Quantcast
Channel: ዓለማየሁ ጉጀ
Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

አቢጃታና ሻላን ከመጥፋት እናድን!

$
0
0

በሮቤ ባልቻ

በቅርቡ በሪፖርተር ጋዜጣ ‹‹አቢጃታን ተዩው›› በሚል ርዕስ የቀረበውን መልዕክት ተመልክቼዋለሁ፡፡ መልዕክቱን ያቀረቡትን ሰለሞን ወርቁ የተባሉ ጸሐፊን አደንቃቸዋለሁ፡፡ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በአገር ተፈጥሯዊ ሀብት ላይ ጎጂ ውሳኔ የሚያሳልፉ፣ ግለሰቦችና መሥሪያ ቤቶች ዕርምጃዎቻቸውን መልሰው እንደሚያጤኑ ጸሐፊው ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡ ከአስተያየታቸውም እንደተረዳሁት ጉዳዩ በጎ ምላሽ  ካላገኘ፣ ለወደፊቱም ገንቢና ቀጣይ መልዕክቶች ይኖሩዋቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

ይህ የአገርን ተፈጥሯዊ ሀብትና ሥነ ምድራዊ ገጽታ የሚጎዳ ጥናትና ውሳኔ ለአቶ ሰለሞን አስተያየት ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ አሁን በአቢጃታና በሻላ ሐይቆች ላይ የተደቀነው አሳሳቢ ሁኔታ፣ ለዛሬውና ለነገው ትውልድ ጎጂ መሆኑን የሚያምን ዜጋ ሁሉ ድምፁን ሊያሰማበት የሚገባ ነው፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት በሐሮማያ ሐይቅ መድረቅ መንስዔ ላይ ጥናት ያካሄዱ ባለሙያ ምክንያቶች ያሉዋቸውን ዝርዝሮችን ሲያቀርቡ፣ በብሔራዊ ቴሌቪዥን መከታተሌን አስታውሳለሁ፡፡

በሐይቁ ዙሪያ የነበሩ ተክሎችና ቁጥቋጦዎች ተመንጥረው አካባቢው መራቆቱን እንደ አንድ መንስዔ አውስተው ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሐይቁ ውኃ ለከተማውና ለአካባቢው ፍጆታ ከአቅም በላይ አገልግሎት ላይ በመዋሉ እንደሆነም ገልጸው፣ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተው እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡  

ዛሬ ጥፋት የተደቀነባቸውን አቢጃታና ሻላ ሐይቆች ስናነሳም ከሐሮማያ ሐይቅ የተለየ ዕጣ እንደማይጠብቃቸው ግልጽ ነው፡፡፡ ከመነሻው በአቢጃታና በሻላ ሐይቆች ዙሪያ መቋቋም የነበረበት የሶዳ አሾ ማምረቻ ፋብሪካ አይደለም፡፡ ለዘመናት ተፈጥሮ በአካባቢው ያለመለመቻቸው የግራር ዛፎችና ሌሎችም ተክሎች በይበልጥ እንዲለመልሙ መሠራት ነበረበት፡፡ የአካባቢው ተፈጥሮ ጥበቃ የሚጠናከርበትና ለቱሪስቶች ዕይታ የሚያመቹ መዝናኛዎች፣ መመልከቻዎችና ማረፊያዎች መዘጋጀት ነበረባቸው፡፡ ቀደም ሲል ተሠርተው አገልግሎት ላይ የነበሩና ዛሬም በመስፋፋት ላይ የሚገኙ የስምጥ ሸለቆ መዝናኛና ማረፊያ ሥፍራዎች በይበልጥ ተሻሽለው፣ ዓለም አቀፍ ደረጃ የጠበቁ እንዲሆኑ ማገዝና መደገፍ ይገባ ነበር፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ የአቢጃታን ሐይቅ ውኃ ሲጠቀም የነበረው ፋብሪካ፣ ውኃው በመቀነሱ ወደ ሻላ ሐይቅ ለመሸጋገር ጥናት በማድረግ ላይ ነኝ ማለቱ አስገራሚ ነው፡፡

አቢጃታና ሻላ ሐይቆች በአፍሪካም ሆነ በዓለም የሚታወቁባቸው የራሳቸው መለያ እንዳላቸው በአቶ ሰለሞን በዝርዝር ቀርቧል፡፡ አቢጃታ፣ ሻላና ጭቱ ሐይቆች ማረፊያ የሆኑት በአገራችን ለሚገኙ የአዕዋፍ ዝርያዎች ብቻ ሳይሆን፣ ከዓለም ዙሪያ ረዥም ርቀት አቋርጠው ለሚመጡ ተሰዳጅ አዕዋፍ ጭምርም እንደሆነ በጸሐፊው ተገልጿል፡፡ እነዚህ ሐይቆች 453 የተለያዩ የአዕዋፋት ዝርያዎች መያዛቸውንም በልዩነት አስቀምጠውታል፡፡ በሐይቆቹም በዓመት 5,000 ያህል ሻሎዎች እንደሚራቡባቸውም አስፍረዋል፡፡ 50,000 ፍላሚንጐዎችና 40,000 ያህል መንቁረ ግልብጥ አዕዋፋት በማረፊያነትና በመመገቢያነት እንደሚገለገሉባቸው አቶ ሰለሞን ጥሩ አድርገው ገልጸውታል፡፡

