Quantcast
Channel: ዓለማየሁ ጉጀ
Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

​ታሪካዊና ምሁራዊ ማረጋገጫ ያጣው መጽሐፍ

$
0
0

ግምገማ፣ በኘሮፌሰር ጳውሎስ ሚልክያስ አመያ

ይህ የአማራና የኦሮሞን የዘር ምንጭ በተመለከተ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ የጻፉትን ‹‹የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ›› መጽሐፍ በአጭሩ የሚዳስስ ቅኝት ነው፡፡ ደራሲው አማራና ኦሮሞ የአንድ ወል የዘር ምንጭ  አላቸው ከማለታቸው ጋር ልዩነት ሊኖረን አይችልም፡፡ በዚያም ምክንያት እኛ ኢትዮጵያውያን በባዕዳን የተዛባውን ታሪካችንን መልሰን መረከብና እጅ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ እኔም የኦሮሞ የዘር ሐረግ ያለኝ ኢትዮጵያዊ ምሁር እንደመሆኔ መጠን ለያዙት ለዚህ አቋም የማያወላውል ድጋፍ እሰጣለሁ፡፡  

በእርግጥ ይህ አንድነት ኦሮሞዎችንና አማራዎችን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ ትግራዮችም፣ ጉራጌዎችም፣ አገዎችም፣ አፋሮችም እንዲሁም በርካታ ሌሎች ብሔረሰቦች፣ በአንድ አካባቢ በመኖራቸው፣ የወል የባህል ውርስ በመስጠታቸውና በጋብቻ በመቀላቀላቸው ሊካድ የማይችል የባሕሪይ፣ የሥነ ልቦናዊ ዘይቤ፣ የቋንቋ፣ የጋራ ዳራዎች አሏቸው፡፡ የአንዱ ከሌላው ይብለጥ ወይም ይነስ እንጂ ሁሉም የኩሽና የሴም የዘር ሥርው አላቸው፡፡ ይኼ የሚጠበቅና የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለብዙ ሺሕ ዓመታት አብረው ኖረዋል፡፡ ሁሉም አፍሪካውያን በቅኝ የመገዛት ቀንበርን ሲሸከሙ ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ፣ የሚሳሱለትን የፖለቲካ ነፃነታቸውን በወል ከወራሪዎች በመከላከል ጠብቀዋል፡፡ በዚህም ከተገኙት አንጸባራቂ የጦርነት ድሎች መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ፣ በዛፋር (518)፣ በወይና ደጋ (1536)፣ በጉንዳጉንዲ (1880)፣ በጋላባት (1882)፣ በአምባ አላጌ (1888) በዓድዋ (1888) የተቀዳጀናቸው እርታታዎች በአንድ ብሔረሰብ ብቻ የተገኙ አልነበሩም፡፡ 

በዓለም ዙሪያ ስንመለከት፣ በመዛግብትና በጽሑፋዊ ሰነድ ጥናቶች፣ በድረ ገጽ አፈላለግ ዘዴዎች፣ በቤተ ሙከራ ምርመራና እንዲሁም ሌሎች እነሱን የመሳሰሉት ምስጋና ይግባቸውና፣ ደንብና ሥርዓት በቆመለት የዘረኝነት ፍልስፍና የሚያምኑ ሁሉ፣ ራሳቸውን እንከንየለሽ አድርገው የሚቆጥሩም ነጭ አሜሪካኖች ሳይቀሩ፣ ዛሬ ዛሬ ስለ ትውልዳቸው እውነታ እየተመራመሩ ትክክለኛውንም ዘይቤ እየተረዱ መጥተዋል፡፡ የዘራቸው ግንድ ሥር በፊት ሲያስቡት እንደ ነበረው ንጹህ ኖርዲክ ሳይሆን ከላቲኖ፣ ከአሜሪካ ሕንድ፣ ከእስያ፣ ከአፍሪካዊ አሜሪካዊ ጋር የተቀያየጠ ሆኖ አግኝተውታል። ከጥቂት ወራት በፊት በሰጠሁት ቃለመጠይቅ፣ በሰፊው እንደተቸሁት ሁሉ፣ ምንም እንኳ ከ82 በላይ የተለያዩ ቋንቋዎች ቢናገሩም፣ ኢትዮጵያውያን በመላ አንድ ሕዝብ ነን በማለት አጠንክሬ መከራከሬን በጥቂቱም ቢሆን የዚያ ቅኝት ታዛቢዎች ያስታውሱት ይሆናል፡፡ በዚህም በድጋሜ ከዶ/ር ፍቅሬ ጋር  እንስማማለን፡፡

