Quantcast
Channel: ዓለማየሁ ጉጀ
Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

አቢጃታ - በእኛ አገር ‹‹የሄደና የሞተ ነው የሚመሰገነው››

$
0
0

በሰለሞን ወርቁ

ከዕለት ወደ ዕለት ኩርማን የማይሞላ ውኃ እየቀረው የመጣው የአቢጃታ ሐይቅ በአፋጣኝ እንዲያገግም ካልተደረገ በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ነጭ አሸዋና ትዝታው ብቻ ይቀራል፡፡ የሐይቁ ውኃ መቀነስና የአካባቢው መራቆት ምክንያት ያደረጉ በርከት ያሉ ጥናቶች በየጊዜው በተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ተጠንተዋል፡፡ ጥናቶቹ የችግሮቹን መነሻ አንስተው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ርምጃዎች የራሳቸውን የይሁንታ ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ በአንጻሩ ግን ይህንን ችግር ከወዲሁ ለመፍታትና ሐይቁንም ከአደጋ ለማዳን የተሞከረ አንድም ፍሬያማ ተግባር አይስተዋልም፡፡ ለችግሩ መንስዔ የሆኑና በቀጥታ የሚመለከታቸው ተቋማትና ድርጅቶች የተጠኑ ጥናቶችን መሠረት አድርገው አፋጣኝ ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ጥፋቱን ላለመቀበል እየተገፋፉ ይገኛሉ፤ ሐይቁም ሞቱን ለመቀበል ያጣጥራል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች በሚያስጠኗቸው ጥናቶችም ለጥፋቱ ድርሻቸውን ለማሳነስና ሌላውን ኩነኔ ለማስገባት ከመሮጥ ይልቅ በተናጠል ያጠፉትን ሀብት በጋራ መክረው ማዳን እንደሚችሉ የተረዱ አይመስልም፡፡

ታደሰ ፈታሂ ካቀረቡት ‹‹ግሪኒንግ ኤ ሮፒካል አቢጃታ፣ ሻላ ሌክስ ናሽናል ፓርክ ኢትዮጵያ - ኤ ሪቪው›› በሚለው ጥናታቸው እንዳቀረቡት፣ ለአቢጃታ ሐይቅ ውኃ መቀነስ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ጉዳዮች አንዱ የቡልቡላ ወንዝ ሙሉ በሙሉ ወደ ሐይቁ መግባት በማቆሙ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህ ከብዙዎቹ አንዱ ሲሆን ሌሎች ተደራራቢ ችግሮችም አልታጡም፡፡ ዝዋይ ሐይቅ በስተምሥራቅ ከመቂ ወንዝ፣ በስተምዕራብ ደግሞ ከከታር ወንዝ ግብሩን ይሰበስባል፤ ከዚያም የቡልቡላን ወንዝ በመጠቀም በተራው ለአቢጃታ ሐይቅ ግብር ያገባ ነበር፡፡ የላንጋኖ ሐይቅም ከሚያገኛቸው ገባር ወንዞችና ጅረቶች የፈቀደውን የውኃ መጠን በሆራ ቀሎ ወንዝ አማካይነት ለአቢጃታ ይለግስ ነበር፡፡ አሁን ይኼ ሁሉ ነበር ሆኗል፡፡ ትልቁ ችግር ያለው ሐይቁ በተፈጥሮው በወንዞች ልግስና ብቻ ህልውናው የቆመ ነገር እንደሆነ ተደርጎ የሚነገረው ጉዳይ፣ ጥፋተኛ አይደለንም ብሎ ለመሸሽ እንደ አማራጭ መወሰዱ ላይ ነው፡፡ የሐይቅ ተፈጥሮ ምንም ይሁን አግባብ ባለው መንገድ የያዘውን ሀብትና ውኃውን ተጠቅመንበት ቢሆን ኖሮ ይህ ችግር ባልተከሰተ ነበር፡፡   

ቡልቡላ ወንዝን ከመነሻው ተቀብሎ በደጁ ዙሪያ ያልለመደውና ከፍተኛውን ድርሻ እየተጠቀመ ያለው ‹‹ሸር ኢትዮጵያ›› (‘ሸር’ በእንግሊዝኛ መሆኑን ልብ ይበሉልኝ) ሲሆን፣ ከሱ የተረፈውንም ሌሎች ተቀብለው እየተጠቀሙት ይገኛሉ፡፡ ካለፈው ዓመት በፊት ወደ ሐይቅ ይገባ የነበረውም የወንዙ ተፋሰስ በሚለቀቀው ኬሚካል የተበላሸ ነበር፡፡ አሁን ከነጭራሹ ያም ቀርቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የእነዚህ ወንዞች ግብር የራቀው ይህ ሐይቅ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ገደማ ለሶዳ አሽ ፋብሪካ ያለስስት ሀብቱን እየሰጠ ነው፡፡ በተለያየ መጠን በዙሪያው ለተቋቋሙ እርሻዎች መስኖ ያለማል፣ ለአካባቢው የቤት እንስሳትም ትሩፋቱን ቀጥሏል፣ አሁንም እንጥፍጣፊውን ልሰን ካልጨረስን ያሉት ከጎኑ አሉ፡፡ ቀደም ሲል ሐይቅ በዓሳ ምርቱ የሚታወቅ የነበረ ሲሆን፣ የዓሳ ዘር የሚባል የጠፋውና ምርቱም የተቋረጠው ከሶዳ አሽ ፋብሪካ መቋቋም ስምንት ዓመት በኋላ ነበር፡፡

ታደሰ ፈታሂ በጥናታቸው ያቀረቡት የሳተላይት ምስል እንደሚያስረዳው፣  አቢጃታ በ1966 ዓ.ም. ገደማ ከነበረው የውኃ ይዞታ ስፋት በ2000 ዓ.ም. ከአንድ መቶ ስኩዌር ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆነውን ይዞታ አጥቷል፡፡ ከ1980 ዓ.ም. እስከ 2000 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ የተከሰተው መቀነስ ሲሰላ ደግሞ ስድሳ ሰባት ስኩዌር ኪሎ ሜትር ያህል ቅነሳ አሳይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የቀረው የውኃ ይዞታ ከፍተኛ ጨዋማነት ያለው በመሆኑና ቀደም ሲል የነበረው ከፍተኛ የአልጌ ሽፋን ጨርሶ በመጥፋቱ ምክንያት ሐይቁ ሕይወት አልባ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ትንሹና ትልቁ ቆልማሚት /Greater and lesser Flamingos/ ማረፊያና መመገቢያ የነበረው ይህ ሐይቅ፣ አሁን እንደ ስባሪ የፊት መስታወት የሚመለከትበትና የሚመለከተው አጥቶ ሰማይ ሰማይ ያያል፡፡  

የአቢጃታ ሐይቅ ገባር የነበሩት ሆራ ቀሎና ቡልቡላ ወንዞች መድረቅ (በትላልቅ የመስኖ እርሻ መጠለፍ ምክንያት) የአቢጃታ ሐይቅን ህልውና ብቻ ሳይሆን ከመነሻቸው እስከ መዳረሻቸው ባለው የወንዙ አካባቢ የሚኖሩትን ማኅበረሰብ ህልውናም ተጋፍቷል፡፡ እኔ የምለው እዚህ አገር ወንዞቻችንን፣ ጅረቶቻችንንና ምንጮቻችንን እንደዚህ በነፍስ ወከፍ እንከፋፈል ካልን ምን ሊደርሰን እንደሚችል አስባችሁታል? እባካችሁ ይህን የንብረት ክፍፍል ነገር እንተወው፡፡ ፍትሐዊ የሆነ የሀብት አጠቃቀም ሲኖር ዘላቂ የሆነ የአረንጓዴ ልማት ግቡን ይመታል፡፡ በአንድም በሌላም መንገድ ሁላችንም የቆምነው ለዚህ እንደሆነ አምናለሁ፡፡   

የሆራ ቀሎና ቡልቡላ ተፋሰስ አካባቢ ኗሪዎች በወንዞቹ መድረቅ ምክንያት እየደረሰባቸው ከሚገኙት ችግሮች መካከል፣ አንድ፡- በቁጥቁጥ ይጠቀሙት የነበረው የወንዝ ውኃ በመድረቁ ወደ ሰማይ አንጋጠው ለእርሻቸው ወቅትን መጠበቅ ይዘዋል፡፡ ሁለት፡- ከብቶቻቸውን በአቅራቢያቸው ማጠጣት ባለመቻላቸው ርቀው በመጓዝ ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገዋል፤ እንዲያውም አብዛኞቹ ወደ ሐይቆቹ በመሰማራት ሌላ ያልተገባ ጥፋት ማጥፋቱን ቀጥለዋል፡፡ ሦስት፡- የአቢጃታ ሐይቅ የውኃ ይዞታ የነበረው ቦታ ሙሉ በሙሉ በመራቆቱ ምክንያት ከፍተኛ አቧራ አካባቢውን በየጊዜው ስለሚሸፍነው ለጤና ችግር ተዳርገዋል፡፡ እነዚህ ችግሮች በአጭር ጊዜ እየተስተዋሉ ያሉ የአካባቢው መራቆት ያስከተላቸው ሲሆኑ፣ ይህ ሁኔታ በዚህ መልኩ ከቀጠለና የአቢጃታን ሐይቅ ማዳን ካልተቻለ ሁለንተናዊ ከሆነ የአየር ንብረት መለወጥ ሳንካ ባሻግር በአካባቢው ኗሪዎች ላይ ሊደርስ የሚችለው ችግር እጅግ ከፍተኛና አጠቃላይ ህልውናቸውን የሚጋፋ ሊሆን እንደሚችል አያጠያይቅም፡፡

ኢትዮጵያ በያዘችው የሽግግር ዕቅድ የአረንጓዴ ልማት ዓቢይ ጉዳይ ሲሆን፣ በዕቅዱ መሳካትም ከካርበን ልቀት የፀዳች መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ለመሆን የታለመው ግብ ይሳከ ዘንድ ዛፍ መትከል ብቻውን በቂ አለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ፓርኮችም ከያዟቸው ብዝኃ ሕይወት ሀብት አንፃር ለዕቅዱ መሳካት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ ከኢኮኖሚ ፋይዳው አንፃር እንኳ ብንመለከተው የአቢጃታ ሻላ ሐይቆች ብሔራዊ ፓርክ ተፈጥሯዊ ይዘቱን ጠብቆ በዓመት የሚያስገኘው ገቢ ሲሰላ ከ15.9 እስከ 308.5 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ነው፡፡ ዘላቂ የሚለው ቃል ከቃል የዘለለ ትርጉም ካልሰጠነው ልማታችንም ይህንን አቅጣጫ ካልተከተለ የምናጣው የተፈጥሮ ሀብታችንን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ህልውናችንንም ጭምር ነው፡፡ እናም ስለ አቢጃታ፣ በሞቱ እጃችሁን የሰደዳችሁ ሁሉ ክርክሩን አሊያም ዝምታውን ትታችሁ ጊዜ ሳትሰጡ ለአንድ ዓይነት እልባት ዛሬውኑ ተነሱ፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው solwors@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

          

       

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

Trending Articles