በመላኩ ገድፍ
ዓለም አንድ መንደር በሆነችበት በ21ኛ ክፍለ ዘመን ማንኛውም ሕጋዊ የሆነ የአንድ አገር ዜጋ በየትኛውም የዓለም ክፍል ተዘዋውሮ የመሥራትና የመኖር መብት እንዳለው ይታወቃል፡፡ ይህ ዓለም አቀፋዊ የሆነው የፍልሰት ሒደትም ዋነኛ ምክንያቱ የተሻለ ኑሮና ሕይወት ከመሻት የሚመጣ የሰው ልጆች ያልተገደበ ፍላጎት የሚያመነጨው ክስተት ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ወቅት ፍልሰት ከፍተኛ በሆነ ደረጃ እየጨመረ ሲሆን፣ ሕገወጥ ስደትም የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ሕገወጥ ስደት ዜጎች ምንም ዓይነት ሕጋዊ የመኖሪያ ሰነድ ሳይኖራቸው ወደ አንድ ሉዓላዊ አገር በሕገወጥ መንገድ ድንበር ጥሰው በመግባት የሚኖሩበት ሒደት ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት በተለያየ ጊዜ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ የሕገወጥ ስደተኞች ቁጥር በሚገርም ፍጥነት እያሻቀበ ይገኛል፡፡
ድርጅቱ ለሕገወጥ ስደት ዋነኛ ምክንያቶች የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ፍትሐዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል፣ የሰላም ዕጦት፣ በቂ የሆነ የሥራ ዕድል አለመኖርና የሕገወጥ ደላሎች መስፋፋት መሆናቸውን ያብራራል፡፡ በመሆኑም ይህንን የዓለማችን አንገብጋቢ የሆነውንና የብዙ ሺሕዎችን ሕይወት በመቅጠፍ ላይ የሚገኘውን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ለመግታት፣ በቀዳሚነት አገሮች የራሳቸው የሆነ የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት አዋጅ ሊኖራቸው ግድ ይላል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያም ቀደም ሲል በሥራ ላይ የነበረውን የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት አዋጅ ቁጥር 632/2001 ሰፊ ክፍተት አለበት በማለት ወደ ዓረብ አገሮች ለሥራ የሚጓዙ ዜጎች ላይ የስድስት ወራት የጉዞ ዕገዳ ከተጣለ ዓመታት ያለፈ ሲሆን፣ አዲሱ አዋጅ ደግሞ የካቲት 11 ቀን 2008 ዓ.ም. በተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል፡፡ ይሁን እንጂ እስከ ዛሬ ድረስ ዕገዳው ተነስቶ ሕጋዊ የሆነ የሥራ ሥምሪት ማድረግ አልተቻለም፡፡ መንግሥት በፊት የነበረውን የተካው አዲሱ የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል፣ የዜጎችን መብትና ፍላጎት የሚያስከብር፣ እንዲሁም የባለ ድርሻ አካላትን ኃላፊነት በግልጽ የሚደነግግ ነው በማለት በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በመለፈፍ ነው፡፡ እስካሁን ግን ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የመንግሥት አካል (የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር) አዋጁ ወደ ሥራ የሚገባበትን ቁርጥ ያለ ጊዜ መወሰን አልቻለም፡፡
