Quantcast
Channel: ዓለማየሁ ጉጀ
Viewing all 88 articles
Browse latest View live

ኢኮኖሚስቶች ስለሥራ አጥነት ምን ይላሉ? በሳይንሳዊ ዓለም ውስጥ ልማዳዊ አስተሳሰብ

$
0
0

በጌታቸው አስፋው

‹‹የእኔን ወሬ ለአንቺ የአንቺን ወሬ ለእኔ የሚያመላልሰው የት አለ ደመወዙ ልብሱን የለበሰው፤›› ማን እንደ ገጠመውና መቼ እንደ ገጠመው አላውቅም፡፡ የዘፈን ግጥም እንደሆነ ግን አውቃለሁ፡፡ በኢኮኖሚክስ ሲተነተን ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ በመጀመሪያ ደመወዝ የሥራ ዋጋ መሆኑን ይነግረናል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ወሬም ሥራ ሆኖ ደመወዝ የሚያስገኝ መሆኑን ይነግረናል፡፡

አፍ ያወራውን እጅ የሚሠራበት እጅ የሠራውን አፍ የሚያወራበት ጊዜዎች ቢኖሩም፣ አፍ አውርቶ እጅ የማይሠራበትና እጅ ሠርቶ አፍ የማያወራበት ጊዜያትም አሉ፡፡ ትልቁ ቁም ነገር የቱ ያመዝናል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እጅ ሳይሠራ አፍ የሚያወራበት ጊዜ አመዝኗል፡፡ ወሬ አመላላሾች ልብስ መልበስ ብቻ ሳይሆን፣ በወርቅና በአልማዝ ጌጣጌጥ ተንቆጥቅጠውም አይተናል፡፡ የወሬ ሙስናው ከገንዘብ ሙስናው ስለሚበልጥና በአገር ላይ ያንዣበበ አደጋ ስለሆነ፣ ለአፍ ልጓም የወሬ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋምም ሊያስፈልግም ይችላል፡፡ ስለዚህም ሥራ በአፍም ይሠራል፣ በእጅም ይሠራል፡፡ ማን በአፍ ይሠራል? ማን በእጅ ይሠራል? የሚለውም ተለይቶ ይታወቃል፡፡ በእጅ የሚሠራው ሰው ደመወዝ ይበልጣል? ወይስ በአፉ የሚሠራው ሰው ደመወዝ ይበልጣል? የሚለውም ይታወቃል፡፡ ለማጥናት የፈለገ አጥንቶ ያውቃል፡፡ ጥናቱን ለአጥኚው ትቼ እኔ ስለተነሳሁበት ዓላማ ስለሥራ አጥነት ልቀጥል፡፡

 

ስለሥራ አጥነትም ሆነ ስለሥራ ፈጠራ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ተብሏል፡፡ አዲሱን ትውልድ በቀድሞ ታታሪ ሰዎች ተሞክሮ ለማነቃቃት እነ አቶ በቀለ ሞላ፣ አቶ ተካ ኤጋኖ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገርም ከባዶ ተነስተው ስለከበሩ ሰዎች ምሳሌ እየተጠቀሰ ተወርቷል፡፡ ስለሥራ ፈጠራ መጻሕፍትም ተጽፈዋል፡፡ የሥራ ፈጠራ ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች በሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶችም ብዙ የሥራ ፈጠራ ሥልጠና ኮርሶች ተካትተዋል፡፡ የሥራ ፈጠራ ጥሪት (Fund) በመንግሥት ተይዟል፡፡ ባንኮች ለወጣቱ የሥራ ፈጠራ ብድር እንዲያመቻቹ ታዘዋል፡፡ የወጣቶች ሥራ ፈጠራ ፕሮግራም ፓኬጅ ተነድፎ በአንደኛውና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመናት፣ በጥቃቅንና በአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች አማካይነት በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ተደርጓል፣ እየተደረገም ነው፡፡

 የብዙ አገሮች ልምድ ተዳሰሰ፣ ቢዝነስ ፕላን ተዘጋጅቶ ተሰጠ፣ ብድር ተመቻቸ፣ የገበያ ትስስር ተፈጠረ፣  የመሥሪያና የመሸጫ ቦታ ተሰጠ፣ ስለሥራ ፈጠራ ያወሩም ደመወዛቸውን ወሰዱ፡፡ በመጀመርያዎቹ ዓመታት ውጤቱ በከፊል ታይቶ ይሆናል፡፡ የኋላ ኋላ ግን እንደ ጀግንነት የጉድ ያህል ተወርቶ ወረት ሆኖ እንደቀረው ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ የኮብልስቶን አንጣፊ መሆን ጋር የሥራ ፈጠራ ወሬውም ቀዝቅዞ ነበር፣ ባለፈው ሰሞን ከተቀሰቀሰው አመፅ ጋር ተያይዞ እንደገና አገረሸ እንጂ፡፡ ከሕዝብ መጨመር ጋርና ለሥራ ዕድሜያቸው ከደረሰ ወጣቶች ጋር ሲነፃፀር የሥራ ፈጠራ ወሬውና የሥራ ፈጠራው ውጤት ዜሮ ድምር ሆኖ ጥረቶቹ ሁሉ መና ቀርተው እዚያው በዚያው ተሽከረከሩ፡፡

አንድ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ባለበትና በዓመት ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ በሚጨመርበት አገር፣ ሁለትና ሦስት የውጭ ኢንቨስተሮች መጡ፡፡ እያንዳንዳቸው ሁለት ሺሕ፣ ሦስት ሺሕ፣ አምስት ሺሕ ሰዎች ይቀጥራሉ ተብሎም እንደ ታላቅ የሥራ አጥነት ቅነሳ ገድል በብሔራዊ ኢኮኖሚ ደረጃ ዘገባ ለሕዝብ ቀረበ፡፡ ስለሥራ ቅጥርና ሥራ አጥነት ያልተነገረውና ለሕዝብ ያልተገለጹ ነገሮች ቢኖሩ የሥራ ቅጥርም ሆነ ሥራ አጥነት የኢኮኖሚክስ ሙያ ማዕከላዊ ነጥብ መሆናቸውና ስለሥራ ቅጥርና ደመወዝ መጣኝ ግንኙነትና ተዛምዶ፣ ምርምር ያደረጉ ታላላቅ ኢኮኖሚስቶች ያደረጓቸው የምርምር ውጤቶች ምን እንደሚሉ ነው፡፡

ጥንታውያን ኢኮኖሚስቶች እንደ ሌሎቹ የኢኮኖሚ ሁኔታ ትንታኔዎቻቸው የሥራ አጥነትንና የሥራ ቅጥርን ሁኔታ የሚያዩት እንደ የግል ኢኮኖሚ ጉዳይ (Microeconomic Phenomena) ሆኖ፣ በሠራተኛ ገበያ ውስጥ በሠራተኛ ፍላጎትና በሠራተኛ አቅርቦት መስተጋብር በሚወሰን የደመወዝ መጣኝ ሁለቱ እኩል እንደሚሆኑ ቢሆንም፣ ከኬንስ ኢኮኖሚክስ ወዲህ ግን የሥራ አጥነትና የሥራ ቅጥር ሁኔታ የጠቅላላ ብሔራዊ ምርት መጠንና የብሔራዊ ኢኮኖሚ ጉዳይ (Macroeconomic Phenomena) ሆኗል፡፡ ብሔራዊ ኢኮኖሚ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርትን ዕድገትና ይህም ከዋጋ ንረት፣ ከሥራ አጥነትና ከውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ክፍያ ሚዛን ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያጠና ነው፡፡ ስለዚህም የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የዋጋ ንረት፣ ሥራ አጥነት፣ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ክፍያ ሚዛን፣ የብሔራዊ ኢኮኖሚ የጥናት መስኮች ናቸው፡፡

አንድ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ባለሙያም የብሔራዊ ኢኮኖሚውን ዕድገትና መመጣጠን የሚለካው በእነኚህ መሥፈርቶች አማካይነት ነው፡፡ ኢትዮጵያም በየዓመቱ አሥራ አንድ በመቶ እያደገች ነው ከሚለው ማረጋገጫ የሌለው ሪፖርት በቀር፣ የብሔራዊ ኢኮኖሚው ሁኔታ መገለጫ በሆኑት በሥራ አጥነት፣ በዋጋ ንረትና በውጭ ምንዛሪ እጥረት ክፉ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ለማንም የተደበቀ ሚስጥር አይደለም፡፡ ገበያ ውስጥ የሚታይ ነገር ስለሆነ ሊደበቅም አይችልም፡፡ የካዱም እያመኑ ናቸው፡፡

በሳይንሳዊ ዓለም የሥራና የደመወዝ ጽንሰ ሐሳቦች

 

ሥራ አጥነትንና የደመወዝ መጣኝን አስመልክቶ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉና እየዳበሩ የመጡ በርካታ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳቦች ተተንትነዋል፡፡ ብዙ አገሮችም የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻቸው ማዕከላዊ ነጥብ አድርገዋቸዋል፡፡ በአጭር ጽሑፍ ውስጥ ሁሉንም ማቅረብ ባይቻልም፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከሚገልጹት ውስጥ ጥቂቶቹ ለግንዛቤ ያህል እንደሚከተለው ይቀርባሉ፡፡  

የዴቪድ ሪካርዶ ጽንሰ ሐሳብ

የመጀመሪው ዘመናዊ የሥራና የደመወዝ ወጥ ጽንሰ ሐሳብ የተተነተነው በእንግሊዛዊ ኢኮኖሚስት ዴቪድ ሪካርዶ ሲሆን፣ የሥራ ዋጋ ደመወዝ መጠን በገበያ ውስጥ የሚወሰነው ሠራተኛው ራሱንና ቤተሰቡን በሕይወት አቆይቶ ዘር ወይም ትውልድ ለመተካት የሚያስችለውን ከእጅ ወደ አፍ የቀለብ ገቢ ብቻ በሚያገኝበት የደመወዝ መጠን ነው ይላል ሪካርዶ፡፡ ደመወዙ ኑሮ ዘር ለመተካት ከሚያስችል ከእጅ ወደ አፍ የቀለብ ገቢ በታች ከሆነ ሠራተኛው ትውልድ ስለማይተካ፣ የሕዝብ ቁጥር በመቀነስ የሠራተኛ አቅርቦት አንሶ ከፍላጎት በታች ስለሚሆን ደመወዝ ወደ ላይ ይወጣል፡፡ ደመወዝ ኑሮ ዘር ለመተካት ከሚያስችል ከእጅ ወደ አፍ የቀለብ ገቢ መጠን በላይ ከሆነ ግን፣ ሠራተኛው ብዙ ሠራተኛ ልጆችን ስለሚወልድ የሕዝብ ቁጥር በመጨመር የሠራተኛ አቅርቦት በዝቶ ከፍላጎት በላይ ስለሚሆን የደመወዝ መጠን ወደ ታች ይወርዳል፡፡ ይህ የሠራተኛ ፍላጎትና አቅርቦት ውጣ ውረድ ደመወዝ አወሳሰን ሥራ አጥነትን ያስወግዳል፡፡

ይህ ዘር መተኪያ ከእጅ ወደ አፍ የቀለብ ገቢ መጠን ደመወዝ የሠራተኛ ፍላጎትና አቅርቦት እኩልነት አወሳሰን ጽንሰ ሐሳብ በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ ዘመናት የምግብ ምርትና ምርታማነት ከሕዝብ ቁጥር በላይ በፍጥነት ማደግ ምክንያት ውድቅ ሆነ፡፡

የጥንታውያን ኢኮኖሚስቶች ጽንሰ ሐሳብ

የሪካርዶ የሥራና የደመወዝ መጠን ጽንሰ ሐሳብ ከጥንታውያን ኢኮኖሚስቶች አስተሳሰብ አንዱ ይሁን እንጂ፣ በአጠቃላይ የጥንታውን ኢኮኖሚስቶች የሥራ አጥነትና የደመወዝ መጣኝ ጽንሰ ሐሳብ ትንታኔ የሚያተኩረው በግል ኢኮኖሚው የሠራተኛ ገበያ ውስጥ ነው፡፡ ይህም የደመወዝ መጣኝን የሚወስነው በሠራተኛ ገበያ ውስጥ የሚታየው የሠራተኛ ፍላጎትና አቅርቦት መስተጋብር ሲሆን፣ በሁለቱ መስተጋብር በሚወሰነው የደመወዝ መጣኝም ሥራ አጥነት አይኖርም፡፡ በሠራተኛ ገበያው ሥራ አጥነት የሚከሰተው የነፃ ገበያው ኢኮኖሚ ሕግጋት በመንግሥትና በሠራተኛ ማኅበራት ጣልቃ ገብነት ሲጣሱ፣ ወይም ሠራተኛውና አሠሪው የረጅም ጊዜ ቅጥር ስምምነት ውል ስለሚዋዋሉ በሠራተኛ ገበያዎች አለመጥራት (Labor Markete Imperfections) ነው፡፡

ስለዚህም ገበያውን በማጥራትና የመንግሥትና የማኅበራትን ተፅዕኖና ጣልቃ ገብነት በማስወገድ፣ በገበያ የሚወሰን የደመወዝ መጣኝ ፍላጎትና አቅርቦትን አጣጥሞ ሥራ አጥነትን ያስወግዳል፡፡ ሥራ አጥነት የሚከሰተው ሥራ ያልተቀጠሩ ሥራ ፈላጊዎች ከተቀጠሩት በዝቅተኛ ደመወዝ ሊሠሩ ቢፈልጉም እንኳ፣ ከላይ በተገለጹት ምክንያቶችና በሌሎች እንደ ሞራልና ሰብዓዊ ስሜት አመለካከቶች በመሳሰሉ ምክንያቶች አሠሪዎች የቀድሞ ሠራተኞቻቸውን አስወጥተው አዲሶቹን በዝቅተኛ ደመወዝ ሊቀጥሩ ስለማይችሉ፣ ወይም ስለማይፈልጉ የሠራተኛ ገበያው የገበያ ኃይሎች በሆኑት በፍላጎትና በአቅርቦት ስለማይመራ ነው፡፡

ካርል ማርክስ

የካርል ማርክስ የደመወዝ ጽንሰ ሐሳብ የሪካርዶን ለሥራ ከእጅ ወደ አፍ ለቀለብ የሚበቃ የደመወዝ መጠንን የመሰለ ሲሆን፣ በካፒታሊዝም ሥርዓት ሠራተኛው ምርት በማምረት ሒደት ውስጥ ለመኖር ከሚበቃው በላይ ያመረተውን ተጨማሪ እሴት፣ በትርፍ መልክ ካፒታሊስቱ ከሠራተኛው የሚበዘብዘው እንደሆነ ነው፡፡ ካፒታል በምርት ሒደት ውስጥ ምንም አስተዋጽኦ የለውም፡፡ ካፒታል ራሱ ተጠራቅሞ ወደ ቴክኖሎጂነት የተቀየረ በምርት ላይ የፈሰሰ የሰው ጉልበት ነው፡፡ ስለሆነም በሶሻሊስት አብዮት ወዛደሩ በካፒታሊስቱ የተነጠቀውንና በዘመናት የሥራ ሒደት ወደ ካፒታልነት የተቀየረውን የተጠራቀመ የሰው ጉልበት ወርሶ፣ ወደ እውነተኛው ባለቤት ወደ ራሱ ማስመለስና ከእንግዲህም ጉልበቱን እንዳይበዘበዝ የካፒታሊዝም የግል ሀብት ይዞታን ያፈርሳል፡፡ በምትኩም በወዛደሩ የሚመራ ማኅበራዊ የሀብት ይዞታን የሶሻሊዝም ሥርዓትና ይህን ሥርዓት የሚመራ መንግሥት  መቋቋም አለበት ይላል፡፡

ይህ የማርክስ የሶሻሊስት አብዮት ጽንሰ ሐሳብም በካፒታሊዝም ሥርዓት ውስጥ በቴክኖሎጂ ዕድገት በፍጥነት መገስገስ፣ ለሠራተኛው ከእጅ ወደ አፍ ለቀለብ ከሚበቃ  በላይ የሚከፍል የበለፀገ የካፒታሊዝም ማኅበረሰብ ከመፈጠር ጋር ማኅበራዊ የሀብት ይዞታና የሶሻሊዝም ሥርዓት ከካፒታሊዝም እኩል ፈጥኖ አለማደግ፣ የሕዝቡንም መሠረታዊ ቁሳዊ ፍላጎቶች ማርካት አለመቻል ይሻላል የተባለው ብሶ በመገኘቱ ምክንያት ከሸፈ፡፡ የሶሻሊዝም ሥርዓተ ኢኮኖሚ ፈራረሰ፡፡ የካፒታሊዝም ሥርዓተ ኢኮኖሚ ያለተቀናቃኝ ብዝበዛውን ቀጠለ፡፡

ኬንስ

ኬንስ ትኩረቱን ከግል ኢኮኖሚ አንስቶ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ላይ በማተኮር፣ የሠራተኛ ገበያዎች ቢፈጠሩምና በግል ኢኮኖሚ ደረጃ የሠራተኛ ፍላጎትንና የሠራተኛ አቅርቦትን የደመወዝ መጣኝ እኩል ቢያደርጉም እንኳ፣ በቁጠባ ከመዋዕለ ንዋይ በላይ መሆን ምክንያት የጠቅላላ አገራዊ ምርት ፍላጎት (የግል ፍጆታ፣ የመዋዕለ ንዋይ፣ የመንግሥት ፍጆታ፣ ኢምፖርት) አገሪቱ ከሚኖራት የሰው ኃይልና የካፒታል ማምረቻ ኃይሎች ምርት የማምረት አቅም (Potential Output Level) በታች ቢሆንም፣ ሥራ አጥነት ይፈጠራል በማለት የሥራ አጥነትን ምክንያት ከሠራተኛ ገበያ ጉድለት አውጥቶ ወደ ምርት ገበያ ጉድለት አመጣው፡፡ ስለዚህም በኬንስ ኢኮኖሚክስ ሥራ አጥነት የሚከሰተው በሠራተኛው ገበያ ውስጥ በደመወዝ ውጣ ውረድ የሠራተኛ ፍላጎትና የሠራተኛ አቅርቦት አለመጣጣም ምክንያት ሳይሆን፣ በምርት ገበያ ውስጥ የምርት ፍላጎት ከማምረት አቅም ወይም ከምርት አቅርቦት በታች ሲሆን ነው፡፡ በተለይም ቁጠባ ከመዋዕለ ንዋይ ሲበልጥ የምርት ፍላጎት ከምርት አቅርቦት ያንሳል፡፡ ምንም እንኳ ጥንታውያን ኢኮኖሚስቶች በግል ኢኮኖሚው ውስጥ የአንድ ማንኛውም ዓይነት ሸቀጥ ዋጋ ፍላጎትና አቅርቦትን እንደሚያመጣጥን ሁሉ፣ በብሔራዊ ኢኮኖሚውም የወለድ መጣኝ በጥሬ ገንዘብ ፍላጎትና አቅርቦት አማካይነት ብሔራዊ ቁጠባና ብሔራዊ መዋዕለ ንዋይን ያመጣጥናሉ ቢሉም፣ ኬንስ ግን በብሔራዊ ኢኮኖሚው ቁጠባና መዋዕለ ንዋይ የሚጣጣሙት በገቢና በምርት መካከል መመጣጠን ሲኖር ነው፡፡ ገቢ የምርት ፍላጎት ምንጭ ሲሆንም የማምረት አቅምም (የሰው ኃይልና ካፒታል) የምርት አቅርቦት ምንጭ ነው ይላል፡፡

ኬንስ በምርት ፍላጎት ማነስ ምክንያት ኢኮኖሚው ለማምረት ከሚችለው በታች ማምረት ዋናው መንስዔ የሕዝቡ ገቢ ማነስ ስለሆነ፣ መንግሥት የበጀት ጉድለት ውስጥም ቢሆን ገብቶ መሠረተ ልማትን በመገንባት የሥራ ዕድልና የገቢ ምንጭ ለሕዝቡ ፈጥሮ ኢኮኖሚውን ማስፋፋት አለበት ይላል፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዋዜማ ከ1930ዎቹ ታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስና የሥራ አጥነት ችግር ምዕራባውያን የወጡት በዚህ የኬንስ ኢኮኖሚክስ ፍልስፍና ነበር፡፡ በዚህም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰንና ዋና አማካሪያቸው ታዋቂው የጥሬ ገንዘብ ኢኮኖሚስት ሚልተን ፍሬድማን ሳይቀሩ፣ ‹‹አሁን ሁላችንም ኬንሳውያን ወይም የኬንስ ኢኮኖሚክስ ተከታይ ነን›› ብለው ነበር፡፡ ሆኖም ቴክኖሎጂ ሲያድግና የምዕራቡ ዓለም ሲዘምን በድርጅቶች ላይ በተፈጠረው ጫና በቅጥር ላይ ያሉት ሠራተኞች ደመወዝ በመጨመሩ ምክንያት፣ ለሠራተኞቻቸው ከምርታማነታቸው ዕድገት በላይ የፈጠነ የደመወዝ ዕድገት መክፈል በመገደዳቸው ለማካካስ የምርታቸውን ዋጋ ሲጨምሩ የዋጋ ንረት ተከሰተ፡፡ በሥራ ላይ ያሉ ሠራተኞች ከምርታማነታቸው በላይ የደመወዝ ዕድገት አገኙ፡፡ ሥራ ፈላጊ ሠራተኞችና ሥራ አጦች በበጎ አድራጎት ድጋፎች መረዳት እስከሚያስፈልጋቸው ድረስ በዋጋ ጭማሪው ምክንያት ኑሮም ተወደደባቸው፡፡

ስታግፍሌሽን

በ1970ዎቹ ሥራ አጥነትና የዋጋ ንረት ጎን ለጎን በመከሰታቸው ምክንያት ቀድሞ ይታመን የነበረውን በሥራ አጥነትና በዋጋ ንረት መጣኞች መካከል አንዱ ሲቀንስ ሌላው የመጨመር በተቃራኒ አቅጣጫ መጓዝ ሥርዓታዊ ተዛምዶ (Systematic Relationship) አለ የሚለው ተዛምዶውን በተነተነው ኢኮኖሚስት ስም ከግራ ወደ ቀኝ የሚወርድ የፊሊፕስ ደጋን መስመር (Phillips Curve) ተብሎ የሚታወቀው በግራፍ የሚመለከት አቅጣጫ አመልካች የሒሳብ ስሌት ኢኮኖሚ ትንታኔ ተፋለሰ፡፡ ከዚህም ጋር አብሮ በኬንስ ኢኮኖሚክስና በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ያለው እምነት በብዙዎች ዘንድ ቀነሰ፡፡ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲ ሥራ አጥነትንና የዋጋ ንረትን ማመጣጠን መቻሉም ጥርጣሬ ላይ ወደቀ፡፡

ይህ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ውጤት ላይ የተፈጠረ ጥርጣሬ ለነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ተሟጋች ጥንታውያን ኢኮኖሚስቶች እንደገና ማንሰራራት ዕድል ሰጠ፡፡ ኬንስ ራሱ ያቋቋማቸው የዓለም ባንክና ዓለም አቀፍ የጥሬ ገንዘብ ድርጅት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ (Neo-liberalism) ተሟጋች ሆኑ፡፡ ታላላቅ ኢኮኖሚስቶችም በሁለቱ ጎራዎች ተከፍለው የየራሳቸውን ኢኮኖሚክስ እየተነተኑ ይገኛሉ፡፡ ሁለቱን አጣምረው የግል ኢኮኖሚና የብሔራዊ ኢኮኖሚ ቅንጅት ኢኮኖሚያዊ ትንታኔ የሚሰጡም አሉ፡፡

ቅጥ ያጣ የደመወዝ ውሳኔና የሥራ አጥነት ችግር

ምንም እንኳ የኢኮኖሚ ባለሟሎቹ የመንግሥት ፖሊሲንና የሥራ አጥነት ተዛምዶን በመጣኝ መለኪያዎች ለክተው ለማስረዳት አቅም ቢያጡም፣ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ትኩረት በኬንስ ትንታኔ መንገድ ገቢን በማሳደግ ብሔራዊ ኢኮኖሚውን የማስፋፋት ሥልት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ሆኖም ያልተለካው የፖሊሲ ዕርምጃ ለጊዜው ውጤት ያሳየ ቢመስልም፣ በረጅም ጊዜ ውጤቱ  ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ከወዲሁ እየታየ ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ አብዛኛው ከተሜ ሠራተኛ የሚያገኘው ደመወዝ መጠን ሥራ ለመኖር ብቻ የሚያበቃ ከእጅ ወደ አፍ ያህል ነው፡፡ የሪካርዶና የማርክስ ጽንሰ ሐሳቦች ከዚያ ወዲህ ከፈለቁት የጥንታውያንና የኬንስ ጽንሰ ሐሳቦች በይበልጥ የኢትዮጵያን የሠራተኛ ገበያ ይገልጻሉ፡፡ የምርት ሸቀጦች ዋጋ ዕድገት ከዝቅተኛ ሠራተኞች ደመወዝ ዕድገት ይልቅ በጣም ፈጣን ነው፡፡ በሌላ በኩል በጣም ጥቂት የሆኑ በአገልግሎት ዘርፍ ላይ ያሉ ሠራተኞች፣ በደርግ ዘመን ያገኙት ከነበረው አንድ ሺሕ ብር በመቶ እጥፍ አድገው በወር እስከ መቶ ሺሕ ብር ደመወዝ ውስጥ ገብተዋል፡፡

ምርታማነታቸው ቢለካ የደመወዛቸውን ሩብ ያህል እንኳ እንደማይሆን ይታወቃል፡፡ ለንግዱ ማኅበረሰብ የረባ አገልግሎት ሳይሰጡ በዓመት ሁለት ሳምንት ኤግዚቢሽን ለማዘጋጀት በየወሩ ሰላሳ፣ አርባና ሃምሳ ሺሕ ብር ቆጥረው የሚቀበሉትን ሰሞኑን ተጠያቂነት የጎደላቸው ተብለው በመገናኛ ብዙኃን የተብጠለጠሉትና የቃላት ዱላ ያረፈባቸውን የንግድ ምክር ቤቶቻችንን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይበቃል፡፡ የሌሎች አገሮችን የደመወዝ ዕድገት ታሪክ ከእኛው ሁኔታ ጋር ብናነፃፀር ከ1950ዎቹ በኋላ በምዕራብ አውሮፓና በአሜሪካ በቴክኖሎጂ ዕድገት ምክንያት ምርታማነት ስለጨመረ፣ የደመወዝ መጠን ከምርት ሸቀጦች ዋጋ በላይ በፍጥነት አደገ፡፡ በመንግሥት ዝቅተኛው የደመወዝ ወለል መወሰን ተጀመረ፡፡ የሠራተኛ ማኅበራትም ለደመወዝና ለልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅሞች መሟገት ጀመሩ፡፡ በብዙ ምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ አገሮች ከብሔራዊ ገቢው ውስጥ የደመወዝ ድርሻ እስከ ሦስት አራተኛ ደርሷል፡፡ ለጡረተኞችና ለሥራ አጦች በደመወዝ የሚለካ እንክብካቤ ይደረጋል፡፡ ተረዳድቶና ተካፍሎ መብላት ልማዳዊ ወግ በሆነበት በእኛ ኅብረተሰብ ውስጥ የገቢ ምንጭ ፖሊሲን ለወጣቱ፣ ለአረጋዊው ብሎ መከፋፈል ከንቱ ውዳሴ ነው፡፡ አባት ልጁን ይጦራል፣ ልጅም አባቱን ይጦራል፡፡ ሕልውናችን የተመሠረተው በመረዳዳት ነው፡፡ አባት ያገኘው ልጅ አገኘው፣ ልጅ ያገኘውም አባት አገኘው ነው፡፡ ብዙ አገሮች በየጊዜው የጡረታ ክፍያን ከዋጋ ንረት ጋር የሚያስተካክሉ ሲሆን፣ ዛምቢያን የመሳሰሉ የአፍሪካ አገሮች እንኳ የመንግሥት ተቀጣሪዎች በሚያስቀምጡት የጡረታ መዋጮ ቦንድ ገዝተውላቸው፣ በሚገኘው ወለድ በጡረታቸው ጊዜ መዋያና መዝናኛ ቦታ ይሠሩላቸዋል፡፡

የወጣቱም የአረጋዊውም ሥራ ማጣት የዚህች አገር ከፍተኛ ችግር መሆኑ ከተስተዋለ ውሎ አድሯል፡፡ የኅብረተሰቡ ግማሽ የሚሆነው ዕድሜው ከአሥራ አምስት እስከ ሰላሳ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለው መሆኑ ደግሞ ችግሩ ለወደፊትም እንደሚቀጥል ጠቋሚ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 የኢትዮጵያንም ጨምሮ የአፍሪካዊ አማካይ ዕድሜ ከ25 እስከ 27 ዓመት ሆኖ ወጣት የበዛበት ትውልድ እንደሚሆን አዋቂዎች ይገምታሉ፡፡ ዕድሜ ቆጥሮ ማረፍ እንኳ በማይቻልባት ኢትዮጵያ ጡረተኞች ዛሬ በጥበቃ፣ በተላላኪነት፣ በጉዳይ አስፈጻሚነትና በደላላነት ከመሰማራታቸውም በላይ ሥራ ያጡም ሥራ ፍለጋ እየተንከራተቱ ነው፡፡

የዛሬ አርባ ዓመት የሆቴል የፆም በየዓይነቱ በአሥራ አምስት ሳንቲም ይበላ በነበረበት ጊዜ ለጡረታ ብለው መንግሥት ዘንድ ያስቀመጧት አንድ ብር፣ በያኔው ዋጋ ሰባት የሆቴል የፆም በየዓይነቱ ትገዛላቸው ነበር፡፡ ዛሬ ያችን ምሳ ለመብላት ሰላሳ ብር መክፈል ሲያስፈልጋቸው፣ በጡረታ መልክ ያስቀመጧትን ያችኑ  አንድ ብር እያገኙ ኑሮው ግን በምሳዋ የቀድሞ ዋጋ ሒሳብ ሁለት መቶ አሥር እጥፍ ተወዶባቸዋል፡፡ አባትና ልጅ ተረዳድተው በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ ደግሞ ይህ ሁለቱንም በድህነት አዙሪት ውስጥ የሚያሽከረክር ነው፡፡ የእነርሱን መንደላቀቅ የአገር ዕድገት አድርገው የሚቆጥሩ ሰዎች፣ ሕዝቡ የኢኮኖሚ ቀውስ አደጋ ላይ እንደሆነ ምን ዓይነት ማስረጃ ተቆጥሮ እንደምን ተደርጎ ቢነገራቸው ይሆን የሚያምኑትና እየተጎዳ ላለውና ወደፊት ለሚጎዳው ሕዝብ የሰብዓዊ ፍጡር መተዛዘን ስሜት የሚሰማቸው፡፡ የራሳቸውን መንደላቀቅ በሁለት ዓይናቸው ሲያዩ ለተጎዳው ሕዝብ በአንድ ዓይናቸው እንኳ ማየት የሚጀምሩት መቼ ይሆን? ዘለዓለም ይኖሩ ይመስል ለምን የእናቶች፣ የሕፃናትና የአረጋውያን ስቃይ አይታያቸውም? ለምንስ ቀጣዩን ትውልድ መከራ ትተውለት ያልፋሉ?

ʻእንደምን አለህ?ʼ ተብሎ የእግዜር ሰላምታ ሲሰጥ፣ ʻዛሬ ከነገ ይሻላልʼ ተብሎ ነገ የሚናፈቅ ሳይሆን የሚፈራ እንደሆነ የሚገምተውን ሕዝብ ቢያስቡት ምን አለበት? እናት ልጇን ተሰደድና ይለፍልህ ብላ ከአጠገቧ ልታርቀው የጨከነችበትን ጊዜ፣ አባት ዕድሜ ልኩን ያጠራቀመውን ጥሪት ለበረሃና ለባህር አሻጋሪዎች ከፍሎ ልጁን አልቅሶ የሚሸኝበትን ጊዜ፣ ከከተማ ወጣቶች ግማሽ ያህሉ በየመንገድ ዳሩ እየጮሁ ሳልባጅ ጨርቅና ቅራቅንቦ ነጋዴ የሆኑበትን፣ ለእያንዳንዱ ሕጋዊ ጉልት ቸርቻሪ ሕጋዊ ካልሆኑ አሥር እጥፍ ተቀናቃኝ ጉልት ቻርቻሪ ነጋዴዎች ለመከላከል ደንብ አስከባሪ መድቦ ዘብ ማቆም ያስፈለገበትን፣ ሰው ከሰው ለቁራሽ እንጀራ የሚናቆርበትና የሚደባደብበትን፣ የየመንደሩ ጎረምሶች እርስ በርሳቸው ተሿሹመው የመኪና ተራ አስከባሪና ዋጋ አስከፋይ የሆኑበትን ጊዜ እንደምን አያዩም?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው Getachewasfaw240@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

Standard (Image)

የተመድ ንግድና ልማት ጉባዔ በጣም ተሳሳተ

$
0
0

በጌታቸው አስፋው

በወደቀ ዛፍ ላይ ምሳር ይበዛበታል እንዲሉ በርካታ ዓመታት ፈጣን ዕድገት አስመዝግባችኋል እንዳላሉን ሁሉ እነዚህ የዓለም ባንክና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ንግድና ልማት ጉባዔ አሁን ምን ዓይተው ነው በአንድ ወር ውስጥ ግራ አጋቢ ዱላ ቀረሽ የማያስደስቱ ሪፖርቶች እየደጋገሙ የሚያወጡብን?

የዓለም ባንክ ሰዎች ብራችሁ በሰባ በመቶ ያህል ያላግባብ ውድ ስለሆነ አርክሱት ባሉን ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ የተመድ የንግድና ልማት ጉባዔ በብዙ ዓመታት የሒሳብ ቀመር የተለፋበትን መካከለኛ ገቢ የመግባት ምኞት አጣጣለብን፡፡ በጦርነት የሚታመሱት የመንና አፍጋኒስታን የቻሉትን እኛን አትችሉም አሉን፡፡ ያልገባን አይምሰላቸው፡፡ ብራችንን በዶላር ምንዛሪ በሰባ በመቶ ቀንሱ ያሉን ነፍስ ወከፍ ገቢያችን በዶላር ሲለካ ከሞላ ጎደል በግማሽ ወደታች እንዲወርድና መካከለኛ ገቢ እንዳንገባ አስበው ነበር፡፡ ብራችንን አናረክስም ብንላቸው በሌላ መንገድ ዙረው አሁንም ቢሆን መካከለኛ ገቢ ውስጥ ልትገቡ አትችሉም አሉን፡፡

ሞኝ መሰልናቸው እንዴ? ሞኞቹስ እነርሱ፡፡ በቁጥር መጫወት የተካንበት ጉዳይ እንደሆነ አያውቁም እንዴ? ሙያ በልብ ነው ብለን እንጂ እንኳንስ የአምናውንና የዘንድሮውን፣ የከርሞውንም ከዓመታት በኋላ የሚሆነውን ምንዛሪ ላይ ቆመን እናውቃለን፡፡ የመጣንበትንም የምንሄድበትንም አቋራጭ መንገድ የጉዟችንን ፍጥነትም እኛ እናውቀዋለን፡፡

ሙያ በልብ ነው እንዲሉ ጊዜው እስከሚደርስ በአዕምሯችን ውስጥ እንያዘው ብለን ነው ዝም ያልነው፡፡ ንገሩን ከአሁኑ አሳውቁን ካሉንም ʻነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌʼ እንዲሉ፣ ከቀደም ተሞክሯችን ምሳሌ ጠቅሰን እናስረዳቸዋለን፡፡ ምሳሌ እንዲሆነኝ ከዚህ ቀደም በአንድ ጽሑፌ ያቀረብኩትን ማስረጃና የማስረጃ ትንታኔ በድጋሚ አቀርበዋለሁ፡፡

እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በቢሊዮን ብር

 

ዘርፍ

የ2003 ምርት መጠን

 

ንፅፅር

በ1992 ዋጋ

በ2003 ዋጋ

ግብርና

64.7

212.5

3.3 እጥፍ

ኢንዱስትሪ

21.2

49.8

2.3 እጥፍ

አገልግሎት

73.4

207.2

2.8 እጥፍ

ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት

157.5

469.5

3.0 እጥፍ

ነፍስ ወከፍ ገቢ

1946

6267

3.2 እጥፍ

 

 

ምንጭ፡ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርና ብሔራዊ ባንክ 

በ1992 ዓ.ም. መለኪያ ቋሚ ዋጋ የተለካው የ2003 ዓ.ም. እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (Real GDP) መለኪያው ወደ 2003 ዓ.ም. ቋሚ የምርት ዋጋ መከለስ ምክንያት፣ በ1992 ዓ.ም. ቋሚ ዋጋ የተለካው የ2003 ዓ.ም. እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርትና ነፍስ ወከፍ ገቢ ሦስት እጥፍ ሆኗል፡፡

የምርት መለኪያ ዋጋውን በየአሥር ዓመቱ እንደምንከልሰውና የ2003 ዓ.ም. መለኪያ ቋሚ ዋጋ አሥር ዓመት ሙሉ ተንከባለው በተጠራቀሙ የዋጋ ግሽበቶች ባበጠው የ2013 ዓ.ም. ቋሚ ዋጋ መለኪያ እንደምንተካም እናውቃለን፡፡ የመካከለኛ ገቢ ደረጃ መግቢያ ዓመቱ በእኛ አቆጣጠር 2017 በአውሮፓውያን 2024 ሳይደርስ፣ በእኛ 2013 ዓ.ም. ከልሰን ነፍስ ወከፍ ገቢያችንን እንኳንስ አንድ ሺሕ ዶላር ሦስት ሺሕ ዶላርም እንደምናደርሰው እኛ እናውቃለን፡፡ ታዲያ እነዚህ የተከበሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ቸኩለው የማይሆን ወሬ ምን አስነገራቸው? ጊዜው ሲደርስ እንነጋገርበት አልነበረም እንዴ?

ሌላው መካከለኛ ገቢ ውስጥ አያስገባቸውም ብለው ያቀረቡት ምክንያት የአመጋገብና የትምህርት ጉዳዮችን በተመለከተ ነው፡፡ የደሃ ደሃና ደሃ የሆኑት ባያገኙም፣ በመካከለኛ ገቢ ውስጥ የሚገኙ ከተሜ ምሁሮቻችንና ልሂቆቻችን ለቁርስ ቢሻቸው ጮርናቄ፣ ቢሻቸው ሳምቡሳ፣ ቢሻቸው ሽልጦ፣ ቢሻቸው ርሚጦ፣ አምባሻም አማርጠው ለምሳም ቢሻቸው ሽሮ ተጋሚኖ፣ ቢሻቸው ሽሮ ፈሰስ፣ ቢሻቸው ሽሮ ፍርፍር አማርጠው ይበሉ የለም እንዴ?

እንደ እናንተ ለቁርስ የዳቦ ቅቤው፣ ማርማላታው፣ ሞርቶዴላው፣ እንቁላሉ፣ ወተቱ ዋናው ቁርስ የብርቱካን ጭማቂው ቀርቦ፣ ለምሳም ፕሪሞ፣ ሰኮንዶ፣ ቴርሶ፣ ዲዘርት እያሉ በቅደም ተከተል ያላግባብ ጠረጴዛ የሚያጣብብ በሰባትና ስምንት ሳህን የሚቀርብ በየዓይነቱ ምግብ መመገብ አቅቷቸው መሰላችሁ እንዴ? ጠረጴዛ ስለሌለ ቢኖርም እንዳይጣበብ ብለው እንጂ፡፡

በእርግጥም የምርታችንን ብዛትና የገቢያችንን መጠን መሬት አውርደን በገበያ ውስጥ ማሳየት አቅቶን ይሆናል፡፡ ዛሬ አንድ ሁለተኛ ደረጃ የጨረሰና በመንግሥት መሥሪያ ቤት በተላላኪነት የተቀጠረ ወጣት የወር ደመወዙ 600 ብር ሲሆን፣ ይህም ሸቀጥን በመሸመት አቅሙ በምግብ፣ በአልባሳትና በመጠለያ መሠረታዊ የኑሮ ደረጃ መለኪያዎች ስንመዝነው ሃያ አራት ኪሎ ጤፍ፣ አንድ ጂንስ ሱሪ፣ ለአንድ ጠባብ ክፍል ቤት የአሥር ቀን ኪራይ ይችላል፡፡ ይሁንና ይህ በተሃድሶው የሚሻሻል ጉዳይ ነው፡፡

ለመንግሥት ሠራተኛው/ዋ የሚከፈለው የወር ስድስት መቶ ብርም በሰዓት ሒሳብ ሲሰላ ሦስት ብር ከሰባ አምስት ሳንቲም እንደሚሆን ሳይታወቅ ቀርቶ አይደለም፣ ከአሜሪካው በሰዓት አሥር ዶላር ወይም በእኛ ገንዘብ በሰዓት ሁለት መቶ ሃያ ብር ዝቅተኛ ደመወዝ ጋር ሲነፃፀር ልዩነቱ የተጋነነ አይደለም ተብሎ እንጂ፣ በሌላ አይደለም ካስፈለገም በተሃድሶው የሚስተካከል ነው፡፡

ጡረተኞችም ድሮ በደህናው ጊዜ ጮማ ይቆርጡባት የነበረችውንና ለጡረታ ያጠራቀሟትን ያቺው አንድ ብር ሳትጨምር ሳትቀንስ ዛሬ ከሰላሳ ዓመት በኋላ ስትከፈላቸው አንድ ሎሚ እንኳ ልትገዛላቸው እንደማትችል ሳይታወቅ ቀርቶ አይደለም፡፡ ትክክል ካልሆነም በተሃድሶው ይስተካከላል፡፡

ነገ ምን እበላለሁ ብሎ የሚያስብና የሚጨነቅ ብዙ ሕዝብ በመገኘቱ ከዓለም አንደኛ እንደምንሆን ሳይገመት ቀርቶ አይደለም፡፡ ሰማንያ አምስት በመቶ የሚሆነው ገበሬ አሥራ አምስት በመቶ የሚሆነውን ከተሜ እንዴት አጥግቦ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ አይችልም ብለን ሳይገርመንና ሳንደነቅ ቀርቶም አይደለም፡፡ የመኪና መንገድ ጠፍቶ ገበያ ባይወጣም ምርቱ የተትረፈረፈ ነው፡፡ ይህም በተሃድሶው መልስ የሚያገኝ ጉዳይ ነው፡፡

በበለፀጉት አገሮች ሁለት በመቶ የሚሆነው ገበሬ ዘጠና ስምንት በመቶ የሚሆነውን ከተሜ የተመጣጠነ ምግብ አጥግቦ እንደሚመግብም እናውቃለን፡፡ እንኳንስ ለሰው ለድመትና ለውሾችም የማስታወቂያ ጋጋታ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን እንደሚያጣብብ ሳንሰማ ቀርተን አይደለም፡፡ ቢሆንም ቢሆንም ድክመታችን ብቻ ሳይሆን ጥንካሬያችንም ቢቆጠር እንደ በለፀጉት አገሮች ቢሊየነሮችንም ያፈራን መሆኑ ቢለካ፣ እንኳን ለመካከለኛ ገቢ ደረጃ ለከፍተኛ ገቢ ደረጃ ልንታጭም እንችላለን፡፡ ይህም ትክክል ካልሆነ በተሃድሶው ይስተካከላል፡፡

ታዋቂው ኢኮኖሚስት ዴቪድ ሪካርዶ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት በገበያ ኃይሎች የሠራተኛ ፍላጎትና አቅርቦት መስተጋብር ሥራ አጥነት የሚወገደው፣ የደመወዝ መጣኝ ሠራተኛው ትውልድ ለመተካት በማይፈልግበት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ሲሆን ነው ብሎ አልነበር?

በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ተከታይነት ከአንደኞቹ እኩል ሆነን የሪካርዶን ጽንሰ ሐሳብ ተጠቅመን የሕዝብና የኢኮኖሚ ማመጣጠን ፖሊሲ መንደፍ ይሻላል ብለን እንጂ ሳናውቅ ቀርተን አይደለም፡፡ ሁልጊዜ ልማታዊ ብቻ ሆነን ልንኖር ኖሯል እንዴ? ካላስፈለገም በተሃድሶው የሚስተካከል ነው፡፡

በትምህርቱስ ቢሆን አስተምረን ለባዕድ አገሮች በግርድናና በሎሌነት እንዲያገለግሉ ላክናቸው እንጂ፣ በመንግሥት ደረጃ ብቻ ከሰላሳ በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተን በየዓመቱ በመቶ ሺዎች አስመርቀን የለም እንዴ? በእርግጥ ብዙዎቹ ወረቀቱ ብቻ እንጂ ዕውቀቱ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ይህም ቢሆን የግለሰቡ ድክመት እንጂ የአገር ድክመት አይደለም፡፡ በግለሰብ ድክመት ደግሞ አገር ልታገኝ የሚገባትን መካከለኛ ገቢ የመግባት ደረጃ ልታጣ አይገባትም፡፡ ካልሆነም በተሃድሶው ይስተካከላል፡፡

በስኬታችን ስንትና ስንት ሽልማት ያገኘንበትን በዩኔስኮ የተመሰከረልንን የልጆች ትምህርት፣ የአዋቂዎች ትምህርት እየተባለ ለመካከለኛ ገቢ ደረጃ አልበቁም እንባላለን እንዴ? ይኼስ በወደቀ ዛፍ ላይ ምሳር ይበዛበታል እንዲሉ ገና ለገና በወንድማማቾች መካከል ሁከት ተከስቶ ነበር ብለው ቤንዚን ሊያርከፈክፉበት አስበው ነው እንጂ፣ እንደ ዘፋኟ እነርሱ አልነበሩም ʻበማደግም በመረጋጋትም የእኛ አንደኛʼ እያሉ ሲዘፍኑልን የነበሩት?

የተመድ ንግድና ልማት ጉባዔ ሰዎች አትቸኩሉ፣ ቸኩላችሁም አትሳሳቱ፡፡ በእኛ 2013 በእናንተ 2020 እንገናኝ፡፡ የምርት መለኪያ ዋጋችንን ከልሰን በቅጽበት ነፍስ ወከፍ ገቢያችንን በሦስት እጥፍ አሳድገን መካከለኛ ገቢ ውስጥ መግባት አለመግባታችንን ያኔ ትወስናላችሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getachewasfaw240@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

Standard (Image)

አገራዊ ፋይዳ ያላቸው መረጃዎች

$
0
0

በጌታቸው አስፋው

አንድ ፈላስፋ አንድ ጊዜ ለጓደኛው ብዙ ገጽ ደብዳቤ ጽፎ የደብዳቤው መጨረሻ ላይ፣ ‹‹ጓደኛዬ ይቅርታ አድርግልኝ ብዙ ገጽ ደብዳቤ የጻፍኩልህ ጊዜ ስላጣሁ ነው፤›› አለው፡፡ ማሰቢያ ጊዜ አጥቼ ዝባዝንኬውን ሁሉ በማተት ጻፍኩልህ ማለቱ ነው፡፡

ለመንግሥት የሚሠሩ የኢኮኖሚ ባለሟሎች ምን ሠርተው ጊዜ እንደሚያጥራቸው ባይታወቅም፣ ጊዜ አጥሯቸው ለባለሥልጣናት የሚያቀርቧቸው ሪፖርቶች የተመረጡ ጥቂት ሆነው ነገር ግን ብዙ ነገሮችን የሚገልጹ አይደሉም፡፡ በሥራ አስኪያጅ ደረጃ የሚወሰኑ ዝባዝንኬ የግል ኢኮኖሚ ጉዳዮች ይበዛባቸዋል፡፡

ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የፖለቲካ ተሿሚዎች የኢኮኖሚ ዝባዝንኬዎችን (Economic Jargons) ማወቅ አይጠበቅባቸውም፡፡ የተመረጡና የተጠቃለሉ ጥቂት መረጃዎች ለፖሊሲ ውሳኔና ለፖለቲካ ፍጆታ ያህል ቢያውቁ በቂ ነው፡፡

እነኚህ ተመርጠው የተጠቃለሉ ጥቂት መረጃዎችም በመገናኛ ብዙኃን ለሕዝብ በባለሥልጣናት ሲቀርቡ፣ ለባለሙያም ስለሚደርሱና ሲተነተኑ ደግሞ አገራዊ ፋይዳ የሌላቸውና ኢሳይንሳዊ ሆነው ትዝብት ላይ እንዳይጥሉ የኢኮኖሚ ባለሟሎች ኃላፊነት ነው፡፡

አንዳንዴ ደግሞ እጅግ የተጠቃለሉ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውና ለኢኮኖሚ ባለሟሎች ለራሳቸውም ሾላ ድፍን የሆኑ የብሔራዊ ኢኮኖሚ መረጃዎችን ለሕዝብ ንግግር እንዲያደርጉ ይሰጧቸዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም በሰሞኑ ንግግር ከአገር ውስጥ ጥቅል ምርት አርባ በመቶ የሚሆነው መዋዕለ ንዋይ ወይም አዲስ ካፒታል ነው የሚል ይገኝበታል፡፡ ጥሩ ነው አሁን መነጋገር እንችላለን፡፡

የመዋዕለ ንዋይ መጠኑ ከኢኮኖሚ ዕድገቱ ጋር ተገናዝቦና በሥሌት ተተምኖ ያመጣው ለውጥ ካልተለካ፣ ጥቅሙና አገራዊ ፋይዳው አይታወቅም ብለን እንሟገታለን፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ጋዜጣዊ መግለጫ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት፣ ከአገር ውስጥ ምርታችን አርባ በመቶውን ለመዋዕለ ንዋይ አውለን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ቢገጥመን አይገርምም ሌሎች አገሮችም በእኛ የዕድገት ደረጃ ላይ በነበሩ ጊዜ አጋጥሟቸው ተወጥተውታል፡፡ ለእኛም ጊዜያዊ ችግር እንጂ የሚያስፈራ አይደለም የሚል ነበር፡፡

 እኔም ያስፈራል አያስፈራም በሚለው ላይ የተለየ አቋም ለማንፀባረቅ ሳይሆን ከእምነቱ ባሻገር መፍትሔም እንዳለ ለመግለጽ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ትርጉም መዋዕለ ንዋይ ምን እንደሆነና መጠኑ ለኢኮኖሚው ዕድገት ምን አንድምታ እንዳለው የማውቀውንና የማስበውን ለማካፈል እሻለሁ፡፡

ስለሆነም ሾላ በድፍኑ ሆኖ ለቀረበው ከአገር ውስጥ ጥቅል ምርት አርባ በመቶው መዋዕለ ንዋይ ነው፡፡ መረጃ በባለሙያ ደረጃ ብቻ ሊታወቁ የሚችሉ መዋዕለ ንዋይን የተመለከቱ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዝባዝንኬዎችን ግልጽ ላደርግ እፈልጋለሁ፡፡

እነሱም በቅደም ተከተል ሁለቱ የመዋዕለ ንዋይ ዓይነቶችና ትርጉማቸው፣ የመዋዕለ ንዋይ ዕድገት ለምን ይጠቅማል? በውጭ ኢኮኖሚ የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለትና በውስጥ ኢኮኖሚ የመዋዕለ ንዋይና ቁጠባ ጉድለት መስተጋብር፣ የሚሉ ናቸው፡፡

ሁለቱ የመዋዕለ ንዋይ ዓይነቶች

በብሔራዊ ኢኮኖሚ መዋዕለ ንዋይ በሁለት ዓይነት ሲከፈል አንዱና ዋናው ቋሚ ካፒታል ምሥረታ (Fixed Capital Formation) እና ሁለተኛው ከዘንድሮ ለከርሞ የተላለፈ ሳይሸጥ የቀረ ምርትና ግብዓተ ምርት ወይም በከፊል የተፈበረኩና ጥሬ ዕቃዎች ክምችት (Inventories) ናቸው፡፡ ቋሚ ካፒታል የሚፈለግና የሚታቀድ መዋዕለ ንዋይ ሲሆን፣ የቀረ ምርትና ግብዓተ ምርት ግን የማይፈለግና የማይታቀድ መዋዕለ ንዋይ ነው፡፡

ስለዚህም የኢኮኖሚ ትንታኔ በሚሰጥበትና ዕቅድ በሚታቀድበት ጊዜ የታቀደ መዋዕለ ንዋይና ትክክለኛ መዋዕለ ንዋይ (Planned and Actual Investment) የተለያዩ ጽንሰ ሐሳቦች መሆናቸውን ማጤን ያስፈልጋል፡፡

ለመሆኑ ከአርባ በመቶው መዋዕለ ንዋይ ውስጥ የቋሚ ካፒታሉና ሳይሸጥ የቀረው ጥሬ ዕቃና በከፊል የተመረተ ድርሻ፣ በባለሟሎቹና ዕቅድ አውጪዎቹ ይታወቅ ይሆን? አውቃለሁ የሚል ይናገር፡፡

የመዋዕለ ንዋይ ዕድገት ለምን ይጠቅማል?

መዋዕለ ንዋይ ወይም አዲስ ካፒታል የወደፊቱን ምርት ዕድገት መጠን ለማሥላት ይጠቅማል፡፡ የካፒታልና የምርት ጥምርታም (Capital - Output Ratio) በለውጥ አምጪ ምክንያቶችና በለውጥ መካከል በሚፈጠር ውስጣዊ መስተጋብራዊ ሒደት አማካይነት፣ የጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት የሚተነበይበት ሥሌት ነው፡፡

አንድ ለረጅም ጊዜ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ሒሳብ ሥራ በኃላፊነት ያገለገለ ጓደኛዬ እንዳጫወተኝ ከሆነ፣ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት በደርግ ጊዜ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርትን ለመተንበይና ለማቀድ በእያንዳንዷ ተጨማሪ ካፒታል ምን ያህል ተጨማሪ ምርት እንደሚመረት (Incremental Capital-Output Ratio (ICOR) ይለካ ነበር፡፡

በዚህ ዘመን የአገር ውስጥ ጥቅል ምርትን ለመተንበይና ለማቀድ የካፒታልን ምርታማነት ወይም የቀጣይ ካፒታል ቀጣይ ምርታማነት (Marginal Productivity of Capital) ተለክቶ አይታወቅም፡፡ 11 በመቶ አገራዊ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት ይገኛል ለማለት በኢሳይንሳዊ መንገድ የግብርና ምርት መጠን ጆንያ መቁጠር ነው የሚቀድመው፡፡ ለንደን ኢኮኖሚክስን ተምሮ ጆንያ ቆጥሮ ዕቅድ ማቀድ እንዴት ይሆናል?