ከዚህም በላይ ኘሮሬሰር መሳይ ከበደና እኔ ከአንድ ከአሠርታት በፊት በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ዓለም አቀፋዊ የሙያ ጋዜጣ እንዲሁም በምሁራዊው የአፍሪካ ቀንድ መጽሔት በሚያሳምን መረጃ የግብፅና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናት እንደሚሉት ንግሥተ ሳባ የመናዊት ሳትሆን ኢትዮጵያዊት መሆኗን፣ ታላቁ የ16ኛው ክፍለ ዘመን ዘርዐ ያዕቆብ፣ ቸሩሊና ኡለንዶርፍ እንደሚሉት የ19ኛው ክፍለ ዘመን ኢየሱሳዊ ቄስ ሳይሆን፣ በስሙ የሚጠራውን መጽሐፍ የደረሰ እሱ ራሱ ስለሆነ፣ ለዚህም እንደ ረኔዴካርትከመሰሉ የዘመኑ ብልሃተኛ የአውሮፓ ፈላስፋዎች እኩል የክብር ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ አጠንክረን ተከራክረናል፡፡ እዚህ ላይ ነው በአንድ በኩል በእኔና በኘሮፌሰር መሳይ ከበደ፣ በሌላ በኩል በዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ መካከል ያለው ክርክር ተመሳሳይነቱ የሚያበቃው፡፡

የሚያሳዝነው በምታት ብቻ ከሚታዩና ከሚታሰቡ ነገሮች ማጣቀሻዎች ያነሳናቸውን ቁም ነገሮች፣ በምናብ ብቻ ከሚታዩ ነገሮች ጋር በማደባለቅ የኛን ዋና ነጥብ ክብደት አሳጥተው ዶ/ር ፍቅሬ ማላገጫዎች አድርገዋቸዋል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ደራሲው ጥቂቶች ሽንጉል ወገኖች እንደሚያምኑት የኢትዮጵያን ታሪክ በአዲስ መልክ አልቀረጹትም፡፡ ከእውነታው ዘለው በቅዠት ዓለም የሚዋዥቅ ውብ ተረትን ነው የሸመኑት፡፡

የዶ/ር ፍቅሬን አባባሎች እንደገና እንቃኛቸውና ስለሚያቀርቧቸው መከራከሪያዎችና መንደርደሪያዎች፣ ስለሚሰጧቸውም ተጨባጭ ማረጋገጫዎች ጉዳይ በጥሞና እንጠይቅ፤

