የአለቃ ደስታ ተክለ ወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት "ሸፈጠ - ሰፈጠ ማለት - ካደ፣ ከዳ፣ ዓበለ፣ አሞኘ፣ አቄለ፣ አታለለ፣ ሸነገለ፤ ነው ይላል፡፡ "ሸፍጥ - ስፍጠት- አሉታ፣ ክዳት፣ የሆነውን የተደረገውን አልሆነም፣ የለም፣ አልተደረገም፣ አይደለም ማለት"መሆኑንም ይገልጻል፡፡ የኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት በበኩሉ "Fraud"የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል "wrongful or criminal deception intended to result in financial or personal gain"ሲል ይተረጉማል፡፡ አባባሉም ወደ አማርኛ ሲመለስ "የፋይናንስ ወይም ግላዊ ትርፍ ለማግኘት ሲባል ሕጋዊ ያልሆነና የተሰሳተ የወንጀል ተግባርን መፈጸም"ማለት ነው፡፡ ስለዚህ "ሸፍጠኛ ሰው"የሆነውን የተደረገውን አልሆነም፣ የተደረገውን አልተደረገም ብሎ ክዶና ዓብሎ የሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት ስለሆነ፣ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በእንግሊዝኛ ልሳን "Insurance Fraud"የሚለውን ባማርኛ "የመድን ሸፍጥ"ብሎ ተርጉሞታል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሥሩ የሚገኙትን የፋይናንስ ተቋማት ለመቆጣጠር የሚያወጣቸው መመርያዎችና ትዕዛዞች (Directives) የሚጻፉት በእንግሊዝኛ ልሳን ነው፡፡ ማዕከላዊ ባንኩ "Insurance and Reinsurance Business Fraud Monitoring Directives SIB/39/2014"በሚል ርዕስ ያወጣው መመርያ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ሲሆን፣ የመመርያው ርዕስ ወደ አማርኛ ሲመለስ "በመድንና በጠለፋ መድን ሥራ ላይ የሚፈጸምን ሸፍጥ ለመቆጣጠር የወጣ መመርያ ቁ. SIB/39/2014"ይላል፡፡
መመርያው ተራ ቁጥር 2.5 ላይ፡- "Fraud means an act or omission by shareholders, directors, employees, customers, policyholders, insurance auxiliaries committed with the intention of gaining dishonest and unlawful advantage for the party committing fraud or for other parties"በማለት "የመድን ሸፍጥ"ትርጉምን አስቀምጧል፡፡ ይኼም አባባል ወደ አማርኛ ሲመለስ "ሸፍጥ ማለት፣ በባለአክሲዮን፣ በዳይሬክተር፣ በሠራተኛ፣ በደንበኛ፣ በመድን ውል ባለቤት፣ በመድን ረዳት ለሸፍጡ ፈጻሚ ወይም ለሌሎች ሕጋዊ ያልሆነ ጥቅም ለማስገኘት በማሰብ የሚፈጽመው ወይም የማይፈጽመው ደርጊት ነው፡፡"
በመመርያው ተራ ቁጥር አራት ላይም እንደተመለከተው መድን ሰጪዎችና የጠለፋ መድን ሰጪዎች የመድን ሸፍጥን ለመለየት፣ ለመቀነስና ሪፖርት ለማድረግ የሚያስችል በግልጽ የተብራራ ፖሊሲና የአፈጻጸም መመርያ አውጥተው በቦርድ ዳይሬክተሮቻቸው እንዲያፀድቁና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ለሠራተኞቻቸው እንዲያስታውቁ ያዛል፡፡ በተጨማሪም መድን ሰጪዎችና የጠለፋ መድን ሰጪዎች የአወቃወርና የአሠራር ሲስተም አዘረጋጋቸው የተፈጸሙትንና የተሞከሩትን የመድን ሸፍጦች ለቦርድ ዳይሬክተሮች፣ ለማኔጅመንትና ለሌሎች ለሚመለከታቸው ሁሉ ለማሳወቅ የሚያስችሉ የግንኙነት መስመሮች መዘርጋታቸውን እንዲያረጋግጡ፣ የተፈጸሙና የተሞከሩ የመድን ሸፍጦችን ለብሔራዊ ባንክ በየ15 ቀኑ እንዲልኩ ይገልጻል፡፡ መመርያው ሌሎችንም በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ያልተጠቀሱትን የአፈጻጸም ሥርዓቶችን ይዟል፡፡
በአጠቃላይ "የሸፍጥ"ድርጊት በማታለል የግል፣ ወይም የጋራ ጥቅም ለማግኘት በሕግ፣ ወይም በሥራ የተሰጠ ኃላፊነትን አለመወጣት፣ ወይም ጉዳት ማድረስን የሚያስከትል ሲሆን፣ "የመድን ሸፍጥ"ስንል ደግሞ ከላይ እንደተገለጸው አንድ ሰው በሸፍጥ ከመድን ውል የማይገባውን "የገንዘብ ጥቅም ወይም ወሮታ" (Financial Benefit or Advantage) ለማግኘት፣ ወይም ሌላ ሰው የሚገባውን ጥቅም እንዳያገኝ በማድረግ የሚፈጸም የወንጀል ተግባር መሆኑን ለመገንዘብ እንችላለን፡፡
በጸሐፊው አመለካከት ከሌሎች የሸፍጥ ወንጀሎች ይልቅ "የመድን ሸፍጥ"በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ የሚያስወስደው ዕርምጃ በአንፃራዊ መልኩ የቀለለ፣ የሚሰጠው ጥቅም ግን ከፍተኛ ነው፡፡ አብዛኞቹ መንግሥታትም ለመድን ሸፍጥ የሚያደርጉት የሕግ ጥበቃ ዝቅተኛ መሆኑን (Low Legal Priority)ነው፡፡ በሁሉም አገሮች የመድን ሸፍጥ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሰ በወንጀሉ ቁጥጥርና ክትትል ረገድ እንደ ሌሎች ወንጀሎች እምብዛም ክብደት ስለማይሰጠው የመድን ሸፍጠኞች ወንጀሉን ለመፈጸም እንደሚበረታቱ አያሌ በውጭ አገሮች የተደረጉ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህም የመድን ሸፍጥ በዓለም ላይ እጅግ እየተስፋፋና እየበዛ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በፋይናንስ ላይ ትኩረት የሚያደርገው "ኢንቬስቶፔዲያ"የተባለው መዝገበ ቃላት በእንግሊዝኛ ልሳን ለመድን ሸፍጥ የሰጠው ትርጉም ለአረዳድ ቀላል ስለሆነ እንደሚከተለው በአማርኛ ልሳን እንጠቅሰዋለን፡፡ "የመድን ሸፍጥ በመድን ውል ሻጭ (በመድን ሰጪ እና በጠለፋ መድን ሰጪ)፣ ወይም በመድን ገዥ (በመድን አመልካችና በመድን ገቢ) የሚፈጸም ወንጀል ነው፡፡ በመድን ውል ሻጭ በኩል የሚፈጸመው የመድን ሸፍጥ የመድን ሥራን ለመሥራት ፈቃድ ሳይኖር ውሎችን መሸጥ፣ የዓረቦን ተመንን ያለማስመዝገብ፣ የኮሚሲዮን ጥቅም ለማግኘት ውሎችን ግልጽ ከማድረግ ይልቅ ማደበላለቅንና ማደናገርን ይጨምራል፡፡ በመድን ገዥዎች በኩል ደግሞ፣ የተጋነኑና የማይገቡ የካሣ ጥያቄዎችን ማቅረብ፣ የተሳሳተ የጤና መረጃ መስጠት፣ ውል የሚጀምርበትን ቀን የኋሊት መጠምዘዝ፣ ቫያቲካል ሸፍጥ፣ ሐሰተኛ የሞት መረጃ ማቅረብ፣ ጠለፋ፣ አፈናና ግድያ፣ ወዘተ ይጨምራል" (http://www.investopedia.com/terms/i/insurance-fraud.aspተመልከት)፡፡
"ቫያቲካል ሸፍጥ (Viatical Fraud)"
በሰሜን አሜሪካ ከሕይወት መድን ውል ጋር የተያያዘ ስምምነት ማለትም "ቫያቲካል ሴትልመንት" (Viatical Settlement)፤ ወይም "ላይፍ ሴትልመንት" (Life Settlement) የሚባል አሠራር ከተጀመረ ዕድሜው ገና 33 ዓመት ነው፡፡ ከላይ በተጠቀሰው መዝገበ ቃላት የመድን ሸፍጥ ትርጉም ውስጥ በእንግሊዝኛው ልሳን "ቫያቲካል ሸፍጥ"በሚል የተገለጸው ወንጀል በአገራችንም ሆነ በሌሎች ታዳጊ አገሮች የሚታወቅ ስላልሆነ፣ ምን ዓይነት ወንጀል እንደሆነ በቅድሚያ አንባቢያን እንዲረዱ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
በመሠረቱ አንድ ሰው "የዕድሜ ልክ የሕይወት መድን ዋስትና (Whole Life Insurance)"የሚገዛው እሱ ሲሞት ተጠቃሚ ያደረገው/ጋቸው ሰው/ሰዎች (Beneficiaries) የመድን ዋስትና ጥቅሙን እንዲያገኙ ለማድረግ ነው፡፡ ስለሆነም "የቫያቲካል ሴትልመንት"ስምምነት የሚደረገው የዕድሜ ልክ የሕይወት መድን ዋስትና ውል ኖሯቸው በተለያዩ የማይድኑ በሽታዎች የተለከፉና የመሞቻ ጊዜያቸውን የሚጠባበቁ ሰዎች፣ ከሕልፈተ ሕይወታቸው በፊት የሕይወት መድን ውላቸው የሚያስገኘውን "የሞት ጥቅም" (Death Benefit) ለሦስተኛ ወገን በቅናሽ ሸጠው በሚያገኙት ገንዘብ ቀሪ ሕይወታቸውን በገንዘብ ዕጦት ምክንያት ከሚደርስባቸው ጎስቋላ ኑሮ ተላቀው በደስታ እንዲኖሩ ለመርዳት ታስቦ የታቀደ ምግባረ ሠናይ ተግባር ነው፡፡
"የቫያቲካል ስምምነት"በራሱ (Perse) የመድን ውል ሳይሆን በመድን ውል ላይ የተመሠረተ "መድን መሰል" (Quasi-insurance) ሕጋዊ ስምምነት ነው፡፡ በመሠረቱ የሕይወት መድን ዋስትና ውል የመድን ገቢው "የግል ንብረት" (Private Property) ስለሆነ እንደማንኛውም ንብረት ከፈለገ ሊሸጠው፣ ሊለውጠው፣ ወይም የውሉን ጥቅሞች ለሌላ ሦስተኛ ወገን ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ ስለዚህ መድን ገቢው የሕይወት መድን ውሉን ያስተላለፈለት ሰው የውሉ ተጠቃሚ ሆኖ ተመዳኙ ሲሞት ጥቅሙን ሊያገኝ ይችላል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ማንኛውም ሰው ከፈለገ መዋዕለ ንዋዩን ሕጋዊ በሆነ "የኢንቨስትመንት መስክ" (Investment Vehicle) ላይ አፍስሶ "የመዋዕለ ንዋይ ጥቅም" (Investment Benefit) ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ "በቫያቲካል ሴትልመንት"የሕይወት መድን ውሉን የሚሸጠው በእንግሊዝኛው ስያሜ "ቫያተር" (Viator) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ በስምምነቱ ገንዘቡን አፍስሶ የመድን ውሉን የሚገዛውና መድን ገቢው/ተመዳኙ ሲሞት የመዋዕለ ንዋይ ጥቅሙን የሚቀበለው ሦስተኛ ወገን ሰው መጠሪያው ያው "ኢንቨስተር"ነው፡፡ ሁለቱን ተዋዋይ ወገኖች ማለትም ቫያተሩንና ኢንቨስተሩን የሚያቀራርቡት ደግሞ ኮሚሽን ከኢንቨስተሩ የሚከፈላቸው "አዋዋዮች" (Brokers) ናቸው፡፡
በአገረ አሜሪካ በሕይወት መድን ውል ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን የሚያፈሱ "ስምና ክብራቸውን የሚጠብቁ" (Reputable Viatical Funding Firms) ኩባንያዎች የመኖራቸውን ያህል፣ በአንፃሩ ደግሞ አደገኛ ሸፍጠኞችም ይገኛሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ የሰሜን አሜሪካ ክፍለ አገሮች "የቫያቲካል ሸፍጥ"መረን እየለቀቀባቸው በመሄዱ፣ ምክንያት ደርጊቱን ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን ሕጋጌዎች አውጥተው ይቆጣጠራሉ፡፡ በዚህ ረገድ "የኒውዮርክ ክፍለ ሀገር"ግምባር ቀደም ተጠቃሽ ነው፡፡ "የቫያቲካል ሴትልመንት"ተግባር የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ1980 ዓ.ም. አጋማሽ ገደማ ሲሆን፤ አነሳሱም በዋናነት ኤችአይቪ ኤድስ በብዙ ሕመምተኞች ላይ ላስከተለው የኑሮ ቀውስ መፍትሔ ለመሻት ነበር፡፡ በዚያን ወቅት በኤችአይቪ ኤድስ ቀሳፊ በሽታ የተለከፉ ሕሙማን ለተወሰነ አጭር ጊዜ ብቻ በሕይወት እንደሚኖሩ ይገለጽ ስለነበር፣ አብዛኞቹም ከላይ እንደተገለጸው ያለቻቸውን አጭር ቀሪ ሕይወት በመልካም ሁኔታ ለመኖር በገንዘብ ዕጦት የሚቸገሩ ነበሩ፡፡ ምክንያቱም ሥራቸውን መሥራት ስለማይችሉ ገቢያቸው ይቋረጣል፣ ጥሪት ያላቸውም ቢሆኑ በሕክምና ወጪ ጨርሰውት ሊሆን ይችላል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ እነዚህ ሕመምተኞች ለወራሾቻቸው፣ ወይም ተጠቃሚዎች አድርገው በውሉ ውስጥ ለሰየሟቸው ሰዎች እነሱ ከሞቱ በኋላ፣ በርከት ያለ "የሞት ጥቅም" (Death benefit) የሚሰጡ የሕይወት መድን ውል ያላቸው ናቸው፡፡