ስለዚህም ስለ ብሔራዊ ኢኮኖሚ ሲናገሩ ከጥሬ መረጃ ባሻገር የለውጥ ምክንያቶችና የለውጥ መስተጋብራዊ ተዛምዶን፣ በመጠንና በዋጋ ተምኖ እውነቱን ከነምናምኑ መናገር አገርን ከጉዳት ያድናል፡፡

በውጭ ኢኮኖሚ የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለትና በውስጥ ኢኮኖሚ የመዋዕለ ንዋይናቁጠባ ጉድለት መስተጋብር

የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚያጋጥመው በዋናነት በቁሳዊና በአገልግሎት ሸቀጦች ኤክስፖርት ኢምፖርት ክፍተት ሲሆን፣ በሚዘረጋላቸው የዕርዳታ እጅ የሚተማመኑ ታዳጊ አገሮች በዕርዳታ ማነስም ለውጭ ምንዛሪ እጥረት ይጋለጣሉ፡፡ የኤክስፖርት ኢምፖርት ክፍተት በዕርዳታ ሊሸፈን ካልቻለ ደግሞ የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለት ይሆናል፡፡

የውስጥ ኢኮኖሚ ጉድለትም በቁጠባና በመዋዕለ ንዋይ መካከል ያለ ክፍተት ነው፡፡ የውስጡ ጉድለት ለውጩ ጉድለት ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ የውጪውም ጉድለት ለውስጡ ጉድለት ምክንት ይሆናል፡፡

የውጭ ኢኮኖሚ ክፍያ ሚዛን ተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለትና የመዋዕለ ንዋይና ቁጠባ ክፍተት የውስጥ ኢኮኖሚ ጉድለትም በመጠን እኩል ናቸው፡፡ የውጭውን ጉድለት በውስጥ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማስተካከል፣ የውስጡን ጉድለትም በውጭ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማስተካከልም ይቻላል፡፡

ስለሆነም በውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ላይ ተፅዕኖ ለማድረግ በምንዛሪ መጣኝ፣ በታሪፍ፣ በኮታ ወይም በኤክስፖርት ማነቃቂያ የሚወሰድ ዕርምጃ በውስጥ ኢኮኖሚ፣ በቁጠባና በመዋዕለ ንዋይ ላይ ተፅዕኖ ያደርጋል፡፡ በውስጥ ኢኮኖሚ መሻሻል የውጪውን የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለት ለማስወገድም ቁጠባን ከመዋዕለ ንዋይ ማስበለጥ ያስፈልጋል፡፡

መዋዕለ ንዋይ ከጥቅል የአገር ውሰጥ ምርት 40 በመቶ ሲሆን፣ ቁጠባ ግን 22  በመቶ ብቻ ስለሆነ የመዋዕለ ንዋይና የቁጠባ ክፍተት ከፍተኛ ነው፡፡ ይህን ያህል ክፍተት ቁጠባን በማበረታታት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይቀረፋል ብሎ ማሰብም ይከብዳል፡፡

ቆጣቢዎችና መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች መንግሥት ወይም ግለሰቦች ስለሚሆኑ፣ የየትኛው አካል ቁጠባ ወይም መዋዕለ ንዋይ ትኩረት እንደሚያስፈልገውም በሚገባ መጠናት አለበት፡፡

የግል ቁጠባና መዋዕለ ንዋይ በፍላጎትና አቅርቦት በገበያ ውስጥ የሚወሰን ስለሆነ፣ በኢኮኖሚው ውስጣዊ ኃይል ግፊት የሚመራ (Autonomous) ነው፡፡ የመንግሥት ቁጠባና መዋዕለ ንዋይ ግን የፖሊሲ ውጤት (Policy Driven) ነው፡፡ እንደ ግል የሚቆጠሩት የመንግሥት ድርጅቶች መዋዕለ ንዋይ ወጪም በአብዛኛው የፖሊሲ ውሳኔ እንጂ በገበያ ውስጣዊ ኃይል የሚመራ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ አውቆ በውስጡ ኢኮኖሚ መስተካከል የውጩን ጉድለት እናስወገድ? ወይስ በውጭ ኢኮኖሚ መስተካከል የውስጡን ጉድለት ማስተካከል ከሚሉት አማራጮች ተስማሚውን መምረጥ ወይም ሁለቱን ማጣመር ያስፈልጋል? የውጩን ኢኮኖሚ ለማስተካከል ብዙ ዓመት ተደክሞ ያልሆነ ነገር ነው፡፡ ስለዚህም የውስጡን ኢኮኖሚ ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ መዋዕለ ንዋይ ከቁጠባ ስለሚበልጥ ወይም መዋዕለ ንዋይን መቀነስ ወይ ቁጠባን ማሳደግ ያስፈልገል፡፡

የውጭ ጉድለቱ በውስጥ ኢኮኖሚ የፖሊሲ ለውጥ ካልተስተካከለ የውጭ ዕዳ ይቆለላል፡፡ ይኼም አበዳሪን ያሸሻል፡፡ የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይንም ያባርራል፡፡ ምናልባትም እንደ አራጣ አበዳሪ የሆዷን በሆዷ ይዛ ቻይና ብቻ ልትሆን ትችላለች አባብላም ላበድራችሁ የምትለው፡፡

 ሰሞኑን በመገናኛ ብዙኃን በተነገረ ወሬ ምዕራባውያን አገሮች በመረጡት ወደ ውስጥ ኢኮኖሚያቸው የመመልከት አዝማሚያ ምክንያት፣ እ.ኤ.አ. የ2017 የአፍሪካ ኢኮኖሚ ዕድገትም ከቻይና የማበደርና የመርዳት በጎ ፈቃድ ጋር እንደሚያያዝ ምሁራኖቻቸው ይገምታሉ፡፡ 

      ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸውgetachewasfaw240@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ የቅድመ ሰው ዘር መገኛ አዲስ ገጽ

$
0
0

በሸዋዬ መርን

ኢትዮጵያ በዓለም ቀዳሚና ገናና የዓለም ሥልጣኔ ቁንጮ በመሆን የምትጠቀስ አገር፣ የተለያዩ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ ብርቅዬ ቅርሶች ባለቤት ናት። የ13 ወራት የፀሐይ ብርሃን ባለፀጋ የገነት ተምሳሌት፣ የዋህና እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ መኖሪያ፣ በልዩነት ውስጥ የአንድነት ተምሳሌት፣ ለዘመናት ነፃነቷን ጠብቃ የኖረች የጀግኖች ምድር፣ የታቦተ ጽዮንና የግማደ መስቀሉ መገኛ እንቁ ምድረ ኢትዮጵያ።

በዘመናችን ካሉ ኃያላን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በላቀ ደረጃና በዓለም ላይ ከተፈጠሩ የሰው ልጆች የፈጠራ ውጤቶች፣ በተለይ ደግሞ የኪነ ሕንፃ ጠበብቶች በቀደምትነት እየመሩ ያሉ ውስብስብና ከአዕምሮ በላይ የሆኑ የምህንድስና ባለቤት መሆኗን የሚመሠክሩ አንድ ወጥ ከሆነ ድንጋይ የተፈለፈሉ 11 ውቅር አብያተ ክርስቲያናት (ላሊበላ)፣ አክሱምና የጎንደር ቤተ መንግሥት ኪነ ሕንፃዎች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።

 ምሥጋና ለቀደሙት ባለብዙ ጥበብ እሳቤ ባለቤቶች አባቶቻችን ይሁንና እነዚህ ተዓምራዊ ቅርሶች የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ሕዝብ ቅርስ ሆነው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና የባህል ድርጅት ከተመዘገቡ ሰንብተዋል። እስካሁን በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበቻቸው ቅርሶች 11 የደረሱ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ ሦስቱ የማይዳሰሱ ቅርሶች ናቸው። የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የአክሱም ሐውልት፣ የጁገል ግንብ፣ የታችኛው አዋሽ ስምጥ ሸለቆ፣ የላይኛው ኦሞ፣ ስሜን ብሔራዊ ፓርክ፣ የጢያ ትክል ድንጋይ ከሚዳሰሱት ይመደባሉ፡፡ መስቀል ደመራ፣ ፊቼ ጨምበላላና የገዳ ሥርዓት ደግሞ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡት የማይዳሰሱት ቅርሶች ውስጥ ይመደባሉ።

እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ አገራችን ግሩም ድንቅ የሆኑ ሌሎች የቱሪዝም መስህብ ቦታዎች እንደነ ሶፍ ዑመር ዋሻ፣ የባሌ ተራሮች፣ ነጭ ሳር፣ ስሜን ተራሮች፣ የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮ (ከደብረ ብርሃን በስተሰሜን 145 ኪሜ) በጓሳ ተራራ ላይ የምትገኝ፣ አርባ ምንጭ የአዞ እርባታ፣ ጣና ሐይቅና ላንጋኖ ጥቂቶቹ ናቸው።

እነዚህ ቅርሶች የማንነታችን መገለጫዎች፣ ብሔራዊ ኩራቶቻችን፣ የኢኮኖሚያችን ዋልታዎች፣ የውጭ ምንዛሪ ምንጮቻችን ብሎም አንድነታችንን የሚያጠነክሩ የህልውናችንና የታሪካችን መሠረቶች ናቸው። ስለሆነም እንደ ዓይናችን ብሌን ጠብቀን በአግባቡ ልንከባከባቸውና ለቀጣይ ትውልድ የማስተላለፍ የሞራል ግዴታ አለብን።

በቱሪዝም ኢንዱስትሪ የሦስቱ ‘መ’ዎች ምንዛሪዎች

በአንድ ቦታ ወይም ጊዜ ቱሪዝም ተካሄደ/ሆነ ለመባል ሦስቱ ነገሮች የግድ መሟላት ይኖርባቸዋል። በማንኛውም ሁኔታ አንድ አገር የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ብሎም ዘርፉን ትኩረት ሰጥቶ መሥራትና መደገፍ ካለበት እነዚህ ሦስት የማይነጣጠሉ የቱሪዝም ምንዛሪዎች (Components) ላይ መሥራት ይኖርበታል።

የመጀመሪያው ጉዳይ የቱሪዝም መስህብ (Attraction) ቦታችን የሚመለከት ሲሆን ታሪካዊ ቅርሶች፣ ባህላዊ ምግብና መጠጦችን፣ ባህላዊ ዳንሶችን፣ ቋንቋዎች፣ የአኗኗርና የአመጋገብ ሥነ ሥርዓቶችና ሁነቶችን የሚያካትት በሙሉ መስህብ ተብሎ ይጠቃለላል። ስለዚህ እነዚህ የቱሪስት መስህቦች በሌሉበት ስለቱሪዝም ማውራት 'ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ'እንደሚባለው የአገራችን ብሒል ይሆናል ማለት ነው።

በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው የቱሪዝም አካል ደግሞ ቱሪዝም ኢንዱስትሪው ለአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገቱ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ይወስነዋል። ምክንያቱም አንድ ቱሪስት በአራቱም ማዕዘናት የሚገኙ የቱሪስት ቦታዎችን ሲጎበኝ በቆይታው መሠረታዊም ፍላጎቶች የሚባሉትን እንደ ምግብ፣ የሆቴል አገልግሎትና የመሳሰሉትን መስተንግዶዎች (Accommodations) ካላገኘ ወይንም ዝግጁ ካልሆኑ በስተቀር የውጭ ምንዛሪን የማግኘቱ ጉዳይ የህልም እንጀራ ሆኖ መቅረቱ አያጠራጥርም።

በመጨረሻ ደረጃ ለቱሪዝም ዕውን መሆን ወሳኝ ሚና የሚጫወተው መገናኛ መንገዶች/ተስማሚነት (Amenity) የሚባለው ነው። የሰው ልጅ በተፈጥሮው በሄደበት ቦታና ጊዜ የሚስማማው የአየር ንብረት፣ የመዝናኛ ቦታዎች፣ የግብይት አገልግሎቶችን እስካላገኘ ድረስ ምንም ያህል የሚያስደንቅ ጥበብ፣ ቅርስ ወይም ቦታ ቢጎበኝ በቆይታው አለዚያም በጉዞው ወቅት ወይም ከደረሰ በኋላ ከድካሙ የሚጠግነውና የሚያዝናናው አገልግሎትና ምቾት ካላገኘ፣ በፈቃዱ ለስቃዩ ብር እንደማይከፍል ዕሙን ነው። ስለዚህ በተለያዩ የቱሪዝም ቦታዎቻችን መዳረሻ ደረጃውን የጠበቀ መንገድ፣ ዘመናዊ ሆቴሎችና መዝናኛ ማዕከላት ሊሟሉ ይገባል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ብዙ የቤት ሥራዎች ያሉባትና የዘርፉን ህልውና ከሚወስኑት ጉዳይ አንዱ ሆኗል።

ቱሪዝም ለአገራዊ ኢኮኖሚ ያለው አስተዋፅኦ

ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ እየተባለ የሚጠራው ቱሪዝም ለአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታል። ለኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት መሻሻል የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ግን ከሴክተሩ በሚገኘው የገቢ መጠን ይወሰናል። ቱሪዝም በዓለም ላይ አንደኛው በተለይ ለታዳጊ አገሮች የኢኮኖሚ ምንድግና (Economic Transformation) ከፍተና አስተዋፅኦ እያበረከተ መጥቷል።

ይህን በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ የቱሪዝም ዘርፉን ከማስተዋወቅና የውጭ አገር ጎብኝዎችን ልብና ኅሊና ከማማለል ሥራ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ መሄድ እንዳለበት የዘርፉ ባለ እሳቤ ልሂቃን ያሳስባሉ።

በተለይ በታዳጊ አገሮች ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው መቀጨጭና የሚፈለገውንና የሚጠበቅበትን ያህል የገቢ ምንጭ ላለማስገኘቱ የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ችግሩ በተለይ በአፍሪካ ሥር የሰደደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አፍሪካን በረሃብ የተመታችና የችግሮች ቤት፣ በብጥብጥና በበሽታ የተወረረች አድርጎ መመልከት ዋነኛ ምክንያቱ ነው፡፡ እውነታው ግን አፍሪካ የብዙ ተፈጥሮአዊ ሀብቶች ባለቤት፣ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛና የተለያዩ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን በአግባቡ አለመረዳት ነው።

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚዳስሱ የተለያዩ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያ 2.9 ቢሊዮን ዶላር በዓመት ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው ታገኛለች። እ.ኤ.አ. በ2015 ቱሪዝም ለአጠቃላይ ብሔራዊ ምርት 9.2 በመቶ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ 8.4 በመቶና 2.9 በመቶ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ  አስተዋፅኦ እንዳበረከተ መገንዘብ ይቻላል።

ለዚህ መሠሰሉ አስተዋፅኦ ደግሞ ለቱሪዝም ዘርፉ የሚመጥን ዘመናዊና ምቹ የመሠረተ ልማት አቅርቦት፣ እንዲሁም በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ጠንካራ ትስስር ፈጥሮ መሥራትን ይጠይቃል።

ኢትዮጵያ በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዷ ከቱሪዝም ዘርፍ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ግብ አስቀምጣ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች። ይህን ግብ ለማሳካትና በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሰነዱ ላይ የተለያዩ የማስፈጸሚያ ስልትና አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል። ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ እምቅ ሀብት ለተቀረው ዓለም በሚገባ ማስተዋወቅና የቱሪስት ፍሰትን በመጨመር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባንን የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪዝም አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማጠናከርና ማብዛት፣ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሆቴሎችን በብዛትና በጥራት መጨመር የመሳሰሉትን ዋና ዋና አቅጣጫዎች በማስቀመጥ እየተሠራ ይገኛል። እነዚህን ሁሉ ተግባራት ለማከናወን በአገር አቀፍ ደረጃ የቱሪዝም ካውንስል የተቋቋመ ሲሆን፣ በዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይልና በጥናትና ምርምር የተደገፈ  የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለመምራት የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የምርምር ማዕከላትን ለማጠናከር ክትትልና ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

የቱሪዝም ዘርፉን ማስተዋወቂያ መንገዶች

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ቱሪዝም በተለይ ለወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል ትልቅ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም፣ ድህነትን የመቀነሻ አንዱ መንገድ እንዲሁም ለሰብዓዊ ልማትና ለአካባቢያዊ ሥነ ምኅዳራዊ  ደኅንነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል። የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በተለያየ መንገድ ለአገራዊ ኢኮኖሚው መሻሻልና ዕድገት ጉልህ  ሚና ቢኖረውም፣ ዘርፉ ግን የተለያዩ  ፈተናዎች ተደቅነውበት ይስተዋላል ። የመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ የተደራጀ የቱሪዝም ማስተዋወቂያ ሥልቶች አለመቀየሳቸው፣ በዘርፉ የተካነ የሰዉ ኃይልና የድጋፍ ማነስ ችግሮች መኖር ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያ የቱሪዝም  ዘርፉን በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቁ ረገድ ብዙ መጓዝ ቢጠበቅምባትም፣ በአሁኑ ወቅት በመጠኑም  ቢሆን  እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች ። ቱሪዝምን ለውጭ ጎብኚዎች የመሸጥ ጥበብ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም  የሚከናወን ይሆናል። ከእነዚህም ውስጥ የመተዋወቂያ ጉዞ ማዘጋጀት፣ ብሔራዊ ግሎትም (Nation Branding)፣ ሮድሸው፣ የንግድ ትርዒት፣ ዲጂታልና የኅትመት ውጤቶችን  በመጠቀም ማስተዋወቅ ይቻላል።

በጣም የተሻለ የቱሪዝም ማስተዋወቂያ መንገድ የሚባለው የመተዋወቂያ ጉዞ ማዘጋጀት ነው። ይህ መንገድ የሚከናወነው ለውጭ የጉዞ ወኪሎች፣ ጋዜጠኞችና ቱር ኦፕሬተሮች ወደ ተለያዩ የአገራችን የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ጉዞ እንዲያደርጉ በማመቻቸት የሚደረግ ሥልት ነው ። ይህን የማስታዋወቂያ  መንገድ መጠቀም የረጅም ጊዜ ተፅዕኖ ለመፍጠርና እነዚህ የጉዞ ወኪሎች፣ ጋዜጠኞችና ቱር ኦፕሬተሮች በቱሪስት መዳረሻዎች ያዩትን ድንቅ የተፈጥሮና ታሪካዊ ቅርሶች እንዲሁም ስለቱሪዝም  ኢንዱስትሪው በጎ ጎን በመጻፍ፣ በመናገርና ኢትዮጵያን በቱር ፓኬጃቸው በማስገባት ብሎም ወደ አገራቸው ሲመለሱ ለተከታዮቻቸው በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠሪያ ሥልት መሆኑ ይነገራል።

የኅትመት ውጤቶችን በመጠቀም የቱሪዝም ዘርፉን የማስተዋወቅ ዘዴ ደግሞ በዝቅተኛ ወጪ ብዙ ሰዎችን መድረስ የሚስያችል የቱሪዝም መሸጫ ጥበብ ነው። እነዚህ የኅትመት ውጤቶች ውብ የቱሪስት መስህብ ቦታዎችን፣ ፎቶግራፎችና ዲዛይኖችን ሆነው በተለያዩ አገሮች ለሚገኙ ቱሪስቶችና የጉዞ ወኪሎች የሚሰጡ ናቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትና ኤግዚቢሽኖች ላይ መሳተፍ ሌላው የቱሪዝም ማስተዋወቂያ መንገድ ነው። የዚህ ማስተዋወቂያ ሥልት ዋና ዓላማው ኢትዮጵያ የታደለቻቸውን የተፈጥሮና ታሪካዊ ቅርሶቻችንን ለውጭው ዓለም ማስተዋወቅ ብሎም የአገሪቱን ገጽታ መገንባትን መሠረት ያደረገ ነው። በዚህ የንግድ ትርዒት ላይ በዘርፉ የተሠማሩና የሚያገባቸው ባለድርሻ አካላት የሚባሉት አገር በቀል የጉዞ ወኪሎች፣ ቱር ኦፕሬተሮች፣ የሆቴል ባለቤቶችና ዝነኛው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጋራ በመሳተፍ በትርዒቱ ከሚሳተፉ አቻዎቻቸው ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ ያግዛል።

በዚህች ሉላዊና በቴክኖሎጂ በመጠቀች ምድር ላይ አካላዊ የቱሪዝም ማስተዋወቂያ ዘዴ ብቻ ዋጋ ሊኖረው አይችልም። ስለሆነም ለአጠቃቀም ቀላልና ብዙ የዓለማችን ቱሪስቶችን በቀላሉ መድረስ የሚያስችል የደረጃውን የጠበቀና ተደራሽ ድረ ገጽ መገንባት ያስፈልጋል (Twitter, Facebook, YouTube and Blogs)፡፡ እንዲሁም የሞባይል ኦፕሊኬሽኖችን በማልማት ቱሪስቶች በቀላሉ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው መረጃዎችን ስለኢትዮጵያ ብሎም ስለቱሪዝም ሀብቶቻችን በማውረድ እንዲጠቀሙ ማድረግ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

ማንኛውም ሰውና አገር የትኛውንም ዓይነት የቱሪዝም ማስተዋወቂያ ሥልቶችን ቢጠቀምም ቅሉ፣ በጣም የተለየና የማንኛውንም ሰው ቀልብ ሊገዛ የሚችል የግንኙነት ሥልት መፍጠሩ አስፈላጊና ወሳኝ ነው። ''Nation Branding'' (ብሔራዊ ግሎትም) መሠረታዊ የሆነ የአገር መለያና የሰዎችን ልብና ኅሊና ለመግዛት የሚስችልና አዲስ አቀራረብን በመያዝ ቱሪስቶችን የማማለያ ሥልት ነው።

አዲሱ የኢትዮጵያ መለያ ''Land of Origins'' (የሰው ዘር መገኛ) በዚህች ዓለም ላይ ያለ እያንዳንዱ ሰው ይህን ሀረግ ሲሰማ ከሦስት ሚሊዮን ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ የእነ ሉሲና ሀዳር አገር የሰው ልጅ መገኛ፣ ኢትዮጵያ የዘር ግንዱ አንድ ተብሎ የሚቆጠርባት ባለውለታው መሆኗን ለማሰብ ይገደዳል።

ቱሪዝም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ከሌሎች ሴክተሮችና ከሰፊው ኢኮኖሚ በላቀ ደረጃ በፍጥነት እንዲያድግ ይጠበቃል። ስለዚህ ቱሪዝም የሥራ ዕድል መፍጠሩንና ፍትሐዊ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጥቅሞችን ለዜጎች ማበርከቱን ይቀጥላል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው shewayemern@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡      

 

Standard (Image)

የአትዮጵያ የዱር እንስሳት ‹‹በአውሬዎች›› ሲበሉ

$
0
0

 በማሚ ኮ.

ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ገነት የሆነ ሥፍራ አለ፡፡ ሱባ የተፈጥሮ ደን በመባል ይታወቃል፡፡ ሱባ ስትደርሱ መግቢያው አካባቢ የተለያዩ መረጃ ጽሑፎችና የሐሳብ መስጫ የምትመስል አነስተኛ ሳጥን አለች፡፡ በሳጥኗ ላይ የተጻፈው ጽሑፍ ጎብኚዎችን የሚያስገርም ብቻ ሳይሆን የሚያመራምርም ነው፡፡ የጽሑፉ መልዕክት ማነው ልብ ያለው ከፍቶ የሚያየው? የሚል ጥያቄ የሚያጭር ነው፡፡ በሳጥኗ ላይ የተጻፈው ጽሑፍ ‹‹አደገኛ አውሬ›› የሚል ነው፡፡ እንዴት በዚህች በምታህል ሳጥን ውስጥ አውሬ ሊኖር ይችላል? በማለት ሁሉም ይጠያየቃል፡፡

 አንዳንዶች ይህን አውሬ ማየት አለብን ሲሉ ሌሎች ደግሞ 'ጎመን በጤና'ብለው ይሸሻሉ፡፡ ደፋሮች ሳጥኗን እየተሳቀቁ ከፈት አድርገው ሲመለከቱ በሳቅ ፍርስ ይላሉ፡፡ ምንድነው? ሲባሉ አይናገሩም፡፡ 'ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል'እንዲሉ ሁሉም አደገኛውን አውሬ ይመለከቱታል፡፡ በሳጥኗ ውስጥ የተቀመጠው የፊት መስታወት ነው፡፡ እናም የሚያዩት የራስዎን ምሥል ነው፡፡

ይህም ለተፈጥሮ አደገኛው አውሬ የሰው ልጅ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በተገላቢጦሹ ግን ምንም የማያውቁትን የዱር እንስሳት እኛ ‹‹አውሬ›› ብለን እንጠራቸዋለን፡፡ ከልጅነታችን ጀምሮ አውሬ የሚለውን ቃል በአስፈሪነትና በጨካኝነት ተምሳሌትነት ተቀርፆብን ስላደግን፣ የዱር እንስሳቱን እንድንፈራና እንደ ጠላት እንድናያቸው ተደርገናል፡፡

የዱር እንስሳቱ ተፈጥሯዊ መኖሪያ ቤታቸው በሰው ልጅ እየተጨፈጨፈ አልሞት ባይ ተጋዳይ በሆኑበት ሁኔታ፣ የአውሬ ተግባር የፈጸመባቸው ሰው በተገላቢጦሹ የዱር እንስሳቱን አውሬ ብሎ ይጠራል፡፡

እኛ ሰዎች ያለንበትን (የሠፈርንበትን) መሬት በአግባቡ ጠብቀን መጠቀም ሲገባን፣ ማልማትን ትተን ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም ፖሊሲ የእኛን ድርሻ ጨርሰን የዱር እንስሳት መኖሪያቸውን ስንመነጥር የዱር እንስሳቱ ቁጡና አደገኛ ቢሆኑ እንዴት አውሬ ሊባሉ ይገባል? የትኛው ግለሰብ ነው አጥሩ ሲነቀነቅ በዝምታ የሚያልፈው? ሁሉንም እንደ ራስ ማየት ተገቢ ነው፡፡ የዱር እንስሳት ካልተተናኮሏቸው በስተቀር በጣም ሰላማዊ መሆናቸውን ከአባቶቻችን ነባር ዕውቀት መረዳት ይቻላል፡፡ ‹‹ግራ ዓይኔን …›› እያሉ ነብርን ያህል አዳኝ እንስሳ በፍቅር ይመልሱታል፡፡ የቃሉን ትርጓሜ ተረድቶ እንዲተዋቸው ሳይሆን የማጥቃት ተልዕኮ እንደሌላቸውና ሰላማዊ መንገደኛ መሆናቸውን ለማሳየት ነው፡፡

መንግሥትም እነዚህን የዱር እንስሳት ብቻ ሳይሆን ብዙኃ ሕይወቱን ለመጠበቅ ከሃያ በላይ ብሔራዊ ፓርኮችን አካሏል፡፡ ፓርኮቹንም በበላይነት እንዲያስተዳድር የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣንን በአዋጅ አቋቁሟል፡፡ ተቋሙ ከዚህ በፊት እንደ ቴኒስ ኳስ ከአንዱ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ወደ ሌላው ከመንከላወሱም በላይ አደረጃጀቱም እስከ መምርያ ደረጃ የወረደ ነበር፡፡ አሁን የተሻለ ሥራ ይሠራል ተብሎ ሲጠበቅ በመምርያ ደረጃ ከነበረበት የበለጠ ዘቅጦ ፓርኮችን ወደ መዝጋት ደረጃ ደርሷል፡፡

በአንድ መድረክ ላይ የባለሥልጣኑ የሥራ ኃላፊዎች በሪፖርታቸው የያንጉዲራሳ ብሔራዊ ፓርክን አካተው ያቀርባሉ፡፡ ከአፋር ክልል የመጡ የዘርፉ የሥራ ኃላፊ ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት በተዘጋ ፓርክ ስም እስከ ዛሬ በጀት ይያዛል ወይስ ሌላ ያንጉዲራሳ ፓርክ አቋቁማችኋል? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ በመድረኩ የነበርን ሁላችን ደንግጠናል፡፡ ያንጉዲራሳ ሠራተኞቹ ተነስተው ተዘጋ እንጂ ከመዘጋት ያልተናነሰ ህልውናቸውን ያጡ ፓርኮች በርካቶች ናቸው፡፡

ብዙዎቻችንም አንድ ብሔራዊ ፓርክ ሲዘጋና ሲጠፋ ሕመሙ አይሰማንም፡፡ ምክንያቱም ፓርኮች ለእንስሳቱ መኖሪያነት እንጂ ለእኛ የውኃ ማማና የንፁህ አየር መሠረት መሆናቸውን ጠንቅቀን ስላልተረዳነው፡፡ ዛሬ ተፈጥሮውን በከፍተኛ ሁኔታ ስለጎዳነው ኤልኒኖ በጎርፍና በድርቅ ሲያሰቃየን ከተማ ላይ ያለነው ዜናውን እንኳን ትኩረት ሰጥተን አናደምጥም፡፡

የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ከ40 በላይ ወንዞች የሚመነጩበት ሥፍራ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ምን ያህል ወንዞች እንደሚመነጩበት የቅርብ ጊዜ መረጃ የለኝም፡፡ ግን አሥር ያህል ወንዞች መመንጨት ከቻሉ በግሌ ደስተኛ ነኝ፡፡

የአገሬ አርሶ አደር ወርቃማ የነበረውን መሬቱን በአግባቡ መጠበቅ ተስኖት በመራቆቱ ዛሬ ለረሃብ ሊዳረግ ችሏል፡፡ አሁን ከተኛበት ነቅቶ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እያለ በጂጊ እንዲሰማራ አስገድዶታል፡፡ ያኔ ግን በመጠበቅ ብቻ ለዚህ ችግር ሳይጋለጥ በኖረ ነበር፡፡

የብሔራዊ ፓርኮቻችን ዕጣ ፈንታም ተመሳሳይ ነው፡፡ ትናንት ያንጉዲራሳ ብሔራዊ ፓርክን ዘግተናል፡፡ ዛሬ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክም ከሞት አፋፍ ስለመሆኑ ሄዶ ማየት ላልቻለ የሪፖርተር ጋዜጣ የእንግሊዝኛውን ዕትም የፌብሩዋሪ 13 ቀን 2016 ማየት በቂ ነው፡፡

ዛሬ በችግር ያልታጠሩ ብሔራዊ ፓርኮች የሉንም፡፡ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እንኳን የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የዕለት ዕቅዱንም የሚፈጽም አይመስልም፡፡ ጫካ ላይ ያሉት የፓርክ ዋርደን (ኃላፊ) እና ስካውቶች (የጥበቃ ሠራተኞች) እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ይከፍላሉ፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከስምንት በላይ ስካውቶች በሕገወጦች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ የባለሥልጣኑ የሥራ ኃላፊዎች ግን ሥራ ላይ ያሉ አይመስሉም፡፡ መሥሪያ ቤቱን የሚቆጣጠር የበላይ አካል ያለው አይመስልም፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ባለጉዳይ የሚያስተናግዱት ሰኞ ቀን በመሆኑ አራት ሰኞዎች ብመላለስም አንዴ ከአገር ውጭ ናቸው፣ አንዴ ስብሰባ ላይ ናቸው በሚል ምክንያት ለአንድ ጉዳይ ከሦስት ወራት በላይ እሳቸውን በአካል ማግኘት አልተቻለም፡፡ ተግባራዊ የማያደርጉትን ፕሮግራም ቢሮአቸው በር ላይ ከሚለጥፉ የብርቅዬውን የደጋ አጋዘን ፎቶ ቢለጥፉ ዓይናችን ጥሩ ነገር አይቶ ይመለሳል፡፡

ተማሪ ሳለሁ የልማታዊ ጋዜጠኝነት መምህራችን የአፍሪካ ጋዜጠኝነት 'የኮክቴል ጆርናሊዝም ነው'ብሎ ነግሮን ነበር፡፡ በእርግጥም ተመርቄ ሥራ እንደጀመርኩ የዜናዎቻችን መቼት ሒልተንና ሸራተን ሆኑ፡፡ ከሰኞ እስከ ሰኞ በየስብሰባ አዳራሹ የሚሰየሙ የሥራ ኃላፊዎችስ ምን እንበላቸው? የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ይሆኑ? እርሳቸውን በሚመለከተው ብቻ ሳይሆን ባለሙያ ሊሳተፍበት በሚገባ ስብሰባ ላይ ሁሉ የሚሳተፉ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ከአገር ውጭ ሲሆን፡፡ ለነገሩ ከወረዳና ከዞን አመራርነት ይዘውት የመጡት የካበተ ልምድ ሊሆን ይችላል፡፡ መደበኛ ሥራቸውን ለመሥራት መቸገራቸውን ያፈጠጡ የተቋሙ ችግሮች ማሳያ ናቸው፡፡

በዚህም የተነሳ በአብዛኞቹ ብሔራዊ ፓርኮች ያሉ ሠራተኞች ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ነግሶባቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ የማኅበራዊ ድረገጽ ከፍተው በአቅማቸው እየታገሉ ይገኛሉ፡፡ እኔም በተቋሙ ያሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመረጃ አሰደግፌ በሌላ ጽሑፍ እመለሳለሁ፡፡ አሁን ግን የተፈጥሮ ሀብቱ መዳን ስላለበት በዚያ ላይ ማተኮሩን ወድጃለሁ፡፡

የኦሞና የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርኮች የተጋረጡባቸውን አንገብጋቢ ችግሮች የሚዳስስ ዓውደ ጥናት ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በሁለቱ ብሔራዊ ፓርኮች ላይ እየደረሰ ያለው ጥፋት በጥናቱ መሠረት ኅሊናን ያደማል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በልጆቻችን መወቀስ ብቻ ሳይሆን፣ እዚያ ሳንደርስ በብዙ ከተሞቻችን የምንሰማው የውኃ ጥማት አጥፍቶ የመጥፋት ተግባራችን ዋነኛ ማሳያ ነው፡፡

እነዚህን ሁለት ብሔራዊ ፓርኮች ለማልማት ከአሥር ዓመት በፊት አፍሪካን ፓርክስ የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ተረክቧቸው ነበር፡፡ የዚህ ድርጅት ባለቤት ሆላንዳዊው ባለሀብት ፓል ቫን ቫሊዝንግን ይባላሉ፡፡ የአፍሪካ መንግሥታት ቅድሚያ የሚሰጧቸው እንደ ጤና፣ ትምህርትና የመሳሰሉ ጉዳዮች ስላሉባቸው የተፈጥሮ ሀብታቸውን ትኩረት ሰጥተው ለመጠበቅ ይቸገራሉ፡፡ ስለሆነም በዚህ በኩል እኛ ልናግዛቸው ይገባል በማለት ነው አፍሪካ ፓርክስን የመሠረቱት፡፡

የባለሀብቱን መልካም ሐሳብ የተረዱት የወቅቱ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ግብዣ ለማቅረብ  የቀደማቸው አልነበረም፡፡ ፓል ቫንም ወደ ትልልቆቹ ብሔራዊ ፓርኮች ሳይሆን የሄዱት፣ በብዝኃ ሕይወቱ የበለፀገው ግን በሰዎች ታጥሮ ሥጋት ላይ ወደ ነበረው ማራኬሌ ጥብቅ ሥፍራ ነበር፡፡ ሃያ ሁለት ሺሕ ሔክታር ላይ የሠፈረውን ጥብቅ ሥፍራ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ግንዛቤ በመፍጠር ከአካባቢው በማስወጣት መሠረተ ልማት ወደ ተሟላበት አካባቢ በማስፈር፣ የማራኬሌ ጥብቅ ሥፍራን ሁለት መቶ ሃያ ሺሕ ሔክታር ስፋት ያለው ብሔራዊ ፓርክ በማድረግ በባለሀብት፣ በመንግሥትና በማኅበረሰብ ተሳትፎ የተመሠረተ ስኬታማ ተግባር ማሳያ ተደርጎ የሚጠቀስ ፓርክ ሆኗል፡፡

አፈሩን ገለባ ያርግላቸውና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ኔዘርላድስ ለሥራ በሄዱበት ወቅት እኚህን ባለሀብት በመንግሥት በኩል የሚጠበቀውን ድርሻ ለመወጣት ቃል ገብተውላቸው በመጋበዝ፣ ድርጅታቸው የኦሞንና የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርኮችን ለማልማት ወደ ኢትዮጵያ ይገባል፡፡ በተለይ በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ውጤታማ የሆነ ሥራ እየሠራ ቢሆንም፣ በመንግሥት በኩል በፓርኩ ውስጥ የሠፈሩትን ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ማንሳት ባለመቻሉ ድርጅቱ ሥራውን ለማቋረጥ ተገዷል፡፡

ይኼ ድርጅት የተፈጥሮ ሀብቱን ጥበቃ እንጂ ትርፍን መሠረት ያደረገ አልነበረም፡፡ በደቡብ አፍሪካ፣ በማላዊ፣ በሞዛምቢክና በናሚቢያ ያከናወናቸው ተግባራት የድርጅቱን ውጤታማነት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ እኛ ግን የመጣልንን አጋዥ እንኳን በአግባቡ መጠቀም አልቻልንም፡፡ የአገራችን መሪ የገቡትን ቃል እንኳን የሚፈጽም አመራር ማግኘት አልቻልንም፡፡ በዚህም የሚጠየቅ አካል አላየንም፡፡

ባለሥልጣኑ በየመድረኩ የሚደሰኩሩ ሰዎች አሉት፡፡ ለተቋሙ መሠረት የሆኑት ብሔራዊ ፓርኮችን ለመታደግ ግን አንድ ስንዝር ሲራመዱ አይስተዋሉም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እንዲህ ዓይነት ተቋማት መመራት ያለባቸው ሳይንሱን በሚረዱ ባለሙያዎች ሊሆኑ ይገባል፡፡ መድረክ ላይ መደስኮርና የተግባር ሰው መሆን ለየቅል ናቸው፡፡ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን ገጽታ በመገንባትና ያሉበትን ጫናዎች ለሕዝብ በማውጣት ተቋሙ ወደ ተሻለ አቅጣጫ እንዲመጣ ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ያስፈልገዋል፡፡

የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በፓርኩ እምብረት ላይ የሠፈሩት ነዋሪዎች ከፓርኩ ክልል ካልወጡ ፓርኩን ለመሰረዝ ዩኔስኮ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ የሥጋት መዝገብ ላይ አስፍሮታል፡፡ እነዚህን በግጭ መንደር የሠፈሩ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር ከ15 ዓመታት በላይ የፈጀ ሒደት ነው፡፡ በባለሥልጣኑ ሳይሆን በክልሉ መንግሥትና በፓርኩ ውስጥ በሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከፍተኛ ጥረት ነዋሪዎቹ በደባርቅ ከተማ ለመሥፈር ተስማምተው የቦታ ርክክብ ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል፡፡ ይኼ ስኬት ለዘርፉ ትልቅ ዜና ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ብሔራዊ ፓርኮቻችን ተምሳሌት የሚሆን ነው፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ ቀድሞ ከአሥር ቀናት በፊት ሲገኝ አንድም የዜና ዘጋቢ ድርጅት አልጠራም፡፡ ‹‹ጥሪ ብትባል ቀድማ ተገኘች›› ነው ያሉት አበው? ሌላው ቀርቶ ብሔራዊ ጣቢያ የሆነውን ኢቢሲን እንኳን አልጠራም፡፡ ይኼ ብቻ ሳይሆን ሥነ ሥርዓቱ ለዶክመንት እንኳን ተቀርፆ እንዳይቀመጥ የተቋሙ የካሜራ ባለሙያ እንዲገኝ አልተደረገም፡፡ በእንዲህ ዓይነት ወሳኝ ሥራ ላይ የተሰጠውን ተግባር የማይፈጽም ኃላፊ የሕዝብ ግንኙነት ተቋሙ በምን ዓይነት አመራር እጅ እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡

የኢትየጵያ የዱር እንስሳት በስብሰባ ናፈቂ ‹‹አውሬዎች›› ተበልተው ሳይጠፉ ልንታደጋቸው ይገባል፡፡ አብዛኞቹ ብሔራዊ ፓርኮቻችን ከዱር እንስሳት ይልቅ የቤት እንስሳት የሚታዩባቸው በመሆኑ የባለሥልጣኑ ተጠሪነት ከባህልና ቱሪዝም በአፋጣኝ ወደ የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር መዛወር ይኖርበታል፡፡ የተፈጥሮ ሀብቱ እንዲመለስ በባለሙያዎች መመራት ስላለበት መንግሥት አፋጣኝ ዕርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ በአገራችን የሚከናወኑ ልማቶች ለማንም ሳይሆን ለእኛ ነው፡፡ የተፈጥሮ ሀብታችን መጠበቁም ለማንም ሳይሆን ለእኛ ነው፡፡ ሁላችንም ማየት ያለብን እንደ አገር እንጂ በተሰማራንበት መስክ ብቻ መሆን  የለበትም፡፡

 በመንገድ ዘርፍ ለተሰማራው ቤቱ ኤሌክትሪክ ያስፈልገዋል፡፡ ይኼኛውም መንገድ ያስፈልገዋል፡፡ እንደ አገር አስበን ሥራ መሥራት ካልቻልን ለሌላው ዘርፍ ትኩረት ሳንሰጥ የተቋማችንን ጥቅም ብቻ ማሰብ ድምር ውጤቱ የዜሮ ብዜት ነው የሚሆነው፡፡ ዛሬ የብዝኃ ሕይወት መጥፋት የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ሆኗል፡፡ ብሔራዊ ፓርኮች ደግሞ ብዝኃ ሕይወትን በመጠበቅ የማይተካ ሚና ነው ያላቸው፡፡ የአገራችንን የዱር እንስሳ ለመታደግ ከቢሮ ‹‹አውሬዎች›› ተጀምሮ እስከ ታች ያሉትን ሕገወጥ ተግባር ፈጻሚ ‹‹አውሬዎች›› ማጥፋት ባይቻል እንኳን ሊቀነሱላቸው ይገባል፡፡          

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

Standard (Image)

መሥራትና ማትረፍ በሥነ ምግባር ካልተደገፈ ለአገር ጠንቅ ነው

$
0
0

በጌታቸው አስፋው

ኢኮኖሚክስ ሲጀምር የሞራልና የሥነ ምግባር ጥበብ ሆኖ ነው የጀመረው፡፡ በአርስቶትልና በፕሌቶ ጭምር ስለሀብት ይዞታና አጠቃቀም በሥነ ምግባር ደንብ የተጠና ሲሆን፣ በተለይም ንግድ የማኅበረሰብ ጠንቅና ውጉዝ ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡ ሮማውያንም የግሪኮችን ወርሰው ለንግድ በጎ አመለካከቶች አልነበራቸውም፡፡ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከጥሬ ገንዘብ ንግድ (ብድር) ወለድ መውሰድን እንደ ነውር ቆጥራ ታወግዝ ነበር፡፡ በእስልምና ሃይማኖት እስከ ዛሬም ድረስ በባንኮች የወለድ አልባ ብድር አገልግሎት ይሰጣል፡፡

ከመካከለኛው ክፍለ ዘመን በኋላም የተለያዩ የኢኮኖሚ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች ተራምደዋል፡፡ አሥራ ሰባተኛውንና አሥራ ስምንተኛውን ክፍለ ዘመን በተለይ የፈረንሣዮችን አመለካከት የገዛው የፊዚዮክራቶች አስተሳሰብ ተጨማሪ እሴት የሚፈጠረው በግብርናው ብቻ ነው፡፡ በሌላው ሥራ ሁሉ በግብርና የተፈጠረውን ተጨማሪ እሴት ለማኅበረሰቡ ማከፋፈል ነው እንጂ፣ ምንም ተጨማሪ እሴት አይፈጠርም ብለው ከግብርና ውጪ ያለውን ሥራ ያናንቁ ነበር፡፡

በካርል ማርክስ የኮሙዩኒዝም ፍልስፍና ካፒታሊዝምን ሲተነትን ካፒታል ራሱን መልሶ ይተካል እንጂ አይወልድም፡፡ ወለድ ካፒታሊስቱ ከወዛደሩ የሚመዘብረው የወዛደሩ ላብ ነው ብሎ ነበር፡፡

 

በቀድሞ የሶሻሊስት አገሮች ከአዕምሮ ሥራ ይልቅ የሚያለፋና የጉልበት ሥራ የበለጠ ደመወዝ ያስገኝ ነበር፡፡ እንደዚሁም ደግሞ የመዝናኛ፣ የሕዝብ ትራንስፖርት፣ የመንግሥት የፍትሕ፣ የፀጥታና የሕግ የማስከበር አገልግሎቶች በሌሎች የሥራ ዓይነቶች የተፈጠረውን ተጨማሪ እሴት ለማኅበረሰቡ የሚያከፋፍሉ እንጂ፣ ምንም ተጨማሪ እሴት አይፈጥሩም ተብለው በአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ቆጠራ አይካተቱም ነበር፡፡

በአውሮፓ ኢኮኖሚውን መምራት የተሳነውን መሳፍንታዊና ባላባታዊ የፊውዳል አስተዳደር ሥርዓት ተክቶ ከ16ኛው እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን የቆየው የአንድ ብሔር አገር (Nation State) ግንባታ ዘመነ ንግድ (Mercantilism) ሥርዓት የብሔራዊ ኢኮኖሚ ሥርዓት ያተኮረው፣ በውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ከገቢ ንግድ ይልቅ ወጪ ንግድን አስበልጦ አትራፊ በመሆን ወርቅና ብር የመሳሰሉትን የከበሩ ድንጋዮችና የውጭ ምንዛሪ ሀብት ለአገር በማግበስበስና በማከማቸት፣ በኃይልና በኢኮኖሚ ከሌሎች አገሮች በልጦ መገኘት ነበር፡፡

በእዚህ ሥርዓት ፍልስፍና አውሮፓውያኑ አፍሪካንና ላቲን አሜሪካን በቅኝ ግዛትነት በመቀራመት ማዕድኖቻቸውን በዘበዙ፣ ጥሬ ዕቃ አቅራቢና የፋብሪካ ሸቀጥ ማራገፊያም አደረጓቸው፡፡ 

ኢኮኖሚክስ ከተለምዶው የሥነ ምግባርና የሞራል ፍልስፍና ጥናት ወጥቶ ዘመናዊ የኑሮ ዘይቤና በውድድር ላይ የተመሠረተ የሀብት ድልድል ዘዴ ተደርጎ መጠናት የጀመረው፣ ከአዳም ስሚዝ እ.ኤ.አ. የ1776 የመንግሥታት ሀብት መጽሐፍ ዘመናዊ ኢኮኖሚ ትንታኔ በኋላ ነው፡፡

አዳም ስሚዝ ዘመነ ንግድ ሥርዓት ጥቂት ከበርቴ ነጋዴዎችንና የመንግሥት ባለሥልጣናትን ብቻ የሚያከብርና የሚጠቅም ሥርዓት ነው በማለት ነቀፋ አድርጎ፣ ለሁሉም ሕዝብ የሚጠቅም በውድድር ላይ የተመሠረተ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓትን ተነተነ፡፡

ሆኖም ኢኮኖሚክስን ከሥነ ምግባርና ከሞራል ፍልስፍና አላቆ ዘመናዊና ሳይንሳዊ የኑሮ ዘይቤ ጥበብ ያድርገው እንጂ፣ የሥነ ምግባሩና የሞራል ጉዳዩ አሁን ድረስም በጎጂዎችና በተጎጂዎች መካከል አታካራና ውግዘት አንዳንዴም አመፅ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ዘወትር በመገናኛ ብዙኃን እንደሚደመጠው ሕዝቡ ዋጋ በተወደደበት ወቅት፣ ሸቀጦች ጥራት በጎደላቸው ወቅት፣ ነጋዴዎች ዋጋ እስከ ሚወደድላቸው ሸቀጥ በሚደብቁበት ወቅት እባካችሁ እንተዛዘን እያለ ይለምናል፣ ይማፀናል፡፡ የሠራተኛ ማኅበራት በየጊዜው ከአሠሪዎች ማኅበራትና ከአሠሪዎች ጋር በደመወዝ ጉዳይ ላይ ይሟገታሉ፡፡ ሀብት መቀራመትም ብጥብጥና ሁከት ያስነሳል፡፡

በጥንታውያን ኢኮኖሚስቶች የታሰበው ሰዎች ጥቅማቸውን የላቀ ለማድረግ የሚበጃቸውን ያውቃሉ፡፡ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ታሳቢ ግምት በኬንስ ሰዎች አንዳንዴ በእንስሳዊ ስሜትም (Animal Spirit) ይነዳሉ በማለት ተተችቷል፡፡ በዚህ ዘመን የምናየው ደግሞ ሰዎች ጥቅማቸውን የላቀ ለማድረግ አዋቂነት ሌላውን ሰው አለመጉዳት ገደብና ጠርዝ እንደሌለው ነው፡፡

የግል ጥቅምን የላቀ ለማድረግ አዋቂ መሆን የነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ሕግጋት ታሳቢ ገደብ ስለሌለው፣ በሕጋዊና በሚፈቀድ መንገድ የሌሎቹን መብትና ጥቅም ለመጉዳት እስከ መሄድንም የሚፈቅድ ይመስላል፡፡ በውስጡ ሀብትን የራስ ብቻ የማድረግ እንስሳዊ ስስት መኖሩ ይታያል፡፡ በስስት የ3.5 ቢሊዮን ሕዝብ ሀብትን የሚያህል በስምንት ሰዎች ብቻ ተያዘ፡፡

 

በስዊዘርላንድ ዳቮስ በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም የቀረበ ዘገባ ተጠቅሶ በመገናኛ ብዙኃን በተነገረ ዜና፣ ስምንቱ የዓለም ሀብታም ሰዎች ሀብት የ3.5 ቢሊዮን ድሆችን ሀብት ያክላል ይላል፡፡

በኢኮኖሚክስ የኖቤል ተሸላሚው ኢኮኖሚስት ጆሴፍ ስቲግሊትዝ ግሎባላይዜሽን ያመጣው ጣጣ ነው በሚል፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚሟገቱ የዚህ ዘመን ታዋቂ ኢኮኖሚስት ሆነዋል፡፡

በቅርቡ ሕይወታቸው ከማለፉ በፊት በአልጄዚራ ቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ የተደረገላቸው ታላቅ ጣሊያናዊ ፈላስፋ ሲናገሩ፣ ባለፉት መቶና ሁለት መቶ ዓመታት ለነፃነት ብዙ ሲሠራ ለዋስትና ምንም ስላልተሠራ ብዙ ሰዎች እየተጎዱ ነው ብለው በማስረጃ ሁኔታዎችን ሲተርኩ ሰምቼ ነበር፡፡

ከማስረጃዎቻቸው ውስጥም የሊቢያ፣ የሶሪያና የኢራቅ ቱጃሮች ዛሬ የኑሮ ዋስትና አጥተው በስደተኛ ካምፕ ወይም በሰው አገር እንደ ሁለተኛ ዜጋ እየተቆጠሩ ለዕለት ጉርሳቸው ለፍተው ጥረው ግረው ይኖራሉ ብለው ነበር፡፡ ለነፃነት ብቻ ስናስብ ‹ዋስትናን ረሳነው›፡፡ የሥራ ዋስትና፣ የቤተሰብ ዋስትና፣ የኑሮ ዋስትና አጣን፡፡ አንድ ሰው ስለራሱ ነፃነት የሚያስብበት ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎች የኑሮ ዋስትናም ያለውን ግዴታ የምናጎላበት ጊዜ ነው፡፡

ዛሬ የተደላደለ ሀብትና ሥልጣን አለኝ ብሎ ግፍ ከመሥራትና ከሌላው ነጥቆ ከመብላት ‹ነግ በእኔ› ማለትም ይገባል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የአረጋውያንን እንባ  መፍራት ያስፈልጋል፡፡ እዚያ ሁሉም በጊዜው መድረሱ አይቀርምና፡፡ በጡረታ መዋጮ መልክ ቆጥቦ መንግሥት፣ ዘንድ ያስቀመጣት ብር ሸቀጥን የመግዛት አቅሟ እንዲቀንስ ያደረገ መንግሥት ተጠያቂነትም ከዋጋ ንረት ጋር ማስተካከያ የማድረግ የሥነ ምግባር ግዴታም አለበት፡፡

ይህች በአረጋውያን ጸሎት ትኖራለች የተባለላት አገር እነ ጄነራል ጃጋማ ኬሎን የመሳሰሉ ጀግኖች ተራቡባት ተብሎ በመገናኛ ብዙኃን ሲቀርብ ምን ያህል አሳዛኝ ፍጡሮች መሆናችንን የሚያመለክት ነው፡፡ ጄነራሉ 1,300 ብር ጡረታ በድሮው የሸቀጥ ዋጋ ቀጭን ጌታ ሆነው ሳይራቡ ሳይታረዙ ሊኖሩ ይችሉ ነበር፡፡ መኖር እስከሚያቅታቸው ድረስ ኑሮን ያስወደደባቸው መንግሥት እንዴት ኃላፊነት አይወስድም?

አቅም ያለውን መፍራትና አቅም የሌለውን መናቅ ከልማታዊ መንግሥት አይጠበቅም፡፡ አንድ መንግሥት ዜጎቹን ‹ጉልበት ያለውና ጉልበት የሌለው› ብሎ በአቅም ከፋፍሎ ከተመለከተም የሆነ ችግር አለበት ማለት ነው፡፡ የቅርብ ጊዜው ሁከት የወጣቱ ደስ አለመሰኘት ነው ተብሎ ሽር ጉድ ሲባልለት ከረመ፡፡ ወጣቱ የሥራና የኑሮ ዋስትና ሊያገኝ ይገባል ማለት ልክ ነው፡፡ ነገር ግን ወጣቱ የእናትና የአባቱ መራብም አያስደስተውም፡፡

‹‹እምዬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ›› ተብሎ የተገጠመው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ባንዶቹ ሲሾሙ እነ በላይ ዘለቀን የመሳሰሉ ጀግኖች በስቅላት በመገደላቸው ነበር፡፡ በጄነራል ጃጋማ ኬሎና በጠቅላላው ኢትዮጵያውያን አረጋውያንና ጡረተኞች ታሪክ ራሱን ደገመ፡፡

የሚራቡ ሰዎች ለመራባቸው ምክንያት መሆን፣ የሚጠሙ ሰዎች ለመጠማታቸው ምክንያት መሆን፣ የሚታረዙ ሰዎች ለመታረዛቸው ምክንያት መሆን ምንኛ  ይሰቀጥጣል፡፡ ‹ዛሬ ያለ ሁሉ ነገ የለም› ሥልጣኑም፣ ገንዘቡም፣ ጤንነቱም ይሸሻል፡፡ የማታ ማታ የበላም ያልበላም፣ የጠጣም ያልጠጣም፣ የለበሰም የታረዘም፣ ፎቅ ቤት የኖረም በረንዳ ያደረም፣ ሁሉም ዶግ ዓመድ  ይሆናል፡፡ ከሌላው ነጥቀው ያጠራቀሙት አብሮ አይሄድም፡፡ መሥራትና ማትረፍ በሥነ ምግባር የተደገፈ ይሁን፡፡ ካልሆነ ግን ለአገር ጠንቅ ነው፡፡ መንግሥትም ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ያስፍን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getachewasfaw240@gmail.com.  ማግኘት ይቻላል፡፡.

