በመታሰቢያ መላከሕይወት ገብረክርስቶስ
በእንግሊዝ አገር የኢንዱስትሪ አብዮት ይካሄድ በነበረበት ወቅት ነበር ባቡርም ተፈልስፎ ሥራ የጀመረው፡፡ በዚህ ጊዜ ካርል ማርክስ በሕይወት የነበረበት ወቅት ነበርና ባቡር የካፒታሊዝም ዕድገት በባቡር አማካይነት በፍጥነት እንደሚሆንና ወደ ሶሻሊዝም የሚደረገው ጉዞ እንደሚፋጠን ጽፎ ነበር፡፡
ካርል ማርክስ እንደተነበየው ካፒታሊዝም በከፍተኛ ፍጥነት ማደግ ቢችልም፣ እንደተባለው ወደ ሶሻሊዝም የሚደረገው ጉዞ ግን የተሳካ አልነበረም፡፡ በዚህ ጽሑፍ በዋናነት ለመዳሰስ የምፈልገው ጉዳይ ባቡር በአንድ አገር ብቻውን ታላቅ ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችል፣ ከባቡር ጋር በርካታ በካፒታሊስታዊ ሥርዓት ሊተገበሩ የሚገቡ ተግባራት መኖራቸውን ነው፡፡
እንደሚታወቀው የባቡር ዋና አስፈላጊነቱ “Mass Load” (ብዝኃ ጭነት) ለማጓጓዝ የሚያገለግል የምድር መጓጓዣ ዘዴ ነው፡፡ ብዝኃ ጭነት ደግሞ የብዝኃ ምርት መኖርን የግድ ይላል፡፡ ብዝኃ ምርት እንዲኖር ደግሞ ዜጎች እንደ ዝንባሌያቸው የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት ያለ ችግር ሚፈልጉትን መሬት እየገዙ፣ ያለ ምንም ውጣ ውረድ ወደ ሥራ መግባት መቻል አለባቸው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ይህንን ተግባር ሕጋዊ የሚያደርግ የሕገ መንግሥት ሥርዓት መኖር አለበት፡፡
እዚህ ላይ ለማሳሰብ የምፈልገው ከላይ ከተጠቀሱት ተግባራት አንዱ እንኳን በአግባቡ ተሟልቶ ካልተገኘ ባቡርን በበቂ ሁኔታ መጠቀም የሚያስችል ምርት ማምረት የማይታሰብ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አሁን የገነባውን ባቡር ውጤታማ ለማድረግ በገበያ መር ኢኮኖሚ የሚመራ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መኖሩ የግድ ይላል፡፡ ይህንን በድፍረትና በተፋጠነ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ ካልተቻለ፣ ባቡሩ የተገነባበትን የብድር ገንዘብ ከሌሎች ዘርፎች ከሚገኝ ገንዘብ ለመክፈል የምንገደድ በመሆኑ አገሪቱን ወደ ከፋ ድህነት ይከታታል፡፡
በቅርቡ ሪፖርተር ጋዜጣ እንዳስነበበን ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች ካላት አቅም አኳያ ከአሥር በመቶ በታች መሆኑ በእጅጉ አስደንጋጭ ዜና ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ለማሻሻል ባቡር አንዱ አማራጭ ቢሆንም ለሁሉም ግን አማራጭ አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ ካላት የሚታረስ መሬት አብዛኛው በዝናብና በመስኖ የሚለማ ሆኖ ሳለ በካፒታል፣ በዕውቀት፣ በገበያ ዕጦት ምክንያት አብዛኛው ገበሬ ዝናብን ጠብቆ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የማምረት ልምድ በበቂ ሁኔታ መለወጥ አልቻለም፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ብዝኃ ምርት ለማምረት በበሬ የሚታረስ መሬት የትም አያደርሰንም፡፡ ከገበሬው ፍጆታ አልፎ ባቡር ላይ የሚጫን ምርት ለማምረት የግድ ዘመናዊ እርሻ መስፋፋት