በኦሜርታ ይበቃል
ዕለቱ ሰኞ ነው ጥር 22 ቀን 2009 ዓ.ም. 11፡30 አካባቢ ከሜክሲኮ አደባባይ ወረድ ብሎ እገኛለሁ፡፡ ወደ ጀሞ ኮንዶሚኒየም ለመጓዝ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት የሚጠባበቁ ሠልፈኞች መጨረሻ ላይ ቆሜያለሁ፡፡ ከፊቴ ያለውን ሠልፈኛ ሕዝበ አዳም ምን ዓይነት ተዓምር መጥቶ እንደሚያነሳውና እንደሚሳፈር አላውቅም፡፡ ደግነቱ ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ ሠልፉ ላይ ያሉ ቆነጃጅትን ማየትና ማድነቅ በመቆም ምክንያት የሚመጣን መሰልቸት ያስረሳል፣ ድካምን ይቀንሳል፡፡ ጀሞ ማለት የት እንደተወለዱ ባናውቅም የቆንጆዎች መሰብሰቢያ የሆነች አዲስ አበባ ውስጥ የምትገኝ አዲስ ውብ ከተማ ሆናለች፡፡ ጓደኛዬ የቤት ኪራይ እየተጨመረበትም ቢሆን ለምን ያን አካባቢ ለቆ መሄድ እንደማይፈልግ የተገለጸልኝ መሰለኝ፡፡ ውበትን ማየትና ማድነቅና ጥሩ ነገር መመልከት የማይወድ ማን አለ? የምጓዘው ጓደኛዬ መጥተህ ውሰድ ብሎ ቃል የገባልኝን መጽሐፍ ለመዋስ ነው፡፡ ደርሼ ለመመለስ ሳይመሽ ሦስት ሰዓት ሆኖ የተከራየሁት ቤት የአጥር በር ሳይቆለፍ ያለዚያ መዘዙ ብዙ ነው ውጭ ማደርም አለ፡፡
ከድካሙም፣ ከመሰልቸቱም፣ ውጭ ከማደሩም ለመውጣት መፍትሔ በቶሎ ትራንስፖርት አግኝቶ መንቀሳቀስ አሊያም ቀኝ ኋላ ዙር ብሎ ወደ ቤት መመለስ ነው፡፡ ይህን እያሰላሰልኩ ለመወሰን ተቸግሬ ቆሜ ሳለ ድንገት ከፊቴ የነበረው ሠልፍ በሚገርም ሁኔታ መቃለል ጀመረ፡፡ እንዴት ሊሆን ቻለ ብዬ ሳይ የተለያየ ቀለም ያላቸው በብዛት ነጭ የሆኑ ጎናቸው ላይ በተለያየ ስም የአገር አቋራጭ አውቶብሶች መሆናቸውን የሚገልጽ ስቲከር የለጠፉ አውቶብሶች ውስጥ በርካታ ሕዝብ እየገባ አውቶብሶቹ ይሄዳሉ፡፡ እኔም ተራዬ ደርሶ ገባሁ፡፡ ብዙ አገልግሎቶች ላይ እጥረትን የሚፈጥረው የፍላጎት መጨመር ብቻ ሳይሆን ያለውን ፍላጎት ተረድቶና ተንብዮ ለምላሽ ያለመጣር፣ በየትኛውም እጥረት ባለበት ዘርፍ ላይ ፍላጎት መኖሩንና እየጨመረ መሄዱን ለማወቅ ያለመፈለግ ነው፡፡ ችግሩን በተጨባጭ ቀምሰው ያለማወቅ ችግር የየዘርፉ ባለሥልጣናት መሠረታዊ እጥረት መሆኑን ድሮ ኢኮኖሚክስ ስማር ያገኘሁትን ዕውቀት አሟጥጬ በመጠቀም ለራሴ ትንታኔ ሰጠሁ፡፡ (ከተነሳብኝ እንዲህ ነኝ በአንድ ጊዜ ራሴን ከዕድር መሪነት አስተሳሰብ ወደ አገር መሪነት አስተሳሰብ ለማሸጋገር ሰከንድ የማይፈጅብኝ ለራሴ ነው ታዲያ) ይህንን የአውቶብስ ትራንስፖርት አገልግሎት ኅብረተሰቡ እንዲያገኝ ሐሳቡን ያመነጨና ተግባራዊ ያደረገ ብሎም እንደ ሌሎች አንዳንድ ሥራዎች ሳይቋረጡ ቀጣይነት እንዲኖራቸው ያደረገን ግለሰብ፣ ቢሮ እንዲያው በአጠቃላይ ችግር ፈቺ የሆነውን አካል ያበቀለች ማህፀን የተባረከች ትሁን አልኩኝ፡፡
አውቶብሱ ውስጥ ገብተን ቁጭ ካልን በኋላ መንግሥት የጀሞ ኮንዶሚኒየምን ገንብቶ ለነዋሪዎች ማስረከቡ ብቻ በቂ አለመሆኑን ተረድቶ በአንድ ወቅት ጎልቶ ይታይ ለነበረው የትራንስፖርት ችግር በዚህ መልኩ ጊዜያዊ መፍትሔ መስጠቱን በማድነቅ፣ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ እየሰማሁ ጉዟችንን ጀመርን፡፡
በዚህ መሀል የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የሚገኝበት ወደ አፍሪካ ኅብረት አካባቢ ስንደርስ የአዲስ አበባ ከተማን ከመንገድና ትራንስፖርት ጋር በተያያዘ ያሉ ሥራዎችን ለመሥራት የተቋቋመውን ቢሮ አቅጣጫ እየጠቆሙ ጨዋታ ተጀመረ፡፡ ቢሮው አዲስ አበባ ከመንገድና ከትራንስፖርት ጋር በተያያዘ ያሉባትን ችግሮች በተሻለ ሁኔታ ለመፍታት በአዲስ መልክ ብዙ ዘርፎችን በመያዝ የተዋቀረ መሆኑንና አዲስ ኃላፊዎች የተመደቡለት መሆኑን፣ እንዲሁም ቢሮው ከሚመራቸው ተቋማት መካከል አንዱ አንበሳ አውቶብስ መሆኑን አንድ እንዲሁ ሲያዩት ለቢሮው ያለው ዕውቀት ሰፋ ያለ የሚመስል ሰው መናገር ሲጀምር፣ ጨዋታው መልኩን ቀይሮ የከተማችን መለያ ምልክት ወደሆነው አንበሳ የከተማ አውቶብስ ድርጅት ዞረ፡፡
