በአበባው አባቢያ
መንግሥታችን ለዜጎች ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው፣ ቀልጣፋና አርኪ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችለው የተለያዩ የለውጥ መሣርያዎችን ከአውሮፓና ከእስያ አገሮች በማስመጣትና በመቀመር፣ ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥት ተቋማት እንዲተገብሩ አድርጓል፡፡ እነዚህ ከፈረንጅ አገሮች የተወሰዱት የተለያዩ የለውጥ መሣርያዎች የመንግሥት ተቋማት አመራርና ሠራተኞች ቢገባቸውም ባይገባቸውም እንዲተገበር ተደርገዋል፡፡ ስለሆነም እየተተገበሩ ያሉትን የለውጥ መሣርያዎች የእንያዳንዱን ጥንካሬ፣ ድክመትና ውድቀትን በዝርዝር ለማሳየት አስቤ ይህን አጭር ጽሑፍ ለማዘጋጀት ተገደድኩ፡፡ መንግሥትም ያለውን እውነታ በጥልቀት በመመልከት የተጀመሩት የለውጥ መሣርያዎችን በአግባቡ እንዲተገበር ቢያደርግ የተሻለ እናድጋለን የሚል እምነትም አለኝ፡፡ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ለመኖር ሲባል ያልተከናወነውን ተከናወነ፣ ያልመጣውን ለውጥ መጣ እየተባሉ የሚቀርቡ ቀልዶች መፍትሔ ሊበጅላቸው ይገባል፡፡ ለእውነት የቆሙ፣ ለእውነት ሥራቸውን የሚሠሩና የእውነት ሪፖርት የሚያቀርቡ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ይህ አስተያየት አይመለከታቸውም፡፡
የመጀመርያው የለውጥ መሣሪያ የመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ነው፡፡ ይህ የለውጥ መሣርያ የተወለደው እ.ኤ.አ. 1990 በአሜሪካን ሲሆን፣ ወደ አገራችን የገበው እንደ እ.ኤ.አ. በ1998 ነው፡፡ ይህ በመንግሥት ተቋማት በዘመቻ እንዲተገበር የተደረገ የለውጥ መሣሪያ ነው፡፡ ስለሆነም የመንግሥት ተቋማት በዚህ የለውጥ መሣሪያ ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥና በጥናት ላይ የተመሠረተ አዲስ ወይም የተሻሻለ አሠራር ለመዘርጋት ብዙ ገንዘብ ወጪ አድርገዋል፡፡ በተዘረገው አዲሱ አሠራርና በተሻሸለው አሠራር ብዛት ያላቸው ሠራተኞች ከሥራ ተፈናቅለው ያለ ሥራ ለዓመታት ደመወዝ ሲከፈላቸው ቆይቶ መጨረሻ ላይ እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡ የለውጥ መሣሪያ በሚያዘው መርህ መሠረት ሥራዎች ተፈጥሯዊ ፍሰትን ተከትለው ተደራጅተዋል በሚል ዕሳቤ የሚቃረኑ ሥራዎች ጭምር በአንድ ሰው አማካይነት ውሳኔ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ እዚህ ላይ የጥቅም ግጭት እንዲስፋፋ ተደርጓል፡፡ በብዙ ሺሕ ብር የተገነቡ የሕንፃ ቢሮዎች ተንደው ሠራተኞች አንድ ላይ እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡ ሥራን ለማቀለጠፍ ሲባል ብዛት ያላቸው ኮምፒዩተሮች ተገዝተዋል፡፡ በአንዳንድ ተቋማት በአዲስ ምደባ ስም ሠራተኞች የደረጃ ዕደገት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ አዲሱን አሠራር ተከትሎ የተዘረጉ አሠራሮችን ለማከናወን ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅ በየተቋሙ መግቢያ በር ላይ በሚያንፀበርቅ ጽሑፍ ተለጣጥፏል፡፡ ተገልጋይ በተቀመጠው ጊዜና ጥራት አገልግሎቱን ባያገኝ የት ማመልከት እንደሚቻልም በሚታይ ቦታ ተለጥፏል፡፡ በጣም ጥሩ ነበር፡፡
የመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ መርሁ በሥራ ሒደት መሠረታዊና ዕመርታዊ ለውጥ በማድረግ ለተገልጋይ ፈጣን፣ ቀልጣፋና አርኪ የሆነ አገልግሎት ለዜጎች መስጠት ነው በአጭሩ፡፡ በእውነትም ከላይ የተገለጹት ሥራዎች ሲከናወኑ በነበረበት ወቅት በተወሰነ ደረጃ የመንግሥት አገልግሎት ቀልጣፋ ነበር፡፡ በዚህ አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡ የመንግሥት ተቋማት እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡
የለውጥ መሣሪያው በተወለደበት አገር በተገቢው ጥቅም ላይ ውሎ በብዙ ተቋማት ውስጥ አመርቂ ውጤት ማምጣቱ ከተለያዩ ጽሑፎች መረዳት ይቻላል፡፡ በአገራችን ግን የተለፋበትንና ወጪ የተደረገበትን ገንዘብ ያህል ለውጥ አምጥቷል ወይ? ቢባል እኔ አላመጣም ነው ምላሼ፡፡ ምክንያቶቹ የመጀመርያው የለውጥ መሣሪያውን በራሱ በትክክል አለመረዳት ወይም በተዛባ መንገድ በመረዳት ሲሆን፣ የለውጥ መሣሪያዎች በመጠቀም አዲሱን አሠራር የዘረጉ ሰዎችም ሆኑ የተዘረጋውን አሠራር የሚተገብሩ ሰዎች በለውጥ መሣሪያው ላይ በቂ ግንዛቤና እምነት አለመያዛቸው ነው፡፡ እንዲሁም በአዲሱ አሠራር በተዋቀረው አደረጃጀት ላይ የተካሄደው ምደባ ፍትሐዊ አይደለም ብለው የሚያምኑ በመኖራቸው የለውጥ መሣሪያውን ለውድቀት ዳርጎታል፡፡ በመሆኑም ከመጀመርያውኑ ውጤት የሚያመጣ የለውጥ መሣሪያ ሆኖ እንዲተገበር አልተደረገም፡፡ አዲሱ የአሠራር ሥርዓት ሲዘረጋ ቢሮዎች ተነድነው ሠራተኞች በተርታ ተቀምጠው ለዜጎች አገልግሎት እንዲሰጡ ቢደረግም፣ አገልግሎቱን የሚሰጡ ፈጻሚዎች በለውጥ መሣሪያው ላይ ዕውቀትና እምነት ስለሌላቸው የተገልጋዩን መንገላታት አላስቀረም፡፡ በእንዝላልነት በተዘረጋው አዲሱ አሠራር ሠራተኞች ያላቅማቸው ውሳኔ ሰጥተዋል፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅመው አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ የግል ጥቅም ማካበቻ ያደረጉ አመራሮችና ሠራተኞች ብዙ ናቸው፡፡ በተለይ እርስ በርሳቸው ለጥቅም ግጭት የተጋለጡ አሠራሮች በአንድ ሰው ኃላፊነት እንዲመሩ በመደረጋቸው፣ በአንዳንድ ተቋማት ውስጥ የመንግሥት በጀት በሕገወጥ መንገድ ለዝርፍያ እንዲጋለጥ መደረጉን መረጃ አለ፡፡ በእርግጥ የተወሰኑና በጣም ጥቂት የመንግሥት ተቋማት የለውጥ መሣሪያውን በመጠቀም የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ እንዳሉ የሚካድ አይደለም፡፡