አለበት፡፡ ይህ ዓይነት የአስተራረስ ዘዴ አምራቾች የእርሻ ባለሙያዎችን እየቀጠሩ የአፈር ምርመራ፣ የአዝርዕት ዓይነቶችንና ሌሎችንም ሳይንሳዊ ሥራዎችን በማከናወን የኤክስፖርት ደረጃ ያሟሉ ምርቶችን እንዲያመርቱ ይረዳቸዋል፡፡ እጅግ አስቸጋሪ የሆነውንና ውድድር የበዛበትን የኤክስፖርት ገበያ አሸንፎ አገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግ መሥራት ካልተቻለ፣ ባቡራችን የዕድገት የብልፅግና ምንጭ መሆኑ ይቀርና ለከፋ ችግር ሊዳርገን ይችላል፡፡
ኢሕአዴግ ደጋግሞ እንደሚነግረን በአነስተኛ ማሳ ላይ የሚከናወን የእርሻ ሥራ ከምንም ዓይነት ሳይንሳዊ ዘዴ ጋር ያልተያያዘ በመሆኑ፣ የትም ሊያደርስ የማይችል መሆኑን ተገንዝበን ፈጣን ዕርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን፡፡
እንደሚታወቀው ባቡር የብዝኃ ምርት ማጓጓዣ እንደመሆኑ መጠን በሦስት የተከፋፈሉ ጉዳዮች ላይ ለማተኮር እንገደዳለን፡፡ አንደኛ በብዛት የተመረተ የእርሻ ምርት፣ ሁለተኛ በብዛት የተመረተ የኢንዱስትሪ ምርትና ሦስተኛ በብዛት የተመረተ የጥሬ ማዕድን ምርት ናቸው፡፡
አሁን ባለንበት የዕድገት ደረጃ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች በባቡር ተጉዘው ከቦታ ቦታ ይጓዛሉ የሚለው ተቀባይነት ይኖረዋል ብዬ አላምንም፡፡ በመሆኑም ባቡሩ በርካታ ሰዎችን በማጓጓዝ ከፍተኛ ገቢ በቅርብ ጊዜ ያገኛል የሚል እምነት የለኝም፡፡
ባቡር እንደሚታወቀው ብዝኃ ምርትን፣ ብዝኃ ትራንስፖርትንና ብዝኃ ፍጆታን የሚረዳ ዓይነተኛ መንገድ ሲሆን፣ ባቡሩ ውጤታማ እንዲሆን ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ሁሉ በበቂ ሁኔታ ተሟልተው መገኘት አለባቸው፡፡ በመሆኑም አንዱን ከአንዱ ለይቶ ማየት ወይም ልዩ ትኩረት መስጠት ትልቅ ስህተት ነው፡፡
ሌላው ትልቁ ቁም ነገር ሕገ መንግሥት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አይለወጥም አይሻሻልም የሚባል ነገር ሳይሆን ሁኔታዎች በተለወጡና ሳይንስ ባደገ ቁጥር፣ የሕዝብ ብዛትና ፍላጎት እየጨመረ ሲመጣ በየጊዜው ወቅትን ተከትሎ መሻሻል ካልቻለ የሚያስከትለው ችግር አገርን እስከ ማፍረስ የሚደርስ ነው፡፡ ይህንንም ክስተት በቅርብ ዓመታት በብዙ የዓለም አገሮች ሲከሰት ተመልክተናል፡፡
በዚህ ጽሑፍ አርዕስት ላይ እንደተጠቀሰው ባቡር የካፒታሊዝም መሠረተ ልማት በመሆኑ፣ መሬት መሸጥ መለወጥም በአንድ ካፒታሊስት ማኅበረሰብ ዋነኛ ተግባር ነው፡፡ ሁለቱን ነጣጥሎ ማየት በምንም ሁኔታ የማይታሰብ ነው፡፡
በዓለማችን በተለያዩ ጊዜያት በኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ያመጡ ቴክኖሎጂዎች ተፈጥረዋል፡፡ ከዛሬ 100 ዓመት በፊት በአውሮፓ ፎቶ ማንሳት ሲጀመር በጣም በርካታ ሠዓሊያን (የሰው ምሥል እየሠሩ ይተዳደሩ የነበሩ ሰዎች) ሥራ አጥ ሆነዋል፡፡ በ1990ዎቹ ደግሞ ዩሮታናል የሚባል በባህር ሥር የተሠራ ዋሻ ከፈረንሣይ እስከ እንግሊዝ ከተገነባ በኋላ፣ የበርካታ ሰዎችን ሥራ ባቡሩ ስለወሰደባቸው ለጊዜው የተወሰነ መንገራገጭ ተፈጥሮ ነበር፡፡