ስለዚህ፣ "ከራስ በላይ ንፋስ"እንዲሉ አዳዲስ ሥራ ፈጣሪዎችና አማካሪዎቻቸው "የመዋዕለ ንዋይ ምንጭ"ከሆኑ ደርጅቶችና ማኅበረሰቦች (Funding Frms/Agencies) ጋራ በመመካከር የሕይወት መድን ዋስትና በእጃቸው ላይ እያለ በገንዘብ ዕጦት ኑሮአቸው ለተጎሳቆለ ሕመምተኞች መፍትሔ ለመሻት ተነሳሱ፡፡ መፍትሔ ሆኖ የተገኘውም ከላይ እንደተገለጸው፣ ሕመምተኞቹ የሕይወት መድን ዋስትና ውላቸውን ለሦስተኛ ወገን ኢንቨስተሮች በተወሰነ ቅናሽ ሸጠው በሚያገኙት ገንዘብ እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ድረስ በደስታ ተመችቷቸው እንዲኖሩ ለማድረግ ነው፡፡ የቫያቲካል ስምምነት መሠረተ ሐሣብም በተመሳሳይ ሁኔታ በዕድሜያቸው የገፉ ሰዎችም እንዲጠቀሙበት ተደርጓል፡፡ እነሆ አስከ ዛሬ ድረስ በልዩ ልዩ ደዌ ተይዘው መሞቻ ቀናቸውን የሚጠባበቁ፤ ወይም በዕድሜያቸው የገፉ ሰዎች (በሰሜን አሜሪካ የኒውዮርክ ክፍለ ሀገር ሕግ እንደሚደነግገው ዕድሜያቸው ከ65 በላይ የሆኑ አዛውንቶች) ጠቀም ያለ የሞት ካሣ ጥቅም ሊከፍል የሚችለውን የሕይወት መድን ውላቸውን ለሦስተኛ ወገን ኢንቨስተር በቅናሽ እየሸጡ፣ በገንዘብ ዕጦት ምክንያት ከተጋረጠባቸው የኑሮ ቀውስ ተላቀው ቀሪውን ሕይወታቸውን በጥሩ ሁኔታ እንዲያሳልፉ ይረዳቸዋል ማለት ነው፡፡
የቫያቲካል ሸፍጠኞች ቫያተሩ ሊያገኝ የሚችለውን ጥቅም በማሳነስ የማይገባ ትርፍ መብላት፣ የመድን ውሉን ባለቤትነት በስማቸው ከተላለፈላቸው በኋላ በተለይም የአልጋ ቁራኛ ለሆኑት ሕመምተኞችና አዛውንቶች መጠነኛ ገንዘብ ብቻ በመወርወር ማታለል፣ አንዳንዴም ጨርሶ አለመክፈል፣ ወዘተ የመሳሰሉትን የወንጀል ተግባራት ይፈጽማሉ፡፡ ስለዚህ ሕመምተኞቹ መልካም ስም ካላቸው መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ጋር ከሸፍጥ ድርጊት የፀዳ ድርድር ማድረግ እንዲችሉና ቫያተሮቹ በሕይወት ከሚቆዩበት ጊዜ ጋር ተመጣጣኝ ጥቅም ማግኘት እንዲችሉ፣ ስምምነቱን መቆጣጠር የሚቻልበትን ሕግ በማውጣት የመድን ሸፍጠኞች በሕመምተኞች ወይም በዕድሜ የገፉት አዛውንቶች ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳት ለመታደግ ተችሏል፡፡ ከላይ በመድን ሸፍጥ ትርጉም ላይ ለአብነት ከተጠቀሱት ወንጀሎች መካከል "ቫያቲካል ሸፍጥ" ጎልቶ የተጠቀሰውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ "Vitical"የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል የተወሰደው "Viticum"ከሚለው የላቲን ቃል ነው፡፡ የቃሉ ትርጉም በእንግሊዝኛ ልሳን "Provisions for a Journey"በአማርኛ ሲተረጎም "የጉዞ ስንቅ"ማለት ነው፡፡ በክርስትና ሃይማኖቶች ዕምነት፣ በተለይም ጸሐፊው በሚያውቀው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ለሞት የተቃረበ ሰው በቅዱስ ቁርባን "የክርስቶስን ሥጋና ደም"ከተቀበለ "የጉዞ ስንቅ"ያገኛል ተብሎ ይታመናል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ዓለም ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት ለመሸጋገር ብርታት እንደሚሰጠው ሁሉ በዚሁ ተምሳሌት በማይድን በሽታ ተለክፈው ወይም ዕድሜያቸው በመግፋቱ ምክንያት የመሞቻ ጊዜያቸውን የሚጠባበቁና የሕይወት መድን ዋስትና ውል ያላቸው ሰዎች የመድን ውሎቻቸውን ለኢንቨስተሮች ሸጠው እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ድረስ ስንቅ የሚሆናቸው ገንዘብ ያገኛሉ ማለት ነው፡፡ የመድንውል በባሕርዩ ለመድን ገቢውም ሆነ ለመድን ሰጪው "የብዝበዛ በር" (Opportunities for Exploitation) ሊከፍት የሚችል ሥራ ስለሆነ፣ መንግሥታት ከሌሎች የንግድ ሥራዎች ይልቅ በጥልቀት የሚቆጣጠሩት ሥራ መሆኑን ቀደም ብዬ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ባቀረብኳቸው ጽሑፎቼ ለማስገንዘብ ሞክሬአለሁ፡፡
"ጥምረትበመድንሸፍጥላይ" (Coalition Against Insurance Fraud)
የመድን ሸፍጥ መድን ገቢውም ሆነ መድን ሰጪው የማይገባቸውን የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ የሚፈጽሙት ድርጊት መሆኑ ከላይ ተብራርቷል፡፡ በሰሜን አሜሪካ የሚገኘውና "ጥምረት በመድን ሸፍጥ ላይ" የተሰኘው ድርጅት "የሸፍጥ"ዋነኛ ምክንያት የሰዎች ስግግብብነት መሆኑን አበክሮ ይገልጻል (www.insurancefraud.org/)፡፡ ስለሆነም የመድን ሸፍጥ ዓይነቶችን ከዚህ ቀጥለን ለአብነት ያህል እንጠቅሳለን፡፡
