በሒሩት ደበበ
በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ አንድ ልብ የሚነካ ግጥምን ማግኘቴ ብቻ ሳይሆን ለተነሳሁበት ርዕሰ ጉዳይ ስለሚመጥን የጽሑፌ መግቢያ ለማድረግ ወደድኩ፡፡ ርዕሱ ‹‹እንባዬ›› የሚል ሲሆን ስንታየሁ ዓለምአየሁ የተባለ ባለቤት ተሰጥቷታል፡፡
ጥቂት ቢበራ ጥቁረቴ፣
አደብ ቢገዛ ስሜቴ፣
ቢፍቅ ቢታጠብ በደሌ፣
ሟሙቶ ቢጠፋ እንዳሞሌ፣
ቢመለስ መልክ ከሥዕሌ፣
ቢያርቅ ‹‹አካል›› ከ‹‹አካሌ››፣
የብረት በሩን ገርስሰህ፣
ቁንን ግድቡን ደርምሰህ፣
የዓይኔን ሽፋሽፍት ገላልጠህ፣
ፍሰስ እንባዬ በፊቴ ላይ፣
ደጉን ከመጥፎው ለይቼ እንዳይ፤
ይላል፡፡ ይኼ ሐዘን እንጉርጉሮ ስንኝ ሐዘንን፣ ሞትና ለቅሶን ተንተርሶ የተሰደረ ነው፡፡ በአገር ደረጃ ብዙዎች ማቅ እያለበሱ ከሚገኙ የሞት ቀሳፊዎች መካከል አንዱ ደግሞ የትራፊክ አደጋ ነው ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡
እንደ አገር ከ100 ሚሊዮን የማያንስ ሕዝብ ይዘን፣ በቆዳ ስፋትም ቢሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ምድር ላይ ተቀምጠን ያሉን የተሽከርካሪዎች ብዛት ከ700 ሺሕ የበለጡ አይደሉም፡፡ የባቡር ትራንስፖርቱም ቢሆን ገና እየጀማመረ ያለ እንጂ ያን ያህል የሚያጨናንቅ አይደለም፡፡
ያም ሆኖ አገራችን ‹‹ውስን ተሽከርካሪ ያላት ግን በጣም ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ የሚከሰትባት›› የሚል ‹‹ማዕረግ›› ካገኘች ውላ አድራለች፡፡ በትራንስፖርት ዘርፍ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ማለትም የትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ የትራፊክ ፖሊስ፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ የመንገድ ሥራ መሥሪያ ቤቶች፣ የትራንስፖርት ማኅበራትና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተለያዩ ምክክሮችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ሕግ አውጭውና ተርጓሚውን ጨምሮ የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎችና አሠራሮችን ለማስተካከል የሚረዱ አካላትም ደጋግመው ሲመክሩ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በፓርላማ ካደረጉት የአደጋው ሥጋት ላይ ያተኮረ ንግግር ጀምሮ ሚኒስትሮችና አፈ ጉባዔዎች የሐዘን መግለጫ እስከማውጣት የደረሱበት አስከፊ ክስተትም ሆኗል - የትራፊክ አደጋ፡፡ ለዚህም ነው ለወራት የወሰደ የትራፊክ አደጋ የንቅናቄና የግንዛቤ ፎረም ተደርጎ የመንግሥት አካላትና ሕዝቡ፣ ልጅ አዋቂው ጉዳዩን አጀንዳ እንዲያደርገው ሰፊ ሥራ ሲከናወን የቆየው፡፡