አሁንም በአገራችን ከአዲስ አበባ እስከ ጂቡቲ ያለው መስመር ሥራ ሲጀመር ለተወሰነ ጊዜ መንገራገጭ መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ነገር ግን በሒደት ከአዲስ አበባ እስከ ጂቡቲ ኮንቴይነር የሚያጓጉዙ የጭነት ተሽከርካሪዎች የሥራቸው ዓይነት ይቀየራል እንጂ ሥራ ፈት አይሆኑም፡፡ ምክንያቱም ባቡር በባህሪው እጅግ ብዙ ጭነት ስለሚፈልግ እነዚህ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ጉዞዋቸው ወደ ባቡር ጣቢያ ይሆናል፡፡ በሒደትም እስካሁን ወደ ውጭ የማንልካቸው በርካታ ምርቶች በባቡር መጫን ሲጀምሩ፣ በአገር ውስጥ ያለው የጭነት ፍላጎት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ስለሚሄድ የሥራ ዕድል ይሰፋል እንጂ አይጠብም፡፡ በመሆኑም ከአዲስ አበባ ጂቡቲ የተሰማሩ ባለ ከባድ ተሽከርካሪዎች ሐሳብ ሊገባቸው አይገባም፡፡
አንድ በአገር ደረጃ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ እንደ ባቡር ያለ ቴክኖሎጂ በሚተዋወቅበት ወቅት፣ ለአንዱ እንጀራ ፈጣሪ ለሌላው ሥራ አጥነትን የማምጣቱ ክስተት የተለመደ ነው፡፡ ቢሆንም ራስን ቶሎ ከሁኔታዎች ጋር በማመሳሰል መፍትሔ ማግኘት ግን የማይቻል አይደለም፡፡ በተለይ በባቡር ጣቢያዎች አካባቢ እጅግ በርካታ የሥራ ዕድል መፈጠሩ ስለማይቀር፣ መንግሥትም ሆነ ባለይዞታዎች በዚህ ዘርፍ ሰፊ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ረቡዕ ጥር 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በወጣው የሪፖርተር ጋዜጣ የፊት ገጽ የዶ/ር ኢንጂነር ጌታቸው በትሩን ፎቶ ይዞ የወጣው ዜና ባቡሩ ስላለበት ዕዳ በርካታዎችን ያስደነገጠ ሲሆን፣ እኔን ያስደነገጠኝ ግን ዕዳው ሳይሆን ዕዳውን ቶሎ ቶሎ መክፈል እንዴት እንደሚቻል ነው፡፡ ለዚህም ባቡሩን ከደረቅ ወደብና ከተለያዩ ዴፖዎች ጋር የማገኛኘት ሥራ አለመሠራቱ በራሱ አስደንጋጭ ሲሆን፣ በዚህ ሪፖርት ላይ ለምን ይህ ጉዳይ ትኩረት እንደተነፈገው አልተገለጸም፡፡
ከላይ እንደተገለጸው ባቡር በርካታ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ለማሳለጥ የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ ይህ ጉዳይ በቂ ትኩረት አለመገኘቱ በግሌ በጣም አሳስቦኛል፡፡ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች የሚደራጁባቸው ዴፖዎችን የግሉ ዘርፍ በከፍተኛ ፍላጎት ሊሠራቸው የሚገባቸው በመሆናቸው ጉዳዩ ሊታሰብበት የሚገባው ገና የባቡር ልማት ሲጀመር ነበር፡፡ እነዚህን ዴፖዎች በአግባቡ መገንባት ከተቻለ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ዕድል ፈጣሪ የመሆን አቅም መፍጠር የሚቻል ከመሆኑም በላይ፣ ከገጠር ለሚሰደዱ ወጣቶች የስበት ማዕከል የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ውጭ ሊላኩ የሚችሉ ዕቃዎች ወይም ምርቶች የሚቀነባበሩባቸው መሠረተ ልማቶች በባቡር ጣቢያው አካባቢ ባለመኖራቸው፣ ነጋዴዎች ምርቶቻቸው፣ ገዢዎቻቸው በሚጠይቁት ደረጃ ማቀነባበር ካልቻሉ በቂ ምርት ቢኖርም መላክ አይቻልም፡፡ ለምሳሌ አንድ ነጋዴ ከየገበሬው ማሳ የመጣን ፍራፍሬ ባቡር ጣቢያ አካባቢ ተረክቦ በተፈለገው መንገድ አቀነባብሮና አሽጎ ባቡር ላይ ለመጫን የሚያስችሉ፣ እንደ መጋዘን የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ መዘጋጀት ነበረባቸው፡፡