- በጣምየተለመደው የመድን ሸፍጥ ዓይነት የጉዳት ካሣን ማጋነን (Inflating Loss) እና ያልደረሰ ጉዳትን የደረሰ አሰመስሎ ለማሳመን የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ ሁኔታውም በመድን ሳይንስ ሰብዓዊ/ሰዋዊ ጉዳት-አሥልጥ (Moral Hazard) በመባል ይታወቃል፡፡
- በበለፀጉትአገሮች ያሉ መድን ሰጪዎች የሚቀርቡላቸው አንዳንድ የጉዳት ካሣ ማመልከቻዎች አጠራጠሪ መሆናቸውን ቢረዱም፣ አንከፍልም ብለው አቋም ቢይዙ ተጎዳን ባይ ሸፍጠኞች ወደ ፍርድ አደባባይ መሄዳቸው አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ በእነዚህ አገሮች የፍርድ ቤት ክርክር ወጪዎች ከፍተኛ ከመሆናቸውም ባሻገር አጋጣሚው ለመልካም ስም ጎጂ ስለሆነ በፍርድ ቤት ክርክር ጊዜንና ገንዘብን ከማባከን ይልቅ፣ የካሣ ጥያቄዎችን ተቀብሎ ማስተናገዱን መድን ሰጪዎች ሊመርጡ ይችላሉ፡፡ እነዚህን በመሳሰሉ ምክንያቶች የመድን ሸፍጠኞች የሆኑ መድን ገቢዎችና አጋሮቻቸው (ለምሳሌ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ አንዳንድ የሕግ ጠበቆች) በአቋራጭ ጥቅም ለማግኘት ሰፊ ዕድል ያገኛሉ፡፡
- የመድንሸፍጥ ወንጀል ሌላው ምክንያት አንድን ንብረት ከትክክለኛው ዋጋ በላይ አብዝቶ የመድን ዋስትና መግባት ነው (Over Insurance)፡፡ የንብረቱ ትክክለኛ ዋጋ መድን ከተገባበት ዋጋ ያነሰ ከሆነ መድን ገቢው የበለጠ ጥቅም ለማግኘት ሲል ሆን ብሎ በንብረቱ ላይ ጉዳት አድርሶ በውጤቱ ለመጠቀም ይገፋፋል፡፡ ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን በተቆጣጠረበት ጥቂት ጊዜ ውስጥ አንዳንዳንድ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ያስገቧቸውን አሮጌ የጭነት ተሽከርካሪዎች በተጋነነ ዋጋ ለባንክ ብድር መያዣ በማድረግ የመድን ዋስትና ከገቡላቸው በኋላ፣ ተሽከርካሪዎቹን በዘዴ በማቃጠል ወይም ገደል በመክተት በርካታ የካሣ ጥያቄዎች መስተናገዳቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ከዚህ ደርጊት በተገኘው ልምድ ባንኮች ለአሮጌ መኪኖች ብድር መስጠት አቁመው እንደነበር ይታወሳል፡፡
- አንዳንድመድን ሰጪዎችም የመድን ዓረቦን ገቢያቸውን ለማሳደግ ሲሉ በተጋነነ መድን ማስገቢያ ዋጋ ዋስትና በመቀበል መድን ገቢዎችን የሚያበረታቱ ከሆነ፣ ይኼም ደርጊት ችግሩን አባባሽ ለመሆኑ አሌ አይባልም፡፡ ገበያ ለማግበስበስ ሲባልም በጣም በዝቅተኛ ዓረቦን ዋስትና ለመሸጥ መሞከርም በገበያ ውስጥ የሚፈጥረውን ቀውስ ያባብሳል፡፡ የመድን ሥራ በአግባቡ ቁጥጥር ካልተደረገበት ሀቀኝነት የጎደላቸው መድን ሰጪዎች ተገቢ ያልሆኑ ደርጊቶችን ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ግልጽ ነው፡፡
የመድንሸፍጥ በሁለት ዓበይት ክፍሎች ይከፈላል
1. "ጠጣርየመድንሸፍጥ" (Hard Insurance Fraud)
የመድን ካሣ ለመቀበል አንድ ሰው ሆን ብሎ በሕይወት በንብረት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ጥፋት (Loss) "ጠጣር የመድን ሸፍጥ"ነው፡፡ ለምሳሌ ሆን ብሎ የተሽከርካሪ አደጋ መፍጠር፣ የሕይወት የመድን ለማግኘት ብሎ የመድን ገቢውን ነፍስ ማጥፋት፣ ንብረትን ሆን ብሎ በእሳት ማቃጠል፣ ከሌቦች ጋር በመሻረክ ንብረትን ሆን ብሎ ማሰረቅና የመሳሳሉት ጠጣር የመድን ሸፍጦች ተብለው ይፈረጃሉ፡፡ በተለይም በመጨረሻ ላይ የተጠቀሰውን ወንጀል ለመፈጸም በአንዳንድ የበለፀጉ አገሮች ውስጥ ተቧድነው ድርጊቱን የሚፈጽሙ ሰዎች ቁጥራቸው ብዙ ነው፡፡ በሰሜን አሜሪካ "የአምቡላንስ አሳዳጆች" (Ambulance Chasers) በመባል የሚታወቁት ጠበቆች የአደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች እያሳደዱ ለራሳቸው ብዙ ጥቅም የሚያስገኝ ሥራ የሚፈጥሩ መኖራቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
2. "ልልየመድንሸፍጥ" (Soft Insurance Fraud)
ከጠጣር የመድን ሸፍጥ ይልቅ "ልል የመድን ሸፍጥ"ብዛቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ይኼውም የካሣ ጥያቆዎቹ ሕጋዊ ሆነው ሳለ በተገኘው የአደጋ አጋጣሚ በመጠቀም የበለጠ የካሣ ክፍያ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ የጉዳቱን መጠን የሚያጋንኑ ልል ሸፍጠኞች አሉ፡፡ የመድን ዋስትና ሲገዙ ዝቅተኛ ዓረቦን ለመክፈል ሲሉም ሆን ብለው የተሳሳተ መረጃ ለመድን ሰጪው የሚሰጡት የልል መድን ሸፍጠኞች ናቸው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ዝቅተኛ ዓረቦን ለመክፈል እንዲችል የሕይወት መድን ማመልከቻ ሲሞላ ዕድሜውን ሆን ብሎ ማሳነስ፣ አደገኛ ሕመም ያለበት መሆኑን እያወቀ ምንም በሽታ የለብኝም ብሎ መረጃ መስጠት፣ ቀደም ሲል የገዛቸው የመድን ውሎች ካሉ እነሱን የሚመለከቱ መረጃዎችን እንዲገልጽ ሲጠየቅ መኖራቸውን ልቡ እያወቀ ምንም የሌለ መሆኑን በመገልጽ ሐሰተኛ መረጃ መስጠትና የመሳሰሉት፣ በዚህ ክፍል ውስጥ የሚመደቡ ሸፍጦች ናቸው፡፡ የሆነውንና የተደረገውን አልሆነም፣ የለም፣ አልተደረገም፣ አይደለም ማለት ሸፍጥ መሆኑ ከላይ ተገልጾአል፡፡
የመድን ሸፍጥ በኅብረተሰቡ ላይ ምን ጉዳት ያስከትላል?