አሁንም ግን የትራፊክ አደጋ በየዕለቱ የብዙዎችን እንባ እያፈሰሰ፣ የንፁኃንንም ሕይወት እየቀጠፈ ይገኛል፡፡ የአካል መጉደሉና የንብረት መውደሙም ቢሆን በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በቅርቡ በትራንስፖርት ሚኒስቴር አዳራሽ በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ እንደተጠቆመው፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ 16,213 ዜጎች ሕይወታቸው በትራፊክ አደጋ ተቀጥፏል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በ2008 ዓ.ም. ብቻ 4,223 ሰዎች ሞተዋል፡፡ በተመሳሳይ የአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥም 50 ሺሕ ዜጎች ለከፍተኛ የአካል መጉደል አደጋ ተጋልጠዋል፡፡
እንግዲህ የቬትናምና የአሜሪካ ወይም የኢራቅና የኢራን እንዲሁም የሶማሊያና የኢትዮጵያ ጦርነት ይመስል በአሥር ሺዎች እየሞቱ፣ በአሥር ሺዎች የሚቆስሉበት የአገራችን የትራፊክ አደጋ መዘዝ የሚያመጣ ሆኗል፡፡ በዚህ ሰፊ ጉዳት በየዓመቱ ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ የአገርና የሕዝብን ንብረት ከመውደሙ ባሻገር፣ በሕይወት ላሉ የተጎጂ ወገኖች ማኅበራዊ ቀውስን የሚደነቅር መሆኑም ያልታየው የመስኩ ሌላው ጉዳት ነው፡፡ ቀደም ሲል በጠቀስነው የምክክር መድረክም ሆነ በሌሎች ዓውዶች የተነሱ የዘርፉ የጉዳት መንስዔዎችና መፍትሔዎች ለውይይት መነሻ በሚሆን ደረጃ ለማስቀመጥ ተሞክሯል፡፡
የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ የችግሩ ዋና አስኳል
በአገራችን ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት ከነበረው የተሻለ የመንገድ አውታር ተዘርግቷል፡፡ በጥራትም በብዛትም ካለፉት ጊዜያት ዘመናዊና አዳዲስ ተሽከርካሪዎች የኢትዮጵያን ጎዳናዎች ሞልተዋል፡፡ በዚያው ልክ በጎዳና ላይ ደም መፍሰሱ በርትቷል፡፡ ለዚህ አስከፊ የትራፊክ አደጋ መባባስ ታዲያ 68 በመቶው የአሽከርካሪው ብቃትና ችሎታ ማነስ መንስዔ እንደሆነ ጥናቶች እያስገነዘቡ ነው፡፡
ለአሽከርካሪዎች ብቃት፣ ሥነ ምግባር መጓደልና ልምድ ማነስ በር እየከፈተ ያለው ደግሞ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ አሰጣጡ እንደሆነ በመንግሥት አካላት ጭምር የሚነገርና በጥናትም የተረጋገጠ ሆኗል፡፡ በአንድ በኩል በአሠልጣኞች፣ በመንጃ ፈቃድ አውጪዎችና በብቃት ሰጪዎች መካከል የሚፈጸም የሙስናና የአቋራጭ መንገድ አለ፡፡ የከፋ የሚባለውም በፎርጅድ መንጃ ፈቃድ ከመሬት ተነስቶ (አንዳንዱ የፈረስ ጋሪ እንኳን ሳያውቅ) መሪ እንዲጨብጥ ብሎም ወደ ሞት ይገሰግሳል፡፡