ይህ ባለመደረጉ አሁንም ባቡሩ ሊጭነው የሚችለው ጭነት በአገር ውስጥ እያለ፣ ነገር ግን መሠረተ ልማቱ ባለመኖሩ ብቻ አገሪቱ የምትችለውን የውጭ ምንዛሪ ታጣለች ማለት ነው፡፡
ባቡሩ ሥራ ሲጀምር በርካታ መደነባበር የሚፈጠር ይመስለኛል፡፡ በተጨማሪም ባቡሩን ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በበቂ ሁኔታ ሠልጥነው ማስተዳደር እስኪጀምሩ ድረስ የሚያስተዳደሩት ቻይናውያን በመሆናቸው፣ እነዚህ ሰዎች ምን ያህል ተቋሙ ዕዳውን ቶሎ ቶሎ ሊከፍል በሚችልበት ደረጃ ያስተዳድሩታል የሚለው አሳሳቢ ይመስለኛል፡፡
እኔ ባሳለፍኩት የሥራ ዘመን የዓለምን ግማሽ አይቻለሁ ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ በዚህ ጊዜ ካየኋቸው የሠለጠኑ አገሮች የባቡር ጣቢያዎች መሠረተ ልማቶች በአጭሩ ለመግለጽ፣ ባቡር ጣቢያዎች በራሳቸው አንድ የከተማ ትልቅ አካል ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ምንም የሚጎድላቸው ነገር የለም፡፡ ሌላ ቀርቶ በብዙ አገሮች የከተማውን ቆሻሻ ሳይቀር ይዘው የሚወጡት ባቡሮች ናቸው፡፡ የቆሻሻ መኪኖች ከከተማው የተለያየ ክፍል የሰበሰቡትን ቆሻሻ ወደ ቆሻሻ ዴፖ ሲወስዱት ባቡሩ ደግሞ ከከተማ ውጪ ይወስደዋል፡፡ ይህ ለምሳሌ ቀረበ እንጂ ዴፖዎችን በተመለከተ ራሱን የቻለ አንድ ሰፊ ጥናታዊ ጽሑፍ ማቅረብ ይቻላል፡፡
ከጂቡቲ እስከ አዲስ አበባ የተዘረጋው የባቡር መስመር ከባህር በላይ አሥር ሜትር ከማይሞላው የጅቡቲ ወደብ ተነስቶ አዲስ አበባ ሲገባ 2,500 ሜትር ከፍታ የሚወጣ ብቸኛ አፍሪካ ውስጥ ያለ የባቡር መስመር ነው፡፡ ወደ ፊት ደግሞ ደጋማ ወደሆኑ ቦታዎች መስመሩ ሲቀጥል ይህ ከፍታ መጨመሩ አይቀርም፡፡ ይህ ማለት በቆላውና በደጋው የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የተለያዩ ምርቶችን ለመለዋወጥ ባቡር ዋነኛ መሣሪያ ነው፡፡ በተለይ በደጋው አካባቢ የሚመረተው የታሸገ ውኃ ለቆላው አገር ሰዎች ለማድረስ ሁነኛ መሣሪያ ነው፡፡ አገሪቱ ከውኃ ኤክስፖርት ከፍተኛ ገቢ የምታገኝ ይመስለኛል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ክረምት ሲሆን በዝቅተኛው አካባቢ የሙቀት መጠን በከፍተኛ መጠን ስለሚጨምር፣ የውኃ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ የሚደራ ይመስለኛል፡፡
ሌላው ደግሞ ለኢትዮጵያ ዜጎች ፍጆታ የሚውለው ምርት ውጭ አገር ተልኮ ዶላር ስለሚያገኝ ብቻ ኤክስፖርት የሚደረገውን ምርት እንኳን በአሁኑ ወቅት በአግባቡ የለየነው አይመስለኝም፡፡ መንግሥት ይህንን ማድረግ ካልቻለ ነጋዴው የሕዝብ ፍጆታ የሆነውን ምርት ሁሉ ባቡር ላይ ጭኖ ወደ ውጭ የሚልከው ከሆነ ያልተጠበቀ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል፡፡ በብዙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ይህ ችግር ለረጅም ጊዜ ተከስቷል፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎች ከባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር ይህንን ሥራ ሥራዬ ብለው ሊይዙት ይችላሉ፡፡