ከታሪክ ማኅደራት ለመገንዘብ እንደሚቻለው የመድን ሸፍጥ የመድን አገልግሎትን ለሕዝብ መሸጥ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የነበረና ዛሬም ያለ ነው፡፡ በዓለም ዙርያ በየዓመቱ "በሁሉም የመድን ዓይነቶች"ላይ በሚቀርቡ ሐሰተኛ የካሣ ክፍያ ጥያቄዎች አገሮቹን ለብዙ ቢሊዮን ብር ብክነት እንደሚዳርጋቸው አያሌ ማስረጃዎች አሉ፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለኅብረተሰብ ጎጂ ከሆኑት ሸፍጦች መካከል ለአብነት ያህል ጥቂቶቹን ቀጥለን እንጠቅሳለን፡፡
(1) የመድን የዓረቦን ተመን እንዲጨምርያደርጋል
የመድን ዓረቦን ተመን እንዲጨምር ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ የመድን ሸፍጥ ነው፡፡ የሐሰተኛ ካሣ ክፍያዎችንና ሌሎች ዓይነት የመድን ወጪዎችን ለመዋጋት በተለይ በውጭ አገሮች የሚገኙ መድን ሰጪዎች ለበርካታ ዓይነት ወጪዎች ይዳረጋሉ፡፡ ወጪዎቹንም ለማካካስ ሲሉ መድን ሰጪዎች በዓረቦን ተመኖች ላይ ጭማሪ መጣላቸው አይቀሬ ነው፡፡ ለምሳሌ ተመዳኞች፣ የካሣ አስተዳደር ሠራተኞች፣ የጥገና ጋራጆችና የተሸከርካሪ መለዋወጫ መደብሮች ባለቤቶችና ሠራተኞች የማይገባቸውን የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት በተናጠልም ሆነ በሽርክና የመድን ሸፍጥ የሚፈጽሙበት ዋና መስመር የተሸከርካሪ መድን ነው፡፡ የመድን ሸፍጥ ከተንሰራፋባቸው የመድን ዓይነቶች መካከል የሠራተኞች የጉዳት ካሣ መድን መሆኑ አይታበልም፡፡ በሐሰት አደጋ ደርሶብናል በሚሉና የካሣ ጥያቄ የሚያቀርቡ ሠራተኞች የመብዛታቸውን ያህል፣ አንዳንድ አሠሪዎችም የመድን ዓረቦን ለመቀነስ ሲሉ ትክክል ያልሆነና የተሳሳተ መረጃ ለመድን ሰጪዎች ስለሚሰጡ፣ ለዓረቦን ተመን ጭማሪ አስተዋፅኦዋቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ስለሆነም መድን ሰጪዎች በዓመቱ መጨረሻ ላይ የመድን ዋስትናዎቹን "የጉዳት-ኪሣራ ቀመር" (Loss Ratio) በመድን ዓይነትም ሆነ በጥቅል ሲያሰሉት "የውል ውጤት ኪሣራ" (Underwriting Loss) ሊደርስባቸው ይችላል፡፡ ምክንያቱም መድን ሰጪዎች በገቢ መልክ ያገኙት ዓረቦን በካሣ መልክ ከከፈሉት ወጪ ጋር ሲመዛዘን የካሣ ክፍያው መጠን ከበለጠ ዋስትናው አክሳሪ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ፤ ክስረቱ ዳግም እንዳይከሰት ለመከላከል የሚቀጥለውን ዘመን ዓረቦን መጨመር ግድ ይሆንባቸዋል፡፡
በአገራችን ለቀላል ሕክምና ወደ ጤና ተቋማት የሄዱ ሠራተኞች በተመላላሽ ሊታከሙ ሲችሉ፣ የሕክምና መድን ዋስትና ያላቸው ከሆኑ ተኝተው እንዲታከሙ ማድረግ፣ ወይም የሕመም ዕረፍት ማግኘት ለማይገባቸው ታካሚ ሠራተኞች የሕመም ዕረፍት በመስጠት በሥራ ላይ ችግሮች ሲፈጠሩ ይስተዋላል፡፡ በውጭ አገር የሚገኙ መድን ሰጪዎችም ከዚህ ችግር የፀዱ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ በጀርመን አንዳንድ የሕክምና ዶክተሮች በተመሳሳይ የመድን ሸፍጥ ላይ ተሠማርተው ስለተገኙ ክስ እንደቀረበባቸው በመዋዕለ ዜናዎች ተዘግበው እናገኛለን፡፡ በብዙ አገሮች የሚገኙ የአነስተኛና የመለስተኛ ደርጅቶች ባለቤቶችች የሕመም መድን ዋስትና ዓረቦን ከአቅማችን በላይ ሆነብን እያሉ የሚያሰሙት እሮሮ ዋና ምክንያቱ የመድን ሸፍጥ መሆኑ አይካድም፡፡
(2) የመድን ሸፍጥ የዕቃዎችና የአገልግሎቶችዋጋዎች እንዲንሩ ያደርጋል
የመድን ዓረቦን በንግድ ደርጅቶች ላይ ሲጨምር የንግድ ድርጅቶቹም በበኩላቸው ጭማሪውን በዕቃዎቻቸውና በአገልግሎቶቻቸው ዋጋ ላይ ያጣጡታል፡፡ የዚህ ደርጊት ውጤት በአጠቃላይ በሸማቹ ኅብረተሰብ ላይ ጫና ማስከተሉ በውጭ በተደረጉ አያሌ ጥናቶች ተረጋግጧል፡፡ በውጭ የሚገኙ ትልልቅ ድርጅቶች የንግድ ሥራ ሸፍጦችን ለመከላከል ከፍተኛ ወጪ ስለሚያወጡ፣ ይኼንኑ በዕቃዎችና በአገልግሎቶች ዋጋ ላይ በመጨመር እንዲሚያቻችሉትም ይታወቃል፡፡
(3) የመድን ሸፍጥ በሰዎች ሕይወት የሚያስከትለው ጉዳት