ከሁሉ በላይ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ አሰጣጡ (ይኼ ጉዳይ በትራንስፖርት ሚኒስቴር ግትርነት እስከ አሁን የቀጠለ ነው) የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበና ደካማ ነው፡፡ በተለይ በልምድ በችሎታና በብቃት አሽከርካሪዎችን ሳይመዝን፣ ለከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ እየተለማመዱ እንዲሄዱ ሳያደርግ፣ በ‹‹ገንዘብ›› ብቻ የፈለጉትን ደረጃ ማውጣታቸው የሞት መጠኑን ጨምሯል፡፡ በተለይ በከፍተኛ ልምድና ብቃት የሚሽከረከሩ ከባድ ካሚዮኖች ከ20ዎቹ ዓመታት ባልዘለሉ ለጋ ወጣቶች የመዛወራቸው ለችግሩ መባባስ ዋነኛ መንስዔ ነው፡፡ ለዜጎች ሕይወት መጥፋትና አካል ጉዳት ምክንያት ነው፡፡ ለከፍተኛ የአገር ሀብት ክስረትም እያጋለጠ ይገኛል፡፡
‹‹የአገራችን አሽከርካሪዎች መሪ ጨብጠው ወዲያና ወዲህ መመላለሳቸውን እንደ ግብ አስቀምጠው የደኅንነት ቀበቶ የማያስሩ ናቸው፤›› የሚለው አደጋው ላይ ያተኮረ ጥናት የቴክኒክ ብቃት እጥረትን በመሠረታዊነት ያነሳል፡፡ ብዙዎቹ ወጣት አሽከርካሪዎች የዘይትና የቅባት ቦታዎችን ለይተው የማይቆጣጠሩ፣ የፍሬንና የመሪ አስፈላጊነትን አጢነው የማይገነዘቡ፣ የአየር ንብረትና የጉዞ ቦታዎችን የማያመዛዝኑ፣ የጨለማ መንገድንና በተለይም በድካም ስሜት ማሽከርከርን የማይረዱ ናቸው ሲል ይዘረዝራል፡፡ ከዚህ በከፋ ደረጃም ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ ምግባር አለመላበሳቸው (ጫት መቃም፣ መጠጣት፣ ሞገደኝነት) አገራዊ ቀውሱን እንደ ደመራ እንጨት እያንቀለቀለው ይገኛል፡፡
በድምሩ በአሽከርካሪ ብቃት አሰጣጥና በአሽከርካሪዎች ብቃት ላይ ያተኮረው የግለሰቦቹ፣ የተቋማቱና የመንግሥት ችግር መሠረታዊ ነው፡፡ በአፋጣኝ ጠንካራ መፍትሔ ካልተሰጠውም ሞቱና እልቂቱን የሚያቆም መግቻ ማግኘት ያስቸግራል፡፡
ነፍስ ለምኔ የሚያስብለው አደጋ
አውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ ከአምስት እስከ አሥር ዓመታት ያሽከረከሩትን ‹‹ሰልቫጅ›› መኪኖች ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው በአገራችን ገበያዎች እንደ ልብ ገዝተን እንነዳለን፡፡ ከፋብሪካ እንደተመረቱ ወደ እኛ አገር የሚገቡ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች (ኦባማ፣ ሲኖትራክና ልዩ ልዩ ዘመናዊ አውቶሞቢሎች) ግን ሕይወት እንደታቀፉ እየወደሙ ነው፡፡ በተለይ ‹‹ፍሬን አልባው›› የሚባለው ሲኖትራክ (ቀይ ሽብር) ከፍተኛ የጥፋት ሆዱን ከፍቶ አሽከርካሪዎችን፣ ተሳፋሪንና እግረኛን እየጎሰጎሰ ይገኛል፡፡ ችግሩ በዋናነት የአሽከርካሪዎች መሆኑ እንዳለ ማለት ነው፡፡
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ለእዚህ ችግር መባባስ አንዱ መንስዔ ተሽከርካሪዎቹን ከአገራችን መልክዓ ምድርና የመንገድ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ያለመጠቀም ተግዳሮት ነው፡፡ ሲኖትራክን በከፍተኛ ጭነት (ከፎርታታውም በላይ)፣ በዳለጠ ጎማ፣ በቁልቁለት ላይ በቀላል ማርሽ መሞከር መቅሰፍትን ያስከትላል፡፡ እንደ ዶልፊን