እኔም ይህንን ከልጅነት እስከ ዕውቀት የተጓጓዝኩበትንና አሁን አሁን ግን እሱን ቆሞ በመጠበቅ ጨጓራዬን ከማቃጥል ወይ ገንዘቤን ወይ እግሬን ባቃጥል ይሻላል ብዬ፣ ረዘም ያለውን መንገድ ተጨማሪ ገንዘብ በመክፈል በሌላ የትራንስፖርት አማራጭ እጠቀማለሁ፡፡ አጫጭሩን ደግሞ በእግሬ በመጓዝ ከአንበሳ ጋር ያለኝን የደንበኝነት ውል እሱ ሳያውቀው አፍርሼአለሁ፡፡ ይህንን እንደ አዲስ ሳስበው ልክ የልጅነት የከንፈር ወዳጅን እያስታወሱ የት ይሆን ያለችው/ያለው እየተባለ በሐሳብ እንደሚኬደው የረጅም ጊዜ ደንበኛዬ የነበረው አንበሳ አውቶብስ የት ምን ደረጃ ያለው የሚል ጥያቄ ስለጫረብኝ፣ ድርጅቱ አሁን ያለበትን ሁኔታ ላጣራና ያገኘሁትን መረጃም ጥሩም ሆነ መጥፎ ለእናንተ ለአንባቢዎቼ ላጋራ፡፡ ምናልባት ሚዛን የሚደፋና ውኃ የሚቋጥር ቁም ነገር ከተገኘበትም ለድርጅቱ ባለድርሻ አካላት (ከመንግሥት ጀምሮ እስከ ግለሰብ ድረስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የዚህ ድርጅት ባለድርሻ ያልሆነ ያለ አይመስለኝ) ወቅታዊ እውነታዎችን ለማድረስ እያሰብኩ ጉዞዬን ጨርሼ መውረጃዬ ደርሶ ወረድኩ፡፡
በ1935 ዓ.ም. የተቋቋመው አንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ይህንን መጠሪያ ስም ከማግኘቱ በፊት በተለያዩ ስሞች እየተጠራ ለ74 ዓመታት ያህል ተጉዞ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ሦስት መንግሥታትን እያፈራረቀ ያየ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ያለፈ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱን በሀብት ደረጃ እንለካው ብንል ካለፉት ሁለት መንግሥታት በጣም በጣም በተሻለ ሁኔታ በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶት የበርካታ አውቶብሶች ባለቤት የሆነበት፣ የዴፖዎች ግንባታ የሚከናወንበትና የመሳሰሉት በብዙ መቶ ሚሊዮኖች ምናልባትም ቢሊዮኖች በሚደርስ ወጪ የተለያዩ የለውጥ ሥራዎች ክንውን የሚስተዋልበት ድርጅት ሆኗል፡፡ ይህን ያህል ሀብት ያለው ከ3,500 በላይ ሠራተኞችን ያቀፈ ድርጅት እንዴት ሆኖ ነው የተሻለ አገልግሎት መስጠት ላይ ለውጥ ማምጣ ያቃተው? ለምንድነው ቆሞ የቀረው (ምናልባትም ወደ ኋላ የተመለሰው)? የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡ ምክንያቱም እኔን ጨምሮ ብዙ ደንበኞች አንበሳን በአንደኛም በሁለተኛም በሦስተኛም ደረጃ ያለ አማራጭ አድርጎ ማሰብ ካቆምን ሰነበትን፡፡ የተሻለ አገልግሎት የሚሰጠውና የደንበኞች ዕርካታ የሚመጣው አንድ ድርጅት ባለው ሀብትና የሰው ኃይል ብዛት ቢሆን ኖሮ አንበሳን እንደ ስሙ አንበሳ ማድረግ በተቻለ ነበር፡፡ ነገር ግን አልሆነም፡፡ መንግሥት ብዙ ሀብት አፍስሶ አውቶብሶች ይገዛል፣ ድጎማ ይሰጣል፣ ሌላም ሌላም ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በእውነት ከሆነ ግን ደንበኞች እየረኩ ነው ለማለት የሚያስችል ሁኔታ የለም፡፡ እስቲ ለዛሬ ድርጅቱ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የሠሩና አሁንም እየሠሩ ካሉ አንዳንድ የድርጅቱን ገመና ከእኔና ከእናንተ በተሻለ ሁኔታ የማወቅ ዕድል ካላቸው ሠራተኞች ጋር ካደረኩት ጭውውት የሰማሁትን፣ ሠራተኞቹ እንደ ወላጅ እናትና አባት የሚያዩትን ድርጅት ለዚህ አበቃብን ብለው በሚያስቡት አመራርና በሠራተኛው መሀል ተቃርኖ ፈጥሮ ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃር ወደፊት እየተጓዝን ነው እየተባለ በማኔጅመንቱ ሲወራለት የነበረውን የኋልዮሽ ጉዞ እንዲከሰት ምክንያት ነው ብለው የሚያስቡትን እነሆ ልበላችሁ፡፡
እንደነዚህ ሠራተኞች አባባል ከሆነ አሁን ከተከሰተው ደካማ የሆነ አገልግሎት አሰጣጥ ዋና መንስዔ ወደኋላ መለስ ብለው በፊት የነበረው ማኔጅመንት የፈጠረው መርህን ሳይሆን ጓደኝነትን፣ ዝምንድናንና ቤተሰባዊ ቅርርብን መሠረት ያደረገ ግንኙነት ነው፡፡ በድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎችና በብዙኃኑ ሠራተኛ መካከል የተፈጠረው ልብ ለልብ ተገናኝቶ መሥራት ያለመቻል አንስቶ አሁን በቅርቡ እስከነበረው በአንድ ወገን ያለ እኔ ብቻ ነኝ የልማትና የለውጥ ኃይል፣ ብቸኛው አማራጭ እኔ ብቻ የምለው ነው ብሎ የግል ይሁን የመንግሥት ያልለየ (ወደኋላ ላይ የግለሰብ መሆኑ ተረጋግጧል ይላሉ) ፍላጎትን የመንግሥት ነው በሚል በኃይልና በአምባገነንነት ለመጫን መሞከርን፣ ሠራተኛው መሀል የሚገኙ አንዳንድ ሆድ አደሮችን ማን ከማን ቆመ? ምን አወራ? ምን አሰበ….የሚል መረጃ አቀባይ እንዲሆኑ በሠራተኛው ላይ የጎበዝ አለቃ አድርጎ በመሾም ሕጋዊ መብታቸውን የሚጠይቁ ሠራተኞችን ጠርቶ ማስፈራራት፣ እንዲሁም በግዴታ የዓመት ፈቃድ እንዲወጡ ማድረግ (ወደኋላ ላይ የተወሰደባቸው ዕርምጃ ትክክል አለመሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ያጡትን ክብርና ጥቅም ማስመለስ ባይቻልም) ነበር የሚልን እንደ ዋና ችግር ሲያነሱ. ሌሎች ችግሮችንም መልካሙ ጊዜ ብለው ከሚጠሩት ወቅት ጋር እያነፃፅሩ ያነሳሉ፡፡
እንደነዚህ ውስጥ አዋቂዎች አባባል የአዲስ አበባን የብዙኃን ትራንስፖርት ችግር ለመፍታት ወሳኝ ሚና ካላቸው ድርጅቶች መካከል አንበሳ አውቶብሶች አንዱ ሆኖ ሳለ ይህንን ችግር ለመረዳትም ሆነ ለመፍታት አቅምም ሆነ አቋም የሌላቸው፣ በሥራቸው ሳይሆን በአፋቸው በሚኖሩ፣ የወገባቸው ጎንበስ ቀና ለሥራ ሳይሆን ለአድርባይነት የሆነ የሥራ ኃላፊዎች መሞላትና በድርጅቱ የበላይ አመራር፣ በድርጅቱ የሥራ እንቅስቃሴ፣ በተለይም ሠራተኞች ላይ የሚደርሰው ሰብዓዊ ክብርና ሞራል የሚነካ፣ ዴሞክራሲያዊነትን ያልተላበሰ፣ አምባገነንነትና ጀብደኝነት የተሞላበት፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ቅሬታ እንዲሰማው የሚያደርግ፣ ያለንበትን ዘመን ግምት ውስጥ ያልከተተ ስድብ አዘል ንግግር (እዚህ ላይ ተሰደብን የሚሉትን ቃል በቃል ያነሳሉ ጸያፍ ነገሮችን መጻፍ አግባብ ስላልሆነ ትቼዋለሁ) የሰዎችን አለማወቅና አለመማር መሳቂያ መሳለቂያ ማድረግ፣ የተማረውንም እኔ በቀደድኩልህ ቦይ ካልፈሰስክ ያንተ ትምህርት ትምህርት አይደለም ዕውቀትህም መና ነው ብሎ ማመን ነው፡፡ በአጠቃላይ ከመንግሥት መርህና ከከተሜው ማኅበረሰብ ወግና ልማድ ውጪ በሆነ መንገድ የነገሮችን መነሻና መድረሻ ራስን ብቻ አድርጎ ማየትን መታገል አለመቻልና በዚያን ወቅት ለተሠሩ ስህተትና ትፋቶች ለድጋፍ ያወጡትን እጅ መልሰው ለተቃራኒው ሐሳብ ያለምንም ልዩነት ሲያመጡ ሲታይና ለምን ሲባሉ የእሳት እራት ላለመሆን ብለን ነው እንጂ፣ ያኔም አናምንበትም ነበር የሚል መልስ ሲሰጡ ያለው የሥራ አመራር ስብስብ በፍርኃት የተሸበበና እስከ አፍንጫው ድረስ በአድርባይነት የተሞላ ነው የሚያሰኝ ሁኔታ እንዳለው ይናገራሉ፡፡