የሕይወት መድን ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች መድን ገቢው ቶሎ ሞቶላቸው ካሣቸውን ለመቀበል ባላቸው ጉጉት ሆን ብለው የሰው ሕይወት ያጠፋሉ፡፡ በጥንት ጊዜ በሰሜን አሜሪካ የመድን ዋስትና በሰው ሕይወት ላይ ለመግዛት "የመድን መብት" (Isurable Interest) እንዲኖር በሕግ ከመደንገጉ በፊት በፔንሲልቫንይ ክፍለ ግዛት የሚኖር አንድ በጣም የደከመና ያረጀ ሰው ነበር ይባላል፡፡ ይኼንን ሰው ስድስት ጎረምሶች ሲመለከቱት በጥቂት ቀናት ውስጥ ሊሞት ይችላል ብለው በመመካከር፣ ሰውየው ሲሞት የሞት ካሣ ገንዘብ ጥቅም ለማግኘት በየወሩ ዓረቦን እየከፈሉ በሽማግሌው ስም የሕይወት መድን ዋስትና ይገዛሉ፡፡ ሰውየው ከዛሬ ነገ ይሞታል ብለው ጎረምሶቹ ሲጠብቁት አልሞት ስላላቸውና ዓረቦኑንም በየወሩ መክፈል ስለከበዳቸው ሽማግሌውን ሆን ብለው ይገድሉታል፡፡ ፖሊስ የሽማግሌውን አሟሟት ሲያጣራ ስድስቱን ጎረምሶች በድርጊቱ ስለጠረጠራቸው ወንጀሉን አጣርቶ ፍርድ ቤት በማቅረብ የጓጉለትን ገንዘብ ሰይበሉት በስቅላት ተቀጥተዋል፡፡ በግዛቱ ውስጥ የመድን መብት ሳይኖር ለራስ ጥቅም የሌላ ሰውን የሕይወት መድን ማስገባት የተከለከለውም ከዚህ የወንጀል ደርጊት በኋላ ነበር፡፡ የሕይወት መድን ዋስትና ያላቸው ተጋቢዎችም አንዱ የአንዱን ሕይወት፣ ሸሪኮች የተሻረኪውን ሕይወት ሆን ብለው በማጥፋት የመድን ገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ወንጀል ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ እንደነዚህ ለመሳሰሉ እኩይ ተግባራት የመድን ሸፍጠኞች ለገንዘብ ሲሉ የሌሎቸ ሰዎችን ሕይወት ያለአግባብ ይቀጥፋሉ፡፡
(4) ሐሰተኛ የተሸከርካሪአደጋዎች
በተለይ በውጭ አገሮች የመድን ሸፍጠኞች የመድን ካሣ ክፍያ ጥቅም ለማግኘት ብለው "በማስመሰል በሚፈጥሩዋቸው የተሽከርካሪ አደጋዎች" (Staged Auto Accidents) ንፁኃን ሰዎችን የአደጋ ሰለባዎች ያደርጋሉ፡፡ በዚህም ተግባራቸው በብዙ አገሮች ሸፍጠኞች ሆን ብለው በሰላም ከሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ጋር ግጭት ይፈጥራሉ፡፡ ሆን ተብሎ የሚደረጉ ግጭቶች በሰሜን አሜሪካ "ግጭት ለጥሬ ብር" (Crash for Cash) በመባል ይታወቃሉ፡፡ በዚህ ዓይነቱ የተሸከርካሪ ግጭት ቴክኒክ የተካኑ ሸፍጠኞች ከፊት ለፊት እየነዱ ድንገት ፍሬን በመያዝ ከኋላ እየተከተለ ያለው ሰላማዊ ተሽከርካሪ እንዲገጫቸው ያደርጋሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም የፀነሰችን ሴት ይዘው ድርጊቱን ስለሚፈጽሙ ሴትዮዋ ባትጎዳም ክፉኛ የተጎዳች በማስመሰል ስለምትንፈራፈር፣ ለሕክምና ዕርዳታ የተሠለፉ ሐኪሞች ሴትዮዋ መፀነሷን ሲረዱ ሕይወቷን ለማትረፍ ፅንሱን ሊያቋርጡት ይችላሉ፡፡ የግጭቱ ውጤት እዚህ ደረጃ ከደረሰላቸው ሸፍጠኞቹ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የመድን ካሣ ገንዘብ እንደሚያፍሱ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዓይነቱ የፍርድ ቤት ክርክር የተካኑና ሆን ብለው የመድን ዋስትና ካሣዎችን ክርክር ለሚከታተሉ አያሌ ጠበቆችም ትልቅ ሲሳይ ይሆንላቸዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1993ዓ.ም. በሰሜን አሜሪካ ኒውጀርሲ ክፍለ ግዛት "የመድን ሸፍጥ መርማሪዎች" (Insurance fraud Investigators) በከተማዋ ውስጥ በተለያየ ቦታ በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ላይ ሆን ብለው "የማስመሰል/ተምሳሌታዊ ግጭት" (Staged Auto Accidents) እንዲደርስባቸው ያደርጋሉ፡፡ አደጋዎቹ በተፈጸሙባቸው ሥፍራዎች በግርግሩ አጋጣሚ ለመጠቀም ብዙ ሰዎች እየዘለሉ አውቶብሶቹ ውስጥ ገብተው አደጋ ደርሶብናል፣ ዕርዳታ አድርጉልን እያሉ መጮህ ይጀምራሉ፡፡ አንዳንዶቹም መኪኖቻቸውን አያቆሙ አውቶብሶቹ ውስጥ የገቡ ናቸው፡፡ ሰዎቹ አውቶብሶቹ ውስጥ እየተንደረደሩ የገቡት የተጎዱ መስለው ያላግባብ የመድን ካሣ ክፍያ ለማግኘት በማሰብ ነው፡፡ በተከታታይ ቀናትም በመቶዎች የሚቆጠሩ የካሣ ጥያቄ ማመልከቻዎች ለአውቶብሶቹ የመድን ዋስትና ሰጪ ኩባንያዎች ቀርቧል፡፡ አውቶብሶቹ የማስመሰል/ተምሳሌታዊ አደጋ እንዲደርስባቸው ሲደረግ በውስጣቸው ከመድን ሸፍጥ መርማሪዎቹና ከአሽከርካሪው በስተቀር ማንም ሌላ ተሳፋሪ አልነበረም፡፡