የመሳሰሉ ባለስድስት ፒስተን ከፍተኛ አቅም ያላቸውን መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻዎች፣ ለአገሪቱ ከሚመጥነው ፍጥነት በላይ መጋለብ ሞትን ያፋጥናል፡፡ በተጨባጭ እየሆነ ያለው ግን ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት የአገራችን የትራፊክ አደጋ በአብዛኛው የሚከሰተው በተሽከርካሪዎች መገልበጥ ነው፡፡፡ ቀጥሎም በመጋጨት፣ በመግጨትና ከግዑዝ ነገር ጋር በመላተም (የእሳት ቃጠሎንም ይጨምራል) ይገኙበታል፡፡ በእነዚህ አስከፊና ዘግናኝ አደጋዎች ውስጥ ዋነኛ ሰለባ ለሚሆኑ ዜጎች ሕይወት ሕልፈት ከላይ የተጠቀሱትን ተሽከርካሪዎች ጨምሮ ብዙዎቹ ዘመናዊ መኪናዎች የአደጋ ሰበብ ሆነዋል፡፡ ለአገራችን መልክዓ ምድር የተፈጠሩ የሚመስሉት አሮጌ ተሽከርካሪዎች (ኤንትሬ፣ ላንድሮቨር፣ ቶዮታ፣ . . . ) አደጋ አያደርሱም ባይባሉም በርክቶ የሚስተዋል አይደለም፡፡
ከዚህ አንፃር ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን ከአመራረታቸው ጀምሮ ድክመትና ጥንካሬዎችን ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ ከመልክዓ ምድርና የመንገድ ሁኔታ ጋር አስተሳስሮ መጠቀም ይገባል፡፡
ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ለችግሩ መባባስ
ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦት የአገር ኢኮኖሚን በመጉዳት ኢፍትሐዊነትን የሚያነግሱ ብቻ አይደሉም፡፡ ይልቁንም በሰው ሕይወትና በማኅበራዊ ኑሮ ላይም የሚያደርሱት ጉዳት የከፋ እንደሆነ አንዱ ማሳያው የትራፊክ አደጋ ነው፡፡ በተለያዩ ጥናታዊ መረጃዎች እንደተረጋገጠው ደግሞ ሙስናም ይባል፣ የመልካም አስተዳደር ብልሽት ሥር ከሰደደባቸው ሴክተሮች ቀዳሚው ይኼው የትራንስፖርት ዘርፍ ነው፡፡
አንዱ ብልሽት ከአሽከርካሪውና ከተቆጣጣሪው (የትራፊክ ፖሊስ፣ የቦሎና ብቃት ሰጪ፣ የብቃት ማረጋገጫ ሰጪ፣ . . .) ጋር የሚገናኘው መሞዳሞድ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ግምገማ ቢካሄድ፣ ሕግ ቢወጣና ትራፊክ ቢበራከት ያልተሻሻለው በገንዘብ ‹‹ብቃትን›› የመግዛቱ ችግር ነው፡፡ ስህተትን በመማሪያነት ከመቅጣት ይልቅ መነገጃ ያደረጉ ጥገኞችም በዙ እንጂ አልቀነሱም፡፡ ለምን ቢባል ሰጪም፣ ተቀባይም ሕገወጥነትን የዘወትር ልብሳቸው አድርገዋል፡፡ መንግሥትም አደጋውን ለማስተካከል እየወሰደው ያለው ዕርምጃ አነስተኛ መሆኑ ሳይዘነጋ፡፡
በትራንስፖርት መስኩ ላይ ያለው ሌላው ብልሽት ከባንክ ብድርና ከኢንሹራንስ ዋስትና ጋርም ይገናኛል፡፡ ዛሬ ዛሬ በባንኮች ‹‹ጉዳይ ገዳይ›› የውስጥ ደላሎችን ያደራጁ፣ ከሥራ አመራር ቦርድ አንስቶ እስከ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች የተሳሰሩ ብድር አቀባባዮች ተበራክተዋል፡፡ እነዚህ ጥገኞች ‹‹በአጭር ለመበልፀግ›› የቋመጡ ነጋዴም ይባሉ አርሶ አደሮች ጋር በመነጋገር በሕግ ያልተፈቀደን የተሽከርካሪ ብድር እየፈነቀሉ ይሰጣሉ፡፡ ኮሚሽናቸውን እንደፈለጉ እየቆረጡም ባለንብረትና አሽከርካሪዎችን በብድር ጭንቀት ውስጥ ይከታሉ፡፡ ብሎም ለሞትና ለመቅሰፍት የሚያጋልጥ ውጥረት ውስጥም ይከታሉ፡፡