አንድ መንግሥት ካለበት ግዴታዎች መካከል አንዱ የተለያዩ አገልግሎቶችን በነፃ ወይም በዝቅተኛ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ማቅረብ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ እንደ ፌዴራልም ሆነ ክልል መንግሥት እነዚህን አገልግሎቶች መንግሥት ለሕዝብ በሚያቀርቡበት ሰዓት ትልቅ ፈተና እየሆነ ያለው የመልካም አስተዳደር ዕጦት ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ከአገልግሎቶቹ እያገኘ ያለው እርካታ ሳይሆን ቅሬታ መሆኑ የመንግሥት ራስ ምታት እየሆነ ያለ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እነዚህን ችግሮች መፍታትና ኅብረተሰቡን ማርካት የሚቻለው የተለያ ማስተካከያዎች ሲያደርጉ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከእነዚህ ማስተካከያዎች አንዱ አገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ ያላቸውን የሰው ኃይል በትምህርትና ሥልጠና በመደገፍ ማብቃት፣ ለዚህ የሚሆን ምቹ ሁኔታ ከሌለና መፍትሔ ካልሆነ የመዋቅር ለውጥና ምደባ እንደ አዲስ በማከናወን ለተገቢው ቦታ ተገቢውን ሰው (The right person to the right place) መመደብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ከሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
ይህንን ታሳቢ በማድረግ አንበሳ አውቶብስ ያለበትን ግዙፍ ችግር ለመፍታት እንዲያስችለው የመዋቅር ጥናት በማድረግ ምደባ ማከናወኑ ይታያል፡፡ እነዚህ ሠራተኞች እንደሚያነሱት ከመዋቅርና ከምደባው ጋር በተያያዘ በአጠቃላይ ለውጥ ለድርጅቱ ዕድገት አስፈላጊና ተገቢ ሆኖ ሳለ አንዳንድ መሠረታዊ ችግሮች ግን ነበሩበት ብለው ያምናሉ፡፡ እንደ ምሳሌም ከሚያነሱት መካከል ተግባራዊ የተደረገው መዋቅር ድርጅቱ ውስጥ ያሉ ሠራተኞችንም ሆነ ገበያ ላይ ያለውን የሰው ኃይል የሥራ ልምድ፣ የትምህርት ዝግጅትና የደመወዝ መጠን ጥያቄና የድርጅቱ የመክፈል አቅምን ግምት ውስጥ ያልካተተ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ነባራዊ ሁኔታን ያልዳሰሰ የመዋቅር ጥናት ለቦርድ ሲቀርብ መፅደቁን እንጠራጠራለን፡፡ ምክንያቱም ቦርዱ መንግሥትን ወክሎ ተቋሙን የሚቆጣጠር አካል ነው፡፡ መንግሥት ማለት ደግሞ ሕዝብ ነው በማለት፡፡ በተጨማሪም አንድ ድርጅት ውስጥ ተግባራዊ ሊደረግ የታሰበ ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ ከተቻለና ሁኔታዎች የሚፈቅዱ ከሆነ ከመላው ሠራተኛ ጋር፣ ካልተቻለም ከሥራ ኃላፊዎች ጋር በጥልቀት መወያየትና የጋራ ማድረግ ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ከመዋቅሩና ከምደባው ጋር በተያያዘ በበቂ ሁኔታ ከሁለቱም አካላት ጋር ውይይት ሳይደረግበት አንድ ነገር ነገ ከነገ ወዲያ ሊያመጣ የሚችለውን ውጤት ጊዜ ወስደው አገናዝበው ለመወሰን ፋታ ሳይኖራቸው፣ አጨብጭበው ተቀብለዋል በሚል በውይይት ያልዳበረ የይድረስ ይድረስ ሐሳብን ይዞ ወደ ተግባር መገባቱ አሁን እየታዩ ላሉ መጠነ ሰፊ መዝረክረኮች አንዱ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም ይላሉ፡፡