ለጥናት ተብሎ በተደረገው በዚህ የማስመሰል/ተምሳሌታዊ አደጋ ከተገኘው አስገራሚ ውጤት በኋላ አሥራ ሰባት ድርጅቶች እያንዳንዳቸው 500,000 ዶላር በማዋጣት "ጥምረት በመድን ሸፍጥ ላይ" (The Coalition Against Insurance Fraud) በሚል ስያሜ "ፀረ መድን ሸፍጥ ተቋም"አቋቋሙ፡፡ የተቋሙም ዓላማና ተልዕኮ የመድን ሸፍጥን በትጋት መዋጋት ነው ፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ያለውን የመድን ሸፍጥ ለመቋቋም ጥምረቱ የግልና መንግሥታዊ ደርጅቶችን በማስተባበር አያሌ ጥረቶችንም ያደርጋል፡፡ አባላቱም የመድን ሸፍጥ ብክነትን ለመቆጣጠር፣ የኅብረተሰብን ደኅንነት ለመጠበቅ፣ ብሎም "የመድን ሸፍጥ ወንጀለኞችን ለማንበርከክ ቆርጠን ተነስተናል" (Bring this Crime Wave to its Knees) ይላሉ፡፡ ሰሜን አሜሪካ በተሽከርካሪ መድን አደጋ ካሣ ክፍያ ላይ በየዓመቱ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ኪሣራ እንደሚደርስባት ተቋሙ ሰፊ ዘገባ ማቅረቡም ይታወቃል፡፡
(5) ሐሰተኛ የእሳት አደጋዎች
ያላግባብ ገንዘብ ለማግኘት ካላቸው ፍላጎት አንፃር መድን በተገባላቸው ንብረቶች ላይ ማለትም መኖሪያ ቤቶችን፣ የንግድ ድርጅቶችን፣ ተሽከርካሪዎችን፣ ወዘተ ሆን ብለው እሳት የሚለኩሱ ተመዳኝ ሸፍጠኞችም አሉ፡፡ እሳት በተለኮሰባቸው ቤቶች፣ ደርጅቶችና ፋብሪካዎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች፣ ጎረቤቶች፣ እሳቱን ለመከላከል የተሰማሩ የእሳት አደጋ ሠራተኞች በድርጊቱ መጎዳታቸው አይቀሬ ነው፡፡ እነዚህን በመሰሉ አደጋዎች ምክንያት የሚወድሙት ንብረቶች የአገር ሀብት ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ በዚህ ተግባር ላይ የሚሰማሩ መድን ገቢዎች የሚያቀርቧቸው የመድን ካሣ ክፍያ ጥያቄዎች በጣም የተጋነኑ ናቸው፡፡ የወንጀል ደርጊቱም እንዳይደረስበት መረጃዎችን ለማጥፋት ቢጥሩም በፖሊስ ምርመራ ሲጋለጡ ይስተዋላል፡፡ ቅድመ ደርግ በአዲስ አበባ ከተማ አምባሳደር ቴአትር ሕንፃ ሥር ይገኝ የነበረ የምሽት ክበብ ላይ የእሳት አደጋ ደርሶበት የክበቡ ንብረት በሙሉ ተቃጥሎ ነበር፡፡ የመድን ካሣ ለማግኘት አስበው በቤንዚን የተሞላ ጀሪካን ክበቡ ውስጥ አስቀምጠው እሳቱን ሆን ብለው ያቀጣጠሉትና በመጨረሻ ዘግተው የወጡት የክበቡ ባለቤት ናቸው፡፡ ክበቡን ባለቤቱ ማቃጠላቸውን መርማሪ ፖሊሶቹ የደረሱበት ቤንዚን የነበረበት ጀሪካን በእሳቱ ግሎ ሲፈነዳ ክዳኑ ተፈናጥሮ ጣሪያ ላይ በረጨው ቤንዚን መረጃ ፖሊስ ተጠራጥሮ ባደረገው ከፍተኛ የምርመራ ሥልት ነበር፡፡ ዓቃቤ ሕግ በሸፍጠኛው የክበቡ በባለቤት ላይ ክስ መስርቶ የዘጠኝ ዓመት እስራት እንዳስወሰነባቸው፣ በጊዜው በነበረው የፖሊስና ዕርምጃው ጋዜጣ ላይ ማንበቡን ጸሐፊው ያስታውሳል፡፡
(6) ሠራተኞችንከሥራ ያፈናቅላል
አንዳንድ የመድን ሸፍጥ እንቅስቃሴዎችም ሠራተኞች ከሥራቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆነው ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በሰሜን አሜሪካ "ማርቲን ፍራንከል (Martin Frankel)"የተባለ ሸፍጠኛ ሰው "ፍራንክሊን አሜሪካን ላይፍ ኢንሹራንስ ካምፓኒ” የሚባል የሕይወት መድን ኩባንያ አቋቁሞ በሚስጥር የኩባንያውን ሀብት ወደ ግል ሒሣቡ በማዛወሩ ምክንያት ኩባንያውን አክስሮ እንዲዘጋ አድርጓታል፡፡ በዚያም ደርጊት ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ከሥራቸው ተፈናቅለዋል፡፡
(7) የመንግሥትንሀብት አቅጣጫ ያስለውጣል
የብዙ አገሮች መንግሥታት ሌሎች ወንጀሎችን ለመቆጣጠር የሚያውሉትን ገንዘብ የመድን ሸፍጥን ለመቆጣጠር ይጠቀሙበታል፡፡ ደርጊቱ በተለይ የኢኮኖሚ ዕድገታቸው አናሳ የሆኑትን አገሮች አቅም በእጅጉ ይፈታተናል፡፡ ስለዚህም የፀረ-መድን ሸፍጥ ቢሮዎች ማቋቋሚያ በጀት፣ እንዲሁም የፖሊስንና የዓቃቤ ሕግ ቢሮዎችን ለማጠናከር ለሚወሰዱ ዕርምጃዎች አያሌ ወጪዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የሰሜን አሜሪካ መንግሥት ለፌዴራልና ለክልል መንግሥታት በጤና ሕክምና ላይ የሚደረገውን ሸፍጥ ለመከላከል በየዓመቱ ብዙ ቢሊዮን ዶላር በጀት ይመድባል፡፡ በዚህ ረገድ የሌሎች አገሮችም ወጪዎች የናሩ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ በሌሎች ጠቃሚ ልማቶች ላይ የሚውለው የሕዝብ ሀብት ሸፍጠኞችን ለመዋጋት አቅጣጫ መቀየሩ አሌ አይባልም፡፡
