አጥሩ የት አለ?
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት፣ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ባረፉ በአራት ዓመታቸው፣ በመካነ መቃብራቸው ላይ የቆመው ሐውልት፣ ሚያዝያ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. መመረቁ ይታወሳል፡፡ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አፀድ ውስጥ የሚገኘው ሐውልታቸው በተመረቀበት ጊዜ፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዮናስ ደስታ፣ የሐውልቱ አጥር ለምረቃው ሲባል አለመደረጉንና ከሰዓት በኋላ ወይም በቀጣዩ ቀን እንደሚተከል ተናግረው ነበር፡፡ ቃላቸው ሳይፈጸም 43 ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ በታላቁ የስፖርት ሰው፣ ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ ሥርዓተ ቀብር ላይ የተገኙ ሐዘንተኞች፣ ‹‹የኚህ የአፈወርቅ ተክሌ ሐውልት እንደ ሌሎች አጥር የለውም እንዴ? ወይስ ተነስቶ ነው?›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ አጥሩም እንደ ሐውልቱ ዘመኑን ይቆጥር ይሆን?
(ፎቶ በመስፍን ሰሎሞን)
ኑ ግቡ…
ሕይወት አያልቅባት…
እልፍኟ ሰፊ ነው
ማእዷ ብዙ ነው፤
ሁሉን አቅርባለች…
ውስጧን ለጎበኘው፤
እምነትና ስርቆት
እጦትና ድሎት
ምስጋናና ስድብ
ዳንስና ድብድብ፣
ሰላም…አምባጓሮ
የምስራች…ሮሮ
ጥላቻና ፍቅር
እፎይታ…ግርግር፣
ለቅሶና ሙዚቃ
እልልታና ሲቃ
ተንኮል ሐቀኝነት
ድጋፍ.. ምቀኝነት
ጭንቀት… ፈንጠዝያ
ነፃነት.. ዘብጥያ፣
ሁሉን አሰባጥራ
ብፌ አርጋ ደርድራ፣
እልፍኟን ክፍት አድርጋ…
ደጃፏ ቆማለች፤
‹‹ብሉልኝ ጠጡልኝ…
ኑ ግቡ›› ትላለች፤
ጥሪዋን አድምጦ…
ደጇ ሰው ሰፈረ፤
የሚገባው ገባ…
ያልገባው ከሰረ፡፡
- ዶ/ር ኤልያስ ሳሙኤል ማቴዎስ፣ ‹‹ከርከሬሻ›› (2008)
* * *
ኔዘርላንድስ እስረኛ አልባ የሆኑ እስር ቤቶችን የስደተኛ መጠለያ አደረገች
በኔዘርላንድ የወንጀል ድርጊት መቀነስን ተከትሎ እስር ቤቶች ባዶ እየሆኑ ሲሆን፣ የአገሪቱ መንግሥትም ባዶ እስር ቤቶችን ለስደተኞች መጠለያ ማድረግ ጀምሯል፡፡
ናሽናል ጂኦግራፊ በድረገጹ እንዳሰፈረው፣ ኔዘርላንድስ በዓረብ አገሮች ተከስቶ የነበረውንና አሁንም ያልተቋጨውን አብዮት ተከተሎና ከሌሎች አገሮች የሚሰደዱትን ጨምሮ 50 ሺሕ የሚደርሱ ስደተኞችንና የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በ2015 ተቀብላለች፡፡
እንደዘገባው ከሆነ፣ በኔዘርላንድስ ወንጀልን ለመከላከል የተቀመጡ ሕጐችና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ለወንጀል መመናመን ያበረከቱት አስተዋጽኦ እስር ቤቶች ባዶ እንዲሆኑ ረድቷል፡፡ ይህም ስደተኞች ሳይጉላሉ የተሟላ ቁሳቁስ ባሏቸው እስር ቤቶች ውስጥ እንዲኖሩ ዕድል ፈጥሯል፡፡
በእስር ቤቱ እንዲጠለሉ ዕድል የተሰጣቸው ስደተኞች በፈለጉት ሰዓት ከእስር ቤቱ መውጣትና መግባት ይችላሉ፡፡ ተቀጥረው መሥራት የማይፈቀድላቸው ሲሆን፣ ወደፊት በኔዘርላንድስ ለሚኖራቸው ሕይወት ወሳኝ የሆኑትን የደች ቋንቋና ብስክሌት መንዳት ይማራሉ፡፡
አሶሽየትድ ፕሬስ አንዳንድ በእስር ቤቱ የሚገኙ ስደተኞችን አነጋግሮ እንደዘገበው፣ ስደተኞች በመጠለያ ውስጥ ሥጋት ሳይገባቸው እየኖሩ መሆናቸውን ወደውታል፡፡
በእስር ቤቱ ስፖርታዊ ጨዋታዎች የሚደረጉባቸው ሥፍራዎችን ጨምሮ፣ በአውሮፓ ደረጃ መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጐቶች ሁሉ ተሟልተው እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡
* * *
የተናገሩትን ውሸት ያለማስታወስ ምስጢር
በሕይወት ዘመን በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ውሸት መናገር ያጋጥማል፡፡ በኢትዮጵያ ‹‹ዋሽቶ ማስታረቅ›› የሚባል ብሂልም አለ፡፡
ከታዳጊነት ዕድሜ ጀምሮ በክፍል ውስጥ ፈተና በመኮራረጅ፣ የቤት ሥራን የራስ አስመስሎ ከሌላ ተማሪዎች መገልበጥ፣ እንዲሁም ለትዳር አጋር ወይም ለጓደኛ ታማኝ አለመሆንም፣ ምንም ዓይነት ምክንያት ይኑራቸው ከውሸት ይመደባሉ፡፡ መንግሥታትም ሕዝባቸውን የሚዋሹበት ሁኔታ አለ፡፡
ውሸት እንዳለ ሆኖ፣ አንድ ሰው ውሸት ከተናገረ በኋላ የሚሰማው ስሜትና ያንን ውሸት ደግሞ የመናገር ወይም የማስታወስ አቅሙ ምን ያህል ነው የሚለው እንደየሰዉ የተለያየ ቢሆንም፣ በአሜሪካ የሚገኙ ሳይንቲስቶች በጥናት ያገኙትን በ‹‹ናሽናል አካዴሚ ኦፍ ሳይንስ ፕሮሲዲንግ›› ላይ አሳትመዋል፡፡
እንደ ግኝቱ ከሆነ፣ ውሸት የሚናገሩ ግለሰቦች አንዴ የተናገሩትን ውሸት በሌላ ጊዜ ራሱን ደግመው መናገር ወይም መፈጸም አይችሉም፡፡ ምንም እንኳን በጥንቃቄ የሚዋሹ ሰዎች ቢኖሩም፣ ጥናቱ ከተካሄደባቸው ሰዎች አብዛኞቹ ቀድመው የተናገሩትን ወይም የፈጸሙትን ውሸት በሌላ ጊዜ አላስታወሱትም፡፡ ይህም አዕምሮ በአብዛኛው መዝግቦ የሚይዘው የሰውን መልካሙን ወይም ውስጡ የሚያውቀውን እውነት መሆኑንና ውሸት አንዴ ከተፈጸመ በኋላ በዋሸው ሰው ዘንድ እየተረሳ እንደሚሄድ ያሳያል፡፡ አዕምሮም ከውሸት ይልቅ እውነትን ይዞ የመቆየት አቅሙም ይበረታል፡፡
* * *
የ100 ዓመቷ አዛውንት የ100 ሜትር ሩጫ ሪከርድ አስመዘገቡ
በደቡብ ካሮሊና ነዋሪ የሆኑት የ100 ዓመቷ አዛውንት የ100 ሜትር ሩጫ በ46.7 ሰከንድ ሮጠው በማጠናቀቅ በእሳቸው ዕድሜ ቀድሞ የተመዘገበውን አንድ ደቂቃ ከ16 ሰከንድ ሰበሩ፡፡
ፎክስ ካሮሊና እንደዘገበው፣ መምህርት የነበሩት ኤላ ኮልበርት ውድድሩን ያደረጉት፣ ‹‹ሚድል ስኩል›› ውስጥ ሲሆን፣ ውጤታቸውም ተረጋግጦ በጊነስ የሚሰፍርበትን ጊዜ እየተጠባበቁ ነው፡፡
ለ36 ዓመታት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት መምህርት ጡረተኛዋ ኮልበርት፣ ‹‹ያስመዘገብኩት ውጤት ተማሪዎች ከሠሩ ውጤት እንደሚያገኙ እንዲገነዘቡ ያበረታታል፤›› ብለዋል፡፡
ኮልበርት 100ኛ ዓመታቸውን ያከበሩት ግንቦት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ነበር፡፡