ምንም ይሁን ምን መዋቅር መሠራቱና ምደባ መከናወኑ ከነችግሮቹ መልካም ሆኖ ሳለ፣ በተመደቡበት ቦታ ላይ ቅሬታ ያላቸው ሠራተኞችን ቅሬታ ለማየት የተቋቋመው ኮሚቴው ልክ ምደባውን እንዳከናወነው ኮሚቴ ከግለሰቦች ማለትም ተቋሙ አናት ላይ ያሉ የሥራ ኃላፊዎች ፍላጎት በሰፊው የተንፀባረቀበት ነው በማለት፣ እንደ አብነትም ግለሰቦች የመወዳደሪያ መስፈርቱን ቢያሟሉም ባያሟሉም እኔ አልፈልገውም ወይም እፈልገዋለሁ በሚል ደረጃ የሚሰጡበት ወይም የሚነፍጉበት ሁኔታ የተስተዋለበት ነበር ብለው አብነቶችን ያነሳሉ፡፡ እዚህ ላይ ከመስጠትና ከመንፈግ በተጨማሪ አሳፋሪ ነው ብለው የሚያነሱት ለመስጠትና ለመከልከል መሥፈርቱ መንግሥት ለዕድገት ጉዞዬ እንቅፋት ሆኖብኛል ብሎ ያስቀመጠው የወንዜ ልጅ ድንበርተኛዬ የሚል አስተሳሰብና ድርጊት መኖሩ ነው፡፡ የአንድ አካባቢ አስተሳሰብ ገኖ የወጣበት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ‹‹ስናገር ያላጨበጨበ ሲያነጥሰኝ መሐረብ ያላቀበለ›› የሚል ትርጉም ያለው፣ የሰዎችን ልምድና የትምህርት ዝግጅት ሳይሆን ግለሰባዊ ቅርርብን መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ በትምህርት ዝግጅት ይበልጡናል ብለው የሚያስቧቸው ግለሰቦችን ልምድ የለውም የሚል (እዚህ ላይ መንግሥት ከየዩኒቨርሲቲው የሚወጡ ወጣቶችን ለማበረታታት በዜሮ ዓመት የሥራ ልምድ ወደ ኃላፊነት እንዲመጡ የሚያግዝ ፖሊሲ የሚያራምድ መሆኑን ልብ ይላል እንኳን በሥራ ዓለም የቆዩትን)፣ ልምድ ያለውን ደግሞ የትምህርት ዝግጅት የለውም ወይም ከሥራ መደቡ ጋር አብሮ አይሄድም የሚል በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ ትክክል የሆነ ነገር ግን ለአንዱ የሚሠራ ለሌላው (ከላይ ለተጠቀሱት የወንዝ ልጆች) የማይሠራ ሁኔታ ነበር ብለው ያነሳሉ፡፡
በመቀጠል የሚያነሱትም በአዲሱ አመራር እየተሠራ ያለው የተፈጠሩትን ችግሮች የማስተካከል ዕርምጃ በጎ ሆኖ ሳለ ችግሩን የፈጠሩ፣ በአገሪቱ ሕግ ሳይሆን በራሳቸው የጀብደኝነትና ዝናን ፍለጋ ስሜት በመንቀሳቀስ (ዝና እንዴት እንደሚመጣ ያለማወቅ ትልቅ እርግማን ነው) የተደረገ ስህተትና ጥፋት ተጠያቂ ማን መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ እንደ አብነትም ዕድሜያቸው ለጡረታ ያልደረሰ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን (240 አካባቢ ናቸው ይላሉ) ጡረታ እንዲወጡ ሕግ ከሚፈቅደው ውጪ ማስገደድ (በኋላ በሕግ እንደማያስኬድ ታውቆ ማስተካከያ ተደርጎ የሚመለሱ በአዲሱ አመራር ተወስኗል)፣ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የትምህርት ዝግጅታቸው ለተወዳደሩበት ቦታ ብቁ የሚያርጋቸው ነገር ግን ቅሬታ አቅርበውም መፍትሔ ያላገኙ መኖራቸው፣ በግለሰቡ ደረጃ እሱን አልፈልገውም ወይም እፈልገዋለሁ በሚል የተደረገ ምደባ መሆኑ፣ ለአንድ ተቋም ዕድገትም ሆነ ውድቀት ከሠራተኛው ይልቅ አመራሩ ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑ እየታወቀ ለአንበሳ ሥራዎች መዳከም ሠራተኛው ብቻውን ተጠያቂ የሆነ ይመስል፣ ሁሉም ወሳኝ የሆነ የማኔጅመንት አካል ምንም ሳይነካካ ባለበት መቀጠሉ በማጥራት ሥራው ወቅት ሊታዩ መጠነ ሰፊ ችግሮች ባለቤቱ ሠራተኛ ብቻ ነበር ወይ? ለወደፊቱስ እነዚህን የሥራ ኃላፊዎች ይዞ ለውጥ ማምጣት ይታሰባል ወይ? የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ እዚህ ላይ ድርጅቱ ያሉት የሥራ መሪዎች የአዲስ አበባን የብዙኃን ትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የድርሻውን ሚና ለመወጣት የሚንቀሳቀስ ድርጅትን ለመምራት የሚያስችል አቅምና አቋም አላቸው ወይ የሚል ጥያቄን በሰፊው የሚያነሱ ብዙ ናቸው፡፡