 

 

Standard (Image)

ያልተቋጨው የአሉባልታና የእውነታ ፍልሚያ በጋምቤላ

$
0
0

በጽጌ ሕይወት መብራቱ

በጋምቤላ እየተካሄደ ያለውን የእርሻ ልማት እንቅስቃሴ ገና ከጅምሩ ከአገር ቤት እስከ ዓለም ዙሪያ የሚገኙ የራሳቸው የሆነ ዓላማ ያነገቡ አካላት ‹‹ከመሬት ወረራ›› ጋር በማያያዝ መነጋገሪያ አድርገውት እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተለይም ከትግረኛ ተናጋሪዎች ጋር በማቆራኘት ያካሄዱት የስም ማጠልሸት ዘመቻ በሒደት ባዶ ጩኸት መሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስ ትኩረት የሳበ አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡

ፍፃሜያቸው በማይታወቅ እጅግ በጣም ብዙ ችግሮችና ከባድ ውጣ ውረዶች ሁለመናው የተተበተበው አሰልቺው የጋምቤላ እርሻ ልማት ከመሬት ወረራው ዘመቻ በመቀጠል፣ ከባንኮች ገንዘብ ዘረፉ ጋር በማያያዝ አነጋጋሪነቱ ቀጥሎ ይገኛል፡፡ በተለይም ይህ ጉዳይ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ትኩረት ከማግኘቱም ባለፈ ብዙ ወገኖች አሉባልታውንና እውነታውን መለየት እስኪያቅታቸው ድረስ ሲደናገሩበት እያየን ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ ምንም እውቀትና ግንዛቤ ሳይኖራቸው በየተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ውጤቶች ላይ የባጥ የቆጡን ሲዘላብዱም ታዝበናል፡፡

ከሁሉም በጣም የሚገርመውና የሚያሳስበው ደግሞ የተሳሳተ መረጃ መሠረት በማድረግ ወይም የቀረበላቸውን ግማሽ ብስል ግማሽ ጥሬ የሆነ እርስ በርሱ የሚጋጭ የጥናት ሪፖርት እንዳለ በመቀበል እየደረሱበት ያለው ድምዳሜ አሳሳቢ መሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በመነሳት ከፍተኛ የአገራችን የሥራ ኃላፊዎች እየሰጡዋቸው ያሉ መግለጫዎችና እየተላለፉ ያሉት ውሳኔዎች ህልቆ መሳፍርት በሌለው የችግር ማዕበል እየተናጠ ያለውን የጋምቤላ እርሻ ልማት ውድቀቱን የሚያፋጥኑ በመሆናቸው ነው፡፡ እኔም ከጉዳዩ ባለቤቶች አንዱ ነኝና መጥፎ ዜና ከመሰማቱና ዘግናኝ ውድቀት ከማጋጠሙ በፊት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት አሉባልታውን ከእውነታው ለያይተው እንዲገነዘቡት በማድረግ የዜግነት ኃላፊነቴን ለመወጣት በማሰብ ነው ይህን ጽሑፍ የማቀርበው፡፡

ከጋምቤላ ፈተናዎች በጥቂቱ

የጋምቤላ የግብርና ኢንቨስትመንት ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ የልማት እንቅስቃሴውን ከዜሮ በታች ብቻ ሳይሆን፣ ከብዙ ዜሮዎችም በታች በጣም ወርዶ ነው አሀዱ ብሎ የተነሳው፡፡ መንግሥታዊ አሠራሩ በአስቂኝ ሁነቶች የተሞላ፣ የመሠረተ ልማት ውጤቶች ሽታቸው እንኳን የሚናፍቅ፣ በሰላም ወጥቶ መግባት እንደ ተዓምር የሚቆጠርበት፣ የሕግ የበላይነት የመይታሰብበት፣ መብትን መጠየቅ እንደ ድፍረት የሚቆጠርበት፣ በአጠቃላይ ሲታይ ሁሉም ነገር ግራ የሚገባበት ነበር ጋምቤላ፡፡ በእርግጥ አሁንም ቢሆን መጠነኛ መሻሻሎች መኖራቸውን ብናደንቅም ተዝቀው የማያልቁ አያሌ ችግሮች እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ ወደ እርሻ ልማቱ ስንገባ ደግሞ ሌሎች አዕላፍ ችግሮች ጥርሳቸውን አግጥጠው ዓይናቸውን ጨፍነው ይጠብቃሉ፡፡ የመሬት ፅዳት (ምንጠራ) ሥራው አድካሚነትና የሚበላው ገንዘብ ብዛት ደምን የሚጠጣ ነው፡፡ የአየር ንብረቱ መጨበጫ የለውም፡፡ የሰው ኃይል እጥረቱ፣ በየመንገዱ የሚጠብቅና ገንዘብን እስከ ሕይወት የሚበላ ሥፍር ቁጥር የሌለው ዘራፊ፣ ጎሳውና ቋንቋው ብዛቱ፣ ይኼን ሁሉ ችግርና ፈተና እየታየ ጋምቤላ ወደ ሥራ ለመግባት ሲወሰን ግን ከደፋርነትና ከቆራጥነት ባሻገር፣ ወደፊት ለውጥ መምጣቱ የማይቀር ሒደት መሆኑን ተስፋ ማድረግና የአካባቢውን ነባር ተወላጆች የሚያደርጉት እንክብካቤና ለልማቱ ያላቸውን መልካም አመለካከት በማስተዋል ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ጋምቤላ የእንግዶችን ሕይወትም፣ ገንዘብም እየበላች የመሬት ወረራ አሉባልታ አጀንዳ እንደሆነች በልማት ጎዳና እያዘገመች እስከ 2005 ዓ.ም. ቆይታለች፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ ደግሞ በተለይ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር አገልግሎት ማቅረብ በመጀመራቸው፣ ጋምቤላ በመሬት ፈላጊ ዜጎች መጥለቅለቅ ጀመረች፡፡ በደላላ ፈቃድ የደም ዝውውሯ ያለሙስና መንቀሳቀስ እስኪያቅተው ድረስ የብዙ ቴአትሮች መታያ መድረክ ሆነች ጋምቤላ፡፡ ብዙ ተዋንያንም መድረኩን ለመቆጣጠር ባደረጉት መሻኮት የአሉባልታ መነኻሪያነቷ ባሰበት፡፡ ሒደቶች ሳያቋርጡ ፈጠኑ፡፡

በአሉባልታ ዘመቻ የተለከፈው ኤጀንሲ

የማያቋርጥ ክትትል፣ ድጋፍና ግምገማ በማካሄድ የግብርና ኢንቨስትመንት ውጤታማነትን ማረጋገጥ ዓላማው ሆኖ በፌዴራል የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሥር የተቋቋመው የግብርና ኢንቨስትመንት አስተዳደር ኤጀንሲና የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ በየአቅጣጫቸው መሬት የማደሉን ሥራ ተያያዙት፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ዘርፉን መደገፍና መከታተሉ ቀርቶ የፌዴራሉ ኤጀንሲ የአሉባልታ ፊታውራሪ መሆን የጀመረው ይላሉ ሁኔታውን የሚከታተሉ ሰዎች፡፡ ሌሎች ታክቷቸው የተውትን የመሬት ወረራ አጀንዳ በማንሳት እስከገንዘብ ዘረፋ በማሻገር ከአንድ ብሔር ተወላጆች ጋር በማስተሳሰር ረዥም ጉዞ ተጉዟል፡፡ በሚያገኛቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የክልሉን ኢንቨስተሮች በመፈረጅ ልማቱን አጣጥሏል፣ አጥላልቷል፡፡ ጥቃቅን ችግሮችን እያጋነነ ባንኮች ብድር መስጠታቸውን እንዲያቆሙ ደብዳቤ በመጻፍ ወትውቷል፡፡  የጋምቤላ ክልል አመራሮች ባለሀብቶቹን በመጥፎ ዓይን እንዲያዩዋቸውና እንዲያውም የመሬት ኪራይን ዋጋ ከአቅማቸው በላይ በማድረግ፣ አስጨናቂ አገዛዝን በማስፈን አክስረውና አበሳጭተው ከክልሉ ሊያባርሯቸው እንደሚገባ የማሳመን መርዛማ ተግባር እንደፈጸመ ይነገራል፡፡ በአጠቃላይ በአገራችን በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት ግንባር ቀደም ተጠያቂ ነው የተባለው ይኼ ኤጀንሲ፣ ወደ እንደዚህ ዓይነት ተግባር የገባው የጋምቤላን መሬት በራሱ ሥር አድርጎ ኪራይ ለመሰብሰብ በነበረው ከፍተኛ ፍላጎት ምክንያት ብቻ ሳይሆን ሌላ ማሳካት የሚፈልገው የተደበቀ ዓላማ ስላለው ሊሆን እንደሚችል፣ የጋምቤላ ኢንቨስተሮች ኅብረት ሥራ ማኅበር አመራር አባላት እምነት ነው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ለዚህ አባባል ማስረገጫ ከሚሆኑት የኤጀንሲው ተግባራት አንዱ በጋምቤላ የተካሄደውን ጥናት የመራውና ያስተባበረው ሌላ አካል ሆኖ እያለ፣ የጥናት ቡድኑ ውጤት በሚመለከተው ሕጋዊ አካል አቅራቢነት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና ግምገማ ተካሂዶበት ይፋ ከማድረጉ አስቀድሞ፣ የኤጀንሲው መሪዎች በማይመለከታቸው ጉዳይ ገብተው ለአገር ውስጥና ለውጭ መገናኛ ብዙኃን የተጣደፈ መግለጫ መስጠታቸው ነው፡፡ በተለይም የጥናቱ ግኝት የተባሉ ግን መሠረተ ቢስ የሆኑትን አፍራሽ ሐሳቦችን አጉልቶ ለማሳየት ያደረጉትን ጥረት ላስተዋለው፣ ለጋምቤላ ልማትና ለልማቱ ተሳታፊዎች ያላቸውን ጥላቻ ቁልጭ አድርጎ ያሳብቅባቸዋል፡፡

ታኅሳስ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል በተካሄደው አገር አቀፍ የግብርና ኢንቨስትመንት ንቅናቄና ከታኅሳስ 22 እስከ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ጋምቤላ ላይ በተካሄደው የክልሉ የግብርና ኢንቨስትመንት ንቅናቄ መድረክ ላይ የጥናቱን ውጤት ገለጻ ባደረጉት የኤጀንሲው ዳይሬክተር ላይ፣ በአገራችን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ፊት የጋምቤላ ኢንቨስተሮች ያሳዩት ተቃውሞና ኃይለ ቃላት የተሞላበት ነቀፋ በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ምን ያህል የተበላሸ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡

በጋምቤላ ባለሀብቶች እንደ አርዮስ እየተወገዘ ያለው ይኼ ተቋም የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣት ያልቻለና ለወደፊትም ሊወጣ የማይችል መሆኑ ታምኖበት እንዲፈርስ በመንግሥት መወሰኑ አስደሳች የነበረውን ያህል፣ በሌላ አደረጃጀት የኤጀንሲው አባላት እንደገና ከጋምቤላ የግብርና ኢንቨስትመንት ሥራ ጋር እንዲገናኙ የመደረጉ ዜና ሲሰማም ሌላ ሐዘንና ግርምታን ፈጥሯል፡፡ ይህም ለክልሉ የእርሻ ልማት ሌላ ተግዳሮትና የንትርክ ዘመን በጋምቤላ መቋጫ ካልተበጀለት ውጤት መጠበቅ ከንቱ ነው፡፡ የተደበቁ ሀቆች በጊዜ ተቆፍረው እንዲወጡ ማድረግ አማራጭ የለውም፡፡

ወርቅ ላበደረ ጠጠር

ጋምቤላ የግብርና ኢንቨስትመንት የነበረበትን ወለል ለሚያውቅ በአሁኑ ወቅት የደረሰበትን ደረጃ አስተውሎ ከማድነቅና ተዓምራዊ መሆኑን ከመመስከር ሊያግደው የሚችል ኃይል የለም፡፡ ይኼ መመፃደቅ ወይም ማጋነን አይደለም፣ ‹‹ዓይን አይቶ ልብ ይፈርዳልና››፡፡ ዓይኑንና ህሊናውን አውቆ ላልሸፈነ መሬቷ እውነትን በቋንቋዋ ትነግረዋለችና፡፡ ተዓምራዊው የእርሻ ልማት የራሱ የሆኑ ጉድለቶች ቢኖሩበትም ሀቁ ግን በታቀደና በተቀነባበረ የቅብብሎሽ ዘዴ እየተነዛበት ካለው በቅናትና በጥላቻ ከተመረዘ ሰይጣናዊ ዘመቻ ውጤት ጋር ሲነፃፀር ልዩነቱ የሰማይና የምድር ያህል ይራራቃል፡፡

ባለሀብቶች የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት በተደጋጋሚ ያቀርቡት የነበረውን የልማት ጥሪ በመቀበል ወደ ክልሉ የገቡት እጅግ በተንጠባጠበ ሁኔታ መሆኑን እስከ 2005 ዓ.ም. ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የመንግሥት የልማት ፖሊሲን መገንዘብ የቀረቡ ማበረታቻዎችን ማስላት ከጊዜ ጋር አብሮ የመሄድ ችሎታ እንዳሉ ሆነው፣ ለዚያውም ደግሞ በጋምቤላ በገሃድ የሚታዩ ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ፀጉር የበዙ ችግሮችን እየተጋፈጥኩ ጉልበቴን፣ እውቀቴንና ጥረቴን እሰዋለሁ ብሎ መወሰንና ቁርጠኝነትና ጥረቴን እሰዋለሁ ብሎ መወሰን መቻል ቁርጠኝነትና ጭካኔን ይጠይቃል፡፡ ዛሬ በየከተማው ማኪያቶና ቢራ እየተጎነጩ ሎሚ መስሎ ማስቲካና ብስኩት እየቸረቸሩ ሚሊዮን ብሮች እንደሚታፈሱ እየታወቀ አሁንም ለዚያውም በጋምቤላ፣ ለዚያውም ከብዙ ዓመታት በኋላ ሊገኝም ላይገኝም የሚችል መልካም ውጤት በማሰብ ወደ እርሻ ሥራ ለመግባት መድፈር ለውስን ሰዎች ብቻ የተቸረ ብቃት ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህም በላይ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የሰው ዘር ጠረን አልፎበት በማያውቅ ጫካ ተበትነው ከተፈጥሮና ከሰው ሠራሽ ችግሮች ጋር ግንባር ከግንባር እየተፋለሙ አፈር መስሎ መኖራቸው ሳያንስ፣ በጥይትና በአራዊት ሕይወታቸውን ያጡ ጀግኖችን ቤታቸው ይቁጠራቸው፡፡ እንግዲህ በዚህ መራራ ትግል ውጤት ነው ጋምቤላ አሁን ካለችበት የመነጋገሪያነት ምዕራፍ የበቃችው፡፡ ከላይ ከጠቀስናቸው የጋምቤላ ልማት ፈር ቀዳጅ ዜጎች ጥረት ቀጥሎ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ አንፀባራቂ ውጤት ያመጡት ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ናቸው፡፡ ንግድ ባንክ በተወሰኑ እርሻዎች ላይ መሳተፉን፣ በተለይም በውጭ አገር ተበዳሪዎቹ ገንዘቡ እንደተዘረፈ ከመስማት ውጪ እውቀቱ ስለሌለኝ ከዚህ በላይ የምለው የለኝም፡፡

በአልሚዎችና በአጥፊዎች የተከበበ ተቋም

ከተመሠረተ አንድ መቶ ዓመቱን የዘለለውና በአገራችን በተመዘገቡ የተለያዩ የልማት ውጤቶች ላይ የማይደበዝዝ አሻራውን ያሳረፈው የልማት ባንካችን፣ የጋምቤላ የግብርና ኢንቨስትመንት በሦስት ዓመት ትንሽ ዕድሜ ላስመዘገበው ከፍተኛ ዕድገት ቀጥተኛ ባለቤት ነው፡፡ ብዙ መቶ ሚሊዮን ብሮችን በማበደር ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ወሳኝ በሆነ መልኩ የደንበኞቹን ችግር በመፍታት ልማቱ እንዲቀላጠፍ አድርጓል፡፡ ለብዙ ሺሕ ዜጎች ሥራ ዕድል እንዲፈጠር አስችሏል፡፡ ጋምቤላ ሁለንተናዊ የዕድገት ጎዳናን እንድንጀምር ረድቷል፡፡ ሀቀኛ ባለሙያዎቹ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ዜግነታዊ ግዴታቸውን ሲወጡ አይተናል፡፡ በተግባር የምናውቀው ዜጎች ለልማት ባንካችን ያለንን አድናቆትና ምሥጋና መደበቅ አንችልም፡፡ በጣም የሚገርመው ግን ይህን የመሰለ ወርቃማ ታሪክ እየሠራ ያለው ባንክ ከውስጥም ከውጭም የሚዥጎደጎድበት የአሉባልታ ውርጅብኝ በራስ የመተማመን ብቃቱን ሰልቦት ይመስላል፣ የራሱን ተግባርና ውጤት የመግለጽ የማሳመን እንጥፍጣፊ አቅም አጥቶ መታየቱ ነው፡፡ መሥፈርቱን ከአሟሉ ተበዳሪዎች ጋር በተናጠል ስምምነት እየፈጸመ የሚያበድር መሆኑ እየታወቀ፣ ለትግራይ ተወላጆች ብቻ ብድር እንደሚሰጥና ገንዘብንም ሆነ ብሎ ለዘረፋ እንዳመቻቸ ተደርጎ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲካሄድበት ይህን የማስተባበልና እውነቱን ለማስረዳት ተግባር የፈጸመ አይመስልም፡፡

በእርግጥም ከእርሻ ሥራ ጋር የሚስማማ በጥልቀት የተጠና የብድር አለቃቀቅ ሥርዓት ወጥነት ባለው መልኩ ለማስፈን ያደረገው ጥረት በተፈለገው  ፍጥነት አለመሄዱ እውነት ነው፡፡ ይህም ቢሆን ጋምቤላ ላይ እየተካሄደ ያለው ልማት በባህርይው ከሌሎች አካባቢዎች በእጅጉ የተለየ ከመሆኑ፣ እንዲሁም የተንቀሳቀሰበት የጊዜ ሥሌት አጭር የሚባል ከመሆኑ አንፃር ወጥ የሆነ አሠራር ለመዘርጋት እንደሚከብድ ግንዛቤ መውሰድ ይገባል፡፡ ይህን እውነት ለማስጨበጥ የተደረገ  ጥረት አናሳ መሆን ነው ያስመዘገበው መልካም ውጤቱ አሉባልታውን ማክሸፍ እንዳይቻል ያደረገው፡፡ የባንኩን መልካም ስም የሚፃረር ብልሹ ተግባር የሚፈጽሙ ኃላፊነት የጎዳላቸው ባለሙያዎች የተሰገሰጉበት መሆኑ ሌላው ፈተና ሆኖበታል፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ ለተሰጣቸው አደራ ደንታ የሌላቸው የተወሰኑ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሠራተኞች የሕገወጥ ጥቅም ተጋሪዎቻቸው ከሆኑ የተወሰኑ ጥገኛ ኢንቨስተሮች ጋር በመመሳጠር የሚፈጽሙት የተበላሸ ተግባር መኖሩ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚህ በመነሳትም የባንኩ ደንበኞች ‹‹የቤት ልጆችና የእንጀራ ልጆች›› በማለት እርስ በእርሳቸው እየተሰያየሙ በአሽሙር እየተወጋጉ ይታዩ የነበረው ያለ ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ የባንኩ የቤት ልጆች የሚባሉት የሚያቀርቡት የብድርም ሆነ ማንኛውንም ጥያቄ በሚገርም  ፍጥነት ይፀድቅላቸዋል፡፡ በተግባር ራሳቸውን መግለጽ ላይ ደሃዎች ሆነው ሳለ ቃላቶቻቸው ታማኝና ከማር የሚጣፍጥላቸው ናቸው፡፡ ከእነሱ በታች መሆኑን አምኖ ለማይቀበልና ለአልንበርክክ ባዮች ደግሞ አደናቃፊዎች ናቸው፡፡ ማንኛውም ጎዶሎአቸው ወደ ውጤት ይቀየርላቸዋል፡፡ አንደኛው ፕሮጀክታቸው አፈጻጸሙ በጣም ዝቅተኛ መሆኑ እየታወቀ በሌሎች በተለያዩ ፕሮጀክቶች ስም ወፋፍራም ተጨማሪ ብድሮች የሚፈቀድላቸው ቅምጥል ደንበኞች ናቸው፡፡ በእርግጥ አንዳንዶቹ በሒደት ወደ ትክክለኛው ውጤት መጥተዋል፡፡

የአበሰኞቹ የእንጀራ ልጆች ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ውጤታማ ሥራቸው ዓይነ ግቡ አይደለም፡፡ እንኳን ቃላታቸው ማንነታቸው ራሱ ቀፋፊ ነው፡፡ የሚጉላሉበት ሰበብ ብዙ ነው፡፡ አቤት ቢሉ ሰሚ አያገኙም፡፡ ምክንያቱም ባንኩ አመራሮች የሚያምኑት የፈላጭ ቆራጭ ባለሙያዎቻቸውን ሪፖርት ነውና፡፡ የእንጀራ ልጆች ፈተና በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ ፍትሐዊ አሠራር በመጠየቃቸውና መብታቸውን በገንዘብ ለመግዛት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ‹‹ሽጉጥ ግንባር ላይ እየደገኑ ያስፈርማሉ፣ ይዝታሉ፣ ይሳደባሉ፣ ጋንግስተሮች ናቸው፣ . . . ››  እየተባለ የሐሰት ክስ ይመሠረትባቸዋል፡፡ ‹‹እንዳያማ ጥራው እንዳይበላ ግፋው›› ቀመር ከኢትዮጵያ ሕዝብ ካዝና የተበደሩትን ገንዘብ ለትክክለኛው ዓላማ ከመጠቀምም ባለፈ፣ ያጋጠማቸውን ጉድለት ከራሳቸው ኪስ በመሙላት ልማታቸውን ውጤታማ እያደረጉ መሆናቸው ግን የጋምቤላ መሬት ትመሰክርላቸዋለች፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክና ሀቀኛ የባንኩን ሠራተኞች የተቀደሰ ዓላማና ጥረት እጀ ሰባራ የሚያደርጉ የባንኩ ምግባረ ቢሶች ተግባራቸው ድንበር የለውም፡፡ ማፈርና መሸማቀቅ ሲገባቸው እንደገና ዞረው ባለቤቶቹ ራሳቸው እንዳልሆኑ ዘንዳ የባንኩ ገንዘብ በትግራይ ተወላጆች እየተዘረፈ መሆኑን የሚቀባጥሩት ፊታውራሪዎቹ እነሱ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በ2007 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ የተፈጸመው ሥነ ምግባር የጎደለው ፍፃሜ ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡

በወቅቱ ከጅማ የባንኩ ቅርንጫፍ ተበዳሪ የሆኑ ደንበኞችና ጥያቄያቸው ገና በሒደት ላይ የሚገኙ ተጠባባቂዎች ስም ዝርዝር ከተበደሩትና ተጠባባቂዎቹ ከጠየቁት የገንዘብ መጠን ጋር ተያይዞ፣ ‹‹በትግራይ ተወላጆች የተዘረፈ ገንዘብ›› የሚል ርዕስ የተሰጠው ሰነድ ከዚያው ከጅማ ልማት ባንክ ወጥቶ በኢሳት ቴሌቪዥን ለዓለም ሕዝብ ሲሰራጭ አይተናል፡፡ እስከ ዛሬው ድረስ ለሚፈልጉት ዓላማ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ሁሉም ተበዳሪዎች ከተለያዩ የአገራችን ብሔር ብሔረሰቦች የተወጣጡ መሆናቸው ሰነዱ ላይ ያለው ዝርዝር በግልጽ እያሳየ፣ ትግራዋይነት በግድ እንዲጫንባቸው የተፈለገበትን ሚስጥር እንዳጋለጠባቸው እንኳን የሚገነዘቡ ዓይነት አይደሉም፡፡ በወቅቱ ስም ዝርዝራቸው የተካተተው ተበዳሪዎች ሁለቱ ‹‹እኩብ›› እና ‹‹ኡጁሉ›› የሚባሉ የጋምቤላ አኞዋኮች እንኳን ሳይቀሩ የጋምቤላን መሬት የወረሩና የልማት ባንክ የዘረፉ ተብለው የትግራዋይነት ታርጋ ተለጥፎባቸው የተመለከቱ ሁሉ ግርምታቸውን በትዝብት ሳቅ ገልጸዋል፡፡ የባንካቸውን ሚስጥር የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ያልቻሉ ደካሞች እንዲህ ዓይነት ተራ ስህተትን እንኳን ማስተዋል የሚችል ህሊና እንዲኖራቸው አይጠበቅም፡፡

የተድፈነፈነ ድግስ

ከመሬት ወረራ እስከ ባንክ ገንዘብ ዘረፋ የተቀጣጠለው ፕሮፓጋንዳ ምን ያህል ረዥም ርቀት በጥንካሬ እንደተጓዘ ያስመሰከረበት ክስተት የታየው ደግሞ፣ በጋምቤላ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በተከበረበት ወቅት ነው፡፡ ይህ የጋምቤላን መልካም ገጽታ ለማሳየት የሚቻልበት ወቅት ነው፡፡ በጋምቤላ የኢንዱስትሪ ልማት፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ….የሚታወቁት በዲስኩር ብቻ ነው፡፡ እያቆጠቆጠ ያለው የኮንስትራክሽን ዘርፍም የግብርናውን ጅምር እንቅስቃሴ ተከትሎ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ብቅ ያለ ለውጥ ነው፡፡ እናም ብቸኛ የጋምቤላ ዋስትና የሆነው የእርሻ ልማት ያለበትን ደረጃ ለእንግዶቿ ከማሳየት ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረም፡፡ ስለዚህ የክልሉ መንግሥትና የኢንቨስተሮች ማኅበር የጋራ ዕቅድ በማዘጋጀት የውይይት መድረክ፣ የመስክ ጉብኝት፣ የተለያዩ ትርዒቶች፣ የእርሻ ውጤቶች፣ ኤግዚቢሽንና ዘጋቢ ፊልሞች ማቅረብ በዕቅዳቸው አካተዋል፡፡ የፕሮፓጋንዳ ሰለባ ከመሆኑ አንፃር የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ለመገምገም የራሳቸው ዝግጅት አድርገው እንደሚመጡ በእርግጠኝነት ይታመናልና ወቅቱን መጠቀምም ግድ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓሉንና ጋምቤላን በተመለከተ ባሰሙት ንግግር ላይ የእርሻ ልማቱን የሚጠቅስ አንድም ቃል ሳይደመጥ ንግግሩ ተቋጨ፡፡ ይባስ ብሎ እስከ በዓሉ ፍፃሜ ድረስ ይህንን አነጋጋሪ ጉዳይ የሚመለከት እንኳን ተግባር የቃል ሽታው እንኳን ናፈቀ፡፡ በዚህ ክስተት ብዙዎች ግራ ተጋቡ፡፡ እንዲያውም የፌዴራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት ጥርግርግ ብለው አዲስ አበባ ገቡና ሁሉንም ኩም አደረጉት፡፡ ሁሉንም ግራ ተጋባና ጠያቂ ብቻ እንጂ መልስ ሰጪ ታጣ፡፡

መልስ የሚሰጠው ይመስል ሁሉም ወደ ኢቢሲ መስኮት ማፍጠጡን ተያያዘው፡፡ በዓሉን በተመለከተ የሚተላለፉ ዜናዎችና ፕሮግራሞች ላይ የጋምቤላን እርሻ እንቅስቃሴ የሚመለከቱ ምልክቶች በስህተት እንኳን ሊታዩ አልቻሉም፡፡ በኢንቨስተሮች ማኅበር ተዘጋጅቶ ስታዲየም በር ላይ የተሰቀለው ’ሬክላም’ እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪቫን ሲቆርጡ አብሮ መታየት እንዳይችል ተደርጓል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ነገሮች ሁሉ ሆን ተብሎ እንደተደረጉ ማመን የተቻለው፡፡ እንዲያውም ከአንዳንድ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር የመገናኘት ዕድል የገጠማቸው ሰዎች ማብራሪያ ለማግኘት ያደረጉት ሙከራ፣ ከኪራይ ሰብሳቢዎችና ከጋንግስተሮች ጋር እንኳን መወያየት ይቅርና አብሮ መታየትም አስፈላጊ እንዳልሆነ የሚያስረዳ መልስ እንዳስገኘላቸው መግለጽ ጀመሩ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው በበርካታ ባለሀብቶች አዕምሮ ላይ የመጠላትና የመገፋት ስሜት ማደሩ በግልጽ መታየት የጀመረው፡፡ ጣጣዋ የማያልቀው ጋምቤላና ፈተናቸው የማያልቀው ባለሀብቶቿ ግን አንገታቸው እየደፉም፣ እያቃኑም የአብሮነት ጉዞውን ከመቀጠል አልተገቱም፡፡

በዚህ ክስተት ዙሪያ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቢኖሩም ለመድረክ እንዳይበቃ የታፈነውን ችግር ተሸክሞ ከመጓዝ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረም፡፡ እንዲያውም ይህ ከፍተኛ መነጋገሪያ የሆነው ጉዳይ የመወያያና የግምገማ መድረኮች ተዘጋጅተው ሁሉም ነገር ይፋ ሊደረግ የሚገባበት ጊዜ ቀደም ማለት ነበረበት እንጂ፣ ችላ መባል አልነበረበትም፡፡ እንደዚህ መሽቶም ግን አልተቻለም፡፡  ስለዚህ ሁሉም ነገር እንደተድፈነፈነ የሚሆነውን ከመጠበቅ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረም፡፡

ያልታሰበው ዱብ ዕዳ

መሪዎቻችን ከጋምቤላ ወደ አዲስ አባባ ተመልሰው ብዙም ሳይቆዩ ባንኮች ለግብርና ኢንቨስትመንት የሚሰጡትን ብድር በአስቸኳይ እንዲያቆሙ መመርያ መሰጠቱ ተገለጸ፡፡ ይህ እንደሚሆን ቀድመው የማወቅ ዕድል ያላቸው የቤት ልጆች የመንግሥትን ውሳኔ ሰምተው እንዳልሰሙ በመምሰል ይሁን በመቅደም የሚፈልጉትን በፍጥነት እንደተሻሙ ጭምጭምታ ተሰማ፡፡ በየጫካው ተበትነው ከቀን እስከ ሌሊት በልማት ተጠምደው ለሚኖሩት ዜጎች ግን ዜናው አስደንጋጭ መርዶ ነበር፡፡ ምክንያቱም ለባንኮች ያስገቡት የብድር መዋጮ በየእርከኑ ሊለቀቅላቸው የነበረ ገንዘብ ሁሉ ተቆልፎበታልና፡፡ በዚህ ሰበብ በተለይም የብድር ገንዘባቸው ሙሉ ለሙሉ ያልተለቀቀላቸው ፕሮጀክቶች እንቅስቃሴ በየነበረበት እንዲቆም ይገደዳልና፡፡ በዚህ ምክንያም ምንጠራ የጨረሰ ማረስ አልቻለም፡፡ ያረሰም ለመዝራት አልቻለም፡፡ ግንባታዎችም በነበሩበት ቆሙ፡፡ እስከዚህ ወቅት ድረስም የታየ ለውጥ የለም፡፡ ብዙ ሀብት ፈሶበት የታረሰ፣ የተመነጠረ መሬት ሁሉ እንደገና ወደ ኋላ ተመልሶ ወደ ጫካነት እየተቀየረ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ በልማቱ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ምን ያህል  እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ ወደ ሥራ ለመግባት እየተዘጋጁ ባለበት ወቅት የመንግሥትን ውሳኔ ሲሰሙ የሆነው እስኪሆን ድረስ በማለት የወሰዱትን ገንዘብ ወደ ሥራ ሳያገቡ ይዘውት እንደተቀመጡ ይነገራል፡፡ በዚህ ምክንያት በልማቱ ላይ የሚያርፈው ተፅዕኖ ምን  ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

የዘገየው ውሳኔ

ከባንኮች ዕገዳ ቀጥሎ የሚመጣው የመንግሥት ውሳኔ ከባንኮች በብድር የተወሰደው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ወይም አለመዋሉን ለማረጋገጥ እንዲችል ማስጠናት ነው፡፡ ይህን ተልዕኮ የያዘ ኮሚቴም ተዋቅሮ ሥራውን ለመጀመር ጋምቤላ እንደደረሰ ነው ተቃውሞ የገጠመው፡፡ የመጀመሪያው በፌዴራል እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንት አስተዳደር ኤጀንሲ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ መካተቱ ነው፡፡ ይህ ኤጀንሲ ከዚህ በፊት አደረጋቸው በተባሉት ተገቢ ያልሆኑ አሠራሮችና እስከ ብሔር የዘለቁ የስም ማጥፋት ቅስቀሳዎች ምክንያት፣ ከጋምቤላ የእርሻ ባለሀብቶች ጋር እጅግ በጣም የከረረ ቅራኔ ውስጥ የገባ ስለሆነ ነው፡፡ እናም ይህ ጥላቻን መሠረት ያደረገ አፍራሽ አቋም የያዘ አካል ጥናቱ በተገቢው መንገድ እንዳይካሄድ ተፅዕኖ ይፈጥራል ከሚል ሥጋት የመነጨ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የጉዳዩ ባለቤቶች የሆኑትን ባለሀብቶች በተወካዮቻቸው አማካይነት የጥናት ኮሚቴው አካል እንዲሆኑ ይደረግ በሚል መነሻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ተቀባይነት ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ ገና ከጅምሩ እንቅፋት ያጋጠመው ኮሚቴ በሁለት ዙር ጥናት ያለውን አጠናቆ በሰኔ ወር 2008 ዓ.ም. ሄደ፡፡ በመሠረቱ የአገር ሀብት እየተዘረፈ ነው እየተባለ ከአገር ቤት እስከ ዓለም ዳርቻ በሰፊው አቤቱታ የሚቀርብበትን ይህን ጉዳይ በስማበለው ሳይሆን ጥናት በማካሄድ ተጨባጩን እውነታ ለማግኘት መንግሥት የወሰደው ዕርምጃ ተገቢ ነው፡፡ ከአሉባልታው ተቀባይነትና ስፋት አንፃር ነው ግን ዕርምጃው ቀደም ቢልና በተለይ የተጀመሩ እርሻዎች የማይቋረጡበት መንገድ ተቀይሶ ቢሆን መልካም ይሆን ነበር፡፡ ሳይንሳዊ ጥናት ማካሄድ ሳይንሳዊ መፍትሔ ለማስቀመጥ እንደሚበጀው ሁሉ፣ መነሻው ትክክለኛ ያልሆነ አካሄድም መድረሻው ትክክለኛ ሊሆን እንደማይችል ዕሙን ነው፡፡ ሁሉም ነገር በሰዓቱና በጊዜው ሲሆን ያምራል፡፡

ጅምላ ፍረጃ

በባንኮች በግብርና ኢንቨስትመንት ለተሠማሩ ባለሀብቶች የተሰጠው ብድርና ከቀረጥ ነፃ የገቡ ዕቃዎች ለተባለው ዓላማ ስለመዋሉ በማረጋገጥና ውጤታማነቱን በማጣራት በጥናት ሪፖርት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማቅረብ የሚል ዓላማውን ከመግቢያው ቀጥሎ በማስቀመጥ፣ ከግቦች እስከ የመረጃ ትንተና ዘዴው ማብራሪያ የሰጠውና በጋምቤላ ብሔራዊ ክልል መንግሥት በግብርና ኢንቨስትመንት ለተሠማሩ ባለሀብቶች የባንክ ብድር አጠቃቀም የጥናት ሪፖርት የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ የጥናት ውጤት፣ በባለድርሻ አካላት በጉጉት እየተጠበቀ ነው የ2009 ዓ.ም. ታኅሳስ ወር የባተው፡፡ ውስጥ ለውስጥ ሹክሹክታዎች መሠራጨት ሲጀምሩ መንግሥት የሪፖርቱን ውጤት ይፋ የሚያደርግበት ወቅት እንደደረሰ ታመነ፡፡ ይኼ በሆነ መንገድ በሚመለከተው አካል ለባለድርሻ አካላት ቀርቦ ውይይትና ግምገማ ይቀርብበታል ተብሎ የሚጠበቀው የዚህ ጥናት ውጤት ከሬድዮ ፋና እስከ ኢሳት ቴሌቪዥን፣ ከፎርቹንና ከሪፖርተር ጋዜጦች እስከ ቪኦኤ ባሉ የመገናኛ ብዙኃን ሥርጭቱ ይፋ የሆነው በድንገት ነበር፡፡ አሉ የተባሉ ችግሮች ማጣፈጫ እየተጨመረላቸው ጋምቤላ ላይ በእርሻ ልማት ስም የአገር ሀብት መዘረፉ አሉባልታ ሳይሆን እውነት መሆኑን የሚያበስሩትን ገለጻዎች የጋምቤላን ባለሀብቶች ክብርና ሞራል አከራካሪ የጎዱ ነበር፡፡ በጋምቤላ እርሻ እያለማሁ ነው ብሎ መናገር እስኪያሸማቅቅ ድረስ፡፡

ለተለያዩ ሚዲያዎች መግለጫውን ከፈጠራ ጋር እያሳመሩ የሚሰጡት ግለሰቦች በጥናቱ እንዳይሳተፉ ተቃውሞ ቀርቦባቸው የነበሩ ኤጀንሲ መሪዎች ‹‹አንበሳ ገዳይ›› ከሚመስል ኩራት ጋር አሁን አገኘናቸው ዓይነት የብቃለ ስሜት እያንፀባረቁ ሲያራግቡት ለመታዘብ ችለናል፡፡ የጥናት ቡድኑ የተመራው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የግብርናና የኢንዱስትሪ ፖሊሲና ዕቅድ አፈጻጸም ክትትል ሚኒስትር ዴኤታ በነበሩ ግለሰብ ስለነበርም ስለጥናቱ ውጤት መግለጫ መስጠት የነበረባቸው እሳቸው መሆን ሲገባቸው፣ ጠላት ተብሎ ለተፈረጀው አካል ተላልፎ የተሰጠበት ሚስጥር ምንድን ነው? የሚል ጥያቄና ሀሜት በሰፊው ተስተጋብቷል፡፡ ኃይለኛ ቁጭትም ፈጥሯል፡፡ ምክንያቱም በተለይም የብድር አጠቃቀምን በተመለከተ የሚባለው ሁሉ ከእውነትነት የራቀ ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ አገር መንግሥት የሚባል ተቋም መኖሩ እንኳን አጠራጣሪ እንዲመስል የሚያደርግ ነበርና፡፡ ያም ሆነ ይህ በሁኔታው የተበሳጩት የጋምቤላ ኢንቨስተሮች ኅብረት ሥራ ማኅበር አመራር አባላትም እውነታው ሌላ መሆኑን የሚያስረዱ ማስረጃዎችን አየጠቀሱ ለመሞገት ጥረት ማድረጉን ተያይዘውታል፡፡ የዚህ ውጤትም ኅብረተሰቡም የተለያዩ ጥያቄዎችን እንዲያነሳና እውነቱም ገና መሆኑን ወደ መቀበል እንዲደርስ ገፍቶታል፡፡

እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን በእርሻ ልማት ስም የሚያጭበረብር የለም ብሎ ለመከራከር የሚደፍር የለም፡፡ የመሬት ብድር ለመውሰድ በሚል ሒሳብ ብቻ መሬት የወሰዱ የለም ተብሎ አይታሰብም፡፡ ፕሮጀክታቸውን በመበደል ገንዘቡን ለሌላ ተግባር ያዋሉ አይኖርም ብሎ የሚከራከር የለም፡፡ በጠቅላላውም ገንዘብ ወስደው ሥራ ያልጀመሩም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሌላም ችግር ያለባቸው እንደሚኖሩ አያጠራጥርም፡፡ እነዚህንም ለይቶ ማቅረብ ለምን አልተቻም ነው ዋናው ጥያቄ ምርትና ገለባው ለምን አልተለየም ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ በጥናቱ ውስጥ ያለው ግኝት ሁሉ ትክክል አይደለም የሚል አይኖርም፡፡ በጣም በርካታ እውነታዎችን የያዘ ጥናት ነው፡፡ በተለይም ከመንግሥት የሥራ አፈጻጸም፣ ከፍትሕና ከድጋፍ ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር አያይዞ ያቀረበው ግኝት ቢያንስ እንጂ አልበዛም፡፡ ነገር ግን በተጨባጭ መሬት ላይ ያሉትን ኢንቨስተሮችን የሚመለከቱ መሠረታዊ ሀቆች አዛብቶ ማቅረብ አልነበረበትም፡፡ እርስ በርሱ የሚጣረስ መሆን አልነበረበትም፡፡ እነዚህ ደግሞ ማንም ተራ ግለሰብ እንኳን ሊፈጽማቸው የማይችሉ ተራ ስህተቶች ተብለው ሊታለፉ የማይችሉ ናቸው፡፡ እናም ሆን ተብሎ የተደረገ ነው እንድንል አስገድዶናል፡፡ ለምሳሌም የተወሰኑትን እንመልከት፡፡  

  1. የጋምቤላ ኢንቨስተሮችን በብድር የደገፉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ልማት ባንክ ናቸው፡፡ ሁለቱም የየራሳቸው የሆነ አሠራርና ዓላማ ያላቸው ስለሆኑ የተበዳሪዎችን ምንነት አውቆ ከማበደር እስከ ብድር አመላለስ ያለውን ክትትል ቅደም ተከተሉን ጠብቆ የሄደውንና ያልሄደውን ለይቶ ያስቀመጠ መሆን ነበረበት፡፡ የተሰጠውን ብድር ከታለመለት ዓላማ ውጪ ያዋሉትና ያላዋሉት የየትኛው ባንክ ተበዳሪዎች መሆናቸውን ለይቶ ማስቀመጥ ነበረበት፡፡ ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዋናው መሥሪያ ቤትና የጅማ ቅርንጫፍ የሥራ ውጤት ተለያይቶ መቀመጥ ነበረበት፡፡
  2. ከሁሉም ባንኮች ብድር ከወሰዱት ተገልጋዮች ውስጥ የውጭ አገር ዜጎችም ይገኙበታል፡፡ ከሦስት በመቶ የማይበልጥ መጠን ያላቸው እነዚህ የውጭ ባለሀብቶች በጋምቤላ ከተሰጠው የባንክ ብድር 50 በመቶ የሚሆን ለእነሱ የተሰጠ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንዲያውም ሁለት የአገር ውስጥ ዜጎች እንደተበደሩ የሚነገርላቸው ስምንት መቶ ሚሊዮን ብር ሲጨመርበት ከስድስት ወይም ከሰባት ለማይበልጡ ተበዳሪዎች ወደ 77 በመቶ የሚሆነውን እንደወሰዱት ያሳያል፡፡ እስከ 192 የሚደርስ ቁጥር ያላቸው የአገር ውስጥ ተበዳሪዎች የወሰዱት ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ ማስላቱ ቀላል ነው፡፡ የ192  የአገር ውስጥ ተበዳሪዎች የመሬታቸው መጠን ባይኖረኝም፣ ከላይ ከተጠቀሰው መጠን 23 በመቶ በገንዘብ ደረጃ ግን ያነሰውን ገንዘብ የተበደሩ መሆኑን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡ እናም እነዚህን እጅግ የሰፋ ልዩነት ያላቸውን ክፍሎች ጨፍልቆ ውጤት መስጠት እያዩ ማየት አለመፈለግን እንጂ ያስተላለፈው ሌላ መልዕክት የለም፡፡ ከእነዚህ የባህር ማዶ ተበዳሪዎች መካከል ከአንዱ በስተቀር ሌሎቹ በሥራ ላይ የሉም፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ የልማት ባንክ ይሁን የንግድ ባንክ መሆኑን ባናውቅም በብድር የወሰዱትን ገንዘብ ወደ ዶላር እየቀየሩ ይዘውት እንደሄዱ ሹክሹክታ አለ፡፡ ይኼ እውነት ከሆነ ማስረጃ አልተገኘም እንዳይባል እንጂ፣ ምዝበራው ግን በአገራችን ባለሥልጣናትና በአገራችን ባንኮች ፊት መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ታዲያ ይኼን ለያይቶ መፈተሽ ያልተቻለው ካለመፈለግ ወይስ ከእውቀት ማነስ ይሆን? ሁሉንም በልማት ባንኩና በአገር ውስጥ ምስኪን ደንበኞች ላይ ኃጢያት ለማብዛት ከሆነም ውጤቱ ለልማታችን መቼ ይጠቅማል?
  3. ለመሬት ልማት ለአገር ውስጥም ለውጪዎችም ከተለቀቀው ገንዘብ ውስጥ 83 በመቶ ለተገቢው ዓላማ መዋሉን በጥናቱ ሰነድ ገጽ ሰባት ላይ ተጽፏል፡፡ የባንኮች ብድር የሚለቀቀው ገንዘብ ለመሬት ልማት ለተሽከርካሪዎች መግዣ፣ ለግንባታ፣ ለሥራ ማስኬጃ፣ . . . በሚሉ ዘርፎች ተመድቦ ነው፡፡ ከባንኮች ለኢንቨስተሮች የተሰጠ ብድር ለታለመለት ዓላማ መዋልና አለመዋሉን የማጥናት ዓላማ ይዤ ተነስቻለሁ ያለው ቡድን፣ ከመሬት ልማት ውጪ ያለውን ገንዘብ አዋዋል በፐርሰንት ሳያስቀምጥልን አልፏል፡፡ በግልባጩ ግን ለእነዚህ ሦስት ዘርፎች የወጣውን ወጪ በአንድ ዓመት የምርት ሽያጭ ለተገኘው ገንዘብ በማካፈል ለታለመለት ዓላማ የዋለው ገንዘብ 18 በመቶ ብቻ መሆኑን አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ 85 በመቶ ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ አልዋለም ማለት ነው፡፡ ይህ በጣም የሚገርም ስሌት ከሀቁ እጅግ በጣም የራቀ መሆኑን ግን እዚያው ላይ ሰነዱ ያጋልጣል፡፡ ይህም ማለት የውጭ ባለሀብቶችን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይት ላይ ያልተገኙ 59 ተሽከርካሪዎች እንዳልተገዙ ታስቦ ዋጋቸው ወደ ባከነ ገንዘብ ተደምሮ እንኳን፣ ከባንክ ከተወሰደው ብድር ጠቅላላ ውስጥ 79 በመቶ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ያሳያል፡፡ 59 ተሽከርካሪዎች ዋጋቸው ተሰልቶ ቢቀነስና የውጭ ተበዳሪዎና የአገር ውስጥ ተበዳሪዎች ጉዳይ ተለይቶ ሲታይ ደግሞ 94 በመቶ ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ነው ሁኔታው የሚያሳየው፡፡ ይኼንን እውነታ በመካድ ስም ማጥፋት ለምን እንደተፈለገ አሁንም ጥያቄያችን ይቀጥላል፡፡ በጣም የሚገርመው 85 በመቶ የባንክ ብድር ለታለመለት ዓላማ አልዋለም እያለ ሲመራን የዋለው የጥናት ሪፖርት ሰነድ፣ እንደገና ተገልብጦ በማጠቃለያው ገጽ 19 አንቀጽ 2 ላይ ‹‹ምንም እንኳን የተሰጠው ብድር በአብዛኛው ለታለመለት ዓላማ ቢውልም የተወሰኑት ባለሀብቶች ብድሩን ከታለመለት ዓላማ ውጪ እንደተጠቀሙበት ያሳያል›› በማለት ራሱን በራሱ ይቃረናል፡፡ በእኔ በኩል ገርሞኝ ገርሞኝ አላልቅ ብሎኛል፡፡
  4. የጥናቱ ዓላማ በመንግሥት የተቀመጠለትን ተልዕኮ እንዲሳካ ቢፈልግ ኖሮ፣ በሔክታር 43 ብር ተሰልቶ የተሰጣቸው የቤት ልጆችና በሔክታር 19 ብር የተሰጣቸው የእንጀራ ልጆች ያሳዩት የልማት ውጤት መለየት ነበረበት፡፡ የመደራረብ ችግር ያለባቸው 27 ይዞታዎች ብቻ መሆናቸውን ቀደም ብሎ ያረጋገጠ አካል፣ እንደገና ተገልብጦ 380 ብሎ የሌለ ችግር እንዳለ አድርጎ ማቅረብ አይገባውም ነበር፡፡ ለእርሻ ሥራ ከቀረጥ ነፃ የሚፈቀደው በምን ዓይነትና ስንት ተሽከርካሪዎች መግባት እንዳባቸው በሕግ የተቀመጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በመኪና አስመጪ ፈቃድ የተለያየ ከቀረጥ ነፃ ለተፈቀደላቸው ግለሰቦች የተሸጡ ተሽከርካሪዎችና ከእርሻ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ማሽነሪዎች ሁሉ በመደማመር 78 መኪናዎች ከቀረጥ ነፃ በአንድ ግለሰብ ወደ ጋምቤላ እንደገቡ አድርጎ፣ ሕዝቡንና መንግሥትን ማሳሳት አይገባም ነበር፡፡ ወደ ዓድዋ የተወሰደን ዓርማታ ብረት ወደ ጋምቤላ ወስዶ መለጠፍ ምን ዓይነት ድንቁርና ያመነጨው ክፋት እንደሆነ የማይገነዘብ ማነው? እንዲህ ዓይነት ወንጀል ሲፈጸም ለመሆኑ አገሪቱ መንግሥት አልነበራትም ወይ? ይህን የሚመልስ ይመልሰው፡፡

ማጠቃለያ

ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ይህ በጥናት ስም የተካሄደ ሪፖርት ለባለድርሻ አካላት ቀርቦ ሳይታይ በጓሮ በር ለመገናኛ ብዙኃን በመሠራጨቱ ብዙ ጉዳት አድርሷል፡፡ ይህ እንዴት እንደሚታደስ ፈጣሪ ይወቀው፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ በተለይም ሬድዮ ፋና ጉዳዩን በተመለከተ ሚዛናዊ ዘገባ ከማቅረብ ይልቅ አንድ ወገንን ብቻ መሠረት ያደረገ ዘገባ ማቅረቡን እስካሁንም ድረስ መቀጠሉ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በግዮን ሆቴልና በጋምቤላ በተካሄዱ የንቅናቄ መድረኮች ለባለድርሻ  አካላት ቀርቦ በተደረገው ግምገማ፣ መንግሥትና ተበዳሪዎችን ሊያግባባ አልቻለም፡፡ በተለይ ጋምቤላ ላይ ለሁለት ቀናት የቆየ ውይይት ቢደረግም ከንትርክ በቀር የተገኘ ትርፍ አለመኖሩ በግልጽ ታይቷል፡፡ ለሁሉም የየራሱን ዋጋ በትክክል ከማስቀመጥ ይልቅ ሁሉንም በጅምላ የጨፈለቀ በመሆኑ፣ መሠረታዊ የሆነውን ዓላማውን የዘነጋና ትክክለኛ መፍትሔ እንዳይገኝ እንቅፋት የሚፈጥር ስለሆነ መንግሥት እንዲገነዘበው ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡

ይሁን እንጂ መንግሥት የጥናቱን ውጤት ተብዬ እንደ ትክክለኛ የተቀበለው ይመስላል፡፡ የአገራችን ከፍተኛ መሪዎች በአንዳንድ መድረኮች የሚሰጧቸውን መግለጫዎች ለዚህ ምሥክር ናቸው፡፡  በጋምቤላ እርሻ ልማት ስም በተወሰደ ብድር የተሠሩ ፎቆች እንዳሉ በተጭበረበረ መንገድ ከቀረጥ ነፃ የገቡ ተሽከርካሪዎች እንዳሉ ወዘተ. . . እነዚህም በቁጥጥር ሥር ውለው ወደ ሕግ እንደሚቀርቡ እየተነገረን ነው፡፡ ይህ በተግባር እንዲገለጥና ሌቦች ዋጋቸውን እንዲያገኙ ሁላችንም እንፈልጋለን፡፡ ውጤቱን ከዛሬ ነገ እንሰማለን በማለት በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ነን፡፡ ለነገሩ ፎቅ ሊያሠራ የሚችል ገንዘብ የተሰጣቸው እነማን እንደሆኑ የሰጣቸው አካልም በሚገባ ያውቃል፡፡ ‹‹ከአንጀት ካለቀሱ እንባ መች ይገድና›› በዚህም አለ በዚያ ተለባብሶ የሚቀር ሊሆን አይገባም፣ ሊቀርም አይችልም፡፡ በተጨባጭ ሁኔታውን በሚገባ ሳይጨብጡ የሚሰጥ ውሳኔ ስህተትን በስህተት በማደስ ስህተትን ከማበራከት ውጪ ሌላ ውጤት አይኖረውም፡፡ የመንግሥትን ፖሊሲና ሥርዓት በመተማመን ሕይወታቸውንና ጥሪታቸውን በየጫካው ውስጥ ለመስዋዕትነት ያቀረቡ ዜጎች በማንኛውም መመዘኛ መጠቃትና መበደል አይኖርባቸውም፡፡ ለልማት ተብሎ ከደሃ እናት አገራችን ካዝና በብድር የወጣው ገንዘብም ወደ ካዝናው መመለስ ይኖርበታል፡፡ ለዘመናት ከልማት ተገልሎ የኖረው የጋምቤላ ክልልም የተጀመረው የልማት ብርሃን ተመልሶ ሊጨልምበት አይገባም፡፡ የአንዱ አካል መውደቅ የሌላውም መውደቅ ስለመሆኑ፣ ማንኛውም የሚመለከተው ሁሉ ትክክለኛውን እውነታ አሸናፊ እንዲሆን ድጋፍ ማድረጉን እንዲቀጥል እያሳሰብኩ፣ እኔም ሕዝብና መንግሥት ሊያውቁት ይገባል ብዬ ያቀረብኩትን ጽሑፍ በዚሁ ቋጨሁ፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፣ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው tsigehiwotmebratu522@gmail.com.  ማግኘት ይቻላል፡፡ 

Standard (Image)

የመንግሥት ተቋማት የለውጥ መሣሪያዎች አፈጻጸም ውጤታማነትና ውድቀት

$
0
0

በአበባው አባቢያ

መንግሥታችን ለዜጎች ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው፣ ቀልጣፋና አርኪ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችለው የተለያዩ የለውጥ መሣርያዎችን ከአውሮፓና ከእስያ አገሮች በማስመጣትና በመቀመር፣ ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥት ተቋማት እንዲተገብሩ አድርጓል፡፡ እነዚህ ከፈረንጅ አገሮች የተወሰዱት የተለያዩ የለውጥ መሣርያዎች የመንግሥት ተቋማት አመራርና ሠራተኞች ቢገባቸውም ባይገባቸውም እንዲተገበር ተደርገዋል፡፡ ስለሆነም እየተተገበሩ ያሉትን የለውጥ መሣርያዎች የእንያዳንዱን ጥንካሬ፣ ድክመትና ውድቀትን በዝርዝር ለማሳየት አስቤ ይህን አጭር ጽሑፍ ለማዘጋጀት ተገደድኩ፡፡ መንግሥትም ያለውን እውነታ በጥልቀት በመመልከት የተጀመሩት የለውጥ መሣርያዎችን በአግባቡ እንዲተገበር ቢያደርግ የተሻለ እናድጋለን የሚል እምነትም አለኝ፡፡ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ለመኖር ሲባል ያልተከናወነውን ተከናወነ፣ ያልመጣውን ለውጥ መጣ እየተባሉ የሚቀርቡ ቀልዶች መፍትሔ ሊበጅላቸው ይገባል፡፡ ለእውነት የቆሙ፣ ለእውነት ሥራቸውን የሚሠሩና የእውነት ሪፖርት የሚያቀርቡ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ይህ አስተያየት አይመለከታቸውም፡፡

የመጀመርያው የለውጥ መሣሪያ የመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ነው፡፡ ይህ የለውጥ መሣርያ የተወለደው እ.ኤ.አ. 1990 በአሜሪካን ሲሆን፣ ወደ አገራችን የገበው እንደ እ.ኤ.አ. በ1998 ነው፡፡ ይህ በመንግሥት ተቋማት በዘመቻ እንዲተገበር የተደረገ የለውጥ መሣሪያ ነው፡፡ ስለሆነም የመንግሥት ተቋማት በዚህ የለውጥ መሣሪያ ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥና በጥናት ላይ የተመሠረተ አዲስ ወይም የተሻሻለ አሠራር ለመዘርጋት ብዙ ገንዘብ ወጪ አድርገዋል፡፡ በተዘረገው አዲሱ አሠራርና በተሻሸለው አሠራር ብዛት ያላቸው ሠራተኞች ከሥራ ተፈናቅለው ያለ ሥራ ለዓመታት ደመወዝ ሲከፈላቸው ቆይቶ መጨረሻ ላይ እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡ የለውጥ መሣሪያ በሚያዘው መርህ መሠረት ሥራዎች ተፈጥሯዊ ፍሰትን ተከትለው ተደራጅተዋል በሚል ዕሳቤ የሚቃረኑ ሥራዎች ጭምር በአንድ ሰው አማካይነት ውሳኔ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ እዚህ ላይ የጥቅም ግጭት እንዲስፋፋ ተደርጓል፡፡ በብዙ ሺሕ ብር የተገነቡ የሕንፃ ቢሮዎች ተንደው ሠራተኞች አንድ ላይ እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡ ሥራን ለማቀለጠፍ ሲባል ብዛት ያላቸው ኮምፒዩተሮች ተገዝተዋል፡፡ በአንዳንድ ተቋማት በአዲስ ምደባ ስም ሠራተኞች የደረጃ ዕደገት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ አዲሱን አሠራር ተከትሎ የተዘረጉ አሠራሮችን ለማከናወን ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅ በየተቋሙ መግቢያ በር ላይ በሚያንፀበርቅ ጽሑፍ ተለጣጥፏል፡፡ ተገልጋይ በተቀመጠው ጊዜና ጥራት አገልግሎቱን ባያገኝ የት ማመልከት እንደሚቻልም በሚታይ ቦታ ተለጥፏል፡፡ በጣም ጥሩ ነበር፡፡

የመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ መርሁ በሥራ ሒደት መሠረታዊና ዕመርታዊ ለውጥ በማድረግ ለተገልጋይ ፈጣን፣ ቀልጣፋና አርኪ የሆነ አገልግሎት ለዜጎች መስጠት ነው በአጭሩ፡፡  በእውነትም ከላይ የተገለጹት ሥራዎች ሲከናወኑ በነበረበት ወቅት በተወሰነ ደረጃ የመንግሥት አገልግሎት ቀልጣፋ ነበር፡፡ በዚህ አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡ የመንግሥት ተቋማት እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡

የለውጥ መሣሪያው በተወለደበት አገር በተገቢው ጥቅም ላይ ውሎ በብዙ ተቋማት ውስጥ አመርቂ ውጤት ማምጣቱ ከተለያዩ ጽሑፎች መረዳት ይቻላል፡፡  በአገራችን ግን የተለፋበትንና ወጪ የተደረገበትን ገንዘብ ያህል ለውጥ አምጥቷል ወይ? ቢባል እኔ አላመጣም ነው ምላሼ፡፡ ምክንያቶቹ የመጀመርያው የለውጥ መሣሪያውን በራሱ በትክክል አለመረዳት ወይም በተዛባ መንገድ በመረዳት ሲሆን፣ የለውጥ መሣሪያዎች በመጠቀም አዲሱን አሠራር የዘረጉ ሰዎችም ሆኑ የተዘረጋውን አሠራር የሚተገብሩ ሰዎች በለውጥ መሣሪያው ላይ በቂ ግንዛቤና እምነት አለመያዛቸው ነው፡፡ እንዲሁም በአዲሱ አሠራር በተዋቀረው አደረጃጀት ላይ የተካሄደው ምደባ ፍትሐዊ አይደለም ብለው የሚያምኑ በመኖራቸው የለውጥ መሣሪያውን ለውድቀት ዳርጎታል፡፡ በመሆኑም ከመጀመርያውኑ ውጤት የሚያመጣ የለውጥ መሣሪያ ሆኖ እንዲተገበር አልተደረገም፡፡ አዲሱ የአሠራር ሥርዓት ሲዘረጋ ቢሮዎች ተነድነው ሠራተኞች በተርታ ተቀምጠው ለዜጎች አገልግሎት እንዲሰጡ ቢደረግም፣ አገልግሎቱን የሚሰጡ ፈጻሚዎች በለውጥ መሣሪያው ላይ ዕውቀትና እምነት ስለሌላቸው የተገልጋዩን መንገላታት አላስቀረም፡፡ በእንዝላልነት በተዘረጋው አዲሱ አሠራር ሠራተኞች ያላቅማቸው ውሳኔ ሰጥተዋል፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅመው አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ የግል ጥቅም ማካበቻ ያደረጉ አመራሮችና ሠራተኞች ብዙ ናቸው፡፡ በተለይ እርስ በርሳቸው ለጥቅም ግጭት የተጋለጡ አሠራሮች በአንድ ሰው ኃላፊነት እንዲመሩ በመደረጋቸው፣ በአንዳንድ ተቋማት ውስጥ የመንግሥት በጀት በሕገወጥ መንገድ ለዝርፍያ እንዲጋለጥ መደረጉን መረጃ አለ፡፡ በእርግጥ የተወሰኑና በጣም ጥቂት የመንግሥት ተቋማት የለውጥ መሣሪያውን በመጠቀም የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ እንዳሉ የሚካድ አይደለም፡፡ 