  1. የሰው ልጅ በሙሉ ጐጃምን ቤቴ ብሎ ሊጠራው ይገባል፣ ምክንያቱም ሁሉም ሰው  የተገኘው ከዚያ ነውና ይሉናል፡፡ በሆነ ኖሮማ እሰየው፡፡ ይኼ አባባል ግን ልብወለድና ተረት ነው። ማለት ለዚህ ታሪካዊና ምሁራዊ ማረጋገጫ የለውም፡፡ የኢትዮጵያዊ ታሪክ ጸሐፊ ኘሮፌሰር ባህሩ ዘውዴና እኔ ለመጨረሻ ጊዜ በተገኘንበት መድረክ ይኼ ጉዳይ ሲነሳ ሁለታችንንም በአንድ ላይ ትንሽ አስቆናል፡፡
  2. ዶ/ር ፍቅሬ አማራዎችና ኦሮሞዎች ወላጅ አባቱ ካልታወቀ ደሽት ከተባለ ሰው ጐጃም ተወለዱ ይሉናል፡፡ ይኸም ታሪካዊና  ምሁራዊ ማረጋገጫ የሌለው አንድም ተጨባጭ ማስረጃ ያልደገፈው ከንቱ ውዳሴ ልብ ወለድና ተረት ነው፡፡
  3. የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊዎች በሙሉ፣ ኦሮሞዎች በአንድ ወቅት ከእስያ ወይም ከውጭ መጡ የሚለውን ትረካ ይቀበላሉ ይሉናል፡፡ ይኼ ከሀቅ የራቀ ፍጹም ሐሰት  ነው፡፡ እንደ ኘሮፌሰር ሞሐመድ ሀሰን ያሉ የኦሮሞ ታሪክ ጸሐፊዎች ሥራን መመርመር ይበቃል፡፡ እኔ ራሴ አፍሪካ ኢን ፎከስ፤ ኢትዮጵያ  በሚለው መጽሐፌ  ኦሮሞዎች በአፍሪካ ቀንድ ለብዙ ሺ ዓመታት የኖሩ የኩሽ ዘር ግንድ ያላቸው  ሕዝብ ናቸው በማለት ደጋግሜ አሳስቤአለሁ፡፡   
  4. ዶ/ር ፍቅሬ፣ ንግሥተ አዜብ የአዘቦ ንግሥት ነበረች ይሉናል፡፡ ዬትና ዬት? ምን አገናኛቸውና? አዘቦ፣ ራያ አጠገብ ያለ፣ ባሁኑ ጊዜ በትግራይ ውስጥ የተካለለ የኦሮሞ ንዑስ ብሔር  ነው። አዜብ በምዕራብና በደቡብ መካከል ያለ የመልክ አምድር የማዕዘን ስም ነው።  ስለዚህ፣ ይህን በተመለከተ የደራሲው ግንዛቤ እንደገና ልብ ወለድና ተረት ተረት ነው ማለት ነው።
  5. የዓለም ታሪክ ጸሐፊዎች ኢትዮጵያ የሚለው ቃል በግሪክ Αιθιοψ በላቲን Aethiops የሚለው መጠሪያ የመጣው  ሁለት ቃላት በፅርዕ ιθιω, "የተቃጠለ"  ὤψ,  "ፊት"ሲደመሩ መሆኑን አረጋግጠዋል:: ዶ/ር ፍቅሬ ግን የተቃጠለ ፊትን ቃል በቃል ትርጉም በመጥላት ይመስል ኢትዮጵያ የሚለው ስም የፈለቀው ሁለት ሺሕ ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ፣ መጀመሪያ በኦሪት ዘፍጥረት፣ ሁለተኛ በመዝሙረ ዳዊት የተጠቀሰው መልከ ጼዴቅ ልጁን ኤቴልን ወደጣና ደሴት ሲልከውና እዚያው ሲያርፍ  በእግዜር ፈቃድ “ኢቲዮጵ” አሰኘው፣ ይኸውም “ብጫ ወርቅ” ማለት ነው ብለው አርፈውታል:: እንግዲህ እንደገና ተጨባጭ ታሪካዊና ምሁራዊ ማረጋገጫ  የሌለው ልብ ወለድና ተረት ተረት ጽፈዋል ማለት ነው።  
  6. እንደ ዶ/ር ፍቅሬ አጻጻፍ መጋል የጅማና የዲማ ኦሮሞዎች አባት ነው ማለት፣ ታሪካዊና ምሁራዊ ማረጋገጫ የሌለው ልብ ወለድ ተረት ተረት ነው።
  7. እንደ ዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ ትረካ፣ ናሙር ወንዝና ኦፌር የአፋር ብሔራዊ መኖሪያ ቦታን አመልካች ነው። እንደገና ተረት ተረት።
  8. እንደ ዶ/ር ፍቅሬ አገላለጽ፥ መቅደሽ ሞቃዲሾን ያመለክታል ማለት ተጨባጭ ታሪካዊና ምሁራዊ ማረጋገጫ አልባ ተረት ተረት ነው።  
  9. በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሶ በአፈታሪክ እንደተተቸው፣ በኮከብ እየተመሩ ሕጻኑን ኢየሱስን በቤተልሔም ለማየት እጅ መንሻ ይዘው ከምሥራቅ  የመጡት ሦስቱ ሰብአ ሰገል ጠቢባን፣ ብዙዎቹ እንደሚሉት አንዱ ብቻ የኢትዮጵያ ንጉሥ ሲሆን፤ እንደ ዶ/ር ፍቅሬ አጻጻፍ ግን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ነበሩ ማለት፤ ሐሰትና ተረት ነው፡፡  
  10. እንደ ዶ/ር ፍቅሬ ትረካ፥ ከዛጔዎች በኋላ የነገሠው የመጀመሪያው ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት ንጉሥ አፄ ይኩኖ አምላክ አዛዥ ጫላ ከተባለ የኦሮሞ ቩም ተወለደ። ይኽም እንደ ሌሎቹ አባባሎቻቸው ታሪካዊና ምሁራዊ ማረጋገጫ የሌለው ልብ ወለድ ተረት  ነው፡፡  
  11. ዶ/ር ፍቅሬ ከዚህ ከተዛባ ፈጠራቸው በፈለቀው  አስተሳሰብ ተመርተው አፄ ይኩኖ አምላክን ኦሮሞ አርገው  አርፈዋል፡፡ ይህን የሚያሰኝ ግን  ተጨባጭ ታሪካዊና ምሁራዊ ማረጋገጫ የለም፡፡ ነገሩ በደፈናው ተረት ተረት የላም በረት እንዲሉ የዘበት ጨዋታ ነው፡፡  
  12. ዶ/ር ፍቅሬ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ፊደል የተበጀው ዘግዱር በተባለ ሰው ነው ይሉናል፤ ግን ይኸ ተጨባጭ ታሪካዊና  ምሁራዊ ማረጋገጫ ያልተሰጠበት አባባል ነው፡፡