የመንግሥት ተቋማት አመራርና ሠራተኞች በአንድ ክፍል ተቀምጠው ለዜጎች አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉ፣ የሚሰጡ አገልግሎቶች የጥራት፣ የጊዜና የመጠን መለኪያ ስታንዳርዶች እንዲኖሩ ተደርገው መቀረፁ ተገቢነት ያለውና የማያጠያይቅ ቢሆንም፣ ሠራተኛውና አመራሩ በአዲሱ አሠራር የተዘረጉትን የአገልግሎት መስጫ ስታንዳርዶችን በደቂቃ፣ በሰዓትና በቀን ለይቶ በመመዝገብና በመለካት የተገኘውን ለውጥ ለማረጋገጥ የማይችሉበት ሁኔታ መኖር ደግሞ በጣም ጥፋት ነበር፡፡ ለተገልጋይ አገልግሎት መቼና እንዴት ይሰጣል? የተሰጠው አገልግሎትና የተገኘው ውጤት እንዴት ይለካል? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ራሱን የቻለ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት የሚያስፈልገው ቢሆንም፣ ይህን ለማድረግ በለውጥ መሣሪያው ላይ በቂ ዕውቀትና እምነት ያለው ቁርጠኛና ብቃት ያለው አመራርና ሠራተኛ ባለመኖሩ የለውጥ መሣሪያው ለውድቀት ተደርጓል፡፡ ተገልጋይም አገልግሎቱ ላይ የሚደረገው መወሳሰብ፣ ቀጠሮ የማብዛትና የማመላለስ፣ መዝገብ የመደበቅ ሁኔታዎች ስለሚሰለቹ አገልግሎት ለማግኘት በተቋም ውስጥ የሚያማልድ ዘመድ ከመፈለግ አልፎ ለመብቱ ጉቦ ለመስጠት እንዲገደድ አድርጎታል፡፡ በጉቦ አገልግሎት እንዲያፋጥንና መብቱን በገንዘብ እንዲገዛ ተደርጓል፡፡ የመልካም አስተዳደር ያለህ እንዲል አድርጎታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአንዳንድ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የመሠረታዊ የሥራ ሒደት የጥናት ሰነዱ ራሱ አይገኝም፡፡ የጥናት ሰነዱን ጥናቱን ያካሄዱ አመራርና ሠራተኞች ተቋሙን ሲለቁ ይዘው ሄደዋል፡፡ ስለሆነም ለውጡ ወድቋል ለሚለው ይህ በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡
የመሠረታዊ የአሠራር ሒደት ጥናት ሲካሄድ የነበሩ አመራሮችና ሠራተኞች በተለያዩ ምክንያቶች ሥራቸውን በመልቀቃቸው፣ አዲስ ተቀጥረው ወይም ተመድበው እንዲሠሩ የሚደረጉት ደግሞ በለውጥ መሣሪያው ላይ በቂ ሥልጠና አላገኙም፡፡ የተዘረጋው የመሠረታዊ የአሠራር ሒደት ለውጥ ጥናት በአብዛኛው ከመንግሥት ተቋማት እየጠፋና እየተረሳ ነው፡፡ በመሠረታዊ የአሠራር ሒደት ጥናት መነሻነት የተዘረጉ አዳዲስ መዋቅሮች እየፈረሱ ወደ ነበሩበት እየተመለሱ ናቸው፡፡ እንዲፈርሱ የተደረጉት ቢሮዎች እንደገና እንዲገነቡና ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ እየተደረጉ ናቸው፡፡ አለቃና ሠራተኞች በጋራ ተቀምጠው ይሠራሉ የተባለው ዛሬ ላይ አለቃዎች ለብቻቸው እየተሞሸሩ ከጸሐፊ ጋር ወደ ቢሯቸው ተመልሰዋል፡፡ የሠራተኞች የመወሰን ደረጃው እየተገደበ ሁሉም ውሳኔዎች በአለቃ ብቻ እንዲወሰኑ እየተደረገ ነው፡፡ ከፍላት መዋቅር ወደ ዕዝ ሰንሰለት መዋቅር የተለወጠውን አደረጃጀት የሚፈቅደውና የሚያፀድቀው የለውጥ ትግበራ ላይ ክትትልና የሚያደርገው አካል መሆኑ ደግሞ ግርምትን ይፈጥራል፡፡ በተለይም ሁለት ተቃራኒ ነገሮች በአንድ ተቋም በመከናወነቸው፣ ለመሠረታዊ የሥራ ሒደት ጥናት በመንግሥት ተቋማት ወድቀትና መጥፋት ተባባሪ አካል እንዳለም መታወቅ ይኖርበታል፡፡
ሁለተኛው የለውጥ መሣሪያ የውጤት ተኮር ሥርዓት ነው፡፡ የዚህ የለውጥ መሣሪያ ውልደት እ.ኤ.አ. በ1992 በአሜሪካ ሲሆን፣ ይህ መሣሪያ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በሁሉም የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ቢገባቸውም ባይገባቸው በስፋት እየተተገበረ ነው፡፡ በዚህ ለውጥ መሣሪያ ላይ የሚታየው የዕውቀት፣ የክህሎትና የእምነት ችግር ነው፡፡ መጀመርያ በአገሪቱ ይህን ሥልጠና የሚሰጠው የሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ነው፡፡ ኢንስቲትዩቱ ሥልጠና መስጠቱ ልክ ቢሆንም ሠልጣኞቹ በቂ ግንዛቤ ጨብጠዋል የሚል ድምዳሜ የለኝም፡፡ ደግሞም ለሠልጣኞቹ ብቃት ፈተና ተሰጥቶ የሚረጋገጥበት አሠራር የለም፡፡ ይሁን እንጂ የለውጥ መሣሪያውን የፈጠሩት ሰዎች ሠልጣኙ በቂ ግንዛቤ ስለመያዙ ፈተና እንዲሰጥ ቅድሚያ ሁኔታ ማስቀመጣቸውን ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ በአንድ ወቅት በአንድ መድረክ ላይ የሰማሁት ሠልጣኝ አንዳንድ ጥልቅ ጥያቄዎችን ሲጠይቅ አሠልጣኞች ከመሥሪያ ቤት መሥሪያ ቤት ይለያል ስለሚሉን በለውጥ መሣሪያው ላይ በቂ ግንዛቤ እየጨበጥን አይደለም ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ቀጥሎም ይህ የለውጥ መሣሪያው በቅጡ ያልገባቸው ሠልጣኞች ወደ ተቋማቸው መጥተው የተቋሙን የውጤት ተኮር ዕቅድ ያቅዳሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ለመንግሥት ሪፖርት ለማቅረብ እንዲያመች ልማዳዊ የሪፖርት አቀራረብ ሥርዓትን የተከተለ ዕቅድ ይታቀዳል፡፡ ስለዚህ በመንግሥት ተቋም ውስጥ የውጤት ተኮር ሥርዓት አስተቃቀድና ትግበራው ጠቃሜታው እምብዛም አይታወቅም፡፡ ተቋማት የበለጠ ትኩረት የሚሰጡት ለልማዳዊ ዕቅድ አስተቃቀድ ሲሆን፣ ጥቅሙን በሚገባ በቅጡ ስለማይረዱት ለውጤት ተኮር ሥርዓት አስተቃቀድ ብዙ ትኩረት አይሰጡትም፡፡ የውጤት ተኮር ሥርዓት የሚጠቀሙት