በዚህ ምክንያትም ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ወደ ተለያዩ ዓረብ አገሮች እየሄዱ ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸው በየቀኑ በሚዲያዎች የምንሰማውና የምናየው ጉዳይ ሆኗል፡፡ ዕገዳው ከተጣለ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ መንገዶች ወደ ዓረብ አገሮች እየተመሙ ይገኛሉ፡፡ የመጀመሪያውን ድርሻ የሚይዘው ዜጎች በሕገወጥ ደላሎች አጉል ተስፋ ተታለውና ብዙ ገንዘብ በመክፈል ባህር አቋርጠው የሚሄዱበት ሲሆን፣ በዚህ መንገድ የሚጓዙ ስደተኞች በብዛት ካሰቡት አገር ሳይደርሱ ለውኃ ጥም፣ ለረሃብ፣ ለአስገድዶ መድፈርና በተለያዩ ችግሮች የአውሬ ቀለብ ሆነው ይቀራሉ፡፡ ይህን ሁሉ ስቃይ አልፈው በሕገወጥ መንገድ ወደ ዓረብ አገሮች የሚገቡ ዜጎችም የተረጋጋ ሕይወት ሳይኖሩ፣ በአሠሪዎቻቸው መብታቸው እየተጣሰ የሰቆቃ ሕይወት ይኖራሉ፡፡
በሌላ በኩል ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ወደ ዓረብ አገሮች የሚያደርጉት ጉዞ ሕጋዊ ሽፋን ተሰጥቶት በቦሌ በኩል የሚካሄድ ሲሆን፣ ሒደቱም ሕገወጥ ደላላው ከዓረብ አገሮች ካሉት ወኪሎች ጋር በሚያደርገው ስምምነት ነው፡፡ ደላላው የተለያዩ ሴት ወጣቶችን የተዛባ መረጃ በመንገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ሕይወታቸውን መቀየር እንደሚችሉ በማሳመን ተጓዦችን ይመለምላል፡፡ በመቀጠልም ለጉዞ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ፖስፖርትን ጨምሮ እንዲያዘጋጁ ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል ዓረብ አገር ያለው ደላላ በበኩሉ የቪዛውን ጣጣ ጨርሶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ልጆቹ ከላኪና ከተቀባይ አገሮች ኢምባሲዎች ዕውቅና ውጪ ወደ ሥራ ይሰማራሉ፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ፣ በዚህ መንገድ ወደ ዓረብ አገሮች የሚሄዱ ሠራተኞች ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ይዳረጋሉ፡፡ የመጀመርያው ችግር ሠራተኞች ይዘውት የሚሄዱት የጉዞ ሰነድ ትክክለኛ አለመሆኑ ነው፡፡
በተለይ ከሕክምና ውጤቶች ጋር በተያያዘ ብዙዎች ለደላላና ለተለያዩ ወጪዎች ያወጡትን ገንዘብ እንኳን ያስመልሱ፣ በኪሳራ ከብዙ እንግልት በኋላ ወዲያውኑ ይጠረዛሉ፡፡ ይህ የሚሆነውም የሕክምና ውጤቱን ሪፖርት የሚሠራው ጤና ጣቢያ ሰዎች ጥቅምን የሚያሳድዱ እንጂ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን የማይወጡ በመሆናቸው ነው፡፡ በተለይ በመርካቶና በአውቶቡስ ተራ አካባቢ የሚገኙ አንዳንድ ክሊኒኮች ከዓረብ አገሮች ኤምባሲዎች ፈቃድ አለን በማለት ምንም ዓይነት የምርመራ መሣሪያዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ ለተጓዦች የሕክምና ምርመራ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ብቁ ባልሆኑ ባለሙያዎችና ባልተሟሉ የላብራቶሪ መሣሪያዎች የሚደረግ የምርመራ ውጤትም በተጓዦች ላይ የሚያስከትለው ችግር በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ከሁለት ወራት በፊት ሰው ልቀበል የአገር ውስጥ በረራ ተርሚናል ውስጥ ያገኘኋቸው ከሳዑዲ ዓረቢያና ከኩዌት የተጠረዙ ወጣት ሴት እህቶቻችን የዚህ ችግር ሰለባ ነበሩ፡፡
