አነስተኛ ሳጥን አለች፡፡ በሳጥኗ ላይ የተጻፈው ጽሑፍ ጎብኚዎችን የሚያስገርም ብቻ ሳይሆን የሚያመራምርም ነው፡፡ የጽሑፉ መልዕክት ማነው ልብ ያለው ከፍቶ የሚያየው? የሚል ጥያቄ የሚያጭር ነው፡፡ በሳጥኗ ላይ የተጻፈው ጽሑፍ ‹‹አደገኛ አውሬ›› የሚል ነው፡፡ እንዴት በዚህች በምታህል ሳጥን ውስጥ አውሬ ሊኖር ይችላል? በማለት ሁሉም ይጠያየቃል፡፡
አንዳንዶች ይህን አውሬ ማየት አለብን ሲሉ ሌሎች ደግሞ 'ጎመን በጤና'ብለው ይሸሻሉ፡፡ ደፋሮች ሳጥኗን እየተሳቀቁ ከፈት አድርገው ሲመለከቱ በሳቅ ፍርስ ይላሉ፡፡ ምንድነው? ሲባሉ አይናገሩም፡፡ 'ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል'እንዲሉ ሁሉም አደገኛውን አውሬ ይመለከቱታል፡፡ በሳጥኗ ውስጥ የተቀመጠው የፊት መስታወት ነው፡፡ እናም የሚያዩት የራስዎን ምሥል ነው፡፡
ይህም ለተፈጥሮ አደገኛው አውሬ የሰው ልጅ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በተገላቢጦሹ ግን ምንም የማያውቁትን የዱር እንስሳት እኛ ‹‹አውሬ›› ብለን እንጠራቸዋለን፡፡ ከልጅነታችን ጀምሮ አውሬ የሚለውን ቃል በአስፈሪነትና በጨካኝነት ተምሳሌትነት ተቀርፆብን ስላደግን፣ የዱር እንስሳቱን እንድንፈራና እንደ ጠላት እንድናያቸው ተደርገናል፡፡
የዱር እንስሳቱ ተፈጥሯዊ መኖሪያ ቤታቸው በሰው ልጅ እየተጨፈጨፈ አልሞት ባይ ተጋዳይ በሆኑበት ሁኔታ፣ የአውሬ ተግባር የፈጸመባቸው ሰው በተገላቢጦሹ የዱር እንስሳቱን አውሬ ብሎ ይጠራል፡፡
እኛ ሰዎች ያለንበትን (የሠፈርንበትን) መሬት በአግባቡ ጠብቀን መጠቀም ሲገባን፣ ማልማትን ትተን ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም ፖሊሲ የእኛን ድርሻ ጨርሰን የዱር እንስሳት መኖሪያቸውን ስንመነጥር የዱር እንስሳቱ ቁጡና አደገኛ ቢሆኑ እንዴት አውሬ ሊባሉ ይገባል? የትኛው ግለሰብ ነው አጥሩ ሲነቀነቅ በዝምታ የሚያልፈው? ሁሉንም እንደ ራስ ማየት ተገቢ ነው፡፡ የዱር እንስሳት ካልተተናኮሏቸው በስተቀር በጣም ሰላማዊ መሆናቸውን ከአባቶቻችን ነባር ዕውቀት መረዳት ይቻላል፡፡ ‹‹ግራ ዓይኔን …›› እያሉ ነብርን ያህል አዳኝ እንስሳ በፍቅር ይመልሱታል፡፡ የቃሉን ትርጓሜ ተረድቶ እንዲተዋቸው ሳይሆን የማጥቃት ተልዕኮ እንደሌላቸውና ሰላማዊ መንገደኛ መሆናቸውን ለማሳየት ነው፡፡
መንግሥትም እነዚህን የዱር እንስሳት ብቻ ሳይሆን ብዙኃ ሕይወቱን ለመጠበቅ ከሃያ በላይ ብሔራዊ ፓርኮችን አካሏል፡፡ ፓርኮቹንም በበላይነት እንዲያስተዳድር የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣንን በአዋጅ አቋቁሟል፡፡ ተቋሙ ከዚህ በፊት እንደ ቴኒስ ኳስ ከአንዱ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ወደ ሌላው ከመንከላወሱም በላይ አደረጃጀቱም እስከ መምርያ ደረጃ የወረደ ነበር፡፡ አሁን የተሻለ ሥራ ይሠራል ተብሎ ሲጠበቅ በመምርያ ደረጃ ከነበረበት የበለጠ ዘቅጦ ፓርኮችን ወደ መዝጋት ደረጃ ደርሷል፡፡
