Quantcast
Channel: ዓለማየሁ ጉጀ
Viewing all 88 articles
Browse latest View live

ትናንት ዛሬ አይደለም

$
0
0

በመርሃጽድቅ መኮንን ዓባይነህ

የኋላ ታሪካችንን ብቻ ደጋግመን በመጥቀስ ስለቀድሞው ታላቅነታችን ያለመታከት ስናወራና ይህንኑ አስመልክቶ የተለያዩ ዲስኩሮችን በየጊዜው ስናሰማ እንደመጣለን፡፡ ይህ ነው የሚባል ጥያቂ በሌለበት ወይም አስተማማኝ ማረጋገጫ ልናቀርብ በማንችልባቸው አጋጣሚዎች ሳይቀር እኛ ሐበሾች ‘ከሁሉም አንደኞች ነን’ ማለቱ አብዝቶ ይቀናናል፡፡ እስከተቻለ ድረስ በየትኛውም ዘርፍ አንደኝነት የሚጠላ ነገር አይደለም፡፡ ሆኖም በምኞት ፈረስ ስለጋለብን ብቻ በቀላሉ የምናገኘው አይሆንም፡፡

በእርግጥ የኋሊት ስንመለከት አኩሪና ፋና ወጊ የሆነ የነፃነትና የተጋድሎ ታሪክ እንዳለን እኛ ብቻ ሳንሆን መላው ዓለም ያለጥርጥር ያውቀዋል፡፡ ሆኖም ይህ የቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ውርሰ ታሪክ ብቻውን እስካሁን ከምንገኝበት ጎስቋላ የኑሮ ደረጃ አንድ ዕርምጃ እንኳ ፈቀቅ አላደረገንም፡፡

ስለሆነም በራሳችን ላይ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት የምንፈልግ ከሆነ በዚህ ረገድ እርማት የሚያስፈልጋቸው አያሌ ጉዳዮች አሉብን፡፡ ለምሳሌ (ለምለሚቱ ኢትዮጵያ) የሚለው ዝነኛው፣ ግና ደግሞ አደናጋሪው የዘወትር እንጉርጉሮአችን ከደን መራቆት፣ ከለም አፈር መከላትና ከበረሃማነት መስፋፋት የተነሳ የአገራችንን ለተደጋጋሚ ጊዜ በከፍተኛ ድርቅ መመታትና የሕዝባችንን ለችጋር መጋለጥ በቅርብ ለተከታተለ ማንኛውም ሰው ፍፁም እንቆቅልሽ ሳይሆንበት አይቀርም፡፡

ታዲያ እስከ መቼ በዚህ ዓይነቱ ራስም አዘውትሮ የመሸንገልና የማታለል አባዜ ክፉኛ እንደቆዘምን እንኖራለን? ስለራሳችን ያለን የተዛባ ሥዕል ሳይውል ሳያድር በአፋጣኝ መስተካከል ይኖርበታል፡፡ ለረዥም ጊዜ ሳያቋርጥ የቀጠለው ይኸው ቅዠታችን ከቶ እንዳላዋጣን መተማመን ይኖርብናል፡፡

እዚህ ላይ ላንዳፍታ ቆም ብሎ ማሰብ ይበጀናል ጎበዝ፡፡ የተሻለ አማራጭ ካልጠፋ በስተቀር አምና ሲማስን በከረመ በሬ ዘንድሮ ጠምዶ ለማረስ መሞከሩ እምብዛም አያተርፈንም፡፡ ስለሆነም ለኋለኛው ታሪካችን ያለን ወደር የሌለው ቀናዒነት እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን የምንገኝበትን እጅግ የተወሳሰበ ፖለቲካዊና ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በጥልቀት መመርመርና ያላንዳች ማወላወል መሠረታዊ የአቋም ሽግሽግ ማካሄድ አለብን፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ አገራችን ኢትዮጵያ ባላት ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት ፀጋ ያን ያህል የምትታማ አይደለችም፡፡ ይሁን እንጂ አብዝቶ የሚነገርለት ይኸው ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብቷ ክምችት በሚገባ ለምቶና በልፅጎ የኛን የዜጎቿን ኑሮ ለማሻሻል ከቶ አልተቻለውም፡፡ ከዚህ አንፃር ቀዳሚውን ሥፍራ መስጠትና እጅ ለእጅ ተያይዘን መረባረብ ያለብን ለዘመናት ስንማቅቅ ከቆየንበት አስከፊ የድህነት አዘቅት ቀስ በቀስ ለመውጣትና በዓለም አደባባይ አንገታችንን ቀና አድርገን ለመታየት መሆን ይኖርበታል፡፡ ያኔ ብቻ ነው ስለጠቅላላው ማንነታችን በተለይ ደግሞ ስለትናንቱ አስመኪ ሥልጣኔያችን እንደ ልባችን በኩራት ለመናገርና በአኅጉራዊም ሆነ በዓለም አቀፋዊ መድረኮች ሳይቀር ሊኖረን ስለሚገባው ሥፍራ ሽንጣችንን ገትረን በከፍተኛ መተማመን ብንከራከር ወይም አጥብቀን ብንሟገት የሚያምርብን፡፡

እኛ ኢትዮጵያዊያን ዘመናትን የተሻገረና ቀድሞውኑ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ ፖለቲካዊ ውቅርና ማኅበራዊ እሴት አለን፡፡ ካሸለብንበት ለመንቃትና ከወደቅንበት ለመነሳት ትንሽ መንፈራገጥ ብቻ ይበቃናል፡፡ በዚህ ረገድ የራሳችን የሆነውን ድርሻ በአግባቡ የተወጣን እንደሆነ የሌሎች ተባባሪ ወገኖችን የማያቋርጥ ድጋፍና ዕርዳታ ለማግኘት ከቶ አያዳግተንም፡፡

ያን ያህል አዲስና እስካሁን ያልተለመደ ነገር ነው ባይባልም በቅርቡ እንደተከታተልነው አገራችን ኢትዮጵያ እነሆ እ.ኤ.አ ጁን 28 ቀን 2016 ኒውዮርክ ከተማ ተካሂዶ በነበረው 70ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ አማካይነት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና ለሁለት ዓመታት ያህል ዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ እንድታገለግል ለሦስተኛ ጊዜ መመረጧን እናስታውሳለን፡፡ ሥራዋን በይፋ ከሌላዋ አፍሪካዊት አገር ከአንጎላ የምትረከበውም ከመጪው ጃንዋሪ 1 ቀን 2017 ጀምሮ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለመላው የመንግሥታቱ ድርጅት አባል አገሮች በዙር የሚዳረሰውን ይህንኑ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ መንበረ ሥልጣን ለማግኘት ሰፊና ተከታታይነት ያለው የዲፕሎማሲ ዘመቻ ሲካሄድ እንደቆየ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን አማካይነት ተደጋጋሚ መረጃ እንዲደርሰን ተደርጓል፡፡ አሁንም አብቅቷል ማለት አይቻልም፡፡ ለነገሩ ባሳለፍናቸው በደርግና በአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥታትም ቢሆን ተመሳሳይ ዕድሎችን አግኝተን አገልግለናል፡፡ የመጀመሪያው እ.ኤ.አ ከ1967 እስከ 1968 ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከ1989 እስከ 1990 እንደነበር ይታወሳል፡፡

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ አገራችን ኢትዮጵያ ከመንግሥታቱ ድርጅት መሥራች አገሮች አንዷ እንደመሆኗ መጠን አሁን ለሦስተኛ ጊዜ ለመመረጥ የበቃችበት አጋጣሚ ቢያንስ እንጂ የሚበዛባት ይሆናል ተብሎ የሚገመት አይደለም፡፡ በእርግጥ ዘግይቶ የተገኘው ይህ የመመረጥ ዕድል ሌላው ወርቃማ አጋጣሚ ነውና ቀደም ሲል ይበልጥ በምትታወቅባቸው በሰላም ማስከበርና በዲፕሎማሲ መስኮች እስካሁን ስታደርገው እንደቆየችው ሁሉ፣ ለመንግሥታቱ ማኅበር ተጨማሪ አገልግሎት በማበርከት ተገቢውን ክብርና ሞገስ ልታገኝበት እንደምትችል አያጠራጥር ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ዘወትር የተለጠጠ ታላቅነት አጥብቆ ለሚሰማን ለእኛ ለዜጎቿ አገራችን የተሻለ መኩሪያና መታበያ ልትሆን የምትችለው፣ ቅድሚያውን ለራሷ ውስጣዊ ሰላምና መረጋጋት በመስጠት አበክራ የሠራች እንደሆነ ብቻ ነው፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ የምንገኝበት ጂኦ ፖለቲካዊ አካባቢ ለማያባሩ የእርስ በርስ ግጭቶችና ደም አፋሳሽ ጦርነቶች ክፉኛ የተጋለጠ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያም ከሁሉ በላይ ለራሷ ዘላቂ ደኅንነት ስትል በዙሪያዋ ያሉት እነዚህ ግጭቶች ጨርሶ እንዳይባባሱና እሷንም እንዳይጠቀልሏት በንቃት መቆምና ራሷን በብቃት መከላከል ይኖርባታል፡፡

በእርግጥ እስካሁን በዚህ ረገድ ሰፊ ችግር ነበረባት የሚያሰኝ ጉልህና ተጨባጭ ህፀፅ ታይቶባታል ለማለት አይቻል ይሆናል፡፡ በአንፃሩ ወደ ግጭት የገቡ አጎራባች አገሮችንና ማኅበረሰቦችን ቀርቦ ለመሸምገልና እርስ በርስ ለማስታረቅ የምታሳየው ትጋት፣ በአንድም ሆነ በሌላ ቀላል ያልሆነ ተቀባይነትን እንዳስገኘላት መካድ አይቻልም፡፡

ያም ሆኖ ታዲያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መልሶ ታላቅ ለመሆን ያለንን ፅኑ ምኞት ከወዲሁ የሚያመክኑና ምናልባትም አገራዊ ህልውናችንን ሳይቀር ክፉኛ የሚገዳደሩ፣ ብሎም ከተፈጥሯዊ ልዩነቶቻችን ባሻገር በዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች ሥርዓት ውስጥ እንደ አንድ ሉዓላዊ ምልዓተ ሕዝብ ለዘመናት እርስ በርስ ተደጋግፈን፣ ተሳስረንና ተጋምደን የቆየንባቸውን መሠረታዊ እሴቶች ቀስ በቀስ የሚሸረሽሩና ወደለየለት ውድቀት የሚገፉ ከባድ ፈተናዎች ይደራረቡብን ጀምረዋል፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በፍፁም ድህነትና ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ዝቅተኛ ያኗኗር ሁኔታ ዘወትር መማቀቃችን አንሶ ከዚህ በፊት አይተነውና ሰምተነው በማናውቀው ሁኔታ ዘር፣ ጎሳና ብሔር ለይተን አንዱ በሌላው ላይ የማጎምጎሙና እርስ በርስ የመቆራቆሱ አሉታዊ ዝንባሌና ከዚሁ የሚመነጨው አፍራሽ እንቅስቃሴያችን፣ እንደኔ ወደፊት የመራመድ ምልክት ሳይሆን የኋላቀርነት ማሳያ ነው፡፡

እንግዲህ ለሌሎች ሕዝቦች ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት አበክራ በምትሠራው ውዲቷ አገራችን ውስጥ ለምን ይህ ይሆናል ብሎ ያለይሉኝታ መጠየቅ የአባት ይመስለኛል፡፡ አሁን አሁን መሬት ላይ እንደሚታየው በእጃችን ላይ ያለው የራሳችን ውስጣዊ ሰላም በተለያዩ ምክንያቶች አልፎ አልፎ ሲናጋ፣ የንፁኃን ዜጎች ሕይወት ያላግባብ ሲቀጠፍም ሆነ ንብረት ሲወድም በዓይናችን በብረቱ እየተመለከትን ዝም ማለት አይገባንም፡፡ ይህንኑ ውስጣዊ ችግር ወደ ጎን በመተው እንደ ድሮው ድንበር ተሻግረንና ውቅያኖስ አቋርጠን የሌሎች አገሮችን ሰላምና መረጋጋት ዕውን ለማድረግ እንተጋለን ብንል ፍፁም ግብዝነት ይሆንብናል፡፡ እንግሊዞች ‘‘ችሮታ የሚጀምረው ከቤት ነው’’ ይላሉ፡፡ ስለሆነም ውስጣዊ ሰላማችንን የሚያደፈርሱ ዓይነተኛ ችግሮች በአገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ የተፈቀደውን የመጨረሻ እልባት ልንሰጣቸው ይገባል፡፡ ወትሮውንም ቢሆን በሽታውን የደበቀ መድኃኒት እንደማይገኝለት የታወቀ ነውና፡፡

እስካሁን የችግሮቻችን ሁሉ ዋና ማጠንጠኛ የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕጦት እንደሆነ በመርህ ደረጃ ተግባብተን ይሆናል፡፡ ይህ ግን አጠቃላይ አነጋገር በመሆኑ ለተጨባጭ ችግሮቻችን ተጨባጭ መፍትሔዎችን አላመጣም፡፡ ይልቁንም አጠቃላይ አነጋገር በፀባዩ ዝርዝሮችን በጉልህ አውጥቶ የማሳየት አቅም የለውም፡፡ ዲያብሎስ ደግሞ ከነገረ ቀደም ራሱን የሚወሽቀው በዝርዝሮች ውስጥ እንደሆነ ከወዲሁ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው merha1@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡ 

Standard (Image)

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የሚካሄዱ ተቃውሞዎች ‹ፈታኝ ተግዳሮቶች› ናቸው - አሜሪካ

$
0
0

በቶም ማልኖውስኪ

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እየተካሄዱ ላሉ ተቃውሞዎች በምላሹ የኢትዮጵያ መንግሥት የተከተለው ‹ራስን የመፃረር› ስልት ነው፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ደኅንነትን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ናይሮቢ ከመድረሳቸው ቀደም ብሎ የጻፍኩት ይህ ጽሑፍ፣  የአዲስ አበባ ‹ቀጣይ ታላቅ ብሔራዊ ተግባር የፖለቲካ ግልጽነትን ለማስፈን የሚያጋጥሙ ተጋድሮቶችን በሚገባ መወጣት› እንደሆነ ያስረዳል፡፡

አሜሪካና ኢትዮጵያ አንዱ ለሌላው አስፈላጊ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ለዓመታት የዘለቀ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የምታደርግ፣ አፍራሽ ጽንፈኝነትን በመዋጋት ረገድ የአሜሪካ ዋና አጋር፣ ከየትኛውም አገር በላይ ብጥብጥና ጭቆናን ሸሽተው የተሰደዱ ስደተኞችን በማስተናገድ ለማመን የሚያስቸገር ልግስና ያሳየች አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያ ድህነትን ለማስወገድ፣ በአካባቢ ጥበቃና ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ለምታደርገው ጥረት አሜሪካ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ላይ ነች፡፡ 

ሁለቱ አገሮች ባላቸው የጋራ ጥቅምና ወዳጅነት ምክንያት አሜሪካ በኢትዮጵያ ብልፅግና፣ መረጋጋትና ስኬታማነት የራስዋ ድርሻ አላት፡፡ ኢትዮጵያ በመልካም ጎዳና ላይ ስትሆን፤ ሌሎችን ማነሳሳትና መርዳት ትችላለች፡፡ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ቀውስ ሲከሰት፣ ሁለቱ አገሮች በጋራ ለማሳካት ያለሙትን ግብ ያኮስሳል፡፡

በቅርቡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እየተካሄዱ ያሉ ተቃውሞዎች ፈታኝ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ተቃውሞዎች ኢትዮጵያውያን በሕገ መንግሥቱ በሰፈረው መሠረት ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ የሚሰጥና የፖለቲካ ብዝኃነትን የሚያሰፍን መንግሥት እንዲኖር መፈለጋቸውን የሚያመለከቱ ናቸው፡፡

በቅርቡ በኢትዮጵያ ባደረግኳቸው ሦስት ጉብኝቶች የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ ያገኘኋቸው ሁሉ፣ ኢትዮጵያውያን በበለፀጉና በተማሩ ቁጥር ይበልጥ የፖለቲካ ተሰሚነት እንዲኖራቸው እንደሚፈልጉ ገልጸውልኛል፡፡ ይህ ፍላጎታቸው ደግሞ ሊሟላላቸው ይገባል፡፡ ምንም እንኳን ጥቂቶቹ ተቃውሞዎች ለብጥብጥ መሣሪያነት ቢውሉም፣ አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሐሳባቸውን እንዲገልጹ የሰጣቸውን መብት እየተገበሩ እንደሆነ እናምናለን፡፡

አሜሪካ የምትሰጠው ማንኛውም ምክር መፍትሔ ለማስገኘት ያለመ ሲሆን፣ በአክብሮት ጭምር ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሐምሌ 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ አሜሪካ ፍፁም እንከን አልባ አገር አይደለችም፡፡ የሕዝብን ብሶት ምላሽ በመስጠት ዙሪያ ከተሞክሯችን ጠቃሚ ትምርት እየተማርን ነው፡፡

ኢትዮጵያ ተጨባጭ የሆነ የውጭ ሥጋት እንደተጋረጠባት እንገነዘባለን፡፡ ኢትዮጵያ በድንበሯ አካባቢ የመሸገውን የአልሸባብ አሸባሪ ቡድንን በጀግንነት ተጋፍጣለች፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩና ራሳቸው ለሰብዓዊ መብት ክብር በማይሰጡ አገሮች የሚደገፉ ግለሰቦችና ቡድኖች አልፎ አልፎ በብጥብጥ ለውጥ ለማምጣት ሳይታክቱ ጥሪ ያቀርባሉ፡፡

ኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን በአግባቡ ትኮንናለች፣ አሜሪካም እንዲሁ፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ተበታትነው የሚኖሩና በኢትዮጵያውያንም ብዙ ተቀባይነት የሌላቸው የጥፋት መልዕክተኞችን በመመከት ረገድ ብዙ ርቀት ተጉዛለች፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለደኅንነቷና ለአንድነቷ እየገጠማት ያለው ችግር ምንጩ ከውስጥ ነው፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በበርካታ ቦታዎች፣ በብዙ ክልሎች ወደ አውራ ጎዳናዎች በመውጣት ሕይወታቸውን በሚነኩ ጉዳዮች ተገቢ ድምፅ እንዲኖራቸው ሲጠይቁ፣ የውጭ ጠላት ሴራ ነው ብሎ ማጣጣል የሚቻል አይሆንም፡፡

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሠልፈኞቹ አግባብነት ያለው ብሶት እንዳላቸውና ተገቢ ምላሽ እንደሚያስፈልጋቸው አምነው ተቀብለዋል፡፡ በዚህም እንደ ሙስናና በቂ የሥራ ዕድሎች ያለመመቻቸትን ለመዋጋት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን የደኅንነት ኃይሎች ከመጠን ያለፈ ኃይል በመጠቀም ኢትዮጵያውያን በሰላማዊ መንገድ እንዳይሰበሰቡ መከልከል፣ በርካቶችን መግደልና ማቁሰል እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ማሰራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተቃውሞ ሠልፎች ላይ ተገኝተዋል በሚል መሠረተ ቢስ ክስ በእስር እንደሚገኙ፣ አብዛኛዎቹም ለሕግ ያልቀረቡ፣ የሕግ አማካሪ የተከለከሉ ወይም በአግባቡ የወንጀል ክስ ያልተመሠረተባቸው እንደሆኑ እናምናለን፡፡

ይህ ደግሞ ራስን የመፃረር ስልት ነው፡፡ የተቃዋሚ መሪዎችን ማሰርና የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማትን መገደብ ሰዎችን ተቃውሞ ከማድረግ አያግዳቸውም፡፡ ይልቁንም መንግሥት በሰላም ለመደራደር የማይችልበትን መሪ አልባ እንቅስቃሴ ይፈጥራል፡፡ የኢንተርኔት መስመርን መዝጋት ተቃውሞን አያረግብም፡፡ ነገር ግን የውጭ አገር ባለሀብቶችንና ጎብኚዎችን ሥጋት ውስጥ ይከታል፡፡ ኃይልን መጠቀም ለጊዜው ተቃዋሚ ሠልፈኞችን ቢያረግብም፣ ይበልጥ ንዴታቸውን የሚያባብስና ወደ ጎዳና ተመልሶ ለመውጣት ምንም ነገር ከግምት ውስጥ እንዳያስገቡ ያደርጋቸዋል፡፡

ማንኛውም መንግሥት ዜጎቹን የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ ነገር ግን ሕጋዊነት ያለውና ስኬታማ መንግሥት ዜጎቹን ያዳምጣል፣ ስህተቱን ያምናል፣ እንዲሁም ያላግባብ ጉዳት ለደረሰባቸውም ካሳ ይከፍላል፡፡ ትችትን በግልጽነትና በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ በራስ መተማመንንና ጥበብን የሚያሳይ እንጂ ድክመት አይደለም፡፡  በመንግሥት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በማኅበረብ ውስጥ ነፃ ድምፆች ቢኖሩ፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት የብዙኃኑን ችግር በሕጋዊ መስመር ቢያስተላልፉና የፖሊሲ መፍትሔዎችን ቢያቀርቡ ኢትዮጵያ የበለጠ ትጠነክራለች፡፡ መንግሥትን የሚተቹ ሁሉ መፍትሔ በማፈላለጉ ሒደት ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን እንዲጋሩ ያደርጋል፡፡ ሥርዓቱን ለማደስ የሚደረግ ሒደትም የሕዝብ ጥያቄዎችን ሙሉ በሙሉ ከመቃወም ወደ መግባባት ያደርሳል፡፡

የኢትዮጵያ ቀጣዩ ብሔራዊ ኃላፊነት የሚሆነውም የኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋቶችን እንዳስወገደ ሁሉ የፖለቲካ ግልጽነት ተግዳሮቶችን መዋጋት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ረሃብና ሽብር ከሰፈነባቸው ጊዜያት የተጓዘችባቸውን ርቀት ከግምት በማስገባት፣ ኢትዮጵያውያን እነዚህን ተግዳሮቶች እንደሚያስወግዱ አሜሪካ ሙሉ ተስፋ አላት፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት ሌላን አገር ለማስደሰት ሳይሆን የራሳቸውን ራዕይ ለማሳካት ነው፡፡ አሜሪካም ሆነች ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች እጃቸውን ለመዘርጋት ዝግጁዎች ናቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የአሜሪካ የዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብትና ሠራተኞች ምክትል ሚኒስትር ናቸው፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

Standard (Image)

የጋራ መኖሪያ ቤት 11ኛው ዙር ዕጣ ቢወጣም እኛና ችግራችን ግን ዛሬም አልተፋታንም

$
0
0

በዮሐንስ ኃይሉ

መዲናች አዲስ አበባ ፈርሳ እየተገነባችና አሮጌ ገጽታዋ እየተለወጠ በትልልቅ ዛፎች ፈንታ ትላልቅ ሕንፃዎች ጫካ እየተሞላች ነው፡፡ ለጥቂት ጊዜያት ወጣ ብለው ሲመለሱ የግንባታዎች ፍጥነት ከተማዋን እየቀያየራት የገዛ ሠፈርዎን ለመጠየቅ ካስገደዱ ዋል አደር ብለዋል፡፡

በተለይ በግለሰብ ደረጃ ይገነባሉ ተብለው ለማመን የሚቸግሩ ትልልቅ የሕንፃዎች መንደር 80 በመቶ ለንግድና ለቢሮ፣ 20 በመቶ ለመኖሪያ የሚከራዩ መሆናቸውን እያየን ነው፡፡ በጭቃ ቤት ውስጥ ተወልደን ለዘመናት እዚያው ጭቃ ቤት ውስጥ እየኖርን ከጋራ መፀዳጃ ቤት ወረፋና ከሳፋ ሻወር አልወጣንም፡፡ በተፋፈገ መኖሪያ ቤት ውስጥ ሆነን ቀን በሥራ የደከመ አካላችንን ሌሊት በሰላም እንድናሳርፍ የሚረብሹንን አይጦች ለማጥፋት አልጋ ሥርና የምግብ ማብሰያ ቦታዎች ወጥመድ በማስቀመጥና በማንሳት ተጨማሪ ሥራ የተጠመድን ብዙዎች ነን፡፡ ‹‹መቼ ይሆን ከኪራይ ቤት ወጥተን እንዳቅሚቲ በሆነች የግል መኖሪያ ቤት ፈታ ብለን መኖር የምንጀምረው?›› የሚል ከምኞት ያልዘለለ ሕይወት እየገፋን፣ የፎቆች መሥሪያ ሚስጥሩ ተሰውሮብን ምኞት ስለማይከለከል ብቻ እኛና ምኞታችን ከነቤተሰቦቻችን ጭምር ከኪራይ ወደ ኪራይ እየተገላበጥን ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡

መንግሥት እንደኛ ላሉት ዜጎቹ የመኖሪያ ቤት ችግራችንን በዘላቂነት ለመፍታት በ1996 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎች ለኪራይ በሚያወጡት ገንዘብ በረዥም ጊዜ ክፍያ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ለማድረግ ዕቅድ አወጣ፡፡ በዚህም መሠረት የናሙና ሥራዎቹን በ1997 ዓ.ም. በዕጣ ለማስተላለፍ በከተማዋ ባሉ ቀበሌዎች ምዝገባ አካሂዶ በወቅቱ በእኩል የዕጣ ተወዳዳሪነት ሁሉም ተመዝጋቢዎች ቀርበው፣ በዓላማው መሠረት እጅግ ፍትሐዊ በሆነ ዋጋ ቤቶቹን ለባለዕድለኞች ማስረከቡ አይዘነጋም፡፡

በዚህም መሠረት የመጀመርያው የጋራ መኖሪያ ቤት ምዝገባ ከተካሄደ 11 ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ እስካሁን በተካሄዱት 11 ዙር የዕጣ አወጣጥ ሥርዓቶች በየጊዜው የሚፈለሰፉ አዳዲስ አሠራሮችና ድንጋጌዎች አሉ፡፡ ለ11 ዓመታት ዕጣ በወጣ ቁጥር እንደ ዜጋ ከችግራችን አንፃር በከፍተኛ ጉጉት የምንጠብቀውን ተመዝጋቢዎች የቤት ዕጣ ተጠቃሚነት መብታችን በየዙሩ እየተሸራረፉና ቤት የማግኘት ዕድላችን እየጠበበ ተስፋው ወደመጨለሙ ተዳርሰናል፡፡

ከ1997 ዓ.ም. የመጀመርያ ዙር ዕጣ አወጣጥ ጀምሮ በዋጋ፣ በአከፋፈል፣ በእኩል ተወዳደሪነት፣ በጥራት፣ በቦታ ርቀትና በብዙ ተዘርዝረው በማያልቁ ልዩነቶች ተጎጂ የሆነውንና በሰበብ አስባብ ወደኋላ እየተጎተትን ተመዝጋቢዎች አለን፡፡ ከፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ከእኩል የዜግነት መብት ተጠቃሚነታችን ተገፍተን የበይ ተመልካች ሆነን መኖር ሊያበቃ ስለሚገባ፣ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅድልን መንገድ ጥያቄያችንን ለመንግሥት በሕጋዊ አካሄድ እናቀርባለን፡፡ የመኖሪያ ቤት ችግራችንን አስመልክቶ ለ11 ዓመታት የተጉላላነው እንዲያበቃና የቤት ግንባታው ዓላማ ከተቋቋመበት ውጪ በየዙሩ እየተጫኑብን የመጡትን አሠራሮች ማስተካከያ እንዲበጅላቸው ጥያቄያችንን ለመንግሥት በጋራ እንድናቀርብ፣ ከሥር በተዘረዘሩ መሠረታዊ ነጥቦች ዋና ዋና ጉዳዮቻችንን ለመነሻት አቅርበናል፡፡

  1. በመጀመርያውና በሁለተኛው ዙር ዕጣ ወቅት የነበረው የቤቶቹ የዋጋ ተመን እጅግ ፍትሐዊና በዝቅተኛና መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ሆኖ፣ በመኖሪያ ቤት ችግር አስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የነበረውን ሕዝብ የቤት ባለቤት በማድረግ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል በአገሪቱ እንዲኖር መሠረት የጣለ አሠራር ተጀምሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሆኖም የ1997 ዓ.ም. የምርጫ ቀውስና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈረጠው የኢኮኖሚ ቀውስ በተለይም በአገራችን እስከ 2000 ዓ.ም. የነበረው የሲሚንቶ፣ የብረታ ብረትና የግንባታ ጥሬ ዕቃ አቅርቦት፣ የባለሙያ የሰው ኃይል እጥረት ግንባታውንም ሆነ የዕጣ አወጣጡን ሒደት ከማጓተቱም በላይ፣ በዋጋ ላይም በመጀመርያዎቹ የቤት ዕድለኞችና አሁን ባሉት የዕጣ ዕድለኞች መካከል በአምስት እጥፍ የዋጋ ልዩነት ጭማሪ እንዲያሳይ ምክንያት ሆኗል፡፡
  2. በመጀመርያዎቹ ዙሮች የነበረውን ሁኔታ ለናሙና ስንመለከት በ1997 ዓ.ም. ለ51 ካሬ ባለሁለት መኝታ ቤት ጠቅላላ ክፍያ 49,000 ብር ከፍሎ መረከብ የሚቻል የነበረ ሲሆን፣ በረዥም ክፍያ ለሚጠቀሙ በ9,800 ብር ቅድመ ክፍያ ቤቱን ተረክበዋል፡፡ ከአራተኛ ዙር ጀምሮ የተመሳሳይ ካሬ ቤት ጠቅላላ ዋጋ 90,095.75 ብር በመሆን ከፍተኛ ልዩነት የተፈጠረ ሲሆን፣ በረዥም ክፍያ ቤቱን መረከብ ለሚፈልጉ ዜጎች 18,019.14 ብር ከፍለው ቤቱን ተረክበዋል፡፡

ከስምንተኛው ዙር ጀምሮ እስከ ዘጠነኛው ዙር የቤቱ ዋጋ ወደ 135,508.18 ብር ከፍ ያለ ሲሆን፣ በቅድመ ክፍያ ለሚረከቡ ብር 27,101.64 ብር በመሆን በከፍተኛ ደረጃ የዋጋ ልዩነት እየፈጠረ ቀጥሏል፡፡ ከላይ በተዘረዘሩት ዙሮች ዕጣው ከወጣ በኋላ ቅድመ ክፍያ ከፍለው የሁለት ዓመት የዕፎይታ ጊዜ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ከዋጋው ጭማሪ ውድነት በቀር ዕጣው ከወጣ በኋላ የሚከፈል የቅድሚያ ክፍያና የሁለት ዓመት የዕፎይታ ጊዜ አሠራር ተቋሙ የተቋቋመለት ዓላማ በትክክል ተግባራዊ የሚያደርግ በመሆኑ፣ የእኛም ተራ ሲደርስ በዜግነታችን እኩል ተጠቃሚ እንደምንሆን በማመን በተስፋ ስንጠብቀውና ስንደግፈው ኖረናል፡፡

ከአሥረኛው ዙር ጀምሮ ግን በዳግም ምዝገባ በቅድመ ክፍያ (ቁጠባ) ሰበብ በርካታ ዜጎች ከወርኃዊ ወጪያቸው በተጨማሪ በኪራይ ቤት እየተጉላሉና በየወሩ የተተመነባቸውን እየቆጠቡ እንዲጠብቁ ከመደንገጉም በላይ፣ ዕጣው ሲወጣ ተመሳሳይ ባለሁለት መኝታ ጠቅላላ ዋጋ በአምስት እጥፍ አድጎ 263,000 ብር ሲሆን፣ ቅድመ ክፍያው ደግሞ ወደ 65,000 ብር ከፍ ብሏል፡፡ በዚህ አሠራር ብዙ ዜጎቻችን ከውድድሩ ውጪ ሆነው የመኖሪያ ቤት ችግራቸው የዕድሜ ልክ ጨለማቸው ሆኗል፡፡

ከላይ እንደተገለጸው የዋጋ ንረት ዋነኛ ምክንያቶች የሲሚንቶ፣ የብረታ ብረት፣ የሰው ኃይልና የአቅርቦት እጥረት የነበረ ቢሆንም፣ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የቀረጥ ነፃ ዕድል በማመቻቸትና ድጎማ በማድረግ ጭምር አስቸኳይና የአጭር ጊዜ መፍትሔ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ እንደ ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ የመሳሰሉ ተቋማትንና ሌሎች የመንግሥት ፋብሪካዎችን ከማቋቋም በላይ፣ በግል ዘርፉም የሲሚንቶና የብረታ ብረት ፋብሪካዎች እንዲበራከቱ ከቀረጥ ነፃ የግብር ዕፎይታና የመሳሰሉ ድጋፎችን በማድረግ፣ እጥረቱን ብቻ ሳይሆን ዋጋውንም ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ አድርጓል፡፡ የሰው ኃይል ችግሩንም ለመፍታት ከቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ጀምሮ እስከ ትላልቅ ሥራ ተቋራጮችን በማኅበር በማደራጀት የጠጠር፣ የብሎኬትና የግንባታ አቅርቦትን ችግር በዘላቂነት በመፍታት አስደናቂ መፍትሔ ሰጥቷል፡፡

ይህ ሁሉ ሆኖ እያለ በርካሽ አቅርቦት የተገነቡትን ቤቶች ሳይቀር እጥረት በነበረበት ጊዜ ከተገነቡት ቤቶች በበለጠ ዋጋ ብቻ ሳይሆን፣ ከተገነቡ በኋላ በሰበብ አስባቡ ከዕጣ ውጪ በማቆየትና ግንባታውንም በማዘግየት ጭምር በቀጣይ ዙሮች በተጋነነ ዋጋ ለተመዝጋቢዎች ማቅረብ፣ ተቋሙ የተቋቋመለትን ዓላማ ያልተገነዘቡና ተቋሙ ሲመሠረት ያልነበሩ ግለሰቦች የተሳሳተ አሠራር እንጂ መንግሥትንም ሆነ የግንባታውን ዓላማ የሚወክል ሊሆን አይችልም፡፡

  1. የመኖሪያ ቤት ችግር እንደ ምግብ፣ ልስብ፣ ጤናና የመሳሰሉት ፍላጎቶች የሁሉም ዜጋ መሠረታዊ ችግር እንጂ በፆታና በሙያ ፈጽሞ የሚፈረጅ አይደለም፡፡ እኛ ለ11 ዓመታት ከዛሬ ነገ ዕጣችን ይወጣል ብለን በተስፋ የምንጠብቅ ዜጎችም እንደማንኛውም ዜጋ የአገራችን ልማትና ዕድገት አካላት እንጂ ሁለተኛ ዜጋ አይደለንም፡፡ ልማትን በተግባር እየደገፍን የተጠቃሚነታችንን ተራ ብንጠባበቅም፣ መንግሥት አሮጌ ሠፈሮችን ባፈረሰ ቁጥር የልማት ተነሽዎች በሚል ሰበብ ተመዝግበው የነበሩም ይሁኑ ያልተመዘገቡትንም ጭምር የቁጠባ ደብተር ሳያሻቸው እየታደላቸው ነው፡፡ እኛ በቆጠብነው የጋራ መኖሪያዎችን ገንብቶ ለእነሱ ማስተላለፍ የእኛን የመፍትሔ ጊዜ በማዘግየት የቤት ጉዳይ ፈጽሞ ተስፋ አስቆራጭ እንዲሆንና ዥንጉርጉ ዜጋ ያላት አገር እንድትሆን ያደርጋል፡፡ በመሆኑም የልማት ተነሺዎችን ጉዳይ ለብቻው ተይዞ ከእኛ ዕጣ አወጣጥ ሥርዓት ውጪ የተሻለ አሠራር ሊበጅለት ይገባል፡፡

ከብዙ በጥቂቱ በእነዚህ ነጥቦች መነሻነት ሌሎች ያልተጠቀሱ ተያያዥ ዝርዝር ጉዳቶቻችንን ለመንግሥት አቅርበን ማስተካከያ እንዲደረግበትና ዘላቂ መፍትሔ ለእኛም ሆነ ለቀጣይ ተመዝጋቢዎች እንጂ ለማድረግ ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖት፣ ከጎሳና ሌሎች ከቤት ችግራችን ጋር ተያያዥ ያልሆኑ አጀንዳዎች ርቀን በሰላማዊ መንገድ ተደራጅተን ለችግራችን በጋራ መፍትሔ ማበጀት እንድንጀምር ትክክለኛ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ለችግራችን መፍትሔ ለመፈለግ በስብሰባዎቻችን ለመገኘት የነባር ተመዝጋቢ ካርዳችን ብቸኛ መለያችን እንዲሆን ይገባዋል፡፡ ከዚህ ውጪ በየቀበሌያችን ያሉ የየትኛውም አደረጃጀቶች ሆኑ ጥያቄያችንን ተገን አድርገው ለሌላ ዓላማ የሚሰባሰቡ ኃይሎች በዚህ ጉዳይ ላይ ፈጽሞ ጣልቃ እንዳይገቡ ብርቱ ጥንቃቄ እንድናደርግ ያስፈልጋል፡፡

በመጨረሻም ሰባቱ እስከ መቼ? 

  • ለቤት ዕጣ ተመዝግበው በ11 ዓመታት ውስጥ በተስፋ እየጠበቁ ዕጣው ሳይወጣላቸው በመኖሪያ ቤት ጉዳይ እረፍትን እንደናፈቁ ለአንዲት ቀን ሳያገኟት ያለፉ የቤተሰብ ኃላፊዎች፣ ከሞቱ በኋላ ዕጣው ወጥቶ ቤተሰቦቻቸው የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን ሳይችሉ ሲቀሩ እስከ መቼ?
  • በሰበብ አስባቡ ግንባታው እየዘገየና በየዙሩ ዋጋ እየጨመረ እስከ መቼ?
  • በፆታ፣ በሙያ፣ በልዩ ኬዝ፣ ነገ በሚፈጠር ሌላ ልዩ ኬዝ እየተባለ የእኩል ዕጣ ተወዳዳሪነታችን ዕድል እየጠበበ እስከ መቼ?
  • ምርጫ በመጣ ቁጥር የተገነቡ ቤቶችን በተስፋ ዳቦነት እየተቁለጨለጭን እስከ መቼ?
  • እኛ እየቆጠብን የተሠሩ ቤቶች ለሌላ እየተላለፉ የበይ ተመልካችነታችን እስከ መቼ?
  • በመጀመርያዎቹ ዙሮች ለዜጎች የተሰጡ ዕድሎችን ተነፍገን እስከ መቼ?
  • መጠለያ፣ ምግብና ልብስ ወዘተ. እኩል የሁሉም ዜጋ ችግር ሆነው ሳለ እስከ መቼ?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው moges_y@yahoo.comማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

 

Standard (Image)

የፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍና የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ

$
0
0

በተክለብርሃን ገብረሚካኤል

ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ‹‹የኦሮሞና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ›› በሚል ርዕስ በሐምሌ ወር 2008 ዓ.ም. አሳትመው ያወጡት መጽሐፍ በኢትዮጵያ ታሪክ ምርምርና ጥናት አዲስ ፈር ቀዳጅ ለመሆኑ ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ አንደኛ የኦሮሞ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ውጪ (ከማዳጋስካር፣ ከኢስያ ክፍሎች) ወደ ኢትዮጵያ ፈልሶ የገባ ሲባል የኖረውን አፈ ታሪክ አሳማኝ ናቸው በሚባሉ ማስረጃዎች አስደግፈው ከእውነቱ የራቀ መሆኑን አሳይተዋል፡፡ ሁለተኛ አማራ የገዥ መደብ ተብሎ በአማራ ሥርወ መንግሥት ኦሮሞን ጨምሮ ሌሎች የባህል ገጽታዎቹን በኃይል ጭኖባቸዋል የሚለው ውግዘት ምንም ታሪካዊ መሠረት እንደሌለውና እንዲያውም፣ በአግአዚ/ሰሎሞናዊና በዛጉዌ ሥርወ መንግሥታት በንጉሠ ነገሥትና ደረጃ አማሮች የበላይነት ይዘው እንደማያውቁና ይልቁንም በዚህ የሥልጣን ደረጃ አብዛኞቹ ኦሮሞዎች እንደነበሩ አረጋግጠዋል፡፡ በተጨማሪም በዘመነ መሳፍንት በባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴነቱ በኢትዮጵያ ሥልጣን ይቀራመቱ የነበሩት አማሮች ሳይሆኑ፣ በተለይ የየጁ ኦሮሞዎች መሆናቸውን ቁልጭ አድርገው ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ አመልክተዋል፡፡ ሦስተኛ አማሮች የዘር ምድባቸው ሴማዊ (ሴሜቲክ) ሳይሆን እንደ ኦሮሞ ኩሻዊ መሆኑን፣ ሁለቱም ጎሳዎች (ጎሳ በቋንቋ መወሰኑን አመልክተዋል) የኢትዮጵያውያን ሁሉ ጥንታዊ አባት ከሆነው ኩሻዊው ኢትዮጵያ ልጅ ከደሽት (ከደሴት) የመጡ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ጂኦግራፊያዊ ወይም መልክዓ ምድራዊ ምንጫቸው ዛሬ ጐጃም እየተባለ የሚጠራው አካባቢ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ አዳዲስ ታሪካዊ ግኝቶች ናቸው፡፡

የፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ ሌላው ዓቢይ ገጽታ ከልዩነት ይልቅ አንድነትና ተመሳሳይነትን፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከበቀል ይልቅ ርኅራኄንና ምሕረትን፣ ከመሻኮት፣ ከመነታረክና ከመጠፋፋት ይልቅ መቻቻልንና በእኩልነት አብሮ መኖርን የሚሰብክ በመሆኑ፣ ሻዕቢያ ሕወሓት/አሕአዴግ ከሚያቀነቅኑት የቂም በቀል፣ የመለያየትና የመጠፋፋት አስተምህሮ ተቃራኒ አመለካከትና ርዕዮት ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ በዚህም ምክንያት ሊሆን ይችላል ገና ካሁኑ አንዳንድ ሰዎች (መጽሐፉን ያነበቡ) ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳን የኢትዮጵያ ታሪክ አባት ብቻ ሳይሆን፣ የፍቅር አባት እያሉ ሲጠሯቸው የሚሰማው፡፡ የታሪክ አባት የተባሉት ብቸኛ የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊና ተመራማሪ ስለሆኑ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ከጥንታዊ ሥረ መሠረቱ ጀምሮ ለማየት በመሞከራቸው ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በመቀጠል የመጽሐፉን አንኳር ይዘቶች፣ በተለይም በአዲስ ግንኙነት ሊመደቡ የሚችሉትን ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

የመጽሐፉ ዓበይት ይዘቶች

መጽሐፉ በሦስት ዋና ክፍሎቹ ተዘጋጅቶ የቀረበ ሲሆን፣ ክፍል አንድ ‹‹ኦሮሞ ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ ያበረከተው አስተዋጽኦ›› የሚል ንዑስ ርዕስ ያለው ሲሆን፣ ክፍል ሁለት ‹‹የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ እውነተኛው የዘር ምንጭ›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ቀርቧል፡፡ ክፍል ሦስት ርዕስ ሳይሰጠው፣ ስለኢትዮጵያ ሥርወ መንግሥታት፣ ስለዘመነ መሳፍንት፣ ስለንግሥት ሳባ ማንነት ሲያወሳ ማጠቃለያና መደምደሚያ የቀረቡት በዚሁ ክፍል ነው፡፡

ከላይ በመግቢያው ላይ ከተጠቀሱት ነጥቦች ሌላ መጽሐፉ አያሌ ቁም ነገሮችን አካትቷል፡፡ በክፍል አንድ ከተጠቀሱት ኦሮሞ ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ ካበረከታቸው አስተዋጽኦዎች፣ ኦሮሚኛ (አፋን ኦሮሞ) ለአማርኛ ቋንቋ ብልፅግና ያደረገው አስተዋጽኦ ተመልክቷል፡፡ ስንቶቻችን ነን የሚከተሉት የአማርኛ ቃላት ከኦሮሚኛ የተገኙ መሆናቸውን የምናውቀው? ጮማ፣ ጭኮ፣ ወጌሻ፣ ደንቃራ፣አንጋፋ፣ በርጩማ፣ ዳክዬ፣ ቡራ ከረዩ፣ አባወራ፣ ቀልብ፣ ወዳጅ፣ ቀዬ፣ ጀብዱ፣ ቢላዋ፣ ወዘተ፡፡ የኦሮሚኛ ፍልስፍናዊ የአስተሳሰብ ሥርዓትን የሚያመለክቱ በርካታ ፈሊጣዊ አነጋገሮችና ይትብሐሎች በአማርኛ ቋንቋም ውስጥ መገኘታቸው በሁለቱ ማኅበረሰቦች መካከል የባህል መወራረሶች መኖራቸውን ያሳያሉ፡፡ ‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል››፣ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው››፣ ‹‹የወደቀ ግንድ ምስጥና ምሳር ይበዛበታል››፣ ‹‹ህልም ፈርተው ሳይተኙ አያድሩም››፣‹‹አህያ ከአልጋ ሲሉት ከአመድ››፣ ወዘተ ከኦሮሚኛ የተወረሱ ብሂሎች ናቸው፡፡

በአምልኮና በሃይማኖት ዘርፍም የኦሮሞ አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡ ኦሮሞ እንደ አማራ በአንድ እግዚአብሔር (ዋቃ) ያምናል፡፡ በመናፍስት ደረጃ ቦረንትቻና አቴቴ ከኦሮሞ የተወረሱ ናቸው፡፡ ውቃቢም ከአቴቴና ከአውሊያ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በፈረስ ግልቢያና በፈረስ ላይ ጨዋታ፣ ጉግስ፣ ሶምሶማ፣ ደንገላሳና ሽምጥ ከኦሮሞ የተቀሰሙ የፈረስ ግልቢያና የጨዋታ ጥበቦች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በአማርኛ ቋንቋ የሚጠበቡ የኦሮሞ ደብተራዎች፣ ሊቃውንትና ቀሳውስት እንዳሉና እንደነበሩ ስንቶቻችን እናውቃለን? ስመ ጥሮች አለቃ ጥበቡ ገኔ፣ አለቃ ደስታ ነገዎ (የገብረ ክርስቶስ ደስታ አባት)፣ መሪ ጌታ ወልዴና መሪ ጌታ ከበደ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ ኦሮሞዎች ለኢትዮጵያ ዳንኪራ፣ ሙዚቃ፣ የንድፍ ጥበብ፣ ወዘተ ያደረጉዋቸው አበርክቶዎች ከፍተኛ ናቸው፡፡

ከላይ እንደተመለከተው በተለይ የኦሮሞ ዘር ምንጭን በተመለከተ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ከታወቁት ኢትዮጵያውያንና የውጭ የታሪክ ተመራማሪዎች ጋር ልዩነት አላቸው፡፡ አባ ባሕርይ፣ አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ፣ አለቃ ታዬ፣ ተክለጻዲቅ መኩሪያ፣ ይልማ ደሬሳ፣ ጀርመናዊው ኤ ሃበርላንድ፣ መሐመድ ሐሰን፣ ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ፣ ወዘተ ስለኦሮሞ አመጣጥ (በአብዛኛው ከኢትዮጵያ ውጭ በፍልሰት) የጻፉትን ፕ/ር ፍቅሬ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል አይቀበሉትም፡፡ አብዛኞቹ እነዚህ መጻሕፍት እንደሚነግሩን፣ ፕ/ር ፍቅሬ የአማራ ሴማዊነትንና የኦሮሞ ኩሻዊነትን በልዩነት አይቀበሉትም፡፡ እሳቸው ሁለቱም ማኅበረሰቦች ኩሻዊ መሆናቸውን ነው የሚያምኑት፡፡ ፕ/ር ፍቅሬ አማርኛና አማራ እንደ ቋንቋና እንደ ሕዝብ ከሦስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ የነበሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ ኦሮሞን በተመለከተ ደግሞ የዘር ግንዱ ከመደባይ፣ ጅማና መንዱ ከሚባሉ ነገዶች መምጣቱን ይገልጻሉ፡፡ የሚገርመው የኦሮሞም ሆነ የአማራ ጥንታዊ የጋራ ቋንቋቸው ሲባ የተባለው መሆኑ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ የኦሮሞና የአማራ ጥንታዊ አባቶች ኢትዮጵያና ዳሸት ነበሩ፡፡

የቀዳማዊ ምኒልክ የልጅ ልጅ ታላቁ አክሱማይት ከሁለት ሺሕ ስምንት መቶ ዓመት በፊት የግብፅ ፈርኦን ሆኖ ሲነግሥ፣ ዙፋኑን የጠበቁለት አማሮች ነበሩ፡፡ እንዲሁም ታላቁ አክሱማይት የመላ ኢትዮጵያ (ያኔ ግዛቷ በጣም ሰፊ ነበር) ንጉሠ ነገሥት ሲሆን፣ ሴት ልጁን ለሜስፖቶሚያ ንጉሥ ለናቡከደነፆር ሲድርለት አጅበውት የሄዱት የአማራ ወታደሮች ስለነበሩ፣ በዛሬዋ ኢራቅ ‹‹አማራ›› የተባለች ከተማ የተሰየመችው ለአማሮች ክብር ነው፡፡ ሌላው አስደናቂ ነገር ፕ/ር ፍቅሬ ስለቅዱስ ያሬድ ዝርያ የጻፉት ነው፡፡ ዛሬ ብዙ ኢትዮጵያውያን እንደሚያምኑት ቅዱስ ያሬድ ትግሬ ሳይሆን፣ የኦሮሞ አያት ካላት መደበይ ይወለዳል፡፡ እርግጥ አክሱም ኖሮአል (የተወለደው 505 ዓ.ም. ነው) ፡፡

የኦሮሞና የአማራ የዘር ምንጭን በተመለከተ ፕ/ር ፍቅሬ ከአራት ሺሕ ዓመት በላይ ወደኋላ ሄደው የዘር ግንዱን ከካምና ኩሽ አያይዘው፣ በመልከ ፄዴቅ በኩል የኢትዮጵያውያን ሁሉ ጥንታዊ አባት ከሆነው ‹‹ኢትዮጵ›› (ለእግዚአብሔር የቢጫ ወርቅ ስጦታ) ጋር ያጣምሩታል፡፡ በዚህም መሠረት፣ ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለው ስያሜ ‹‹ፊቱ በፀሐይ የተቃጠለ›› ከሚል የግሪክ ቃል (የግሪክ መዝገበ ቃላት ይህን አይልም) የመጣ ሳይሆን፣ ከጥንታዊው የኢትዮጵያውያን ሁሉ አባት ስም የተገኘ መሆኑን ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከግሪክ ሥልጣኔ ቀድሞ የተከሰተ እንደመሆኑ፣ ግሪኮች ለኢትዮጵያውያን ስም ሊያወጡ እንደማይችሉ ፕ/ር ፍቅሬ ይነግሩናል፡፡ በመሆኑም ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለው ስያሜ የተገኘው የኢትዮጵያውያን ሁሉ አባት ከሆነው ከኢትዮጵያ ሲሆን፣ እሱ ከሚስቱ ሲና የወለዳቸው አሥር ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆቹ አያሌ ጎሳዎችና ነገዶች አፍርተው የሁሉም ኢትዮጵያውያን አባቶችና እናቶች ለመሆን በቅተዋል ይሉናል ፕ/ር ፍቅሬ፡፡

በፕ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ ውስጥ ሌላው አዲስ ነገር ሆኖ የቀረበው ጉዳይ የጎሳንና የነገድን ትርጉም የሚመለከት ነው፡፡ ጎሳ ‹‹ጎፊ›› ከሚለው የግዕዝ ቃል የመጣ ሲሆን፣ ትርጉሙም ‹‹ተናገረ›› ማለት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ጎሳ አንድ የጋራ ቋንቋ ያለው ማኅበረሰብ ማለት እንደሆነ ፕሮፌሰሩ ይገልጻሉ፡፡ ነገድ የጎሳ ቅርንጫፍ ወይም ክፍል ሲሆን፣ በዘዬ የሚለያዩ ነገር ግን መሠረታቸው አንድ የሆነ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ማኅበረሰቦችን ያመለክታል፡፡ የባህል ልዩነቶችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የሶማሌ ሕዝብ ነው፡፡ በመሠረቱ ቋንቋቸው አንድ ቢሆንም ብዙ ነገዶችን ያካትታል፡፡ ከእነዚህም ነገዶች መካከል ኢሳ፣ ሀብረወል፣ ገደቡርሲ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ለማንኛውም በፕሮፌሰሩ ትርጓሜ መሠረት ኦሮሞና አማራ ጎሳዎች ናቸው፡፡ በውስጣቸው ተመሳሳይ ቋንቋ (በዘዬ የሚለይ) እና ለየት ያሉ ባህሎች ያሏቸው ነገዶች ይኖራሉ፡፡ እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ጎሳ የዘር ወይም የደም ምደባ ሳይሆን የቋንቋ ምደባ መሆኑን መገንዘብ ነው፡፡ እንደ ፕ/ር ፍቅሬ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ከአንድ የዘር ግንድ የመጡ እንደመሆናቸው፣ ልዩነታቸው በአብዛኛው የቋንቋ እንጂ የዘር ወይም የደም አይደለም፡፡ ይህ ከሕወሓት/ኢሕአዴግ አስተሳሰብ የተለየ ነው፡፡ በፕ/ር ፍቅሬ አመለካከት፣ ‹‹ብሔር››፣ ‹‹ጎሳ›› ለሚለው ቃል ምትክ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ‹‹ብሔር›› የቦታ ስያሜ ነው (ዘብሔረ ቡልጋ፣ ዘብሔረ አማራ፣ ዘብሔረ ኦሮሞ እንዲሉ)፡፡ በመሆኑም ይላሉ ፕሮፌሰሩ፣ በኢትዮጵያ ያለው ጥያቄ ‹‹የብሔረሰብ ጥያቄ›› ወይም ‹‹የብሔር ጥያቄ›› ሳይሆን፣ የጎሳ (የቋንቋ) ጥያቄ ነው፡፡

‹‹አገር›› የሚለው ቃል ደግሞ ጎሳ የሚኖርበት አካባቢ እንጂ መላ ኢትዮጵያ ማለት እንዳልሆነ ፕሮፌሰሩ ያመለከቱ ሲሆን፣ ለመላ ኢትዮጵያ ‹‹ዜጋ›› የሚለው ቃል እንደሚሻል አሳስበዋል፡፡ በዚህም መሠረት ጎንደር፣ ጐጃም፣ ወለጋ፣ ሸዋ… አገር ናቸው፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ‹‹ጠቅላይ ግዛት››፣ በደርግ ጊዜ ደግሞ ‹‹ክፍለ አገር›› ይባሉ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ፕ/ር ፍቅሬ ‹‹አገር›› የሚለውን ቃል እስካሁን በለመድነው መንገድ (ማለትም ለኢትዮጵያ) ብንጠቀምበት ጉዳት እንደሌለው አመልክተዋል፡፡ ቋንቋን በተመለከተ የባቢሎን ግንብ እስከፈረሰበት ጊዜ የሰው ልጅ ቋንቋ (ልሳነ-ሰብዕ) ሱባ የሚባለው ቋንቋ እንደነበርና ከዚያ በኋላ ግን የካህናት ቋንቋ ብቻ ሆኖ በኢትዮጵያ ከመልከ ፄዴቅ ወደ ኢትዮጵያ፣ ከኢትዮጵያ ወደ ደሸት (ደሴት)፣ ከደሸት ወደ እስያኤል (እሴ ወይም አፄ) ተላልፎ፣ በመጨረሻ ንግሥት ሳባ እሴን ገድላ በዙፋን ከተቀመጠች በኋላ በወለደችው (ከሰለሞን) ቀዳማዊ ምኒልክ በአዋጅ እንዲጠፋ ተደርጐ በግዕዝ እስኪተካ ድረስ መገልገያ ቋንቋ ሆኖ ጠቅሟል፡፡

የዛሬዎቹን ጃማይካዎች በተመለከተ ፕ/ር ፍቅሬ የሚሉት አስገራሚ ነው፡፡ ጃማይካውያን በግራኝ መሐመድ ለዓረቦች የተሸጡ የጀማና የአማራ ልጆች ሲሆኑ፣ የተጫኑባቸው መርከቦች በስፔናውያን ተማርከው በአሁኗ ጀማይካ ሊኖሩ መቻላቸውን ነግረውናል፡፡ እውነትም ያስገርማል፡፡ በሌላ በኩል የኦሮሞ ዝርያዎች ወደ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ ድረስ ዘልቀው መሄዳቸውን ፕሮፌሰሩ አመልክተዋል፡፡ ምናልባትም እነአለቃ አፅመ ጊዮርጊስ፣ እነ አለቃ ታዬና እነ አቶ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ በኩል ከእስያ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ጎሳ ነው እስከማለት የደረሱት በዚህ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ፕሮፌሰሩ ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል የንግሥት ሳባና የሰለሞን ልጅ ቀዳማዊ ምኒልክ የሱባን ቋንቋ ከማጥፋቱም በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ (የመደባዮች፣ የአማሮች) የኮከብ ዓርማ በይሁዳ አንበሳ ምሥል ተክቶታል፡፡ በሱባ ቋንቋ የተጻፉ መጻሕፍትን ሲያቃጥል፣ ሌሎቹን ከጥፋት ለማዳን የሞከሩት መደባዮች ስያሜአቸው ወደ ኦሮሞ ተለውጧል፡፡ በሱባ ቋንቋ ኦሮሞ ማለት ‹‹ዕውቀት ገላጭ፣ ተርጓሚ፣ ብልህ›› ማለት ነው፡፡ ይህን ሁሉ የሚነግሩን ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ናቸው፡፡ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን (መደባዮችና አማሮች) ከቀዳማዊ ምኒልክ ጋር ከእስራኤል የመጡ አርባ ሺሕ ሰዎች (በአብዛኛው ከጋዛ ነው የመጡት) ጋር እንዲደባለቁ ተገድደው የሱባ ቋንቋን ትተው ግዕዝ ተናጋሪዎች ለመሆን እንደበቁ ፕሮፌሰሩ በመጽሐፋቸው ውስጥ ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ አርባ ሺሕ አጋዚያን ራሳቸውን ያዳቀሉ ‹‹አቡሳውያን›› ሲሆኑ፣ ሐበሻ የሚለው ቃልም ከዚሁ የመዳቀል ገጽታ የመጣ ቃል ነው፡፡ ሐበሻ የሚለው ቃል ‹‹አበሳ›› (በመከለስ ወይም በመዳቀል የመጣ አበሳ ወይም እንከን) የሚል ክብረ ነክ ፍቺ ያለው መሆኑን ፕሮፌሰሩ ነግረውናል፡፡ ያም ሆኖ የሸዋው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ራሳቸውን ‹‹የጋላ እና የኢቢሲኒያ ንጉሥ እያሉ ሲጠሩ፣ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ደግሞ ‹‹ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ ስዩመ እግዚአብሔር ድል አድራጊው የይሁዳ አንበሳ›› በሚል የማዕረግ ስም ይጠሩ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በሰለሞናዊው (የቀዳማዊ ምኒልክ) ሥርወ መንግሥት ስም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ለመሆን የማይታለፍ ግዴታ ነበር፡፡ ሁሉም ግን የኦሮሞ መሠረት ያላቸው ናቸው፡፡ የሰለሞናዊውን ሥርወ መንግሥት ያስመለሰው ይኩኖ አምላክ ጭምና መሠረቱ ኦሮሞ ነው፡፡ ይኩኖ አምላክ የጊፍቲ መንደያ ልጅ ነው፡፡

ሌላው ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ አስደናቂ ግኝት የግዕዝ ፊደል እየተባለ ስለሚጠራው ያሰፈሩት ሐሳብ ነው፡፡ ይህ ፊደል ብዙ ጊዜ እንደሚባለው፣ ከአርመን የፊደል ገበታ የተቀዳ ሳይሆን፣ ከሁለት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የነበረ ነው፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ግሪኮች ናቸው ፊደል ከኢትዮጵያ የቀዱት፡፡ ከግሪክ ፊደል በፊት የኢትዮጵያ የሱባ ቋንቋ ፊደል ነበር፡፡ እውነትም አስገራሚ ግኝት! ምን ይኼ ብቻ፣ ራሱ የላቲን ፊደል ከሱባ ቋንቋ ፊደል ሳይኮርጅ ይቀራልን? ከዚህም ተነስተው፣ ፕ/ር ፍቅሬ ኦሮሚኛን በላቲን ፊደል መጻፍ የሚያኮራ ሳይሆን የሚያሳፍር ድርጊት ነው ይሉናል፡፡ ከዚህም በላይ ኦሮሚኛን በሳማዊ (በግዕዝ) ፊደል (ከጊዜ በኋላ ሱባ ወደ ሳባ ቋንቋ ተቀይሮአል) መጻፉ በአምስት ዓበይት ምክንያቶች ተመራጭ እንደሚያደርገው ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል፡፡ እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡፡

  1. የግዕዝ ፊደላት ከላቲኑ በተሻለ የኦሮሞን የንግግር ድምፆች ይወክላሉ፣
  2. ኦሮሚኛን በኢትዮጵያ ፊደላት መጻፍ ጊዜና ገንዘብ ይቆጥባል፣
  3. ሳባዊ/ግዕዝ ፊደላት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በደንብ ይታወቃሉ፣
  4. ሳባዊ/ግዕዝ ፊደል ኦሮሞን ጨምሮ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አንጡራ የባህል ሀብት ነው፣
  5. ከላቲን ይልቅ በግዕዝ ፊደል መጠቀም ኦሮሞዎችን እንደ ባዕድ ከመታየት ያድናቸዋል (ከላይ እንደተመለከተው ኦሮሞዎች የኢትዮጵያ መሥራች ሕዝብ ናቸው)፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፕ/ር ፍቅሬ ኦሮሚኛ በኢትዮጵያ ከአማርኛ ጐን ለጐን ሁለተኛው የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም ፕ/ር ፍቅሬ ኦሮሞዎችን ‹‹ኦሮሚያ›› በምትባል ጠባብ ቦታ መገደብ ከመሠረቷት ኢትዮጵያ ማራቅ ስለሆነ፣ ሐሳቡን እንደማይደግፉ ገልጸዋል፡፡

አስደናቂ ሊባሉ የሚችሉ ሌሎች ቁም ነገሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የተፈጠረችው ከሦስት ሺሕ አራት መቶ ዓመት በፊት በንግሥና ስሙ ‹‹ሰንደቅ ዓላማ›› ይባል በነበረው አፄ ወይም እሴ ነው፡፡ ሙሴን በእግዚአብሔር ሥርዓት ያሠለጠነው ኢትዮጵያዊው ጥንት አባት የትሮአብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበረው አፄ ወይም እሴ (ከላይ የተጠቀሰው) በዚህች መሬት ላይ 480 ዓመት ኖሮአል፡፡ የግራኝ መሐመድ ወታደሮች ሙስሊሞች ብቻ አልነበሩም፤ ክርስቲያን አማሮች፣ ኦሮሞዎችና ሌሎች ጎሳዎች ነበሩባቸው፡፡ ሰአፄ ዮሐንስ በአፄ ቴዎድሮስ ላይ ቂም የያዙት የቴዎድሮስ ወታደር ሆነው ሲዋጉ ጀብዱ ባለመሥራታቸው ቴዎድሮስ ዝቀተኛ የሆነውን የባላምባራስ ማዕረግ ስለሰጧቸው ነው፡፡››

በመጽሐፉ ክፍል ሦስት ከተመዘገቡ አበይት ፍሬ ነገሮች መካከል ደግሞ የሚከተሉት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

‹‹አማራው እንደ ሥርወ ኢትዮጵያን አልገዛም፡፡ በየክፍለ አገሩ ግን የአማራ ንጉሦች ነበሩ (በንጉሠ ነገሥትነት አይደለም) ፡፡ በተመሳሳይ፣ የትግሬ ወይም የኦሮሞ ሥርወ መንግሥታት የሚባሉ አልነበሩም፡፡ ባለፉት ሦስት ሺሕ ዓመታት የነበሩት ሥርወ መንግሥታት የሰለሞንና የዛግዌ ሥርወ መንግሥታት ሲሆኑ፣ በእነዚህ ውስጥ ለሰባት መቶ ዓመታት በንጉሠ ነገሥትነትና በንግሥተ ነገሥትነት የገዙት የኦሮሞ ጎሳ አባላት ናቸው፡፡ አማሮች የገዥ መደብ አካላት ተደርገው የሚወሰዱት በተለይ አማርኛ አገራዊ የመግባቢያ ቋንቋ ሆኖ ስላገለገለ ነው፡፡ አፄ ምኒልክ አልገብርም ካሉት የአካባቢ ንጉሦች በስተቀር፣ በሰላም የገቡትን መሪዎች በአካባቢያቸው የነበራቸውን ሥልጣንና ጥቅም አልነኩም፡፡ ባለፉት አራት ሺሕ ዓመታት በኢትዮጵያ አራት ሥርወ መንግሥታት ነበሩ፡፡ እነሱም ኩሻዊ፣ የኢትዮጵ፣ ሰለሞናዊና የዛጉዌ ሥርወ መንግሥታት ናቸው፡፡ የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት መሥራች ንጉሥ ሰለሞን ሳሆይ ከምትባል ኢትዮጵያዊት ሴት (ከንግሥት ሳባ ጋር ሰለሞንን ለመጐብኘት የሄደች) የወለደው ነው፡፡ ቀዳማዊ ምኒልክ በአሥራ አራት ዓመቱ አባቱን ሰለሞንን ለመጐብኘት ወደ እስራኤል ሄዶ ሲመለስ፣ አርባ ሺሕ የኢየሩሳሌምና የጋዛ ወታደሮችን አስከትሎ ስለነበር፣ የአገሬው ሰዎች የነበሩት ራያና አዘቦ አናስገባም በማለት ጦርነት ገጥመውት የነበረ ቢሆንም፣ በድል አድራጊነት ዙፋን ላይ ሊቀመጥ በመቻሉ፣ በኢትዮጵያውያን ላይ የአይሁድ ሥርዓተ አምልኮና ባህል ሊጭን ችሏል፤ ወታደሮቹንም (አይሁዳውያንና የነገደ የቅጣን አባላት) ‹‹አግአዚ›› የሚል ስያሜ አውጥቶላቸዋል፡፡ ግዕዝ ከክርስቶስ ልደት ከአንድ ሺሕ ስድስት መቶ ዓመት በፊት ጀምሮ የአግአዚ መንግሥት ቋንቋ ሆኖ ያገለገለ ሲሆን፣ እስካሁንም በቤተክርስቲያን እያገለገለ ይገኛል፡፡ ትግሬዎች (ተጋሩ፣ ተጋሩዎች) ከክርስቶስ ልደት በፊት በ330 ዓ.ዓ. አካባቢ ከጥንቷ ባቢሎን (ከዛሬዋ ኢራቅ) እና ከሶሪያ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ናቸው፡፡ በመሆኑም ተጋሩዎቹ ከአግአዚያኖቹ የተለዩ ናቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕድሜው ከ22 እስከ 25 ዓመት በነበረበት ጊዜ ለሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ኖሮአል፡፡ የክርስትና ሃይማኖት በይፋ የኢትዮጵያ ሃይማኖት የሆነው በአራተኛው ክፍለ ዘመን ይሁን እንጂ፣ ሃይማኖቱ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ከአንደኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከ325 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1951 ዓ.ም. ድረስ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርኮች ይሾሙ የነበሩት ከግብፅ አሌክሳንደሪያ ነበር፡፡ ሼህ ሁሴን ጅብሪል (የወሎው ኦሮሞ ነብይ) የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በእናታቸው ላይ ቅድመ አያት ናቸው፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ በወንድ አያታቸው በኩል ደግሞ ቅድመ አያታቸው ወልደ መለኮት የሚባሉ የትግሬ ሰው ናቸው፡፡ ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች ነፃነት እስከ መገንጠል›› የሚለው መብት፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት ለውስጥ አስተዳደር ነፃነት ራስ ገዝነትን ጨምሮ›› በሚል ቢተካ ይመረጣል፡፡ ከሪፐብሊክ በተቃራኒ ያለው የዲሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ ወደፊት በጥልቀት መጠናት አለበት፡፡››

ከላይ የተገለጹትና ነጥብ በነጥብ የተዘረዘሩት ፍሬ ነገሮች ለእኔ አዲስ የመሰሉኝና እንዲሁም አንድምታቸው ክብደት የሚሰጣቸው ናቸው ያልኳቸው ሲሆኑ፣ በመጽሐፉ ውስጥ የንዑስ ርዕስ ሥር የተመለከቱትን ዝርዝር ትርክቶች ለማወቅና ለመረዳት ሙሉ መጽሐፉን ከዳር እስከ ዳር ማንበብ እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ ቀጥለን ለማየት የምንሞክረው፣ የመጽሐፉን ይዘት ተዓማኒነት ይሆናል፡፡

የመጽሐፉ ተዓማኒነት

ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ በመጽሐፋቸው ውስጥ ከአራት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት በላይ ወደኋላ እየሄዱ የትርክታቸውን መሠረት ስለሚገነቡ፣ ከጊዜው ርቀት አኳያ የተዓማኒነት ጥያቄ ቢነሳ የሚያስገርም አይሆንም፡፡ ለሩቆቹ ዘመናት ፕሮፌሰሩ ከተጠቆሙባቸው የመረጃ ምንጮች መካከል በሱዳን የዛሬ ሃምሳ ዓመት ከቤተ ክርስቲያን ፍርስራሽ ውስጥ የተገኙ ጥንታዊ የግዕዝ ብራና ጥቅሎች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህም ‹‹መጽሐፈ ሱባዔ›› እና ‹‹የኢትዮጵያ ትንሳዔ ታሪክ›› በሚሉ ርዕሶች የተጻፉ ሰነዶች ናቸው፡፡ ሰነዶቹ ከአራት ሺሕ ዓመት በፊት የነበረውን ታሪክ የሚናገሩ ቢሆንም፣ ዕድሜያቸው ግን ሦስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት ግድም ነው፡፡ ሰነዶቹ በመጀመሪያ የተጻፉት በጥንታዊው የኢትዮጵያ ቋንቋ በሱባ ቋንቋ ሲሆን፣ አክሱማዊው ሲራክ የተባለ ሰው (በ879 ዓ.ም. አካባቢ የነበረ) ከሱባ ቋንቋ ወደ ግዕዝ ተርጉሞታል፡፡ አፄ ላሊበላ ከሱዳን ቋንቋ ወደ ግዕዝ ተርጉሞታል፡፡ አፄ ላሊበላ በሱዳን በኩል ሲያልፍ፣ የኑቢያ (የሱዳን) ንጉሥ ለላሊበላ ‹‹የመጽሐፈ ሱባዔን›› ቅጂ እንደሰጠው ይታመናል፡፡ ላሊበላም ቅጂውን አባዝቶ በቤተ መጻሕፍቱ እንዳኖራቸውና ከዚያም አፄ አምደ ጽዮን ቅጂዎቹን እንደገና አባዝቶ በየገዳማቱ እንዳኖራቸው ተገምቷል፡፡ ይሁንና ከግብፅ የመጣው ፓትሪያርክ ቅጂዎቹን ሲያወድም አንድ ቅጂ ተርፎ፣ ይህ የተረፈው ቅጂ ነው በቤተ ክርስቲያን ፍርስራሽ ውስጥ የተገኘው፡፡

እዚህ ላይ የሚነሱት የተዓማኒነት ጥያቄዎች ሰነዶቹ እንዴት ሦስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት ሊቆዩ ቻሉ?