ስልክ አስደውለን በማለት የቀረቡኝ እነዚህ ልጆች ከክልሎች እንደመጡ አለባበሳቸውንና የንግግር ዘይቤያቸውን ሰምቶ መገመት ይቻላል፡፡ ዓይኖቻቸው ብዙ ከማልቀሳቸው የተነሳ ቀልተዋል፡፡ ብርዱና የረሃብ ስሜቱ ተደማምሮ ፊታቸውን አጠውልጎታል፡፡ ‹‹ማሽላ እያረረ ይስቃል›› እንዲሉ በጉዞ ላይ ያሳለፉትን አጋጣሚ እያወሩ በጥቂቱ ፈገግ ይላሉ፡፡ በነበረን ቆይታ የተፈጠረውን ችግር እንዲያስረዱኝ ጠየቅኳቸው፡፡ ዕድሜዋ 17 መሆኑን የነገረችኝ የሳዑዲ ተመላሿ ልጅ የሄደችበትን ሁኔታና የተመለሰችበትን ምክንያት ስታስረዳኝ ድንገት ከገረጡ ዓይኖቿ የሚወጡ እንባዎች ጉንጮቿን አቋርጠው እየፈሰሱ ነበር፡፡ ሲቃ በተናነቀው ድምፅ ንግግሯን ቀጠለች፡፡ የመጣችው ከኦሮሚያ ክልል ገጠራማ አካባቢ ሲሆን፣ አባቷ በልጅነቷ ስለሞተ እናቷ እንደ አባትም እንደ እናትም ሆና ሌሎች እህትና ወንድሞቿ ጋር ተቸግራ አሳድጋታለች፡፡ ትምህርትም እንደ እኩዮቿ በተገቢ ሁኔታ ባይሆንም እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምራለች፡፡ የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ተፈትናም ወደ ዘጠነኛ ተዛውራለች፡፡ ነገር ግን የዘጠነኛ ክፍልን ለመማር በአካባቢው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ነበረባት፡፡ ይህንን ለማድረግ የአሳዳጊ እናትዋ አቅም አልፈቀደምና ትምህርቷን ለማቋረጥ ተገደደች፡፡ ጓደኞቿ በተሳካ ሁኔታ ትምህርታቸውን ሲቀጥሉ የእሷ ቤት መቀመጥ አንገበገባት፡፡ ይህ ሁኔታም ድንገት ዓረብ አገር የመሄድን ሐሳብ ወለደላት፡፡
በአካባቢዋ ብዙ ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸውን መቀጠል እየቻሉ በሕገወጥ ደላሎች ተታለው ትምህርታቸውን አቋርጠው ይሄዳሉ፡፡ እሷ ግን ምንም አማራጭ ስላልነበራት ወደ ዓረብ አገር መሄድ መወሰኗ ትክክል ነበር ብላ ታምናለች፡፡ ሰዎቹ ልጅቷ የተመለሰችበትን ምክንያት በግልጽ ባይነግሯትም ቅሉ፣ ችግሩ ግን በተሳሳተ የሜዲካል ምርመራ ውጤት ምክንያት እንደሆነ ሳትሸሽግ ነግራኛለች፡፡ እንደ ልጅቷ እምነት ችግሩ የተፈጠረው የሜዲካል ምርመራ የሚሰጠው የሕክምና ተቋም ሕጋዊ አለመሆኑንና መሥፈርቱን የሚያሟላ የላብራቶሪ መሣሪያ የሌለው ከመሆኑ ጋር እንደሚሆን ትናገራለች፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከዚህ የተላከው የሜዲካል ውጤትና እዚያ ደርሳ ስትመረመር የተገኘው ውጤት ፍፁም የተለያየ መሆኑ ነው፡፡
ከደቡብ ክልል የመጣችው ዕድሜዋ 25 ዓመት መሆኑን የነገረችኝ ፈርጣማዋ ወጣት ወደ ኩዌት ለሥራ ስትሄድ ይህ ሁለተኛ ጊዜዋ ነው፡፡ የተመለሰችበት ምክንያትም የሁለት ወር ነፍሰ ጡር ሆና በመገኘቷ ሲሆን፣ እንደ ልጅቷ ገለጻ ስህተቱ የተሠራው የሜዲካል ምርመራ ባካሄደችበት ጊዜና በረራ ባደረገችበት ጊዜ መካከል የሦስት ወር ልዩነት በመኖሩ ልትሄድ ስትል በድጋሚ ምርመራ ባለማድረጓ ምክንያት የመጣ ነው ባይ ነች፡፡ በሌላ በኩል በሕገወጥ መንገድ ባህር አቋርጣ ሳዑዲ ዓረቢያ ለሥራ የገባችዋ ወጣት በየትና እንዴት ሳዑዲ እንደገባች የምታውቀው ነገር የላትም፡፡ በጉዞ ወቅት ብዙ አስቸጋሪ ስቃዮችን ተጋፍጣ እንዳለፈኝ ትናገራለች፡፡ አብረዋት ጉዞ የጀመሩ ጓደኞቿ የት እንደደረሱ አታውቅም፡፡ ሕገወጥ ደላሎች በራሳቸው ሕገወጥ የጉዞ መረቦች እንደፈለጉ ይቀባበሏቸዋል፡፡ መሀሉ አይነገርም. . . እንዲሉ ለመናገር የሚቀፉ ብዙ ድርጊቶች በሕገወጥ ስደተኞች ላይ ሲፈጸሙ አስተውላለች፡፡