በመንግሥት ተግብሩ ስለተባለ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም በዕቅድ ዝግጅት ላይ ያለውን የስህተት መጀመርያ እናያለን፡፡ ዕቅዱ ሲዘጋጅ ውስጣዊና ውጫዊ ዳሰሳ ችግሮች ላይ ዝርዝር ትንተና ይካሄድበታል፡፡ የሚታቀደው ዕቅድ ግን የተነተኑትን ችግሮች ሊፈታ የሚችል አይደለም፡፡ ተቋም በሕግ ሲቋቋም አንድን ዓላማ ለማሳከት ስለሚሆን ዕቅድ ሲዘጋጅ ተልዕኮው በግልጽ ይቀመጣል፡፡ የራዕይ ዝግጅት ግን ግልጽነት የሚጎለው ነው፡፡ ሊለካ የማይችል ራዕይ ይነደፋል፡፡
አብዛኛዎቹ ተቋማት አፍሪካን ወይም ዓለምን መምሰል የሚያስችል ራዕይ ይነድፋሉ፡፡ ይህ ራዕይ በአፍሪካ ወይም በዓለም የየትኛውን አገር ያህል እንደሚሆን ግን አይታወቅም፡፡ አፍሪካ ወይም ዓለም የተቋሙ ራዕይ እስከሚሳካ ድረስ ቆመው አይጠብቁም፡፡ በጣም ሊለወጡ ይችላሉ፡፡ ይሁንና በአፍሪካ ወይም በዓለም. . . ሆኖ መገኘት እየተባለ የሚነደፈው ራዕይ ለእኔ አይገባኝም፡፡ የአብዛኞቹ ተቋማት ራዕይ በዚህን ጊዜ የዜጎችን እምነት ይህን ያህል ተብሎ ሲታቀድ አይቼ አለውቅም፡፡ ካለም ጥሩ ነው፡፡ የሚቀረፁ እሴቶች ደግሞ የሥነ ምግባር ወይም የመልካም አስተዳደር መርሆዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን የተቋሙ አመራርና ሠራተኛ የቀረፁትን እሴት አይመስሉም፡፡ ተግባሮቻቸውም ይህን ለማረጋገጥ የሚያስችል አይደለም፡፡
ስትራቴጂካዊ የትኩረት መስኮች ንድፍ ዕቅዱን ለሚያዘጋጁትን ግልጽ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ የትኩረት መስኮች አንድ ተቋም በስትራቴጂካዊ ዘመን ውስጥ ትኩረት ሰጥቶ መፍትሔ የሚሰጣቸው ወይም ውጤት የሚያስመዘግባቸው ዋና ጉዳዮች መሆናቸውን የለውጥ መሣሪያውን የፈጠሩት ሰዎች ይገልጻሉ፡፡ ለትኩረት መስክ ውጤት ይነደፋል፡፡ ነገር ግን የተነደፈው የትኩረት መስክ ውጤት የሚለካ አይደለም፡፡ በመሆኑም ተቋማት የትኩረት መስኩ ውጤታማ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ማቅረብ የሚችሉ አይመስለኝም፡፡ በመጀመርያ ስትራቴጂካዊ ዘመን የተነደፉት የትኩረት መስኮች ስለመሰካታቸው ማረጋገጫ ሳያቀርቡ፣ በተቀጣይ ስትራቴጂካዊ ዘመን ሌላ የትኩረት መስክ ይነድፋሉ፡፡ ካልሆነም የመጀመርያውን የትኩረት መስክ ቀጣይ ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን መቼ ውጤት እንደሚመጠ አይታወቅም፡፡