ከዚህ የምንገነዘበው ተፈጥሮ ሐይቆቹን ውብ አድርጎ እንደሰጠን ነው፡፡ በተፈጥሯዊ ውበቱ ላይ ደግሞ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው አዕዋፋት ሠፍረውበታል፡፡ በቦታው ተገኝቶ የማየት ዕድል ያላገኘ ሰው እንኳን ጽሑፉን በማንበብ ብቻ በሐይቆቹ የሚኖረውን ትዕይንትና ውበት በዓይነ ህሊናው መመልከት ይችላል፡፡ ጊዜና ሁኔታ ሲፈቅድለትም ሄዶ ለመጎብኘትም ያስባል፣ ያቅዳል፡፡ ይህንን ተፈጥሯዊ ሀብት በዘላቂነት መጠበቅ ከተቻለ ደግሞ፣ በአግባቡ አስተዋውቆና የቱሪስት መስኅብ አድርጎ እንደ ሌሎች አገሮች ተጠቃሚ መሆን ይቻላል፡፡ በእኔ ግምት የሶዳ አሾ ፋብሪካው የሐይቁን ውኃ መጠቀሙ ብቻ ሳይሆን፣ በዙሪያው መቋቋሙ ራሱ በሐይቁ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ይኖረዋል፡፡ የጉዳቱን ዓይነትና መጠን ግን የመስኩ ባለሙያዎች አጥንተው ቢያቀርቡት ይመረጣል፡፡

ከሶዳ አሾ ፋብሪካው በተጨማሪ በባቱ (ዝዋይ) ከተማ የመስኖ ሥራ የሚያከናውኑ የአበባ፣ እርሻና የወይን እርሻ ድርጅቶች 6,000 የሚደርሱ የውኃ መሳቢያ ፓምፖች በመትከል የአቢጃታን ሐይቅ በመጠቀም ላይ እንደሚገኙ ምንጭ ጠቅሰው አቶ ሰለሞን አስፍረዋል፡፡ በእኔም አስተያየት ይህ ተግባር የአቢጃታን ሐይቅ ሞት እንደ ሐሮማያ ሐይቅ የሚያፋጥን ድርጊት ነው፡፡ አቶ ሰለሞንም ይህንኑ ጠቅሰዋል፡፡      

የአበባና የወይን እርሻዎቹ ገና ሲቋቋሙ በአቢጃታ ውኃ ላይ ተማምነው ሥራ መጀመር አልነበረባቸውም፡፡ ፈቃድ ሰጪው ክፍልም የኢንቨስትመንት ፈቃዱን ከሌላ አማራጭ ጋር ሊሰጣቸው ይገባ ነበር፡፡ ሁለቱም ድርጅቶች በተናጠል ወይም በጋራ በሌሎች አማራጮች ዙሪያ ጥናት እንዲያደርጉ ማሳሰብ ይቻል እንደነበር እገምታለሁ፡፡ ለእኔ የሚታዩኝ አማራጮች ጥልቅ ጉድጓዶች ቁፋሮ፣ በቅርበት ያሉ ወንዞችን አጎልብቶ መጥለፍና ውኃ ማቆር ናቸው፡፡ የዚህ ዘርፍ ባለሙያ ባልሆንም፣ እነዚህን አማራጮች በተናጠል ወይም በማዳበር እርሻዎቹ መጠቀም ይችሉ እንደነበር መገመት እችላለሁ፡፡፡ ከመነሻው ሌላ አማራጭ ሳይታይ ዝግጁ ሆኖ ያለን የተፈጥሮ ሀብት እንደ መጨረሻ መፍትሔ ወስዶ ለጥፋት መዳረግ ግን የሚደገፍ አይደለም፡፡ አማራጮች ቀርበውላቸው ባለሀብቶቹ ከአቢጃታ ሐይቅ ውጪ ሌሎቹን የማይቀበሉ ከሆነ፣ ስምምነቱ እዚያው ላይ መቆም ነበረበት፡፡ በአግባቡ ከሠራንበትና ጥቅም ላይ ካዋልነው፣ ዛሬ ለእኛ ነገ ደግሞ ለልጆቻችን የሚተርፍ ውብ ሀብት ከሚጠፋ የአበባ ልማቱና የወይን ምርቱ ቢቀር ይመረጣል፡፡