አፄ ምንሊክ የገነቡት የባቡር መስመር ምንም እንኳን ኢትዮጵያን ለማሳደግ አስተዋጽኦ ቢያደርግም፣ በስተመጨረሻ ተንገራግጮ የቆመው የአገሪቱ ፖለቲካል ኢኮኖሚ በተፈለገው መልኩ ወደ ካፒታሊስታዊ ሥርዓት መለወጥ ባለመቻሉ ነው፡፡ በመሆኑም ባቡር፣ ካፒታሊዝምና ተጓዳኝ ሕገ መንግሥታዊ መሻሻሎች አብረው መሄድ አለባቸው፡፡
ብዙ ጊዜ ወደ ቃሊቲ አካባቢ የተጓዘ ሰው አንድ የሚመለከተው ነገር አለ፡፡ ይኸውም ከባድ ተሸከርካሪ ያላቸው ባለሀብቶች የከባድ ተሸከርካሪውን ተሳቢ በዋናው መኪና ላይ በመጫን ወደ ጅቡቲ የሚደረግ ጉዞ አለ፡፡ ይህ የሚነግረን በእርግጠኛነት ከአገር ውስጥ በቂ ጭነት ወደ ውጭ አገር የሚላክ አለመኖሩን ነው፡፡
አሁን ደግሞ ባቡር ገንብተን ጨርሰናል፡፡ ባቡሩ ከ30 በላይ ታሳቢ ይዞ የሚጭነው ጭነት አጥቶ ወደ ጂቡቲ የሚጓዝ ከሆነ እንዴት ነው ዕዳውን የሚከፍለው? ጭነት ለማግኘት በዋናነት እኛ ኢትጵያውያን ጠንክረን መሥራት አለብን፡፡ ጠንክሮ ለመሥራት ደግሞ ለሥራ የሚመች ሕግና አስተዳደር መኖር አለበት፡፡
አብሮ ለመሥራት የሚያችል የአክሲዮን ማኅበራት አደረጃጀት የማይታሰብ በሆነበት አገር እንዴት አብሮ መሥራት ይቻላል? በጣም በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ንግድ ሚኒስቴር የሚባል መሥሪያ ቤት በቅርቡ ስለማውቀው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮ ለመሥራት የሚያደርገውን ጥረት ለመቆጣጠር የሚያስችል ቁመና እንደሌለው ነው፡፡ በግል ደግሞ የሚደረግ መፍጨርጨር ከአገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለኤክስፖርት የሚሆን ምርት ማምረት ከቶውንም የማይታሰብ ነው፡፡
በዚህ ላይ በአገራችን በስፋት የተንሰራፋው የዘር ፖለቲካ ሌላኛው ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ ለመሥራት የማያስችል እንቅፋት ነው፡፡ ለዚህ ነው ከባቡሩ ጋር የሚሄድ መንግሥታዊ አወቃቀርና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ይኑረን የምለው፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ለልጆቻችን የምናወርሰው ባቡሩ ያወጣውን ቱሩፋት ሳይሆን የባቡሩን ዕዳ ይሆናል፡፡ ወይም ደግሞ ዓባይን ገድበን የኤሌክትሪክ ኃይል ሸጠን የምናገኘውን ገንዘብ ለባቡሩ ዕዳ እናውለዋለን ማለት ነው፡፡
በመሆኑም አገሪቱን የሚያስተዳድረው ኢሕአዴግ ወደቡን ጠበቅ አድርጎ በቂ ሥራዎች የሚሠራበት ወቅት አሁን ነው፡፡ ለአሥር ዓመታት በተከታታይ በሁለት አኃዝ ያደገ ኢኮኖሚ ባቡር ላይ የሚጫን ምርት እንዳለው የሚፈትሽበት ወቅት አሁን ነው፡፡ የሪፖርተር ዓምደኛ አቶ ጌታቸው አስፋው ደጋግመው እንደፈረጁት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በበሬ ከሚታረስና ከጆንያ ኢኮኖሚ ያልወጣ በመሆኑ፣ ይህ ዓይነት የኢኮኖሚ ሥርዓትና የባቡር ልማት አብረው መሄዳቸውን የምናይበት ወቅት አሁን ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
