የ74 ዓመቱ ህንዳዊ አዛውንት ፓርካሽ ሪሺ የ366 አገሮችን፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማትን ሰንደቅ ዓላማዎችና የመሪዎች ምስልን በመነቀስ የዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ስማቸውን ማስፈራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ አዛውንቱ ከ20 በላይ ሪከርዶችን መስበራቸውን የሚናገሩ ሲሆን በአጠቃላይ ሰውነታቸው ላይ ያለው ንቅሳት (ታቶ) 500 ይሆናል፡፡ 500 የመጠጥ ስትሮዎችን እንዲሁም 50 የሚበሩ ሻማዎችን በአፋቸው ለመያዝ ያስችላቸው ዘንድ ጥርሳቸውን በሙሉ አስወልቀዋል፡፡ ምንም እንኳ በሰውነታቸው ላይ ያኖሩት ንቅሳት ከ500 በላይ ቢሆንም፣ ከባዱ ነገር ግን በርካታ ስትሮዎችን ከአፋቸው ማኖር እንደሆነ ራሳቸውን ጊነስ ሪሺ እያሉ የሚጠሩት አዛውንት ይናገራሉ፡፡ ‹‹496 ስትሮዎችን በአንድ ጊዜ በአፌ ይዣለሁ፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ሁሉንም ጥርሶቼን ማስወገድ ነበረብኝ፤›› በማለት ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡ ከሰንደቅ ዓላማዎች በተጨማሪ አዛውንቱ፣ የህንዱን ጠቅላይ ሚኒስትርና የባራክ ኦባማን፣ የንግሥት ኤልሳቤጥንና የማህተመ ጋንዲን ምስሎች ተነቅሰዋል፡፡ አሁንም የሌሎች የዓለም መሪዎችን ምስል እንደሚጨምሩ አሳውቀዋል፡፡
አንድ ቀን
አንድ ቀን አድጌ አንድ ቀን ተምሬ
አንድ ቀን ሠርቼ አንድ ቀን ከብሬ፤
አንድ ቀን ወድጄ አንድ ቀን አግብቼ
አንድ ቀን ወልጄ አንድ ቀን አርጅቼ፤
አንድ ቀን! አንድ ቀን! አንድ ቀን አርፋለሁ
እያልኩ አንድ ቀኔን ስናፍቃት አለሁ፡፡
ነገር ግን ውሏ’ድሮ ዘግይቶ ሲገባኝ
ቀኔን መሸኘቴን አንድ ቀን እያልኩኝ፤
አልገባኝም እንጂ ሁሌም የምመኘው
ለካስ አንድ ቀኔ ሕይወቴ ዛሬ ነው፡፡
መላኩ ደምለው፣ ‹‹ብልጭታ›› (2008)
* * *
የቆላ አገር በጊዜ መከራ መሥሪያ ሥራ
በአገራችን ኢትዮጵያ በ1928 ዓ.ም. በጥንታዊ ጠላቷ በተወረረች ጊዜ የግርማዊ ንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን አርአያ በመከተልና ለሕዝባቸውም በየጊዜው በዲስኩር የገለጹትን መልካም ምክርና ትዕዛዝ መሠረት በማድረግ የአርበኞች ማኅበር በየስፍራው ተመሠረተ፡፡
ኢትዮጵያ ከሦስት ሺሕ ዘመን በፊት የነበረች ሥርወ መንግሥት ስለሆነች ከጥንት ጀምራ እስከ ዛሬም በጀግኖቿና በንጉሠ ነገሥቷ እየተመካች፤ በኮረብታዋና በበረሃዋ እየኮራች ትኖራለች፡፡ የሚመጣበትን ማናቸውንም ጠላት ባላት መሣሪያ በጀግኖች ደፋርነት እየመከተች የምትኖር ነች እንጂ ያልሠለጠነች ወይም አሠልጣኝ የሚያሻት አለመሆኗን ለማስረዳት ጀግኖቿም በሰፊው ሰዓት ያደረጉት ተጋድሎ የሚያስረዳ ሆኗል፡፡ በእነሱም ምንም እንኳ መከራ ቢበዛባቸው በተፈጥሮዋቸው የአደጋ ችሎታ ያላቸው ብርድ ትኩሳት ረሃብ፣ ውኃ ጥም፣ በሽታ፣ ጦር፣ የማይፈሩ ስለሆኑ ጠላትን በድፍረት ይቃወሙት ጀመር፡፡
አርበኞች ወደ ጦር ሜዳ የተሰማሩት ከጥንት ተያይዞ ዘር በዘር እየተቀዳ በሚተላለፍና ከአባቶቻቸው ባገኙት ጀግንነት ነው እንጂ በስብከት ወይም በጭቆና መሰቀቅ የሸሹ አልነበሩም፡፡ ጠላት የሚወጋቸውም በጃቸው ባለ መሣሪያ ዓይነት ሳይሆን በአውሮፕላን አደጋ በቦምብ በመርዝ በብርቱ ጭከና ነበረ፡፡
ኢጣልያኖች ባላገሩን ወንዱን፣ ሴቱን እየገደሉ ሕፃኑን እየሰለቡ፣ ቤቱን፣ ሰብሉን እያቃጠሉ፣ ከብቱን እያረዱ የአርበኝነት ሥራ ከሀገር ላይ እንዲጠፋ ለማድረግ ምንም እንኳ ቢያስብ ከሞት የተረፈው ባላገር ከብት ካለበት አገር ከብት እየገዛ፤ መግዣም ያጣ በያረሁ በዶማ እየቆፈረ ራሱ ረሃቡን ታግሶ በጦር ውስጥ የሚውሉት ቢበሉት ይሻላል በማለት ስንቅ እያቀበለ የታመመውን በቤቱ እየደበቀ ያስታምም ጀመረ የሞተውንም አርበኛ ምንም እንኳ ኢጣሊያ በቤተ ክርስቲያን እንዳይቀበር ቢያውጅ ቀሳውስትም ቢገዝቱ አዋጁን አፍርሶ በክርስቲያን ሕግ እየቀበረ ከጥንት ጀምሮ ከአባቶቹ በክብር ለተቀበላት ነፃነቱ ይጋደልላት ጀመረ፡፡
አባቶቻችን በግራኝ ዘመን ዕረፍት ያገኙት ከ15 ዓመት በኋላ አይደለምን? ይህ ሁሉ ቤተክርስቲያን የተሠራና ይህ ሁሉ ሰው የበዛስ ከዚያ ወዲህ አይደለምን? ከአባቶቻችን እንደሰማነው መቼውንም ቢሆን የቆላ አገር በመከራ ጊዜ ሥራ መሥሪያ ነው፡፡
- ከ1 ኢትዮጵያዊ ተጻፈ “የአርበኞች ትግል ከፋሺስት ጋር” (በ1936 ዓ.ም.)
* * *
ራሱን ለማጥፋት ለየት ያለ ሙከራ ያደረገው ሰው
በቺሊ ዋና ከተማ የሚገኝ አንድ የእንስሳት ዙ ቅዳሜ ዕለት ሁለት አንበሶችን ለመግደል ተገደደ፡፡ አንበሶቹን ለመግደል ምክንያት የሆነው ነገር ከወትሮው ለየት የሚል ይመስላል፡፡ ራሱን ማጥፋት የፈለገ አንድ ወጣት ከአንበሶቹ ክፍል በመግባቱ የሰውየውን ሕይወት ለማዳን አንበሶቹን መግደል ግድ እንደነበር የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ የአፍሪካ አንበሶች ካሉበት የሽቦ አጥር ዘሎ የገባውን ሰው ወዲያው ሁለቱ አንበሶች ያጠቁት ጀመር፡፡ መጀመሪያ በተወርዋሪ ማደንዘዣ አንበሶቹን ለማቆም ቢሞክርም አንበሶቹ በዚህ ሊቆሙ አልቻሉም፡፡ ስለዚህም መግደል ብቸኛው አማራጭ ሆነ፡፡ አንበሶቹ በመጠለያው ለ20 ዓመታት ያህል የኖሩ ሲሆን ዕድሜው በ20ዎቹ ውስጥ የሚገኘውና ራሱን በተጠቀሰው መልክ ለመግደል የሞከረው ወጣት በከባድ ጉዳት ወደ ሆስፒታል ተወስዷል፡፡
* * *
ቀይ ወፎች በቀላሉ ጥንዳቸውን ያገኛሉ
በአሜሪካ በሴንት ሉዊዝ ዩኒቨርሲቲ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው ቀይ ቀለም ያላቸው ወንድ ወፎች በቀላሉ ተጓዳኝ (አጋር) ያገኛሉ፡፡ አጋር የማግኘት ዕድላቸውም ሌላ ቀለም ካላቸው ወፎች ጋር ሲነፃፀር ሰፊ ነው፡፡ ጥናቱ እንደሚያመለክተው ቀይነት በብዙ የወፍ ዝርያ ጥንዶች እንደ ጥራት የሚታይ ነገር ነው፡፡ በሌላ በኩል የተወሰኑ ወፎች እንደ ካናሪስና ዜብራ ፊንችስ ያሉ ቢጫ ቀለም የሚሰጣቸውን እንደ ጥሬ፣ ፍራፍሬና ነፍሳት ይመገባሉ፡፡ በተጨማሪም ቀይ ቀለምን በመለየትና ቀይ ቀለም በመያዝ ረገድም የተለየ ነገር ያላቸው የወፍ ዝርያዎች እንዳሉ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡
* * *