ዛሬም ቢሆን የአበባና የወይን እርሻዎቹ ሌሎች አማራጮች ከአሁኑ እንዲፈልጉ ቀጣይ ድርድር ማመቻቸት ይገባል፡፡ የሐይቁ ውኃ እየቀነሰ መጥቷል ተብሏል፡፡ እየቀነሰ ከመጣ ደግሞ ነገ መድረቁ የማይቀር ነው፡፡ ነገ ሲደርቅ እርሻዎቻቸው ሥራ ከሚያቆሙ ከአሁኑ በአማራጮች ዙሪያ ጥናት ማካሄድ ይኖርባቸዋል፡፡ ጥናታቸው ግን በቅርባቸው ወደሚገኙ ሌሎች ሐይቆች መሸጋገርን የሚጨምር ሊሆን አይገባም፡፡

አቢጃታንና ሻላን የመሳሰሉ ሐይቆች አካባቢ የማዕድን ቁፋሮና የማምረቻ ፋብሪካ ሲታሰብ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ተነጋግረውበት ይወስናሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡

ለምሳሌ በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት አስመልክቶ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት የሚመለከተው መሥሪያ ቤት፣ የማዕድን ኮርፖሬሽን፣ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣንና የኢንቨስትመንት ጉዳዮች የሚመለከተውን መሥሪያ ቤትና ሌሎችንም ማንሳት ይቻላል፡፡

ከእነዚህ ግዙፍ መሥሪያ ቤቶች ሶዳ አሾ ፋብሪካ በሐይቁ አካባቢ መቋቋሙና የሐይቁን ውኃ መጠቀሙ ተፈጥሯዊ ሚዛኑን ሊያዛባ እንደሚችል ገምቶ፣ አማራጭ ሥፍራ እንዲፈልግ የሚያደርግ ባለሙያና ክፍል እንዴት ይታጣል? በእርግጥ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዕርምጃው በተፈጥሮ ላይ ጉዳት እንደሚኖረው አመልክቶ ሰሚ ማጣቱ ተጠቅሷል፡፡ የተቀሩት መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎችና ኤክስፐርቶቻቸው ሊከተል የሚችለው ጉዳት እንዴት አልታያቸውም? የአበባና የወይን እርሻዎቹስ ይህንኑ የሐይቅ ውኃ እንዲጠቀሙ እንዴት ተፈቀደ? ለምንስ ሌሎች አማራጮች አልቀረቡባቸውም?

ፋብሪካውና እርሻዎቹ የሚገለገሉበት የሐይቁ ውኃ እየቀነሰ ሲመጣ ፋብሪካው ወደ ሻላ ሐይቅ ለመሸጋገር ጥናት መጀመሩንስ እነዚህ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንዴት ያዩታል? ውብ የተፈጥሮ አካባቢዎችን ለተሻለ ልማት እንጂ፣ በቀጣይነት ለጥፋት የሚዳርግ ውሳኔ ውስጥ እንደማይገቡ ተስፋ ይደረጋል፡፡

የአቢጃታና የሻላ ሐይቆች ተፈጥሯዊ ውበት እንደተጠበቀ እንዲቆይና አዕዋፋቱም ቀጣይ ሕይወት እንዲኖራቸው በየኃላፊነታችንና በሙያችን ዕገዛ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ አቢጃታ ሙሉ በሙሉ ከመድረቁ በፊት ፋብሪካውና የመስኖ እርሻ የሚጠቀሙ ድርጅቶች አማራጭ መፍትሔዎች ሊፈለግላቸው ይገባል፡፡ ወደ ሻላ ወይም ሌሎች የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ለመሸጋገር የሚደረግ ማንኛውም ጎጂ እንቅስቃሴ ቢገታ፣ የተፈጥሮ ሀብቶቹን ለመንከባከብ ድርሻ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡

በስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ዙሪያ አዳዲስና ዘመናዊ የቱሪዝም ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ይዘው የሚቀርቡ አልሚዎች እንዲበረታቱ ያስፈልጋል፡፡

ተፈጥሮን ስንደግፋትና ስንንከባከባት እሷም መልሳ ትክሳናለች፡፡ በግድ የለሽነት ያለበቂ ጥናት ስናጠፋት እሷም በተራዋ ምላሽ አላት፡፡ በሚከተለው ተፈጥሯዊ ጉዳትም መጪው ትውልድ ተወቃሽ ያደርገናል፡፡

አቢጃታ ሐይቅና ብርቅዬ አዕዋፋቱ ከጥፋት ድነው የልማትና የቱሪዝም ማዕከል እናድርጋቸው፡፡ ሻላ ላይ የታቀደው የአማራጭነት ትልምም ይቁም፡፡ ውብ የተፈጥሮ አካባቢዎችን መጠበቅና የበለጠ ምቹ አድርጎ መያዝም ሌላው የልማት ዘርፍ መሆኑ ይሰመርበት፡፡ ይህንን ማድረግ መቻል ደግሞ የአገራችንን ተፈጥሯዊ ሀብቶች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የመጠበቅ አንዱ አካል ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

         

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

Trending Articles