በአንድ መድረክ ላይ የባለሥልጣኑ የሥራ ኃላፊዎች በሪፖርታቸው የያንጉዲራሳ ብሔራዊ ፓርክን አካተው ያቀርባሉ፡፡ ከአፋር ክልል የመጡ የዘርፉ የሥራ ኃላፊ ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት በተዘጋ ፓርክ ስም እስከ ዛሬ በጀት ይያዛል ወይስ ሌላ ያንጉዲራሳ ፓርክ አቋቁማችኋል? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ በመድረኩ የነበርን ሁላችን ደንግጠናል፡፡ ያንጉዲራሳ ሠራተኞቹ ተነስተው ተዘጋ እንጂ ከመዘጋት ያልተናነሰ ህልውናቸውን ያጡ ፓርኮች በርካቶች ናቸው፡፡
ብዙዎቻችንም አንድ ብሔራዊ ፓርክ ሲዘጋና ሲጠፋ ሕመሙ አይሰማንም፡፡ ምክንያቱም ፓርኮች ለእንስሳቱ መኖሪያነት እንጂ ለእኛ የውኃ ማማና የንፁህ አየር መሠረት መሆናቸውን ጠንቅቀን ስላልተረዳነው፡፡ ዛሬ ተፈጥሮውን በከፍተኛ ሁኔታ ስለጎዳነው ኤልኒኖ በጎርፍና በድርቅ ሲያሰቃየን ከተማ ላይ ያለነው ዜናውን እንኳን ትኩረት ሰጥተን አናደምጥም፡፡
የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ከ40 በላይ ወንዞች የሚመነጩበት ሥፍራ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ምን ያህል ወንዞች እንደሚመነጩበት የቅርብ ጊዜ መረጃ የለኝም፡፡ ግን አሥር ያህል ወንዞች መመንጨት ከቻሉ በግሌ ደስተኛ ነኝ፡፡
የአገሬ አርሶ አደር ወርቃማ የነበረውን መሬቱን በአግባቡ መጠበቅ ተስኖት በመራቆቱ ዛሬ ለረሃብ ሊዳረግ ችሏል፡፡ አሁን ከተኛበት ነቅቶ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እያለ በጂጊ እንዲሰማራ አስገድዶታል፡፡ ያኔ ግን በመጠበቅ ብቻ ለዚህ ችግር ሳይጋለጥ በኖረ ነበር፡፡
የብሔራዊ ፓርኮቻችን ዕጣ ፈንታም ተመሳሳይ ነው፡፡ ትናንት ያንጉዲራሳ ብሔራዊ ፓርክን ዘግተናል፡፡ ዛሬ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክም ከሞት አፋፍ ስለመሆኑ ሄዶ ማየት ላልቻለ የሪፖርተር ጋዜጣ የእንግሊዝኛውን ዕትም የፌብሩዋሪ 13 ቀን 2016 ማየት በቂ ነው፡፡
ዛሬ በችግር ያልታጠሩ ብሔራዊ ፓርኮች የሉንም፡፡ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እንኳን የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የዕለት ዕቅዱንም የሚፈጽም አይመስልም፡፡ ጫካ ላይ ያሉት የፓርክ ዋርደን (ኃላፊ) እና ስካውቶች (የጥበቃ ሠራተኞች) እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ይከፍላሉ፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከስምንት በላይ ስካውቶች በሕገወጦች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ የባለሥልጣኑ የሥራ ኃላፊዎች ግን ሥራ ላይ ያሉ አይመስሉም፡፡ መሥሪያ ቤቱን የሚቆጣጠር የበላይ አካል ያለው አይመስልም፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ባለጉዳይ የሚያስተናግዱት ሰኞ ቀን በመሆኑ አራት ሰኞዎች ብመላለስም አንዴ ከአገር ውጭ ናቸው፣ አንዴ ስብሰባ ላይ ናቸው በሚል ምክንያት ለአንድ ጉዳይ ከሦስት ወራት በላይ እሳቸውን በአካል ማግኘት አልተቻለም፡፡ ተግባራዊ የማያደርጉትን ፕሮግራም ቢሮአቸው በር ላይ ከሚለጥፉ የብርቅዬውን የደጋ አጋዘን ፎቶ ቢለጥፉ ዓይናችን ጥሩ ነገር አይቶ ይመለሳል፡፡
ተማሪ ሳለሁ የልማታዊ ጋዜጠኝነት መምህራችን የአፍሪካ ጋዜጠኝነት 'የኮክቴል ጆርናሊዝም ነው'ብሎ ነግሮን ነበር፡፡ በእርግጥም ተመርቄ ሥራ እንደጀመርኩ የዜናዎቻችን መቼት ሒልተንና ሸራተን ሆኑ፡፡ ከሰኞ እስከ ሰኞ በየስብሰባ አዳራሹ የሚሰየሙ የሥራ ኃላፊዎችስ ምን እንበላቸው? የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ይሆኑ? እርሳቸውን በሚመለከተው ብቻ ሳይሆን ባለሙያ ሊሳተፍበት በሚገባ ስብሰባ ላይ ሁሉ የሚሳተፉ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ከአገር ውጭ ሲሆን፡፡ ለነገሩ ከወረዳና ከዞን አመራርነት ይዘውት የመጡት የካበተ ልምድ ሊሆን ይችላል፡፡ መደበኛ ሥራቸውን ለመሥራት መቸገራቸውን ያፈጠጡ የተቋሙ ችግሮች ማሳያ ናቸው፡፡
በዚህም የተነሳ በአብዛኞቹ ብሔራዊ ፓርኮች ያሉ ሠራተኞች ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ነግሶባቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ የማኅበራዊ ድረገጽ ከፍተው በአቅማቸው እየታገሉ ይገኛሉ፡፡ እኔም በተቋሙ ያሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመረጃ አሰደግፌ በሌላ ጽሑፍ እመለሳለሁ፡፡ አሁን ግን የተፈጥሮ ሀብቱ መዳን ስላለበት በዚያ ላይ ማተኮሩን ወድጃለሁ፡፡
የኦሞና የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርኮች የተጋረጡባቸውን አንገብጋቢ ችግሮች የሚዳስስ ዓውደ ጥናት ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በሁለቱ ብሔራዊ ፓርኮች ላይ እየደረሰ ያለው ጥፋት በጥናቱ መሠረት ኅሊናን ያደማል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በልጆቻችን መወቀስ ብቻ ሳይሆን፣ እዚያ ሳንደርስ በብዙ ከተሞቻችን የምንሰማው የውኃ ጥማት አጥፍቶ የመጥፋት ተግባራችን ዋነኛ ማሳያ ነው፡፡
እነዚህን ሁለት ብሔራዊ ፓርኮች ለማልማት ከአሥር ዓመት በፊት አፍሪካን ፓርክስ የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ተረክቧቸው ነበር፡፡ የዚህ ድርጅት ባለቤት ሆላንዳዊው ባለሀብት ፓል ቫን ቫሊዝንግን ይባላሉ፡፡ የአፍሪካ መንግሥታት ቅድሚያ የሚሰጧቸው እንደ ጤና፣ ትምህርትና የመሳሰሉ ጉዳዮች ስላሉባቸው የተፈጥሮ ሀብታቸውን ትኩረት ሰጥተው ለመጠበቅ ይቸገራሉ፡፡ ስለሆነም በዚህ በኩል እኛ ልናግዛቸው ይገባል በማለት ነው አፍሪካ ፓርክስን የመሠረቱት፡፡