ሳዑዲ ዓረቢያ ከገባች አንድ ዓመት ቢያልፋትም ያሰበችውን ሳታሳካ በፖሊሶች ተይዛ ሁለት ወር ከታሰረች በኋላ ወደ እናት አገሯ ተመልሳለች፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ልጆች ዕድል ብሎ በሰላም ወደ አገራቸው ይመለሱ እንጂ፣ በዚህ መንገድ የሚሄዱ ብዙ ወገኖቻችን ሕገወጥ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በእስር የሚማቅቁ፣ በድብደባ አካላቸው የጎደለ፣ በአሠሪዎቻቸው አስገድዶ መደፈር የደረሰባቸው፣ ከፎቅ የሚወረወሩ፣ በአሠሪዎቻቸው የሠሩበትን ክፍያ የተከለከሉ፣ ብሎም ለአዕምሮ ሕመም የተዳረጉ ቡዙዎች መሆናቸው የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ዘወትር በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች እንደሚያሳዩት፣ ኢትዮጵያውያን ከሌሎች የሩቅ ምሥራቅ አገር ዜጎች በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ የመብት ጥሰት ይፈጸምባቸዋል፡፡ ለዚህ ሁሉ የመብት ጥሰት ዋነኛ ምክንያት አሠሪዎች ኢትዮጵያውያኑ ሠራተኞች ሕገወጥ መሆናቸውን ስለሚያውቁ፣ ሠራተኞቹን ኃላፊነት በጎደለው መንገድ እንደፈለጉ ለማሠራትም ሆነ ከዚያ ያለፉ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ዘንድ የልብ ልብ ይሰማቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዓረብ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች ስደተኞች ለሚያሰሙት የድረሱልኝ ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸው ሁኔታውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያባባሰው ይገኛል፡፡ ስደተኞች በማኅበራዊ ሚዲያ እንደሚገልጹት ከሆነ በዓረብ አገሮች የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ይጠራጠራሉ፡፡ ሕጋዊም ሆኑ ሕገወጥ ስደተኞች ከአሠሪዎቻቸው የመብት ጥሰት ሲደርስባቸው ወደ ቆንስላው አቤት ማለታቸው አይቀርም፡፡ ይሁን እንጂ ኤምባሲዎች አስቸኳይ መፍትሔ አይሰጡም፡፡ ይልቁንም በብዛት ስደተኞች የሚደርስባቸውን የመብት ጥሰት ተቋቁመው እንዲኖሩ የሚገፋፉ ናቸው፡፡
በዓረብ አገሮች ያሉ የኢትዮጵያ ቆንስላዎች የዜጎቻቸውን መብት ለማስከበር የሚያችል የተደራጀና ወጥ የሆነ አሠራር የላቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት በዓረብ አገሮች የሚሠሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን በቆንስላዎቹ ምንም ዓይነት እምነት የሌላቸው በመሆኑ፣ የሚደርስባቸውን በደል እየተቋቋሙ የነገ ህልማቸውን ለማሳካት ሕይወታቸውን በሰቆቃ የተሞላ ሆኗል፡፡ በኩዌት የኢትዮጵያ ኤምባሲ በቅርቡ በፌስቡክ ገጹ ላይ የለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምሥል እንደሚያሳየው፣ አንዲት ኢትዮጵያዊት ሠራተኛ አሠሪዎቿ ያለምንም ክፍያ ለአምስት ዓመታት እንዳሠሯት ትናገራለች፡፡ ልጅቷ እንደምትናገረው አሠሪዎቿ ከማንም ጋር እንዳትገናኝ በማገት ለአምስት ዓመታት ያለ ምንም ሰባራ ሳንቲም ሲበዘብዟት ኖረዋል፡፡ እንደዚህች እህታችን ዓይነት ስደተኞችና ለብዙ ዓመታት አግተው ካሠሯቸው በኋላ ከተጠያቂነት ለማምለጥ ከፎቅ የሚወረወሩ፣ አላስፈላጊ ድብደባ፣ እንዲሁም የአስገድዶ መደፈር ወንጀል የሚፈጸምባቸው እህቶቻችን ምን ያህል እንደሆኑ ቤት ይቁጠረው፡፡