አክሱማዊው ሲራክ የሱባ ቋንቋን ማወቁ እንዴት ይረጋገጣል? ሲራክ ያውቃቸው የነበሩት ሁለት ሌሎች ቋንቋዎች (ከግዕዝ ሌላ) የትኞቹ ነበሩ? የግብፅ ፓትሪያርክ (ለኢትዮጵያ የመጣው) የመጽሐፉን ቅጂዎች በሙሉ (ከአንድ ቅጂ በስተቀር) እንዴት ሊያስወድማቸው ቻለ? አፄ አምደ ጽዮን ቅጂዎቹን በየገዳማቱ አሰራጭቷቸው ስለነበር፣ ሁሉንም በአንድ ጊዜ ለማውደም (ሴራው ሳይደረስበት) አስቸጋሪ አይሆንም ነበር ወይ? ሰነዶቹ ወደ ግዕዝ ሲተረጎሙ፣ የትርጉም ስህተቶች ሊኖሩ አይችሉም ወይ? በአጠቃላይ ሰነዶቹ በተቀነባበረ ሴራ የተቀመሩ የፈጠራ ታሪኮች አለመሆናቸውን በምን እናረጋግጣለን? ስለነዚህ ጥንታዊ ሰነዶች የዚህን ያህል የተዓማኒነት ጥያቄ የሚነሳ ከሆነ፣ የእስካሁኖቹ የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊዎች (የአገር ውስጥም የውጭ አገርም ተመራማሪዎች) የተጠቀሙባቸው የመረጃ ምንጮች ሁሉ ዋጋ ቢስ ይሆናሉን? በሌላ በኩል የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት የሚጠራጠሩ ሰዎች፣ ለምሳሌም ከክርስትና ውጪ ያሉ ሃይማኖቶችና በሳይንስ ብቻ ነው የምናምነው የሚሉ ኢ አማኒያን፣ ከቅዱስ መጽሐፍ የተጠቀሱትን ማስረጃዎች እንዴት አምነው ሊቀበሉ ይችላሉ? ለምሳሌ አፄ ወይ እሴ 480 ዓመት ኖረ የሚለውን አንድ በሳይንስ ብቻ ነው የማምነው የሚል ኢ አማኒ እንዴት ሊቀበለው ይችላል? ትግሬዎች ከሶሪያና ከኢራቅ ነው የመጡት የሚባለውን ትግሬዎች ይቀበሉታል ወይ?

በሌላ በኩል በሳይንስ ጭምር የሰው ልጅ መገኛ ኢትዮጵያ መሆኗ ስለተረጋገጠ (ሉሲና አርዲ)፣ የሰው ልጅ ሥልጣኔም የጀመረው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ቢባል ያስኬዳል፡፡ ኦሮሞና አማራ በጊዜ ሒደት በቋንቋ ተለያዩ እንጂ የዘር ግንዳቸው አንድ ነው፣ አገራቸውም ኢትዮጵያ ነች ቢባል ከሳይንሱ ተነስቶ መላምትም ቢሆን፣ ተቀባይነት የሌለው ሐሳብ አይሆንም፡፡ ከግብፅ፣ ከግሪክ፣ ከሮም፣ ከቻይና፣ ከህንድ በፊት የሰው ልጅ ሥልጣኔ የጀመረው ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሆነ፣ የሱባ ቋንቋ ሥልሳ ሰብ ነበር፣ የመጀመሪያው የሰው ልጅ ፊደል የሱባ ፊደል ነበር ብንል ማን ይረታናል? በተመሳሳይ፣ ከጥንታዊ ሥልጣኔአችን በመጀመሪያ በሱባ ቋንቋ በኋላ በግዕዝ የተተረጐሙ ‹‹መጽሐፈ ሱባዔ››፣ ‹‹የኢትዮጵያ ትንሳዔ ታሪክ››፣ ወዘተ የተባሉ የብራና ሰነዶች እጃችን ገብተዋል ብንል፣ የሰው ልጅ መገኛ እስከሆንን ድረስ ማነው ደፍሮ የሚጠይቀን? ፕ/ር ፍቅሬ እንደሚሉት በስንፍናችን ነው ጥንታዊ ታሪካችንን ለሌሎች አሳልፈን የሰጠነው! እናም ለወጉ ያህል የተዓማኒነት ጥያቄዎች አነሳሁ እንጂ፣ የፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ትርክት ለእኔ በጣሙን ነው የተመቸኝ፡፡ ቀጥለን መጽሐፉ ወደፊት ለምንገነባት ኢትዮጵያ ያለውን አንድምታ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡

የመጽሐፉ አንድምታዎች

መጽሐፉ ተደብቀው የኖሩ አዳዲስ የኢትዮጵያ ታሪክ ገጽታዎችን ይፋ ስላደረገ፣ የአገሪቱን ታሪክ በአዲስ መልክና ዕይታ እንደገና ለመጻፍ ያስችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ለምሳሌ ኦሮሞ በማዳጋስካር በኩል ከእስያ የመጣ ጎሳ ነው የሚባለውን አፈ ታሪክ ከእንግዲህ ለመቀበል አዳጋች ነው የሚሆነው፡፡ ይህን ነገር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳም በመጽሐፋቸው (የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ) ውስጥ ገልጸውታል፡፡ እሳቸው ኦሮሞ ከየትም የመጣ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ነባር ሕዝብ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ በፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ መሠረት፣ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከሁሉም የዓለም ሥልጣኔዎች (ከግብፅም ጭምር) ቀደምትነት ያለው (የሰው መገኛ ኢትዮጵያ ስለሆነች) እና በተለይ በአካባቢው ወዳሉት አገሮች (ግብፅ፣ ዓረቢያ፣ ሲሪያ፣ ኢራቅ፣ ህንድ፣ ወዘተ) ተስፋፍቶ የነበረ መሆኑን አስረግጦ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ እንደገና በአዲስ መልክ መጻፍ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥልጣኔ (ቢያንስ ከ4,500 ዓመታት በፊት ጀምሮ) በጊዜ ሒደት ወደ ዘመናዊ (የአውሮፓ) ሥልጣኔ መሸጋገር ስላቃተው፣ መጨንገፉን መካድ የሚቻል አይመስለኝም፡፡

አገረ ኢትዮጵያን በተመለከተ ፕ/ር ፍቅሬ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን አስተምረውናል፡፡ በመጀመሪያ ‹‹አገር›› የሚለውን ቃል የምንጠቀምበት ለተወሰነ አካባቢ መጥሪያ ቢሆንም፣ በጊዜ ሒደት ለመላ አገሪቱ መጠሪያ ስለሆነ፣ በዚሁ መቀጠሉ የሚበጅ መሆኑን ቢያሳስቡም፣ የእሳቸው ምርጫ ግን ‹‹ዜጋ›› የሚለው ቃል መሆኑን ነግረውናል፡፡ እኔም ‹‹አገር›› የሚለው ቢቀጥል እመርጣለሁ፡፡

ከፕ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ እንደተረዳሁት፣ ‹‹ኢትዮጵያ›› በግሪክኛ ቋንቋ ‹‹በፀሐይ የተቃጠለ ፊት ያላቸው ሰዎች የሚኖሩባት አገር›› ማለት ሳይሆን፣ ከጥንታዊ የኢትዮጵያውያን አባት ከ‹‹ኢትዮጵ›› የመጣ መጠሪያ መሆኑን ነው፡፡ ትርጉሙም ‹‹ለእግዚአብሔር የቢጫ ወርቅ ስጦታ›› ማለት ነው፡፡ ይህም በጣም ተመችቶኛል፡፡ እንዲሁም ባለሦስት ቀለማቱ የኢትዮጵያ ሰንደቀ ዓላማ ከ3,400 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ ሲሆን፣ በመጀመሪያ የነበረው ዓርማ ኮከብ፣ በኋላ ደግሞ ይታይበት የነበረው ዓርማ የይሁዳ አንበሳ እንደነበር ፕሮፌሰሩ ገልጸውልናል፡፡ የዚህ አንድምታ ግልጽ ነው፡፡ ኮከቡ ከክርስትና ሃይማኖት ጋር የተያያዘ በመሆኑና እንዲሁም የአንበሳው ዓርማ ከይሁዲነት ጋር የተቆራኘ ስለሆነ (የሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት)፣ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሙስሊሞችም አገር ስለሆነችና የይሁዲነትን የበላይነት የምንቀበልበት ምክንያት ስለሌለ፣ ሁለቱም ምልክቶች በባንዲራችን ላይ መኖር የለባቸውም ወደሚለው ሐሳብ አጋድላለሁ፡፡ በዚህም መሠረት ከኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ የኢሕአዴግ ኮከብም መነሳት ያለበት ይመስለኛል፡፡

‹‹ብሔር ብሔረሰብ›› ስለተባለው ድርብ ቃል ፕ/ር ፍቅሬ የጻፉት አሳማኝ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ‹‹ብሔር›› የቦታ ስም ነው፣ ዘብሔረ ቡልጋ እንዲሉ፡፡ ‹‹ብሔረሰብ›› ደግሞ የሰው አገር እንደማለት ነው፡፡ ፕ/ር ፍቅሬ በእነዚህ ቃላት ፈንታ በ‹‹ጎሳ›› እና ‹‹ነገድ›› ተጠቅመዋል፡፡ ‹‹ጎሳ›› በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ፍቺ አለው፡፡ ለምሳሌ ኦሮሞ ኦሮሚኛ ተናጋሪ ሕዝብ ወይም ጎሳ ነው፡፡ ‹‹ነገድ›› የጎሳ ቅርንጫፍ ነው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ለ‹‹ብሔር››፣ ‹‹ብሔረሰብ›› እና ለ‹‹ሕዝብ›› አንድ ትርጉም ነው የሰጠው፡፡ በመሆኑም ልዩነታቸውን ማወቅ አይቻልም፡፡ በአሳሳችና በአደናጋሪ ቃላት ከመጠቀም ይልቅ፣ ትርጉማቸው ግልጽ በሆኑት ‹‹ጎሳ›› እና ‹‹ነገድ›› መጠቀሙ ስለሚሻል፣ ‹‹ብሔር›› እና ‹‹ብሔረሰብ›› የሚባሉትን ቃላት አሁን ባላቸው ትርጉም ባንጠቀምባቸው እመርጣለሁ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሕወሓት/የኢሕአዴግ ‹‹የብሔር ጥያቄ›› በፕ/ር ፍቅሬ ትርጉም ‹‹የጎሳ ጥያቄ›› ስለሚሆን፣ ይህ ደግሞ የቋንቋ ጥያቄ ስለሚሆን፣ የችግሩ አፈታት ኢሕአዴግ ከተጠቀመበት መፍትሔ በጣም የተለየ ነው የሚሆነው፡፡ ፕ/ር ፍቅሬ ከአማርኛ ቀጥሎ ብዙ ኢትዮጵያውያን የሚናገሩት ኦሮሚኛ ቋንቋ (አፋን ኦሮሞ) ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ በእኔ ግምት ትክክለኛው መፍትሔ ይህ ይመስለኛል፡፡ የሚጻፈውም በግዕዝ ፊደል ይሆናል፡፡

ሌላው ክብደት የሚሰጠው አንድምታ አማራ እንደ ሕዝብ፣ እንደ ሥርወ መንግሥት ወይም እንደ ገዥ መደብ ማንንም አልጨቆነም ብለው ፕ/ር ፍቅሬ ከደረሱበት ድምዳሜ የሚመነጨው አመለካከትና የፖሊሲ ሐሳብ ነው፡፡ ከዚህ አመለካከት ተነስተን፣ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሌሎች ማኅበረሰቦችን (ጎሳዎችን) በተለይም ኦሮሞውን ‹‹ከአማራ ጭቆና ነፃ አወጣኋችሁ›› የሚለው ምንም ታሪካዊ መሠረት የሌለውና ለራሱ ሥልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ ብቻ ሆኖ መታየት እንዳለበት መገንዘብ እንችላለን፡፡ እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ ‹‹የኦሮሞ ደም የእኔ ደም›› ነው የሚለው አማራና ‹‹የአማራ ደም የእኔ ደም ነው›› የሚለው ኦሮሞ፣ ለእውነታው የቀረበ አገላለጽ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ በሌላ በኩል ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ‹‹ኦሮሚያ›› የተባለውን ክልል በተመለከተ፣ ለኢትዮጵያ ልጅ ኦሮሞ ትጠበዋለች፤ የተፈጠረባትና ያስተዳደራት ሰፊዋ ኢትዮጵያ እያለችለት፣ በጠባቧ ‹‹ኦሮሚያ›› መወሰንና መገደብ አይገባውም ይላሉ፡፡ የዚህም አንድምታ ግልጽ ባይሆንም፣ ፕሮፌሰሩ ‹‹ኦሮሚያ›› የሚባለው ክልል ጨርሶ ቢታጠፍ፣ ቢታጠር ወይም ባይኖር የሚቃወሙ አይመስለኝም፡፡ በእሳቸው አተያይ ኦሮሚያ የቋንቋ (የጎሳ) ክልል ከሆነና ኦሮሚኛ ቋንቋ የመላ ኢትዮጵያ ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ሐሳብ ካቀረቡ፣ ኦሮሚያ እንደ ቋንቋ ክልል የሚኖርበት ምክንያት አይኖርም፡፡ በተመሳሳይ አማራ ክልል የቋንቋ (የአማርኛ) ክልል ስለሆነ፣ አማርኛ ደግሞ የመላ ኢትዮጵያ የመግባቢያ ቋንቋ እንደመሆኑ፣ የአማራ ክልል መኖር ትርጉም የለውም፡፡

የፌዴራል አወቃቀርን በተመለከተ ፕ/ር ፍቅሬ የሚደግፉት ይመስላል፡፡ ግን የኦሮሞንና የአማራን በቋንቋ መካከል (ኦሮሚያና አማራ ክልሎች) ስለማይደግፉ፣ በጎሳ ላይ የተመሠረተውን ፌዴራሊዝምን የሚቃወሙ ይመስለኛል፡፡ ይህ ከሆነ ፕሮፌሰሩ የሚደግፉት በጎሳ ላይ ያልተመሠረተ ፌዴራሊዝምን ነው ብሎ መደምደም የሚቻል ይመስለኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የመጽሐፉ አንድምታ ይህ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የጎሳ ያልሆነውም ፌዴራሊዝም በከፊልም ቢሆን የጎሳ ፌዴራሊዝም የሚሆንበት ተጨባጭ ሁኔታ ስላለ፣ የውስጥ አስተዳደር ነፃነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለኢትዮጵያ የሚበጃት ዴሞክራሲያዊ አሀዳዊነት (ዲሞክራቲክ ዩኒተሪ ስቴት) ይመስለኛል፡፡ የጎሳ ባልሆነም ፌዴራሊዝም ትግራይ ክፍለ አገር ትግራይ ሆና ስለምትቀጥልና ፌዴራሊዝሙ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ትግራዊነትን እያጎላ ስለሚሄድ፣ ይህንን አሉታዊ አዝማሚያ በዴሞክራሲያዊ አሀዳዊነት መግታቱ ብልህነት ነው፡፡ በትግራይ ብቻ ሳይሆን፣ ይህ አዝማሚያ በአፋር፣ በኦጋዴን፣ በጋምቤላ፣ ወዘተ እየጠነከረ የሚሄድበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ የመንግሥት ሥርዓትን በተመለከተ ፕ/ር ፍቅሬ ከዴሞክራሲ ይልቅ ሪፐብሊካኒዝምን እንደሚመርጡ ገልጸዋል፡፡ እዚህ ላይ ብዙ ግልጽ ያልሆነ ነገር አለ፡፡ ሪፐብሊክ የሚቋቋመው በዴሞክራሲ አይደለም እንዴ? በሌላ በኩል ሪፐብሊክ ብዙ ጊዜ የሚመራው በሕዝብ በተመረጠ ፕሬዚዳንት ስለሆነ፣ እኔ ከማስበው ሥርዓት ጋር የተጣጣመ ነው፡፡ በእኔ አነስተኛ አመለካከት ለኢትዮጵያ የሚበጃት ዴሞክራሲያዊ፣ አሀዳዊ፣ ፕሬዚዳንታዊ የፖለቲካና የመንግሥት ሥርዓት ነው፡፡

ለማጠቃለል፣ መጽሐፉ የተመሠረተባቸው የሩቅ ጊዜ ማስረጃዎች የተዓማኒነት ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ፍቅርን፣ መተሳሰብንና አብሮነትን የሚሰብክ መጽሐፍ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ እጅግ አዎንታዊ እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡ ከጥንታዊ አባቶቻችን ከኢትዮጵያና ከደሸት ያስተዋወቁንና በሁሉም ኢትዮጵያውያን መካከል ሰላምና ፍቅር እንዲሰፍን የሚሰብኩት ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ የታሪክና የፍቅር አባት ቢባሉ አይበዛባቸውም እላለሁ፡፡ ሰላም!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

  

  

      

     

Standard (Image)

የአደጋ ጠርዝ ላይ የጣሉን የኢኮኖሚ ጉዳዮች

$
0
0

በጌታቸው አስፋው

ኢትዮጵያን የለውጥ ፍላጎት እየናጣት ነው፡፡ የለውጡ ዋና ምክንያት ገና ባይለይም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ጉዳዮች ጎን ለጎን እየተነሱ ነው፡፡ የትኛው ዋና ጥያቄ ነው? የትኛው ተሳቦ የቀረበ ነው? ገና ያልለየለት ጉዳይ ነው? ሦስቱም ተደበላልቀው እየቀረቡ ነው፡፡ የሦስቱም ችግሮችና መፍትሔዎች የተለያዩ ናቸው፡፡ ሦስቱም በችግርም በመፍትሔም ተወራራሽና ተደራራቢ ቢሆኑም የራሳቸው የተናጠል  ልዩ ባህሪም አላቸው፡፡ ቀዳሚው የብጥብጡ መንስዔ ባይለይም የኢኮኖሚ ቀውሱ ገና ስላልበሰለ የብጥብጥ ግንባር ቀደም አልሆነም፡፡ ፖለቲካውና ማኅበራዊው ቀድመውታል፣ ቢሆንም እየበሰለ ነው፡፡ ነገር ግን እጅ መቆረጣጠም የጀመረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ በፖለቲካዊና ማኅበራዊ መንስዔዎች ብጥብጡ ተቀጣጥሎ ራሱን የቻለ የኢኮኖሚ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ የኢኮኖሚ ብጥብጥ በስፋት ዓይነት ክልላዊ ሳይሆን አገር አቀፋዊ ስለሚሆን አደገኝነቱ የከፋ ነው፡፡

በየተራ ከመምጣት ይልቅ ተደራርበውና ተጋግዘው መምጣታቸው ከታሰበበትና በሰላም ለመጨረስ መልካም ፍላጎት ካለ፣ ለሦስቱም የሰከነና የማያዳግም የችግሮች ሁሉን አቀፍ መፍትሔ ለመሻት ይጠቅማል፡፡ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት የመጨረሻ ተስፋ የተጣለባቸው ቱሪዝምና የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ በሰላም መደፍረስ ምክንያት እንዳይስተጓጎሉ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይበጃል፡፡ በዚህ ዘመን አገር ለመገንባትና ለማፍረስ ከጦር ኃይል አቅም ይልቅ የኢኮኖሚ ብርታትና መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን ከደርግ ምርጫ ትምህርት መውሰድ ይጠቅማል፡፡ ወደ ኢኮኖሚው የሚያደሉትን የብጥብጥ መንስዔዎች ለይቶ ማወቅ ቢያስፈልግ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ፣ ሥራ አጥነቱ፣ የዋጋ ንረቱ፣ የመሬት ይዞታ ፖሊሲው፣ የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲው፣ የሀብትና የገቢ ክፍፍሉ፣ ወዘተ የመሳሰሉ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ፖለቲካውና ማኅበራዊው በዜግነት እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚሰማኝ ቢሆንም፣ ሙያው ስለሌለኝ ሙያዊ ትንታኔ ልሰጥበት አልችልም፣ ልቀባጥርም አልፈልግም፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዩን ግን ሙያዬ ስለሆነ ሳልዋሽ ሳልቀባጥር ስሜታዊ ሳልሆን መተርጎምና መተንተን እችላለሁ፡፡ ከሙያው ውጪ ብዙ የሚያወራ ሰው ቀባጣሪ እንደሚሆን እገነዘባለሁ፡፡ የቀባጣሪዎች መብዛትም ኢትዮጵያን ክፉኛ እየተፈታተናት ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊው ጉዳይ በችግር መጠንና ዓይነትም ሆነ በመፍትሔ አፈላለግ ከሌሎቹ ከፖለቲካውና ከማኅበራዊው ይለያል፡፡ የሚለይባቸውን ጥቂት ነጥቦች ለማንሳት ያህል፣

  1. የመልካም አስተዳደር ችግር ሳይሆን የፖሊሲ ችግር ነው፣
  2. የሚያሳስበው የትናንትናውና የዛሬው ጉዳይ ሳይሆን የነገው ነው፣
  3. የችሎታ ጥያቄ ስለሆነ ሥልጣን በመጋራት ድርድር አይፈታም፣
  4. ክልላዊ ጉዳይ ሳይሆን አገር አቀፋዊ ነው፣
  5. የኑሮ መደባዊ ባህሪ ስላላቸው በኢኮኖሚ ተጎጂውን ብቻ ይመለከታሉ፣

የአንድን አገር ኢኮኖሚ በጥቂት ገጾች ጽሑፍ አጠቃሎ መግለጽ ከባድ ነው፡፡ ቢሆንም ግን አጠቃሎ ለመግለጽ የሚያስችሉ ጥቂት የብሔራዊ ኢኮኖሚ መለኪያዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም አንዱና ዋናው የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ሒሳብ ነው፡፡ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ሒሳብ የውስጡ ነፀብራቅ ነው፡፡ የውጭው ስኬት የውስጡን ስኬት ያንፀባርቃል፡፡ የውጭው ጉድለትም የውስጡን ጉድለት ያንፀባርቃል፡፡ የተሠሩትን የመኪና መንገዶች፣ የባቡር መንገዶች፣ የኃይል ማመንጫዎች፣ የስልክ መስመሮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት፣ ወዘተ አላየም እንዴ ብላችሁ የምትጠይቁ ሰዎች ካላችሁ፣ እኔ የምናገረው ስለ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አስተዳደር ነው እንጂ ስለልማት አይደለም፡፡ ልማት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አጋዥ እንጂ ምትክ አይደለም፡፡ ዋናው የኢኮኖሚ ችግር የሚመነጨውም ልማት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አጋዥ እንጂ ምትክ አለመሆኑን ካለመረዳት ነው፡፡

የቁጥሮች ቀጥተኛ ትርጉምና ንፅፅራዊ ትንታኔ

በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በቀረበ አገር አቀፍ ጥናት ስልሳ በመቶ የሚሆነው ገበሬ የመሬት ይዞታ ከአንድ ሔክታር በታች ነው፡፡ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቀረበ ጥናት በአማራ ክልል አሥራ አራት በመቶ የሚሆነው ገበሬ ተከራይቶ አራሽ ወይም የእኩል አራሽ ነው፡፡ በሌላ አንድ ጥናት ኢትዮጵያ የግብርና ግብዓተ ምርት በመጠቀም ከብዙ አገሮች በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነች፡፡ እርፍ ጨብጦ ለማረስ የሚዳዳቸው የግብርና ፖሊሲ አውጪዎችና የአፈጻጸም ባለሥልጣናት መሬት ወድቀው ቢንከባለሉ እንኳ፣ የኢትዮጵያውያን ሕዝብ በግብርና ምርት አያጠግቡም፡፡

በአንድ ወቅት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ባህር ዳር ለጉብኝት ሄደው የዓባይ ፏፏቴና ጣና ዳር ላይ ቁጭ ያሉት ባለሥልጣናት ችግራችሁ ምንድን ነው ተብለው ቢጠየቁ የውኃ እጥረት ነው ስላሏቸው፣ ኮሎኔሉ ቆይ ከጎዴ እንስብላችኋለን ብለው አሾፉባቸው ይባላል፡፡ ለም አፈርና ድንግል መሬት ያላት ኢትዮጵያ ባለፉት አሥር ዓመታት በግብርና መር ፖሊሲ መርህ በዓመት አሥራ አንድ በመቶ አድጋለች የተባለች ኢትዮጵያ፣ ከጎረቤት ሱዳን ሽንኩርት ኢምፖርት ታደርጋለች ጤፉ ነው የቀረን፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ሥራ ፈጠራና የኮብልስቶን ንጣፍ ወሬ ሞቶ ተቀብሯል፡፡ ወጣቱ ለሥራ ተነሳሽነት ዝቅተኛ ነው እየተባለ ተወቃሽ ሆኗል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አልገባ ማለት ከምክር አልፎ ወደ ዝልፊያና ማንቋሸሽ አምርቷል፡፡ በውጭ ባለሀብቶች ላይ ከመጠን ያለፈ እምነት ተጥሏል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መፍትሔ ያጣ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ዛሬ በመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ብዛት ከዚህ ቀጥሎ በሚቀርበው በቁጥሮች መረጃ ተደግፎ የተተነተነ የኑሮ ሁኔታ ላይ ነን፡፡ ከአንድ ትውልድ በኋላ በሁለት መቶ ሚሊዮን የሕዝብ ብዛት ምን እንሆናለን? መልሱን አንባቢ ለራሱ ይናገር፡፡ ከብሔራዊ ኢኮኖሚ ዋና ዋና ቁጥራዊ መረጃዎች ውስጥ አንዱ የሆነውንና የጠቅላላ ኢኮኖሚውን ገጽታ የሚወክለውን በብሔራዊ ባንክ የተዘጋጀ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት የክፍያ ሚዛን ሠንጠረዥ (Balance of Payment Table) ቁጥሮችን በመተርጎምና በመተንተን የሁኔታ ዳሰሳ ካደረግን በኋላ፣ የችግሮችን መንስዔ ከነመፍትሔያቸው እንመለከታለን፡፡

የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ክፍያ ሚዛን መረጃ (በሚሊዮን ብር)

ዝርዝር

2006

2007

የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለት

-4,352.3

-8,012.6

  • ቁሳዊ ሸቀጥ ኤክስፖርት

3,300.1

3,019.3

  • ቁሳዊ ሸቀጥ ኢምፖርት

13,712.3

16,458.6

  • የቁሳዊ ሸቀጦች ንግድ ሒሳብ ጉድለት

-10,412.2

-13,439.3

  • የአገልግሎት ንግድ ሒሳብ /የተጣራ/

559.5

-341.4

  • የግል ዕርዳታ/የተጣራ/

4,039.4

4,881.6

  • የመንግሥት ዕሰርዳታ /የተጣራ/

1,461.0

886.5

የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ካፒታል ሒሳብ

4,134.6

7,030.6

  • ብድር የተጣራ

2,667.6

4,828.3

  • የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ

1467.0

2202.2

  • የምዝገባ ስህተት

120.8

460.6

  • አጠቃላይ ሚዛን /ጉድለት/

-96.9

-521.4

የጉድለት አሸፋፈን

96.9

521.4

  • ከመጠባበቂያ ክምችት በመቀነስ

96.9

521.4

  • ከብሔራዊ ባንክ

+0.04

+0.09

  • ከንግድ ባንክ

-0.1

-0.6

  • ከዕዳ ስረዛ /ማስተላለፍ/

-0.004

0.0

በአገሪቱ የተቆለለ የውጭ ዕዳ /በቢሊዮን ዶላር/

13.9

18.2

  • ከመንግሥታትና ከአገሮች

8.4

8.9

  • ከግል የንግድ አበዳሪዎች

5.5

9.3

 

 

ሠንጠረዡ ውስጥ በቀረቡት የሁለት ዓመት መረጃዎች በ2006 እና በ2007 ዓ.ም. በሁለቱም ዓመታት ከቁሳዊ ሸቀጥ ኤክስፖርት ገቢያችን ያገኘነው ሦስት ሦስት ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ለቁሳዊ ሸቀጥ ኢምፖርት ወጪያችን ያወጣነው በ2006 ዓ.ም. አሥራ ሦስትና በ2007 ዓ.ም. አሥራ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ የኤክስፖርት ገቢና የኢምፖርት ወጪ ተቀናንሶ የቁሳዊ ሸቀጦች ንግድ ጉድለት (Trade Deficit) በ2006 ዓ.ም. አሥር ቢሊዮንና በ2007 ዓ.ም. አሥራ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ሆኗል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ከገቢ ወጪ የተጣራ የአገልግሎት ሸቀጥ ሽያጭ የአምስት መቶ ስልሳ ሚሊዮን ዶላር ትርፍ ያስገኘ ቢሆንም፣ በ2007 ዓ.ም. ግን የሦስት መቶ አርባ አንድ ሚሊዮን ዶላር ከገቢ ወጪ የተጣራ ኪሳራ ደርሶብናል፡፡ የአገልግሎት ሸቀጥ ንግድ የሚባሉት ቱሪዝምን፣ ትራንስፖርትን፣ የባንክ አገልግሎትን፣ የመንግሥት አገልግሎትን፣ ወዘተ የመሳሰሉ የአገልግሎት ሸቀጦች ማለት ነው፡፡ በቱሪዝም ላይ ብዙ እንደሚሠራ እየተነገረ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትርፍ በትርፍ ሆነ እየተባለ፣ በኮንፈረንስ ቱሪዝም እየተንበሸበሽን በአገልግሎት የውጭ ግንኙነት ጉድለት ውስጥ መግባታችን ወደድንም ጠላንም ተስፋ የሚያጨልም ነው፡፡

በቁሳዊ ሸቀጦች ንግድና በአገልግሎት ሸቀጦች ንግድ የደረሰብንን ኪሳራ በከፊል የሸፈንነው ለግልና ለመንግሥት ከውጭ በሚመጣው ዕርዳታ ነው፡፡ በሠንጠረዡ ላይ እንደምንመለከተው የግሉ ዕርዳታ ከመንግሥት ዕርዳታ አራት እጥፍ ያህል ስለሚበልጥ፣ ወደፊት ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝ ወይም ከማንኛውም የውጭ ለጋሽ አገር ይበልጥ በኢትዮጵያ ውስጥ የፖሊሲ ለውጥ እንዲደረግ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉት የግል ዕርዳታ ላኪዎች ስደተኛ (ዳያስፖራ) ዜጎች ናቸው፡፡ በ2006ም ሆነ በ2007 ዓ.ም. በእያንዳንዱ ዓመት የንግድ እንቅስቃሴውና ዕርዳታው ተደማምረው በውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ተንቀሳቃሽ ሒሳብ (Current Account) አሁንም በ2006 ዓ.ም. የአራት ቢሊዮን ሦስት መቶ ሃምሳ ሁለት ሺሕ ዶላርና በ2007 ዓ.ም. የስምንት ቢሊዮን አሥራ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ኪሳራዎች ውስጥ እንደተዘፈቅን ነው፡፡ ስለዚህም ጉድለቱን በከፊል የተቋቋምነው የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት የካፒታልና ገንዘብ ፍሰት (Capital and Financial Inflow) ሒሳብ ውስጥ በሚገኙት የካፒታል ገቢዎች ነው፡፡ ከእነኚህ ሁለት ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ የረጅም ጊዜ ወጪ አገልግሎት የሚውሉ የተጣራ ካፒታል ወደ ውስጥ ፍሰት ሒሳቦች ውስጥ ከመጀመሪያው ቀጥታ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ወደ ውስጥ ፍሰት ይልቅ፣ ሁለተኛው የወደፊት ዕዳ የሆነው የውጭ ብድር ፍሰት ሁለት እጥፍ ያህል ይበልጣል፡፡

ዓመታዊው የቁሳዊና የአገልግሎት ሸቀጦች ንግድ ጉድለት በዓመታዊ የውጭ ዕርዳታው መሸፈን አቅቶት በውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለት ሆኖ ተመዝግቦ፣ በረጅም ጊዜ የተጣራ ካፒታል ወደ ውስጥ ፍሰት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ተደጉሞም ሙሉ በሙሉ ሊሸፈን አልቻለም፡፡ ስለሆነም በተንቀሳቃሽ ሒሳብ የውጭ ዕርዳታውም በካፒታል ወደ ውስጥ ፍሰትም ሊሸፈን ያልበቃው ዘጠና ሰባት ሚሊዮን ዶላር የ2006 ዓ.ም. አጠቃላይ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ጉድለትና አምስት መቶ ሃያ አንድ ሚሊዮን ዶላር የ2007 ዓ.ም. አጠቃላይ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ጉድለት ክፍያ የተሸፈነው ባለፉት ዓመታት ከተጠራቀመው የውጭ ምንዛሪ ሀብት መጠባበቂያ ክምችት ሒሳብ ተቀንሶ ነው፡፡ ኪሳራ በኪሳራ ሆነናል፡፡ የግል ድርጅት ቢሆን ኖሮ ተዘግቶ ያርፈው ነበር፡፡ አገር ግን አስይዛ የምትበደረው ሀብት አታጣም፡፡

ከላይ የቀረበው የክፍያ ሚዛን ሒሳብ እንደሚያመለክተው አጠቃላይ ጉድለቱ የተሸፈነው ከንግድ ባንኮች ሒሳብና ከዕዳ ስረዛ (ማስተላለፍ) ሲሆን፣ ከመጠን በላይ የጎደለው የብሔራዊ ባንኩ መጠባበቂያ ተቀማጭ የውጭ ምንዛሪ ሀብት ግን ዕዳ በመክፈል ፋንታ፣ ከብድርና ከውጭ መዋዕለ ንዋይ በተገኘው የተጣራ የካፒታል ሒሳብ ተደጉሟል፡፡ ይህ የሚያመለክተው በንግድ ባንኮች እጅ ያለው የውጭ ምንዛሪም በብሔራዊ ባንኩ ቁጥጥር ሥር መሆኑን ነው፡፡ ከአንዳንድ አገሮች በቀር የሁሉም አገሮች ብሔራዊ ባንኮች በንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ላይ የማዘዝ ሥልጣን የላቸውም፡፡

በሌላ በኩል የብሔራዊ ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ሀብት በብድር ቢደጎምም የውጭ ዕዳም እየተቆለለ ነው፡፡ በሦስት ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርትና በአሥራ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ኢምፖርት ወደፊትም ቢሆን ዕዳ የባሰ ይቆለላል እንጂ፣ መቼም ቢሆን አይቃለልም፡፡ ከዚህም በላይ የካፒታል ወደ ውስጥ ፍሰት ገቢን በመጨመር የውስጥ ጊዜያዊ የፍጆታ መስፋፋትን ፈጥሮ በኋላ ግን የተጠራቀመ ዕዳ በመክፈያ ወቅት ፍጆታው እንደገና ይኮማተራል፡፡ የኢኮኖሚው ዕድገትም እንደዚሁ፡፡ በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ከመንግሥት በጀት እስከ ሰላሳ አምስት ቢሊዮን ብር በውጭ ምንዛሪ ተመንዝሮ ለዕዳ ክፍያ እንደሚውል የመንግሥት በጀት ድልድል ያመለክታል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ከጠቅላላው አሥራ አራት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ አርባ በመቶ ድርሻ ይዞ የነበረው አምስት ተኩል ቢሊዮን ዶላር ከግል የንግድ አበዳሪዎች የብድር ዕዳ በ2007 ዓ.ም. ከጠቅላላው አሥራ ስምንት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ ውስጥ፣ ዘጠኝ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ድርሻውም ከሃምሳ በመቶ በላይ ሆኗል፡፡

ከመንግሥታትና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚወሰድ ብድር በጊዜ ብዛት ክፍያው ለወደፊት ይተላለፋል ወይም ዕዳው ይሰረዛል፣ የወለድ መጣኙም ዝቅተኛ ነው፡፡ ከግል ነጋዴዎች መበደር ግን ይኼ ሁሉ ዕድል የለውም፡፡ ጊዜውን ጠብቆ በግድም በውድም ይከፈላል፡፡ እጅ ጠምዝዘው አንገት አንቀው ያስከፍላሉ፡፡ የወለድ ወለዱም ቀላል አይደለም፡፡ አገራዊው የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀማጭ ሀብት ሲቀንስ አገራዊው የውጭ ምንዛሪ ዕዳ እየጨመረ ነው፡፡ ሁላችንም በዕዳ ተጠያቂዎችና ዕዳ ከፋዮች ነንና ምን እየመጣ እንደሆነ ጠርጥሩ፡፡ ያልጠረጠረ ተመነጠረ ነው፡፡

ዓይን ጆሮ አይደለም

አዲስ አበባን ጨምሮ በብዙ ከተሞች ተዘዋውሮ የተመለከተ ሰው በሥራ ቀንና በሥራ ሰዓት እጅግ በጣም ብዙ ሰው ሥራ ፈትቶ ሲንቀዋለል ይመለከታል፡፡ በመንግሥትና በግል መሥሪያ ቤቶች ጥናት ቢደረግ ለስምንት ሰዓት ሥራ የተቀጠረ ሰው በቀን አራት ሰዓትም አይሠራም፡፡ ከግልጽ ሥራ አጥነቱ ሥውር ሥራ አጥነቱ ተባብሷል፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ተደራጅተው ሥራ ከጀመሩት አብዛኞቹ ገበያ አጥተው ድርጅታቸውን ዘግተው የተበደሩትንም ሳይከፍሉ ወደ ዓረብ አገር ኮብልለዋል፡፡ የቀሩትም የሞት ሽረት ዕድሜ እየገፉ ነው፡፡ አዲስ ማደራጀቱ ቀዝቅዟል፣ ወጣቱም ግራ ተጋብቷል፡፡ ዓይን ጆሮን አይደለም የነገሩትን በሞኝነት አይሰማም፡፡ ራሱ ያያል ባየውም ይፈርዳል፡፡ በሪፖርተር ጋዜጣ በወጣ አንድ ዘገባ ታማሚ በመምሰል መንገድ ላይ ተኝቶ ሲለምን የነበረ ወጣት በልመና ካገኘው ሦስት መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር ጋር በፖሊስ ተያዘ ተብሎ አነበብን፡፡ ወጣቱ ለአገሩና ለሕዝብ ምንም ሳይሠራ ከአገሪቱ ምርት ውስጥ የሦስት መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር ሸቀጥ መግዛት ይችላል፡፡ ኅብረተሰቡም ወጣቱ ሠርቶ ሊያቀርብለት የሚገባውን ሦስት መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር የሚያወጣ ምርት አጥቷል፡፡ በውስጥ እርስ በርሳችን፣ በውጭም ከግለሰቦችና ከመንግሥታት እየለመንና እየተበደርን ልጆቻችንን ለውጭ አገር ቀጣሪዎች ግርድናና አሽከርነት አገልግላችሁ ከምታገኙት ላኩልን ብለን አደጋ ውስጥ እየጣልናቸው እንኖራለን፡፡

ሳይሠሩም ሳይለምኑም ከሚሠራ ዘመድ ተቀብለው ገበያውን የሚያጣብቡና እንደሚሠራ ሰው ወር ቆጥረው ደመወዝ በመቀበል ገበያ ውስጥ የሚጋፉትን ሳይቆጥሩም ሳይጽፉም በዓይን ብቻ ዓይቶ መለየትና መገመት ይቻላል፡፡ ዓይን ራሱ ዓይቶ ስለሚለካ እንደ ጆሮ ሌላ ሰው (የመንግሥት የኢኮኖሚ ባለሟል ወይም በሁለት ቀን ቆይታው ለተደረገለት ቀይ ሥጋጃ የተነጠፈበት አቀባበል ውለታ በሚቀባጥር ፈረንጅ) ተለክቶ በተነገረ ቁጥር አይታለልም፡፡ በአንድ ወቅት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ሲናገሩ ‘በሕይወቴ ትልቅ ጥፋት አጠፋሁ የምለው የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተርን ቀይ ሥጋጃ አንጥፌ መቀበሌ ነው ብለው ነበር፡፡ ቀይ ሥጋጃ ላይ በተረማመደ ቀባጣሪ ፈረንጅ ምስክርነት ስለኢኮኖሚው የተባለው ሁሉ ውሸት ሆኖ ሊቆጨን እየጀመረ ነው፡፡ በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ እንዳለው ልጅ መንግሥትም ቀድሞ በቀጣችሁኝ ኖሮ የሚልበት ጊዜ ላይ ደርሷል፡፡ ምርት የሚያመርተው ሰው ጥቂት ሆኖ የሚበላው ሰው ግን ብዙ መሆን የአገሪቱን ኢኮኖሚ እየገዘገዘው ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በየዓመቱ አሥራ አንድ በመቶ እንደሚያድግ በሚነገርበት ጊዜ ይህ ሁሉ ሥራ አጥ መኖሩ፣ ከውጭም ከውስጥም በዕርዳታና በልመና ካልተደጋገፉ መኖር አለመቻሉ፣ በዋጋ ንረት እየተማረሩ መኖሩ ምንን ያመለክታል? የምናየው ሌላ የምንሰማው ሌላ ከዓይናችንን በላይ ጆሯችንን ልናምን አንችልምና የምትዋሹ አትዋሹ፡፡

የሚሸጡት ቢያጡ ራሳቸውን ሸጡ

በደላላ ተሳበበ እንጂ ባለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት ኢትዮጵያ ልጆችዋን ቪዛና ፓስፖርት ሰጥታ በሎሌነት እንዲያገለግሉ እንጀራ ፍለጋ ወደ ውጭ አገሮች አፍልሳ በሚልኩላት ዕርዳታ ጉልበታቸውን ሸቀጥ አድርጋ ለንግድ አቅርባለች፡፡ ስደተኛ ልጆችዋን ‘ዳያስፖራ’ በሚል የቁልምጫ ቃል እያባበለች ወተታቸውን ለማለብ አንዳንዱን አገር ወዳድ ነው ብሎ በማሞካሸት፣ አንዳንዱን በመሬት እሰጥሃለሁ በመደለል እያግባባች ትኖራለች፡፡ ሰላሳ ዓመት አገሩንና መንግሥቱን ያገለገለ የመንግሥትና የግል ሠራተኛ አንድ ክፍል ስቱድዮ የኮንዶሚንየም ቤት ዕጣ እስከሚደርሰው እየጠበቀ፣ ስደተኛው መጥተህ መሬት በነፃ ውሰድ ደረጃውን የጠበቀ ኮንዶሚንየም ተሠርቶልሀል ይባላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጠቀሰው አባት ቤት ያለውን ልጁን ትቶ የጠፋው ልጁን ፍሪዳ አርዶ ተቀበለው እንደተባለው ይሆን? ወይስ ከሎሌነት ጉልበቱ ዋጋ መረቅ ጨመር አድርጎ እንዲልክ ማግባቢያ ነው፡፡

መንግሥትን ከስደተኛ ሎሌዎች እስከመለመን ያዋረደው ጉዳይ ምን ይሆን? በቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ተቀምጠው የሚለምኑ ምንዱባን እንኳ ቀና ብለው የሰው ዓይን ለማየት እያሳፈራቸው ለመንግሥት ይህን ያህል የልመና ድፍረት የሰጠው ማን ነው? የሰው አገር ሎሌነትን እየካበ ወጣቶች በምድርም በባህርም እንዲኮበልሉስ ለምን ይገፋፋቸዋል? በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ላይ ቆመን የምንሸጠው ብናጣ ራሳችንን እየሸጥን አይደለምን? ስደተኛም እንበለው ዳያስፖራ እዚህ ካለነው ብዙ እጥፍ ስለሚሻል በሎሌነት ሥራ ባገኘው ገንዘብ ኢንቬስትር እንዲሆን ጠርተን ስብሰባ ተቀምጦ ባለበት ሰዓት፣ የውስጥ ችግራችን ፈንቅሎ ወጥቶ አሳፈረን፡፡ ዘንድሮስ በዳያስፖራ እንግዶች ፊት ያዋረደን ከድርቅ የከፋ ዝናብና ክረምት ነው የገጠመን፡፡

የማህፀን ኪራይ ጋብቻ ገቢ

አንድ ሰሞን ደግሞ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽኑም የዓባይ ግድቡም ወሬ ቀዝቀዝ ብሎ የጋዜጦችን ዓምድ ያጣበበው የኢንዱስትሪዎች ፓርክ ዜና ነው፡፡ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከእስያ፣ ከአፍሪካም ኢንቨስተሮች እንደመጡም ይነገራል፡፡ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ሠርቶ ያላለፈልን መቶ ፈረንጅ ሠርቶ ያሳልፍልናል የሚል ተስፋ ተጥሏል፡፡ ሕዝባችንን ውጭ አውጥተን መሸጡ አልበቃ ብሎን መሬታችንን በኪራይ ለመሸጥ እየተዋዋልን ነው፡፡ ከቅርብ ወራት ወዲህ ኢሕአዴግ ሰማንያ አምስት በመቶ ከሚሆነው በግብርና ከሚተዳደረው የገጠሩ ገበሬ፣ በሚሊዮን ከሚቆጠረው በጥቃቅንና አነስተኛ ከተደራጀው የከተማ ወጣት፣ በሺዎች ከሚቆጠሩት ከአገር ውስጥ ባለፀጎች ድጋፍ ላይ የተመሠረተ የኢኮኖሚ ዕድገት የአቅርቦት ጎን ፖሊሲው ትኩረቱን ወደ የውጭ ኢንቨስተሮች ቀይሯል፡፡ በአምራቾች ድጋፍ የአቅርቦት ጎን ፖሊሲ በዚህም በዚያም ብሎ አልሆን ቢለው፣ የምድሪቱን ማህፀን ለውጭ ኢንቨስተር ከማከራየት በሚገኝ ገንዘብ ላይ ተማምኗል፡፡

ሐዋሳ ከትመው መሬታችንን በኪራይ ለማግባት የጥሎሽ ቆጠራ ሥነ ሥርዓቱን የተካፈሉ ኢንቨስተሮች ለአገሪቱ ምን እንደሚያመጡ በመገናኛ ብዙኃን ብዙ ተወርቶላቸዋል፡፡ ተቆነጃጅተን አማምረን እንጠብቃቸዋለን ጥሎሹንም በየጊዜው እየጨመርንላቸው ነው፡፡

ከቀረጥ ነፃ ዕቃ ማስገባቱ፣ የግብር ዕረፍቱ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታው፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ ዝግጅቱ፣ ከአገር ውስጥ ባንክ ብድር ማግኘቱ ምድሪቱን ከውጭ ኢንቨስተሮች በኪራይ ለማጋባት የምንሰጣው ጥሎሾች ሆነዋል፡፡ በውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ጨለምተኛ አመለካከት ባይኖረኝም፣ ጥቅምና ጉዳትን ማመዛዘኛ መረጃም ባይኖረኝም፣ ሃያ ዓመት ሙሉ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ሲመላለሱ ለነበሩ የውጭ ኢንቨስተሮች ሥራቸው ሚዜነት የሆነ የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች እንደ አዲስ ሙሽራ  ኃይሎጋ ጭፈራ ገርሞኛል፡፡

የውጭ ኢንቨስተሮች ከ1985 እስከ 2007 ዓ.ም. በነበሩት 22 ዓመታት በ10,229 ፕሮጀክቶች 520.7 ቢሊዮን ብር መዋዕለ ንዋይ አፍስሰው በገበያችን ውስጥ ልንሸምተው የቻልነው እዚሁ የተመረተ በቂ የፋብሪካ ሸቀጥ አላገኘንም፡፡ በዕዳ ከመዘፈቅም አልዳንም፣ መሠረተ ልማቶች ተሟልተው የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተገነቡላቸው አዲሶቹ ኢንቨስተሮችም ምርታቸውን የሚሸጡት በውጭ ገበያ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ስልሳ ሺሕ ተቀጣሪዎች የደመወዝ ገቢ የሚያገኙ ሲሆን ያመረቱት ምርት ግን በአገር ውስጥ ገበያ አይቀርብም፡፡ ወደ ውጭ ተልኮ ለኢትዮጵያውያን የውጭ ምንዛሪ የኤክስፖርት ገቢም አያመጣም፣ የሽያጭ ገቢው ለኢንቬስተሮቹ ነው፡፡ የምናገኘው ገቢ የምድራችንን ማህፀን ለውጭ ኢንቨስተሮች ከማከራየትና ከአንዳንድ የመንግሥት ግብርን ከመሳሰሉ ሌሎች የገቢ ዓይነቶች ነው፡፡ 

ከኢንቨስተሮቹ ጋር የሚሠሩት ሠራተኞች ግን በተከፈላቸው ደመወዝ በገበሬው፣ በወዛደሩ፣ በአገልግሎት ሰጪው በአገር ውስጥ የተመረቱትን ሸቀጦች የመግዛት አቅም ያገኛሉ፡፡ በዚህም ለአገር ውስጥ የሚመረቱ ሸቀጦች የጤፉ፣ የዘይቱ፣ የምስሩ፣ የሽንኩርቱ፣ የቲማቲሙ፣ የቃሪያው፣ የሎሚው ዋጋ ይጨምራል፡፡ ተጠቃለን የግብርና ምርት ውስጥ ገብተን እነኚህን የምግብ ምርቶች ልቁጠር እንጂ ገቢያችንን የምንደለድልበት ሌላ ምን ፍጆታ አለን፡፡ የእኛ ሥራ ከስደተኛ ልጆቻችን ላብና ከምድራችን ማህፀን ኪራይ ጋብቻ የሚመጣውን ሀብት ቁጭ ብሎ መብላት ሊሆን ነው ማለት ነው፡፡ በወጣትነቷ በሴተኛ አዳሪነት የኖረች ውብ ኮረዳ በስተርጅና ኑሮዋ ቆነጃጅት ሴተኛ አዳሪዎችን መመልመል ነውና እኛም የመሬታችንን ማህፀን የሚያገባ ኢንቬስተር እየመለመልን እንኖራለን፡፡

ከዚህ በላይ የቀረበው የመረጃ ትንታኔና የባለሙያ ሐሳብ የአደጋ ጠርዝ ላይ ከጣሉን የኢኮኖሚ ችግሮች ጥቂቶቹን ብቻ የሚያብራራ ሲሆን፣ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀማጭ መሟጠጥ ችላ የማይሉት የአደጋ ምልክት መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ መንግሥት በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የሚያጋጥም ነው እያለ የመዘናጋት ስሜት እያንፀባረቀ ነው፡፡ ከዚህ በመቀጠል የችግሮች ምክንያትና መፍትሔዎች ላይ እናተኩራለን፡፡

ጥንዳዊ አፈጣጠርና ጥንዳዊ ፖሊሲ

እግዚአብሔር ብዙ ነገሮችን ሙሉ እንዲሆኑ ጥንድ አድርጎ ፈጠራቸው፡፡ ሁለት ዓይን፣ ሁለት ጆሮ፣ ሁለት እጅ፣ ሁለት እግር አድርጎ ሠራቸው፡፡ በግራም በቀኝም እንዲያዩ፣ በግራም በቀኝም እንዲሰሙ፣ በግራም በቀኝም እንዲሠሩ፣ በግራም በቀኝም እንዲራመዱ አደረጋቸው፡፡ አንድ ዓይን ብቻውን አስተውሎ አያይም፣ አንድ ጆሮ ብቻውን አጥርቶ አይሰማም፣ አንድ እጅ ብቻውን አሳምሮ አይሠራም፣ አንድ እግር ብቻውን አስተካክሎ አይራመድም፡፡ ሰውና እንሰሳትንም ወንድና ሴት ጥንዶች አድርጎ ፈጠራቸው፡፡ በትዳር ውስጥ አንዱ ብቻ ያለው ጎደሎ ሲሆን ሁለቱም ያለው ሙሉ ነው፡፡ በፈረሰ ትዳር ውስጥ ነዋሪው አንድ ብቻ ሲሆን ቤቱ በሀብት ቢበለፅግም አንዱ ከጎኑ ስለሌለ ሌላው ጎደሎ ነው ከቶ ምንም ቢሆን ሙሉ ሊሆን አይችልም፡፡ አንድ አይነድ አንድ አይፈርድ፣ አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብ ብለን በጥንድነት ላይ እምነት እንጥላለን፡፡

ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴም በጥንድነት የተገነባ ነው፡፡ እንደ ጥንድነታቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችም ጥንድ ባህሪይ አላቸው፡፡ ፖሊሲዎች ከቀጣሪው፣ ከአሠሪው፣ ከአምራቹ፣ ከመዋዕለ ንዋይ አፍሳሹ በአጠቃላይ አጠራር ከአቅርቦት ጎንና ከተቀጣሪው፣ ከሠራተኛው፣ ከሸማቹ፣ ከቆጣቢው፣ በአጠቃላይ አጠራር ከፍላጎት ጎን ታይተው እንደሚደጋገፉም ተደርገው በጥንድነት ይነደፋሉ፡፡ በአንድ ዓይን ሳይሆን በሁለት ዓይን ይታያሉ፡፡ በአቅርቦት ጎን ፖሊሲ ኢሕአዴግ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም፡፡ ግን በየቀኑ በየዓመቱ ከድጡ ወደ ማጡ ነው የሄደው፡፡ ከዚህ በፊት ዓመቱን ሙሉ በተደጋጋሚ ስለዚህ ጉዳይ የጻፍኩ ቢሆንም፣ አሁን ላለንበት ሁኔታ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ከጊዜው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አዛምጄ ደግሜ ለመናገርና ለመጻፍ እፈልጋለሁ፡፡ መፍትሔው አንድ ብቻ ነው ይኸውም የአቅርቦት ጎን ፖሊሲንና የፍላጎት ጎን ፖሊሲን ማጣመር ነው፡፡ ፍላጎትን በፈለገው መንገድ የሚያሽከረክረውና የፍላጎት ጎን መሠረት የገቢ መጠን ሲሆን፣ አቅርቦትን በፈለገው መንገድ የሚያሽከረክረውና የአቅርቦት ጎን መሠረት የትርፍ መጠን ነው፡፡ ስለሆነም የፍላጎት ጎን ፖሊሲ የገቢ መጠን ፖሊሲ ሲሆን፣ የአቅርቦት ጎን ፖሊሲ የትርፋማነት ፖሊሲ ነው፡፡ የገቢ ምንጭ ሥራና ሀብት ሲሆን፣ የትርፋማነት ምንጭም ምርታማነት ነው፡፡ የአንድ አገር ፖሊሲ በሥራና በሀብት ገቢ እና በምርታማነት ላይ ማትኮር አለበት፡፡

የኢሕአዴግ የሃያ አምስት ዓመት ፖሊሲ ያተኮረው ከምርታማነት ውጪ በሚገኝ ትርፋማነት ላይ ሲሆን ይህም ወልጋዳ የአቅርቦት ጎን ፖሊሲ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ለአምራቹ ትርፋማነትን ለማሳደግ የተጠቀማቸው ፖሊሲዎች አንዱ ለአምራቹ በቀጥታ ድጋፍ መስጠት ሲሆን፣ ሌላው የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲው ነው፡፡ የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲን ለአምራቹም ለሸማቹም እንደሚመች አድርጎ መመጠን ሲቻል፣ ኢሕአዴግ ያተኮረው በአምራቹ ትርፋማነት ላይ ብቻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ ከስልሳ ብር ተነስቶ ሁለት ሺሕ ብር ገባ፡፡ ሐሰተኛ የፖሊሲ ባለሟሎች የጤፉን መወደድ ግብር ገብሮ ደመወዝ በሚከፍላቸው ነጋዴ እንደሚያሳብቡት ሳይሆን፣ በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መብዛት ምክንያት የመጣ ነው፡፡ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ የኩንታል ጤፍ ዋጋ አራት ሺሕም ስምንት ሺሕም ለመግባት የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ አምራችም ሸማች፣ ሸማችም አምራች ናቸውና የጤፉ መወደድ እንዳይጎዳቸው የተወሰኑ አምራቾች የወር ደመወዛቸው ከሁለትና ሦስት ሺሕ ብር ተነስቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላሳ፣ አርባ፣ መቶ ሺሕ ብር ገባ፡፡ በዋጋ ውድነቱ የተጎዱት የሕዝቡን ግማሽ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ለሥራ ያልበቃ ልጆችና ወላጆቻቸው፣ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች፣ የአዋቂዎችን ግማሽ የሚሆኑት የቤት እመቤቶች፣ ታማሚዎች፣ ሥራ አጥ ወጣቶች፣ በደመወዝ መደራደር የማይችሉት የመንግሥት ሠራተኞች፣ ጡረተኞችና አቅመ ደካሞች ናቸው፡፡ የተጎዱት ሲደማመሩ ከጠቅላላው ሕዝብ ዘጠና አምስት በመቶ ይሆናሉ፡፡

የፍላጎትና የአቅርቦት አዋቂነትና አላዋቂነት

በገቢያቸው መጠን ላይ ተመሥርቶ ሸማቾች በሸመታቸው አምራቾችም በምርታቸው አላዋቂ (Irrational) ከሆኑ የግል ኢኮኖሚውና የብሔራዊ ኢኮኖሚው ጤናማ ግንኙነት ይፋለሳል፡፡ አላዋቂነት ማለት ሸማቾች በገቢያቸው ላይ ተመርኩዞ በሚሸምቱት የፍጆታ ሸቀጥና አምራቾች በትርፍ ላይ ተመርኩዞ በሚያመርቱት ምርት ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጣቸውን ለመምረጥ አለመቻል ማለት ነው፡፡ በሸማቾች በኩልም ይምጣ ወይም በአቅራቢዎች በኩል አላዋቂነት ካለ የግል ኢኮኖሚው ለብሔራዊ ኢኮኖሚው የመሠረት ድንጋይ መሆን ይሳነዋል፡፡ በተለይም ሸማቾች በሸቀጥ ጣዕማቸው አምራቹን ምን እንደሚያመርት አዛዦች ስለሆኑ፣ የእነሱ አላዋቂ መሆን አምራቹንም አላዋቂ ያደርገዋል፡፡ በሸማቾች ትዕዛዝ አምራቾች ለኑሮ ከሚበጅ ሸቀጥ ይልቅ ትርኪ ምርኪ ሸቀጥ በማምረት ሥራ ላይ ይሰማራሉ፡፡ ሸማቾች አዋቂ ሸማች እንዲሆኑ የመንግሥት ፖሊሲ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የገቢ መጠን ግብና የገቢ ድልድል ግብ መንግሥት ሸማቹን የሚመራባቸው መንገዶች ሲሆኑ፣ የገቢ መጠንና የገቢ ድልድል ግቦች የሚወሰኑት በመንግሥት በጀትና በጥሬ ገንዘብ መጠን ፖሊሲዎች ነው፡፡ መንግሥት በበጀትና በጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ ኢኮኖሚውን መምራት አለመቻሉን ከፍ ብለን የተመለከትነው የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት የመረጃዎች ትንታኔ ያመለክተናል፡፡

ለገቢ ድልድል ፍትሐዊነትም ዝቅተኛው የሠራተኛው ደመወዝ ወለል መጠንንና የካፒታል ትርፋማነት ጣሪያ መጠንን በሕግ መወሰንም ይቻላል፡፡ በሞኖፖል ንግድ አምራቾች የሸማቾችን ገንዘብ ያላግባብ እንዳይዘርፉም ውድድርን የሚፈጥሩ ፖሊሲዎች መንደፍ ይቻላል፡፡ አምራቾች አዋቂ አምራች እንዲሆኑ ዛሬ በኢትዮጵያ እንደሚታየው ለአንዱ እንዲያመርት መሬትና ገንዘብ መስጠት ለሌላው መከልከል ሳይሆን፣ በነፃ ገበያ ሕግ መሠረት ሁሉም ሰው እኩል ዕድል አግኝቶ ውድድር ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ነው፡፡ ድጋፍ ከውድድር በኋላ ሊመጣ የሚችል እንጂ ውድድርን የሚተካ መሆን አልነበረበትም፡፡ መሬትና ገንዘብ በፍላጎትና አቅርቦት መስተጋብር ዋጋቸው በገበያ ውስጥ የሚተመን የነፃ ገበያ ሸቀጦች እንጂ፣ መንግሥት ለፈለገው የሚሰጠውና ለሌላው የሚነሳው የመንግሥት ንብረቶች አልነበሩም፡፡