እንዲያው በአጠቃላይ ሲታይ ድርጅቱ ውስጥ የነበረው ሁኔታ የሠራተኞች መብት የተጣሰበት፣ ግለሰቦች ያላግባብ ተጎጂ ወይም ተጠቃሚ የሆኑበት፣ የአንድ ሰው ከሕዝብና ከመንግሥት ፍላጎት ውጪ መንቀሳቀስና ፈላጭ ቆራጭ መሆን ገኖ የታየበት፣ የግለሰቡ መንግሥትን ከሚመራው ኢሕአዴግ መርህ ውጪ ራስን ከፓርቲ፣ ከመንግሥትና ከሕዝብ በላይ ነኝ የሚል አስተሳሰብ ገዝፎ የታየበት (ፓርቲው ካሁን በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ግለሰቡ ከሄዱበት ተቋም ተጠርተው እንዲመጡ በማድረግ ስህተትና ጥፋታቸውን አምነው እንዲቀበሉ አድርጓል፣ ይህም ገዚው ፓርቲ ይዘገያል እንጂ አይቀርም የሚለውን በወቅቱ የማስተካከያ ዕርምጃ ያለመውሰድ ሐሜት ያጠናክራሉ) ሠራተኛው እስከሚበቃው ስድብ የጠጣበት፣ ለሠራተኛው መብት ለመታገል የሞከሩ ሠራተኞች ቃል በቃል ካላረፍክ ምላስህን ነው የምቆርጠው ተብለው ታሪክን አስታውሰው ያዘኑበት ነበር እያሉ እነዚሁ ሠራተኞች ያወሳሉ፡፡ መንግሥት የነበረውን ሁኔታ በቅጡ መረዳቱን እንጠራጠራለን፣ ምክንያቱም እነዚህን የሥራ ኃላፊዎች በማረም ፈንታ ድፍን አዲስ አበባን እየዞሩ የስድብ ፀበል እንዲረጩ ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት ማዛወር ለከተማው ሕዝብ አለማሰብ ነው የሚል አስተያየት ያቀርባሉ፡፡
ሌላው እነዚህ ሠራተኞች የሚያነሱት ደግሞ እንደ አንበሳ ያሉ ብዙ ሠራተኛና ሀብትን የሚያስተዳድሩ ድርጅቶችን ለመምራት የሚያስፈልገው የካበተ ስድብና ዘለፋ ሳይሆን የሥራ ልምድ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህንንም መንግሥት የሚያጣው አይመስለንም፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱና ሌሎች የአገሪቱ ሕጎች ላይ ያሉ የዜጎች መብትና ሰብዓዊ ክብሮች በአንዳንድ ሕዝብ ከመንግሥትና ሹመኞቹ ምን እንደሚፈልግ ያልተገለጸላቸው ወይም በእምነት ያልተቀበሉ መሪዎች ሲጣሱ መዘዙ ብዙ እንደሚሆን ነው፡፡ በቀላሉ ሊፈቱ የማይችሉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ በተለይም ደግሞ ፖለቲካዊ ቀውሶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ገምቶ መንቀሳቀስ ያሻል፡፡ መንግሥት በአሁን ጊዜ ለኅብረተሰቡ የሚሰጣቸውን የተለያዩ አገልግሎቶች ለማሻሻልና መልካም አስተዳደርን ማስፈን ያስችለው ዘንድ መድረኮችን እየፈጠረ ከተለያዩ የኅብረተሰብ አካላት ጋር በመወያየት በጥልቀት መታደስን እውን ለማድረግ እየታተረ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ የኅብረተሰብ አካላት ደግሞ አንዱ የአንበሳ አውቶብስ ሠራተኞች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ሠራተኞቹ እንደሚያነሱት ከሆነ በጥልቀት የመታደስ ውይይቱ እየተከናወነ ሳይቀር እዚያው መድረክ ላይ ሌላ ጥልቅ ተሃድሶ የሚያስፈልገው ድርጊት መፈጸም (ተሰደብን የሚሉትን ይጠቅሳሉ)፣ ከተሃድሶው ጋር በተያያዘ የመንግሥትን ፍላጎት አለማወቅ አሊያም በእምነት ያለመቀበል ውጤት ነው ይላሉ፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም ሆኑ የተለያዩ ተቋማት አንዱ ለአንዱ ያለውን ምርጥ ተሞክሮ ለማጋራት የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ አንበሳ አውቶብስም ሌሎች ተቋማት ያላቸውን ምርጥ ተሞክሮ በመውሰድና ያለውን በመስጠት መሥራት ይገባዋል፡፡፡ እነዚህ ውስጡን በደንብ እናውቀዋለን የሚሉ ሠራተኞች እንደሚሉት መዋቅርና ምደባ በአግባቡ ካልተሠራና የሠራተኛውን የሥራ ሞራል የሚጎዱና ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ አላስፈላጊ ንግግሮች ከታከሉበት፣ እንዲሁም እውነት ሳይሆን ቅዠት የሚመስሉ፣ አሁን ባለንበት ደረጃ መሬት እውን ለማድረግ የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የማይፈቅድላቸው፣ በመማር ወይም ማስተማር ሒደት ውስጥ የሚገኙ ቲዎሪዎችን የተቋሙን አቅም፣ ወቅትንና አገራዊ ሁኔታን ሳያገናዝቡ ተግባራዊ አደርጋለሁ ብሎ መነሳት በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ ለለውጥ መነሳሳትን የሚያሳይ ሊመስል ይችላል፡፡ የአንዱን ተግባር ውጤት ሳይመዝኑና ለስኬቱም ሆነ ለውድቀቱ ባለቤት ሳይሰጡ ወደ ሌላው መዝለል (ፓይለት ፕሮጀክት ተብሎ የወጣውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብና የባከነውን ጊዜ ከተገኘው ውጤት ምንም መሆን ጋር አያይዘው ያነሳሉ) በመንግሥት ሀብት መቀለድና የግብር ከፋዩን ኅብረተሰብ ገንዘብ ማባከን መሆኑን ያምናሉ፡፡ እንዲያው በአጠቃላይ ድርጅት እንዴት እንደሚመራ ሳይሆን እንደማይመራ፣ አላስፈላጊ ቃላትና ድርጊቶች አስፈላጊ የሆነ ልምድ ያለውን ሠራተኛ ፍልሰት እንደሚያስከትሉ (ይህንን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ልምድ ያላቸው ሠራተኞች በተለይም ወጣቶች ድርጅቱን እየለቀቁ ይገኛሉ)፣ ያለውንም ሠራተኛ የሥራ ሞራል እንደሚገድሉና በዚህም ድርጅቱን ምን ያህል ዋጋ እንደሚከፍል ለማወቅና ከመሰል ድርጊት ለመቆጠብ እንዲቻል፣ ሌሎች ተቋማት እየመጡ የተሞክሮ ልውውጥ ሊያደርጉ ይገባል ይላሉ፡፡
እዚህ ላይ የእውነት መልካም ተሞክሮ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ችግሩን ፈጥረዋል የተባሉት የሥራ ኃላፊ ካሉበት መጥተው ማብራሪያ እንዲሰጡ መደረጉ፣ አሁን ለተፈጠረው ውጥንቅጡ የወጣ ሁኔታ የድርሻቸውን ስህተትና ትሩፋት አምነው እንዲቀበሉ መደረጉ ጥሩ ሆኖ ሳለ፣ ተግባሩ የበለጠ ቅብልነት ያለው ሙሉ እንዲሆን የጠፋው ጥፋት መጠን ተለክቶ ተጠያቂ መሆን ያለበት አካል በሙሉ ተጠያቂ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ ያለዚያ ሰዎች እንዳፈተታቸው በሠራተኛው፣ በሕዝብና በመንግሥት ሥራዎችና ሀብት ላይ እየተጫወቱና ሕዝብን በመልካም አስተዳደር ዕጦት እያንገላቱ ‹‹አዎ አጥፍቻለሁ›› እያሉ (ሊያውም ከብዙ መወራጨት በኋላ) ምንም ሳይሆኑ የሚቀጥሉ ከሆነ፣ ራሳቸውም ሆኑ ሌሎች ከመሰል ድርጊት በተለይ ቆመንለታል የሚሉት ድርጅት መርጦ ወደ ሥልጣን ያወጣውን ሕዝብ ከመናቅና ከመስደብ ይቆጠራል፡፡ ራስን ከሕዝብ፣ ከፓርቲና ከሕግ በላይ አድርጎ ከማሰብና በተግባር ከመቀስቀስ፣ በመንግሥት ሥልጣን ውስጥ ያለ ኢመደበኛ ግንኙነትን እንደ መደበቂያ ከመውሰድ፣ እንዲሁም ድርጅቶችን ከማተራመስ ወደኋላ ስለማይሉና ይህ ደግሞ ሕዝብና መንግሥትን ያራርቃል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ለከተማው ሕዝብ አስተዳዳሪነት የከተማውን ሕዝብ ባህልና ባህሪ የሚያውቁ፣ ሕዝብን ማክበር ባህላቸው ያደረጉ፣ በመልካም ሥነ ምግባር የታነፁ አመራሮችን እንጂ፣ እንዲህ ዓይነት መሪዎችን መመደብ በሕዝብ፣ በሠራተኛው መብትና ክብር ረገጣ ላይ ድርሻ ያላቸው የሥራ ኃላፊዎችን በሕግ ወይም በሌላ ማናቸውም መንገድ ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ጉዳዩ ለተፈጸመበት ቦታ ብቻ ሳይሆን እንደ አገርም ለመንግሥት ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ (የጥልቅ ተሃድሶው ዓላማም ይኼው ነው) አለው እያሉ ያነሳሉ፡፡
