በዳግም አሳምነው ገብረወልድ
የዚህ ጽሑፍ መነሻ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ‹‹የተናገሩት›› በሚል ‹‹አዲስ ልሳን›› የተባለ መንግሥታዊ ጋዜጣ ያወጣው ዜና ነው፡፡ ርዕሱ ‹‹መንግሥት የግሉን ሚዲያ ተሳትፎ ለማሳደግ ይሠራል›› የሚል ሲሆን፣ አገሪቱ ያላትን የግል ሚዲያዎች ተደራሽነትና ተሳትፎ በማስፋት ጥረቱን በማሳደግና ተወዳዳሪነቱን በማጠናከር ረገድ ያለውን የአቅም ክፍተት በመድፈን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ሚና ያሳድጋል ይላል፡፡ በነሐሴ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. የጋዜጣው እትም፡፡
ዜናው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ባዘጋጀው አንድ ዓውደ ጥናት ላይ ተመሥርቶ የተሠራ ሲሆን፣ በመድረኩ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች መቅረባቸውንም አውስቷል፡፡ ይሁንና ‹‹ከአንድ ሺሕ በላይ ከተመዘገቡ የኅትመት ሚዲያዎች በሥርጭት ላይ ያሉት 18 ጋዜጦችና 43 መጽሔቶች ብቻ ናቸው›› ከሚል ፀፀት በስተቀር ባለፉት 12 ዓመታት ተደጋግመው የተባሉ ሐሳቦች በመድረኩ መሰንዘራቸውን የሚያመለክት ነው፡፡
በዚህ ጽሑፍ እንደመከራከሪያ ነጥብ ለማንሳት የምሻው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትም ሆነ የክልል ቢሮዎች ከተቋቋሙ ወዲህ እንኳንስ የግሉ ሚዲያ ሊስፋፋ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንም መዳከማቸውን ነው፡፡ በአንድ በኩል ‹‹ልማታዊ ጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን›› ሚናቸው ተቀላቅሎ የተበራከቱበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በሌላ በኩል የአገሪቱ አንጋፋ የመገናኛ ብዙኃን በአዋቂ ከመመራት ይልቅ በካድሬ፤ በልምድ ከመሥራት ይልቅ በጥራዝ ነጠቆች እየኮሰመኑ ያሉበት ወቅት ላይ በመሆናቸው ነው፡፡
መንግሥት ‹‹የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች›› የተባለውን ተቋም ከፌዴራል እስከ ወረዳ በአዲስ መልክ ሲያደራጅ የተጣሉ ተስፋዎች ነበሩ፡፡ አንደኛው የመንግሥት ሕዝብ ግንኙነት (ማስታወቂያ) ሥራ ከቃል አቀባይነት አልፎ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ድልድይ መሆን እንዲችል ነበር፡፡ ይህ ፍፁም ላለመሳካቱ አሁን የተያዘው የሕዝቡ ጥያቄ ሕዝብ ግንኙነቱ ከሚያነበንበው ፕሮፖጋንዳ ጋር ያለው ተቃርኖ ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ›› መሆኑ አመላካች ነው፡፡
ሌላኛውና የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ የመሥሪያ ቤቱ መቋቋም የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት ሕጉ በተሟላ መንገድ እንዲተገበር ነበር፡፡ ይህም የዜጎችን የሐሳብ ነፃነት ይበልጥ በማረጋገጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲያብብ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑ ይታመናል፡፡ በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው እውነት ግን ሚኒስቴሩ አራት የሥራ ኃላፊዎችም ተቀያይረውበት ስንዝር የለውጥ ምልክት አለመታየቱን ነው፡፡ ይህን መሠረታዊ ክፍተት ደግሞ መንግሥት ራሱ ከሚመራቸውና ከሚያስተዳድራቸው ‹‹የሕዝብ›› ሚዲያዎች መዳከም ጋር አስተሳስሮ መመልከት ያስፈልጋል፡፡
የሕትመት ሚዲያው መንገታገት
በክልል መንግሥታት ከሚታተሙት የፓርቲና የመንግሥት ልሳኖች ባሻገር በፌደራል ደረጃ የኅትመት መገናኛ ብዙኃን ሥራ የሚሠራ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተባለ ተቋም አለ፡፡ ይህ አንጋፋ መሥሪያ ቤት አዲስ ዘመን፣ ኢትዮጵያን ሔራልድ፣ ዘመን መጽሔት፣ በሬሳና አልዓለም የተባሉ ኅትመቶችን በተለያዩ ቋንቋዎች እያዘጋጀ ያሠራጫል፡፡ በክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን እየታተሙ የሚሠራጩ ጋዜጦች (ትግራይ - መቓልህ ትግራይ፤ ኦሮሚያ፣ አማራ በኩር፣ ደቡብ - ንጋት፣ አዲስ አበባ - አዲስ ልሳን) የተባሉ የኅትመት ውጤቶች አሉ፡፡
እነዚህና ሌሎች ያልተጠቀሱ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ ከ25 በላይ የኅትመት ውጤቶች የየራሳቸው ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ቢኖራቸውም፣ ሕገ መንግሥቱና አዋጅ 590/2000 ‹‹የፕሬስ ነፃነትን›› ቢያስተጋቡም፣ በጥብቅ ‹‹የኤዲቶሪያል ኮሚቴ አሠራር›› የተከረቸሙ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ራሳቸው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መሥሪያ ቤቶች በሳምንታዊ አቅጣጫ፣ በቦርድ ሰብሳቢነትና ‹‹በአቅም ግንባታ ሥልጠና›› ስም እንዳይላወሱ ስላደረጓቸው ነው፡፡ የእጅ አዙር ቅድመ ምርመራ ይሉሃል ይህንኑ ነው፡፡
ለረዥም ጊዜ በሙያው ውስጥና በአንጋፋ የኅትመት ተቋማት የሠሩ ጋዜጠኞች እንደሚናገሩት፣ መንግሥት በአገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳይ የሚዲያ ትኩረት አቅጣጫ መስጠቱ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ‹‹ይህን ጻፍ፣ ያንን አትጻፍ፣ እገሌ አባባሉ በሚዲያው እንዳይስተናገድ ወይም ሕዝቡ የሚነጋገርበትን ጉዳይ አትንካው…›› እያለ የሚገድብ መንግሥታዊ አካል ካለ ሞቶ የተቀበረው ቅድመ ምርመራ ተመልሶ ስለመምጣቱ ዋስትና የለም ባዮች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የኅትመት መገናኛ ብዙኃን አንዳንድ ሙያተኞች በግል ጥረት የሚያሳዩትን የሐሳብ ነፃነትና መንግሥታዊ ሒስ ጭምር ሊገፉበት እንደማይችሉ ዕሙን ነው፡፡ (እዚህ ላይ ዶ/ር ጀማል መሐመድ ‹‹ደንባራዎቹ መገናኛ ብዙኃን›› ሲሉ በጥልቀት የታዘቡትን ጽሑፍ በነሐሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ሪፖርተር ጋዜጣ መመልከት ይገባል፡፡
ክቡር ሚኒስትርና የቀድሞው የዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህሩ እንደሚያውቁት ጋዜጠኝነት የህሊና ነፃነትና ሚዛናዊነትን ግድ የሚል ሙያ ነው፡፡ በዚህ ረገድ እውን አሁን ባሉት መንግሥታዊ የመገናኛ ብዙኃን ከፓርቲ አባልነት ውጪ የሆኑ ኤዲተሮችና አዘጋጆችን ማግኘት ይቻላል?! ታዲያ በየትኛው መርህ (በፓርቲ አባልነቱ ወይስ በጋዜጠኝነቱ) እየተመሩ ነው ለሐሳብ ብዝኃነት ልዕልና በመሥራት ዴሞክራሲውን የሚያሳድጉት!? መፈተሽ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡
በአገሪቱ ያሉት ዋና ዋናዎቹ የመንግሥት የኅትመት መገናኛ ብዙኃን አይደለም በደርግ ዘመን በንጉሡም ጊዜ የነበሩ ናቸው፡፡ ልዩነቱ ያኔ መነግሥት በጀት መድቦ እንዲታተሙ ያደርግ ነበር፡፡ አሁን ግን በራሳቸው የማስታወቂያ ገቢ እየተንገዳገዱ (ያለምንም የመንግሥት በጀት ድጎማ) መታተማቸው ነው፡፡ በይዘት ረገድ የታዩ እንደሆነም ትናንትም ሆነ ዛሬ ‹‹የየሥርዓቶቹ አገልጋዮች ናቸው›› በሚል አንባቢው ደምድሞ ቁጭ ካለ ከራርሟል፡፡ የልማት ጋዜጠኝነትን ሸርፎ መጓዝ ያመጣው ጣጣ ይኼ ነው፡፡
ሌላው አሳዛኝ እውነታ ከ75 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያላቸው ጋዜጦች ስርጭት አሁንም ከአሥር ሺሕ ያለመዝለሉ ነው፡፡ (እንዲያውም ደርግ በግዳጅ ስርጭትም እስከ 35 ሺሕ በማድረሱ ቢያንስ ለንባብ ባህልና ለሥነ ጽሑፍ ዕድገት የተጫወቱት ሚና የሚናቅ አልነበረም፡፡) በባለሙያ ረገድም ብዙዎቹ የተባ ብዕር ያላቸውና እያረገፉ በድዳቸው ቀርተዋል፡፡ ጥቂት ስሜትና ሙያ ያላቸው ታታሪ ጋዜጠኞች የሉም ባይባልም ኢንዱስትሪው ከሚፈልገው ነፃነት፣ ብርቱ የአመራር ድጋፍ፣ በቂ ክፍያና ጥቅማ ጥቅም አንፃር እርካታ በማጣት ቀለማቸው እየደረቀ ሄዷል፡፡ ሥር ነቀሉን ለውጥ ለማምጣትም የሚቻላቸው አይደሉም፡፡
የብሮድካስቱ ሚዲያ ፈር እየለቀቀ መሄድ
አንድ ለእናቱ የነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአሁኑ ‹‹ኢቢሲ›› ከመሪ ቃሉ አንስቶ ለብዝኃነት የቆመ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ይሁንና ለቋንቋ፣ ብሔርና ለጾታ ብዝኃነት የሚጨነቀውን ያህል (ያውም ከተጨነቀ) ለአመለካከት ብዝኃነት ደንታም የለውም፡፡ በዚህች አገር ውስጥ በርካታ አስተሳሰቦች እንደሚራመዱ ብቻ ሳይሆን ጫፍና ጫፍ ላይ ቆመው እንደሚካረሩ ቢታወቅም የምርጫ ሰሞን የሚያደርገውን ሙከራ ያህል እንኳን ፎረም አይፈጥርም፤ አጀንዳ አይቀርፅም፤ ከመንግሥት (የገዢው ፓርቲ) አቋም የተለየ ሐሳብ ማስተላለፉን (የሐሳብ ሙግት ማድረግን) ‹‹እንደ ወንጀል›› ቆጥሮ ዓይኑን ከጨፈነም ውሎ አድሯል፡፡ ይኼ ለዴሞክራሲ ተግባር ደግሞ በሕግ ባይደገፍም በኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አቅጣጫ እንደተቆለፈ አለመጠርጠር የዋህነት ነው፡፡
በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ የሬዲዮ ጣቢያዎች አካሄድ ከቴሌቪዥን የመሻል ነገር ቢኖረውም ተመሳሳይ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በሕዝቡ ውስጥ ለዓመታት ሲቦካ፣ ሲጋገር የነበረውን የሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት አጀንዳ በቆሪጥ ሲመለከቱ ከርመው አሁን ላይ በመንግሥት (ፓርቲ) ውሳኔ ‹‹ሙሰኛ መጠየቅ ሲጀምር›› ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት አሳፋሪ ነው፡፡