ምርት ለማምረት ከሚያስፈልጉት አራት የምርት ግብረ ኃይሎች መሬት፣ ካፒታል፣ የሰው ኃይልና ከሰው ጋር ከተዋሀደው ሥራ ፈጠራ ችሎታ (Entrepreneurship Skill) መንግሥት ከነፃ ገበያው ያልነጠቀው የኋለኞቹን ሁለቱን ብቻ ነው፡፡ እስከ መቼ ድረስ ከሰው የሥራ መሣሪያውን ነጥቆ ባዶ እጅህን ሥራ ፍጠርና ሥራ ይባላል? መሬትና ካፒታል የሌለው ሰው ወይም ቀጥሮ የሚያሠራው ድርጅት ያላገኘ ሰው ምን ሠርቶ ይኖራል? እስከ መቼስ ነው የሥራ መሣሪያ ሀብት ለሕዝብ በራሽን የሚከፋፈለው? ሕዝቡ የሥራ መሣሪያውን ተነጥቆ ባዶ እጅህን ሥራ ፈጥረህ ሠርተህ ብላ በመባሉ የተፈጠረውን ችግርና መፍትሔ ቀጥለን የአቅርቦት ፖሊሲንና የፍላጎት ጎን ፖሊሲን በየተራ በመተንተን እንመልከት፡፡

ምርትና አቅርቦትን የተመለከቱ ፖሊሲዎች

የበጀትና የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲዎች በአቅርቦት ላይም በፍላጎት ላይም ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ ስለዚህም ሁለቱንም ወገኖች በሚጠቅም መልኩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአቅርቦት ላይ ያሳደሩትን ተፅዕኖ እንመልከት፡፡ የበጀት ፖሊሲ በአቅርቦት ላይ ያደረሰው ተፅዕኖ መንግሥት ለገበያ የሚቀርቡ ሸቀጦችን እኔ ላምርት ብሎ በሚያደርገው የሀብት ሽሚያ የግሉን አምራች ከገበያ በማስወጣት ነው፡፡ መንግሥት ኢኮኖሚና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን፣ መሠረተ ልማቶችን፣ እንዲሁም እጅግ ወሳኝ የሆኑ መሠረታዊ የፍጆታና የካፒታል ምርቶችን ማምረት ቢገባውም፣ የገበያ ሸቀጦችን ለገበያው መተው ሲኖርበት ከነፃ ገበያ መርህ ውጪ እያመረተ ይገኛል፡፡ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ የቁጠባና የማበደርያ ወለድ መጣኝ የሚወሰነው በጥሬ ገንዘብ አቅርቦትና ፍላጎት መስተጋብር ቢሆንም፣ መንግሥት የወለድ መጣኙ ላይ በፖሊሲ አማካይነት ተፅዕኖ ለማድረግ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠንን መቀያየር ይችላል፡፡ ይህም በመዋዕለ ንዋይ አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ የምርት መጠንን የመቀነስ፣ የመጨመርና የመለወጥ አቅም ይፈጥራል፡፡ ከዚህ ውጪ መንግሥት ራሱ በቀጥታ የወለድ መጣኝን በመወሰን በቁጠባና በመዋዕለ ንዋይ ላይ ተፅዕኖ መፍጠር ግን የነፃ ገበያ መርህ አይደለም፡፡

 

የኢሕአዴግ ወልጋዳ የአቅርቦት ጎን ፖሊሲ ለአምራቾች የሚሰጠው ድጋፍ ነው፡፡ ድጋፍ ሰጪ ድጋፍ ሲሰጥ የራሱን ንብረት መሆን አለበት፡፡ አምራቾች ድጋፍ እንደሚስፈልጋቸውም አይካድም፡፡ ኢሕአዴግ የሚሰጠው የራሱን ንብረት ሳይሆን የሕዝብ የሆነውን መሬትና በሶሻሊዝም ሥርዓት ተወርሶ፣ የሕዝብ ንብረት የሆነውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የልማት ባንክ ገንዘብ ነው፡፡ የድጋፍ ዓይነት የተዥጎደጎደላቸውና ኢሕአዴግ የተማመነባቸው ብልጣብልጥ አምራቾች ነን ባይ ራስን አንጋሾች ባገኙት የማይገባ የአቅርቦት ጎን ድጋፍ ፖሊሲ፣ እውነተኛ አምራቾች በእኩል ሜዳ እኩል ዕድል አግኝተው እንዳይወዳደሩ ስላደረጋቸው ለኢኮኖሚው ፍትሐዊ ዕድገት ጠንቅ ሆኗል፡፡ አምራቹ የሚታዘዘው በቅርቡ ላለው ገንዘብ ለሚሰጠው ለሸማቹ እንጂ በሩቅ ሆኖ በድጋፍ ብዛት ለሚያግባባውና ለሚለምነው መንግሥት አይደለም፡፡ አምራች ነጋዴ ከፈጣሪውና ከአምላኩ ቀጥሎ የሚፈራውና የሚያከብረው የህልውናው ጌታ አድርጎ የሚያየውም ሸማቹን እንጂ፣ ከሩቅ እየተማፀነ የሚለምነውንና በቁጣ የሚያስፈራራውን መንግሥት አይደለም፡፡ የአገር ሀብት ጥቅሙ ወደ ተሻለ ምርት ዘርፍ አዙሮ መጠቀምና የኢኮኖሚውን የማምረት አቅም ማሳደግ ከሰው ሳይመፀወቱና ሳይበደሩ ወይም የውጭ ኢንቨስተርም ሳይለምኑ፣ በራስ አቅም አቅርቦትን ከፍላጎት እኩል ማድረግ የሚቻለው ሸማቹና አምራቹ እንዲናበቡ በማድረግ ነው፡፡

ሸማቹንና ፍላጎትን የተመለከቱ ፖሊሲዎች

በሸማቹ ላይ ተፅዕኖ አድርጎ የሸመታ ዓይነትና መጠኑን ለመቀያየር፣ ለመጨመር፣ ለመቀነስ ወይም ለመለወጥ የገቢ መጠንን የመቀነስ የመጨመርና የመለወጥ ግብ ወይም የገቢ ክፍፍሉን የማመጣጠን ግብ በመንግሥት በጀትና በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲዎች ይገራል፡፡ የፍላጎት ጎን ፖሊሲ ሰዎችን መርጦ ስለማያበላልጥ አድልኦ የሌለበት ፖሊሲ ነው፡፡ በውጭ ምንዛሪ መጣኝ የብርን ዋጋ በማርከስ (Devaluation) ከአገር ውስጥ ምርት ጋር ሲነፃፀር የውጪውን ሸቀጥ ውድ በማድረግ ሸማቹ ከውጭ አገር ምርት ይልቅ፣ የአገር ውስጥ ምርትን እንዲመርጥ ዓለም አቀፍ የንግድ ስምምነቶችን ሳይጥሱ በፖሊሲ ተፅዕኖ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከውጭ ሸቀጥ ጋር የሚወዳደር ሸቀጥ በአገር ውስጥ መቼ ተመረተና ነው ብላችሁ አትጠይቁኝ፡፡ እኔ በመስማት ደረጃ የማውቀው ኢኮኖሚያችን ለአሥራ አምስት ዓመታት በተከታታይ በአሥራ አንድ በመቶ ማደጉን ነው፡፡

ሸማቾች የሚበሉት ምግብ፣ የሚጠጡት ውኃ፣ የሚለብሱት ልብስ፣ የሚኖሩበት ቤት፣ ምግብ ማብሰያቸው፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች፣ የሚጓጓዙበት የሞተር ትራንስፖርት፣ የሚታከሙበት ሐኪም ቤት፣ ለልጆቻቸው ትምህርት ቤት፣ እንዴትና በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚያገኙ የግላቸው ጥረት ቢወስነውም፣ እነዚህ መሠረታዊ የኑሮ ሸቀጦችና ሌሎችም ሸቀጦች ለሕዝቡ እንዴት እንደሚዳረሱ ለዕድልና ለዕጣ ፈንታ የሚተው ጉዳይ አይደለም፡፡ የሸመታ አቅምንና የሸቀጥ ጣዕምን የሚገራ የመንግሥት ፖሊሲም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ኢኮኖሚው በራሽን ይከፋፈል ማለት አይደለም፡፡ ፍላጎትን የመቆጣጠርና ካስፈለገም የመግራትና የመግታት ፖሊሲ የሚነደፈው የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለትን ወይም የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማቃለልና ከዕርዳታና ከብድር ተፅዕኖ ለመላቀቅም ነው፡፡ ወይም በውስጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሸማቹን ከዋጋ ግሽበት ለመከላከል ነው፡፡

በገቢ ድልድል ግብ ብዙ አገሮች ዝቅተኛውን የደመወዝ መጠን በሕግ በመደንገግ ሠራተኛውን ከብዝበዛና ከአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ይከላከላሉ፡፡ የሠራተኛው ገቢና የሸመታ አቅሙ ሲጨምርም አስተማማኝ ሸማች ሆኖ አምራቾችን ያበረታታል፡፡ በሺሕ አምስት መቶ ብር ደመወዝ ከከተማ ወጣ ያለ ደሳሳ ጎጆ በሺሕ ብር ተከራይቶ ከነቤተሰቡ አምስትና ስድስት ሆኖ የሚኖር ሸማች፣ በምንም መልኩ አምራቾችን ሊያበረታታ አይችልም፡፡ የገቢ መጠንና የገቢ ክፍፍል ለውጥ በሰዎች የሸቀጥ ሸመታ ዓይነት ጣዕም ላይ ብርቱ ተፅዕኖ ስለሚኖረው ገቢ ሲቀንስ በቅድሚያ ከገበያ የሚወጡት ትርኪምርኪ ሸቀጦች ናቸው፡፡ ገቢ ሲጨምርም ወደ ገበያ የሚገቡት እነኚሁ ሸቀጦች ናቸው፡፡ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የጥቂቶች ገቢ ሰማይ ደርሶ እንደ ዕርቃን ዳንስ ምሽቶች፣ የመዝናኛና ስፖርት ወሬዎችና ተረቶች የመሳሰሉ ትርኪምርኪ ሸቀጦችን እንዳግበሰበሰች የማያውቅ የለም፡፡ በመረጃ ላይ የተደገፈ የገበያ ጥናት ቢደረግ በገቢና በዋጋ ለውጥ የሸቀጥ ፍላጎት ልጠት (Income and Price Elasticity of Demand) ልኬቶች ገቢ ሲጨምርና ሲቀንስ፣ ወይም ዋጋ ሲጨምርና ሲቀንስ የትኞቹ ሸቀጦች በቅድሚያ ከገበያ እንደሚወጡና ወደ ገበያ እንደሚገቡ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

የፖሊሲ አቀንቃኞች ትምህርትና ጤና ለሁሉም እንዲዳረስ በመደረጉ የኑሮ እኩልነቱና መመጣጠኑ ተረጋግጧል፡፡ በዓለም አቀፍ የእኩልነት ኑሮ መለኪያ  (Gini Coefficient) መሠረት የኑሮ እኩልነቱ የተመጣጠነ የኑሮ ደረጃ ካላቸው (Welfare States) በመባል ከሚታወቁት ስዊድንን ከመሳሰሉ የስካንዲኔቪያን አገሮች ጋር የሚመሳሰል ነው ይላሉ፡፡ ለማስላትና ለመናገር ባይፈልጉም ሁላችንም እኩል ደሃ በነበርንበት የደርግ ዘመን በሀብት ፍትሐዊ ድልድል የስካንድኔቪያን አገሮችን እናስከነዳ ነበር ማለት ነው፡፡ ራሳቸው የኢኮኖሚ ባለሟሎቹንም ጨምሮ ብዙ የመንግሥት ሠራተኞች ከሃያና ሰላሳ ዓመት አገልግሎት በኋላም አራትና አምስት ሺሕ ብር የተጣራ የወር ደመወዝ እያገኙ፣ በድጋፍ በሚያብጡት የግል ንግድ ተቋማት ግን የእነሱን ያህል የሥራ ልምድ የሌላቸው ከሃምሳ እስከ መቶ ሺሕ ብር የወር ደመወዝ እንደሚያገኙ ሳያውቁ ቀርቶ ይሆንን? የእነሱን የወር ደመወዝ ያህል ሌሎች በሰዓታት የቦርድ ስብሰባ ተሳትፎ እንደሚያገኙስ አያውቁምን?

በቀድሞ ጊዜ በውጭ አገር የኑሮ ደረጃ ለሠራተኞቻቸው ይከፍሉ የነበሩትን የተባበሩት መንግሥታት አካል ድርጅቶች የሚያህል ክፍያ፣ ዛሬ የሠራተኛውን ምርታማነት ያላገናዘበ የወር ደመወዝ የአገር ውስጥ የግል ድርጅት ከሸማቹ ከሚመዘብረው ትርፍ ለሠራተኛው ይከፍላል፡፡ ምንም እንኳ ባለመታደላችን በቃላት ምስክርነት የመንግሥት ፖሊሲ አቀንቃኝ ምሁር ከመሆን አልፎ ተርፎ የደመወዝ ዕድገት የሥራ ቅጥርን ቀንሶ ሥራ አጥነትን እንደሚያስፋፋ በሒሳብ ለክቶ የሚያሳየን የኢኮኖሚ ባለሙያ ባይኖረንም፣ ጽንሰ ሐሳብን በተግባር ፈትሸው ከሚያረጋግጡት የፈረንጆቹ ምሁራን የሚሉትን በሰማነው ልክ ማመን እንችላለን፡፡

ፈረንጆቹ ከዚህም ባሻገር የደመወዝ ዕድገት ከምርታማነት ዕድገት በላይ ከፈጠነ ክስረት መሆኑንም ያረጋግጡልናል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የጥቂቶች የገቢ ዕድገት ከምርታማነት ዕድገት በመብለጥ ስትከስር ኖራለች፡፡ ይኼ ክስረትና ከሚያመርቱት በላይ ሸቀጦችን ለመሸመት መቻል ነው ዛሬ ልትፈነዳ አድርሶ አደጋ ላይ የጣላት፡፡ ሰው በማግኘቱ የሚጠላ ሰው የለም፡፡ በተለይም ኢኮኖሚስት ዋናው ሥራው ስለማግኘት እንጂ ስለማጣት አይደለም፡፡ ለመጨመር እንጂ ለመቀነስ ኢኮኖሚስት አያስብም፡፡ ነገር ግን ለአንዱ መጨመር ለሌላው መቀነስ ከሆነና የአንዱ ከልክ በላይ መጥገብ ሌላውን የሚያስርብ ከሆነ፣ የጠገበው ጥጋቡ እስከ ዕርቃን ዳንስ የሚያዋርደው ከሆነ ኢኮኖሚስትም ስለመቀነስ ያስባል፡፡

የውጭ ምንዛሪ መጣኝ መስተካከል አንድምታ

የገጠመንን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር ቀደም ብለን ተመልክተናል፡፡ የኤክስፖርቱና የኢምፖርቱን ንግድ ስንገመግመው ከዓመት ዓመት ክፍተቱ እየሰፋ እንጂ እየጠበበ አልመጣም፡፡ ብድሩም ስለተቆለለ ዕዳው ሳይከፈል በፊት ሌላ ብድር ማግኘት ሊቸግር ይችላል፡፡ የምንዛሪ መጣኙ ቢስተካከል የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ችግር ይቀረፍ ይሆን? የዓለም የገንዘብ ድርጅትም መንግሥትን የምንዛሪ መጣኙን አርክሱ (Devalue) እያለ እየወተወተ ስለሆነ ማርከሱ ይጠቅማል፡፡ የብድር ከፋይነት አቅም ገማች ድርጅቶችም መንግሥት በቀጥታ ከወሰደው ይልቅ፣ ባለበጀት ያልሆኑ የመንግሥት ድርጅቶች የወሰዱት ብድር አሳሳቢ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ የምንዛሪ መጣኙ መለወጥ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ይቀርፍ እንደሆን ለመረዳት ስለባንኮች ጥሬ ገንዘብ ሀብት (Monetary Assets of Banks) ዓይነትና መጠን፣ ስለጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠን (Money supply) እና ስለየውጭ ምንዛሪ መጣኝ አወሳሰን ሥርዓቶች (Exchange Rate Regimes) አንዱ በሌላው ላይ ስለሚያሳድረው ተፅዕኖና በገበያ ውስጥ ስለሚያደርጉት መስተጋብር ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ምንጮች የባንኮች ገንዘባዊ ሀብቶች ሲሆኑ፣ እነርሱም ከዕዳ ቀሪ የተጣራ የውጭ ምንዛሪ ሀብት (Net Foreign Asset) እና የአገር ውስጥ ብድር ሀብት (Domestic Credit) ተብለው በሁለት ይከፈላሉ፡፡ አንዱን በሌላው በመሸጥና በመግዛት ግብይት ምክንያት አንዱ ሲጨምር ሌላው ይቀንሳል፡፡ ወይም በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠን ፖሊሲ ምክንያት ሁለቱም ሊጨምሩም ይችላሉ፡፡ የሁለቱም መጨመር የሸቀጦችን ዋጋ ያንራል፡፡ በሌላ የብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት ውስጥ ባለ የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ መረጃ መሠረት፣ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ምንጭ ከሆኑት ሁለት የባንኮች (የብሔራዊ ባንክና የንግድ ባንኮች በአንድነት) ጥሬ ገንዘብ ሀብቶች ውስጥ ከዕዳ ቀሪ የተጣራ የውጭ ምንዛሪ ሀብት እየቀነሰ፣ በምትኩ የአገር ውስጥ ብድር ሀብት እየጨመረ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

ለምሳሌም በ2006 ዓ.ም. አርባ ስድስት ቢሊዮን ብር በብር የተመነዘረ ከዕዳ ቀሪ የተጣራ የውጭ ምንዛሪና ሦስት መቶ ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ብድር የባንኮች ጥሬ ገንዘብ ሀብት፣ በ2007 ዓ.ም. ሰላሳ ስምንት ቢሊዮን ብር በብር የተመነዘረ ከዕዳ ቀሪ የተጣራ የውጭ ምንዛሪና ሦስት መቶ ዘጠና ሦስት ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ብድር የባንኮች ጥሬ ገንዘብ ሀብት በመሆን በቅንብሩ በ2007 ዓ.ም. የተጣራ የውጭ ምንዛሪ ሀብት ድርሻ ቀንሶ የውስጥ ብድር ሀብት ድርሻ ጨምሯል፡፡ ወደኋላ ሄደን ስንመለከትም በ2003 ከነበረው ጠቅላላ የባንኮች ጥሬ ገንዘብ ሀብት ውስጥ ሃምሳ አምስት ቢሊዮን ብር በብር የተመነዘረ ከዕዳ ቀሪ የውጭ ምንዛሪ ሀብት ሲሆን፣ የአገር ውስጥ ብድር ሀብት አንድ መቶ ሰላሳ ስድስት ቢሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ መረጃዎቹ በየዓመቱ የተጣራ የውጭ ምንዛሪ የባንኮች ሀብት እየቀነሰ የአገር ውስጥ ብድር ሀብት መጨመሩን ያሳያሉ፡፡

ስለጥሬ ገንዘብ ምንጮች ይህን ያህል ካወቅን ስለውጭ ምንዛሪ መጣኝ አወሳሰን ሥርዓቶች ደግሞ አንዳንድ ነጥቦችን እንመልከት፡፡ ሦስት ዓይነት የውጭ ምንዛሪ መጣኝ አወሳሰን ሥርዓቶች አሉ፡፡ እያንዳንዱም የየራሱ ጥቅምና ጉዳት አለው፡፡ በተንሳፋፊ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ አወሳሰን ሥርዓት (Floating Exchange Rate Regime) የውጭ ምንዛሪ መጣኙ በገበያ ዋጋ ስለሚወሰን፣ ብሔራዊ ባንክ በገበያ ውስጥ ተሳትፎ ለማድረግ ጣልቃ አይገባም፡፡ በአገር ውስጥ ብድር የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠን ላይ ብቻ አትኩሮ በሸቀጦች ዋጋ ውጣ ውረድ አማካይነት የውጭ ምንዛሪ መጣኝን በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲው ተቆጣጥሮ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትና አቅርቦት እንዲጣጣሙ ያደርጋል፡፡ በተንሳፋፊ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ አወሳሰን ሥርዓት የአገር ውስጥ ምርት ሸቀጦች የገበያ ዋጋ ከውጭ ከሚገቡ የኢምፖርት ሸቀጦች የገበያ ዋጋ ጋር በሚደረግ ንፅፅር የውጭ ምንዛሪ ተፈላጊነትና አቅርቦት በራሱ የውስጥ ሒደት ተስተካክሎ፣ ዋጋውም በገበያ ኃይላት መስተጋብር ይወሰናል፡፡ መንግሥት በቀጥታ የውጭ ምንዛሪ ገበያው ውስጥ ሳይገባ የሸቀጦችን ዋጋ በጥሬ ገንዘብ አቅርቦቱ እየተቆጣጠረ የውጭ ምንዛሪ መጣኙ ላይ በተዘዋዋሪ መንገድ ተፅዕኖ ያደርጋል ማለት ነው፡፡

ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ግብይት ተፅዕኖ አሳድሮ በአገር ውስጥ ብድር ጥሬ ገንዘብ መብዛትና ማነስ የሸቀጦች ዋጋን በማስወደድና በማርከስ፣ በእርግጠኛ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ (Effective Real Exchange Rate) የብር ዋጋ እንዲቀንስ ወይም እንዲጨምርም ያደርጋል፡፡ እርግጠኛ መመነዛዘሪያ መጣኝ የአንድ አገር ምንዛሪ ሸቀጦችን በመግዛት አቅሙ ከሌላው ተገበያይ አገር ምንዛሪ ሸቀጦችን ከመግዛት አቅም ጋር ሲወዳደር፣ ወይም በተመናዛሪዎቹ አገሮች ውስጥ ያለውን የዋጋ ንረት ልዩነት ከግምት ያስገባ የመመነዛዘሪያ መጣኝ ማለት ነው፡፡ ይህም ኤክስፖርትን ለማሳደግና ኢምፖርትን ለመግታት አገሮች የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው፡፡ ለምሳሌ ሃያ ብር በአንድ የአሜሪካ ዶላር ይመነዘር ከነበረና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የአሥር በመቶ የዋጋ ንረት ተከስቶ በአሜሪካ ግን የአምስት በመቶ ብቻ የዋጋ ንረት ከተከሰተ፣ የዋጋ ንረቱ ተቀናንሶ ከዶላር ዋጋ አንፃር የብር ዋጋ በአምስት በመቶ ዝቅ ስለሚል የብርና የዶላር መመነዛዘሪያ አንድ ዶላር በሃያ አንድ ብር ይሆናል፡፡ በዚህም አንድ ዶላር የሚያወጣ የአሜሪካ ሸቀጥ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ በአንድ ብር ተወዶ ሃያ አንድ ብር ሲሆን፣ ሃያ ብር የሚያወጣ የኢትዮጵያ ሸቀጥ ወደ አሜሪካ ሲገባ ግን ዋጋው ዘጠና አምስት የአሜሪካ ሣንቲም ብቻ በመሆን በአምስት የአሜሪካ ሣንቲም ይረክሳል፡፡ ለኢትዮጵያ ሁኔታው ኤክስፖርት በመርከስ በአሜሪካ ገበያ ተወዳዳሪ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ገበያ የአሜሪካ ኢምፖርት ውድ ስለሚሆን ተወዳዳሪ አይሆንም፡፡  

በቅድሚያ በሚወሰን ቋሚ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ አወሳሰን ሥርዓት (Fixed Exchange Rate Regime) በፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ምክንያት የውጭ ምንዛሪው መጣኝ ከተወሰነው እንዳይቀያየር፣ ብሔራዊ ባንኩ በገበያው ውስጥ በቀጥታ ተሳትፎ አድርጎ የውጭ ምንዛሪ በመግዛትና በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትና አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ በማድረግ ይከላከላል፡፡ በቋሚ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ ሥርዓት ብሔራዊ ባንክ የምንዛሪ መጣኙ እንዳይለወጥ የውጭ ምንዛሪ ሲገዛና ሲሸጥ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ጥሬ ገንዘብ ሀብቱን መጠን (Foreign Reserve)፣ የእርሾ ጥሬ ገንዘብን መጠን (Reserve Money) እና በአጠቃላይ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦትን መጠን (Money Supply) የመቆጣጠር አቅሙን ያጣል፡፡ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠን በፖሊሲ የሚወሰን በመሆን ፈንታ በኢኮኖሚው ውስጣዊ መስተጋብር ኃይል የሚወሰን ይሆናል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ለመግዛት በሚወጣው የአገር ውስጥ ብድር ጥሬ ገንዘብ መብዛት የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በውጭ ምንዛሪ ግዢ ምክንያት የተፈጠረውን ተጨማሪ የአገር ውስጥ ብድር ጥሬ ገንዘብ ለማምከን (Neutralization)፣ በአገር ውስጥ የሰነድ ገበያ ሰነዶችን ሸጦ ጥሬ ገንዘብ ከገበያ ውስጥ በማስወጣት መጠኑን መቀነስ ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ግን የተደራጀ የሰነዶች ገበያ ስለሌላትና ለማምከን ብላ ብዙ የመንግሥት ሰነዶችን ከሸጠች ከጊዜ በኋላ የወለድ መጣኙን ለመክፈል ከባድ የበጀት ጫና ስለሚፈጥርባት ማምከን የምትችለው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እርሾ ጥሬ ገንዘቧ በውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀመቀጯ ያልተደገፈ መሆኑን የመጠን ልዩነታቸው ስለሚገልጽ ግን የማምከን ዕድሉ አላት፡፡ አንዳንድ አገሮች ምንም እንኳ የገንዘብ አቅርቦት መጠንን መወሰን አቅም ቢያሳጣቸውም የውጭ ምንዛሪ መጣኛቸውን ዝቅተኛ የዋጋ ንረት ካለው አገር ምንዛሪ ጋር ተለጣፊ (Pegged) ያደርጋሉ፡፡ በዚህም የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲያቸው የሚወሰነው ተለጣፊ በሆኑበት አገር የብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ ሲሆን፣ በውጭ ምንዛሪ መጣኝ ገበያ ሙሉ ተሳትፎ አድርገው የውጭ ምንዛሪ በመግዛትና በመሸጥ የክፍያ ሚዛን ሒሳባቸውን ጉድለት ማስተካከል አይችሉም፡፡ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ መጣኟን ከአሜሪካ ዶላር ጋር አስተሳስራ ተለጣፊ ስላደረገች፣ በውጭ ምንዛሪ ገበያ ሙሉ በሙሉ ያልሆነ በምንዛሪ ቦርድ የሚወሰን ከፊል ተሳትፎ ስለምታደርግ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀማጭ ሀብቷን የመደጎም አቅሟ በምንዛሪ ገበያ ተሳትፎዋ ልክ የተገደበ ነው፡፡ ስለሆነም ከኢትዮጵያ ጋር የንግድ ግብይት በሚያደርጉ አገሮች ምንዛሪና በአሜሪካ ዶላር የምንዛሪ መጣኝ ለውጥ ሲደረግ በተመነዛዛሪ አገሮቹ የእርግጠኛ የምንዛሪ መጣኝ ለውጥ ምክንያት፣ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸውና ወደ ውስጥ የምታስገባቸው ሸቀጦች ዋጋዎች ተለውጠው ከለውጡ ተጠቃሚም ተጎጂም የምትሆንበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡

በየትኛው ምርትና ሸቀጧ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ፈልጋ እንደሆነ ባይታወቅም፣ አገሪቱ በውጭ ንግድ ፖሊሲዋ ኤክስፖርት ተኮር ፖሊሲ እንደምትከተል ትለፍፋለች፡፡ ይልቁንስ ጧት ማታ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ግቡ የምትላቸው ባለሀብቶች ከቻይና ኢምፖርት ሸቀጥ ወረራ ጥበቃ ካልተደረገላቸው፣ ለሕዝባቸው የኢምፖርት ሸቀጥ ምትክ የሚሆን የፍጆታ ምርት ማምረት እንደማይችሉ ብታስብበት ይበጃት ነበር፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ ቢወጣ ቢወርድ በግለሰብ ደረጃ ለሰፊው የኢትዮጵ ሕዝብ አይበርደው አይሞቀው፡፡ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው ገቢው በአገር ውስጥ ለሚመረት የግብርናና አገልግሎት ምርት፣ ቀሪው አሥር በመቶም ለልባሽ (ሳልቫጅ) ጨርቅና ጫማ ለሆነ ሕዝብ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ መውጣት መውረድ ምን ትርጉም አለው? ኑሮው ከዓለም ሕዝብ የኑሮ ዓይነት ጋር ለመዋሀድ ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ አገር አይጎበኝ፣ አውሮፕላን አይሳፈር፣ የአውሮፓና የአሜሪካ ሸቀጦች አይሸምት፡፡ ቻይና በምታራግፍበት ትርኪምርኪ ሸቀጥ ምናልባት መጠነኛ ጉዳት ሊደርስበት ይችል ይሆናል፡፡ የድህነት ቅነሳውን ለክተው ከሌሎች አገሮች ጋር የሚያነፃፅሩትና ቀነሰ የሚሉ ሰዎች ስህተት እዚህ ላይ ነው፡፡ የፍጆታ ሸቀጦች ቅርጫታችን ከዓለም ሕዝብ የፍጆታ ሸቀጦች ቅርጫት ጋር የሚነፃፅረው በንጥረ ነገር (ኒዩትሪሽን) መጠን ብቻ እንጂ፣ ጥራቱ በሚሰጠን ደስታና እርካታም ጭምር አይደለም፡፡ አሰስ ገሰስ ሰብሳቢዎች ሆነናል፡፡

በውጭ ምንዛሪ መጣኙ መውጣት መውረድ ተጠቃሚና ተጎጂ የሚሆኑት የመንግሥት ሜጋ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ እንደ አገር ስናስብ ግን የመንግሥትም ሆነ የግል ልማት ሲደናቀፍ የሚጎዳው ሁሉም ኅብረተሰብ ነው፡፡ በግለሰቦች ደረጃ ግን የውጭ ምንዛሪ መጣኙ መውጣትና መውረድ የሚጎዳውና የሚጠቅመው ጥቂት የውጭ ሸቀጦች ተጠቃሚ ሀብታሞችን ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ነዋሪዎች ይልቅ የስደተኛ (ዳያስፖራ) ዜጎች በውጭ ምንዛሪ መጣኙ መውረድና መውጣት ተጎጂና ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ምክንያቱም በሚኖሩበት አገር የኑሮ ደረጃ ልክ የሚከፈላቸው የውጭ ምንዛሪ ወደ ኢትዮጵያ ብር ተቀይሮ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገዛላቸው ቋሚ ንብረት ኑሯቸውን ስለሚለውጠው ነው፡፡ ወደ አገር ቤት ሲመጡ ከውጭ ዜጎች እኩል የትልልቅ ሆቴሎች ተጠቃሚ የሚሆኑትም እነሱ ናቸው እንጂ፣ የአገር ውስጥ ነዋሪ ዜጋማ በምን አቅሙ በደጃፋቸው ቢያልፍ ይበቃዋል፡፡ ውጭ እየኖሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ቤት ገዝቶ ወይም ሠርቶ በጥበቃ ሠራተኛ ማስጠበቅ ተለምዷል፡፡ አብዛኞቹ የሚኒባስ ታክሲዎች ባለቤቶች ዓረብ አገር በግርድና ሁለትና ሦስት ዓመት የሠሩ ናቸው፡፡ እኔም አንድ ሁለት ዓመት ዱባይ ወይም ደቡብ አፍሪካ ሄጄ ጉልበቴን ሸቅዬ (ሸቅጬ) ብመጣ ሳይሻለኝ አይቀርም፡፡

በውጭ ምንዛሪ ተጠቃሚው ሰው ማነስ ምክንያትም ነው ባለፉት ሃያ ዓመታት የአገር ውስጥ ሸቀጦች ዋጋ እስከ ሃያ እጥፍ ሲያድግ፣ የዶላር ምንዛሪ ዋጋ ግን በሦስት እጥፍ ብቻ ያደገው፡፡ ሌላው የምንዛሪ መጣኙ ቢወድቅ ቢነሳ ሕዝቡ በግል ደረጃ እንደማይሞቀውና እንደማይበርደው አመላካች የጥቁር ገበያውና የኦፊሴል መመነዛዘሪያ ዋጋው ተመጣጣኝ መሆን ነው፡፡ የጥቁር ገበያው ተገበያዮች ሻጩም ገዢውም ቁጥር እጅግ አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ፣ በኦፊሴል የመገበያያ ዋጋው ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድርና በፍጥነት ሊቀያይረው አልቻለም፡፡ ይህ ያልገባቸው ወይም ማደናገር የሚፈልጉ የኢኮኖሚ ባለሟሎች የፖሊሲያቸው ትክክለኛነት በጥቁር ገበያው ዋጋ የተረጋገጠ ይመስላቸዋል፣ ወይም ያስመስላሉ፡፡

ማጠቃለያ

ሃያ አምስት ዓመት ሙሉ በአንድ በአቅርቦት ዓይን ብቻ ሲያይ የኖረው የኢሕአዴግ መንግሥት ማጣፊያው ጠፍቶታል፡፡ በውጭ ምንዛሪ ዕጦት ምክንያት ኢምፖርቱን ቢገድብ የካፒታል ዕቃዎችን ማስገባት አቅቶት ኢኮኖሚው አሥራ አንድ በመቶ ላያድግ ነው፡፡ ገና ከጅምሩ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መኖሩ ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶቹ ተንጠልጥለዋል፡፡ የካፒታል ፕሮጀክቶች መንጠልጠል  ወዲያው ችግሩ ወደ ኅብረተሰቡ በፍጆታ ሸቀጦች እጥረት መልክ አይሸጋገርም፣ ቀን ይጠብቃል፡፡ በዚህ ሁኔታ እያለ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋን ጨምሮ የቀድሞው ቦታ ቢመለስ እንኳ የሚገባበት ቀዳዳ ያጣል፡፡ የጥሬ ገንዘብ አስፋፊ ፖሊሲ ተጠቅሞ ኤክስፖርትን ርካሽ፣ ኢምፖርትን ውድ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀማጩን ሊያሳድግ ቢሞክር የሸቀጦች ዋጋ ግሽበት የውስጥ ኢኮኖሚ ቀውስ ስለሚፈጠር ግራ ገብቶታል፡፡

 የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት አሥጊነት ደረጃን ለመወሰን ሌሎች ወሳኝ ጉዳዮችም ከግምት ውስጥ ይገባሉ፡፡ እነሱም በቅርብ ጊዜ መከፈል የሚገባቸው የውጭ ዕዳዎች ክምችት፣ የአገሪቱ አዲስ የውጭ ምንዛሪ የመበደር አቅም፣ ኤክስፖርትና ኢምፖርት የውጭ ንግድ ከአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ድርሻ እንደ አብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀማጭ ብዙም ይሁን ጥቂት አንዲት አገር ባላት የውጭ ምንዛሪ ክምችት መጠን ላይ መተማመኗ፣ ከውጭ አገሮች ጋር በሚኖራት ግንኙነትና በድርድር ሊገኙ ከሚችሉ አጋጣሚዎች አንፃር ሊታይም ይችላል፡፡ የዕዳ ስረዛና ልዩ ድጋፍ ማግኘት፣ የዕዳ ክፍያ ጊዜን የማስተላለፍ፣ የውጭ ዕዳን ከነወለዱ ሳይከፍሉ ማከማቸት፣ የመሳሰሉት ሁኔታዎች የውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረትን ሥጋት የሚቀንሱ ናቸው፡፡ ‘ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል’ ይባላል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎች መንግሥት የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀማጭ እጥረት እንዳለበት ደብቆ ሊያቆይ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ናቸው፡፡ ሆኖም እንደ ፀጉራሙ ውሻ አንድ ቀን ሞት መጥቶ ይወስደዋል፡፡ የዚህ ሞት ዓይነት ድባብ በኢኮኖሚያችን ውስጥ እየተስተዋለ ነው፡፡

የኢሕአዴግ መንግሥት እስከዛሬ አገሪቱ ያላትን ጂኦ ፖለቲካ በመጠቀም ከውጭ መንግሥታት ጋር በመወዳጀትና ዕርዳታና ድጋፍ በማግኘትና ደርግ የወረሳቸውን የሕዝብ ንብረቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች በመሸጥ፣ የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾችን በመጋበዝ፣ የአገሪቱ ሕዝቦች ወደ ውጭ ሄደው ጉልበታቸውን ሸጠው የውጭ ምንዛሪ ለዘመዶቻቸው እንዲልኩ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን በከፊል ተቋቁሞታል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ለሁልጊዜው አይቀጥልም፡፡ በአንድ እጅ የሚያጨበጭቡ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካሪዎች ፍላጎትን ትተው ስለአቅርቦት ብቻ እያሰቡና እያወሩ ገደል ሊከቱን ነው፡፡ ስለኑሮአችን ከእኛ በላይ ሊያስብ የሚችል ሰው የለም፡፡ ዝምታም ሁላችንንም ገደል ውስጥ ይከተናል፡፡ ኢኮኖሚው ወደ መውደቅ ያዘነበለ መሆኑ የሚታያቸው ሁሉ ደመናውን ለመግፈፍ አስተያየታቸውን ቢለግሱ ጥቅሙ ለሁላችንም ነው፡፡ የፖሊሲ ስህተት እንደ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ሰውን በመቆጣትና በማስፈራራት በአጭር ጊዜ ውስጥ አይታረምም፡፡ መንግሥት ግን የፖሊሲ ድክመት የሌለ ለማስመሰል ጉዳዩን በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት እያሳበበ ጊዜ መግዛቱን መርጧል፡፡ ሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነትም ቢሆኑ የሚፈሩት ተቆጪ ሰው ሲኖር ነው የሚታረሙት፡፡ ከላይ ያለው ሙሰኛ ከታች ያለውን ሙሰኛ ሲቆጣው፣ ከታች ያለውም የበታቹን ሲያስፈራራ እኛ ቴአትር ቤት ያለን ይመስል ቁጭ ብለን እንመለከታለን፡፡ ጎርፉ ሲመጣ የላይኛውንና የታችኞቹን ሙሰኞች ብቻ ሳይሆን እኛንም ይወስደናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው Getachewasfaw240@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

Standard (Image)

የፀረ ሙስና ትግሉን ለማስተባበር ከመንግሥት እውነተኛ የሆነ በቂ ድጋፍ ሊገኝ ይገባል

$
0
0

በይስማ እውነቱ

ሙስና በኢትዮጵያ ለዘመናት እንደ ባህል ጭምር እየተወሰደ የኖረ ነው፡፡ የሙስና ተቀባይና ሰጪም እንደ መብትና ግዴታ አድርጎ የሚጠቀሙበት ዘርፍም ነበር፡፡ ከደርግ መንግሥት በፊት ‘ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል’ እየተባለ በተለይም የመንግሥት ሹመኞችና የጎበዝ አለቃ የሆኑ ሰዎች በጠራራ ፀሐይ ጉቦ ይሰጡና ይቀበሉ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ጉዳይ ለማስመፈጸም፣ ሹመት ለማግኘት፣ የተጣሉትን ሰው ለመበቀል፣ አንድ ጉዳይ ከአንዱ ተነጥቆ ለሌላ እንዲሰጥ ጉቦ ይሰጥ ነበር፡፡ ጉቦ የሚሰጠው በጥሬ ገንዘብ ወይም በንብረት ነበር፡፡ ለምሳሌ ከጥሬ ገንዘብ በተጨማሪ ሠንጋ በሬ፣ በግ፣ መሬት፣ ቤት ወይም ፋብሪካ መስጠት፣ አንዳንዴ ሴት ልጅ በመዳርም ጭምር እንደ ጉቦ ይወሰድ ነበር፡፡ የደርግ መንግሥት ሲመጣ የዕዝ ኢኮኖሚ ሥርዓት ሲያራምድ ስለነበር በግሉ ዘርፍ እዚህ ግባ የሚባል የግል ባለሀብት አልነበረም፡፡ ሁሉም ነገር የመንግሥት ስለነበር፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ሹመኞች አንዳንድ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ጉቦ ይጠይቁና ይቀበሉ ነበር፡፡ ጉቦ ብቻም አይደለም የሚወስዱት፡፡ ከጉቦ ውጪ በዘመድ፣ በሃይማኖት፣ በብሔር የማዳለት፣ የመንግሥት ንብረት የመስረቅ፣ የማጭበርበር ከደርግ መንግሥት በፊትም ሆነ በኋላ የተለመደ ነበር፡፡ ጉቦ መስጠትና መቀበል ቢኖርም የጉቦ ገንዘብ መጠኑ ግን በጣም ትንሽ ነበር፡፡ የባለሀብት የካፒታል መጠንም ውስን ስለነበር፡፡

ስለ ደርግ ሥርዓት ዛሬ ላይ የሥራ ውጤታማነትን ብዙ ባላውቀውም የሠርቶ አደር ቁጥጥር ኮሚቴ የተዋቀረው ጉቦ የሚወስዱትን ሰዎች ለመቆጣጠር ነበር ሲባል ሰምቼለሁ፡፡ በጥቁርና በነጭ ካሜራ ቪዲዮ የተቀረፀ ጉቦ ‘ጉቦ…’ የሚባል ዘፈንም በቴሌቪዥን አይ ነበር፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የደርግን ሥርዓት ገርስሶ ወደ ሥልጣን የመጣ ሰሞን እነዚህን የሕዝብ ነቀርሳ የሆኑ ጉዳዮች ላይ አቋሙ በጣም ጠንካራ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ እንዲያውም ወደ ግንቦትና ሰኔ ወር 1983 ዓ.ም. አካባቢ ስርቆት የፈጸሙትን ሰዎች አስፋልት ላይ ይረሽን ነበር፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የዕዝ ኢኮኖሚ ሥርዓትን በማፍረስ ወደ ካፒታሊስት ሥርዓት ሲቀይር አንዳንድ የመንግሥት ተቋማት ወደ ግል ይዞታ ይዞሩ ነበር፡፡ ያኔ ነው እንግዲህ የመንግሥት ኃላፊዎች የጉቦ የገንዘብ መጠንን በማሳደግ መጠየቅና መቀበል የጀመሩት፡፡ ብዙዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ማረሚያ ቤት ገብተው እንደነበር እስታውሳለሁ፡፡ በተለይም አቅም ያላቸው የግል ባለሀብቶች ብቅ ብቅ ማለት ሲጀምሩ ዘመናዊ ሆቴሎች፣ መዝናዎች፣ የግል ሆስፒታሎች፣ ሪዞርቶች፣ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች ሲገነቡ፣ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች አገር ውስጥ መግባት ሲጀመሩ በቃ የመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞች ይህን እያዩ በመጓጓት ድርሻችንን እንውሰድ በሚል ዕሳቤ ወደ ሙስና ጭልጥ ብለው የገቡ ይመስለኛል፡፡ ዘመናዊ አልባሳትም ወደ አገሪቱ መግባት ጀመረ፡፡ የመንግሥት በጀትም ከአሥር ቢሊዮን በታች የነበረው ወደ 100 ቀጥሎም ወደ 200 ቢሊዮን አሁን ደግሞ ወደ 300 ቢሊዮኖች እያደገ ነው፡፡ ዕቃ ከአገር ውስጥ ወደ ውጭ በብዛት መላክ ወይም ከውጭ ወደ አገር ውስጥ በብዛት ማስገባት ተጧጧፈ፡፡ ተጨቁነው የኖሩት የግል ባለሀብቶች ብዙ ገንዘብ መያዝ ጀመሩ፡፡ የዶለር ዋጋ ምንዛሪ ከ2.07 ወደ 21 እና በላይ አደገ፡፡  

በዚህም ሀብት የሚፈልጉ የመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞች ልባቸውን ያማለለውንና ለሕዝብ ከመኖር ይልቅ ለራሳቸው መኖርን መርህ አድርገው ተያያዙት፡፡ ኃላፊነት መርሳት ጀመሩ፡፡ በሀብት ላይ ሀብት የሚፈልግ ባለሀብት ለመንግሥት ሹመኞች ጉቦ መስጠት የጀመረው በቂ ገንዘብ ማግኘት ሲጀምር ነው፡፡  አንዳንዱ ባለሀብት በብድር ባገኘው 5000 ብር የጀመረውን የንግድ እንቅስቃሴ አሥር ዓመት ባልሞላበት ጊዜ ውስጥ አሥር ሚሊዮን አደረሰው፡፡ ይህ ዕድገት ሜርኩሪ ወይም አልማዝ ሸጦ ሳይሆን በሰጥቶ መቀበል መርህ ከመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞች የተቸረው ስጦታ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ እዚህ ላይ በልፋታቸው ያደጉትን ባለሀብቶች ይህ ጉዳይ አይመለከትም፡፡ ብዙ ልማታዊ ባለሀብት አለና፡፡ ገንዘብ የሚፈልግና ሕዝብን በመርሳት ለራሱ መኖር የጀመረው የመንግሥት ሠራተኞም ሆነ ሹመኛ የተሰጠውን ኃላፊነት ተጠቅሞ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለአንዱ በማዳላት ሌለውን በመጉዳት ጥቅም ማግኘትን ሙያ እያደረገ መጣ፡፡ የመንግሥትን ጥቅም በማስቀረት ቢያንስ ሲሶውን ወደ ኪሱ ማስገባት ጀመረ፡፡ አመቺ መንገድ ሲያገኝ በግልም ሆነ ከሌላ ጋር በመሆን የመንግሥት ሀብትና ንብረት መስረቅ ጀመረ፡፡ በማጭበርበር ገንዘብ ማግኘት እንደ ጀብዱና እንደ መብት እየወሰደ መጣ፡፡ ሌሎች ምቹና አዋጪ ነው ያላቸውን ዘዴዎችን በሙሉ በመጠቀም ገንዘብና ሀብት አገኘ፡፡

ከፍተኛ ገንዘብ ያገኘው የመንግሥት ሹመኛ ባገኘው ገንዘብ ንብረት አፈራ፣ ዛሬ ላይ የመንግሥት ሹመኛ ሆኖ ከሚከፈለው ከ3,500 እስከ 5,000 ብር ባልሞላ ገንዘብ ዘመናዊ ቤት ገነባ፣ በዶለር ማከራየት ወይም ከ30 እስከ 50 ሺሕ ብር በላይ በማከራየት መንግሥት በሹመቱ በሰጠው ቤት ውስጥ በነፃ መኖር ሥራዬ ብሎ ተያየዘ፡፡  ልጆቹን አገር ውስጥ ወይም ውጭ አገር ጥሩ ትምህርት ቤት ያስተምራል፡፡ ዘመናዊ ሆቴልና ሪዞርት ሚስቱንና ልጆችን ይዞ እንደ ልቡ ይዝናናል፡፡ ሲያስፈልግ ውጭ አገር ሄዶ ይዝናናል፡፡ ልማታዊ ያልሆነው ባለሀብት የአየር መንገድ ትኬት እየገዛለትና ወጪውን እየቻለለት ይዝናናል፡፡ በድህነት ጊዜ ያገባትን ሚስቱን ትቶ በጣም ውብና ዘመናዊ ሴት ያገባል ወይም ቤት ተከራይቶ ያስቀምጣል (ጎተራ አካባቢ ያለውን ኮንዶሚኒየም ይመለከቷል) ወይም ይወሽማል፡፡ ያኔ ሳይማር ያስተመረውን ኅብረተሰብ ይረሳል፣ ለኅብረሰብ መኖር ይረሳና ለራሱና ለቤተሰቡ ብቻ መኖር ይጀምራል፡፡ ቅንጦት ሕይወትን ስለለመደ የመረጠውን ሕዝብን አያስታውስም፡፡ በሐዝብ ስም ይምላል፣ ነገር ግን ጭንቅላቱ በጥጋብና በትዕቢት ስለተወጠረ ሕዝብን ይረሳል፡፡ ሕዝብ የት እንዳለም አያውቅም፣ ሁሉም እንደ እሱ ደልቶት የሚኖር ይመስለዋል፡፡ የሙሰኛ ሹመኛ የመጨረሻ እውነታውም ይህ ነው፡፡

በሰጠው አገልግሎት ዝቅተኛ ጥቅም የሚያገኘው የመንግሥት ሠራተኛም ቢሆን ዘመናዊ ሞባይል ይገዛል፡፡ ሳምሰንግ፣ አፕል፣ ዘመናዊ ልብስ ገዝቶ ይለብሳል፡፡ በተለይም ወጣት ከሆነ መኪና ያስፈልጋዋል፣ ከሴት ጓደኛው ጋር ዘመናዊ ሆቴልና  የመዝናኛ ቦታ ላይ መታየትንና ጊዜ ማሰለፍ ይፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ ወጣት ስለሆነ መዝናናት ይፈልጋል፡፡ ሙሰኛ የመንግሥት ሠራተኞች የቤት ሽሮ መብላት አይፈልጉም፡፡ ምሳ ቋጥረው ቢሮ አይመጡም፡፡ ከተማ ውስጥ እንደ አንበሳ የሚበላው ጥሬ ሥጋ እንደ አሸን ተደራሽ ከሆነው ቢራ ጋር ማጣጣም ይፈልጋል፡፡ የቤት ኪራይ በአሁኑ ጊዜ ውድ ስለሆነ ቢያንስ የተሻለ ኮንዶሚኒየም ቤትም ቢሆን ተከራይቶ መኖር ይፈልጋል፡፡ ብዙዎቹበቂ ገንዘብ ካለቸው ኮንዶሚኒየም ይገዛሉ፡፡ ካልሆነም የገበሬ መሬት ይገዛሉ፣ ቤት ይሠራሉ፣ ሕገወጥ ተብሎ ካልፈረሰ ቤት አለኝ ለማለት ይፈልጋሉ፡፡ ይህ በዕውቀታቸውና በክህሎታቸው በአንስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው ሀብታም ለመሆን የሚጥሩ መልካም ዜጋ የሆኑ ወጣቶችንና ሌሎችን አይመለከትም፡፡ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው ለጥቅም ብለው ሕዝብን የሚያጉላሉ ወጣት ተቀጣሪ ሠራተኞች ብቻ ለማለት ነው፡፡ ይህንን ስል ወጣት ያልሆኑት ሙስና አይሠሩም ማለቴ አይደለም፣ ይሠራሉ፡፡ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ በዕድሜ ከፍ ያሉና ሙስና የሚሠሩት ሰዎች በብዛት ሹመኞች ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ሠራተኞችና ሹመኞች የተጣለባቸውን የሕዝብ አደራ ወደኋላ በመተውና በመርሳት ወደ ገንዘብ ፍለጋ በሚሰጡት አገልግሎት ላይ ኅብረተሰቡን የሚያጉላሉት፡፡ አንድ ጊዜ ክፍለ ከተማ የመጀመሪያ ቀን ጃኬት ለብሼ አገልግሎት ፍለጋ ሄድኩ፡፡ የሚያናግረኝን አጥቼ ተመለስኩ፡፡ በሌላ ቀን ስብሰባ ነበረኝና ሙሉ ልብስ ለብሼ አጋጣሚውን ተጠቅሜ ባለፈው ጊዜ የሚያነግረኝ ወደ አጣሁበት ቢሮ ስሄድ እንደ ንብ ነበር እየወራሩ ምን እንደምፈልግ የተጠየቅኩት፡፡ ላለው አገልግሎት አሰጣጥ ፈጣን ነው፡፡ በገንዘቡ አገልግሎቱን ያፈጥናል፡፡ የመንግሥት ሹመኞች የመንግሥትና የሕዝብ ሀብትና ንብረት ይዘርፋሉ፡፡ ለዘረፋውም ስትራቴጂና ሥልት ቀይሰው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የሚገርመው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር፣ የመልካም አስተዳደር ማስፋን በሚሉ ጉዳዮች ግንባር ቀደም ሆነው መፈክር የሚያስሙት እነሱ መሆናቸው ነው፡፡ በአጭር ቃል ኪራይ ሰብሳቢነትን ደፍቀን፣ የሁለተኛውን ዕድገትና ትራንስፎሜሽን በመሳካት፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን የኢትዮጵያን ህዳሴ ዕውን እናደርጋለን ሲሉ እነሱን የሚቀድም የለም፡፡ የጆሮ ታምቡር እስከሚበጠስ ኪራይ ሰብሳቢነት የመልካም አስተዳደር ችግር ነው እያሉ ያስተጋባሉ፣ ይዘምራሉ፡፡ ይጮሃሉ፣ ይጮሃሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ማንም አይችላቸውም፣ በጣም የተካኑ ናቸው፡፡  ሙስና የማይሠሩ ሰዎች ደግሞ አድማጭ ናቸው፡፡ የተናጋሪዎችን ሌብነት ስለሚያውቁ ከንፈር ይነክሳሉ፡፡ ይገረማሉ፡፡ ኢሕአዴግ ራሱ ሌባ ነው ይላሉ፣ ያማሉ፡፡ ዕርግማናቸው ግን አይደርስላቸውም፡፡

በአንድ መንግሥት ተቋማት ውስጥ ቢበዛ 20 ሠራተኞችና ሹመኞች ጥቅም ሊያስገኝ በሚችል ቦታ ላይ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ እነዚህ 20 ሠራተኞችና ሹመኞች ከ100 በላይ ባለሀብቶች ጋር ግንኙነት ይኖራቸዋል፡፡ ባለሀብቱ በተለይም በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚፈልግ ከሆነ ለመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞች በማንኪያ ጥቅም ሰጥቶ በአካፋ የሚገመት የራሱን ጥቅም ያጋብሳል፡፡ ሁሌም በተለይም ‘ኢንተርፕሩነር’ የሚሆኑ ሰዎች ሀብታሞች እንደሚሆኑ ዕሙን ነው፡፡ ስለሆነም ለመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞች ጉቦ ሲሰጡ ወይም ሲያጭበረብሩ ወይም ሲሠሩ የኢንተርፕሩነር ዕውቀታቸውን በሚገባ ይጠቀማሉ፡፡ ለዋና ሥራቸው ብቻ ሳይሆን ለሙስና ሥራም የኢንተርፕሩነር ክህሎት ያላቸው ስለሆኑ፣ የመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞችን በቀላሉ በማማለል ሙስና ውስጥ ያስገባቸዋል፡፡ ሙስና የሚሠሩ የመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞችም የኢንተርፕሩነር ክህሎት እንዳለባቸው አንርሳ፡፡ ሌሎች ጥቅም ሊያስገኝ የማይችል ሥራ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞችና ሹመኞች ለሙስና ባይተዋር ስለሆኑ ጠቋሚ ይሆኑ እንደሆነ እንጂ የሚያገኙት ጥቅም አይኖራቸውም፡፡ እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት ጉዳይ በአንድ ወቅት ጥቅም ሊገኝ በሚችል ቦታ ላይ ተሰማርተው ሲሠሩ የነበሩ ሠራተኞችና ሹመኞች የሌሎችን የሙስና ወንጀል ለመጠቆም በጣም የተካኑ ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በቀጥታም ሆነ በተዛዋዋሪ ጥቅም ፈልገው ወይም አንዱ ሲጎዳ ዕርካታ ማግኘት ፈልገው ጥቆማ የሚያቀርቡ ሠራተኛ ያልሆኑ ሰዎችም እንዳሉ ሳንዘነጋ ማለቴ ነው፡፡

እንግዲህ የኢሕአዴግ መንግሥት ከላይ የተገለጹት የሙስና ወንጀሎች እየተንሰራፉ ከመጡ በአገር ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ከወዲሁ በመገንዘብ ነበር፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽንን በግንቦት ወር 2003 ዓ.ም. በሕግ ያዋቀረው፡፡ ይህ ተቋም ሦስት ዋና ዋና ዓላማዎች ነበሩት፡፡ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ትምህርቶችን ማስተማር፣ በመንግሥት ተቋማት ሙስናና ብልሹ አሠራር መከላከል፣ የሙስና ወንጀል ጥቆማዎችን መቀበል፣ መመርመር፣ መክሰስ፣ ማስቀጣትና የተመዘበረ ሀብት ማስመለስ ሦስቱ ዓላማዎች ነበሩ፡፡ ይህ ተቋም ከተቋቋመ አሥራ አምስት ዓመታት አልፈውታል፡፡ በአሥራ አምስተኛው ዓመት ላይ ግን በአዋጅ ቁጥር 943/2008 የምርመራና የዓቃቤ ሕግ ሥራ ከኮሚሽኑ ተቀንሶ ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ለፌዴራል ፖሊስ ተሰጠ፡፡ በዓለም ላይ የተለያዩ የፀረ ሙስና ኮሚሽን አደረጃጀቶች ሲኖሩ፣ አንድም አገር የሙስና ወንጀል ምርመራ ሥራን በፖሊስ ሥር አላደራጀም፡፡ በዓለም ላይ በፀረ ሙስና ሥራ ተጠቃሽ የሆኑ እንደ ሆንግ ኮንግ ያሉት አገሮች የዓቃቤ ሕግ ሥራ ብቻ በፍትሕ ሚኒስቴር ወይም በጠቅላይ ዓቃቤ ሥር አደራጅተው የምርመራ ሥራ የሚከናወነው ግን በፀረ ሙስና ኮሚሽን ነው፡፡ የሙስና ምርመራ ሥራ ነፃና ገለልተኛ በሆነ ሁኔታ በማደራጀት ለአገሪቱ መሪ ያደረጉ አገሮችም አሉ፡፡ ቀደም ሲል እንደ ኮሚሽኑ ዓይነት የምርመራና ዓቃቤ ሕግ ሥራ አንድ ላይ አደራጅተው የፀረ ሙስና ትግል ላይ ውጤታማ የሆኑ አገሮችም በብዛት አሉ፡፡

በአገራችን በአንድ ወቅት የቅጽበታዊ እንቅስቃሴ የምርመራ ሥራን በፌዴራል ፖሊስ ሥር እንዲደራጅ መደረጉ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ እዚህ ላይ ሙሰኛ የሆኑ አንዳንድ አዋቂ ነን የሚሉ ሰዎች ዓላማቸው ፀረ ሙስናን ማዳከም ስለሆነ፣ የማይሆነውንና ከዕውነታ ውጪ የሆኑ ነገሮችን ሲቀባጥሩ አነባለሁ፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች በአንድ ወቅት በሙስና ወንጀል የተከሰሱና የተቀጡ እንደሆኑ እገምታለሁ፣ ወይም ዘመዶቻቸው የሙስና ተጠያቂ የሆነባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ የሆነ ሆኖ በሆንግ ኮንግ ፀረ ሙስና ኮሚሽን እ.ኤ.አ በ1974 የተቋቋመው በፖሊስ ውስጥ ሙስና በጣም እየተስፋፋ ስለመጣ ነበር፡፡ መንግሥታችን የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ሙስናን መከላከልና መዋጋት የሞት ሽረት  ጉዳይ እንደሆነ በግልጽ ባስቀመጠበት ሁኔታ፣ የምርመራ ሥራን ወደ ፌዴራል ፖሊስ መውሰዱ የአገሪቱን የሙስና ወንጀል ችግር ይቀረፋል ብሎ አስቦ ከሆነ በጣም ተሰስቷል፡፡ የፖሊስ ሥራ በአብዛኛው እስከታችኛው አደረጃጀት ድረስ በኅብረተሰብ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ፣ እንደ እኛ ባለ አገር ውስጥ ፍትሐዊ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ይሰጣል ተብሎ ታስቦ ከሆነ ራስን እንደማታለል ይቆጠራል፡፡ ምናልበት ለመንግሥት ቅርበት ባለው የፖሊስ አደረጃጀት ውስጥ ፍትሐዊ አገልግሎት ሊሰጥ ይችል ይሆናል፡፡

አሁን ደግሞ የኮሚሽኑ የሥራ እንቅስቃሴ ውጤታማ ነበር ወይ? ኮሚሽኑ ሦስቱን ዓላማዎች ለማሳካት ችሎ ነበር ወይ? የሚለውን በዝርዝር ማየት ያስፈልጋል፡፡ ኮሚሽኑ ተግባራቱን የሚያከናውነው በመንግሥት በተመደበ በጀት ነው፡፡ በኮሚሽኑ በሥነ ምግባርና በፀረ ሙስና ሙያ ላይ ስፔሻለይዝድ ያደረገ ባለሙያ የለውም፡፡ ሚዲያን በነፃ እንዲጠቀም አልተፈቀደለትም፡፡ የሙስና ወንጀል ጥቆማ ከጠቋሚዎች በመቀበል እንጂ የራሱ የሆነ ‘ኢንተለጀንስና ሰርቪላንስ’ የለውም፡፡ ቀደም ሲል በዝርዝር በተገለጸው ሁኔታ የመንግሥት ሹመኞች ተቋሙን አይደግፉም፣ እንዲኖር አይፈልጉም፡፡ በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚፈልጉ ባለሀብቶች ከመንግሥት ሹመኞች በስተጀርባ በመሆን የኮሚሽኑን የማስፈጸም አቅም ይፈታተናሉ፡፡ መንግሥት ሀብትና ንብረት ለመዝረፍ ወይም ከሚሰጡት አገልግሎቶች ጥቅም የሚፈልጉ የመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞች የስም ማጥፋት ዘመቻ ያደርጉበታል፡፡ በጣም ያስወራሉ፣ ያወራሉ፡፡ በዚያ ላይ በሙስና ወንጀል የተከሰሰ ሰው ያላቸው የኅብረተሰብ አባላት የኮሚሽኑ እውነተኛ ጠላቶች ናቸው፡፡ ቢችሉ ኖሮ ሕንፃውን ያቀጥሉ ነበር፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ላይ ጭፍን ጥላቻ ያላቸው ተቃዋሚዎችና ሌሎች ሀብታሞች ሲሆኑ ወይም በአንድ ወቅት ደሃ የነበሩ የመንግሥት ሹመኞች የኑሮ መሻሻልን ስለሚያዩ፣ ኮሚሽኑ ኢሕአዴግ ሥራ የሚለውን የሚሠራና ሰውን ያላግባብ የሚያጠቃ ተቋም ነው ስለሚሉ ልፋቱን ጥላሸት ይቀቡታል፡፡ የኮሚሽኑን ሠራተኞችም የኅብረተሰቡ አካል ስለሆኑ በሙሰኞች መደለላቸው አይቀርም፣ በደላሎች ይጠፈራሉ፡፡ በዚህና በመሳሰሉት ኮሚሽኑ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ቢኖሩም አመርቂ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ቢያንስ ሙስና የአገሪቱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር መሆኑን በኅብረተሰቡ አዕምሮ ውስጥ በጥልቀት እንዲገባ አድርጓል፡፡

ኮሚሽኑ በመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሰደረው ተፅዕኖም የሚናቅ አልነበረም፡፡ ኮሚሽኑ ተቋማትን በተደጋጋሚ በመጎበኘቱ ብቻ ሙስና በአገሪቱ ቢያንስ በይፋ ሰው በሚያየው ሁኔታ በግልጽ አይሠራም፡፡ እንደ ሌሎች አገሮች በጠራራ ፀሐይ ኅብረተሰቡ ስለሙስና አይጠይቅም፡፡ የነበረው ችግር ግን አንዳንድ ሕገወጦች ሕገወጥ ጉዳዮችን ለማስፈጸም የመንግሥት ሠራተኞችንና ሹመኞችን የሙስና አካል ስለሚያደርጉ፣ የመንግሥት ሠራተኞችና ሹመኞችን የግል ተጠቃሚነት መሠረት ያደረጉ አገልግሎት ስለሚሰጡ፣ እንዲሁም በሕጋዊ መንገድ ጉዳይ የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙ የኅብረተሰብ አካላት ለሙስና ባይተዋር ተመልካች በመሆናቸው ኮሚሽኑ ምንም አልሠራም ስለሚሉ ኮሚሽኑን እጀ ሰበራ አድርጎታል፡፡

ኮሚሽኑ በኅብረተሰቡ ዘንድ በብዛት የሚታወቀው በሙስና ወንጀል ምርመራና በዓቃቤ ሕግ ሥራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሙስና ምርመራ ሥራ የሚከናወነው ከኅብረተሰቡ በመጣ ጥቆማ ነው፡፡ ጥቆማ አቅራቢዎች ደግሞ ራሳቸው ብዙ ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ ያቀረቡት ጥቆማ በአንድ ሌሊት ተመርምሮ ሰዎች ማረሚያ ቤት እንዲገቡ ተደርገው እነሱ ያሰቡት እንዲሳካላቸው በጣም ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ላይ በተለይም ባለሀብት ወይም የመንግሥት ሹመኛ ወይም የሹመኛ ዘመድ ታስሮ ከሆነ፣ በየፊናው ለማስለቀቅ የሚደረገው ጥረት  የፀረ ሙስና ትግሉን የሚፈታተን ነው፡፡ በዚህ ላይ የደላሎች ጉዳይ በጣም ከባድና ለማጥፋትም የሚቻል አይደለም፡፡ ደላሎች ደግሞ የመንግሥት ሹመኞችና ባለሀብቶች መሆናቸው ጉዳዩን በጣም ያወሳስበዋል፡፡ አንድ ባለሀብት ወይም ሹመኛ ከታሰረ የኮሚሽኑ መርማሪና ዓቃቤ ሕግ ባለሙያዎችና ዳኞች  ተደጋጋሚ የደላሎች ጉብኝት አለባቸው፡፡ የሙስና ተጠርጣሪዎችን ለማስፈታት የመንግሥት ሹመኞች ተፅዕኖ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የደላሎች ሚና በጣም በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ የሄዱበት መንገድ ካልተሳካላቸው ለእነሱኮሚሽኑ ሌባ ነው፡፡ ስለሆነም ይህም የኮሚሽኑን ልፋት እጀ ሰበራ አድርጎታል፡፡ ስለሆነም መንግሥት ይህን የኅብረተሰብ ነቀርሳ የሆነ የሙስና ችግሮችን ለመቀነስ እንዲቻል የኮሚሽኑን የማስፈጸም አቅም በበቂ ሁኔታ መገንባት ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ የፀረ ሙስና ትግሉን ለማጎልበት የሚከተሉት ትኩረት ተሰጥተው ሊተገበሩ ይገባል፡፡

  1. ኮሚሽኑ ለሚያከናውነው ሥራ በቂ በጀት፣ የሰው ኃይልና ቁሳቁስ መመደብ ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ በፀረ ሙስና ትግሉ ውጤታማ የሆኑ ተቋማትን ተሞክሮ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ሠራተኞች በሥነ ምግባር ታንፀው የፀረ ሙስና ትግሉን በኃላፊነት ስሜት እንዲያከናወኑ፣ ኮሚሽኑም በሙያው ልምድ ያካበቱ ሠራተኞች ለማቆየት እንዲችል የኮሚሽኑ ሠራተኞች ከፍተኛ የደመወዝ ተከፋይ ማድረግ ይገባል፡፡
  2. የመንግሥት ሹመኞች፣ ባለሀብቶችና ደላሎች በኮሚሽኑ ሥራ ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድሩ ገለልተኛና ነፃ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ የፈረጠመ የማስፈጸም አቅም ያለው ተቋም ሊሆን በሚችል ሁኔታ መደራጀት አለበት፡፡ መንግሥትም ያለበትን ችግር በቅርበት በመከታተል ድጋፉን መስጠት ይኖርበታል፡፡
  3. ያለወቅታዊ ጥናትና መረጃ በግለሰቦች የክፋት ፍላጎትና ጥንስስ ለፌዴራል ፖሊስ የተሰጠው የሙስና ወንጀል ምርመራ ሥራ ተመልሶ በኮሚሽኑ ሥር እንዲደራጅና ኮሚሽኑ የራሱ የሆነ ኢንተለጀንስና ሰርቪላንስ በማደራጀት እንዲንቀሳቀስ ቢደረግ መልካም ነው፡፡ የዓቃቤ ሕግ ሥራ በሌሎች አገሮችም ለብቻው ተደራጅቶ ስለሚንቀሳቀስ ተቋሙ ብቃትና ክህሎት ባለው የባለቤትነት ስሜት በተላበሰ ቁርጠኛ አመራር ሊመራ ይገባል፡፡
  4. ኮሚሽኑ በተለይም ሕፃናትና ወጣቶች በሥነ ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ የሚያስችሉ ሥራዎችን እንዲሠራ ነፃ የመንግሥት ሚዲያ ይፈቅድለት፡፡ ኮሚሽኑም የተሰጠውን የመንግሥት ነፃ ሚዲያ ተጠቅሞ የኅብረተሰቡን የሥነ ምግባር ደረጃ የሚያሳድጉ ትምህርቶችን እንዲያስተምር ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር ይደረግ፡፡
  5. ኮሚሽኑ የአደረጀጀት ስፋቱን በማሳደግ በተለያዩ ቦታዎች ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን እንዲከፍትና በተለይም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ አስተዳደር ተደራሽነቱን ማሳደግ ይኖርበታል፡፡
  6. ኮሚሽኑ ከላይ የተቀመጡት ተፈጽመውለት የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ሥራዎችን በተጠናከረ እንዲያከናውን ብቃትና ክህሎት ያለው አመራር በየደረጃ ስለሚያስፈልገው፣ መንግሥት የአሁኑን ነባራዊ ሁኔታ በመፈተሽ ጠንካራ፣ ተነሳሽነቱ ያለው፣ በዕውቀት፣ በክህሎትና በቁርጠኝነት ሊመራ የሚችል አመራር ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡
  7. የኮሚሽኑ የፀረ ሙስና ትግል እንቅስቃሴም ዕውቀትና ክህሎት፣ ነፃና ገለልተኛ አዕምሮ ባለቸው አካላት በግልጽና በመረጃ እየተደገፈ የሱፐርቪዥን፣ የክትትልና ድጋፍ ሥራ እንዲያከናውን ሊደረግ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይታደጋል!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው bekeleayele2008@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

 

Standard (Image)

የፖለቲከኞችና የምሁራን ሐሳቦች ማጠቃለያ ገጾችና የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ

$
0
0

ሪፖርተር ጋዜጣን በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ የመልካም አስተዳደር መስፈን ውስጥም ሆነ ሚዛናዊ ዘገባን ለማቅረብ ከሚጥሩ የአገራችን የኅትመት ሚዲያዎች በቀዳሚነት እጠቅሰዋለሁ፡፡ ለዚህ አባባል መነሻ የሚሆነው ጋዜጣው በርዕሰ አንቀጹ ሳይቀር ለተከታታይ ሳምንታት፣ ወራትና ዓመታት ምን ላይ አተኩሮ ሲወተውት ነበር የሚለውን ዘወር ብሎ በጥናት መመርመር፣ በተለይ ለፖሊሲ አውጭውና ለገዥው ፓርቲ ሰዎች መጠቆም ይኖርብኛል፡፡

ዞሮ ዞሮ የጽሑፌ መነሻ ሪፖርተርን ማወደስ ወይም ለገዥው ፓርቲ ‹‹ሲነግሩህ ለምን አትሰማም?›› የሚል ወቀሳ ማድረስ ባለመሆኑ ይህን እዚሁ ላይ ልግታና ወደ ጉዳዬ ልግባ፡፡ አሁን ኢትዮጵያችን ምቾት የሚሰጥ ሁኔታ ላይ እንዳልሆነች ጠንቋይ መሆን አያስፈልግም፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚያቀርባቸው እንግዶችም ሆኑ ጽሑፎችም ይህንኑ ተረድተው ለመፍትሔው የሚጮኹ ናቸው፡፡

በአገሪቱ በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በተለያየ ምክንያት የተነሳ ‹‹የሕዝብ ጥያቄ›› ቀስ በቀስ አቅጣጫውን እየሳተ ነው፡፡ መንግሥት በጽንፈኛ ተቃዋሚዎችና የውጭ ኃይሎች አጀንዳ ‹‹የሕዝቡ ጥያቄ እየተጠለፈ ነው›› ቢልም፣ የተደራጀና ጠንካራ የፖለቲካ ኃይል የማይመራው የሕዝብ ቅሬታ በማኅበራዊ ድረ ገጾችና ውጭ ባሉ መገናኛ ብዙኃን ይቀጣጠል ይዟል፡፡

በዚህም ምክንያት በተጠቀሱት ክልሎች በተለይም አንዳንድ ዞኖች ከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየታየ ነው፡፡ ገበያ የለም፣ የንግድና የአገልግሎት መስኩ ተዳክሟል፣ ዜጎች በግጭት ሥጋትም ይባል በተለያዩ ምክንያቶች በሰላም ወጥተው መግባት አልቻሉም፡፡ በአንዳንድ የገጠር ወረዳዎችም ቀደም ሲል በኦሮሚያ እንደታየው የመንግሥት መዋቅሩን የማፈራረስና አመራሩን የማሳደድ የለየለት ሕገወጥነት ታይቷል፡፡ ይህ ድርጊት ለጊዜው ጋብ ያለ ቢመስልም ሥጋቱ እንዳረበበ ነው፡፡

የእነዚህ ክስተቶች ድምር ውጤት በአገሪቱ ንግድና ኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝምም ሆነ በአገር ገጽታ ግንባታው ላይ ያለ ጥርጥር የጎላ ጥላ አጥልቷል፡፡ የገዥው ፓርቲና የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከመደበኛ ሥራቸው ላይ እግራቸውን ነቅለው፣ ‹‹ዳግም ተሃድሶ የ15 ዓመታት የአገሪቷ ጉዞ ስኬቶችና ፈተናዎች››ን ዋነኛ አጀንዳ አድርገው መምከር ይዘዋል፡፡ ይህ ምክክር ይበልጥ ሕዝቡንና ገለልተኛውን ወገን (ምሁሩንና ሰላማዊውን ፖለቲከኛ) ካሳተፈ የአገር ግንባታው አካል ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ በር ዘግቶ የሚደረግ ማሻሻያ ግን በቀላሉ ሕዝቡን ያረካል ለማለት ያዳግታል፡፡

በዚህ ወሳኝ የሕዝቡ የለውጥ ፍላጎት ከፍ ባለበትና መንግሥትም ‹‹ለዳግም ተሃድሶ›› በተዘጋጀበት ወቅት ላይ ነው እኔም ይህን ብዕር ለማንሳት የወደድኩት፡፡ ይኸውም ቢያንስ ባለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የሚባሉ፣ ድምፃቸውን ያሰሙና ያመኑበትን ሐሳብ ያራመዱ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና የአገር ተቆርቋሪ ሰዎችን ሐሳቦች ለመመርመር የተገደድኩት፡፡ በየመጻሕፍቱ  የማጠቃለያ ገጾች ላይ የተሰነዘሩ ጠቃሚ የሚመስሉኝን አገራዊ ምክሮች እንወያይባቸው ዘንድ ወደዚህ ለማምጣት የወደድኩት፡፡

መጻሕፍቱ ግን ታስቦባቸው የተደራጁ ሳይሆኑ በአጋጣሚ እጅ የገቡ መሆናቸውን መግለጽ ይኖርብኛል፡፡ እንደ ነፃ አስተያየት ግን በየመጻሐፍቱ ውስጥ የተጠቀሱ ሚዛናዊና አገራዊ ምክረ ሐሳቦች ለመንግሥትና ለሕዝብ ጥቅም አንድ አስተዋጽኦ ያበረክቱ እንደሆን እንጂ የሚጎዱ አይደሉም፡፡ ከ25 ዓመታት በኋላ ‹‹25ኛው ተሃድሶ›› ለሚለው ኢሕአዴግም ዓይኑን ሊገልጡለት የሚችሉ ይመስለኛል፡፡

ኢትዮጵያዊነትና የብሔር ብሔረሰብ መብቶች እንደማይጣጣሉ አድርጎ መገንዘብና መተግበር

ይህን ሐሳብ ከእነርዕሱ የተጠቀሙበት የ‹‹ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ›› ደራሲና ፖለቲከኛ አቶ ገብሩ አሥራት በገጽ 384 ላይ ነው፡፡ ዶ/ር ዘውዱ ውብ እንግዳ ‹‹የፌዴራላዊ መንግሥት አመጣጥ››፣ አቶ ኃይሉ ሻውል ‹‹ሕይወቴና የፖለቲካ ዕርምጃዬ››፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ‹‹ዳንዲ. . .›› እና መሰል ትንታኔዎች በአንድም በሌላም የተንፀባረቁ ሐሳቦች ናቸው፡፡

አቶ ገብሩ፣ ‹‹ኢሕአዴግ ከሥልጣን ቢወገድም በአገራችን ዘላቂ ዕድገትና መረጋጋት እንዳይሰፍን ምክንያት የሆነው የጠላትነት ፖለቲካ ካልጠፋ፣ ልማትና መረጋጋት ይገኛል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው፤›› ብለው ከተዛባው ታሪካዊ ፉክክር በመውጣት፣ የጋራ እሴትና የጋራ አመለካከት የገነቡ ብሔር ብሔረሰቦች ከታጠሩበት ክልልና ብሔር ወጥተው በዴሞክራሲያዊነት ላይ የተገነባ ኢትዮጵያዊነትን በጋራ መፍጠር ይኖርባቸዋል ሲሉ አትተዋል፡፡

ለዚህም ከሕዝቡ በላይ በአገራዊ ስሜት የተደራጁ ኅብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች መፈጠርና መጠናከር አለባቸው፡፡ ምሁራን ከብሔር ባርኔጣ እየወጡ በአገራዊ ጃንጥላ ውስጥ ታቅፈው መምከር ይገባቸዋል፡፡ የሲቪክ ማኅበራትን ጨምሮ እነዚህ ኃይሎች በኢትዮጵያዊነትና በብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበር መካከል ያለውን አንድነትና ልዩነት በሚገባ አጢነው መጓዝ ይኖርባቸዋል ነው የሚሉት፡፡

በዚህ ሐሳብ ላይ የጠቃቀስኳቸው ሰዎችም ሆኑ ብዙዎቹ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ የሚከታተሉ ወገኖች ከኢሕአዴግ ዓይነቱ ‹‹ዘውጌ ጠመድ›› (የብሔር ልዩነት ላይ ይበልጥ የሚያተኩር ፖለቲካ) ከደርግ ዓይነት ጽንፈኛ አሃዳዊነት (አንድ ጸሐፊ በመውደድ ብዛት ልጇን ከልክ በላይ አቅፋ እንደገደለች እናት ብለውታል) ውጪ የሆነ አስተሳሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡ በፌዴራል ሥርዓት ማንነቱን፣ ታሪኩን፣ ቋንቋውንና ባህሉን እንዲያውቅና እንዲያዳብር መደረግ አለበት፡፡ በአገሩ ደግሞ በፍትሐዊና በእኩልነት መርህ እየተጠቀመና እየተሳተፈ አንድነቱን ማጠናከር አለበት፣ ይገባልም፡፡

ይህ ወሳኝና አማራጭ መንገድ የግድ የሚፈለግበት ጊዜ መቃረቡን አሁን መሬት ላይ ያለው ሀቅ ቁልጭ አድርጎ እያሳየ ነው፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት አገሪቱ ወድቃ እየተነሳች ለውጥ አስመዝግባለች፡፡ በየትኛውም የአገሪቱ ጫፍ ቢሆን ደርግ ሲሄድ በነበሩበት ይዞታ ላይ ያሉ ዜጎችና አካባቢዎች እንደሌሉ አፍ ሞልቶ መናገር ይቻላል፡፡ ገጽታችንም መሻሻል ጀምሯል፡፡ ይኼም ሆኖ ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ የትግራይ ሕዝብ ብቸኛ ተጠቃሚ መሆኑ እየተቀነቀነ ነው፡፡

ሰፊ የሚባሉት የአማራና የኦሮሚያ ክልል ሕዝቦች ደግሞ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥቅማቸው እንደቀረ፣ አናሳ የሚባሉ ሌሎች ብሔረሰቦችም (በተለይ ደቡብ) በሌሎች የክልሉ ብዙኃን ተገፍተናል የሚል ቅሬታ ውስጥ ናቸው፡፡ እነዚህን ሁለት ጫፍ የነኩ ዝንባሌዎች እያረመ ሊሄድ የሚችለው ደግሞ ዴሞክራሲያዊና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የአገሪቱ ሕዝቦች የየራሳቸው ቋንቋ ቢኖራቸውም የጋራ መግባቢያ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የየራሳቸው ባንዲራ ቢኖራቸውም ከፍ ብሎ የሚሰቀልና ሁሉም የተግባቡበት የአንድነት መገለጫ ሰንደቅ ሊኖር ይገባል፡፡ የየራሳቸው ታሪክ ቢኖራቸውም ሁሉን ያቀፈ አገራዊ ታሪክ፣ አገራዊ ትምህርት፣ አገራዊ የጋራ የኢኮኖሚ ፕሮጀክት (እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ)፣ አገራዊ ሠራዊት፣ አገራዊ አየር መንገድ፣ አገራዊ የእግር ኳስ ቡድንና አገራዊ ፓርቲ. . . ሊኖር ግድ ነው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲን ነገር ካነሳን ኢሕአዴግ እንኳን ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ መሆን አልቻለም፡፡ የብሔራዊ ድርጅቶች የጋራ ግንባር ብቻ ነው፡፡ እንደ ቅንጅት፣ ደቡብ ኅብረት፣ መድረክና አንድነት . . . ያሉትም ተወልደው በእግራቸው ሳይቆሙ የመከኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ በዚህች አገር 80 የብሔር ፓርቲዎች ተበጣጥሰው በመንደር ልጅነት እየተሰበሰቡ ፈቃድ ከሚያወጡ፣ ተባብረውና በአንድ አገራዊ ራዕይ ሥር ተሠልፈው ሦስትና አራት ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ቢሆኑ ምንኛ በታደልን ነበር? (እዚህ ላይ የህንድን ተሞክሮ እንመልከት ከ1,500 በላይ ማንነት ያላቸው ብሔሮች ቢኖሯትም፣ ፖለቲካው የሚወሰነው ግን በሁለትና በሦስት አገራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ነው፡፡ በቃ!

እውነተኛና የማያከራክር የፌዴራል ሥርዓትን መተግበር

በመሠረቱ በኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት መከተል ላይ የሚነሱ ልዩነቶች እየጠበቡ ነው የመጡት፡፡ አሁን አሁን ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነውን ‹‹የቀድሞ ባንዲራ›› በመምዘዝ የአሃዳዊነት አቀንቃኝ የሚመስሉ ወገኖች ቢታዩም (እነሱ ዓላማቸው በግልጽ ገና አልተነገረም)፣ አብዛኞቹ የፖለቲካ ኃይሎች ከአሃዳዊነት እሳቤ መላቀቃቸውን በምርጫ ክርክሮች፣ በፓርቲዎች ማኒፌስቶዎችና በልዩ ልዩ መግለጫዎች ሲገልጹ ተደምጧል፡፡

ከዚያ ይልቅ አሁን ክርክሩ በተግባር ላይ በዋለው ፌዴራሊዝም ቋንቋ (ብሔር) ተኮር መሆን ላይ ሆኗል፡፡ እርግጥ ይህ ሙግትና ከሕገ መንግሥቱ መፅደቅ አንስቶ ‹‹አገራዊ ስሜትን ያጠፋል፣ ሕዝብን ከሕዝብ ያለያያል፣ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላ ሄዶ ለመሥራት እንቅፋት ይፈጥራል. . .›› ተብሎ ሲነቀፍ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡  (የዶ/ር ዘውዱ ውብ እንግዳን ‹‹የፌዴራላዊ መንግሥት ታሪካዊ አመጣጥና የመንግሥት ግንባታ ችግሮችና ኢትዮጵያን›› ከ15 ዓመታት በፊት የቀረበ መጽሐፍ ይመለከቷል)

ብዙዎቹ ድርሳናት እንደሚስማሙበት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የተሞከረው እ.ኤ.አ. ከ1952 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ የኤርትራ ፌዴራላዊ ግንኙነት ነበር፡፡ እሱም ከሸፈ፡፡ ደርግም ብዙ ዋጋ ከተከፈለ በኋላ በዚያው በኤርትራ መዘዝ የራስ ገዝና የልዩ ራስ ገዝ (Regional Autonomus and Special Regional Autonomus) ሥርዓት ለመተግበር ሞክሯል፡፡ ‹‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ›› ሆነ እንጂ፡፡ የኢሕአዴግ የፌዴራል አወቃቀር ላይ የጋራ አስተዳደር (Shared Rule) እና የራስ አስተዳደር (Self Rule) መርሆች በተሟላ መንገድ እየተተገበሩ አለመሆናቸው ይወሳል፡፡

ከዚህም በላይ ግን አሁን ያለው ፌዴራሊዝም ብሔርና ቋንቋ ተኮር በመሆኑ፣ የብሔር ብሔረሰቦችን ታሪካዊና መልከዓ ምድራዊ ግንኙነትን እንደዘነጋ ይተቻል፡፡ ለዚህ ሐሳብ አቶ ገብሩ (በገጽ 387) በስፋት ያተቱት ዘገባ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ‹‹በአገሪቱ ከአፋር፣ ከሶማሌና ከኦሮሚያ በስተቀር ሌሎች አካባቢዎች በርካታ ብሔረሰቦችን ይዘው ነው፤›› ይሉና በትግራይ ከትግሪኛ በተጨማሪ የኢሮብና የኩናማ ብሔረሰቦች ያውም ልዩ ዞን ወይም አደረጃጀት ሳይኖራቸው፣ የአማራ ክልልም ከአማርኛ ተናጋሪው በተጨማሪ የአገው፣ የኦሮሞና የአርጎባ ብሔረሰቦችን በልዩ ዞን ደረጃ ለይቶ ይዟል፡፡ ቤንሻጉል አምስት፣ ጋምቤላ ከአራት በላይ፣ ሐረሪ ቢያንስ ሦስት ብሔረሰቦችን፣ ደቡብ ክልል ደግሞ ከ52 በላይ ብሔሮችን ይዘዋል ይላሉ፡፡

በዚህ መነሻ ብዙዎቹን ጸሐፍት የሚያስማማው በክልሎች ብዙኃን ከሚባለው ማኅበረሰብ ውጪ ያሉ ጎሳዎችና ሕዝቦች የመደመጥ ዕድላቸው ይቀጭጫል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ታሪካዊ ትስስርና ጂኦግራፊያዊ ቅርበት በመዘንጋቱ አፍንጫው ላይ ያለውን መዋቅርት ትቶ ሌላ ጫፍ ለመሄድ ይዳረጋል፡፡ ከሁሉ በላይ የክልሎች ነፃነት ተጨፍልቆ ፌዴራላዊ ጠቅላይነት ሲጎላ፣ በዴሞክራሲያዊና በማዕከላዊነት ሥልጣንና ትዕዛዝ ሲንቆረቆር ብሎም የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ሲደፈቅ ሥርዓቱ ‹‹ሥውር አሃዳዊ›› መሆኑ አይቀርም ነው የሚሉት፡፡

የብሔር ተኮር ፌዴራላዚም ጣጣው ዜጎች ‹‹ማንነታቸውን›› ብቻ የሀብትና የሥልጣን ማግኛ አድርገው መውሰድ ሲጀምሩና አሁን እየታየ እንዳለው ዓይነት አመለካከት እየጎላ ሲመጣ ነው፡፡ ለምሳሌ በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል የውዝግብ ምንጭ ሆኖ የታየው የወልቃይትና የጠለምት አካባቢ በትግራይ ክልል ውስጥ ከገባ 25 ዓመታት ሆኖታል፡፡ ከዚያ በፊትም በተለያዩ ታሪካዊ ክስተቶች አንዴ ወዲህ ሌላ ጊዜ ወዲያ ሆኗል፡፡ ያለ ጥርጥርም በአካባቢው የተወለደና የተሳሰረ ‹‹ወልቃይትነቴን›› የገነባ ማኅበረሰብም ተፈጥሯል፡፡ ግን ዛሬ ዘሩንና አንጓውን እየቆጠረ መሳሳብ ፈለገ፡፡

‹‹ለምን?›› ሲባል በትግራይ መከለሌ ልማት አላመጣልኝም፣ ሥልጣን አላስገኘልኝም፣ ውክልና በተሟላ መንገድ አላገኘሁም. . . እያለ ፌዴራሊዝሙ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ሰበዞችን መዘዘ፡፡ በተመሳሳይ በደቡብ ክልል በኮንሶ በክልሉ የተደራጀውን ዞንና የመንግሥት አወቃቀርን እስከመበተን ደርሶ በጎሳው ሥሪት መተዳደር የጀመረው ‹‹የማንነት ጥያቄ አልተመለሰም›› በሚል ነው፡፡ አሁን አሁን አንዱ የሥርዓቱ ችግር መስሎና ሆኖ ጎልቶ በመረጃ እየተደገፈ የሚቀርበው ለዓመታት የተገፋው በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉልና በሶማሌ የኖረ የመሀል አገር ሕዝብ ጉዳይ ነው፡፡

ይህ ሕዝብ በመላው አገሪቱ ቢያንስ ከ100 ዓመታት ለበለጠ ጊዜ ሠርቶ ከመኖር ባሻገር ተዋልዶና ተጋብቶ ‹‹ባለአገር›› እንዳልነበረ በሥርዓቱ የመደራጀት፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት ዕጦት ደርሶበት ለችግር ዳርጎታል የሚሉ ነበሩ፡፡ በተለይ ሕዝቡ ከቀደሙ ገዥዎች አንፃር የሚያስደምረው ‹‹ነፍጠኛ›› የሚል ስያሜ ሲለጠፍበት ከፍተኛ መከራና እንግልትም ሊደርስበት ችሏል፡፡ ይህ ያልተገባ አዝማሚያ ዛሬ ደግሞ ተገልብጦ በመላ አገሪቱ በላባቸው ሠርተውና ለፍተው ለዘመናት የኖሩ የሌሎች ክልሎች ተወላጆች ላይ ሲነጣጠር ታይቷል፡፡

ከእነዚህ እውነታዎች አንፃር የፌዴራል ሥርዓቱ በጠባብ ብሔርተኛውም ሆነ በጠቅላይነት በሚታማው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ ሳይናወጥ የሁሉንም ሕዝቦች የግልና የቡድን መብቶች የሚያስከብር መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ከብሔርና ከቋንቋ ባሻገር መልከዓ ምድር፣ ሥነ ልቦናና ታሪካዊ ቁርኝት ብሎም የማንነት ባህል መስተጋብርን መሠረት ማድረግ ሊኖርበት ይችላል፡፡ ይህን መፈተሽ የዚህ ትውልድ ቀዳሚ ድርሻ መሆን አለበት፡፡

እውነተኛ ዴሞክራሲና ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ፍትሕን ማስፈን

ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የሚከተለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ የእውነተኛ ዴሞክራሲ መልክ የለውም፡፡ ‹‹አስመሳይና ለዘብተኛ አምባገነን ነው፤›› የሚሉ ምሁራንና ፖለቲከኞች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ የተነሳሁት የመጽሐፍ ገጾችን በመምዘዝ ነውና ከዶ/ር መረራ፣ ዶ/ር ነጋሶ፣ ፕ/ሮ መስፍን፣ (የክደት ቁልቁለት)፣ አቶ ገብሩ አሥራት፣ አቶ ስዬ አብረሃ፣ አቶ ልደቱ አያሌውና አቶ ኃይሉ ሻውል አንስቶ በፖለቲካ ምክንያት ከጋዜጠኝነታቸው ወደ ተንታኝነት የተቀየሩት ‹‹ትንንሾቹ›› ጸሐፍት ድረስ የኢሕአዴግ ዴሞክራሲ ምኅዳረ ጠባብ፣ ባለ ልጓምና በገደብ የተሰናከለ መሆኑን ደግመው ደጋግመው ሰልቀውታል፡፡ ጽፈውታል፡፡

መንግሥትም ቢሆን አልፎ አልፎ ‹‹ዴሞክራሲያችን ገና ለገና ታዳጊ ነው›› በሚል ለመፅናናት ከመሞከር ውጪ አካሄዱን እንደ ጤነኝነት ቆጥሮ ቁጭ አለ፡፡ ሕዝቡም አውቆ እንዳላወቀ፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱም ሆነ ፍትሐዊ የማኅበረ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንደተሸራረፈ እያወቀ ‹‹ዝም አለ››፡፡ ይህ አካሄድ ግን ሄዶ ሄዶ የሚጋብዘው ነውጥ፣ ግጭትና ቀውስን እንጂ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግልን አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ነፃ ሐሳብ፣ መደራጀት፣ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግን የቀመሰ ትውልድ በዝቷል፡፡ ዓለም የዘረጋው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልቅ የመረጃ ግብይት ውስጥ ከቶታል፡፡ በነፃነት የመምረጥ ሙከራን አጣጥሟል፡፡ ይህ ግን መቀጠል አልቻለም፡፡ በማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ፍትሕ ረገድ ቀስ በቀስ ከድህነት እየወጣ ያለ አገር ቢሆንም በነፍስ ወከፍ ገቢ፣ በሥራ ዕድልና በድህነት ቅነሳ ረገድ ገና የችግር ማጥ ውስጥ ያለው ሕዝብ ቁጥር ትንሽ አይደለም፡፡ አሁንም በከተሞች ድህነት፣ ልመናና ሴተኛ አዳሪነት፣ በገጠርም የተባባሰ ስደትና ፍልሰት አለ፡፡ ከሁሉ በላይ በአጭር ጊዜ እሴት ሳይፈጥር የሚበለፅግ ሀብታምና ከመሬት ያልተነሳ ደሃ እየተራራቀ የመጡበት ሁኔታ ጎልቶ እየታየ ነው፡፡ የኑሮ ውድነት የሚያናውዘው፣ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ያስመረረውም ዜጋ ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ጉዳይ ሲነሳ ተወቃሹ መንግሥት ብቻ እንዳልሆነ ግን እርግጥ ነው፡፡ በቀዳሚነት በምን ቸገረኝነትና በግዴለሽነት የተጥለቀለቀው ‹‹የተማረው ክፍል›› ኃላፊነቱን አልተወጣም ሊባል ይችላል፡፡ በአገር ሽማግሌነትና በሃይማኖት መሪነት የሚታወቁ ‹‹አንጋፋ ሰዎች›› አድርባይነትና ከሕዝቡ ስሜት የተነጠሉ መሆናቸውም ሌላው ችግር ነው፡፡ ዋነኞቹ ተወቃሾች ግን ሰላምንና ዴሞክራሲን መርህ አድርገው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች  (አባላትና መሪዎቻቸው) ናቸው፡፡

ማንኛውም ኃይል የፖለቲካውን መድረክ ሲቀላቀል ሕዝባዊ ኃላፊነትን ለመሸከም፣ አገሪቱ የጎደላትን ለመሙላትና ሌላው ዓለም የደረሰበት እንድትደርስ ለማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ትልቅ ዓላማ ደግሞ የሚከፈለው የኑሮ ውጣ ውረድን መስዋዕት አድርጎ፣ ተቻችሎና ተደማምጦ መሆን አለበት፡፡ ሰው መቼም ገንዘብ ለማግኘት፣ ድጎማና ፍርፋሪ ለመለቃቀም ፖለቲከኛ ያውም ‹‹ትልቅ›› ፖለቲከኛ መሆን አያስፈልገውም፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ እየዋኙ ያሉ ኃይሎች ከጽንፈኛና ከጥላቻ ፖለቲካ ሊወጡ አልቻሉም፡፡ ቢወጡም ግንባር ቀደም ታጋይና የመስዕዋትነት ሰው መሆን የሚችሉ አይደሉም፡፡ ከሁሉም በላይ አገራዊና ኅብረ ብሔራዊ መሆን የተሳናቸው ድንክዬዎች ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ደግሞ እውነተኛውን ዴሞክራሲም ሆነ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ተወዳዳሪነትን ማበልፀግ ፈጽሞ ሊሳካ የሚችል አይደለም፡፡

በአጠቃላይ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ስለልማትና ዕድገት ብቻ የሚታሰብበት ሳይሆን፣ ቅድሚያ ለሰላምና ለዘላቂ አገራዊ ፖለቲካ መነጋገርን የግድ የሚባልበት ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ልዕልናና እኩልነት የሚያስቡና ለአገሪቱ አብሮነትና ሰላም የሚጨነቁ ኃይሎች ሁሉ ሊያጤኑት የሚገባው ጉዳይም ይኸው ነው፡፡ በግሌ ከላይ እንደጠቃቀስኩት ባነበብኳቸው ፖለቲካ ነክ ኅትመቶች የማጠቃለያ ገጾች ላይ ያገኘኋቸውንና በጋራ አቋም የተያዘባቸውን ቢያንስ በሁለት ነጥቦች አቅርቤያለሁ፡፡ በቀጣዩ ጊዜም ቀሪ ነጥቦችን ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡ እናንተም የምታነሷቸው ምክረ ሐሳቦች ካሉ እንወያይባቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊዋን በኢሜይል አድራሻቸው   hdebebe@yahoo.comማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

 

Standard (Image)

የመነጋገሪያው ጊዜ ካለፈ የምንነጋገርበት ጉዳይ አይኖርም

$
0
0

በሳሙኤል ረጋሳ

የነገሮች ክስተት በጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ የተገደቡ ናቸው፡፡ ስለተፈጠረው ክስተት ለመነጋገርና ለመረዳዳት፣ እንዲሁም ለማሰብና ለመወሰን የምንችለው በዚሁ ውስን ወቅት ነው፡፡ አንዳች ነገር ማድረግ እየተገባን ምንም ሳናደርግ ብንቀር ወይም ማድረግ የማይገባንን አድርገን ጥፋት ቢደርስ ኃላፊነቱ የዚያ ዘመን ትውልድ ይሆናል፡፡ ሐሳባችንን ለመግለጽ ባንፈልግም ለመደበቅ ደግሞ የሚያስቸግሩ ሁኔታዎች አሉ፡፡

የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ስናጤነው ዛሬ ያለችበት ወቅት ያለምንም ማመንታት አደገኛ ሁኔታ መሆኑን በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው አገሪቱን ለማዳን የሚችለውን ማከናወን ይኖርበታል፡፡ ሕዝብና መንግሥት፣ መንግሥትና ተቃዋሚ ድርጅቶች ሊነጋገሩም ሆነ ሊደማመጡ አልቻሉም፡፡ በየፊናቸው በተናጠል የሚናገሩትም የአንዱ ለሌላው በማይገባ የባቢሎን ቋንቋ ነው፡፡ የመነጋገሪያውና የመደማመጫው ጊዜ ግን አሁንና አሁን ብቻ ነው፡፡ ይኼ የመጠቀሚያ ጊዜያችን አልፎ ነገሮች አሁን በተያዙት አቅጣጫ ይበልጥ እየተወሳሰቡ ከሄዱ ውሉ የጠፋበት ልቃቂት ስለሚሆኑ፣ ብዙዎቻችን አሁን ላይ ሆነን ለመገመት የሚያስቸግረን የጥፋት ዘመን ሊከተለን ይችላል፡፡ በተለይ መንግሥት ነገሮችን ከቁብ ባለመቁጠሩ ይሁን በንቀት ችግሮችን ተቀብሎ የመፍትሔ ሐሳብ ሲያስቀምጥ አይታይም፡፡

አሁን በመንግሥት ዘንድ የሚታየው ትልቅ ክፍተት አዲስ ሐሳብ የሚያመነጭ፣ እንዲሁም ለችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ የሚሰጥ ጠንካራ የበላይ አመራር ያለመኖር ይመስላል፡፡ አማካሪ እየተባሉ በማዕከል የተኮለኮሉት የቀድሞ ባለሥልጣናት የአሁንም ቢባል ያስኬዳል እንዳሁኑ ዓይነት አስደንጋጭ ሁኔታ ሲከሰት በቂ ጥናት በማካሄድ መንግሥትን የማማከር ሚናቸው ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ በተጨባጭም ከሰሞኑ በቴሌቪዥን እንዳየናቸው የኢሕአዴግ ፖሊሲና አቅጣጫ የመንግሥተ ሰማያት መንገድ መሆኑን ሊያሳዩን እንዳየናቸው፣ የኢሕአዴግ ፖሊሲና አቅጣጫ ምንም ችግር የሌለበት ትክክለኛ መንገድ መሆኑን ለማስተማር ካድሬ እንጂ አማካሪ መሆን አያስፈልግም፡፡ ለነገሩማ ምክርም የሚሰጠው ለሚሰማና ጆሮ ላለው ነው፡፡ ኢሕአዴግ በተፈጥሮው የተጠናወተው ክፉ በሽታ የሦስተኛ ወገን ሐሳብን እንዳስፈላጊነቱ መቀበል ሳይሆን፣ በራሱ የድርጅት ግምገማ ተወቅጦና ተሰልቅጦ የሚቀርብለትን የራሱን ድርጅታዊ አሠራር የሚያጠናክር የቡድን ሐሳብን ነው፡፡

ይኼ በረሃ በነበሩበት ጊዜ ግለሰቦች የተለያየ አመለካከት እንዳይዙና እንዳያፈነግጡ ተብሎ ድርጅታቸውን ለማጠናከር ሲገለገሉበት የነበረ አሠራር ነው፡፡ በወቅቱ ተገቢነት ይኖረው ይሆናል፡፡ ችግሩ መንግሥት ሆነውም ይኼው ለ25 ዓመታት በዚሁ ቀጥለዋል፡፡ አሁን አስፈላጊው ነገር መንግሥት ከራሱ አባላት ብቻ ሳይሆን ወጣ ብሎ መስማት ያለበትና ሊቀበለው የሚገባውም የሕዝቡን የልብ ትርታ አዳምጦ ፍላጎቱ ምን እንደሆነ ማወቁ ነው፡፡ ማወቅ ብቻ ሳይሆን እንደ መንግሥት ሊፈጽም የሚችለውንና የሚገባውን መፈጸም፣ የማይቻለውን ግን ከነምክንያቱ ለሕዝቡ በማስረዳት ከሁሉም አካላት እምነት ማግኘት አለበት፡፡

ያለበለዚያ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ከኑሮዬ አፈናቀለኝ፣ መኖሪያዬን አሳጣኝ፣ ልጆቼ ተበተኑ ብሎ በስንት ትግል በሕዝብ ጥያቄ እንዲቆም የተደረገውን የማፈናቀል ሥራ፣ አደባባይ ወጥቶ ‹‹ሕዝቡ የማይገባው ስለሆነ ለጊዜው በእንጥልጥል አቆየነው እንጂ ነገ መልሰን እናፈናቅላችኋለን›› ብሎ በድፍረት ለኢትዮጵያ ሕዝብ መንገር፣ ያለውን ውጥረት ለማርገብ ሳይሆን በእሳት ላይ ቤንዚን መጨመር ነው፡፡

ኢሕአዴግ ሆይ! አሁን እንዲህ አድርግ፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ዜጐች የሆኑ ተቃዋሚዎች ተሰብስበው በአገሪቱ ፖለቲካዊና ወቅታዊ ችግሮች ላይ እንዲወያዩ መንገዱን አመቻችላቸው፡፡ አንተም በዚሁ መድረክ ላይ የራስህንና የምታምንበትን አቋም አራምድ፡፡ እነሱ የሚያቀርቡት በኢሳትና በኦኤምኤን የሚያስተላልፉትን ነው፡፡ አንተም የምታቀርበው በኢቢሲና በአዲስ ዘመን የምታቀርበውን ነው፡፡ ሕዝቡ ግን ጐን ለጐን ተቀምጣችሁ ሐሳባችሁን የምትገልጹበትን መንገድና ለአገር ጠቃሚ የሆነውን ሐሳብ ይገመግማል፡፡ በተለይ መድረክ አጥተው ታፍነን ሞተናል የሚሉ ተቃዋሚዎች ይህን ዕድል ሲያገኙ የሕዝባቸውን መንፈስ ይረዳሉ፡፡ ሐሳባቸውን በአደባባይ ማቅረባቸውን እንደ አንድ ውጤት ይቆጥሩታል፡፡ በመጨረሻም ሕዝቡ የሚቀበለው ሐሳብ በዲሞክራሲያዊ አሠራር እንዲተገበር ይደረጋል፡፡

ከዚህ በተረፈ አሁን ባለው ሁኔታ ሠልፍ የወጣን፣ የተቃወመን፣ ሥራ ያቆመን፣ ቤት የዋለን፣ ገበያ ያልወጣን፣ ሱቅ የዘጋን ሁሉ መሣሪያ በያዙ አካላት መቆጣጠር እንደማይቻል መንግሥት ማወቅ አለበት፡፡ ይኼ የሌባና የፖሊስ ጨዋታ እሽክርክሮሽ መሞከርም የለበትም፡፡ ሰሞኑን ኦሮሚያ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ግለሰቦች ሱቅ ዘግተዋል፡፡ ገበያዎች ሳይቆሙም ቀርተዋል፡፡ በዚህ ሒደት በዋናነት የሚጎዳው መንግሥት አይደለም፡፡ የፀጥታ ችግር ጉዳይም የለበትም፡፡ ተጐጂው አካል ምርቱን አምርቶ ለዓመት በዓል ገበያ ሊያቀርብ ያልቻለው አምራችና በገበያው መጠቀም ያልቻለው ሸማች ሕዝብ ነው፡፡ የሱቆችም መዘጋት እንዲሁ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ዕርምጃዎች ረዘም ላለ ጊዜ ሊቀጥሉ የማይችሉ ግን የተቃውሞ ምልክት ናቸው፡፡ በራሳቸው ጊዜ የሚቆሙ ናቸው፡፡ ነገር ግን መንግሥት የተዘጉትን ሱቆች ሁሉ በማሸግ ለድርጊቱ መባባስ ተባባሪ መሆን የለበትም፡፡

በየከተማው የቆሙትን ባጃጆችና ታክሲዎች ታርጋ መፍታትና የመሳሰሉት ዕርምጃዎችን መውሰድ ከመንግሥት የሚጠበቅ ተግባር አይደለም፡፡ ይኼን ያደረጉት አብዛኞቹ ሰዎች ባልታወቁ ሰዎች በንብረታችን ላይ ጉዳት ይደርሳል ከሚል ሥጋት ነው፡፡ በፈቃዳቸው ያደረጉ ቢኖሩም ባናሟሙቀው ይሻላል፡፡ ለመሆኑ መንግሥት ያሸጋቸውን ሱቆችና ታርጋቸውን የፈታባቸውን ተሽከርካሪዎች ምን ሊያደርጋቸው ነው? አንድ ግልጽ ነገር አለ፡፡ መንግሥት የከለከለውን ሁሉ ይፈቅዳል፡፡ እሽጉም ይቀደዳል፣ ሰሌዳውም ይመለሳል፡፡ የዚህ ዓይነት ድርጊቶች መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተዓማኒነትና መንግሥታዊ ግርማ ሞገሱን ያሳጡታል፡፡ መንግሥት ለሚያልፍ ነገር ሁሉ ከሕዝብ ጋር እልህ መጋባትና አታካሮ ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ እነዚህ የዕለት ተዕለት አምባጓሮዎች የሕይወትና የንብረት መስዋዕትነት እየጠየቁ ነው፡፡ ይኼን ሁሉ ወደ ጐን አድርገን ወደ ውይይት እንግባ፡፡

ለመሆኑ የኢሕአዴግ መንግሥት አንድ ቀን ሥልጣኔን እለቃለሁ ሌላም የሚተካኝ ይመጣል ብሎ ያስባል? ነገሩ ቢታሰብም ባይታሰብም ውሎ አድሮም ቢሆን አይቀሬ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ሁልጊዜ መጣር ያለበት ከዕለት ሥራው ጐን ለጐን አገሪቱን በሰላማዊ መንገድ ሌሎች የሚረከቡበትን የረጅምም ሆነ የአጭር ጊዜ ዓላማ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይኼ የአስተሳሰብ ጠቃሚነቱ ለሁሉም ነው፡፡ በተለይ የገዢው ፓርቲ መንግሥት ጥሮ ግሮ ያስመዘገባቸው የልማትም ሆነ የፖለቲካ ውጤቶች እውቅና ያገኛሉ፡፡ በክብርም ለትውልድ ይተላለፋሉ፡፡ በእልህና በጉልበት የመጠቀሙ ጉዳይ ሕይወትና ንብረት የሚያወድምና የተለፋበትን ሁሉ ውጤት አልባ የሚያደርግ ነው፡፡

ሌላው የኢሕአዴግ መንግሥት ዋና ችግር የአቅም ጉዳይ ነው፡፡ አብዛኞቹ ሹሞች የሚሾሙት በፖለቲካ ወገንተኝነታቸው እንጂ በእውነተኛ ትምህርት፣ ብቃት፣ ብስለትና ለቦታው ተገቢ በመሆን አይደለም፡፡ አብዛኞቹ ባለሥልጣናት ዲግሪው በልካቸው የተፈጠረላቸው እንጂ እነሱ በያዙት ዲግሪ እኩል ቀርቶ ግማሹም ችሎታ የላቸውም፡፡ ዛሬ የማስተርስ ዲግሪ ይዘው በአስተርጓሚ ካልሆነ በስተቀር የውጭ ዜጐችን በእንግሊዝኛ አነጋግሮ ሐሳብ መረዳትና የራስ ሐሳብን ማስረዳት የሚችሉ የሉም ማለት ይቻላል፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን እንደያዘ የተማሩ አባላትን ሲመለምል ከጐን ያሉት ነባር ታጋዮች ቦታዬን የሚቀማኝ መጣ በማለት ያለጥፋት በግምገማ ያባርሩ እንደነበር ይፋ አድርጐ ነበር፡፡ ዛሬም ይኼ አስተሳሰብ የለም ይሆን?

የአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሚኒስትር ዴኤታ የነበረ ሰው በውጭ ቴሌቪዥን በየቀኑ የሚሰጠውን አስተያየት ያዳመጠ ሁሉ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሚኒስትር ደረጃም ቢሆን ብስለታቸውንና እውቀታቸውን ለመገምገም በቂ ናሙና ነው፡፡ ይኼ ሰው የግለሰቦችን ስም እያጠፋ የሚሰጠው አስተያየት በጣም የሚቀፍ ነው፡፡ የአገር ተቆርቋሪነትና የአገርን ሚስጥር መጠበቅ ብሎ ነገር አልፈጠረበትም፡፡ መንግሥትን መቃወሙን ብቻ ነው የሚያየው፡፡ የሚናገራቸው ነገሮች ሁሉ ታስበውና ተጠንተው ለሚዲያ የሚቀርቡ አይደሉም፡፡ እንዲሁ አፉ ላይ የመጣውን ሁሉ ያለ ይሉኝታ ይዘረግፈዋል፡፡ ታዲያ ኢሕአዴግ ይኼንንና ብዙ የእሱ ቢጤዎችን ከተራ የመንደር ጐረምሶች ውስጥ ሲሾም መሥፈርቱ ምንድን ነበር?  ይኼ ሰው ምንም ሳይታወቅ በክልሎች ኮታ የተሾመ ይመስላል፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት አሿሿም ሲገርመን ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ በቅርቡ በሪዮ ኦሊምፒክ ጭቅጭቅ የፈጠረው የኦሊምፒክ ውጤት ማሽቆልቆልን ተከትሎ፣ በአትሌቶችና በባለሙያዎች መካከል የተፈጠረው ያለመግባባት እስካሁን አልበረደም፡፡

የሚገርመው ነገር ኢሕአዴግ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ካቋቋመ ጀምሮ በፕሬዚዳንትነት የሚመራው በቋሚነት የአማራ ክልል ተወካይ ነው፡፡ ቦታው ለአማራ ክልል የተሰጠ በመሆኑ አባላት ከየክልሉ መጥተው ሲሰበሰቡ የአማራ ክልል አቶ እከሌን የላከልን ስለሆነ ቀጣይ ፕሬዚዳንታችን እሳቸው ናቸው ተብሎ ያለምርጫ በጭብጨባ ይደመደማል፡፡ ስለዚህ ይኼ ቦታ የአማራ ነው የሚል ስም ይሰጠዋል፡፡ ሌሎች በርካታ መሥሪያ ቤቶችም እንደዚሁ ናቸው፡፡

ቀደም ሲል በነበሩት መንግሥታት የአንድ ክፍለ ሀገር ፖሊስ አዛዥ የሚሾመው በፖሊስ ትምህርት የገፋ፣ በሙያውና በአገልግሎቱ ቢያንስ የብርጋዴር ጄኔራልነት ማዕረግ የነበረው ሰው ነበር፡፡ አሁን ግን ከአንድ በላይ ክፍለ ሀገሮች ተሰብስበው አንድ ክልል በሆኑበት ዘመን የክልል ፖሊስ አዛዥ የሚሆነው ስለፖሊስ ሥራና ትምህርት ምንም እውቀት የሌለው፣ በሥራ ልምዱም ሆነ በዕድሜው ያልገፋ ጃኬትና ቲሸርት ለባሹ ወጣት የድርጅት አባል ነው፡፡ ታዲያ ይኼ ሰው በማያውቀው ሙያና ከፍተኛ ኃላፊነት በሚጠይቀው የፖሊስ አመራር ላይ ተመድቦ ስህተቶች ቢፈጸሙ ኃላፊነቱ የማን ነው? በአሁን ጊዜ መንግሥት ስለሰዎች ብቃትና የሥራ ጥራት የሚጨነቅ አይመስልም፡፡ የሚያስጨንቀው ነገር ቢኖር መዋቅሮቹ ሁሉ በአባላት መሞላታቸው ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የኢሕአዴግ አባል በመሆናቸው የማያውቁትን ሥራ ሊያከናውኑ አይችሉም፡፡ እንዲያውም ያበላሹታል፡፡ መንግሥትን ከሕዝብ እያቆራረጠ ያለው አንዱ ጉዳይም ይኼ ነው፡፡ ሁሉም ሥራዎች በተገቢው ሠራተኛ መሞላት አለባቸው፡፡ የተለያዩ የአሠራር ድክመቶችና የመልካም አስተዳደር ዕጦት አንዱ መነሻ ይኼ ነው፡፡

ሌላው የአገራችን መፃኢ ዕድል ሊያጨልመው የሚችለው በውጭ አገር ያሉ የተቃዋሚዎች ሁኔታ ነው፡፡ መንግሥትን አምርሮ በመጥላት በጥፋት መንገድ ጭምር ከሥልጣን ለማውረድ ሰፊ ቅስቀሳ ያካሂዳሉ፡፡ ነገር ግን ሐሳባቸው እንኳ ቢሳካ አገሪቱን ለማረጋጋት አንድም ሐሳብ ሆነ ሥጋት አይታያቸውም፡፡ በተለያዩ ቋንቋዎች የ24 ሰዓት የአየር ጊዜ ስላላቸው ሙሉውን ጊዜ በመጠፋፋት መንግሥትን እናውርድ እያሉ ይሰብካሉ፡፡ ‹‹የቸገረው ደሃ ይገባል ከውኃ›› እንደሚባለው ይህንን የመጠፋፋት ቅስቀሳ የሚከታተሉና የሚደግፉ በአገር ውስጥም መኖራቸው ነው፡፡ ምክንያቱም የመንግሥት ሚዲያዎች ትልልቅ የአገር ጉዳዮችን ወደ ጐን በመተው በአሰልቺ ፕሮግራሞች በመጠመዳቸው ነው፡፡

የቂሊንጦ እስር ቤት ተቃጥሎ ቤተሰብና ሕዝብ በጭንቀት ውስጥ እያለ የእኛ ሚዲያዎች ምንም እንዳልተፈጠረ ሕዝቡ ለመንግሥት የሚሰጠውን ድጋፍ ያስተላልፋሉ፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ሳይወድ ሙሉ በሙሉ እንኳ እውነትነት ባይኖረው ስለቃጠሎው ፍንጭ ይሰጡኛል ብሎ እነዚህን የውጭ ሚዲያዎችና ማኅበራዊ ድረ ገጾችን ሲከታተል ይውላል፡፡ እነዚህ የውጭ ሚዲያዎችን ለመጠፋፊያነት የሚጠቀሙ ጽንፈኛ ዳያስፖራዎች ምን ዓይነት የፖለቲካ አጀንዳ አላቸው? እርስ በርሳቸውስ ተግባብተው አገሪቱን መምራት ቀርቶ ብቁ አመራር እንዲፈጠር ማድረግ ይችላሉ? ወይስ እንደ ዶሮዋ ‹‹ባልበላውም አፈሰዋለሁ›› ነው፡፡

አሁን ኢሕአዴግን ሰንገው የያዙት ኢሳትና ኦኤምኤን ጣቢያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ጣቢያዎች የአማራና የኦሮሞን ሕዝብ ስሜታዊነት አይተው ጥግ ድረስ ሄደው ለመቀስቀስ የሚሞክሩ ናቸው፡፡ በየፊናቸው የሚያስተላልፉት ፕሮግራም ይዘት ግን ሁለቱን ሕዝቦች የሚያቃርኑና የሚያለያዩ ናቸው፡፡ አንዱ የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ በጎሰኝነት ፈርጆ ስለአንዲት ኢትዮጵያ ያወራል፡፡ ሌላው ስለብሔር ጭቆና ብቻ የሚመለከተው ይመስላል፡፡ ለመሆኑ ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን ያስባሉ? አሀዳዊት ወይስ ፌዴራላዊት? ፌዴራላዊት ካሉ ክልሎች እንዴት ይፈጠራሉ? እንዳሁኑ በብሔር ብሔረሰብ አሠፋፈር ወይስ ሁሉንም ሕዝቦች አንድ ላይ አሰባጥረው ሌላ ክልል ነው የሚፈጥሩት፡፡ ጣቢያውን የሚመሩት ወጣት ልጆች በዚች ጉዳይ እንኳ ዝንተ ዓለም አይስማሙም፡፡ የሚያስማማቸው አንድ ነገር ቢኖር ኢሕአዴግን ማስወገድ ነው፡፡ ይኼ እነሱ የሚስማሙበትን አንድ ነገር ብዙ ሰው ይጋራዋል፡፡ ነገር ግን የዕለት ጉዳይን ብቻ የሚያስቡ ክፍሎች ነፃ የአየር ጣቢያ አገኘን ብለው ቀኑን ሙሉ የሚሰብኩንን ፍሬ አልባ ዲስኩር በጭፍን መቀበል ይቸግራል፡፡ ከኢሕአዴግ አገሪቱን ተረክቦ የሚመራንና በሰላም የሚያሸጋግረን፣ እንዲሁም የማረጋጋት ሥራ በብቃት ሊወጣ የሚችል ድርጅት ያስፈልገናል፡፡ በተለይ በአገር ውስጥ ያላችሁ ተቃዋሚዎች ይህንን ማሟላት ይጠበቅባችኋል፡፡

በመጨረሻ ወጣቶቻችን ይኼን ጉዳይ እንዴት ማየት ይገባቸዋል? የኢትዮጵያን ሕዝብ ችግር ወጣቶች ሲያስተጋቡ ኖረዋል፡፡ ችግሮችን በሚያነሱበት ጊዜ ሁሉ ሊከተል የሚችለውን መጨረሻ አይገምቱትም፡፡ በጣም የሚያስቆጨው በ1966 ዓ.ም. ወጣቱ በረጅም ትግል ሊያገኝ የተቃረበውን ድል በስሜታዊነት በመምራቱ ድሉን በቀላሉ ለወታደራዊ አገዛዝ አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ይቺ ትንሽ የምትመስል ስህተትና ወጣትነት ያስከተለው የወደፊትን በርቀት ያለማስተዋል የአገሪቱን ዕድል መቀመቅ ከትቶታል፡፡

ብዙ ነገሮች አዕምሮአችንን የሚገዙት በተደጋጋሚ በምናየውና በምንሰማው ነገር ነው፡፡ አዕምሮአችን በተደጋጋሚ ያየውንና የሰማውን በውስጣችን ጥልቅ መሠረት ያስይዛቸዋል፡፡ እንደ አቀባበላችን ሁኔታና እንደ ነገሩ ይዘት የፍቅር ወይም የጥላቻ ስሜት ይፈጥርብናል፡፡ ይኼ ቅቡልነት በአንድ ጫፍና በሌላ ጫፍ የጥላቻ ወይም የፍቅር መደብ ስለሚይዝ ሰዎች እንደተፈጠረባቸው ስሜት በአመለካከት ይለያየሉ፡፡ የነገሮች የውስጥ ስርፀት ባደገ ቁጥር አንዱ በአንዱ ላይ በምክንያት ሳይሆን በስሜት የሚፈጠር ጥላቻ ይኖረዋል፡፡

በስሜታዊነት አንመራ፡፡ ስሜታዊነት ያልፋል፡፡ የእሱ ውጤት የሆነው ጥላቻም ይኖረዋል፡፡ የሚያስከተለው ፀፀትና ቁጭት ግን ዝንተ ዓለም አያልፍም፡፡ ስለአገራችን ሁኔታ አንድ የተጨበጠ ነገር ተወያይተን ማግኘት አለብን፡፡ ሰዓት በጨመረ ቁጥር ቀኑ ሊጨልም ነው፡፡ አሁን ለዓይን ያዝ ባደረገበት አመሻሽ ላይ ነን፡፡ መንግሥት መብራት አብርቶ ሕዝቡ እንዲተያይና እንዲወያይ ያድርግ፡፡ ልንነጋገርባቸው የሚገቡን ነገሮች ሁልጊዜ አይኖሩም፡፡ ትክክለኛው የመነጋገሪያ ጊዜ ካለፈ የምንነጋገርበት ጉዳይ ስለማይኖር መፍትሔው ሌላ አማራጭ ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

        

 

Standard (Image)

ጥልቅ ተሃድሶ የማድረጉ ተስፋና የተጋረጠው ፈተና

$
0
0

  በአስፋወሰን በኃይሉ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መራሹ መንግሥት ኢትዮጽያን ለ25 ዓመታት አስተዳደሯል፡፡ ይህ አራት አባል ፓርቲዎችንና ቢያንስ አራት አጋር ድርጅቶችን የያዘ ፖለቲካዊ ሥርዓት ፌዴራላዊ አስተዳደርን በመተግበሩም ይጠቀሳል፡፡ ይህ ኃይል ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ በአገሪቱ ይብዛም ይነስም ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ታይቷል፡፡ በዚያው ልክ የአገሪቱ ሕዝብ ወደ እጥፍ ገደማ አድጓል፡፡ የፖለቲካና የዴሞክራሲያዊ ፍላጎቱ በዚያው ልክ ጨምሯል፡፡ ዓለም በቴክኖሎጂና በመረጃም ወደ አንድ መንደርነት በመምጣቱ ሁሉንም እውነት ገላልጦት አርፏል፡፡

እነዚህ ነባራዊ ሁኔታዎች በተንሰራፋባት ሁኔታ በየትኛውም አገር ያሉ መንግሥታትን የሚገጥም ጫና (Challenge) ኢሕአዴግን ገጥሞታል፡፡ በየትኛውም የአገሪቱ ጫፍ የሚፈጸም የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የዴሞክራሲ መብት አፈና ከዳር ዳር ይጋለጣል፡፡ ቢሮክራሲ ውስጥ የሚፈጠር የመልካም አስተዳደር ጥሰትና ሙስናም ያስመረረውን ዜጋ ብቻ ሳይሆን መላውን ሕዝብ የሚያቆስል እስከመሆን ይደርሳል፡፡

ድርጅቱ ከነበረው ታሪካዊ ጉዞ አንፃር የነበረው ‹‹ሚስጥራዊነት›› እንኳን የነገር ወንፊት ተክቶታል፡፡ በኢሕአዴግ ምክር ቤትና በየብሔራዊ ድርጅቱ የተናገሩት ሕዝብ የሚያስከፉ ንግግሮች በቅፅበት እየወጡ አደባባይ ላይ ውለዋል፡፡ ከሁሉ በላይ ኢሕአዴግን በመሠረቱት ፓርቲዎች መካከል ለ25 ዓመታትና ከዚያ በላይ የነበረው ‹‹ኢእኩልነት›› እየተጋለጠ መጥቷል፡፡ አድርባይነትም ይባል ችሎ ማለፍ ተሸክሞት የኖረው ፖለቲከኛ ሁሉ ‹‹ለምን?›› ማለት ጀምሯል፡፡

ከዚህ የከፋው ነገር ደግሞ ከአንድነትና ኅብረት ይልቅ ልዩነትንና የመንደር ማንነትን ሲያቀነቅን የከረመው አስተሳሰብ ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡ ‹‹በእንቁላል ጊዜ በቀጣሽኝ›› እንዲሉ ገና ከመነሻው አንተ የእኔ ብሔር አባል አይደለህም ከክልሌ ውጣ ማለት ሲመጣ ‹‹ተው!›› ባለመባሉ ዛሬ አንዱ ብሔር የሌላውን ሀብት እያወደመ እርቃኑን ማሳደድ ይዟል፡፡ መፍትሔ ካልተበጀለትም ማንም የአገሪቱ ዜጋ ዋስትና ኖሮት በፈለገው ቦታ ሀብት ለማፍራት የሚደፍርበት መብት ጥያቄ አስነስቷል፡፡

እርግጥ ጠባብነትም ይባል ዘረኝነት ለሚባለው ኋላቀር ርዕዮት በውስጥም ሆነ በውጭ ያለው ፅንፈኛ ኃይል የራሱን አሉታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በራሱ በፌዴራል ሥርዓቱ ውስጥ ሲቀነቀን የኖረውን የቋንቋና የዘር አጀንዳ መሠረት አድርጎ ባለሥልጣናትን (እስከ ቀበሌ አስተዳዳሪ ድረስ)፣ ጄኔራሎችን፣ ባለሀብቶችን፣ ሕንፃዎችንና ትልልቅ ድርጅቶችን መቁጠር ጀምሯል፡፡ በተቃራኒው የታሰረውንና የተሰደደውን ዜጋ በኢትዮጵያዊነቱ ሳይሆን በብሔር ማንነቱ እየተጠቀሰ ‹‹አንዱ ልጅ ሌላው እንጀራ ልጅ›› የሚል አገላለጽ ከጓዳ እስከ አደባባይ ያስተጋባል፡፡

አሁን መሬት ላይ ያለውን እውነታ የተገነዘበው ገዥው ፓርቲም ችግሩ የውስጣችን ነው ብሎ አምኗል፡፡ በእሱ ብቻ ሳይሆን መፍትሔውም ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ማድረግ ነው በሚል ቢያንስ ከ15 ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ የተፈጠረውን በጎና መጥፎ ነገር ፈርጅ በፈርጅ መገምገም ጀምሯል፡፡ በሥራ አስፈጻሚ፣ በኢሕአዴግ ምክር ቤትና በአባል ድርጅቶቹ የማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ የተሰነበተበት ግምገማ፣ ባሳለፍናቸው ሳምንታት ደግሞ በየደረጃው የሚገኙ የሥራ መሪዎች አድርሶ ወደ ሕዝቡ ለመውረድ እየተንደረደረ መሆኑ በመነገር ላይ ነው፡፡

በመድረኮቹ ከቀረበው መነሻ ጽሑፍና በተለያዩ መድረኮች ከተነሱ ሐሳቦች አንፃር ውስጥ አዋቂ ምንጮችን መሠረት በማድረግ ለጋዜጣ በሚሆን መንገድ አቀርበዋለሁ፡፡ በዚህ መነሻም ገዢው ፓርቲ ሊያደርገው ያሰበው ተሃድሶ ምን ተግዳሮት ይገጥመዋል፤ እስከምን ድረስስ ሊሄድ ይችላል የሚል ፍተሻ አንባቢዎች እንዲያደርጉ ዕድል ለመስጠት እንሻለን፡፡

የሙስናውና አቋራጭ ብልፅግናው

አሁን ባለው የአገሪቱ መንግሥት ውስጥ ሙስናና ብልሹ አሠራር ሕዝብን እያማረረ ስለመሆኑ ከሪፖርተር ጋዜጣ በላይ ደጋግሞ ያስተጋባ የለም፡፡ እርግጥ ገዢው ፓርቲም ደፍሮ የእርምት ዕርምጃ መውሰድ አይቻል እንጂ ችግሩ እንዳለ ደጋግሞ አንስቷል፡፡ አሁን በተሃድሶው ላይ አዲስ ነገር ሆኖ የመጣው የዝቅጠት አደጋው (ከ1993 ዓ.ም. በላይ) በሥርዓት ደረጃ እየተፈጸመ ነው/አይደለም የሚለው ውዝግብ ነው፡፡

በተለይ ብሔርን፣ በትጥቅ ትግሉ የነበረ አስተዋጽኦን ወይም ‹‹ቀደም ሲል ተበድለናል›› በሚል ሽፋን በሕገወጥ መንገድ ካለውድድርና በአቋራጭ እየበለፀጉ ያሉ ወገኖች መበርከታቸው ተነስቷል፡፡ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ጭምር ባለግዙፍ ሕንፃና ትልልቅ ኩባንያ ባለቤት የሆኑ፣ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ማሽነሪዎችን የሚያከራዩ ባለሥልጣናትና ዘመዶቻቸው በሕዝቡ ይታወቃሉ፡፡ በሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶችም የተያዘ መረጃ እየወጣ ነው፡፡

አሳዛኙ ነገር በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች (ሰበታ፣ ቡራዩ፣ ሱሉልታ፣ ለገጣፎ፣ 44 ማዞሪያ፣ ሆለታ፣ ዓለም ገና…) የተፈጸመው የመሬት ወረራ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ከ1997 ዓ.ም. የኢሕአዴግ በተቃዋሚዎች የመነቅነቅ አደጋ በኋላ በመንግሥት ‹‹አሠራር›› የተደገፈ የሚመስል ወንጀል ተፈጽሟል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ደረጃና በየአካባቢው የተመደቡ ‹‹አመራሮች›› የአምስትና የአሥር ቦታዎች ካርታ እጃቸው አስገቡ፡፡ ለፈለጉት ወገን በርካሽና በስጦታ ጭምር ቸበቸቡ፡፡ በዚህ መሀል በፌዴራል መንግሥት ኃላፊነት፣ በደኅንነት፣ በመከላከያና በፌዴራል ፖሊስ በተለይ አዛዥነትና መስመራዊ መኮንን ደረጃ ላይ ያለው የድርሻውን አነሳ፡፡

በዚህ ድርጊት ውስጥ የገቡ የመንግሥትና የገዢው ፓርቲ ሰዎች ብቻ አይደሉም፡፡ ሕገወጥ ደላሎችና የሕዝብ መሬት አግበስባሾችም ናቸው፡፡ ስለዚህ ይህ ችግር ወደ አንድ ወገን (ብሔር) የሚገፋ ሳይሆን የሥርዓቱ ድክመትና ንቅዘት ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡ ስለሆነም አሠራርና አደረጃጀትም ዘርግቶ በገፍ የተዘረፈውን ሀብት በሕግ ጠይቆም ሕዝባዊና አብዮታዊ እርምት ሊወስድ የሚችለው ራሱ ኢሕአዴግ ብቻ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻለም የከፋ ቅሬታና ውድቀት ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡

ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ ቀስ በቀስ እየገነገነ የመጣው ሌላው የሙስናና የኢኮኖሚ ዳባ ተግባር በገቢዎችና ጉምሩክ መስኩ የተፈጸመ ነው፡፡ ይህ የአንድ አገር የፖለቲካ ኢኮኖሚ ዋነኛ መሣሪያ አንዱን ወገን የመበደል፣ ሌላውን ያላግባብ የማበልፀግ በር የሚከፍትበት ነው፡፡ መንግሥት በጠንካራ አሠራርና ሕግ፣ እንዲሁም በሥነ ምግባርና ፍትሐዊ አስተዳደር ካመራው ለአገር ለውጥ በእጅጉ የሚጠቅም ነው፡፡

ከዚህ አንፃር በአገሪቱ አሁን ለተደረሰበት ለውጥ የሕዝቡ ግብርና ታክስ የመክፈል አቅምና አድማስ መስፋት አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡ ከቀረጥ ነፃ ታክስ ከገባው ባሻገር በገቢና በወጪ ምርት ላይ የጉምሩክ ቀረጥ ተጠናክሮ መተግበሩም ዋነኛው መሣሪያ ነበር፡፡ በዚህ ሒደትም ውስጥ ግን ‹‹ዘግናኝ›› የሚባሉ የሙስና ወንጀሎች እንደተፈጸመበት ከሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የተገኙ መረጃዎች ያስገነዝባሉ፡፡

‹‹ከዓመታት በፊት በቁጥጥር ሥር ከዋሉ የዘርፉ ተጠርጣሪ ባለሥልጣናት (ዋና ዳይሬክተር) ጀምሮ የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች፣ የመምርያ ኃላፊዎች፣ ከሳሽ ዓቃብያነ ሕግና ባለሙያዎች በአገር ሀብት አሻጥሩ ውስጥ ተሰማርተዋል፤›› የሚለው መረጃ በአገሪቱ ‹‹አንቱ›› ሲባሉ የከረሙ ባለሀብቶችም በቀረጥና በጉምሩክ አሻጥር ጭቃ ውስጥ ተዘፍቀው በመገኘታቸው ወህኒ ወርደዋል፡፡

በዚያ ወንጀል ምርመራና ተጠርጣሪዎች መያዝ ወቅት እንደተመለከትነው፣ አንዳንዱ ባለሥልጣን ለአሥር ቤተሰብ የሚያገለግል የቤት ካርታ ብቻ አልነበረም የያዘው፡፡ በርከት ያለ ሕገወጥ መሣሪያና የመከላከያ ሠራዊት ልብስ ጭምር ተይዟል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ነው አሁን ሙስናውን ገፍቶ ለመታገል የሚያስቸግረው የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ሙሰኞች በሕገወጥ ድርጊት የሰከሩ በመሆናቸው የግለሰቦችን ጌጣጌጥ ሳይቀር ይነጥቁ እንደበርም እያፈርን ተመልክተናል፡፡

በኮሚሽኑ ድክመትም ይባል በመንግሥት ቁርጠኝነት ማጣት ያልተከሰሱ፣ ተጀምሮ ክሳቸው የተቋረጠ፣ ተከሰውና መረጃ ተደራጅቶባቸውም ውሳኔ ያልተሰጣቸው ሙሰኞችም እንዳሉም ይነገራል፡፡ ለአብነት የብረታ ብረት አስመጪዎችና ‹‹የሪል ስቴት›› አልሚ ተብዬ ነጣቂዎች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በጥቅም ተካፋይ ባለሥልጣናት እየተደገፉ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር የአገር ሀብት ለግል ጥቅም እንዳዋሉም መረጃ አስደግፈው የሚያስረዱ አሉ፡፡

በሲሚንቶ፣ በስኳር፣ በቡና፣ በጫትና በመሳሰሉት ወጪና ገቢ ምርቶች፣ በተሽከርካሪና በማሽነሪ ከቀረጥ ነፃ በማስገባት ከፍተኛ ዝርፊያ ተፈጽሟል፡፡ ለጥቂቶች ብቻ የተፈቀደ በሚመስለው ‹‹ትራንዚተርነት›› በቅፅበት የከበሩትን በየመንደራችን አይተናል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ የከፍተኛ ግብር ከፋዮችን ዓመታዋ ክፍያ በመሸሸግና በመቀነስ ሙስና የሚያሳድዱ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አንዳንድ ጥገኞችም ገና ፍትሕ አላገኙም፡፡

እንግዲህ ሙስና ሲነሳ መሬትና ግብርን አነሳን እንጂ በመንግሥት ግዢና ሽያጭ፣ በአገልግሎት አሰጣጥና የኮንትራት ግዢ ሁሉ የደራ ሌብነት አለ፡፡ መጠኑና ዓይነቱ ከመለያየቱ በስተቀር የሻገተው የሥርዓት ንቅዘትም ገና የሚገታውን ዕርምጃ አላገኘም፡፡

የፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ረገድ

የኢሕአዴግ ተሃድሶ ቁልፍ ጉዳይ ሆኖ እየመጣ ያለው ሌላው አነጋጋሪ አጀንዳ እነ እገሌ በአጭር ጊዜ በለፀጉ እኛ ተጎዳን የሚለው ቅስቀሳ ነው፡፡ በተለይ ሕወሓትን መሠረት አድርገው ያሉ ባለሥልጣናትን ስም በመጥቀስ በሁሉም መስክ ተጠቃሚ የሆኑ ወገኖች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ምንም እንኳን ሁሉም ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው ቢያስተዳድሩም የፌዴራሉን ‹‹ቁልፍ›› የሚባሉ ቦታዎች የአንድ ብሔረሰብ ሰዎች እንደያዙ ነው የሚለው ትችት ከምክር ቤቶች እስከ መንደር ቡና መጣጫዎች የሚሰለቅ ሆኗል፡፡

አንዳንድ ተቺዎችም የመሥሪያ ቤቶችን ስምና የኃላፊዎችን ዝርዝር እስከ መጥቀስ ድረስ ይወርዳሉ፡፡ የተለያዩ ተቋማትንና ግለሰቦችን ስም በመጥቀስ ብዙ ነገሮች ይባላሉ፡፡ ይህ ከተግባርና ከሥነ ምግባር ውጤታማነት ውጪ የሆነ አሠራር ባለፉት 60 ዓመታት ገደማ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለሚያወዛግቡ ድርጊቶች የተጋለጠ ነው፡፡

ነገር ግን አሁን ላለው ውዝግብ ወደ ዳር የማይገፋ አንድ ጭብጥ ሆኗል ጉዳዩ፡፡ አገሪቱ 25 ዓመታት በዕድገትና ለውጥ ውስጥ እንደመሆኗ ቀላል ቁጥር የሌላቸው ግለሰቦች ከፍ ያለ ሀብት ማፍራታቸው አይቀርም፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ባለተሽከርካሪ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩም ቤትና ደመወዝ አግኝተዋል፡፡ ከዚህ አልፎ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ባለ ሕንፃ፣ ባለትልቅ ፋብሪካና ባለሰፋፊ እርሻና ማሽነሪ ባለቤቶች የሆኑ ሰዎች ከሕዝብ ሀብት ጋር ያላቸው ቁርኝት ሊመረመር የሚገባው ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ከታዳጊ ክልሎች እስከ አዲስ አበባ በመመንዘር ‹‹እገሌ ከየት አምጥቶ!?›› የሚሉ ዜጎች ዋነኛ መከራከሪያቸው ይኼው ነገር ሆኗል፡፡

በተቃራኒው በአገሪቱ ከመነጨው ሰፊ የሚባል ሀብት በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ የሚገልጹ ወገኖች አሉ፡፡ በተለይ በመሠረተ ልማት ሥርጭት፣ በኢንዱስትራላይዜሽን፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና ብድርን በማመቻቸት በኩል ‹‹ምን ተደረገልን?!›› የሚሉ አካባቢዎች አሉ፡፡ ምንም እንኳን በትምህርትና በጤና ተቋማት ፍትሐዊ ክፍፍል ቢኖርም፣ ከላይ በተጠቀሱት ሰፊ ሀብት በሚፈልጉ ተግባራት ሕዝቡን ወደ ማርካት መሄድ ያስፈልጋል፡፡

መንግሥት ሌሎች አገሮች በሚሄዱበት የነፍስ ወከፍ ገቢና በመሳሰሉት መለኪያዎች ብቻ ዜጎች ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል አግኝተዋል ሊል አይችልም፡፡ አሁንም አገሪቱ ያላትን ውስን ሀብት በግልጽ፣ ተጠያቂነት በተላበሰና በፍትሐዊነት ሕዝቡ እንዲጠቀምበት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማን ሁኔታ እንደ አንድ አብነት ብንወስድ ከቀበሌ ቤት፣ ከጋራ ኮንዶሚኒየምና ከጥቃቅንና አነስተኛ አደረጃጀት ጋር የሚያያዙ የአሠራር ክፍተቶች ለዚህ ዓይነቱ ቅሬታ በር ይከፍታሉ፡፡

አሁን እየወጡ እንዳሉት መረጃዎች በሺዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ቤቶች ሁለትና ከዚያ በላይ ባላቸው ሰዎች ተይዘዋል፡፡ ‹‹ሕገወጥ›› ተብለው ወደ መንግሥት የተመለሱት 1,400 ቤቶችም ለእነማን እንደሚሰጡ ግልጽ አሠራር አልተበጀም፡፡ ከ800 የማያንሱቱ ደግሞ አሁንም እየታወቀ ወደ ግል ይዞታነት በንጥቂያ ተዛውረዋል፡፡ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ደረጃ አራት ሺሕ የሚደርሱ ያላግባብ ተይዘው ያሉ ክፍት ቤቶችስ ለምን ጥቅም ማዋሉ? እነማን ናቸው እየገቡባቸው ያሉት?… ዝርዝሩ ብዙና ውስብስብ ነው፡፡

በሌላ በኩል ከትልቁ አገራዊ ‹‹ኬክ›› በአግባቡ መከፋፈል ያልቻሉ የገጠር ወጣቶችም ወደ አዲስ አበባ እያደረጉት ያለው ፍልሰት መፈተሽ ያለበት ነው፡፡ በተለይ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው ሰፋ ያለ ፍልሰት ለሥራ አጥነትና ለኑሮ ውድነት ብቻ ሳይሆን ለወንጀልና ለከተማ ደኅንነት ዕጦትም ይዳርጋል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ዜጋ በያለበት የአቅሙን ያህል እንዲንቀሳቀስ ዕድሎችን መፍጠር ጠቃሚ ነው፡፡ ቢያንስ ፍልሰቱም ወደ ክልሎችና ዞን ከተሞች ቢሆን (ለዚህ የሰው ጉልበት ያለበት ማዕከል መፈጠር ያስፈልጋል) የተሻለ ይሆናል፡፡

ሰላምና መረጋጋትን የመመለስ ጉዳይ

አንድ ታዋቂ ጦማሪ የአሁኑ የኢሕአዴግ አመራር የጂቲፒ ሁለት ትግበራ ‹‹ሠላምና ደኅንነትን ማረጋገጥ ነው›› ያለውን አባባል እጋራለሁ፡፡ ይነስም ይብዛም ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት ጎላ ያለችግር ተፈጥሮ የነበረው በምርጫ 97 ወቅት ነው፡፡ ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ ግፋ ቢል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣  አንዳንዴ በአምልኮ ሥፍራዎች የሚነሳ ወቅታዊ ግርግር ካልሆነ በስተቀር የበረታ የሰላም መደፍረስና የመረጋጋት ሥጋት አጋጥሟል ለማለት አያስደፍርም፡፡

ካሳለፍነው ዓመት ጀምሮ እነሆ ወደ አዲሱም የተሸጋገረው ሕዝባዊ እንቢተኘነት ግን ኃይል የተቀላቀለበት ሆኗል፡፡ የቅርብ ጊዜውን በደብረዘይት ኢሬቻ በዓል ላይ ተረጋግጠው ያለቁ ዜገችን ጨምሮ በጣም በርካታ ዜጎች እርስ በርስና ከፀጥታ ኃይል ጋር በመፋለም ወድቀዋል፡፡

እዚህ ላይ ዜጎች ሰላማዊና ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ማንኛውንም ጥያቄ ሊያቀርቡ ይገባል፡፡ ግን አልፈው ንብረት ማውደምና ፀጥታን ማወካቸው ድርጊቱ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲሄድ ማድረጉ አይቀርም፡፡ የፀጥታ ኃይሉም ቢሆን የዜጎችም ሆነ የንብረት ደኅንነት አደጋ ላይ እስካልወደቀ ድረስ የአንድም ሰው ሕይወት እንዳይጠፋ መጠንቀቅ አለበት፡፡ ይሁንና ለማደናገጥም ወይም ሆን ተብሎ የሕዝብ ጥያቄን ለመጨፍለቅ የፀጥታ ኃይሉ ተኮሰ እየገደለ ይገኛል፡፡

እውነት ለመናገር ይህ አካሄድ የትም ሊያደርስ አይችልም፡፡ በመንግሥት ላይ የተነሳውን የሕዝብ ቅሬታ ከማባባስና ከማስፋት በስተቀር፡፡ በተለይ በውጭ ያለው ፅንፈኛ ኃይል ሆን ብሎ ዘር እየለየ ለማፋጀት የሚከተለው አደገኛ ሥልት ሲታከልበት መጪው ጊዜ አርማጌዲዮን እንዳይሆን ያሳስባል፡፡ መንግሥትና መሪው ፓርቲም በሆደ ሰፊነትና በጥልቀት ሊመረምሩት ይገባል፡፡

ገና ለጋ በሆነው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ቀላል ግምት የማይሰጠው የሕዝብና የግለሰቦች ንብረት እየወደመ መሆኑም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ከሰሞኑ ብቻ በቄለም ወለጋ፣ ደንቢ ዶሎ አምቦ፣ ነጆ፣ ዝዋይ፣ መቂ፣ ሻሸመኔና አገረ ማርያምን በመሳሰሉ ከተሞች በርካታ ተሽከርካሪዎችና የመንግሥትና የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ወድመዋል፡፡

በየአካባቢው ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተረጋግተው ሥራ ለመሥራት ተቸግረዋል፡፡ ብጥብጡና ሁከቱ ደግሞ አገረሸ በማለት በተለይ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል የሚኖሩ አንዳንድ የሌላ ብሔር ተወላጆች እየተጨነቁ ነው፡፡ ተሽከርካሪዎች (በተለይ አውቶቡሶችና ከባድ የጭነት መኪኖች) ደፍረው የአገር አቋራጭ መንገዶችን መያዝ እየፈሩ ነው፡፡ እየደረሰ ባለው አደጋ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ቢሆኑ ከፍተኛ ቅሬታ ውስጥ ናቸው (ቢያንስ በቅርቡ በባለሀብቶች ኢንቨስትመንቶች፣ ፋብሪካዎችና ተሽከርካሪዎች ላይ የደረሰው አደጋ ይመለከታቸዋልና)፡፡

በመንግሥት በኩል እየተወሰደ የለው ዕርምጃ ግን ጥይትና ስብሰባ ብቻ እየመሰለ ነው፡፡ ‹‹የት አለ እውነተኛው ዳቦ?!›› እንዲሉ ፈጥኖ የእርምትና የማሻሻያ ተግባር ካልታየ የአገርን ሰላምና የሕዝብን አጋርነት መልሶ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም፡፡ ለምሳሌ ገዢው ፓርቲ አሁን እንጀመረው ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› እያለ በስብሰባ ጊዜ መብላት ሳይሆን በሌብነት፣ በጠባብነትና ሕዝብን በማገልገል ድክመት የሚወቀሰውን ሁሉ ማራገፍ አለበት፡፡ ዓይን ባወጣ ሌብነት የተዘረፈ የሕዝብ ሀብት ማስመለስና ወንጀለኞችንም በሕግ ማስጠየቅ ይኖርበታል፡፡

እንዳስፈላጊነቱ የሕዝቡን ፍላጎትና ጥያቅ እያዳመጡ ከሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር መወያየት፣ የፖለቲካ እስረኞችን በአፋጣኝ መፍታትም አለበት፡፡ ባሳለፍነው ጊዜ በተከሰተው ግጭት ጉዳት የደረሰባቸውን አቅም በፈቀደ መጠን መካስ፣ ካልሆነም ይቅርታ መጠየቅና ዕርቅ መፈጸም የጨዋነት ባህሪ ነው፡፡

ከሁሉ በላይ አንዱን ሕዝብ በሌላው ላይ ለማስነሳት የሚደረግን ፀያፍ ድርጊት መከላከልና ራሱም እንደ ሥርዓት መቆጠብ አለበት፡፡ አንዱ ወገን አዛኝ፣ ሌላውን በዳይ እያስመሰሉ በእሳት መጫወት ቀውስን አይፈታም፡፡ አሁን በተጨባጭ እየታየ እንዳለው የሕዝቢን ጥያቄና አለመርካት ራሱ በኢሕአዴግ መዋቅር ውስጥ ያለው፣ አንዳንዱ የመንግሥት ተሿሚና ሠራተኛ በግልጽ እየደገፈው ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ከሰሞኑ በመቶ ሺሕ የሚቆጠረው የኢሬቻ በዓል ተሳታፊ በአንድነት ያሰማው ተቃውሞ ነው፡፡

ይህን እውነት ወደ ግራም ቢሉ ወደቀኝ መካድ አይቻልም፡፡ አጉል ከመላላጥ በስተቀርም ለመንግሥት የሚያስገኝለት ፋይዳም አይኖርም፡፡ ስለሆነም የዴሞክራሲ ምኅዳሩ ይስፋ፣ የፕሬስ ነፃነት ይረጋገጥ፣ ኢፍትሐዊ የሚመስለው የሥልጣንና የሀብት ክፍፍል በአፋጣኝ ይታረም፡፡ ካልሆነ በየጊዜው አንድ ዓይነት መዝሙር (የኢሕአዴግን ውለታ፣ የውጭ ጠላትን ደባና ‹‹ፀረ ሰላም›› ኃይሎችን በመውቀስ) የሚመጣ ለውጥ ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡

በአጠቃላይ የኢሕአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ተስፋ ቢኖረውም የተጋረጠበት ፈተና ከባድ ነው፡፡ በተለይ የድርጅቱ መሪዎችና አባላት እውነተኛ ቁርጠኝነት ካላሳዩ ሥርዓቱን ከሞት ማዳን አይችሉም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው Behail11@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

 

 

Standard (Image)

የቱሪዝም ሴክተሩ የሚታደገው ይፈልጋል!

$
0
0

   በአሳምነው ጎርፉ

በብዙዎች የሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት አገሮችን ኢኮኖሚ አሳድጓል፡፡ በመቶ ሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ የኢኮኖሚያቸው መሠረት ነው፡፡ በእጅጉ ሰላምና መረጋጋትን ቢፈልግም የፖለቲካ ልዩነትም ሆነ የርዕዮተ ዓለም ተገዳዳሪነት ሳይገድብ የሰው ልጅን ወዲያ ወዲህ የሚያስብል መስክ ነው የቱሪዝም ኢንዱስትሪው፡፡

ቱሪዝም ለሚባለው መስክ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት (United Nations World Tourism Organization - UNWTO) የሰጠው ትርጉም አለ፡፡ ቱሪዝም ጎብኚ ተብለው በተለዩ ሰዎች የሚፈጸም ክንዋኔ ነው፡፡ ጎብኚ ደግሞ በመደበኝነት ከሚኖሩበት አካባቢ ተነስቶ ቢያንስ ለአንድ ዓመት ቆይታ በዓልን ማክበር፣ ጊዜ ማሳለፍና መዝናናትን የሚያዘወትረውን ነው፡፡ እንዲሁም ሥራን፣ ሕክምናን፣ ትምህርትን ጨምሮ ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ ሌላ መዳረሻ የሚጓዝን ሰውም ይመለከታል፡፡ 

ባሳለፍነው የመስከረም ሁለተኛ ሳምንት ላይ የዓለም ቱሪዝም ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ37ኛ ጊዜ ሲከበር በአዲስ አበባ በልዩ ልዩ ተግባራት ተከናውኗል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ 157 አገሮችን ያቀፈው የዓለም ቱሪዝም ድርጅት መሪ ቃሉን ‹‹ቱሪዝም ለሁሉም ዓለም አቀፈ ተደራሽነት!›› በሚል ነው የሰየመው፡፡ በዚሁ በዓል ላይ የተለያዩ ዓውደ ርዕዮችና ዓውደ ጥናቶች ተካሂደዋል፡፡

የታጨቀው ሀብትና ያልተጋገረው ዳቦ

ኢትዮጵያ ዕምቅ የቱሪስት መስህብ ባለቤት ነች፡፡ በሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ሀብቷ ብቻ ሳይሆን፣ በእንግዳ ተቀባይ፣ በሰላም ወዳድና እንግዳ ተቀባይ ሕዝቧ፣ እንዲሁም ታሪኳና ሃይማኖታዊ ዳራዋ ለቱሪስት ቀዳሚ ተጠቃሽ አፍሪካዊት አገር ነች፡፡ በዩኔስኮ የተመዘገቡ 11 ቅርሶች የያዘች መሆኗም ከአፍሪካ ቀዳሚ ያደርጋታል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገቡትን ብናይ የአክሱም ሐውልቶች፣ የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት፣ የጎንደር አብያተ መንግሥት፣ የሐረር ጀጎል ግንብ፣ የጥያ ትክል ድንጋዮች፣ የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ፣ የኮንሶ ሰው ሠራሽ የመሬት አቀማመጥ፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ፣ ወዘተ. ብሎ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በማይጨበጥ ቅርስነት ደግሞ በቅርቡ ያከበርነው የደመራና የመስቀል በዓል፣ የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፌቼ ጨንበላላ ናቸው፡፡

ሌሎች በምዝገባ ሒደት ላይ ያሉ ቅርሶችም አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የድሬ ሺክ ሁሴን መስጊድ፣ የሶፍ ኡመር ዋሻ፣ የጌዲዮ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ መልክዓ ምድር፣ የመልካ ቁንጡሬ የአርኪዮሎጂ ሥፍራ፣ ከባህላዊ ቅርሶች ደግሞ የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት፣ የትግራይና የአማራ (ሰቆጣ) የአሸራዳ/አሻንዲዬ በዓላት ይገኙበታል፡፡

በዚህ ላይ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛነቷ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዕድሜ ባስቆጠረችው የሉሲ (ድንቅነሽ) አፅም ተረጋግጦላታል፡፡ የአረቢክ ቡና ዝርያ መገኛ የመሆናችን ሚስጥርም ተነግሮ የከረመ ሀቅ ነው፡፡ የዓለም ረጅሙን ወንዝ ዓባይን ጨምሮ ኢትዮጵያን ‹‹የውኃ ጋን›› ያስባሏት በርካታ ወንዞችና ሐይቆች ይገኛሉ፡፡ በዚህ ላይ የታሪክና የሃይማኖት ቅርሶቻችን ተነግረው የማያልቁ ቱባና ዕምቅ ሀብቶች ናቸው፡፡

ይህ ሁሉ ሊጎበኝ የሚገባውና የሚያስደምም ሀብት ያላት አገር ግን በቱሪዝም በአፍሪካ ደረጃ እንኳን ከጎረቤት ኬንያ፣ ኡጋንዳና ታንዛኒያም አንሳ 17ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ነች፡፡ ከዓለም ደግሞ 121ኛ ተርታ ላይ ነው ያለችው፡፡ ኢትዮጵያን የጎበኙ ቱሪስቶችን ስንመለከት ደገሞ በ2004 ዓ.ም. አፍሪካን ከጎበኙ 52.3 ሚሊዮን ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ከ597 ሺሕ የማይበልጡት ናቸው፡፡ ከእነዚህ የአፍሪካ ጎብኚዎች የተገኘው 34 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ ያገኘችው ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር እንደማይበልጥ ራሱ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያረጋገጠው መረጃ ያስገነዝባል፡፡

የተለያዩ ጥረቶች ታክለውበት በ2006 ዓ.ም. እስከ 2.5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገቢ ቢገኝም ዕድገቱ እንደተገመተው ፈጣን መሆን አልቻለም፡፡ በእርግጥ በ2008 ዓ.ም. ክረምት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት በተጠቀሰው ዓመት አንድ ሚሊዮን ጎብኚዎችን ለመሳብ ታቅዶ 900 ሺሕ መምጣታቸውንና 3.4 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገቢ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ወደ አገር ውስጥ እንደገባ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ቢባል በዚያ አገሪቱ ያላትን ዕምቅ ሀብት ያህል የሚያረካ ጎብኚ አላገኘችም፡፡ በተለይ እየተሻሻለ ከመጣው የኢኮኖሚ ዕድገትና ለማሳደግ እየተሞከረ ካለው የገጽታ ግንባታ አንፃር፣ መዲናችን አዲስ አበባ የቱሪዝም ኮንፈረንስ ማዕከል እንደሆነች ከመምጣቷ አኳያ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ ብቻ ሳይሆን፣ በርካታ ወጣቶች በዘርፉ ማሰማራትም ይቀራል፡፡

በእርግጥ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ ሎጆችና የእንግዳ ማረፊያዎች ተገንብተዋል፡፡ አስጎብኚ ድርጅቶችና የተሽከርካሪ አከራዮችና ትራንስፖርተሮችም አሉ፡፡ ያለጥርጥር ለእነዚህ የተፈጠረ ምቹ ሁኔታ አለ፡፡ ከዚህም በላይ ግን በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ከዩኒቨርሲቲዎች እየተመረቁ ‹‹ሥራ አጥ›› ከሚሆኑ በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ ወጣቶች መካከል ከፊሉን እንኳን ዘርፉ መቀበል ይኖርበታል፡፡

በቅርቡ በተካሄደው ዓውደ ጥናት ላይ እንደተገለጸውም በቱሪስት መስህብ ሥፍራዎች አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ ከመስኩ የሚጠበቀውን ያህል ባለመጠቀሙ፣ የቱሪዝም ቅርሶችና መሠረተ ልማቱን እንደ ራሱ ሀብት እየጠበቀ አይደለም፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯም እንደተናገሩት በትልልቅ ፓርኮች፣ ጥብቅ ደኖች፣ ጥንታዊ ቅርሶችና የተፈጥሮ መስህቦች አካባቢ የተጠናከረ የማኅበረሰብ ተኮር የልማት ሥራዎችን ማስፋፋት ካልተቻለ፣ መስህቦችን በቋሚነት መንከባከብም ሆነ ዘርፉን ማሳደግ አዳጋች መሆኑ አይቀርም፡፡

በዚህ ረገድ በአንዳንድ አካባቢዎች የተጀማመሩ ሥራዎች መኖራቸው ባይካድም በላሊበላን፣ በጎንደር (ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መቀዝቀዝ ቢታይም)፣ በአክሱምና የደቡብ ክልል ልዩ ልዩ መስህቦች አቅራቢያ የሚኖሩ ወጣቶች በተደራጀ መንገድ ሥራ አልተፈጠረላቸውም፡፡ በዚህም የአገርን ጥቅም በማስቀደምና በሥነ ምግባር እንግዶችን ማገልገል ላይ የጎላ ችግር እየታየባቸው ነው፡፡

የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በአግባቡ ባለመመራቱ ለሚያጋጥሙ የማኅበራዊ ቀውስ አደጋዎች መጋለጥም እየታየ ነው፡፡ በተለይ ‹‹Sex Tourism›› ለሚባለው የምዕራባዊያኑ ወረርሽኝ የተጋለጡ ለጋ ወጣቶችና የተሻለ ንቃት የሌላቸው ዜጎችን በጥናት ማግኘት ይቻላል፡፡ ልመናና ሌሎች የውርደት ገጽታዎችን ለመመከት የሚቻልበት ግልጽ አሠራርና ትግበራ አለመታየቱንም ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚተቹት፡፡ በድምሩ አገሪቱ ያላትን የታመቀ ሀብትና መስህብ ያህል ቱሪዝሙ ገና በቂ ዳቦ አልተጋገረበትም፡፡

ቱሪዝም መሻሻል ቢያሳይም አልተመነደገም

የአገራችንን የቱሪዝም ሀብት ስፋት በማነፃፀር በቂ ውጤት አልተገኘበትም ብንልም፣ መስኩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ለመካድ ያዳግታል፡፡ በቅርቡ ከተቋቋመው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ጀምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተናጠልና በተቀናጀ መንገድ የሚሠሩት ሥራ ቀስ በቀስ ፍሬ እያመጣ ነው፡፡ አንድ አብነት እንኳን ብንወስድ በ2008 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባከናወነው የቱሪዝም ዲፕሎማሲና የገጽታ ግንባታ ሥራ 104 ዓለም አቀፍ አስጎብኝ ድርጅቶች ኢትዮጵያን የቱሪዝም ፓኬጃቸው ውስጥ ማስገባታቸው ተነግሯል፡፡ ምንም እንኳን የሚጠበቀውን ያህል ጎብኝ መላክ ባይችሉም፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የኢትዮጵያ መገለጫ የሆኑ ሰው ሠራሽ እሴቶቻችንም ብዙዎችን የመሳብ ዕድላቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ በተለይ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ በቅርቡ እንደታየው ያለ መደነቃቀፍ ካልገጠመው ‹‹ድህነትን የማሸነፍ ተምሳሌት›› ሆነን በሌላ ገጽታ መፈለጋችንም አይቀርም፡፡ ልክ የጎረቤት ስደተኞችን በመቀበልና የሰላም ማስከበር ዓለም አቀፍ ተልዕኮ ላይ እንዳለን ስም ማለት ነው፡፡

ያም ሆኖ ለቱሪዝም መስኩ መመንዳና እንደ እንቅፋት የሚወስዱ ተግዳሮቶችን መመርመሩ ተገቢነት ይኖረዋል ብዬ በማመን አንድ በአንድ ለመጠቃቀስ እሞክራለሁ፡፡

  • ዘርፉ በፌዴራል፣ በክልሎች ደረጃም ሆነ በከተማ አስተዳደሮች በሙያው በሠለጠኑ፣ ብቃት ባላቸውና በተወዳዳሪነት እየተመራ አለመሆኑ አንዱ ችግር ነው፡፡ እዚህ ላይ ምንም እንኳን በጥናት ላይ ሳንመሠረት ያሉትን ኃላፊዎች በጅምላ መተቸት ቢያዳግትም፣ በአብዛኛው በ‹‹ፖለቲካ ታማኝነት›› እና በብሔር ውክልና የተቀመጡ ኃላፊዎች ከምሕንድስና፣ ከስፖርት ከመምህርነት፣ ከግብርና ባለሙያነት፣ ወዘተ. የተሰበሰቡ መሆናቸውን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በሚጠይቀው ዘርፍ ውስጥ እንደ ሙሴ ‹‹ባህር ሰንጥቆ›› የማለፍ ብቃትን ቢመኙትም ሊያገኙት አይችሉም ባይ ነኝ፡፡
  • በተመሳሳይ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የተመደቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሙያተኞች ምንም እንኳን የቋንቋ፣ የሥነ ጽሑፍ የባህል (ፎክሎር) ትምህርት ዝግጅት ቢኖራቸውም በሌላው ዓለም ያለው ዓይነት ብቃት እያሳደጉ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በግብፅ በመንግሥት ከተቀጠሩ 1,500 የታሪክ፣ የባህልና የሃይማኖት ሊቅ የሆኑ የቱሪዝም ኤክስፐርቶች ብቻ በአሥር ቢሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ገቢ ይገኛል፡፡ እነዚህ ሙያተኞች በጥናት ላይ በተመሠረተ ዕውቀት፣ በተተነተነና በዳበረ መረጃ የአገራቸውን ገጽታ ለዓለም ያሠራጫሉ፡፡ ጎብኚዎች የሚስተናገዱበት፣ የሚመሩበትና ሀብት የሚያመነጩበት አሠራር ዘርግተው ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ አስጎብኚዎች ተልዕኮአቸውን እንደወሰዱና የአገራቸውን ገጽታ ከፍ እንዲያደርጉ ያነሳሳሉ፡፡
  • የዜጎች አገራዊ ስሜትና ብሔራዊ መግባባት ተጠናክሮ አለመውጣት፡፡ ይህ አባባል ከላይ ከላይ ሲመለከቱት ፖለቲካዊ ይምሰል እንጂ በተለይ ለቱሪዝሙ ዘርፍ ያለው ፋይዳ የሚናቅ አይደለም፡፡ እዚህ ጥሩ አብነት የሚሆነው በራሳችን በአገር ውስጥ ያለው የአገር ውስጥ የጉብኝት ባህል ነው፡፡ ስንቶቻችን ከምንኖርበት ወደ ሌላ አካባቢ ሄደን (የተሻለ ገቢ እንኳን ቢኖር) ለመጎብኘትና ለመደመም እንመኛለን፡፡ ከራሳችን መንደር ወጥተን በሌሎች ክልሎች የሚገኙ ቅርሶችን ማወቅና ማስተዋወቅ ላይስ በምን ደረጃ ላይ እንገኝ ይሆን? የኢትዮጵያን አዲሱን የቱሪዝም መለያ ‹‹ኢትዮጵያ የሁሉ መገኛ ምድር (Ethiopia Land of Origins)›› ከልብ አውቆ ተንትኖ ማብራራት ያልቻለ ምሁርም ይባል ዲፕሎማት ወይም ነጋዴ ወይም ወታደር ሌሎች አገሮች የደረሱበት ለመድረስ ቢመኙ ዋጋ አይኖረውም፡፡
  • ከአገር ሉዓላዊነትና የሕዝብ ደኅንነት ጋር በሚያያዘው ልክ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ማበብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው የሰላምና ደኅንነትም ጉዳይ ሊጤን የሚገባው ነው፡፡ በነገራችን ላይ የሰላም መታወክ ካሳለፍነው ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ ክልል (ኮንሶ አካባቢ) በመታየቱ ብቻ አይደለም የሚገለጠው፡፡ ይልቁንም የአገሪቱ መንግሥት የሚከተለው የአገዛዝ ሥርዓት (ዴሞክራሲያዊነትና ሕዝቡን አሳታፊ መሆኑ) የሚያሳድረው በጎ አስተዋጽኦ አለ፡፡ (ለዚያ ለዚያማ ኤርትራን ወይም ሰሜን ኮሪያን ማን ጓጉቶ ሊጎበኝ ይችላል?) ስለዚህ የሰላም መደፍረስ በጦርነት ውስጥ መሆን ወይም በሽብር በመጠቃት ብቻ አይደለም፡፡ ዝርፊያ፣ ውንብድና የጠባብነትና የዘረኝነት ችግር፣ ቅጥ ያጣ ድህነት፣ የኃይል ዕርምጃ አለመኖርንም ይሻል፡፡ ስለዚህ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በተሟላ ገጽታ ግንባታ ታጅቦ እንዲመነደግ የሰላምና ደኅንነት ብሎም የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ጉዳይ ሊዘነጋ አይችልም፡፡ (በነገራችን ላይ በቅርብ ጊዜው አገራዊ ግጭትና ሁከት እነ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና አንዳንድ አገሮች መግለጫና ማስጠንቀቂያ ማውጣታቸው የመስቀል በዓልን እንኳን የውጭ ቱሪስቶች ጭር እንዲሉበት ሆኗል፡፡)
  • የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ አንዱ አማራጭ ለስብሰባ፣ ለሥልጠናም ሆነ ለጉብኝት የሚመጡ የውጭ ሰዎችን የቆይታ ጊዜ ማራዘም አንዱ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የአፍሪካ የውጭ ጎብኚዎች አማካይ የቆይታ ጊዜ ስድስት ቀናት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አምስት ቀናት እንደሆነ የመስኩ ጥናት ያመለክታል፡፡ ይህን ቢያንስ ወደ ሰባትና ስምንት ቀናት ለማድረስ የተቀናጀ የቱሪዝም አገልግሎትና የጉብኝት ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡ የቱሪስቱን ደኅንነት ለማስጠበቅና የመስኩን ባለሀብቶችም ለማበረታታት መንግሥት የጎላ ሚናውን ሊጫወት ይገባል፡፡ ይህ እንግዲህ ከመሠረተ ልማትና ከማኅበረ ኢኮኖሚው ጉዞ በተደማሪነት የሚታይ ነው፡፡ ለምሳሌ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተሰብሳቢዎች የሚያርፉባቸውና የሚጎበኙዋቸው ድንቃ ድንቅ ሀብቶችን ማስተዋወቅ፣ አመቺ ማድረግና ጎብኚዎችን ማማለል ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት መስክ ነው፡፡ ያም ሆኖ የተነገረለትን ያህል ያልፈካና ተጠቃሚ ያላደረገን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት ብቻውን ከመጣጣር ወጥቶ የአገሪቱ ዜጎች በፖለቲካ፣ በብሔር ወይም በሃይማኖት ሳይለያዩ እንዲሠሩበት የሚያደርግ አብዮት ሊቀሰቅስ ይገባዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ ለአገሪቷ አጠቃላይ ምርት (GDP) እዚህ ግባ የማይባል አስተዋጽኦ ነው ያበረከተው፡፡ ሌሎች አገሮች ግን በውስን መስህብ ተዓምር እየሠሩባት ነው፡፡ ስለዚህ በዕውቀት፣ በጥናትና በብልጠት የታገዘ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ውስጥ መግባት መቻል አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ ቱሪዝማችንን በሚገባ ልንታደገው ይገባል፡፡          

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

Standard (Image)

ይድረስ የኢትዮጵያ ሕዝቦች መጪው ዕጣ ለሚያስጨንቃቸው ሁሉ

$
0
0

በገነት ዓለሙ

      አገራችን ውስጥ ምሬት ኩፍ ብሏል፡፡ ንብረት እስከ ማጥፋት የተቆጣና ገዢውን ክፍል ውረዱልን እስከማለት የደፈረ ተቃውሞ አስገምግሟል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ለህልውናችን አደጋ ነው ብለው፣ ይህንንም ፖሊሲያቸውን የሕዝባቸው ግንዛቤ ያደረጉ፣ የኢትዮጵያን መጠንከር ከሥጋት የሚቆጥሩና ከዚህ ቀደምም የኤርትራን ትግል በማዳከሚያነት ሲጠቀሙት የኖሩ፣ ስለዚህም የኢትዮጵያ መተራመስ ይጠቅመናል ያሉ የውጭ ጠላቶችም ዕጣን በማጫጫስ ላይ ናቸው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥትም ያልተጠበቀ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሕግ አውጇል፡፡ ይህንን ሕግ የተቃወሙ ተቃዋሚዎችም አሉ፡፡ ገዢው ፓርቲ ሕጋዊነቱን (ሌጅተማሲውን) አጥቷል፣ የመተማመን ምርጫ ያካሂድ ያሉም አሉ፡፡

በሌላ ጎን የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ጉባዔ ተቃዋሚዎችና መንግሥት ተቀራርበው እንዲነጋገሩ አደርጋለሁ የሚል ድምፅ አሰምቷል፡፡ የአገር ሽማግሌዎች ስብስብ የአገሪቱ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ጥያቄ ያላቸው ወገኖች፣ ወዘተ የተካተቱበት መወያያ መድረክ እንዲፈጠር አሠራለሁ ማለቱን ሰምተናል፡፡

መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም በተከፈተው የተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ደግሞ፣ ኢሕአዴግ ስላሰባቸው ወይም ስላሰበልን ለውጥ አንዳንድ ጉዳዮች ጠቁመውናል፡፡

‹‹….. አገራችን በምትከተለው የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት በመመራት ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በድምሩ ለአሥር ጊዜ አገራዊ፣ ክልላዊ፣ ከባቢያዊ ምርጫዎች›› መካሄዳቸውን፣

‹‹በእነዚህ ምርጫዎች የብዙ ፓርቲዎች ተሳትፎ የነበረ ሲሆን በተለይ ባለፉት ሁለት ምርጫዎች እንደተከሰተው በምክር ቤቶቻችን፣ የገዢው ፓርቲ ሙሉ የበላይነት ያለበት ሁኔታ …›› መስተዋሉን፡፡

‹‹ይህ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተካሄደ ምርጫ የሕዝብ ድምፅ ያስገኘው ውጤት እንደሆነ ባያጠያይቅም ተቃዋሚዎችን የመረጡ የኅብረተሰብ ድምፆች በመኖራቸውና በአብላጫ ድምፅ ወንበር የማግኘት የምርጫ ሥርዓታችን መሠረት በአገራችን ወሳኙ የሥልጣን አካል በሆነው ምክር ቤት የማይወከሉ ድምጾች እንዲኖሩ›› ማድረጉን ገልጸው፣

‹‹ይህን የመሰለው ሁኔታ ሥርዓታችን ተረጋግቶ እንዲቀጥል ከማድረግ አኳያ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያስከትል በመሆኑ በተቻለ መጠን፣ ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ዴሞክራሲያዊ መድረኮችን በማስፋትና በቀጣዩ ምርጫም በሕግ ማዕቀፍ በተደገፈ አኳኃን የሕዝብ ምክር ቤቶች የተለያዩ ድምፆች የሚሰሙባቸውና የሚፎካከሩባቸው መድረኮች እንዲሆኑ በማድረግ መስተካከል ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

      በአጠቃላይ የአብላጫ ድምፅ መመዘኛው የተበለጡትን ከውክልና ውጪ ስለሚያደርግ፣ ይህንን እንከን ለማረም ሕግ ተሻሽሎ በድምፅ የተበለጡም ውክልና የሚያገኙበት ዕድል በመጪው ምርጫ ይኖራል ተብሏል፡፡ ሲቪክ ማኅበራትንም ስለማካተት የታሰበው ነገር ተነግሮናል፡፡ የሕግ አስፈጻሚው አካል ማለትም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም ካቢኔው እንደገና እንደሚደራጅም ተገልጾልናል፡፡ በምርጫ ወደ መወከል በሚያደርሰው ምኅዳርና ተቋማዊ አስተናባሪነት ላይ ስላለው ወሳኝ ችግር ምንም አልተነገረንም፡፡

ምክር ቤታዊ ውክልናን የማስፋት መፍትሔ ዴሞክራሲን ለማጥለቅም ሆነ ገዢውን ፓርቲና ተቃዋሚዎቹን ለማቀራረብ በእርግጥ በቂ ነው ወይ? ቁጣን ወደ እርቅ ለውጦ በዴሞክራሲያዊ ሰላም ወደፊት የመራመድ ተግባር በአሁኑ ጊዜ የደቀነው ዝቅተኛው ወይም መነሻ የጋራ መገናኛ ምንድነው? በእኔ በኩል የሚከተለው ይታየኛል፡፡

የአገሪቱ ፓርቲዎች ተገናኝተው በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን በአግባቡ የማቋቋም ተግባርን የጋራ አደራቸው አድርገው መግባባታቸው፣ ለዚህም የሚሆን መርሐ ግብር መንደፋቸውና አጠቃላይ የእርቅ መንፈስን ማወጃቸው ቁልፍ መነሻ ነው፡፡ እዚህ መነሻ ላይ በመቆም፣

ሀ) • ‹‹የሕዝብ ፀር›› ‹‹የጥፋት መልዕክተኛ››፣ ‹‹ዘረኛ››፣ ወዘተ ከሚሉ መፈራረጅ የመራቅና፣ ፍረጃዎችን ከመገናኛ ብዙኃን መድረክ የማስወገድ ስምምነት ማድረግ፣

  • ከመጠማመድና ከጥላቻ በፀዳ መንፈስ ለአገሪቱና ለሕዝቦችዋ ግስጋሴና ሰላም ሊሠሩ የሚፈልጉ በትጥቅ ትግልም ሆነ ከትጥቅ ትግል ውጪ ያሉ የፖለቲካ ቡድኖች ወደ እርቅ እንዲመጡ መጋበዝ፣
  • በአገር ውስጥም በእስር ላይ ያሉ በፖለቲካ ወንጀል ታስረዋል የሚባሉ ሰዎችን መፍታት፣
  • በአጠቃላይ በፓርቲዎችም ሆነ በማኅበረሰቦች ግንኙነት ውስጥ ያሉ ጥርጣሬን፣ ፍራቻን፣ ሥጋትን፣ መሸካከርን የሚፈረካክሱና የሚያጥቡ በነፃ ተሳትፎ የደመቁ እንቅስቃሴዎች ማካሄድ፣
  • የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ሥራ አስፈጻሚዎች የሕዝብ ከበሬታና ተሰሚነት አግኝተው፣ የኢኮኖሚና የዴሞክራሲ መርሐ ግብሮችን ለማሳካት እንዲችሉ ለሕዝብ ጥቆማ ቦታ በሰጠ ሁኔታ በሕዝብ ዘንድ የታመነባቸውን (ከተቃዋሚም ከፓርቲ ፖለቲካ ውጪ ከሆኑም ውስጥ) እንዲያካትት ማድረግ፣
  • ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች የሚገናኙበት በሩ ለአዲስ መጪዎች ያልተዘጋ በዴሞክራሲ የእርቅ መቃናት ላይ የሚሠራ የመገናኛ ብዙኃን የአየር ጊዜም፣ የተሰጠው መድረክ ማቋቋም፣

ለ) • ሐሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብና በሰላም የመቃወም መብቶች ላይ ከሕግ ውጪ የሚደረግን የሹም አፈና በፈጣን ተጠያቂነት መከላከል ጥያቄዎችና ቅሬታዎች በውይይት በድርድርና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ከሚስተናገዱ በቀር በወንጀልና በጉልበት እንዳይደፈጠጡ ነቅቶ በመጠበቅና ይህንኑ በደል በመፋረድ ላይ መስማማት፣ ይህንንም የሕዝብ ግንዛቤ ማድረግ፣

  • ከዴሞክራሲ መብቶች ተከባሪነት ጎን፣ የአደባባይ ሠልፎችንና ስብሰባዎችን በሰውና በንብረት ላይ ጥቃት መፈጸሚያ መሣሪያ ማድረግ ነውረኛ ተግባር መሆኑንና በሕግ የመጠየቁን ተገቢነት ሕዝብ ከልብ እንዲቀበለው ማድረግ፣
  • ለዴሞክራሲያዊ የሕዝብ መነቃቃት የማይበጁ ድንጋጌዎችን የመሰረዝ፣ የማሻሻል ወይም አዲስ በማውጣት የመተካት ሥራ ማካሄድ፣ በተለይም ከሁሉም በላይ ደግሞ ዝሆን የማይጥሰው ጫካ የወረሰውንና ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሚገኘውን የፀጥታ ኃይሎች የ‹‹ኃይል አጠቃቀም›› ሥርዓት እንደገና መመርመር፣ መልሶ መላልሶ መፈተሽና በዝርዝርና በነቂስ አፍታትቶ መደንገግ (በዚህ ውስጥ በተቃውሞ ትዕይንት ውስጥ የውኃ ግፊት፣ አስለቃሽ ጪስ፣ ቆመጥና አፈሳ ማካሄድን አግባብ የሚያደርጉ ከዚህም አልፎ በሰው ላይ እውነተኛ ጥይት መተኮስን የሚፈቅዱ ፀጥታ የማስከበር ሁኔታዎችን በሕግ አፍታትቶ መወሰን፣ ተጠያቂነትን ማበጀትና ሳይጠየቁ መቅረትን መዋጋት፣
  • በነፃ መደራጀትንና ነፃ ንቁ ተሳትፎን ማነቃቃት፣ እንዲሁም በሚዛናዊነት መከራከርን፣ መተንተንና መዘገብን ማጎልመስ ከዚሁ ጋር የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን ከገዢው ፓርቲ ልሳንነት አውጥቶ የኅብረተሰቡ ልሳንና መገልገያ ማድረግ፣
  • አወዛጋቢ የአከላለል ችግሮች በደንብ ተብላልተው፣ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታና አንጀት አግኝተው እንዲፈቱ መሥራት፣
  • የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትን፣ የፌዴራል አወቃቀሩንና ሰንደቅ ዓላማውን ጭምር የአንድ ፓርቲ ሥራ አድርጎ እስከመቁጠር የሄደ የመግባባት ችግር ስላለ፣ ይህንን ለመዝጋት አገር (ኅብረተሰቡ) እንዳለም ሆነ አሻሽሎ በቀጥተኛ ድምፁ የራሱ የሚያደርግበትን ተግባር ለወደፊት ቀይሶ ለዚሁ የሚረዱ ግምገማዎችና ጥናቶች እንዲካሄዱ ማድረግ፣
  • የአገሪቷ ሕዝቦች የጋራ ታሪክ ተጣርቶ የሕዝብ ንቃት ለመሆን መቻል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጥበቅ ያለው ጠቀሜታ ከወዲሁ ታውቆ፣ ያለፖለቲካዊ ወገናዊነት የአገሪቱን ሕዝቦች ታሪክ መርምሮና አደራጅቶ የሚያቀርብ ግብረ ኃይል ማቋቋም፣

ሐ) • መራራ ስሜቶች ሟሽሸው፣ እርቃዊ ስሜት እየተቃና በመጣበት ደረጃ ላይ በገለልተኝነታቸውና ለሥራ አደራቸው በመታመን ጥንካሬያቸው በተመረጡ አባላት የተሞላ የምርጫ አስፈጻሚ አውታር ከላይ እስከ ታች ማደራጀትና ሕዝብ አመኔታ የነፈጋቸው የምክር ቤቶች አባላት (በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ) ቢኖሩ የማሟያ ምርጫ ማካሄድ፣

  • የአገሪቱ የመከላከያ፣ የመረጃና ደኅንነት፣ የዳኝነት፣ የፖሊስና የዓቃብያነ ሕግ አውታራት፣ የዋናው ኦዲተር፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽን በፖለቲካዊ ወገናዊነትም ሆነ በንቅዘት ሳይሰናከሉ ለአደራቸው በመታመን ላይ እንዲተጉ መሥራት፣
  • ምርጫን ነፃና ፍትሐዊ ለማድረግ በሚደረግ ዝግጅት ውስጥ ምርጫ የሞት ሽረትና የዝርፊያ ግብግብ ወደ መሆን ወርዶ ገና ያልጠናውን (ይልቁንም ያልለየለትን) የዴሞክራሲ ግንባታ እንዳይጎዳ የመጠበቅና የማጎልመስ ተግባር፣ አጠቃላይ ኅብረተሰቡንና ሁሉንም አካባቢዎች ያደረሰ ልማትን የማፋጠኑ ተልእኮ ገና የሁሉንም ፓርቲዎች ርብርብ የሚሻ መሆኑን ያስተዋለ የጋራ መርሐ ግብር መንደፍ፣
  • የሰብዓዊ መብት ተቋማት በየትም ሥፍራ ተንቀሳቅሰውና ቅርንጫፋቸውን አስፋፍተው የገመና መስታወት እንዲሆኑ ክልከላዎችን፣ ገደቦችንና መሰናክሎችን ማንሳትና ነፃነታቸውን ማስፋት፣
  • የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎቻቸው የተቃውሞም ሆነ ሥልጣን ላይ ያለ ፖለቲካ አጫፋሪ ከመሆን የሚርቁበት መንግሥትና ቡድኖችም ቤተ እምነቶችን መሣሪያ ለማድረግ ከመታከክ የሚቆጠቡበትን የተግባር ጨዋነት ማጎልበት፣

መ) • መንግሥታዊ የሕዝብ አገልግሎት አውታራት እንደ ተቋም ከፖለቲካ ወገናዊነት ነፃ ይሁኑ ማለት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ የፖርቲዎች የምልመላ መሻሚያ ሜዳ መሆናቸውም በሥራ ላይ ጉዳት አድርሷልና ሠራተኛን ሁሉ አባል እያደረጉ የመንግሥት መሥሪያ ቤትን ወደ ፓርቲነት ከመቀየር ይልቅ፣ ህሊናን በመርታት ላይ መሥራት ለሁሉም የሚበጅ መሆኑ ላይ መግባባት፣

  • የሥልጣንና የፍትሕ ምሰሶ በሆኑ ተቋማት ውስጥ የተሰማሩ፣ ማለትም በቀጥታ የፓርቲ አባል መሆን የማይችሉ ሠራተኞችም ፓርቲ ከመቃወምና ከመደገፍ መብታቸው በገዛ ውዴታቸው ተቆጥበው ወደ ገለልተኛነት ማዘንበላቸው፣ ለዴሞክራሲና ለእኩል አስተዳደር መጠናከር ትልቅና የቅርብ ጠቀሜታ እንዳለው እንዲረዱ መሥራት፣
  • በሕዝብ አገልግሎት ውስጥ የሥራ ኃላፊነትንና ተገልጋይን አክብሮ በቅልጥፍናና በጨዋነት ሥራን የማከናወን ትጋት ከጊዜያዊ መነቃቃት ያለፈ ወረትን የተሻገረ ባህርይ ውስጥ የገባ ምግባር ሆኖ እንዲዘልቅ፣ የሥራ ስሜትን ለማደስ የሚያስችሉ ሥርዓቶችን ዘርግቶ መረባረብ፣
  • የቴሌ ልዩ ልዩ የግንኙነት አገልግሎቶችን፣ የሥራ አስፈጻሚው አካል ባሻው ጊዜ እንዳያቋርጥና የሰብዓዊ መብትን ለመጣስ እንዳያውላቸው ለመከታተልና ለመጠየቅ የሚያስችል የአወቃቀርና የሕግ  መጠበቂያ ማበጀት፣
  • በመሬት ይዞታ ሥርዓቱ ላይ አስፈጻሚው የመንግሥት አካልና ቅርንጫፎቹ የመሬት አገናኝነትን እንዳሻቸው እንዳያዙበት (መሬት የመንግሥታዊና የግል ነቀዞች መቀራመቻ እንዳይሆን) የሚያስችል የአወቃቀር፣ የግልጽ አሠራርና ከሕዝብ ዓይን ውስጥ የማስገባት ማሻሻያ ማድረግ እንዲሁም መሬቶችን ለታወቁ ዓላማዎች የተመደቡና የማይነኩ ጥብቅ ብሎ መለየትና በዚያ ውስጥ ተወስኖ መሥራትን ተግባራዊ ማድረግ፣
  • በእነዚህ ተግባሮች ላይ ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች ከሞላ ጎደል መገናኘት ከቻሉ በወጣት የተሞላው ኅብረተሰባችን እነዚህን ተግባሮች ማትኮሪያ፣ ፍላጎቶቹና ጥያቄዎቹ ካደረጋቸው የአገራችንና የሕዝቦቿ ዕጣ ብሩህ እንደሚሆን ተስፋችንም ምኞታችንም ነው፡፡

የተስፋችንና የምኞታችን ተጨባጭነት ‹‹ሀ›› ብሎ የሚጀምረው የኢትዮጵያ ችግሮች በአንድ ፓርቲ ገዢነትና መንከውከው ወይም መፍጨርጨር ብቻ ወይም በማማረር ወይም በጠመንጃ ኃይል እንደማይቃለሉ ከማወቅ ነው፡፡ እስካሁን በ25 ዓመታት ውስጥ ኢሕአዴግ ብቻውን ዴሞክራሲን በመገንባት በኩል ያደረገው ጥረት ወይም አደረግሁት ያለው ጥረት ለራሱምና በራሱም መለኪያ እንኳን የሚፈልገውንና የሚፈለገውን ያህል ውጤት አላስገኘም፡፡ የጠላትነት ፖለቲካ ሕዝብ ድረስ ዘልቆ ማወኩ እየሰፋና እየከፋ እንጂ እየቀነሰ አለመምጣቱንና ሐሳብን በመግለጽ በኩል የነበረው ውስን ነፃነት በድኅረ 1997 ዓ.ም ምርጫ ወደኋላ መመለሱ የዚህ ምስክር ነው፡፡ አንዱ ማስረጃ ነው፡፡

በጥላቻና በፍጥጫ መስክ ላይ ዴሞክራሲ ሊገነባ አይችልም፡፡፡ ኢሕአዴግ ከሥልጣን ከወረደ ወይም አንድ ወይም ሌላ ፓርቲ ሥልጣን ላይ ከወጣ አገሪቷ ትበታተናለች፣ የብሔር ብሔረሰቦች መጨፋጨፍ ይመጣል የሚል ፍርኃትና እምነት ይዞ የሚታመስ አገር ዴሞክራሲን ሊገነባ አይችልም፡፡ እነዚህን ፍራቻዎች፣ ጥርጣሬዎችና ጥላቻዎች እንዲጠናከሩ የሚሹም ዴሞክራሲን በጭራሽ ሊያጎለብቱ አይችሉም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ኃይሎች በለየለት ጠላትነት ውስጥ ተጠማምደውም ሆነ ላይ ላዩን እየተሳሳቁ የሚገኙበት አጥፊ ሁኔታ መቀየር አለበት፡፡ ከ1997 ዓ.ም የምርጫ ጊዜ ጀምሮ በተለይም በዚያ ጊዜ አካባቢ ይባል እንደነበረው የገዢው ፓርቲና የተቃዋሚ አብሮ መሥራት ዛሬም ሲበዛ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ አብሮነት በሥልጣን ላይ ቢገለጽም ጥሩ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አብሮ የመሥራት ቅድመ ሁኔታ ሊሆን አይገባም፡፡

በአሁኑ ወቅት ከልዩነት ጋር ተቻችሎ አብሮ የመሥራቱ ሒደት ከአንድ ትልቅ ኮንፍረንስ ተነስቶ ዓላማው የሰፋ የፓርቲዎች የጋራ መድረክ በመፍጠር፣ በአገሪቱ ልዩ ልዩ ችግሮች ላይ በመመካከርና በመተጋገዝ ሊጀምር ይችላል፡፡ ፓርቲዎች የገዛ ራሳቸውን ነፃ ህልውና ይዘውና በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲያቸውም አብበው መቆም ያለባቸው መሆኑ ሳይረሳና ሳይድበሰበስ፣ ፓርቲዎች ቅርበታቸውንና የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን እያሻሻሉና ከሕዝቦች ጋር እየተጣጣሙ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ብዙ ተግባር ሊያከናውኑ ይችላሉ፡፡ የሚቀጥለውን ምርጫም ሆያ ሆዬው፣ ቱልቱላውና ክብረ በዓላዊ ባህርይው ያሰለቸ ግርግርና የበጀት ጥፋት ከመሆን አትርፈው እርስ በርስ ተባብረው የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታውን ለማሳካት የሚጓዙበትና የመላውን ሕዝብ ይሁንታ ያገኘ ርብርብ መክፈቻ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ የሚቀጥለው ምርጫ ማለት ከሕገ መንግሥቱ ውጪ መሆን ወይም ሕገ መንግሥቱን ማከምም ሆነ መዝለል ሳያስፈልግ ከ2012 ዓ.ም በፊት ማድረግም ይቻላል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 60 ተፈጻሚነት ይህንን ይፈቅዳል፡፡

ወደዚህ የ2012 ዓ.ም ምርጫም በሰላም ለመድረስና ከዚያም በፊት ሊኖር ስለሚችል ምርጫ ለማውራት የፖለቲካ ኃይሎች አብሮ መሥራት መጀመር የሚያስገድደው፣ በአገሪቱ ላይ ያንዣበበውን ማንም ወገን ለብቻው በአሸናፊነት የማይወጣበትን አደጋ መገንዘብ አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች የግድ አብሮ መሥራት አለባቸው፡፡ አብሮ በመሥራት የጨዋታው ሕግ ላይም መስማማት ይገባቸዋል፣ ማፈርም የለባቸውም፡፡

የፖለቲካ ኃይሎች አብሮ መሥራት ከጀመሩ ፀረ ዴሞክራሲያዊና አድሏዊ የሆኑ ችግሮችንና መሰናክሎችን ማቃለል አያስቸግርም፡፡ የአንድ ፓርቲ ባህርይ በራሱ የውስጥ ማንነት ብቻ ሳይሆን በተቀናቃኙም ባህርይ የሚወሰን ነውና በጎ ግንኙነት የሁለት ወገን የጠባይ መሻሻልን ማስከተሉ አይቀርም፡፡ በብሔራዊ መግባባት ውስጥ እየተለያዩና እየተከራከሩ፣  እየተቻቹና እየተራረሙ ሕዝቦች በስሜት የሚሳተፉበት የዴሞክራሲ፣ የፍትሕና የኢኮኖሚ ጉልህ ዕርምጃ ሊያቀጣጥሉ እንደሚችሉ አያጠራጥርም፡፡ የዚህ ምክንያት በሕዝቦች ውስጥ ሲታዩ የቆዩት የመሸካከር፣ የመፈራራት፣ የመጠራጠርና የዝምታ ገጽታዎች ዞሮ ዞሮ ከፖለቲካ ቡድኖች የሚመነጩ ነበሩና፣ የፖለቲካ ኃይሎች አብሮ መሥራት በቀጥታ የብሔር ብሔረሰቦችንና የሕዝቦችን መተማመን ይዞ ይመጣል፡፡ ሌሎች ጥቅሞችም አሉ፡፡ ለምሳሌ፣

  • የመንግሥት ከግጭቶችና ከሁከቶች ጋር መተናነቅ ይመነምናል ተቃውሞን ለመከላከል የሚውለው የገንዘብ፣ የጉልበት፣ የጊዜ አቅም አቅጣጫውን ቀይሮ በተሃድሶና በለውጥ ላይ ያተኩራል፡፡ ከዚህ አይነት የመንግሥት ወጪ ጋር ተያይዞ ከሚመጣ የዋጋ ግሽበት ለመዳን ይቻላል፡፡
  • በትምህርት ጥራት ውድቀት በወጣት አጥፊነት ለዕፅ ተገዢነት፣ በኤድስ ሥርጭት ላይ ፈጣን መዳከም የሚያስከትል ለውጥ ስሜት ይቀጣጠላል፣ ወዘተ…

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

Standard (Image)

የአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ዳሰሳ

$
0
0

በጎንደር ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት

የአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ልክ እንደ ኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 341/1995 የተቋቋመ ሲሆን፣ በተመሠረተበት በ1999 ዓ.ም. ወቅት 13 የከተማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችና አንድ የክልል ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን በአባልነት ይዞ የተመሠረተ ነበር፡፡

ዓላማውም በክልሉ ውስጥ ያሉ ሕጋዊ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትን መብትና ጥቅም ማስከበር፣ ግዴታቸውን ማስረዳት፣ አቅማቸውን ማጠናከር፣ ንግድ ነክ አዋጆችን ደንቦችንና መመርያዎችን እንዲያውቁ ማገዝ፣ የተለያዩ ሥልጠናዎችን መስጠት፣ ችግሮች ሲከሰቱ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመወያየት መፍትሔ ማፈላለግ፣ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትና ባዛሮችን በማካሄድ የክልሉን የኢንቨስትመንት አማራጮች ማስተዋወቅና የገበያ ትስስር መፍጠር ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ምክር ቤቱ ከተቋቋመበት ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2004 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ያሉት የከተማ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባላት ቁጥር ከ28 የማይበልጥና አባላቱም 14 ሺሕ ብቻ የነበሩ ሲሆን፣ የክልሉ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ከወረዳና ከከተማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ጋር ባደረገው ጠንካራ የቅንጅት ሥራ የከተማና ወረዳ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባላት ወረዳዎችን ቁጥር 167፣ ነጋዴዎችን ደግሞ ከ240 ሺሕ በላይ ማድረስ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባል ከሆኑት ማኅበራት አንዱ የሆነው የአማራ ክልል የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከተቋቋመበት ጀምሮ ስድስት ጠቅላላ ጉባዔዎች ያካሄደ ሲሆን፣ በመጀመርያው ጠቅላላ ጉባዔ አቶ ይርጋለም አድማሱን በፕሬዚዳንትነት እንዲሁም አቶ ጌታቸው አየነውን በምክትል ፕሬዚዳንትነት መርጦ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በተካሄዱት ከሁለተኛው ጠቅላላ ጉባዔ እስከ ስድስተኛው ጠቅላላ ጉባዔ አምስት ጠቅላላ ጉባዔዎች አቶ ጌታቸው አየነው በፕሬዚዳንትነት የተመረጡ ሲሆን፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች በአምስቱ ጠቅላላ ጉባዔዎች ከክልሉ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የሚወከሉ የተለያዩ አምስት ግለሰቦች ተመርጠዋል፡፡

በዚህ ጽሑፍ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ አቫንቲ ሆቴል የተከናወነውን ስድስተኛውን ጠቅላላ ጉባዔና የስብሰባውንና የምርጫውን ክስተት ይተነትናል፡፡ ስብሰባው ሲጀመር ፕሬዚዳንቱ አቶ ጌታቸው አየነው የጠቅላላ ጉባዔ ወንበር ብዛት 200 መሆኑንና በአጠቃላይ 167 የከተማና የወረዳ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች፣ እንዲሁም አንድ ክልላዊ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በአባልነት መኖሩን ጠቅሰው ለእያንዳንዱ አባል ምክር ቤት አንድ አንድ ወንበር የተሰጠ ሲሆን፣ ከ3,500 አባላት በላይ ያላቸው አባል ምክር ቤቶች እንደ ቁጥራቸው ተጨማሪ ወንበር እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ጥሪ ከተደረገላቸው 200 የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ውስጥ 106 አባላት በቦታው መገኘታቸውንና ከግማሽ በላይ መሆኑን በማረጋገጥ ጠቅላላ ጉባዔው መቀጠል እንደሚችል ተናገሩ፡፡

በክብር እንግድነት የተገኙት አቶ ተዋቸው የአማራ ክልል ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ በተጋባዥነት አቶ ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር የኢትዮጵያ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና አቶ አበባው መኮንን የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ተገኝተዋል፡፡

የ2007 ዓ.ም. እና የ2008 ዓ.ም. የሥራ ክንውን ሪፖርት በፕሬዚዳንቱ ሲቀርብ  አበረታች ተግባራት፣ ከአባላት ጋር ያለ የግንኙነት መረብ፣ ስለ ምክክር መድረክ፣ ስለቢዝነስ ዳይሬክተሪ፣ ንግድ ትርዒትና ባዛር፣ የጽሕፈት ቤት ግንባታ ቦታ ጉዳይ፣ በገቢና በወጪ እንዲሁም በመሳሰሉት ዝርዝር ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፣ ያጋጠሙ ችግሮችም ተዳሰውበታል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሪፖርታቸውን አጠናቀው ወደ ውይይት ከመግባት አስቀድሞ እንግዶቹ አቶ ተዋቸው፣ አቶ ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔርና አቶ አበባው መኮንን አስቸኳይ ሥራ እንዳለባቸው ተገልጾ የስብሰባ አዳራሹን ለቀው ሲሄዱ የጠቅላላ ጉባዔውም አባላት ተነስተው በክብር ሸኝተዋቸዋል፡፡ አመቻች ኮሚቴ ተሳታፊው የተለያዩ ሐሳቦችን ካቀረበ በኋላ ከተሰናባች ቦርድ አባል የሆኑ ሦስቱ ማለትም አቶ አሰፋ አላምረው ሰብሳቢ፣ አቶ ደመላሽና አቶ አማረ ሰለሞን አባላት ሆነው መድረክ ላይ ተሰየሙ፡፡ አመቻች ኮሚቴው የምርጫ ሕጎችን በማፅደቅ ሦስት አስመራጭ ኮሚቴዎችን በማስመረጥ መድረኩን ለአስመራጭ ኮሚቴዎች በማስረከብ አመቻች ኮሚቴው መድረኩን ሲለቅ አስመራጭ ኮሚቴው መድረክ ላይ በመውጣት ምርጫው ተከናወነ፡፡

ትዝብቶች

  1.  የአመቻች ኮሚቴ ሰብሳቢ አስመራጭ ኮሚቴ ለማስመረጥ ዕድል ሲሰጡ ሁለቱን ዕድል ከተሰናባች የቦርድ አባላት የሰጡ ሲሆን፣ አንዱን ደግሞ ለባህር ዳር ዘርፍ ቦርድ ተወካይ በመስጠት ገና ከጅምሩ የምርጫው ፍትሐዊነት ጥያቄ ውስጥ መግባት ጀመረ፡፡ የጉባዔው ተሳታፊዎች ጉዳዩን ቢቃወሙም ንግግራቸው የጆሮ ቀለብ ከመሆን አልዘለለም፡፡
  2. የምርጫ አመቻች ኮሚቴ ሰብሳቢ የፕሬዚዳንቱን ምርጫ በተመለከተ ለውይይት አቅርቦ ሲያፀድቅ ለፕሬዚደንትነት ሦስት ዕጩዎች እንደሚቀርቡና የወደቁት ሁለቱ ዕጩዎች ያለውድድር በቀጥታ የቦርድ አባል እንዲሆኑ በማፀደቅ የምርጫውን አቅጣጫ አስቀድሞ ለታለመለት ሰው እንደተዘጋጀ ያሳብቅ ነበር፡፡
  3. አስመራጭ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት ለማስጠቆም በሰጠው ዕድል አመቻች ኮሚቴው የሠራውን ሥራ በመድገም የባህር ዳር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ተወካይ ፕሬዚዳንት የአመቻች ኮሚቴ ሰብሳቢውን አቶ አሰፋ አላምረውን ሲጠቁም፣ የተሰናባች የቦርድ አባል የሆኑት ደግሞ አቶ ጌታቸው አየነውን ጥቆማ ሲሰጡ፣ የደሴ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ታምራት ደግሞ ከደሴ ተጠቁመዋል፡፡ በዚህ ዕድል የመስጠት ሥርዓት በርካታ ሰዎች እጃቸውን ያወጡ ቢሆንም የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢው ከወልድያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የመጡት አስቀድሞ ለማን ዕድል መስጠት እንዳለበት ተወስኖ የተሰጣቸው መሆኑን በሚያሳብቅባቸው ሁኔታ ለእነዚህ ሦስት ሰዎች ብቻ ዕድሉን በመስጠት ተልዕኳቸውን በአግባቡ መወጣት ችለዋል፡፡
  4. ለፕሬዚዳንትነት የተወዳደሩት አቶ አሰፋ አላምረውና አቶ ታምራት ራሳቸውን እንዲገልጹ ዕድል ተሰጥቷቸው መድረክ ላይ ሲወጡ ሁለቱም በተመሳሳይ ቃል በፕሬዚዳንትነት መምራት እንደማይችሉ፣ ከእነሱ ይልቅ አቶ ጌታቸው አየነው በፕሬዚዳንትነት ለአሥረኛ ዓመት ቢቀጥሉ ደስተኛ እንደሚሆኑ በመግለጽ ሜዳውን ለአቶ ጌታቸው ብቻ በማመቻቸት ብቻቸውን ተወዳድረው ለእሳቸው ብቻ ቦታው እንዲሰጥ ቃላቸውን ሲሰጡ ሁለቱ ተወዳዳሪዎች ግን ሚዜ በመሆን የቦርድ አባልነታቸውን ብቻ ማረጋገጥ እንደሚፈልጉ ገለጹ፡፡ ይህም በተራ ቁጥር ሁለት ያነሳነው የዕጩዎቹ ጉዳይ ለምን እንደዚያ እንደሆነ የበለጠ ግልጽ እየሆነ መጣ፡፡

      ለፕሬዚዳንትነት የተወዳደረ ዕጩ ተወዳዳሪ ከቦርድ አባልነት ዕጩነት ውጪ ይደረግ ቢባል ኖሮ ሁለቱ ለውድድር አይቀርቡም ነበር፡፡ ለፕሬዚዳንትነት ዕጩ በመሆን ለውድድር በመቅረብ ነገር ግን የቦርድ አባል ብቻ መሆን እንደሚፈልጉ ከመግለጽ ባሻገር፣ ሌላ ተወዳዳሪ ከአቶ ጌታቸው ጋር እንዳይወዳደር በማድረግ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደሚባለው ሆኖ ጉዳዩ የተበላ ዕቁብ እንደሆነ አብዛኛው የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ተገነዘቡ፡፡

  1. አስመራጭ ኮሚቴው የቦርድ አባላትን ለማስመረጥ ባደረገው የጥቆማ ሥነ ሥርዓት አሁንም ተደጋጋሚ ዕድሎች ለነባሩ የቦርድ አመራሮች በመስጠት አብዛኛዎቹ የቦርድ አመራሮች በድጋሚ ተመርጠው የምርጫው ድራማ ተጠናቋል፡፡ አንድ አረጋዊ የጠቅላላ ጉባዔው አባል ሁኔታውን ታዝበው ስለአካሄዱ በጠቅላላ ጉባዔው ፊት ሲናገሩ እንዲህ አሉ፡፡ ‹‹እኔ እንግዳ ነኝ፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉባዔ ስሳተፍ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ሁላችሁንም አላውቃችሁም፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ መድረክ ላይ የነበረው ከታች ያለውን ዕድል ይሰጥና ከታች ያለው ከላይ ይወጣል፡፡ ከላይ የወጣው ደግሞ መልሶ ለዚያው ሰው ዕድል ይሰጣል፡፡ በተደጋጋሚ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ዕድሉ ተሰጠ፡፡ ይህ ከሆነ ያንን ያህል ኪሎ ሜትር አቋርጠን ከወረዳችን ለምን መጣን? ተመራጩ እየታወቀ ለምን ታደክሙናላችሁ?›› በማለት በአረጋዊነት የንግግር ለዛ ሲናገሩ ሁሉም በፈገግታና በአግራሞት አዳምጧቸዋል፡፡
  2. የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት የሆኑት ሦስቱ መድረክ ላይ ሆነው በተደጋጋሚ ባደረጉት ተመሳሳይ ንግግር የቦርድ ሥራ ለመሥራት ራቅ ካሉ ከተሞችና ወረዳዎች ከሆኑ የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን ስለማይመች፣ ጥቆማ ሲሰጥ ከቅርብ ያሉት ሰዎች ቢጠቆሙ ይመረጣል በማለት የአስመራጭ ኮሚቴ ማልያን ለብሰው ለማን ክለብ እንደሚጫወቱ አስቀድመው ከማስታወቃቸው ባሻገር የምርጫውን ሱሪ ሊመረጡ አስቀድመው በወሰኗቸው ሰዎች ልክ መስፋት ጀመሩ፡፡

ይህንን ሐሳብ ሦስቱም አስመራጭ ኮሚቴዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ አንድ አስተያየት ሰጪ አካሄዱን በመንቀፍ፣ ‹‹እናንተ ምርጫ እንድታስፈጽሙ እንጂ መራጩን አቅጣጫ እንድታስይዙ አልተመረጣችሁም፤›› በማለት ቢነግራቸውም አስቀድመው የተዘጋጁበትን ተግባራዊ ለማድረግ ቆርጠው የተነሱ በመሆናቸው አብዛኛዎቹ ነባር አመራሮች እንዲቀጥሉ ሆነዋል፡፡ የጎንደር የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ለቦርድ አመራርነት ቢጠቆሙም በምርጫው ፍትሐዊነት ስለማናምንበት መመረጥ አልፈልግም በማለት ከሌሎች የጎንደር የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባላት ጋር በመሆን ስብሰባውን ረግጠው ወጥተዋል፡፡

  1. ጠቅላላ ጉባዔው ከመካሄዱ ሁለት ቀናት አስቀድሞ በዕለተ ዓርብ መስከረም 27 ቀን 2009 ዓ.ም. የክልሉ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባካሄደው የቦርድ ስብሰባ፣ የወቅቱን ሁኔታ እንደ ምክንያት በማድረግ ጋዜጠኛ በጠቅላላ ጉባዔ ተሳታፊ እንዳይሆንና ምንም ዓይነት ሪፖርት ወደ ውጪ እንዳይወጣ አስቀድሞ የመከላከል ሥራ ተሠርቷል፡፡ ይኼም የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማኅበራትና የአገር አቀፍ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ምርጫን በተመለከተ በመገናኛ ብዙኃን በስፋት መገለጹ፣ በአማራ ክልል የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ስድስተኛ ጠቅላላ ጉባዔም እንዳይደገም የተሠራ ሥራ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
  2. ይህ ጠቅላላ ጉባዔ በሚከናወንበት ወቅት የምርጫውን ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ በታዛቢነት መገኘት ያለባቸው የክልሉ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ እንዲሁም የእናት ማኅበሩ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተወካዮች መገኘት የነበረባቸው ቢሆንም፣ ምርጫው ሲካሄድ ምንም ዓይነት ታዛቢና ዕርምት ሰጪ በሌለበት በየጊዜው የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱን ምርጫ ወደፈለጉት አቅጣጫ በመውሰድ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ቡድኖች በአብዛኛው እንግዳና አዲስ የሆኑትን ከከተሞችና ወረዳዎች የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የመጡትን የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ባስገረመ መልኩ ያለታዛቢ ምርጫው ተከናውኗል፡፡
  3.  ጠቅላላ ጉባዔው የተካሄደው ዕለተ እሑድ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲሆን፣ አንድም አባል ምክር ቤት ለጠቅላላ ጉባዔ የጥሪ ደብዳቤ አልደረሰውም፡፡ ለሁሉም አባል ምክር ቤቶች ጥሪ የተላለፈው በስልክ ሲሆን፣ የስልክ መልዕክቱም መተላለፍ የተጀመረው ከአምስት ቀናት በፊት ከመስከረም 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዓርብ መስከረም 27 ቀን 009 ዓ.ም. ድረስ ነው፡፡ የጠቅላላ ጉባዔ ጥሪ አንድ ቀን እስኪቀረው እየተላለፈ ቢቆይም በዚህ ወቅት ከኔትወርክ ውጪ የሆኑና ስልካቸው ዝግ የሆነ አባላት መልዕክቱ ሳይደርሳቸው ቀርቷል፡፡ እንግዲህ ከአዲአርቃይ ወረዳና ከጃናሞራ ወረዳ ጀምሮ እስከ ደጀን ከተማና የሰሜን ሸዋ ወረዳ ከተሞች ድረስ ያሉትን 167 የወረዳና የከተማ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ መልዕክት ሲተላለፍ አብዛኞቹ ስልካቸው በመዘጋቱ፣ አካባቢቸው ኔትወርክ ባለመኖሩና ከጊዜው ማጠር የተነሳ እንዲሁም አስቀድመው በሌላ ፕሮግራም ጊዜያቸው በመያዙ መገኘት ያልቻሉ አሉ፡፡
  4.  ከጠቅላላ ጉባዔው ክንውን አንድ ቀን በፊት ላለፉት ሦስት ዓመታት ይዘጋጅ የነበረው የንግድ ማውጫ (Business Directory) የተመረቀ ሲሆን፣ በውይይት ወቅት አስተያያት ሰጪዎች ሐሳብ ሲሰጡ የቢዝነስ ዳይሬክተሪው ኅትመትና ጥራት ይዘት በጠንካራ ጎኑ በማንሳት ጠቅላላ ጉባዔው መደረግ የነበረበት በታኅሳስ 2008 ዓ.ም.  ሲሆን፣ እስከ ዛሬ የዘገየው ይህንን የንግድ ማውጫ በማስመረቅ የምርጫ መቀስቀሻ ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ እንደሚመስል አንስተዋል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ በቢዝነስ ዳይሬክተሪው የፋይናንስ እንቅስቃሴ ሪፖርት  3,408,500 ብር ቃል የተገባ ሲሆን፣  2,442,775 ብር የተሰበሰበና የሚሰበሰብ ደግሞ 965,725 ብር መሆኑን ሲገልጹ የኦዲት ሪፖርት አልቀረበም፡፡  ከተሳታፊው ለምን ኦዲት ሪፖርት እንዳልቀረበ ተጠይቆ ሲመለስ በምክንያትነት የቀረበው ገንዘቡ ተጠቃሎ ገቢ ባለመደረጉ እንደሆነ ቢገለጽም፣ በኦዲት ሕግ ተሰናባቹ ቦርድ በተሰብሳቢ አስይዞ ኦዲት ማስደረግ እየቻለ አለማስደረጉ ቀጣዩ አመራር ራሳቸው እንደሚሆኑ አመላካች ከመሆኑም ባሻገር፣ በሒሳብ እንቅስቃሴውም በጠቅላላ ጉባዔው አባላት በኩል ጥርጣሬን አጭሮ አልፏል፡፡
  5.  ለጠቅላላ ጉባዔው ዝግጅት መጽሔት የታተመ ቢሆንም የጠቅላላ ጉባዔ መጽሔት እንደመሆኑ የሥራ ክንውን ሪፖርትና የኦዲት ሪፖርት በመጽሔቱ ተካቶ አልታተመም፡፡ ይህንን ሐሳብ በጉባዔው ያነሳው ተሳታፊ ቢኖርም፣ ከዚህ በፊትም በተካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔዎች ሐሳቡ ቀርቦ የነበረና በየጊዜው ለምን ማካተት እንደማይፈለግ ግልጽ አይደለም፡፡
  6.  ምርጫው ተከናውኖ ካለቀ በኋላ ለነባር የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት የምስክር ወረቀት በፍሬም ተዘጋጅቶ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ሌላውን ሽልማት ግን የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ቢሮ በመሄድ እንዲወስዱ ተነግሯቸው ጠቅላላ ጉባዔው ተበትኗል፡፡ የቦርዱ አባላት ወደ ቢሮ ሄደው ያገኙት ሽልማት ‹ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ› እንደሚባለው ለእያንዳንዳቸው የላፕቶፕ ኮምፒዩተር ሽልማት ሲሆን፣ ጠቅላላ ግምቱ 120,000 ብር አካባቢ በማውጣት በመሸላለም ተወዳድሰውበታል፡፡ ከ11ዱ የቦርድ አባላት ሁለቱ በስብሰባ በአብዛኛው ስለማይገኙ በሚል ያልተሸለሙ ሲሆን፣ ለጠቅላላ ጉባዔ ዝግጅት ስፖንሰር ካደረጉ ድርጅቶች ከተገኘ ገንዘብ የተገዛ መሆኑንና ከጽሕፈት ቤቱ መደበኛ ሒሳብ ገንዘብ ወጪ አለመደረጉን ሲገልጹ ከመስማት ባሻገር፣ ላፕቶፕ ያልተሸለሙ የቦርድ አባላት ቅሬታቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡

ጠቅላላ ጉባኤው ከተበተነ በኋላ የላፕቶፕ ሽልማቱን ጉዳይ የሰሙት የጠቅላላ ጉባዔው አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል አንደኛ ሽልማቱን ከጠቅላላ ጉባዔው ፊት ከምስክር ወረቀቱ ሥጦታ ጋር አብሮ ያልተደረገው ለምንድን ነው? ሁለተኛ ቦርዱ ለራሱ ሽልማት ራሱ መወሰን ይችላል ወይ? ሦስተኛ ከ11ዱ የቦርድ አባላት መካከል ሁለት የቦርድ አባላት ሳይሸለሙ የቀሩት ለምንድነው? በማለት ተጠያቂ በሌለበት ጉዳዩን አንስተዋል፡፡

  1.  የጠቅላላ ጉባዔ ተሳታፊ የሚሆኑ ሁሉም አባላት ማለትም የቦርድ አባላትን ጨምሮ የንግድ ሥራቸውን ከሚያከናውኑበት ከተማና ወረዳ ተወክለው የመጡ መሆን እንዳለባቸው ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ከሥር መሠረታዊ ንግድና ዘርፍ ማኅበራቸው በተሠራው ቀመር መሠረት ተወክለው መምጣት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ነባሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርቱን ካቀረበና በሪፖርቱ ላይ አስተያየት ተቀብሎ ካፀደቀ በኋላ፣ ለምርጫ ተሳታፊ መሆን የሚችሉት ከሚኖሩበት ከተማና ወረዳ ንግድና ዘርፍ ማኅበራቸው ተወክለው ከመጡ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም አሁን በፕሬዚዳንትነት የተመረጡትና ሌሎች ሁለት የቦርድ አባላት ነዋሪነታቸው ባህር ዳር ከተማ ሲሆን፣ የባህር ዳር ከተማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በጠቅላላ ጉባዔ እንዲሳተፉ ወክሎ የላካቸው አለመሆኑ እየታወቀ፣ እንኳንስ ለአመራርነት መመረጥ ቀርቶ በምርጫው ወቅት የጠቅላላ ጉባዔ አባል መሆን የማይችሉበትን የሕግ ሥርዓት በመጣስ ከዚህ በፊት በተካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔዎች በተመሳሳይ መንገድ ሕግ እየተጣሰ ዕርማት የሰጠ ባለመኖሩ ዛሬም ሕግ ተጥሷል፡፡ አዳዲስ የወረዳና የከተማ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አመራሮች ዕይታ በዚህ ጠቅላላ ጉባዔ ለመጀመርያ ጊዜ የተገኙ ከተለያዩ ከተማና ወረዳ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት የመጡ አዲስ አመራሮች በሰጡት አስተያየት፣ በክልሉ ምርጫ እንዲህ ዓይነት የቡድን ስሜት በተንፀባረቀበት መንገድ ምርጫ ይካሄዳል ብለው እንደማይጠብቁና እኛ ከመጣንበት ወረዳና ከተማ አንተ ትሻላለህ፣ አንቺ ትሻያለሽ በመባባል በፍፁም ትህትና የተመራረጥን ነው፡፡ እዚህ ስንመጣ ያየነው ግን ከዚህ በተቃራኒ ለመመረጥ ይህን ያክል ተደራጅቶ በመግባት ለረዥም ዓመታት ቦታውን በመያዝ ለሌላ ተተኪ ለመልቀቅ አለመፈለግ ያውም በነፃ ለሚከናወን አገልግሎት በጣም ተደንቀናል ብለዋል፡፡ መቼም ይህንን ያህል ዋጋ ከፍለው፣ ለመመረጥ ሰማዕትነት ከፍለው፣ ስማቸው ጠፍቶ ይህንን ሁሉ ልፋት የሚለፉት ለፅድቅ ወይም ለነፍስ ነው? ለማለት ከመቸገር ባለፈ የንግዱን ማኅበረሰቡን ለማገልገልም ካለ ፍላጎት ነው ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው ሲሉ አክለው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በነፃ ያለዋጋ ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጥበት ተቋም ቢሆንም ከዓላማ ውጭ የግል መጠቀሚያ የማድረግ፣ ሥራውን መተዳደሪያ የማድረግ፣ የአንዳንድ ጥቅማ ጥቅም ማግኛ ማዕከል እያደረጉት ሳይሆን እንደማይቀር የታዘቡ አሉ፡፡ የክልል የንግድና ዘርፍ ማኅበራት እንዲህ ይሆናል ብለው እንደማይጠብቁም ገልጸዋል፡፡ የንግድ ሚኒስቴርና የአማራ ክልል ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ የነጋዴው ማኅበር የተጠናከረና ለአገር የኢኮኖሚ ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን በመገንዘብ ሁልጊዜ የሚደረገውን ድጋፍ፣  ክትትልና እገዛ ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው በተቋሙ ግልጽነትና ተጠያቂነት የተሞላበት

አሠራር ሲሰፍን በመሆኑ፣ እንዲህ ዓይነቱ የተበላሸና የቡድን ስሜት የተንፀባረቀበት አሠራር ባህል እየሆነ የመጣ ስለሆኑ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱንና የቢሮውን ሥራ በዜሮ የማባዛት ያህል ነው፡፡

በመሆኑም ለንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የዕውቅና ምስክር በመስጠት አደራጅ የሆነው የንግድ፣ ሚኒስቴርና የአማራ ክልል ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ፣ እንዲሁም እናት ማኅበር የሆነው የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በተከናወነው ኢዴሞክራሲያዊ ምርጫና የቡድን ስሜት የተንፀባረቀበትን መሠረታዊ የሕግ ክፍተቶች ያለበትን ጉባዔ በዕንጭጩ እንዲቋጭ በማድረግ አስተማሪ ዕርምጃ መውሰድ የሚቻልበትን አሠራር ማስፈን ካልተቻለ፣ የድራማው ተዋናዮች በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደተሰማው ይህ ጉዳይ የአንድ ሰሞን ነው፡፡ ሁልጊዜ ምርጫ ሲከናወን የተወሰኑ ሰዎች ቢያጉረመርሙም ማንም ምንም ሊያደርግ አይችልም እያሉ፣ በአጠቃላይ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የግለሰቦች መፈንጫ መሆናቸውና የተቋቋሙበትን ዓላማ የማያሳኩ ሽባ ተቋማት ሆነው እንደሚቀጥሉ ሥጋት ስላለ፣ ማን ምን የማድረግ ሥልጣን እንዳለው ማሳየት ቢቻል መልካም ነው፡፡

ስለዚህ ጠቅላላ ጉባዔው በአጠቃላይ ያሉበትን መሠረታዊ የሕግ ክፍተቶች በማስረጃ በተደገፈ ሙያዊና ከአሉባልታ በፀዳ መንገድ በሰዎች ምስክርነትና በሰነድ ማስረጃነት ሊመረምር የሚችል አካል ተቋቁሞ ምርመራ በማካሄድ፣ የሚመለከተው አካል ነፃና ገለልተኛ ውሳኔ በመስጠት ሕግን ማስከበር ይገባል፡፡ የጎንደር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፡፡ (የማይነበብ ፊርማና ማኅተም አለው)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው gondarchamber@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡  
 

 

 

Standard (Image)

የባንክ ኢንዱስትሪው እንዴት ትርፋማ ሆነ?

$
0
0

በተክለብርሃን ገብረሚካኤል

ይህን መጣጥፍ እንዳቀርብ የቀሰቀሱኝ፣ እሁድ መስከረም 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በወጣው ‹‹ሪፖርተር›› (በአማርኛ ቋንቋ) ላይ የወጡት ሁለት ድንቅ ጽሑፎች ናቸው፡፡ አንደኛው ጽሑፍ ‹‹ባንኮች በተጠናቀቀውና በመጪው ዘመን›› በሚል ርዕስ በጋዜጣው ሪፖርተር የቀረበው ምርጥ ዘገባ ሲሆን፣ ሁለተኛው ጽሑፍ ደግሞ፣ ‹‹የአደጋ ጠርዝ ላይ የጣሉን የኢኮኖሚ ጉዳዮች›› በተሰኘ ርዕሰ ጉዳይ ብዙ ጊዜ በዚሁ ጋዜጣ ላይ በኢኮኖሚና ፋይናንስ ነክ ጉዳዮች ላይ የሚጽፉ ዓምደኛ ጌታቸው አስፋው ያስነበቡን ሙያዊ መጣጥፍ ነው፡፡ ሁለቱንም ጸሐፊዎች እያመሰገንኩ፣ እግረ መንገዴን በኢትዮጵያችን የጋዜጠኝነት ሙያ ታሪካዊ ሊባል የሚችል እምርታ እንዲያሳዩ ላደረገው ‹‹ሪፖርተር›› ጋዜጣ ያለኝን ከፍተኛ አድናቆት ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

በአቶ ጌታቸው አስፋው የኢኮኖሚ ትንታኔ እንጀምር፡፡ ጌታቸው የኢትዮጵያን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሁኔታ ለመቃኘት የሞከሩት ከአገሪቱ የውጭ ክፍያዎች ሚዛን/ሒሳብ (ባላንስ ኦፍ ፔይመንትስ አካውንት) አኳያ ነው፡፡ ሒሳቡ አስደንጋጭ የኢኮኖሚ ውድቀት ምልክቶችን ያሳያል፡፡ ጸሐፊው የተጠቀሙባቸው የኢኮኖሚ አኃዞች የ2006 እና የ2007 ዓ.ም. ናቸው፡፡ በ2007 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ሸቀጦች (ቁሳዊ) ወይም የምርት ኤክስፖርት ያገኘችው ጠቅላላ የውጭ ምንዛሪ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ያህል ብቻ ሲሆን፣ በዚያው ዓመት ከውጭ ለምታስመጣቸው ቁሳዊ ሸቀጦች (ኢምፖርት) የከፈለችው የውጭ ምንዛሪ 16.5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው፡፡ በዚህ መሠረት፣ የውጭ የሸቀጥ ንግድ ጉድለቱ 13.5 ቢሊዮን ዶላር መሆኑ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የኤክስፖርት ገቢ የኢምፖርት ወጪውን የሚሸፍነው በአሥራ ስምንት በመቶ ብቻ ነው (ሃያ በመቶ እንኳን አልሞላም)፡፡ በጣም አስደንጋጭ የኢኮኖሚ ውድቀት ምልክት ነው፡፡ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ፣ ኤክስፖርት በ2006 ዓ.ም. ከነበረበት 3.3 ቢሊዮን ዶላር፣ በ2007 ዓ.ም. ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር መቀነሱና ከዚህ በተቃራኒ ኢምፖርት ከ13.7 ቢሊዮን ዶላር ወደ 16.5 ቢሊዮን ዶላር መጨመሩ ነው፡፡

ሌላው አስደንጋጭ ክስተት እንደ ቱሪዝምና የአየር ትራንስፖርት (የኢትዮጵያ አየር መንገድ) ካሉት አገልግሎቶች የምናገኘው የውጭ ምንዛሪ ወጪን እንኳን መሸፈን ሳይችል ቀርቶ፣ በ2007 ዓ.ም. 341 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ማስመዝገቡ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአብዛኛው ‹‹ዳያስፖራው›› የሚልከውን ሐዋላ የሚያካትተው ከግል ምንጮች የሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ በ2006 ዓ.ም. ከነበረበት አራት ቢሊዮን ዶላር ወደ 4.8 ቢሊዮን ዶላር ቢጨምርም፣ የሚያመለክተው ኢኮኖሚያዊ ስኬትን ሳይሆን ጥገኝነትን ነው፡፡

ከላይ ከቀረበው መረጃ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አገሪቱ ከመንግሥታዊ ምንጮች የምታገኘው የውጭ ዕርዳታ የቀነሰ ሲሆን፣ የውጭ ብድር ግን ከ2.7 ቢሊዮን ዶላር ወደ 4.8 ቢሊዮን ዶላር ጨምሯል፡፡ በተመሳሳይ የውጭ ኢንቨስትመንትና የተከማቸ የውጭ ዕዳ ከፍተኛ ጭማሪዎች አስመዝግበዋል፡፡ አገሪቱ ከመንግሥታዊ ምንጮች የምታገኘው የውጭ ዕርዳታ የቀነሰው፣ ምናልባት ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ከመንግሥት ሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር በተዛመደ የሚያደርገው አሉታዊ ተፅዕኖ ሊሆን እንደሚችል የተገመተ ሲሆን፣ የውጭ ብድርና የተከማቸው የውጭ ዕዳ የጨመሩት ደግሞ መንግሥት ለልማት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከግል አበዳሪዎች ጭምር ለማግኘት በመሞከሩ እንደሆነ ይታመናል፡፡

እንዲያውም መንግሥት በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ የተከማቸው የአገሪቱ የውጭ ዕዳ ሃያ አንድ ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን፣ አንዳንድ የውጭ ምንጮች አኃዙን ወደ ሰላሳ ቢሊዮን ዶላር ያስጠጉታል፡፡ አቶ ጌታቸው ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለውጭ ዕዳ ክፍያ (ለዋናውና ለወለድ ክፍያ) 35 ቢሊዮን ብር ወይም አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ (በአንድ ዶላር 22 ብር ሒሳብ) እንደምትከፍል ነግረውናል፡፡ ይህ ክፍያ እየጨመረ ከሚሄደው የውጭ ዕዳ ጫና (የተከማቸው) አብሮ እያደገ እንደሚሄድ መገመት አያዳግትም፡፡ የውጭ ዕዳ ክፍያውና የኤክስፖርት ገቢ መቶኛ ምጣኔ ከሃምሳ ሦስት በመቶ በላይ መሆኑ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በኤክስፖርታችን ከሃምሳ በመቶ በላይ ለውጭ ዕዳ ክፍያ የምናውል ከሆነ፣ የኢምፖርት ወጪውን በምን እንሸፍነዋለን? ኢምፖርቱን እያደገ በሚሄድ የውጭ ብድር ለመሸፈን ከተገደድን፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አዙሪት ቀለበት ውስጥ እንደምንገባ ጥርጥር የለውም፡፡

የውጭ ኢንቨስትመንት የኢምፖርትን ወጪ በከፊል ሊሸፍን ይችላል፡፡ ግን ይህም ራሱ የውጭ ዕዳነት ባህሪ አለው፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች የሚያገኙትን ትርፍ በውጭ ምንዛሪ ወደየአገሮቻቸው የመላክ መብት አላቸው፡፡ ኢንቨስትመንታቸውን ዘግተው ሲሄዱ ደግሞ ቢያንስ በውጭ ምንዛሪ ያስገቡትን ካፒታል ያህል ወደየአገሮቻቸው ይዘው መመለስ ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የውጭ ክፍያዎች ሒሳብ የሚያሳየው አጠቃላይ ጉድለትን ሲሆን፣ ይኼንን ኪሳራ ለመሸፈን የአገሪቱን መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሪ መቀነስና ብሎም ማሟጠጥ ስለሚያስፈልግ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊፈታ በማይችል የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር ውስጥ የመግባት አደጋ ሊከሰት እንደሚችል፣ እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ ችግሩ መከሰት ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ ውድቀቱ ዋና መገለጫ እየሆነ መጥቷል፡፡

አቶ ጌታቸው ሌሎች አጠቃላይ የኢኮኖሚ ውድቀት ምልክቶችንም እንደሚከተለው መዝግበውልናል፡፡ ስልሳ በመቶ የሚሆነው የገበሬ መሬት ይዞታ ስፋት ከአንድ ሔክታር በታች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሱዳን ሽንኩርት ‹‹ኢምፖርት›› ታደርጋለች፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የውጭ ጥገኝነቱ በውጭ ዕርዳታና ብድር ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹ዳያስፖራው›› በሚልከው ሐዋላ ላይም ነው፡፡ ሥራ አጥነት ተንሰራፍቷል፡፡ ሥራ አጥነት ስውር ሥራ አጥነት እንዲጨምር ተደርጐ ከተሰላ፣ ለሥራ የበቃው ሕዝብ ሁሉ እንደ ሥራ አጥ የሚቆጠርበት ደረጃ ሊደርስ ይችላል፡፡ በቀን ለስምንት ሰዓት የተቀጠረ የመንግሥትና የግል ሠራተኛ፣ በቀን አራት ሰዓት ከሠራ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የስውር ሥራ አጥነት መጠን እጅግ ሰፊ ነው፡፡ የጥቃቅንና የአነስተኛ ድርጅቶች እንቅስቃሴ በእጅጉ ቀዝቅዟል፡፡ ‹‹የኮብልስቶን›› ሥራም እንደዚሁ ተቀዛቅዟል፡፡ ሳይሠራ የሚበላው ሕዝብ ቁጥር በጣሙን ጨምሯል፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ ግልጽና ስውር ሥራ አጥነት በተንሰራፋበት የኢኮኖሚ ዕድገቱ እንዴት አሥራ አንድ ነጥብ ምናምን በመቶ ሊሆን ቻለ? ብለው ይጠይቃሉ አቶ ጌታቸው፡፡ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን እንዲህ እያሉ ይቀጥላሉ፡፡ ኢትዮጵያ የገዛ ልጆቿና የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ወደ ዓረብና ሌሎች አገሮች እንዲኮበልሉ ቪዛና ፓስፖርት እየሰጠች መሸኘት ከጀመረች አያሌ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ሠርቶ ያላለፈልንን፣ መቶ ፈረንጆች ‹‹ኢንዱስትሪ ፓርኮች›› አቋቁመው እንዲያልፍልን መንግሥታችን ሌት ከቀን እየሠራ ነው፡፡ የገቢና የሀብት ልዩነት ጣሪያ ነክቷል፡፡ በመጨረሻምአቶ ጌታቸው እንደሚከተለው በማለት ማስጠንቀቂያና ምክር ይሰጡናል፡፡ ‹‹ዝምታ ሁላችንንም ገደል ውስጥ ይከተናል፡፡ ኢኮኖሚው ወደ መውደቅ ያዘነበለ መሆኑ የሚታያቸው ሁሉ ደመናውን ለመግፈፍ አስተያየታቸውን ቢለግሱ ጥቅሙ ለሁላችንም ነው፤›› ሸጋ መክረውናል፣ ተገቢም ማስጠንቀቂያ ሰጥተውናል፡፡ የጋዜጣው ሪፖርተር ዘገባ ግን ከዚህ በጣም የተለየ ነው፡፡ ለባንክ ኢንዱስትሪው መጪው ጊዜ ብሩህ መሆኑን ብቻ አይደለም የሚነግረን፣ ያለፉትም ዘመናት በትርፋማነት የተንበሸበሹ እንደነበሩ ነው የሚያበስረን፡፡ ይገርማል፣ አንድ እውነታ ሁለት መነጽሮች ያስብላል፡፡ ለማንኛውም እስኪ አሁን ደግሞ ወደ ጋዜጣው ሪፖርተር ዘገባ እንዙር፡፡

የባንክ ኢንዱስትሪው ትርፋማነት

የሁለቱ የመንግሥት ባንኮች (የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ) እና የአሥራ ስድስት የግል ባንኮች ድምር ወይም ጠቅላላ ትርፍ (ከታክስ በፊት) በ2007 በበጀት ዓመት ከነበረበት ደረጃ በመጨመር፣ በ2008 የበጀት ዓመት ወደ 21.5 ቢሊዮን ብር ገደማ አሻቅቧል፡፡ ከዚህ ውስጥ የአሥራ ስድስት የግል ባንኮች ጥቅል ትርፍ 6.3 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻውን 13.4 ቢሊዮን ብር አትርፏል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ትርፍ ደግሞ (ይህ የተጣራ መሆኑ ተገልጿል) 414 ሚሊዮን ብር ያህል ሆኗል፡፡ የአሥራ ስድስቱ የግል ባንኮች ጥቅል ትርፍ በ2007 የበጀት ዓመት 5.4 ቢሊዮን ብር ገደማ ስለነበር፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ድምር ትርፋቸው በአንድ ቢሊዮን ብር ያህል ማደጉን ያመለክታል፡፡

በሌላ በኩል የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በ2008 የበጀት ዓመት ከፍተኛ የትርፍ መቀነስ ሁኔታ ታይቶበታል፡፡ ይህ ችግር ምናልባት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያ ክልል ከተከሰተው ያለመረጋጋት ሁኔታ የተዛመደ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ብርሃን ባንክ ትርፉን በከፍተኛ መጠን ማሳደጉ ተዘግቧል፡፡

የባንክ ኢንዱስትሪው ስኬት በትርፋማነት ብቻ አልተወሰነም፡፡ የጋዜጣው ሪፖርተር ስኬቶቹን እንደሚከተለው በዝርዝር ያቀርባቸዋል፡፡ አዲስ ወጥ የሆነ የቼክ ክፍያ ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ማሽኖች (ኤቲኤሞች) በሁሉም ባንኮች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ሥርዓቱ የተዘረጋላቸው ኢትስዊች በሚባል ኩባንያ ነው፡፡ በሌላ በኩል በተለይ ከቡና ዋጋ መውረድ ጋር በተያያዘ የባንክ ዕዳቸውን በወቅቱ መክፈል የታያቸው የደቡብ ቡና ነጋዴዎች ለብድር ያስያዙት ንብረት በሐራጅ ተሸጦ ችግር ውስጥ እንዳይገቡ የእፎይታ ጊዜ መስጠቱ (በብሔራዊ ባንክ) እንግዳ ነገር ቢሆንም፣ ነጋዴዎቹን በመታገድ ረገድ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ፈላጊዎች ለአገልግሎቱ ከአንድ በላይ ባንክ መጠቀም እንደማይችሉ የተላለፈው መመርያ ደግሞ በአገሪቱ የደረሰውን አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያመለክታል፡፡ በሌላ በኩል ሁሉም ባንኮች በኮር ባንኪንግ ቴክኖሎጂ እንዲተሳሰሩ መደረጉ እንደ አንድ ትልቅ ስኬት ተቆጥሯል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁ ነው የሚባለውን የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ማስጀመሩም የሚጠቀስ ነው፡፡ ኤጀንት ባንኮች የሚባሉትም ሥራ መጀመራቸው ተዘግቧል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክን መጠቅለሉም ትልቅ የቢዝነስ ዜና ሆኖ አልፎአል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ፣ ሌሎች ባንኮችም ሊጠቃለሉ እንደሚችሉ ተወስቷል፡፡

ከባንክ ኢንዱስትሪው ስኬታማነት ጋር ሊታይ የሚችለው ሌላው ጉዳይ፣ የአንዳንድ የባንክ ሥራ አስኪያጆችና ፕሬዚዳንቶች የወር ደመወዝ ከመቶ ሺሕ ብር በላይ ማሻቀቡ ነው፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ መመደቡ፣ በባንኩ ሥርዓት አድሎአዊ አሠራር እንዳለ አመላካች ሆኖአል፡፡ ዝርዝር ዘገባቸው በመቀጠል የሁለቱ የመንግሥት ባንኮችና የአሥራ ስድስቱ የግል ባንኮች ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ 435 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተመልክቷል፡፡ ይህ አኃዝ በ2007 በጀት ዓመት ከነበረው 367.4 ቢሊዮን ብርና በ2006 በጀት ዓመት ከነበረው 292.8 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል፡፡

በተመሳሳይ አሥራ ስድስት የግል ባንኮች ተቀማጭ ገንዘባቸውን ከ100 ቢሊዮን ብር ገደማ በ2008 ዓ.ም. ወደ 147 ቢሊዮን ለማሳደግ ችለዋል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻውን የተቀማጭ ገንዘቡን መጠን ወደ 288.4 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ መቻሉ የባንኩን አንፃራዊ ግዙፍነት ያመለክታል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2008 በጀት ዓመት የሰጠው አዲስ ብድር (ክምችት አይደለም) 92 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ 16ቱ የግል ባንኮች ደግሞ በድምሩ 93 ቢሊዮን ገደማ አዲስ ብድር ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2008 በጀት ዓመት የሰጠው ብድር መጠን ደግሞ 11.84 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተመልክቷል፡፡ የባንክ ሥራ ጤናማነትን ለመለካት ጥቅም ላይ ከሚውሉት አብይ መሥፈርቶች የተበላሸ ብድር ጥምርታ (ምጣኔ) አንዱ ነው፡፡ ይህ መስፈርት ብሔራዊ ባንክ ከደነገገው አምስት በመቶ ከበለጠ (ብድር/የተበላሸ ብድር ጥምርታ) የባንኮች ጤናማነት ጥሩ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ የጤናማነት መለኪያ መሠረት የሁሉም ባንኮች ማለት ይቻላል አማካይ ጥምርታ አምስት በመቶ አካባቢ በመሆኑ፣ ሁሉም ባንኮች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡ የአንድ ባንክ ጥምርታ 7.9 በመቶ በመድረሱ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል የመንግሥት ቦንድ ግዢ (27 በመቶ) በ2008 ዓ.ም. ይቀራል ወይም ይሻሻላል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ግን አምስት ዓመት የሞላው ግዢ እየታሰበ ተመላሽ መሆን ጀምሯል፡፡ የባንኮችን የ2009 ዓ.ም. ዕቅድ በተመለከተ፣ ሁሉም ባንኮች ከ25 እስከ 30 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ አስበዋል፡፡ የጋዜጣው ዘጋቢ ይህን በመረጃ የታጀበ ግሩም ዘገባቸውን እዚህ ላይ ይደመድማሉ፡፡

ትንታኔ፣ ድምዳሜ፣ ማጠቃለያና የመፍትሔ ሐሳብ

ከላይ የቀረቡት ሁለት ዘገባዎች የኢኮኖሚውን እንቆቅልሽ ያመለክታሉ፡፡ አጠቃላይ ኢኮኖሚው የመውደቅና የመዝቀጥ አዝማሚያ እያሳየ ነው እየተባለ፣ የባንክ ኢንዱስትሪው ግን የትርፋማነትና በአጠቃላይም የኢኮኖሚ ስኬት ደሴት መስሎ ይታያል፡፡ ለምሳሌም የአጠቃላዩ ኢኮኖሚ የውጭ ክፍያዎች ሚዛን በጊዜው ዋጋም እንኳን ከፍተኛ የውጭ ንግድ ጉድለት ያሳየ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ሒሳቡም ያስመዘገበው ኪሳራ ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ሥራ አጥነትና ስውር ሥራ አጥነት መኖር የቁሳዊ ምርት አለማደግን፣ ወይም በአነስተኛ መጠን ብቻ ማደግን፣ ወይም መቀነስን ስለሚያመለክት አቶ ጌታቸው እንደሚሉት የኢኮኖሚውን ወደ ውደቀት ማዘንበል ያሳያል፡፡ የአጠቃላይ ኢኮኖሚውን ሁኔታ በገንዘብ ሳይሆን፣ በቁሳዊ ምርትና በተጨባጭ አገልግሎት ስንለካው፣ ያሉት የምርትና የአገልግሎት እጥረቶች ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ምናልባት በሕዝብ ዕድገት መጠን እንኳን አለማደጉን ነው የሚጠቁሙት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት በዓመት በ2.7 በመቶ እንደሚያድግ ይገመታል፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የምግብ ምርት ዕድገት በዓመት በ2.7 በመቶ ካደገ፣ ከድሮው የባሰ የምግብ እህል ምርት እጥረት ሊኖር አይገባም ወይም በፊት እጥረት ካልነበረ፣ ዛሬ እጥረት ይፈጠራል ተብሎ አይገመትም፡፡ ከዚህ ምሳሌ አኳያ መንግሥት ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት በአሥራ አንድ በመቶ አደገ ሲል፣ ካለው የተጨባጭ ምርትና አገልግሎት እጥረት ጋር የሚጣጣም ነገር አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው በአሁኑ ጊዜ የንፁህ ውኃ፣ የምግብ፣ የትራንስፖርት፣ የመኖሪያ ቤት፣ ወዘተ እጥረቶች እየተባባሱ ነው እንጂ የመጡት አልተሻሻሉም፡፡

አጠቃላዩ ቁሳዊ ኢኮኖሚ በተጨባጭ ምርትና አገልግሎት ሲለካ፣ ከላይ እንደተመለከተው፣ ምናልባት በዓመት በሦስት በመቶ አድጎ ሊሆን ይችላል እንጂ፣ መንግሥት እንደሚለው በየዓመቱ በአሥራ አንድ በመቶ ማደጉን ለመቀበል በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በሌላ በኩል ኢኮኖሚው በገንዘብ ሲለካ ዕድገቱ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ሊሆን የሚችለው በአብዛኛው ኢኮኖሚው ውስጥ ለመገበያያ የሚውለው የጠቅላላ ገንዘብ መጠን ዕድገት ከምርት ዕድገት ሲበልጥ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ መንግሥት የሚያወጣቸው የኢኮኖሚ አኃዞች ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት በጊዜው ዋጋ 1.3 ትሪሊዮን ብር ገደማ መድረሱን ያመለክታሉ፡፡ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን የገንዘብ መጠን ዕድገት የሚወስኑት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እያሳተመ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚያስገባው ጥሬ ገንዘብ፣ በዚህ ላይ ተመሥርተው (በተቀማጭ ገንዘብ በኩል) ባንኮች በብድር መልክ የሚፈጥሩት ገንዘብ፣ የተጣራ የውጭ ምንዛሪ ግኝትና የገንዘብ ዝውውር ፍጥነት ናቸው፡፡ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ገንዘብ መጠን ዕድገት ከቁሳዊ ምርትና ተጨባጭ አገልግሎት ዕድገት ከበለጠ፣ የመጨረሻ ውጤቱ የዋጋ ንረት ይሆናል፡፡

ከላይ የቀረበው ምሳሌ የሚያሳየን፣ ምርት ሳያድግም፣ በገንዘብ መጠን ማደግ ምክንያት ዋጋ ከናረ፣ ምርት በገንዘብ ሲለካ (በዋጋ ሲለካ)፣ ከፍተኛ ዕድገት ሊታይ እንደሚችል ነው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ለጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት በጊዜው ዋጋ የሚሰጠው የ1.3 ትሪሊዮን ብር አኃዝ ምናልባት በዚህ መንገድ ዋጋው የናረ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ባንኮች ግን በመሠረቱ የገንዘብ ነጋዴዎች እንደመሆናቸው፣ ገቢያቸውና ወጪያቸው ከገንዘብ መጠን ዕድገትና ከዋጋ ንረት ጋር አብሮ የማደግ አዝማሚያ ስላለው፣ ትርፋቸው በጊዜው ዋጋ የመጨመር አዝማሚያ ቢያሳይ የሚጠበቅ ነው፡፡ ለምሳሌ በኢምፖርት ሌተር ኦፍ ክሬዲት አገልግሎት ላይ የሚያስከፍሉት የአገልግሎት ክፍያ ዋጋው ከጨመረው ከኢምፖርት ጋር አብሮ ይወጣል፡፡ የኢምፖርት ዋጋው ከ100,000 ብር ወደ 5,000,000 ብር ከናረ፣ ባንኮች የሚያስከፍሉት የአገልግሎት መቶኛ ክፍያ ሁለት በመቶ ከሆነ፣ ገቢያቸው ከሃያ ሺሕ ብር ወደ መቶ ሺሕ ብር ያድጋል (በጊዜው ዋጋ) ፡፡ እዚህ ላይ ገቢያቸው በዋጋ ንረቱ መጠን ስላደገ፣ በቁሳዊ ምርት ገቢያቸው ሲለካ አልጨመረም፣ አልቀነሰም፡፡ በሌላ በኩል በሚሰጡት ብድር ላይ በሚያስከፍሉት የወለድ ተመንና በተቀማጭ ገንዘብ ላይ በሚከፍሉት ወለድ መካከል ያለው ልዩነት ከዋጋ ንረት ካነሰ፣ በጊዜው ዋጋ ያተረፉ ቢመስሉም ትርፋቸው ከዋጋ ንረት በተጣራ መንገድ ከተሰላ የሚያስመዘግቡት ኪሳራ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከባንኮች ገቢዎች ኢምፖርት/ኤክስፖርት ሌተር ኦፍ ክሬዲት፣ የውጭና የአገር ውስጥ ሐዋላ አገልግሎትና ሌሎች አገልግሎቶች ከዋጋ ንረት ጋር አብረው እንዳደጉ ስለሚገመት፣ ለትርፋቸው (በጊዜው ዋጋ) መጨመር አስተዋጽኦ ሲያደርጉ፣ ቁሳዊ ምርት በመግዛት ኃይላቸው ግን ብዙም ለውጥ እንዳላደረጉ ይገመታል፡፡

በሌላ በኩል ከባንኮች ወጪዎች መካከል የቅርንጫፍና የዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ፣ የተሽከርካሪና የኮምፒዩተር ግዥ፣ የቤንዚንና የሌሎች ቁሳቁሶች ግዢ ከዋጋ ንረት ጋር አብረው ስለሚወጡ፣ በጊዜው ዋጋ ትርፋቸውን የመቀነስ ተፅዕኖ ያደርጋሉ፡፡ የደመወዝ ወጪ ላይ ግን ባንኮች ዕድገቱን ከዋጋ ንረት በታች ለማድረግ ስለቻሉ፣ ለትርፋቸው (በጊዜው ዋጋ) በዋጋ ንረት መጠን አለመቀነስ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይኼውም በአጠቃላይ የባንክ ሠራተኞች ደመወዝ ከመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ በአማካይ በከፍተኛ መጠን ይበልጣል፡፡ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የመንግሥት ሠራተኞች (ሲቪል ሰርቪስ) አማካይ ደመወዝ በአራትና በአምስት እጥፍ ገደማ ሲጨምር (በጊዜው ዋጋ) የባንክ ሠራተኞች ደመወዝ ግን ቢያንስ አሥር እጥፍ እንደጨመረ ይገመታል፡፡ ለምሳሌ አንድ የቢኤ ዲግሪ ያለው የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ በመንግሥት መሥሪያ ቤት በደርግ ዘመን ያገኘው የነበረው የጀማሪ ደመወዝ 500 ብር የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ከ2,000 እስከ 2,500 ብር ያገኛል፡፡ በሌላ በኩል በጋዜጣው እንደተገለጸው የባንክ ሥራ አስኪያጆች ደመወዝ በአሁኑ ጊዜ ከወር ከመቶ ሺሕ ብር በላይ አሻቅቧል ከተባለ፣ በፊት ከነበረበት አሥር ሺሕ ብር ገደማ ስለሆነ እዚህ የደረሰው ጭማሪው አሥር እጥፍ መሆኑ ነው፡፡ ይሁንና ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የገበያ ዋጋ በሰላሳ እጥፍ ስለጨመረ (የጤፍ ዋጋን ያስታውሷል፡፡ ከ60 ብር ወደ 1,800 ብር በኩንታል)፣ የባንክ ሥራ አስኪያጆች ደመወዝ ማደግ የነበረበት ወደ መቶ ሺሕ ብር ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ሦስት መቶ ሺሕ ብር ነበር ማለት ነው፡፡

ለባንክ ኢንዱስትሪው አትራፊነት አስተዋጽኦ ካደረጉ ነገሮች መካከል በመንግሥት ትዕዛዝ የሚደረገው የባንክ ዕዳ ስረዛ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ለ‹‹ኢንዶውመንቶች›› በመንግሥት ትዕዛዝ የተደረገው የ2.5 ቢሊዮን ብር ዕዳ ስረዛ የሚታወስ ነው፡፡ ይህ አድራጎት አሁንም እንዳልቀረ ይነገራል፡፡ የባንኮች የተበላሸ ብድር መሥፈርት ጤናማ ነው (ከአምስት በመቶ በታች) የሚባለው ዕዳ እየተሰረዘ በመሆኑ፣ የባንኮች ትርፋማነት አጠያያቂ ነው፡፡ ዕዳ ሲሰረዝ የመጠባበቂያ ገንዘብ ስለሚቀንስ (ፕሮቪዥንስ)፣ ትርፍ እንደሚጨምር የታወቀ ነው፡፡ ሌላው በጣም አሳሳቢ ጉዳይ የባንክ ኢንዱስትሪው አትራፊነትና ስኬታማነት በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ አለመታየቱ ነው፡፡ እንዲያውም የባንክ ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ላይ ያለው ተፅዕኖ አዎንታዊ መሆን ሲገባው፣ አሉታዊ ሆኖአል እየተባለ ይተቻል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚያሳትመው ገንዘብና ንግድ ባንኮች በብድር አማካይነት በሚፈጥሩት ተጨማሪ ገንዘብ ምክንያት የዋጋ ንረቱ ጣሪያ ስለነካ፣ የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ አመሰቃቅሎታል፡፡ ሌላው ትችት ባንኮች ሕዝቡን አዘርፈውታል የሚለው ነው፡፡ ለብድር ብቁ ያልሆኑ ሰዎች ከባንክ ከፍተኛ ብድር እየተሰጣቸው፣ ከሕዝቡ መሬትና ቦታ በሊዝ ሽፋን እየተሰጣቸው፣ ከሕዝቡ መሬትና ቦታ በሊዝ ሽፋን እየነጠቁሕንፃዎችን ገንብተዋል፣ ሌሎች ንብረቶችንም አፍርተዋል ነው የሚባለው፡፡ እንዲሁም የባንክ ሠራተኞችና የባንክ ባለአክሲዮኖች የደመወዝ፣ የትርፍ ክፍፍልና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን በተመለከተ ከቀረው ሕዝብ የተሻለ ሁኔታ ላይ ስለሚገኙ፣ ለሕዝቡ ሊያበረክቱት የሚችሉት አስተዋጽኦ አናሳ ነው እየተባሉም ይወቀሳሉ፡፡

ከላይ ከቀረበው ትንታኔ የምንደርስባቸው ድምዳሜዎች ምንድን ናቸው? ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

  • የባንኮች ትርፍ በጊዜው ዋጋ በከፍተኛ መጠን የጨመረ ቢመስልም፣ ተጨባጭ ምርትና አገልግሎት በመግዛት ኃይሉ ግን ቀንሷል፣
  • የባንክ ኢንዱስትሪው አንፃራዊ ትርፋማነትና ስኬታማነት ከአጠቃላዩ የኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር አይጣጣምም፣
  • በባንኮች የሚሰጠው ብድር ከምርት ዕድገት ይልቅ ከፍተኛ የዋጋ ንረት በማስከተሉ፣ በኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ የኑሮ ችግር አስከትሏል፣
  • ባንኮች የሙስናና የዝርፊያ መሣሪያ ሆነው አገልግለዋል፣
  • የባንኮች ትርፋማነት በከፊል በትዕዛዝ ከሚሰረዝ የባንክ ዕዳ ጋር የተቆራኘ ነው፣
  • የባንክ ኢንዱስትሪው በለሙት ኢኮኖሚዎች እንደሚደረገው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመቀጠም እያደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው ነው፣
  • የባንክ ኢንዱስትሪው ለነፃ ውድድር በሚያመች ሁኔታ ገና በደንብ ሳይስፋፋ ወደ ማጠቃለል ሒደቱ ውስጥ መግባቱ (ንግድ ባንክ የኮንስትራክሽን ባንክን እንደጠቀለለው) ጤናማ የዕድገት አቅጣጫ አይደለም፣
  • በመሠረቱ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትና የማስፋቱ ተግባር የአጠቃላዩ ኢኮኖሚ ድርሻ እንጂ በቀዳሚነት ከባንክ ኢንዱስትሪው የሚጠበቅ አይደለም፣
  • የሥራ አጥነትና የስውር ሥራ አጥነት መንሰራፋት ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ከሕዝብ ዕድገት በላይ አለማደጉን ከማመልከቱም በተጨማሪ፣ ምናልባትም የነፍስ ወከፍ ምርት ቀንሶ፣ የሕዝቡ የኑሮ ደረጃ ማሽቆልቆሉን እንደሚያሳይም ይታመናል፣
  • በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የአገሪቱ የተከማቸ የውጭ ዕዳ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ሲሆን፣ ለዚህ ዕዳ ክፍያ የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ከኤክስፖርት ከሚገኘው ከሃምሳ በመቶ በላይ ሆኖአል፣
  • እስካሁን የውጭ ኢንቨስትመንት ለምርት ዕድገትና ለሥራ ስምሪት መስፋፋት ያደረገው አስተዋጽኦ አነስተኛ ነው፤

ለማጠቃለል ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በኢኮኖሚው የታየው ዕድገት የተጨባጭ ምርትና አገልግሎት ዕድገት ሳይሆን፣ የገንዘብ መጠን ዕድገትና በዚህም ምክንያት የሚከሰተው የዋጋ መናር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሥራ ስምሪትንና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን የማስፋት አቅሙ ዝቀተኛ ሲሆን፣ በአጠቃላይም ዕድገቱ መንግሥት እንደሚለው ባለሁለት አኃዝ ሳይሆን፣ ምናልባት ከሕዝብ ዕድገት ጋር ብቻ የሚመጣጠን እንደሆነ ይገመታል፡፡ በሌላ በኩል የባንክ ኢንዱስትሪው በዚህ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዓውድ ውስጥ ለብቻው እንደ አንድ የኢኮኖሚ ስኬታማነት ደሴት ሆኖ መውጣቱ የጤናማነት ምልክት እንዳልሆነ ይገመታል፡፡ ከዚህ ማጠቃለያ በመነሳት፣ ሊቀርቡ የሚችሉት አጠቃላይ የመፍትሔ ሐሳቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡

  • የኢትዮጵያ ርዕዮተ ዓለማዊ አቅጣጫ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲና ከልማታዊ መንግሥት ወደ ሊበራል ዴሞክራሲና ፍትሐዊ ካፒታሊዝም እንዲቀየር ማድረግ፣
  • ፍትሐዊ የመሬት ይዞታ ሥርዓት ማዋቀር፣
  • የትምህርትና የሙያ ሥልጠናን የጥራት ደረጃ በከፍተኛ መጠን ማሻሻል፣
  • የባንክ ብድር አስፈላጊዎቹን ቅድመ ግዴታዎችን ለሚያሟሉ፣ ለብድር ብቁ ለሆኑና የቢዝነስ ክህሎት ላላቸው ሰዎች ብቻ እንዲሰጥ ማድረግ፣
  • በትዕዛዝ የባንክ ብድር የመስጠትንና የባንክ ዕዳ የመሰረዝና አድሎዓዊ አሠራር ማስቀረት፣
  • የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር በኢኮኖሚክስ ሳይንስ ላይ የተመሠረተ የገንዘብና የመንግሥት በጀት ፖሊሲ መቅረፅ (ሞኒተሪ ኤንድ ፊስካል ፖሊሲ)፣
  • የተወዳዳሪ ባንኮች ቁጥር ከኢኮኖሚው ስፋት ጋር የሚመጣጠን ሳይሆን፣ ብዛታቸውን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ማቆም፣
  • ከጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት እያደገ የሚሄድ ድርሻ ለኤክስፖርት እንዲውል የሚያበረታቱ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን መውሰድ፡፡

እነዚህንና ሌሎች የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ፣ የባንክ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለብቻው የኢኮኖሚ ስኬታማነት ደሴት ሆኖ የሚወጣበትን ሁኔታ ማስቀረት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ የባንኮች ዕድገትና ትርፋማነት የአጠቃላይ ኢኮኖሚው ዕድገትና ስኬት የሚሆንበትን መላ ልንፈልግ ይገባል እላለሁ፡፡ በመጨረሻም፣ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ባቀረቡት ጽሑፎች ተነሳስቼ ይህን መጣጥፍ ለማቅረብ ያስቻሉኝን አቶ ጌታቸው አስፋውንና የጋዜጣውን ዘጋቢ በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡ ሰላም!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

       

                       

            

Standard (Image)

በተሻሩት አሥራ አንድ በመቶ ካደግን በተሾሙት ስንት በመቶ ልናድግ ነው?

$
0
0

በጌታቸው አስፋው

የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ይለውጣል የተባለ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ሹም ሽር መንግሥታዊ ዕርምጃ ተወስዶ በዝምታ ማለፍ አይቻልም፡፡ የተሰማንን ስሜት መግለጽና በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ አንዳንድ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ባልተለመደ ሁኔታ አስተያየታችሁን ስጡን እያሉ ሕዝብን ሲጋብዙ ሰንብተዋል፡፡ የኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች ከጭፈራ፣ ከስፖርትና ከተረት ወሬ ተላቀው ሙያዊ አስተያየት መጠየቅ መጀመራቸው ያስደስታል፡፡ ስለሆንም ይህንን አጠር ያለ ሙያዊ አስተያየት በለመድኩት መንገድ በሪፖርተር ጋዜጣ ለማቅረብ ወሰንኩ፡፡

መንግሥትም እንደተናገረው ዓለምም እንዲቀበል ባሳመነው መሠረት ላለፉት አሥር ዓመታት በጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ዓመታዊ ዕድገት፣ የአፍሪካንና የዓለምን አማካይ በእጥፍና በየእጥፍ እጥፍ በልጠን በአሥራ አንድ በመቶ አድገናል፡፡

በተለይም ደግሞ በኢኮኖሚ ልማት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በመንገድ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ወዘተ. ረገድ የተመዘገቡት ውጤቶች ወደር የላቸውም ብሏል፣ ብዙዎችም አምነውታል፡፡

በተሻሩት ባለሥልጣናት የተመዘገበው አሥራ አንድ በመቶ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገትና የኢኮኖሚ ልማት ውጤት ካልበቃ፣ አዲስ በተሾሙት ባለሥልጣናት የስንት በመቶ ዓመታዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ወይም የኢኮኖሚ ልማት ውጤት ሊጠበቅ ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ የተኩት አምና ያቋቋሙትን ካቢኔ ቢሆንም፣ ሚኒስትሮቹ ግን በአየር ንብረት ምክንያት ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ ስምንት በመቶ ዕድገት ቢወርድም፣ ከዚያ በፊት ለአሥር ዓመታት በተከታታይ አሥራ አንድ በመቶ ዕድገት ካስመዘገቡ ከፍተኛ የመንግሥት ሹማምንት አካላት ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡

በጥረታቸው በአበረከቱት አስተዋጽኦ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥፍ ሊሆን ዋዜማ ላይ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ጂቡቲ ባቡር መስመር ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የሥራ ዓለምን ለመቀላቀል ዝግጁ ሆነዋል፡፡ የመንግሥት ሜጋ ፕሮጀክቶች በመጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ናቸው፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየተሻሙ ነው፡፡

እነኚህ ሁኔታዎች የተሻሩት ሚኒስትሮች የኢኮኖሚ ዕድገቱን ከአሥራ አንድ በመቶም በላይ ሊያደርሱት ይችሉ በነበሩበት ቁመና ላይ እንደነበሩ የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ በአዲሶቹ ተሿሚዎች የኢኮኖሚው ዕድገት ከአሥራ አንድ በመቶውም በእምርታ እንደሚዘል ሊጠበቅ ይችላል ማለት ነው፡፡

ሆኖም ግን የሹም ሽሩ ዋና ዓላማ የሆኑትን በቅርቡ ለተቀሰቀሰው ሁከት ዋና ምክንያቶች ናቸው የተባሉትን የሥራ አጥነት፣ የዋጋ ግሽበትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግሮች ይፈታል ብሎ ለማለት ግን ጠለቅ ያለ ጥናት የሚጠይቅ ይሆናል፡፡

በግርድፉ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ እንኳ ለመናገር ቢያስፈልግ ኢኮኖሚው ሲያድግ የዋጋ ግሽበቱና የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ እየባሰባቸውም ሊሄድ ስለሚችል፣ ሥራ በመፍጠር ረገድም የኢኮኖሚ ልማቱ በግንባታ ወቅት ብቻ ጥቂት ጊዜያዊ ሥራዎችን ቢፈጥርም፣ የረጅም ጊዜና ቋሚ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም ግን የለውም፡፡ ለብዙዎች የረጅም ጊዜ ቋሚ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም ያለው የገበያ ኢኮኖሚው ብቻ ነው፡፡ ችግርን ለይቶ ማወቅ ለመፍትሔ ግማሽ መንገድ እንደ መጓዝ ነው ይባላል፡፡ የሰሞኑ ሁከት በችግሮቻችን ላይ ምንም ጥናትና ምርምር ሳናደርግ፣ ወረቀትና እርሳስ ሳንጠቀም፣ ሳንደምርና ሳንቀንስ በማያወላዳ መንገድ በግልጽና በገሀድ ነግሮን አልፏል፡፡ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ደረጃ የወጣቱ ሥራ ማጣት፣ የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ዋነኞቹ ችግሮቻችን እንደሆኑ ሁከቱ አሳይቶናል፡፡ እነኚህ ችግሮች ደግሞ የኢኮኖሚ ልማት ችግሮች ሳይሆኑ የገበያ ኢኮኖሚ ችግሮች ናቸው፡፡

በብሔራዊ ኢኮኖሚ ደረጃ ከተጠቀሱት ችግሮች በተጨማሪ በአገልግሎት አሰጣጥ አንዳንድ የክፍላተ ኢኮኖሚዎች ችግሮችም እንደሚኖሩ ባያጠራጥርም፣ ለብሔራዊ ኢኮኖሚ ችግሮች የክፍላተ ኢኮኖሚዎችን አስፈጻሚ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች መቀያየር ብቻውን የሚፈለገውን ለውጥ አያመጣም፡፡ ለገበያ ኢኮኖሚ ችግር መፍትሔ ችግሩ ካለበት ከገበያ ኢኮኖሚው ብዙ ሳይርቁ መፈለግ ይገባል፡፡

ብዙ አገሮች የገጠሟቸውን የገበያ ኢኮኖሚ ችግሮች እንዴት እንደፈቱ እናውቃለን ለምሳሌ ባራክ ኦባማ እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን እንደመጡ ለገበያ ኢኮኖሚ ችግሮች መፍትሔ እንዲፈልጉ ትልቅ ኃላፊነት የሰጡት፣ ለገንዘብ ሚኒስትራቸውና ለብሔራዊ ባንክ ገዥው ነበር፡፡ ግሪክም በቅርቡ የገበያ ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ስትገባ ለመፍትሔ አፈላላጊነት በውጭ አገር በዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርነት ከሚሠሩበት ተመርጠው የተሾሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ ሌሎች አገሮችም ተመሳሳይ ችግሮች ሲገጥሟቸው ተመሳሳይ ዕርምጃ ነው የሚወስዱት፡፡

በኢኮኖሚው ረገድ እነኚህ ሁለት የኃላፊነት ቦታዎች የየትኛውም አገር የመንግሥት መሪዎች፣ ፕሬዚዳንቶችና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ቀኝ እጆች ናቸው፡፡ በሁለቱ ኃላፊነት ቦታዎች ተሿሚዎችም የዲግሪ ዓይነትና መጠን የቆለለ ወይም የዓመታት የሥራ ልምድ ያካበተ ሰው ብቻ ሳይሆን፣ በልዩ መንገድ የሚመረጡ ዕውቀትን ከሥራ ልምድ ጋር ያጣመሩ ሌላው ቀርቶ የተማሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎችና የሠሩባቸው ዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች ሳይቀሩ ለምርጫ እንደ መሥፈርት የሚወሰዱባቸው ናቸው፡፡

በእነኚህ ሁለት ኃላፊነቶች የሚመደቡ ሰዎች ከዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋማትና ከሌሎች አገሮች አቻ ኃላፊዎች ጋር በገንዘብ ኢኮኖሚክስ ቋንቋ መነጋገር፣ ማሳመንና ማመን የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ አለመታደል ሆኖ እኛ ኢትዮጵያውያን በአገርኛ ቋንቋ የጥሬ ገንዘብ ዓይነቶችን በጥሬነት ደረጃ (Liquidity Level) ከፋፍለን ልንናገር እንኳ ባለመቻላችን፣ ስለጥሬ ገንዘብ ኢኮኖሚክስ የምናነበውን ቀርቶ በውጭ አገር ቋንቋ የምንናገረውንና ከአፋችን የወጣውንም በትክክል መረዳታችን ያጠያይቃል፡፡

የቁሳዊ ምርት ኢኮኖሚ የሚለካው በጥሬ ገንዘብ መሆኑ ራሱ በጥሬ ገንዘብና በቁሳዊ ኢኮኖሚ መካከል ያለውን ተዛምዶና መስተጋብር አጥንቶና መርምሮ ማወቅና ማስተካከል፣ ከምንም በላይ  በቅድሚያ ሊሠራ የሚገባው መሆኑን ያመለክታል፡፡ ሥራን የሚፈጥር ጥሬ ገንዘብ ነው፡፡ የሸቀጥ ዋጋን የሚወስን ጥሬ ገንዘብ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ መጣኝን የሚወስንም ጥሬ ገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህም በጥሬ ገንዘብና በቁሳዊ ምርት ኢኮኖሚ መካከል ያለውን ተዛምዶና መስተጋብር ጠንቅቆ ማወቅና ለምርት ዕድገት፣ ለሥራ ፈጠራ፣ ለዋጋ ንረት፣ ለውጭ ምንዛሪ መጣኝ የሚስማማ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ላይ ውሳኔ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ለገጠማት የገበያ ኢኮኖሚ ችግር የክፍላተ ኢኮኖሚዎች አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎችን ለመቀያየር ከመታሰቡም በፊት፣ በጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ (Monetary Policy) ከተለምዶ አሠራር ለመውጣት የእነዚህ ሁለት መሥሪያ ቤቶች የሥራ ኃላፊነትና አደረጃጀት የእስከ ዛሬ ጠንካራ ጎንና ድክመት እንደገና መፈተሽ፣ መተቸት በብዙ የዘርፉ ምሁራን አስተያየት መሰጠትም አለበት፡፡ ሊሾሙላት የሚገባቸው የገንዘብ ሚኒስትሮችና የብሔራዊ ባንክ ገዥዎችም በዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋማት የገንዘብ ኢኮኖሚስት ሆኖ ለረጅም ጊዜ የሠሩ ወይም በታወቀ ዩኒቨርሲቲ የገንዘብ ኢኮኖሚክስ የተማሩና ያስተማሩ መሆን አለባቸው፡፡ ይህን የሚያሟሉ ኢትዮጵያውን በአገር ውስጥ ባይኖሩም እንኳ የተከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል ማምጣት ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ለመቀላቀልና የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየተገደደችና እየተንቀሳቀሰች ያለች አገር እንደመሆኗ ወደፊት ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለሥራ አጥነት፣ ለዋጋ ግሽበት፣ ለውጭ ምንዛሪ መጣኝ  የሚስማማ ጤናማ የገንዘብና የጥሬ ገንዘብ ገበያና የገንዘብና የጥሬ ገንዘብ ዋጋ መፍጠር ይኖርባታል፡፡

የዓለም ኢኮኖሚ አካል ሲኮን የውስጥ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ኢኮኖሚ ሁኔታዎችም ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ በአውሮፓና በእስያ የሸቀጦች ዋጋ ለውጥ ወይም የአሜሪካ ዶላር ከሌሎች አገሮች ጥሬ ገንዘቦች ጋር መመነዛዘሪያ ዋጋ ለውጥ በእኛ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እያደገ መጥቷል ወደፊትም ያድጋል፡፡

የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የውጭ ባንኮች ገብተው እንዲሠሩ እየተገደድን ነው፡፡ ባንኮቹ መጥተው መሥራታቸውና የሚያስተዋውቁት የጥሬ ገንዘብ ዓይነትና ቅንብርን የሚቀይር አዳዲስ ቴክኖሎጂ በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት፣ ዓይነትና መጠን ላይ ምን ለውጥ እንደሚያመጣ አናውቅም፡፡ በቅርቡ በአገር ውስጥ ንግድ ባንኮች እየተሞከሩ ያሉት የስልክና የካርድ ክፍያ መንገዶች፣ ኤቲኤም፣ በልዩ ልዩ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ዓይነትና መጠን ላይ ምን ለውጥ እንዳመጡ እንኳ አላጠናንም፡፡  

ከቁጠባ የባንክ ተቀማጭ በሞባይል ወይም በካርድ የግዥ ክፍያ መፈጸም ከተቻለ፣ በተንቀሳቃሽ የባንክ ተቀማጭ (Demand Deposit ወይም Current Acccount) እና በቁጠባ የባንክ ተቀማጭ (Saving Deposit) ወይም (Saving Account) መካከል ያለው የጥሬነት ደረጃ (Liquidity Level) ልዩነት ትርጉም ስለሚያጣ፣ ልዩ ልዩ የጥሬ ገንዘብ ዓይነቶችን በጥሬነት ደረጃ  መከፋፈል የማይቻል ይሆናል፡፡

ከዚህ በላይ አጠር አድርጌ በሹም ሽሩ ላይ ያቀረብኩት አስተያየት ሹም ሽሩን የሚቃወም ሳይሆን፣ ከሹም ሽሩ በተጨማሪነት ሊሠሩ ይገቡ የነበሩ ለሰሞኑ ሁከት ዋና ምክንያቶች ናቸው ያልኳቸውንና ለወደፊት የኢኮኖሚ ቀውስ እንዳይከሰት መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ የምላቸውን የፖሊሲ ለውጦች ለመጠቆም ነው፡፡

የተከሰተው ችግር የፖሊሲ ሳይሆን የአፈጻጸም ብቻ ነበር ብሎ ለማለትና በአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎችን በመተካት ብቻ ችግሩን ሙሉ በሙሉ አስወግዳለሁ ብሎ ለመተማመን፣ ወይ አሥራ አንድ በመቶ አላደግንም ነበር ወይ ደግሞ አሥራ አንድ በመቶ ማደግ በቂ አልነበረም ብሎ ማመን ያስፈልጋል፡፡ ከመንግሥት ወገን ሁለቱንም ለማለት ድፍረቱ ያለው ሰው ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡

አዲሶቹ ተሿሚዎች በምርታማነታቸው ከተሻሩት ልቀው ከአሥራ አንድ በመቶ በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊፈጥሩ ይችሉ ይሆናል፡፡ ያለ ፖሊሲ ለውጥ የገበያ ኢኮኖሚውን ችግሮች በማስተካከል ሥራ አጥነት፣ የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የብሔራዊ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት ችግሮች ይቀረፋሉ ማለት ግን አይቻልም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው Getachewasfaw240@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡   

Standard (Image)

ኅዳር (መንግሥት) ሲታጠን (በጥልቅ ሲታደስ)

$
0
0

በልዑልሰገድ ግርማ

ኅዳር ወር በኢትዮጵያ ታሪክ የተለያዩ በሽታዎችን በማስተናገድ ትታወቃለች፡፡ እ.ኤ.አ. በኅዳር 1535 በቱርክና በየመን ወታደሮች የተደገፉት የኢማም አህመድ ኢብን ኢብራሂም ወታደሮች በወረርሽኝ በሽታ እንደተጠቁ ታሪክ ይዘክራል፡፡ በተመሳሳይ ወር አፄ ቴዎድሮስን ለመዋጋት የመጣው እንግሊዛዊው ጄኔራል ናፒየር ወታደሮቹ በወረርሽኝ በሽታ ተጠቅተዋል፡፡ በኅዳር 1888 ዓ.ም. ጣሊያኖች በከብቶች አማካይነት ተላላፊ በሽታን ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት አገራችን አብዛኛውን የከብት ሀብቷን እንድታጣ አድርገዋል፡፡ ከ1918 ዓ.ም. እስከ 1919 ዓ.ም. ዓለምን ባጠቃው የስፔን ኢንፍሉዌንዛ አገራችን በኅዳር ወር በመጠቃቷ ‹‹የኅዳር በሽታ›› በመባል ይታወቃል፡፡ የንፋስ በሽታ በመባልም ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ሁሌም በየዓመቱ ኅዳር 12 ቀን ቆሻሻን ሰብስቦ በማቃጠል የኅዳር በሽታን እያስታወስነው እንገኛለን፡፡ ይኼ ልማድ ከፍተኛ አገር በቀል ማኅበራዊ እሴት መሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል፡፡

በየዓመቱ ኅዳር 12 ቀን ሁሉም ሰው ቤቱንና አካባቢውን በቋሚነት በማፅዳትና ቆሻሻን በማቃጠል ይታወቃል፡፡ በተለይም አዲስ አበባ በዕለቱ በጭስ ጉም በመታፈን ለዓለም የአየር ብክለት አስተዋፅኦ የምታደርግ ይመስላል፡፡ ይኼ ልምድ እጅግ ጠቃሚ መሆኑ ቢታመንም፣ በዓመት አንድ ቀን ብቻ መሆኑ ግን ጥቅሙን አናሳ ያደርገዋል፡፡ በተለይም አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት በቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ችግር ተተብትባ ባለችበት ወቅት፣ እያንዳንዱ ቀን ኅዳር 12 የሚል ስያሜ ቢሰጠው አይበዛበትም፡፡ የቆሻሻን አላስፈላጊነት በመረዳት የፅዳት ዘመቻው መካሄዱ ቁልፍ ማኅበረሰባዊ ተግባር መሆኑ አያጠራጥርም፡፡  

አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አገርን ለአደጋ የሚያጋልጡ የውስጥ ችግሮቹን ለመፍታት የአሥራ አምስት ዓመታት ውዝፍ ሒሳቡን ለማወራረድ ከአንድ ዓመት በላይ ሊወስድ የሚችል እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ መንግሥት የሚታጠነው ወይም የሚታደሰው ትምክህተኝነት፣ ጠባብነትና ኪራይ ሰብሳቢነት የተባሉ ቆሻሻዎቹን ለማፅዳትና ለማቃጠል ነው፡፡ መንግሥት የሕዝብ ተወካይ እንደመሆኑ መጠን በመታጠኑ (በመታደሱ) ሒደት ሕዝብን እንደሚያሳትፍም ቃል ገብቷል፡፡ የመታጠኑ (የመታደሱ) ሒደት አሥራ አምስት ዓመታትን ጠብቆ መሆኑ ግን ተገቢ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ማግሥት ጀምሮ ያስመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ እንዲሁም በ2008 ዓ.ም. በተለያዩ አካባቢዎች በተነሱ የከተማና ከተማ ቀመስ አካባቢዎች ረብሻዎች በመነሳት እያደረጋቸው ያለው ተሃድሶዎች (መታጠኖች) ኢሕአዴግን ‹‹በመከራ ብቻ የሚመከር ፓርቲ›› ያደርገዋል፡፡ ተሃድሶአዊ እንቅስቃሴዎች ዘላቂና ተቋማዊ ባለመሆናቸው ዋጋ እንደሚያስከፍሉ አይተናቸዋል፡፡ የደረሱብን ችግሮች ምንም ዕድገት ካለመመዝገብ ጋር የተያያዙ ሳይሆኑ፣ ዓለም የመሰከረላቸው ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገቶች ከሕዝብ ቁጥር ዕድገትና በየዓመቱ እንደ አሸን ከሚፈላው የተማረ የሰው ኃይል ቁጥር ጋር ባለመመጣጠናቸው ብቻ ነው፡፡ ጠባብነት፣ ትምክህተኝነትና ሙስና ደግሞ ዋነኞቹ የችግሮቹ ማባባሻዎች ናቸው፡፡

 

አገራችን ኢትዮጵያ ከነበረችበት ዘርፈ ብዙ እርስ በርስ የመቆራቆስ አባዜ ወጥታ የራሷ በሆነ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሞዴል ሆና መንቀሳቀስ ከጀመረች ሁለት ተኩል አሥርት ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ በእነዚህ ጊዜያት አገራችን አካታች የሆነ የሽግግር መንግሥት በመመሥረት፣ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚያውጅ ሕገ መንግሥት በማፅደቅና ተግባራዊ በማድረግ፣ ሥር ሰዶ የነበረውን የድኅነት መጠን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ የተለያዩ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ፣ የውጭ ግንኙነታችንን ከብሔራዊ ደኅንነታችን ጋር በማስተሳሰር፣ የአፍሪካ ቀንድን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ሌት ተቀን በመትጋት፣ የአፍሪካን ጥቅሞች ለማስከበርም በዓለም አቀፍ ደረጃ ድምጿን በማሰማት፣ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ለፍትሐዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም በማስተባበርና በማስተሳሰር፣ እንዲሁም ግድቡን በራሷ አቅም መገንባት በመጀመርና ሌሎችንም ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸውን ሥራዎች በማከናወን በዓለም ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ጥቂት አገሮች ተርታ ለመሠለፍ በቅታለች፡፡

ሆኖም እነኚህ ዓመታት አልጋ ባልጋ ሆነው አላለፉም፡፡ የኦነግ ከሰላማዊ ትግሉ በይፋ መውጣትና ያስከተለው አሰቃቂ ጭፍጨፋ፣ የኤርትራ መንግሥት እብሪተኛ ወረራ፣ የሕወሓት ለሁለት መሰንጠቅ፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተፅዕኖ፣ የድኅረ 1997 ዓ.ም. ምርጫ ምስቅልቅልና የቅርቡ የኦሮሚያና የአማራ ብጥብጦች ካጋጠሙን ችግሮች በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህና ሌሎች ችግሮች መነሻዎቻቸውን ያበረከቱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ትምክህተኝነት፣ ጠባብነት፣ እብሪተኝነት፣ ኢሕገመንግሥታዊ በሆነ መንገድ ሥልጣን መሻት፣ ሙስናና የመልካም አስተዳዳር ዕጦት ጥቂቶቹ አንገራጋጭ ምክንያቶች ሲሆኑ፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ መዋቅራዊ ሽግግር ውስጥ ላሉ አገሮች በብዛት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ናቸው፡፡ በርካታ ከፍተኛ የዕድገት እርከን ላይ የደረሱ አገሮችም ተመሳሳይ ችግሮችን በማሳለፍ ዜጎቻቸው የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ አድርገዋል፡፡

የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ትርምስም በሽግግር ላይ ለምትገኝ አገር አስገራሚ ባይሆንም፣ ይኼንንና ተመሳሳይ ችግሮችን ለመቅረፍ መንግሥትና ሕዝብ እጅና ጓንት ሆነው መጓዝ ይገባቸዋል፡፡ ለእዚህም የችግሮቹን መንስዔ ከሥር መሠረቱ ለይቶ ማወቅና መግባባት የመጀመርያው ተግባር ነው፡፡ በተለያዩ ሚዲያዎች መከታተል እንደተቻለው የሁከቱ መነሻዎች ሁለት ናቸው፡፡ የመልካም አስተዳደር ሙሉ አለመሆኑና ይኼንኑ የሕዝብ ጥያቄ በመጥለፍና የቀለም አብዮትን በማስነሳት የሥልጣን ጥምን፣ እንዲሁም የጠባብነትን አጀንዳን ለማራመድ የሚፈልጉ ኃይሎች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ እዚህ ላይ ደርግ የሕዝብን ጥያቄ በመጥለፉ አገራችን የኋልዮሽ እንድትጓዝ መደረጓን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡

ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ላይ መንግሥት መመሥረት ያስፈለገው በኢትዮጵያ ለዘመናት የተጠራቀሙትን ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመቅረፍና የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት ለማረጋገጥ ሲሆን፣ ለሃያ አምስት ዓመታት በተጓዘበት ጉዞ ላይ ውስጣዊና ውጫዊ ጋሬጣዎችን እየተቋቋመ እዚህ ደርሷል፡፡ እንደ እሳት በሚንቦገቦግ የአፍሪካ ቀንድ አንፃራዊ የሆነ ሰላምን በማስፈንና የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ኢሕአዴግ የሚመሰገን ሲሆን፣ ውስጡን ተብትበው በያዙት ችግሮች ምክንያት ግን በየቀኑ መታጠን ያለበት ፓርቲ መሆኑን አያከራክርም፡፡ በከባድ ውጣ ውረድ ያለፈባቸውን መንገዶች በመጠነኛ ተሃድሶ (መታጠን) ብቻ በማሳለፍ ዘርፈ ብዙ የሆኑ የዕድገት ምንጮችን ጉዞ ወደኋላ አስቀርቷል፡፡ ነገር ግን የሁሉም አስተዋፅኦ እንዳለበት ደግሞ አያጠራጥርም፡፡ የመጣንበት ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሁኔታ እንዳንተማመንና በጎሪጥ እንድንተያይ ማድረጉ፣ የብሔራዊነት ስሜትን የሚፈጥሩ ሥልቶች አለመነደፋቸውና ራስን በራስ ማስተዳደር የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ መርህ በቅጡ አለመረዳት ወይም አጣሞ ማቅረብ ዋና ዋናዎቹ ችግሮች ናቸው፡፡

የኅዳር 12 ቀን የመታጠን ልምድ መነሻ ያደረገው በኅዳር ወር 1918 ዓ.ም የገባው የኅዳር በሽታ ነው፡፡ በመሆኑም የአካባቢ ንፅህና እጅግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ ሁሉም ከየቤቱ ያወጣውን ቆሻሻ በማቃጠል በሽታውን ለማስወገድ ጥረት አድርጓል፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥትም ቤቱን በመጥረግ እያወጣ ያለውን ቆሻሻ እያቃጠለ መሆኑ ጭሱ ምስክር ነው፡፡ ከላይ የተጀመረው የካቢኔ ለውጥም ትምህርትን፣ የሥራ ልምድንና ስኬትን በማጣመር የተደረገ በመሆኑ አዲስ ጅማሮ ሊባል የሚችል ሲሆን፣ ሁሉም በየመስኩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ አንድ ነባር የሕወሓት ታጋይ እንደተናገሩት ምሁራን ሚኒስትሮቹ ስኬታማ ሊሆኑ የሚችሉት ዕውቀት ካላቸው ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰው ስለተማረ ብቻ ስኬታማ ሊሆን እንደማይችል የሚያወሱት እነኚሁ ነባር ታጋይ፣ ለውጥ ለማምጣት ከትምህርትና ከልምድ የተገኘ ዕውቀት ወሳኝ ነው ይሉናል፡፡ ይኼው የካቢኔ አሰያየም እየወረደ እስከ ቀበሌ እንደሚደርስም ተገልጾልናል፡፡ ‹‹መንግሥት ሲታጠን እንዲህ ነው›› ማለት ነው፡፡ 

መንግሥት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ አይታጠንም፡፡ በአብዛኛው ከአመለካከት ለውጥ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ጊዜ መፍጀቱ አይቀሬ ነው፡፡ ለሃያ አምስት ዓመታት የተከማቸ ቆሻሻ በአንድ ቀን አይቃጠልም፡፡ ቆሻሻውን ከደህናው የመለየት ሥራም እንዲሁ ጊዜ የሚፈጅ ነገር ነው፡፡ ዋናው ነገር በዕቅድ መጓዙ ነው፡፡ መታጠኑ እንዳለ ሆኖ የተጀመሩ የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ መንገዶችን ማስፋት ዋናው ሥራ ነው፡፡ ይኼንን ከሚያኮላሹ የውጭ ኃይሎችና አገርን መበታተን የስኬታቸው መንገድ አድርገው የሚወስዱትን የውስጥ ሴረኞችንም ቢሆን መካላከል ወሳኝ ሥራ ነው የሚሆነው፡፡

መንግሥት መታጠን የሚያስፈልገው ብቸኛው አካል አይደለም፡፡ በቢሊዮኖች በሚቆጠር ገንዘብ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በማባበል የሕዝብ ፕሮጀክቶች ከሚገባው የጥራት ደረጃ በታች እንዲከናወኑና ረዥም ጊዜ በመፍጀት ጥቅም እንዳይገኝባቸው በማድረግ የግሉ ሴክተር አባላት ዋነኛ ተዋናይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ልምድ የወሰደችባቸው ኮሪያና ታይዋን የግል ባለሀብቶች በመጀመርያዎቹ የዕድገት ዓመታት እንኳን የገንዘብ ጥማቸውን ለማርካት ሲሉ በሕዝብ ፕሮጀክቶች ጥራትና ጊዜ ላይ አይደራደሩም ነበር፡፡ በመሆኑም ብሔራዊ ዕድገትንና ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ አልነበሩም፡፡ ሆኖም እነዚህን ኪራይ ሰብሳቢዎች ባለማቋረጥ በመታገል አገሮቹ አሁን የደረሱበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ መታጠን (መታደስ) ማለትም ‹‹ያለማቋረጥ መታገል›› ማለት ነው፡፡

የመንግሥትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መታጠን ከሚገባቸው መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ትምህርትን እንደ መሣሪያ ከማስታጠቅ ይልቅ ጥርጣሬንና ጥላቻን የሚዘሩ መምህራንን በጉያቸው አቅፈው የሚገኙት በርካታ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ መምህራን የተሠለፉበትን የትምህርት መስክ በሚገባ ማወቃቸውም አጠራጣሪ ነው፡፡ የትምህርትን ውጤት በዘርና በፖለቲካ አመለካከት የሚለኩም አሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ከእነዚህ የትምህርት ተቋማት የሚወጡ ወጣት ባለሙያዎችም የተበረዘ ዕውቀት በመያዝ በአጭር ጊዜ ለመክበር በሚደረግ ጥረት ሲባዝኑ ይታያሉ፡፡ የተቋማቱ ስኬታማነት የተመሠረተው በሚያስመርቋቸው ተማሪዎች ብዛት ነው፡፡ የጥራቱ ነገር ለማን እንደተተወ አይታወቅም፡፡ የዲፓርትመንት አመዳደብ፣ የሬጅስትራር አገልግሎት፣ የመምህራን ዝግጅት፣ የተማሪዎች አቀባበልና ተያያዥ ጉዳዮች አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተማሪዎች የሚሞሉ መምህራንን መገምገሚያ ቅጾች በዘረኝነት ላይ የተመሠረቱ ሆነው ይታያሉ፡፡ ብቃት የሌለውን መምህር የወንዜ ልጅ ነው በማለት ብቻ ዓይኔን ግንባር ያድርገው በማለት የመጠቀ ምሁር አድርገው ያቀርቡታል፡፡ የዲፓርትመንት ኃላፊዎችና የፋካልቲ ዲኖችም አልፎ አልፎ በወዳጅነት ሲሾሙ ይታያል፡፡ በአንድ የግል ኮሌጅ የሲቪክ መምህር የነበረ ወዳጄ የተማሪዎችን ግሬድ ካስገባ በኋላ ተጠርቶ የወደቁ ተማሪዎችን ግሬድ እንዲያስተካክልና እንዲፈርም ይጠይቁታል፡፡ በእዚህ ክፉኛ የደነገጠው ወዳጄ ግሬዱን ራሳቸው እንደገና እንዲሠሩትና እንዲፈርሙበት በመንገር ከተቋሙ ጋር የነበረውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አቁሟል፡፡ በእዚህ መልኩ ከከፍተኛ የትምህርት ቤት ተቋማት የሚወጡ ምሩቃን ምን ዓይነት አገልጋይ እንደሚሆኑ መገመት ይቻላል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት የፅድቅም የኩነኔም ቦታዎች ናቸው፡፡ ተቋማቱ ምዕመናኖቻቸውን መንፈሳዊ ምግብ እየመገቡ ከክፉ ሥራ እንዲርቁ በማድረግ ለመንግሥተ ሰማያት እንዲበቁ በርትተው እንደሚሠሩ ሁሉ ስኳር በብዛት የሚላስባቸው ቦታዎችም ናቸው፡፡ በአገራችን የሚገኙ በርካታ የሃይማኖት ተቋማትም ሊታጠኑና በየራሳቸው ሃይማኖታዊ ፍልስፍና ያለማቋረጥ ፀሎት የሚገባቸው ናቸው፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ አማኝ እንደመሆኑ፣ የሃይማኖት ተቋማት የሚኖራቸው ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም፡፡ በእነዚሁ ተቋማት ውስጥ ዓለማዊ የሆነው የገንዘብ ፍቅር በመበርታቱና ይኼንኑ ለመሸፈን በሚደረግ ጥረት ትምክህተኛነትና ጠባብነት ሰተት ብለው ገብተው ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ የበርካቶች ሃይማኖቶች መገኛ እንደመሆኗ መጠን መቻቻል ወሳኙ አብሮ የመሆኛ ሥልት እንደመሆኑ በጥንቃቄ ሊኬድበት ይገባል፡፡ ለእዚህም የተቋማቱ የሥራ መሪዎች ዓለማዊና መንፈሳዊ ተሃድሶ (መታጠን) ያስፈልጋቸዋል፡፡

መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መንግሥት ባልተሰማራባቸው የሥራ መስኮች እንዲሁም በክፍተቶች ውስጥ በመግባት ሕዝብንና መንግሥትን ለማገዝ የተቋቋሙ አካላት ናቸው፡፡ በሁሉም ባይሆን በእነዚሁ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ አመራሮች የግል ጥቅማቸውን ሲያካብቱ ይታያል፡፡ መንግሥት የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያወጣውን የ70 - 30 ደንብ አምርረው ይቃወማሉ፡፡ ይኼ ችግር ወደ ሲቪክ ተቋማት ሲመጣ ደግሞ ጉዳቱ እጥፍ ድርብ ነው፡፡ ገንዘብን ከማጭበርበር በላይ ትምክህተኝነትንና ጠባብነትን የሚያስተናግዱ የእነዚሁ ተቋማት መሪዎች ቤት ይቁጠራቸው፡፡ የሚታገሏቸውን ኢፍትሐዊነት፣ ኢዴሞክራሲያዊነት፣ የፆታ መድሎዎች፣ ሙስና፣ ጠባብነትንና ትምክህተኝነትን በየከረባታቸው ሥር ደብቀው ‹‹ሙያ በልብ ነው›› የሚሉ እንዲሁ በርካቶች ናቸው፡፡ እነዚህ መታጠንም መጠረግም የሚገባቸው ናቸው፡፡

የግሉ የሚዲያ ዘርፍም ሌላው ሊታጠን የሚገባው የሙያ ዘርፍ ነው፡፡ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን የሚገባቸውን ባለመወጣታቸው መታጠን የሚገባቸው ቢሆንም፣ እንደግሉ የሚዲያ ዘርፍ በተለይም እንደ ግሉ ፕሬስ ጥፋታቸው የከፋ አይደለም፡፡ ለማንም ሳይወግኑ ወይም ውግንናቸውን ለሕዝብ ለማድረግ ለእውነትና ለእውነት ብቻ መቆም ሲገባቸው ሕዝብን በመከፋፈልና ጥላቻን በመዝራት የሚታወቁ የግሉ ፕሬስ ወገኖች ተፈጥረው ሲከስሙ ተመልክተናል፡፡ የግሉ ፕሬስ የተለያዩ አመለካከቶች ማስተናገጃ እንጂ ፅንፍ በመያዝ የግል ዓላማን ማሳኪያ መሣሪያ አይደለም፡፡ በሩዋንዳ የተከሰተውን የዘር ጭፍጨፋ የግሉ የሚዲያ ዘርፍ ምን ያህል እንዳከፋው የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ተመሳሳይ ጉዳዮች እንዳይከሰቱ ልጓም ማበጀቱ ምንም ዓይነት ክፋት የለውም፡፡

በአገራችን ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሥርተዋል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች (አብዛኛዎቹ) ዋና ዓላማቸው በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የምርጫ ውድድር በማድረግ ለሥልጣን መብቃት ሳይሆን፣ ኢሕአዴግን ከሥልጣን ማውረድ ነው፡፡ ገዢውን ፓርቲ ዕለት በዕለት በመከታተል የሚሠራቸውን ህፀፆች በማሳየት ለሕዝብ የሚጠቅም ሐሳብና አማራጭ ማቅረብ ሲገባቸው፣ ከአስተሳሰብና ከዓላማ ችግር በመነጨ የረባ ነገር ሳያከናውኑ እየባዘኑ ይገኛሉ፡፡ የምርጫ ወቅትን ብቻ ጠብቀው የሚያደርጓት መፍጨርጨር ለምን ሌላኛው ምርጫ እስከሚመጣ እንደማይቀጥል ግልጽ አይደለም፡፡ ምናልባትም የበጀት ዕጥረት የሚኖርባቸው ይመስላል፡፡ የበጀት፣ የአመለካከትና የስትራቴጂ ጉድለቶቻቸውን አሟልተው እስከሚገኙ ግን ኢትዮጵያ የመድበለ ፖለቲካ ፓርቲ ሥርዓት ምች እንደመታት ይቀራል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተግባር፣ ፕሮግራም፣ ፖሊሲና አካሄድ ያልገባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት በብዛት የሚገኙበት አገር ኢትዮጵያ ሳትሆን አትቀርም፡፡ የትምህርትና ሥልጠና ዕጥረት ለክህሎቱ አለመኖር አስተዋጽኦ አለው፡፡

ከእነዚህ ችግሮችም ባሻገር ኢሕአዴግን ለማስወገድ ብለው ከሻዕቢያ ጋር ወዳጅነት የፈጠሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ነን ባዮችም አሉ፡፡ ኢትዮጵያን ለማደፍረስ ሌት ተቀን ከአሸባሪዎች ጋር ከሚሠራ ቡድን ጋር አብሮ መገኘት አሸባሪነት እንጂ ሌላ ምን ይባላል? ፍትሐዊ ሐሳብና ምክንያታዊነት ናፍቆናል፡፡ ሕዝቡን በዘር መከፋፈል፣ ከፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር መተባበር፣ ኢትዮጵያ ብድርም ሆነ ዕርዳታ እንዳታገኝ ለጋሾችን መወትወት፣ ታጣቂ ከሆኑ ጽንፈኞች ጋር አብሮ መሠለፍ፣ ብሔራዊ ፕሮጀክቶችን ማጥላላትና በመሳሰሉት ሁኔታዎች መጠለፋቸው ከርመውም እንጭጭ መሆናቸውን ያሳብቅባቸዋል፡፡ ሁሉም እንዲህ ናቸው ማለት ግን አይደለም፡፡ በፕሮግራምና በመልካም አስተዳደር ዕጦት የሚሰቃዩት እነኚሁ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ኢሕኢዴግን ለማብጠልጠል ግን ቁጥር አንድ ናቸው፡፡ ኢሕአዴግን ከሥልጣን ማስወገድ ብቸኛው ፕሮግራማቸውና አጀንዳቸው የሆኑ በርካቶች ናቸው፡፡ ከተመረጥኩኝ በኃላ መራጮቼን አማክሬ ፕሮግራም እቀርፃለሁ ሲሉ የተደመጡም አሉ፡፡ የሚቀለድበት ክፍለ ዘመን ላይ አለመሆናቸውን አያውቁትም? በየደቂቃው መታጠን አለባቸው፡፡

መታጠን ያለባቸው ከላይ የተጠቀሱት ብቻ አይደሉም፡፡ ብንዘረዝራቸው በርካቶች ናቸው፡፡ ዋናው ጥያቄ ካልታጠንን ምን እንሆናለን? የሚለው ነው፡፡ ካልታጠንን የዓለም ራስ ሆነን እንደነበርን ሁሉ የዓለም ጭራ እንሆናለን፡፡ አሁን የጀመርነው የዕድገት ጉዞ በአጭሩ ይቀጫል፡፡ በአካባቢያችንም ሆነ በዓለም ዙሪያ የምናደርገው ሰላምን የማስፈን፣ የአየር ብክለትን የመዋጋትና ዘላቂ ልማትን የማምጣት ውጥናችን ወረቀት ላይ ብቻ ይቀራል፡፡ በዘመናችን የራሳችንን አሻራ የማንተው እንሆናለን፡፡ የውጭና የውስጥ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች መፈንጫ እንሆናለን፡፡ በመሆኑም የተጀመረው ተሃድሶ ለመንግሥት (ለኢሕአዴግ) ብቻ ሳይሆን ሁሉም እንደሚመለከተው አውቆ በፍጥነት መንገድ ላይ ጉዞውን መጀመር አለበት፡፡ ከሁሉም በላይ የአመለካከት ለውጥ ላይ መሥራት ዋናው የመታጠን ዘንግ መሆን ይገባዋል፡፡ የመንግሥትም ሆነ የግሉ ሚድያ የመታጠን አስተሳሰቦችን ማቀንቀን አለባቸው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ለውጡን (መታጠኑን) መታደሱን የማያቋርጥ ማድረግ ነው፡፡

ያለንበት ዘመን ዓለም እየደረሰችበት ያለውን የቴክኖሎጂ የዕድገት ደረጃ እግር በእግር በመከተል የአገልግሎታችን፣ የግብርናችንንና እንዲሁም የኢንዱስትሪ ዕድገታችንን የምናዘምንበት፣ ዜጎቻችንን በወቅቱ ዕውቀትና ክህሎት የምናስታጥቅበት፣ ከዓለም አቀፍ የምርት ሥርዓት ጋር ለመጣጣም የትብብር ደረጃችንን እጅግ ከፍ የምናደርግበት፣ እንደ የአየር ንብረት ለውጥ ካሉ ድንበር የለሽ ዓለም አቀፋዊ ችግሮችን ለመቋቋም ልዩ ጥረት የምናደርግበት፣ ከሕዝብ ብዛት መጨመር ጋር ተያይዞ የሚመጡ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት የማያቋርጥ ጥረት የምናደርግበት ጊዜ ነው፡፡ ይኼ ሲሆን ብቻ ነው ዘላቂ ልማት ማምጣት የሚቻለው፡፡

ዘላቂ ዕድገትን ለማምጣት ዛሬ ላይ ያለና ለስኬት የሚያበቃን የለውጥ ስትራቴጂን የራስ በማድረግ የዕድገት መሰላሉን መውጣት ይቻላል፡፡ ለዚህም ዜጎች ለተለዋዋጩ ዓለም ራሳቸውን በማዘጋጀት ተራራውን መውጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም ታዳጊ አገሮች ፍትሐዊ ዕድገትን ለሕዝቦቻቸው ለማጎናፀፍ ዘርፈ ብዙ መዋቅራዊ ለውጦችን ማስፋፋት አለባቸው፡፡

ለእዚህም ዓለም እየተጓዘበት ባለበት መንገድ ራስን ማስገባት የግዴታ ነው፡፡ ከድኅነት ለመውጣትም ራስን ከጊዜው የዓለም ሁኔታ ጋር ማስማማት የማያቋርጥ እንቅስቃሴ በሆነበት በእዚህ ዘመን፣ ባለፈውና በተከናወነው ታሪክ በትዝታና በቁዘማ ቂም በቀልን እያኘኩ መኖር የትም አያደርስም፡፡

አገራዊ ፖሊሲዎቻችን ከዓለም አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታዎችና እንደ አየር ንብረት ለውጥ ካሉ ድንበር የለሽ ተፅዕኖ አድራጊዎች ጋር የተጣጣመ መሆን አለበት፡፡ ከላይ የተጠቀሱት አንገራጋጮች መስመር እየያዙና እየሰከኑ ሲሄዱ ዜጎች በሰላምና በደስታ መግባትና መውጣት ይጀምራሉ፡፡ ለአገራቸውና ለወደፊቱ ትውልድም የተሻለ ነገር ጥለው ያልፋሉ፡፡ በመሆኑም አንገራጋጮቹን በማንገራገጭ ሽግግራዊ መንገራገጩን ጤናማ ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው መፍትሔ ውይይት፣ ውይይትና ውይይት ብቻ ናቸው፡፡ መታደስ (መታጠን) የማያቋርጥ እንቅስቃሴ መሆን አለበት፡፡

ከአዘጋጁ፡-ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው leulsegedg@yahoo.com. ማግኘት ይቻላል፡፡

         

 

Standard (Image)

“ጥልቅ ተሃድሶ” በወጣቱ ላይ ያለው አመለካከት

$
0
0

 በደጀኔ አሰፋ ዳ.

እንደምን ሰነበታችሁ? በአካዳሚክ ዓለሙም ሆነ በፕሮግራም ቀረፃና ትግበራ በተሰማሩ ምሁራን  ዘንድ ታዳጊ ማን ነው ወጣት የሚባሉትስ ከስንት እስከ ስንት ዓመት ዕድሜ የምላቸው ናቸው? የሚሉት ጥያቄዎች አሁንም ድረስ አከራካሪ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የዕድሜ ወሰኑም በየአገሮቹና አኅጉራት በሚወጡ ቻርተሮች ከመለያየቱ ባሻገር፣ እንደየ ተቋማቱም ልዩነት አለው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአገራችን አጠቃላይ ሕዝብ ብዛት የወጣቱ ቁጥር ታዳጊዎችን ጨምሮ ከ45 በመቶ በላይ እንደሆነ በአሁኑ ወቅት እየወጡ ያሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይኼም አገራችን ኢትዮጵያ የወጣት አገር ናት የሚያስብል ሁኔታ ነው፡፡ እሰይ! እንኳንም የወጣት አገር ሆነች! ምክንያቱም ወጣት ማለት ያልተነካ ኃይል ነው፣ እምቅ ሀብት ነው፣ የአገር ተስፋ የአገር ተረካቢ ነው … ወዘተ፡፡  ‹‹ወጣት የነብር ጣት›› እንዲሉ! የወጣት ትርጉም ይኼ ሆኖ ሳለ በአገራችን በተለይም በመንግሥት ዘንድ ወጣትን በተመለከተ በደህናው ጊዜና በአስቸጋሪ ወቅቶች እየተሰጡ ያሉ ስሞችና አስተያየቶች እርስ በርስ የሚጣረሱ ከመሆናቸው በላይ ከዚህ የተለየም ሆኖ የሚስተዋልበት ሁኔታ አለ፡፡ የዚህ አጭር መጣጥፍ ዓላማም ይኼንን ጉዳይ ‹‹በወፍ በረር›› እየዳሰሰ ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ውጤትም በተዋረድ ለማሳየት ነው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች አገሮች ሁሉ የተለያዩ ሥርዓቶችን አስተናግዳለች፡፡ ብዙ ታሪክም ያላት አገር ናት፡፡ የወጣቱም እንዲሁ፡፡ በአገሪቱ በተከሰቱ ዋና ዋና ታሪካዊ ክስተቶች የወጣቱ ሚና ጉልህ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡ ምንም እንኳን በኢኮኖሚው ዘርፍ የመሪነት ሚና እንዳይጫወት በአገሪቱ የነበረው አስከፊ ድህነትና ሌሎች ብርቱ ተግዳሮቶች ተጭነውት የነበረ ቢሆንም፣ እነዚህን ሁኔታዎች ለመለወጥ ግን አንድም ቀን አልቦዘነም፡፡ በተለይም በፖለቲካውና በማኅበራዊ ዘርፎች የሾፌሩን ቦታ በመያዝ በነፍሱ ተወራርዶ በሕይወቱ ታላቅ ተጋድሎን እየታገለ አሌ የማይባል መስዋዕትነትን ከፍሏል፡፡ ያ ትውልድ በኢትዮጵያ! ከታሪክ የምንረዳውና አንድ በጋራ የምንስማማበት ሀቅ ቢኖር በየትኛውም ዘመን የነበረው የአገሪቱ ወጣት ለከርሱ ያደረ ራስ ወዳድ እንዳልነበር ነው፡፡ ይልቅ ዘር፣ ነገድ ሳይለይ ለተጨቆነው ጭሰኛ፣ ላብ አደር፣ ለተበዘበዘው፣ ለተረገጠው፣ መብቱ ላልተከበረለት የትኛውም የአገሩ ሕዝብ የቆመ፣ የታገለና ያታገለ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ወጣት የራሱን ዳቦ ለማወፈር የታገለ አይመስለኝም፡፡ ለዚህ እውነት እንደ ማስረጃነት የሚያገለግሉን ታጋዮች በዙሪያችን እንደ ደመና ሳይሆን በተጨባጭ በሕይወት አሉ፡፡ ካስፈለገ እነሱ ይናገሩ፣ ካልሆነም የተሰውት ታሪካቸው ድምፅ አውጥቶ ይመሰክራል፡፡

እንደ አለመታደል ሆኖ ባለፈው የወታደራዊ ደርግ ሥርዓት ወጣቱ ‹‹ብሔራዊ ወታደር” ከመሆን የዘለለ ዕድል ፈንታ አልነበረውም፡፡ በዘመኑ ወጣት ማለት ወታደር፣ ወታደር ማለት ወጣት እንደሆነ ሊታሰብ በሚችል ደረጃ በዩኒቨርሲቲ ያሉ ወጣቶችን ጭምር ወታደር ለማድረግ የወቅቱ ፕሬዚዳንትና ካድሬዎቻቸው ምን ዓይነት ማራኪና አማላይ ዲስኩር ያደርጉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ወጣቱም “ክብር ከብር ይበልጣል” በሚል እሳቤ ይመስላል ዩኒቨርሲቲውን ጥሎ ወደ ብላቴ ያቀናው፡፡ በአጠቃላይ በዘመኑ ስንት ወጣት ረገፈ? ስንቱስ ህልሙ ተኮላሸ? ይኼም ቢሆን እንኳን ያመነበት በውዴታ ያላመነበት በግዴታም ቢሆን ለአገር እንጂ ለዳቦ የተከፈለ አልነበረም፡፡ ያለፈው ታሪክ አሳዛኝ ቢሆንም፡፡

እነዚህን እንደ መግቢያ ስጠቅስ ታሪክን የኋሊት ለመተረክ ሳይሆን፣ ባለፉት ሥርዓቶች የነበሩ መንግሥታት ምንም እንኳን እንደ ተመልካቹ ጥሩም ባይባሉ መጥፎውን ወደ ጎን ትተን ለወጣቱ የነበራቸውን ቦታና ክብር ለማሳየት ነው፡፡ በአፄውም ዘመን ወጣቱ በተለይም ተማሪው ምንኛ ይከበር እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ሆኖም በአንዳንዶቻችን ዘንድ ያለፉት መንግሥታት ለራሳቸው ጥቅም እንጂ ለወጣቱ አስበው አልነበረም የሚል ሐሳብ ሊኖር እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ እዚህ ላይ ግን ማሳየት የተፈለገው ዋና ጉዳይ ወጣቱን የሚያዩበትን ዕይታ ብቻ ነው፡፡ ካስፈለገም ግን ለራሳቸው ጥቅምም እንኳን ቢሆን (ለጥሩም ይሁን ለመጥፎ) ወጣቱን ማነሳሳትና መጠቀም ከቻሉ ጉብዝና እንጂ ሌላ ሊባል የሚችል አይመስለኝም፡፡

ከዚህ አንፃር ወጣቱን በተመለከተ አሁን ባለው መንግሥታችን በየወቅቱ እየተንፀባረቀ ያለው የተለያየ አመለካከት እንዴት ይመዘናል? ምን ዓይነትስ ውጤት ይኖረዋል? የሚለውን ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ በተለይም በደህና ጊዜያት ምርጫን ጨምሮ መንግሥት ስለወጣቱ የሚናገረው ለምሳሌ ወጣቱ የልማት ኃይል እንደሆነ፣ ያለ ወጣቱ ተሳትፎ አገር ማደግ እንደማትችል… ወዘተ ሲገልጽ ደስ እንደምንሰኝ ሁሉ በአንፃሩ አገሪቱ የሆነ አጣብቂኝ ጊዜ ካሳለፈች በኋላ ስለወጣቱ የሚነዙ ደስ የማይሉ ዲስኩሮችና መጠሪያ ስሞች እንደ ገደል ማሚቱ አንዱ ካንዱ እየተቀባበሉ ወጣቱን ሲወቅጡት ማየት እንዴት ያማል መሰላችሁ? መቼስ አገር ሲባል ሺሕ ተሚሊዮን መልካም አጋጣሚዎች ቢኖሩትም ሺሕ ተቢሊዮን ተግዳሮቶች አያጡትም፡፡ መንግሥትም ጥቂት የሚባሉትን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም ህልቆ መሳፍርት የሌላቸውን ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ይጥራል፡፡ በእዚህ ረገድ ወጣቱ አገሪቱ ካላት መልካም አጋጣሚዎች አንዱ እንደሆነ ሊታሰብ የሚገባ ይሆናል፡፡ ለዚህም ይመስለኛል መንግሥት በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወጣትን በሚመለከት ራሳቸውን የቻሉ ፖሊሲዎችን እየቀረፀ ለመተግበር እየሞከረ ያለው፡፡ ሌሎችም ጥቂት ማሳያዎች ይኖራሉ፡፡ አሁን የተመደበውን 10 ቢሊዮን ብር ጨምሮ ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ ጅምሮች በቂ እንዳልሆኑ ቢታወቅም እንደ መልካም ጅምር ሊያድጉና ሊበረታቱ የሚገባቸው እንደሆኑ ግን ዕሙን ነው፡፡

ይኼ ሆኖ ሳለ ወጣቱን በሚመለከት ከሚሰነዘሩ አስተያየቶችና ስሞች መካከል ለእኔ አሳዛኝ ሆነው ካገኘኋቸው መካከል ሁለቱን ብቻ ለንፅፅር በሚያመች መልኩ በከተማ ላለው ወጣት የወጣለት ስምና በገጠር ወይም በክፍለ አገር ላለው ወጣት የተመረጠለትን የዳቦ ስም እጠቅሳለሁ፡፡ የመጀመርያው ስም ምርጫ “1997 ዓ.ም.”ን ተከትሎ በተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኘው ወጣት የወጣለት ‹‹የወል ስም›› ነው፡፡ ‹‹ደገኛ ቦዘኔ››!በእርግጥ ይኼ መጠሪያ ሁለት ቃላትን ይዟል፡፡ ቅፅል የሆነው ‹‹አደገኛ›› የሚለውንና ስም (Noun) የሆነውን ‹‹ቦዘኔ›› የሚለውን፡፡ ከእዚህ መረዳት የሚቻለው መንግሥት በአዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ‹‹ቦዘኔ›› ወይም ሥራ ፈት አሊያም ሥራ አጥ እንዳለ ያውቅ ነበር ማለት ነው፡፡ ቢያውቅም ግን ቦዘኔነትን ለማስቀረት በቂ ጥረት ሲያደርግ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ቦዘኔ ተብሎ የተፈረጀው በፖለቲካ አነጋገር ለሥርዓቱ አደጋ በሚሆን ደረጃ ወደ አደገኝነት እስካልተሸጋገረ ድረስ እንደማለት ያስመስልበታል፡፡ ሊያስጨንቀው የሚገባው ግን ቦዘኔነትን እንዴት ማስወገድ (መቀነስ) እንዳለበት ነበር፡፡

ለዚያም ይመስላል ወጣቱ “ቦዘኔ” መሆኑ፣ መደረጉ ወይም መባሉ ሳያንሰው “አደገኛ ቦዘኔ” የሚል ድሪቶን የተከናነበው፡፡ በዚህም ስንት ወጣት አዘነ፣ ሞራሉ ተጎዳ፣ ስንቱስ ስለ አገሩ ያለውን አመለካከት ለወጠ … ወዘተ ቤት ይቁጠረው፡፡ እሺ… መንግሥት የወጣቱን መጎዳት ወደ ጎን ቢተወውና ከቁብም ባይቆጥረው ይኼን “አደገኛ ቦዘኔ” የሚለውን ቃል ግን ሌሎች አገር በቀል ፓርቲዎች እንዴት ተጠቀሙበት የሚለውን እንኳን እንደ ገዥ ፓርቲ ምንም ትምህርት የወሰደበት አይመስልም፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ ዓይነት አመለካከት በወጣቱ ሰብዕና ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ አለው የሚል ጥናት ቢሠራ ምንኛ ደስ ባለኝ፡፡ እንደኔ ግምት ግን “አደገኛ ቦዘኔ” ከሚለው መጠሪያ በኃላ የሥራ አጥ ቁጥር ያሻቀበ ይመስለኛል፡፡ ‹ላይክ አትራክትስ ላይክ› እንዲሉ! በመጽሐፍ ቅዱስም በጥብቅ ከተከለከሉ ስድቦች (በተለይም ሕፃናትና ወጣቶች እንዳይሰደቡ) መካከል “ደደብ” አትበል የሚለው ነው፡፡ ለምሳሌ ልጅህን ዛሬ “ደደብ” ብትለው ነገ ስማርት “ደደብ” ወይም ሰቃይ “ደደብ” ሆኖ ታገኘዋለህ እንደ ማለት ነው፡፡ እኛ ደግሞ ስማርት ፎን እንጂ ‹‹ስማርት …›› አንሻም፡፡

ሌላኛው የጅምላ ፍረጃ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት ተከትሎ በክልልና በገጠር ላሉ ወጣቶች የወጣላቸው መጠሪያ ነው፡፡ የጥፋት ኃይል፣ የኤርትራ ተላላኪ፣ የጥፋት አጀንዳ ተሸካሚ፤… ወዘተ፡፡ “አደገኛ ቦዘኔ” ከሚለው ይልቅ ይኼኛውን የከፋ የሚያደርገው የውጭ ኃይሎች ከርቀት ሆነው የሚያበሩትና የሚያጠፉት እንጂ በራሱ የሚያስብና የሚያመዛዝን አይደለም የሚል አንድምታ ስላለው ነው፡፡ ይኼ ደግሞ እንዴት ጎጂ እንደሆነ አትጠይቁኝ፡፡ ወጣቱ አመዛዛኝ አይደለም ዝም ብሎ የሚነዳ ነው ተብሎ ከታመነበት ደግሞ ይኼ አባባል ራሱ መንግሥትን በሌላ መንገድ ተጠያቂ የሚያደርገው ይሆናል፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት ወጣት በዚህ ዘመን ለመፈጠሩ ከሥርዓቱ የበለጠ ተጠያቂ የሚሆን አለ ብየ አላስብም፡፡

አንድን ሰው አንተ ተሳስተሃልና ከመንገድህ ተመለስ ብሎ መምከርም ሆነ መገሰፅ ያባት ነው፡፡ መንግሥትም የሕዝብ አባት ነውና መገሰፅ፣ መምከር፣ ማሰር፣ ማስተማር፣ ወዘተ የሚቻልበት ሕገ መንግሥታዊ መብትም ግዴታም አለበት፡፡ ታዲያ ይኼን ሁሉ ማድረግ የሚችልበት ሥልጣንና አቅም በእጁ እያለው በጅምላ ለዚያውም አሉታዊ አንድምታ ባለው ሁኔታ ልጆቹን ስለምን ይጠራቸዋል፡፡ ለምሳሌ ከግርግሩ በኃላ በዚህ ዓመት የመጀመርያ የፓርላማ ስብሰባ ወቅት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ወጣቱን በሚመለከት የተናገሩትን ንግግርም ሆነ ከዚያ ቀጥሎ የሰማኋቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክቶች፣ ብሎም ሌሎች ጎምቱ ባለሥልጣናት በየሚዲያው ሲናገሩ የነበሩት ነገር ልቤን አስከፍቶታል፡፡ ጠቅለል አድርጌ ላቅርብው የሁሉም ንግግር አብዛኛው ወጣቱ የኢኮኖሚ ችግር እንዳለበትና ሥራ አጥነት እንደጨመረ ያሳይ ነበር፡፡ ይኼንንም ክፍተት የውጭ የጥፋት ኃይሎች ወጣቱን በገንዘብ እየደለሉ የጥፋት ተልዕኮን እንዳሸከሙትና የእነሱ ተላላኪ፣… ወዘተ እንደሆነ ያትታል፡፡ ለዚህም ክቡር ፕሬዚዳንቱ፣ “ለወጣቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ የሚሆን 10 ቢሊዮን ብር መድበናል፤” ብለው ተናገሩ፡፡ እዚህ ላይ መንግሥት ሊመልሳቸው የሚገቡ ጥያቄዎችን ያስነሳል፡፡ እነኝህም፡-

1ኛ) ይኼ 10 ቢሊዮን ብር የተበጀተው የወጣቱ ችግር የኢኮኖሚ ችግር ብቻ እንደሆነ በጥናት ተረጋግጦ ለዚያ ማስፈጸሚያ የሚሆን ነው? ወይስ…

2ኛ) የውጭ ኃይሎች ወጣቱን በብር ስለገዙት (ስለደለሉት) እኔስ ከማን አንሼ ብሎ መንግሥት አቅም እንዳለው ለማሳየትና ወጣቱን በበጀት ለማባበል? ወይስ….

3ኛ) የጥፋት ኃይል፣ ተላላኪ፣ ተሸካሚ፣ … ወዘተ በሚል አመለካከት ወጣቱን እያየንና የወጣቱን ሞራልና ሰብዕና እየነካን በዚህ በጀት ተፈላጊውን ለውጥ ማምጣት እንችላለን? የሚሉትን ጥያቄዎች ያጠቃልላል፡፡

ለእነዚህ ጥያቄዎች መልሶች ምንም ይሁን ምን ከኮሙዩኒኬሽን አንፃር ግን መንግሥት በብዙ መንገድ የሚታዩ ግልጽ ክፍተቶች እንዳሉበት ከቀድሞ ጊዜያት ጀምሮ ይስተዋላል፡፡ ለአብነት የአክሱም ሐውልትን፣ ሰንደቅ ዓላማን፣ የፖለቲካ ታማኝነትን፣ የኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ ጥያቄን (ሕዝብ ስል ወይም ወጣቱ ስል ቁጥሩን አይገልጽም)፤… ወዘተ በሚመለከቱ ጉዳዮች መንግሥት የገለጽበት ሁኔታ (ትክክል ናቸው ተብሎ በፓርቲው ቢታመን እንኳን) ትክክል (አዋጭ) ነበር ማለት አያስደፍርም፡፡ ምክንያቱም ለአብዛኛው ሕዝብ በሚመጥን፣ ሊረዳው በሚችል፣ አሊያም በሚያሳምንና በተገቢው ክብር የቀረቡ ባለመሆናቸው ቅሬታን መፍጠራቸው አልቀረምና ነው፡፡ ከእዚህ አንፃር መንግሥት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበና በሕዝቡ ዘንድ መልካም ስሜትን ሊፈጥር በሚችል መልኩ ተግባቦትን መፍጠር የሚችሉ ጎበዝ (ንቁ) የተግባቦት አመቻቾች (Spin Doctors) እንደሚሏቸው ዓይነት ሰዎችም ሆኑ ተቋማት ዕጦት ያለበት ይመስላል፡፡ ቢያንስ እውነት የሆነን ነገር እንኳን የሚገልጽበትም ሆነ ሕዝቡን የሚያስረዳበት ቋንቋና መንገድ የበለጠ የሚያናድድ እንጂ የሚያረጋጋ ሲሆን አይስተዋልም፡፡

አንድ ምሳሌ ልጥቀስና ልጨርስ፡፡ ‹‹እነሆ ዘሪ ዘርን ሊዘራ ወጣ፡፡ ዘሩንም በጭንጫ፣ በእሾህ ላይና በመልካም መሬት ላይ ዘራው፡፡ በመልካም መሬት የተዘራው 100 እጥፍ፣ በእሾህ ላይ የተዘራው 60 እጥፍ፣ በጭንጫ ላይ የተዘራው 30 እጥፍ አፈራ፤›› ይላል፡፡ በእዚህ ምሳሌ ዘሪው መንግሥት ነው ብንል፣ ዘሩ በጀት ቢሆን መሬቱ (ማሳው) ደግሞ ተቀባዩ ወይም ተዳራሹ የኅብረተሰብ ክፍል ይሆናል፡፡ ከእዚህ ጋር ተያይዞ መጠየቅ ያለበት ቢኖር ዘሪው ይኼንን ዘር (በጀት) በምን ዓይነት መሬት ላይ ነው ለማፍሰስ ያሰበው የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ እንደኔ ዕይታ ከሆነ ዘሩ ከመዘራቱ በፊት ማሳውን የማረስም ሆነ የማለስለስ ግዴታ በዘሪው ላይ የወደቀ ይመስለኛል፡፡ ማረስና ማለስለስ ደግሞ ቢያንስ የመሬቱን ባህሪ ማወቅና እንደ ባህሪው ማስተናገድ ይጠይቃል፡፡ ካልሆነ ግን አሥር ቢሊዮን አይደለም መቶ ቢሊዮኖች ብንመድብ እንኳንስ ልናተርፍ የወጣውን ገንዘብ ያህል ምርት መሰብሰብ የምንችል አይመስለኝም፡፡ ብርም ከክብር፣ ፍትፍትም ከፊት አይቀድምም፡፡ ለዚያም ነው የአገሬ ሰው “ከፍትፍቱ ፊቱ” የሚለው፡፡ ስለዚህም በየትኛውም ተቋምና የሥልጣን (የአገልግሎት ሰጪነት) እርከን የምንገኝ ሁላችንም በወጣቱ ዙሪያ ጥልቅ ተሃድሶ ያስፈልገናል ብዬ አምናለሁ፡፡

‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ከእዚህ አንፃር ምን እንደሆኑ ለመጥቀስ እሞክራለሁ፡፡ ያሉትን መልካም እሴቶች ማንበር፣ አንዳንድ ክፍተቶችን በመሙላትና መሠረታዊ ታሳቢዎችን በመቀየር አዳዲስ ሥልቶችን መተለም ከብዙ በጥቂቱ የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ ሕዝቡን በተለይም ወጣቱን በሚመጥን ሁኔታ በጥሩ ኮሙዩኒኬሽን (Participatory Communication) ልቡን መሳብ፣ ቀልቡን መግዛት፣ ሞራሉንና ተስፋውን ማነሳሳትና ሰብዕናውን በመልካም ባህሪያት ማነፅ ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ አገሩን እንዲወድ፣ ዴሞክራሲያዊና ሲቪክ አስተሳሰብን እንዲላበስ፣ የመሪነት አቅሙን የማሳደግ፣ ሞዴል የወጣት መሪዎች እንዲወጡ የማመቻቸት፣  ደጋፊም ይሁን ተቃዋሚ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማስጠበቅና ማስቀጠል የሚችልበትን ሲቪክ ከባቢ የመፍጠር፣ የባይተዋርነት ስሜትን አጥፍቶ የያገባኛል ስሜትን እንዲያጎለብት፣ በሚመለከተው ጉዳዮች እንዲሳተፍና የውሳኔ ሰጪነት ሚናውን የማረጋገጥ፣… ወዘተ ከመንግሥት በትንሹ ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም አገሪቱ የወጣት አገር ናት፡፡ ያሉ መልካም ጅምሮችንም ሆነ በእዚህ ሥርዓት የመጡ ለውጦችን ይዞ ማስቀጠል የሚችለውም እሱ ነውና! ለእዚህ ደግሞ የመጀመርያው ቁልፉ ነገር ወጣቱን በሚመለከት በጎ አመለካከት፣ ቅንነትና በወጣቱ ላይ ሊኖራቸው በሚገባ ፅኑ ዕምነት ዙሪያ በተቋማቶቻችን ማረጋጋጥን (Institutional Mainstreaming) ይሻል፡፡ ይኼ ደግሞ ከውጥኑ መንግሥት ወጣቱን የሚያስብበት መንገድ (Perception) መሠረታዊ በሚባል ደረጃ መለወጥን ይጠይቃል፡፡ አስተሳሰብ የተሃድሶ መጀመርያ ነውና! ወጣቱ ቢያጠፋ (አጥፊ ነው) ቢባል እንኳን መንግሥት በልበ ሰፊነት እየታገሰ፣ የነገዋን አገር ከሩቅ እየተመለከተ፣ እንደ መልካም እረኛ ወደ ለመለመው መስክ ሊያሰማራ እንጂ በፖለቲካዊ ቃላት መሳደብና ማንኳሰስ አይገባውም፡፡ በተለይ በሚዲያ! እዚህ ላይ ከወጣቱ የሚጠበቁ ነገሮች የሉም ለማለት ሳይሆን በሌላ ጊዜ የምመለስበት ሰፊ ጉዳይ ስለሆነና የእዚህ ጽሑፍ ዓላማ ይኼኛው ስለሆነ ነው፡፡ ቸር እንሰንብት!

ከአዘጋጁ፡-ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን ኢሜይል አድራሻቸው djmamaru@gmail.com.  ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

 

Standard (Image)

ፊደል ካስትሮ የዓለም የነፃነት ታጋዮች ትዕምርት

$
0
0

 

ፊደል ካስትሮ

የዓለም የነፃነት ታጋዮች ትዕምርት

በሞላ ዘገየ፣ የሕግ አማካሪና ጠበቃ

የታላቁ አብዮተኛና የነፃነት ታጋይ የፊደል ካስትሮ ሕልፈተ ሕይወት ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ፣ በእኚህ የሃያኛው ክፍለ ዘመን የነፃነት ተጋድሎ ትዕምርት (Icon) ሕይወት ዙሪያ ሰፊ ዘገባና ትንታኔ ሲቀርብ ሰንብቷል፡፡ ነገሩ የጀግና ሞቱ ልደቱ እንደሚባለው ነው፡፡ ፊደል በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ካነጋገሩትም በላይ ካለፉ በኋላ ስለእሳቸው ብዙ እየተባለ፣ ብዙ እየተተነተነ ይገኛል፡፡ አንዳንዶች በተለይ ምዕራባውያኑ ፊደል ካስትሮ አምባገነነን ነበሩ ብለው ሲከሷቸው፣ የተቀረው ዓለም አብዮተኛነታቸውንና የነፃነት ታጋይ መሆናቸውን ያስተጋባል፡፡ እኔ በበኩሌ ዝቅ ብዬ በምትጠቅሳቸው መሠረታዊ መነሻዎች ምክንያት ፊደል ካስትሮ ታላቅ የነፃነት ታጋይና አብዮተኛ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የነፃነት ትግሎች በተቀጣጠሉበትና በየአካባቢው አብዮቶች በሚከሰቱበት ዘመን፣ በተለይ በሃያኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ (1960ዎቹና 70ዎቹ) ካስትሮ፣ ቸጉቬራና ሆቺሚኒ ከሁሉም ታጋዮች አንደበት የማይጠፉ፣ በርካታ የነፃነት ትግሎችና አብዮቶች እንዲቀሰቀሱና እንዲቀጣጠሉ መንገድ የጠረጉ የነፃነት ተጋድሎ ትዕምርቶች ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን በተለያዩ ጎራዎች የተሠለፈው፣ በተለምዶ “ያ ትውልድ” እየተባለ የሚጠራው የአገራችን አብዮታዊ ትውልድ፣ ለእነዚህ የነፃነት ታጋዮች ከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት ነበረው፡፡ ጽሑፎቻቸውን አንብቧል፣ መንገዳቸውን ለመከተልም ሞክሯል፡፡ በዚያ ሒደት አተረፍን ወይስ ከሰርን የሚለውን ጥያቄ ለጊዜው እናቆየውና ብዙዎቻችን የእነ ካስትሮ አድናቂዎችና የእነሱ ፈለግ ተከታዮች እንደነበርን ግን በሕይወት ያለነው ምስክሮች ነን፡፡  

ለዚህች ጽሑፍ መነሻ ከሆኑኝ ምክንያቶች ውስጥ ዕድሜያቸውን ሙሉ ከሚገፉትና ከሚጠቁት ወገኖች ጎን ቆመው በመታገል ላሳለፉት ካስትሮ ያለኝ ታላቅ አክብሮት የሚጠቀስ ሲሆን፣ በጽሑፌ የሶማሊያ ተስፋፊ አገዛዝ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ካስትሮና የኩባ ሕዝብ ለአገራችን የዋሉትን ውለታ ለመዘከር፣ በተለይ ደግሞ ከጦርነቱ በኋላ በነበረው የጅጅጋ መልሶ ማቋቋም መርሐ ግብር ሒደቱን በአውራጃ አስተዳዳሪነትና በአስተባባሪነት ስመራ የኩባ ሠራዊት አባላት በመልሶ ማቋቋም ሥራው የተጫወቱትን ሚና በቅርብ ስለማውቅ፣ የተወሰኑ ትውስታዎችን ለማጋራትና በሥራ አጋጣሚ ወደ ኩባ የመሄድ ዕድል አጋጥሞኝ ስለነበር በጉዞዬ እነ ካስትሮ የመሠረቱት ሥርዓት ለኩባ ሕዝብ ያስገኘውን ትሩፋት በወፍ በረር የማየት ዕድል አግኝቼ ስለነበር፣ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ አንዳንድ ነጥቦችን ለአንባቢያን ላጋራ እፈልጋለሁ፡፡

ፊደል የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለውለታ

ፊደል ካስትሮና የኩባ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባለውለታ ናቸው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያስታውሰው በዚያድ ባሬ የሚመራው የሶማሊያ ተስፋፊ አገዛዝ ዓለም አቀፍ ሕግጋትንና የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ቻርተር ወደጎን ብሎ፣ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ጥሶ አገራችን በወረረበት በዚያ እጅግ አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ከቆሙት ጥቂት አገሮች መካከል ኩባ በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች፡፡ ኢትዮጵያ በአብዮቱና አብዮቱን እንመራዋለን በሚሉ ኃይሎች የእርስ በርስ ሽኩቻ ምክንያት ተዳክማለች በሚል ሥሌት ከሰኔ ወር 1969 ዓ.ም. ጀምሮ በአገራችን ላይ ለመስፋፋት ወረራ የጀመረው የሶማሊያ ወራሪ ሠራዊት፣ እስከ ኅዳር ወር 1970 ዓ.ም. ድረስ ለስድስት ወራት በተለያዩ አቅጣጫዎች በከፈተው ጥቃት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ አካባቢዎችን በቁጥጥር ሥር ከማድረጉም በላይ፣ በንብረትና በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ ነበር፡፡

በተስፋፊው የዚያድ ባሬ መንግሥት አሻፈረኝ ባይነት ምክንያት ሳይሳካ ቢቀርም፣ ሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ወደ አላስፈላጊ ጦርነት እንዳይገቡና የሰው ሕይወት በከንቱ እንዳይጠፋ ለማድረግ ፊደል ካስትሮ ከደቡብ የመን መሪዎች ጋር በመሆን፣ የኢትዮጵያና የሶማሊያ መሪዎች ችግራቸውን በውይይትና በድርድር እንዲፈቱት ለመሸምገል ሞክረዋል፡፡ አወንታዊ ውጤት አልተገኘም፡፡

የሶማሊያ መንግሥት የሶሻሊዝምን ፈለግ እንደሚከተል የሚምልና የሚገዘት፣ ነገር ግን እጅግ ኋላቀርና ተስፋፊ የሆነ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የሚከተል መንግሥት ነበር፡፡ በአንድ በኩል ተራማጅ በመምሰል ከሶሻሊስቱ ጎራ፣ በተለይ ከሶቪየት ኅብረት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ለመመሥረት እየሠራ፣ እዚያው በዚያው ከአሜሪካና ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጉያ ውስጥ ለመግባት የሚፈልግ አገዛዝ እንደነበረም የሚታወቅ ነው፡፡ በኋላ እንደታየውም ሶሻሊስት አገሮች በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል የሚደረገውን ጦርነት እንደማይደግፉ ጠቅሰው፣ የሚሻለው ችግሩን በሰላማዊ መንገድ መፍታት መሆኑን በገለጹለት ማግሥት አቅጣጫውን ወደ ዓረብ አገሮችና አሜሪካ አዙሯል፡፡ 

ይህን የዚያድ ባሬን መንታ አካሄድና መሰሪነት በሚገባ የተገነዘቡት ፊደል ካስትሮ፣ በዚያ ብዙዎች የሶማሊያን አሸናፊነት በፍፁም እርግጠኛነት በሚናገሩበትና አገራችን ችግር ላይ በነበረችበት እጅግ ፈታኝ ወቅት ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጋር ሆነው የተቃጣብንን ወረራ ለመመከት ቁርጠኛ አቋም በመያዝ በርካታ ኩባውያን ወታደሮችን፣ ወታደራዊ ቁሳቁሶችንና የሕክምና ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ልከዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያስታውሰው በዚያ በተስፋፊው ሠራዊት የተቃጣብንን ወረራ ለመመከት በተደረገው ከፍተኛ መስዋዕትነት የጠየቀ ጦርነት ኩባውያን በቆራጥነት ተሳትፈዋል፡፡ ከመካከላቸውም ብዙ ወታደሮች መስዋዕት ሆነዋል፡፡ የኩባ የሕክምና ባለሙያዎችም ቢሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

ጦርነቱን በድል ከተወጣን በኋላ የጅጅጋን ከተማ እንደገና መልሶ መገንባትና ማልማት ትልቅ ብሔራዊ አጀንዳ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ጅጅጋ ከተማን መልሶ ለማቋቋም ብሔራዊ ጥሪ አድርጎ ከፍተኛ ርብርብ በሚያደረግበት ወቅት በኮሎኔል ፔሪ  የሚመራው የኩባ ጦር ያደረገው አስተዋጽኦ በጣም ከፍተኛ እንደነበር የዓይን ምስክር ነኝ፡፡ ከጦርነቱ በኋላ የጅጅጋ አስተዳዳሪና የመልሶ ማቋቋሙ አስተባባሪ ስለነበርኩ፣ ኩባውያን በጦርነት የደቀቀውን አካባቢ መልሶ ለመገንባት በተደረገው ጥረት ውስጥ ያደረጉት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን በሒደቱ የተሳተፍን ሁሉ በአድናቆት የምናስታውሰው ነው፡፡ በዚያ ፍፁም የአገርና የሕዝብ ፍቅር በተሞላበት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያውያንና በኩባውያን ትብብር የተገነቡትን መሠረተ ልማቶች የኢትዮጵያ ሶማሊያ ሕዝብ ያስታውሳቸዋል፡፡ በበኩሌ በዚያ የታሪክ አጋጣሚ ከበርካታ ኩባውያን ጋር የመገናኘትና የመሥራት ዕድል አጋጥሞኝ ስለነበር ኩባውያን ምን ያህል ግልጽ፣ ቅንና ሥራ ወዳዶች እንደሆኑ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ከእነሱ ጋር ያሳለፍኩትን ጊዜም በልዩ ሁኔታ አስታውሰዋለሁ፡፡

በእርግጥ የኩባ ድጋፍና አስተዋጽኦ በዚህ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ በአብዮቱ ዘመን በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች ልዩ ልዩ መስኮች ሁኔታዎችን ለማሻሻልና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማስፋት ባደረግናቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ የኩባውያን ድጋፍ ቀላል ግምት የሚሰጠው አልበረም፡፡ በርካታ ኩባውያን የጤና ባለሙያዎች፣ የእንስሳት ሐኪሞች፣ መምህራን፣ ወዘተ. ወደ አገራችን መጥተው የልማት ሥራዎቻችንን ደግፈዋል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የፊደል ካስትሮ መንግሥት በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ምክንያት ወላጆቻቸውን ላጡ ኢትዮጵያውያን ነፃ የትምህርት ዕድል በማመቻቸት አያሌ ኢትዮጵያውያን ወደ ኩባ አቅንተው በልዩ ልዩ መስኮች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በዚህ መርሐ ግብር አማካይነት ወደ ኩባ ሄደው ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ አገራቸው የተመለሱት ኢትዮጵያውያን የእኚህን የነፃነት ታጋይ ሕልፈተ ሕይወት አስመልክተው መታሰቢያ ዝግጅት ማድረጋቸውን በመስማቴ በእጅጉ ተደስቻለሁ፡፡ ውለታን አለመዘንጋት ታላቅነት ነው፡፡ ሊከበርም ይገባዋል፡፡ የፊደል ካስትሮና የኩባ ሕዝብ ውለታ ሁልጊዜም ሲታወስ ይኖራል፡፡

ይህን ክፍል ከመዝጋቴ በፊት አንድ ሊታወስ የሚገባውና የፊደል ካስትሮንና የመንግሥታቸውን አርቆ አሳቢነት የሚያሳይ ነጥብ ላንሳ፡፡ እንደሚታወቀው የሶማሊያ ተስፋፊ ኃይል ከተደመሰሰ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት “በምሥራቅ የተገኘው ድል በሰሜንም ይደገማል” በማለት ትኩረቱን ወደ ሰሜን፣ በተለይም ወደ ኤርትራ አድርጎ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በምሥራቅ ባገኘው ድል ተበረታቶ፣ አማፂያኑንም በተመሳሳይ ሁኔታ ለማንበርከክ የሶሻሊስት አገሮች የጦር መሣሪያና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርጉለት ቢጠይቅም፣ የኩባ መንግሥት ጉዳዩ የእርስ በርስ ጦርነት መሆኑን አስታውሶ እንደዚያ ባለ ጦርነት እንደማይሳተፍ አቋሙን ግልጽ አድርጓል፡፡ ከዚህም በላይ ብዙም ዝርዝር መረጃ ባይኖረኝም፣ ካስትሮ አማፂዎችንና መንግሥትን ለመሸምገልም ሙከራ ሳያደርጉ የቀሩ አይመስለኝም፡፡ በእኔ አስተያየት በወቅቱ የኩባ መንግሥት የወሰደው አቋም፣ ማለትም በውስጥ ጉዳያችሁ አንገባም ማለቱ እጅግ የሚያስደንቅ አቋም ነው፡፡ በአንድ ሕዝብ መሀል ገብተን አናቦካም ማለታቸው ሲሆን፣ ይህም ከቆሙለት የነፃነት ትግል አንፃር ትክክለኛ አቋም ነው፡፡

ካስትሮ ለእምነታቸው ኖረው በእምነታቸው ፀንተው አለፉ

ፊደል ካስትሮ ለእምነታቸው ኖረው፣ በእምነታቸው ፀንተው ያለፉ ታላቅ የነፃነት ታጋይና አብዮተኛ ናቸው፡፡ “ለእምነታቸው ኖሩ፣ በእምነታቸው ፀንተው አለፉ” የምልበትን ምክንያት ትንሽ ዘርዘር አድርጌ ለማቅረብ ልሞክር፡፡ የሕይወት ታሪካቸው እንደሚያስረዳው እ.ኤ.አ ነሐሴ 13 ቀን 1926 ሃቫና ውስጥ የተወለዱት ፊደል፣ በስኳር አገዳ ልማት የተሰማሩና ደህና ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ልጅ ነበሩ፡፡ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ምርጥ ከሚባሉት የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ከተከታተሉ በኋላ፣ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ሃቫና ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት አጠናቀዋል፡፡ የነበራቸው ቤተሰባዊ መሠረትና የተከታተሉት የትምህርት መስክ በጊዜው የተሻለ ኑሮ መምራት የሚያስችላቸው ቢሆንም፣ ፊደል የመረጡት ይህን አልበረም፡፡ ጥቂቶች የቅንጦት ሕይወት የሚመሩባትና ብዙኃኑ ሕዝብ በከፍተኛ ችጋር ውስጥ የሚኖርባትን የዚያን ጊዜዋን ኩባን አዕምሯቸው ሊቀበላት አልፈቀደም፡፡ የጥብቅና ፈቃድ አውጥተው ለድሆች ለመቆም ቢሰማሩም  ብዙም ሳይቆይ እንዲዘጋ ሆኗል፡፡

ፊደል ገና ከወጣትነታቸው ጊዜ ጀምሮ የላቲን አሜሪካ አምባገነንና የአሜሪካ አሻንጉሊት የሆኑ መሪዎችን ለማስወገድ፣ በተለይ የዶሚኒካን ሪፐብሊክና የኮሎምቢያን አምባገነናዊ መሪዎች ለማስወገድ በተደረጉት እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ይህ ገና ከወጣትነት ዘመናቸው ጀምሮ የነበራቸው ከተጠቁትና ከተገፉት ጋር የመቆም ስሜት የባቲስታን አምባገነናዊ አገዛዝ አስወግደው ሥልጣን ከያዙ በኋላም ይበልጥ ተጠናክሮ በመቀጠሉ ፊደል በተለያዩ የላቲን አሜሪካ፣ የአፍሪካና እስያ አገሮች ውስጥ ሲካሄዱ ለነበሩ የነፃነት ትግሎች ወታደር፣ ወታደራዊ ቁሳቁስና የሕክምና ባለሙያዎችን በመላክ ዓለም ሲያስታውሰው የሚኖር አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በአፍሪካ የነበራቸውን ተሳትፎ በምሳሌነት ብንጠቅስ ለአልጄሪያ፣ ለኮንጎ ብራዛቪል፣ ለአንጎላና ለሞዛምቢክ የነፃነት ንቅናቄዎች ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካን የነፃነት ታጋዮች ሳይታክቱ ደግፈዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ የነፃነት ትግሉን የደገፉትን ኃይሎች ባመሰገኑበት አጋጣሚ፣ በግንባር ቀደምትነት የጠቀሱት የፊደል ካስትሮንና የኩባን ሕዝብ ውለታ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ምዕራባውያን በተለይ የአሜሪካ ተከታታይ መሪዎች እነ ማንዴላን በአሸባሪነት መዝገብ ውስጥ ሲያስቀምጧቸው፣ ካስትሮ የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ መሪዎችን በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በሞራል እየደገፉ ዘረኛውን የአፓርታይድ ሥርዓት በፅኑ ታግለዋል፡፡ ከሚጠቁትና ከሚገፉት ጎን መቆም ማለት ይኼ ነው፡፡ ለነፃነትና ለፍትሕ መቆም ማለት ይኼ ነው፡፡

በሥራ ምክንያት ወደ ኩባ በሄድኩበት ወቅት በግልጽ የተረዳሁት ነገር ቢኖር፣ ኩባ ውስጥ የኮሙዩኒስት ፓርቲ አባል መሆን ማለት የሕዝብ አገልጋይ መሆን ማለት ነው፡፡ የኮሙዩኒስት ፓርቲ አባል መሆን ማለት ከሕዝብ በታች እየኖሩ፣ ለሕዝብ ልዕልና መኖር ማለት ነው፡፡ ኩባ ከመሄዴ ቀደም ብሎ በትምህርትና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ወደተለያዩ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ለመሄድና በእነዚህ አገሮች ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለማየት ችዬ ነበር፡፡ የኩባ ኮሙዩኒስት ፓርቲና የፓርቲው አሠራር ከቻይና፣ ከሰሜን ኮሪያ፣ ከምሥራቅ አውሮፓ ኮሙዩኒስት ፓርቲዎች፣ ወዘተ ጋር በዓይነቱም በይዘቱም በጣም የተለየ ነው፡፡ ለምሳሌ የአንድ ዕቃ እጥረት ተፈጥሮ ዜጎች ከተሠለፉ፣ የመጨረሻው ሠልፍ ላይ የሚገኘው የኮሙዩኒስት ፓርቲ አባል ነው፡፡ የአገር ግንባታ ጥሪ የተደረገ እንደሆነ ደግሞ ግንባር ቀደም ሆነው መስዋዕትነት የሚከፍሉት የኮሙዩኒስት ፓርቲው አባላት ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ የኮሙዩኒስት ፓርቲ አባላት በኅብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ አድናቆትና ከበሬታ አላቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ የኮሙዩኒስት ሥርዓትን የሚጠሉ ሰዎች እንኳን ኮሙዩኒዝምን እጠላለሁ ካስትሮን ግን እወደዋለሁ ይሉ ነበር ፡፡

እዚህ ላይ ሊጠቀስ የሚገባው ሌላ መሠረታዊ ነገር አለ፡፡ በአብዛኞቹ ሶሻሊስት አገሮች ሀብት ማካበትና ሙስና ዋናው የሥርዓቱ መገለጫ ሲሆን፣ የኩባ ኮሙዩኒስት ፓርቲ አባላት በአንፃሩ በምንም ዓይነት ሁኔታ በሙስናና በሀብት ማካበት አይታሙም፡፡ ሌላው ቀርቶ ፊደል ካስትሮን ጨምሮ ትልልቆቹ የፓርቲ አባላት የግል መኖሪያ ቤት እንኳን የላቸውም፡፡

የሕዝቦችን እኩልነት በሚመለከት ረገድም የኩባ ሁኔታ የሚያስደንቅና ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ ጥቁርና የነጭ እኩልነት የተከበረበት አገር ነው ኩባ፡፡ ኩባ ውስጥ በምንም ዓይነት የዘር መድሎ የሚባል ነገር የለም፡፡ በሕግም ያስቀጣል፡፡ በሞራል ሕግም ያስንቃል፡፡ ነጭና ጥቁር እኩል ተከብሮ የሚኖርበት አገር ነው ኩባ፡፡ የሴቶች መብትና ነፃነት ደግሞ በጣም የተከበረ ነው፡፡ ከእነሱ 90 ማይል ርቆ የሚገኘውና በዴሞክራትነቱና በሰብዓዊ መብት ጠባቂነቱ የሚኩራራው የአሜሪካ ማኅበረሰብ እስካሁንም በዚህ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ በእጅጉ ወደኋላ የቀረ ነው፡፡ አሜሪካ አሁንም ሰዎች በተለይ ጥቁሮች የሚናቁበት፣ በገፍ የሚታሰሩበትና የሚሞቱበት አገር ስለሆነ፣ በዚህ በዜጎች እኩልነትና መከባበር ጉዳይ ላይ ከኩባውያን የሚማረው ብዙ ነገር አለ፡፡

የኩባ መንግሥት በትምህርት፣ በጤናና መሠረተ ልማት ግንባታና በወንጀል መከላከል በኩል በጣም ውጤታማ መንግሥት ነው፡፡ ኩባውያን ልጅ ሲወልዱ ልጃቸውን እንዴት እንደሚያስተምሩ አያስቡም፡፡ የአገሪቱ ልጆች ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ዩኒቨርሲቲ ለሚማሩት ትምህርት ሁሉንም ውጪ የሚሸፍነው የኩባ መንግሥት ነው፡፡ ትምህርትንና ጤናን በሚመለከት አንድም ወላጅ ልጄን እንዴት ላስተምር፣ እንዴት ላሳክም ብሎ አይጨነቅም፡፡ የኩባ መንግሥት ነው ኃላፊነቱን የሚወስደው፡፡  ትምህርትንና ጤናን በሚመለከት ረገድ በልጽገዋል የሚባሉት አገሮችም የኩባን ያህል ለሕዝባቸው አገልግሎት አይሰጡም፡፡ ፊደል በዚህ ምክንያት በኩባ ሕዝብ ለዘለዓለም ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡

ሁሉም ዜጋ ወንጀልን የሚዋጋና ወንጀለኞችን አሳልፎ የሚሰጥ በመሆኑ የወንጀለኞችና የተደራጁ ማፍያዎች በሚርመሰመሱበት አኅጉር ውስጥ በኩባ  ወንጀል የለም፡፡  ጥቁር ገበያና የሴት ልጅ መደፈር በከፍተኛ ደረጃ የሚያስቀጡ ወንጀሎች ናቸው፡፡ በጥቁር ገበያ ተሳትፈው የሚገኙትንና ሴት ልጅ የሚደፍሩትን ሕዝቡ ራሱ አሳልፎ ስለሚሰጣቸው በእነዚህ ወንጀሎች የሚሳተፍ የለም፡፡

እንደሚታወቀው የአሜሪካ መንግሥታት በተደጋጋሚ ጊዜያት ፊደል ካስትሮን ለመገልበጥ ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ አደርጎባቸው ሙከራዎች ሁሉ ከሽፈዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ፊደል ካስትሮና ጓዶቻቸው የመሠረቱት ሥርዓት ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ተባይነት ስላለውና ሕዝቡ ከመንግሥት ጋር ስለሚቆም ነው፡፡ አሜሪካውያን ያን ሁሉ የኩባ ዳያስፖራ እያደራጁና በዚያች አገር ላይ ማዕቀብ እየጣሉ ሥርዓቱን ለማሽመድመድ ቢሞክሩም እስካሁን አልተሳካላቸውም፡፡  

በነገራችን ላይ አንዳንድ ሰዎች በተለይ የምዕራብ መገናኛ ብዙኃን የፊደል ወንድም ራውል ካስትሮ ፊደልን ተክተው የአገሪቱ መሪ መሆናቸውን እየጠቀሱ፣ ካስትሮ የቤተሰብ ሥረወ መንግሥት መሥርተዋል እያሉ ይከሷቸዋል፡፡ ይህ ግን አንድም እውነታውን ካለማወቅ፣ ወይም ደግሞ በምዕራቡ ሚዲያ አካባቢ በተደጋጋሚ እንደሚስተዋለው እውነታውን ከመካድ የሚመጣ “ስህተት” ነው እንጂ ራውል ካስትሮ ራሳቸው ከወጣትነታቸው ጊዜ ጀምሮ የነፃነት ታጋይና አብዮተኛ ናቸው፡፡ የኩባ ሕዝብ ራውል ካስትሮ ልክ እንደ ወንድማቸው ለደሃዎች የሚቆሙ የነፃነት ታጋይ መሆናቸውን በሚገባ ስለሚያውቅና ስለሚቀበላቸው ነው የሽግግሩ ሒደት ኮሽታ ያልነበረው፡፡

ታላቁ አብዮተኛና የነፃነት ታጋይ ፊደል ካስትሮ በተወለዱ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ቢለዩም፣ በአገራቸውና በዓለም ዙሪያ ሁሉ የሠሯቸው አኩሪ ሥራዎች ስማቸውን ከመቃብር በላይ የሚያውሉ ናቸው፡፡ ነፍስ ይማር !!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው molla.zegeye@yahoo.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

Standard (Image)

የሙያና የብዙኃን ማኅበራት የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ ነው ወይ?

$
0
0

በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ

የኢፌዴሪ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ በአዋጅ 621/2001 ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት እንዲስፋፉና ተልዕኳቸውን በሕግ መሠረት እንዲወጡ ብሎም አሠራራቸው ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን እየሠራ ይገኛል፡፡ ኤጀንሲው በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 31 የተደነገገውን የዜጎች የመደራጀት መብት ዕውን ለማድረግ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራትን መዝግቦ ፈቃድ በመስጠት፣ ዘርፈ ብዙ የክትትልና የድጋፍ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ማኅበራት በአገራቸው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና የልማት ሥራዎች ላይ የመሳተፍ ዕድል አግኝተዋል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሙያና የብዙኃን ማኅበራት ተደራጅተው ፈቃድ በመውሰድ በአገሪቱ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

ምንም እንኳ አብዛኞቹ ማኅበራት ተመዝግበው መንቀሳቀስ የጀመሩት በቅርብ ዓመታት ውስጥ ቢሆንም፣ ከተመሠረቱ ግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ማኅበራትም አሉ፡፡ ሆኖም እንደ ቁጥራቸው ብዛትና እንደ ዕድሜያቸው ልክ የሙያ ማኅበራት በአገሪቷ የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ አኑረዋል ማለት ግን አይቻልም፡፡ የሙያም ሆኑ የብዙኃን ማኅበራት የሕዝብን ጥያቄ በተደራጀ መልኩ እያቀረቡ እንዲፈቱ ለማስቻል በመንግሥትና በኅብረተሰቡ መካከል እንደ ድልድይ ሆነው እያገለገሉ አይደለም፡፡ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ተመዝግበው ፈቃድ የወሰዱ በጥቅሉ 333 ገደማ የሚሆኑ የሙያና የብዙኃን ማኅበራት ቢኖሩም፣ የረባ ሥራ ሠርተዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ሆኖም በጥቅሉ ሁሉም ማኅበራት ለተቋቋሙለት ዓላማ በተገቢው ሁኔታ አስተዋፅኦ አላበረከቱም ማለታችን አይደለም፡፡ ለአብነት የሚጠቀሱ ስኬታማ ሥራ መሥራት የቻሉ ማኅበራት መኖራቸው አይካድም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ያሉ ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው በጣት የሚቆጠሩ ማኅበራት መኖራቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡ 

አብዛኞቹ የሙያና የብዙኃን ማኅበራት የሚፈለገውን ውጤት እንዳያመጡ እንቅፋት የሆነባቸው አገሪቱ በዘርፉ የምትከተለው ሕግ መሆኑን በአፅንኦት ይገልጻሉ፡፡ ለምሳሌ የ10/90 ሕግ ማኅበራት የገንዘብ ድጋፍ ከውጭ አገር እንዳያገኙ በማድረጉ ለመዳከማቸው ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ሕገ መንግሥቱ በደነገገው መሠረት በማኅበር የመደራጀት መብት የተሰጠው ለዜጎች ብቻ ነው፡፡ በአዋጅ 621/2001 መሠረት የኢትዮጵያ ማኅበራት ፈቃድ ወስደው ለመሥራት ሁሉም አባላት ኢትዮጵያዊ መሆን ይኖርባቸዋል እንዲሁም የገቢ ምንጫቸው ከአገር ውስጥ መሆን እንዳለበት ተደንግጓል፡፡

 በመሆኑም በሕግ ከተፈቀደው ውጪ ከውጭ የገንዘብ ምንጭ መጠቀም አይቻልም፡፡ የሙያና የብዙኃን ማኅበራት የአባላትን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሠሩ በመሆናቸው፣ እንደ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ሰፊ የሀብት መጠን ላያስፈልጋቸው ይችላል፡፡ 90 በመቶ የሚሆነውን ሀብት ከአገር ውስጥ በማመንጨት፣ እንዲሁም ከአሥር በመቶ የማይበልጠውን ከውጭ አገር በማምጣት ከሠሩ የተቋቋሙለትን ዓላማ ከዳር ማድረስ ይችላሉ፡፡ ማኅበራት የአባላትን መብትና ጥቅም ለማስከበር የውጭ ዕርዳታ ሳያስፈልግ በአገር ውስጥ ሀብት መሥራት ይችላሉ፡፡

በመሆኑም በአገራችን እየተንቀሳቀሱ ያሉ ማኅበራት የ10/90 ሕግ ውጤታማ ላለመሆናቸው ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ሕግ ሲወጣ ማኅበራት ሀብት የማግኘት አቅማቸው እንዳይዳከም ብዙ ታሳቢ የተደረጉ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለአብነት ያህል ማኅበራት ከተቋቋሙለት ዓላማ ጋር ግንኙነት ባላቸው ብሎም ዓላማቸውን ለማስፈጸም ብቻ የሚውሉ የተለያዩ ገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ አማራጮች ተቀምጠዋል፡፡ የንግድ ሕግ ጠብቀው ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ መሰማራት ይችላሉ፡፡ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመው ሕዝባዊ መዋጮ በማካሄድ ከአገር ውስጥ ሀብት ማመንጨት ይችላሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ አማራጮች ተጠቅመው ከጥገኝነትና ከተመፅዋችነት አመለካከት ተላቀው ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ ስለሚችሉ፣ የ10/90 ሕግ አላሠራንም ማለት ምክንያታዊና ከሕግ አንፃርም ተገቢነት የሌለው በመሆኑ ማኅበራት ቆም ብለው ማጤን ይኖርባቸዋል፡፡ ህልውናቸው የሚወሰነው ራሳቸውን ለማጠናከር በሚሠሩት ሥራ ነው፡፡

ይህ ሲባል የብዙኃንና የሙያ ማኅበራት ምንም ተግዳሮቶች የሉባቸውም ማለት አይደለም፡፡ አብዛኞቹ ሥራ መሥሪያ ቢሮ የላቸውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለሥራቸው ግብዓት የሚሆኑ ቁሳቁሶችን የማግኘት ችግር አለባቸው፡፡ በየዘርፉ ያሉ የመንግሥት ተቋማት ለሙያና ብዙኃን ማኅበራት ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል፡፡ የሙያ ማኅበራትም ለአባላት ሥልጠናና የትምህርት ዕድልን ከማመቻቸት ባለፈ ያላቸውን ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ፣ ለፖሊሲና ለስትራቴጂዎች ግብዓት የሚሆኑ የመፍትሔ ሐሳቦችን በማቅረብ እንዲሁም መንግሥትን በማማከር ለአገሪቷ አቅም መፍጠር አለባቸው፡፡ ይህንን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ማኅበራት የጎላ አስተዋፅኦ አድርገዋል ማለት አይቻልም፡፡

በቀጣይ በመስኩ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ የሙያ ማኅበራት በየዘርፋቸው ከሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ጋር የጠበቀ ቁርኝት ፈጥረው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እጅና ጓንት ሆነው መፍታት አለባቸው፡፡ የሙያ ማኅበራት ውጤታማ የሚሆኑት ያላቸውን እምቅ ዕውቀትና ክህሎት ሳይሰስቱ ለአገራቸው ማበርከት ሲችሉ ነው፡፡ በሌላ በኩል 10/90 ለሚተገብሩ የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት እንዲጠናከሩ መንግሥት የማኅበራዊ ተጠያቂነት ፈንድ (Social Accountability Fund) ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ አለበት፡፡  

የሙያና የብዙኃን ማኅበራት በራሳቸው የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ተምሳሌት መሆን መቻል አለባቸው፡፡ የአባላትን መብትና ጥቅም በማስከበር፣ በጠቅላላ ጉባዔ መሪዎችን መምረጥ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት እንዲፈቱ ማድረግ፣ ያልተመለሱ መብቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲመለሱ አባላትን በማለማመድ እንደ አገር በሚደረገው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መነሻና ትምህርት ቤት መሆን አለባቸው፡፡ የአንዳንድ ማኅበራት የሥራ ኃላፊዎች የጊዜ ሰሌዳቸውን ጠብቀው ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት የሥራ አፈጻጸማቸውን አያቀርቡም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለበርካታ ዓመታት ሥልጣናቸውን ለሌሎች አባላት ሳይለቁ የሚቆዩበት ሁኔታ አግባብነት የለውም፡፡

የመተዳደሪያ ደንባቸው ላይ በተቀመጠው መሠረት በየሁለት ዓመቱ ጠቅላላ ጉባዔ  በማካሄድ ሥልጣናቸውን አዲስ ለሚመረጡ ለሌሎች አባላት አሳልፈው መስጠት አለባቸው፡፡ የማኅበራት አመራር አባላቱን በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እያወያዩ ዜጎች የጠራ አመለካከት ይዘው ለልማት እንዲነሳሱ የበኩላቸውን ሚና መጫወት አለባቸው፡፡ የሙያና የብዙኃን ማኅበራት የአገሪቷ ዓይን፣ ጆሮና አፍ መሆን አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል ማኅበራት በውስጣቸው ሰፊ ቁጥር ያላቸው አባላትን በመያዛቸው ወሳኝ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸው የጠራ ግንዛቤ፣ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላል፡፡

የሙያና የብዙኃን ማኅበራት ውስጣዊ አሠራርም ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት መሆን አለበት፡፡ ይህ መሆን ሲችል ነው መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲያዊ አሠራር ሊጎለብት የሚችለው፡፡ ማኅበራት በአገሪቷ የፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ሲችሉ፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማስከበር ላይ ጉልህ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ አቅም ሲፈጥሩ በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላሉ፡፡ በዚህ ረገድ የሙያም ሆኑ የብዙኃን ማኅበራት በጉልህ የሚታይ ነገር አልሠሩም፡፡

አሁን በአገራችን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የብዙኃን ማኅበራት ገዢው ፓርቲ ያቋቋማቸውና ለእሱ በመወገን የፖለቲካ ሥራ እንደሚሠሩ አድርጎ የሚቆጥሩ አካላት አሉ፡፡ ነገር ግን የሙያና የብዙኃን ማኅበራት ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ነፃ ሆነው በገለልተኝነት ለዜጎች እኩል የሚሠሩ ናቸው፡፡ ሕጉም ይህንኑ ነው የሚደነግገው፡፡ በሌላ በኩል የሙያና የብዙኃን ማኅበራት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን ነቅሰው በማውጣት እንዲፈቱ ጫና እየፈጠሩ አይደለም፡፡ በእርግጥ ማኅበራት ይህንን እንዲያደርጉ መንግሥት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል ወይ የሚለው ጥያቄ በአግባቡ መፈተሽ አለበት፡፡ ሌላው ቀርቶ የአባላትን መብትና ጥቅም ማስጠበቅ የሚችሉበት ደረጃ ላይ አልደረሱም፡፡ ምንም እንኳን ሁሉንም ማኅበራት የሚገልጽ ባይሆንም ማኅበራት የሙያ ብቃት ባላቸው ግለሰቦች እየተመሩ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ ማኅበራት ሥልጣን ለመያዝ በሚያደርጉት ሽኩቻ በመጠመዳቸው ትርጉም ባለው ሁኔታ አገራዊ ራዕይ አንግበው ሙያውን ለማሳደግ እየሠሩ አይደለም፡፡ ይህም በዘርፉ የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ አሉታዊ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ 

የሙያም ሆኑ የብዙኃን ማኅበራት በሥነ ምግባር የታነፁና በዕውቀት የበለፀጉ አገር ተረካቢ ዜጎችን በማፍራት ረገድ ትኩረት ሰጥተው መሥራት አለባቸው፡፡ የአባላትን አቅም በመገንባት ዙሪያ ብዙም የተሠራ ሥራ የለም፡፡ ማኅበራት በተጨባጭ አባላትን ማፍራትና አቅም መገንባት መቻል አለባቸው፡፡ ማኅበራት ሲጠናከሩ የአባላትን መብትና ጥቅም ማስከበር ይችላሉ፡፡ የፋይናንስ አቅማቸው እንዲጠናከር የአገር ውስጥ ባለሀብቶችና ለጋሾች ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ማኅበራት እንቅስቃሴያቸው በበጎ ፈቃደኞች እንዲደገፍ ለማስቻል የበጎ ፈቃደኝነት ባህል እንዲዳብር ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ የኅትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ትኩርት ሰጥተው የሙያና የብዙኃን ማኅበራትን የሥራ እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም ያሉባቸው ተግዳሮቶች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በሰፊው መሥራት አለባቸው፡፡ ሚዲያዎች በዘርፉ ያሉ ድክመቶችን ለመፍታት የሚያስችል ጥልቅ ዕይታ መሠረት አቅጣጫ አመላካች የመፍትሔ ሐሳቦችን መስጠት መቻል አለባቸው፡፡

የሙያ ሥነ ምግባርና ብቃትን ከማሳደግ አንፃር የሙያ ማኅበራት ብዙ መሥራት ያለባቸው ሥራዎች ቢኖሩም፣ አሁንም የሚጠበቅባቸውን ያህል ርቀው መጓዝ አልቻሉም፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት የሚቆጠረው የሙያ ማኅበራት ተዝቆ የማያልቅ ትልቅ አቅም እያላቸው፣ ከስብሰባ የዘለለ ትርጉም ያለው ሥራ ለመሥራት ያላቸው ቁርጠኝነት ማነስ እንደ ድክመት የሚጠቀስ ነው፡፡ ሆኖም ለማኅበራት ተገቢው እገዛ ሳይደረግ በድፍኑ መውቀሱ አግባብ ባይሆንም፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ለሙያና ለብዙኃን ማኅበራት ትኩረት ሰጥተው አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለባቸው፡፡ የብዙኃንና የሙያ ማኅበራት ያላቸውን ምርጥ ተሞክሮ ቀምሮ ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ የአገር ውስጥም ሆነ ያደጉ አገራት ተሞክሮዎችን ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ማስፋፋት ቅድሚያ የሚሰጠው ለነገ የማይባል ተግባር ሊሆን ይገባል:: እንደ አገር የሙያም ሆኑ የብዙኃን ማኅበራት በዜጎች መብት ነክ ጉዳዮችና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደት ውስጥ በንቃት መሳተፍ የሚያስችላቸው አሠራር መዘርጋት አለበት እንላለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው chsainfo@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

Standard (Image)

የአፍሪካ ቀንድ ወደ ጂኦፖለቲካዊ ፉክክር ቀጣናነት

$
0
0

 በአበበ ዓይነቴ

በዓረቡ ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የእስልምና አክራሪነትና አሸባሪነት ከላይ ከተጠቀሰው አመለካከት በተቃራኒው በመቆም ሁሉንም በጠላትነት እየፈረጀም ቢሆን፣ አሁን ያለውን የዓለም ሥርዓት በመቃወም ከመላው ዓለም ደጋፊና አጋዥ እያስገኘለት መምጣቱ ችግሩን ውስብስብ ያደረገዋል፡፡

የጂኦፖለቲካዊ ፉክክር እንደ አዲስ ማቆጥቆጥ መጀመሩ ጉልቶ የታየው በዩክሬን ነው፡፡ ይህ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ኅብረትና በሩሲያ መካከል ያለው ፍጥጫ፣ እንዲሁም አሜሪካ በእስያ ፓስፊክ ባደረጋገቻቸው እንቅስቃሴዎች የተነሳ የወቅቱ የዓለም ፖለቲካ ሥርዓት ወደ ቀድሞው ጂኦፖለቲካዊ ፉክክር እየተመለሰ መሆኑን አመላካች ተደርጐ እየተወሰደ ይገኛል፡፡

የቻይና አዲሱ የሲልክ ሮድ ፕሮጀክት የአፍሪካን አንድ ጫፍ ከሌላው በመገናኛ አውታሮች በማስተሳሰርና የንግድ ትስስር በመፍጠር፣ የሰላምና የዕድገት ቀጣና ለማድረግ የተጀመረው ሒደት ለዘመናት በዕርዳታ በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሥር ለነበሩ አገሮች እንደ አማራጭ መቅረቡ ፉክክሩን ጉልህ አድርጐታል፡፡

በአጠቃላይ የዓለም ሥርዓት በአዲስ መልክ በጂኦፖለቲካዊ ፉክክር ውስጥ እንዲገባ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱና ትልቁ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጠረው የፖለቲካ ክፍተትና የቻይና በኢኮኖሚ፣ የሩሲያ በወታደራዊ ኃይል ጠንክረው መውጣት ነው፡፡ በሌላ በኩል መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች በኢኮኖማ ዕድገት ማስመዝገባቸውና አቅም መፍጠራቸው ተጠቃሽ ነው፡፡

ይህም የተለያዩ የበጐ አድራጎት ድርጅቶች እንዲመሠረቱና አክራሪነትን በፖለቲካና በገንዘብ እንዲደገፉ በር ከፍቶላቸዋል፡፡ የኒዩ ሊብራል ኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት የበላይነት ማግኘቱ በጐ ያልሆነው አመለካከት በዓለም ላይ በቀላሉ እንዲስፋፋና መሠረት እንዲያገኝ አድርጓል፡፡ የኢኮኖሚ ቀውስ በአሜሪካና በአውሮፓ መከሰቱ ችግሩን አወሳስቦታል፡፡ በዚህ የተነሳ አክራሪነትና አሸባሪነት የዓለም ቁጥር አንድ አደጋ ወደ መሆን አድርሷል፡፡ መፍትሔውን ውስብስብ የሚያደርግ ነው፡፡

በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ አገሮች ያላቸው የእርስ በእርስ ፉክክርና አንዱ በሌላው ላይ የበላይ ለመሆን ያለው ፍላጐት፣ የዓረቡን የፖለቲካ የበላይነት ለብዙ ጊዜ ይዛ የቆየችው ግብፅ በሳዑዲ ዓረቢያ ቦታዋን መነጠቋ፣ ግብፅና ሳዑዲ ዓረቢያ ቅሬታ ውስጥ መግባታቸው፣ ግብፅ የሳዑዲ ዓረቢያ ባላንጣ ከሆነችው ኢራን ጋር ወዳጅነት ለማጠናከር መፈለጓ፣ ይህ በኢራን ዋነኛ ጠላት ተደርጋ በምትታየው እስራኤልና ተፎካካሪዋ ሳዑዲ በበጐ ዓይን ያለመታየቱ ፉክክሩን ያጐለዋል፡፡ አሁን በቀይ ባህር እየታየ ያለው ምልክት ተጠናክሮ እንዲወጣ ያደርጋል፡፡

   ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢትዮጵያየውጭግንኙነትስትራቴጂካዊጥናትኢንስቲትዩት ባልደረባ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው abe.eiipd@gmail.com  ማግኘት ይቻላል፡፡

<span lang="NL" style="font-size:12.0pt;line-height:200%;font-family:&quot;Ge" ez-1","sans-serif";="" mso-bidi-font-family:"ge\0027ez-1";color:black;mso-ansi-language:nl'=""> 

Standard (Image)

ስለማይናገሩት የዱር እንስሳት እኛ እናውራላቸው

$
0
0

በታደሰ ማሞ

ጊዜ የለም፡፡ ምናልባትም አሉን የምንላቸው የዱር እንስሳት ነበር ሆነው በፎቶግራፍና በሥዕል ብቻ ለመጪው ትውልድ የምናሳይበት ጊዜ እየቀረበ ያለ ይመስላል፡፡ የዱር እንስሳት ከሰው ራቅ ብለው በራሳቸው የመኖሪያ ሥፍራ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ተደርገው ቢፈጠሩም፣ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖና የሰው ልጅ ወደ መኖሪያቸው ዘልቆ እየገባና በአደን መውጫ መግቢያ እያሳጣቸው ስላዋከባቸው፣ እነሆ በመጨረሻው የመጥፊያ ዘመናቸው ላይ ሆነውና መንታ መንገድ ላይ ቆመው የድረሱልን ጥሪ በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህ ጽሑፍ መነሻና መድረሻው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የዱር እንስሳትና የመኖሪያ አካባቢያቸው በከፍተኛ አደጋ ላይ መውደቃቸውንና ከመኖር ወደ አለመኖር እየተንደረደሩ መሆኑን መግለጽ ነው፡፡ እነዚህ የአገርና የሕዝብ ሀብት የሆኑት የተፈጥሮ ስጦታዎች አንዴ ከምድር ላይ ከጠፉ መልሶ ለማግኘት የሚቻልበት መንገድ ባለመኖሩ፣ ሳይቃጠል በቅጠል የሚለውን ብሂል በማስቀደም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ከጥፋት እንዲታደጓቸው አደራ ማለትና የእነሱ አንደበት ሆኖ ማስተጋባት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ በቱሪዝም መስህብነት በተለይ በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገቡት እንደ ላሊበላ፣ ፋሲል ግንብ፣ የሐረር ጀጎል ግንብ፣ የአክሱም ሐውልቶችና የመሳሰሉት አስታዋሽ አግኝተው እድሳት ሲደረግላቸው፣ በኢትዮጵያ ብቻ በብርቅዬነት የተመዘገቡት የዱር እንስሳት ግን አስታዋሽ አጥተው ህልውናቸው ከፍተኛ ችግር ውስጥ መውደቁን መንግሥትና ሕዝብ ተገንዝበው አስቸኳይ መፍትሔ እንዲፈልጉ ማድረግ የዚህ ጽሑፍ ቀዳሚ ዓላማ ነው፡፡

ለዚህም ነው ስለማይናገሩት የዱር እንስሳት እኛ እናውራላቸው፣ ልሳን እንሁናቸው፣ አንደበት እንሁናቸው በሚል ርዕስ ይህን ጽሑፍ ማዘጋጀት የፈለግኩት፡፡ ወዲህም የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የሥራ ባልደረባ በመሆን፣ በአገሪቱ የሚገኙ የዱር እንስሳት መኖሪያ ፓርኮችና መጠለያዎችን ከሞላ ጎደል ለመጎብኘት በመታደሉ በዱር እንስሳቱ ላይ የተፈጠሩ ጫናዎችን በቅርብ ርቀት ለማየት ችሏል፡፡ በዚህ መነሻ በምናቡ የሚመላለሰውን ዕረፍት የሚነሳ ጉዳይ ለአደባባይ ማብቃት መፈለጉም ሌላው ለዚህ ጽሑፍ መጻፍ ተጠቃሽ ምክንያት ነው፡፡

እዚህ ላይ ዶዶ የተባለችውን የወፍ ዝርያ በምሳሌነት ላንሳ፡፡ ዶዶ የተባለችው የወፍ ዝርያ በህንድ ውቅያኖስ አካባቢ በምትገኘውና የአፍሪካ አኅጉር ክፍል በሆነችው የሞሪሽየስ ደሴት ጫካዎች ውስጥ፣ እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የአካባቢው ጌጥ ሆና ትኖር የነበረች ፍጡር ናት፡፡ አውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች በተይም ፖርቹጋሎች ሥፍራውን እያሰሱ ሲደርሱ ግን የዚህች ወፍ ዕጣ ፈንታ ለጥፋት መጋለጥ ሆነ፡፡

ዶዶ መብረር የማትችል ነገር ግን ለመሮጥ የታደለች ቁመቷ እስከ አንድ ሜትርና ክብደቷም ከ10 እስከ 20 ኪሎ ግራም የሚመዝን እንዳነበረች በቅርቡ በእሷ ላይ ይፋ የሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ እነዚህ የቅኝ ግዛት አባዜ የተጠናወታቸው አሳሾች የዶዶ ዝርያዎችን እያጠመዱና እየያዙ ቀለባቸው በማድረግ ለወሬ ነጋሪ እንኳን ሳያስተርፉ ጨረሷቸው፡፡ ወደ ሌላ አካባቢ ለመሸሽ አቅሙ ያልነበራት ዶዶ የተፈጥሮ ጠላቶቹ ከሆኑት በተጨማሪ የሰው ልጆችም ዋና አሳዳጆቿ ሆነው ዝርያዋን አጠፉት፡፡ በሌላ ዓለም አንድም ተመሳሳይ ያልነበራት ዶዶ ታሪክ ሆና ነበረች ተብላ ቀረች፡፡ ሌላው ቀርቶ ዶዶ የጠፋችው ከካሜራ መፈልሰፍ በፊት በመሆኑ ትክክለኛ ገጽታዋንና መልኳን በዓይን አይተዋት የገለጿትን ሰምቶ ከመናገር በስተቀር፣ አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ስለማንነቷ ማስፈር አልተቻለም፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2007 ወዲህ በሞሪሽየስ ጫካዎችና ዋሻዎች በተደረገ አሰሳ በተገኙ ቅሪተ አካሎቿ ምን ዓይነት ቅርፅና መልክ እንደነበራት በመላምት ማስቀመጥ ተችሏል፡፡ ለዶዶ ከምድር መጥፋት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠያቂዎቹ የፖርቹጋል ቅኝ ገዢዎች ናቸው፡፡ የዶዶ መጥፋት መዘዙ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ዛሬ እንደ ዶዶ ለጥፋት የተጋለጡ ብዙ የዱር እንስሳት በአገራችን አሉ፡፡

በዚያው በሞሪሽየስ ምድር ላይ የሚገኘው ታምባላክ አኪዩ ወይም የዶዶ ዛፍ (Tambalac Ocque or Dodo Tree) የተባለው የዛፍ ዓይነት ወፏ ከጠፋች ከጥቂት ዓመታት በኋላ፣ ዝርያው ምን እንደነካው ሳይታወቅ ምድርን መሰናበት ጀመረ፡፡ ተመራማሪዎቹ ግራ ተጋብተው እሳት ሳይነካው የመጥረቢያ ዘር ሳያርፍበት እየጠፋ በሄደው በዚህ ዛፍ ላይ ምርመራቸውን ሲያደርጉ ምክንያቱን ደረሱበት፡፡ ለካስ የዚህ ዛፍ ፍሬ መብቀል የሚችለው ዶዶ የተባለችው ወፍ ከበላችው በኋላ በሆዷ ውስጥ አልፎ ከኩሷ ጋር መልሳ ስትጥለው እንደነበረ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ ሆኖም የዶዶ ወፍ በምድር ላይ ስለሌለች የዛፉን ፍሬ ተርኪ በተባለው የወፍ ወይም የዶሮ ዝርያ ከርስ እንዲያልፍ በማድረግና መልሶ የሚበቀልበትን ዘዴ በመፈለግ ዛፉን ለጊዜው ከመጥፋት ታድገውታል፡፡

የዶዶን ነገር ያለምክንያት አላነሳሁትም፡፡ በምድር ላይ የአንዱ መኖር ለአንዱ የቱን ያህል አስፈላጊ እንደሆነና የተፈጥሮ ሕግን ጠብቆ ሚዛናዊ በማድረግ ረገድ ምን ያህል የተቆላለፈና የተሳሰረ ነገር እንዳለ ለማሳየት ነው፡፡ ሆኖም ይህ የተፈጥሮ ሚዛን የሰው ልጅ ጣልቃ ሲገባበት በአጭር ጊዜ ተንዶ የቱን ያህል ለአደጋ እንደሚጋለጥም፣ ሌሎች ይህን መሰል አያሌ ምክንያቶችን በማንሳት ማስረዳት ይቻላል፡፡

የዱር እንስሳት በመንታ መንገድ ላይ

የዱር እንስሳት በተፈጥሮ በታደሉትና ከሰው ንክኪ ነፃ በሆነ ጫካ፣ ደን፣ ቁጥቋጦ፣ ሜዳማና ተራራማ ሥፍራ አሊያም በተራሮችና በውኃማ አካላት ውስጥ የሚኖሩ የተፈጥሮ ሀብትና በረከቶች ናቸው፡፡ ከደቃቃ ወይም ጥቃቅን ነፍሳት አንስቶ እስከ ትልቁ ዝሆንና ሻርክ ድረስ፣ እንዲሁም ከትንንሽ የአረም ዝርያዎች አንስቶ እስከ ትልልቁ የዋርካና የባህር ዛፍ ድረስ ተጠቃሽ የሆኑት የእንስሳትና የዕፅዋት ዝርያዎች፣ የዱር ሕይወትን ዑደትና መስተጋብር በመጠበቅ ብሎም ለአንዱ መኖር የአንዱ ማለፍ ግድ እየሆነና ተፈጥሮአዊ ሚዛኑን በመጠበቅ፣ ሚስጥራዊነታቸው እንደተጠበቀ ዛሬ ድረስ መዝለቃቸው ዋናው የተፈጥሮ ሚስጥር ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ ዛሬ የሰው ልጅ የቅርብ አጋር የሆኑት የቤት እንስሳት ቀደም ባለው ጥንታዊ ዘመን የዱርና የጫካ ነዋሪ እንደነበሩ በተለያዩ ጥናቶች ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬም ድረስ በየጫካው የሚኖሩ አምሳያዎቻቸውን በቅርብ ርቀት በመመልከት መገንዘብ ይቻላል፡፡ የሰው ልጅ በዱር ሕይወት ላይ በፈጠረው ጫናና አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት እ.ኤ.አ. እስከ 2014 ባለው ጊዜ የዱር ሕይወት ሀብት የሆኑ 52 በመቶ የዱር እንስሳትና ዕፅዋት ብቻ ቀርተው፣ 48 በመቶ የሚሆኑት መውደማቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የተፈጥሮን ዑደት በማመጣጠን በምድር ላይ የነበረው ሁሉ እንደነበረ እንዲዘልቅና የተፈጥሮ መዛባት እንዳይከሰት፣ በዱር ሕይወት ውስጥ የሚገኙ የዱር እንስሳትና ዕፅዋት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል፡፡ በየሚኖሩበት የአየር ፀባይና ሥፍራ ለመኖርና ራሳቸውን ለመተካት በሚያደርጉት ትግል ሲወድቁም ሆነ ሲጥሉ፣ የአኗኗር ዘይቤያቸውን በደመነፍስ በማስፈጸም የተፈጥሮ ግዴታቸውን ይወጣሉ፡፡ የዱር እንስሳቱ ለሰው ልጅ የምግብ ምንጭ ከመሆን አልፈው የምድርን ለምነት ለመጠበቅ፣ እንዲሁም ዕፅዋቱ ከምግብ ምንጭነታቸው ሌላ የባህላዊ መድኃኒቶች ምንጭ በመሆንና የሰው ልጆች የሚተነፍሱትን ንፁህ አየር ሰጥተው ካርቦንዳይ ኦክሳይድን በመውሰድ ረገድ፣ ተኪ የሌለው ድርሻ እንደሚያበረክቱ ተደጋግሞ የተባለ ጉዳይ ነው፡፡

በዱር እንስሳት ላይ የተጋረጠ አደጋ

የተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ እጅግ ሰፊ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት በተለይ ብርቅዬና ዋና ዋና በሆኑት የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ላይ የተጋረጠውን አደጋ የመብረቅ ብልጭታ በሚመስል ሁኔታ ማሳየት ግድ ይለኛል፡፡ በኢትዮጵያ 24 ብሔራዊ ፓርኮች፣ 21 የዱር እንስሳት ቁጥጥር አደን ቀበሌዎች፣ ሁለት የዱር እንስሳት መጠለያዎች፣ አምስት የዱር እንስሳት መኖሪያ ቀጣናዎችና አሥር የኅብረተሰብ ተኮር የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ ውስጥ 12 ብሔራዊ ፓርኮችና ሁለት የዱር እንስሳት መጠለያዎች በኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን በቀጥታ የሚተዳደሩ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ እንደ አቀማመጣቸውና የሚገኙበት አካባቢ በክልል መንግሥታት ይተዳደራሉ፡፡ ባለሥልጣኑ ከአንድ ክልል በላይ የሚያዋስናቸውን ፓርኮችና መጠለያዎች የሚያስተዳድር ሲሆን፣ ክልሎች ደግሞ በገጸ ምድራቸው ውስጥ ከሌላ ክልል ጋር የማይዋሰኑ ፓርኮችን ያስተዳድራሉ፡፡ ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚዋሰኑትም በባለሥልጣኑ እንደሚተዳደሩ ይታወቃል፡፡

በአጠቃላይ በእነዚህ ፓርኮችና መጠለያዎች ውስጥ ብዙ ሺሕ ቁጥር ያላቸው የዱር እንስሳት ይኖራሉ፡፡ ስለእያንዳንዳቸው ለመግለጽ ቦታና ጊዜ የማይበቃ ከመሆኑም በላይ፣ አንባቢያንም ማሰልቸት ስለሚሆን በዋናነት በባቢሌ በዝሆን፣ በስንቅሌ በስዌይን ቆርኬ፣ በሰሜን ተራራዎች በዋልያ፣ በባሌ በቀይ ቀበሮና በደጋ አጋዘን፣ በአዋሽ በሳላና በመሳሰሉት ላይ የተጋረጡ አደጋዎችን በማሳየትና በወፍ በረር ቅኝት በመቃኘት፣ የሚመለከታቸው ሁሉ ከተኙበት እንዲነቁ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አምኜበታለሁ፡፡

የዋልያ የመጨረሻ ድምፅ

ዋልያን ከሌሎቹ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ብርቅዬ የዱር እንስሳት መካከል የተለየ የሚያደርገው፣ ከኢትዮጵያም በሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ብቻ የሚገኝ ለመጥፋት የተቃረበ የዱር እንስሳ መሆኑ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ለግጦሽ በነፃነት የሚሰማራባቸው በፓርኩ ውስጥ ያሉት እንደ ሳንቃበር፣ ቧሂት፣ ምጪብኝ፣ ጨነቅ፣ ሲሊቅና የሊማሊሞ ተራራ ጥጋ ጥጎችና ጫፎች ከአካባቢ አየር መለዋወጥ ጋር ተያይዞ ባለው ሁኔታ የቀድሞ ይዞታቸውን ከመልቀቃቸው በተጨማሪ፣ ነዋሪዎች ከብቶችን ይዘው ወደ አካባቢው መዝለቃቸው የዋልያን ኑሮ የበለጠ አጣብቂኝ ውስጥ ከተውታል፡፡

ዋልያ የተፈጥሮ ጥቃት አድራሾቹ የሆኑትን እንደ ነብር፣ ጅብ፣ የሎስ አሞራ፣ ቀበሮና የመሳሰሉትን ለመሸሽና ዝርያውን ለማስቀጠል የሚያደርገው ትግል በሰው ልጆች ጣልቃ ገብነትም እየተረበሸ መሆኑ ዘወትር በፓርኩ ውስጥ የሚስተዋል ጉዳይ ነው፡፡ የሰሜን ተራሮችን በዓለም አቀፍ ቅርስነት የመዘገበው ዩኔስኮ በአካባቢው የተፈጠረውን የሰዎች ጣልቃ ገብነት በአስቸኳይ ማስቆም ካልተቻለ፣ ፓርኩን ከዓለም አቀፍ መዝገብ ላይ እሰርዛለሁ ማለቱን ተከትሎ በመንግሥት ደረጃ የሚከናወኑ ሥራዎች ቢኖሩም ፈጥነው መፍትሔ የሚያመጡ ባለመሆናቸውና ከአንጀት ጠብ ለማለት ጊዜ የሚፈጅባቸው መሆኑ ለዋልያው ራስ ምታት የፈየደው ነገር የለም፡፡ ድምፅ በሌላቸው አካባቢ ሠራሽ ወጥመዶች እየታነቀ የሚያልቀው የዋልያ ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ የተፈጠረው ሁለገብ ጫና በዋናነት በዚያው አካባቢ ብቻ ለመኖር ተገዶ በሚገኘው ዋልያ አይቤክስ ላይ የፈጠረው ችግር፣ የዱር እንስሳው አድኑኝ ብሎ የሚጮህበት የመጨረሻ ወቅት ላይ የሚገኝ አስመስሎታል፡፡ የፓርኩ ጫና ከዋልያ በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኙትንና ብርቅዬ የሆኑትን ጭላዳ ዝንጀሮ፣ ቀይ ቀበሮ፣ የምኒሊክ ድኩላና የመሳሰሉት ላይ ውጥረት እንደፈጠረ ልብ ማለት ይገባል፡፡ በተለይ ቁጥሩ አንድ ሺሕ ለማይሞላውና የአካባቢው ጌጥ ለሆነው ዋልያ ፈጥነን ልንደርስለት ይገባል፡፡

የስዌይን ቆርኬ በውኃ ጥም የተቃጠለው አሳዛኝ ፍጡር

የስዌይን ቆርኬ ሌላው ኢትዮጵያዊ ብርቅዬ የዱር እንስሳ ነው፡፡ ይህን የዱር እንስሳ ከሻሸመኔ ወደ ሃላባ በሚወስደው መንገድ አጄ ላይ ሲደርሱ በስተግራ ተገንጥሎ በመግባት፣ ዙሪያዋን በሰዎች በተከበበችው የስንቅሌ የቆርኬዎች መጠለያ ሜዳ ላይ ግራ ተጋብቶ ወዲያ ወዲህ ሲል መንጋውን ማየት ይቻላል፡፡

በዚች የበሬ ግንባር በምታህል ሣራማ ምድር ላይ ቀንም ሌትም ወዲህ ወዲህ እያሉ የሚውሉት ከሰባት መቶ ያልዘለሉ ቆርኬዎች፣ በተለይ ለመኖር አስፈላጊ የሆነውን ውኃ ለመጠጣት የሚችሉበት አማራጭ ሁሉ በሰዎች ከበባ በመታፈኑ በምን ተዓምር እየኖሩ እንደሆነ ለመረዳትም ይከብዳል፡፡ ገራገሮቹ የመጠለያው ሠራተኞች የጧት ጤዛ እየላሱ ነው የውኃ ጥማቸውን ለመመለስ የሚሞክሩት የሚል ቀልድ መሰል እውነታ ቢናገሩም፣ ቀደም ባለው ዘመን ወደ ሐዋሳ ሐይቅና ከአካባቢው በቅርብ ርቀት ወደሚገኘው ብላቴ ወንዝና ገባሮቹ እየዘለቁ ይጠጡ የነበረበት መንገድ ሁሉ በአካባቢው በሰፈሩ ዜጎች ስለተዘጋ፣ መድረሻው ጠፍቷቸው እልቂታቸውን እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡

ዋናው ችግራቸው የውኃ ጥም ይሁን እንጂ የሚወልዷቸው ጥጆችና መንጋው ራሱ በተለይ በአካባቢው በብዛት በሚገኘው የጅብ መንጋ መወረራቸው፣ እንዲሁም የግጦሽ መሬታቸው በቤት እንስሳት ዘወትር መወረሩና በአካባቢው የእርስ በርስ ግጭት በተፈጠረ ቁጥር የእልህ መወጫና የጥይት ሲሳይ መሆናቸውም ሌላውም አጣብቂኝ ነው፡፡ በተለይ የከርሰ ምድር ውኃን ለማውጣት የተደረገው ጥረት ከመሬት ሥር በቅርብ ርቀት ውኃ አልተገኘም በሚል ሰበብ ፍፃሜ አለማግኘቱን፣ ሌሎችም ተደራራቢ ችግሮች በአፋጣኝ ምላሽ ካልተሰጣቸው የስዌይን ቆርኪ ጉዳይ በቅርቡ ተረት ተረት ይሆናል የሚል ሥጋት በሁሉም ዘንድ አለ፡፡

የደጋ አጋዘን አደን መውጫ መግቢያ አሳጥቶታል

በባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ፣ በአርሲና በምዕራብ ሐረርጌ ተራራማ ቦታዎች ላይ ደጋውን የአየር ክልል እየተከተለ የሚኖረው የደጋ አጋዘን ሌላው ኢትዮጵያዊ ብርቅዬ የዱር እንስሳ ነው፡፡ ይህ እንስሳ የግጦሽና የመጠጥ ውኃ ችግሩ በአንፃራዊነት ከሌሎች የተሻለ መሆኑ ቢነገርለትም፣ ሕጋዊም ሆኑ ሕገወጥ አዳኞች በብርቱ የሚፈልጉት በመሆናቸው ሁልጊዜም የጥይት ድምፅ ሲያስበረግገው ይኖራል፡፡

ሕጋዊ አዳኞች ለአንድ ለአደን ለደረሰ የደጋ አጋዘን 15 ሺሕ ዶላር እንዲከፍሉ መጠየቃቸው ተፈላጊነቱን ያበዛው ሲሆን፣ ብርቅዬ እንስሳ መሆኑ እየታወቀ በሕጋዊ አደን ስም ህልውናው ለአደጋ የተጋለጠ እንዲሆን የተፈረደበት መሆኑ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ተራራ እየተከተለ በሚኖርባቸው አካባቢዎች ያሉ ትልልቅ ዕፅዋት ለፋብሪካ ፍጆታ የሚመነጠሩ መሆናቸውና አንዳንዴም ግራ እየተጋባ ለአደጋ በሚያጋልጠው ሥፍራ እንዲኖር መገደዱም የደጋ አጋዘን ሌላው ሥጋት ነው፡፡

ሳላና አዋሽ እየተራራቁ ነው

በእርግጥ ሳላ ብርቅዬ የዱር እንስሳ አይደለም፡፡ ሆኖም ማንኛውም ወደ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ የሚዘልቅ እንግዳ ሳላን ሳይመለከት መመለስ ራስ ምታት ይሆንበታል፡፡ በረጃጅም ቀንዶቹ ጀርባውን እያከከ በአዋሽ ሳራማ ሜዳዎችና በዋናው መንገድ ዳር ይታይ የነበረው ሳላ ዛሬ ዛሬ ህልም ሆኗል፡፡

በዋናነት የሚውልበት መስክ በቤት እንስሳት መወረሩ፣ ከሁሉ በላይ ውኃ ለመጠጣት ወደ አዋሽ ወንዝ ያቀናባቸው የነበሩ መንገዶች በኢንቨስትመንት ሰበብ የሰው መተራመሻ መሆናቸው፣ እንዲሁም ሕገወጥ አዳኞች ለሥጋው ሲሉ እሱ ላይ መተኮሳቸው የአዋሽ ጌጥ የሆነውን ሳላ ዱካው ከአካባቢው እንዲጠፋ ምክንያት ሆነውታል፡፡

የባቢሌው ዝሆን ሊያከትም ጫፍ ደርሷል

የዱር እንስሳትን ጫና ተመልክተው የሚያዝኑ ሰዎች ከሁሉ በላይ ደም እንባ የሚያለቅሱበት ሥፍራ የባቢሌው ዝሆን ስቃይ መሆኑን ሁሉም ይስማሙበታል፡፡ በግዙፍነቱ ልዩ ግርማ ሞገስ የተላበሰውን የአፍሪካ ዝሆን ለመጠበቅ ተብሎ የተከለለው የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ሥፍራ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ በሕገወጥ ሰፋሪዎችና ዝሆንን ለጥርሱ ሲሉ በሚያድኑ ሰዎች በመሞላቱ የባቢሌ ዝሆኖች ጠፍተዋል ማለት ይቀላል፡፡ ቁጥራቸው 50 የማይሞላ ዝሆኖች ከሰዎች ንክኪ የተሻለ ነው በሚባለው ፈዲስ አካባቢና ሌሎች ሥፍራዎች ወዲያ ወዲህ እያሉ ራሳቸውን ለማቆየት ቢሞክሩም፣ ጫናው ከመቼውም ጊዜ በላይ በርክቶባቸው ዋና ዋናዎቹና ትልልቆቹ ዝሆኖች አልቀው፣ ትንንሾቹ ወይም ኤልሞሌ የሚባሉት ብቻ በጥቂቱ እየታዩ እንደሆነ ለማየት ዕድሉ የተፈጠረላቸው የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ፡፡ በየዓመቱ አርባና ሃምሳ ዝሆኖች እየተገደሉ ቁጥራቸው ከ300 የማይበልጡ ዝሆኖች አሁን በባቢሌ አሉ እያሉ ለመናገር የማይቻልበት ጊዜ ላይ እንደተደረሰ መረዳት ይቻላል፡፡ ባቢሌን ያለ ዝሆን ማሰብ እንዴት ይከብዳል? በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው ቀይ ቀበሮም በተለይ ከለማዳ ውሾች ጋር በሚኖረው ግንኙነት በውሻ በሽታና በአላስፈላጊ መዳቀል ዝርያው አደጋ ላይ እየወደቀ መሆኑን ተመራማሪዎች እየገለጹ ነው፡፡

ማጠቃለያ

ለማሳያ ያህል በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ላይ የተጋረጡት ችግሮች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ የዱር እንስሳት የመኖሪያ ፓርኮች ያለባቸው ጫና የበረታበት ጊዜ ነው፡፡ እነ ቻይና በአንድ ወቅት የተፈጥሮ ሀብታቸውን አውድመው ከችግር ከወጡ በኋላ፣ መልሰው ደኑን መትከልና አካባቢን አረንጓዴ ማድረግ ቢችሉም በደኑ ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን የዱር እንስሳት ግን መመለስ አልቻሉም፡፡

አሁን በኢትዮጵያችን እየተፈጠረ ያለው ሁኔታም የዚህ ተመሳሳይ በመሆኑ፣ በተለይ ለብርቅዬዎቻችንና ዳግም ልንተካቸው ለማንችላቸው የዱር እንስሳቶቻችን ፈጥነን ልንደርስላቸው ይገባል፡፡ ለመሆኑ ይህንን ከባድ አገራዊ አደራ መሸከም ያለበት ማን ይሆን? ʻቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝምʼ እንዳይሆን ብቻ!               

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው tademaa@yahoo.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

Standard (Image)
Viewing all 88 articles
Browse latest View live