የመንግሥት ተቋማት አመራርና ሠራተኞች በአንድ ክፍል ተቀምጠው ለዜጎች አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉ፣ የሚሰጡ አገልግሎቶች የጥራት፣ የጊዜና የመጠን መለኪያ ስታንዳርዶች እንዲኖሩ ተደርገው መቀረፁ ተገቢነት ያለውና የማያጠያይቅ ቢሆንም፣ ሠራተኛውና አመራሩ በአዲሱ አሠራር የተዘረጉትን የአገልግሎት መስጫ ስታንዳርዶችን በደቂቃ፣ በሰዓትና በቀን ለይቶ በመመዝገብና በመለካት የተገኘውን ለውጥ ለማረጋገጥ የማይችሉበት ሁኔታ መኖር ደግሞ በጣም ጥፋት ነበር፡፡ ለተገልጋይ  አገልግሎት መቼና እንዴት ይሰጣል? የተሰጠው አገልግሎትና የተገኘው ውጤት እንዴት ይለካል? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ራሱን የቻለ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት የሚያስፈልገው ቢሆንም፣ ይህን ለማድረግ በለውጥ መሣሪያው ላይ በቂ ዕውቀትና እምነት ያለው ቁርጠኛና ብቃት ያለው አመራርና ሠራተኛ ባለመኖሩ የለውጥ መሣሪያው ለውድቀት ተደርጓል፡፡ ተገልጋይም አገልግሎቱ ላይ የሚደረገው መወሳሰብ፣ ቀጠሮ የማብዛትና የማመላለስ፣ መዝገብ የመደበቅ ሁኔታዎች ስለሚሰለቹ አገልግሎት ለማግኘት በተቋም ውስጥ የሚያማልድ ዘመድ ከመፈለግ አልፎ ለመብቱ ጉቦ ለመስጠት እንዲገደድ አድርጎታል፡፡ በጉቦ አገልግሎት እንዲያፋጥንና መብቱን በገንዘብ እንዲገዛ ተደርጓል፡፡ የመልካም አስተዳደር ያለህ እንዲል አድርጎታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአንዳንድ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የመሠረታዊ የሥራ ሒደት የጥናት ሰነዱ ራሱ አይገኝም፡፡ የጥናት ሰነዱን ጥናቱን ያካሄዱ አመራርና ሠራተኞች ተቋሙን ሲለቁ ይዘው ሄደዋል፡፡ ስለሆነም ለውጡ ወድቋል ለሚለው ይህ በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡

የመሠረታዊ የአሠራር ሒደት ጥናት ሲካሄድ የነበሩ አመራሮችና ሠራተኞች በተለያዩ ምክንያቶች ሥራቸውን በመልቀቃቸው፣ አዲስ ተቀጥረው ወይም ተመድበው እንዲሠሩ የሚደረጉት ደግሞ በለውጥ መሣሪያው ላይ በቂ ሥልጠና አላገኙም፡፡ የተዘረጋው የመሠረታዊ የአሠራር ሒደት ለውጥ ጥናት በአብዛኛው ከመንግሥት ተቋማት እየጠፋና እየተረሳ ነው፡፡ በመሠረታዊ የአሠራር ሒደት ጥናት መነሻነት የተዘረጉ አዳዲስ መዋቅሮች እየፈረሱ ወደ ነበሩበት  እየተመለሱ ናቸው፡፡ እንዲፈርሱ የተደረጉት ቢሮዎች እንደገና እንዲገነቡና ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ እየተደረጉ ናቸው፡፡ አለቃና ሠራተኞች በጋራ ተቀምጠው ይሠራሉ የተባለው ዛሬ ላይ አለቃዎች ለብቻቸው እየተሞሸሩ ከጸሐፊ ጋር ወደ ቢሯቸው ተመልሰዋል፡፡ የሠራተኞች የመወሰን ደረጃው እየተገደበ ሁሉም ውሳኔዎች በአለቃ ብቻ እንዲወሰኑ እየተደረገ ነው፡፡ ከፍላት መዋቅር ወደ ዕዝ ሰንሰለት መዋቅር የተለወጠውን አደረጃጀት የሚፈቅደውና የሚያፀድቀው የለውጥ ትግበራ ላይ ክትትልና የሚያደርገው አካል መሆኑ ደግሞ ግርምትን ይፈጥራል፡፡ በተለይም ሁለት ተቃራኒ ነገሮች በአንድ ተቋም በመከናወነቸው፣ ለመሠረታዊ የሥራ ሒደት ጥናት በመንግሥት ተቋማት ወድቀትና መጥፋት ተባባሪ አካል እንዳለም መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ሁለተኛው የለውጥ መሣሪያ የውጤት ተኮር ሥርዓት ነው፡፡ የዚህ የለውጥ መሣሪያ ውልደት እ.ኤ.አ. በ1992 በአሜሪካ ሲሆን፣ ይህ መሣሪያ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በሁሉም የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ቢገባቸውም ባይገባቸው በስፋት እየተተገበረ ነው፡፡ በዚህ ለውጥ መሣሪያ ላይ የሚታየው የዕውቀት፣ የክህሎትና የእምነት ችግር ነው፡፡ መጀመርያ በአገሪቱ ይህን ሥልጠና የሚሰጠው የሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ነው፡፡ ኢንስቲትዩቱ ሥልጠና መስጠቱ ልክ ቢሆንም ሠልጣኞቹ በቂ ግንዛቤ ጨብጠዋል የሚል ድምዳሜ የለኝም፡፡ ደግሞም ለሠልጣኞቹ ብቃት ፈተና ተሰጥቶ የሚረጋገጥበት አሠራር የለም፡፡ ይሁን እንጂ የለውጥ መሣሪያውን የፈጠሩት ሰዎች ሠልጣኙ በቂ ግንዛቤ ስለመያዙ ፈተና እንዲሰጥ ቅድሚያ ሁኔታ ማስቀመጣቸውን ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ በአንድ ወቅት በአንድ መድረክ ላይ የሰማሁት ሠልጣኝ አንዳንድ ጥልቅ ጥያቄዎችን ሲጠይቅ አሠልጣኞች ከመሥሪያ ቤት መሥሪያ ቤት ይለያል ስለሚሉን በለውጥ መሣሪያው ላይ በቂ ግንዛቤ እየጨበጥን አይደለም ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ቀጥሎም ይህ የለውጥ መሣሪያው በቅጡ ያልገባቸው ሠልጣኞች ወደ ተቋማቸው መጥተው የተቋሙን የውጤት ተኮር ዕቅድ ያቅዳሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ለመንግሥት ሪፖርት ለማቅረብ  እንዲያመች ልማዳዊ የሪፖርት አቀራረብ ሥርዓትን የተከተለ ዕቅድ ይታቀዳል፡፡ ስለዚህ በመንግሥት ተቋም ውስጥ የውጤት ተኮር ሥርዓት አስተቃቀድና ትግበራው ጠቃሜታው እምብዛም አይታወቅም፡፡ ተቋማት የበለጠ ትኩረት የሚሰጡት ለልማዳዊ ዕቅድ አስተቃቀድ ሲሆን፣ ጥቅሙን በሚገባ በቅጡ ስለማይረዱት ለውጤት ተኮር ሥርዓት አስተቃቀድ ብዙ ትኩረት አይሰጡትም፡፡ የውጤት ተኮር ሥርዓት የሚጠቀሙት በመንግሥት ተግብሩ ስለተባለ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም በዕቅድ ዝግጅት ላይ ያለውን የስህተት መጀመርያ እናያለን፡፡ ዕቅዱ ሲዘጋጅ ውስጣዊና ውጫዊ ዳሰሳ ችግሮች ላይ ዝርዝር ትንተና ይካሄድበታል፡፡ የሚታቀደው ዕቅድ ግን የተነተኑትን ችግሮች ሊፈታ የሚችል አይደለም፡፡ ተቋም በሕግ ሲቋቋም አንድን ዓላማ ለማሳከት ስለሚሆን ዕቅድ ሲዘጋጅ ተልዕኮው በግልጽ ይቀመጣል፡፡ የራዕይ ዝግጅት ግን ግልጽነት የሚጎለው ነው፡፡ ሊለካ የማይችል ራዕይ ይነደፋል፡፡

አብዛኛዎቹ ተቋማት አፍሪካን ወይም ዓለምን መምሰል የሚያስችል ራዕይ ይነድፋሉ፡፡ ይህ ራዕይ በአፍሪካ ወይም በዓለም የየትኛውን አገር ያህል እንደሚሆን ግን አይታወቅም፡፡ አፍሪካ ወይም ዓለም የተቋሙ ራዕይ እስከሚሳካ ድረስ ቆመው አይጠብቁም፡፡  በጣም ሊለወጡ ይችላሉ፡፡ ይሁንና በአፍሪካ ወይም በዓለም. . . ሆኖ መገኘት እየተባለ የሚነደፈው ራዕይ ለእኔ አይገባኝም፡፡ የአብዛኞቹ ተቋማት ራዕይ በዚህን ጊዜ የዜጎችን እምነት ይህን ያህል ተብሎ ሲታቀድ አይቼ አለውቅም፡፡ ካለም ጥሩ ነው፡፡ የሚቀረፁ እሴቶች ደግሞ የሥነ ምግባር ወይም የመልካም አስተዳደር መርሆዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን የተቋሙ አመራርና ሠራተኛ የቀረፁትን እሴት አይመስሉም፡፡ ተግባሮቻቸውም ይህን ለማረጋገጥ የሚያስችል አይደለም፡፡

ስትራቴጂካዊ የትኩረት መስኮች ንድፍ ዕቅዱን ለሚያዘጋጁትን ግልጽ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ የትኩረት መስኮች አንድ ተቋም በስትራቴጂካዊ ዘመን ውስጥ ትኩረት ሰጥቶ መፍትሔ የሚሰጣቸው ወይም ውጤት የሚያስመዘግባቸው ዋና ጉዳዮች መሆናቸውን የለውጥ መሣሪያውን የፈጠሩት ሰዎች ይገልጻሉ፡፡ ለትኩረት መስክ ውጤት ይነደፋል፡፡ ነገር ግን የተነደፈው የትኩረት መስክ ውጤት የሚለካ አይደለም፡፡ በመሆኑም ተቋማት የትኩረት መስኩ ውጤታማ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ማቅረብ የሚችሉ አይመስለኝም፡፡ በመጀመርያ ስትራቴጂካዊ ዘመን የተነደፉት የትኩረት መስኮች ስለመሰካታቸው ማረጋገጫ ሳያቀርቡ፣ በተቀጣይ ስትራቴጂካዊ ዘመን ሌላ የትኩረት መስክ ይነድፋሉ፡፡ ካልሆነም የመጀመርያውን የትኩረት መስክ ቀጣይ ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን መቼ ውጤት እንደሚመጠ አይታወቅም፡፡

ቀጥሎ የሚነደፉት ስትራቴጂካዊ ግቦችና መለኪያዎች ናቸው፡፡ በቁጥር በርከት ያሉ ስትራቴጂያዊ ግቦች ይነደፋሉ፡፡ መረጃ በትክክል ተሰብስቦ መለካት የማይቻሉ ስትራቴጂካዊ የአፈጻጸም መለኪያዎች ለእያንዳንዱ ስትራቴጂካዊ ግብ ይቀረፃሉ፡፡ መለኪያዎቹ ውስጥ አብዛኛዎቹ መረጃ ቀርቦባቸው የሚላኩ ሳይሆኑ የታቀደ ተከናወነ ለማለት ያህል የተቀመጡ ናቸው፡፡ መቶ ታቀደ ተብሎ መቶ ተከናወኑ የሚባልበት ሁኔታ በብዛት እንደሚኖር በጣም እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስትራቴጂካዊ ዕርምጃ ለምን እንደሚነድፉ አይታወቅም፡፡ ምክንያቱ በጀት ያልተፈቀደላቸውና ለዕቅድ ያህል የታቀዱ ናቸው፡፡ ይህ ስትራቴጂካዊ ዕርምጃ ስለመሳካቱ ማንም ክትትል የሚያደርግ አይመስለኝም፡፡ የተነደፉት ስትራቴጂካዊ ግቦችና ዕርምጃዎች ከበጀት ጋር ትስስር ስላሌለቸው የተቋሙ ስትራቴጂ ተሳክቷል ለማለት ያስቸግራል፡፡ በአጠቃላይ የውጤት ተኮር ሥርዓት ዕቅድ ለተቋም ምኑም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሠራተኞች እንዲያከናወኑ ተከፋፍሎ የሚሰጠው የውጤት ተኮር ሥርዓት ዕቅድ ቢታቀድም ባይታቀድም፣ መሥራት የሚገባቸው ዕቅዶች እንዲያከናወኑ ይደረጋል፡፡ የፈጻሚ ሥራ ውጤት የሚለካው የውጤት ተኮር ሥርዓትን ተከትሎ ሳይሆን፣ የተፈለገው ዕቅድ ታቅዶ እንዲጠናቀቅ ታሳቢ ተደርጎ የተሰጠው ዕቅድ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ባለሙያ በቀን ስንት ሰው ማስተናገድ ይችላል ተብሎ ታቅዶ ይሰጣል፡፡ ፈጻሚውም ሰላምታ ያቀረበውን ጭምር ማስተናገዱን ደምሮ ይህን ያህል አስተናግጄያለሁ ብሎ ባቀረበው ሪፖርት የዕቅድ አፈጻጸም ምዘና ይካሄዳል፡፡ መሆን የነበረበት ግን ካስተናገደው ተገልጋይ ምን ያህሉ ረክቷል የሚል ቢሆን ኖሮ በአሁኑ ወቅት እየተከሰተ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር ቁልፍ መፍትሔ ማግኘት ይቻል ነበር፡፡ ይህ ነበር የውጤት ተኮር ሥርዓት ትግበራ ፋይዳው፡፡

ስለሆነም ሠራተኞችን ለመለካትና ለመንግሥት ሪፖርት ለማቅረብ የሚታቀደው ዕቅድ በተቋሙ ውስጥ ለብቻው ስለሚታቀድ፣ የውጤት ተኮር ሥርዓት የታቀደው ዕቅድ ለተቋሙ በምንም አግባብ ውጤታማነትን ለመለካት አያገለግልም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሪፖርት ተቀባይ የመንግሥት አካል ሪፖርትን የሚፈልገው በውጤት ተኮር ሥርዓት ሳይሆን፣ የቀድሞውንና የተለመደውን ቁልፍና ዓቢይ ተግባራት የዕቅድ አፈጻጸም የተከተለ ሪፖርት ነው፡፡ ይህም የውጤት ተኮር ሥርዓት ትግበራ የተልጋይን ዕርካታና አመኔታ በማምጣት የሚሰጠውን ትልቁን ሚና እንዳይጨወት አድርጎታል፡፡ ወድቋል ያልኩትም ለዚህ ነበር፡፡

ይህም ሆኖ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስከ ወረዳ ድረስ ያሉት ተቋማት በየቢሮው አሸብርቀው የሚያስቀምጡት የውጤት ተኮር ሥርዓት ዕቅድ፣ በተለይም የስትራቴጂ ማፕ ለቢሮ በር አካባቢ ዕይታ እንዲያምር ካልሆነ በስተቀር ማንም የሚረዳው አይመስለኝም፡፡ ለኅትመት ሥራ ከፍተኛ ወጪ ማውጣት አስፈላጊ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ኃላፊነት የተሰጠው የመንግሥት አካል የውጤት ተኮር ሥርዓት አስተቃቀድ ለምን ዓለማ እንደሚጠቅምና ምን ውጤት ለመምጣት እንደሚያግዝ በቅጡ የማስገንዘብ፣ እንዲሁም በትክክል በማይፈጽሙት ላይ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ግዴታውን በንግግርና በወረቀት ሳይሆን በአካልና በተግባር ሊወጣ ይገባል፡፡ የውጤት ተኮር ሥርዓት የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት ያለውን ሚና በተገቢ መንገድ መጠቀም ይኖርብናል፡፡

የዜጎ ቻርተር ሦስተኛው የለውጥ መሣሪያ ነው፡፡ የዜጎች ቻርተር ተቋማት ለዜጎች አሠራራቸው ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው ስለማድረጋቸው ቃል የሚገቡበት የቃል ኪዳን ሰነድ ነው፡፡ በተቋማት የተዘጋጀው የዜጎች ቻርተር አንድን ቻርተር ለማዘጋጀት መከተል የሚገባውን መርህ በአብዛኛው የተከተለ ቢሆንም፣ ችግሩ አገልግሎቱ በተጠቃሚ ዜጎች እምብዛም አለመታወቁ ነው፡፡  ከላይ በመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ጥናት የተነደፉ ስታንዳርዶች በዜጎች ቻርተር ላይ የአገልግሎት አሰጣጥ ስታንዳርድ ተብለው የሚቀመጡ ቢሆንም፣ አገልግሎት ሰጪውም ሆነ አገልግሎት ተቀባዮቹ በትክክል የተረዱት ነገር ስለማይሆን ዜጋውም የተባለውን አገልግሎት በሰታንዳርዱ መሠረት ባለመቀበሉ ለምን በማለት አይጠይቅም፡፡ አገልግሎት ሰጪውም በአገልግሎት ስታንዳደርዱ ላይ በቂ ግንዛቤ ያልያዘ ከመሆኑም በላይ፣ አገልግሎት በስታንዳርዱ መሠረት ባለመስጠቱ የሚጠይቀው ያለ አይመስለኝም፡፡ የዚህ ሰነድ ዝግጅትና ኅትመት ወጪ አስፈላጊነቱም አሁንም ግልጽ አይደለም፡፡ የዜጎች፣ የተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ያለባቸውን የተጠያቂነት ደረጃ ከማሳየቱም በላይ መልካም አስተዳደር ለማስፈን ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ስለሆነ፣ የሚመለከተው አስፈጻሚ አካል የሚጠበቅበትን ኃላፊነቱን በተገቢው ሊወጣ ይገባል፡፡

አራተኛው የለውጥ መሣሪያ የለውጥ ሠራዊት ግንባታ ላይ ያለው ብዥታ ነው፡፡ የለውጥ ሠራዊት ተገነባ የሚባለው አንድ ዓለማ እንዲያሳኩ የተደራጁ የቡድን አደረጃጀቶች ሥራቸውን በእምነት፣ በዕውቀት፣ በባለቤትነት ስሜትና በፍቅር በማከናወን ከተጠበቀው ዕቅድ ወይም በላይ በቅልጥፍና ማሳከት ሲችሉ ነው፡፡ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚሠሩት ሠራተኞች ለዚህ የተዘጋጁ ናቸው ወይ የሚባሉ አይደለም፡፡ የአቅም ውስነነት ያለቸው ሠራተኞች በብዛት አሉ፡፡ በዚያ ላይ እነሱን የሚመራ አመራር ከእነሱ የባሰ አልምጥ ወይም ዳተኛ ነው፡፡ የለውጥ ቡድን አደረጃጀቱን በራሱ የፖለቲካ ሥራ አድርገው የሚያስቡ በርካታ ናቸው፡፡ እንዴት ሆኖ ነው ይህን በችግር የተበተበ የመንግሥት ሠራተኛ ግንባር ቀደም ይሆናል ተብሎ የሚታሰበው? ከአደረጃጀት ውስጥ በእርግጥ በቁጥር በጣም ውስን የሆኑ ጎበዝና የሥራ ፍቅር ያላቸው ሠራተኞች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነሱም ቢሆኑ መደበኛ የሥራ ሰዓት የሚያከብሩና ተገልጋይ በትህትና የሚያስተናግዱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዕውቀትና በክህሎት ግን የተካኑ አይሆኑም፡፡ አብዛኛዎቹ ግን ይህን መሥፈርት የሚያሟሉ ባለመሆናቸው የለውጥ ሠራዊትን በመንግሥት ተቋማት መገንባት በጣም ችግር ይሆናል፡፡ አመለ ሸጋውን ሠራተኛ ግንባር ቀደም የምንል ከሆነም በጣም የተሳሰትን ይመስለኛል፡፡ ሥራን ማቀለጠፍና መፍጠር የሚችል አመራርና ሠራተኛ ነው ለኔ ግንባር ቀደም፡፡ የተሰጠውን በየዕለቱ የሚያከናውን ወይም የሚያጠናቅቅ፣ ከአቅም በታች እያቀደ ሥራውን ከዕቅድ በላይ አከናወንኩ የሚል ሠራተኛ ግንባር ቀደም መባል የለበትም፡፡

በመንግሥት ተቋም ውስጥ የተፈጠረውን አሠራር ማከናወን የማይችል ዳታኛ ሠራተኛ በብዛት ስላለ የሚመለከተው አካል ብዙ ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ከትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ አቅም መገንቢያ ሥራዎች በስፋት መሠራት ይኖርባቸዋል፡፡ አንዴ የተወላገደውን ለማቃናት በተለይም የመንግሥት ተቋም ጊዜ ማጥፋት ያለበት አይመስለኝም፡፡ ግንባር ቀደም የሚባል አመራርና ሠራተኛ ግንባር ቀደም ለመሆን በቅድሚያ የለውጥ መሣሪያዎችን ጠንቅቆ የሚያውቅና መተግበር የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡ ያቀደውን ሥራ በቅልጥፍና፣ በፈጠራ በታገዘ ሁኔታ ማከናወን መቻል አለበት፡፡ ካልሆነ ግን ከአቅም በታች እያቀደ ብዙ ሠራሁ የሚለውን፣ በየሰዓቱ ከአለቃ ቢሮ የማይጠፈውን፣ አጎብዳጅ፣ ለአለቃ ወሬ የሚያመላልስ፣ ሰላምታ የሚያበዛ፣ ከበር መልስ የሚጋብዝ፣ ለቅሶና ሠርግ የማይቀር፣ የታመመ የሚጠይቅ፣. . . ሠራተኛና አመራርና ግንባር ቀደም የምንል ከሆነ አገሪቱን እየገደልን መሆናችንን መርሳት የለብንም፡፡ ይህ እኔ በተጨባጭ ያያሁት ስለሆነ፡፡ ሁላችንም የመንግሥት ተቋማት አመራርና ሠራተኛ ተገልጋይ የሚፈልገውን አገልግሎት በተፈለገው ጊዜ፣ ጥራትና መጠን በመስጠት እርካታና አመኔታን በማሳደግ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን እናድርግ፡፡ የለውጥ መሣሪያ አስፈጻሚ ተቋምም ለውጥን በወረቀት ሳይሆን በተግባር ለመገምገም ጥረት ያድርግ፡፡ ቸር ይግጠመን!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው goitomtekele640@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

Standard (Image)

ባቡር የካፒታሊዝም መሠረተ ልማት ስለሆነ ከዘመኑ ዕድገት አኳያ እንጠቀምበት

$
0
0

 

በመታሰቢያ መላከሕይወት ገብረክርስቶስ

በእንግሊዝ አገር የኢንዱስትሪ አብዮት ይካሄድ በነበረበት ወቅት ነበር ባቡርም ተፈልስፎ ሥራ የጀመረው፡፡ በዚህ ጊዜ ካርል ማርክስ በሕይወት የነበረበት ወቅት ነበርና ባቡር የካፒታሊዝም ዕድገት በባቡር አማካይነት በፍጥነት እንደሚሆንና ወደ ሶሻሊዝም የሚደረገው ጉዞ እንደሚፋጠን ጽፎ ነበር፡፡

ካርል ማርክስ እንደተነበየው ካፒታሊዝም በከፍተኛ ፍጥነት ማደግ ቢችልም፣ እንደተባለው ወደ ሶሻሊዝም የሚደረገው ጉዞ ግን የተሳካ አልነበረም፡፡ በዚህ ጽሑፍ በዋናነት ለመዳሰስ የምፈልገው ጉዳይ ባቡር በአንድ አገር ብቻውን ታላቅ ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችል፣ ከባቡር ጋር በርካታ በካፒታሊስታዊ ሥርዓት ሊተገበሩ የሚገቡ ተግባራት መኖራቸውን ነው፡፡

እንደሚታወቀው የባቡር ዋና አስፈላጊነቱ “Mass Load” (ብዝኃ ጭነት) ለማጓጓዝ የሚያገለግል የምድር መጓጓዣ ዘዴ ነው፡፡ ብዝኃ ጭነት ደግሞ የብዝኃ ምርት መኖርን የግድ ይላል፡፡ ብዝኃ ምርት እንዲኖር ደግሞ ዜጎች እንደ ዝንባሌያቸው የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት ያለ ችግር ሚፈልጉትን መሬት እየገዙ፣ ያለ ምንም ውጣ ውረድ ወደ ሥራ መግባት መቻል አለባቸው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ይህንን ተግባር ሕጋዊ የሚያደርግ የሕገ መንግሥት ሥርዓት መኖር አለበት፡፡

እዚህ ላይ ለማሳሰብ የምፈልገው ከላይ ከተጠቀሱት ተግባራት አንዱ እንኳን በአግባቡ ተሟልቶ ካልተገኘ ባቡርን በበቂ ሁኔታ መጠቀም የሚያስችል ምርት ማምረት የማይታሰብ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አሁን የገነባውን ባቡር ውጤታማ ለማድረግ በገበያ መር ኢኮኖሚ የሚመራ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መኖሩ የግድ ይላል፡፡ ይህንን በድፍረትና በተፋጠነ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ ካልተቻለ፣ ባቡሩ የተገነባበትን የብድር ገንዘብ ከሌሎች ዘርፎች ከሚገኝ ገንዘብ ለመክፈል የምንገደድ በመሆኑ አገሪቱን ወደ ከፋ ድህነት ይከታታል፡፡

በቅርቡ ሪፖርተር ጋዜጣ እንዳስነበበን ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች ካላት አቅም አኳያ ከአሥር በመቶ በታች መሆኑ በእጅጉ አስደንጋጭ ዜና ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ለማሻሻል ባቡር አንዱ አማራጭ ቢሆንም ለሁሉም ግን አማራጭ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ ካላት የሚታረስ መሬት አብዛኛው በዝናብና በመስኖ የሚለማ ሆኖ ሳለ በካፒታል፣ በዕውቀት፣ በገበያ ዕጦት ምክንያት አብዛኛው ገበሬ ዝናብን ጠብቆ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የማምረት ልምድ በበቂ ሁኔታ መለወጥ አልቻለም፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ብዝኃ ምርት ለማምረት በበሬ የሚታረስ መሬት የትም አያደርሰንም፡፡ ከገበሬው ፍጆታ አልፎ ባቡር ላይ የሚጫን ምርት ለማምረት የግድ ዘመናዊ እርሻ መስፋፋት አለበት፡፡ ይህ ዓይነት የአስተራረስ ዘዴ አምራቾች የእርሻ ባለሙያዎችን እየቀጠሩ የአፈር ምርመራ፣ የአዝርዕት ዓይነቶችንና ሌሎችንም ሳይንሳዊ ሥራዎችን በማከናወን የኤክስፖርት ደረጃ ያሟሉ ምርቶችን እንዲያመርቱ ይረዳቸዋል፡፡ እጅግ አስቸጋሪ የሆነውንና ውድድር የበዛበትን የኤክስፖርት ገበያ አሸንፎ አገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግ መሥራት ካልተቻለ፣ ባቡራችን የዕድገት የብልፅግና ምንጭ መሆኑ ይቀርና ለከፋ ችግር ሊዳርገን ይችላል፡፡

ኢሕአዴግ ደጋግሞ እንደሚነግረን በአነስተኛ ማሳ ላይ የሚከናወን የእርሻ ሥራ ከምንም ዓይነት ሳይንሳዊ ዘዴ ጋር ያልተያያዘ በመሆኑ፣ የትም ሊያደርስ የማይችል መሆኑን ተገንዝበን ፈጣን ዕርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን፡፡

እንደሚታወቀው ባቡር የብዝኃ ምርት ማጓጓዣ እንደመሆኑ መጠን በሦስት የተከፋፈሉ ጉዳዮች ላይ ለማተኮር እንገደዳለን፡፡ አንደኛ በብዛት የተመረተ የእርሻ ምርት፣ ሁለተኛ በብዛት የተመረተ የኢንዱስትሪ ምርትና ሦስተኛ በብዛት የተመረተ የጥሬ ማዕድን ምርት ናቸው፡፡

አሁን ባለንበት የዕድገት ደረጃ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች በባቡር ተጉዘው ከቦታ ቦታ ይጓዛሉ የሚለው ተቀባይነት ይኖረዋል ብዬ አላምንም፡፡ በመሆኑም ባቡሩ በርካታ ሰዎችን በማጓጓዝ ከፍተኛ ገቢ በቅርብ ጊዜ ያገኛል የሚል እምነት የለኝም፡፡

ባቡር እንደሚታወቀው ብዝኃ ምርትን፣ ብዝኃ ትራንስፖርትንና ብዝኃ ፍጆታን የሚረዳ ዓይነተኛ መንገድ ሲሆን፣ ባቡሩ ውጤታማ እንዲሆን ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ሁሉ በበቂ ሁኔታ ተሟልተው መገኘት አለባቸው፡፡ በመሆኑም አንዱን ከአንዱ ለይቶ ማየት ወይም ልዩ ትኩረት መስጠት ትልቅ ስህተት ነው፡፡

ሌላው ትልቁ ቁም ነገር ሕገ መንግሥት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አይለወጥም አይሻሻልም የሚባል ነገር ሳይሆን ሁኔታዎች በተለወጡና ሳይንስ ባደገ ቁጥር፣ የሕዝብ ብዛትና ፍላጎት እየጨመረ ሲመጣ በየጊዜው ወቅትን ተከትሎ መሻሻል ካልቻለ የሚያስከትለው ችግር አገርን እስከ ማፍረስ የሚደርስ ነው፡፡ ይህንንም ክስተት በቅርብ ዓመታት በብዙ የዓለም አገሮች ሲከሰት ተመልክተናል፡፡

በዚህ ጽሑፍ አርዕስት ላይ እንደተጠቀሰው ባቡር የካፒታሊዝም መሠረተ ልማት በመሆኑ፣ መሬት መሸጥ መለወጥም በአንድ ካፒታሊስት ማኅበረሰብ ዋነኛ ተግባር ነው፡፡ ሁለቱን ነጣጥሎ ማየት በምንም ሁኔታ የማይታሰብ ነው፡፡

በዓለማችን በተለያዩ ጊዜያት በኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ያመጡ ቴክኖሎጂዎች ተፈጥረዋል፡፡ ከዛሬ 100 ዓመት በፊት በአውሮፓ ፎቶ ማንሳት ሲጀመር በጣም በርካታ ሠዓሊያን (የሰው ምሥል እየሠሩ ይተዳደሩ የነበሩ ሰዎች) ሥራ አጥ ሆነዋል፡፡ በ1990ዎቹ ደግሞ ዩሮታናል የሚባል በባህር ሥር የተሠራ ዋሻ ከፈረንሣይ እስከ እንግሊዝ ከተገነባ በኋላ፣ የበርካታ ሰዎችን ሥራ ባቡሩ ስለወሰደባቸው ለጊዜው የተወሰነ መንገራገጭ ተፈጥሮ ነበር፡፡

አሁንም በአገራችን ከአዲስ አበባ እስከ ጂቡቲ ያለው መስመር ሥራ ሲጀመር ለተወሰነ ጊዜ መንገራገጭ መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ነገር ግን በሒደት ከአዲስ አበባ እስከ ጂቡቲ ኮንቴይነር የሚያጓጉዙ የጭነት ተሽከርካሪዎች የሥራቸው ዓይነት ይቀየራል እንጂ ሥራ ፈት አይሆኑም፡፡ ምክንያቱም ባቡር በባህሪው እጅግ ብዙ ጭነት ስለሚፈልግ እነዚህ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ጉዞዋቸው ወደ ባቡር ጣቢያ ይሆናል፡፡ በሒደትም እስካሁን ወደ ውጭ የማንልካቸው በርካታ ምርቶች በባቡር መጫን ሲጀምሩ፣ በአገር ውስጥ ያለው የጭነት ፍላጎት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ስለሚሄድ የሥራ ዕድል ይሰፋል እንጂ አይጠብም፡፡ በመሆኑም ከአዲስ አበባ ጂቡቲ የተሰማሩ ባለ ከባድ ተሽከርካሪዎች ሐሳብ ሊገባቸው አይገባም፡፡

አንድ በአገር ደረጃ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ እንደ ባቡር ያለ ቴክኖሎጂ በሚተዋወቅበት ወቅት፣ ለአንዱ እንጀራ ፈጣሪ ለሌላው ሥራ አጥነትን የማምጣቱ ክስተት የተለመደ ነው፡፡ ቢሆንም ራስን ቶሎ ከሁኔታዎች ጋር በማመሳሰል መፍትሔ ማግኘት ግን የማይቻል አይደለም፡፡ በተለይ በባቡር ጣቢያዎች አካባቢ እጅግ በርካታ የሥራ ዕድል መፈጠሩ ስለማይቀር፣ መንግሥትም ሆነ ባለይዞታዎች በዚህ ዘርፍ ሰፊ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ረቡዕ ጥር 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በወጣው የሪፖርተር ጋዜጣ የፊት ገጽ የዶ/ር ኢንጂነር ጌታቸው በትሩን ፎቶ ይዞ የወጣው ዜና ባቡሩ ስላለበት ዕዳ በርካታዎችን ያስደነገጠ ሲሆን፣ እኔን ያስደነገጠኝ ግን ዕዳው ሳይሆን ዕዳውን ቶሎ ቶሎ መክፈል እንዴት እንደሚቻል ነው፡፡ ለዚህም ባቡሩን ከደረቅ ወደብና ከተለያዩ ዴፖዎች ጋር የማገኛኘት ሥራ አለመሠራቱ በራሱ አስደንጋጭ ሲሆን፣ በዚህ ሪፖርት ላይ ለምን ይህ ጉዳይ ትኩረት እንደተነፈገው አልተገለጸም፡፡

ከላይ እንደተገለጸው ባቡር በርካታ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ለማሳለጥ የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ ይህ ጉዳይ በቂ ትኩረት አለመገኘቱ በግሌ በጣም አሳስቦኛል፡፡ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች የሚደራጁባቸው ዴፖዎችን የግሉ ዘርፍ በከፍተኛ ፍላጎት ሊሠራቸው የሚገባቸው በመሆናቸው ጉዳዩ ሊታሰብበት የሚገባው ገና የባቡር ልማት ሲጀመር ነበር፡፡ እነዚህን ዴፖዎች በአግባቡ መገንባት ከተቻለ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ዕድል ፈጣሪ የመሆን አቅም መፍጠር የሚቻል ከመሆኑም በላይ፣ ከገጠር ለሚሰደዱ ወጣቶች የስበት ማዕከል የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ውጭ ሊላኩ የሚችሉ ዕቃዎች ወይም ምርቶች የሚቀነባበሩባቸው መሠረተ ልማቶች በባቡር ጣቢያው አካባቢ ባለመኖራቸው፣ ነጋዴዎች ምርቶቻቸው፣ ገዢዎቻቸው በሚጠይቁት ደረጃ ማቀነባበር ካልቻሉ በቂ ምርት ቢኖርም መላክ አይቻልም፡፡ ለምሳሌ አንድ ነጋዴ ከየገበሬው ማሳ የመጣን ፍራፍሬ ባቡር ጣቢያ አካባቢ ተረክቦ በተፈለገው መንገድ አቀነባብሮና አሽጎ ባቡር ላይ ለመጫን የሚያስችሉ፣ እንደ መጋዘን የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ መዘጋጀት ነበረባቸው፡፡

ይህ ባለመደረጉ አሁንም ባቡሩ ሊጭነው የሚችለው ጭነት በአገር ውስጥ እያለ፣ ነገር ግን መሠረተ ልማቱ ባለመኖሩ ብቻ አገሪቱ የምትችለውን የውጭ ምንዛሪ ታጣለች ማለት ነው፡፡

ባቡሩ ሥራ ሲጀምር በርካታ መደነባበር የሚፈጠር ይመስለኛል፡፡ በተጨማሪም ባቡሩን ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በበቂ ሁኔታ ሠልጥነው ማስተዳደር እስኪጀምሩ ድረስ የሚያስተዳደሩት ቻይናውያን በመሆናቸው፣ እነዚህ ሰዎች ምን ያህል ተቋሙ ዕዳውን ቶሎ ቶሎ ሊከፍል በሚችልበት ደረጃ ያስተዳድሩታል የሚለው አሳሳቢ ይመስለኛል፡፡

እኔ ባሳለፍኩት የሥራ ዘመን የዓለምን ግማሽ አይቻለሁ ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ በዚህ ጊዜ ካየኋቸው የሠለጠኑ አገሮች የባቡር ጣቢያዎች መሠረተ ልማቶች በአጭሩ ለመግለጽ፣ ባቡር ጣቢያዎች በራሳቸው አንድ የከተማ ትልቅ አካል ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ምንም የሚጎድላቸው ነገር የለም፡፡ ሌላ ቀርቶ በብዙ አገሮች የከተማውን ቆሻሻ ሳይቀር ይዘው የሚወጡት ባቡሮች ናቸው፡፡ የቆሻሻ መኪኖች ከከተማው የተለያየ ክፍል የሰበሰቡትን ቆሻሻ ወደ ቆሻሻ ዴፖ ሲወስዱት ባቡሩ ደግሞ ከከተማ ውጪ ይወስደዋል፡፡ ይህ ለምሳሌ ቀረበ እንጂ ዴፖዎችን በተመለከተ ራሱን የቻለ አንድ ሰፊ ጥናታዊ ጽሑፍ ማቅረብ ይቻላል፡፡

ከጂቡቲ እስከ አዲስ አበባ የተዘረጋው የባቡር መስመር ከባህር በላይ አሥር ሜትር ከማይሞላው የጅቡቲ ወደብ ተነስቶ አዲስ አበባ ሲገባ 2,500 ሜትር ከፍታ የሚወጣ ብቸኛ አፍሪካ ውስጥ ያለ የባቡር መስመር ነው፡፡ ወደ ፊት ደግሞ ደጋማ ወደሆኑ ቦታዎች መስመሩ ሲቀጥል ይህ ከፍታ መጨመሩ አይቀርም፡፡ ይህ ማለት በቆላውና በደጋው የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የተለያዩ ምርቶችን ለመለዋወጥ ባቡር ዋነኛ መሣሪያ ነው፡፡ በተለይ በደጋው አካባቢ የሚመረተው የታሸገ ውኃ ለቆላው አገር ሰዎች ለማድረስ ሁነኛ መሣሪያ ነው፡፡ አገሪቱ ከውኃ ኤክስፖርት ከፍተኛ ገቢ የምታገኝ ይመስለኛል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ክረምት ሲሆን በዝቅተኛው አካባቢ የሙቀት መጠን በከፍተኛ መጠን ስለሚጨምር፣ የውኃ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ የሚደራ ይመስለኛል፡፡

ሌላው ደግሞ ለኢትዮጵያ ዜጎች ፍጆታ የሚውለው ምርት ውጭ አገር ተልኮ ዶላር ስለሚያገኝ ብቻ ኤክስፖርት የሚደረገውን ምርት እንኳን በአሁኑ ወቅት በአግባቡ የለየነው አይመስለኝም፡፡ መንግሥት ይህንን ማድረግ ካልቻለ ነጋዴው የሕዝብ ፍጆታ የሆነውን ምርት ሁሉ ባቡር ላይ ጭኖ ወደ ውጭ የሚልከው ከሆነ ያልተጠበቀ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል፡፡ በብዙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ይህ ችግር ለረጅም ጊዜ ተከስቷል፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎች ከባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር ይህንን ሥራ ሥራዬ ብለው ሊይዙት ይችላሉ፡፡

አፄ ምንሊክ የገነቡት የባቡር መስመር ምንም እንኳን ኢትዮጵያን ለማሳደግ አስተዋጽኦ ቢያደርግም፣ በስተመጨረሻ ተንገራግጮ የቆመው የአገሪቱ ፖለቲካል ኢኮኖሚ በተፈለገው መልኩ ወደ ካፒታሊስታዊ ሥርዓት መለወጥ ባለመቻሉ ነው፡፡ በመሆኑም ባቡር፣ ካፒታሊዝምና ተጓዳኝ ሕገ መንግሥታዊ መሻሻሎች አብረው መሄድ አለባቸው፡፡

ብዙ ጊዜ ወደ ቃሊቲ አካባቢ የተጓዘ ሰው አንድ የሚመለከተው ነገር አለ፡፡ ይኸውም ከባድ ተሸከርካሪ ያላቸው ባለሀብቶች የከባድ ተሸከርካሪውን ተሳቢ በዋናው መኪና ላይ በመጫን ወደ ጅቡቲ የሚደረግ ጉዞ አለ፡፡ ይህ የሚነግረን በእርግጠኛነት ከአገር ውስጥ በቂ ጭነት ወደ ውጭ አገር የሚላክ አለመኖሩን ነው፡፡

አሁን ደግሞ ባቡር ገንብተን ጨርሰናል፡፡ ባቡሩ ከ30 በላይ ታሳቢ ይዞ የሚጭነው ጭነት አጥቶ ወደ ጂቡቲ የሚጓዝ ከሆነ እንዴት ነው ዕዳውን የሚከፍለው? ጭነት ለማግኘት በዋናነት እኛ ኢትጵያውያን ጠንክረን መሥራት አለብን፡፡ ጠንክሮ ለመሥራት ደግሞ ለሥራ የሚመች ሕግና አስተዳደር መኖር አለበት፡፡

አብሮ ለመሥራት የሚያችል የአክሲዮን ማኅበራት አደረጃጀት የማይታሰብ በሆነበት አገር እንዴት አብሮ መሥራት ይቻላል? በጣም በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ንግድ ሚኒስቴር የሚባል መሥሪያ ቤት በቅርቡ ስለማውቀው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮ ለመሥራት የሚያደርገውን ጥረት ለመቆጣጠር የሚያስችል ቁመና እንደሌለው ነው፡፡ በግል ደግሞ የሚደረግ መፍጨርጨር ከአገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለኤክስፖርት የሚሆን ምርት ማምረት ከቶውንም የማይታሰብ ነው፡፡

 በዚህ ላይ በአገራችን በስፋት የተንሰራፋው የዘር ፖለቲካ ሌላኛው ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ ለመሥራት የማያስችል እንቅፋት ነው፡፡ ለዚህ ነው ከባቡሩ ጋር የሚሄድ መንግሥታዊ አወቃቀርና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ይኑረን የምለው፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ለልጆቻችን የምናወርሰው ባቡሩ ያወጣውን ቱሩፋት ሳይሆን የባቡሩን ዕዳ ይሆናል፡፡ ወይም ደግሞ ዓባይን ገድበን የኤሌክትሪክ ኃይል ሸጠን የምናገኘውን ገንዘብ ለባቡሩ ዕዳ እናውለዋለን ማለት ነው፡፡

በመሆኑም አገሪቱን የሚያስተዳድረው ኢሕአዴግ ወደቡን ጠበቅ አድርጎ በቂ ሥራዎች የሚሠራበት ወቅት አሁን ነው፡፡ ለአሥር ዓመታት በተከታታይ በሁለት አኃዝ ያደገ ኢኮኖሚ ባቡር ላይ የሚጫን ምርት እንዳለው የሚፈትሽበት ወቅት አሁን ነው፡፡ የሪፖርተር ዓምደኛ አቶ ጌታቸው አስፋው ደጋግመው እንደፈረጁት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በበሬ ከሚታረስና ከጆንያ ኢኮኖሚ ያልወጣ በመሆኑ፣ ይህ ዓይነት የኢኮኖሚ ሥርዓትና የባቡር ልማት አብረው መሄዳቸውን የምናይበት ወቅት አሁን ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

Standard (Image)

አንበሶቹ የታሉ?

$
0
0

በኦሜርታ ይበቃል

ዕለቱ ሰኞ ነው ጥር 22 ቀን 2009 ዓ.ም. 11፡30 አካባቢ ከሜክሲኮ አደባባይ ወረድ ብሎ እገኛለሁ፡፡ ወደ ጀሞ ኮንዶሚኒየም ለመጓዝ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት የሚጠባበቁ ሠልፈኞች መጨረሻ ላይ ቆሜያለሁ፡፡ ከፊቴ ያለውን ሠልፈኛ ሕዝበ አዳም ምን ዓይነት ተዓምር መጥቶ እንደሚያነሳውና እንደሚሳፈር አላውቅም፡፡ ደግነቱ ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ ሠልፉ ላይ ያሉ ቆነጃጅትን ማየትና ማድነቅ በመቆም ምክንያት የሚመጣን መሰልቸት ያስረሳል፣ ድካምን ይቀንሳል፡፡ ጀሞ ማለት የት እንደተወለዱ ባናውቅም የቆንጆዎች መሰብሰቢያ የሆነች አዲስ አበባ ውስጥ የምትገኝ አዲስ ውብ ከተማ ሆናለች፡፡ ጓደኛዬ የቤት ኪራይ እየተጨመረበትም ቢሆን ለምን ያን አካባቢ ለቆ መሄድ እንደማይፈልግ የተገለጸልኝ መሰለኝ፡፡ ውበትን ማየትና ማድነቅና ጥሩ ነገር መመልከት የማይወድ ማን አለ? የምጓዘው ጓደኛዬ መጥተህ ውሰድ ብሎ ቃል የገባልኝን መጽሐፍ ለመዋስ ነው፡፡ ደርሼ ለመመለስ ሳይመሽ ሦስት ሰዓት ሆኖ የተከራየሁት ቤት የአጥር በር ሳይቆለፍ ያለዚያ መዘዙ ብዙ ነው ውጭ ማደርም አለ፡፡

ከድካሙም፣ ከመሰልቸቱም፣ ውጭ ከማደሩም ለመውጣት መፍትሔ በቶሎ ትራንስፖርት አግኝቶ መንቀሳቀስ አሊያም ቀኝ ኋላ ዙር ብሎ ወደ ቤት መመለስ ነው፡፡ ይህን እያሰላሰልኩ ለመወሰን ተቸግሬ ቆሜ ሳለ ድንገት ከፊቴ የነበረው ሠልፍ በሚገርም ሁኔታ መቃለል ጀመረ፡፡ እንዴት ሊሆን ቻለ ብዬ ሳይ የተለያየ ቀለም ያላቸው በብዛት ነጭ የሆኑ ጎናቸው ላይ በተለያየ ስም የአገር አቋራጭ አውቶብሶች መሆናቸውን የሚገልጽ ስቲከር የለጠፉ አውቶብሶች ውስጥ በርካታ ሕዝብ እየገባ አውቶብሶቹ ይሄዳሉ፡፡ እኔም ተራዬ ደርሶ ገባሁ፡፡ ብዙ አገልግሎቶች ላይ እጥረትን የሚፈጥረው የፍላጎት መጨመር ብቻ ሳይሆን ያለውን ፍላጎት ተረድቶና ተንብዮ ለምላሽ ያለመጣር፣ በየትኛውም እጥረት ባለበት ዘርፍ ላይ ፍላጎት መኖሩንና እየጨመረ መሄዱን ለማወቅ ያለመፈለግ ነው፡፡ ችግሩን በተጨባጭ ቀምሰው ያለማወቅ ችግር የየዘርፉ ባለሥልጣናት መሠረታዊ እጥረት መሆኑን ድሮ ኢኮኖሚክስ ስማር ያገኘሁትን ዕውቀት አሟጥጬ በመጠቀም ለራሴ ትንታኔ ሰጠሁ፡፡ (ከተነሳብኝ እንዲህ ነኝ በአንድ ጊዜ ራሴን ከዕድር መሪነት አስተሳሰብ ወደ አገር መሪነት አስተሳሰብ ለማሸጋገር ሰከንድ የማይፈጅብኝ ለራሴ ነው ታዲያ) ይህንን የአውቶብስ ትራንስፖርት አገልግሎት ኅብረተሰቡ እንዲያገኝ ሐሳቡን ያመነጨና ተግባራዊ ያደረገ ብሎም እንደ ሌሎች አንዳንድ ሥራዎች ሳይቋረጡ ቀጣይነት እንዲኖራቸው ያደረገን ግለሰብ፣ ቢሮ እንዲያው በአጠቃላይ ችግር ፈቺ የሆነውን አካል ያበቀለች ማህፀን የተባረከች ትሁን አልኩኝ፡፡

አውቶብሱ ውስጥ ገብተን ቁጭ ካልን በኋላ መንግሥት የጀሞ ኮንዶሚኒየምን ገንብቶ ለነዋሪዎች ማስረከቡ ብቻ በቂ አለመሆኑን ተረድቶ በአንድ ወቅት ጎልቶ ይታይ ለነበረው የትራንስፖርት ችግር በዚህ መልኩ ጊዜያዊ መፍትሔ መስጠቱን በማድነቅ፣ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ እየሰማሁ ጉዟችንን ጀመርን፡፡

በዚህ መሀል የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የሚገኝበት ወደ አፍሪካ ኅብረት አካባቢ ስንደርስ የአዲስ አበባ ከተማን ከመንገድና ትራንስፖርት ጋር በተያያዘ ያሉ ሥራዎችን ለመሥራት የተቋቋመውን ቢሮ አቅጣጫ እየጠቆሙ ጨዋታ ተጀመረ፡፡ ቢሮው አዲስ አበባ ከመንገድና ከትራንስፖርት ጋር በተያያዘ ያሉባትን ችግሮች በተሻለ ሁኔታ ለመፍታት በአዲስ መልክ ብዙ ዘርፎችን በመያዝ የተዋቀረ መሆኑንና አዲስ ኃላፊዎች የተመደቡለት መሆኑን፣ እንዲሁም ቢሮው ከሚመራቸው ተቋማት መካከል አንዱ አንበሳ አውቶብስ መሆኑን አንድ እንዲሁ ሲያዩት ለቢሮው ያለው ዕውቀት ሰፋ ያለ የሚመስል ሰው መናገር ሲጀምር፣ ጨዋታው መልኩን ቀይሮ የከተማችን መለያ ምልክት ወደሆነው አንበሳ የከተማ አውቶብስ ድርጅት ዞረ፡፡

እኔም ይህንን ከልጅነት እስከ ዕውቀት የተጓጓዝኩበትንና አሁን አሁን ግን እሱን ቆሞ በመጠበቅ ጨጓራዬን ከማቃጥል ወይ ገንዘቤን ወይ እግሬን ባቃጥል ይሻላል ብዬ፣ ረዘም ያለውን መንገድ ተጨማሪ ገንዘብ በመክፈል በሌላ የትራንስፖርት አማራጭ እጠቀማለሁ፡፡ አጫጭሩን ደግሞ በእግሬ በመጓዝ ከአንበሳ ጋር ያለኝን የደንበኝነት ውል እሱ ሳያውቀው አፍርሼአለሁ፡፡ ይህንን እንደ አዲስ ሳስበው ልክ የልጅነት የከንፈር ወዳጅን እያስታወሱ የት ይሆን ያለችው/ያለው እየተባለ በሐሳብ እንደሚኬደው የረጅም ጊዜ ደንበኛዬ የነበረው አንበሳ አውቶብስ የት ምን ደረጃ ያለው የሚል ጥያቄ ስለጫረብኝ፣ ድርጅቱ አሁን ያለበትን ሁኔታ ላጣራና ያገኘሁትን መረጃም ጥሩም ሆነ መጥፎ ለእናንተ ለአንባቢዎቼ ላጋራ፡፡ ምናልባት ሚዛን የሚደፋና ውኃ የሚቋጥር ቁም ነገር ከተገኘበትም ለድርጅቱ ባለድርሻ አካላት (ከመንግሥት ጀምሮ እስከ ግለሰብ ድረስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የዚህ ድርጅት ባለድርሻ ያልሆነ ያለ አይመስለኝ) ወቅታዊ እውነታዎችን ለማድረስ እያሰብኩ ጉዞዬን ጨርሼ መውረጃዬ ደርሶ ወረድኩ፡፡

በ1935 ዓ.ም. የተቋቋመው አንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ይህንን መጠሪያ ስም ከማግኘቱ በፊት በተለያዩ ስሞች እየተጠራ ለ74 ዓመታት ያህል ተጉዞ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ሦስት መንግሥታትን እያፈራረቀ ያየ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ያለፈ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱን በሀብት ደረጃ እንለካው ብንል ካለፉት ሁለት መንግሥታት በጣም በጣም በተሻለ ሁኔታ በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶት የበርካታ አውቶብሶች ባለቤት የሆነበት፣ የዴፖዎች ግንባታ የሚከናወንበትና የመሳሰሉት በብዙ መቶ ሚሊዮኖች ምናልባትም ቢሊዮኖች በሚደርስ ወጪ የተለያዩ የለውጥ ሥራዎች ክንውን  የሚስተዋልበት ድርጅት ሆኗል፡፡ ይህን ያህል ሀብት ያለው ከ3,500 በላይ ሠራተኞችን ያቀፈ ድርጅት እንዴት ሆኖ ነው የተሻለ አገልግሎት መስጠት ላይ ለውጥ ማምጣ ያቃተው? ለምንድነው ቆሞ የቀረው (ምናልባትም ወደ ኋላ የተመለሰው)? የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡ ምክንያቱም እኔን ጨምሮ ብዙ ደንበኞች አንበሳን በአንደኛም በሁለተኛም በሦስተኛም ደረጃ ያለ አማራጭ አድርጎ ማሰብ ካቆምን ሰነበትን፡፡ የተሻለ አገልግሎት የሚሰጠውና የደንበኞች ዕርካታ የሚመጣው አንድ ድርጅት ባለው ሀብትና የሰው ኃይል ብዛት ቢሆን ኖሮ አንበሳን እንደ ስሙ አንበሳ ማድረግ በተቻለ ነበር፡፡ ነገር ግን አልሆነም፡፡ መንግሥት ብዙ ሀብት አፍስሶ አውቶብሶች ይገዛል፣ ድጎማ ይሰጣል፣ ሌላም ሌላም ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በእውነት ከሆነ ግን ደንበኞች እየረኩ ነው ለማለት የሚያስችል ሁኔታ የለም፡፡ እስቲ ለዛሬ ድርጅቱ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የሠሩና አሁንም እየሠሩ ካሉ አንዳንድ የድርጅቱን ገመና ከእኔና ከእናንተ በተሻለ ሁኔታ የማወቅ ዕድል ካላቸው ሠራተኞች ጋር ካደረኩት ጭውውት የሰማሁትን፣ ሠራተኞቹ እንደ ወላጅ እናትና አባት የሚያዩትን ድርጅት ለዚህ አበቃብን ብለው በሚያስቡት አመራርና በሠራተኛው መሀል ተቃርኖ ፈጥሮ ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃር ወደፊት እየተጓዝን ነው እየተባለ በማኔጅመንቱ ሲወራለት የነበረውን የኋልዮሽ ጉዞ እንዲከሰት ምክንያት ነው ብለው የሚያስቡትን እነሆ ልበላችሁ፡፡

እንደነዚህ ሠራተኞች አባባል ከሆነ አሁን ከተከሰተው ደካማ የሆነ አገልግሎት አሰጣጥ ዋና መንስዔ ወደኋላ መለስ ብለው በፊት የነበረው ማኔጅመንት የፈጠረው መርህን ሳይሆን ጓደኝነትን፣ ዝምንድናንና ቤተሰባዊ ቅርርብን መሠረት ያደረገ ግንኙነት ነው፡፡ በድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎችና በብዙኃኑ ሠራተኛ መካከል የተፈጠረው ልብ ለልብ ተገናኝቶ መሥራት ያለመቻል አንስቶ አሁን በቅርቡ እስከነበረው በአንድ ወገን ያለ እኔ ብቻ ነኝ የልማትና የለውጥ ኃይል፣ ብቸኛው አማራጭ እኔ ብቻ የምለው ነው ብሎ የግል ይሁን የመንግሥት ያልለየ (ወደኋላ ላይ የግለሰብ መሆኑ ተረጋግጧል ይላሉ) ፍላጎትን የመንግሥት ነው በሚል በኃይልና በአምባገነንነት ለመጫን መሞከርን፣ ሠራተኛው መሀል የሚገኙ አንዳንድ ሆድ አደሮችን ማን ከማን ቆመ? ምን አወራ? ምን አሰበ….የሚል መረጃ አቀባይ እንዲሆኑ በሠራተኛው ላይ የጎበዝ አለቃ አድርጎ በመሾም ሕጋዊ መብታቸውን የሚጠይቁ ሠራተኞችን ጠርቶ ማስፈራራት፣ እንዲሁም በግዴታ የዓመት ፈቃድ እንዲወጡ ማድረግ (ወደኋላ ላይ የተወሰደባቸው ዕርምጃ ትክክል አለመሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ያጡትን ክብርና ጥቅም ማስመለስ ባይቻልም) ነበር የሚልን እንደ ዋና ችግር ሲያነሱ. ሌሎች ችግሮችንም መልካሙ ጊዜ ብለው ከሚጠሩት ወቅት ጋር እያነፃፅሩ ያነሳሉ፡፡

እንደነዚህ ውስጥ አዋቂዎች አባባል የአዲስ አበባን የብዙኃን ትራንስፖርት ችግር ለመፍታት ወሳኝ ሚና ካላቸው ድርጅቶች መካከል አንበሳ አውቶብሶች አንዱ ሆኖ ሳለ ይህንን ችግር ለመረዳትም ሆነ ለመፍታት አቅምም ሆነ አቋም የሌላቸው፣ በሥራቸው ሳይሆን በአፋቸው በሚኖሩ፣ የወገባቸው ጎንበስ ቀና ለሥራ ሳይሆን ለአድርባይነት የሆነ የሥራ ኃላፊዎች መሞላትና በድርጅቱ የበላይ አመራር፣ በድርጅቱ የሥራ እንቅስቃሴ፣ በተለይም ሠራተኞች ላይ የሚደርሰው ሰብዓዊ ክብርና ሞራል የሚነካ፣ ዴሞክራሲያዊነትን ያልተላበሰ፣ አምባገነንነትና ጀብደኝነት የተሞላበት፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ቅሬታ እንዲሰማው የሚያደርግ፣ ያለንበትን ዘመን ግምት ውስጥ ያልከተተ ስድብ አዘል ንግግር (እዚህ ላይ ተሰደብን የሚሉትን ቃል በቃል ያነሳሉ ጸያፍ ነገሮችን መጻፍ አግባብ ስላልሆነ ትቼዋለሁ) የሰዎችን አለማወቅና አለመማር መሳቂያ መሳለቂያ ማድረግ፣ የተማረውንም እኔ በቀደድኩልህ ቦይ ካልፈሰስክ ያንተ ትምህርት ትምህርት አይደለም ዕውቀትህም መና ነው ብሎ ማመን ነው፡፡ በአጠቃላይ ከመንግሥት መርህና ከከተሜው ማኅበረሰብ ወግና ልማድ ውጪ በሆነ መንገድ የነገሮችን መነሻና መድረሻ ራስን ብቻ አድርጎ ማየትን መታገል አለመቻልና በዚያን ወቅት ለተሠሩ ስህተትና ትፋቶች ለድጋፍ ያወጡትን እጅ መልሰው ለተቃራኒው ሐሳብ ያለምንም ልዩነት ሲያመጡ ሲታይና ለምን ሲባሉ የእሳት እራት ላለመሆን ብለን ነው እንጂ፣ ያኔም አናምንበትም ነበር የሚል መልስ ሲሰጡ ያለው የሥራ አመራር ስብስብ በፍርኃት የተሸበበና እስከ አፍንጫው ድረስ በአድርባይነት የተሞላ ነው የሚያሰኝ ሁኔታ እንዳለው ይናገራሉ፡፡

አንድ መንግሥት ካለበት ግዴታዎች መካከል አንዱ የተለያዩ አገልግሎቶችን በነፃ ወይም በዝቅተኛ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ማቅረብ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አሁን አሁን  ደግሞ እንደ ፌዴራልም ሆነ ክልል መንግሥት እነዚህን አገልግሎቶች መንግሥት ለሕዝብ በሚያቀርቡበት ሰዓት ትልቅ ፈተና እየሆነ ያለው የመልካም አስተዳደር ዕጦት ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ከአገልግሎቶቹ እያገኘ ያለው እርካታ ሳይሆን ቅሬታ መሆኑ የመንግሥት ራስ ምታት እየሆነ ያለ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እነዚህን ችግሮች መፍታትና ኅብረተሰቡን ማርካት የሚቻለው የተለያ ማስተካከያዎች ሲያደርጉ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከእነዚህ ማስተካከያዎች አንዱ አገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ ያላቸውን የሰው ኃይል በትምህርትና ሥልጠና በመደገፍ ማብቃት፣ ለዚህ የሚሆን ምቹ ሁኔታ ከሌለና መፍትሔ ካልሆነ የመዋቅር ለውጥና ምደባ እንደ አዲስ በማከናወን ለተገቢው ቦታ ተገቢውን ሰው (The right person to the right place) መመደብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ከሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ ነው፡፡

ይህንን ታሳቢ በማድረግ አንበሳ አውቶብስ ያለበትን ግዙፍ ችግር ለመፍታት እንዲያስችለው የመዋቅር ጥናት በማድረግ ምደባ ማከናወኑ ይታያል፡፡ እነዚህ ሠራተኞች እንደሚያነሱት ከመዋቅርና ከምደባው ጋር በተያያዘ በአጠቃላይ ለውጥ ለድርጅቱ ዕድገት አስፈላጊና ተገቢ ሆኖ ሳለ አንዳንድ መሠረታዊ ችግሮች ግን ነበሩበት ብለው ያምናሉ፡፡ እንደ ምሳሌም ከሚያነሱት መካከል ተግባራዊ የተደረገው መዋቅር ድርጅቱ ውስጥ ያሉ ሠራተኞችንም ሆነ ገበያ ላይ ያለውን የሰው ኃይል የሥራ ልምድ፣ የትምህርት ዝግጅትና የደመወዝ መጠን ጥያቄና የድርጅቱ የመክፈል አቅምን ግምት ውስጥ ያልካተተ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ነባራዊ ሁኔታን ያልዳሰሰ የመዋቅር ጥናት ለቦርድ ሲቀርብ መፅደቁን እንጠራጠራለን፡፡ ምክንያቱም ቦርዱ መንግሥትን ወክሎ ተቋሙን የሚቆጣጠር አካል ነው፡፡ መንግሥት ማለት ደግሞ ሕዝብ ነው በማለት፡፡ በተጨማሪም አንድ ድርጅት ውስጥ ተግባራዊ ሊደረግ የታሰበ ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ ከተቻለና ሁኔታዎች የሚፈቅዱ ከሆነ ከመላው ሠራተኛ ጋር፣ ካልተቻለም ከሥራ ኃላፊዎች ጋር በጥልቀት መወያየትና የጋራ ማድረግ ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ከመዋቅሩና ከምደባው ጋር በተያያዘ በበቂ ሁኔታ ከሁለቱም አካላት ጋር ውይይት ሳይደረግበት አንድ ነገር ነገ ከነገ ወዲያ ሊያመጣ የሚችለውን ውጤት ጊዜ ወስደው አገናዝበው ለመወሰን ፋታ ሳይኖራቸው፣ አጨብጭበው ተቀብለዋል በሚል በውይይት ያልዳበረ የይድረስ ይድረስ ሐሳብን ይዞ ወደ ተግባር መገባቱ አሁን እየታዩ ላሉ መጠነ ሰፊ መዝረክረኮች አንዱ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም ይላሉ፡፡

ምንም ይሁን ምን መዋቅር መሠራቱና ምደባ መከናወኑ ከነችግሮቹ መልካም ሆኖ ሳለ፣ በተመደቡበት ቦታ ላይ ቅሬታ ያላቸው ሠራተኞችን ቅሬታ ለማየት የተቋቋመው ኮሚቴው ልክ ምደባውን እንዳከናወነው ኮሚቴ ከግለሰቦች ማለትም ተቋሙ አናት ላይ ያሉ የሥራ ኃላፊዎች ፍላጎት በሰፊው የተንፀባረቀበት ነው በማለት፣ እንደ አብነትም ግለሰቦች የመወዳደሪያ መስፈርቱን ቢያሟሉም ባያሟሉም እኔ አልፈልገውም ወይም እፈልገዋለሁ በሚል ደረጃ የሚሰጡበት ወይም የሚነፍጉበት ሁኔታ የተስተዋለበት ነበር ብለው አብነቶችን ያነሳሉ፡፡ እዚህ ላይ ከመስጠትና ከመንፈግ በተጨማሪ አሳፋሪ ነው ብለው የሚያነሱት ለመስጠትና ለመከልከል መሥፈርቱ መንግሥት ለዕድገት ጉዞዬ እንቅፋት ሆኖብኛል ብሎ ያስቀመጠው የወንዜ ልጅ ድንበርተኛዬ የሚል አስተሳሰብና ድርጊት መኖሩ ነው፡፡ የአንድ አካባቢ አስተሳሰብ ገኖ የወጣበት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ‹‹ስናገር ያላጨበጨበ ሲያነጥሰኝ መሐረብ ያላቀበለ›› የሚል ትርጉም ያለው፣ የሰዎችን ልምድና የትምህርት ዝግጅት ሳይሆን ግለሰባዊ ቅርርብን መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ በትምህርት ዝግጅት ይበልጡናል ብለው የሚያስቧቸው ግለሰቦችን ልምድ የለውም የሚል (እዚህ ላይ መንግሥት ከየዩኒቨርሲቲው የሚወጡ ወጣቶችን ለማበረታታት በዜሮ ዓመት የሥራ ልምድ ወደ ኃላፊነት እንዲመጡ የሚያግዝ ፖሊሲ የሚያራምድ መሆኑን ልብ ይላል እንኳን በሥራ ዓለም የቆዩትን)፣ ልምድ ያለውን ደግሞ የትምህርት ዝግጅት የለውም ወይም ከሥራ መደቡ ጋር አብሮ አይሄድም የሚል በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ ትክክል የሆነ ነገር ግን ለአንዱ የሚሠራ ለሌላው (ከላይ ለተጠቀሱት የወንዝ ልጆች) የማይሠራ ሁኔታ ነበር ብለው ያነሳሉ፡፡

በመቀጠል የሚያነሱትም በአዲሱ አመራር እየተሠራ ያለው የተፈጠሩትን ችግሮች የማስተካከል ዕርምጃ በጎ ሆኖ ሳለ ችግሩን የፈጠሩ፣ በአገሪቱ ሕግ ሳይሆን በራሳቸው የጀብደኝነትና ዝናን ፍለጋ ስሜት በመንቀሳቀስ (ዝና እንዴት እንደሚመጣ ያለማወቅ ትልቅ እርግማን ነው) የተደረገ ስህተትና ጥፋት ተጠያቂ ማን መሆን  አለበት የሚል ነው፡፡ እንደ አብነትም ዕድሜያቸው ለጡረታ ያልደረሰ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን (240 አካባቢ ናቸው ይላሉ) ጡረታ እንዲወጡ ሕግ ከሚፈቅደው ውጪ ማስገደድ (በኋላ በሕግ እንደማያስኬድ ታውቆ ማስተካከያ ተደርጎ የሚመለሱ በአዲሱ አመራር ተወስኗል)፣ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የትምህርት ዝግጅታቸው ለተወዳደሩበት ቦታ ብቁ የሚያርጋቸው ነገር ግን ቅሬታ አቅርበውም መፍትሔ ያላገኙ መኖራቸው፣ በግለሰቡ ደረጃ እሱን አልፈልገውም ወይም እፈልገዋለሁ በሚል የተደረገ ምደባ መሆኑ፣ ለአንድ ተቋም ዕድገትም ሆነ ውድቀት ከሠራተኛው ይልቅ አመራሩ ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑ እየታወቀ ለአንበሳ ሥራዎች መዳከም ሠራተኛው ብቻውን ተጠያቂ የሆነ ይመስል፣ ሁሉም ወሳኝ የሆነ የማኔጅመንት አካል ምንም ሳይነካካ ባለበት መቀጠሉ በማጥራት ሥራው ወቅት ሊታዩ መጠነ ሰፊ ችግሮች ባለቤቱ ሠራተኛ ብቻ ነበር ወይ? ለወደፊቱስ እነዚህን የሥራ ኃላፊዎች ይዞ ለውጥ ማምጣት ይታሰባል ወይ? የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ እዚህ ላይ ድርጅቱ ያሉት የሥራ መሪዎች የአዲስ አበባን የብዙኃን ትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የድርሻውን ሚና ለመወጣት የሚንቀሳቀስ ድርጅትን ለመምራት የሚያስችል አቅምና አቋም አላቸው ወይ የሚል ጥያቄን በሰፊው የሚያነሱ ብዙ ናቸው፡፡

እንዲያው በአጠቃላይ ሲታይ ድርጅቱ ውስጥ የነበረው ሁኔታ የሠራተኞች መብት የተጣሰበት፣ ግለሰቦች ያላግባብ ተጎጂ ወይም ተጠቃሚ የሆኑበት፣ የአንድ ሰው ከሕዝብና ከመንግሥት ፍላጎት ውጪ መንቀሳቀስና ፈላጭ ቆራጭ መሆን ገኖ የታየበት፣ የግለሰቡ መንግሥትን ከሚመራው ኢሕአዴግ መርህ ውጪ ራስን ከፓርቲ፣ ከመንግሥትና ከሕዝብ በላይ ነኝ የሚል አስተሳሰብ ገዝፎ የታየበት (ፓርቲው ካሁን በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ግለሰቡ ከሄዱበት ተቋም ተጠርተው እንዲመጡ በማድረግ ስህተትና ጥፋታቸውን አምነው እንዲቀበሉ አድርጓል፣ ይህም ገዚው ፓርቲ ይዘገያል እንጂ አይቀርም የሚለውን በወቅቱ የማስተካከያ ዕርምጃ ያለመውሰድ ሐሜት ያጠናክራሉ) ሠራተኛው እስከሚበቃው ስድብ የጠጣበት፣ ለሠራተኛው መብት ለመታገል የሞከሩ ሠራተኞች ቃል በቃል ካላረፍክ ምላስህን ነው የምቆርጠው ተብለው ታሪክን አስታውሰው ያዘኑበት ነበር እያሉ እነዚሁ ሠራተኞች ያወሳሉ፡፡ መንግሥት የነበረውን ሁኔታ በቅጡ መረዳቱን እንጠራጠራለን፣ ምክንያቱም እነዚህን የሥራ ኃላፊዎች በማረም ፈንታ ድፍን አዲስ አበባን እየዞሩ የስድብ ፀበል እንዲረጩ ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት ማዛወር ለከተማው ሕዝብ አለማሰብ ነው የሚል አስተያየት ያቀርባሉ፡፡

ሌላው እነዚህ ሠራተኞች የሚያነሱት ደግሞ እንደ አንበሳ ያሉ ብዙ ሠራተኛና ሀብትን የሚያስተዳድሩ ድርጅቶችን ለመምራት የሚያስፈልገው የካበተ ስድብና ዘለፋ ሳይሆን የሥራ ልምድ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህንንም መንግሥት የሚያጣው አይመስለንም፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱና ሌሎች የአገሪቱ ሕጎች ላይ ያሉ የዜጎች መብትና ሰብዓዊ ክብሮች በአንዳንድ ሕዝብ ከመንግሥትና ሹመኞቹ ምን እንደሚፈልግ ያልተገለጸላቸው ወይም በእምነት ያልተቀበሉ መሪዎች ሲጣሱ መዘዙ ብዙ እንደሚሆን ነው፡፡ በቀላሉ ሊፈቱ የማይችሉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ በተለይም ደግሞ ፖለቲካዊ ቀውሶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ገምቶ መንቀሳቀስ ያሻል፡፡ መንግሥት በአሁን ጊዜ ለኅብረተሰቡ የሚሰጣቸውን የተለያዩ አገልግሎቶች ለማሻሻልና መልካም አስተዳደርን ማስፈን ያስችለው ዘንድ መድረኮችን እየፈጠረ ከተለያዩ የኅብረተሰብ አካላት ጋር በመወያየት በጥልቀት መታደስን እውን ለማድረግ እየታተረ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ የኅብረተሰብ አካላት ደግሞ አንዱ የአንበሳ አውቶብስ ሠራተኞች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ሠራተኞቹ እንደሚያነሱት ከሆነ በጥልቀት የመታደስ ውይይቱ እየተከናወነ ሳይቀር እዚያው መድረክ ላይ ሌላ ጥልቅ ተሃድሶ የሚያስፈልገው ድርጊት መፈጸም (ተሰደብን የሚሉትን ይጠቅሳሉ)፣ ከተሃድሶው ጋር በተያያዘ የመንግሥትን ፍላጎት አለማወቅ አሊያም በእምነት ያለመቀበል ውጤት ነው ይላሉ፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም ሆኑ የተለያዩ ተቋማት አንዱ ለአንዱ ያለውን ምርጥ ተሞክሮ ለማጋራት የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ አንበሳ አውቶብስም ሌሎች ተቋማት ያላቸውን ምርጥ ተሞክሮ በመውሰድና ያለውን በመስጠት መሥራት ይገባዋል፡፡፡ እነዚህ ውስጡን በደንብ እናውቀዋለን የሚሉ ሠራተኞች እንደሚሉት መዋቅርና ምደባ በአግባቡ ካልተሠራና የሠራተኛውን የሥራ ሞራል የሚጎዱና ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ አላስፈላጊ ንግግሮች ከታከሉበት፣ እንዲሁም እውነት ሳይሆን ቅዠት የሚመስሉ፣ አሁን ባለንበት ደረጃ መሬት እውን ለማድረግ የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የማይፈቅድላቸው፣ በመማር ወይም ማስተማር ሒደት ውስጥ የሚገኙ ቲዎሪዎችን የተቋሙን አቅም፣ ወቅትንና አገራዊ ሁኔታን ሳያገናዝቡ ተግባራዊ አደርጋለሁ ብሎ መነሳት በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ ለለውጥ መነሳሳትን የሚያሳይ ሊመስል ይችላል፡፡ የአንዱን ተግባር ውጤት ሳይመዝኑና ለስኬቱም ሆነ ለውድቀቱ ባለቤት ሳይሰጡ ወደ ሌላው መዝለል (ፓይለት ፕሮጀክት ተብሎ የወጣውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብና የባከነውን ጊዜ ከተገኘው ውጤት ምንም መሆን ጋር አያይዘው ያነሳሉ) በመንግሥት ሀብት መቀለድና የግብር ከፋዩን ኅብረተሰብ ገንዘብ ማባከን መሆኑን ያምናሉ፡፡ እንዲያው በአጠቃላይ ድርጅት እንዴት እንደሚመራ ሳይሆን እንደማይመራ፣ አላስፈላጊ ቃላትና ድርጊቶች አስፈላጊ የሆነ ልምድ ያለውን ሠራተኛ ፍልሰት እንደሚያስከትሉ (ይህንን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ልምድ ያላቸው ሠራተኞች በተለይም ወጣቶች ድርጅቱን እየለቀቁ ይገኛሉ)፣ ያለውንም ሠራተኛ የሥራ ሞራል እንደሚገድሉና በዚህም ድርጅቱን ምን ያህል ዋጋ እንደሚከፍል ለማወቅና ከመሰል ድርጊት ለመቆጠብ እንዲቻል፣ ሌሎች ተቋማት እየመጡ የተሞክሮ ልውውጥ ሊያደርጉ ይገባል ይላሉ፡፡

እዚህ ላይ የእውነት መልካም ተሞክሮ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ችግሩን ፈጥረዋል የተባሉት የሥራ ኃላፊ ካሉበት መጥተው ማብራሪያ እንዲሰጡ መደረጉ፣ አሁን ለተፈጠረው ውጥንቅጡ የወጣ ሁኔታ የድርሻቸውን ስህተትና ትሩፋት አምነው እንዲቀበሉ መደረጉ ጥሩ ሆኖ ሳለ፣ ተግባሩ የበለጠ ቅብልነት ያለው ሙሉ እንዲሆን የጠፋው ጥፋት መጠን ተለክቶ ተጠያቂ መሆን ያለበት አካል በሙሉ ተጠያቂ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ ያለዚያ ሰዎች እንዳፈተታቸው በሠራተኛው፣ በሕዝብና በመንግሥት ሥራዎችና ሀብት ላይ እየተጫወቱና ሕዝብን በመልካም አስተዳደር ዕጦት እያንገላቱ ‹‹አዎ አጥፍቻለሁ›› እያሉ (ሊያውም ከብዙ መወራጨት በኋላ) ምንም ሳይሆኑ የሚቀጥሉ ከሆነ፣ ራሳቸውም ሆኑ ሌሎች ከመሰል ድርጊት በተለይ ቆመንለታል የሚሉት ድርጅት መርጦ ወደ ሥልጣን ያወጣውን ሕዝብ ከመናቅና ከመስደብ ይቆጠራል፡፡ ራስን ከሕዝብ፣ ከፓርቲና ከሕግ በላይ አድርጎ ከማሰብና በተግባር ከመቀስቀስ፣ በመንግሥት ሥልጣን ውስጥ ያለ ኢመደበኛ ግንኙነትን እንደ መደበቂያ ከመውሰድ፣ እንዲሁም ድርጅቶችን ከማተራመስ ወደኋላ ስለማይሉና ይህ ደግሞ ሕዝብና መንግሥትን ያራርቃል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ለከተማው ሕዝብ አስተዳዳሪነት የከተማውን ሕዝብ ባህልና ባህሪ የሚያውቁ፣ ሕዝብን ማክበር ባህላቸው ያደረጉ፣ በመልካም ሥነ ምግባር የታነፁ አመራሮችን እንጂ፣ እንዲህ ዓይነት መሪዎችን መመደብ በሕዝብ፣ በሠራተኛው መብትና ክብር ረገጣ ላይ ድርሻ ያላቸው የሥራ ኃላፊዎችን በሕግ ወይም በሌላ ማናቸውም መንገድ ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ጉዳዩ ለተፈጸመበት ቦታ ብቻ ሳይሆን እንደ አገርም ለመንግሥት ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ (የጥልቅ ተሃድሶው ዓላማም ይኼው ነው) አለው እያሉ ያነሳሉ፡፡

ከላይ እንደተባለው መልካም አስተዳደርን ለማስፈን አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ተጠያቂነት (Accountability) ማስፈን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ አሁን ባለው አሠራር የመንግሥት ተቋማት የሳምንቱ፣ የወሩ፣….ምርጥ ፈጻሚ እያሉ ዕውቅና እንደሚሰጡ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ መጀመር ያለበት አሠራር ቢኖር የሳምንቱ፣ የወሩ፣ የድርጅቱ፣ የመሥሪያ ቤቱ….ምርጥ አጥፊ በሚል ዕውቅና በመስጠት ተጠያቂነትን መፍጠር ቢጀመር ጥሩ ይመስላል፡፡ መንግሥት አንበሳ አውቶብስ ውስጥ ለተፈጠሩ ችግሮች በተለይም ሕገ መንግሥታዊ ለሆነው የዜጎች ሰብዓዊ ክብር መጣስ ባለቤት ሊፈጥርና ትክክል ሆኖ ከተገኘም ተጠያቂ ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ ሠራተኛውም በመንግሥትና በመንግሥት ሹመኞች መካከል ያለውን አንድነትና ልዩነት ለይቶ በማወቅ ሥራውን በአግባቡ መሥራትና የድርጅቱን ህልውና ማስቀጠል፣ ድርጅቱን እየለቀቁ ያሉ ወጣት ባለሙያዎችም ሁኔታዎች እንደሚለወጡ ተረድተው ጊዜ ወስደው ማየት እንጂ፣ እውነታው ሰዎች እንደሚሉት አለመሆኑን ተረድተው (መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አንድ ሰውና አንድ ጠመንጃ እስኪቀር ድረስ…እንዳለው ሰላሳ አውቶብስና ሰላሳ ሰው እስኪቀር ድረስ ማንም ሰው መልቀቅ ይችላል ተብለናል፣ ስለዚህ የእኛ መኖር ለድርጅቱ የሚጨምረው፣ መልቀቃችን የሚያጎድለው ነገር የለም የሚል ስሜት የተሚላበት ንግግር የሚናገሩ አሉ) መጠበቅ ይገባቸዋል የሚሉ የነገሮችን አዎንታዊ ጎን ማየት የሚቀናቸው አንዳንድ ሠራተኞች አሉ፡፡

በተጨማሪም በድርጅቱ ላይ የደረሰው ድንገተኛ የእሳት አደጋ፣ የብዙ አውቶብሶች በብልሽት ምክንያት ከአገልግሎት ውጪ መሆን፣ እንዲሁም በሌሎች ምክንያት የተፈጠረው ችግር ተሻግሮ የድርጅቱን ህልውናና የሠራተኛውን የሥራ ዋስትና ማስቀጠል የሚቻለው ሠራተኛው ትናንት የተፈጠሩ ስህተቶችና ጥፋቶችን መንግሥት እልባት እንደሚያበጅላቸው ማመን ይገባል፡፡ ያሉትን ችግሮች ወደ ጎን አድርጎ ከቁዘማና ከኩርፊያ ወጥቶ ሥራውን መሥራት፣ መንግሥትም ሕዝብን እንዲያስተዳድሩ የሚመድባቸው ሹመኞች ሕዝባዊነት የተላበሱ ናቸው ወይስ ሕዝበኝነት የተጠናወታቸው የሚለውን አይቶ የማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድና በመንግሥትና በሕዝብ መሀል የሚፈጥሩትን መቃቃር ለማስወገድ ኃላፊነቱን ራሳቸው መውሰድና ተጠያቂነት እንዲኖርባቸው ማድረግ አለበት፡፡ በዋናነት ጠቀሜታው ለመንግሥት መሆኑን ተረድቶ መሥራት ይገባዋል፡፡ እስከዚያው ግን እንደኔ ደንበኛ የነበራችሁና ልክ እንደ ዱሩ አንበሶች የከተማውም አንበሶች መመናመን አስጨንቋችሁ አንበሶቹ የት አሉ? የሚል ጥያቄ ላነሳችሁ መልሱ አንበሶቹ በአሠሪና በሠራተኞቻቸው ተግባብቶ መሥራት ያለመቻል ምክንያት በገጠማቸው በሙሉ አቅም መሥራት ያለመቻልና አድርባይነት ችግር ተተብትበው፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ በአዲስ አበባ አስፋልቶች ላይ እያገሱ ከመንጎማለል ይልቅ በዋሉበት ቅጥር ግቢ ቆመው ለማደር ተገደው የኋልዮሽ ጉዞዋቸውን አጠናክረው ተያይዘውታል ነው መልሱ፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡

ከአዘጋጁ፡ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

Standard (Image)

ሊቢያ የሰው ልጆች የምድር ገሃነም

$
0
0

በዳዊት ከበደ አርአያ

ሰሜን አፍሪካዊቷ ሊቢያ የሙአመር ጋዳፊ ሥርዓት እ.ኤ.አ በ2011 መውደቁን ተከትሎ፣ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት በማጣቷ ቅጥ ወደ አጣ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ገብታለች፡፡ ይህ እንደ መልካም አጋጣሚ ሆኖ የተፈጠረላቸው በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ድርጊት የተሰማሩት ቡድኖች ደግሞ፣ ብዙዎችን እያሰቃዩ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያፈሱባት ነው፡፡ ይህች በሜድትራንያን ባህር ጫፍ የምትገኝ አገር ወደ አውሮፓ በተለይም ወደ ጣሊያን በሕገወጥ መንገድ ለመሻገር የሚፈልጉ ስደተኞች ተመራጭ ያደርጓታል፡፡ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችም በዚህች ማዕከላዊ መንግሥት በሌላት አገር ከምሥራቅና ከምዕራብ አፍሪካ የሚሄዱ ስደተኞችን እየተቀበሉ፣ የሰው ልጅ በገዛ አምሳያው ፍጡር ሊፈጽመው የማይገባ አስነዋሪ የጭካኔ ተግባር ይፈጽሙባቸዋል፡፡

በቅርቡ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ባወጣው ሪፖርት፣ በዓለም ላይ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ከሚታወቁት አካባቢዎች በስደተኞች ላይ ከሚፈጸሙ ኢሰብዓዊ ተግባራት 80 በመቶ፣ ከሱዳን እስከ ሊቢያ ባለው የሰሀራ ምድረ በዳ እንደሚፈጸም ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነ ስደተኞች ወዳሰቡበት ሳይደርሱ በሰሀራ ምድረ በዳና ከሊቢያ ወደ አውሮፓ ለመሻገር በሜዲትራንያን ባህር በሚደረግ ጉዞ እንደሚሞቱ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ እ.ኤ.አ 2017 ዓ.ም ከገባ በኋላ ባሉት 53 ቀናት ብቻ 366 ስደተኞች ባህር ውስጥ እንደሞቱ፣ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎችም ከምንጊዜውም በከፋ ሁኔታ ከፕላስቲክና ከእንጨት በተሠሩ ትንንሽ ጀልባዎች ከአቅም በላይ በመጫን በግድ የለሽነት ወደ ባህር እንደሚወረውሩዋቸው የድርጅቱ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

የዛሬ ሁለት ሳምንት 120 ስደተኞችን ጭና ከሊቢያ የተነሳች አነስተኛ የፕላስቲክ ጀልባ በሜድትራንያን ባህር ሰጥማ ተሳፍረውባት የነበሩት ስደተኞች በሙሉ አልቀዋል፡፡ በወቅቱ የ87 ስደተኞች ሬሳ በሊቢያ የባህር ዳርቻ ተንሳፎ የተገኘ ሲሆን፣ የቀሪዎቹ አስከሬን እስከ አሁን ሊገኝ አለመቻሉን የተለያዩ የዓለማችን ትልልቅ መገናኛ ብዙኃን ዘግበውታል፡፡

የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጓቾችና መገናኛ ብዙኃን እንደሚገልጹት ከሆነ፣ እነዚህ ሕገወጥ ቡድኖች በዚያች አገር በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ያለምግብ፣ መፀዳጃና በቂ አየር እንኳን በማያገኙበት መጋዝን አሽገው ቁም ስቅላቸውን ያሳዩዋቸዋል፡፡ በሊቢያ የሚገኙ ስደተኞች አያያዝን በተመለከተ ለመዘገብ ወደ ሥፍራው የተጓዘ ቫይስ ኒውስ የተባለ የሚድያ ተቋም ጋዜጠኛ፣ ‹‹በሕይወቴ ከአየሁዋቸው እጅግ በጣም አስፈሪና አደገኛ ሥፍራ፣ መሬቱ፣ አየሩና ንፋሱ ሁሉ ሞት ሞት ይሸታል፤፡፡›› በማለት ገልጾታል፡፡ ‹‹በአካባቢው በምጓዝበት ወቅት በየሥፍራው የተጣሉ ሻንጣዎች፣ ጫማዎች፣ የሕፃናትና የጎልማሶች አልባሳት፣ እንዲሁም ሥጋቸው አልቆ አጥንት ብቻ የቀሩ አስከሬኖች ማየት ሌላው አስፈሪ ትዕይንት ነው፤›› በማለትም ምስክርነቱ ሰጥቷል፡፡ ‹‹ከሁሉም በላይ እስካሁን ድረስ ከአዕምሮዬ ያልጠፋው በሰሀራ በረሃ ያየሁት የሁለት ሕፃናትና የአንዲት እናት አጥንት ብቻ የቀረው አስከሬን ነው፡፡ ይህች እናት በዚያ አደገኛ በረሃ ሁለት ልጆቿን ይዛ ስትጓዝ ነው ረዳት አጥታ ሁለት ልጆቿን እንደታቀፈች ወድቃ የቀረችው፡፡ በጣም ዘግናኝ ነው፤›› ሲል ይናገራል፡፡

‹‹ከሱዳን እስከ ሰሀራ ምድረ በዳና እስከ ሊቢያ ሜድትራንያን ባህር ጠረፍ የተበተኑት ሕገወጥ አዘዋዋሪዎችና ደላሎች ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ርህራሔ ያልፈጠረባቸው የሰው ደም የጠማቸው፣ በሰው ልጅ ስቃይና ፍዳ እርካታ የሚሰማቸው የተለዩ ፍጡራን ናቸው፤›› ካለ በኋላ፣ ‹‹የሰው ልጅ በአካሉ ብቻ ሰው የሚባል ካልሆነ በስተቀር በመንፈሳቸውና በኅሊናቸው ግን 'መልዓከ ሞት'ናቸው ብል ይሻለኛል፤›› ሲልም ይገልጻል ጋዜጠኛው፡፡

ወደ እንደዚህ ዓይነቱ የመቅሰፍት ምድር ነው እንግዲህ ብዙዎች የአፍሪካ ወጣቶች ወደ አውሮፓ ለመሻገር በየቀኑ ሳይሆን በየሰዓቱ የሚጓዙት፡፡ ብዙዎቹ ግን ያሰቡትን ሳያገኙ አስፈሪው በረሃ በልቷቸዋል፡፡

ዓምደ ማርያም በርሃ ይባላል የ34 ዓመት ጎልማሳ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሊቢያ እስር ቤት ውስጥ ከአንድ ወር በላይ ግፍና መከራው አሰቃይቶት የ60 ዓመት አዛውንት መስሏል፡፡ እሱ እንደሚለው ከሆነ ከሱዳን ካርቱም ውስጥ በሾፌርነት ተቀጥሮ በሚሠራበት ወቅት አንድ ሱዳናዊ ጓደኛው ሊቢያ ቢሄድ በቀላሉ ወደ አውሮፓ እንደሚሻገርና የተሻለ ገቢ እንደሚያገኝ ከነገረው በኋላ፣ ከሕገወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች ጋር ያገናኘዋል፡፡ ከዚህ በፊት ያጠራቀመውንና ከቤተሰቡ ተበድሮ አምስት ሺሕ ዶላር ከከፈላቸው ጣሊያን እንደሚያደርሱት ተናግረው ጉዞ ወደ ሊቢያ ይጀምራል፡፡ ሊቢያ እስኪደርስ በሰሀራ በረሃ ያጋጠመው የስቃይና የሞት ትዕይንት ግን ከሚገልጸው በላይ ነው፡፡ ሲያስታውሰው ያንቀጠቅጠዋል፡፡

‹‹በምድረ በዳው ሽፍቶች ወይም ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ብቻ አይደለም የሚሰቃዩህ፡፡ የመንግሥት ድንበር ጠባቂ ወታደሮችና ፖሊሶችም ጭምር ናቸው፤›› የሚለው ዓምደ ማርያም፣ ‹‹ይህን ሁሉ ስቃይና መከራ ከማየት መሞት ብትፈልግ እንኳን እነሱ የተለያዩ እገዛ አድርገው ከሞት አፋፍ አውጥተው ዳግም ያሰቃዩሃል፤›› ብሏል፡፡ ‹‹በሰው ልጅ ስቃይ ደስታና እርካታ የሚሰማው ፍጡር ይኖራል ብዬ አስቤ አላውቅም፤›› የሚለው ዓምደ ማርያም፣ ‹‹ሚስት ባሏ እግሩና እጆቹ ታስሮ ዓይኑ እያየ ለሁለትና ለሦስት እየተፈራረቁ ሲደፍሯት፣ እርጉዝ ሴት አምጣ አሸዋ ላይ ደሟ ሲፈስና ስትወልድ እያዩ ምንም ዓይነት ርህራሔ አይሰማቸውም፤›› ብሏል፡፡

በቅርቡ የወጣ አንድ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከሆነ፣ ሴቶች እርጉዝ ሆነው ከቤታቸው እንደማይሰደዱ ነው፡፡ እነዚህ ሴቶች በየቦታው ከሚደፍሩዋቸው ሽፍቶችና ደላሎች ነው የሚያረግዙት፡፡ ለዚህም ነው እነዚህ ደላሎች የ13 ዓመት ሕፃናት ሴቶችን ሳይቀር ገና ከአገራቸው ከመውጣታቸው በፊት በጉዞው እንደሚደፈሩ ስለሚያውቁ፣ የእርግዝና መከላከያ እንደሚሰጥዋቸው የተረጋገጠው፡፡

በቅርቡ በዚህ በርሃ አልፈው በጣሊያንዋ ላምፔዱዛ ደሴት የደረሱት በዚሁ የዕድሜ ክልል የሚገኙት ሕፃናት ሴቶች ላይ በተደረገው የማህፀን ምርመራ እንደተረጋገጠው፣ በጨቅላ ዕድሜያቸው የእርግዝና መከላከያ መድኃኒት እንደተሰጣቸው ነው፡፡ በደሴቷ ከረድኤት ድርጅቶች ጋር የሚሠሩት ዶ/ር ሔለን ሮድሪጌዝ፣ በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች የእርግዝና መከላከያ መስጠት በጣም አደገኛና ያለ ዕድሜቸው የወር አበባቸው እንዲቆምና ልጅ መውለድ እንዳይችሉ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር ሔለን ምርመራ ካደረጉላቸው ሴቶች አምስቱ ለዚህ ችግር እንደተጋለጡና ያለዕድሜያቸው የመውለድ ተፈጥራዊ ፀጋቸው እንደተነጠቁ አረጋግጠዋል፡፡

ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በሕገወጥ መንገድ በደላሎች ውሸትና የማይጨበጥ ተስፋ ተታለው ከአገራቸው የሚሰደዱ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ በጉዟቸው ውስጥ የሚያጋጥማቸውን ፈተናና ስቃይ በዚህ ጽሑፍ ለመግለጽ ይከብዳል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ይህን ሁሉ የሰሀራ በረሃ አደገኛ ጉዞ ጨርሰው በዕድል ተርፈው ሊቢያ ሲደርሱ የሚያጋጥማቸው ደግሞ ከድጡ ወደ ማጡ ነው፡፡ ሌሎች ሰው በላ አውሬዎች ይቀበሉዋቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ስደተኞች ሙቀቱ እስከ 50 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በሚደርስ ምድረ በዳ ከቆርቆሮ በተሠሩ እስር ቤቶች ታጉረው የድረሱልን ጥሪ ያሰማሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ሥጋቸው አልቆ አጥንታቸው ይቆጠራል፡፡ የቁም አስከሬን መስለዋል፡፡ ገሚሶቹ በተኙበት የሞት ጣር ያሰማሉ፡፡ ያረገዙ ሴቶች ያለ ረዳት ወለል ላይ በተነጠፈ ሰሌን ወድቀው ያለቀናቸው በምጥ ይሰቃያሉ፡፡ አንድ ከጋምቢያ የመጣ ስደተኛ መፀዳጃ ቤት እንደማያውቁ፣ ሽንታቸውንና ዓይነ ምድራቸውን በተኙበት እንደሚያመልጣቸው ሲናገር ለማመን ይከብዳል፡፡ ‹‹የምድር ገሃነም ውስጥ ነው ያለነው፤›› ሲል ለጋዜጠኛው መልሶለታል፡፡ ለዚህ ነው የጽሑፌን ርዕስ ከዚህ ስደተኛ አባባል የተዋስኩት፡፡ ጋዜጠኛው ይቀጥላል፡፡

…… እስር ቤቱ ውስጥ ሕፃናት አቅፈው ፍዝዝ ብለው እንባቸውን እንደ ዝናብ የሚያፈሱ ኢትዮጵውያን ሴቶች በማውቀው የአገሬ ቋንቋ በአማርኛ፣ ‹‹እባካችሁ ከዚህ ጉድ አውጡን፤›› ስትል ትማፀናለች፡፡ ሰውነቴ ራደ፡፡ እኔም እምባዬን ቪዲዮው ውስጥ ከማያት የአገሬ ልጅ ጋር ለቀቅኩት፡፡ ምንም እንኳን አቅም ኖሮኝ ደርሼ ካለችበት የመከራና የስቃይ ሕይወት ባላወጣትም ብዕሬን ላንሳና ልናገርላት፣ እሷን ማዳን ባልችልም ምንም ዓይነት ዕውቀትና ግንዛቤው ሳይኖራቸው በደላሎችና በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ተታለው ለመጓዝ እየተደራደሩ ያሉትን የአገሬ ልጆች ስለጉዞው አደገኛነትና ዘግናኝነት ለመግለጽ እየሞከርኩኝ ነው፡፡ አዎ እየሞከርኩኝ ነው ብል ይሻላል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያሉበት ዘግናኝ ሕይወት በጽሑፍና በቃላት ለመግለጽ ይከብዳል፡፡ የቱን ጽፈን የቱን እንደምተው ግራ ያጋባል፡፡

እዚህ ላይ ግን አንድ ሳልገጸው ማለፍ የማልፈልገው ጉዳይ የአገራችን ሚዲያዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ሥራ አለመሥራታቸው ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የትኛውም በዓለማችን ያሉ ግዙፍ የሚዲያ ተቋማት ከቴሌቪዥን ጣቢያዎቻቸው እስከ ድረ ገጻቸው በዚህ ጉዳይ ይዘግባሉ፣ መረጃ ያሠራጫሉ፡፡ ወደ አገራችን ስንመጣ ግን ሚዲያዎች ለአውሮፓ የእግር ኳስ የሚሰጡትን የአየር ሰዓት እንኳን ለዚህ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን እያጠፋ ያለውን ሕገወጥ ስደትን አንድ አሥረኛው ጊዜ ሊሰጡት አለመፈለጋቸው ያሳዝናል፡፡ በእውነት አገራችን ውስጥ የሚዲያ የአየር ሰዓት በማይጠቅምና ምንም ዓይነት አገራዊ ፋይዳ በሌለው ጉዳይ ላይ ኅብረተሰቡን ማደንቆሩ በጣም ያሳዝናል፡፡

አገራችን ውስጥ የሚዲያ የአየር ሰዓት መጫወቻ ሆኗል ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ እባካችሁ ሚዲያው፣ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ቢያንስ በችግር ውስጥ ያሉትን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ማዳን እንኳን ባንችል፣ አሁንም ብዙ ወገኖቻችን በማይጨበጥ ባዶ ተስፋ እየተታለሉ ገንዘባቸውን አፍስሰው ሕይወታቸውን ለዚህ አደገኛ ጉዞ ለመገበር እየተንደረደሩ ነው፡፡ እውነታውን እንዲውቁትና የጉዞውን አደገኛነት እንዲገነዘቡት በማድረግ ረገድ በተለይ ሚዲያው ትልቅ ኃላፊነት ይጠበቅበታል ………… ቸር እንሰንብት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው kebededawit2016@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡      

 

 

Standard (Image)

ድህነትና የአየር ብክለት ሲዛመዱ መዘዛቸው የከፋ ነው

$
0
0

በአሳምነው ጎርፉ

ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በየሩብ ዓመቱ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያሳትመው ‹‹ፋይናንስና ልማት›› የሚባል የምርምር መጽሔት አለው፡፡ ይኼ መጽሔት ከወራት በፊት ኒኮላስ ስተርን በተባለው ዓምደኛው “The Low Carbon Road” በሚል ርዕስ ጠንካራ ትንታኔ አቅርቧል፡፡ በዚህ የመጪው ዓለም በተለይም የሦስተኛው ዓለም ተግዳሮት ላይ ያተኮረ ጽሑፍ ድህነትና የአየር ብክለት የከፋ መዘዞች እንደሆኑ አስቀምጧል፡፡ መንግሥታትና ሕዝቦች በትኩረት ሊያስቡበት ስለሚገባው ጉዳይም በአፅንኦት ጠቁሟል፡፡

እንደ ኒኮላስ ትንታኔ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የዓለም አገሮች ለዓመታት በትኩረት የሠሩባቸው የምዕተ ዓመታት ግቦች ተግባራት ተጠናቀዋል፡፡ በኋላም የዘላቂ ልማት ግቦች እ.ኤ.አ. በመስከረም 2015 ፀድቀው በፍጥነት እንዲተገበሩ አቅጣጫ ወርዷል፡፡ በዚህም በተለይ ታዳጊ አገሮች ለመሠረተ ልማት መስፋፋት፣ ከብክለት ለፀዱ የኃይል አማራጮችና ማዕድናትን የማበልፀግ ሥራዎች፣ እንዲሁም ለኢንዱስትሪ መስፋፋትና ለከተሞች ማደግ መስጠት ያለባቸው ትኩረት ጎልቶ ተመልክቷል፡፡ ከዚህ አንፃር የእኛም አገር የጀማመረቻቸው ሥራዎች እንዳሉ የተሰወረ አይደለም፡፡

በእንግሊዛዊው ኢኮኖሚስት ትንታኔ መሠረት ዓለማችን በቀጣዮቹ 13 ዓመታት (እ.ኤ.አ እስከ 2030) ለመሠረተ ልማት ግንባታ ማስፋፊያና መልሶ ማደስ ብቻ 90 ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ያስፈልጋታል፡፡ ይኼ ብቻ ሳይሆን አሁን በዓለም ከተሞች የሚኖረው 3.5 ቢሊዮን ሕዝብ እ.ኤ.አ. በ2050 እስከ 6.5 ቢሊዮን እንደሚደርስ ተገምቷል፡፡ ይኼ አኃዝ ይበልጥ የሚጨምረው ደግሞ በታዳጊ አገሮች መሆኑ ታምኖበታል፡፡  

በዚህ ፈጣን የመሠረተ ልማት ግንባታና የከተሞች ዕድገት ታዲያ በጥንቃቄና በዕቅድ ካልተመራ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት ውድመትና የአየር ንብረት ብክለት እንዲከሰት በር እንዳይከፍት ተሠግቷል፡፡ የሚከናወኑ ልማቶች ፍትሐዊነትን ተላብሰው፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መንገድ መከናወን ካልቻሉም ጠቅላይ ባለሀብቶች (ሞኖፖሊስቶችን) በማብዛት ድህነት መስፋፋቱ አይቀርም፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ የአፍሪካ ኅብረትን የመሳሰሉ ተቋማት  በሦስትና በአራት አሥርት ዓመታት የተቀነበበ ግብ ማስቀመጣቸው ከዚሁ ነባራዊ ሥጋት በመነሳት ነው፡፡ ዓለም ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በፍጥነት እያሟጠጠች፣ በዚያው ልክ የሕዝብ ብዛቱ በከፍተኛ ፍጥነት እየገሰገሰ መሄዱ በአንዳች  ዓይነት ምጣኔ ሀብታዊ ሥሌት እየተጣጣመ እንዲሄድ ሁሉም ትረኩረትና ቀልቡን ሊነፍግ አይገባም፡፡   

ትኩረታችን መሆን ያለበት የአገራችን ጉዳይ ላይ ነውና ወደዚያው እንመለስ፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ያለማቅማማት ከአሥር ዓመታት ለበለጠ ጊዜ ፈጣንና ተከታታይ ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በዓመት ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በታች የግብርና ሰብል ምርት ወደ 300 ኩንታል ማደጉ ብቻ አይደለም፡፡ ወይም ከአሥር ዓመታት በፊት በአፍሪካ አንደኛ ደረጃ ላይ የሚያስቀመጥን የቁም እንስሳት ሀብት በአሥር ሚሊዮን መጨመሩ አይደለም፡፡ ይልቁንም አገሪቱ በፈጣን የመሠረተ ልማት፣ የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ላይ አተኩራ በመሥራቷ ነው፡፡ ለአንዳንዶች እንደ መንገድ፣ ቴሌኮም፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ የመጠጥ ውኃ፣ የከተማ መኖሪያ ቤቶች፣ ወዘተ ላይ የተደረገው አመርቂ ርብርብ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡

የእነዚህ መንግሥት የሕዝብን አቅምና ሀብት ተጠቅሞ የዘረጋቸው የልማት ሥራዎች መጠናከር የአገር ውስጡንም ሆነ የውጭ ባለሀብቱን ወደ ልማት የማተኮር ፍላጎት አነሳስተዋል፡፡ መጠኑና ዓይነቱ ይለያይ እንጂ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት መስክ እንዲሁም በንግድ ማኅበራዊ ኢንቨስትመንት ያለው የተነቃቃ እንቅስቃሴ ለአብነት ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ መንግሥትም ቢሆን አለኝ ከሚለው ‹‹ልማታዊ›› ባህሪይ አኳያ የገበያ ክፍተትን በመሙላት የሚሰማራባቸው መስኮች፣ ለተገኘው ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አላበረከቱም ማለት ክህደት ነው፡፡

ያም ሆኖ ግን አሁንም የዓለም አቀፉ ተፅዕኖም ሆነ የራሱ የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ተደምሮ ድህነትና ኋላቀርነት የኢትዮጵያ ሥጋት መሆኑ አልቀረም፡፡ የአየር ንብረት መበከልና የኤልሊኖ ተፅዕኖም አሁንም የሚሊዮኖችን ሕይወት በመገዳደር ላይ ይገኛል፡፡ የድርቅና የችግርን ቀቢፀ ተስፋ ተመላላሽ ክስተት ደጋግመን ማየታችንም ሊጤን ይገባዋል፡፡

ድህነት አንዱ መሰናክል

Africa Renewal (May, 2016) ዕትም “How did partnerships work for Africa” (አገሮች በአፍሪካ ምን እየሠሩ ነው?) የሚል ጽሑፍ አስነብቦ ነበር፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለቤትነት የሚታተመው ይኼ መጽሔት አፍሪካ ከሰላሳና ከአርባ ዓመታት በፊት በነበረችበት ጥቅል ቁመና ላይ እንዳልሆነች ገልጾ፣ ያም ሆኖ ግን አሁንም በሰላም፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ በልማትና ዘላቂ ዕድገት ላይ ያለው አተያይ ወጣ ገብነት ያለበት፣ አፈጻጸሙም ዥንጉርጉር ገጽታ ያለው መሆኑን አትቷል፡፡

የኢትዮጵያን ሁኔታ ሲነሳም አገሪቱ በጤና፣ በትምህርት፣ በመሠረተ ልማትና በመሰል ጉዳዮች የምዕተ ዓመቱን ግብ ማሳካቷን ያወሳል፡፡ አሁንም ግን የድህነት አጀንዳ (በተለይም 100 ሚሊዮን እየደረሰ ካለው ሕዝብ አንፃር) ጫና መፍጠሩን ግን አልሸሸገም፡፡

በአገሪቱ 22 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ከዓለም አቀፍ መሥፈርት አኳያ በድህነት ውስጥ ያለ (ከሁለት ዶላር በታች የቀን ገቢ የሚያገኝ) ነው፡፡ 17 በመቶ የሚሆነው ወጣትና አምራች ኃይልም በሥራ አጥነት አሠላለፍ ውስጥ መገኘቱ በመንግሥት መረጃ መረጋገጥ ተችሏል፡፡ እርሱ ብቻ ሳይሆን ከስምንት እስከ አሥር ሚሊዮን የሚደርስ የአገሪቱ ቆላማ አካባቢ ሕዝብም የዕለት ዕርዳታ የሚፈልግ ሆኗል፡፡ ይኼ በተለይ ባለፈው ዓመት ከተከሰተው ድርቅ አንፃር መባባሱ ባይካድም፣ በኋላቀር አኗኗር ውስጥ መቆየቱ የራሱ ተፅዕኖ አልነበረውም ለማለት አይቻልም፡፡

የኢትዮጵያ የፀረ ድህነት ትግል ጉዳይ ሲነሳ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ በአጭር ጊዜ ከድህነት መውጣቱ፣ በተለይ በጥቃቅንና አነስተኛ ኑሮውን መምራቱ ይጠቀሳል፡፡ በገጠርም ምርታማነት መጨመሩ፣ በባለሀብቱና በመንግሥት ፕሮጀክቶችም የሥራ ዕድል በብዛት መፈጠሩም ይወሳል፡፡ ያም ሆኖ ግን በአገሪቱ መሠረታዊ የመልካም አስተዳደርና ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ዝንባሌ መታየቱ የድህነት ቅነሳና ማስወገድ ሥራውን መጎተቱ የሚታወቅ ነው፡፡  

ኢትዮጵያ ውስጥ በፍጥነት የበለፀጉ ሚሊዮኖች በብዛት እንዴት ተፈጠሩ? ለዕለት ጉርስ ብቻ የሚሠሩ ወጣቶች ለምን አልተመጣጠኑም? ዜጎች በተለይ በከተሞች ለከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ችግር ለምን ተጋለጡ? በዘላቂ ልማት (የከተሞች መስፋፋት፣ መሠረተ ልማት ዝርጋታና ኢንቨስትመንት) ሲባል ሚሊዮኖች ለምን ያለ በቂ ካሳ ይፈናቀላሉ? የአገሪቱ ወጣቶች ለስደትና አስከፊ ፍልሰት እየተጋለጡ ያለው ለምንድነው….? የሚሉ ጥያቄዎች ወቅታዊና አንገብጋቢ መሆናቸውን የሚገልጹ ሀቲቶችን በጥልቀት መመርመር ያስፈልጋል፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (CPJ)፣ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል . . የመሳሰሉት ተቋማት የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ባህል፣ የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ግንባታና ዘላቂ ልማት የሚሞግቱበት መንገድም ብርቱ ልቦናን የሚሻ ነው፡፡ ‹‹በአንድ አገር ውስጥ ዴሞክራሲ ከሌለ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና እኩል ተጠቃሚነት ብሎ ነገር የለም›› የሚሉ ትንታኔዎች ከፍ ከፍ ባሉበት ጊዜ በማንነት፣ በፆታ፣ በብሔር፣ በእምነት፣ በፖለቲከ አመለካከት፣ ወዘተ የአንድ አገር ዜጎች ጉራማይሌ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይዘው ረዥም ርቀት መሄድ አይችሉም፡፡ ከዜሮ ድምር ፖለቲካ ለመውጣትም ፈተና መደራረቡ አይቀሬ መሆኑን የሚገልጹ ተንታኞች እየበረከቱ ነው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዝኃነት ያለባቸው አገሮች ፖለቲካዊ ሁለንተናዊነት አለመረጋገጥና የግልጽነትና የተጠያቂነት ባህል አለመገንባት፣ በየትኛውም መስክ የሚገነባን ኢኮኖሚና ፀረ ድህነት ትግል ማወኩ አይቀሬ ነው፡፡ በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ እንደ አገር የታዩ የሕዝብና መንግሥት አለመግባባቶች፣ ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ይልቅ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታየት ዘላቂ ልማትን መፈተኑ አይቀርም፡፡ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳይኖርና ፀረ ድህነት ትግል እንዲዳከምም ያደርጋል፡፡ ይኼ ከላይ በተጠቀሱ ትንታኔዎችም ሆነ በዘርፉ ልሂቃን የተመሰከረ ጉዳይ ነውና በወጉ ሊጤን ይገባል፡፡

የአየር ብክለት ሌላኛው ተግዳሮት

ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙዎቹ የአኅጉሩ አፍሪካ አገሮች በግብርና ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ያላቸው ናቸው፡፡ በራሳቸው ብቻ ሳይሆን ሌላው ዓለም በአየር ንብረት ብክለት ላይ በደነቀረው ሳንካ ምክንያት ዋጋ እየከፈሉ ያሉትም ለዚሁ ነው፡፡ እዚህ ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ ፎረሞች አደራዳሪነት እ.ኤ.አ. በ2012፣ 13፣ 14ና 15 ድረስ በየዓመቱ እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር የበለፀጉ አገሮች ለደሃ አገሮች ለመስጠት (ለመደጎም) የአየር ብክለት ድጎማ ስምምነት ሲደረግ የነበረው፡፡ ያም ሆኖ በኢንዱስትሪ የተበከለ ጋዝ ልቀትና በውቅያኖስም ሆነ በንፁህ አየር መታወክ የሚወቀሰው ዓለም እዚህ ግባ የሚባል ካሳ ሲሰጥ አልታየም፡፡ ምናልባት እንደ ቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ያሉት የደሃው ዓለም መሪዎችም የጀመሩት ህልምም እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ማምጣቱ አልታየም፡፡ በእርግጥ አገሮች ሕዝቦቻቸው በራሳቸው ጥረት ያስመዘገቡዋቸው መልካም ውጥኖች (በተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ በመልሶ ልማትና አካባቢ ጥበቃ እንዲሁም በታዳሽ ኃይል ልማት መጠናከር) እንደ በጎ ጅምር ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡

ዓለም አቀፍ የአየር ብክለት ግን የአካባቢ ሁኔታን በማዛባት ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም፡፡ እነሆ በአፍሪካ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለድርቅ ያጋለጠው መንስዔው ይኼው ነው፡፡ በአንዳንድ የምሥራቅና ምዕራብ አገሮች የከፋ ድርቅ፣ የተባባሰ ሰደድ እሳት፣ አሊያም የጎርፍ አደጋ ለመከሰቱ መንስዔውም ይኼውና ይኼው ብቻ ነው፡፡

ከሕዋ ሥነ ምህዳርና ከአካባቢ መበከል ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ታዳጊ አገሮች በውስጣቸው ያለው የኑሮ ተስማሚነት ደረጃም መጤን ያለበት ነው፡፡ የተሻለ መኖሪያ ቤት፣ ተመጣጣኝ ምግብ፣ የተሟላ አልባሳት ያላገኘ ሕዝብ የታመቀባቸው አገሮች በነፍስ ወከፍ ገቢ ሥሌት ብቻ አደጉ ማለት አዳጋች መሆኑን ኒኮላስ ስተርን በዝርዝር ጽፎታል፡፡

በዚህ ረገድ አገራችን ከተሞችና የኢንዱስትሪ ቀጣናዎችም የተደቀነባቸው ፈተና ቀላል አይደለም፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ ከተሞቻችን በደረቅ ቆሻሻ ክምር የተሞሉና የፈሳሽ አወጋገዳቸው በቴክኖሎጂ ያልታገዘ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ከኢንዱስትሪና ከአነስተኛ ማምረቻዎች የሚወጣ ብክለት የከርስና የገጸ ምድር ውኃን እስከ ማጥፋት የሚያደርስበት ጊዜ ትንሽ አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ እጅግ ሰፋፊ የሚባሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች፣ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች፣ በሚሊዮን ሔክታር የሚገመት የተፋሰስና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ፣ የታዳሽ ኃይል አጠቃቀም (ለምሳሌ በኤሌክትሪክ የሚሠራ ባቡር . . .)  መጠናከራቸው በጎ ጅምር ሊባል ይችላል፡፡ በዚያው ልክ ግን አሁንም በገጠርና በአርብቶ አደሩ አካባቢ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የእንስሳት ሀብት (ጥራቱ ዝቅተኛ ነው) ብክለትን የሚያመጣ ነው፡፡ በተለይ ልቅ ግጦሽን ሙሉ በሙሉ ማስቆም ባለመቻሉ የጉዳት መጠኑ እንደ ኢንዱስትሪ ብክለት አይሁን እንጂ፣ ለድርቅ ሥጋት አንድ መንስዔ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በኢትዮጵያ ሁኔታ በቆላማ አካባቢዎች ላለው የድርቅ ሥጋት እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ሌላው ችግር አሁንም ከዝናብ ጠባቂነት ያልተላቀቀ ኢኮኖሚ የመኖሩ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ኋላ ቀርና የድህነት መገለጫ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ለመላቀቅ ብርቱ ሥራ ማስፈለጉ ብቻ አይደለም መዘንጋት የሌለበት፡፡ ይልቁንም በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ ፍትሐዊ የልማት ትግበራና ፍትሐዊ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ መኖሩ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በኒኮላስ ስተርን ትንታኔም የሦስተኛው ዓለም አገሮች የድህነትና የአየር ብክለት ተፅዕኖ አስጨናቂ ፈተና ትንተናም የሚቆመው በዚሁ ሐሳብ ላይ አተኩሮ መሆኑ ሲታይ የዚህ ጽሑፍ ድምዳሜን ትክክለኛነት ያሳያል፡፡ አገራችንን ጨምሮ ታዳጊ አገሮች ድህነትን ለማስወገድ በተለይም በፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና የአየር ብክለት ተፅዕኖ መቋቋም ካልቻሉ ከመፍገምግም መውጣት አይቻልም፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

    

 

 

 

 

Standard (Image)

የኢትዮጵያ መሠረተ ካፒታል ምንድነው?

$
0
0

በመታሰቢያ መላከሕይወት ገብረክርስቶስ

በአማርኛ ቋንቋችን መሠረት ትምህርት፣ መሠረተ ጤና፣ መሠረተ ልማት፣ መሠረተ ፍጆታ፣ ወዘተ በስፋት የምንጠቀምባቸው ቃላት ሲሆኑ፣ መሠረተ ካፒታል የሚለው ቃል በስፋት ሥራ ላይ ውሏል ማለት አይቻልም፡፡ ቃሉን በአጭሩ ለመግለጽ መሠረተ ካፒታል ማለት አንድን አገር ለማደግ ስትወስን ያላትን የተፈጥሮና የሰው ሀብት ለማልማት የምትጠቀምበት የመጀመሪያ መነሻ ካፒታል ወይም ሀብት ብለን ልንገልጸው እንችላለን፡፡ ይህ ደግሞ በአገር ደረጃም ሆነ በግለሰብ  ደረጃ የሚሠራ ነው በእንግሊዝኛ ቋንቋ (Paidup Capital) እንደ ማለት ነው፡፡

ዛሬ በልፅገው ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ አገሮችን ታሪክ ስናጠና የምንረዳው ነገር ቢኖር፣ ሁሉም ያደጉበት መንገድ የተለያየ መሆኑን ነው፡፡ ለምሳሌ እንግሊዞች ለማደግ የተጠቀሙበት መንገድ አገራቸውን ጥለው ወደ ሌሎች የዓለም ክፍል በማምራት፣ የሌሎች ሕዝቦችን የተፈጥሮ ሀብትና ጉልበት በመበዝበዝ መነሻ ካፒታል መፍጠር ችለዋል፡፡ እንግሊዞች በታሪክ የሚታወቁበትን ወርቅና አልማዝ ተገኘ በተባለበት ቦታ ሁሉ በብዛት በመጓዝ ያንን ሀብት እንደ መነሻ ተጠቅመው፣ በዓለም ላይ ሰፊ ወታደራዊ ኃይል መገንባት ችለዋል፡፡ ይህንን ወታደራዊ ኃይል ደግሞ ተጠቅመው ቅኝ አገዛዝን፣ ቋንቋቸውንና ባህላችውን አስፋፍተዋል፡፡

አሜሪካኖች ደግሞ የሚታወቁት ከአገራቸው ወጥተው ሌሎች አገሮችን በመውረር ሳይሆን፣ ከአፍሪካ የሚመጡ ባሪያዎችን ጉልበት በመጠቀም ወረው የያዙትን የሰሜን አሜሪካ ግዛት በማቅናት አስደናቂ ዕድገትና ሥልጣኔ መገንባት ችለዋል፡፡

በቅርቡ ደግሞ አስደናቂ ሥልጣኔ መገንባት የቻሉት የዓረብ አገሮች የነዳጅ  ሀብትን እንደ መነሻ ካፒታል በመጠቀም፣ ለሰው ልጆች ኑሮ ተስማሚ ባልሆነው በረሃማው አገራቸው ላይ ትልቅ የግንባታ ጥበብና ሥልጣኔ ማምጣት ችለዋል፡፡

የፖለቲካ ምሁራን ይህንን ዓይነት ሥልጣኔ (Lumpenish Civilization) ብለው ይጠሩታል፡፡ ይህ ማለት ሥልጣኔው በአንድ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ብቻ የተመረኮዘ፣ ከትውልድ ትውልድ የማይተላለፍ፣ የሥልጣኔ ሳይንስ ሥርዓትን ያልተከተለ እንደ ማለት ነው፡፡ እኔ ይህንን ቃል ወደ አማርኛ ስመልሰው ‹‹ድሪቶ ሥልጣኔ›› ብሎ መሰየም የተሻለ ይመስለኛል፡፡ የአንድ አገር ግንባታ ፍፁም በሳይንስና በሳይንቲስቶች ተመርቶ፣ ዘመኑ ያፈራውን ዕውቀት ተከትሎ የማይመራ ከሆነ ከላይ የተጠቀሰው ስም ጥሩ ይመስለኛል፡፡

በሩቅ ምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ እስያ ያሉ አገሮች ደግሞ እንግሊዞችና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ርካሽ የሰው ጉልበት ፍለጋ ዕውቀታቸውን ይዘው በእነዚህ አገሮች ባደረጉት ከፍተኛ መስፋፋት ምክንያት፣ ዘመናዊውን ዕውቀት መተዋወቅ በመቻላቸው ይህን ዕውቀት በመጠቀም በአገራቸው ባደረጉት የኢንዱስትሪ አብዮት ከፍተኛ መሠረተ ካፒታል መፍጠር ችለዋል፡፡ ከአውሮፓውያን በተማሩት ዕውቀት ላይ የራሳቸውን ፈጠራ በመጠቀም አሁን በዓለማችን እጅግ አስደናቂ ልማት ላይ መድረስ ችለዋል፡፡

ከላይ በአጭሩ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በሁሉም አገሮች ያለው መሠረተ ካፒታል አፈጣጠር የተለያየ መሆኑን ነው፡፡

ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ ኢትዮጵያ ገና ያላደጉ አገሮች ተብለው ከሚጠሩ አገሮች ተርታ የምትመደብ ሲሆን፣ አስተማማኝና ዘለቄታ ያለው ሥልጣኔ መገንባት እንድትችል መጠቀም ያለባት መሠረተ ካፒታል እንዴትና ምን እንደሆነ አግባቡ ማወቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮና የሰው ሀብት ዜጎችን ሕይወት ሊለወጥ በሚችል መንገድ እንደ መነሻ የሚሆን የካፒታል ምንጭ ወይም መሠረተ ካፒታል እንዴት ማግኘት ትችላለች የሚለው ድምዳሜ ላይ ለመድረስ፣ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው የኢሕአዴግ መንግሥት እየሄደበት ያለውን መንገድ መመልከቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን እንደያዘ መጀመሪያ ዕርዳታ መቀበልን እንደ ዋና ስትራቴጂ አድርጎት ቆይቷል፡፡ ከዚያም በመቀጠል ከውጭ አገር መንግሥታትና ባንኮች ብድር በመውሰድ ልማትን ማፋጠን ይቻላል የሚል አቅጣጫ አስቀምጦ ላለፉት 26 ዓመታት ሲጓዝ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን እነዚህ አማራጮች አስተማማኝ እንዳልሆኑና የዜጎችን ሕይወት በመለወጥ በኩል አመርቂ ውጤት ማምጣት እንደማይቻል በጊዜ በመገንዘብ፣ ሌሎች አማራጮችን ማፈላለግ ይገባው ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡

በተለይ የማዕድን ሀብትን በአፋጣኝ በማልማት በራስ አቅም ከፍተኛ መሠረተ ካፒታል መፍጠር የሚቻል ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ ግን ‹‹ለኢትዮጵያ ሕዝብ የማዕድን ልማት አያስፈልገውም›› የሚል አቋም ይዞ ከፍተኛ ጊዜ ያቃጠለ ከመሆኑም በላይ፣ አሁንም በመንግሥት ደረጃ ግልጽና አሻሚነት የሌለው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕድገት መነሻ ካፒታል ሊሆን የሚችለውን አቅጣጫ በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡

እዚህ ላይ እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ ለአገራችን ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጠውን የዓባይን ግድብ ለመገንባት የሚያስችል የገንዘብ ምንጭ ለማግኘት ምን ያህል እንደተቸገርን ለሁላችንም ግልጽ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚያ በፊት የማዕድን ልማት እንዲፋጠን ተግተን ሠርተን ቢሆን ኖሮ፣ ዓባይን ለመገደብ ብዙ ሳንቸገርና በራሳችን አቅም ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችን ሳንጎዳ ማልማት በቻልን ነበር፡፡

ካለፉት 40 ወይም 50 ዓመታት በፊት በዓለማችን ያልነበረ አሁን በስፋት ያለ ነገር ቢኖር፣ በብዙ የዓለማችን ክፍሎች  የተትረፈረፈ የገንዘብ ክምችት መፈጠሩ ነው፡፡

ለምሳሌ በአሁን ወቅት በትሪሊዮን የሚቆጠር የዶላር ክምችት ያላት ቻይና የዛሬ 40 ወይም 50 ዓመት እጅግ ደሃ ከሚባሉ አገሮች ውስጥ የምትመደብ ነበረች፡፡  ቻይና የዜጎችዋን ጉልበት እንደ መሠረተ ካፒታል በመጠቀም ዛሬ በዓለማችን አስደናቂ ሥልጣኔ መገንባት የቻለች አገር ሆናለች፡፡ ሰሞኑን ቢቢሲ እንዳስነበበን ቻይና እ.ኤ.አ ከ2012 እስከ 2015 በአገርዋ የተጠቀመችው የሲሚንቶ መጠን አሜሪካ ከ1900 እስከ 1999 ድረስ ከተጠቀመችው ሲሚንቶ ማለት 20ኛው ክፍለ ዘመን ጋር እኩል መሆኑን ነው፡፡ ይህ በእጅጉ የሚያስደንቅ ዜና ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ወይ ቱታ ለብሰን እንደ ኮሙዩኒስት አገሮች በወታደራዊ ዲሲፕሊን እየተመራን ዶማና አካፋ ጨብጠን የካፒታል መሠረት መፍጠር አልቻልንም፡፡ ወይም ደግሞ ገንዘብ ያለው ባለሀብት ያለ ገደብ ወደ አገር ውስጥ እየገባ እኛ ያንን ገንዘብ በመጠቀም የአገራችንን መሬት እያለማን ካፒታል መፍጠር አልቻልንም፡፡ ታዲያ የኢትዮጵያ ርዕዩተ ዓለማዊ የልማት አቅጣጫ ምንድነው? ይህ ጥያቄ በእጅጉ ወሳኝ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

በዓለማችን ያሉ ሁሉም ሥልጣኔዎች አንድ የሚያርጋቸው ባህርይ ተወደድም ተጠላም የግድ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ትውልድ ጉልበት ተበዝብዞ፣ ተጨቁኖ ወይም ሌላ መስዋዕትነት ሳይከፍል ዕድገትን መመኘት ከቶውንም የሚታሰብ አይደለም፡፡ ሁሉም ሥልጣኔዎች የጀርባ ታሪካቸው ቢጠና እጅግ አስቸጋሪና እልህ አስጨራሽ ሒደቶችን አልፈው ነው ዕድገት ማማ ላይ የተፈናጠጡት፡፡ ሌላው እኔን የሚያሳስበኝ ጉዳይ አሁን እኛ እየሠራናቸው ያሉ  ተግባራት በአብዛኛው ሲገመገሙ በበቂ ሳይንሳዊና ደረጃቸውን ጠብቀው በርካታ ትውልዶች ተጠቃሚ ሊያደርጉ በሚችሉበት ሁኔታ ሳይሆን እየተተገበሩ ያለው፣ ጊዜያዊ ችግርን ለመቅረፍና ለፕሮፓጋዳ ፍጆታ ወይም ቁጥር ለማሟላት በሚችል መንገድ መካሄዳቸው ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እነዚህን ፕሮጀክቶች (Feel Good Projects) ብለን ልንጠራቸው እንችላለን፡፡ ይህ ማለት ለአካባቢው ማኅበረሰብ ይህ ነገር ተሠራልህ ለማለት ያህል የተሠሩ እንጂ፣ ኅብረተሰቡ ኪስ ሊገባ የሚችል ፋይዳ የላቸውም፡፡

የተፈጥሮ ሀብትን በመጠቀም መሠረተ ካፒታል ከመፍጠር አኳያ በርካታ የአፍሪካ አገሮች በርካታ ስህተቶች የሠሩ በመሆናቸው፣ እኛ ከእነዚህ ስህተቶች በመማር የተሻለ የመሥራት ዕድሉ አለን፡፡

ለምሳሌ ናይጄሪያ ያላትን የነዳጅ ሀብት ተጠቅማ የዜጎችዋን ሕይወት መለወጥ ሲገባት፣ በአሁኑ ጊዜ ናይጄሪያ ውስጥ ያለው ድህነት የነዳጅ ሀብት ባለቤት ከመሆንዋ በፊት ከነበረው ድህነት በእጅጉ የከፋ ነው፡፡ ይህ የሆነው በተለያዩ ጊዜያት የተፈራረቁ መንግሥታት ይህንን ሀብት በአግባቡ ማስተዳደር ባለመቻላቸው ነው፡፡ ገንዘብ ተበድረው ለአልባሌና በአግባቡ ላልተጠና ፕሮጀክት እያዋሉ፣ ገሚሱ ደግሞ በሙስና እየተዘረፈ አገሪቱን ማለቂያ ለሌለው ለዕዳ ጫናና ለድህነት ሲዳርጋት ቆይቷል፡፡

እኛ ከዚህ ስህተት በመማር የተሻለ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያው የተፈጥሮ ማዕድን በሚገኝበት ጊዜ ያንን ማዕድን ባለበት ቦታ በዓለማችን የተትረፈረፈ የገንዘብ ሀብት ላላቸው አገሮች እዚያ መሬት ውስጥ እንዳለ በግልጽ ጨረታ በመሸጥ፣ በ50 ወይም በ100 ዓመታት ጊዜ ውስጥ  አልምተው እንዲወስዱት በማድረግ በአንድ ጊዜ አገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንድታገኝ ማድረግ ይቻላል፡፡ አሁን ያለውን ትውልድና መጪውን ትውልድ በአስተማማኝ ሁኔታ የሚጠቅም መሠረተ ካፒታል ወይም ዕዳ አልባ የሆነ የገንዘብ ክምችት መፍጠር ይቻላል፡፡

እስካሁን ባለው አሠራር በቁጥ ቁጥ ገንዘብ እየተበደርን አንዱ ልማት ከሌላኛው ጋር መናበብ እያቃተው፣ የተገነባው ልማት ከወጣለት ወጪ አኳያ ጥቅም ሳይሰጥ ዕዳው ብቻ እየቆለለ የሚሄድበት ሁኔታ ባለፉት ዓመታት በተጨባጭ የታየ ጉዳይ ነው፡፡

ለምሳሌ በመላው አገሪቱ ብዙ ሚሊዮን ዶላሮች ተበድረን የገነባነው የመንገድ መሠረተ ልማት ሁሉም ሊባል በሚቻል መልኩ ከአቅም በታች እያገለገለ ነው፡፡ መሻሻል አላሳየም፡፡ እዚህ አጠገባችን ያለው የአዲስ - ለአዳማ የፍጥነት መንገድ ተገንብቶ ከተመረቀ በርካታ ወራት ያሳለፈ ቢሆንም፣ አሁንም በመንገዱ ላይ ያለው የትራፊክ ፍሰት እጅግ አናሳ ነው፡፡

ሌላው ሥለ መሠረተ ካፒታል ስንነጋገር የሁሉም ኢኮኖሚዎች መሠረት የሆነውን መሬት በተመለከተ እያራመድን ያለው ፖሊሲ፣ አሁንም ከ26 ዓመታት በኋላ አጨቃጫቂ መሆኑ ነው፡፡

ሰሞኑን በቴሊቪዥን እየተመለከተ ነው ያለው የኢሕዴግና የተቃዋሚ ፓርቲዎች  ድርድር ገና ወደ ፍሬ ነገሩ ያልተገባ ቢሆንም፣ በጣም በእርግጠኝነት ልናገረው የምንችለው ነገር ወደ ዋናው ድርድር መገባት ከተጀመረ አሁንም የመጀመሪያው አጀንዳ ሆኖ የሚቀርብ ይመስለኛል፡፡

ከ1966 ዓ.ም. አብዮት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ እየጠየቀ ያለው መሬት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የዜጎች የባለቤትነት መብት እንዲረጋገጥ ሆኖ ሳለ፣ አሁንም በተለይ የገጠር መሬት ገበሬው በባለቤትነት ስሜት ሊያለማው፣ አስይዞ ሊበደርበት፣ ሊሸጠውና ሊለውጠው ባለመቻሉ አገሪቱ ማለቂያ ለሌለው የድህነት አዙሪት ውስጥ ለመኖር ተገዳለች፡፡ ገበሬው በመሬቱ ላይ የባለቤትነት ስሜት ስለሌለው ገንዘብንና ጉልበቱን ለቋሚ ሀብት እያዋለ አይደለም፡፡

እዚህ ላይ ሒሳባዊ ሥሌት እንሥራ፡፡ መንግሥት እንደነገረን በአገራችን ሊታረስ የሚችል ከ40 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በላይ እንዳለ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ የዋለው 13 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ብቻ ነው፡፡ ይህንን 13 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ብቻ ውሰደን እያንዳንዱ አባወራ አንድ ሔክታር አለው እንበልና በዚህ መሬት ላይ እያንዳንዱ ገበሬ በዓመት 10,000 ብር የሚያወጣ ቋሚ ሀብት ቢያፈራ፣ 10,000x13 ሚሊዮን= 130 ቢሊዮን ብር አገራዊ ሀብት እናፈራለን፡፡ 130 ቢሊዮንxበ26 ዓመት (ማለት ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ያስተዳደረበት ጊዜ) 3.380 ትሪሊዮን ብር የሚያወጣ ቋሚ ሀብት በገጠሪቷ ኢትዮጵያ እናፈራለን ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን ይህንን ሀብት የሚወርስ ወጣት ትውልድ እንዴት አድርጎ ነው ስደት የሚሄደው? ይህ ሥሌት በዝቅተኛው የብር መጠን ተሠራ እንጂ ከዚህ በበለጠ ሊያድግ የሚችልበት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ባለፉት 26 ዓመታት ይህን ያህል ሀብት ሳናፈራ ቀርተናል ማለት ምን ያህል ጉዳት እንደሚያስከትል ለማንም ጤነኛ አዕምሮ ላለው ሰው በቀላሉ መረዳት የሚቻል ጉዳይ ነው፡፡

መሬት  የመንግሥት ነው የሚለው አዋጅ ምን ያህል ለድህነት እንዳደረገን ከላይ የተገለጸው ማስረጃ ከበቂ በላይ ይመስለኛል፡፡ በከተሞች ደግሞ እጅግ የተጋነነ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ያላገናዘበ አልፎ አልፎም እጅግ ከበለፀጉ አገሮች የመሬት ዋጋ ጋር እንኳን ሲነፃፀር በእጅጉ የበለጠ ዋጋ እየቀረበ ነው፡፡ ይህ በእርግጠኝነት ጤነኛ ያልሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓት በአገራችን መኖሩን ለማስረዳት ከበቂ በላይ ነው፡፡

አሁን ለድርድር እያኮበኮቡ ያሉትም የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር አጀንዳዎችን ወይም (Road Map) መራሔ መንገድ ምን እንደሆነ ለሕዝብ ቢያነብቡና ለውይይት ቢቀርብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ አሁንም የዛሬ 26 ዓመት የተሠራው ስህተት እንዳይደገም፣ ማንኛውም የሕገ መንግሥት መሻሻል ወይም የፖሊሲ ለውጥ በዓለም ደረጃ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችልና የኢትዮጵያን ሕዝብ እርካታ ሊፈጥር የሚችል መሆን አለበት፡፡ ኢሕአዴግ የዛሬ 26 ዓመት ብቻውን አገር በመቆጣጠር በማናለብኝነት ሊታረም የማይችል ታላላቅ ታሪካዊ ስህተቶች ሠርቷል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ ይህንን ለመዳሰስ አልፈልግም፡፡ ነገር ግን ሁላችንም ይህንን ስለምናውቀው አሁን ስህተት ላለመሥራት  ድርድሩና ውይይቱ በመንግሥትና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ምሁራን በሁሉም መስክ ተሳታፊ መሆን አለባቸው፡፡

አሁን ባሉት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የኢትዮጵያ ምሁራን በበቂ ሁኔታ አሉ ለማለት አያስደፍርም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተው በየምርጫው በመሳተፍ ኢሕአዴግን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አስመሰሉት እንጂ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም የፈየዱት ነገር የለም፡፡ የመጫወቻ ሜዳ በሌለበት ሁኔታ የፖለቲካ ጨዋታ ሲጫወቱ ነው የከረሙት፡፡ የኢሕአዴግ የምርጫ ሠርግ በየአምስት ዓመቱ ሲደገስ እንደ ሚዜ ሲያጫፍሩ ከርመው፣ ኢሕአዴግ ሙሽራው ቤተ መንግሥት ሲገባ እነሱ ወደ ጎጆአቸው ያቀናሉ፡፡ አንድም የፖለቲካ ፓርቲ ዝርዝር ማኒፌስቶውን እንኳን በስፋት አዘጋጅቶ በየመጻሕፍት ቤቱ ለመሸጥ የሞከረ የለም፡፡ ይህ ማለት የኢትዮጵያ ሕዝብ እነዚህን ፓርቲዎች እንዴት ሊረዳቸው ይችላል፡፡

ባለፉት 100 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የምዕራባውያን ትምህርት ተስፋፍቶ የነበረ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ያላት አንዱ ትልቅ ሀብት የምሁራን ሀብት ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ምሁራን በበቂ ሁኔታ ያሳተፈ የፖለቲካ ድርድር ካልተካሄደ፣ አሁንም እንደገና እርማት የሚፈልግ ሕገ መንግሥትና የመንግሥት ፖሊሲ ነው የሚኖረን፡፡ ኢሕአዴግ ገፍተው ወደፊት የመጡትን ምሁራን ብቻ ሳይሆን ለማቅረብ መሞከር ያለበት፣ ምሁራን ከያሉበት ተፈልገው ለአገራቸው እንዲሠሩ መጋበዝ አለባቸው፡፡

ባለፉት 100 ዓመታት ከአፄ ምኒልክ በስተቀር ሌሎች መንግሥታት ኢትዮጵያ መሠረተ ካፒታል እንድታፈራ የሠሩት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ መንግሥት ደግሞ ከወጣቱ ብዛትና አቅም ጋር የሚመጣጠን መሠረተ ካፒታል ፈጥሮ የወጣቱን እርካታ መፍጠር ካልቻለ፣ የመጨረሻው ውጤት የፖለቲካ አለመረጋጋትና የአገር መፍረስ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም በዚህ አቅጣጫ ሰፊ ሥራ መሠራት አለበት፡፡

መሠረተ ካፒታል በመፍጠር ሒደት ላይ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ መውሰድ ጠቃሚ ቢሆንም፣ ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር መጣጣሙን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ኢሕአዴግ በርካታ ትምህርቶች ከደቡብ እስያ አገሮች እንደተማረ ደጋግሞ ይነግረናል፡፡ ነገር ግን የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮችና እኛ ያለን የተፈጥሮ ሀብት በእጅጉ ይለያያል፡፡ መሬትን ብንወስድ በደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች እጅግ ውስን ሀብት ሲሆን፣ በአገራችን ደግሞ በእጅጉ የተትረፈረፈ ሀብት ነው፡፡ በረሃ የሚባሉት የአፋርና የሱማሌ ክልሎች እንኳን ያላቸው የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር የውኃ ሀብት እጅግ ሰፊ ነው፡፡ በመሆኑም በምሁራኖቻችን (በካድሬዎች ሳይሆን) የሚጠቅመንን ፖሊሲ ማጥናት በእጅጉ ወሳኝ ተግባር ነው፡፡

ኢሕአዴግ የዛሬ 26 ዓመት ሥልጣን ላይ ሲወጣ ለምሁራን ፖሊሲ በማውጣት ሒደት ላይ ሰፊ ዕድል ባለመስጠቱ፣ ዛሬ የምናያቸው ውስብስብ ችግሮች ሊፈጠሩ ችለዋል፡፡ አሁንም ይህ ስህተት እንዳይደገም ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡

ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ተፈተው ምርጫ ከተወዳደሩ በኋላ አንድ የተናገሩት አስደናቂ አባባል አለ፡፡ ‹‹በምርጫ ውጤት ከ75 በመቶ በላይ ባገኝና ፓርላማውን ተቆጣጥሬ ለብቻዬ ሕግ አውጪ ብሆን ኖሮ፣ በሕግ ማውጣት ሒደት ላይ ብዙ ስህተት እሠራ ነበር፡፡ ነገር ግን ከ75 በመቶ በታች በማግኘቴ ከሌሎች ጋር የማወጣው ሕግ ለአገር የሚጠቅም ይሆናል፤›› ብለው ነበር፡፡ ይህ አባባል ለሁላችንም በቂ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ በተጨማሪም የአንድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫ ነው፡፡ አገር የጋራ እንደ መሆንዋ ሁሉ፣ ሁሉንም ዓይነት አስተሳሰቦች በነፃነት የሚስተናገዱበት መድረክ መፍጠር እጅግ ቢዘገይም አሁን ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው metasebyamelaku@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡      

 

Standard (Image)

‹‹ስምዎ ማን ነው?›› ወይስ ‹‹ስምዎ ምንድን ነው?››

$
0
0

በልዑል ካሕሳይ

ኣንድ ጊዜ ኣንድ ወዳጄ የኣንዲትን ትንሽ ልጃገረድ ስም የጠየቅሁበትን የኣማርኛ ኣባባል ሰምቶ በኣግርሞት ኣረመኝ። የወዳጄ እርማት ከዓመታት በፊት በሁለት ካናዳውያን ወዳጆቼ መካከል የተከሰተ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ኣጠቃቀም እርማትን ኣስታወሰኝ። እኔ ልጅትን “ስምሽ ምንድን ነው?” እንደ ኣልሁ ኣት ነበር “ስምሽ ማን ነው?” ማለት እንደ ነበረብኝ ወዳጄ በለሆሳስ የኣሳሰበኝ። ነገር ግን ከኣማርኛ ከሰዋስው ኣንጻር እኔ ትክክል ነበርሁ። በተቃራኒ፣ በካናዳውያኑ ወዳጆቼ መካከል ተከስቶ የነበረው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ኣጠቃቀም እርማት ኣንደኛው “more better” የሚል የትንንሽ ልጆችን ኣነጋገር የሚመስል ድርብ ንፅፅርን ያሰለፈ ሰዋስዋዊ ወንጀል በመፈጸሙ ነበር። የኣማርኛ ቋንቋ ለእኔም ሆነ ለወዳጄ የኣፍ መፍቻ (የመጀመሪያ) ቋንቋችን በመሆኑ ቋንቋውን ኣስመልክቶ ብንተራረም ምንም ኣይነት የመሳለቅ ስሜት ኣንዳችን በሌላኛችን ላይ ኣሳድረን እንደ ኣልነበር ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ኣልነበረም። በተመሳሳይ፣ የእኔን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ኣጠቃቀም ህጸጾች ኣንዴም ለማረም ደፍረው የኣላወቁ ካናዳውያኑ ወዳጆቼ፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ለእነርሱ የመጀመሪያ ቋንቋቸው ስለ ነበር እርስ በርስ ለመተራረም ኣንዳችም ኣልተሳቀቁም ነበር። በማሕበረሰብ ውስጥ ኣንድን ቋንቋ እንደ ሁለተኛ ቋንቋቸው ለየሚጠቀሙ ሰዎች ሰዋስዋዊም ሆነ ዘዬ-ኣዊ እርማቶችን መስጠት በሰዎቹ ላይ ሊያመጣ ከሚችለው ምናልባት ስነልቦናዊ ተጽዕኖ ኣንጻር ብዙ የተለመደ ኣይደልም። እንዲያውም ሃሳባቸውን እስከ ገለጹ ድረስ ስህተቶቻቸውን ችላ ብሎ ማለፍ በብዙዎች ዘንድ የጨዋነት ምልክት ነው።

ጉዳዩ ግን ግራ-ኣጋቢ የሚሆነው እንደ ኢትዮጵያ በኣሉ የተዋበ ቋንቋ እየ ኣላቸው የቋንቋቸውን ሰዋስዋዊ ሕግጋት በስነጽሑፍም ሆነ በስነኣንደበት ሳያዳብሩ በቀሩ እና በተለያዩ ማህበራዊ እና ምጣኔሃብታዊ ምክንያቶች የቋንቋቸው የመግለጽ ብቃት እንደ ግመል እዳሪ እየ ኣደር ወደ ኋላ በሚቀርባቸው ሕብረተሰቦች ውስጥ ነው። በእነኚህ ሕብረተሰቦች ውስጥ የተሳሳተ የቋንቋ ኣጠቋቀም ከሚፈጥረው ግርታ ይልቅ፣ የቀና የቋንቋ ኣጠቃቀም የሚፈጥረው ግርታ እየከፋ መጥቶ ኣል።

የሰው ስም ግኡዝ ነው እንጂ እንደ የስሙ ባለቤት ህያው ኣይደለም። እንዲያውም በየኣማርኛ ሰዋስዋዊ ሕግ መሰረት፣ ቃሉ “ማን” በጅምላ ለማንኛውም ህያው ነገሮች ሳይሆን ለግለሰዎች (ለምሳሌ፦ ሰው፣ ኣምላክ፣ እና መላእክት) ብቻ ነው የሚያገለግል። ለምሳሌ፣ ‘ድመቱ ማን ነው?’ ኣንልም፤ ‘ሰውየው ማን ናቸው?’ ግን እንል ኣለን። ስም ኣንድን ሰው የሚወክል በራሱ ግን ሰብዕና የሌለው ነገር ነው። ሰዎች ከስም በተጨማሪ ሌሎች መለያዎች ሊኖሩ ኣቸው ይችል ኣሉ፣ ነገር ግን ቃሉን “ማን” በየትኛውም መለያዎች ላይ ማዋል ህጸጽ ነው። ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የኣንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃዎች ተማሪ እንደ ነበርሁ እንደ ሌሎች ተማሪዎች በየዓመቱ የመለያ ተራ ቁጥር ይሰጠኝ እንደ ነበር፣ ነገር ግን ማንም “ቁጥርህ ማን ነው?” ብሎ ጠይቆኝ ኣያቅ እንደ ነበር ኣስታውስ ኣለሁ።

በምትኩ ምን ማለት ይሻል ኣል? “ስምዎ ምንድን ነው?” ትክክለኛ ኣባባል ሲሆን፣ ከወዳጅ ዘመድ ግርታ እና ኣግራሞት ለመዳን ከፈለጉ ግን ባጭሩ ሁሌም የምንጠቀምበትን “ማን ልበል?” ን መጠቀም ይችል ኣሉ። ከሌሎች ኣማራጮች ኣንዱ ደግሞ “ስምዎን ቢነግሩኝ” ነው።

ኣንድ ሰው ግን ሰዎች እስከ ተግባቡ ድረስ በዘፈቀደ ቢነጋገሩ ምን ችግር እንደ የሚኖረው ይጠይቅ ይሆን ኣል። እንዲያው ኣንዳንዶች ቋንቋ የመግባቢያ መሳሪያ ስለ ሆነ ምንም ደንብ ሊወጣለት እንደ የማይገባ ይከራከር ኣሉ። በመሰረታዊ ደረጃ፣ በነዚህ በቀደሙት ሁለት ኣረፍተ-ነገሮች ውስጥ ከተካተቱት ኣንድምታዎች ጋር በኣብዛኛው እስማማ ኣለሁ። ማንም በትክክል የተግባቡ ኣካላትን “የተግባባችሁ የሰዋስው ሕግታትን በትክክል ሳትጠቀሙ ስለ ሆነ መግባባታችሁ ውድቅ ነው” ሊል ኣቸው ኣይችልም ወይም ኣይገባም። እንደዚሁም፣ ማንም በራሱ ኣነሳሽነት የቋንቋን ሕግጋት ሊደነግግ ኣይችልም። የሚገርመው ነገር ግን፣ እነዚሁ ሁለቱ ሃሳቦች ናቸው ቋንቋዎች መዳበር እና ሰዋስዋዊ ሕግጋትን ተከትለው መሄድ እንደ ኣለባቸው የሚያስገድዱ።

ለመሆኑ መግባቢያ እንዴት ነው የሚሰራ? በሕብረተሰብ ውስጥስ በኣንድ ቋንቋ ምክንያት ስልጠታዊ መግባባት መኖሩ እንዴት ነው የሚታወቅ? የስልጠታዊ መግባባት ጉድለት መዘዙስ ምንድር ነው? ኣፄ ኃይለ ሥላሴ ለምን ነበር ስለ “የሃገራችን የቋንቋ ድኽነት” የተናገሩ? ቋንቋ እንደ ማንኛውም ሃገራዊ ሃብት ሊበለጽግ ኣሊያም ሊኮሰምን ይችላል። ሰዎች ከጋርዮሽ ሕብረተሰብ የኣኗኗር ስልት ብዙም ሳይርቁ በኖሩባቸው ዘመናት፣ ስልጠታዊ መግባባት ብዙም ኣይፈልጉ ይሆን ነበር። ነገር ግን በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ለምንኖር ለእኛ በመግባባት ውስጥ የሚከሰቱ እንከኖች ኣያሌ ግላዊ፣ ማህበራዊ፣ ምጣኔሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ኣንድምታዎች ይኖሩ ኣቸው ኣል። ለምሳሌ፣ በኣማርኛችን ውስጥ ሰዋስዋዊ ጊዜያት የክንውኖችን ቅደም ተከተል በኣግባቡ እንድ ይገልጹ ስለ የማንጠቀምባቸው ንግግሮቻችን የተንዛዙ ብቻ ሳይሆኑ፣ ቁንጽል ኣንዳንዴም ኣስደንጋጭ መልእክቶችን ነው በኣብዛኛው የሚያስተላልፉ።

በኣንድ ወቅት ኣንድ የተከበሩ መልካም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቴሌቪዥን ቃለምልልስ ላይ “እኔ ተደባዳቢ ነኝ፤ ሰዎችን እፈነክት ኣለሁ፤ ጫትም እቅም ኣለሁ” እንደ ኣሉ ኣስተውዬ በጣም ነበር የደነገጥሁ። ከእይታው ሙላት እንደ ተረዳሁት፣ ሰውየው በእርግጥ ለማለት የፈለጉ “እኔ ተደባዳቢ ነበርሁ፤ ሰዎችን እፈነክት ነበር፤ ጫትም እቅም ነበር” ነበር።

ኣንዳንዴ ግን እንዲህ ኣይነቱ ሕጸጽ በህክምና እና በመሳሰሉ ስልጠታዊ መግባባትን በሚጠይቁ ሞያዎች ላይ ኣደገኛ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፣ በሽተኛው መርፌ “ተወግቶ ኣል” እና “ተወግቶ ነበር” ትልቅ የትርጉም ልዩነት ኣላቸው። እንደዚሁም፣ ኣንድ ሰው “ሞተ” (ወይም “ሞቶ ኣል”) እና “ሞቶ ነበር” ትልቅ የትርጉም ልዩነት ኣላቸው። እንዲያውም “እከሌ ሞቶ ነበር” ኣይባልም፣ ምክንያቱም አንድምታው “እከሌ ኣሁን ግን ከሞት ተነስቶ ኣል” ስለ የሚሆን። “እከሌ መርፌ ተወግቶ ነበር” ግን ይባላል፤ ነገር ግን ትርጉሙ ‘ኣሁን እከሌ ለሁለተኛ ዙር መርፌ ዝግጁ ነው፤ በመሆኑም በኣስቸኳይ ሌላ መርፌ ይሰጠው’ ማለት ሊሆን፣ ኣሊያም ‘በመርፌው ምክንያት ተፈወሰ’ ወይም ‘ሞተ’ ማለት ሊሆን ይችላል። ዞሮ ዞሮ ይህ ኣባባል የሚያሳየው፣ የመርፌ ውጋቱ የተከሰተ ከጊዜ ኣንጻር ኋላ ላይ ከተከስተ ወይም ሊከሰት ከሚገባው ኣንድ ሌላ ነገር በፊት መሆኑን ነው።

ነገር ግን ኣንድ ሰው “መርፌ ተወግቶ ኣል” ካልን፣ ኣሁናዊ የቅርብ እላፊ ስለ የሚሆን፣ በሽተኛው ሌላ መርፌ ሊሰጠው ኣይገባም በመሆኑም ከመርፌው ውጋት ወዲህ የተከሰተ እና ከሰዋስው ኣንጻር ሊዘገብ የተገባ ነገር የለም ማለት ነው። እንዲያውም፣ ይህ ሰው ሌላ መርፌ ቢደገመው እንደ መድሃኒቱ ጥንካሬ መጠን መርፌው ለህይወቱ ኣስጊ ሊሆን በት ይችል ኣል ማለት ይሆናል። የእንግሊዝኛ ቋንቋ የኣፍ መፍቻቸው ለሆኑ ሰዎች ይህን ኣይነተ የኣረፍተ-ነገሮችን ኣገባብ ለማስረዳት መሞከር ‘ለቀባሪ ኣረዱት’ ኣይነት የሚሆን ሲሆን፣ በሕብረተሰባችን ውስጥ ግን የሰዋስዋዊ ጊዜያት ጉዳይ እያደር እየተብላሸ ከመግባባት ይልቅ ኣለመግባባታችን እየጨመረ ይገኛል። በመሆኑም ኣንድ ጉዳይ ለመረዳት ወይም ለማስረዳት ሰዎች በቃላት ዙሪያ-ጥምጥም መሄድ ይኖርባቸው ኣል ኣሊያም ሙሉ ለሙሉ ሳይግባቡ ስህተቶች ይከሰታሉ።

የባዕዳን ቃላት በቋንቋችን ውስጥ እንደ ኣሸን መፍላት፣ ሰዎች ኣንደበታቸውን በፈቱበት ቋንቋ ሃሳባቸውን በጥራት እና በፍጥነት መግለጽ ኣለመቻላቸው፣ በቋንቋችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ኣለማስተማራቸው፣ ትልልቅ ሃግራዊ ተቋማት እና ታላላቅ መሪዎች ሳይቀሩ ከሞላጎደል እንግሊዝኛን በጉዲፈቻ ማዳበላቸው፣ ሰዎች ባዶ ቃላትን (“እንትን”) በንግግሮቻቸው ውስጥ ኣብዝተው መጠቀማቸው፣ ዜጎች በገዛ ሃገራቸው የባዕድ ቋንቋ ባለመቻላቸው፣ በሃኪሞች እና በህመምተኞች መካከል ኣስታራቂ የሆኑ ሃገራዊ የህክምና ቃላት መጥፋታቸው፣ በኣጠቃላይ ኣገራችን ኣጠቃላይ የሆነ የቋንቋ ቀውስ ውስጥ እንደ ኣለች የሚያመላክቱ ናቸው።

“ስምዎ ማን ነው?” ስለ ተባለ የዓለም መጨረሻ ኣይሆንም፣ ነገር ግን ‘የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ እንደ የሚያስታውቅ ሁሉ’ ቋንቋውን ያላዳበረ ሕብረተሰብም ካሉት መለያዎች ኣንዱ እንደዚህ ኣይነት ህጸጽ የተሞሉ ኣባባሎች ናቸው።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የ‹‹Proposed Language Reform for Ethiopia: Volume I (Orthography)›› [ውጥንየቋንቋህዳሴለኢትዮጵያ፦ቅጽስርዓተ-ጽሕፈት] ደራሲናቸው። ጽሑፉ ከነአጻጻፉና ሆሄያት አጠቃቀሙ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው info@threequa.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

​ታሪካዊና ምሁራዊ ማረጋገጫ ያጣው መጽሐፍ

$
0
0

ግምገማ፣ በኘሮፌሰር ጳውሎስ ሚልክያስ አመያ

ይህ የአማራና የኦሮሞን የዘር ምንጭ በተመለከተ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ የጻፉትን ‹‹የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ›› መጽሐፍ በአጭሩ የሚዳስስ ቅኝት ነው፡፡ ደራሲው አማራና ኦሮሞ የአንድ ወል የዘር ምንጭ  አላቸው ከማለታቸው ጋር ልዩነት ሊኖረን አይችልም፡፡ በዚያም ምክንያት እኛ ኢትዮጵያውያን በባዕዳን የተዛባውን ታሪካችንን መልሰን መረከብና እጅ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ እኔም የኦሮሞ የዘር ሐረግ ያለኝ ኢትዮጵያዊ ምሁር እንደመሆኔ መጠን ለያዙት ለዚህ አቋም የማያወላውል ድጋፍ እሰጣለሁ፡፡  

በእርግጥ ይህ አንድነት ኦሮሞዎችንና አማራዎችን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ ትግራዮችም፣ ጉራጌዎችም፣ አገዎችም፣ አፋሮችም እንዲሁም በርካታ ሌሎች ብሔረሰቦች፣ በአንድ አካባቢ በመኖራቸው፣ የወል የባህል ውርስ በመስጠታቸውና በጋብቻ በመቀላቀላቸው ሊካድ የማይችል የባሕሪይ፣ የሥነ ልቦናዊ ዘይቤ፣ የቋንቋ፣ የጋራ ዳራዎች አሏቸው፡፡ የአንዱ ከሌላው ይብለጥ ወይም ይነስ እንጂ ሁሉም የኩሽና የሴም የዘር ሥርው አላቸው፡፡ ይኼ የሚጠበቅና የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለብዙ ሺሕ ዓመታት አብረው ኖረዋል፡፡ ሁሉም አፍሪካውያን በቅኝ የመገዛት ቀንበርን ሲሸከሙ ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ፣ የሚሳሱለትን የፖለቲካ ነፃነታቸውን በወል ከወራሪዎች በመከላከል ጠብቀዋል፡፡ በዚህም ከተገኙት አንጸባራቂ የጦርነት ድሎች መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ፣ በዛፋር (518)፣ በወይና ደጋ (1536)፣ በጉንዳጉንዲ (1880)፣ በጋላባት (1882)፣ በአምባ አላጌ (1888) በዓድዋ (1888) የተቀዳጀናቸው እርታታዎች በአንድ ብሔረሰብ ብቻ የተገኙ አልነበሩም፡፡ 

በዓለም ዙሪያ ስንመለከት፣ በመዛግብትና በጽሑፋዊ ሰነድ ጥናቶች፣ በድረ ገጽ አፈላለግ ዘዴዎች፣ በቤተ ሙከራ ምርመራና እንዲሁም ሌሎች እነሱን የመሳሰሉት ምስጋና ይግባቸውና፣ ደንብና ሥርዓት በቆመለት የዘረኝነት ፍልስፍና የሚያምኑ ሁሉ፣ ራሳቸውን እንከንየለሽ አድርገው የሚቆጥሩም ነጭ አሜሪካኖች ሳይቀሩ፣ ዛሬ ዛሬ ስለ ትውልዳቸው እውነታ እየተመራመሩ ትክክለኛውንም ዘይቤ እየተረዱ መጥተዋል፡፡ የዘራቸው ግንድ ሥር በፊት ሲያስቡት እንደ ነበረው ንጹህ ኖርዲክ ሳይሆን ከላቲኖ፣ ከአሜሪካ ሕንድ፣ ከእስያ፣ ከአፍሪካዊ አሜሪካዊ ጋር የተቀያየጠ ሆኖ አግኝተውታል። ከጥቂት ወራት በፊት በሰጠሁት ቃለመጠይቅ፣ በሰፊው እንደተቸሁት ሁሉ፣ ምንም እንኳ ከ82 በላይ የተለያዩ ቋንቋዎች ቢናገሩም፣ ኢትዮጵያውያን በመላ አንድ ሕዝብ ነን በማለት አጠንክሬ መከራከሬን በጥቂቱም ቢሆን የዚያ ቅኝት ታዛቢዎች ያስታውሱት ይሆናል፡፡ በዚህም በድጋሜ ከዶ/ር ፍቅሬ ጋር  እንስማማለን፡፡

ከዚህም በላይ ኘሮሬሰር መሳይ ከበደና እኔ ከአንድ ከአሠርታት በፊት በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ዓለም አቀፋዊ የሙያ ጋዜጣ እንዲሁም በምሁራዊው የአፍሪካ ቀንድ መጽሔት በሚያሳምን መረጃ የግብፅና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናት እንደሚሉት ንግሥተ ሳባ የመናዊት ሳትሆን ኢትዮጵያዊት መሆኗን፣ ታላቁ የ16ኛው ክፍለ ዘመን ዘርዐ ያዕቆብ፣ ቸሩሊና ኡለንዶርፍ እንደሚሉት የ19ኛው ክፍለ ዘመን ኢየሱሳዊ ቄስ ሳይሆን፣ በስሙ የሚጠራውን መጽሐፍ የደረሰ እሱ ራሱ ስለሆነ፣ ለዚህም እንደ ረኔዴካርትከመሰሉ የዘመኑ ብልሃተኛ የአውሮፓ ፈላስፋዎች እኩል የክብር ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ አጠንክረን ተከራክረናል፡፡ እዚህ ላይ ነው በአንድ በኩል በእኔና በኘሮፌሰር መሳይ ከበደ፣ በሌላ በኩል በዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ መካከል ያለው ክርክር ተመሳሳይነቱ የሚያበቃው፡፡

የሚያሳዝነው በምታት ብቻ ከሚታዩና ከሚታሰቡ ነገሮች ማጣቀሻዎች ያነሳናቸውን ቁም ነገሮች፣ በምናብ ብቻ ከሚታዩ ነገሮች ጋር በማደባለቅ የኛን ዋና ነጥብ ክብደት አሳጥተው ዶ/ር ፍቅሬ ማላገጫዎች አድርገዋቸዋል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ደራሲው ጥቂቶች ሽንጉል ወገኖች እንደሚያምኑት የኢትዮጵያን ታሪክ በአዲስ መልክ አልቀረጹትም፡፡ ከእውነታው ዘለው በቅዠት ዓለም የሚዋዥቅ ውብ ተረትን ነው የሸመኑት፡፡

የዶ/ር ፍቅሬን አባባሎች እንደገና እንቃኛቸውና ስለሚያቀርቧቸው መከራከሪያዎችና መንደርደሪያዎች፣ ስለሚሰጧቸውም ተጨባጭ ማረጋገጫዎች ጉዳይ በጥሞና እንጠይቅ፤

  1. የሰው ልጅ በሙሉ ጐጃምን ቤቴ ብሎ ሊጠራው ይገባል፣ ምክንያቱም ሁሉም ሰው  የተገኘው ከዚያ ነውና ይሉናል፡፡ በሆነ ኖሮማ እሰየው፡፡ ይኼ አባባል ግን ልብወለድና ተረት ነው። ማለት ለዚህ ታሪካዊና ምሁራዊ ማረጋገጫ የለውም፡፡ የኢትዮጵያዊ ታሪክ ጸሐፊ ኘሮፌሰር ባህሩ ዘውዴና እኔ ለመጨረሻ ጊዜ በተገኘንበት መድረክ ይኼ ጉዳይ ሲነሳ ሁለታችንንም በአንድ ላይ ትንሽ አስቆናል፡፡
  2. ዶ/ር ፍቅሬ አማራዎችና ኦሮሞዎች ወላጅ አባቱ ካልታወቀ ደሽት ከተባለ ሰው ጐጃም ተወለዱ ይሉናል፡፡ ይኸም ታሪካዊና  ምሁራዊ ማረጋገጫ የሌለው አንድም ተጨባጭ ማስረጃ ያልደገፈው ከንቱ ውዳሴ ልብ ወለድና ተረት ነው፡፡
  3. የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊዎች በሙሉ፣ ኦሮሞዎች በአንድ ወቅት ከእስያ ወይም ከውጭ መጡ የሚለውን ትረካ ይቀበላሉ ይሉናል፡፡ ይኼ ከሀቅ የራቀ ፍጹም ሐሰት  ነው፡፡ እንደ ኘሮፌሰር ሞሐመድ ሀሰን ያሉ የኦሮሞ ታሪክ ጸሐፊዎች ሥራን መመርመር ይበቃል፡፡ እኔ ራሴ አፍሪካ ኢን ፎከስ፤ ኢትዮጵያ  በሚለው መጽሐፌ  ኦሮሞዎች በአፍሪካ ቀንድ ለብዙ ሺ ዓመታት የኖሩ የኩሽ ዘር ግንድ ያላቸው  ሕዝብ ናቸው በማለት ደጋግሜ አሳስቤአለሁ፡፡   
  4. ዶ/ር ፍቅሬ፣ ንግሥተ አዜብ የአዘቦ ንግሥት ነበረች ይሉናል፡፡ ዬትና ዬት? ምን አገናኛቸውና? አዘቦ፣ ራያ አጠገብ ያለ፣ ባሁኑ ጊዜ በትግራይ ውስጥ የተካለለ የኦሮሞ ንዑስ ብሔር  ነው። አዜብ በምዕራብና በደቡብ መካከል ያለ የመልክ አምድር የማዕዘን ስም ነው።  ስለዚህ፣ ይህን በተመለከተ የደራሲው ግንዛቤ እንደገና ልብ ወለድና ተረት ተረት ነው ማለት ነው።
  5. የዓለም ታሪክ ጸሐፊዎች ኢትዮጵያ የሚለው ቃል በግሪክ Αιθιοψ በላቲን Aethiops የሚለው መጠሪያ የመጣው  ሁለት ቃላት በፅርዕ ιθιω, "የተቃጠለ"  ὤψ,  "ፊት"ሲደመሩ መሆኑን አረጋግጠዋል:: ዶ/ር ፍቅሬ ግን የተቃጠለ ፊትን ቃል በቃል ትርጉም በመጥላት ይመስል ኢትዮጵያ የሚለው ስም የፈለቀው ሁለት ሺሕ ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ፣ መጀመሪያ በኦሪት ዘፍጥረት፣ ሁለተኛ በመዝሙረ ዳዊት የተጠቀሰው መልከ ጼዴቅ ልጁን ኤቴልን ወደጣና ደሴት ሲልከውና እዚያው ሲያርፍ  በእግዜር ፈቃድ “ኢቲዮጵ” አሰኘው፣ ይኸውም “ብጫ ወርቅ” ማለት ነው ብለው አርፈውታል:: እንግዲህ እንደገና ተጨባጭ ታሪካዊና ምሁራዊ ማረጋገጫ  የሌለው ልብ ወለድና ተረት ተረት ጽፈዋል ማለት ነው።  
  6. እንደ ዶ/ር ፍቅሬ አጻጻፍ መጋል የጅማና የዲማ ኦሮሞዎች አባት ነው ማለት፣ ታሪካዊና ምሁራዊ ማረጋገጫ የሌለው ልብ ወለድ ተረት ተረት ነው።
  7. እንደ ዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ ትረካ፣ ናሙር ወንዝና ኦፌር የአፋር ብሔራዊ መኖሪያ ቦታን አመልካች ነው። እንደገና ተረት ተረት።
  8. እንደ ዶ/ር ፍቅሬ አገላለጽ፥ መቅደሽ ሞቃዲሾን ያመለክታል ማለት ተጨባጭ ታሪካዊና ምሁራዊ ማረጋገጫ አልባ ተረት ተረት ነው።  
  9. በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሶ በአፈታሪክ እንደተተቸው፣ በኮከብ እየተመሩ ሕጻኑን ኢየሱስን በቤተልሔም ለማየት እጅ መንሻ ይዘው ከምሥራቅ  የመጡት ሦስቱ ሰብአ ሰገል ጠቢባን፣ ብዙዎቹ እንደሚሉት አንዱ ብቻ የኢትዮጵያ ንጉሥ ሲሆን፤ እንደ ዶ/ር ፍቅሬ አጻጻፍ ግን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ነበሩ ማለት፤ ሐሰትና ተረት ነው፡፡  
  10. እንደ ዶ/ር ፍቅሬ ትረካ፥ ከዛጔዎች በኋላ የነገሠው የመጀመሪያው ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት ንጉሥ አፄ ይኩኖ አምላክ አዛዥ ጫላ ከተባለ የኦሮሞ ቩም ተወለደ። ይኽም እንደ ሌሎቹ አባባሎቻቸው ታሪካዊና ምሁራዊ ማረጋገጫ የሌለው ልብ ወለድ ተረት  ነው፡፡  
  11. ዶ/ር ፍቅሬ ከዚህ ከተዛባ ፈጠራቸው በፈለቀው  አስተሳሰብ ተመርተው አፄ ይኩኖ አምላክን ኦሮሞ አርገው  አርፈዋል፡፡ ይህን የሚያሰኝ ግን  ተጨባጭ ታሪካዊና ምሁራዊ ማረጋገጫ የለም፡፡ ነገሩ በደፈናው ተረት ተረት የላም በረት እንዲሉ የዘበት ጨዋታ ነው፡፡  
  12. ዶ/ር ፍቅሬ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ፊደል የተበጀው ዘግዱር በተባለ ሰው ነው ይሉናል፤ ግን ይኸ ተጨባጭ ታሪካዊና  ምሁራዊ ማረጋገጫ ያልተሰጠበት አባባል ነው፡፡

ልብ እንበል፣ እዚህ እኔ የምተቸው ኢትዮጵያውያን በቋንቋ ይለያዩ እንጂ አንድ ሕዝብ ናቸው ስለሚለው የዶ/ር ፍቅሬ መንደርደሪያ አይደለም፡፡ አባባሉ የሚያከራክር አይደለም፡፡ እኔ የማነሳው የማስረጃን ጉዳይና ደራሲው አባባሎቻቸውን ለመደገፍ ስለሚያቀርቧቸው መከራከሪያዎች፣ እንዲሁም የታሪክን አጻጻፍ ሥርዓትና ደንብ ወይም መመሪያን በተመለከተ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ከእሳቸው ጋር ያለኝ ችግር፣ ሐተታ ሲሰጥ፣ በምርምር ላይ መመሥረት ያለባቸው ማረጋገጫዎችን የሚያንጸባርቅ ዘይቤ ባለመጠቀማቸው ነው፡፡

ለምሳሌ አንድ ነጥብ  ላንሳ። ዶ/ር ፍቅሬ በመጽሐፋቸው ሽፋን ገጽታ ላይ በጣም የሚያጓጓ፣  ዋና የአርኪዎሎጂ ግኝት አስመስለው መሪራስ በተባለ ሰው በፈጠራ የተበጀ፣ ተሰምቶ የማይታወቅ የሱባ ፊደላት በማለት ተጠቅመውበታል፡፡ ለምን የሥነ ጥበብ ተመራማሪዎች በጥንቃቄ ይፈትሹት ዘንድ ዶ/ር ፍቅሬ ወይም ተባባሪዎቻቸው ይህን ግኝት አሁን የአውስትራላፕቴኩስኣፋሬንሲሷ - ሉሲ (ማለት የድንቅነሽ) አጽም ለተዘረጋበት ለብሔራዊ ቤተመዘክር አያበረክቱትም? በተጨማሪም ምሁራዊ እይታን ላለማዛባት ዩኔስኮ ይህን ታላቅ ግኝት በተመለከተ ለምን ዝም እንዳለ፥ ለምንስ በታዋቂ የቅርስ መዝገቡ ውስጥ እንዳላሰፈረው ያስረዱን ዘንድ መጠየቅ ተገቢ ነው።  

በአሁኑ ጊዜ፥ የዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ምንም ግንዛቤ በሌላቸው  ተላላ ግለሰቦች፣ እንዲሁም አሁን ያለውን ሥርዓት በሚቃወሙት ሰዎች ዘንድ እንደ ተወዳጅ የቡሔ ዳቦ እየተዘከረ፣ እየተገዛና በገፍ እየተናኘ ነው። ምንም እንኳ ስለ ትረካው እውነተኛነት ጥርጣሬ ቢኖራቸውም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሚያሳዝን ሁኔታ ጉዳዩን ችላ ብለውታል። ስለ አገራቸው ታሪክ የጠለቀ ግንዛቤ የሌላቸው ዘመናዊ ወጣቶች ግን መጽሐፉን ባያነቡትና፣  በምርምር ሥራቸውም ጠቅሰው ባይጠቀሙበት ምንኛ በበጀ፡፡

በፕሮፌሰር ፍቅሬ በተከተበው በዚህ መጽሐፍ የተዘረዘሩት ነገሮች ሙሉ በሙሉ ልብወለድና ሙሉ በሙሉ ተረቶች ናቸው፡፡ ይኸን ታሪክ ነው ብሎ መጻፍ  የጫት ሱሰኞች ከመቃማቸው ፋታ ሲወስዱ፣ ዱካካቸው የሚሰጣቸውን እውነት መሳይ  ቅዠት ይዘው እንደሚቀባጥሩት እንቶ ፈንቶ ነው፡፡ እንዲያውም በዚህ ባለንበት ተጨባጭ ዓለም ሳይሆን በሌላ የሕልም ዓለም መኖር ማለት ነው። ከጀርባ ሆኖ ከሚያናግር ጋንጩር የተሰጠውን ትዕዛዝ መቀበልና አጎብድዶ መመዝገብ ይመስላል፡፡

ወጣም ወረደም ይህ መጽሐፍ፣ ማንም አርታኢ የፈለገውን በሚጽፍበትና እርማት ሊያደርግ በሚችልበት በዊኪፒዲያ መድረክ ሊኖረው ይችላል፡፡ ለምን ቢባል አብዛኛውን ጊዜ ዊኪፒዲያ ባንድ በኩል ያልተረጋገጠ ዝባዝንኬን የማስገባትና በሌላ በኩል ያልተረጋገጠ ዝባንኬን የማስወጣት ግብር ስላለው ነው፡፡ በአገር ውስጥም፣ በውጪም ላሉ ወገኖች ያለኝ የወዳጅነት ማስጠንቀቂያ፣ በዊኪፒም ሆነ በዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱ ታማኝ የታሪክ መግለጫዎች አሉ ብላችሁ የምታምኑ ከሆነ፣ እንግዲያውስ ሳትሰሙት አትቀሩም፥ በሀበሻ  የተረት ወግ መሠረት የኢትዮጵያ መኳንንት፣ ልዑላንና ነገሥታት ሳይቀሩ በሕይወታቸው ዘመን በጠንቋይ ድግምት በማሳብ ያናግሩት ነበር እየተባለ ይወራለት በነበረው፥  በቢሾፍቱ ሐይቅ ይኖራል ተብሎ በሚታመነው፣ ደም በሚጠጣው፣ ቆበር በሚያስደፍቀው፣ ሕልሞችን፣ መታለሎችን፣ እንቆቅልሽዎችን ሁሉ በመተት ለመፍታት ይችላል  ተብሎ ባንዳንዶች ሰዎች በሚታመንበት በአየር ጋኔን፣ በቆሪጥ ብታምኑ ይቀላችኋል።  

(ይቀጥላል)

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በካናዳ ሞንትሪያል በሚገኘው ኮንኮርዲያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው pmilkias@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለ መቅሰፍት

$
0
0

 

በሒሩት ደበበ

በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ አንድ ልብ የሚነካ ግጥምን ማግኘቴ ብቻ ሳይሆን ለተነሳሁበት ርዕሰ ጉዳይ ስለሚመጥን የጽሑፌ መግቢያ ለማድረግ ወደድኩ፡፡ ርዕሱ ‹‹እንባዬ›› የሚል ሲሆን ስንታየሁ ዓለምአየሁ የተባለ ባለቤት ተሰጥቷታል፡፡

ጥቂት ቢበራ ጥቁረቴ፣

አደብ ቢገዛ ስሜቴ፣

ቢፍቅ ቢታጠብ በደሌ፣

ሟሙቶ ቢጠፋ እንዳሞሌ፣

ቢመለስ መልክ ከሥዕሌ፣

ቢያርቅ ‹‹አካል›› ከ‹‹አካሌ››፣

የብረት በሩን ገርስሰህ፣

ቁንን ግድቡን ደርምሰህ፣

የዓይኔን ሽፋሽፍት ገላልጠህ፣

ፍሰስ እንባዬ በፊቴ ላይ፣

ደጉን ከመጥፎው ለይቼ እንዳይ፤

ይላል፡፡ ይኼ ሐዘን እንጉርጉሮ ስንኝ ሐዘንን፣ ሞትና ለቅሶን ተንተርሶ የተሰደረ ነው፡፡ በአገር ደረጃ ብዙዎች ማቅ እያለበሱ ከሚገኙ የሞት ቀሳፊዎች መካከል አንዱ ደግሞ የትራፊክ አደጋ ነው ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡

እንደ አገር ከ100 ሚሊዮን የማያንስ ሕዝብ ይዘን፣ በቆዳ ስፋትም ቢሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ምድር ላይ ተቀምጠን ያሉን የተሽከርካሪዎች ብዛት ከ700 ሺሕ የበለጡ አይደሉም፡፡ የባቡር ትራንስፖርቱም ቢሆን ገና እየጀማመረ ያለ እንጂ ያን ያህል የሚያጨናንቅ አይደለም፡፡

ያም ሆኖ አገራችን ‹‹ውስን ተሽከርካሪ ያላት ግን በጣም ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ የሚከሰትባት›› የሚል ‹‹ማዕረግ›› ካገኘች ውላ አድራለች፡፡ በትራንስፖርት ዘርፍ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ማለትም የትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ የትራፊክ ፖሊስ፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ የመንገድ ሥራ መሥሪያ ቤቶች፣ የትራንስፖርት ማኅበራትና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተለያዩ ምክክሮችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ሕግ አውጭውና ተርጓሚውን ጨምሮ የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎችና አሠራሮችን ለማስተካከል የሚረዱ አካላትም ደጋግመው ሲመክሩ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በፓርላማ ካደረጉት የአደጋው ሥጋት ላይ ያተኮረ ንግግር ጀምሮ ሚኒስትሮችና አፈ ጉባዔዎች የሐዘን መግለጫ እስከማውጣት የደረሱበት አስከፊ ክስተትም ሆኗል - የትራፊክ አደጋ፡፡ ለዚህም ነው ለወራት የወሰደ የትራፊክ አደጋ የንቅናቄና የግንዛቤ ፎረም ተደርጎ የመንግሥት አካላትና ሕዝቡ፣ ልጅ አዋቂው ጉዳዩን አጀንዳ እንዲያደርገው ሰፊ ሥራ ሲከናወን የቆየው፡፡

አሁንም ግን የትራፊክ አደጋ በየዕለቱ የብዙዎችን እንባ እያፈሰሰ፣ የንፁኃንንም ሕይወት እየቀጠፈ ይገኛል፡፡ የአካል መጉደሉና የንብረት መውደሙም ቢሆን በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በቅርቡ በትራንስፖርት ሚኒስቴር አዳራሽ በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ እንደተጠቆመው፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ 16,213 ዜጎች ሕይወታቸው በትራፊክ አደጋ ተቀጥፏል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በ2008 ዓ.ም. ብቻ 4,223 ሰዎች ሞተዋል፡፡ በተመሳሳይ የአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥም 50 ሺሕ ዜጎች ለከፍተኛ የአካል መጉደል አደጋ ተጋልጠዋል፡፡

እንግዲህ የቬትናምና የአሜሪካ ወይም የኢራቅና የኢራን እንዲሁም የሶማሊያና የኢትዮጵያ ጦርነት ይመስል በአሥር ሺዎች እየሞቱ፣ በአሥር ሺዎች የሚቆስሉበት የአገራችን የትራፊክ አደጋ መዘዝ የሚያመጣ ሆኗል፡፡ በዚህ ሰፊ ጉዳት በየዓመቱ ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ የአገርና የሕዝብን ንብረት ከመውደሙ ባሻገር፣ በሕይወት ላሉ የተጎጂ ወገኖች ማኅበራዊ ቀውስን የሚደነቅር መሆኑም ያልታየው የመስኩ ሌላው ጉዳት ነው፡፡ ቀደም ሲል በጠቀስነው የምክክር መድረክም ሆነ በሌሎች ዓውዶች የተነሱ የዘርፉ የጉዳት መንስዔዎችና መፍትሔዎች ለውይይት መነሻ በሚሆን ደረጃ ለማስቀመጥ ተሞክሯል፡፡

የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ የችግሩ ዋና አስኳል

በአገራችን ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት ከነበረው የተሻለ የመንገድ አውታር ተዘርግቷል፡፡ በጥራትም በብዛትም ካለፉት ጊዜያት ዘመናዊና አዳዲስ ተሽከርካሪዎች የኢትዮጵያን ጎዳናዎች ሞልተዋል፡፡ በዚያው ልክ በጎዳና ላይ ደም መፍሰሱ በርትቷል፡፡ ለዚህ አስከፊ የትራፊክ አደጋ መባባስ ታዲያ 68 በመቶው የአሽከርካሪው ብቃትና ችሎታ ማነስ መንስዔ እንደሆነ ጥናቶች እያስገነዘቡ ነው፡፡

ለአሽከርካሪዎች ብቃት፣ ሥነ ምግባር መጓደልና ልምድ ማነስ በር እየከፈተ ያለው ደግሞ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ አሰጣጡ እንደሆነ በመንግሥት አካላት ጭምር የሚነገርና በጥናትም የተረጋገጠ ሆኗል፡፡ በአንድ በኩል በአሠልጣኞች፣ በመንጃ ፈቃድ አውጪዎችና በብቃት ሰጪዎች መካከል የሚፈጸም የሙስናና የአቋራጭ መንገድ አለ፡፡ የከፋ የሚባለውም በፎርጅድ መንጃ ፈቃድ ከመሬት ተነስቶ (አንዳንዱ የፈረስ ጋሪ እንኳን ሳያውቅ) መሪ እንዲጨብጥ ብሎም ወደ ሞት ይገሰግሳል፡፡

ከሁሉ በላይ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ አሰጣጡ (ይኼ ጉዳይ በትራንስፖርት ሚኒስቴር ግትርነት እስከ አሁን የቀጠለ ነው) የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበና ደካማ ነው፡፡ በተለይ በልምድ በችሎታና በብቃት አሽከርካሪዎችን ሳይመዝን፣ ለከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ እየተለማመዱ እንዲሄዱ ሳያደርግ፣ በ‹‹ገንዘብ›› ብቻ የፈለጉትን ደረጃ ማውጣታቸው የሞት መጠኑን ጨምሯል፡፡ በተለይ በከፍተኛ  ልምድና ብቃት የሚሽከረከሩ ከባድ ካሚዮኖች ከ20ዎቹ ዓመታት ባልዘለሉ ለጋ ወጣቶች የመዛወራቸው ለችግሩ መባባስ ዋነኛ መንስዔ ነው፡፡ ለዜጎች ሕይወት መጥፋትና አካል ጉዳት ምክንያት ነው፡፡ ለከፍተኛ የአገር ሀብት ክስረትም እያጋለጠ ይገኛል፡፡

‹‹የአገራችን አሽከርካሪዎች መሪ ጨብጠው ወዲያና ወዲህ መመላለሳቸውን እንደ ግብ አስቀምጠው የደኅንነት ቀበቶ የማያስሩ ናቸው፤›› የሚለው አደጋው ላይ ያተኮረ ጥናት የቴክኒክ ብቃት እጥረትን በመሠረታዊነት ያነሳል፡፡ ብዙዎቹ ወጣት አሽከርካሪዎች የዘይትና የቅባት ቦታዎችን ለይተው የማይቆጣጠሩ፣ የፍሬንና የመሪ አስፈላጊነትን አጢነው የማይገነዘቡ፣ የአየር ንብረትና የጉዞ ቦታዎችን የማያመዛዝኑ፣ የጨለማ መንገድንና በተለይም በድካም ስሜት ማሽከርከርን የማይረዱ ናቸው ሲል ይዘረዝራል፡፡ ከዚህ በከፋ ደረጃም ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ ምግባር አለመላበሳቸው (ጫት መቃም፣ መጠጣት፣ ሞገደኝነት) አገራዊ ቀውሱን እንደ ደመራ እንጨት እያንቀለቀለው ይገኛል፡፡

በድምሩ በአሽከርካሪ ብቃት አሰጣጥና በአሽከርካሪዎች ብቃት ላይ ያተኮረው የግለሰቦቹ፣ የተቋማቱና የመንግሥት ችግር መሠረታዊ ነው፡፡ በአፋጣኝ ጠንካራ መፍትሔ ካልተሰጠውም ሞቱና እልቂቱን የሚያቆም መግቻ ማግኘት ያስቸግራል፡፡

ነፍስ ለምኔ የሚያስብለው አደጋ

አውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ ከአምስት እስከ አሥር ዓመታት ያሽከረከሩትን ‹‹ሰልቫጅ›› መኪኖች ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው በአገራችን ገበያዎች እንደ ልብ ገዝተን እንነዳለን፡፡ ከፋብሪካ እንደተመረቱ ወደ እኛ አገር የሚገቡ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች (ኦባማ፣ ሲኖትራክና ልዩ ልዩ ዘመናዊ አውቶሞቢሎች) ግን ሕይወት እንደታቀፉ እየወደሙ ነው፡፡ በተለይ ‹‹ፍሬን አልባው›› የሚባለው ሲኖትራክ (ቀይ ሽብር) ከፍተኛ የጥፋት ሆዱን ከፍቶ አሽከርካሪዎችን፣ ተሳፋሪንና እግረኛን እየጎሰጎሰ ይገኛል፡፡ ችግሩ በዋናነት የአሽከርካሪዎች መሆኑ እንዳለ ማለት ነው፡፡

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ለእዚህ ችግር መባባስ አንዱ መንስዔ ተሽከርካሪዎቹን ከአገራችን መልክዓ ምድርና የመንገድ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ያለመጠቀም ተግዳሮት ነው፡፡ ሲኖትራክን በከፍተኛ ጭነት (ከፎርታታውም በላይ)፣ በዳለጠ ጎማ፣ በቁልቁለት ላይ በቀላል ማርሽ መሞከር መቅሰፍትን ያስከትላል፡፡ እንደ ዶልፊን የመሳሰሉ ባለስድስት ፒስተን ከፍተኛ አቅም ያላቸውን መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻዎች፣ ለአገሪቱ ከሚመጥነው ፍጥነት በላይ መጋለብ ሞትን ያፋጥናል፡፡ በተጨባጭ እየሆነ ያለው ግን ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የአገራችን የትራፊክ አደጋ በአብዛኛው የሚከሰተው በተሽከርካሪዎች መገልበጥ ነው፡፡፡ ቀጥሎም በመጋጨት፣ በመግጨትና ከግዑዝ  ነገር ጋር በመላተም (የእሳት ቃጠሎንም ይጨምራል) ይገኙበታል፡፡ በእነዚህ አስከፊና ዘግናኝ አደጋዎች ውስጥ ዋነኛ ሰለባ ለሚሆኑ ዜጎች ሕይወት ሕልፈት ከላይ የተጠቀሱትን ተሽከርካሪዎች ጨምሮ ብዙዎቹ ዘመናዊ መኪናዎች የአደጋ ሰበብ ሆነዋል፡፡ ለአገራችን መልክዓ ምድር የተፈጠሩ የሚመስሉት አሮጌ ተሽከርካሪዎች (ኤንትሬ፣ ላንድሮቨር፣ ቶዮታ፣ . . . ) አደጋ አያደርሱም ባይባሉም በርክቶ የሚስተዋል አይደለም፡፡

ከዚህ አንፃር ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን ከአመራረታቸው ጀምሮ ድክመትና ጥንካሬዎችን ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ ከመልክዓ ምድርና የመንገድ ሁኔታ ጋር አስተሳስሮ መጠቀም ይገባል፡፡

ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ለችግሩ መባባስ

ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦት የአገር ኢኮኖሚን በመጉዳት ኢፍትሐዊነትን የሚያነግሱ ብቻ አይደሉም፡፡ ይልቁንም በሰው ሕይወትና በማኅበራዊ ኑሮ ላይም የሚያደርሱት ጉዳት የከፋ እንደሆነ አንዱ ማሳያው የትራፊክ አደጋ ነው፡፡ በተለያዩ ጥናታዊ መረጃዎች እንደተረጋገጠው ደግሞ ሙስናም ይባል፣ የመልካም አስተዳደር ብልሽት ሥር ከሰደደባቸው ሴክተሮች ቀዳሚው ይኼው የትራንስፖርት ዘርፍ ነው፡፡

አንዱ ብልሽት ከአሽከርካሪውና ከተቆጣጣሪው (የትራፊክ ፖሊስ፣ የቦሎና ብቃት ሰጪ፣ የብቃት ማረጋገጫ ሰጪ፣ . . .) ጋር የሚገናኘው መሞዳሞድ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ግምገማ ቢካሄድ፣ ሕግ ቢወጣና ትራፊክ ቢበራከት ያልተሻሻለው በገንዘብ ‹‹ብቃትን›› የመግዛቱ ችግር ነው፡፡ ስህተትን በመማሪያነት ከመቅጣት ይልቅ መነገጃ ያደረጉ ጥገኞችም በዙ እንጂ አልቀነሱም፡፡ ለምን ቢባል ሰጪም፣ ተቀባይም ሕገወጥነትን የዘወትር ልብሳቸው አድርገዋል፡፡ መንግሥትም አደጋውን ለማስተካከል እየወሰደው ያለው ዕርምጃ አነስተኛ መሆኑ ሳይዘነጋ፡፡

በትራንስፖርት መስኩ ላይ ያለው ሌላው ብልሽት ከባንክ ብድርና ከኢንሹራንስ ዋስትና ጋርም ይገናኛል፡፡ ዛሬ ዛሬ በባንኮች ‹‹ጉዳይ ገዳይ›› የውስጥ ደላሎችን ያደራጁ፣ ከሥራ አመራር ቦርድ አንስቶ እስከ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች የተሳሰሩ ብድር አቀባባዮች ተበራክተዋል፡፡ እነዚህ ጥገኞች ‹‹በአጭር ለመበልፀግ›› የቋመጡ ነጋዴም ይባሉ አርሶ አደሮች ጋር በመነጋገር በሕግ ያልተፈቀደን የተሽከርካሪ ብድር እየፈነቀሉ ይሰጣሉ፡፡ ኮሚሽናቸውን እንደፈለጉ እየቆረጡም ባለንብረትና አሽከርካሪዎችን በብድር ጭንቀት ውስጥ ይከታሉ፡፡ ብሎም ለሞትና ለመቅሰፍት የሚያጋልጥ ውጥረት ውስጥም ይከታሉ፡፡

በኢንሹራንስ በኩልም የሚታዩ አንዳንድ ክፍተቶች አሉ፡፡ በእርግጥ የአገራችን ኢንሹራንሶች እየከሰሩም ቢሆን ለአካል፣ ለሕይወትና ለንብረት ጉዳት የመድን ዋስትና ሽፋን እንዲሰጥ ማድረጋቸው የሚበረታታ ነው፡፡ በመንግሥት ድጎማም ጭምር ማኅበራዊ ቀውስ እንዳይባባስ የመድን ካሳ ካለ ውስብስብ ውጣ ውረድ እንዲፈጸም መደረግ አለበት፡፡ ይሁንና አሁንም በመስኩ መደራደር፣ ሙስናና አሻጥር አሉ፡፡ በተለይ በመሐንዲሶች፣ በግምት አፅዳቂዎች፣ በኃላፊዎችና በመርማሪዎች፣ . . .  የሚፈጸም ቅብብሎሽ አለ፡፡ ባለሀብቶችንና ኢንሹራንሶችን የሚጎዱ ብሎም አገር የሚያቆረቁዙ ተግባሮችም በስፋት ይፈጸማሉ፡፡

በአጠቃላይ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦቱ ከመንገድና ከትራንስፖርት ቢሮዎች እስከ ጎዳናዎችና በመንደር ውስጥ እስካሉ የተሽከርካሪ ማደሪያዎች ድረስ ተባብሷል፡፡ ብርቱ የሕዝብ ትግልና የመንግሥት ቁርጠንኝነትንም ይፈልጋል፡፡

ማጠቃለያ

አሁን ባለው መረጃ በአገር ደረጃ በቀን ከ12 እስከ 15 ዜጎችን ሕይወት የሚቀጥፈው የትራፊክ አደጋ የብዙዎችን ሕይወት ያሳጣ መቅሰፈት ነው፡፡ ያውም አምራቹን ኃይልና ለአገርም የሚበጀውን ተንቀሳቃሽ ትውልድ፡፡ ስለዚህ መፍትሔው ቢያንስ አደጋውን ለመቀነስ ነገ ዛሬ ሳይባል መነሳት ያስፈልጋል፡፡ በየዕለቱ በመገናኛ ብዙኃን ከምንሰማው መርዶ ባሻገር የሁሉንም ቤት እያንኳኳ ያለውን የሞት ጥሪም ለመግታት ከፀሎት ጀምሮ፣ እስከ መፍትሔው የተግባር ዕርምጃ ከሁሉም የሚጠበቅ ነው፡፡

በየተራ እንባ ማፍሰስ ብቻ የሕዝብና የአገርን ለቅሶ አያስቆምም፡፡ መንግሥት አገር እንደሚመራ አካል ቆሞ ከመመልከት በመውጣት የብቃት ማረጋገጫ አሰጣጡን ይፈትሽ፡፡ ከላይ የተጠቃቀሱ ብልሽቶችንም ያስተካክል፡፡ መንገድ ከመገንባትም ባለፈ ስለመንገድ ሥነ ሥርዓት ከሚሠራውም በላይ ያስገንዝብ፡፡ አሽከርካሪዎች፣ እግረኞች፣ ሕዝቡም በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት የየድርሻቻውን ይወጡ፡፡ በነካ ነካ የለውጥ ፍላጎት ይኼን አደጋ ማስቀረት የሚቻል አይሆንም፡፡

የትራፊክ አደጋ ከሕዝቡ ጉዳትም አልፎ የአገሪቱን ገጽታ በማጠልሸት ‹‹በተሽከርካሪ ወይም በጎዳና የማይኬድበት አገር›› ሊያስብል  የሚችል ነው፡፡ ምንም እንኳን በአፍሪካ (እነ ግብፅ፣ አልጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያ፣ ወዘተ) የትራፊክ አደጋ የሚከሰትባቸው አገሮች ቢሆኑም፣ ከእኛ በሁለትና በሦስት እጥፍ የሚበልጡ ተሽከርካሪዎች እያሉዋቸው የአደጋው መጠን ግን ከእኛ ያነሰ ነው፡፡ ከዚህ ውርደት ለመውጣት ተግቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

    

  

Standard (Image)

ታሪካዊና ምሁራዊ ማረጋገጫ ያጣው መጽሐፍ

$
0
0

ግምገማ፣ በኘሮፌሰር ጳውሎስ ሚልክያስ አመያ

ክፍልሁለት

ይህ ክፍል ሁለት ቅኝት፣ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ በክፍል አንድ ያቀረብኳቸውን አያሌ ጥያቄዎችን በተመለከተ በድረ ገጽ የሰነዘሩትን የእንካ ስላንትያ ድንፋታ በሰከነና በምሁራዊ ማስረጃ ይዳስሳል። ዶ/ር ፍቅሬ ራስን በማዳን ደመ ነፍስ የወነጨፏቸውን ወደ ኋላ ትተን፣ በታሪክ ስም የሸመኑትን እንግዳ ተረት በጥሞና ስንቃኝ ሥራው እውነትን፣ ልብወለድን፣ ሃይማኖትንና ኮከብ ቆጠራን የሚያደባልቅ ለመረዳት እጅግ አስቸጋሪ የሆነ አባባል ሆኖ እናገኘዋለን። በዚህም ምክንያት እውነት አስመስለው ለሸረቧቸው ነገሮች ማስረጃ የሚሆኑ፣ ላነሳኋቸው አሥራ ሁለት ጥያቄዎች አንድም እንኳ ተጨባጭ ማረጋገጫ አላቀረቡም፡፡

ዶ/ር ፍቅሬ፣ ለተጠቀሙባቸው አጠራጣሪ ምንጮች ለግልጽና የተደላደለ ውይይት ኃላፊነት በመውሰድ ፈንታ፣ ለሚያገለግላቸው ውዥንብርና ራስን በመከላከል ድብብቆሽ ችግሩን ወደሌላ ለማላከክ ይዳክራሉ፡፡ ከመጀመሪያው ግልጽ እንዲሆንላቸው የምፈልገው ማረጋገጫ የመስጠቱ የኃላፊነት ሸክም በእኔ ላይ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም እኔ እንግዳ ነገርና ተሰምተው የማይታወቁ ትረካዎችን አላፈለቅሁም፡፡ ይህ ድርጊት የተፈጸመው በዶ/ር ፍቅሬ ስለሆነ፣ ወለም ዘለም ብለው ለማምለጥ አይችሉም፡፡ አገርን ለሚያክል ለመለያውና ለመታወቂያው ፈር እቀዳለሁ የተስተካከለ ታሪኩን አስተምራለሁ ብሎ በድፍረት የተነሳ ማንም ሰው ታማኝና ብረት ለበስ ማስረጃ ማቅረብ ግዴታው ነው፡፡

መልስ ካልተሰጠባቸው ከደርዘን ጥያቄዎቼ በተጨማሪ የሚቀጥሉትን ይመልሱ ዘንድ አሁንም ዶ/ር ፍቅሬን እጠይቃለሁ። አንደኛው አማራና ኦሮሞ የሚወለዱት የሰላም ንጉሥና በምድር የእግዚአብሔር ከፍተኛ ካህን ተበሎ በታወቀው የኢየሩሳሌም መሥራችና፣ አብርሃምና ሌሎች ነገሥታት የሰገዱለት አሥራትም ካወጡለት ከመልከ ጼዴቅ ነው ይሉናል። ሌላው ደግሞ ቀዳማዊ ምኒልክ በአገሩ ውስጥ የሠፈሩት የተለያዩ ብሔረሰቦች ሲሸፍቱበት የአጋዚ (የግእዝ ተናጋሪ) ብሔረሰብ ሰዎችን ከእሱ ጦር ጋር ተመሳጥረው ይዋጉለት ዘንድ ከጋዛ ወደ ኢትዮጵያ አመጣቸው ይላሉ፡፡ ምኒልክንም ክልስብለው በአግቦ እንደወረፉት ይጠቅሳሉ። ይህን የአማርኛ ቃል በምን ተዓምር ከሦስት ሺሕ ዓመታት በፊት ለመጠቀም እንደቻሉ ጸሐፊው ብቻ ናቸው የሚያውቁት።

ዶ/ር ፍቅሬ ኤቴል ወደ ኢትዮጵያ ሔዶ፣ ዛሬ ጐጃም ተብሎ በሚጠራው በሠፈረበት ጊዜ፣ ዘጠኝ ልጆች እንደነበሩት በስም ይዘረዝራሉ። ከእነዚህ አንዱ ቶሎሳ ነበረ ይሉና በተጨማሪ ‹‹በነገራችን ላይ የአጎቴ፣ ማለት የአባቴ ወንድም ስም ቶሎሳ ነው›› ይላሉ፡፡ ዶ/ር ፍቅሬ! እንኳን ለአጎትዎ ሞክሼ አገኙ፤ ነገር ግን እነዚህ እንግዳ መልዕክቶች ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ወይስ ከሌላ የሃይማኖት ድርሳናት የተጠቀሱ ናቸው? እርስዎስ ራስዎ ይህን በተመለከተ እውነት ለመሆኑ ማስረጃ ለሌለው በፈጠራ ለተቀነባበረ ትረካ የተዓማኒነት ሚዛን ይሰጣሉ ወይ? አዝናለሁ፤ ፈጠራና ሃይማኖታዊ እንጂ በምንም ተዓምር ሥራው ተጨባጭ ታሪክ ነው ተብሎ የሚቆጠር አይደለም፡፡

ዶ/ር ፍቅሬ፣ ታሪክ ሳይንስ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ይጠይቃሉ፡፡ አዎ፣ ታሪክ ሳይንስ ሊሆን ይችላል፤ እናም ነው። ለምን ቢባል፣ ታሪክም እንደሌሎች የማኅበረሰባዊ የጥበብና የዕውቀት መስኮች በአስተማማኝ መረጃ ላይ በመመሥረት የተፈጥሮን የዓለም ታሪክ ለማስረዳት፣ የሰው ልጅ ባለፈው ጊዜ ምን እንዳከናወነ በምንስ አኳኋን የዘመን ኑሮውን እንዳሳለፈ ጎልጉሎ፣ አበጥሮ ንጥረ ፍሬውን በሥርዓት ለመዘርዘርና ለመቃኘት የተዘጋጀ የምሁር መሣሪያ ነው።

ትክክለኛ ታሪክ ለብርቱ የሰው ጥረትና ግረት ምቹ መዝገብ ሲሆን፣ በጥበብ ሒደቱ ከሃይማኖት፣ ከፈጠራ ወሬና ከአፈ ታሪክ ተረት በአያሌው ይለያል፡፡ ለሚያቀርባቸው ሐሳቦች ሁሉም መውጫ አንቀጽ አሉት። ማስረጃው ወይም የመረጃ ጥርቅሞቹ ከገመቱት ሐሳብ ጋር በጥብቅ የሚመሳሰል ካልሆነ በስተቀረ ተመራማሪ ጠቢባን ወይም ሊቃውንት ሐሳባቸውን ሙሉ በሙሉ ይለውጣሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት እንግዲህ የመረጃን አንድምታዎች ለመቀበል ላላቸው የአሠራር ዘዴ ተገዥነታቸውን ለማረጋገጥ ሲሉ ነው፡፡

ከተሰነዘረው የይሆን ይሆናል ግምት ጋር የሚጣጣመውን መቀበል ወይም ተቃራኒ የሆነውን እርግፍ አድርጐ መተው የሰከነ ሊቅ ተግባር ነው፡፡ የምሁራዊም ጥበብ ምርምር መሠረቱ ይህ ነው፡፡ በአንድ በኩል ሳይንስን በሚመለከት በአርስጣጣሊስ ሥነ አመክንዮ አስተሳሰብ (ሲሎጅዝም) መሠረት ከዳሰስነው ከአጠቃላይ ወደ ዝርዝር ውሩድ አመክንዮ የሚራመደው (ዲደክቲቭ ሎጅክ) አለዚያም ከዝርዝር ወደ አጠቃላይ የሚራመደው ገንቢ አመንክዮ (እንደክቲቭ ሎጅክ)፣ ወደ ትክክለኛ አስተሳሰብ በሚያደርስ ሥሌት ሊረጋጋጥ በሚችል እውነታ ነው፡፡ ገንቢ አመክንዮ ትክክለኛ መሆኑ የሚታወቀው የመነሻው እውነታ የመደምደሚያውን እውነታ የሚያረጋግጥ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው። ስለሆነም ከዝርዝር ሁኔታዎች ወደ አጠቃላይ ሁኔታዎች የሚራመደው ሥነ አመክንዮ፣ አንድ ማሟላት ያለበት ጉዳይ አለ፡፡ በዚህ ሒደት የሁሉም ከሁሉም የሆነው የዋናው ፅንሰ ሐሳብ መንስዔ እንከን የለሽ መሆን ይኖርበታል፡፡ ውሩድ አመክንዮ ግን የእምነት ጉዳይ ስለሆነ የማረጋገጫ አቅራቦት ግዴታ የለበትም፡፡

ዶ/ር ፍቅሬ በመረጡት እውነተኛነቱ ባልተረጋገጠ የብራና ጽሑፍ ላይ በተመሠረተው አፈ ታሪክ ተረት ተመርተን፣ እንደ ሃይማኖት በጭፍን የፈጠራን ሐሳብ በእምነት መቀበል፣ ከአጠቃላይ ወደ ዝርዝር የሚተነተነው ሥነ አመክንዮ ምቹ የሆነለት ሲሆን፣ በሁለቱ አማራጮች መካከል ግን የማይታለፍ ልዩነት አለ፡፡ የመጀመሪያው የሳይንስ ምርምር መንገድ ሆኖ ሳለ ሁለተኛው ግን የዕምነት ማረጋገጫ ዓምድ ነው። ምሁራዊ ታሪክ የመጀመሪያውን ሒደት ሲከተል የዶ/ር ፍቅሬ ዓይነቱ የሁለተኛውን መንገድ ተከታይ ነው። በአጭሩ ዶ/ር ፍቅሬ የኢትዮጵያ ምሁራዊ ታሪክ ጸሐፊ ሳይሆኑ እመኑልኝ ብለው ለሚማጠኑለት የፈጠራ ተረት ጥብቅና የቆሙ የልብ ወለድ ደራሲ ናቸው።

ዶ/ር ፍቅሬ  ለአብዛኞች መደምደሚያዎቻቸው የሚተማመኑበት ጃንሸዋ  የተሰኘው መጽሐፍ፣ እሳቸው እንደሚሉት እውነት የጥንታዊ ቅርስ ግኝት መሆኑ  አልተረጋገጠም፡፡ ስለዚህ ለሚተቿቸው ነገሮችና ሐተታዎች አስተማማኝ ዋቢ ሊሆን  አይችልም፡፡ በሥነ አመንክዮ አነጋገር ይኸን በተመለከተ ደራሲው “ጥያቄውን የመለመን” (ቤጊንግኲዌስሽን) ተግባር ውስጥ ገብተዋል ማለት ነው። ስለ ሥነ አመንክዮ ለማወቅ ለሚፈልጉት  አንድ ክርክር ጥያቄውን ይለምናል የሚባለው  አስቀድሞ የክርክሩን መደምደሚያ ሲቀበል ነው፡፡  የአንድ ምሁር ዋና ኃላፊነት በመሠረታዊ እውነትና በሐሳዊ መረጃ መካከል ያለውን ልዩነት ፍንትው አድርጐ ማሳየት፣ አስተማማኝ ምንጮችን ከአጠራጣሪዎች ለመለየት የሚያስችሉ ምሁራዊ ውጤቶችን ማስገኘት ነው፡፡ በዚህ  አንፃር የዶ/ር ፍቅሬ ምንጮች ምሁራዊ ማስረጃ ከመሆን የራቁ የሐሰት ፈሊጦች ናቸው፡፡

ደራሲው በመሪራስ ሰነድ በሰፊው መመካታቸው ግልጽ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ግን ቴዎድሮስ ለተባለ የኢቢኤስጋዜጠኛ በርዕዮትቪዲዮ ፕሮግራም ቃለ ምልልሳቸው (ttps://www.youtube.com/watch?v=vOgiBKbvPl0ይመልከቷል) ይህንን የሚመኩበትን ጃንሸዋየተባለ የብራና ግኝት ጭራሽ አላየሁትም ብለው በግልጽ ተናዘዋል። ተዓምር ነው! ምሁር ነኝ የሚል ሰው እንዴት ያላየውን ሰነድ ዋቢ አድርጎ  ያቀርባል?

‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ዶ/ር ፍቅሬ በኩራት እንደ ምሁራዊ  መረጃ ከዘረዘሯቸውና ዋቢ አድርገው ካቀረቧቸው ማረጋገጫዎች ውስጥ ማንም ሊጽፈውና  ማንም ሊገድፈው የሚችለውዊኪፒዲያመጣጥፍ ይገኝበታል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም። ጀርመን ባለው ሃምቡርግ ዩኒቨርሲቲ መምህር በሆኑት በፕሮፈሰር ባይሩ ታፍላ አንደተጠቀሰው፣ የዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ የሌሎችን ደራሲዎች ሥራ በቅንፍ ውስጥ አለማስገባት ብቻ ሳይሆን፣ እንዲያውም የግርጌ ወይም የመጨረሻ ማስታወሻ ምስክርነት ሳያክሉ (ገጽ 207ን ይዩ) ኢትዮጵያናኢትዮጵያዊነትከተባለው የንቡረዕድ ኤርሚያስ ከበደ መጽሐፍ ስለ ንግሥተ ሳባ ታሪክ ቃል በቃል ተጠቅመዋል (ኢትዮሚዲያጃኑዋሪ 12 ቀን 2017)። እንዲሁም ፕሮፌሰር ባይሩ እንዳሳሰቡት፣ የአብርሃም ክንፈ ጽሑፍ በዶ/ር ፍቅሬ ‹‹የኦሮሞናየአማራእውነተኛውየዘርምንጭ››መጽሐፍ ውስጥ ያለቅንፍና ያለ አጣቃሽ ማስታወሻ ቃል በቃል ሰፍረው ተገኝተዋል፤ (በዚያውቦታይዩ)

በዓይናቸው አዩትም አላዩትም ዶ/ር ፍቅሬ በድረ ገጽ ሐተታቸው፣ ወሳኝ ምንጭ የሆነውን የመሪራስ የብራና ጽሑፍ መጽሐፈጃን ሸዋን በተመለከተ ጀበልኑባ (ኑቢያ) ተገኘ የሚሉትን ጥንታዊ የብራና ግኝት፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዘክር ስለመስጠት  ጉዳይ ዶ/ር ጳውሎስ ደኅንነቱን ማረጋገጥ ከቻሉ አግኚው መሪራስ ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ ናቸው ብለዋል፡፡ አሁን ነፍሳቸውን ይማረውና እኚህ ሰው በቅርብ ቀን ስላረፉ ወራሻቸው መጽሐፉን ለቤተ መዘክሩ ገፀ በረከት ካደረጉ ከድንቅነሽ ቅሪት ያላነሰ ልዩ ጥበቃ ይደርግለት ዘንድ ማረጋገጫ ለመስጠት እደፍራለሁ። ችግሩ መጽሐፉ ይህን ያህል እንክብካቤ የማያሻው ተዓማኒ በማስመሰል በመሪራስ የተቀነባበረ የደባ ጥንስስ መሆኑን በግዕዝና በሴም ቋንቋዎች ሊቅነት ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ የተመሰከረላቸው ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ ጥርጣሬያቸውን ከሰነዘሩ እነሆ ጊዜው ከርሟል። ይሁንና ዶ/ር ፍቅሬ የግል አባባሎቻቸውን ለመደገፍ ሁለት የግርጌ ማስታወሻዎችን ሲያሠፍሩ በአንደኛው ከ63ቱ 31፣ ከሁለተኛው ከ56ቱ 30 ምንጮች፣ በመሪራስ ምሁራዊ ሥልጣን ስም የሠፈሩ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ እንግዲህ የዶ/ር ፍቅሬ ግራ የሚያጋቡ አባባሎች ተቀባይነት ይኖራቸው ዘንድ ከሁሉ በፊት የመሪራስ የብራና መጽሐፍ እውነተኛነት መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ የመሪራስ ታላቅ ግኝት መጽሐፈጃንሸዋተገኘ የተባለበትን ቦታና ጊዜ ጠለቅ ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የተጻፈበት ጊዜ የተጻፈበት ፊደላት መልክና ቅርጽ መመርመር አለበት፡፡

ስለ መጽሐፈጃንሸዋ  ተዓማኒነት ለምን ይህን ያህል መጨነቅ ያስፈልጋል? የመሪራስ ሥራ አቀራረቡ እውነት መሳይ፣ ግን ሐሳዊ ቢሆንሳ? ምሁራዊ መቋሚያው  ምኑ ላይ ነው? ለዚህ ችግር ማሳያ ምሳሌ እንመልከት። እ.ኤ.አ. በ1983፣ ከ1932  እስከ 1945 ያሉትን ዓመታት የሚሸፍን የሂትለር የቀን ማስታወሻ ደብተር ተገኘ ተብሎ ወሬው የዘመናችን ታላቅ የታሪክ ግኝት ተብሎ በዓለም የመገናኛ አውታሮች  ተሰራጭቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ባለሙያዎች  በጥሞና መርምረው ሐሳዊ ግኝት ነው ሲሉ አሰናበቱት፡፡ በምርምር ጠቢባኑ ፍረጃ ዕፁብ ድንቅ ግኝት ተብየውን ለማቀነባበር በጥቅም ላይ የዋሉት ንጥረ ነገሮች እስከ ሂትለር  መጨረሻ ድረስ እንዳልነበሩ፤ አሁንም በተጨማሪ ሲፈትሹት ዘመናዊ አብራሂ አልትራ የሌት ብርሃን በተጻፈበት ወረቀት ላይ ተስተውሎ ተገኘ፡፡ ከዚህም በላይ የቀን ማስታወሻው መጠረዣ ናሙና በአንድ አቅጣጫ የብርሃን ማጉያ ሲፈተሽ፣ ዘመናዊ ሰው ሠራሽ ንጥረ ነገርን መያዙ ተደርሶበታል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ይህ አጠራጣሪ የመሪራስ መጽሐፍ እንደ አስተማማኝ ዋቢ ሆኖ ሊጠቀስ ይገባው ዘንድ ጥብቅ ምርመራ እንዲደረግበት መፈለጉ።

በአጭሩ ዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፋቸውን ለመጻፍ ያነሳሳቸው ምክንያት ምንም ይሁን ምን አጣቃሽ ምንጮቻቸው እውነታን ለማረጋገጥ ሠፈሩም አልሠፈሩም የአንጦርጦስ መቀመቅ ድክመቶች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

አንድ ነጥብ ልብ እናድርግ፡፡ በምሁራዊ አስተሳሰብ አግባብ ያለው ጠንካራ መከራከሪያ በማቅረብ ፈንታ ዶ/ር ፍቅሬ አዎንታዊ ስሜቶችን በመቀስቀስ፣ እንዲሁም ፍላጐቶችን በማነቃቃት፣ ከሕዝብ ስምምነት ለማግኘት አቤቱታ ያቀርባሉ፡፡ ይህ ግን በአመንክዮ እይታ፣ አንድ ነገር እውነት ነው ብለው ብዙዎች ሰዎች ስለሚያምኑበት እንዲሁ በዘወረደ መቀበልና መሠረታዊ አስተሳሰብን የማዛባት ስህተትን የሚጋብዝ ነው፡፡ በደራሲው አመለካከት በቀረበው ሐሳብ ላይ ሰዎች ጥያቄ እስካላነሱ ድረስ ነጥቡ እንደ እውነት ተደርጎ መወሰድ አለበት ማለት ነው፡፡ ይህ ዓይን እያየ፣ ጆሮ እየሰማ፣ አዕምሮ እያወጣና እያወረደ አደገኛ የማስተዋል ግድፈት መፈጸም ነው፡፡

ለምሳሌ ከኮርፐርኒከስና ከጋሊሊዮ ጋሊሊዮ በፊት፣ መሬት ዝርግና  የማትንቀሳቀስ የኮስሞስ ማዕከል መሆኗን፣ ለሕዋሶቻችን እንደሚመስለው ሁሉ ፀሐይ በዙሪያዋ እንደምትሽከረከር ምዕመኖቻቸው ይቀበሉ ዘንድ የሃይማኖት መሪዎች አጥብቀው ይለፍፉ ነበር፡፡ ለዚህ ነው በመጽሐፍ ቅዱስ አቀራረብና በነበረው እምነት ኢያሱ እግዚአብሔርን ፀሐይ ባለችበት እንድትቆም ያደረገውና ልመናው የተሳካለት፡፡ በዚያም እግዚአብሔር ፀሐይን ቀጥ ብላ ካለችበት እንድትቆም ሲያዛት እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን ለመበቀል በቁ ተብሎ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ሠፍሯል፡፡ (መጽሐፈ ኢያሱ 10፥13)፡፡  በጊዜው የነበሩ ከ90 በመቶ የሚሆኑት እስራኤላውያን በአገላለጹ ያመኑትና በሱም ደስተኞች እንደነበሩ በቀላሉ ልንገምተው እንችላለን፡፡ እስራኤላውያን በአገላለጹ  በማመናቸው ግን መሬት ዝርግና የማትንቀሳቀስ የኮስሞስማዕከል፣ ፀሐይም በዙሪያዋ ትሽከርከር ነበር ማለት አይደለም፡፡ ፀሐይ በመሬት ዙሪያ እንደምትሽከረከር የጥንት  ሰዎች ስላመኑም ይህ ግምት እውነት ሆነ ማለት አይደለም፡፡ በዚህ አመክንዮ ከሔድን ዘንዳ ብዙ ሰዎች ስላመኑበት በዶ/ር ፍቅሬ የቀረበውና ዒላማውን የሳተ አስተሳሰብ የመጽሐፉን መግለጫዎች ተገቢ ያደርጋቸዋል ማለት ተላላነትና የአዕምሮ መናዘዝ ምልክት ይሆናል፡፡

ዶ/ር ፍቅሬ የመጽሐፋቸው አንድምታ በምሁራን ዘንድ እንደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተቆጥሯል ይላሉ፡፡ በዚህ ብቻም አልተወሰኑም፡፡ ‹‹እውነተኞቹ ምሁራን›› መጽሐፉ በኢትዮጵያ ዜና መዋዕል በአርአያነት ነባር እምነትን ከመሠረቱ የፈነቀለ አዲስ የታሪክ ብልጭታ ነው በማለት ገምግመውልኛል እስከማለት ደፍረዋል፡፡ ዶ/ር ፍቅሬ ይህን የሚሉት እውነት ከልባቸው ነው? በእርግጥ እውነተኞቹ ምሁራን የእሳቸው መጽሐፍ የኢትዮጵያ ታሪክ አቀራረብ ፈር ቀዳጅና ተራራን የሚያንቀጠቅጥ ብለው ከጠረጠሩት፤ ያ ለውጥ ከእውነታ ወደ ልብ ወለድ፣ ከታሪክ ወደ ተሸመነ ተረት ማሸጋገሩን ሲጠቁሙ መሆን አለበት፡፡ እስቲ ይህን ለማረጋገጥ ታዋቂ የኢትዮጵያ ታሪክ መምህራንን ከብዙው በጥቂቱ እንጥቀስና የሳቸውን ሐሳቦች ይደግፉ እንደሆነ እንጠይቅ። ቀጥሎ የተጠቀሱት ምሁራን እውነት የዶ/ር ፍቅሬን ታሪካዊ ልብ ወለድ በመስካቸው ፈር ቀዳጅ ብለው ያምኑ ይሆን? እስቲ ተጠየቁ ኘሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፣ ኤፍሬም ይስሐቅ፣ መሳይ ከበደ፣ መሐመድ ሀሰን፣ ተሰማ ታኣ። አዎ፣ እስቲ ተጠየቁ! እናንተ የኢትዮጵያ ታሪክ ምሁራን ፣ ስለዚህ የተዛባ ሥራ ዝምታችሁን ሰብራችሁ ሐሳባችሁን ለግሱ። ይህን ማድረግ ደግሞ ኃላፊነታችሁም ነው።

ዶ/ር ፍቅሬ እኔ ለዘመናት ከኢትዮጵያ ውጭ እንደኖርኩና በዚሁም ምክንያት ኢትዮጵያ ካለው እውነታ በእጅጉ እንደራቅኩ ይተርካሉ፡፡ ነገሮችን በትክክል ለማስቀመጥ ያህል፣ እውነት ከአገሬ ርቄ ብዙ ዓመታት መቀመጤ አይካድም። በእኔ ግምት ዶ/ር ፍቅሬም ቢሆኑ እንዲሁ ለብዙ ዓመታት ውጪ ከርመዋል፡፡ የሆነ ሆኖ ከሳቸው የበለጠ ካገሬ የራቅኩ አይመስለኝም። ለምሳሌ በ1981 ዓ.ም. ጎብኚ ኘሮፌሰር ሁኜ እንዳስተምር በተባበሩት መንግሥታት ተልኬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎቴን አበርክቻለሁ፤ በዚያም ምሁራዊ ጥናት አድርጌያለሁ፡፡ እንዲሁም በስዊድን መንግሥት ድጋፍ በዚያው ዩኒቨርሲቲ ጐብኚ ኘሮፌሰር ሆኜ በ2004 ዓ.ም. አስተምሬያለሁ፡፡ በተጨማሪም፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጋብዤ ኤምፒኤችዲ. የድኅረ ምረቃን ፕሮግራም ለማቋቋም በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ካሉት ብዙ ተሰጥዎ ካላቸው ታዋቂ ምሁራን ጋር በሰፊው ተካፍያለሁ። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የምሁር አበል እየከፈለኝ የፖለቲካ ሳይንስ የፒኤችዲተመራቂዎችን ውጤት እንድገመግም ተመድቤ ሠርቻለሁ። ዩኒቨርሲቲዬ እየከፈለኝ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ በርካታ ምርምሮችን አካሂጃለሁ፡፡ ይህንንም ለማሟላት በዓመት ቢያንስ ሦስት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሄጃለሁ፡፡ እናም በ2008 ዓ.ም. ለአራት ወራት አዲስ አበባ ነበርኩ፡፡ ይህም በዌስተርን ሚሽገን በተደገፈና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተደረገ ምሁራዊ ስብሰባ ላይ የጥናት ወረቀት ለማቅረብ ነበር፡፡ በዚያም በማኅበረሰብ ጥናት ፎረም ግቢ ሳለሁ ዶ/ር ፍቅሬ በሌላ ቦታ መጽሐፋቸውን እየፈረሙ በመሸጥ ተጠምደው በነበረበት ሰዓት፣ ባለፈው የግምገማ መቅድም እንደጠቀስኩት፣ እኔ ደግሞ ከኘሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ጋር ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ እየተወያየሁ ነበርኩ፡፡ ስለዚህ እኔም ከአገሬ እውነታዎች ከእሳቸው በበለጠ የራቅኩ አይደለሁም፡፡

ለወጣትና በማቆጥቆጥ ደረጃ ላይ ላሉ ምሁራን የሰጠሁትን ምክር በተመለከተ አዎ እነሱን ያልተረጋገጠ መረጃ ተጠቂዎች ከመሆን ለማዳን ስል በምርጫ ሞግዚታዊ ሚናን ለመጫወት ወስኛለሁ፡፡ ለበርካታ አሠርት መምህር ሆኜ የኖርኩ እንደመሆኑ መጠን፣ በዚህ ጊዜ የማስተማር ዓላማዬን አለማቋረጤን አንባቢዎች እንዳትስቱት በማያቋርጥ ዘዴ በማንኛውም ረገድ ወጣቱን በጥብቅ ለመምከር ቆርጫለሁ፡፡

ሟቹ ሱማሌያዊ ወዳጄ፣ የረትገርስ ዩኒቨርሲቲ ኘሮፌሰር የነበረው ሰይድ ሳመታር፣ እናንተ የኢትዮጵያ አስተማሪዎች ወጣቶቻችሁን የብዙ ሶማሌ ወንዶች አንጐልን ካቃወሰው ጫት ማራቅ አለባችሁ ይል ነበር፡፡ ምሁራዊ የሥነ ጥበብ ጥናቶች እንደደመደሙት ጫት የአንጐል ነቀርሳ ብቻ ሳይሆን ብዙ ተጨማሪ የጤና ጠንቅ እንደሚያስከትል ተረጋግጧል። ይበልጥ የሚያሳዝነው አስተማሪዎች በጥንቃቄ ካለመከታተላቸው የተነሳ፣ ከወዲሁ ብዛት ያላቸው ከባድ የጫት ሱሰኞች የአንጐል የደም ሐረግ የተዛባባቸውና ትስስሩ የተቃወሰባቸው ለክፉ የአዕምሮ ደዌ ተዳርገዋል፡፡ ከእነዚህ ጥቂቶች ያሉት የአገሪቱን ሆስፒታሎች ያጨናንቃሉ፤ የቀሩት ስድ ተለቀው በመረንነት ተግባር ላይ ተሰማርተዋል፡፡ እንደዚህ ያሉ ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ እንገንዘብ፡፡ ምክንያቱም የሚኖሩት በሁለመናው በተለየ ኮስሞስ፣ ያለ የሚመስል ግን የሌሉ ድምጾችን የሚሰሙበት የዝንጋኤ ዓለም ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ምሁር ነኝ ባዮች ከመካከላቸው ፈንጠር ብለው የቆጡን የባጡን የሚቀባዥሩት። ሌላ ዓለም ውስጥ ስለሚኖሩ የሚሉትን ሁሉ ያምኑበታል። ችግሩ ሌሎችን ግራ ያጋባሉ። ዋና መድኃኒቱ ታዳጊዎችን በጨቅላ ዕድሜአቸው ከጫት ማራቅ ብቻ ነው። አስተማሪዎች እንደመሆናችን እኛ ወጣቶቻችን ከዚህ ዓይነቱ አዋኪ አደጋ ለመጠበቅ በብርታት መሥራት ይኖርብናል፣ ይህን ማድረግም ኃላፊነታችን ነውና፡፡

ዶ/ር ፍቅሬ የኦሮሞና የአማራ ጥንታዊ የጋራ ቋንቋቸው ‹‹ሱባ›› ነው ይሉናል፡፡ ግን ይህ ጭራሽ ያልነበረ መቶ በመቶ የመሪራስና የዶ/ር ፍቅሬ ፈጠራ መሆኑ አያጠራጥርም። ወደ መሠረቱ እንሒድና በትክክል እንገንዘብ። ምሁራዊ ጥናት እንደሚያሳየው ኩሽና ሴም ከአንድ አባት የሚወለዱ ሁለት ቅርንጫፎች የሆኑት ከአራት ሺሕ ዓመታት በፊት ጀምሮ ነው። የፈለቁትም ከአፍሪቃ ነው። በምሥራቅ፣ በሰሜን በአፍሪቃ ቀንድ እንዲሁም በምዕራብ ኤስያ ያሉት ቋንቋዎች በሙሉ አንድ ግንድ እንዳላቸው ከተረጋገጠ መቶ ዓመታት አልፈዋል። እነዚህም ቋንቋዎች አፍሮ-ኤሲያቲክ ይባላሉ። የኢትዮጵያም ቋንቋዎች በሙሉ እዚህ ውስጥ ይጠቃለላሉ። የካም ወይም የኩሽ ቋንቋዎች የጥንቱን የግብፅ ቋንቋ ጨምሮ፣ ኑቢያ በርበር፣ አገው፣ ቤጃ፣ ኦሮሞ፣ ሶማሊ፣ አፋር ሳሆ፣ ብሌን የማሊ ቱኣሬግ ታሜሼክ፣ የቶጎ ካቢዬ፣ ቻሚርን፣ ያጠቃልላል። የሴም ቋንቋዎች ደግሞ ግእዝ፣ ትግረ፣ ትግርኛ፣ አማርኛ፣ ጉራግኛ፣ ዓረብኛ፣ ዕብራይስጥ፣ አራማይስጥ፣ ባቢሎናዊና ኣሶራዊ፣ አዶማዊ ሞኣባዊ፣ ካነዓናዊና ፊንቂኣዊን ያጠቃልላል። ዛሬ አራት አምስተኛ የኩሽ ቋንቋና የሴም ቋንቋ ተናጋሪዎች በአፍሪቃ ክፍለ ዓለም ነው የሚኖሩት። የኩሽ ቋንቋ በአፍሪቃ ብቻ ሲወሰን የሴም ቋንቋ በአፍሪቃም በደቡብ ኤሲያም ተስፋፍቷል። የቋንቋ ጠቢባን አንደሚሉት ሁለቱም ቅርንጫፎች የተኮተኮቱት ኢትዮጵያን ማዕከል ባደረገ በአፍሪቃ ቀንድ ነው። ሁለቱም ቋንቋዎች ከኢትዮጵያ አካባቢ ተነስተው ነው ወደ ሰሜን አፍሪቃና ወደ ኤሲያ የተስፋፉት።

ከዚህ በላይ የተዘረዘረው ሁሉ የማይካድ እውነታ ሲሆን፣ ዶ/ር ፍቅሬ አንድ ከባድ ክህደት ፈጽመዋል፡፡ በፈጠራ ሥራቸውም የአገርን ታሪክ በአያሌው አዛብተዋል። አንባቢዎች በሕዝብ ላይ የተወነጨፈውን ቧልት የኦሮሞናየአማራእውነተኛውየዘርምንጭተብሎየተጻፈውንየዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳን መጽሐፍ ገጽ 67 ግለጡና ተመልከቱ። አስገራሚና አስቂኝ በሆነ ዘዴ ትግሬዎችን ከአክሱም ሥልጣኔ ማስወገድ ብቻ ሳይሆን፤ ምንም የጽሑፍ ሆነ የአፈታሪክ ትውፊት በሌለበት በግድየለሽነት የተፈጠሩ፣ ተሰምተው የማይታወቁትን እንደ ጉራጌዎች አደርጋለሁ ብለው ሰባት ልብ ወለዳዊ ነገድ ፈጥረውላቸዋል፡፡ እነዚህም የኢትዮጵያን ፊደል ‹‹ረ››ን መሠረት በማድረግ የተራቡ አዲስ የጐሳ ስያሜ ናቸው፡፡ በዚህ አሳሳች ፈጠራ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ፊደላት፣ ማለት (ትግ)ን እንዳሉ በመጠቀም የግዕዙን አራቢ 7 ፊደል ተራዎች ማለት፣ ግዕዝ፣ ካዕብ፣ ሣልስ፣ ራብዕ፣ ምስ፣ ሳድስ፣ ሳብዕ የመጨረሻዎቹን በመለወጥ ብቻ ከዚያም ‹‹ትግ›› እና ሪ፣ር፣እያለ በዚሁ ቅደም ተከተል ተሰምተው የማይታወቁ ሰባቱን ብርቅዬ የትግሬ ጎሣዎች ፈጥረው አርፈዋል፡፡ በዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ የተዘረዘሩት፣ ከላይ ለመግለጽ በተሞከረው ሁኔታ የሰባቱ የፈጠራ የትግሬ ጐሳዎች፡ ትግረ፣ትግሩ፣ትግሪ፣ትግራ፣ትግሬ፣ትግርእናትግሮሆነውእናገኛቸዋለን፡፡

ዶ/ር ፍቅሬ ሆይ ይህ አስቂኝ የነገድ ራዕይ መሐደምት እንዴት ነው የተገለጠልዎት? ለመሆኑ የአንዱን ታላቅ የኢትዮጵያ ነገድ ብሔራዊ ታሪክ በሚያስገርምና በሚያሳዝን ሁኔታ ሲያመሰቃቅሉ ስመ ገናናውንና ታላቁን የአገራችንን ሕዝብ እንዴት ቢንቁት ነው? ቁጭ ብለው የፈጠራ ነገድ የፈጠሩለት እንዴትስ ተገቢውን ክብር ለመንፈግ ቢነሳሱ ነው? ምን ዓይነት ትምክህት ነው በሕዝብ ላይ መቀለድ?

የሚገርመው ነገር ደራሲው ‹‹የኦሮሞእናየአማራእውነተኛውየዘርምንጭ››በተባለው መጽሐፋቸው አዲስ ጐሳ ሲፈጥሩ በዚህች ትንሽ ዘዴ የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የምሁራኑን አዕምሮአዊ ብቃትና የአመክንዮ ደረጃ ለመፈታተን መሞከራቸው ነው፡፡ እንዲሁ በአጭሩ ለመደምደም በዚህ ዕርምጃቸው ብንመዝናቸው ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ ግጉይ ግለሰብ ናቸው ለማለት ያስደፍራል። አለዚያ ደግሞ ከመጠን ያለፉ ደፋር ሰው በመሆናቸው ሳይውል ሳያድር የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርባቸዋል!

ይቀጥላል

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በካናዳ ሞንትሪያል በሚገኘው ኮንኮርዲያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው pmilkias@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

Standard (Image)

‹‹ሕዝብ ሀብት ነው›› የሚለው አነጋገር እስከምን ድረስ ነው?

$
0
0

በሮቤ ባልቻ

ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረ አንድ የመካከለኛው ምሥራቅ ንጉሥ፣ ባለሟሎቹ በመላ አገሪቱ ተዘዋውረውና ሕዝቡን ቆጥረው፣ ውጤቱን እንዲያቀርቡለት አዝዞ እንደነበር በብሉይ መጽሐፍ ተጽፏል፡፡ ባለሟሎቹ ግን ‹‹ሕዝብ መቆጠር የለበትም፣ ይህ ከንጉሡ ሐሳብ ይራቅ›› ብለው ቢከራከሩም የንጉሡ ቃል ፀና በመጨረሻም ቆጠራው ተካሄደ ባለሟሎቹ ሪፖርታቸውን አቀረቡ፡፡ ‹‹ሰይፍ መምዘዝ የሚችል ጎልማሳ›› ይህን ያህል ብለው ጀምረው ሕፃናት፣ ሴት፣ ወንድ፣ ሽማግሌውን ከፋፍለው በማስቀመጥ ለንጉሡ አቀረቡ፡፡

ዘመኑ ግጭትና ጦርነት በአካባቢው የሰፈነበት፣ መሬት ነጥቆ መያዝ የበዛበት ስለነበር የንጉሡ ፍላጎት ‹‹ሰይፍ መምዘዝ›› የሚችለውን ጎልማሳ ብዛት የማወቅ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ በዘመኑ ቋሚ የሚባል ሠራዊት ስለሌለ፣ ከወራሪ ጠላት ለመከላከልና ሲያስፈልግም ለማጥቃት አቅምን መፈተሹ ብልህነት ነበር፡፡

ዛሬ አገሮች የሕዝባቸውን ቁጥር በየዕድሜ ክልሉና ፆታ መድበው ማወቅ የሚፈልጉት እንደ ጥንቱ ዘመን የጦር ሜዳ አቅማቸውን ለማጤን አይደለም፡፡ የተፈጥሮ ሀብቶቻቸውን አጠቃቀም ሚዛናዊ ለማድረግ የማኅበራዊ አገልግሎት አሰጣጣቸውን ተደራሽነት ለመገምገምና፣ ይኼ ተዛብቶ ሲገኝ ደግሞ በዕቅድ ላይ የተመረኮዘ አፋጣኝ ማስተካከያ ለማድረግ ነው፡፡

 

በኢትዮጵያም የሕዝብ ቁጥር ማወቅ አስፈላጊነት ታምኖበት ጉዳዩን የሚከታተል መሥሪያ ቤት ከተቋቋመ ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ በዚሁ መሥሪያ ቤት ቆጠራ ላይ ተመሥርቶ ከሃምሳ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ሃያ ሚሊዮን እንደሆነ በየትምህርት ቤቱ ሲነገረን ነበር፡፡ እኛ የዚያን ጊዜ ተማሪዎች ዛሬ አዛውቶች ነንና የአሁኑ ቁጥራችን ከመቶ ሚሊዮን በላይ ማሻቀብ ሳያስገርመን አይቀርም፡፡

በዘመኑ ለነበርን ሃያ ሚሊዮን የሕዝብ ቁጥር ብዙ ነው፡፡ የአንድ ሚሊዮን ብር ቃል መስማትም እንግዳ ነበር፡፡ እንደ ሕዝቡ ቁጥር ኢኮኖሚውም ዝቅ ያለና በዝግታ የሚሄድ ነበር፡፡ የሕዝብ ብዛቱ ዝቅተኝነትና የመግዛት አቅሙም ደካማ መሆን የሚፈለገውን አገራዊ ምርት በቀላሉና በንፅፅር በዝቅተኛ ዋጋ እንድናገኝ ረድቶናል፡፡ የዚያን ዘመን ሰዎች ‹‹ . . ደጉ ዘመን . . . ››፣  ‹‹ . . ዱሮ ቀረ . . .  ›› ብለን አንዳንዴ የምናስበው ብሶት ከዚያ የመጣ ይመስላል፡፡

ምንም እንኳን የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚና የገበያ ሥርዓት በአገራችን ላይ የሚያሳርፈው ጫና ቀላል ባይሆንም ዛሬ በምድራችን ላይ ያለው ለውጥና ዕድገት ከዱሮው በብዙ እጅ የላቀ ነው፡፡ የማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፎች ብዛትና የኢኮኖሚ መስኮቹ ስፋት የጎላ ልዩነት እንዳላቸው በግልጽ የሚታይ ነው፡፡

ሆኖም ግን ለውጡና የሚካሄደው የኢኮኖሚ ዕድገት ከከፊሉ ሕዝብ በግልጽ የሚታይ አይደለም፡፡ የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መሄድና የምርትና የተፈጥሮ ሀብቶች አጠቃቀም ውስንነት ፍሬው ለሁሉም እኩል እንዳይታይ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖር፣ መልካም አስተዳደር አለመስፈን የችግሮቹን ስፋት ያገዝፉታል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት የአገራችንን ሕዝብ ቁጥር ሚዛናዊነት የሚከታተል፣ ለኅብረተሰቡም ስለቤተሰብ ምጣኔ አስፈላጊነት ትምህርት የሚሰጥና ቅስቀሳ የሚያካሄድ መሥሪያ ቤት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ መሥሪያ ቤቱ የአጭርና በረዥም ጊዜ ፖሊሲዎችን በመቅረፅና በመንግሥት በማስፀደቅ ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያካሄድ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ሥር የሚገኘውና የሥነ ሕዝብ ጉዳይ የሚመለከተው ድርጅትም ድጋፍ በማድረግ አብሮ ይሠራ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ይኼ መሥሪያ ቤት ራሱን ችሎ ባይቆምም በጤና ጥበቃ ሥር ተጠቃሎ እንደ አንድ ዘርፍ የሚንቀሳቀስ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ በአሁኑ የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ በአገር ደረጃ የሥነ ሕዝብ ፖሊሲን ውጤታማ ለማድረግ ከክልሎች ጋር በቅርበት ምን ያህል እየሠራ እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በተጨባጭ የሚታየውና እርግጠኛ መሆን የሚቻለው ግን ፈጣን የሕዝብ ቁጥር መጨመር እየተስተዋለ መሆኑ ነው፡፡ ዛሬ በአዲስ አበባ በዙሪያዋ የሚንቀሳቀሰውን ሕዝብ የሚያስተናግድ የእግረኛ መንገድ እየጠበበ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ከተሞችና ክልሎችንም ብንመለከት የሕዝቡ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

‹‹ሕዝብ ሀብት ነው!›› የሚለው አነጋገር የአገሪቷን የተፈጥሮ ሀብት የኢኮኖሚ ደረጃና የሰው ሀብት አጠቃቀም ብቃትን ከግምት ያስገባ ሲሆን ነው፡፡ 

ቁጥሩ እየጨመረና እየበዛ የመጣ ዜጋ፣ በገጠርም ይሁን በከተማ ብቁ የመሠረታዊ ፍላጎት፣ አገልግሎቶቹ እንዲሟሉለት ይፈልጋል፡፡ ከምግብና መጠለያ ሌላ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና አገልግሎት የሥራ መስክና ሌሎችም እንዲሟሉለት ይፈልጋል፡፡ ቁጥሩ በፍጥነት እየጨመረ ለሚመጣው ዜጋ ደግሞ እነዚህን ፍላጎቶች ለማሟላት አገር አቅም ስታጣ ተስፋ መቁረጥ ይመጣል፡፡ ተስፋ መቁረጥ ደግሞ ውጤቱና መዘዙ ብዙ ነው፡፡ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የኮረብታዎችና ከፍታዎች ዛፎችና ቁጥቋጦዎች ተመንጥረው፣ ለቤት መሥሪያና ለእርሻ ተግባር እየዋሉ መሆናቸውን የምንመለከተው ለዚህ ነው፡፡ ጨፌያማና ረግረግ የነበሩ፣ ቄጠማና ሳር እየታጨደ ለተለያየ አገልግሎትና ለከብት መኖ ይዘጋጅባቸው የነበሩ በርካታ የአገራችን አካባቢዎች ዛሬ ላይ ደርቀዋል፡፡ በዙሪያቸው የነበሩ ተክሎችና ዛፎች ያላግባብ እየተመነጠሩ ወደ እርሻ ማሳነት ስለተቀየሩ መሬት ርጥበት ማቆየትና ውኃ መያዝ አልቻለችም ነበር፡፡ የእርሻ ማሳና የግጦሽ ሥፍራዎች ማስተናገድ የሚችሉት የሕዝብ ቁጥር በአየካባቢው ይታወቃል፡፡ የሚወለደው አዳዲስ ትውልድ በነበረው የገጠር መሬት መስተናገድ የማይችልበት ሁኔታ ሲፈጠር፣ ጥብቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን መጠቀም ይጀምራል፡፡ ይህ ደግሞ ለአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት ጥፋት ይዞ ይመጣል፡፡

ዛሬ በአንዳንድ ክልሎችና ዞኖች አካባቢዎችን መልሶ ለማልማት ብርቱ እንቅስቃሴዎች ሲካሄዱ ይታያሉ፡፡ ይህ መልካም የበለጠ ሊተጋበት የሚገባ ተግባር ነው፡፡

በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ጋራው ሸንተረሩ እየተመነጠረ ወደ እርሻ ማሳነትና ቤት መሥሪያ ሲውል ከአዲስ አበባ ቅርብ ርቀት ላይ መመልከት ይቻላል፡፡ ከሚካሄደው የመልሶ ማልማት ጥረት በተቃራኒ የሚስተዋሉ ተግባራትም አሉ ማለት ነው፡፡

የሕዝብ ቁጥር አካባቢዎች ሊያስተናግዱ ከሚችሉት በላይ ሆኖ እያደገ ከመጣ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ያላግባብ መጠቀም ይከተላል፡፡ ይኼ በአገራችን መታየት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

ሌላው ደግሞ ከትውልድ አካባቢው እየለቀቀ ወደ ከተሞች የሚሰደድ የኅብረተሰብ ክፍል ይበዛል፡፡ በከተሞች አካባቢ ያሉ ኢንዱስትሪዎች፣ ፋብሪካዎችና ሌሎች የልማት ተቋማት የሰው ኃይል መፈለጋቸው አይቀርምና መልካም ነው ሊባል ይችላል፡፡ ወደ አዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች ከየክልሉ የሚገባው የሰው ኃይል ቁጥር ግን ሥራው ከሚፈለገው በላይ ነው፡፡ ሥራ በማጣት በየከተሞች የሚንገላታውና በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋል ያልቻለው የሰው ኃይል ባክኖ የምንመለከተው በአብዛኛው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ሌላው የታዳጊ ሕፃናት በአዲስ አበባና በሌሎችም የክልል ከተሞች በርክቶ መታየት ነው፡፡ የሕፃናቱ ዕድሜ ሲታይ የትምህርት፣ የቤተሰብ ክብካቤና መልካም አስተዳደግ ማግኘት የሚገባቸው ዕድሜ ላይ እንዳሉ እንመለከታለን፡፡ ይኼ ሳይሆን ቀርቶ፣ በወላጆች ፈቃድ ወይም በሌላ መንገድ ወደ የከተሞች እየፈለሱ የማይገባ ሕይወት እየኖሩ ነው፡፡ አንዳንዶቹም ለተለያዩ ችግሮች ሲዳረጉ ይታያሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ያገኙትን ትናንሽ ሥራዎች እየሠሩ ለመኖር ሲጣጣሩ ይታያሉ፡፡ ቤተሰብ ከስድስት እስከ አሥራ አንድ ዓመት ዕድሜ ክልል ያሉትንና በየከተሞች የሚታዩትን ሕፃናት ልጆቹን ለምን ወደ ከተሞች ይለቃል? ብለን ስንጠይቅ በአብዛኛው ምክንያቱ የአቅም ችግር ወይም ድህነት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ማሳደግ ከሚችለው በላይ እያንዳንዱ ቤተሰብ ልጅ እየወለደ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በርግጥ በየአካባቢው የተሟላ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ በግርድፉ ግን በመጓጓት የወለደውን አንድ ሁለት ልጁን ከቤት ወጥቶ እንዲለየው የሚመርጥ  ወላጅ አይኖርም፣ ቢኖርም በጣም ጥቂት ነው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡

ፌዴራል መንግሥትና ክልሎች የሥራ ኃይል የሆነው ወጣቱን ክፍል ሥራ ፈጣሪና በአገሪቱ ልማት ተሳታፊ እንዲሆን የሚያካሂዱት ጥረት ይታያል፡፡ ጥራቱ የሚደገፍና በስፋትም መቀጠል የሚኖርበት ነው ብሎ አስተያየት መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ግን ከአገሪቱ የሕዝብ ብዛት ከግማሽ በላይ ቁጥር ከያዘው ወጣት ምን ያህሉን ማገዝ ይቻላል? ነው ጥያቄው፡፡

የአገር ኢኮኖሚና ሥራ ላይ እየዋለ ያለው የተፈጥሮ ሀብት፣ ሥራ ፈላጊውንና ዕውቀቱ እና ክህሎቱ ያለውን ኃይል በስፋት ማቀፍ የሚችል አይደለም፡፡ በአገሪቱ ያለው የሥራ ዕድል ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር መጣጣም ሲሳነው፣ እያንዳንዱ ሰው አማራጭ የመሰለውን ያልተገባ ዕርምጃ ወደ መውሰድ ይመለከታል፡፡

ዛሬ መንግሥታዊ ተቋማትና ሕዝቡ ሊቋቋሙት የሚሞክሩት ሕገ ወጥ ስደትና የሰዎች ዝውውር ተግባር የማይመለከተው ይህን ነው፡፡ በእርግጥ የአገሪቱ የተፈጥሮ ሀብት መጪውን ትውልድ የማስተናገድ አቅም ገና አለው ሊባል ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ዕውቀት፣ ክህሎትና የኢኮኖሚ አቅም በበቂ ሳይኖር አገር ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በብቃት መጠቀም አይቻልም፡፡ ዛሬ ወጣቱ ባለው የሙያ መስክ በኅብረት እየተደራጀ የራሱን የሥራ መስክ እንዲመሠርት መንግሥት ያበረታታል፡፡ የመሥሪያ ቦታና መነሻ ብድር ፈንድም ተዘጋጅቶለታል፡፡ ይህ መልካም ጅምር ነው፡፡ ብዙ ቁጥር ያላቸው ወጣቶችም በዕድሉ ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል፡፡ ዕውቀቱ፣ ክህሎቱና ፍላጎቱ ላላቸው ይኼንን ዕድል በአገር ደረጃ በስፋት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በየመስኩ ሥልጠናዎችና ማበረታቻዎች መስጠትም ጎን ለጎን መሄድ ያለበት ነው፡፡ በተለይም ወደ ዋና ከተማው የሚደረገውን ፍልሰትና ወደ ውጭ የሚደረገውን ሕገ ወጥ ስደት ለመቀነስ ክልሎች የሥራ ዕድሎችን በስፋት እንዲከፍቱ ብዙ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ኢንቨስትመንት በክልሎች እንዲስፋፉ መሠረታዊ የልማት አውታሮች የመዘርጋቱ ሥራ ተጠናክሮ መካሄድ ይኖርበታል፡፡ ዛሬ ያለውን የሰው ኃይል ፀጋ በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል አድካሚና ሰፊ ሀብት የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል፡፡ በሙያዊ ጥናት ከታገዘ ግን ያለው እምቅ የሰው ኃይል ለዕድገት እንጂ ለድህነትና ለስደት እንደማይውል ተስፋ አድርጎ በጥንካሬ መሠራት ያስፈልጋል፡፡

ሐሳቤን ለማጠቃለል ለወደፊቱስ ምን መደረግ አለበት? በሚለው ነጥብ ላይ ጥቂት አስተያየቶች ልስጥ፡፡

የቤተሰብ ምጣኔ ትምህርቶችን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች የሚያስተላልፉ መንግሥታዊና የግል ድርጅቶች በአገር ውስጥ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በሬዲዮና በቲቪ የሚሰጡዋቸውን መልዕክቶች አልፎ አልፎ እንከታተላለን፡፡ እነዚህ ድርጅቶች በዚህ ብቻ ባይወሰኑና ሕዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ለጥቂት ደቂቃዎች መድረክ እየተሰጣቸው መልዕክቶች የማስተላለፍ ልምድ ቢያዳብሩ ይረዳል፡፡

በክልሎችና በገጠር መንደሮችም ጭምር የተቀናጀ ሥራ በየቋንቋው መሥራት የሚቻልበት ሁኔታ ቢታሰብበት፣ ካለም ቢጠናከር መልካም ነው፡፡ የየአካባቢውን ሕዝብ ባህልና እምነት በማይነካ መልኩ መልዕክቶች እንዲተላለፉ የሃይማኖት አባቶችና የአካባቢ ሽማግሌዎች በቂ ግንዛቤ ጨብጠው፣ የሐሳቡ ተካፋይ  እንዲሆኑ ማስቻልም ጠቀሜታ አለው፡፡ የመልዕክቱ ዋና ማጠንጠኛ ሊሆን የሚገባው የትዳር ጓደኛሞች መውለድ ያለባቸው የልጆች ቁጥር በአግባቡ ማሳደግ የሚችሉትን ያህል ብቻ እንዲሆን የምክር አገልግሎትና ትምህርት መስጠት ነው፡፡ ይህ አገልግሎት በአንዳንድ ሥፍራዎች እየተካሄደም ቢሆን፣ መዳበርና መስፋፋት ይኖርበታል፡፡

ይህንን ትምህርትና አገልግሎት ለአብዛኛው ሕዝብ ማዳረስ በጽሑፍ እንደምገልጸው ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ በቂ በጀት፣ የሠለጠነ የሰው ኃይልና ከልብ ለዓላማው ስኬት መሠለፍን ይጠይቃል፡፡ በተለይም ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ የአመራር አካላትን ይህንን ሥራ ወደ ተግባር ለመቀየር ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል፡፡

ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ቤተሰቦች ባሉባቸው አካባቢዎች የጎልማሶች ትምህርት በበጎ ፈቃደኞች ድጋፍ ተስፋፍቶ እንዲቀጥል ሁኔታዎች መመቻቸት ይኖርባቸዋል፡፡ በቤተሰብ ምጣኔ ላይ የሚዘጋጁ የበራሪ ወረቀቶችና ፓምፍሌቶች ኅትመት ትኩረት ሊያገኙ ይገባል፡፡ ለቤተሰብ በቂ ትምህርት፣ ቅስቀሳና ተፈላጊዎቹን አገልግሎቶች የሚያዳርሱ ባለሙያዎች በብቃት መሠልጠንና መሰማራት ይኖርባቸዋል፡፡

ይህንን አገልግሎት ለብዙኃኑ ሕዝብ ለማዳረስ ጠንካራ አመራር ሊሰጥ የሚችል ባለበጀት የሥነ ሕዝብ ቢሮ ከአሁኑ በተሻለ መልኩ መልሶ ማደራጀት ወይም ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

ከአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅምና የዕድገት ጉዞ በጣም በፈጠነ መልኩ የሕዝብ ቁጥር መጨመሩን ከቀጠለ ጉስቁልናና ድህነት የሚለቀን አይመስልም፡፡ ቤተሰብ ልጆች አፍርቶ ለማሳደግ አቅም ከሌለው፣ መንግሥታዊ ተቋማትም የሚሰጡት ድጋፍ ሁሉን ተደራሽ ለማድረግ አቅሙ ከሌላቸው፣ ዛሬ የምናየው ችግር እየተባባሰ ይሄዳል፡፡ የሕፃናት ወደ ከተሞች ስደት፣ የወጣቶች ለሕገ ወጥ ደላሎች ሴራ መጋለጥና መንከራተት ተንሰራፍቶ ይቀጥላል፡፡

አገር አቅሟን መጥና የሰው ሀብት ማፍራት አለባት፡፡ ልትንከባከበውና ልታሳድገው የማትችለውን የሰው ቁጥር ያለበቂ ምክርና የቁጥጥር አገልግሎት ዝም ብሎ ማፍራቱ የሚያስከትለው ጎጂ ውጤት ሊታየን ይገባል፡፡

በኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚፈጠር ሕዝብ በቂ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክብካቤ አግኝቶ፣ ሰብአዊ ክብሩ ተጠብቆ በየአካባቢው የሚኖርበት ዘመን መምጣት አለበት፡፡ እዚያ ዘመን ላይ ለመድረስ ደግሞ የጉዞው መጀመሪያ ከአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ አቅም ጋር የሚጣጣም የሕዝብ ቁጥር መኖር ነው፡፡ ይኼ አቅጣጫ ሳይዘነጋ ብርቱ ትኩረት ሊያገኝ ይገባል፡፡ ጋራውና ሸንተረሩ የውበት፣ የልምላሜ፣ የምንጮች መፍለቂያ ይሁኑ፤ መጪው ዘመን የተመጠነ የሕዝብ ቁጥር ታይቶ፣ ሁሉም ዜጋ መልካም ኑሮና ሕይወት እንዲያገኝ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በስፋት ይሠራበት፡፡

በየመስኩ የሠለጠኑ ባለሙያዎችም የተሻለ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት በምድሪቱ እንዲኖር የድርሻቸውን ያለመሰልቸት ሊወጡ ይገባል፡፡ ይህ ሁሉ ግቡን ሊመታ የሚችለው ግን መንግሥት በቂ ትኩረት ለዚህ አካባቢ ሲሰጥ ነው፡፡ ዘርፉ በበቂ በጀትና ዕቅድ እንዲመራ በተለይም የመስኩ ባለሙያዎች መንግሥትን የማሳመንና አብሮ የመሥራት ትልቁን የኃላፊነት ድርሻ መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡     

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

     

 

Standard (Image)

ሕገ መንግሥቱና የአዲስ አበባ ፈጣን ዕድገት

$
0
0

 

በመታሰቢያ መላከሕይወት ገብረክርስቶስ

በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሲናገሩ ‹‹እኔ ለአዲስ አበባ ጉዳዬም አይደል፣ ለሐዋሳ ጉዳዬም አይደል፣ ለአዳማ ጉዳዬም አይደል፣ እኔን የሚያሳስበኝ የገጠሩ ሕዝብ ኑሮ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡ ይህንን የተናገሩት በመጀመሪያዎቹ ጥቂት የሥልጣን ዘመናቸው ላይ ነበር፡፡

ከላይ የተጠቀሰው አባባል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተናገሩት በርካታ ዓመታት በኋላ፣ ዛሬ በተጨባጭ በመላው ኢትዮጵያ በክልልም ሆነ በከተማ ደረጃ የሚታየው ዕድገት በየጊዜው በመንግሥትም ሆነ በምሁራን መገምገሙ ለሰላምም ለሁሉም ነገር በእጅጉ ጠቃሚ ነገር ይመስለኛል፡፡

ባለፉት 26 ዓመታት በአዲስ አበባ የታየው ዕድገት ከመላው አገሪቱ ዕድገት ጋር ሲነፃፀር ምን ይመስላል? ወደፊትስ እንዲህ መቀጠል አለበት ወይ? የሚለው ጉዳይ በእኔ እምነት ከሁሉም በላይ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡

አዲስ አበባን ልዩ ከሚያደርጋት ባህርይዋ አንዱና ዋነኛው ከአምስት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ እንደሚኖርባት መታመኑ ሲሆን፣ የሚቀጥለው ትልቁ ከተማ አዳማ ደግሞ የሕዝብ ቁጥሩ ከ400 ሺሕ ያልዘለለ ነው፡፡ ሌሎች በኢትዮጵያ ያሉ ከተሞች የሕዝብ ቁጥራቸው ከአዲስ አበባ ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ያነሰ ነው፡፡

በተለይ ከላይ እንደተጠቀሰው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሕአዴግ መሪ እንዳስቀመጡት ሳይሆን፣ የተገላቢጦሽ አዲስ አበባ እንዴት ልታድግ ቻለች የሚለውን ጉዳይ ማንሳት ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

የአዲስ አበባ ዕድገትና የገንዘብ እጥበት

በአገራችን የተለያዩ ክልሎች ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና በእጅጉ እንደተስፋፉ መንግሥትም ያመነው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በክልል ከተሞችና መስተዳድሮች ያሉ ሙሰኞች በተለያዩ መንገዶች ጤነኛ ባልሆነ መንገድ እጃቸው የገባን ገንዘብ እዚያ ክልላቸው መልሰው ወደ ልማት ቢቀይሩት በቀላሉ የኅብረተሰቡን ትኩረት መሳባቸው ስለማይቀር፣ ገንዘቡን ይዘው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሰፊና ምንም በማያውቃቸው ከተማ ወደ ቋሚ ሀብትነት ይለውጡታል፡፡ በዚህ ጊዜ የሚከሰተው ችግር በርካታ ነው፡፡ አንደኛ ያ ገንዘብ የተሰረቀበት ማኅበረሰብ ውስጥ ቢሽከረከር በተለያየ መንገድ ለማኅበረሰቡ ጠቀሜታ መስጠቱ አይቀርም፡፡ ነገር ግን ከዕይታ ለመራቅና ለመደበቅ አዲስ አበባ ውስጥ ወጪ ከተደረገ እነዚህ ሰዎች ከተጠያቂነት ለመዳን ሰፊ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ ሁለተኛ ተገቢ ያልሆነ የካፒታል ፍልሰት ይፈጥራል፡፡ ሦስተኛ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ አላስፈላጊ የኑሮ ውድነት ይፈጠራል፡፡ በተለይ በቋሚ ገቢ ለሚተዳደሩ ደመወዝተኞች ኑሮ እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ አራተኛ የአዲስ አበባ መስተዳድርም ይህ ጤነኛ ያልሆነ ገንዘብ በተለያየ መንገድ እጁ ስለሚገባ፣ ለመንገድና ለሌሎች መሠረተ ልማቶች ስለሚጠቀምበት የከተማዋ ዕድገት በከፍተኛ ፍጥነት እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡ ዜጎች ጤነኛ ባልሆነ መንገድ ያገኙትን ገንዘብ ወደ ቋሚ ሀብትነት ስለሚቀይሩ ገንዘቡ ታጠበ ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አዲስ አበባ የገንዘብ እጥበት ማዕከል ሆናለች ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥት አፋጣኝና ተገቢ ዕርምጃ ካልወሰደ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ዜጎች ላይ ቅሬታ ማስነሳቱ ስለማይቀር የመጨረሻ ውጤት ጥሩ አይሆንም፡፡

በአዲስ አበባ ሀብት ያፈራ የሚኖረው መብት

በአዲስ አበባ ሀብት ያፈራ ሰው ከሌሎች ክልሎች በተሻለ ለንብረቱ መተማመኛ የሚፈጥርለት ከመሆኑም በላይ፣ ዋጋው በየጊዜው የማደግ ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ደግሞ ይህ ዜጎች ገንዘባቸውን ወደ አዲስ አበባ ይዘው እንዲፈልሱ የሚገፋፋ ነው፡፡ በሌሎች ክልሎች የተገነባ ቋሚ ሀብት ዋጋ የመጨመር ዕድሉ ከአዲስ አበባ ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ዝቅተኛ ነው፡፡

አዲስ አበባ ያለ ቋሚ ሀብት ጥበቃ የማግኘት ዕድሉ

አዲስ አበባ ያለ ሀብት ከተማዋ የማዕከላዊ መንግሥት መቀመጫ በመሆኗና በርካታ ሕግ አስከባሪ ተቋማት ስላሉ፣ ለቋሚ ሀብት የሚገኘው ጥበቃ በእጅጉ የተሻለ ነው፡፡ በሌሎች ክልሎች ያሉ ባለንብረቶች ንብረታቸውን የሚጠብቅላቸው የተጠናከረ የፀጥታ ኃይል ካለመኖሩም በተጨማሪ፣ በብዙ አገሮች እንደሚደረገው ራሳቸውን መጠበቅ እንዲችሉ በቂ ትጥቅ የላቸውም፡፡ ቢኖራቸውም ትጥቁን በመጠቀም በሌሎች ላይ ጉዳት ቢያደርሱም ተጠያቂነቱ ከፍተኛ በመሆኑ፣ እስከ አሁን ራሱን ከጥቃት (ያለ ሕግ አስከባሪ አካላት) በበቂ ሁኔታ የተከላከለ ባለሀብት የለም፡፡ ይህ ደግሞ አገሪቱ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት እንዳታገኝ ትልቅ ፈተና ሊሆን  የሚችልበት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡

እነዚህን ከላይ የተጠቀሱት ሦስት ምክንያቶች እንውሰድና ወደ ሕገ መንግሥቱ ስንመጣ ዜጎች በማንኛውም ክልል ሀብት ማፍራት እንደሚችሉ የሚደነግግ ቢሆንም፣ ይህ ሁኔታ ግን መሬት ላይ ወርዶ በተግባር በበቂ ሁኔታ መታየት አልቻለም፡፡ እውነቱን ለመናገር አዲስ አበባ ማንኛውም ዜጋ እንደ ልቡ መሬት አግኝተው ወደ ልማት መግባት እንደተቻለው ሁሉ፣ በገጠሪቷ ኢትዮጵያም ያለ ገደብ ዜጎች መሬት እያገኙ በልማት ቢሰማሩ ዛሬ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እንደተናገሩት በዋናነት የገጠሩ ሕዝብ ተጠቃሚ ይሆን ነበር፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን አንዳንድ ዕድለኛ  የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በደርግ ዘመን በነፃ ያገኙትን መሬት በአሥር ሚሊዮኖች ሸጠው የንጉሥ ኑሮ መኖር የቻሉበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፣ መንግሥት ቆም ብሎ ይህ ገንዘብ ከየት መጣ ብሎ አፋጣኝ እርምት መውሰድ ባለመቻሉ ነው፡፡

አዲስ አበባ ቱሪስቶች በብዛት የማይታዩባትና ከፍተኛ የሆነ ምርት እያመረተች ወደ ዓለም ገበያ በመላክ ገንዘብ ማግኘት ያልቻለች ከተማ ሆና፣ ይህ ሁሉ ሀብትና ግንባታ ከየት መጣ ብሎ መጠየቅ ማንኛውም ጤነኛ አዕምሮ ያው ሰው ሊያደርገው የሚገባ ተግባር ነው፡፡

ሌላው ደግሞ ከተማዋ ምንም ዓይነት የፌዴራል ድጎማ ስታገኝ ሌሎች ክልሎች  ደግሞ ከፍተኛ  የሚባል ድጎማ እያገኙ፣ አዲስ አበባ ከክልል ከተሞች በላቀ ሁኔታ እንዴት ልታድግ ቻለች ብሎ መጠየቅ ደግሞ ሌላው ተገቢ ጥያቄ ይመስለኛል፡፡

አንድ ከውጭ አገር የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች እያስመጣ የሚሸጥ ነጋዴ ሸቀጡን የሚሸጠው በመላው አገሪቱ ሆኖ ሳለ፣ ያገኘውን ትርፍ እዚህ አዲስ አበባ ብቻ ወደ ቋሚ ሀብትነት የሚለውጠው ከሆነ ይህ ጤነኛ ነገር ነው ወይ? ያገኘውስ ትርፍ ሌሎች ክልሎች ሄዶ ወደ ቋሚ ሀብትነት ለመለወጥ ችግሩ ምንድነው፡፡

አንድ አንደኛ ደረጃ ኮንትራክተር በርካታ ሚሊዮኖች በሚያወጡ የልማት ሥራዎች ይሳተፋል፡፡ ከዚያ የሚያገኘውን የተጣራ ትርፍ ወደ ቋሚ ሀብትነት ሲለወጥ በመላው አገሪቱ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ኢንቨስት ለማድረግ ምን አገደው? አገሪቷ የምታውቀው በዋናነት የእርሻ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ እንደምታገኝ ነው፡፡ ከዚህ የሚገኘው የተጣራ ትርፍ ወደ ቋሚ ሀብትነት የሚለወጠው የት ነው?

እነዚህንና ሌሎችም ጥያቄዎችን በማንሳት ተገቢውን እርምት ለማድረግ የምንቆጥበው ጊዜ መኖር የለበትም፡፡ እኔ እንደ አንድ ዜጋ እንኳን ግለሰቦች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚያከናውነው የኢንቨስትመንት መጠን ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ጋር ሳነፃፅር በእጅጉ ያሳስበኛል፡፡

በጣም የሚገርመው ጉዳይ አዲስ አበባ ውስጥ አንዱ የገነባው ሕንፃ እስከ ሦስተኛ ፎቅ ድረስ ብቻ ተከራይቶ ሌላው ፎቅ ባዶውን ሆኖ፣ ከጎኑ ሌላ ባለሀብት ረጅም ሕንፃ ሲገነባ ይታያል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ሌላ ከተማ ሄዶ የልማት ሥራ አያከናውንም፡፡ ይህ ጉዳይ ሰፊ ምርምርና ጥናት የሚጠይቅ ነው፡፡ አገራችን ያላትን ውስን የገንዘብ ሀብት በአግባቡ ሥራ ላይ ካላዋልን ዕድገት እንዴት ሊመጣ ይችላል?

በእኔ እምነት ለዚህ ሁሉ ችግር ምንጩ (ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለማሳሰብ እንደተሞከርኩት) የሕገ መንግሥት ክፍተቶች በመሆናቸው፣ ይህ ጉዳይ በቂ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ያለፈውን ሩብ ክፍለ ዘመን እንዳሳለፍነው፣ ሌላ ሩብ ክፍለ ዘመን ይህንን ችግር ይዘን ከቀጠልን የሚፈጠረው ማኅበራዊና አገራዊ ቀውስ ጥሩ አይመስለኝም፡፡

እዚህ ላይ አንድ ጥሩ ነገር አለ ብሎ መናገር የሚቻል ይመስለኛል፡፡ በአገራችን እየተገነቡ ያሉ የኢንዱስትሪ መንደሮችና የባቡር መሠረተ ልማቶች ይህንን ከላይ የተጠቀሰውን ሁኔታ በመሠረቱ የመቀየር አቅም አላቸው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ የኢንዱስትሪ መንደሮች በከፍተኛ ደረጃ ከተሞች እንዲያድጉ የሚያስችሉ በመሆናቸው፣ በዚህ ዘርፍ ተግተን ከሠራን በአገራችን ባሉ ከተሞች ተቀራራቢ ዕድገት እንዲኖር ይረዳል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ከዚህ ተግባር ጋር በተጓዳኝ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የዚህ ሒደት አካል ለመሆን በራስ መተማመናቸውን እንዲያሳድጉ ተገቢውን ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

የክልል ባለሥልጣናትም የክልል ሕጎችም ከዚህ በጎ ተግባር ጋር አብረው መራመድ መቻላቸው በበቂ ሁኔታ መመርመር አለበት፡፡ የክልል ባለሥልጣናት በምንም ሁኔታ በአዲስ አበባ ዙሪያ ሊደረግ የነበረውን የልማት ሥራ የማደናቀፍ ውሳኔ እንዳይወስኑ ተገቢው ሥራ መሠራት አለበት፡፡

ሌላው ለከተሞች ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚደረገው አሁን የተጀመረው የባቡር ልማት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ደጋግሜ ለማሳሰብ እንደሞከርኩት ከባቡሩ ልማት ጎን ለጎን ሌሎች የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎችን በተገቢው ፍጥነት ማድረግ ከተቻለ፣ ዜጎች ከቦታ ቦታ ያለ ችግር እየተንቀሳቀሱ የሚሠሩ ከሆነ ከተሞች ያድጋሉ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይፋጠናል፣ ባቡር ካሉት በርካታ ጥቅሞች ቀጥሎ ያለው ማኅበራዊ ፋይዳ በእጅጉ የጎላ ነው፡፡ እጅግ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ዜጋም ሩቅ ቦታ በባቡር መጓዝ ስለሚችል ከተሞች እንዲያድጉ ይረዳል፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው አዲስ አበባ የፌዴራል በጀት ሳይመደብላት በራሷ ገቢ ብቻ እንዴት በከፍተኛ ፍጥነት ልታድግ ቻለች? እንዴት እንደ ሸንበቆ ፈጣን ዕድገት አመጣች? የሚለው ጉዳይ ሰፊ ምርምር የሚሻ ቢሆንም፣ ሌሎች ክልሎች የራሳቸውን ገቢ እያመነጩና የፌዴራል በጀት እያገኙ እንዴት ዕድገታቸው አዝጋሚ ሆነ የሚለውም  ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ነው፡፡

በ2008 ዓ.ም. በተከሰተው ሕዝባዊ አመፅ መሠረቱ ከአዲስ አበባ ውጪ መሆኑ ሌላው ምርምር የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ በተለምዶ በአመዛኙ ባለፉት ሥርዓቶች ላይ አመፅ ከዋና ከተማ ነበር የሚመነጨው፡፡ የ2008 አመፅ የተካሄደበት ጊዜ ደግሞ በክረምት ወቅት ተማሪዎች ትምህርት ቤት በሌሉበት፣ ገበሬው በከፍተኛ ሥራ ተወጥሮ ባለበት ጊዜ መካሄዱ ደግሞ በኢትዮጵያ የአመፆች ታሪክ ልዩ ያደርገዋል፡፡ አመፅ በአመዛኙ የሚካሄደው በየካቲት ወር ገደማ ሲሆን፣ ይህም ምክንያቱ አንደኛ ተማሪዎች በበቂ ሁኔታ የሚተዋወቁበት ጊዜ በመሆኑ፣ ሁለተኛ በገጠር ደግሞ ገበሬው የግብርና ሥራውን አጠናቆ ፋታ የሚገኝበት ወቅት ስለሆነ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ለማንሳት እስከ አሁን ተመራጭ ወቅት ነበር፡፡

ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳይ እንመለስና ሕገ መንግሥቱ በእኔ እምነት ለአዲስ አበባ (ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች) ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በክልል የሚኖሩ ሕዝቦች የአዲስ አበባን ምሥል በቴሊቪዥን ባዩ ቁጥር ወይም ወደ አዲስ አበባ ብቅ ብለው ሲመለከቱ ይህ ዕድገት እኛ ዘንድ ለምን አልመጣም የሚል ጥያቄ እያነሱ ያለበት ወቅት እንደሆነ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይቶች ሲደረጉ በየጊዜ የምንሰማው ነው፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች በሕንፃ ሲታጠሩ የክልል ከተሞች ደግሞ የቢጫ ጄሪካን ሠልፍ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አሀዳዊ ያልሆነ የአስተዳደር ሥርዓትና አሐዳዊ የሆነ የገንዘብ ሥርዓት በተገቢው ላጠናው ሰው ትልቅ ቀውስ እየፈጠረ ነው፡፡ ክልሎች በክልላቸው የተገኘን ገንዘብ ከክልላቸው እንዳይወጣ ለመከላከል የሚችሉበት ምንም ዓይነት አሠራር አልተዘረጋም፡፡

አሁንም በድጋሚ ለማሳሰብ የምፈልገው ዜጎች ያለ ገደብ እንደ ፍላጎታቸው፣ በመሉ በራስ መተማመን ከቦታ ቦታ ሄደው ሥራቸውን መሥራት ካልቻሉ ይህ ፍትሐዊ ያልሆነ ዕድገት መቀጠሉ የማይቀር ነው፡፡ ኢሕአዴግ ያሳለፈው 26 የሥልጣን ዓመታት የትኛው ተግባር ጥሩ እንዳልሆነ፣ የትኛው ደግሞ ትክክል እንዳልሆነ መለየት ከተሳነው በራሱ ላይ ችግር መጋበዙን መገንዘብ አለበት፡፡

ከተሞች ደግሞ ማደግ ካለባቸው ትልቁ ፍጆታ ምግብ በመሆኑ ከአነስተኛ ማሳ ወጥተን በሰፋፊ እርሻዎች፣ ዋጋው ርካሽ የሆነ የምግብ ምርት በበቂ ሁኔታ ከከተሞችና ለኢንዱስትሪ መንደሮች ማቅረብ ካልተቻለ አሁንም ብዙ የተደከመለት ግንባታ ተንገራግጮ ነው የሚቆመው፡፡ አሁን ያለውን የአዲስ አበባ ሁኔታ ብንመለከት ከፍተኛ የሆነ የምግብ ዋጋ ውድነት በስፋት ይስተዋላል፡፡ የኢትዮጵያ አብዛኛው ገበሬ የሚያመርተው አሁንም ከእጅ ወደ አፍ በሆነ አሠራር በመሆኑ፣ ለከተሞች የሚቀርበው የምግብ ምርት በእጅጉ አናሳ ነው፡፡ ለዜጎች መቅረብ የሚገባቸው ግን ልክ እንደ ቅንጦት ምርት ለዓመት በዓል ዕለት ብቻ ነው የምናያቸው አሉ፡፡ ለምሳሌ የዶሮ ምርት እዚህ አካባቢያችን ባሉ የአፍሪካ አገሮች እንኳን በየመንገዱ እየተጠበሰ (እንደኛ አገር ቆሎ ማለት ነው) የሚሸጥ ሆኖ ሳለ፣ እኛ አገር ዶሮ ለመብላት የግድ ሁለት ወር ሙሉ መፆም ይጠበቅብናል፡፡ ለኢንዱስትሪ ሠራተኞች ደግሞ ተመጣጣኝ የሆነና ኃይል ሰጪ የሆኑ ምግቦችን ማግኘት ካልቻሉ ምርታማ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በጤናቸው ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ብዙ ጊዜ አንድ ግንባታ በሚከናወንበት ቦታ ከፍተኛ የጉልበት ሥራ የሚሠሩ ሠራተኞች ምሳቸውን ዳቦ በሙዝ በልተው ነው ጉልበት ወደሚጠይቁ ሥራዎች የሚሄዱት፡፡ ይህ ሁኔታ የግድ መለወጥ አለበት፡፡

በአጠቃላይ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ በከተሞችና በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ያለው ግንኙነት በምንም ሁኔታ ጤነኛ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይህ ደግሞ ካልተስተካከለ ዕድገትን መመኘት  የዋህነት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው metasebyamelaku@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡ 

Standard (Image)

እያንጓለለ . . . !

$
0
0

 

በፀዳሉ ንጉሤ

በዚህ ርዕስ ዙሪያ ላነሳው ላሰብኩት አንጓ ጉዳይ መነሻ እንዲሆነኝ አንድ ሐሳብ ላስቀድም፣ የአመራር ኃላፊነት ከምንም ነገር በፊትና በላይ ችግር መለየት (Problem Identification) እና መፍታት ነው፡፡ በዚህ መሠረት አመራር ከትናንት ለዛሬ የተላለፈን ችግር ለይቶ መፍታት አለበት፡፡ በተጨማሪም ዛሬ በራሱ ምክንያት የፈጠራቸውን ችግሮችም እንደዚሁ ለይቶ መፍታት ይገባዋል፡፡ እንደገና ደግሞ ነገ ሊፈጠሩ የሚችሉና ኅብረተሰብን ሊያቃውሱ የሚችሉ ችግሮችን ከወዲሁ ለይቶ በበቂ ዝግጅት ሊያስወግዳቸው መሥራት ይገባዋል፡፡ (አዲስ ራዕይ መጽሔት፣ 11ኛ ዓመት፣ ቅፅ 5፣ ቁጥር 4፣ መጋቢት - ሚያዝያ 2008፣ ገጽ 30፡፡)

እውነት ነው ተልኮውን ጠንቅቆ የተረዳ፣ በጥቅም ያልታወረና ልቡ ያልደነደነ አመራር ማድረግ ያለበትና መሆንም ያለበት ከላይ የተጠቀሰውን ነው፡፡ ‹‹የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ›› እንዲሉ፣ አንዳንድ የወረደ ሥነ ምግባር ያላቸው ኪራይ ሰብሳቢዎች አሁን አሁን የሚያሳዩት ትዕቢትና እብሪት ገደቡን እያለፈ ድርጊታቸውም ቅኖችን እየተፈታተነ ነው፡፡ በኪራይ ሰብሳቢ አስተሳሰብና ተግባር በተዘፈቁ ሰዎች ላይ መወሰድ ያለበት ዕርምጃ በዘገየ ወይም በግማሽ ልብ ብቻ የሚፈጸም ሲሆን . . . ኪራይ ሰብሳቢዎች የልብ ልብ እየተሰማቸው የአይነኬነት መንፈስ እያዳበሩ ይሄዳሉ፡፡

(ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 34) የሚለው አገላለጽ አሁን አሁን በገሀድ እየተፈጸመ ነው፡፡ መንግሥትን ምን ነካው እያስባለም ነው፡፡ ለትዝብት ያህል ይኼን ካልሁኝ ይበቃል፡፡ ወደ ርዕሰ ጉዳዬ ልመለስ፡፡

‹‹በ2015 ዓ.ም. ሙስና ለልማትና መልካም አስተዳደር እንቅፋት ከማይሆንበት ደረጃ በማድረስ በዓለም ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ከሆኑ የፀረ ሙስና ተቋማት አንዱ ሆኖ #Uንም$ እንዲሉ የተቋሙን ችግር በመንግሥት ለማላከክ የወሬ ዘመቻ ከከፈቱ ሰንበትበት ብለዋል፡፡ ወሬው አልፎ ተርፎም የኪራይ ሰብሳቢዎች እጅ አለበት እስከማለት ተደርሷል፡፡ የጎራ መደበላለቅ ይላል ይኼ ነው፡፡ ይኼ ራሱ ብዙ የሚያነጋግር ጉዳይ ቢሆንም በይደር ልለፈውና ወደ ዋናው ጉዳይ ልመለስ፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የዓቃቤ ሕግ ሙያተኞችን ወደ ራሱ ሲያዛውር የሄደበት አግባብ አብዛኛውን የኮሚሽኑን ሠራተኞች ያስደመመና ያስገረመ ሆኖ አልፏል፡፡ ይህ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ድርጊት ውስጠ ወይራ ነው፡፡ እያንጓለለ! እያንጓለለ! እያንጓለለ! ‘አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ'ብዙኃኑን ሠራተኞች ጉድ አስብሏል፡፡ ይህ ጉዳይ በሠራተኞች ዘንድ ብዙ ጥያቄዎችንም አስነስቷል፡፡ ለምሳሌ፡- 

  • ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በቅርብ ሙያውን የተቀላቀሉትንና ምንም ተሞክሮ የሌላቸውን ተቀብሎ ሰፊ ልምድና ተሞክሮ ያላቸውን፣ በሙያው ተክነናል የሚሉትን፣ በአመራር ላይ የነበሩትንም ሳይቀር ለምን ተዋቸው? ብለው የሚጠይቁ በርካቶች ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ፣
  • ለካ መንግሥት  ውስጥ አወቅ ነው፣ ብዙ ነገር ይታወቃል ማለት ነው? ግን ይኼ ነገር በእንደዚህ መታለፉ አስተማሪ ነው? የሚሉም አልታጡም፡፡

ይሁንና ይህ በእንዲህ እንዳለ #[ጅም ጦር ባይወጉበትም ያስፈራሩበት$ ሆነ እንጂ፡፡

እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጉዳይ የአንድ ተቋም አመራር የተቋሙን ዓላማ አስፈጻሚ የሥራ ሒደቶች ዓላማ የማስፈጸም ድርሻ በእኩል ዓይን በማየት፣ ሁሉም ዓላማ አስፈጻሚ የሥራ ሒደቶች የሥራ ድርሻቸውን በትክክል እንዲወጡ ተገቢውን ድጋፍና እገዛ  ሊያደርግ ይገባል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ አመራሩ አንዱን ዓላማ አስፈጻሚ የሥራ ሒደት አግዝፎ ሌላውን አኮስሶ/አሳንሶ በማየት የሚደረግ አመራር፣ በተቋሙ ውጤታማነት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡

በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ላለፉት ዓመታት የሥራ እንቅስቃሴ ስኬት መታጣት አንዱ የአመራሩ በዓላማ አስፈጻሚ የሥራ ሒደቶች ላይ የነበረው የተንሸዋረረ አመለካከት ነው ማለት ይቻላል፡፡

የኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች የሕግ ሰዎች መሆናቸው ይመስላል የሙስናና የብልሹ አሠራር ችግሮች ሕግን በማስፈጸም ብቻ የሚፈቱ እስከሚመስል ድረስ ትልቅ ትኩረት ይሰጥ የነበረው፣ ለምርመራና ዓቃቤ ሕግ የሥራ ሒደት ነበር፡፡ (ሕግ የማስፈጸሙ ሥራስ በትክክል ይፈጸም ነበር ወይ? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ) የምርመራና ዓቃቤ ሕግ የሥራ ሒደት ሥራ ደግሞ ራሱ በባህሪው ለሙስናና ለብልሹ አሠራር ተጋላጭ በመሆኑ፣ የሥነ ምግባር ችግር/ስብራት ያለባቸው አመራሮችም ሆኑ ፈጻሚዎች በችግሩ ውስጥ አልወደቁም ማለት አይቻልም፡፡ ለዚህም ነው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እያንጓለለ! እያንጓለለ! እያንጓለለ! በድርጊቱ የከፋውንና የተበላሸውን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ ዝውውሩን የቋጨው፡፡

የሙስና ወንጀል ድርጊት ይጋባል/ይሸጋገራል የሚለው የምሁራን አገላለጽ እውነትነት አለው፡፡ በኮሚሽኑ በምርመራና የዓቃቤ ሕግ የሥራ ሒደት የሥነ ምግባር ችግር ባለባቸው ሠራተኞች የተጀመረው የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር አነሰም በዛ፣ ቀስ በቀስ ወደ ሌሎች ዓላማ አስፈጻሚና ድጋፍ ሰጭ የሥራ ሒደቶችም በመዛመቱ ሙስናና ብልሹ አሠራር እንደ ችግር ማይታይበት ደረጃ ዝቅ እንዲል ‹‹ግሎ ያታግላል››የተባለለት የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ በኅብረተሰቡ ዕይታ ጥያቄ ውስጥ የገባበት ሁኔታ ተስተውሎ አልፏል፡፡

ለምሳሌ፡- ላለፉት ጥቂት ዓመታት የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ራሱ በሚያመቻቻቸው የትምህርት/ሥልጠና መድረኮች፣ በታዳሚ የኅብረተሰቡ አካላት ዘወትር ከሚነሱ ጥያቄዎች ጥቂቱን ልጥቀስ፡-

  • ራሱ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከሙስናና ከብልሹ አሠራር ነፃ ነው ወይ?
  • የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከተቋቋመ ወዲህ ሙስና ጨምሯል ወይስ ቀንሷል?
  • ለፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሌላ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሊቋቋምለት ይገባል የሚሉ ሰዎች አሉ፣ መነሻቸው ምን ሊሆን ይችላል?
  • የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከወገብ በታች ነው የሚሠራው ይባላል፣ እንዲህ የሚባለው ከምን መነሻ ነው?
  • በሚዲያ የምትለቋቸው ቅጣቶች ከተፈጸመው ወንጀል ጋር ተመጣጣኝ አይደሉም፣ ቅጣቱ በጣም ዝቅተኛ ነው፣ ይኼ ሌሎችም ወንጀሉን እንዲፈጽሙ የሚያበረታታ አይሆንም ወይ? ወዘተ…

እነዚህና መሰል ከኅብረተሰቡ የሚነሱ አሽሙር አዘል ጥያቄዎች የኮሚሽኑ አመራር መለስ ብሎ ራሱን እንዲያይና ጉድለቶቹን እንዲያርም ጉልህ ግባቶች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ‹‹አስተሳሰቡ ያልተለወጠ ለውጥ አያመጣም›› እንዲሉ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ፣ ኅብረተሰቡም በኮሚሽኑ ላይ የነበረው አመኔታ ጥያቄ ውስጥ እየገባ እንደሄደ ከላይ የተጠቀሱ ጥያቄዎች እውነተኛ ማሳያ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

መንግሥት ለተቋሙ በአዋጅ የሰጠው ተግባርና ኃላፊነት በጣም  ሰፊ፣ ለአገር ሰላማና ህልውና ወሳኝ ሆኖ ሳለ ተቋሙ መሆን የሚገባውን ሆኖ ባለመገኘቱ በአገርና በሕዝብ ላይ ተጋርጦ የነበረው ጥፋትና አደጋ ቀላል እንዳልነበረ ግልጽ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ‹. . . የት ላይ እንደወደቅክ ሳይሆን የት ላይ እንዳዳለጠህ ተመልከት› እንዲሉ፣ ድጥን ለይቶ ውድቀትን ተቀብሎ ለዘላቂ መፍትሔ እየተሠራ አይደለም፡፡

ሠራተኞች በፌዴራል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ እየለቀቁ ይገኛሉ፡፡ አመራሩም በኮሚሽኑ የሸፈነውን የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ብልሹ አሠራር በጥልቀት አጥንቶ ከመፍታት ይልቅ፣ <span style="font-size:12.0pt;line-height:200%;font-family: &quot;Ge" ez-1","sans-serif";mso-fareast-font-family:mingliu;mso-bidi-font-family:="" mingliu;color:black'="">#Wራተኞች የሚለቁት ለተሻለ ገቢ ፍለጋ ነው<span style="font-size:12.0pt; line-height:200%;font-family:&quot;Ge" ez-1","sans-serif";mso-fareast-font-family:="" mingliu;mso-bidi-font-family:mingliu;color:black'="">$ በሚል ሽፋን በማደናገር የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አሁንም ከሰፊ ችግሩ ጋር ይገኛል፡፡

በስተመጨረሻም የምርመራና የዓቃቤ ሕግ የሥራ ሒደት ከፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መነሳት በኮሚሽኑ አፈጻጸም ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ ምን ሊሆን ይችላል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ተገቢ ስለሚሆን በማስከተል በጥቂቱ በማሳየት ሐሳቤን ላጠቃል፡፡  

የምርመራና የዓቃቤ ሕግ የሥራ ሒደት ከኮሚሽኑ ቢነሳም የኮሚሽኑን ራዕይ ለማሳካት አሁንም የሥራው 83.3 በመቶ ያለው በኮሚሽኑ ነው፡፡ ምናልባትም የተነሳው የሥራ ሒደት የሥራ ድርሻ የሥራው 16.6 በመቶ እንደሆነ በቀላል የሒሳብ ሥሌት ማወቅ ይቻላል፡፡ በኮሚሽኑ ስድስት ዓላማ አስፈጻሚ የሥራ ሒደቶች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የተነሳው አንዱ ነው፡፡ አምስቱ አሁንም አሉ፡፡ ስድስቱ ዓላማ አስፈጻሚ የሥራ ሒደቶች መቶ በመቶ የሚያስፈጽሙ ከሆነ፣ አምስቱ ስንት በመቶ? አንዱስ ስንት በመቶ? በሚል ሒሳባዊ ሥሌት በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ አመራሩ 83.3 በመቶ ሥራው በኮሚሽኑ ያለ መሆኑን ተረድቶ፣ የሥራውን 16.6 በመቶን ደግሞ ከፌዴራል ፖሊስና ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጋር በሚኖር ቅንጅታዊ አሠራር ተግቶ በመሥራት ራዕይን፣ ተልዕኮንና ዓላማን ለማሳካት ቁርጠኝነቱ፣ ቀናነቱና በጎ አመለካከቱ አለ ወይ? ብሎ ለሚጠይቅ አሁንም እዚያ ላይ ሰፊ ክፍተት አለ፡፡

ሙስናና ብልሹ አሠራርን ታግሎ የማታገል ሥራ ችላ ሊባል የሚገባው ጉዳይ እንዳይደለ ግልጽ ይመስለኛል፡፡ በአንድ ሥርዓተ ማኅበር ውስጥ ሙስናና ብልሹ አሠራር ከተስፋፋና ከተንሰራፋ አገርን እስከማፈራረስ ድረስ ይደርሳል፡፡ በመንግሥት ተቋሙ ትኩረት ሊቸረው ይገባል በማለት ሐሳቤን በአጭሩ እቋጫለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

Standard (Image)
Viewing all 88 articles
Browse latest View live