ቀጥሎ የሚነደፉት ስትራቴጂካዊ ግቦችና መለኪያዎች ናቸው፡፡ በቁጥር በርከት ያሉ ስትራቴጂያዊ ግቦች ይነደፋሉ፡፡ መረጃ በትክክል ተሰብስቦ መለካት የማይቻሉ ስትራቴጂካዊ የአፈጻጸም መለኪያዎች ለእያንዳንዱ ስትራቴጂካዊ ግብ ይቀረፃሉ፡፡ መለኪያዎቹ ውስጥ አብዛኛዎቹ መረጃ ቀርቦባቸው የሚላኩ ሳይሆኑ የታቀደ ተከናወነ ለማለት ያህል የተቀመጡ ናቸው፡፡ መቶ ታቀደ ተብሎ መቶ ተከናወኑ የሚባልበት ሁኔታ በብዛት እንደሚኖር በጣም እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስትራቴጂካዊ ዕርምጃ ለምን እንደሚነድፉ አይታወቅም፡፡ ምክንያቱ በጀት ያልተፈቀደላቸውና ለዕቅድ ያህል የታቀዱ ናቸው፡፡ ይህ ስትራቴጂካዊ ዕርምጃ ስለመሳካቱ ማንም ክትትል የሚያደርግ አይመስለኝም፡፡ የተነደፉት ስትራቴጂካዊ ግቦችና ዕርምጃዎች ከበጀት ጋር ትስስር ስላሌለቸው የተቋሙ ስትራቴጂ ተሳክቷል ለማለት ያስቸግራል፡፡ በአጠቃላይ የውጤት ተኮር ሥርዓት ዕቅድ ለተቋም ምኑም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሠራተኞች እንዲያከናወኑ ተከፋፍሎ የሚሰጠው የውጤት ተኮር ሥርዓት ዕቅድ ቢታቀድም ባይታቀድም፣ መሥራት የሚገባቸው ዕቅዶች እንዲያከናወኑ ይደረጋል፡፡ የፈጻሚ ሥራ ውጤት የሚለካው የውጤት ተኮር ሥርዓትን ተከትሎ ሳይሆን፣ የተፈለገው ዕቅድ ታቅዶ እንዲጠናቀቅ ታሳቢ ተደርጎ የተሰጠው ዕቅድ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ባለሙያ በቀን ስንት ሰው ማስተናገድ ይችላል ተብሎ ታቅዶ ይሰጣል፡፡ ፈጻሚውም ሰላምታ ያቀረበውን ጭምር ማስተናገዱን ደምሮ ይህን ያህል አስተናግጄያለሁ ብሎ ባቀረበው ሪፖርት የዕቅድ አፈጻጸም ምዘና ይካሄዳል፡፡ መሆን የነበረበት ግን ካስተናገደው ተገልጋይ ምን ያህሉ ረክቷል የሚል ቢሆን ኖሮ በአሁኑ ወቅት እየተከሰተ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር ቁልፍ መፍትሔ ማግኘት ይቻል ነበር፡፡ ይህ ነበር የውጤት ተኮር ሥርዓት ትግበራ ፋይዳው፡፡
ስለሆነም ሠራተኞችን ለመለካትና ለመንግሥት ሪፖርት ለማቅረብ የሚታቀደው ዕቅድ በተቋሙ ውስጥ ለብቻው ስለሚታቀድ፣ የውጤት ተኮር ሥርዓት የታቀደው ዕቅድ ለተቋሙ በምንም አግባብ ውጤታማነትን ለመለካት አያገለግልም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሪፖርት ተቀባይ የመንግሥት አካል ሪፖርትን የሚፈልገው በውጤት ተኮር ሥርዓት ሳይሆን፣ የቀድሞውንና የተለመደውን ቁልፍና ዓቢይ ተግባራት የዕቅድ አፈጻጸም የተከተለ ሪፖርት ነው፡፡ ይህም የውጤት ተኮር ሥርዓት ትግበራ የተልጋይን ዕርካታና አመኔታ በማምጣት የሚሰጠውን ትልቁን ሚና እንዳይጨወት አድርጎታል፡፡ ወድቋል ያልኩትም ለዚህ ነበር፡፡
ይህም ሆኖ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስከ ወረዳ ድረስ ያሉት ተቋማት በየቢሮው አሸብርቀው የሚያስቀምጡት የውጤት ተኮር ሥርዓት ዕቅድ፣ በተለይም የስትራቴጂ ማፕ ለቢሮ በር አካባቢ ዕይታ እንዲያምር ካልሆነ በስተቀር ማንም የሚረዳው አይመስለኝም፡፡ ለኅትመት ሥራ ከፍተኛ ወጪ ማውጣት አስፈላጊ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ኃላፊነት የተሰጠው