Quantcast
Channel: ዓለማየሁ ጉጀ
Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

መሥራትና ማትረፍ በሥነ ምግባር ካልተደገፈ ለአገር ጠንቅ ነው

$
0
0

በጌታቸው አስፋው

ኢኮኖሚክስ ሲጀምር የሞራልና የሥነ ምግባር ጥበብ ሆኖ ነው የጀመረው፡፡ በአርስቶትልና በፕሌቶ ጭምር ስለሀብት ይዞታና አጠቃቀም በሥነ ምግባር ደንብ የተጠና ሲሆን፣ በተለይም ንግድ የማኅበረሰብ ጠንቅና ውጉዝ ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡ ሮማውያንም የግሪኮችን ወርሰው ለንግድ በጎ አመለካከቶች አልነበራቸውም፡፡ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከጥሬ ገንዘብ ንግድ (ብድር) ወለድ መውሰድን እንደ ነውር ቆጥራ ታወግዝ ነበር፡፡ በእስልምና ሃይማኖት እስከ ዛሬም ድረስ በባንኮች የወለድ አልባ ብድር አገልግሎት ይሰጣል፡፡

ከመካከለኛው ክፍለ ዘመን በኋላም የተለያዩ የኢኮኖሚ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች ተራምደዋል፡፡ አሥራ ሰባተኛውንና አሥራ ስምንተኛውን ክፍለ ዘመን በተለይ የፈረንሣዮችን አመለካከት የገዛው የፊዚዮክራቶች አስተሳሰብ ተጨማሪ እሴት የሚፈጠረው በግብርናው ብቻ ነው፡፡ በሌላው ሥራ ሁሉ በግብርና የተፈጠረውን ተጨማሪ እሴት ለማኅበረሰቡ ማከፋፈል ነው እንጂ፣ ምንም ተጨማሪ እሴት አይፈጠርም ብለው ከግብርና ውጪ ያለውን ሥራ ያናንቁ ነበር፡፡

በካርል ማርክስ የኮሙዩኒዝም ፍልስፍና ካፒታሊዝምን ሲተነትን ካፒታል ራሱን መልሶ ይተካል እንጂ አይወልድም፡፡ ወለድ ካፒታሊስቱ ከወዛደሩ የሚመዘብረው የወዛደሩ ላብ ነው ብሎ ነበር፡፡

 

በቀድሞ የሶሻሊስት አገሮች ከአዕምሮ ሥራ ይልቅ የሚያለፋና የጉልበት ሥራ የበለጠ ደመወዝ ያስገኝ ነበር፡፡ እንደዚሁም ደግሞ የመዝናኛ፣ የሕዝብ ትራንስፖርት፣ የመንግሥት የፍትሕ፣ የፀጥታና የሕግ የማስከበር አገልግሎቶች በሌሎች የሥራ ዓይነቶች የተፈጠረውን ተጨማሪ እሴት ለማኅበረሰቡ የሚያከፋፍሉ እንጂ፣ ምንም ተጨማሪ እሴት አይፈጥሩም ተብለው በአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ቆጠራ አይካተቱም ነበር፡፡

በአውሮፓ ኢኮኖሚውን መምራት የተሳነውን መሳፍንታዊና ባላባታዊ የፊውዳል አስተዳደር ሥርዓት ተክቶ ከ16ኛው እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን የቆየው የአንድ ብሔር አገር (Nation State) ግንባታ ዘመነ ንግድ (Mercantilism) ሥርዓት የብሔራዊ ኢኮኖሚ ሥርዓት ያተኮረው፣ በውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ከገቢ ንግድ ይልቅ ወጪ ንግድን አስበልጦ አትራፊ በመሆን ወርቅና ብር የመሳሰሉትን የከበሩ ድንጋዮችና የውጭ ምንዛሪ ሀብት ለአገር በማግበስበስና በማከማቸት፣ በኃይልና በኢኮኖሚ ከሌሎች አገሮች በልጦ መገኘት ነበር፡፡

በእዚህ ሥርዓት ፍልስፍና አውሮፓውያኑ አፍሪካንና ላቲን አሜሪካን በቅኝ ግዛትነት በመቀራመት ማዕድኖቻቸውን በዘበዙ፣ ጥሬ ዕቃ አቅራቢና የፋብሪካ ሸቀጥ ማራገፊያም አደረጓቸው፡፡ 

ኢኮኖሚክስ ከተለምዶው የሥነ ምግባርና የሞራል ፍልስፍና ጥናት ወጥቶ ዘመናዊ የኑሮ ዘይቤና በውድድር ላይ የተመሠረተ የሀብት ድልድል ዘዴ ተደርጎ መጠናት የጀመረው፣ ከአዳም ስሚዝ እ.ኤ.አ. የ1776 የመንግሥታት ሀብት መጽሐፍ ዘመናዊ ኢኮኖሚ ትንታኔ በኋላ ነው፡፡

አዳም ስሚዝ ዘመነ ንግድ ሥርዓት ጥቂት ከበርቴ ነጋዴዎችንና የመንግሥት ባለሥልጣናትን ብቻ የሚያከብርና የሚጠቅም ሥርዓት ነው በማለት ነቀፋ አድርጎ፣ ለሁሉም ሕዝብ የሚጠቅም በውድድር ላይ የተመሠረተ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓትን ተነተነ፡፡

ሆኖም ኢኮኖሚክስን ከሥነ ምግባርና ከሞራል ፍልስፍና አላቆ ዘመናዊና ሳይንሳዊ የኑሮ ዘይቤ ጥበብ ያድርገው እንጂ፣ የሥነ ምግባሩና የሞራል ጉዳዩ አሁን ድረስም በጎጂዎችና በተጎጂዎች መካከል አታካራና ውግዘት አንዳንዴም አመፅ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ዘወትር በመገናኛ ብዙኃን እንደሚደመጠው ሕዝቡ ዋጋ በተወደደበት ወቅት፣ ሸቀጦች ጥራት በጎደላቸው ወቅት፣ ነጋዴዎች ዋጋ እስከ ሚወደድላቸው ሸቀጥ በሚደብቁበት ወቅት እባካችሁ እንተዛዘን እያለ ይለምናል፣ ይማፀናል፡፡ የሠራተኛ ማኅበራት በየጊዜው ከአሠሪዎች ማኅበራትና ከአሠሪዎች ጋር በደመወዝ ጉዳይ ላይ ይሟገታሉ፡፡ ሀብት መቀራመትም ብጥብጥና ሁከት ያስነሳል፡፡

በጥንታውያን ኢኮኖሚስቶች የታሰበው ሰዎች ጥቅማቸውን የላቀ ለማድረግ የሚበጃቸውን ያውቃሉ፡፡ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ታሳቢ ግምት በኬንስ ሰዎች አንዳንዴ በእንስሳዊ ስሜትም (Animal Spirit) ይነዳሉ በማለት ተተችቷል፡፡ በዚህ ዘመን የምናየው ደግሞ ሰዎች ጥቅማቸውን የላቀ ለማድረግ አዋቂነት ሌላውን ሰው አለመጉዳት ገደብና ጠርዝ እንደሌለው ነው፡፡

የግል ጥቅምን የላቀ ለማድረግ አዋቂ መሆን የነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ሕግጋት ታሳቢ ገደብ ስለሌለው፣ በሕጋዊና በሚፈቀድ መንገድ የሌሎቹን መብትና ጥቅም ለመጉዳት እስከ መሄድንም የሚፈቅድ ይመስላል፡፡ በውስጡ ሀብትን የራስ ብቻ የማድረግ እንስሳዊ ስስት መኖሩ ይታያል፡፡ በስስት የ3.5 ቢሊዮን ሕዝብ ሀብትን የሚያህል በስምንት ሰዎች ብቻ ተያዘ፡፡

 

በስዊዘርላንድ ዳቮስ በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም የቀረበ ዘገባ ተጠቅሶ በመገናኛ ብዙኃን በተነገረ ዜና፣ ስምንቱ የዓለም ሀብታም ሰዎች ሀብት የ3.5 ቢሊዮን ድሆችን ሀብት ያክላል ይላል፡፡

በኢኮኖሚክስ የኖቤል ተሸላሚው ኢኮኖሚስት ጆሴፍ ስቲግሊትዝ ግሎባላይዜሽን ያመጣው ጣጣ ነው በሚል፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚሟገቱ የዚህ ዘመን ታዋቂ ኢኮኖሚስት ሆነዋል፡፡

በቅርቡ ሕይወታቸው ከማለፉ በፊት በአልጄዚራ ቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ የተደረገላቸው ታላቅ ጣሊያናዊ ፈላስፋ ሲናገሩ፣ ባለፉት መቶና ሁለት መቶ ዓመታት ለነፃነት ብዙ ሲሠራ ለዋስትና ምንም ስላልተሠራ ብዙ ሰዎች እየተጎዱ ነው ብለው በማስረጃ ሁኔታዎችን ሲተርኩ ሰምቼ ነበር፡፡

ከማስረጃዎቻቸው ውስጥም የሊቢያ፣ የሶሪያና የኢራቅ ቱጃሮች ዛሬ የኑሮ ዋስትና አጥተው በስደተኛ ካምፕ ወይም በሰው አገር እንደ ሁለተኛ ዜጋ እየተቆጠሩ ለዕለት ጉርሳቸው ለፍተው ጥረው ግረው ይኖራሉ ብለው ነበር፡፡ ለነፃነት ብቻ ስናስብ ‹ዋስትናን ረሳነው›፡፡ የሥራ ዋስትና፣ የቤተሰብ ዋስትና፣ የኑሮ ዋስትና አጣን፡፡ አንድ ሰው ስለራሱ ነፃነት የሚያስብበት ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎች የኑሮ ዋስትናም ያለውን ግዴታ የምናጎላበት ጊዜ ነው፡፡

ዛሬ የተደላደለ ሀብትና ሥልጣን አለኝ ብሎ ግፍ ከመሥራትና ከሌላው ነጥቆ ከመብላት ‹ነግ በእኔ› ማለትም ይገባል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የአረጋውያንን እንባ  መፍራት ያስፈልጋል፡፡ እዚያ ሁሉም በጊዜው መድረሱ አይቀርምና፡፡ በጡረታ መዋጮ መልክ ቆጥቦ መንግሥት፣ ዘንድ ያስቀመጣት ብር ሸቀጥን የመግዛት አቅሟ እንዲቀንስ ያደረገ መንግሥት ተጠያቂነትም ከዋጋ ንረት ጋር ማስተካከያ የማድረግ የሥነ ምግባር ግዴታም አለበት፡፡

ይህች በአረጋውያን ጸሎት ትኖራለች የተባለላት አገር እነ ጄነራል ጃጋማ ኬሎን የመሳሰሉ ጀግኖች ተራቡባት ተብሎ በመገናኛ ብዙኃን ሲቀርብ ምን ያህል አሳዛኝ ፍጡሮች መሆናችንን የሚያመለክት ነው፡፡ ጄነራሉ 1,300 ብር ጡረታ በድሮው የሸቀጥ ዋጋ ቀጭን ጌታ ሆነው ሳይራቡ ሳይታረዙ ሊኖሩ ይችሉ ነበር፡፡ መኖር እስከሚያቅታቸው ድረስ ኑሮን ያስወደደባቸው መንግሥት እንዴት ኃላፊነት አይወስድም?

አቅም ያለውን መፍራትና አቅም የሌለውን መናቅ ከልማታዊ መንግሥት አይጠበቅም፡፡ አንድ መንግሥት ዜጎቹን ‹ጉልበት ያለውና ጉልበት የሌለው› ብሎ በአቅም ከፋፍሎ ከተመለከተም የሆነ ችግር አለበት ማለት ነው፡፡ የቅርብ ጊዜው ሁከት የወጣቱ ደስ አለመሰኘት ነው ተብሎ ሽር ጉድ ሲባልለት ከረመ፡፡ ወጣቱ የሥራና የኑሮ ዋስትና ሊያገኝ ይገባል ማለት ልክ ነው፡፡ ነገር ግን ወጣቱ የእናትና የአባቱ መራብም አያስደስተውም፡፡

‹‹እምዬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ›› ተብሎ የተገጠመው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ባንዶቹ ሲሾሙ እነ በላይ ዘለቀን የመሳሰሉ ጀግኖች በስቅላት በመገደላቸው ነበር፡፡ በጄነራል ጃጋማ ኬሎና በጠቅላላው ኢትዮጵያውያን አረጋውያንና ጡረተኞች ታሪክ ራሱን ደገመ፡፡

የሚራቡ ሰዎች ለመራባቸው ምክንያት መሆን፣ የሚጠሙ ሰዎች ለመጠማታቸው ምክንያት መሆን፣ የሚታረዙ ሰዎች ለመታረዛቸው ምክንያት መሆን ምንኛ  ይሰቀጥጣል፡፡ ‹ዛሬ ያለ ሁሉ ነገ የለም› ሥልጣኑም፣ ገንዘቡም፣ ጤንነቱም ይሸሻል፡፡ የማታ ማታ የበላም ያልበላም፣ የጠጣም ያልጠጣም፣ የለበሰም የታረዘም፣ ፎቅ ቤት የኖረም በረንዳ ያደረም፣ ሁሉም ዶግ ዓመድ  ይሆናል፡፡ ከሌላው ነጥቀው ያጠራቀሙት አብሮ አይሄድም፡፡ መሥራትና ማትረፍ በሥነ ምግባር የተደገፈ ይሁን፡፡ ካልሆነ ግን ለአገር ጠንቅ ነው፡፡ መንግሥትም ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ያስፍን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getachewasfaw240@gmail.com.  ማግኘት ይቻላል፡፡.

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

Trending Articles