ልብ እንበል፣ እዚህ እኔ የምተቸው ኢትዮጵያውያን በቋንቋ ይለያዩ እንጂ አንድ ሕዝብ ናቸው ስለሚለው የዶ/ር ፍቅሬ መንደርደሪያ አይደለም፡፡ አባባሉ የሚያከራክር አይደለም፡፡ እኔ የማነሳው የማስረጃን ጉዳይና ደራሲው አባባሎቻቸውን ለመደገፍ ስለሚያቀርቧቸው መከራከሪያዎች፣ እንዲሁም የታሪክን አጻጻፍ ሥርዓትና ደንብ ወይም መመሪያን በተመለከተ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ከእሳቸው ጋር ያለኝ ችግር፣ ሐተታ ሲሰጥ፣ በምርምር ላይ መመሥረት ያለባቸው ማረጋገጫዎችን የሚያንጸባርቅ ዘይቤ ባለመጠቀማቸው ነው፡፡

ለምሳሌ አንድ ነጥብ  ላንሳ። ዶ/ር ፍቅሬ በመጽሐፋቸው ሽፋን ገጽታ ላይ በጣም የሚያጓጓ፣  ዋና የአርኪዎሎጂ ግኝት አስመስለው መሪራስ በተባለ ሰው በፈጠራ የተበጀ፣ ተሰምቶ የማይታወቅ የሱባ ፊደላት በማለት ተጠቅመውበታል፡፡ ለምን የሥነ ጥበብ ተመራማሪዎች በጥንቃቄ ይፈትሹት ዘንድ ዶ/ር ፍቅሬ ወይም ተባባሪዎቻቸው ይህን ግኝት አሁን የአውስትራላፕቴኩስኣፋሬንሲሷ - ሉሲ (ማለት የድንቅነሽ) አጽም ለተዘረጋበት ለብሔራዊ ቤተመዘክር አያበረክቱትም? በተጨማሪም ምሁራዊ እይታን ላለማዛባት ዩኔስኮ ይህን ታላቅ ግኝት በተመለከተ ለምን ዝም እንዳለ፥ ለምንስ በታዋቂ የቅርስ መዝገቡ ውስጥ እንዳላሰፈረው ያስረዱን ዘንድ መጠየቅ ተገቢ ነው።  