በኢንሹራንስ በኩልም የሚታዩ አንዳንድ ክፍተቶች አሉ፡፡ በእርግጥ የአገራችን ኢንሹራንሶች እየከሰሩም ቢሆን ለአካል፣ ለሕይወትና ለንብረት ጉዳት የመድን ዋስትና ሽፋን እንዲሰጥ ማድረጋቸው የሚበረታታ ነው፡፡ በመንግሥት ድጎማም ጭምር ማኅበራዊ ቀውስ እንዳይባባስ የመድን ካሳ ካለ ውስብስብ ውጣ ውረድ እንዲፈጸም መደረግ አለበት፡፡ ይሁንና አሁንም በመስኩ መደራደር፣ ሙስናና አሻጥር አሉ፡፡ በተለይ በመሐንዲሶች፣ በግምት አፅዳቂዎች፣ በኃላፊዎችና በመርማሪዎች፣ . . . የሚፈጸም ቅብብሎሽ አለ፡፡ ባለሀብቶችንና ኢንሹራንሶችን የሚጎዱ ብሎም አገር የሚያቆረቁዙ ተግባሮችም በስፋት ይፈጸማሉ፡፡
በአጠቃላይ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦቱ ከመንገድና ከትራንስፖርት ቢሮዎች እስከ ጎዳናዎችና በመንደር ውስጥ እስካሉ የተሽከርካሪ ማደሪያዎች ድረስ ተባብሷል፡፡ ብርቱ የሕዝብ ትግልና የመንግሥት ቁርጠንኝነትንም ይፈልጋል፡፡
ማጠቃለያ
አሁን ባለው መረጃ በአገር ደረጃ በቀን ከ12 እስከ 15 ዜጎችን ሕይወት የሚቀጥፈው የትራፊክ አደጋ የብዙዎችን ሕይወት ያሳጣ መቅሰፈት ነው፡፡ ያውም አምራቹን ኃይልና ለአገርም የሚበጀውን ተንቀሳቃሽ ትውልድ፡፡ ስለዚህ መፍትሔው ቢያንስ አደጋውን ለመቀነስ ነገ ዛሬ ሳይባል መነሳት ያስፈልጋል፡፡ በየዕለቱ በመገናኛ ብዙኃን ከምንሰማው መርዶ ባሻገር የሁሉንም ቤት እያንኳኳ ያለውን የሞት ጥሪም ለመግታት ከፀሎት ጀምሮ፣ እስከ መፍትሔው የተግባር ዕርምጃ ከሁሉም የሚጠበቅ ነው፡፡
በየተራ እንባ ማፍሰስ ብቻ የሕዝብና የአገርን ለቅሶ አያስቆምም፡፡ መንግሥት አገር እንደሚመራ አካል ቆሞ ከመመልከት በመውጣት የብቃት ማረጋገጫ አሰጣጡን ይፈትሽ፡፡ ከላይ የተጠቃቀሱ ብልሽቶችንም ያስተካክል፡፡ መንገድ ከመገንባትም ባለፈ ስለመንገድ ሥነ ሥርዓት ከሚሠራውም በላይ ያስገንዝብ፡፡ አሽከርካሪዎች፣ እግረኞች፣ ሕዝቡም በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት የየድርሻቻውን ይወጡ፡፡ በነካ ነካ የለውጥ ፍላጎት ይኼን አደጋ ማስቀረት የሚቻል አይሆንም፡፡
የትራፊክ አደጋ ከሕዝቡ ጉዳትም አልፎ የአገሪቱን ገጽታ በማጠልሸት ‹‹በተሽከርካሪ ወይም በጎዳና የማይኬድበት አገር›› ሊያስብል የሚችል ነው፡፡ ምንም እንኳን በአፍሪካ (እነ ግብፅ፣ አልጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያ፣ ወዘተ) የትራፊክ አደጋ የሚከሰትባቸው አገሮች ቢሆኑም፣ ከእኛ በሁለትና በሦስት እጥፍ የሚበልጡ ተሽከርካሪዎች እያሉዋቸው የአደጋው መጠን ግን ከእኛ ያነሰ ነው፡፡ ከዚህ ውርደት ለመውጣት ተግቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