የመንግሥት አካል የውጤት ተኮር ሥርዓት አስተቃቀድ ለምን ዓለማ እንደሚጠቅምና ምን ውጤት ለመምጣት እንደሚያግዝ በቅጡ የማስገንዘብ፣ እንዲሁም በትክክል በማይፈጽሙት ላይ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ግዴታውን በንግግርና በወረቀት ሳይሆን በአካልና በተግባር ሊወጣ ይገባል፡፡ የውጤት ተኮር ሥርዓት የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት ያለውን ሚና በተገቢ መንገድ መጠቀም ይኖርብናል፡፡
የዜጎ ቻርተር ሦስተኛው የለውጥ መሣሪያ ነው፡፡ የዜጎች ቻርተር ተቋማት ለዜጎች አሠራራቸው ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው ስለማድረጋቸው ቃል የሚገቡበት የቃል ኪዳን ሰነድ ነው፡፡ በተቋማት የተዘጋጀው የዜጎች ቻርተር አንድን ቻርተር ለማዘጋጀት መከተል የሚገባውን መርህ በአብዛኛው የተከተለ ቢሆንም፣ ችግሩ አገልግሎቱ በተጠቃሚ ዜጎች እምብዛም አለመታወቁ ነው፡፡ ከላይ በመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ጥናት የተነደፉ ስታንዳርዶች በዜጎች ቻርተር ላይ የአገልግሎት አሰጣጥ ስታንዳርድ ተብለው የሚቀመጡ ቢሆንም፣ አገልግሎት ሰጪውም ሆነ አገልግሎት ተቀባዮቹ በትክክል የተረዱት ነገር ስለማይሆን ዜጋውም የተባለውን አገልግሎት በሰታንዳርዱ መሠረት ባለመቀበሉ ለምን በማለት አይጠይቅም፡፡ አገልግሎት ሰጪውም በአገልግሎት ስታንዳደርዱ ላይ በቂ ግንዛቤ ያልያዘ ከመሆኑም በላይ፣ አገልግሎት በስታንዳርዱ መሠረት ባለመስጠቱ የሚጠይቀው ያለ አይመስለኝም፡፡ የዚህ ሰነድ ዝግጅትና ኅትመት ወጪ አስፈላጊነቱም አሁንም ግልጽ አይደለም፡፡ የዜጎች፣ የተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ያለባቸውን የተጠያቂነት ደረጃ ከማሳየቱም በላይ መልካም አስተዳደር ለማስፈን ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ስለሆነ፣ የሚመለከተው አስፈጻሚ አካል የሚጠበቅበትን ኃላፊነቱን በተገቢው ሊወጣ ይገባል፡፡
አራተኛው የለውጥ መሣሪያ የለውጥ ሠራዊት ግንባታ ላይ ያለው ብዥታ ነው፡፡ የለውጥ ሠራዊት ተገነባ የሚባለው አንድ ዓለማ እንዲያሳኩ የተደራጁ የቡድን አደረጃጀቶች ሥራቸውን በእምነት፣ በዕውቀት፣ በባለቤትነት ስሜትና በፍቅር በማከናወን ከተጠበቀው ዕቅድ ወይም በላይ በቅልጥፍና ማሳከት ሲችሉ ነው፡፡ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚሠሩት ሠራተኞች ለዚህ የተዘጋጁ ናቸው ወይ የሚባሉ አይደለም፡፡ የአቅም ውስነነት ያለቸው ሠራተኞች በብዛት አሉ፡፡ በዚያ ላይ እነሱን የሚመራ አመራር ከእነሱ የባሰ አልምጥ ወይም ዳተኛ ነው፡፡ የለውጥ ቡድን አደረጃጀቱን በራሱ የፖለቲካ ሥራ አድርገው የሚያስቡ በርካታ ናቸው፡፡ እንዴት ሆኖ ነው ይህን በችግር