በአጠቃላይ ለእነዚህ ሁሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መነሻው በአገሮች መካከል ለሚደረግ የሥራ ውል ስምምነት አገሮቹ የዜጎቻቸውን መብትና የሥራ ፍላጎት የሚያስከብር የሥራ ሥምሪት አዋጅ አለመኖሩ፣ ቢኖርም ተፈጻሚነቱ የላላ መሆኑ ነው፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው አገራችን ኢትዮጵያ ‹‹ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ›› እንዲሉ ከሁለት ዓመት በፊት ሳዑዲ ዓረቢያ ሕገወጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በኃይል ከአገሯ ማስወጣቷን ተከትሎ፣ የስድስት ወራት የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ላይ ዕገዳ በመጣል አዲስ የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት አዋጅ አውጥታለች፡፡ ይህ አዋጀ በፍጥነት ወደ ሥራ ባለመግባቱ ምክንያትም ከሳዑዲ ዓረቢያ በኃይል ከተባረሩት ስደተኞች ውስጥ ብዙዎቹ በባህር በር እያቋረጡ በሕገወጥ መንገድ ወደ መጡበት ሳዑዲ መመለሳቸውን፣ መገናኛ ብዙኃን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ሳዑዲ ከአራት ዓመት በፊት ሕገወጥ ኢትዮጵያውያንን በኃይል ብታስወጣም ቅሉ፣ በሕገወጥ መንገድ ወደ አገሯ የሚገቡትን ግን ማስቆም አልቻለችም፡፡ በዚህ የተነሳም በቅርቡ ለሦስት ወራት የሚቆይ የምሕረት አዋጅ በማውጣት አገሯን ለቀው ይወጡ ዘንድ እያሳሰበች ትገኛለች፡፡ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ›› እንዲሉ ኢትዮጵያም ከዚህ ቀደም ይሠራበት የነበረውን የውጭ አገሮች ሥራ ሥምሪት አዋጅ ክፈተት ያለበት በመሆኑ፣ ይህንን ክፍተት ለማሻሻልም አዲስ የሥራ ሥምሪት አዋጅ ወጥቶ ወደ ሥራ ባለመገባቱ ለሕገወጥ ስደት በር በመክፈት በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ወደ ተለያዩ አገሮች ገብተዋል፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ የዓለም አቀፍ የስደተኞችን ድርጅት ሪፖርት ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ባለፉት ስድስት ወራት ከ40 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን በጦርነት እየታመሰች ወዳለችው የመን መሰደዳቸውን ያመለክታል፡፡ ስለሆነም አዲሱ የሥራ ሥምሪት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎበት በፍጥነት ወደ ሥራ የማይገባ ከሆነ፣ ብዙ ወገኖች የበረሃ ሲሳይ መሆናቸው ይቀጥላል፡፡ የበረሃውንና ስቃይና መከራ አልፈው ወደ ዓረብ አገሮች የሚሄዱ ዜጎች (አብዛኞቹ ወጣት ሴቶች) ከፎቅ መወርወር፣ አካል መጉደል፣ በሽተኛ መሆን፣ ሞት፣ አስገድዶ መደፈር፣ የሠሩበትን ደመወዝና ያፈሩትን ጥሪት ሳይዙ ባዶ እጃቸውን መባረር የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህንን ችግር ይቀርፋል ተብሎ የተዘጋጀው አዲሱ የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ረቂቅ አዋጅ የሠራተኞችን መብት፣ ደኅንነትና ክብር ለማስጠበቅ ከበፊቱ በጣም የተሻለና ጠበቅ ያለ መሆን አለበት፡፡ በአዋጅ የተጠቀሱት ደንቦችም በሁሉም ባለድርሻ አካላት ዘንድ ተፈጻሚነት ይኖራቸው ዘንድ የጠነከረ ክትትልና ምዘና መካሄድ አለበት፡፡ በላኪና በተቀባይ አገሮች መካከል ባሉ ኤጀንሲዎች መካከል ጥብቅ የሆነ ግንኙነት እንዲፈጠር ከመቼውም በላይ አዋጁ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ፣ በኢትዮጵያና በሌላኛው ተቀባይ አገር መካከል የጋራ ወጥ የሆነ ስምምነት መኖር አለበት፡፡ ለምሳሌ ወደ አንድ አገር ለሥራ የሚሄዱ ዜጎች የሥራ ልምዳቸውንና የትምህርት ደረጃቸውን ግምት ውስጥ ያስገባ የደመወዝ እርከን መኖር አለበት፡፡ በዓረብ አገሮች የሚሠሩ ዜጎች እንደሚናገሩት በሕጋዊ መንገድ ለሥራ ወደ አገሪቱ ከገቡ በኋላ፣ አሠሪዎቻቸው የሚከፍሏቸው ወርኃዊ ደመወዝ አነስተኛ በመሆኑ የተሻለ ክፍያ ለመፈለግ ከአሠሪዎቻቸው በመጥፋት በሕገወጥ መንገድ ሌላ የሥራ ቦታ ይቀይራሉ፡፡
ይህ ጠፍተው የሚሠሩበት አሠሪም ሕገወጥ መሆናቸውን ስለሚያውቅ በተለየ ሁኔታ የዜጎችንን መብት እንዲጥስ ያበረታታዋል፡፡ ሠራተኞቹም ዘወትር ከአገሪቱ ፖሊስ ጋር ሌባና ፖሊስ ሲጫወቱ የተረጋጋ ሕይወት ካለመኖራቸው ባለፈ፣ ለእስርና ለድብደባ የሚጋለጡ የትየለሌ ናቸው፡፡ ስለሆነም ይህንን መሰሉን ችግር ለማስወገድ ላኪና ተቀባይ አገሮች ወቅታዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ የደመወዝ የክፍያ እርከን ሊያወጡ ይገባል፡፡
በሌላ በኩል መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአብዛኛው በውጭ አገሮች በተለያዩ የሥራ መስኮች በተሰማሩ ዜጎች ላይ የሚደርሱ ችግሮች ከዕውቀትና ከክህሎት ክፍተት ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ ስለሆነም አዲሱ የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት አዋጅ ለሥራ ወደ ውጭ የሚሄዱ ዜጎችን ሄደው ለሚሠሩበት የሥራ መደብ በቂ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ሥልጠና ከመስጠት ባለፈ፣ ለሥራው ብቁ መሆናቸውንን መመዘን አለበት፡፡
በተጨማሪም በአሠሪኛ በሠራተኛ መካከል በሚፈጠር አለመግባባት ላይ ሊሠራ የሚገባ አካል መቋቋም አለበት፡፡ በተቀባይ አገሮች የሚኖሩ የኢትዮጵያ ቆንስላዎች ይህንን ኃላፊነት በተገቢው ሁኔታ መወጣት አለባቸው፡፡ በተለያዩ የመረጃ ምንጮች በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እንደምናየው በዓረብ አገሮች የሚሠሩ ሴት እህቶቻችን ከሌሎች ዜጎች በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ የመብት ጥሰት በአሠሪዎቻቸው ይፈጸምባቸዋል፡፡ ይህ የሚሆነውም በአገሮቹ ውስጥ የሚገኙ ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች የተፈጠረውን ችግር አጣርተው ሕጋዊ የሆነ ዕርምጃ ካለመውሰዳቸው የሚመጣ ነው፡፡ ስለሆነም በአሠሪና በሠራተኛ መካከል ለሚኖረው አለመግባባት መፍትሔ ለመስጠት፣ ከአገናኝ ኤጀንሲዎች በተጨማሪ ኢምባሲዎችም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው mellegedif@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡
