Quantcast
Channel: ዓለማየሁ ጉጀ
Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

የነገውን ሰው ማነፅ - ይድረስ ለወላጆች !!

$
0
0

በመምህር ሣህሉ ባዬ

የዛሬዋ መጣጥፌ መልዕክቷን የምትጀምረው ባሳለፍነው ዓመት ሕፃናት ጤናማ የሆነ አካል፣ አዕምሮ፣ ስሜትና ማኅበረ ሥነ ልቦና ተላብሰው እንዲያድጉ በማስቻል ረገድ አስፈላጊውን ጥረት ላደረጋችሁ የኅብረተሰብ አባላት እንኳን ለ2010 ዓ.ም. አዲስ ዓመትና አዲሱ የትምህርት ዘመን በሰላም አደረሳችሁ በማለት ነው፡፡

ትምህርት ለአንድ አገር ዕድገት ወሳኝ መሣሪያ መሆኑ ተደጋግሞ ሲገለፅ የቆየ ዕውነታ ነው፡፡ ከዚህ መሠረታዊ ሐሳብ በመነሳት ዘመናዊ ትምህርት በአገራችን ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የዕውቀት ገበታን ለማዘመን በርካታ ጥረቶች ተከናውነዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዘመናዊ ትምህርትን በጥራት ደረጃ ለማዘመን ብዙ የሚቀሩን የቤት ሥራዎች ቢኖሩም ጥረታችን በበጎ መልኩ እየቀጠሉ መምጣታቸው ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ለምሳሌ ትምህርትን ለማስፋፋት የተደረገው ጥረት በመደበኛ ትምህርት ሥርዓተ  ማዕቀፍ ውስጥ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትንና የኢኮኖሚ ዕድገት ፍላጎት የሚጠይቀውን የሠለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት በሚያስችሉ የሦስተኛ ደረጃ ሥልጠናዎች ላይ ያተኮረ መሆኑ መልካም ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ግን ሕፃናት ገና ከመጀመሪያዎቹ የዕድገት ዓመታት ጀምሮ በአካል፣ በአዕምሮ፣ በሕይወት ክህሎትና መልካም ማኅበረ ሥነ ልቦና ታንፀው እንዲያድጉ የወላጆችና መምህራን ትብብርን የማሳደጉ ጥረት ግን ብዙ ትኩረት ያገኘ አይመስልም፡፡ ስለሆነም በመግባባትና በዕቅድ ላይ የተመሠረተ የወላጆችና የመምህራን ትብብር ለነገው ሰው ሁለንተናዊ ዕድገት ምትክ የሌለው አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት የበርካታ አገሮች ተሞክሮ ያሳያል፡፡

በማኅበረሰባቸውና ዜጎቻቸው ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ (ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መደላድል) መፍጠር የቻሉ አገሮች ሕፃናትን ከመነሻው ኮትኩቶ ማሳደግ የነገውን አገር ዛሬ እንደመሥራት የሚቆጠር መሆኑን ስላመኑበት የላቀ ትኩረት በመስጠት ብሔራዊ አጀንዳ አድርገውታል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የወላጆችና መምህራን ጥምረት ትልቁን ድርሻ እንደያዘ በዘርፉ የተከናወኑ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ስለሆነም ወላጆች ለትምህርት ቤቶች ግዙፍ ሀብት መሆናችንን በመገንዘብ ልጆቻችን ስለሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች መረዳት፣ በእንቅስቃሴዎች ውስጥ መሳተፍ፣ ስለ ትምህርት ቤቶቹ መርሐ ግብሮችና ስለሚኖሩን ተሳትፎዎች መጠየቅ ይገባናል፡፡ በዕቅድ ላይ የተመሠረተ የወላጆች ተግባራዊ ተሳትፎና የውይይት መርሐ ግብር በእጅጉ አስፈላጊ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ከተቻለም ሌሎች የቤተሰብ አባላት በውይይቱ ሒደት ቢካፈሉ ጠቀሜታው የተሻለ ይሆናል፡፡ ወላጆች ከልምዳችንና ማኅበራዊ መሠረታችን በመነሳት በተወሰኑ ርዕሶች ላይ ተጋባዥ መምህራን በመሆን ልምዳችንንና ተሞክሯችን ለተማሪዎች ብናካፍል ተጨማሪ ግብዓት ይሆናል፡፡

አንድ ሕፃን መደበኛ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት የነበረው የቤት ውስጥ ተሞክሮ ለቀጣዩ የትምህርት ስኬት ወይም ውድቀት ወሳኝ ምክንያት መሆኑን የትምህርት ሥነ ልቦና ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡ የሕፃኑ የትምህርት ዝግጁነት ማለትም ትምህርት ቤት ገብቶ ለመማር የሚያስችለውን ፍላጎት፣ ክህሎት፣ ጥበብና ዘዴ የመላበሱ ሁኔታ፤ ወይም የችሎታ ውስንነት፣ ምኞት፣ ፍርሃት፣ ድንጋጤ፣ ሐዘንና የስሜት ጉዳት…ወዘተ መጠን በቤት ውስጥ ከነበረው ማኅበራዊ መሠረቶች ወይም ልምዶች ጋር የተቆራኘ ስለመሆኑ የመስኩ ተመራማሪዎች ሮሆቦት ሄስና ቨርጅንያ ሽፕማን በጥናታቸው አረጋግጠዋል፡፡ በመሆኑም ወላጆች የልጆቻቸውን ሁኔታ በትዕግስት ማስተዋል ይጠበቅባቸዋል፡፡

የእያንዳንዱ ሕፃን ዕድገት በእያንዳንዱ የዕድገት ሒደት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሕፃናት በተለያዩ የዕድገት አቅጣጫዎች በአካል፣ በአዕምሮ፣ በማኅበራዊ ሥነ ልቦናና በስሜት ያድጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ሕፃን በአንዱ የዕድገት አቅጣጫ ቀድሞ ሲገኝ በሌላው አቅጣጫ አዝጋሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ይኼ የሚያሳየን ፈጣን የዕድገት ሒደት ማለት በጣም የተሻለ ነው ማለት አለመሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም የሕፃናትን ተፈጥሮ ለመረዳት ማሰተዋልን ይጠይቃል፡፡ በሕፃናት አስተዳደግ ላይ ጥናት ያደረጉት ሚስ አሊኖር ኮሎምበስ፣ አንድ ያልታወቀ ፈላስፋ ስለ ሕፃናት አፈጣጠርና የባሕርይ ልዩነቶች ያሰፈረውን አስተውሎት በሚከተሉት ሥነ ቃሎች አቅርበውልናል፡፡

  • አንዳንድ ሕፃናት እንደ ጋሪ ግፊት ይፈልጋሉ፡፡
  • አንዳንድ ሕፃናት እንደ ታንኳ መቀዘፍ ይፈልጋሉ፡፡
  • አንዳንድ ሕፃናት ፈጣን ስለሆኑ ትኩረት ይሻሉ፡፡
  • አንዳንድ ሕፃናት በአንድ ነገር ላይ ለማተኮር ትዕግስት የላቸውም፡፡
  • አንዳንድ ሕፃናት እንደ ተሳቢ መኪና መጎተትና መሳብን ይሻሉ፡፡
  • አንዳንድ ሕፃናት በነፋስ እንደተሞሉና ለመፈንዳት እንደተዘጋጁ ነገሮች አያያዝ ጥንቃቄ ይሻሉ፡፡
  • አንዳንድ ሕፃናት ዘወትር እምነት የሚጣልባቸው ተባባሪና ተግባቢ ናቸው፡፡

ምንም እንኳን የእያንዳንዱ ሕፃን ባሕርይ የተለየ ቢሆንም ሁሉም ሕፃናት የሚጋሯቸው ተመሳሳይ መሠረታዊ ባሕርያትም አሏቸው፡፡ ለምሳሌ ፍቅር፣ ደኅንነት፣ ጥበቃ፣ ዋስትና፣ መረጋጋት፣ መልካም አመጋገብ፣ ሥርዓት፣ አካላዊ እንቅስቃሴ፣ ከለላ፣ ቁጥጥር፣ ተቀባይነት ወይም ተሰሚነት፣ መወደድ…ወዘተ. ከሚያመሳስሏቸው ባሕርያት ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ማንኛውም ሕፃን በራስ የመተማመን ባሕርይ እያዳበረ ሲመጣና ራሱን ለመቻል አንድ ዕርምጃ ወደፊት በሚራመድበት ወቅት የምክር አገልግሎት ሊያገኝና የቁጥጥር ሥርዓት ሊበጅለት ይገባል፡፡ ይኼንንም ሥራ ወላጆችና መምህራን በመተባበር የምናከናውነው ተግባር መሆኑን መረዳት ይኖርብናል፡፡

በሕፃናት የዕድገት ሒደት ውስጥ እንደ አካላዊና አዕምሯዊ ዕድገቶች ሁሉ የሕፃኑ ማኅበራዊና ስሜታዊ ዕድገቶችም በጣም አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ አንድ ሕፃን ነፃና ብቁ ሆኖ  በመማር ማስተማሩ ሒደት ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጎት የሚያሳየው በአካባቢው ተስማሚ ስፍራ ያለው መሆኑ ሲሰማው ነው፡፡ የሕፃኑ የዕድገት አካባቢዎች አንዱ ከሌላው የተያያዙ መሆናቸው በእጅጉ ጠቃሚ ነው፡፡ በለውጥ ሒደት ውስጥ የመረጋጊያ ወቅቶችን ተከትለው የሚመጡ አካላዊ ለውጦች የሚስተዋሉባቸውና አዳዲስ ትምህርቶች የሚቀሰሙባቸው ጊዜ አሉ፡፡ እነዚህ ክስተቶች በሌሎች የማስተካከያ ሒደቶች ውስጥ ያልፋሉ፡፡ እያንዳንዱ የዕድገት ሒደት ሕፃኑን ለቀጣይ የዕድገት ሒደት ያዘጋጀዋል፡፡ በአጠቃላይ ጤናማ የሕፃናት ዕድገት የወላጆችን፣ የመምህራንና የማኅበረሰቡን ትብብር የሚሻ አንኳር ጉዳይ መሆኑን እየጠቆምኩ በቀጣይ መምህራን ሚና ላይ በምታተኩረው መጣጥፌ እስከምንገኛኝ ድረስ ለአዲሱ ዓመት በጎውን ሁሉ እየተመኘሁ እሰናበታለሁ፡፡  መልካም መልካሙን ለሕፃናት!!!

 

  ከአዘጋጁ፡-መምህር ሣህሉ ባዬ የትምህርትና የአስተዳደር ባለሙያ (MBA, MA, BA & IDPM) ናቸው፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው Eecd@ethionet.et and/or sahilubaye@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 88

Trending Articles