የባለሀብቱን መልካም ሐሳብ የተረዱት የወቅቱ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ግብዣ ለማቅረብ የቀደማቸው አልነበረም፡፡ ፓል ቫንም ወደ ትልልቆቹ ብሔራዊ ፓርኮች ሳይሆን የሄዱት፣ በብዝኃ ሕይወቱ የበለፀገው ግን በሰዎች ታጥሮ ሥጋት ላይ ወደ ነበረው ማራኬሌ ጥብቅ ሥፍራ ነበር፡፡ ሃያ ሁለት ሺሕ ሔክታር ላይ የሠፈረውን ጥብቅ ሥፍራ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ግንዛቤ በመፍጠር ከአካባቢው በማስወጣት መሠረተ ልማት ወደ ተሟላበት አካባቢ በማስፈር፣ የማራኬሌ ጥብቅ ሥፍራን ሁለት መቶ ሃያ ሺሕ ሔክታር ስፋት ያለው ብሔራዊ ፓርክ በማድረግ በባለሀብት፣ በመንግሥትና በማኅበረሰብ ተሳትፎ የተመሠረተ ስኬታማ ተግባር ማሳያ ተደርጎ የሚጠቀስ ፓርክ ሆኗል፡፡
አፈሩን ገለባ ያርግላቸውና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ኔዘርላድስ ለሥራ በሄዱበት ወቅት እኚህን ባለሀብት በመንግሥት በኩል የሚጠበቀውን ድርሻ ለመወጣት ቃል ገብተውላቸው በመጋበዝ፣ ድርጅታቸው የኦሞንና የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርኮችን ለማልማት ወደ ኢትዮጵያ ይገባል፡፡ በተለይ በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ውጤታማ የሆነ ሥራ እየሠራ ቢሆንም፣ በመንግሥት በኩል በፓርኩ ውስጥ የሠፈሩትን ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ማንሳት ባለመቻሉ ድርጅቱ ሥራውን ለማቋረጥ ተገዷል፡፡
ይኼ ድርጅት የተፈጥሮ ሀብቱን ጥበቃ እንጂ ትርፍን መሠረት ያደረገ አልነበረም፡፡ በደቡብ አፍሪካ፣ በማላዊ፣ በሞዛምቢክና በናሚቢያ ያከናወናቸው ተግባራት የድርጅቱን ውጤታማነት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ እኛ ግን የመጣልንን አጋዥ እንኳን በአግባቡ መጠቀም አልቻልንም፡፡ የአገራችን መሪ የገቡትን ቃል እንኳን የሚፈጽም አመራር ማግኘት አልቻልንም፡፡ በዚህም የሚጠየቅ አካል አላየንም፡፡
ባለሥልጣኑ በየመድረኩ የሚደሰኩሩ ሰዎች አሉት፡፡ ለተቋሙ መሠረት የሆኑት ብሔራዊ ፓርኮችን ለመታደግ ግን አንድ ስንዝር ሲራመዱ አይስተዋሉም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እንዲህ ዓይነት ተቋማት መመራት ያለባቸው ሳይንሱን በሚረዱ ባለሙያዎች ሊሆኑ ይገባል፡፡ መድረክ ላይ መደስኮርና የተግባር ሰው መሆን ለየቅል ናቸው፡፡ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን ገጽታ በመገንባትና ያሉበትን ጫናዎች ለሕዝብ በማውጣት ተቋሙ ወደ ተሻለ አቅጣጫ እንዲመጣ ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ያስፈልገዋል፡፡
የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በፓርኩ እምብረት ላይ የሠፈሩት ነዋሪዎች ከፓርኩ ክልል ካልወጡ ፓርኩን ለመሰረዝ ዩኔስኮ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ የሥጋት መዝገብ ላይ አስፍሮታል፡፡ እነዚህን በግጭ መንደር የሠፈሩ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር ከ15 ዓመታት በላይ የፈጀ ሒደት ነው፡፡ በባለሥልጣኑ ሳይሆን በክልሉ መንግሥትና በፓርኩ ውስጥ በሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከፍተኛ ጥረት ነዋሪዎቹ በደባርቅ ከተማ ለመሥፈር ተስማምተው የቦታ ርክክብ ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል፡፡ ይኼ ስኬት ለዘርፉ ትልቅ ዜና ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ብሔራዊ ፓርኮቻችን ተምሳሌት የሚሆን ነው፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ ቀድሞ ከአሥር ቀናት በፊት ሲገኝ አንድም የዜና ዘጋቢ ድርጅት አልጠራም፡፡ ‹‹ጥሪ ብትባል ቀድማ ተገኘች›› ነው ያሉት አበው? ሌላው ቀርቶ ብሔራዊ ጣቢያ የሆነውን ኢቢሲን እንኳን አልጠራም፡፡ ይኼ ብቻ ሳይሆን ሥነ ሥርዓቱ ለዶክመንት እንኳን ተቀርፆ እንዳይቀመጥ የተቋሙ የካሜራ ባለሙያ እንዲገኝ አልተደረገም፡፡ በእንዲህ ዓይነት ወሳኝ ሥራ ላይ የተሰጠውን ተግባር የማይፈጽም ኃላፊ የሕዝብ ግንኙነት ተቋሙ በምን ዓይነት አመራር እጅ እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡
የኢትየጵያ የዱር እንስሳት በስብሰባ ናፈቂ ‹‹አውሬዎች›› ተበልተው ሳይጠፉ ልንታደጋቸው ይገባል፡፡ አብዛኞቹ ብሔራዊ ፓርኮቻችን ከዱር እንስሳት ይልቅ የቤት እንስሳት የሚታዩባቸው በመሆኑ የባለሥልጣኑ ተጠሪነት ከባህልና ቱሪዝም በአፋጣኝ ወደ የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር መዛወር ይኖርበታል፡፡ የተፈጥሮ ሀብቱ እንዲመለስ በባለሙያዎች መመራት ስላለበት መንግሥት አፋጣኝ ዕርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ በአገራችን የሚከናወኑ ልማቶች ለማንም ሳይሆን ለእኛ ነው፡፡ የተፈጥሮ ሀብታችን መጠበቁም ለማንም ሳይሆን ለእኛ ነው፡፡ ሁላችንም ማየት ያለብን እንደ አገር እንጂ በተሰማራንበት መስክ ብቻ መሆን የለበትም፡፡
በመንገድ ዘርፍ ለተሰማራው ቤቱ ኤሌክትሪክ ያስፈልገዋል፡፡ ይኼኛውም መንገድ ያስፈልገዋል፡፡ እንደ አገር አስበን ሥራ መሥራት ካልቻልን ለሌላው ዘርፍ ትኩረት ሳንሰጥ የተቋማችንን ጥቅም ብቻ ማሰብ ድምር ውጤቱ የዜሮ ብዜት ነው የሚሆነው፡፡ ዛሬ የብዝኃ ሕይወት መጥፋት የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ሆኗል፡፡ ብሔራዊ ፓርኮች ደግሞ ብዝኃ ሕይወትን በመጠበቅ የማይተካ ሚና ነው ያላቸው፡፡ የአገራችንን የዱር እንስሳ ለመታደግ ከቢሮ ‹‹አውሬዎች›› ተጀምሮ እስከ ታች ያሉትን ሕገወጥ ተግባር ፈጻሚ ‹‹አውሬዎች›› ማጥፋት ባይቻል እንኳን ሊቀነሱላቸው ይገባል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