የመድንሸፍጥ ስታትስቲካዊ መረጃ
በአገራችን በመድን ሸፍጥ የሚባክነውን የአገር ሀብት የሚገልጽ አስተማማኝ የሆነ መረጃ ስላልተገኘ፣ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ለማቅረብ አልተቻለም፡፡ ሆኖም የመድን ሸፍጥ "ኢኮኖሚያዊ ወንጀል" (Economic Crime) በመሆኑ በአንድ አገር ኢኮኖሚ ላይ ምን ያህል ጉዳት እንደሚያደርስ ለአንባቢ ግንዘቤ ለማስጨበጥ ሌሎች አገሮች ያጠናቀሩትን ስታትስቲካዊ መረጃ ዝቅ ብሎ በሚገኘው ራሱ አስረጅ በሆነው ሰንጠረዥ አማካይነት ለአብነት ያህል ማቅረብ ተችሏል፡፡ መረጃው የተቀዳው "NHS Counter Fraud and Security Management Service, July 2006" - The International Fraud And Corruption Report - A study of selected countries (www.slideshare.net/…/the-international-fraud-and...) በሚል ርዕስ ከተዘጋጀው ሪፖርት ላይ ነው፡፡ በሰንጠረዡ ውስጥ አገሮቹ ካላቸው የሕዝብ ብዛትና ዓመታዊ ገቢያቸው አንፃር በመድን ሸፍጥ ከሚባክነው ሀብታቸው ጋር ተነፃፅሮ ይታያል፡፡
አገር
የሕዝብ
ብዛት
ዓመታዊ ገቢ ምርት
(GDP)
በመድን ሸፍጥ
የሚባክነው ሀብት
ከዓመታዊ ገቢ ምርት (%)
አውስትራሊያ
20.1 ሚሊዮን
8.1 ትሪሊዮን ዶላር
5.8 ቢሊዮን ዶላር
1.3
ካናዳ
31.0 ሚሊዮን
980 ቢሊዮን የካ. ዶላር
20 ቢሊዮን የካ. ዶላር
2.1
ፈረንሣይ
61.9 ሚሊዮን
1.7 ትሪሊዮን ዩሮ
መረጃ የለም
2
ጀርመን
82.5 ሚሊዮን
2.1 ትሪሊዮን ዩሮ
200 ቢሊዮን ዩሮ
9
አየርላንድ
4.02 ሚሊዮን
148.9 ቢሊዮን ዩሮ
6.31 ቢሊዮን ዩሮ
4
ሰሜን አሜሪካ
296 ሚሊዮን
11.7 ትሪሊዮን ዶላር
660 ቢሊዮን ዶላር
6
መደምደሚያ
የመድን ዓረቦን እንዲጨምር ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ የመድን ሸፍጥ መሆኑን ከላይ ተብራርቷል፡፡ ያላግባብ የሚከፈሉ የካሣ ክፍያዎችም ሆኑ በዚያ ዙርያ የሚከፈሉ ሌሎች ተመሳሳይ ወጪዎች እየተደማመሩ የመድን ጉዳት ክስረት አካፋይ ቀመሩን (Loss ratio) ስለሚያንሩት ወጪዎችን ለማጣጣት መድን ሰጪዎች ዓረቦን እንዲጨምሩ፣ ነጋዴዎች ደግሞ የመድን ዓረቦን ሲንርባቸው ወጪአቸውን በሸቀጦችና በዕቃዎች ዋጋ ላይ እንደሚያጣጡ ተገልጾአል፡፡ ስለዚህ የዓረቦን ተመን በናረ ቁጥር ኅብረተሰብ የመድን ዋስትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት አዳጋች ይሆንበታል፡፡ ከዚህ አንፃር በጥቅሉ ሲታይ የመድን ሸፍጥ የሚጎዳው ከመድን ሰጪዎች ይልቅ የመድን ተጠቃሚውን ኅብረተሰብ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ዓረቦን ቢወደድም "መድን አልባነት" (Uninsurance - the state of being uninsured) የሚያስከትለው የጉዳት ክስረት (loss) ስለሚከፋ የሠለጠነ ኅብረተሰብ መድን ከመግዛት አይቆጠብም፡፡ በዓለም ዙርያ ከላይ የተጠቀሱትን የመድን ሸፍጥ ችግሮች ለመከላከል መንግሥታትና መድን ሰጪዎች ትልቅ ፈተና ተጋርጦባቸዋል፡፡ በአገራችንም ቢሆን የመድን ሸፍጥ ያው የሙስና ወንጀል ስለሆነ መንግሥት፣ መድን ሰጪዎችና ኅብረተሰቡ የችግሩን ስፋት በጥልቀት ተረድተው የመሸ ቢሆንም ሳይነጋ አጥብቀው ሊዋጉት ይገባል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው [BA, LLB (GD), Graduate Dipl. in Development Administration (India), ACII, Chartered Insurer (UK), ACS (USA)] ለረጅም ዓመታት በመድን ሥራ፣ በሥልጠና፣ በመድን ምርምርና ሥነ ጽሑፍ ሰፊ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ሲሆኑ፣ የመድን ባለሙያዎች ማኅበር (SIP) የመጀመርያው ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው eyosono@gmail.comወይም leeyobed@yahoo.comወይም በቴሌፎን ቁ. +251 0911 43 15 50 ማግኘት ይቻላል፡፡