ከላይ እንደተባለው መልካም አስተዳደርን ለማስፈን አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ተጠያቂነት (Accountability) ማስፈን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ አሁን ባለው አሠራር የመንግሥት ተቋማት የሳምንቱ፣ የወሩ፣….ምርጥ ፈጻሚ እያሉ ዕውቅና እንደሚሰጡ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ መጀመር ያለበት አሠራር ቢኖር የሳምንቱ፣ የወሩ፣ የድርጅቱ፣ የመሥሪያ ቤቱ….ምርጥ አጥፊ በሚል ዕውቅና በመስጠት ተጠያቂነትን መፍጠር ቢጀመር ጥሩ ይመስላል፡፡ መንግሥት አንበሳ አውቶብስ ውስጥ ለተፈጠሩ ችግሮች በተለይም ሕገ መንግሥታዊ ለሆነው የዜጎች ሰብዓዊ ክብር መጣስ ባለቤት ሊፈጥርና ትክክል ሆኖ ከተገኘም ተጠያቂ ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ ሠራተኛውም በመንግሥትና በመንግሥት ሹመኞች መካከል ያለውን አንድነትና ልዩነት ለይቶ በማወቅ ሥራውን በአግባቡ መሥራትና የድርጅቱን ህልውና ማስቀጠል፣ ድርጅቱን እየለቀቁ ያሉ ወጣት ባለሙያዎችም ሁኔታዎች እንደሚለወጡ ተረድተው ጊዜ ወስደው ማየት እንጂ፣ እውነታው ሰዎች እንደሚሉት አለመሆኑን ተረድተው (መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አንድ ሰውና አንድ ጠመንጃ እስኪቀር ድረስ…እንዳለው ሰላሳ አውቶብስና ሰላሳ ሰው እስኪቀር ድረስ ማንም ሰው መልቀቅ ይችላል ተብለናል፣ ስለዚህ የእኛ መኖር ለድርጅቱ የሚጨምረው፣ መልቀቃችን የሚያጎድለው ነገር የለም የሚል ስሜት የተሚላበት ንግግር የሚናገሩ አሉ) መጠበቅ ይገባቸዋል የሚሉ የነገሮችን አዎንታዊ ጎን ማየት የሚቀናቸው አንዳንድ ሠራተኞች አሉ፡፡
በተጨማሪም በድርጅቱ ላይ የደረሰው ድንገተኛ የእሳት አደጋ፣ የብዙ አውቶብሶች በብልሽት ምክንያት ከአገልግሎት ውጪ መሆን፣ እንዲሁም በሌሎች ምክንያት የተፈጠረው ችግር ተሻግሮ የድርጅቱን ህልውናና የሠራተኛውን የሥራ ዋስትና ማስቀጠል የሚቻለው ሠራተኛው ትናንት የተፈጠሩ ስህተቶችና ጥፋቶችን መንግሥት እልባት እንደሚያበጅላቸው ማመን ይገባል፡፡ ያሉትን ችግሮች ወደ ጎን አድርጎ ከቁዘማና ከኩርፊያ ወጥቶ ሥራውን መሥራት፣ መንግሥትም ሕዝብን እንዲያስተዳድሩ የሚመድባቸው ሹመኞች ሕዝባዊነት የተላበሱ ናቸው ወይስ ሕዝበኝነት የተጠናወታቸው የሚለውን አይቶ የማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድና በመንግሥትና በሕዝብ መሀል የሚፈጥሩትን መቃቃር ለማስወገድ ኃላፊነቱን ራሳቸው መውሰድና ተጠያቂነት እንዲኖርባቸው ማድረግ አለበት፡፡ በዋናነት ጠቀሜታው ለመንግሥት መሆኑን ተረድቶ መሥራት ይገባዋል፡፡ እስከዚያው ግን እንደኔ ደንበኛ የነበራችሁና ልክ እንደ ዱሩ አንበሶች የከተማውም አንበሶች መመናመን አስጨንቋችሁ አንበሶቹ የት አሉ? የሚል ጥያቄ ላነሳችሁ መልሱ አንበሶቹ በአሠሪና በሠራተኞቻቸው ተግባብቶ መሥራት ያለመቻል ምክንያት በገጠማቸው በሙሉ አቅም መሥራት ያለመቻልና አድርባይነት ችግር ተተብትበው፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ በአዲስ አበባ አስፋልቶች ላይ እያገሱ ከመንጎማለል ይልቅ በዋሉበት ቅጥር ግቢ ቆመው ለማደር ተገደው የኋልዮሽ ጉዞዋቸውን አጠናክረው ተያይዘውታል ነው መልሱ፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡
ከአዘጋጁ፡ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