በአሁኑ ጊዜ፥ የዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ምንም ግንዛቤ በሌላቸው  ተላላ ግለሰቦች፣ እንዲሁም አሁን ያለውን ሥርዓት በሚቃወሙት ሰዎች ዘንድ እንደ ተወዳጅ የቡሔ ዳቦ እየተዘከረ፣ እየተገዛና በገፍ እየተናኘ ነው። ምንም እንኳ ስለ ትረካው እውነተኛነት ጥርጣሬ ቢኖራቸውም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሚያሳዝን ሁኔታ ጉዳዩን ችላ ብለውታል። ስለ አገራቸው ታሪክ የጠለቀ ግንዛቤ የሌላቸው ዘመናዊ ወጣቶች ግን መጽሐፉን ባያነቡትና፣  በምርምር ሥራቸውም ጠቅሰው ባይጠቀሙበት ምንኛ በበጀ፡፡

በፕሮፌሰር ፍቅሬ በተከተበው በዚህ መጽሐፍ የተዘረዘሩት ነገሮች ሙሉ በሙሉ ልብወለድና ሙሉ በሙሉ ተረቶች ናቸው፡፡ ይኸን ታሪክ ነው ብሎ መጻፍ  የጫት ሱሰኞች ከመቃማቸው ፋታ ሲወስዱ፣ ዱካካቸው የሚሰጣቸውን እውነት መሳይ  ቅዠት ይዘው እንደሚቀባጥሩት እንቶ ፈንቶ ነው፡፡ እንዲያውም በዚህ ባለንበት ተጨባጭ ዓለም ሳይሆን በሌላ የሕልም ዓለም መኖር ማለት ነው። ከጀርባ ሆኖ ከሚያናግር ጋንጩር የተሰጠውን ትዕዛዝ መቀበልና አጎብድዶ መመዝገብ ይመስላል፡፡

ወጣም ወረደም ይህ መጽሐፍ፣ ማንም አርታኢ የፈለገውን በሚጽፍበትና እርማት ሊያደርግ በሚችልበት በዊኪፒዲያ መድረክ ሊኖረው ይችላል፡፡ ለምን ቢባል አብዛኛውን ጊዜ ዊኪፒዲያ ባንድ በኩል ያልተረጋገጠ ዝባዝንኬን የማስገባትና በሌላ በኩል ያልተረጋገጠ ዝባንኬን የማስወጣት ግብር ስላለው ነው፡፡ በአገር ውስጥም፣ በውጪም ላሉ ወገኖች ያለኝ የወዳጅነት ማስጠንቀቂያ፣ በዊኪፒም ሆነ በዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱ ታማኝ የታሪክ መግለጫዎች አሉ ብላችሁ የምታምኑ ከሆነ፣ እንግዲያውስ ሳትሰሙት አትቀሩም፥ በሀበሻ  የተረት ወግ መሠረት የኢትዮጵያ መኳንንት፣ ልዑላንና ነገሥታት ሳይቀሩ በሕይወታቸው ዘመን በጠንቋይ ድግምት በማሳብ ያናግሩት ነበር እየተባለ ይወራለት በነበረው፥  በቢሾፍቱ ሐይቅ ይኖራል ተብሎ በሚታመነው፣ ደም በሚጠጣው፣ ቆበር በሚያስደፍቀው፣ ሕልሞችን፣ መታለሎችን፣ እንቆቅልሽዎችን ሁሉ በመተት ለመፍታት ይችላል  ተብሎ ባንዳንዶች ሰዎች በሚታመንበት በአየር ጋኔን፣ በቆሪጥ ብታምኑ ይቀላችኋል።  

(ይቀጥላል)

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በካናዳ ሞንትሪያል በሚገኘው ኮንኮርዲያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው pmilkias@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

Trending Articles