የብሮድካስት ሚዲያ የሚባሉት የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎች አንድ ጊዜ መሠረተ ልማቱ ከተዘረጋላቸው እንደ ኅትመት ሚዲያ ያለ የኅትመት ወጪ አያስጨንቃቸውም፡፡ ይሁንና ሕዝቡ ውስጥ በጥልቀት ደርሰው ተፅዕኖ ለመፍጠር የብዙኃኑን ሐሳብ የሚያካትት፣ በአንፃሩም ቢሆን ሚዛናዊና ገለልተኛ አካሄድ መከተል አለባቸው፡፡ አሁን ከተጣባቸው የአንድ ወገን መረጃና የስኬት ዘገባ (Success Story) ማማ ላይ ወርደው ወደ አዝመራው ውስጥ ገብተው ማረምና መድከም ካልቻሉም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ጠብታ አስተዋጽኦ ሊኖራቸው አይችልም (እዚህም ላይ የዶ/ር ጀማልን ጽሑፍ ያጤኑዋል!)፡፡
የብሮድካስት ሚዲያው ፈሩን እየለቀቀ ነው የሚባለው ግን ሕገ መንግሥታዊውን የሐሳብ ነፃነት በመገደቡ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም የማንነት፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የአመለካከት… ብዝኃነት በታጨቀበት አገር ውስጥ፤ ድህነቱ እንደ መርግ የከበደው ዜጋ ቁጥር በሚያኩራራ ደረጃ ገና ሳይራገፍ ለውጭው ዓለም ስፖርትና መዝናኛ እንዲሁም ለቧልትና እንቶ ፈንቶ ወግ የመደቡት የአየር ሰዓት በመብዛቱ ነው፡፡ (በኢቢሲ፣ ሬዲዮ ፋናና አዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን ለመዝናኛ የተሸጡ የአየር ሰዓቶችን ያስታውሷል፡፡)
በመሠረቱ በኢትዮጵያ የሚዲያ ምህዳር ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጎልቶ እየታየ ያለው ብቃት ያለው ሙያተኛ ረሃብ ቀላል ችግር አይደለም፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እጃቸውን የፈቱና ‹‹ዕውቅና›› የሸመቱት ሁሉ ለምን የብሮድካስቱን ሚዲያ እየተዉ ወጡ? በእንዴት ያለ ፍጥነት የግል አየር ሰዓት ለመክፈትስ ቻሉ፣ ብሔራዊውን ሚዲያ ተመሳሳይ አመለካከትና እምነት በያዙ ሙያተኞች መሙላቱስ ጉዳቱና ጥቅሙ ምንድን ነው? ብሎ የሚመረምር ያለ አይመስልም፡፡ እውነታው ግን ኢትዮጵያን መምሰል ያለባቸውና በሙያ ብቃትና ግልፅ አሠራር ሊመሩ የሚገባቸው የሚዲያ ተቋማት ሳይቀሩ ያልሆነ መልክ እየያዙ መምጣታቸውን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡
የሚዲያው አመራር ምን ያህል ተራማጅ ነው?
በአገራችን የመገናኛ ብዙኃን ታሪክ ውስጥ በስም ተጠቃሽ የሥራ ኃላፊዎች፣ ኤዲተሮችና ጋዜጠኞች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ብዙም በማያፈናፍኑት የፖለቲካ ሥርዓቶች ሐሳባቸውን በግልጽም፣ በገደምዳሜም የሚያወጡ፣ የሕዝቡን ጥያቄ ለመንግሥት ለማድረስ የሚጥሩም ነበሩ፡፡ (ከዚህም በላይ በአገሪቱ ሥነ ጽሑፍ ዕድገት ውስጥ ጉምቱ አሻራ ያሳረፉ ጋዜጠኞችና አርታዕያን ዛሬም ድረስ ስማቸው ይጠራል፡፡ (እነ በዓሉ ግርማ፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፣ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ብርሃኑ ዘሪሁን… ከኅትመት ዘርፍ እንዲሁም ከብሮድካስት እነ አሳምነው ገብረወልድ፣ ታምራት አሰፋ፣ ሻምበል ግዛው ዳኜ፣… አፈሩ ይቅለላቸውና ይጠቀሳሉ፡፡) በሕይወት ያሉም ብዙዎችን ማውሳት ይቻል ይሆናል፡፡ እስኪ ከዚህኛው ትውልድ ማንን እንጥቀስ፡፡ በተለይ በመንግሥት ሚዲያው ውስጥ ‹‹ማንን አንቱ እንበል!?›› ብሎ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የጋዜጠኝነት ሙያን ጠንቅቆ አውቆ፣ ሠርቶ ከሚያሠራው ኃላፊና አርታዒ ይልቅ በበረኝነት ታዛዥነት ‹‹ጉብዝናው›› የተመረጠው በርክቷል፡፡ ዓለም የደረሰበትን ሁኔታ ተገንዝቦ፣ የአገሪቱን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ፍላጎት ተረድቶ የሐሳብ ብዝኃነትን ከሚያስተናግደው ይልቅ በቀድሞዎቹ ሥርዓቶች አንጎበር እየተንገዳገደ የሚመራው ብዙ ነው፡፡ ይህን ደግሞ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ጠንቅቆ ከማወቅም በላይ ይገነዘበዋል፡፡ ሊለውጠውም ፍላጎት የለውም፡፡
በመሠረቱ ተራማጅነት (Progressiveness) የሚመዘነው የተለያዩ አዳዲስ አስተሳሰቦችን፣ ጊዜው የሚጠይቀውን ብቃት በመያዝና በመተግበር ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ አገራችንም ሆነች ሕዝቦቿ ከአሥር ዓመታት በፊት በነበሩባት ቁመና ላይ አይደሉም፡፡ የሚዲያ ኢንዱስትሪው ራሱ በማኅበራዊ ድረ ገጾችና እንደ አሸን በሚፈሉ የሳተላይት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በግልጽ እየተፈተነ ነው፡፡ የአገራችን የመንግሥት ሚዲያ አብዛኛው አመራሩ ግን ይህን ‹‹ቻሌንጅ›› ስለመኖሩ ማሰብ አይፈልግም፡፡ ከሙያው ተወዳዳሪነት ይልቅ በስመ ‹‹ካድሬነት›› የተሰጠውን ወንበር እየጠበቀ ካለለውጥ ሕዝቡንም፣ መንግሥትንም እንዳስቀየመና እንዳራራቀ መቀጠል ይሻል፡፡
በፌዴራሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት እየተመደበ ‹‹ድጋፍ›› የሚደረግለት ይኼ ኃይል በየሩብ ዓመቱ እየተገናኘ ሥራውን ይገመግማል፡፡ ኃላፊዎች፣ ዋና አዘጋጆችና መምሪያ ኃላፊዎች ሁሉ በተገኙበት በሚደረገው የጋራ ፎረም ግን ተሞጋግሶ፣ አለባብሶ ከመሄድ ያለፈ ውጤት አላሳየም፡፡ ወይ በጅምላ ይወቀሳል፡፡ አልያም ‹‹የሕዝብ ሚዲያው›› ተብሎ በአንድነት ይመሰገናል፡፡ እንጂ ደካማ፣ ከጠንካራ አይለይም፡፡ ዕውቅና አይሰጥም፤ ምርጥ ተሞክሮ ተለይቶ እንዲሰፋ አይሞከርም፡፡ ታዲያ ይኼ እውነታ እየታወቀ በየትኛው ብርታት ነው ከመንግሥት ሚዲያ አልፎ የግሎቹን ለማጠናከር የሚቻለው!? ያው የተለመደ ቧልት ካልሆነ በስተቀር፡፡
በየትኛውም የሥራ መስክ ቢሆን ሙያተኛውም ሆነ ራሱ ተቋሙ (መሥሪያ ቤቱ) አመራሩን መምሰሉ አይቀርም፡፡ በሚዲያው ዘርፍም ይህ ሐቅ ሲንፀባረቅ እንደሚታይ ሙያተኞች ይናገራሉ፡፡ አንዳንድ በሙያ ብቃት የሚታወቁ የሥራ መሪዎች ሥልጠናና ድጋፍ ከመስጠት አልፈው፣ ጠንካራ ፎረምና ‹‹ዲስኮርስ›› እንዲጀመር አድርገዋል፡፡ አብዛኛው ‹‹የዘልማድ›› የሚዲያ መሪ ግን የመንግሥትና የፓርቲ ሥራን እየደበላለቀ፣ በጎሳና በመንደር ልጅነት እያደራጀ፣ ተላላኪና ካለመርህ የሚታዘዝን እየኮለኮለ ካለውጤት የሚውል ነው፡፡ መጠላለፍ የበዛባቸው የሚዲያ ክፍሎችም ሙያተኛውን አሽቀንጥረው እየገፉት ይገኛሉ፡፡
በመንግሥት የመገናኛ ብዙኃኖች ውስጥ ጎልቶ የሚታየው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግር፣ የአደረጃጀት ጉድለት የሥልጠናና ግንባታ ማነስ ሁሉ የአመራሩ ውድቀት ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡ በሚያሳዝን ደረጃ አንጋፋዎቹ ጋዜጦች የአንድ ግለሰብ ጦማሪ (ብሎገር) ያህል ድረ ገጽና ጎብኝ የላቸውም፡፡ በአንድ የሚዲያ ተቋም ውስጥ አንድ የድረ ገጽ ባለሙያ መረጃ ጭኖ፣ ለአስተያየት መልስ ሰጥቶ፣ ግብረ መልስ ሰብስቦ እንዴት ይቻላል? በአንድ እጅ ከማጨብጨብ አይለይም፡፡ (ዓለም በቴክኖሎጂ ሲገሰግስ ሚዲያው ወደኋላ ይመለስ የተባለ ይመስል ተደጋግሞ የሚታይ ክፍተት አሁንም አለ፡፡ የሬዲዮ ጣቢያ ወይም የቴሌቪዥን መስኮት ይዞ ፖርታል (ድረ ገጽ) አለመኖር ከዚህ ውጭ ምን ሊባል ይችላል!?
‹‹የልማት ጋዜጠኝነት›› በተሸራረፈ መንገድ ተገንዝቦ ዴሞክራሲን ለመገንባት በሚታትር ሕዝብ ውስጥ መተግበር አዳጋችነቱ ግልጽ ሆኗል፡፡ ያውም ኮሙንኬተሩና ጋዜጠኛው ሚናቸው ተቀላቅሎ ሁሉም ዜና ሠሪዎች በሆኑበት፣ ፕሮፓጋንዳውና መሬት ላይ ያለው እውነት በሚጋጭበት፣ የምርመራ ዘገባን አጥብቆ ለመያዝ ባልተቻለበት ሁኔታ የልማት ጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ብቸኛ አማራጭ ‹‹ይሁን!›› መባሉም በጥልቀት ሊፈተሽ የሚገባው ነው፡፡ ካልሆነ ግን የሐሳብ ነፃነትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አደጋ ላይ መውደቃቸው አይቀሬ ነው፡፡ በተጨባጭም እየወደቁ እንደሆነ መታየቱን ተገንዝቦ ዘላቂ መፍትሔ ለማመላከት የሚደፍር አንድም የሚዲያ አመራር፣ የዘርፉ ምሁራን ሙያተኛ አልታየም፡፡ ‹‹ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም››፡፡
እንግዲህ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ነው እንኳንስ ለሰፊዋ ኢትዮጵያ ይቅርና ለራሱ ለኢሕአዴግ (ለመንግሥትም) የሚበጅ አይደለም የሚባለው፡፡ ለተጀመረው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የሕዳሴ ጉዞም ቢሆን አረም ይሆን እንደሁ እንጂ ‹‹ኮምፖስት›› ለመሆን አይቻለውም፡፡
በጥቅሉ ‹‹ማን ላይ ሆነሽ ማንን ታሚያለሽ?›› እንዲሉ፣ ክቡር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትሩ በመንግሥት ሚዲያው ላይ የተንሰራፋውን ችግር ተሸክመው፣ ሌላውን እናድናለን ማለታቸው ነው ፀሐፊውን ኮርኩሮ ብዕር ለመጨበጥ ያነሳሳው፡፡ እናም ይህን ለዘመናት ያልታየ ዘርፍ መንግሥት ፈትሾ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን እንዲያጠናክር የግል ምክር ከመሰንዘር ሌላ ምን ይባላል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