የተበተበ የመንግሥት ሠራተኛ ግንባር ቀደም ይሆናል ተብሎ የሚታሰበው? ከአደረጃጀት ውስጥ በእርግጥ በቁጥር በጣም ውስን የሆኑ ጎበዝና የሥራ ፍቅር ያላቸው ሠራተኞች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነሱም ቢሆኑ መደበኛ የሥራ ሰዓት የሚያከብሩና ተገልጋይ በትህትና የሚያስተናግዱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዕውቀትና በክህሎት ግን የተካኑ አይሆኑም፡፡ አብዛኛዎቹ ግን ይህን መሥፈርት የሚያሟሉ ባለመሆናቸው የለውጥ ሠራዊትን በመንግሥት ተቋማት መገንባት በጣም ችግር ይሆናል፡፡ አመለ ሸጋውን ሠራተኛ ግንባር ቀደም የምንል ከሆነም በጣም የተሳሰትን ይመስለኛል፡፡ ሥራን ማቀለጠፍና መፍጠር የሚችል አመራርና ሠራተኛ ነው ለኔ ግንባር ቀደም፡፡ የተሰጠውን በየዕለቱ የሚያከናውን ወይም የሚያጠናቅቅ፣ ከአቅም በታች እያቀደ ሥራውን ከዕቅድ በላይ አከናወንኩ የሚል ሠራተኛ ግንባር ቀደም መባል የለበትም፡፡
በመንግሥት ተቋም ውስጥ የተፈጠረውን አሠራር ማከናወን የማይችል ዳታኛ ሠራተኛ በብዛት ስላለ የሚመለከተው አካል ብዙ ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ከትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ አቅም መገንቢያ ሥራዎች በስፋት መሠራት ይኖርባቸዋል፡፡ አንዴ የተወላገደውን ለማቃናት በተለይም የመንግሥት ተቋም ጊዜ ማጥፋት ያለበት አይመስለኝም፡፡ ግንባር ቀደም የሚባል አመራርና ሠራተኛ ግንባር ቀደም ለመሆን በቅድሚያ የለውጥ መሣሪያዎችን ጠንቅቆ የሚያውቅና መተግበር የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡ ያቀደውን ሥራ በቅልጥፍና፣ በፈጠራ በታገዘ ሁኔታ ማከናወን መቻል አለበት፡፡ ካልሆነ ግን ከአቅም በታች እያቀደ ብዙ ሠራሁ የሚለውን፣ በየሰዓቱ ከአለቃ ቢሮ የማይጠፈውን፣ አጎብዳጅ፣ ለአለቃ ወሬ የሚያመላልስ፣ ሰላምታ የሚያበዛ፣ ከበር መልስ የሚጋብዝ፣ ለቅሶና ሠርግ የማይቀር፣ የታመመ የሚጠይቅ፣. . . ሠራተኛና አመራርና ግንባር ቀደም የምንል ከሆነ አገሪቱን እየገደልን መሆናችንን መርሳት የለብንም፡፡ ይህ እኔ በተጨባጭ ያያሁት ስለሆነ፡፡ ሁላችንም የመንግሥት ተቋማት አመራርና ሠራተኛ ተገልጋይ የሚፈልገውን አገልግሎት በተፈለገው ጊዜ፣ ጥራትና መጠን በመስጠት እርካታና አመኔታን በማሳደግ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን እናድርግ፡፡ የለውጥ መሣሪያ አስፈጻሚ ተቋምም ለውጥን በወረቀት ሳይሆን በተግባር ለመገምገም ጥረት ያድርግ፡፡ ቸር ይግጠመን!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው goitomtekele640@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡
